Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
534 photos
45 videos
1 file
841 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
+++ ይግባኝ! +++

አንድ ሰው ለብዙ ዘመናት አብሮት በፍቅር ይኖር የነበረ ወዳጁን በቅንዓት ተነሳስቶ ይገድለዋል፡፡ በዚህም የወንጀል ሥራው ተከስሶ የፍርድ ብይን ያገኝ ዘንድ ሰዎች ከችሎት ፊት አቆሙት፡፡ ዳኛውም ወንጀለኛው ለፈጸመው የጭካኔና ሰብአዊነት የጎደለው ክፉ ተግባር በሕጉ መሠረት የሚገባውን የዕድሜ ልክ እስራት ወሰኑበት፡፡ወንጀላኛውም በተሰጠው ፍርድ ፍትሐዊነት ላይ እንዳላመነበት እና ለፍርዱ ማቅለያ የሚሆን የይግባኝ ጥያቄን ማቅረብ እንደሚፈልግ በእጁ እየጠቀሰ ዳኛውን ተለማመነ፡፡

በዚህ ጊዜ ዳኛው ምን ዓይነት ይግባኝ እንደሚያቀርብ ለመስማት የጓጉ መሆናቸውን በሚያሳብቅ መልኩ ቸኩለው እድሉን ሰጡት፡፡

ወንጀለኛ፡-ክቡር ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትልኝ የምፈልገው አንድ ነገር አለ፡፡በርግጥ ይህን ሰው መግደሌን አልካድኩም፣ ነገር ግን እርሱን ለመግደል የፈጀብኝ እኮ አፍታ ነች እንደው ቢበዛ ዐሥር ደቂቃ ቢሆን ነው፡፡ ታዲያ እንዴት በዚህች አጭር ጊዜ ላጠፋሁት ጥፋት ዕድሜ ልክ ይፈረድብኛል? በማለት ጥያቄውን አቀረበ፡፡

ዳኛው ምን ብለው የሚመልሱለት ይመስላችኋል? መቼም ወንጀሉን ለመፈጸም ከፈጀበት ጊዜ ጋር ተነጻጽሮ ፍርዱ ሊቀልለት ይችላል የሚል የየዋሕ ሰው ግምት እንደማይኖራችሁ አልጠራጠርም፡፡ በፍርዱ ሂደት የሚታየው ወንጀሉን ሲፈጽም የወሰደበት የጊዜ መጠን ሳይሆን በዚያች ሰዓት የፈጸማት የወንጀሏ ክብደት ናት፡፡

ውድ ምዕመናን! አሁን እኛ የፍርድ ቤት ዘገባ ምን ይጠቅመናል ትሉ ይሆናል? ከዚህ በኋላ ግን የምንነጋገረው ፍትሕ ስለማይገኝባት ስለዚህች ምድር ፍርድ አይደለም፤ ስለ ሰማያዊው ፍርድ ነው እንጂ። ስለ ሥጋዊው የዳኝነትም ሥርዓት አይደለም፤ ስለመንፈሳዊው ፍርድ ነው እንጂ፡፡ ብዙ ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ስለ እግዚአብሔር ፍርድ ዘላለማዊነት (eternal punishment) ባሰቡ ቁጥር ‹የሰው ልጅ በዚህች ምድር የሚኖረው የዕድሜ ልክ ስልሳ እና ሰባ ቢበዛም ሰማንያ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የዕድሜ ወሰን ውስጥ ለተሠራ ኃጢአት እንዴት እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍርድን ይፈርዳል?› የሚል ጥያቄ በኅሊናቸው ይላወስባቸዋል፡፡

አንዳንዶቹም ለተገፉ ጠበቃ የሚሆን የእውነት ፈራጅ እግዚአብሔርን ፍርዱ ኢ-ፍትሐዊ (unfair judgment) ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ምንም ስለ ‹ዘላለማዊ ሽልማቱ› (eternal reward) ‹ለምን ዘላለማዊ ሆነ?› የሚል ጥያቄን አለማቅረባቸው ትዝብት ውስጥ የሚጥላቸው ቢሆንም እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ግን ከላይ ባለው አጭር ምሳሌ መልሳቸውን ያገኛሉ፡፡

አስተውሉ! ለወንጀለኛ መቼም ፍርድ እንደሚገባው ማንም የሚያምንበት ጉዳይ ነው፡፡ ወንጀለኛ ከወንጀል እስካልጸዳ ድረስ ፍርድ ከእርሱ ጋር እንደ ጥላ ትከተለዋለች፡፡ ቅጣትንም እንደ አክሊል በራሱ ላይ ደፍቶ ይመላለሳል፡፡ ለኃጢአተኛም እንዲሁ ነው፡፡ ራሱን በንስሓ መርምሮ ፣ወድቆ ተነሥቶ ፣በሥጋው በደሙ(ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል) አምላኩን እስካልታረቀ ድረስ ሁል ጊዜም ኃጢአተኛ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ኀዘኑን እጥፍ የሚያደርገው ያ ኃጢአተኛ በዚህ አቋሙ እያለ በሞት ከተወሰደ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚድንበትን መንፈሳዊ ተግባር ማከናወን የሚችለው በምድር በሕይወተ ሥጋ እስካለ ድረስ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከራሷ ከክርስቶስ ከታነጸችበት የሐዋርያት ትምህርትም አላገኘችውምና ሰው ከሞተ በኋላ በሰማይ የሚሰግድበት ፣መንፈሳዊ ምግባራትን የሚያደራጅበትና ኃጢአቱን የሚያስወግድበት ሥፍራ አለ ብላ አታምንም፡፡ ‹እም ድኅረ ሞቱ ለሰብእ አልቦቱ ንስሓ›/ ‹ለሰው ከሞቱ በኋላ ንስሓ የለውም› የሚለውን የአበው ቃል መመሪያዋ ታደርጋለች እንጂ፡፡

ስለዚህም በዚህ መልኩ የሞተ ሰው ኃጢአተኝነቱ ለዘላለም ነውና ፍርዱም ለዘላለም በማይጠፋ በዲንና በሚቃጠል የእሳት ባሕር ይሆናል፡፡ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡(ራእይ 21፤8) ከእንግዲህስ ከነኃጢአታችን ብንሞት የምንድንበት መሥዋዕት የለምና፣ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ አምላክ በዓይነ ምሕረቱ እንዲመለከተን የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደተባሉት ወደ ተሾሙ ካህናት እንገስግስ። ንስሓ እንግባ፣ ቀኖናችንንም እንፈጽም። መጠየቅን በሚወድ በእርሱ ፊት ለፍርድ በቆምን ጊዜ መልስ የሚሆነንን የጽድቅን ጥሪት እናከማች!

‹አቤቱ እንደ ቸርነትህ ነው እንጂ እንደ በደላችን አይሁንብን!›

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ የተዘጋች አፍ +++
ከፊቴ ያለውን መከራ በማየት
ቸኩዬ እንዳልፈርድ በአንደበቴ እንዳልስት
ስጠኝ ጌታዬ ሆይ የተዘጋች አፍን
በዝምታዬ ውስጥ እንዳይ ቸርነትኽን
+++

አመስግኖ አጥፊ መርቆ ረጋሚ
ሊገድል የሚያድን ሊነቅል አራሚ
ሆኖብኛልና አንደበቴ ከፍቶ
ላክልኝ መልአኩን ያሳርፈኝ ዘግቶ
+++

የማዳንህን ቀን ጊዜውን ሳላውቀው
በራሴ ቀጠሮ መልስኽን ጠብቄው
ቀረህብኝ ብዬ ለጊዜው ብከፋም
ትዕግስት ነገረኝ የመጠበቅን ጣዕም
+++

በሚሸልቱህ ፊት ዝም ያልከው አምላክ
ለከሳሾች ሙግት ቃልህን የከለከልክ
እባክህ አስተምረኝ እኔም ልምሰል አንተን
ተሰድቦ ተነቅፎ ዝም የማለት ጸጋን

ግጥም: ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ዜማ: ዲያቆን ዘላለም ታከለ (ዘጎላ)

ዘማሪ: መምህር አቤል ተስፋዬ
https://youtu.be/B146rrcdXgA
የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል የስሙ ትርጉም ‹እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው›/‹God’s healer› ማለት ነወ፡፡ ቁጥሩ የሰው ልጆችን ጸሎት ከሚያሳርጉት ሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እንደሆነ በመጽሐፈ ጦቢት ላይ ራሱ መልአኩ ሲናገር እናነባለን፡፡(ጦቢ 12፥15) ጻድቁ ሄኖክም ‹በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆች ቁስል ላይ የተሾመ› መልአክ እንደሆነ ጽፏል፡፡(ሄኖ 10፥13) ዓይነ ስውር የነበረውን ጦቢያ የዓሣ ሐሞት ዓይኑን እንዲቀባው ልጁ ጦቢትን በመምከር ብልዙን ከብሌኑ ላይ አንሥቶ ዓይኑን ያበራለት መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡(ጦቢ 11) በዮሐንስ ወንጌል ላይም እንደተቀመጠው ብዙ ሕመምተኞች ተጠምቀው የሚድኑበትን በቤተ ሳይዳ የሚገኘውን የመጠመቂያ ውኃ በሳምንት አንድ ጊዜ ያናውጸው (ይባርከው) የነበረው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነበር፡፡(ዮሐ 5፥4)

ሌላው ጽንስ በማኅጸን ከተቋጠረ ከአርባኛው ቀን ጀምሮ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው የማይለየው ሲሆን፣ አንዲት ሴትም የመውለጃዋ ቀን ደርሶ ምጥ በያዛት ጊዜ ሕመሙን የሚያቀልላት እና ማኅጸኗን የሚፈታው ይኸው መልአክ ነው፡፡ ከዚህም ሥራው የተነሣ ‹ፈታሔ ማኅጸን› በመባል ይጠራል፡፡

እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን!

ሩፋኤል አሳድገኝ...
ሩፋኤል አሳድገኝ...

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++‹ሞቴን ባሰብኩ ጊዜ›+++

ዕድሜ በጨመርኩ ቁጥር የዓለምን ከንቱነት እና አለመረጋጋት የበለጠ እየተረዳሁ እመጣለሁ፡፡ ስለምን ራሳችንን በከንቱ ነገር እናደክማለን? የዕድሜ ዘመናችን እንደ ሕልም ያጠረ ፤ እንደ አመድ እና ትቢያ ሆነን በጥቂት ጊዜ ጥፋትን የምንቀምስ አይደለምን!፡፡ ዛሬ ጤና አለን ነገ ግን እናጣዋለን፡፡ ዛሬ እንስቃለን ነገ ግን ቁጡ እና ኀዘንተኞች እንሆናለህ፡፡ ዛሬ ከደስታ ብዛት የተነሣ ዓይኖቻችን የእንባን ዘለላዎች አዝለዋል። በቅርቡ ግን በኀዘን እና ሕመም ምክንያት ዓይኖቻችን የልቅሶ እንባን ያዘንባሉ፡፡ ዛሬ ሃብታችን የሚያስተማምን ነው፤ ነገ ግን በክፉ ገጠመኝ ያለን ይበተንብናል ይወድማልም፡፡ ዛሬ መልካም ዜናን (የምሥራችን) ተቀብለናል፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን መልካሙ በመጥፎ (ክፉ ዜና) ዜና ይተካል፡፡ በከንቱ ነገር ራሳችንን እናደክማለን፡፡ ሕይወት እንደ ሌሊት ሕልም እንደ ጥላም ናት፡፡ ወላጆቻችን ፣ወንድም እኅቶቻችን ፣ የቀደሙ አያቶቻችንስ ወዴት አሉ? እነዚህን ሁሉ መቃብር ተቀብላቸዋለች፡፡ ሁሉም በስብሰዋል በነፍሳትም ተበልተዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን መበስበስ እና መቃብር እኛንም እንዲሁ ልታደርግ ትጠብቀናለች! ወዮ…ወዮ… ሞት ሆይ አንተን ማሰብ ምን ያህል ምሬት ነው!

መድኃኔዓለም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ሥልጣን ሰጥቶናል(ዮሐ 1፤12)፡፡ ምሕረት የሌለው ጠላታችንንም እንዋጋበት ዘንድ ብዙ አምላካዊ የጦር መሳሪያዎችን አስታጥቆናል፡፡ ነገር ግን እኛ ከሁሉም በላይ ደግሞ የምሆን ‹እኔ›ን ጨምሮ ክርስቶስ የሰጠንን የጦር እቃ ቸል በማለት የጠላታችን (የሰይጣን) እስረኛ ሆነናል፡፡የነፍሳችንንም ከሥጋችን መለየት ከመፍራታችን የተነሣ ወደ ሞት በቀረብን ጊዜ በስቃይ እና ጣር የምንንቀጠቀጥ ፤ በተገኘው መንገድ ሁሉ ምድራዊ ሕይታችንን ለማቆየት የምንጥር ሆነናል፡፡ ሞት ለምን አስፈሪ ሆነብን? እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን ለምን አልተበረታታንም? ወደማናውቀው እና እንግዳ ወደሚሆን ንጉሥ ነው እንዴ የምንሄደው? አይደለም! ንጉሡማ ነፍሳችንን ከጠላት እጅ ያድናት ዘንድ ደሙን ያፈሰሰልን መድኃኒታችንና ፈጣሪያችን እኮ ነው!፡፡ታዲያ ለምን ብርታትን እናጣለን? ለምንስ እንፈራለን? በእርግጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች› እንዳለ ሞትስ በጠባይዋ ቀዝቃዛ ናት፡፡ አዎን! ሞት በጠባዕይዋ የቀዘቀዘች ናት፡፡ነገር ግን ፍርሃት የሚመጣው ከእኛው ሕሊና ነው፡፡ ነፍስ በተገቢው መንገድ እንዳልኖረች ፣በሕግጋቱም እንዳልጸናች ፣የሰርግ ልብሷንም በበጉ ደም እንዳላጠበች ሕሊና በተረዳ ጊዜ ‹ይቀበለኝ ይሆን ወይስ አላውቅሽም ይለኝ? እድን ይሆን ወይንስ እኮነን?› በሚል ፍርዱን በማሰብ ከሚመጣ ፍርሃት በመነሣት በንጉሡ ፊት ራስን ማቅረብ ሐፍረት ይሆናል፡፡ ኃጢአታችንን ፈጽመን ሳንናዘዝ ንስሐም ሳንገባ ነፍሳችን ከሥጋችን ብትለይ ይህች ቀን ነቢዩ ኤርሚያስ የጠቆመን ክፉ ቀናትና ወዮ! ወዮታ አለብን፡፡(ኤር 17፡17)

‹ስለበጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም› በእኛ የሚሠራ አምላካችን እግዚአብሔር ከእውነተኛ ትህትና ጋር የጸጸትን መንፈስ ፣የሚገባ የንስሐ ፍሬ ማፍራትን ፣የምሕረት እና የፍቅርንም ሥራ በመስጠት ከዚህ ያድነን ዘንድ እንለምነው (ፊሊ 2፡13)፡፡ እንዲህም ከሆነ የእግዚአብሔር እውነተኛ ፍርዱ በእኛ ዘንድ ምሕረት ይሆንልናል፡፡ ስለዚህም የምታስፈራው የሞታችን ሰዓት በመጣች ጊዜ ነፍሳችን በእግዚአብሔር ቸርነት ትበረታታለች ‹ምሕረቱ በእኔ በተዋረደው ባሪያው ላይ እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁ›ም ትላለች!፡፡

++++++አሜን እንዲህም ይሁንልን!++++++++

የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር ብርሃን በመጣ ጊዜ በለቅሶ ነው፡፡ሕይወቱንም በሙሾ እና በኃዘን ያሳልፋል በመጨረሻም በእንባ እና በሕመም ይህችን ዓለም ይሰናበታል፡፡ ሁሉም የከንቱ ከንቱ ነው! ምኞት ትጠፋለች! ሰውም ወደ ትክክለኛው የሕይወት እውነታ ይነቃል፡፡ ይህችም ከንቱ ሕይወት እንዴት እንደምትነጉድ (እንደምታልፍ) ማንም አያስተውልም፡፡ ዓመታት ያልፋሉ ወራትም ይጠቀለላሉ ጊዜያትም ሳይገቡን ይሳሳባሉ ድንገትም ‹ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል› የሚል መልእክት ይመጣልናል(ኢሳ 38፡1)፡፡ ያን ጊዜም የሰይጣን ማተለል ያለግርዶሽ የተገለጠ ይሆናል፡፡የሚሞትም ዓለም ስለ እርሱ ምን ዓይነት ጠቃሚ ሚና እንደተጫወተች በመረዳት ይሞታል፡፡ ጸጸት እና ጭንቀትን ይሞላል፡፡ በዋዛ ላለፉበትም ጊዜያት ዋጋን ይከፍላል፡፡ንስሐም ገብቶ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ይችል ዘንድ አንዲት ቀን ለመግዛት ዕድሜ ዘመኑን ያጠራቀመውን ሃብት ሁሉ መስጠትን (መለወጥን) ይሻል፡፡ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አንዲት ዕድል እንኳን አያገኝም፡፡ ቀድሞ በሥጋው ወራት ‹ጊዜ› ለዓመታት በእርሱ ግልጋሎት ስር የነበረ ቢሆንም ከመጠን በላይ በሥራ በመጠመድ ፣ በመጠጥ ቤቶች ፣ በፊልም ቤቶች እና በአሳፋሪ ምኞቶች አባክኗቸዋልና፡፡ ጠቢብስ የዚህችን ዓለም ጊዜያዊ የምድር ሕይወት ማታለል የተረዳ ፤ ከብዙም ትርፍ ጋር በሰማይ በእግዚአብሔርም ከተማ ካለው ሃብት ያገኘው ዘንድ ስንቁን ወደ ላይኛው ቤት የሚያግዝ ብልህ ነጋዴ ነው፡፡ ጠቢብስ መከራ የሌለበት የጽድቅን ሕይወት ለዘላለም የሚኖር ነው፡፡ ሰካራም ፣ ስግብግብ ፣ ገንዘብ ወዳድ ፣ ነውረኛ ፣ ነፍሰ ገዳይ እንዲሁም የቀሩት ከእኔ ጋር የኃጢአት ማኅበርተኞች የሆኑ እና ዋናቸው የምሆን እኔ ሰነፍ ግን ወደማይጠፋ እሳት እንጣላለን፡፡

እነሆ አሁን ፀሐይ ታበራለች ፤ ቀንም ውብ ብርሃኗን በእኛ ላይ አድርጋለችና ከሕይወት በኋላ የሚሆነው መጪው ጨለማ ሳይቆጣጠረን ወደምንታረምበት ጎዳና ፈጥነን እንራመድ! በዚያች ጊዜ (ከሞት በኋላ) ልንላወስ አንችልምና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በማይሞት ቃሉ እንዲህ ሲል ይጮሃል ‹የተወደደ ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው› (2ኛ ቆሮ 6፥2)

(source:-By Elder Ephraim: On Rememberance of Death, Hell, and judgement)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
አዲሱ ዓመት ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የተሰጠን ሌላ አዲስ ዕድል ነው። አማኑኤል ከእኛ ጋር ለመሆን የእኛን ሥጋ ተዋሕዷል። አምላክነቱ ሳያሳስበው የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አድርጉዋል። በደሃ ቤት አድሯል፣ በበረት ተወልዷል፣ ከብርድ መከለያ ጨርቅን ፈልጓል፣ ፍጥረትን የሚመግብ እርሱ ከእናቱ የድንግልናዋን ወተት ለምኖ አልቅሷል፣ እንደ ሕፃናት በጉልበቱ ድኋል፣ ለእናቱ እየታዘዛት ጥቂት በጥቂት አድጓል። ከአደገም በኋላ ራሱን የሚሰውርበት ጎጆ ሳይኖረው በተራራ ተንከራቷል፣ ተርቧል፣ ከኃጢአተኞች በደረሰበት ተቃውሞ ተሰድቧል፣ ተገፍቷል። ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ሆኗል።

ከእኛ ጋር ለመሆን ብቻ ሳይሆን በእኛ ውስጥ ለመኖር ደግሞ በእለተ አርብ በመስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ተሰጥቶናል። እኛስ ወደ እርሱ ሊያቀርበን ይህን ሁሉ ከሆነልን አምላክ ጋር ለመኖር ምን አደረግን? ለእርሱ ብለን ክፋትን አወገዝን? የተሸከምነውን ኃጢአት በንስሐ አራገፍን? ሥጋ ወደሙን ተቀበልን? 

ከእግዲህስ በኃጢአት ያረጀ ማንነታችንን እንተው። አዲሱን ዓመት  "ማለዳ ማለዳ አዲስ" ከሆነው ፈጣሪያችን ጋር ለመኖር ለራሳችን ብሩህ ተስፋ እንሰንቅ። እስኪ አምና ወድቀን ከተሰበርንበት የዘር፣ የጥላቻ ጉድጓድ ወጥተን ዘንድሮን ተዋድደን፣ ተፋቅረን በሰላም እንኑር። እስኪ ደግሞ ወደ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበን ይህችን ዓመት በሰላም ጀምረን እንፈጽማት።

መልካም አዲስ ዓመት!!!


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
የጌታውን እናት የሰላምታ ድምጽ ሰምቶ በማኅጸን በደስታ የዘለለውን (የሰገደውን) ጽንስ፣ በንጉሡ ፊት በክፉት የደነሰችው ልጅ አንገቱን አስቆረጠችው።

ጽንሱ ስለ ሕይወት መምጣት በጠባቡ አዳራሽ በማኅጸን ሲያመሰግን፣ የሄሮድያዳ ልጅ ግን የነቢዩን ሕይወት ስለ ማስጠፋት በሰፊው የንጉሡ አዳራሽ ዘፈነች።

አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ልጆች በሄሮድያዳ ምክር የማይሄዱበት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ሆነው የሚያድጉበት በጎ ዘመን ያድርግልን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
📕 የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የአንባብያን ኅብረት
በ2014 ዓ.ም. ለአንባብያን ታላቅ የምሥራች 📘

ከወርኃዊው የመጻሕፍት ዳሰሳ ጋር በአንድ ላይ የሚካሄድ አንባብያንን የሚያነቃቃ ባለ 12 ዙር የጥያቄና መልስ ውድድር መስከረም 30 ይጀምራል:: ቅዱስ ፊልጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ያቀረበውን "የምታነብበውን ታስተውለዋለህን?" የሚለውን ወርቃማ ጥያቄ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ለዚህ ዘመን አንባቢዎች ድጋሚ ለማቅረብና ስለሚያነብቡአቸው መጻሕፍት ያላቸውን ማስተዋልና መረዳት ለመለካት "ፊልጶስ እና ባኮስ" የተሰኘ እጅግ ደማቅ የጥያቄና መልስ ውድድር አዘጋጅቶአል::

📚 ተወዳዳሪዎች

የጥያቄና መልስ ውድድሩ ላይ ለመሳሣተፍ አንባብያን ሁሉ የተጋበዙ ሲሆን ለተወዳዳሪነት የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላት በየወሩ የመጀመሪያ አምስት ቀናት በGoogle form መመዝገብ ይቻላል:: ተወዳዳሪዎች ቅጹን እንደሞሉበት ቅደም ተከተል በውድድሩ ላይ የመካፈል ዕድል የሚያገኙ ሲሆን በዚህ የውድድር ዓመት በ12 ዙር የ ፊልጶስ እና ባኮስ ጥያቄና መልስ ውድድር ላይ የሚካፈሉት በየዙሩ 6 በጠቅላላው 72 ተወዳዳሪዎች ይሆናሉ::

📚 የጥያቄና መልሱ ይዘት

ፊልጶስና ባኮስ የጥያቄና መልስ ውድድር ዲያቆኑ ፊልጶስ እና ጃንደረባው ባኮስ እንደተጠያየቁበት "ትንቢተ ኢሳይያስ" ሁሉ ጥያቄና መልሱ የሚያጠነጥነው በአንድ የተመረጠ መጽሐፍ ላይ ብቻ ነው::

ለምሳሌ :- ለመስከረም 30፣ 2014 ዓ.ም. ለ"ፊልጶስ እና ባኮስ ጥያቄና መልስ ውድድር" የተመረጠው መጽሐፍ :- የዲያቆን ያረጋል አበጋዝ "ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ" የተሰኘው መጽሐፍ ሲሆን በውድድሩ ላይ የሚወጡት ጥያቄዎችም ሙሉ በሙሉ ከዚህ መጽሐፍ ላይ ብቻ ይሆናሉ::

በዚህ መሠረት በየወሩ በፊልጶስና ባኮስ የጥያቄና መልስ ውድድር ላይ የሚወዳደሩ ተወዳዳሪዎች አስቀድሞ በወሩ መጀመሪያ ላይ ከምዝገባው ጋር ይፋ የሚሆነውን የተመረጠውን መጽሐፍ ከጫፍ እስከጫፍ አንብበው ለውድድሩ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል::

📚 ሽልማቶች :-

በፊልጶስና ባኮስ ወርኃዊ የጥያቄና መልስ ውድድር ላይ በየዙሩ የሚሣተፉና ከ1-3 የሚወጡ ተወዳዳሪዎች በውድድሩ ዕለት እዚያው ሽልማት ያገኛሉ:: በዚህም መሠረት :-

1ኛ ለሚወጡ :- የአንድን የጥንት ወይም የቅርብ መንፈሳዊ መጽሐፍ ደራሲ ሁሉንም ሥራዎች ስብስብ (Full collection)

2ኛና 3ኛ ለሚወጡ :- የዚያኑ ደራሲ አንድ አንድ መጻሕፍት ይሸለማሉ::

በ12ቱ ዙሮች ተወዳድረው አንደኛ የሚወጡ አንባብያን ደግሞ ለአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር የሚቀርቡ ሲሆን በመጨረሻው ዙር አሸናፊዎች :-

1ኛ ለሚወጣ (ለምትወጣ):- በብዙ መጻሕፍት የተሞላ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ የመጽሐፍ መደርደሪያ ሼልፍ

2ኛ ለሚወጣ (ለምትወጣ) :- በሶፍት ኮፒ መጻሕፍት የተሞላ የመጽሐፍ ማንበቢያ ኪንድል (Kindle)

3ኛ ለሚወጣ :- በማይክሮ ፊልም በተነሡ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት የተሞላ ሀርድ ዲስክ የሚሸለሙ ይሆናል::

መስከረም 30 የሚካሔደው የመጀመሪያው ዙር የፊልጶስና ባኮስ የጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ለመካፈል ለምትፈልጉ አንባብያን ምዝገባው ከመስከረም 1-5 ባሉት ቀናት መሆኑን እንገልጻለን::

#የሚከለክለኝ_ምንድን_ነው?

ለመመዝገብ ይህንን ይጫኑ

https://forms.gle/hS8YCaMJC6GGSpTA8

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ
ቅዱስ ባስልዮስ "ሰውነታችን ያለ እስትንፋስ መኖር እንደማይችል፣ ነፍሳችንም ፈጣሪዋን ሳታውቅ ሕያው ሆና ልትኖር አትችልም። የነፍስ ሞቷ እግዚአብሔርን አለማወቋ ነውና" ይለናል፣ እውነት ነው፤ ለመሆኑ እግዚአብሔርን ማወቅ ምን ማለት ነው?

እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት ስለ እርሱ የተጻፉ መጻሕፍትንና የተነገሩ ትምህርቶችን ማንበብ፣ መስማት ብቻ አይደለም። እነዚህ ብቻቸውን "ስለ እግዚአብሔር እንድናውቅ" እንጂ "እግዚአብሔርን እንድናውቀው" አያደርጉንም። "ስለ እግዚአብሔር ማወቅ" የመጨረሻው ዓላማችን ወደ ሆነው "እግዚአብሔርን የማወቅ ሕይወት" የምንገሰግስበት መንገድ እንጂ ራሱን ችሎ መዳረሻና ማረፊያ ወደብ አይደለም።

"እግዚአብሔርን ማወቅ" በተግባር የሚገለጥና ከፈጣሪ ጋር የምናደርገው የአንድነት ሕይወት ነው። እኛ በእርሱ፣ እርሱም በእኛ የሚኖርበት ልዩ ምሥጢራዊ ውሕደት ነው። "እግዚአብሔርን ማወቅ" ማለት ስለ እርሱ ሲነገር በጆሮ የሰሙለትን አምላክ ከብቃት ደርሶ ማየትና በፍጹም ልብ መውደድ ነው። ይህ ደግሞ ራሱ ጌታችን በወንጌል እንደተናገረው የዘላለም ሕይወት ነው።(ዮሐ 17፥3)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ "እየጠላን የምናደርገው" +++

ብዙ ሰው ‹‹እኔ ሐሜት አልወድም፡፡ ግን ማማት የሚወዱ ጓደኞች አሉኝ›› ይላል፡፡ አሁን እርሱ ምን እያደረገ ነው? ‹‹ወዳጆቼ ሐሜተኞች ናቸው›› ሲል እያማቸው አይደለምን? ወይስ ለእርሱ ሲሆን ሐሜቱ ተለውጦ የመረጃ ቅብብል ይሆናል?! በነገራችን ላይ ይህ የዚህ ጽሑፍ መግቢያ ራሱ ሐሜት ነው።

የማንወደው ነገር ግን እየጠላንም ቢሆን የምናደርገው ኃጢአት ሐሜት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐሜተኛ ሆኖ የተጠቀሰው በእባብ ያደረው ሰይጣን ነው፡፡ በመጀመሪያ የታማው ደግሞ እግዚአብሔር ሲሆን፣ ሐሜቱን ሰምታ ሳትመረምር የተቀበለችውና ለስሕተት የቸኮለችው ሴት ሔዋን ነበረች፡፡(ዘፍ 3፥1-5)

የሰይጣን ሐሜት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንደኛ "አትሞቱም፤ እንደ እርሱ እንዳትሆኑ ነው የከለከላችሁ" በሚለው ንግግሩ "እግዚአብሔር ዋሽቷችኋል" እያለ ፍቅሩን እንድትጠራጠር እያደረገ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ከዛፉ ብትበሉ እንደ እርሱ ትሆናላችሁ በማለት የእግዚአብሔር አምላክነት "የዛፍ ፍሬ" በመብላት የተገኘ መሆኑንና እርሱም እንደ እነርሱ የነበረበት ጊዜ እንዳለ እንድታስብ እየገፋፋት ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ስም ማጥፋት (Character assassination) ከየት ሊገኝ ይችላል? ሰይጣን በነገር ሁሉ ፍጹም የሆነን አምላክ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ሐሰት ፈጥሮ ለማማት ወደ ኋላ ካላለ፣ አንዳች ጉድለት የማያጣብን እኛማ ከሐሜቱ ጅራፍ ልናመልጥ እንደማንችል ሊታወቅ ይገባል፡፡

በተለይ በአሁን ጊዜ ሐሜት በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ሥሩን ሰድዷል። እንደውም ባልንጀራን ማማት እንደ ምግብ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቻችን በዚህች ደሃ አገር ከመጠን በላይ ወፍረን እንቸገር ነበር። ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችን የሐሜት አውድማዎች ሆነዋል። በየገጾቻችን ከሽነን የምናቀርባቸው ጽሑፎች ጠረናቸው የሰው ሥጋ የሰው ሥጋ ይላሉ። ፊታችን በሐሜት ወይቦ ሁለት መልክ ካወጣን ቆየን። ይኸው ሳንባችን በማማት አየር ተመርዞ ሳሉ ከበረታብን ሰነባብተናል። ወዳጃችንን የማናማበት ብቸኛው ጊዜ ከእርሱ ጋር የምንሆንበት ሰዓት ነው። ያውም ደግሞ ያንኑ ጊዜ ሌላኛውን ሰው ለማማት ካልተጠቀምንበት ማለቴ ነው።

ሊቁ ዮሐንስ ካዝያን እንደሚናገረው ሰው ከሚጠቅመው ቃለ እግዚአብሔር ይልቅ የማይጠቅመው ሐሜት ያጓጓዋል። የአምላክ ቃል ሲነገር እንቅልፍ እንቅልፍ የሚለው ሁሉ፣ የሐሜት ነገር ሲሆን ግን እንደ እርሱ ንቁ የሚሆን የለም። በጥፍሩ ቆሞ ይሰማል። ሌሊቱን ሁሉ ሳይተኛ ቢያድር ደስ ይለዋል።

ለመሆኑ ባልንጀራችንን ስለ ምን በቀስታ እናማዋለን? የወዳጃችንንስ ውድቀት በማውራት በእኛ ላይ የምንጨምረው ምን በጎ ነገር አለ? በሰው ፊት መልካም እየመሰልን ከኋላው ግን ስለ እርሱ ውድቀት በማውራት የራሳችንን ደረጃ ከፍ ማድረግ አይቻልም። ስለ ሌሎች በማውራት የምናጠፋውን ሰዓት ራሳችንን ለማሳደግ ብንጠቀምበት ኖሮ "መኖራችንን ትርጉም እንዲኖረው" ማድረግ ይቻለን ነበር።

"ንጹሕ ወዳጅነት" ሐሜትና ማሾክሾክ የሌለባት የታማኞች ጌጥ ናት። የሐሜት ስለታቸውን ያልጣሉ ሰዎች "እውነተኛ ባልንጀርነት"ን አያውቋትም። አንተ በፍቅር ወዳጅ አድርገህ ከፊትህ ስታቀርባቸው እነርሱ ከኋላህ ሆነው የሚያሙህን አትጥላቸው፤ አትጣላቸው። ነገር ግን የሐሜቱ እርሾ እንዳያገኝህ ቶሎ ተለያቸው። ከፊትህም አድርገህ አታሰቃያቸው። የእነርሱ ቦታ ከኋላህ መሆን ነው።

ሐሜት የሰይጣን ነው። ሰውን የሚያማ በገዛ ፈቃዱ አንደበቱን ለሰይጣን አሳልፎ የሰጠ ነው። ማማት በቤተ ክርስቲያን መለያየትን ያመጣል፣ ቤተሰብ ይበትናል፣ ወንድሞችን ያጣላል። ብንችል ስለ ሰው የምናውቀውን ጥሩውን እናውራ። የምናወራው ጥሩነት ከሌለው ደግሞ ቢያንስ ምንም አንበል።

ሔዋን ልክ እንደ አዳም እባብን "ሂጅልኝ" ብላ ብታባራት ኖሮ እነርሱም ከፈጣሪ ባልተጣሉ ሐሜትም ወደ ዓለም ባልገባ ነበር። ሐሜትን ማጥፋት ከፈለግን ሐሜተኛን እሺ አንበል። ማር ይስሐቅም "ወዳጁን በፊትህ የሚያንኳስሰውን ሰው አፉን መዝጋት ባትችል እንኳን ቢያንስ ሐሜቱን ከመስማት ተቆጠብ" ይላል። ሐሜትን ደስ ብሎህ ካልሰማኸው ደስ ብሎት የሚያማን ሰው ልትፈጥር አትችልም።

"ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ" ገላ 5፥15

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ "እግዚአብሔር የጣላት እሳት" +++

በደብተራ ኦሪት በመሠዊያው ላይ የሚነደውና መሥዋዕቱ ይቃጠልበት የነበረው እሳት ከሰማይ የወረደ ነበር። ይህም እሳት ዘወትር እንዳይጠፋ የአሮን ልጆች (ካህናቱ) ማለዳ ማለዳ እንጨት እየጨመሩ እንዲያቀጣጥሉና እንዲያነዱት እግዚአብሔር አዝዟቸዋል።(ዘሌዋ 6፥12) ከማዕጠንት ጀምሮ እስከ እንስሳት በድንኳኑ የሚቀርቡ ማናቸውም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ሁሉ የሚበሉት ከሰማይ በወረደው በዚህ "የእግዚአብሔር እሳት" ነው።

ታዲያ ከእለታት በአንዱ ቀን የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እንዲህ አደረጉ። ለእግዚአብሔር የእጣን መሥዋዕት ማቅረብ ፈልገው ለየራሳው ጥናውን (ማዕጠንት) አነሡ። ነገር ግን በጥናው ውስጥ ያደረጉት ከሰማይ የወረደውን "የእግዚአብሔር እሳት" ሳይሆን፣ ከመንደር ጭረው ያመጡትን ወይም ራሳቸው ያቀጣጠሉትን "ሌላ እሳት" ነበር። በዚህም እግዚአብሔር ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት ስላቀረቡ አምላክ ተቆጣ። በፊቱም እሳት ወጥቶ እንዲበላቸው አደረገ። እነርሱም ወዲያው ሞቱ።(ዘሌ 10፥1-3) ሊቀ ካህናቱ አሮንን እየተከተሉ እንዲያገለግሉ የተመረጡት ሁለቱ ልጆቹ ገና አገልግሎታቸውን በቅጡ ሳይጀምሩ ተቀሰፋ። ለመሆኑ እነዚህ ሁለት የኦሪት ወጣት ካህናት የተቀጡበት "የሌላ እሳት" ታሪክ ለሐዲስ ኪዳኑ ዘመን ምን ምሳሌ ይኖረው ይሆን?

እግዚአብሔር በኦሪቱ ድንኳን እሳትን እንዳወረደ፣ በሐዲስ ኪዳንም የሰውን ልጅ ለማዳን ከሰማይ ሲወርድ ይዞልን የመጣው እሳት አለ። "እሳተ አምጻእኩ ለብሔር፤ ወምንተ እፈቅድ ዘእንበለ አንድዶታ" - "በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ?" እንዳለን።(ሉቃ 12፥49) ይህ መድኃኒታችን በምድር ላይ የጣለው እሳት ምንድር ነው? አገልግሎቱስ እንዴት ነው?

ጌታችን በምድር የጣላት እሳት "ወንጌል" ትባላለች። ሰው ሰውነቱን ንጹሕና የተቀደሰ ሕያውም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብባት "የእግዚአብሔር እሳት" ወንጌል ነች። ይህች ወንጌል ጌታ አንድ ጊዜ በምድር የጣላት፣ እኛ ደግሞ ለዘወትር እንዳትጠፉ የምናቀጣጥላትና የምናነዳት እሳት ነች። የማቀጣጠያው እንጨቶችም ቃለ እግዚአብሔርን መስማት እና ማንበብ ናቸው። ያለ ወንጌል እሳትነት ምንም መሥዋዕት እንድናቀርብ አልተፈቀደልንም። ነገር ግን እንደ አሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ ከመንደር ቆስቁሰን ወይም ራሳችን አቀጣጥለን የምናመጣቸው "ሌላ እሳት" የተባሉ ከንቱ ፍልስፍናዎችና እንግዳ ትምህርቶች የእግዚአብሔርን ቁጣ ይቀሰቅሱብናል።

ዳግመኛም እሳት የተባለው በጥምቀት ጊዜ በሁላችንም ላይ የወረደው ጸጋ እግዚአብሔር ነው። ይህም ጸጋ ለመዳናችን ዓይነተኛ ሚና አለው። ይሁን እንጂ ልክ በደብተራ ኦሪት እንደ ወረደው እሳት ካልተንከባከብነው እና ካላቀጣጠልነው ሊዳፈን እና የሌለ ሊመስል ይችላል። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ "እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው...በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ሥጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ" በማለት የሚመክረው።(2ኛ ጢሞ 1፥6) እግዚአብሔር ለሰጠን ጸጋ ማቀጣጠያዎቹ ደግሞ ጾም፣ ጸሎትና መንፈሳዊ ትሩፋት ሁሉ ናቸው። እርሱ የሰጠንን የጸጋ እሳት ከማቀጣጠል ይልቅ "ሌላ እሳት" እናምጣ ያልን ቀን ግን ታላቅ ጥፋት ያገኘናል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኹት፥ እርስዋንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ የዘላለም ማረፊያው በሆነች በእናቱ ፍቅር እኖር ዘንድ፤ እርሷን ደስ አሰኝ ዘንድ ፤ ያማረው የፊቷንም ብርሃን እመለከት ዘንድ፤ በዓለም ካሉት አእላፋት ዝና ይልቅ ልቤ የድንግልን ፍቅር ይመኛል፣ የዓለሙ ዝና ነፍስን ለሚያቆስል ትዕቢት አሳልፎ ስለሚሰጥ ምን ይጠቅመኛል? የድንግል ፍቅር ግን ዕረፍትና ጸጥታ ይሆነኛል፣ ወደ መዳን መንገድም ስቦ ያስገባኛል፤ ልቡናዬ የክብርሽን ገናንነት ይናገር ዘንድ ይወዳል፥ መላሴ ግን በኃጢአት ፍሕም የተበላ ኮልታፋ ሆኖ ተቸግሯል፤ የልሳኔን ልቱትነት አርቀሽ፥ እኔ ደካማ ባሪያሽን በምስጋናሽ ቃል የምትሞይበት የኃይል ቀን መቼ ነው? ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደ ምትናፍቅ እኔም ምስጋናሽን እየተጠማሁ ያቺን ቀን እናፍቃለሁ። መቼ እደርሳለሁ? መቼስ አንቺን አመሰግንሻለሁ?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ ‹‹እስክ ዛሬ ያላወቅነው›› +++


በዚህ ዓለም ካሉ ነገሮች ውስጥ በጣም የምታውቀው ማንን ነው? ተብለህ ብትጠየቅ መጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጣው መልስ ምንድን ነው? ‹‹ራሴን ነዋ!›› አትልም; ብዙ ሰው በጣም እርግጠኛ ሆኖ ከሚያውቃቸው ነገሮች ውስጥ የመጀመሪያው ራሱን እንደ ሆነ ሊያስብ ይችላል፡፡ በርግጥ ላንተ ከአንተ የተሻለ አንተን የሚቀርብ ሌላ አካል የለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ከራስህ ጋር ያለህ ቀረቤታ ራስህን ለማወቅህ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ለዓይን ከቅድብ የቀረበ ምን አለ? ነገር ግን በመስታወት ካልታገዘ በቀር ዓይናችን አንድም ቀን ቅንድቡን አይቶት አያውቅም፡፡

በተለይ የኖርንበት ማኅበረሰብ እና ያደግንበት ባሕል ‹‹ራስን ስለ ማወቅ›› ያለው ግንዛቤ ትንሽ ያልጠራ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ ‹‹ዐዋቂ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹‹ዐዋቂ›› የሚለው ስያሜ ተምሮ በያዘው ዲግሪ፣ ዲፕሎማ፣ ወይም ባደረገው አንዳች ማኅበራዊ አስተዋጽዎ ምክንያት የተሰጠው አይደለም፡፡ ‹‹ራሱን የሚያውቅ›› ለማለት ነው፡፡ ሌላው ጠንከር ያለ ወቀሳና ምክር የደረሰበትም ሰው ከሚዘንብበት ትችት ለማምለጥ የሚጠቀምባት አመክንዮ ‹‹እኔ ልጅ አይደለሁም፤ ራሴን ዐውቃለሁ›› የምትል ነች፡፡ ወይ ራስን ማወቅ!

ራስን ማወቅ እንዲህ እንደምናስበው በቀላሉ የሚደረስበት ነገር አይደለም፡፡ ትክክለኛው ማንነታችንን ለማየት መጀመሪያ መውጣት የሚጠበቅብን አድካሚ የሆነ የትሕትና ዳገት አለ፡፡  ከእኛ ውጭ ያለን ሌላ ቁስ ለማየት የቻልነው እርሱ በቆመበት ቦታ ላይ ስላልቆምን ነው፡፡ ራሳችንንም መመልከት ከፈለግን መጀመሪያ እኛ የሌለንበትን ተቃራኒ አቅጣጫ ፈልገን ማግኘት አለብን፡፡ ይህ ራሳችንን ቆመን የምናይበት ትክክለኛው እና እኛ የሌለንበት ተቃራኒ አቅጣጫ ደግሞ ትሕትና ነው፡፡ እርሱ ላይ ስንቆም ራሳችንን እያየን መታዘብ ትጀምራለህ፡፡ ‹‹አሁን እንዲህ ማድረግ ትክክል ነው?›› እያልን ራሳችንን እንጠይቃለን፣ እንወቅሳለን፣ እናርማለን፡፡

ለሰው ራስን ማወቅ ምን ያህል እንደሚከብደው የምንረዳው በሌሎች ላይ ሲፈርድ ስናይ ነው፡፡ እንደ ግንድ ተሸክሞት ያጎበጠው ኃጢአቱን ትቶ የሌሎችን ስህተት ቀና ብሎ ሲመረምር፣ እንደ ግመል ገዝፎ በዓይኑ ፊት የቆመው የገዛ ድክመቱን ውጦ እንደ ትንኝ ያነሰውን የወንድሙን ጥፋት ሲያጠራ ማየት ‹‹ሰው ምን ያህል ራሱን ባያውቅ ነው?›› ያሰኛል፡፡ ጌታም በወንጌል ‹‹እናንተ እውሮች መሪዎች፤ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ›› ሲል የገሰጻቸው እንዲህ ዓይነቱን ጠባይ የተላበሱ ፈሪሳውያንን ነው፡፡(ማቴ 23፡24) በመጽሐፈ መነኮሳት እንደ ተጻፈ አንድ ወጣኒ መነኩሴ ወደ አረጋዊ አባት መጥቶ ‹‹ለምንድር ነው ሁል ጊዜ በሌሎች ላይ የምፈርደው?›› ሲል ቢጠይቃቸው፣  ‹‹እስከ ዛሬ ራስህን ስላላወቅህ ነው›› ብለው መልሰውለታል፡፡ ስለዚህ ራሱን እያጸደቀ የወንድሞቹን ስህተት ነቃሽ ለሆነ ኃጢአተኛ ሰው ፍቱን መድኃኒቱ ‹ራሱን ማወቁ› ነው፡፡

ሰዎች ራሳቸውን ሳያውቁ የሚቀሩት ስላልቻሉ ብቻ አይደለም፡፡ ራስን ማወቅ ስለማይፈልጉም ጭምር ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ‹ራስን ማወቅ› ይዞ የሚያመጣው ጊዜያዊ ሕመም ወይም ትንሽ ስቃይ አለ፡፡ ወደ ራሳችን መመልከት ስንጀምር የማንፈልገውን ‹‹እኛነት›› በውስጣችን ልናገኘው እንችላለን፡፡ በዚህም መረበሽ፣ መቆጨት፣ ኃፍረት ይሰማን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ስሜት ለማምለጥ ብለን ቅዠታዊ ዓለም ይሄድ ዘንድ ለራሳችን ልንፈቅድለት አይገባም፡፡ ለእኛ ከማንም በላይ ጠላት የሚሆንብን ይህ በውስጣችን የተደበቀውና ማወቅ የማንፈልገው ‹‹ስውር እኛነታችን›› ነው፡፡ ስለዚህም በጊዜ ራስን መርምሮ አፋጣኝ መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ራስን ዐውቆ፣ ከራስ ጋር ተዋውቆ፣ ለንስሐ አባት ድክመትን አሳውቆ፣ የፈጣሪ ጸጋ እና ረድኤቱን እየጠየቁ በትሕትና ለመኖር ያብቃን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ "ለውኃ ለውኃማ..." +++

ብቻ መሆን ከባድ ነው። ለብዙ ፈተናዎች ያጋልጣል። የቀደመች እናታችን ሔዋን ሰይጣን አሰነካክሎ የጣላት ብቻዋን መሆኑዋን አይቶ ነው። ብቻ ሲሆኑ እያየ መፈተን የለመደ ሰይጣን ክርስቶስንም በቆሮንቶስ በረሃ ብቻውን ባየው ጊዜ ፈተናውን ይዞ ወደ እርሱ ቀርቦ ነበር። ክርስቶስ ግን የማንም ምክርና እገዛ የማያስፈልገው አምላክ በመሆኑ በገዛ ሥልጣኑ ድል አድርጎታል። በኋላም የሰው ልጅ "ያለ መካሪ ሲቀር ደስ የሚለው" የሰይጣን መጫወቻ እንዳይሆን የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዎቹ ካህናት ሐዋርያትን ሰጠን።

የክርስቶስ አካሉ የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿ በራሳቸው ማስተዋል ተደግፈው እንዳይጠፉባት፣ ቀዛፊ እንደ ሌለው ታንኳ በየአቅጣጫው በሚነፍሰው የወሬ ነፋስ እንዳይነዱ የሚጠብቁላትና በቀናው ጎዳና እየመሩ በጎውን መንገድ የሚያስተምሩላት ካህናት አሏት። እነዚህም ካህናት በዋናነት ሁለት አገልግሎት አላቸው። አንደኛው "በምድር የፈታችሁት በሰማያት የተፈታ ይሆናል" ተብሎ በተሰጣቸው አምላካዊ ሥልጣን መሠረት ንስሐ ለሚገቡ ምእመናን ላለፈው በደላቸው ሥርየትን ማሰጠት ነው።(ማቴ 16፥19) ሁለተኛው ደግሞ እነዚያ ንስሐ የገቡ ምእመናን ከገቡበት የኃጢአት ወጥመድ የሚወጡበትንና ጤናማ የሆነ የተረጋጋ ሕይወት የሚመሩበትን በጎ ምክር መለገስ ነው።

ይሁን እንጂ አንዳንዶቻችን ንስሐ ለመግባት ካልሆነ በቀር ካህናትን ቀርቦ ለማማከር ብዙም ፈቃደኝነት አናሳይም። ችግሮቻችን ተረድተው መፍትሔ የሚሰጡንም አይመስለንም። እንደውም ትንሽ የዘመኑን ሳይንስ የቀመስን ከሆንማ "አባም ጋር ብሄድ ያው የሚሉኝ ነገር የታወቀ ነው። ታዲያ ለምክሩ፣ ለምክሩ አንደኛዬን የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ጋር ብሄድ አይሻልም" የሚል አስተያየት እንሰጣለን። በርግጥም በዚህ ረገድ ጥሩ አገልግሎት የሚሰጡ በዓለም ያሉ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች አሉ። ወደ እነርሱ መሄድም ኃጢአት አይደለም። አንተን የሚያስወቅስህ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ጋር መሄድህ ሳይሆን፣ በካህናቱ በኩል ልታገኝ የምትችለውን ጠቃሚ ምክርና መፍትሔ አሳንሰህ ማየትህ ነው።

የሶርያ የጦር ሠራዊት አለቃ የነበረው ንዕማን ሰውነቱ በለምጽ በነደደ ጊዜ ፈውስን ፍለጋ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መጥቶ ነበር። ነቢዩም ንዕማንን ከደጃፉ እንደ ቆመ ባወቀ ጊዜ "ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ" ብሎ መልእክተኛ ላከበት።(2ኛ ነገ 5፥10) ንዕማንም የነቢዩን ቃል ሲሰማ ተቆጣ። እኔ የአምላኩን ስም እየጠራ በእጆቹ ዳስሶ ይፈውሰኛል ስል፣ እርሱ እንደ ቀላል ነገር በዮርዳኖስ ታጠብ ይለኛል። ደግሞ ለውኃ ለውኃ "የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን?" አለ። ወታደሩ "በዮርዳኖስ ውኃ ታጠብ" የሚለውን ትእዛዝ እንጂ በነቢዩ ቃል አድሮ የሚሠራውን ኃይለ እግዚአብሔር አላስተዋለም። ስለዚህም የዮርዳኖስን ወንዝ እርሱ ከሚያቃውቃቸው የአገሩ ዝነኛ ተፋሰሶች ጋር አነጻጸረው። በኋላ ግን በባሪያዎቹ አሳሳቢነት ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ቢል ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ሥጋ ለመለመለት።

በርግጥ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ ካህናት የሚሰጡህ ምክሮች ከሌላ ባለሙያዎች ልታገኛቸው የምትችላቸውን ዓይነት ሊሆኑብህ ይችላሉ። አንዳንዴም አንተ የምታውቀው ቦታ ላይ የሚሰጠው የምክር አገልግሎት ልክ እንደ ደማስቆ ወንዞች ካህናቱ ከሚሰጡህ ምክር የበለጠ በንድፈ አሳቦችና በትግበራዎች የበለጸጉ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ። ነገር ግን ከካህናቱ አንደበት የምትሰማው ምክር "ለውኃ ለውኃማ" ብለህ የምታቃልለው ባዶ ቃል አይደለም። በውስጡ ልቡናን የሚመረምርና የሚለውጥ ኃይለ እግዚአብሔርን፣ ረድኤተ እግዚአብሔርን የተሸከመ ክቡድ ቃል ነው። እንደ ለምጽ ከወረረህ ችግር ሁሉ ሊገላግልህ የሚችል የሚሠራ ቃል ነው።

በትዳር ጉዳይ በሮማውያን ሸንጎ ፊት እየተካሰሱ ካህናቱን ያሳጡ እንደ ነበሩት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች፣ እኛም አንዳች እክል ሲገጥመን መካሪ እንደ ሌላት ነገር ፈጥነን ቤተ ክርስቲያንን እየጣልን  ወደ አንኮብልል። አንዱን ለመያዝ ሌላውን ማንጠልጠልና ማንኳሰስ አይጠበቅብንም። ካህናቱን እናማክር፣ የሥነ ልቡና ባለሙያዎችንም ቸል አንበል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+ የቄስ ትምህርት ቤት +

በመሳይት ውበት
/በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ
የቄስ ትምህርት ቤት ፕሮጀክት ሰብሳቢ/

ከሰሞኑ እጄ የገባውን ጥናታዊ ጽሑፍ ለማንበብ ስገልጠው በመጀመሪያው መግቢያ ላይ “የአንድ ሰው የከበረ ንብረት ለሌላኛው የወደቀ ቆሻሻ ነው፣ የአርስቶትል ራስን ማወቅ የሚለው የፍልስፍና ሃሳብ የራስን የከበረ ሀብት አሽቀንጥረን እንዳንጥል እና የሰዎችን የወደቀ ቆሻሻ እንዳንሰበስብ ይጠብቀናል" (One person’s treasure is another person’s trash. Aristotle’s ‘Know Thy Self’ protects not to trash one’s treasure and not to treasure another’s trash)” የሚል ዐረፍተ ነገር አነበብኩ፡፡

ገና ከርእሱ ቀልቤን የሳበውን ጥናት የበለጠ ወደድኩት፡፡ ጸሐፊዎቹን እያመሰገንኩም እየመረቅኩም ማንበቤን ቀጠልኩ፡፡ መረጃን ሰድሮ ማስቀመጥ እንደ ዛሬው ሳይቀል፣ ዘመናዊ ትምህርት በየመንደሩ ሳይከፈት፣ ስለ ዓለም ማወቅ እንዲህ እንደ አሁኑ እንጀራ መጉረስ ባልሆነበት ዘመን ባሕልን፣ ጥበብን፣ ሥርዓትን፣ ዕውቀትን እና ሃይማኖትን ከነ ሙሉ ክብሩ ሳይሸራረፍ ዘመንን አሻግሮ፣ ትውልድን አሳልፎ ለኛ ስላደረሰው፣ ባለውለታችን ስለሆነው የቄስ ትምህርት ቤት ያትታል፣ መረጃና ማስረጃን እያጣቀሰ ስለ ሀብትነቱ እና ስለ መልካም አበርክቶዎቹ ይናገራል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር በላይ ተፈራ እና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር በላይ ሐጎስ የተጠናው ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ትምህርት ጆርናል (The Ethiopian Journal of Education Vol. XXXVII No. 2) ታትሞ የሚገኝ ሲሆን፣ እንደ ውጪዎቹ አቆጣጠር በ2017 እንደተጠና ያሳያል፡፡

“ራስን ማወቅ: የልጅነት ትምህርት በተለዋጭ የባሕላዊ ቄስ ትምህርት ቤት አተገባበር (Know Thy Self: Viability of Early Childhood Education Delivery through Traditional Priest Schools)” የሚል ርእስ ያለው ጥናት ነበር፡፡ በጣም ጥቂት እና በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም በተለያየ አጋጣሚዎች ያነበብኳቸውን ስለ ቄስ ትምህርት ቤት የሚያወሱ ጽሑፎችን አስታወሱኝ፡፡

ቀደም ሲል ያነበብኳቸውን ጥቂቶቹን ገጣጥሜ መነሻ ይሆነኝ ዘንድ ስለ ምንነቱ ጥቂት ልበል፡፡ የቄስ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ የትምህርት ሥርዓት ሲሆን፣ አንድ ቄስ ወይም በሃይማኖት ትምህርት ከፍተኛ ዕውቀት አለው ተብሎ የሚታመን ሰው ሕፃናትን ሰብስቦ ፊደልን ከማስቆጠር ጀምሮ፣ አቦጊዳን፣ መልእክተ ዮሐንስን እና መዝሙረ ዳዊትን በግእዝ እና በአማርኛ የሚያስተምር ሲሆን፣ ማንበብ እና መጻፍንም ጠንቅቀው ይችሉ ዘንድ ሕፃናትን በሚገባ የሚያበቃ የትምህርት ሥርዓት ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን አጥቢያዎች እና በገዳማት አካባቢ በሚኖሩ አበው መነኮሳት እና ቀሳቀወስት መምህርነት የሚመሠረት ሲሆን፣ አንድ መምህር ከጀማሪ ሕፃን ጀምሮ ያሉትን ተማሪዎችን በአንድ አድርጎ የማስተማር ጥበብን የያዘ የትምህርት ሥርዓት ነው፡፡

እረኛው ሐኪም በሚለው የግለ ታሪክ መጽሐፍ ላይ ስለ ቄስ ትምህርት ቤት ጸሐፊው ሲገልፁ “መምህሩ አነስ ካለች ከእንጨት የተሠራች ወንበራቸው ላይ ዛፉን ከጀርባቸው ተግነው የቀመጣሉ፡፡ ዝንብ ኖረም አልኖረም የተሠራውን የዝንብ ማባረሪያ ጭራቸውን ይዘው ፊታቸው ላይ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ ያወናጭፋሉ” በማለት በኅሊና ምስልን በሚፈጥር ሁኔታ ገልጸውታል፡፡ ከአገላለጹም እንደምንረዳው ለመማሪያ ይሆን ዘንድ ከሰፊ ዛፍ ጥላ ሥር ትምህርቱ እንደሚሠጥ ያስረዳል፡፡ በአንድንድ ሁኔታዎችም በቤተ ክርስቲያን ጊቢዎች እና በመምህራኑ ቤት ውስጥም እንደሚሰጥ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እንደ ጥናቱ ከሆነ ይህ ሕፃናትን ፊደል ማስቆጠር እና ማስተማር በሀገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረው በ4ኛው ክፍለ ዘመን ክርስትና ወደ ሃገር ውስጥ መግባትን ተከትሎ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሌላኛው በፕሮፌሰር ዳርጌ የተጠናውም ጥናት ይህንን ሃሳብ አጠናክሮ ያስረዳል፡፡ የቄስ ትምህርት ቤት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባለቤትነት ከብዙ ምዕተ ዓመታት በፊት ጀምሮ በተያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች ሲሠጥ የነበረ እንደሆነ እና በተለይም በሰሜኑ የሃገራቸን ክፍል እንደሚገኝ ይጠቅሳል፡፡

አያይዞም የቄስ ትምህርት ቤት ረጅም የሚባል የፍልስፍና፣ የኅብረት ዜማዊ ጸሎት (ቅዳሴ) እና የሥነ ትምህርት ባሕል በውስጡ እንደ ያዘ ይገልጻል፡፡ ሕፃናት ዕድሜያቸው ለፊደል መቁጠር እና መማር ዝግጁ እንደ ሆኑ በመምህራኖቹ ሲታመን እና ሲፈቀድላቸው ፊደልን በመቁጠር ትምህርታቸውን ይጀምራሉ፡፡ ስለ ሕፃናት ትምህርት ሲነሣ “ውይ መች እዚህ ሀገር ተጀመረ ገና”፣ “ኋላ ቀር ነን በዚህማ” እያልን ስንቶቻችን ሀገራችንን እንደ ወቀስን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ዕድሜ እና ጤና ለጸሐፍቱ ይሁንና ዓለም ስለ ሕፃናት ትምህርት እና እድገት ማቀንቀን ሳይጀምር እና በኅሊናውም ሳይገባ አባቶቻችን ግን የሕፃናትን ማስተማሪያ ዘዴ ተረድተው፣ ቦታውን አመቻችተው፣ ለትምህርታቸው ደረጃ አውጥተው (ከቀላል ወደ ከባድ / easy to complex)፣ የሕፃናቱን አቀማመጥ አደራጅተው እና ሃሳቡን አቅለው ህፃናትን ሰብስበው አስተምረዋል፣ ድሮ፡፡

የቄስ ትምህርት ቤት በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ እጅግ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን፣ በከተማ አካባቢዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ እየጠፋ መጥቶአል፡፡ የሀገራችን የመንግሥት ፖሊሲዎች እና በሀገራዊ ሰነዶች የቄስ ትምህርት ቤትን ውለታ ለማስታወስ እና ስለ ነበራቸው ፋይዳ የሚያመሰግኑበት ቦታ እንኳን አላገኙም፡፡ መጻሕፍትና ጥናቶችም ቢሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸውም ባሻገር በሀገሪቷ ላይ ያለውን የቄስ ትምህርት ቤት በተመለከተ ምንም አይነት የተጣራ መረጃ ሊሰጥ የሚችል ስለ ተቋማት ቁጥር፣ የተማሪ ብዛት፣ መገኛ ቦታ እና የመሳሰሉትን የሚገልፅ ምንም ነገር አለመኖሩ በጥናቱ የተመላከቱ ነጥቦች ሲሆኑ፤ የተገኙትም የተወሰኑት ጥናቶች የቄስ ትምህርትን ሀብትነት እና ጥቅም የሚያጎሉ ሳይሆኑ ደካማ ጎኑን በመፈለግ እና በማጉላት የቄስ ትምህርትን ሃይማኖታዊ ብቻ የሆነ፣ ኋላ ቀር፣ በማንበብ እና በመፃፍ ብቻ ላይ ያተኮረ፣ ሳይንሳዊ ያልሆነ፣ የሕፃናትን እድሜ የማይመጥን፣ በማስታወስ ላይ ብቻ የተመሠረተ እና ሌሎችም ብዙ ሚዛናዊ ያልሆኑ ፍርዶችን አስተናግዷል፡፡

ያጎረሰንን እጅ መንከስ ልማድ ሆኖብን የተነሡትን ችግሮች በቅጡ እንኳን ሳንመረምር እና ሳንመለከት ሀብታችንን አሽቀንጥረን ጥለን ዘመናዊ ያልነውን ትምህርት ተቀብለን እንኖር ዘንድ ተፈርዶብን እንጂ፣ በቅጡ ለማየት ብንሞክር ያለው እውነታ እጅጉን የተለየ እና ተቃራኒ ነበር፡፡ ለነዚህ ፍትሐዊ ላልሆኑ አስተያየቶች ምላሽ የሚሆኑ ሃሳቦችን ከመሰንዘሬ በፊት፣ "እረኛው ሃኪም፡ ከእረኝነት እስከ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትነት"፣ በሚል ርዕስ በዶ/ር ምትኩ በላቸው ተጽፎ በአዜብ ወርቁ በተተረጎመው ግለ-ታሪክ መጽሐፍ ላይ በቄስ ትምህርት ፊደል መቁጠራቸውን ብቻ ሳይሆን የማስተማሪያ ሥነ-ዘዴውን እና የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ብለው ገልፀውታል፡፡

ተማሪዎች የምንቀመጠው ከየኔታ (የቄስ ትምህርት ቤት መምህር የኔታ ተብሎ ይጠራል) ፊት ለፊት በግማሽ ክብ ሲሆን ከግንባር የሚቀመጡት ግን በአማርኛ ዳዊት መድገም የደረሱት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከእነሱ ቀጥለው ሁለተኛው ረድፍ
የሚቀመጡት ወንጌል የሚቀጽሉት ናቸው፡፡ የዳዊትም ሆነ የወንጌል ተማሪዎች የሚያነቡትን በቃላቸው ይዘው የማስታወስ ችሎታቸውን ለማዳበር መለማመድ አለባቸው፡፡ ከእነሱ በኋላ የሚቀመጡት አቦጊዳ ላይ የደረሱ ሲሆኑ መጨረሻው ረድፍ ላይ የሚቀመጡት ደግሞ ፊደል መቁጠር የጀመሩት ናቸው፡፡ የኔታ የፈለጉትን ተማሪ ጠቆም የሚያደርጉባት ዘንግ ይይዛሉ፡፡ እኔ ጀማሪ ስለሆንኩ የምቀመጠው ከበስተኋላ ነበር፡፡

ትምህርት እንደ ጀመርኩ በካርቶን ላይ የተለጠፈ የፊደል ገበታ ተሰጠኝ፡፡ ከፊታችን የተቀመጡት የአቡጊዳ ተማሪዎች ፊታቸውን ወደ እኛ ያዞሩ እና ፊት ለፊታችን ይቀመጣሉ፡፡ የፊደል ገበታዬን በግራ እጄ እይዝና በቀኝ እጄ በምይዘው ቀጭን ስንደዶ ፊደሎቹን ጠቆም ሳደርግ ተማሪው ፊደሉን ማን እንደሆነ ይነግረኛል፡፡ እሱ የነገረኝን ጮክ ብዬ እየደገምኩ ወደፊት እና ወደኋላ እየተወዛወዝን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ፊደሎቹን ተራ በተራ በዜማ እየጠራን እንቀጥላለን፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ ከእሱ በንባብ ዕውቀት አነስ ያለውን ተማሪ ይረዳል፡፡ እሱም በተራው ከእሱ በእውቀት ሻል ባለ ሌላ ተማሪ እየተረዳ መጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ ከየኔታ አጠገብ ሆኖ ይማራል፡፡ በዚህ መማማር መሃል አንዳች ስህተት ከተፈጠረ ከየኔታ ጆሮ አያመልጥም፡፡ የተሳሳተውን ተማሪ በረጅሙ ዘንጋቸው ጎንተል አድርው ያርሙታል፡፡

ይህ በሁለት አንቀጽ የተተየበው ግለ-ታሪክ የቄስ ትምህርት የሚሰጥበትን ሥነ ዘዴ የሚያሳይ ሲሆን፣ ከዚህ አንድ ገጽ ከማይሞላ ጽሁፍ ብዙ የሚባል ምዕራባዊው ሳይንስ አሁን እንደ ዘመናዊ ግኝት የሚኩራራበትን ህፃናትን የማስተማሪያ ዘዴዎች እናገኛለን፡፡ መነሻዬ የሆነውም ጥናት እንደሚገልጸው ዘመናዊ ብለን የጠራነው የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ሁሉ፣ ሳናውቅ በስህተት ዐውቀን በድፍረት ከጣልነው የቄስ ትምህርት ቤት ሥነ ሥርዓት መውጣቱ እና የራሳችንን ጥበብ እና መሠረት ሳይንስ አድርገው ለራሳችን መልሰው ሲሰጡን፣ እኛም ዘመናዊ ብለን ተቀብለን ማጽደቃችን እራሳችንን ወደ ውስጥ እንድንመረምር እና በሚገባ ያለንን እንድንመለከት የሚያደርገን ነው ይላል፡፡

የግለ ታሪኩን የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር እንኳን ብንመለከት “ተማሪዎች የምንቀመጠው ከየኔታ ፊት ለፊት በግማሽ ክብ ሲሆን” የሚል ዐረፍተ ነገር እንመለከታለን ይህን በኅሊናችሁ ይዛችሁ ወደ መረጃ መረብ ሄዳችሁ “What is the best seating arrangement for a classroom?” ብላችሁ ጎግልን ብትጠይቁት ሁሉም በሚያስብል ደረጃ የእንጊሊዘኛውን “U” የአማርኛውን ደግሞ “ሀ” ቅርጽ ብሎ ያመጣላችኋል፡፡ “ሀ” ቅርጽ፣ ደብል “ሀ” ቅርፅ እያለም ይቀጥላል፡፡ ይህም "ሀ" ቅርጽ ጸሐፊው ግማሽ ክብ ብለው የገለፁት ነው፡፡ ወደ ሁለተኛው የቄስ ትምህርት ቤት ሳይንስ ስንሄድ የተለያየ የዕውቀት ደረጃ ላይ ያሉ ህፃናትን በአንድ ላይ ሰብስቦ ስለማስተማር ያወራል ታዲያ ይህንንም “Mixed age learning” ብለው በሺዎች የሚቆጠሩ ጽሁፎችን አውጥተውበታል። አክለውም ይህ የትምህርት ሥነ ዘዴ እንዲሠራ እርስ በእርስ (አቻዊ) መረዳዳትን ወይም በነሱ አጠራር “Peer learning” የሚለውን ጨምረውበታል፡፡ ታዲያ እርሱም ቢሆን የአቡጊዳው ተማሪ ጀማሪ ፊደል ቆጣሪውን ያግዛል፣ ዳዊት አንባቢው ወንጌል አንባቢውን ያግዛል የሚለውን የእርስ በርስ የመማማር እና የመረዳዳት ጥበቡ እዚሁ የቄስ ትምህርት ውስጥ እንዳለ ያሳያል፡፡ ወረድ ብለን ስናየው “ወደፊት እና ወደኋላ እየተወዛወዝን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ፊደሎቹን ተራ በተራ በዜማ እየጠራን እንቀጥላለን” የሚል ዓረፍተ ነገር እናያለን። ከዚህም ላይ “እየተወዛወዝን” እና “በዜማ” የምትለውን ያዙልኝ፡፡ ታዲያ አሁንም በድጋሚ “Preschool teaching method and strategies” ብላችሁ ብትፈልጉ ሙዚቃን እና የሰውነት እንቅስቃሴን እንደ ዋና የማስተማሪያ ሥነ ዘዴ ሲጠቅሱት ትታዘባላችሁ፡፡ ሌላኛው በየትኛውም የትምህርት ሁኔታ ውስጥ የምታገኙት ከቀላል ወደ ከባድ (simple to complex) የሚለው የትምህርት ባሕርይ ነው። ይህንንም በጥንቱ የቄስ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሀ ሁ መቁጠር ዳዊትን በግእዝ እስከ ማንበብ ድረስ በደረጃቸው ተሰድረው እና ተቀምጠው ታገኙአቸዋላችሁ፡፡

ታዲያ ይህንን ሁሉ ነገር ከአንድ ገጽ ባነሰ ጽሑፍ ውስጥ ካገኘን ስለ መምህሮቹ ሥነ ምግባር፣ የማስተማሪያ ሥነ ዘዴዎች፣ የቦታ ሁኔታ፣ የመማሪያ ቋንቋ እና ሌሎች ብዙ ነገሮችን ብንመረምር ከዚህም በላይ ትልልቅ ምሥጢሮችን፣ ጥበቦችን እና ዕውቀቶችን እናገኝ ነበር፡፡ ለራሳችን ባሕል ፣ እምነት እና ስልጣኔ ትኩረት ብንሰጥ ኑሮ ከዓለም በፊት ጀምረን ከዓለም በኋላ ዞረን ከሌሎች እንደ አዲስ የምንቀበል አንሆንም ነበር፡፡ የሥልጣኔ መጀመሪያ፣ የጥንት ከተማን የፈጠርን፣ የአክሱም ስልጣኔ ባለቤቶች፣ የ13 ወር ጸጋ የተሰጠን፣ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ቤት፣ እንግዳ ተቀባይ እና ኩሩ ሕዝብ እንደሆንን ለዓለም ለመንገር በምንተጋበት መንገድ የሳይንሱም፣ የሥርዓቱም፣ የሕፃናት መምህርነቱም ባለቤቶች እና መሥራቾች እንደ ሆንን ብንናገር ምንኛ መልካም በሆነ ነበር፡፡

ሌላ ምስክር እንኳን ሳንጠራ እረኛው ሐኪም ዶ/ር ምትኩ በላቸው በቄስ ትምህርት ፊደል ቆጠራ ትምህርትን ጀምረው፣ ከኢትዮጵያ አልፈው ዓለም ያከበራቸው እና ያደነቃቸው የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስትነት መድረሳቸው፤ በሕፃንነት ጊዜ ያለው የትምህርት እና የዕድገት ሁኔታ እስከ መጨረሻው የሚከተለን እና ወሳኝ ነው ብለን ለምናምን ለኛ እንዲሁም ለሳይንሱ ሰዎች የቄስ ትምህርት ቤት መልካም የሕፃንነት ጅማሮ እንደሆነ ማሳየት ይችላል፡፡ ሙሉ በሙሉ ከውጪ የተቀዳውም የዘመናዊ የሕፃናት ትምህርት ቤት የተመሠረተው በ1963 እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የተመሠረተውም የነበረውን መልካም የሆነ የትምህርት ሥርዓት (የቄስ ትምህርት ቤት) በማጥፋት ላይ እንጂ የነበረውን በማስፋፋት እና የታየበትን ክፍተት በማስተካከል፣ ያለው ላይ በመጨመር አይደለም፡፡ በነበረው የሀገር ሀብት ላይ አዲስ ነገር በመፍጠር ሳይሆን ያለውን ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ አዲስ የምዕራብ ዓለም ትምህርትን ምዕራባዊ ባልሆነ ሕዝብ ላይ በመጫን ነው፡፡ ታዲያ ከዛ በፊት ልጅነታቸውን የጀመሩ ኢትዮጵያ ላይ ብሎም ዓለም ላይ ተጽእኖ ማሳደር የቻሉ የብሩህ አእምሮ ባለቤቶች ፊደል መቁጠር የጀመሩት በቄስ ትምህርት አይደለምን? ታዲያ ቄስ ትምህርት ቤት መልካም አበርክቶ አልነበረውምን? ደግሞስ "የሚያስተምረው ሃይማኖት ብቻ ነው" ተብሎ የሚወቀሰው፣ እንደ እርሱ ቢሆንስ ምንድን ነው ጥፋቱ? የተነሣሁበት ጥናት ላይ “ሃይማኖታዊ ብቻ ነው” ለሚለው ወቀሳ የተቀመጠው ምላሽ አጥጋቢ ሆኖ ስላገኘሁት የእነርሱን ምላሽ ላስቀምጥ፡፡

“የትምህርቱ አድማስ በምንም መልኩ ቢለካ በሃይማኖታዊ ትምህርት ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡ በተለይም ለሕፃናት የሚሰጠው የመነሻ ትምህርት ለልጆች መሠረታዊ የንባብ እና የጽሑፍ ትምህርት ስለሆነ፣ ፊደልን ከመቁጠር እና እሱንም ለማንበብ ከመጣር በቀር ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ተብሎ ሊቆጠር የሚችል የትምህርት ዓይነት እንደሌለ በማስረዳት ምናልባት ለንባብ የሚጠቅሙ መጻሕፍት ከሃይማኖት መጻሕፍት ሊወሰዱ እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ተብሎ የሚታየው ትምህርት የሚጀምረው ተማሪው በሃይማኖት ትምህርት መቀጠል ሲወስን እና ሲቀጥል እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡(የአብነት ትምህርት ቤት) ቀጠል አድርገውም እንደ ኢትዮጵያ ባለ 99 በመቶ የሚሆነው ማኅበረሰብ
በሆነበት ሀገር ውስጥ እየተኖረ ትምህርትን ከሃይማኖት ነጻ አድርጎ ማሰብ ትክክል እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡ ደግሞም ጥያቄን ይጠይቃሉ "ሃይማኖታዊስ ቢሆኑ ዕውቀትን አላስተላለፉም? ጥበብን አልገለጡም? ሥርዓትን አላሳዩም? በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የመተባበር፣ የመከባበር፣ አብሮ የመኖር ባሕልን አልፈጠሩም? ታዲያ ችግሩ ምንድነው ሃይማኖታዊስ ቢሆኑ? ::” በማለት ምላሻቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የጥናቱ ዓላማ ይህ በመጥፋት ላይ ያለው የሀገር ሀብት የቄስ ትምህርት ቤት ጥበቡ እና አበርክቶው እንዳለ ሆኖ፣ እንደ አዲስ በሃገሪቷ ላይ መሠጠት ቢጀምር ይህ ለደሃው ልጅ መድረስ ያልቻለው ዘመናዊ የሕፃናት ትምህርት ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ከነ ሙሉ ጥበቡ እና ሀብትነቱ መድረስ እንደሚቻል ለማሳየት ነበር፡፡ ታዲያ ሲያጠቃልሉ የቄስ ትምህርት ቤትን ወደ ቀድሞው ጥቅሙ ለመመለስ እና ለመጠቀም መደረግ ያለባቸውን ነጥቦች ያስቀምጣሉ፡፡ ነጥቦቹን ጠቅለል ሳደርጋቸው የሚከተለውን ሃሳብ ይዘዋል፡፡ እንደ ጥናቱ ገለጻም የቄስ ትምህርትን ማስተካከል እና ማረም የሚለው ደረጃ ጋር ከመደረሱ በፊት በቁሙ የተቀበረውን እና የጥበብ ባለቤት የሆነውን የቄስ ትምህርት ማነቃቃት እና እንደ አዲስ በሀገሪቷ ማስጀመር የመጀመሪያው ተግባር መሆን አለበት ይላሉ፡፡

ቀጥለውም በተማረው ማኅበረሰብ መካከል ሃሳቦችን በማንሳት ክርክሮችን እና ውይይቶችን ማካሄድ፣ ከፖሊሲ አውጪዎች ጀምሮ ለሕፃናት ትምህርት ባለሙያዎች እና ለሚለከታቸው አካላት በሙሉ በማወያየት ያለውን መልካም ያልሆነ ሃሳብ በማስቀየር የቄስ ትምህርት ለማስጀመር የሚሆን የመንግስት የሥራ ንድፍ ማውጣት። ለንድፉም አተገባበር መመሪያ ማዘጋጀት እንዲሁም ከተዘጋጀ በኋላ በሥራ ላይ በሚገኙ እና በተዘረጉት የትምህርት መስኮች ላይ በማስጀመር አቅምን ማጠናከር እና ዕድሎችን መፈለግ። እንደ ምሳሌ የሚሆኑ የቄስ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እነዚህ የጠፋውን የቄስ ትምህርት ለማስጀመር መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች እንደ ሆኑ ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህም ሳያቆሙ በሚመሠረቱት ምሳሌ ትምህርት ቤቶች ላይ አጋር ድርጅቶችን በማሳተፍ የተሻለ አቅም እንዲኖር ማድረግ። በተጨማሪም ትምህርቱን በተለያዩ ቋንቋዎች መሞከር ብሎም የሌሎች ሃይማኖቶችም ይህንን የትምህርት አይነት በራሳቸው ዘዬ እንዲቀጥሉት ማድረግ የማንነታችን አካል የሆነውን እና እንደማህበረሰብ ለመፈጠራችን ትልቅ አበርክቶ ያደረገውን የቄስ ትምህርት ቤት እንደገና ለማስጀመር የሚቻል መሆኑን ገልጸው ጥናታቸውን ያጠቃልላሉ፡፡

ታዲያ እኔም ጽሑፌን ሳጠቃልል በኅሊናቸው አስበው፣ ጊዜ ሰጥተው ፣ አውርደው፣ አውጥተው፣ አንብበው፣ ሰርዘው፣ ደልዘው ለጻፉ ጥበበኞች እድሜን ከጤና፣ ዕውቀትን ከጥበብ፣ ጸጋን ከበረከት አብዝቶ ጨምሮ ይስጣችው በማለት ነው። እኛ ያነበብን ደግሞ ትውልድ እንዳይወቅሰን በቻልነው በአቅማችን ባለ ውለታችን የሆነውን የቄስ ትምህርት ቤት ሳይንስ እንዲሆን በሳይንሳዊ መድረኮቻችን እና በጥናቶቻችን፣ የሰው ጆሮ እንዲደርስ በሚዲያዎቻችን፣ ቢጠፋ ቢጠፋ በሻይ ሰዓታችን ከወዳጆቻችን ጋር በመሆን ሃሳቡን ተነጋግረን አጠንክረን እና አዳብረን ለሚቀጥለው ትውልድ እንደ ተረከብን ብናስረክብ መልካም ነው እያልኩ በዚሁ አጠቃልላለሁ፡፡ ስንት ዕውቀት እና ስንት ልፋት የወጣበትን ሥራ በጥቂት ገጾች፣ በማያምሩ ቃላት ሳይገባኝ ስለተየብኩ ይቅርታዬን ለጥናቱ ባለቤቶችም ለአንባቢዎችም እጠይቃለሁ። ይቅርታችሁን እንደማትነፍጉኝም ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡

REFERENCE

Hagos, B., & Tefera, B. (2017). Know Thy Self: Viability of Early Childhood Education Delivery through Traditional Priest Schools. The Ethiopian Journal of Education, 37(2), 67-102.
Wole, D. (2020). Factors Affecting the Study of Qiné in Ethiopian Orthodox Church Schools. The Ethiopian Journal of Education, 40(2), 119-164.
እረኛው ሃኪም፡ ከእረኝነት እስከ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትነት" በሚል ርዕስ በዶ/ር ምትኩ በላቸው ተፅፎ በአዜብ ወርቁ በተተረጎመው ግለ-ታሪክ መፅሃፍ
Gemechu, E. (2016). Quest of traditional education in Ethiopia: A retrospective study. Research Journal of Educational Sciences, 4(9), 1-5.
Haile gebriel dagne, (2003) the ethiopian orthodox church school system, https://www.ethiopianorthodox.org/english/ethiopian/school.html

Traditional, religious school system in Ethiopia, Ethiopia press, https://www.press.et/english/?p=24243#