Yismake Worku
20.6K subscribers
334 photos
9 videos
1 file
69 links
Bilingual content in English & Amharic, author tips, book reviews, behind-the-scenes writing insights, and interactive community discussions.

Buy ads: https://telega.io/c/yismakeworku
Download Telegram
ይህን የማያውቁ፣ጥቂቶች አሉና፣ ቢያልመዘምዟቸው
እንዲመረመሩ፣ የፈጣሪ መስኮት፣ይከፈትላቸው

...
ዘላለም ምህረቱ እንደፃፈው
#ከመቃብር_ቆፋሪዎች_ማዶ
(ከቅንነት የመነጨ ፈገግታ )
ብዙ ሰው ብዙ ነገር አለው። በተፈጥሮ ወይም በጥረት። ያላቸውን በቅንነት እንበለ-ግብዝነት የሚሰጡ ትቂቶች ናቸው። ሀብታሙ በመስገብገብ፥ምሁሩ በመታበይ፥ባለስልጣኑ በመሰይጠን፤ ድርጊታችን ሁሉ ለታይታ ወይም "በግብር ይውጣ" እንጂ የቅንነት ፀዳል ያረፈበት አይደለም። ሁሉም ነገር የፍቅር፥የታጋሽነት እና የቅንነት ፀዳል ካልለበሰ ለተቀባዩ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ እርካታ አይኖረውም። ለዚህም ነው የሀገሬው ሰው "ከፍትፍቱ ፊቱ" የሚለው።
ዶ/ር ተሻገር ለእኔ እውቀት ብቻ ሳይሆን ቅንነት ከጎበኛቸው ሰዎች አንዱ ናቸው። ሰው በሰው ጉዳይ እንደዚህ ሲብሰለሰል፥ በታጋሽነትና በቅንነት ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ ያየሁ እሳቸውን ነው። መሠል ነገሮች ለእኔ ተፈጥሮና ሰብዕና አዲስ ባይሆኑም፤በዘመነ "እኔነት" ከግብዝነት ነፃ የሆነ ቅንነት የተላበሱ ሰዎችን ማግኘት በርባኖስ ነው። የብዙ ደጋግ ኢትዮጵያውያን ጥረት፣ የዶ/ር ተሻገር ቅንነት፣ የሾን ሜዲካል ሴንተር እና የሌሎች ተቋማት ባለሙያዎች ጥረት ይስማዕከን ዳግም ወደ ደራሲነቱ እንዲመለስ ከፈጣሪ በታች ውለታ ውለውለታል።
"ያልተሳለ የለም፥ ያልተወረወረ
ስጋዬ እንጂ ቅሉ፥ መንፈሴ አልደደረ" በሚል የትካዜ ጉዞ ይመስላል ደራሲው፤ ከባህር ማዶ መልስ ወደ ትናንት ለመመለስ እራሱን መፅሐፍ ውስጥ ቀብሮ ማደር ጀመረ። መድኃኒቱን በኮረጆ አንጠልጥሎ ተራራና ጋራውን፥ ሜዳና ሸንተረሩን መውጣትና መውረድ ጀመረ። በብዙ የደህንነት ስጋት ውስጥ " #ደህንነቱ "ን ወለደ። ደህንነቱ ዳግም በአካለ ሰብዕ ሳይሆን በአካለ መንፈስ እንዲቆም ጠጠረ ለደገፉ ሰዎች ሁሉ በስጦታ የተበረከተ የዘመናችን "ኢትዮጵያ" ስንክሳር ነው። ፅድቃችንንና መርገማችንን መሳ ለመሳ የሚተርክ ስንክሳር።
ይህ ስጦታ ከሚበረከትላቸው ሰዎች ቀዳሚው ሰው ደግሞ ቅኑ ዶ/ር ተሻገር ናቸው። የፈጣሪ ነገር ሁለት ነገሮችን ግጥምጥም አደረጋቸው። "ደህንነቱ"የተሰኘው መፅሐፍ ታትሞ ወደ ገባያ ሲወጣ እኒህ ቅን ሰው ቤተሰብ ጥየቃ አዲስ አበባ መጡ። ደራሲ ይስማዕከም አፍታውን በክብር አበረከተላቸው። እኛም "ያለቀሱ ሁሉ ይስቃሉ አንድ ቀን" ብለን በፈገግታ አጀብን። እኔም በቅንነት ለቅኑ ሰው ዝቅ ብዬ አመሰገንሁ። ለወትሮው የተደበቀ ፊቴን ከቅኑ ሰው ጋር ፊት ለፊት አሰጣሁት። በአካል ስላገኘሁዎት ደስ ብሎኛል። ስላሳለፍናት አጭር ጣፋጭ ጊዜም እንዲሁ! የቅንነትዎን ዋጋ ፈጣሪ በቤተሰብዎ ይከፈልዎ!
የእኔም ትንሽ ጠጠር መደገፍ መሠል ሀሳቦችን ዳግም እንዲያበረክት ከመመኘት እንጂ ፎቶ አብሮ ለመነሳት የመጎምጀት አልነበረም። ወይም እንደ ዘመኑ ሰዎች አልነበረም። እሱም ከፈጣሪ ጋር ተሳክቶልኛል። ከዚህ ባለፈ "ዛፍ አድርቅ" የሆንን ማህበረሰቦች ነንና ስላለፈውና ስለሆነው ነገር ሁሉ ቅር አይለኝም። "ሲኖሩ ከሳሽ፥ሲሞቱ አልቃሽ" የሆነው ማህበረሰባዊ የስነ-ልቦና ስሪታችን ከ"መቃብር ቆፋሪነት" ወደ "ሰው ሰሪነት" እንዲመለስ ፅኑ ምኞቴ ነው።
መልካም ንባብ!
ሻሎም!
ከአንድ ዓመት በፊት ስለ ዶ/ሩና ስለ እኔ ተምኔት እንዲህ ብዬ ነበር፤
¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢
ከጀርመኑ ሆስፒታል ጋር የተደረገው የህክምና ሂደት እንዲሳካ ትልቅ እገዛ ያደረገው እዛው ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩት ቅን ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ተሻገር (ኒሮሎጅስት፣ ሳይካትሪስት) ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከእንደዚህ አይነት ቅን ሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ ያለች ይመስለኛል፡፡ እኒህ ሀኪም ሆስፒታሉ የህክምና ዋጋ እንዲቀንስ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ለአስታማሚ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ፣ እራሳቸው እንደ ቤተሰብ አስታማሚ በመሆን ትልቅ እገዛ አድርገውለታል፡፡ ለ10 ሳምንታት የታቀደውን ህክምና አሁንም በገንዘብ እጥረት ምክንያት በ4 ሳምንት እንዲደረግ እገዛ ያደረጉት እኒህ ሰው ናቸው፡፡ ዋጋቸውን እሱ ይክፈላቸው!
የህክምናው ውጤት፡
ሆስፒታል በገባበት እለት ጀምሮ በተለያዩ መሳሪያዎች ሙሉ የጤና ምርመራ ተደርጎለታል፡፡ በየዘርፉ የተመደቡት 10 ስፔሻሊስት ሐኪሞች (በውሉ በተስማማንበት መሰረት) እና ነርሶች ከፍተኛ የሆነ ህክምና እገዛ አድርገውለታል፡፡
ይስማዕከ በድርሰቱ ባለው የምናብ ጥልቀት እና የፈጠራ ትርክት በአዳዲስ ስራዎችና አስተሳሰቦች ከተፍ ብሎ ከጎኑ የነበሩ አድናቂዎቹንና መላ ወገኖቹን እንደሚያስደስት ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
መልካም ጤና!
¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢¢





!
@yismakeworku
👍3