ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
58.3K subscribers
68 photos
69 videos
19 files
1.72K links
ዳዒ ወሒድ በኢሥላም እና በክርስትና መካከል ያለውን ልዩነት እና አንድነት በንጽጽር የሚያስቀምጥ ወንድም ነው። ለዚህም የቋንቋ፣ የሰዋስው፣ የዐውድ፣ የተዛማች እና የሥነ አመክንዮ ሙግት በማቅረብ የሚታወቅ ተሟጋች እና ጦማሪ ነው። ለሙግቱ ነጥብ በዋነኝነት የሚጠቀምባቸው ቋንቋ ዐማርኛ፣ ግዕዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ዐረቢኛ፣ ዕብራይስጥ እና ግሪክ ናቸው። መልካም የንባብ፣ የጥናት፣ የማነጻጸር ጊዜ ይሁንልዎ!
Download Telegram
አንዱ አምላክ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥163 አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፥ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡ وَإِلَـٰهُكُمْ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ ۖ لَّا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الرَّحْمَـٰنُ الرَّحِيمُ

አይሁዳውያን "አምላክ አንድ ነው፥ እርሱም አንድ ማንነት ነው" የሚል ጽኑ አቋም ከጥንት ጀምሮ አላቸው፦
ዘዳግም 6፥4 እስራኤል ሆይ ስማ! አምላካችን ያህዌህ አንድ ያህዌህ ነው። שְׁמַע, יִשְׂרָאֵל: יְהוָה אֱלֹהֵינוּ, יְהוָה אֶחָד.
ዮሐንስ 8፥54 እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው።

ኢየሱስ "አባቴ" የሚለው እስራኤላውያን "አምላካችን" የሚሉትን አንዱን አምላክ ያህዌህን ነው። ኢየሱስ "ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው" በሚል ኃይለ ቃል አንዱ ጌታ አምላክ የሚለው አባቱን እንደሆነ ኢራኒየስ ዘሊዮን ተናግሯል፦
ማርቆስ 12፥29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ "እስራኤል ሆይ ስማ!  ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው"።
"ኦሪት ያወጀው፣ ነቢያት ያስተማሩት፣ እንዲሁ ክርስቶስ አባቱ እንደሆነ የመሰከረለት፦ "እስራኤል ሆይ ስማ! ጌታ አምላካችን አንድ አምላክ ነው" የሚል አይደለምን?" ዘዳግም 6፥4 ።
Against Heresies (St. Irenaeus) Book V(5) Chapter 11 Number 1

የአይሁድ ሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን "አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም" ብለህ መልካም ተናገር በማለት የኢየሱስ ተልእኮ ከጥንት ነቢያት የተለየ እንዳልሆነ አረጋግጦአል፦
ማርቆስ 12፥32 ጻፊውም፦ “መልካም ነው፥ መምህር ሆይ! "አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም" ብለህ በእውነት ተናገርህ።

"አብ" אָ֑ב የሚለው የዕብራይስጥ ቃል "አስገኝ" በሚል የተቀጸለ ነው፥ ይህ አንድ አምላክ የፍጥረት አስገኚ ስለሆነ "አንድ አባት" ተብሎ የተቀመጠ ነው፦
ኢዮብ 31፥15 እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ የቀረጸን "አንድ" አይደለንምን? הֲ‍ֽ֝לֹא־בַ֭בֶּטֶן עֹשֵׂ֣נִי עָשָׂ֑הוּ וַ֝יְכֻנֶ֗נּוּ בָּרֶ֥חֶם אֶחָֽד׃
ሚልክያስ 2፥10 ለሁላችን "አንድ አባት" ያለን አይደለምን? "አንድ አምላክስ" የፈጠረን አይደለምን? הֲלֹ֨וא אָ֤ב אֶחָד֙ לְכֻלָּ֔נוּ הֲלֹ֛וא אֵ֥ל אֶֽחָ֖ד בְּרָאָ֑נוּ
ዮሐንስ 8፥41 "አንድ አባት" አለን፥ እርሱም "አምላክ" ነው። ἕνα Πατέρα ἔχομεν τὸν Θεόν.

"አብ" אָ֑ב ማለት "አስገኝ" ለሚለው "ዘይቤአዊ አገላለጽ"Analogical Term" የመጣ እንጂ "ወላጅ" በሚል "ባሕሪያዊ አገላለጽ"Ontological Term" የመጣ አይደለም። ኢየሱስ "እኔ" የሚለውን ማንነቱን ከአንዱ አምላክ ነጥሎ ሲያስቀምጥ አርጌንስ ዘእስክንድርያ ይህ አንዱ አምላክ አብ እንደሆነ አስቀምጧል፦
ማርቆስ 10፥18 *"ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር "እኔን" ትለኛለህ? ከአንዱ አምላክ በቀር ቸር ማንም የለም"። ὁ δὲ Ἰησοῦς εἶπεν αὐτῷ Τί με λέγεις ἀγαθόν; οὐδεὶς ἀγαθὸς εἰ μὴ εἷς ὁ θεός.
"ስለዚህ እንዲሁ አዳኙ እራሱ በወንጌል በትክክል፦ "ከአንዱ አምላክ ከአብ በቀር ቸር ማንም የለም" ብሏል"።
De Principiis (Origen) > Book I(1) Chapter 2 Number 13

የአዲስ ኪዳን ጸሐፊያን መካከል ትልቁን ክፍል የያዘው ጳውሎስ "አንድ አምላክ" ብሎ ያስቀመጠው አብን ብቻ እና ብቻ ነው፦
1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥5 አንድ አምላክ አለና፥ εἷς γὰρ Θεός, εἷς
ገላትያ 3፥20 መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም አምላክ ግን አንድ ነው። ὁ δὲ μεσίτης ἑνὸς οὐκ ἔστιν, ὁ δὲ Θεὸς εἷς ἐστιν.
1ኛ ቆሮንቶስ 8፥4 ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።
1 ቆሮንቶስ 8፥6 ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን "አንድ አምላክ" አብ አለን።
ኤፌሶን 4፥6 ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉ የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።
"እንግዲህ ይህ አምላክ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እንደሆነ ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ተናግሯል፦ "ከሁሉ በላይ የሚሆን፣ በሁሉ የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ"።
Against Heresies (St. Irenaeus) Book II(2) Chapter 2 Number 5

ጥንት የነበሩት ሐዋርያነ አበው"Apostolic Fathers" ከላይ ያሉትን "አንድ አምላክ" የሚሉትን የባይብል አናቅጽ ለኢየሱስ አባት ለአብ ብቻ እና ብቻ ይጠቀሙባቸው ነበር። እስቲ እንመልከት፦

፨ አግናጢዎስ ዘአንጾኪያ"Ignatius of Antioch"፦
"በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እራሱን የገለጠ አንድ አምላክ አለ"።
Epistle to the Magnesians (St. Ignatius) Chapter 8

፨ ኖላዊ ዘሄርማስ"The Shepherd of Hermas፦
"በመጀመሪያ ሁሉን ነገር የፈጠረ እና የፈጸመ፥ ሁሉንም ነገር ያለ ምንም የፈጠረው አንድ አምላክ እንዳለ እመኑ። እርሱ ብቻ ሁሉን ያካበበ ነው፥ እርሱ በምንም አይካበብም"።
The Shepherd of Hermas > Book II(2) Number 1

፨ ኢራኒየስ ዘሊዮን"Irenaeus of Lyon"፦
1. "ሁሉን ነገር የፈጠረ አምላክ እርሱ ብቻ አንድ እንደሆነ ታወቀ፥ እርሱ ብቻ ሁሉን ቻይ ነው። ሁሉንም ነገር የሚጠግንና የሚሠራ እርሱ ብቻ አብ ነው"። ከእርሱ በቀር ሌላም የለም፥ ከእርሱም በላይ የለም። ለእርሱ እናት የለውም፥ እርሱን በውሸት ይመጡኑታል። ሁለተኛም አምላክ የለም። እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ነው"።
Against Heresies (St. Irenaeus) > Book II(2) Chapter 30 Number 9

2. "የወንጌል የመጀመሪያ መርሖች እንደነዚህ ያሉት ናቸው፦ "የአጽናፉ ዓለም ፈጣሪ አንድ አምላክ አለ፥ እርሱ በነቢያቱ የተናገረ እና በሙሴ የኦሪትን ዘመነ መግቦት የነደፈ ነው። መርሆቹ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት የሚያውጁ ናቸውና ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ ወይም አባት ችላ በሉ"።
Against Heresies (St. Irenaeus) > Book III(3) Chapter 11 Number 7

3. "እርሱ ሰውን የፈጠረ ነው፥ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ እና የያዕቆብ አምላክ ነው። ከእርሱ በላይ ሌላ አምላክ ወይም ቀዳማይ መንስኤ ወይም ኃያል አሊያም ሙሉ ፍጹም የለም፥ እርሱም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ነው"።
Against Heresies (St. Irenaeus) > Book XXII(22) Chapter 22 Number 1

4. "አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ አስቀድሜ አረጋግጫለሁ፥ ነገር ግን ይህንን ከራሳቸው ከሐዋርያት እና ከጌታ ንግግር እገልጣለሁ። የነቢያቱን፣ የጌታን እና የሐዋርያትን ቃል ብንተው የማስተዋል ቃል የማይናገሩትን ሰዎች እንስማ ዘንድ ምን ዓይነት ምግባር ይሆን ነበር?"።
Against Heresies (St. Irenaeus) Book II(2) Chapter 2 Number 5
፨ አርጌንስ ዘእስክንድሪያ"Origen of Alexandria"፦
1. "አምላክ እንዴት የልጁ አባት ተብሎ እንደተጠራ ተረዳ"።
De Principiis (Origen) > Book I(1) Chapter 2 Number 6

2. "ስለዚህ አምላክ የአንድያ ልጁ አባት እንደሆነ ሁልጊዜ እንይዛለን"።
De Principiis (Origen) > Book I(1) Chapter 2 Number 2

3. "በቅድሚያ ሁሉን የፈጠረ እና ያደራጀ፥ ምንም ሳይኖር ሁሉን ወደ መኖር የጠራ አንድ አምላክ አለ። ሁሉን ወደ መኖር ጠራው፥ ይህም አምላክ አስቀድሞ በነቢያት ቃል ገብቶ እንደ ተናገረ በመጨረሻው ዘመን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ላከ"።
De Principiis (Origen) > Preface Number 4

፨ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ"Gregory of Nyssa"፦
"ግን የሚከተሉትን ቃላት እንመርምር! እርሱ ሁልጊዜ ፍጹም አንድ ነው፥ ብቸኛው አምላክ በወጥነት እና ባለመለወጥ ይኖራል። አውናኒዎስ ስለ አብ የሚናገር ከሆነ ከእሱ ጋር እንስማማለን፥ ምክንያቱም አብ ፍጹም ብቻውን አንድ እና ሁልጊዜ አንድ ወጥ እና የማይለወጥ ነው።
Against Eunomius (Gregory of Nyssa) Book II(2) Number 5

በተለምዶ የሐዋርያት የእምነት መግለጫ ተብሎ የተቀመጠው፦ "የሰማይ እና የምድር ፈጣሪ ሁሉን ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር አብ አምናለው" የሚል ነው። በ 325 ድኅረ ልደት የተካሄደው 1ኛው የኒቂያ ጉባኤ፦ "የሚታየው እና የማይታየውን፣ የሁሉንም ነገር፣ የሰማይ እና የምድር ፈጣሪ በሁሉን ቻዩ አንድ አንድ አምላክ አብ እናምናለን" የሚል ነው።

በተለምዶ የሐዋርያት የእምነት መግለጫ ተብሎ የተቀመጠው፦ "ብቸኛ ልጁ በሚሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለው" የሚል ሆኖ ሳለ የኒቂያ የእምነት መግለጫ ላይ "በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተወለደ የአምላክ ልጅ፥ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከአምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባሕርይው ከአብ ጋር የተስተካከል በሆነው እናምናለን" በማለት አረቀቁት። ሆነም ቀረ በአቋማቸው አንድ አምላክ አብ ሲሆን ወልድ የአንድ አምላክ ልጅ እንጂ ሁለተኛው የአንድ አምላክ አባል አልነበረም፦
"አንድ አምላክ እንዳለ እናምናለን፥ ነገር ግን በሚከተለው ዘመነ መግቦት ሥር እንደተባለው ይህ አንድ ብቸኛ አምላክ እንዲሁ ልጅ አለው"።
Against Praxeas (Tertullian) Chapter 2

አሁንም አንድ አምላክ አብ ብለው "አንዱ አምላክ ልጅ አለው" የሚል ሺርክ ይጨምራሉ እንጂ "አንድ አምላክ አብ ነው" የሚል አቋም እንደተጠበቀ ነው። ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት"Gregory the Wonderworker" የተባለው አባት "አንድ እውነተኛ አምላክ" የሚለው አብን ነው፦
"ስለዚህ አንድ እውነተኛ አምላክ የመጀመሪያው መንስኤ አንዳለ እና አንድ ልጅም ከአምላክ የተገኘ አምላክ እውቅና እንሰጣለን"።
A Sectional Confession of the Faith (St. Gregory Thaumaturgus) Number 15

አንድ አምላክ አብ እንጂ በአብ የገለጠ አይደለም፥ አንድ አምላክ አብ እንጂ አብ አንድ አምላክን የሚጋራ ማንነት አይደለም። አንድ አምላክ ማን ነው? አዎ! አንድ አምላክ አብ እንጂ እራሱን በአብ የገለጠ አንድ አምላክ የለም፥ አብ አንድ አምላክን ከሌላ አካል ጋር የሚጋራ ሳይሆን እራሱ አንድ አምላክ ነው። የግሪክ ኦርቶዶክስ ኤጲስ ቆጶስ የነበሩት ዮሐንስ ዚዚዩላስ"John Zizioulas" ስለ አብ በመጽሐፋቸው እንዲህ ብለው ነበር፦
"አንድ አምላክ አንድ ኑባሬ አይደለም፥ ነገር ግን አባት ነው። እርሱም የወልድ ልደት እና የመንፈስ ቅዱስ ሥርጸት መንስኤ ነው"።
Being as Communion: Studies in Personhood and the Church(John D. Zizioulas) Page 40-41.

"አንድ አምላክ አንድ ኑባሬ ሳይሆን ወልድ ያስገኘ አብ ነው" ከተባለ መጻሕፍት "አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ናቸው" ወይም "አንድ አምላክ ሦስት አካላት አሉት" በፍጹም እና በጭራሽ አይሉም። ኢየሱስ አባቴ የሚለው ከእግዚአብሔር ውጪ የለም፥ ለአብ ከእግዚአብሔር ሌላ ስም አላገኘንለትም፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 79 ቁጥር 21
"ከእግዚአብሔር በስተቀር አባቴ የሚለው ማንን ነው?
መጽሐፈ ምሥጢር ምዕራፍ 29 ቁጥር 53
"አብ" ከዘላለም እስከ ዘላለም "እግዚአብሔር" ይባላል፥ ለአብ ከእግዚአብሔር ሌላ ስም አላገኘንለትም"

የኢየሱስ ክርስቶስ አባት አንድ አምላክ ነው፥ እርሱ ሁለተኛም አይደለም፣ ሦስተኛ አይደለም፣ አይጨመርበትም። ብቻውን ለዘላለሙ የሚኖር አንድ ነው፦
ሥርዓተ ቅዳሴ ምዕራፍ 5 ቁጥር 33
"የኢየሱስ ክርስቶስ አባት በሚሆን ፍጥረቱን ሁሉ በፈጠረ በአንድ አምላክ እናምናለን"
ሥርዓተ ቅዳሴ ምዕራፍ 5 ቁጥር 35
"ሁለተኛም አይደለም፥ ሦስተኛ አይደለም። አይጨመርበትም፥ ብቻውን ለዘላለሙ የሚኖር አንድ ነው እንጂ"።
ሥርዓተ ቅዳሴ ምዕራፍ 5 ቁጥር 36
"የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር አንድ ነው"

"እግዚአብሔር አንድ ነው" ከተባለ ይህም አንድ እግዚአብሔር "የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ነው" ከተባለ እንግዲያውስ ኢየሱስ ወልድ እንጂ አብ ሳልሆነ "አንድ እግዚአብሔር" በሚል ፈርጅ ውስጥ ኢየሱስ አይካተትም።
ክርስቲያኖች ሆይ! አምላካችሁም አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፥ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። ስለዚህ አምልኩት! እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፦
2፥163 አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፥ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡ وَإِلَـٰهُكُمْ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ ۖ لَّا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الرَّحْمَـٰنُ الرَّحِيمُ
6፥102 ይህ ጌታችሁ አሏህ ነው፥ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ ነገርን ሁሉ ፈጣሪ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ ۖ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ ۖ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ فَاعْبُدُوهُ ۚ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ

አምላካችን አሏህ የተውሒድን ብርሃን ያብራላችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ሞንአርኼስ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

43፥15 ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን ልጅ አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡ وَجَعَلُوا لَهُ مِنْ عِبَادِهِ جُزْءًا ۚ إِنَّ الْإِنسَانَ لَكَفُورٌ مُّبِينٌ

"ሞንአርኼስ" μονᾰ́ρχης የሚለው ቃል "ሞኖስ" μόνος እና "አርኼስ" άρχης ከሚል ሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው፥ "ሞኖስ" μόνος ማለት "ብቸኛ" ማለት ሲሆን "አርኼስ" άρχης ማለት ደግሞ "ዋና"Main" "ገዥ"Ruler" "ምንጭ"Source" "አስገኝ"Originator" ማለት ነው። በጥቅሉ "ሞንአርኼስ" μονᾰ́ρχης ማለት "ብቸኛው ገዥ፣ ምንጭ፣ አስገኝ፣ ዋና" ማለት ሲሆን አብ ብቻውን አምላክ እና ገዥ መሆኑን እነዚህን አናቅጽ ተመልከት!
ዮሐንስ 17፥3 ሮሜ 16፥27 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥17 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥15 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥16 ይሁዳ 1፥4 ይሁዳ 1፥25

አብ መንስኤ አልባ የመንስኤዎች ሁሉ መንስኤ"Un Causes The Cause of Causes" ስለሆነ "ሞንአርኼስ" ነው፥ "አስገኝነት"Monarchy" የአብ ብቸኛው ገንዘብ ነው። አብ የወልድ ህልውና ምንጭ እና ሥር መሆኑን አንብሮስ ዘሚለን"Ambrose of Milan" ተናግሯል፦
"አብ የወልድ ኑባሬ ምንጭ እና ሥር ነው"
Exposition of the Christian Faith (Ambrose)> Book IV(4) Chapter 10 Number 133

አብ አስገኚ ከሆነ ወልድ ግኝት ከሆነ አምላክ ከራሱ ባሕርይ እና አካል ሁለተኛ አምላክ የሆነ አካል "ከባሕርይ ባሕርይ ወስዶ ተወለደ" የሚባል ልጅ ክፍልፍል ነው። ስለ አብ አስገኝነት ጠርጡሊያኖስ ዘካርቴጅ"Tertullian of Carthage" እንዲህ ሲል ይናገናል፦
"አብ አጠቃላይ ባሕርይ ነው፥ ነገር ግን ወልድ የአጠቃላዩ መገኘት እና ክፍል ነው"
(Against Praxeas (Tertullian), Chapter 9).

አንድ አምላክ አብ በማንነት መለያየት"Distinction" የሌለበት፣ በባሕርይ መከፋፈል"Segmentation" የሌለበት፣ በመለኮት መነጣጠል"Separation" የሌለበት የማይከፈል"Indivisible" አንድ ነው፥ ከእርሱ የሚከፈል ክፍል ከሌለው "ወልድ የአብ ክፍል ነው" ማለት አንድነቱን ያናጋል። ከአንድ አምላክ የሚገኘው ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይደለም፦
"ስለዚህ አምላክ የአንድያ ልጁ አባት እንደሆነ ሁልጊዜ እንይዛለን። በእውነት ወልድ ከእርሱ የተወለደ እና ከእርሱም የተገኘ ነው"።
De Principiis (Origen) > Book I(1) Chapter 2 Number 2

በኒቂያ ጉባኤ "አንድ አምላክ አብ" ተብሎ ሳለ ከእዚህ አንድ አምላክ ሀለተኛ አካል የሆነ አምላክ ተገኘ ማለት የጤንነት አይደለም፥ "ቴዎን ኤክ ቴዉ" Θεὸν ἐκ Θεοῦ ማለት "ከአምላክ የተገኘ አምላክ ነው" ማለት ሲሆን "አምላክ አምላክን አህሎ እና መስሎ፣ ከባሕርይ ባሕርይ ወስዶ፣ ከአካል አካል ወስዶ ተወለደ" ማለታቸው መለያየት ነው። "ከአብ የተገኘው ወልድ የአብን አምላክነት ይጋራል" ማለት መከፋፈል ነው፥ "ሆ ቴዎስ ሆ ሁዎስ" Ο Θεός ο γιος ማለት "እግዚአብሔር ወልድ"God the Son" ሲሆን ይህ ቃል የጸደቀው በኒቂያ ጉባኤ ነው።

አንድ አምላክ አብ ሲሆን ወልድ ከአንድ አምላክ ስለተገኘ ወልድ አምላክነትን ያገኘው የአብ አምላክነት ወደ ወልድ ተላልፎ ስለመጣ እንደሆነ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ ተናግሯል፦
"የአብ አምላክነት ያለ ፍሰት እና ያለ መከፋፈል ወደ ወልድ አልፏል"።
Statement of Faith (Athanasius) Number 2

አምላክነት ልክ እንደ አብራክ ፍሉጥ የሚተላለፍ አርጎ ማስቀመጥ ይህ እልም ያለ ትልቅ ሺርክ ነው። አምላክ አንድ ከሆነ ይህም አንድ አምላክ የኢየሱስ አባት ከሆነ ከእርሱ ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይገኝም። ሔዋን፦ "ሰው ከያህዌህ አገኘሁ” አለች፦
ዘፍጥረት 4፥1 እርስዋም፦ “ሰው ከያህዌህ አገኘሁ” አለች። וַתֹּ֕אמֶר קָנִ֥יתִי אִ֖ישׁ אֶת־יְהוָֽה׃

"አገኘሁ" ለሚለው የገባው ቃል "ቃኒቲ" קָנִ֥יתִי ሲሆን ያገኘችው ወንድ ልጅ ከአምላክ የተፈጠረ ሰው መሆኑን ጉልኅ ማሳያ ነው። ኢየሱስም በትንቢት መነጽር "ያህዌህ ፈጠረኝ" በማለት ተናግሯል፦
ምሳሌ 8፥22 "ያህዌህ ፈጠረኝ"። יְֽהוָ֗ה קָ֭נָנִי

"ቃናኒ" קָ֭נָנִי ማለት "አስገኘኝ" "ፈጠረኝ" ማለት ነው፥ አብ ከማንም ያልሆነ መንስኤ አልባ ሲሆን ወልድ ግን ከአብ የሆነ ስለሆነ ግኝት እንጂ አስገኝ ወይም መንስኤ አልባ አይደለም። ከሰው ሰው ስለሚገኝ ከአብራክ የተገኘው ሰው እና የመገኘት መንስኤው የሆነው ሰው ሁለት ሰዎች ናቸው፥ በምድር ላይ ያለው ሁሉም ሰው በምንነት አንድ ሲሆን በማንነት ግን ብዙ ሰው ስላለ "ሰዎች" እንባላለን። ለምሳሌ፦
ኢያሱ 2፥4 ሴቲቱም "ሁለቱን ሰዎች" ወስዳ ሸሸገቻቸው። וַתִּקַּ֧ח הָֽאִשָּׁ֛ה אֶת־שְׁנֵ֥י הָאֲנָשִׁ֖ים

ኢያሱ የላካቸው ሰዎች "ሁለቱ ሰዎች" የተባሉት በአካል ስለሚለያዩ እንጂ በባሕርይ አንድ ከሆኑ አብ እና ወልድ በአካል ተለያይተው በባሕርይ አንድ ከሆኑ ሁለት አምላክ እንጂ አንድ አምላክ አይሆኑም። አብርሃም አንድ አካል ሆኖ ሳለ እስማኤልን እና ይስሐቅን ሲወልድ በዝቷል፦
ኢሳይያስ 51፥2 "አንድ ብቻውን" በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም "አበዛሁትም"። אֶחָ֣ד קְרָאתִ֔יו וַאֲבָרְכֵ֖הוּ וְאַרְבֵּֽהוּ׃ ס
ዕብራውያን 11፥12 ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው "ከአንዱ ተወለዱ"።

"ከአንዱ ተወለዱ" የሚለው ይሰመርበት! ከአንዱ አካል ሌላ አካል ከተወለደ ብዙ ሰው እንጂ የወለደውን ሰው እና የተወለደው ሰው አንድ ሰው ማለት ከሥነ ኑባሬ ጥናት ጋር መታለም ነው፥ "መለኮት ይዋለዳል" ማለት ድብን ያለ ሺርክ ነው።
በዲኑል ኢሥላም መሢሑ ኢየሱስ ከተከበሩ የአሏህ ባሮች አንዱ ነው፥ ይህንን መሢሕ "ከአምላክ የተገኘ አምላክ" በማለት ለአሏህ ቁራጭን ልጅ አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፦
43፥15 ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን ልጅ አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡ وَجَعَلُوا لَهُ مِنْ عِبَادِهِ جُزْءًا ۚ إِنَّ الْإِنسَانَ لَكَفُورٌ مُّبِينٌ

ለጀሀነም ከሚዳርግ ከሺርክ እና ከኩፍር ሕይወት አምላካችን አሏህ አውጥቶ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
አውቶቴዎስ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥255 አሏህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፡፡ اللَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ

"አውቶቴዎስ" αὐτοθεός "እራሱን የቻለ አምላክ"The self existent God" ማለት ሲሆን አብ የፍጥረት ሁሉ "አስገኚ"Orginator" ስለሆነ እራሱን የቻለ አምላክ"Aseity" ከአብ ውጪ የለም፦
"ሁሉም ነገሮች በአምላክ የተፈጠሩ ናቸው፥ ሁሉም ነገር ከእርሱ የተገኘ እንጂ የሚኖር ፍጡር የለም"።
De Principiis (Origen) > Book I(1) Chapter 3 Number 3

"ሁሉም ነገር ከእርሱ የተገኘ" የሚለው ይሰመርበት! አርጌንስ ኢየሱስ ከአንዱ አምላክ "የተገኘ ነው" ብሏል፦
"ስለዚህ አምላክ የአንድያ ልጁ አባት እንደሆነ ሁልጊዜ እንይዛለን። በእውነት ወልድ ከእርሱ የተወለደ እና ከእርሱም የተገኘ ነው"።
De Principiis (Origen) > Book I(1) Chapter 2 Number 2

ጠርጡሊያስ ዘእስክንድርያ እንዳስቀመጠው አንዱ አምላክ ወልድን ከመውለዱ እና ከማስገኘቱ በፊት ነበረ፥ አንድ ሰው ሰው የሚለው ባሕርይው እራሱ እንደሆነ እና ልጅ ሲወልድ አባት እንደሚባል አንዱ አምላክም ኢየሱስ ሲወልድ አባት ሆነ ይለናል፦
"እርሱ ከፍጥረት በፊት እስከ ወልድ ውልደት ነበረ፥ ከሁሉ ነገር በፊት አምላክ ብቻውን ነበረ"።
Against Praxeas (Tertullian) Chapter 5.
"ምክንያቱም አምላክ እንዲሁ አብ ነው፥ እንዲሁ ደግሞ እርሱ ፈራጅ ነው። ሁልጊዜም አምላክ በሆነው መሠረት ላይ ብቻ እርሱ ግን ሁልጊዜ አባት እና ፈራጅ አልነበረም፥ ከልጅ በፊት አባት ሊሆን አይችልም፤ እንዲሁ ከኃጢአት በፊት ፈራጅ ሊሆን አይችልም"።
Against Hermogenes (Tertullian) chapter 3

ይኸው አባት ጠርጡሊያስ፦ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት አልነበረም፥ ለኢየሱስ ልጅነት እና ለአንዱ አምላክ አባትነት ጅማሬ እንዳላቸው ተናግሯል፦
"ነገር ግን በእርሱ ዘንድ ኃጢአት ባልነበረበት እና እንዲሁ ልጅ ባልነበረበት ወቅት ጊዜ ነበር፥ የመጀመሪያው ጌታ ፈራጅ ሆኖ እና የኃለኛ አባት ሆኖ መመሥረት ነበር"።
Against Hermogenes (Tertullian) chapter 3
"በዚህ መንገድ እርሱ ጌታ ሊሆን ከነበረባቸው ነገሮች በፊት ጌታ አልነበረም፥ ነገር ግን እርሱ ግን ወደፊት በሆነ ጊዜ ብቻ ጌታ ሊሆን ነበር። ልክ እንደዚሁ እርሱ በልጅ አባት እንደ ሆነ በኃጢአትም ፈራጅ ሆነ"።
Against Hermogenes (Tertullian) chapter 3

በእርሱ እሳቤ ወላጅ አምላክ እና ተወላጅ ኢየሱስ ሂደቱ የተከናወነው ከፍጥረት በፊት በዘላለም ጊዜ ውስጥ ነው፥ "ዘላለም" ማለት "የማይቆጠር ጊዜ እና ጅማሮ የሌለው ጊዜ" በሚል ተረድተውት ዘላለም ፍጡር ውስጥ አያካትቱትም። ከዚህ የተነሳ አውናኒዎስ ዘሳይዚከስ"Eunomius of Cyzicus" እና አርዮስ ዘሊቢያ "ኢየሱስ ጅማሮ እና መነሻ ስላለው ፍጡር ነው" በማለት ሞግተዋል፦
"አምላክ ሁልጊዜ አባት አልነበረም፥ "አምላክ" አባት ያልነበረበት ጊዜ ነበር"።
The Deposition of Arius (Athanasius) Number 2

አውናኒዎስ እና አርዮስ "ከፍጥረት በፊት በነበረው ጊዜ ውስጥ አንዱ አምላክ ኢየሱስን ፈጥሮታል" የሚል ጽኑ አቋም አላቸው፦
ምሳሌ 8፥22 ጌታ የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ በቀድሞ ሥራው ፈጠረኝ። κύριος ἔκτισέν με ἀρχὴν ὁδῶν αὐτοῦ εἰς ἔργα αὐτοῦ
"ከራሱ በመውጣት የእርሱ የመጀመሪያ የተወለደ ልጅ ሆነ"።
Against Praxeas (Tertullian) Chapter 7

"መወለድ" የሚለው ፍካሬአዊ ቃል "መፈጠር" የሚለውን እማሬአዊ ቃል ስለሚያመልክት እና "የመጀመሪያ" የሚለው ቀጣይ ፍጥረታዊ ልጆች መላእክትን አመለካች ነው" የሚል ሙግት ሞግተዋል።
ይህን ውዝግብ ለመፍታት የኒቂያ ጉባኤ ተካሂዶ ጉባኤው "የተወለደ እንጂ አልተፈጠረም" በማለት አርዮስን አወገዙት፥ በመቀጠል በቆስጠንጢኒያ ጉባኤ ኢየሱስን ከዘመናት በፊት ከአብ የተወለደ" በማለት በማለት አውናኒዎሳውያንን አወገዙ።

በቆስጠንጢኒያ ጉባኤ "ጌታ፣ ሕይወት ሰጪ እና ከአብ በሠረጸ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን" በማለት ሦስተኛው አካል "እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ"God the Holy Spirit" አሉት።
መንፈስ ቅዱስ የተባለው ሦስተኛ የሥላሴ አባል ኢየሱስ ከአብ መወለድ በኃላ ከአብ እና ከወልድ የሠረጸ አካል እንደሆነ አውግስጢኖስ ተናግሯል፦
"ወልድ አስቀድሞ ከአብ የተወለደ እንደ ሆነ ከዚያም በኃላ መንፈስ ቅዱስ ከሁለቱም ሠርጿል"።
(On the Trinity Book 15: Chapter 26)

"መንፈስ ቅዱስ የሚሠርጸው ከማን ነው? የሚል ሰፊ ውዝግብ ነው። ሆነም ቀረ ቅድመ ዓለም "ጊዜ" የለምና ውልደት እና ሥርጸት ቅድመ ተከተል ስላላቸው አብ መንስኤ"Cause" ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ውጤት"Effect" ናቸው፥ ሁለቱም መነሾ"Orgin" ስላላቸው በመካከላቸው በቅድመ ተከተል የሂደት እና የመንስኤ ውጤት መቀዳደም አለ። እንደ ሥላሴ ትምህርት ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ እንደ አብ አንድ አምላክ እና እራሳቸውን የቻሉ አምላክ ሳይሆኑ ከአንዱ አምላክ የተገኙ ግኝት"Origination" ናቸው። "አምላክ" የሚለው አካላዊ ስም የሌላቸው ምንነታቸው ከአብ ምንነት እንዲሁ ማንነታቸው ከአብ ማንነት በልደት እና በሥርጸት የተገኘ ነው፦
፨ "አብ የወልድ ኑባሬ ምንጭ እና ሥር ነው"
Exposition of the Christian Faith (Ambrose) > Book IV(4) Chapter 10 Number 133
፨ "አብ አጠቃላይ ባሕርይ ነው፥ ነገር ግን ወልድ የአጠቃላዩ መገኘት እና ክፍል ነው"
(Against Praxeas (Tertullian), Chapter 9).

በእርግጥ አሏህ ራሱን ቻይ ነው፥ እርሱም አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱ ልጅ ያለው ከመኾን የጠራ ነው፥ በሰማያት እና በምድር ያለ ሁሉ የእርሱ ነው፦
2፥255 አሏህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፡፡ اللَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ
2፥171 አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱ ልጅ ያለው ከመኾን የጠራ ነው፡፡ በሰማያት እና በምድር ያለ ሁሉ የእርሱ ነው፡፡ መመኪያም በአሏህ በቃ፡፡ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ ۖ سُبْحَانَهُ أَن يَكُونَ لَهُ وَلَدٌ ۘ لَّهُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ ۗ وَكَفَىٰ بِاللَّهِ وَكِيلًا

አሏህ መውለድ እና መወለድ የሚባል ባሕርይ የለውም፥ አደም በቀዋሚ ማንነት"Indivisual person" አንድ ሰው እያለ ከእርሱ እልፍ አእላፋት ሰዋዊ አካላት ሲገኙ ብዙ ሰዎች እንጂ አንድ ሰው እንደማንል ሁሉ አብ በቀዋሚ ማንነት አንድ አምላክ እያለ ከእርሱ ሁለት አምላካዊ አካላት ሲገኙ ሦስት አማልክት እንጂ አንድ አምላክ አይባሉም።
ለጀሀነም ከሚዳርግ ሺርክ ወጥታችሁ በአንድነቱ ላይ ሁለትነት ሦስትነት የሌለበትን አሏህን እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ፊሊኦኬ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

4፥171 «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ ۚ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ

"ሥርጸት" የሚለው የግዕዙ ቃል "ሠረጸ" ማለትም "ወጣ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "መውጣት"Procession" ማለት ነው፥ በመንፈስ ቅዱስ ሥርጸት እሳቤ ወጥ የሆነ የአበው ስምምነት"consensus patrum" የለም። የመንፈስ ቅዱስ ሥርጸት ሥነ መለኮታዊ ውስብስብ"Theological Jargon" ነው፥ በታሪክ ውስጥ መንጫጫት እና ማንጫጫት የለመዱ ግሪክ ወሮም ክርስትና በ 381 ድኅረ ልደት በተካሄደው በቆስጠንጢንያ ጉባኤ ያሳለፉት አንቀጸ እምነት መንፈስ ቅዱስን "ከአብ የሠረጸ" የሚል ነው። "ቶ ኤክ ቱ ፓትሮስ ኤክፖሮዮሜኖን" τὸ ἐκ τοῦ Πατρὸς έκπορευόμενον ማለት "ከአብ የሠረጸ" ማለት ሲሆን ካቶሊክ የመንፈስ ቅዱስ ባሕርይ ከአብ ብቻ የሠረጸ ነው" የሚል እምነት አላቸው፥ በካቶሊክ እምነት መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከባሕርይ ባሕርይን ወስዶ ሠረጸ የሚል ይህ ሥርጸት ባሕርያዊ ሥርጸት"Ontological Procession" ይባላል። ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ"Gregory of Nazianzus" መንስኤነት"Causality" የአብ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል፦
"ነገር ግን ለአብ ያለው ሁሉ ከመንስኤነት በቀር የወልድ ነው"።
Orations (Gregory Nazianzen) Oration 34 Number X(10)

ካቶሊክ "የመንፈስ ቅዱስ አካል ከአብ እና ከወልድ የሠረጸ ነው" የሚል እምነት አላቸው፥ "ካይ ቱ ሁዩ" καὶ τοῦ Υἱοῦ ማለት "እና ከወልድ" ማለት ነው። አውግስጢኖስ ዘሂፓ"Augustine of Hippo" መንፈስ ቅዱስ በዋነኝነት(በባሕርይ) የሚሠርጸው ከአብ እንደሆነ እና በአካል ደግሞ ከሁለቱም ማለትም ከአብ እና ከወልድ እንደሆነ ተናግሯል፦
"በዋነኝነት መንፈስ ቅዱስ የሚሠርጸው ከአብ ሲሆን ያለ ምንም የጊዜ ልዩነት በጋራ ከሁለቱም ሥርጸትን አብ ሰጥቶአልና"።
On the Trinity <St. Augustine> Book XV(15) Chapter 26 Number 47

"እና ከወልድ" የሚለው የእምነት መገለጫ የጸደቀው ሦስተኛው የቶሊዶ ጉባኤ በ 589 ድኅረ ልደት በስፔን ነው፥ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ ከአካል አካልን ወስዶ የሠረጸበት ሥርጸት አካላዊ ሥርጸት"hypostaticl Procession" ይባላል። የሐዋርያት የእምነት መግለጫ ላይ የሌሉ ነገር ግን በኒቂያ እና በቆስጠንጢንያ ጉባኤ ላይ ብዙ ቃላት እንደተጨመሩ በቶሊዶ ጉባኤ ላይ "እና ከወልድ" የሚለው ተጨምሯል፥ ቅሉ እና ጥቅሉ ግን ብዙ የቤተክርስቲያን አበው መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ እንደሠረጸ ተናግረዋል። ለምሳሌ፦
፨ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ"Cyril of Alexandria"፦
"እርሱ በእውነት ከአብ እና ከወልድ ይሠርጻል"።
Treasury of the Holy Trinity, thesis 34

፨ አትናቴዎስ  ዘእስክንድርያ"Athanasius of Alexandria"፦
"መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ ነው፥ እርሱ ሠረጸ እንጂ አልተወለደም አልተፈጠረም"።
Athanasian Creed, verse 17

፨ አንብሮስ ዘሚለን"Ambrose of Milan"፦
"መንፈስ ቅዱስም ከአብ እና ከወልድ ሲሠርጽ ከአብ አይለይም፥ ከወልድም አይለይም"።
On the Holy Spirit (Ambrose) > Book I(1) Chapter 11 Number 120

አውግስጢኖስ ዘሂፓ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ እንደሠረጸ አስረግጦ በተደጋጋሚ ተናግሯል፦
፨ "መንፈስ ቅዱስ ከአብ እና ከወልድ የሠረጸ ስለሆነም እርሱ ወልድ ወደ ተወለደበት ወደ እርሱ(አብ) ተመለሰ"።
On the Trinity <St. Augustine> Book IV(4) Chapter 20 Number 29

፨ "ወልድ አስቀድሞ ከአብ የተወለደ እንደ ሆነ ከዚያም በኃላ መንፈስ ቅዱስ ከሁለቱም ሠርጿል"።
On the Trinity <St. Augustine> Book XV(15) Chapter 26 Number 45

ወልድ ከአብ መወለድ ቅድሚያ ሲሆን ቀጣይ መንፈስ ቅዱስ ከሁለቱም መሥረጹ ነው፥ በትምህርቱ የመንፈስ ቅዱስ ሥርጸት ከፍጥረት በፊት ቢሆንም በሥላሴ መካከል የሂደት መቀዳደም አለ፦
"ስለዚህ የወልድ ልደት ከጊዜው ውጪ ከአብ እንደሆነ እንደሚረዳ ሁሉ እንዲሁ የመንፈስ ቅዱስ ሥርጸት ከጊዜው ውጪ ከሁለቱም እንደሆነ መረዳት መቻል አለበት"።
On the Trinity <St. Augustine> Book XV(15) Chapter 26 Number 47

፨ "ለወልድ ለአብ ያለው ካለው መንፈስ ቅዱስም ከእርሱ(ወልድ) ዘንድ እንዲሠርጽ በእርግጥ ከአብ ዘንድ አለው"።
(On the Trinity <St. Augustine> Book XV(15) Chapter 26 Number 47

፨ "እንደተረዳሁኝ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ይሠርጽ ዘንድ አብ በራሱ እንዳለው እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ ይሠርጽ ዘንድ ለወልድ ሰጠው እላለው"።
On the Trinity <St. Augustine> Book XV(15) Chapter 26 Number 47
አብ በራሱ ለወልድ መንፈስ ቅዱስ ከወልድ እንዲሠርጽ ከሰጠው መቀዳደም የለምን? "ፊሊኦኬ"Filioque" የላቲን ቃል ሲሆን "ከወልድም" ማለት ነው፥ ይህ ውዝግብ ሄዶ ሄዶ 1053 ድኅረ ልደት በሮም በተደረገው ጉባኤ ተወጋግዘው ካቶሊክ እና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ"Eastern Orthodox" በሚል ተከፋፍለዋል። ይህ ክፍፍል "ታላቁ ክፍፍል"great Schism” ሲሆን የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አቋም "መንፈስ ቅዱስ የሠረጸው ከአብ በወልድ በኩል ነው" የሚል ነው፥ "ፐር ፊሊዩም"per filium" የላቲን ቃል ሲሆን "በወልድ በኩል" ማለት ነው። ይህንን አቋም ጠርጡሊያኖስ ዘካርቴጅ እና ዮሐንስ ዘደማስቆ"John of Damascus" የሚቋደሱት አቋም ነው፦
፨ "መንፈስ ከአብ በወልድ በኩል ካልሆነ በቀር ከሌላ ምንጭ እንደማይሠርጽ አምናለሁ"።
Against Praxeas (Tertullian) Chapter 4

፨ "መንፈስ ቅዱስ የመለኮትነቱን ስውር ምሥጢር የሚገልጥ የአብ ኃይል ነው፥ ለራሱ በሚያውቀው መንገድ ከአብ በወልድ በኩል የሠረጸ ነው"።
An Exposition of the Orthodox Faith (John of Damascus) Book I(1) Chapter 12

መንፈስ ቅዱስ ዓለም ሳይፈጠር አብን አህሎ እና መስሎ ከአብ አካል አካልን ከአብ ባሕርይ ባሕርይን ወስዶ ወጣ ተብሎ የሚታመን ሦስተኛ የሥላሴ አባል ነው፦
"የዛፍ ፍሬ ከሥር ሦስተኛ እንደሆነ፣ የወንዝ ዥረት ከምንጭ ሦስተኛ እንደሆነ፣ የጨረር ጫፍ ከፀሐይ ሥስተኛ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁ መንፈስ ከአምላክ እና ከወልድ ሦስተኛ ነው"።
Against Praxeas (Tertullian) Chapter 8

የእነርሱን የእርስ በርስ መጎንተል እና መጎናተል ትተን እንደ ባይብሉ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ከአብ አፍ እና አፍንጫ የሚወጣ እስትንፋስ ነው፦
መዝሙር 33፥6 ሠራዊታቸውም ሁሉ "በ-"አፉ እስትንፋስ" ጸኑ።  וּבְר֥וּחַ פִּ֝֗יו כָּל־צְבָאָֽם׃
ዘጸአት 15፥8 "በ-"አፍንጫህ እስትንፋስ" ውኆች ተከመሩ። וּבְר֤וּחַ אַפֶּ֙יךָ֙ נֶ֣עֶרְמוּ מַ֔יִם

እነዚህ ሁለት አናቅጽ ላይ "እስትንፋስ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ሩሓህ" רוּחַ ሲሆን "መንፈስ" ማለት ነው፥ መንፈስ በተለያየ ጊዜ ለተለያየ ሥራ ከአፉ ወይም ከአፍንጫው የሚወጣ እስትንፋስ ከሆነ እራሱን የቻለ ማንነት እና አምላክ በፍጹም አይደለም። ቀለል ያለ ጥያቄ፦
፨ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ፣ አብ አሥራጺ፣ ወልድ አሠራጺ ከሆኑ ወልድ ከመወለድ ግብር ተጨማሪ የማሣረጽ ግብር አለውን?
፨ "መሥረጽ" ማለት "መውጣት" ማለት ከሆነ ወልድስ ከአብ ወጥቶ የለምን? ለምን ሠራጺ አልተባለም?
፨ "መወለድ" ማለት "መውጣት" ማለት ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ወጥቶ የለምን? ለምን ተወላዲ አልተባለም?

ለአጽራረ ተውሒድ የምንለው ነገር ቢኖር  «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው" የሚል ነው፦
4፥171 «ሦስት ነው» አትበሉ! ተከልከሉ! ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አሏህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ وَلَا تَقُولُوا ثَلَاثَةٌ ۚ انتَهُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ إِنَّمَا اللَّهُ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ

አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
በክርስትና "አምላክ ነው" ተብሎ የሚታመን ግን የማይወልድ እና የማይወለድ ማንነት አለ። ይህ ማንነታዊ አምላክ ማን ነው?
ሦስት ፀሐይ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

16፥74 ለአሏህ አምሳያዎችን አታድርጉ፡፡ فَلَا تَضْرِبُوا لِلَّهِ الْأَمْثَالَ

አምላካችን አሏህ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነው፥ ለእርሱ ሞክሼ የለውም፦
19፥65 እርሱ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና አምልከው! እርሱን በአምልኮቱ ላይ ታገስ፡፡ ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን? رَّبُّ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَا بَيْنَهُمَا فَاعْبُدْهُ وَاصْطَبِرْ لِعِبَادَتِهِ ۚ هَلْ تَعْلَمُ لَهُ سَمِيًّا

አሏህ ከፍጥረት የሚመስለው ምንም ነገር የለም፥ ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም፦
42፥11 የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡ لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ
114፥4 «ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም»። وَلَمْ يَكُن لَّهُ كُفُوًا أَحَدٌ

"ኩፉው" كُفُو ማለት "ወደር" "እኩያ" "አቻ" "ቢጤ" "አምሳያ" "ተፎካካሪ" "ባላንጣ" ማለት ሲሆን እርሱ የሚተካከለው አቻ እና እኩያ እንዲሁ የሚመሳሰለው አምሳያ እና ቢጤ የለውም። በዲኑል ኢሥላም ለአሏህ አምሳያዎችን ማድረግ ሺርክ ነው፦
16፥74 ለአሏህ አምሳያዎችን አታድርጉ፡፡ فَلَا تَضْرِبُوا لِلَّهِ الْأَمْثَالَ

ነገር ግን በቤተክርስቲያን አበው አምላክን በፀሐይ ይመስሉታል፥ ፀሐይን ለአምላክ ሦስትነት ይጠቀሙበታል። "የፀሐይ ክበቡ አብ፣ ብርሃኑ ወልድ፣ ሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ" በማለት ይናገራሉ፥ ይህ የአምላክን ሦስትነት ያሳያልን?
፨ ሲጀመር ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አብ ካልሆኑ ብርሃን እና ሙቀት ግን ከክበቡ ከመውጣታቸው በፊት እራሱ ክበቡ ናቸው።
፨ ሲቀጥል ከክበቡ የሚወጡት ሦስት ናቸው፥ እነርሱም ብርሃን፣ ሙቀት፣ ጨረር ናቸው፥ ከክበቡ ጋር አራት ይሆናሉ።
፨ ሢሰልስ ለወልድ ምሳሌ የተሰጠው ብርሃን ከነበረ "ብርሃናት" የብርሃን ብዙ ቁጥር ነው፥ አንዱ ብርሃን አብ ሁለቱ ብርሃናትን ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በጥቅሉ ሦስት ብርሃናት ናቸው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 10 ቁጥር 6
"ዕውቀትን የሚገልጹ ብርሃናት ናቸው"።
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 10 ቁጥር 12
"አብ ብርሃን ነው፣ ከአብ የተወለደ ቃሉ ወልድ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፣ እንዲሁ ከአብ የሠረፀ መንፈስ ቅዱስም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው"።

፨ ሲያረብብ ፀሐይ አንድ አካል(Body) እንጂ ሦስት አካል አይደለችም፥ ክበብ፣ ብርሃን፣ ሙቀት፣ ጨረር የፀሐይ ክፍሎች እንጂ ማንነት(Person) አይደሉም። እንደ ሥላሴ ትምህርት ሦስቱ አካላት ማንነት እንጂ ክፍሎች"Particles" አይደሉም፥ ፀሐይ አንድ ስትሆን ሥላሴ ግን ሦስት ፀሐይ፣ ሦስት የብርሃን አዕማድ፣ ሦስት የእሳት ባሕርይ ናቸው፦
"ሦስት ፀሐይ" ብለው አስቀምጠዋል፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘረቡዕ ምዕራፍ 4 ቁጥር 21
"ሦስት ፀሐይ አንድ ብርሃን ነው"።
ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 21
"ሦስት የብርሃን አዕማድ በመጠን ግን አንድ ነው"።
ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 17
"ሦስት የእሳት ባሕርይ ነገር ግን አንድ ብርሃን ነው"።

አንዱን አምላክ በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? ይህ እኮ ነውር ነው፦
ኢሳይያስ 40፥18 እንግዲህ አምላክን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ?
ኢሳይያስ 46፥5 በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?

ፈጣሪ፦ "በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ? እያለ እናንተ በፀሐይ፣ በውኃ፣ በእንቁላል፣ በሻማ፣ በባሕር እንዴት ትመስሉታላችሁ? አምላካችን አሏህ ሂዳያ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን!

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
መልአክ ይመለካልን?

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

7፥206 እነዚያ እጌታህ ዘንድ ያሉት መላእክት እርሱን ከማምለክ አይኮሩም። ያወድሱታልም፥ ለእርሱ ይሰግዳሉ፡፡ إِنَّ الَّذِينَ عِندَ رَبِّكَ لَا يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِهِ وَيُسَبِّحُونَهُ وَلَهُ يَسْجُدُونَ

ሰዎች የማይሉትን እና የማያምኑትን እንደሚሉ እና እንደሚያምኑ አርጎ ሙግትን አዋቅሮ እና አደራጅቶ መሞገት ቁልመማዊ ሕፀፅ"strawman fallacy" ነው፥ አንድ ሰው ሰዎች የማይሉትን እና የማያምኑትን እንደሚሉ እና እንደሚያምኑ አርጎ ቁልመማዊ ሕፀፅ ማፀፅ የአጠይቆትን እሳቤ በቅጡ ያልተረዳ ሰው ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ "እንዚራ ስብሐት" በሚል መድብሉ "የአምልኮ መሥዋዕትንም ለአንቺ እሠዋለሁ" "የአምልኮ መሥዋዕትን ለአንቺ አቀርብልሻለሁ" በማለት በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ ማርያምን እንደሚያመልክ ይናገራል፦
እንዚራ ስብሐት ምዕራፍ 12 ቁጥር 98 "ለአንቺም የምስጋና እጅ መንሻን አቀርባለሁ፣ በመፍራት እገዛልሻለሁ፣ በመስገድም እጅ እነሣሻለሁ። "የአምልኮ መሥዋዕትንም ለአንቺ እሠዋለሁ"።
እንዚራ ስብሐት ምዕራፍ 13 ቁጥር 113
"ማርያም ሆይ! ያማረ ፍጹም ምስጋና አቀርብልሻለሁ። የሚጣፍጥ "የአምልኮ መሥዋዕትን ለአንቺ አቀርብልሻለሁ"።

"ለአንቺ" የሚለው ይሰመርበት! ለዚህ ጥያቄ መልስ ቀጥታ መመለስ ያቃተው ዲያቆን ዘማርያም(ቴዲ) "በባይብልም እኮ መልአክ እንደሚመለክ ይናገራል፥ ያ ትርጉም ከገባችሁ ይህንን መረዳት ቀላል ነው" በማለት ተቃራኒ አጸፋ ከመስጠት ይልቅ ከትካች አጸፋ በመስጠት አግባባዊ ሕፀፅ"Relevance fallacy" ሲያፅፅ ነበር። አንዱ ቀዳዳን ለመድፈን ሌላው ሲቦተረፍ የታየበትን ጥቅስ እንመልከት፦
የሐዋርያት ሥራ 27፥23 የእርሱ የምሆን እና ደግሞ የማመልከው የአምላክ መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና። παρέστη γάρ μοι ταύτῃ τῇ νυκτὶ τοῦ Θεοῦ, οὗ εἰμι, ᾧ καὶ λατρεύω, ἄγγελος

"ላትሬኦ" λατρεύω ማለት "አምልኮ" ማለት ሲሆን "የማመልከው" የሚለው የሚጠጋው "አምላክ" ወደሚለው እንጂ "መልአክ" ወደሚለው አይደለም፥ ይህ ሰው እንግሊዝኛ፣ ግዕዝ እና ግሪክ ቢያንስ እንዲያጠና ምከሩት! "የአስቀሪዬ የኡሥታዝ ልጅ ሰላም አለኝ" ብል "የአስቀሪዬ" የሚለው የሚጠጋው "ኡሥታዝ" ወደሚለው እንጂ "ልጅ" ወደሚለው አይደለም። አንድ ተመሳሳይ የሰዋስው አወቃቀር እስቲ እንመልከት፦
ራእይ 6፥9 የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። εἶδον ὑποκάτω τοῦ θυσιαστηρίου τὰς ψυχὰς τῶν ἐσφαγμένων

ሰው እንጂ ነፍስ እንደማይታረድ እሙን እና ቅቡል ነው፥ ቅሉ እና ጥቅሉ ግን "የታረዱትን" የሚለው የሚጠጋው "ሰዎች" ወደሚለው እንጂ "ነፍሳት" ወደሚለው አይደለም። "የ" የሚል አገናዛቢ ዘርፍ ያለበት "ሰዎች" የሚለው ቃል ባለቤትን ስለሚያሳይ "የታረዱትን" የሚለው የሚጠጋው "ሰዎች" ወደሚለው እንደሆነ ሁሉ "የ" የሚል አገናዛቢ ዘርፍ ያለበት "አምላክ" የሚለው ቃል ባለቤትን ስለሚያሳይ "የማመልከው" የሚለው የሚጠጋው "አምላክ" ወደሚለው ነው፥ ጳውሎስ የማመልከው የሚለው አምላክን እንጂ መልአክን በፍጹም አይደለም፦
2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥3 ሌሊት እና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን አምላክን አመሰግናለሁ። Χάριν ἔχω τῷ Θεῷ, ᾧ λατρεύω ἀπὸ προγόνων ἐν καθαρᾷ συνειδήσει, ὡς ἀδιάλειπτον ἔχω τὴν περὶ σοῦ μνείαν ἐν ταῖς δεήσεσίν μου νυκτὸς καὶ ἡμέρας,

"የማመልከውን አምላክን" የሚለው ኃይለ ቃል የሚመለከው አምላክ መሆኑን ቁልጭ እና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። "እንደ አባቶቼ አድርጌ" የሚለው ቃል ከጥንት ጀምሮ አባቶች ሲያመልኩት የነበረው መልአክን ሳይሆን አምላክን ነው፥ የኦርቶዶክስን አምልኮተ ማርያም ስህተት ለመሸፈን ባይብል ውስጥ ገብቶ መደበቅ አግባብ አይደለም።

ይህንን መጣጥፍ መልስ ለመስጠት የተነሳሁበት ዓላማ ኦርቶዶክሳውያን "እኛ ማርያምን አናመልክም፥ ቁርኣን ቁልመማዊ ሕፀፅ ሐፅፆአል" ብለው ለከሰሱት የሐሰት ክስ ምላሽ ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ "እንዚራ ስብሐት" መድብል ላይ አንብበን ያቀረብነው እኛ ሙሥሊሞች ነን፥ ይህንን ሙግት ፕሮቴስታንቱ ከእኛ ተቀብለው ሲያራግቡ ዲያቆን ዘማርያም መልስ ብሎ የመለሰው ገለባ መልስ እኛ ስለሚመለከት ብቻ ነው እንጂ በሰው ጉዳይ ለመፈትፈት አይደለም።

አሳብ መሞገት የሚበረታታ ጉዳይ ነው፥ በአሳብ ሉዓላዊነት፣ ልዕልና፣ ገዢነት እና ዘውግ የሚያምን ሰው ረብጣ የሆነ አሳብ ሲመጣለት በተሻለ አሳብ ማረቅ እና ማሳለጥ እንጂ እርር እና ምርር ብሎ መንጨርጨር እና መንተክተክ አግባብ አይደለም።

ከአንዱ አምላክ በቀር ለአንዳች ነገር የአምልኮ መሥዋዕት መሠዋት በገሃነም ሊያስጠፋ የሚችል ወንጀል ነውና ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፈርታችሁ ከዚህ ድርጊት ተቆጠቡ፦
ዘጸአት 22፥20 ከያህዌህ በቀር ለአንዳች አምላክ የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ።
ማቴዎስ 10፥28 ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።

ከአምልኮተ ማርያም ወጥታችሁ አሏህን በብቸኝነት እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ትንቅንቅ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

40፥41 «ወገኖቼም ሆይ! ወደ መዳን የምጠራችሁ ስኾን ወደ እሳትም የምትጠሩኝ ስትኾኑ ለእኔ ምን አለኝ? وَيَا قَوْمِ مَا لِي أَدْعُوكُمْ إِلَى النَّجَاةِ وَتَدْعُونَنِي إِلَى النَّارِ

“ኢሥላም” إِسْلَٰم ማለት "አምላክ አንድ አምላክ ብቻ ነው" ብሎ ለእርሱ ብቻ መገዛት ነው፦
22፥34 አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱም ብቻ ታዘዙ፡፡ ለአላህ ተዋራጆችንም አብስራቸው፡፡ فَإِلَـٰهُكُمْ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ فَلَهُ أَسْلِمُوا ۗ وَبَشِّرِ الْمُخْبِتِين

እዚህ አንቀጽ ላይ “ታዘዙ” ለሚለው ቃል የተቀመጠው “አሥሊሙ” أَسْلِمُوا ሲሆን “አሥለመ” أَسْلَمَ ማለትም “ታዘዘ”፣ “ተገዛ”፣ ” አመለከ” ከሚል ግስ የመጣ ነው፥ “አሥሊሙ” የሚለው ቃል “ሙሥሊም” مُسْلِم ለሚለው ቃል ትእዛዛዊ ግሥ ነው። ሙሥሊም ወደ አሏህ በመጥራት ቃሉ ያማረ ነው፦
41፥33 *ወደ አሏህ ከጠራ እና መልካምንም ከሠራ፦ «እኔ ከሙሥሊሞች ነኝ» ካለም ሰው ይበልጥ ቃሉ ያማረ ማን ነው?* وَمَنْ أَحْسَنُ قَوْلًا مِّمَّن دَعَا إِلَى اللَّهِ وَعَمِلَ صَالِحًا وَقَالَ إِنَّنِي مِنَ الْمُسْلِمِينَ

ሙሥሊም ሰዎችን የሚጠራው ወደ መዳን ነው፥ ሰዎች ከእሳት እንዲያመልጡ ነው። ሙሽሪክ ደግሞ ወደ እሳት ነው የሚጠራው፦
40፥41 «ወገኖቼም ሆይ! ወደ መዳን የምጠራችሁ ስኾን ወደ እሳትም የምትጠሩኝ ስትኾኑ ለእኔ ምን አለኝ? وَيَا قَوْمِ مَا لِي أَدْعُوكُمْ إِلَى النَّجَاةِ وَتَدْعُونَنِي إِلَى النَّارِ

ሙሽሪክ ጥሪው በአልምህ ለማስካድ እና በእርሱም ዕውቀት የሌለንን ነገር በእርሱ እንዳጋራ እንድናጋራ ነው፥ ሙሥሊም ግን ወደ አሸናፊው መሓሪው አሏህ ነው፦
40፥42 «በአሏህ ልክድ እና በእርሱም ለእኔ ዕውቀት የሌለኝን ነገር በእርሱ እንዳጋራ ትጠሩኛላችሁ፡፡ እኔም ወደ አሸናፊው መሓሪው አሏህ እጠራችኋለሁ፡፡ تَدْعُونَنِي لِأَكْفُرَ بِاللَّهِ وَأُشْرِكَ بِهِ مَا لَيْسَ لِي بِهِ عِلْمٌ وَأَنَا أَدْعُوكُمْ إِلَى الْعَزِيزِ الْغَفَّارِ

እንግዲህ በሙሥሊም እና በሙሽሪክ መካከል ያለው ትንቅንቅ ይህ ነው፥ ወደ አሏህ መጣራት ይህ መንገዳችን ነው። ከአጋሪዎች አይደለንም፥ ይህም ቀጥተኛ  መንገድ ነው። ሌሎች የጥመት መንገዶችንም አትከተል፥ ከቀጥተኛው መንገድ እኛን ለመለየት ነው ጥሪው፦
12፥108 «ይህች መንገዴ ናት፡፡ ወደ አላህ እጠራለሁ፡፡ እኔም የተከተለኝም ሰው በግልጽ ማስረጃ ላይ ነን፡፡ ጥራትም ለአሏህ ይገባው፡፡ እኔም ከአጋሪዎቹ አይደለሁም» በል፡፡ قُلْ هَـٰذِهِ سَبِيلِي أَدْعُو إِلَى اللَّهِ ۚ عَلَىٰ بَصِيرَةٍ أَنَا وَمَنِ اتَّبَعَنِي ۖ وَسُبْحَانَ اللَّهِ وَمَا أَنَا مِنَ الْمُشْرِكِينَ
6፥153 «ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ ተከተሉትም፡፡ የጥመት መንገዶችንም አትከተሉ፡፡ ከቀጥተኛው መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና፡፡ እነሆ ትጠነቀቁ ዘንድ በእርሱ አዘዛችሁ፡፡» وَأَنَّ هَـٰذَا صِرَاطِي مُسْتَقِيمًا فَاتَّبِعُوهُ ۖ وَلَا تَتَّبِعُوا السُّبُلَ فَتَفَرَّقَ بِكُمْ عَن سَبِيلِهِ ۚ ذَٰلِكُمْ وَصَّاكُم بِهِ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

አምላካችን አሏህ ይህንን እውነተኛ የተውሒድ መንገድ አመጣልን፥ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች እውነቱን ጠይዎች ናቸዉ፦
43፥78 እውነተኛውን መንገድ በእርግጥ አመጣንላችሁ፡፡ ግን አብዛኞቻችሁ እውነቱን ጠይዎች ናችሁ፡፡ لَقَدْ جِئْنَاكُم بِالْحَقِّ وَلَـٰكِنَّ أَكْثَرَكُمْ لِلْحَقِّ كَارِهُونَ

ሙስሊም ወደ አንድ አምላክ መንገድ  ሲጣራ መጣራት ያለበት “ስሙር ሙግት”valid argument”  ተጠቅሞ ነው፤ ይህ ሙግት በእማኝነትና በአስረጂነት ጠቅሶና አጣቅሶ መሟገት ነው፤ በትክክለኛው የአስተላለፍ ስልትና አወቃቀር ስለተዋቀረ የራሱ የሆነ መንደርደሪ፣ የሙግት ነጥብ”premise” እና መደምደሚያ ያለው ነው፤ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ማስረጃ በአጽንኦትና በአንክሮት ለማዳመጥ ጥልና ጥንፍፍ ያለ መረዳት ነው፤ ይህን ሙግት አምላካችን አላህ መልካም ክርክር ይለዋል፤ ይህ ዘዴ ርቱዕ አካሄድ”optimistic approach” ነው፦
16፥125 ወደ ጌታህ መንገድ በብልሃትና በመልካም ግሣጼ በለዘብታ ቃል ጥራ”፤ በዚያችም እርሷ መልካም በሆነችው “ዘዴ ተከራከራቸው”። ٱدْعُ إِلَىٰ سَبِيلِ رَبِّكَ بِٱلْحِكْمَةِ وَٱلْمَوْعِظَةِ ٱلْحَسَنَةِ ۖ وَجَٰدِلْهُم بِٱلَّتِى هِىَ أَحْسَنُ ۚ إِنَّ رَبَّكَ هُوَ أَعْلَمُ بِمَن ضَلَّ عَن سَبِيلِهِۦ ۖ وَهُوَ أَعْلَمُ بِٱلْمُهْتَدِينَ

“ሙሽሪክ” مُشْرِك የሚለው ቃል “አሽረከ” أَشْرَكَ ማለትም “አጋራ” ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን በአንድ አምላክ ላይ ሌሎች ማንነቶችንና ምንነቶችን "አጋሪ" ማለት ነው፥ ድርጊቱ  “ሺርክ” شِرْك ማለትም  “ማጋራት” ይባላል፤ በአላህ ላይ የሚያጋሩት ማንነትና ምንነት “ሸሪክ” شَرِيك ማለትም “ተጋሪ” ይባላሉ።    
ይህ ትንቅንቅ ይቀጥላል፤ ሙሽሪክ፦
1ኛ  ሦስት ማንነቶችን ማለትም ሥላሴን እንድናመልክ ይጠሩናል፥ ግን መመለክ ያለበት አንድ ማንነት ብቻ ነው።
2ኛ  ሰው እንድናመልክ ይጠሩናል፤ ኢየሱስ ሰውነቱ ይመለካል፥ በሰውነቱ ፍጡር ነው ይላሉና።
3ኛ ፍጡራንን እንድናመልክ ይጠሩናል፥ ፍጡራንን በሌሉበት ወደ እነርሱ መጎባደድ፣ መተናነስ፣ ማሸርገድ፣ መለማመን፣ መጸለይ፣ ስለት መሳል፣ መስዋዕት ማቅረብ፣ ስማቸውን መጥራት የአምልኮ ክፍል ነው፤ ሁሉን የሚሰማ፣ የሚያይ፣ የሚያውቅ አንድ መለኮት ብቻ ሆኖ ሳለ ወደ መላእክትና ቅዱሳን ይህንን ማድረግ ሺርክ ነው።
4ኛ. ለተቀረጸ ምስል እንድንሰግድ ይጠሩናል፤ ለተቀረጸ ምስል አትስገድ ተብሎ ነገር ግን በተቃራኒው ከእንጨት፣ ከብር፣ ከወርቅ፣ ከብረት፣ ከድንጋይ ለተቀረጹ መስቀል፣ ስዕል እና ሃውልት ይሰግዳሉ። ወገኖቼም ሆይ! ወደ መዳን የምጠራችሁ ስኾን ወደ እሳትም የምትጠሩኝ ስትኾኑ ለእኔ ምን አለኝ? እሳት መግባት አልፈልግም፦
40፥41 «ወገኖቼም ሆይ! ወደ መዳን የምጠራችሁ ስኾን ወደ እሳትም የምትጠሩኝ ስትኾኑ ለእኔ ምን አለኝ? وَيَا قَوْمِ مَا لِي أَدْعُوكُمْ إِلَى النَّجَاةِ وَتَدْعُونَنِي إِلَى النَّارِ

ወደ ዲኑል ኢሥላም እንድትመጡ ጥሪያችን ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
መንበርከክ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

3፥51 «አሏህ ጌታዬ እና ጌታችሁ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» አላቸው፡፡ إِنَّ اللَّهَ رَبِّي وَرَبُّكُمْ فَاعْبُدُوهُ ۗ هَـٰذَا صِرَاطٌ مُّسْتَقِيمٌ

ፈጣሪ በመጀመሪያ መደብ "ጕልበት ሁሉ “ለ”-እኔ ይንበረከካል" በማለት ይናገራል፦
ኢሳይያስ 45፥23 ጕልበት ሁሉ “ለ”-እኔ ይንበረከካል። כִּי־לִי֙ תִּכְרַ֣ע כָּל־בֶּ֔רֶךְ

"ሊ" לִי֙ ማለት "ለእኔ" ማለት ሲሆን "እኔ" በሚል ተውላጠ ስም መነሻ ላይ ያለው "ለ" የሚል መስተዋድድ መንበርከክ ለእርሱ እንደሆነ ቁልጭ አርጎ ያሳያል፥ "ለ" ቀጥታ የሚንበረከኩለት ማንነት እና ምንነት ነው፦
ሮሜ 14፥11 "ጉልበት ሁሉ "ለ"-እኔ ይንበረከካል"። ὅτι ἐμοὶ κάμψει πᾶν γόνυ, 

"ኩርዮስ" Κύριος ከቀኝ ወደ ግራ የሚነበቡት ቴትራግራማቶን ስለሚያመለክት እና ከኢሳይያስ 45፥23 ላይ ስለተጠቀሰ "ዮድ ሔ ቫቭ ሔ" יְהוָה֮ የተባለውን አብን አመላካች ነው፦
ኤፌሶን 3፥15 ስለዚህ ምክንያት በሰማይ እና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ። ἐξ οὗ πᾶσα πατριὰ ἐν οὐρανοῖς καὶ ἐπὶ γῆς ὀνομάζεται,

"ከአብ ፊት እንበረከካለሁ" የሚለውን አስምረህ በሰማይ እና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ ለአብ የሚንበረከከው "በ"-ኢየሱስ ስም እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል፦
ፊልጵስዩስ 2፥10 ይህም በሰማይ እና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ "በ"-ኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው። ἵνα ἐν τῷ ὀνόματι Ἰησοῦ πᾶν γόνυ κάμψῃ ἐπουρανίων καὶ ἐπιγείων καὶ καταχθονίων,

እዚህ አንቀጽ "በ" ለሚለው መስተዋድድ የገባው ቃል "ኤን" ἐν ሲሆን "በኩል" ማለት ነው፥ "ዲይ" δἰ ወይም "ዲያ" διά ከሚል ቃል ጋር ተለዋዋጭ ነው። "ኤን ቱ ኦኖማቲ የሱ" ἐν τῷ ὀνόματι Ἰησοῦ ማለት "በኢየሱስ ስም" ማለት ስለሆነ የተለያዩ ዕትማት በትክክሉ "በኢየሱስ ስም"in the name of Jesus" በማለት አስቀምጠዋል፦
1. American Standard Version
Philippians 2፥10 "in the name of Jesus"
2. Aramaic Bible in Plain English
Philippians 2፥10 "in the name of Jesus"
3. English Revised Version
Philippians 2፥10 "in the name of Jesus"
4. Literal Standard Version
Philippians 2፥10 "in the name of Jesus"
5. Young's Literal Translation
Philippians 2፥10 "in the name of Jesus"

ብዙ ክርስቲያን ሚሽነሪዎች "በኢየሱስ ስም" የሚለው "ለኢየሱስ ስም" በማለት እያጠናገሩ ስለሆነ ትኩረት ሰቶ ማንበብ ያሻል፦
ኤፌሶን 5፥20 ሁልጊዜ ስለ ሁሉ "በ"-ጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንን እና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። εὐχαριστοῦντες πάντοτε ὑπὲρ πάντων ἐν ὀνόματι τοῦ Κυρίου ἡμῶν Ἰησοῦ Χριστοῦ τῷ Θεῷ καὶ Πατρί,

አሁንም "በ" ለሚለው መስተዋድድ የገባው ቃል "ኤን" ἐν ሲሆን "በኩል" ማለት ነው፥ ጳውሎስ "አምላካችንን እና አባታችንን" ያለው አብን በኢየሱስ ስም ስለማመስገን ብዙ ቦታ ይናገራል፦
ሮሜ 1፥8 አምላኬን “በ”-ኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። εὐχαριστῶ τῷ Θεῷ μου διὰ Ἰησοῦ Χριστοῦ 
ሮሜ 7፥25 “በ”-ኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን “ለ”-እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።χάρις τῷ Θεῷ διὰ Ἰησοῦ Χριστοῦ τοῦ Κυρίου ἡμῶν. 
ሮሜ 16፥27 ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን! አሜን። μόνῳ σοφῷ Θεῷ, διὰ Ἰησοῦ Χριστοῦ, ᾧ ἡ δόξα εἰς τοὺς αἰῶνας τῶν αἰώνων· ἀμήν.

ሦስቱም አናቅጽ ላይ "በ" ለሚለው የገባው ቃል "ዲያ" διά ሲሆን ምስጋናው "አምላኬ" ለሚለው ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር አብ ነው፦
ቆላስይስ 3፥17 እግዚአብሔር አብን “በ”-እርሱ እያመሰገናችሁ። εὐχαριστοῦντες τῷ Θεῷ Πατρὶ δι’ αὐτοῦ.
ዕብራውያን 13፥15 እንግዲህ ዘወትር “ለ”-እግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ “በ”-እርሱ እናቅርብለት። δι’ αὐτοῦ οὖν ἀναφέρωμεν θυσίαν αἰνέσεως διὰ παντὸς τῷ Θεῷ, τοῦτ’ ἔστιν καρπὸν χειλέων ὁμολογούντων τῷ ὀνόματι αὐτοῦ.

ሁለቱም አናቅጽ ላይ "በ" ለሚለው የገባው ቃል "ዲይ" δἰ ሲሆን ምስጋናው “ለ”-እግዚአብሔር አብ" ነው፥ "ለ" መስተዋድዱ የሚጠጋው ብቻውን ለሆነ አምላክ እና መድኃኒት ነው፦
ይሁዳ 1፥25 ብቻውን "ለ"-ሆነ አምላክ እና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ "በ"-ጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን! አሜን። μόνῳ Θεῷ Σωτῆρι ἡμῶν διὰ Ἰησοῦ Χριστοῦ τοῦ Κυρίου ἡμῶν δόξα μεγαλωσύνη κράτος καὶ ἐξουσία πρὸ παντὸς τοῦ αἰῶνος καὶ νῦν καὶ εἰς πάντας τοὺς αἰῶνας· ἀμήν.
እዚህ አንቀጽ "በ" ለሚለው የገባው ቃል "ዲያ" διά ሲሆን "በኩል" ማለት ነው፥ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ለአብ በክርስቶስ በኩል መሆንን ያሳያል። ይህንን ከተረዳን ዘንድ ኢየሱስ መንበርከኪያ መሣሪያ"Instrument" እንጂ የሚንበረከኩለት ማንነት እና ምንነት አይደለም፥ "ፊልጵስዩስ 2፥10 ላይ መንበርከክ ለኢየሱስ እንደሆነ ያሳያል" የሚለው ሙግት ውኃ የማያነሳ እና የማይቋጥር ሙግት ነው። “በ” አስመላኪ ሲሆን “ለ” ደግሞ ተመላኪ ነው፥ “በ” የሚለውን “ለ” ብሎ ከተረዱት እንግዲያውስ “በ”-ጽዮን” የሚለውን “ለ”-ጽዮን” ብለው መረዳት ይኖርባቸዋል፦
መዝሙር 65፥1 አቤቱ “በ”-ጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል።  לַמְנַצֵּ֥חַ מִזְמֹ֗ור לְדָוִ֥ד שִֽׁיר׃ לְךָ֤ דֻֽמִיָּ֬ה תְהִלָּ֓ה אֱלֹ֘הִ֥ים בְּצִיֹּ֑ון

ዋናው ነጥብ ጉልበት ሁሉ የሚንበረከክ ለኢየሱስ ስም ሳይሆን በኢየሱስ ስም ለፈጣሪ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ አስመላኪ እንጂ ተመላኪ አይደለም፥ ለፈጣሪው ተንበርክኮ የሚያመልክ አካል ተመልሶ ተመላኪ አይሆንም። ኢየሱስ እራሱ በጉልበቱ ተንበርክኮ እና በፊቱ ተደፍቶ ወደ ፈጣሪ ይጸልይ ነበር፦
ማቴዎስ 26፥39 ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀ እና ሲጸልይ። καὶ προελθὼν μικρὸν ἔπεσεν ἐπὶ πρόσωπον αὐτοῦ προσευχόμενος
ሉቃስ 22፥41 ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ "ተንበርክኮም" ጸለየ። καὶ αὐτὸς ἀπεσπάσθη ἀπ’ αὐτῶν ὡσεὶ λίθου βολήν, καὶ θεὶς τὰ γόνατα προσηύχετο

ሸብረክ እና ብርክክ ብሎ ለፈጣሪው ሡጁድ የሚወርድ ኢየሱስ እራሱ አምላኪ መሆኑን ይህ ጥቅስ ጉልኅ ማሳያ ነው፥ እንደው ለኢየሱስ ቢንበረከኩለት እንኳን መንበርከክ በእስራኤል ባህል አክብሮትን ለማሳየት ይመጣል፦
2ኛ ነገሥት 1፥13 በኤልያስ ፊት በጒልበቱ "ተንበረከከ"። וַיִּכְרַ֥ע עַל־ בִּרְכָּ֣יו לְנֶ֣גֶד אֵלִיָּ֗הוּ

"ዪክራ" כְרַ֥ע የሚለው የግሥ መደብ "ካራ" כָּרַע ለሚለው አሁናዊ ግሥ ነው፥ ታዲያ አምሳ አለቃው ለኤልያስ በጒልበቱ ስለተንበረከከ ኤልያስን እያመለከው ነበርን? እረ በፍጹም። ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን የምድረ በዳ ዘላኖች እንደሚንበረከኩለት ተናግሯል፦
መዝሙር 72፥9 የምድረ በዳ ዘላኖች በፊቱ ይንበረከካሉ። לְ֭פָנָיו יִכְרְע֣וּ צִיִּ֑ים

"ጺዪ" צִיִּי ማለት "የምድረ በዳ ዘላን" ማለት ሲሆን የጺዪ ብዙ ቁጥር ደግሞ "ጺዪም" צִיִּ֑ים ነው፥ ይህም ቃል የበረሃ ሰውን ወይም የዱር አውሬን ለማመልከት ይመጣል። እዚህ አንቀጽ ላይ "ይንበረከካሉ" ለሚለው የገባው ቃል "ይክራዩ" יִכְרְע֣וּ ሲሆን "ካራ" כָּרַע ማለትም "ተንበረከከ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ነው፥ ስለዚህ መንበርከክ በራሱ አምልኮ አይደለም። ዋናው ነጥባችን "ፊልጵስዩስ 2፥10 ላይ በሰማይ እና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ "በ"-ኢየሱስ ስም የሚንበረከኩት ለአብ እንደሆነ የሚናገር ክፍል ነው" የሚል ሰፊ ሙግት ነው፥ በእርግጥ ለእኛ ለሙሥሊሞች የጳውሎስ ንግግር መረጃ"Information" እንጂ ማስረጃ"Evidence" አይደለም። የአምላካችን የአሏህ ንግግር ማስረጃችን ሲሆን ኢየሱስ የመልእክቱ ጭብጥ «አሏህ ጌታዬ እና ጌታችሁ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» የሚል እንደነበር አሏህ በቅዱስ ቃሉ ነግሮናል፦
3፥51 «አሏህ ጌታዬ እና ጌታችሁ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» አላቸው፡፡ إِنَّ اللَّهَ رَبِّي وَرَبُّكُمْ فَاعْبُدُوهُ ۗ هَـٰذَا صِرَاطٌ مُّسْتَقِيمٌ

ፍጡር ከማምልከ ነጻ ወጥታችሁ አሏህን በብቸኝነት እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ቃቢል

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

5፥27 በእነርሱም ላይ የአደምን ሁለት ልጆች ወሬ ቁርባንን ባቀረቡ እና አሏህ ከአንደኛቸው ተቀብሎ ከሌላው ባልተቀበለ ጊዜ የኾነውን በእውነት አንብብላቸው፡፡ وَاتْلُ عَلَيْهِمْ نَبَأَ ابْنَيْ آدَمَ بِالْحَقِّ إِذْ قَرَّبَا قُرْبَانًا فَتُقُبِّلَ مِنْ أَحَدِهِمَا وَلَمْ يُتَقَبَّلْ مِنَ الْآخَرِ

በባይብል በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ አዳም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ተራክቦ በመፈጸም የበኵር ልጅ ቃየን ፀንሳ ወለደች፦
ዘፍጥረት 4፥1 አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም፦ “ወንድ ልጅ ከያህዌህ አገኘሁ” አለች። וְהָ֣אָדָ֔ם יָדַ֖ע אֶת־חַוָּ֣ה אִשְׁתֹּ֑ו וַתַּ֙הַר֙ וַתֵּ֣לֶד אֶת־קַ֔יִן וַתֹּ֕אמֶר קָנִ֥יתִי אִ֖ישׁ אֶת־יְהוָֽה׃

እዚህ አንቀጽ "ቃየን" ለሚለው የገባው ቃል "ካዬን" קַיִן ሲሆን "የተገኘ" ማለት ነው፥ "አገኘሁ" ለሚለው የገባው ቃል "ካኒቲ" קָנִ֥יתִי ሲሆን "ካዬን" קַיִן የሚለው የስም መደብ ሆነ "ካኒቲ" קָנִ֥יתִי የሚለው የሥም መደብ ሥርወ ቃሉ "ካና" קָנָה ነው።

ይህ ሆኖ ሳለ “ወንድ ልጅ ከያህዌህ አገኘሁ” ያለችውን በታርገም ዮናታን ላይ "ወንድ ልጅ ከጌታ መልአክ አገኘሁ” በማለት ያስቀምጣል፦
ታርገም ዮናታን ዘፍጥረት 4፥1 አዳምም መልአኩን የፈለገችው ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም፦ “ወንድ ልጅ ከጌታ መልአክ አገኘሁ” አለች። וְאָדָם יְדַע יַת חַוָה אִיתְּתֵיהּ דַהֲוָה חֲמֵידַת לְמַלְאָכָא וְאַעֲדִיאַת וִילֵידַת יַת קַיִן וַאֲמָרַת קָנִיתִי לְגַבְרָא יַת מַלְאָכָא דַיְיָ

"መልአኩን የፈለገችው ሚስቱን" የሚለውን አስምርበት! ሔዋን ልጁን ያገኘችው ከአዳም ሳይሆን ከምትፈልገው ከመልአኩ ሰለሆነ "ወንድ ልጅ ከጌታ መልአክ አገኘሁ" አለች። ሳጥናኤል የተባለው የጌታ መልአክ ሥጋ ሆኖ ያ ሥጋ እባብ ሲሆን በዔድን ገነት ውስጥ የሔዋንን ክብረ ንጽሕና ወስዶ አስረገዛት፦
ታርገም ዮናታን ዘፍጥረት 3፥6 የሞት መልአክን ሳማኤልን አየችው እና ፈራች፥ እሷ ግን ዛፉ ለመብላት ጥሩ እንደ ሆነ አውቃለች። וְחָמַת אִתְּתָא יַת סַמָאֵל מַלְאָךְ מוֹתָא וּדְחִילַת וְיַדְעַת אֲרוּם טַב אִילָנָא לְמֵיכַל וַאֲרוּם אָסוּ הוּא

"ሳማኤል" סַמָּאֵל ማለት "የአምላክ መርዝ" ማለት ሲሆን ይህ የሞት መልአክ ሳማኤልን ሔዋንን ያፀነሰ የቃየን አባት ተብሎ የሚታመን በእባብ ሥጋ የተሠገወ መልአክ ነው። ሔዋን ከእባቡ ጋር ማግጣ ቃየንን የወለደችውን የሚሉት ይህንን ዳራ ይዘው ነው፦
1ኛ ዮሐንስ 3፥12 ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም።

"ቃየል ከክፉው ሰይጣን ነበረ" ማለት አንዳንድ በኋላ የአይሁድ መጻሕፍት "የቃየን አባት ራሱ ዲያብሎስ ነው" ይላሉ፦
"የቃየንን ኃጢአተኛነት የአይሁድ ትውፊት በሰፊው አብራርቷል አስምሮበታል፥ እርሱ ከክፉው ነበረ። ነፍሰ ገዳይ የዲያብሎስ ልጅ ነበር(ቁ. 10)፥ ከዲያብሎስ የመጀመሪያ ሥራዎቹ አንዱ ለአዳም ሞት ማምጣት ነበር(ዮሐ 8፥44 ላይ ያለውን ማስታወሻ ተመልከት!)። አንዳንድ በኋላ የአይሁድ መጻሕፍት "የቃየን አባት ራሱ ዲያብሎስ ነው" ይላሉ"።
The NIV Cultural Backgrounds Study Bible 1st John 3፥12

"የተወለደው ልጅ ቃየን የእባቡ ልጅ ነው" የሚል ትርክት ከጥንት ጀምሮ የመጣው በዚህ ምክንያት ነው፦
"ነገር ግን ሔዋን ከወደቀች በኋላ ሰይጣን በእባቡ ተመስሎ ወደ እርስዋ ቀረበ፥ እናም የአንድነታቸው ፍሬ ቃየን ነበር። በአምላክ ፊት ያመፁ የክፉ ትውልድ ሁሉ አባት ሲሆን በአምላክ ላይ ተነሳ። ቃየን በሱራፌል መገለጡ የተገለጠ የመልአኩ ሳማኤል ዘር ነው፥ በተወለደ ጊዜ ከሔዋን፦ "ወንድ ልጅ ከጌታ መልአክ አገኘሁ" የሚል ድምፅ ተሰምቷል፥ ቃየንን ሔዋን ባረገዘች ጊዜ አዳም ከእርሷ ጋር አልነበረም"።
Legends of the Jews 1:3

የፊሊጶስ ወንጌል ይህንን ዳራ እና ፍሰት ይዞ "ቃየን በዝሙት ተወለደ፥ የእባቡ ልጅ ነበረ" ይለናል፦
የፊሊጶስ ወንጌል 61፥5 ዝሙት መጀመርያው ተጀመረ፥ ከዚያ ግዲያ ቀጠለ። ቃየን በዝሙት ተወለደ፥ የእባቡ ልጅ ነበረ። እርሱ ልክ እንደ አባቱ ነፍሰ ገዳይ ሆነ።

በሁለተኛ ክፍለ ዘመን የተገኘው የፊሊጶስ ወንጌል ቅጂ በቫሊንቲንዮስ የተዘጋጀ ሲሆን "ቃየልን ሔዋን ከእባቡ የፀነሳችውን በዝሙት ነው" የሚለውን እሳቤ ኢራኒየስ ዘሊዮን"Irenaeus of Lyon" በማውገዝ ቫሊንቲንዮስ የሚለውን እንዲህ ያቀርብልናል፦
"ቀድሞ ራሱን እባብ አባት ብሎ የሚጠራው ውሸታም ነበረ፥ እናም ወንድ እና የመጀመሪያዋ ሴት ከዚህ በፊት ሲኖሩ ይህቺ ሴት ሔዋን ዝሙት በመፈጸም ኃጢአት ሠርታለች"።
Against Heresies (St. Irenaeus) Book I(1) Chapter 30 Number 7

በቫሊንቲንዮሳውያን ዘንድ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ከሔዋን ጋር ኃጢአትን አድርጓል ተብሎ ይታመናል፦
1ኛ ዮሐንስ 3፥8 ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።

በክርስትና እና በአይሁድ እሳቤ የመላእክት ጋብቻ የሚባል ቅሰጣዊ ትምህርት አለ። ይህንን ሊንክ ያስፈንጥሩ፦ https://tttttt.me/Wahidcom/1849

ወደ ዲኑል ኢሥላም ስንመጣ "ቃቢል" قَابِيْل ማለት "ቃየን"Cain" ማለት ሲሆን የአደም እና የሐዋእ የበኵር ልጅ ነው፥ "ሃቢል" هَابِيل ማለት "አቤል"Abel" ማለት ሲሆን ሁለተኛው የአደም እና የሐዋእ ልጅ ነው። "ነበእ" نَبَأ ማለት "ወሬ" ማለት ሲሆን ለነቢይ የሚወርድለት "ግልጠተ መለኮት ነው፥ "ነቢይ" نَبِيّ አሏህ የሩቅ ወሬ የሚተርክለት ሰው ነው። አምላካችን አሏህ አላፊ የሆነውን የአደምን ሁለት ልጆች የሩቅ ወሬ በተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ላይ እንዲህ ሲል ይተርካል፦
5፥27 በእነርሱም ላይ የአደምን ሁለት ልጆች ወሬ ቁርባንን ባቀረቡ እና አሏህ ከአንደኛቸው ተቀብሎ ከሌላው ባልተቀበለ ጊዜ የኾነውን በእውነት አንብብላቸው፡፡ وَاتْلُ عَلَيْهِمْ نَبَأَ ابْنَيْ آدَمَ بِالْحَقِّ إِذْ قَرَّبَا قُرْبَانًا فَتُقُبِّلَ مِنْ أَحَدِهِمَا وَلَمْ يُتَقَبَّلْ مِنَ الْآخَرِ

"የአደምን ሁለት ልጆች" የሚለው ይሰመርበት! ይህ አንቀጽ ቃቢል የአደም ልጅ መሆኑን ፍንትው እና ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፥ ስለዚህ ቃቢል የኢብሊሥ ልጅ ሳይሆን የአደም ልጅ ነው። በእናታችን ሐዋእ ላይ የቀጠፉትን ቀጣፊዎች አምላካችን አሏህ የእጃቸውን ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ዲኑል ኢሥላም ከአሏህ ዘንድ ሰዎች የሚድኑበት ምርጫ እንጂ ከባጢል ውስጥ የምናማርጠው አማራጭ በፍጹም አይደለም።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
ወደ ቻናሉ የምትገቡ አዳዲስ አንባቢያን ከላይ ጀምሩ፦ https://tttttt.me/Wahidcom/18
ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
Video
የኦርቶዶክስ ትርምስ

በልጅነታችን "ታቦት በውስቴታ ኦሪት በውስቴታ
ውቱረ ይከድንዋ በወርቅ" ወይም "ውስቴታ ታቦት በውስቴታ ኦሪት በውስቴታ ይኬልልዋ በወርቅ ይኬልልዋ" ሲባል ያደግንበትን ነገር መምህር ብርሃኑ አድማስ "የብሉይ ኪዳን ታቦት የለንም" ሲሉ የነበረው ወይስ እኛ ሳናውቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እድሳት አረገች? በተቃራኒው መምህር ዘበነ ለማ ደግሞ "የብሉይ ኪዳን እና የአዲስ ኪዳን ታቦት ልዩነት እንደሌለው እና የብሉይ ኪዳን ታቦት በአዲስ ኪዳን የቀጠለ ነው" ብለዋል።

በእርግጥ ታቦት በብሉይ ኪዳን ነበረ፥ ያ ታቦት መሠዊያ ወይም ጠረጴዛው ሳይሆን እራሱን የቻለ የጽላት ማስቀመጫ ሳጥን ነው፦
ዘጸአት 26፥34 በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ።
ዘዳግም 10፥5 ጽላቶችንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው።

ታቦት መቀመጫው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ነው፥ ጠረጴዛ ደግሞ በቅድስት ውስጥ ሲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ደግሞ በአደባባይ ላይ አሊያም ከሰፈር ውጪ ያለ ነበር፦
ዕብራውያን 9፥2 ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙ እና "ጠረጴዛው" የመስዋዕቱም ኅብስት ነበረባት።
ዘጸአት 17፥15 ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም፡ ይህዌህ ንሲ፡ ብሎ ጠራው።
ዕብራውያን 13፥11 ሊቀ ካህናት ስለ ኃጢአት ወደ ቅድስት የእንስሶችን ደም ያቀርባልና፤ ሥጋቸው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል።

ስለዚህ አዲስ ኪዳን ላይ ታቦት የሚባል በጉባኤ መካከል ያለ የለም፥ ጠረጴዛ እና መሠዊያ ደግሞ ለየቅል የሆኑ ነገሮች ሲሆኑ "ታቦት" ተብለው እንደተጠሩ የሚያሳይ ምንም ዓይነት የአዲስ ኪዳን ፍንጭ የለም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የወከለችው መምህር ማንን ነው? "የብሉይ ኪዳን ታቦት የለንም" የሚለውን መምህር ብርሃኑ አድማስን ወይስ "የብሉይ ኪዳን እና የአዲስ ኪዳን ታቦት ልዩነት እንደሌለው እና የብሉይ ኪዳን ታቦት በአዲስ ኪዳን የቀጠለ ነው" የሚለውን መምህር ዘበነ ለማ?
የጌቶች ጌታ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

6፥164 በላቸው «እርሱ አላህ የሁሉ ነገር ጌታ ሲሆን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን? ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም፡፡ قُلْ أَغَيْرَ ٱللَّهِ أَبْغِى رَبًّۭا وَهُوَ رَبُّ كُلِّ شَىْءٍۢ ۚ وَلَا تَكْسِبُ كُلُّ نَفْسٍ إِلَّا عَلَيْهَا

ባይብል ሴት ለባሏ እንድትገዛ ይናገራል፥ ሕግ ደግሞ "ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም "ገዥሽ" ይሆናል" ይላልና፦
1ኛ ቆሮንቶስ 14፥34 ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፥ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና።
ዘፍጥረት 3፥16 ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም "ገዥሽ" ይሆናል።

ወንድ የሴት "ራስ" ነው፥ ሴት ባሏን "ጌታ" እያለች ከታዘዘች ትሸለማለች፦
1ኛ ጴጥሮስ 3፥5 ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፥ እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም፦ ጌታ" ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት።
1 ቆሮንቶስ 11፥3 ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስ ራስ አምላክ እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ። Θέλω δὲ ὑμᾶς εἰδέναι ὅτι παντὸς ἀνδρὸς ἡ κεφαλὴ ὁ Χριστός ἐστιν, κεφαλὴ δὲ γυναικὸς ὁ ἀνήρ, κεφαλὴ δὲ τοῦ Χριστοῦ ὁ Θεός.

"የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት! ወንዶች ሁሉ የሴቶች ራሶች ከሆኑ የወንዶች ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፥ "ራስ" እና "ጌታ" ተለዋዋጭ ቃላት ናቸው፦
የሐዋርያት ሥራ 5፥31 ይህን አምላክ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ "ራስ" እና መድኃኒትም "አድርጎ" በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። τοῦτον ὁ Θεὸς Ἀρχηγὸν καὶ Σωτῆρα ὕψωσεν τῇ δεξιᾷ αὐτοῦ τοῦ δοῦναι μετάνοιαν τῷ Ἰσραὴλ καὶ ἄφεσιν ἁμαρτιῶν.
የሐዋርያት ሥራ 2፥36 ኢየሱስን አምላክ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ። ἀσφαλῶς οὖν γινωσκέτω πᾶς οἶκος Ἰσραὴλ ὅτι καὶ Κύριον αὐτὸν καὶ Χριστὸν ἐποίησεν ὁ Θεός, τοῦτον τὸν Ἰησοῦν.

አንዱ አምላክ ኢየሱስን "ራስ" እና "ጌታ" ካደረገው ኢየሱስ "የራሶች ራስ" "የጌቶች ጌታ" ነው። ክርስቶስ "የጌቶች ጌታ" የተባለው በአንጻራዊ ደረጃ ስለሆነ እርሱ እራሱ ከእርሱ በላይ ራስ አለው፥ ይህም ኢየሱስን ራስ ያደረገው አንዱ አምላክ ነው፦
1 ቆሮንቶስ 11፥3 ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስ ራስ አምላክ እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ። Θέλω δὲ ὑμᾶς εἰδέναι ὅτι παντὸς ἀνδρὸς ἡ κεφαλὴ ὁ Χριστός ἐστιν, κεφαλὴ δὲ γυναικὸς ὁ ἀνήρ, κεφαλὴ δὲ τοῦ Χριστοῦ ὁ Θεός.

"የክርስቶስ ራስ አምላክ እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ" ከተባለ የኢየሱስ ራስነት በመደረግ ላይ የተመሠረተ ነው፥ ምክንያቱም "ራስ" አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው" ስለሚል ነው። "ራስ" ተብሎ የገባው ቃል "አርኬጎስ" ἀρχηγός ሲሆን "አለቃ" "ገዥ" ማለት ነው፦
ራእይ 1፥5 የምድርም ነገሥታት "ገዥ" ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ለእናንተ ይሁን። καὶ ὁ ἄρχων τῶν βασιλέων τῆς γῆς. Τῷ ἀγαπῶντι ἡμᾶς 

"የምድርም ነገሥታት ገዥ" ማለት "የጌቶች ጌታ" ማለት ነው፥ ሁሉንም ከእግሩ በታች ያስገዛለት አንዱ አምላክ ሲሆን ኢየሱስ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለአንድ አምላክ ይገዛል፦
ኤፌሶን 1፥22 ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት።
1 ቆሮንቶስ 15፥27 ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፦ "ሁሉ ተገዝቶአል" ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው።
1 ቆሮንቶስ 15፥28 ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።

ኢየሱስን "ራስ" "ገዥ" "ጌታ" ያደረገው አንዱ አምላክ ጌትነቱ የባሕርይ ሲሆን ኢየሱስ ግን "የጌቶች ጌታ" የተባለው "የነገሥታት ንጉሥ" በተባለበት ሒሣብ ነው፦
ራእይ 17፥14 በጉ "የጌቶች ጌታ እና "የነገሥታት ንጉሥ" ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል።
ሉቃስ 1፥32 ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል።

ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ንግሥና ከሰጠው እርሱ "የነገሥታት ንጉሥ" የተባለው በአንጻራዊ ደረጃ እና በሥዩም ሢመት ነው። በባይብል "የነገሥታት ንጉሥ" የተባለው ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን አርጤክስስ እና ናቡከደነጾርም ጭምር ናቸው፦
ዕዝራ 7፥12 "ከ-"ነገሥታት ንጉሥ" ከአርጤክስስ ለሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ለዕዝራ ሙሉ ሰላም ይሁን።
ዳንኤል 2፥37 አንተ ንጉሥ ሆይ! የሰማይ አምላክ መንግሥትን፣ ኃይልን፣ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ "የነገሥታት ንጉሥ" አንተ ነህ።

ሰው ሰውን የሚገዛው መገዛዛት የግብር መገዛዛት ሲሆን አምላክ ሰውን የሚገዛበት መገዛዛት የባሕርይ መገዛዛት ነው። የኢየሱስ ጌታ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፦
ማቴዎስ 11፥25 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ! የሰማይና የምድር ጌታ።
የሐዋርያት ሥራ 17፥24 ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም።
የሐዋርያት ሥራ 2፥36 ኢየሱስን አምላክ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ። ἀσφαλῶς οὖν γινωσκέτω πᾶς οἶκος Ἰσραὴλ ὅτι καὶ Κύριον αὐτὸν καὶ Χριστὸν ἐποίησεν ὁ Θεός, τοῦτον τὸν Ἰησοῦν.
እዚህ አንቀጽ ላይ "አምላክ" ባለቤት ሲሆን "ኢየሱስ" ተሳቢ ነው፥ በባለቤት እና በተሳቢ መካከል "እንዳደረገው" የሚል ተሻጋሪ ግሥ አለ። ጌታ አድራጊው አንዱ አምላክ ሲሆን ጌታ ተደራጊው ኢየሱስ ነው፥ አምላክ ኢየሱስን ጌታ ካረደገው የኢየሱስ ጌትነት መነሾ እና ጅማሮ ያለው ነው። ጌታ ከመደረጉ በፊት በባዶነት ስለሚቀደም ጌትነቱ ሥልጣን እና ሹመት ያሳያል፥ አንዱ አምላክ ኢየሱስን የጌቶች ጌታ ካደረገው ዘንዳ የመሢሑ ጌትነት የማዕረግ ነው። "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י ማለት "ጌታዬ" ማለት ነው፥ መሢሑ በትንቢት መነጽር ያህዌህን "ጌታዬ" ብሎታል፦
ኢሳይያስ 61፥1 "የ-"ጌታዬ" የያህዌህ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ ያህዌህ ቀብቶኛልና። ר֛וּחַ אֲדֹנָ֥י יְהוִ֖ה עָלָ֑י יַ֡עַן מָשַׁח֩ יְהוָ֨ה אֹתִ֜י לְבַשֵּׂ֣ר עֲנָוִ֗ים

እዚህ አንቀጽ ላይ "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י ማለት "ጌታዬ" ማለት ከሆነ ኢየሱስ አምላኩን "ጌታዬ" ማለቱ በራሱ የሚገዛለት ጌታ እንዳለው አመላካች ነው። ኢየሱስ በትንቢት መነጽር የፈጠረው ጌታ እንዳለው ተናግሯል፦
ምሳሌ 8፥22 "ጌታ" በቀድሞ ተግባሩ "ፈጠረኝ"። κύριος ἔκτισέν με ἀρχὴν ὁδῶν αὐτοῦ εἰς ἔργα αὐτοῦ

በግሪክ ሰፕቱአጀንት እዚህ አንቀጽ ላይ "ፈጠረኝ" ለሚለው የገባው ቃል "ኤክቲሴን ሜ" ἔκτισέν με ሲሆን፣ በዕብራይስጥ ማሶሬት "ቃናኒ" קָ֭נָנִי ሲሆን፣ በግዕዝ ደግሞ "ፈጠረኒ" ነው፥ ቀደምት የቤተክርስቲያን አበው ምሳሌ 8፥22 ላይ "ፈጠረኝ" የሚለው ኢየሱስ እንደሆነ ያለምንም ልዩነት በወጥ ፍሰት አብራርተዋል።
ኢየሱስን የፈጠረ ጌታ ጌትነቱ የባሕርይ ሲሆን የዓለማቱ ጌታ ነው፥ በጌትነቱ ላይ ባርነት የሌለበት ይህ ጌታ ኢየሱስን "ባሪያዬ" ይለዋል፦
ኢሳይያስ 42፥1 እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። הֵ֤ן עַבְדִּי֙ אֶתְמָךְ־בֹּ֔ו בְּחִירִ֖י רָצְתָ֣ה נַפְשִׁ֑י נָתַ֤תִּי רוּחִי֙ עָלָ֔יו מִשְׁפָּ֖ט לַגֹּויִ֥ם יֹוצִֽיא׃

በጌትነቱ ላይ ባርነት ያለበት ኢየሱስ የባሕርይ ጌታ አለመሆኑን ይህ ጥቅስ በቂ አስረጅ ነበር። ማርያም እና ዮሴፍ ኢየሱስ በጌታው ፊት ሊያቆሙት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፦
ሉቃስ 2፥24 "በጌታ ፊት ሊያቆሙት"፥ በጌታም ሕግ፦ “ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች፡” እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት።

"በጌታ ፊት ሊያቆሙት" የሚለው ይሰመርበት! የተወሰደው ኢየሱስ እና ጌታው በማንነት ሆነ በምንነት ሁለት ለየቅል የሆኑ ሃልዎት ናቸው።
ኢየሱስ ከአሏህ የተሰጠው ተልእኮ "ጌታዬን እና ጌታችሁን አሏህን አምልኩ" የሚል ነበር፦
5፥117 በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል "ጌታዬን እና ጌታችሁን አሏህን አምልኩ" ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَا أَمَرْتَنِي بِهِ أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ رَبِّي وَرَبَّكُمْ

"የባሕርይ ጌታ" ማለት "በራሱ የተብቃቃ እና ጌትነቱ ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ጌታ" ማለት ነው፥ አሏህ የሁሉ ነገር ጌታ ሲሆን ጌትነቱ የባሕርይ ነው፦
6፥164 በላቸው «እርሱ አሏህ የሁሉ ነገር ጌታ ሲሆን ከአሏህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን? ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም፡፡ قُلْ أَغَيْرَ ٱللَّهِ أَبْغِى رَبًّۭا وَهُوَ رَبُّ كُلِّ شَىْءٍۢ ۚ وَلَا تَكْسِبُ كُلُّ نَفْسٍ إِلَّا عَلَيْهَا

አምላካችን አሏህ "ጌታ" የተባለበት ቃል "ረብ" رَّبّ ሲሆን አሏህ ብቻውን ፍጥረትን ፈጥሮ፣ ብቻውን ሙሐከማትን አውጥቶ፣ ብቻውን በፍርዱ ቀን ባወጣው ሙሐከማት የሚፈርድ ነው። እንግዲህ ኢየሱስ ጌታ ካለው፣ ለጌታው ባሪያ ከሆነ፣ ጌትነቱ በመደረግ ላይ የተመሠረተ መነሻ እና ጅማሮ ካለው እንግዲያውስ በጌትነቱ ባርነት የሌለበትን የባሕርይ ጌታ አሏህን በብቸኝነት አምልኩ! እንደ ኢየሱስ ለጌታችን ባሪያ መሆን ምንኛ መታደል ነው? ስለዚህ የኢየሱስን ጌታ እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። ጌታችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም