ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
59.4K subscribers
68 photos
70 videos
19 files
1.73K links
ዳዒ ወሒድ በኢሥላም እና በክርስትና መካከል ያለውን ልዩነት እና አንድነት በንጽጽር የሚያስቀምጥ ወንድም ነው። ለዚህም የቋንቋ፣ የሰዋስው፣ የዐውድ፣ የተዛማች እና የሥነ አመክንዮ ሙግት በማቅረብ የሚታወቅ ተሟጋች እና ጦማሪ ነው። ለሙግቱ ነጥብ በዋነኝነት የሚጠቀምባቸው ቋንቋ ዐማርኛ፣ ግዕዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ዐረቢኛ፣ ዕብራይስጥ እና ግሪክ ናቸው። መልካም የንባብ፣ የጥናት፣ የማነጻጸር ጊዜ ይሁንልዎ!
Download Telegram
የባሰው ደግሞ በክሌመንት ላይ፦ “እግዚአብሔር አብ ለወልድ እና ለመንፈስ ቅዱስ እንፍጠር” አላቸው ይለናል፦

1ኛ. ግዕዙ፦
ቀለሚንጦስ 1፥33 *ወይቤሎሙ እግዚአብሔር አብ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ንዑ ንግበር ሰብእ በአርአያነ ወበአምሳሊነ*።

2ኛ. አማርኛው፦
ቀለሚንጦስ 1፥33 *እግዚአብሔር አብ ለወልድ እና ለመንፈስ ቅዱስ በአርአያችንና በአምሳላችን ሰውን እንፍጠር አላቸው*።

ታዲያ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ናቸውን? ምክንያቱም ኩፋሌ ላይ “ፈጣሪያችን” ብለዋልና። እሺ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ “ፈጣሪ” ወይስ “ፈጣሪዎች” ? መልክአ ሥላሴ ላይ ሥላሴ “ፈጣሪዎች” ተብለዋል፦
መልክአ ሥላሴ ቁጥር 39
*”ሥሉስ ቅዱስ ሆይ! የአደምና የሔዋን “ፈጣሪዎቻቸው” እንደመሆናችሁ”*።

ሥላሴን “ፈጣሪዎች” ከተባሉ ሦስት ፈጣሪ መሆናቸው ነው። ይህንን የሥላሴ ውዝግብና ትርምስ የሚፈታው የዐለማቱ ጌታ አላህ ለመላእክት ምን ብሎ እንደነበር በሚናገርበት አንቀጽ ነው፦
38፥71 ጌታህ ለመላእክት *«እኔ ሰውን ከጭቃ እፈጥራለሁ»* ባለ ጊዜ አስታውስ፡፡ إِذْ قَالَ رَبُّكَ لِلْمَلَائِكَةِ إِنِّي خَالِقٌ بَشَرًا مِّن طِينٍ

ቁርኣን ከወረደበት ግብና አላማ፣ ፋይዳና ሚና አንዱ ከእነርሱ ጋር ያለውን መለኮታዊ እውነት ለማረጋገጥ እና ቀጥፈው የጨመሩትን ሐሰት ሊያርም ነው፤ ከእነርሱ ጋር ያለውን እውነትን ስለሚያረጋግጥ “ሙሰዲቃን” مُصَدِّقًا ማለትም “አረጋጋጭ” ሲባል፤ የሰዎች ንግግር የገቡበትን በማረሙ ደግሞ “ሙሃይሚን” مُهَيْمِنًا ማለትም “አራሚ” correcter” ወይም “ተቆጣጣሪ”supervisor” የሚል ስም አለው፦
5፥48 *ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭ እና በእርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በእውነት አወረድን*። وَأَنزَلْنَآ إِلَيْكَ ٱلْكِتَٰبَ بِٱلْحَقِّ مُصَدِّقًۭا لِّمَا بَيْنَ يَدَيْهِ مِنَ ٱلْكِتَٰبِ وَمُهَيْمِنًا عَلَيْهِ

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
የብረት ጥሩር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

34፥11 *"ሰፋፊዎችን "ጥሩሮች" ሥራ! በአሠራርዋም መጥን! መልካምንም ሥራ ሥሩ*፡፡ እኔ የምትሠሩትን ነገር ሁሉ ተመልካች ነኝና" አልነው፡፡ أَنِ اعْمَلْ سَابِغَاتٍ وَقَدِّرْ فِي السَّرْدِ ۖ وَاعْمَلُوا صَالِحًا ۖ إِنِّي بِمَا تَعْمَلُونَ بَصِيرٌ

የታሪክ ተመራማሪዎች ለታሪክ ምንጭ ሁለት መረጃዎች አሏቸው፥ አንደኛው ትውፊት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሥነ-ቁፋሮ ጥናት ነው። የታሪክ ተመራማሪዎች ያለፈውን ክስተት ሲፈጸም በቦታው ስላልነበሩ ከትውፊት እና ከሥነ-ቁፋሮ ግኝት በስተቀር ሙሉ ዕውቀት የላቸውም፥ አንድ ያለፈ ክስተት እነርሱ አላገኙትም ማለት ክስተቱ አልተከሰተም ማለት አይደለም። የክርስትናው ዐቃቤ እምነት አንቶንይ ሮጀርስ፦ "በዳዊት ዘመን የብረት ጥሩር ስለሌለ በቁርኣን በዳዊት ጊዜ ስለ ብረት ጥሩር የተገለጸው ገለጻ ስህተት ነው" ይለናል፦
34፥11 *"ሰፋፊዎችን "ጥሩሮች" ሥራ! በአሠራርዋም መጥን! መልካምንም ሥራ ሥሩ*፡፡ እኔ የምትሠሩትን ነገር ሁሉ ተመልካች ነኝና" አልነው፡፡ أَنِ اعْمَلْ سَابِغَاتٍ وَقَدِّرْ فِي السَّرْدِ ۖ وَاعْمَلُوا صَالِحًا ۖ إِنِّي بِمَا تَعْمَلُونَ بَصِيرٌ

"ሣቢጋት" سَٰبِغَٰت የሚለው ቃል "አሥበገ" أَسْبَغَ ማለትም "አገራ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "የተገራ" ማለት ነው። አላህ ለዳውድ ሐዲድን ማግራቱን የሚያሳይ ነው፦
34፥10 ለዳውድም ከእኛ የኾነን ችሮታ በእርግጥ ሰጠነው፡፡ «ተራራዎች ሆይ! ከእርሱ ጋር ውዳሴን መላልሱ» አልን። በራሪዎችንም ገራንለት፡፡ *ብረትንም ለእርሱ አለዘብንለት"*፡፡ وَلَقَدْ آتَيْنَا دَاوُودَ مِنَّا فَضْلًا ۖ يَا جِبَالُ أَوِّبِي مَعَهُ وَالطَّيْرَ ۖ وَأَلَنَّا لَهُ الْحَدِيدَ

የታሪክ ተመራማሪዎች የብረት ጥሩር በሦስተኛ ክፍለ ዘመን አገኙ ማለት ከዚያ በፊት ላለመኖሩ ማስረጃ መሆን አይችልም፥ ይህ ሙግት ሥነ-አመክንዮን ታሳቢና ዋቢ ያላደረገ ስሑት ሙግት ነው። ለምሳሌ በዳዊት ዘመን የነበሩ ሰዎች ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት አሥር ሺህ “ዳሪክ” እንደሰጡ የዜና መዋዕል ጸሐፊ ይነግረናል፦
1ኛ ዜና 29፥7 ለ*"እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት *አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና አሥር ሺህ “ዳሪክ”፥ አሥር ሺህም መክሊት ብር፥ አሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ*።

ዳሪክ ደግሞ መገበያያነቱ የተጀመረው በ 521-486 ቅድመ-ልደት በፐርሺያን ንጉሥ በዳሪዮስ ዘመነ-መንግሥት እንደሆነ የታሪክ ተመራማሪዎች ያትታሉ። ታዲያ በዳዊትና በዳሪዮስ መካከል የ 400 ዓመት ልዩነት ካለ፥ ታሪክ ስላላገኘው ትርክቱ ትክክል አይደለም ብሎ በአራት ነጥብ መደምደም ይቻላልን?
"ጥሩር" በዕብራይስጥ "ተህራ" תַחְרָ֛א ወይም "ሲሪዩን" שִׁרְיוֹן ነው፥ "ጥሩር" ከዳዊት በፊት በሙሴ ዘመን እና በዳዊትም ጊዜ ነበር፦
ዘጸአት 28፥32 *ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት እንዳይቀደድም እንደ "ጥሩር" תַחְרָ֛א የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት።
ዘጸአት 39፥23 በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም እንደ "ጥሩር" שִׁרְיוֹן תַחְרָ֛א የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ነበረ*።
1ኛ ሳሙኤል 17፥5 *በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፥ "ጥሩርም" שִׁרְיוֹן ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስ ነበረ"*።
1ኛ ሳሙኤል 17፥38 *"ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው"*።

የታሪክ ተመራማሪዎች የብረት ጥሩር በሦስተኛ ክፍለ ዘመን ስላገኙ ባይብል "ጥሩር ከዳዊት በፊት በሙሴ ዘመን እና በዳዊትም ጊዜ ነበር" የሚለው ገለጻ ስህተት ነው ብሎ ተብሎ መደምደም ይቻላል። ግን ቅሉና ጥቅሉ "አንድ ያለፈ ክስተት የታሪክ ተመራማሪዎች አላገኙትም ማለት ክስተቱ አልተከሰተም ማለት አይደለም" የሚል ነው፥ የቁርኣኑንን ትርክትም በዚህ ልክና መልክ ተረዱት።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ርኅሩኅ እና አዛኝ ነቢይ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

9፥128 *"ከራሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን ላይ ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ"*፡፡ لَقَدْ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مِّنْ أَنفُسِكُمْ عَزِيزٌ عَلَيْهِ مَا عَنِتُّمْ حَرِيصٌ عَلَيْكُم بِالْمُؤْمِنِينَ رَءُوفٌ رَّحِيمٌ

አምላካችን አላህ በእርግጥ ርኅሩኅ አዛኝ ነው፥ እርሱ ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነው፦
16፥47 ወይም ቀስ በቀስ በማጉደል ላይ የሚይዛቸው መኾኑን አይፈሩምን? *"ጌታችሁም በእርግጥ ርኅሩኅ አዛኝ ነው"*፡፡ أَوْ يَأْخُذَهُمْ عَلَىٰ تَخَوُّفٍ فَإِنَّ رَبَّكُمْ لَرَءُوفٌ رَّحِيمٌ
21፥83 አዩብንም ጌታውን «እኔ መከራ አገኘኝ፥ *"አንተም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነህ»* ሲል በተጣራ ጊዜ አስታውስ፡፡ وَأَيُّوبَ إِذْ نَادَىٰ رَبَّهُ أَنِّي مَسَّنِيَ الضُّرُّ وَأَنتَ أَرْحَمُ الرَّاحِمِينَ

"ረሒም" رَّحِيم በነጠላ "አዛኝ" ማለት ሲሆን "ራሒሚን" رَّاحِمِين ደግሞ በብዜት "አዛኞች" ማለት ነው። ከአዛኞች መካከል አንዱ ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ናቸው፥ እርሳቸው በምእምናን ላይ ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ ናቸው፦
9፥128 *"ከራሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን ላይ ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ"*፡፡ لَقَدْ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مِّنْ أَنفُسِكُمْ عَزِيزٌ عَلَيْهِ مَا عَنِتُّمْ حَرِيصٌ عَلَيْكُم بِالْمُؤْمِنِينَ رَءُوفٌ رَّحِيمٌ
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 43, ሐዲስ 164
ሙሐመድ ኢብኑ ጁበይር ኢብኑ ሙጥዒም ከአባቱ ሰምቶ እንደተረከው፦ "የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *“እኔ ሙሐመድ ነኝ፣ እኔ አሕመድ ነኝ፣ እኔ አላህ በእኔ ሰበብ ክህደትን የሚደመስስብኝ አል-ማሒ ነኝ፣ እኔ ያ ሰዎች ከእርሱ ኋላ ተከትለውት የሚቀሰቀሱበት አል-ሓሺር ነኝ፣ ከዚህ በኃላ ነብይ የለምና እኔ ዓቂብ(መጨረሻ) ነኝ። በእርግጥም አላህ ርኅሩኅ አዛኝ ብሎ የጠራው ነኝ"*። عَنْ مُحَمَّدِ بْنِ جُبَيْرِ بْنِ مُطْعِمٍ، عَنْ أَبِيهِ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ "‏ إِنَّ لِي أَسْمَاءً أَنَا مُحَمَّدٌ وَأَنَا أَحْمَدُ وَأَنَا الْمَاحِي الَّذِي يَمْحُو اللَّهُ بِيَ الْكُفْرَ وَأَنَا الْحَاشِرُ الَّذِي يُحْشَرُ النَّاسُ عَلَى قَدَمَىَّ وَأَنَا الْعَاقِبُ الَّذِي لَيْسَ بَعْدَهُ أَحَدٌ ‏"‏ ‏.‏ وَقَدْ سَمَّاهُ اللَّهُ رَءُوفًا رَحِيمًا

እኛ ክርስቲያኖችን፦ "ኢየሱስ ፍጡር ሆኖ ሳለ ለምን ታመልኩታላችሁ" ብለን ስንጠይቅ፥ እከክልኝ ልከክልህ በሚል ስሜት፦ "ጌታችሁም በእርግጥ ርኅሩኅ አዛኝ ነው፥ ያም ርኅሩኅ አዛኝ በምእምናን ላይ ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ ነው። ስለዚህ ነቢያችሁ ጌታችሁ ነው" ብለው አረፉት። ይህ ቁርኣንን አገላብጦ ካለማንበብና ካለመረዳት የሚመጣ የተውረገረገ፣ የተንሸዋረረ፣ የተሳከረ፣ የደፈረሰ መረዳት ነው። አምላካችን አላህ የሚመስለው ምንም ነገር የለም፥ እርሱ ሰሚ ተመልካች ነው፦
42፥11 የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ *"እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው"*፡፡ لَيْسَ كَمِثْلِهِۦ شَىْءٌۭ ۖ وَهُوَ ٱلسَّمِيعُ ٱلْبَصِيرُ

ሰውም አላህ በምንም አይመስልም፥ ግን ሰውም ሰሚ ተመልካች ነው፦
76፥2 እኛ ሰውን በሕግ ግዳጅ የምንፈትነው ስንኾን ቅልቅሎች ከኾኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነው፡፡ *ሰሚ ተመልካችም አደረግነው*፡፡ إِنَّا خَلَقْنَا الْإِنسَانَ مِن نُّطْفَةٍ أَمْشَاجٍ نَّبْتَلِيهِ فَجَعَلْنَاهُ سَمِيعًا بَصِيرًا

አላህ የሚመስለው ምንም ነገር ስለሌለ አላህ ሰሚ እና ተመልካች የተባለው ሰው ሰሚ እና ተመልካች በተባለበት ስሌትና ቀመር እንዳልሆነ እሙንና ቅቡል ነው። አምላካችን አላህ የሚመስለው ምንም ነገር የለም፥ እርሱ አመስጋኝ ታጋሽ ነው፦
64፥17 ለአላህ መልካም ብድርን ብታበድሩ ምንዳውን ለእናንተ ይደራርበዋል፥ ለእናንተም ይምራል። *"አላህም አመስጋኝ ታጋሽ ነው"*፡፡ إِن تُقْرِضُوا اللَّهَ قَرْضًا حَسَنًا يُضَاعِفْهُ لَكُمْ وَيَغْفِرْ لَكُمْ ۚ وَاللَّهُ شَكُورٌ حَلِيمٌ

ሰውም አላህ በምንም አይመስልም፥ ግን ሰውም ታጋሽና አመስጋኝ ተብሏል፦
42፥33 ቢሻ ነፋሱን የረጋ ያደርገዋል፡፡ በባሕሩም ጀርባ ላይ ረጊዎች ይኾናሉ፡፡ *"በዚህ ውሰጥ በጣም ታጋሽና አመስጋኝ ለኾነ ሁሉ በእርግጥ ምልክቶች አሉ"*፡፡ إِن يَشَأْ يُسْكِنِ الرِّيحَ فَيَظْلَلْنَ رَوَاكِدَ عَلَىٰ ظَهْرِهِ ۚ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّكُلِّ صَبَّارٍ شَكُورٍ

አላህ የሚመስለው ምንም ነገር ስለሌለ አላህ አመስጋኝ እና ታጋሽ የተባለው ሰው አመስጋኝ እና ታጋሽ በተባለበት ስሌትና ቀመር እንዳልሆነ እሙንና ቅቡል ነው። አምላካችን አላህ የሚመስለው ምንም ነገር የለም፥ እርሱ ርኅሩኅ ታጋሽ ነው፦
2፥225 *"አላህም በጣም ርኅሩኅ ታጋሽ ነው"*፡፡ وَاللَّهُ غَفُورٌ حَلِيمٌ

ሰውም አላህ በምንም አይመስልም፥ ለምሳሌ ኢብራሂም ርኅሩኅ ታጋሽ ተብሏል፦
9፥114 *"ኢብራሂም በእርግጥ በጣም ርኅሩኅ ታጋሽ ነውና"*፡፡ إِنَّ إِبْرَاهِيمَ لَأَوَّاهٌ حَلِيمٌ
አላህ የሚመስለው ምንም ነገር ስለሌለ አላህ ርኅሩኅ እና ታጋሽ የተባለው ኢብራሂም ርኅሩኅ እና ታጋሽ በተባለበት ስሌትና ቀመር እንዳልሆነ እሙንና ቅቡል ነው። እስቲ ለናሙና ያክል ከባይብል በንጽጽር እንይ! እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው። ሰይጣን ፈታኝ ነው፦
ዘፍጥረት 22፥1 ከእነዚህም ነገሮች በኋላ *”እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው”*፥
ማቴዎስ 4፥3 *”ፈታኝም”* ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።

እግዚአብሔር ፈታኝ ሰይጣን ነውን? ማነው ፈታኝ? እግዚአብሔር ወይስ ሰይጣን? እግዚአብሔር አጥፊ ተብሏል። ሰይጣንም አጥፊ ተብሏል፦
ዘጸአት 12፥12 እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ *”በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ”*።
ዕብራውያን 11፥28 *”አጥፊው”* የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ።
ራእይ 9፥11 *”በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል”*።

በዕብራይስጥ “አብዶን” ማለት እና በግሪክ “አጶልዮን” ማለት ትርጉሙ “አጥፊ” ማለት ነው። እግዚአብሔር የጥልቁ መልአክ ሰይጣን ነውን? ማነው አጥፊ? እግዚአብሔር ወይስ ሰይጣን? እንዲህ ማነጻጸር ይቻላል። "እረ ወሒድ ምን ነካህ? እግዚአብሔር ፈታኝና አጥፊ የተባለው ሰይጧን ፈታኝና አጥፊ በተባለበት ሒሳብ አይደለም" ካላችሁ እንግዲያውስ በሰፈሩት ቁና መሰፈር ይሉካል እንደዚህ ነው።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
አብርሃም ቤት የገቡት ሦስት ሰዎች መላእክት እንጂ ሥላሴ አለመሆናቸው ድርሳነ ሚካኤል እንዲህ ይናገራል፦
ድርሳነ ሚካኤል ዘሚያዝያ ቁጥር 11
ግዕዙ፦
*ወካዕበ መጽኡ መላእክት ወበጽሑ ኀበ አብርሃም ወነገርዎ ከመ ይትወለድ ይስሐቅ*።
አማርኛው፦
*ዳግመኛ መላእክት ወደ አብርሃም ዘንድ መጥተው ይስሐቅን እንደሚወልድ ነገሩት*።
ሦስቱ መላእክት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

29፥31 *መልእክተኞቻችንም ኢብራሂምን በብስራት በመጡት ጊዜ «እኛ የዚህችን ከተማ ሰዎች አጥፊዎች ነን፡፡ ሰዎቿ በዳዮች ነበሩና» አሉት*፡፡ وَلَمَّا جَاءَتْ رُسُلُنَا إِبْرَاهِيمَ بِالْبُشْرَىٰ قَالُوا إِنَّا مُهْلِكُو أَهْلِ هَـٰذِهِ الْقَرْيَةِ ۖ إِنَّ أَهْلَهَا كَانُوا ظَالِمِينَ

ኦሪት ዘፍጥረት ላይ አብርሃም ቤት ሦስት ሰዎች በእንግድነት እንደተስተናገዱ ይናገራል፤ ዐበይት ክርስቲያኖች፦ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና አንግሊካን እነዚህ ሦስት ሰዎች ሥላሴ ናቸው ይላሉ፤ እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ 220 ድህረ-ልደት”AD” ቱርቱሊያም ይህንን አንቀጽ ይዞ የሥላሴን ቶኦሎጅይ ቴኦሌጃይዝ ያደረገው፤ በአገራችንም በየወሩ በሰባተኛው ቀን የአብርሃሙ ሦላሴ እየተባለ ይዘከራል፤ እውን ይህ አንቀጽ ለሥላሴ ተስተምህሮት መደላለል ይሆናልን? እስቲ ጥንልልና ጥንፍፍ አርገን እናስተንትነው፦
ዘፍጥረት 18፥1-2 በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ *እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት*። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ *ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ*፤

እዚህ ጥቅስ ላይ ስለ ሥላሴ ምንም ሽታው እንኳን የለም። እነዚህ ሦስት ሰዎች አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ናቸው የሚል ዐውዱ ላይ ምንም አናገኝም። ይህንን አንቀጽ ለሥላሴ የተጠቀመ ነብይም ሆነ ሃዋርያ የለም፤ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው ታዲያ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለዐውደ ንባቡ ቦታውን እንልቀቅ፦
ዘፍጥረት 18፥16 *ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ* አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ።
ዘፍጥረት 18፥22 *ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ* አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር።

እነዚህ ሰዎች ከአብርሃም ቤት ወደ ሰዶም አቀኑ፣ ወደ ሰዶምም ሄዱ፤ ከዚያስ? በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፦
ዘፍጥረት 19፥1 *ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ*፤

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ሲነጋገር የነበረው በሦስት ሰዎች ነው፤ ሁለቱ ሰዎች ሲሄዱ ግን “አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር” ይላል፤ እግዚአብሔር በአንዱ ሰው ሲነጋገር ሁለቱ ሰዎች ሎጥ ቤት ገብተዋል፦
ዘፍጥረት 19፥10 *ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት*።
ዘፍጥረት 19፥12 *ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት*።
ዘፍጥረት 19፥13 *እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል*።

“ሁለቱ ሰዎች” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት፤ ምን ትፈልጋለህ? ከአብርሃም ቤት ወጥተው ወደ ሎጥ ቤት የገቡት ሰዎች በቁጥር ሁለት መሆናቸውን እና ሁለት መላእክት መሆናቸውን ተገልጻል፤ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ በአንድ ሰው ይናገራል፤ ይህም ሰው መልአክ ተብሏል፤ ለምሳሌ ያዕቆብ ሲታገለው የነበረው መልአክ ሰው ተብሏል፦
ዘፍጥረት 32፥28 አለውም፦ ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ *ከእግዚአብሔር እና ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና*።
ሆሴዕ 12፥3-4 በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፥ በጕልማስነቱም ጊዜ *ከአምላክ ጋር ታገለ፤ ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ*፤ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም *ከእኛ ጋር ተነጋገረ*።

“ከእኛ ጋር ተነጋገረ” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት፤ እግዚአብሔር እዚህ አንቀጽ ላይ፦ “እኛ” የሚለው መልአኩን ጨምሮ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይለዋል፤ ምነው ገብርኤል ሰው ተብሎ የለ እንዴ? መላእክት በሰው ቅርጽ ስለሚመጡ ሰው ይባላሉ፦
ዳንኤል 9፥21 ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው *የነበረው ሰው ገብርኤል* እነሆ እየበረረ መጣ፤ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ።

እግዚአብሔር ግን ሰው አይደለም፤ አይበላም አይጠጣምም፦
ሆሴዕ 11፥9 *እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና*፥
መዝሙር 50፥12 *ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን?*

ፈጣሪ፦ እበላለሁን? እጠጣለሁን? ሲል በምጸታዊ አነጋገር አልበላም አልጠጣም እያለ ነው፤ አንዳንድ ቂሎች፦ “አብርሃም ቤት የገቡት ሰዎች ምግብ በልተዋል፤ መላእክት እንዴት ይበላሉ? ብለው ይጠይቃሉ፤ የቱ ይቀላል መጋቢ ፈጣሪ መብላቱ ወይስ ፍጡር የሆኑት መላእክት መብላታቸው? አዎ መላእክቱ በልተዋል ይለናል፦
ዘፍጥረት 18፥8 እርጎና ወተትም ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ *እነርሱም በሉ*።
ዘፍጥረት 19፥3 እጅግም ዘበዘባቸው ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ *እነርሱም በሉ*።

ሎጥ ቤት የበሉት መላእክት ሥላሴ ናቸው ብላችሁ እንዳታርፉት፤ የዕብራውያን ጸሐፊ፦ “አንዳንዶች በእንግድነት መላእክትን ተቀብለዋል” በማለት አብርሃምን እና ሎጥን ያስታውሰናል፦
ዕብራውያን 13፥2 *እንግዶችን መቀበል አትርሱ*፤ በዚህ አንዳንዶች *ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና*።
ሎጥ ቤት የበሉት መላእክት ሥላሴ ናቸው ብላችሁ እንዳታርፉት፤ የዕብራውያን ጸሐፊ፦ “አንዳንዶች በእንግድነት መላእክትን ተቀብለዋል” በማለት አብርሃምን እና ሎጥን   ያስታውሰናል፦
ዕብራውያን 13፥2 *እንግዶችን መቀበል አትርሱ*፤ በዚህ አንዳንዶች *ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና*።

ከሎጥ ሌላ በእንግድነት እግር አጥቦና ጋብዞ እንግዳ የተቀበለ አብርሃም ነው። ደግሞም ድርሳነ ሚካኤል አብርሃም ቤት ገብተው አብርሃምን ያበሰሩት መላእክት እንደሆኑ ይናገራል፦
ድርሳነ ሚካኤል ዘሚያዝያ ቁጥር 11
ግዕዙ፦
*ወካዕበ መጽኡ መላእክት ወበጽሑ ኀበ አብርሃም ወነገርዎ ከመ ይትወለድ ይስሐቅ*።
አማርኛው፦
*ዳግመኛ መላእክት ወደ አብርሃም ዘንድ መጥተው ይስሐቅን እንደሚወልድ ነገሩት*።

አምላካችን አላህ ወደ ኢብራሂም ቤት በብስራት የመጡት መልእክተኞቹ እንደሆኑና እነዚህም መላእክትም ወደ ሉጥ ቤት እንደገቡ ይናገራል፦
29፥31 *መልክተኞቻችንም ኢብራሂምን በብስራት በመጡት ጊዜ «እኛ የዚህችን ከተማ ሰዎች አጥፊዎች ነን፡፡ ሰዎቿ በዳዮች ነበሩና» አሉት*፡፡ وَلَمَّا جَاءَتْ رُسُلُنَا إِبْرَاهِيمَ بِالْبُشْرَىٰ قَالُوا إِنَّا مُهْلِكُو أَهْلِ هَـٰذِهِ الْقَرْيَةِ ۖ إِنَّ أَهْلَهَا كَانُوا ظَالِمِينَ
11፥77 *መልእክተኞቻችንም ሉጥን በመጡት ጊዜ በእነርሱ ምክንያት አዘነ፡፡ ልቡም በነሱ ተጨነቀ፡፡ «ይህ ብርቱ ቀን ነውም» አለ*፡፡ وَلَمَّا جَاءَتْ رُسُلُنَا لُوطًا سِيءَ بِهِمْ وَضَاقَ بِهِمْ ذَرْعًا وَقَالَ هَـٰذَا يَوْمٌ عَصِيبٌ

እነዚህ መላእክት የቁጥራቸው መጠን ቁርኣን ላይ በእርግጥ አልተገለጸም፤ እንዲሁ ቁርኣን እነዚህ መላእክት በሉ አይልም፤ ኢብራሂም የተጠበሰን የወይፈን ስጋ ሲያመጣላቸው እጆቻቸውም ወደ ምግቡ የማይደርሱ መኾነቸውን ባየ ጊዜ ሸሻቸው፤ ምግብ የማይበሉ መሆናቸውን ሲረዳ ከእነርሱም ፍርሃት ተሰማው፦
11፥69 *መልእክተኞቻችንም ኢብራሂምን በልጅ ብስራት በእርግጥ መጡት፡፡ ሰላም አሉት፡፡ ሰላም አላቸው፡፡ ጥቂትም ሳይቆይ ወዲያውኑ የተጠበሰን የወይፈን ስጋ አመጣ*፡፡ وَلَقَدْ جَاءَتْ رُسُلُنَا إِبْرَاهِيمَ بِالْبُشْرَىٰ قَالُوا سَلَامًا ۖ قَالَ سَلَامٌ ۖ فَمَا لَبِثَ أَن جَاءَ بِعِجْلٍ حَنِيذٍ
11፥70 *እጆቻቸውም ወደ እርሱ የማይደርሱ መኾነቸውን ባየ ጊዜ ሸሻቸው፡፡ ከእነርሱም ፍርሃት ተሰማው፡፡ «አትፍራ እኛ ወደ ሉጥ ሕዝቦች ተልከናልና» አሉት*፡፡ فَلَمَّا رَأَىٰ أَيْدِيَهُمْ لَا تَصِلُ إِلَيْهِ نَكِرَهُمْ وَأَوْجَسَ مِنْهُمْ خِيفَةً ۚ قَالُوا لَا تَخَفْ إِنَّا أُرْسِلْنَا إِلَىٰ قَوْمِ لُوطٍ

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
እንፍጠር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

6፥102 *"ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፥ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ ነገርን ሁሉ ፈጣሪ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው"*፡፡ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ ۖ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ ۖ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ فَاعْبُدُوهُ ۚ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ

ከአንድ አይሁዳዊ ምሁር ጋር እየተጨዋወትን ቀበል አርጌ፦ "ኤሎሂም እነማንን ነው እንፍጠር ያለው? ብዬ ጠየኩት፥ እርሱ፦ "በዚህ አንቀጽ ላይ በአይሁድ ጥንታዊ ምሁራን እና ዘመናዊ ምሁራን ዘንድ የተለያየ መልስ ተሰቶበታል" አለኝ። ከተሰጡት መልሶች መካከል፦
1ኛ. ኤሎሂም ከመላእክት ጋር እየተነጋገረ ነው፣
2ኛ. ከምድር ጋር እየተነጋገረ ነው፣
3ኛ. እራሱ ለግነት የብዜት ግስ እየተጠቀመ ነው፣
4ኛ. እራሱ ከራሱ ባሕርያት ጋር በዜቢያዊ አነጋገር እየተናገረ ነው" የሚል ነው፦
ዘፍጥረት 1፥26 ኤሎሂምም አለ፦ *"ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር"*።

አራተኛው ሰምቼ የማላውቀው ስለሆነ ትኩረቴ ሳበው። አንዱ አምላክ ብቻውን ሁሉን ነገር ፈጥሯል፥ ሰውንም የፈጠረ አንድ አምላክ ብቻ ነው፦
ሚልክያስ 2፥10 ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? *"አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን?"*

አንዱ አምላክ ያህዌህ ኤሎሂም ሰውን ከምድር አፈር በእጆቹ ፈጠረው፦
ዘፍጥረት 2፥7 ያህዌህ ኤሎሂም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው"*።
ኢዮብ 33፥6 *"እኔ ደግሞ ከጭቃ የተፈጠርሁ ነኝ"*።
መዝሙር 119፥73 *”እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም”*።

ኤሎሂም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፥ ኤሎሂም እንፍጠር ያለው መፍጠር ለሚችሉ ለእጆቹ ነው። ዳዊት፦ "እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም" ሲል ሰውን ያበጃጁት እጆቹ ከሆኑ፥ ኤሎሂም እጆቹ የራሱ ባሕርያት እንጂ ከኤሎሂም ውጪ ያሉ አካላት አይደለም። ታዲያ አንድ ማንነት ከራሱ ባሕርያት ጋር እንዴት ይነጋገራል? ከተባለ ዳዊት ለራሱ ነፍስ እና አጥንቶች፦ "ነፍሴ ሆይ፥ ያህዌህን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ የተቀደሰ ስሙን ባርኩ" ብሏል፦
መዝሙር 103፥1 *"ነፍሴ ሆይ፥ ያህዌህን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን"*።

ዳዊት በሁለተኛ መደብ በትእዛዛዊ ግስ የራሱን ነፍስ እና አጥንቶች "ባርኩ" ካለ፥ የራሱን ነፍስ ነፍሴ ሆይ! ባርኪ፣ አመስግኚ፣ ታመኚ፣ አትርሺ፣ ተመለሺ ካለ ኤሎሂም ሰውን የሚሠሩትንና የሚያበጁትን የራሱን እጆች "እንፍጠር" ቢል ምን ይደንቃል? ፈጣሪ ብቻውን ሰማያትን እና ምድርን እንደፈጠረ እሙን እና ቅቡል ነው፦
ኢሳይያስ 44፥24 *"ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ ያህዌህ እኔ ነኝ ከእኔ ጋር ማን ነበረ”*?

ከእኔ ጋር "ምን" ነበረ? ሳይሆን "ከእኔ ጋር "ማን" ነበረ? ነው ያለው። ከዚህ ከአንድ እኔነት ጋር አብረው የፈጠሩ ማንነቶች እንደሌሉ ቁልጭ እና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህ ሆኖ ሳለ ሰማያት እና ምድርን የፈጠሩ አሉ፥ እነርሱም እጁ፣ ቀኙ፣ ጣቶቹ ወዘተ ናቸው፦
ኢሳይያስ 48:13 *”እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች”*።
መዝሙር 8፥3 *”የጣቶችህን ሥራ” ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ"*።

እነዚህን ባሕርያት ሸንሽነን ማንነት ሰጥተን ከሦስቱ ሥላሴ በላይ ስንት አካላት ልናረጋቸው ነው? ያህዌህ በጥበቡ፣ በማስተዋሉ፣ በኃይሉ ሰማያትን እና ምድርን ፈጥሯል፦
ምሳሌ 3፥19 *"ያህዌህ በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና”*።
ኤርምያስ 10፥12 *"ምድርን ”በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ” እርሱ ነው"*።

ጥበቡ፣ ማስተዋሉ፣ ኃይሉ የራሱ ባሕርያት እንጂ የሚያማክሩት አካላት በፍጹም አይደሉም። እርሱ ራሱ እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንጂ ከራሱ ውጪ የሆኑ አካላትን እንፍጠር እያለ እየተመካከረ የሚሠራ በፍጹም አይደለም፦
ኤፌሶን 1፥11 *"እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ"*።

ከላይ ያለው አራተኛው እይታ ከሥነ-አመክንዮ አንጻር ድንቅ እይታ ነው። በቁርኣን ከሄድን ነገርን ሁሉ የፈጠረ ፈጣሪ ጌታችን አላህ ነው፥ ነገርን ሁሉ ብቻውን ፈጥሯል። ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፥ እርሱን ብቻ በብቸኝነት እናመልካለን፦
6፥102 *"ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፥ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ ነገርን ሁሉ ፈጣሪ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው"*፡፡ ذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ ۖ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ ۖ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ فَاعْبُدُوهُ ۚ وَهُوَ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ምድር

ገቢር አንድ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፦ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

65፥12 *"አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው፡፡ ከምድርም መሰላቸውን ፈጥሮአል"*። اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ وَمِنَ الْأَرْضِ مِثْلَهُنَّ

"አርድ”أَرْض ማለት "ምድር" ማለት ሲሆን አምላካችን አላህ ምድርንም መፍጠሩ ከአስደናቂ ታምራቶቹ ነው፥ በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ተዓምራቶች አሉበት፦
30፥22 *"ሰማያትን እና "ምድርንም" መፍጠሩ፣ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት፣ ከአስደናቂ ታምራቶቹ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለዐዋቂዎች ተዓምራቶች አሉበት*፡፡ وَمِنْ آيَاتِهِ خَلْقُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَاخْتِلَافُ أَلْسِنَتِكُمْ وَأَلْوَانِكُمْ ۚ إِنَّ فِي ذَٰلِكَ لَآيَاتٍ لِّلْعَالِمِينَ

"አርድ"أَرْض የሚለው ቃል "ምድርን" "መሬትን" "አህጉርን" "አገርን" ለማመልከት ይመጣል። ለምሳሌ አላህ ዐረብ አገርን "አርድ"أَرْض ይለዋል፦
17፥76 *"ከምድሪቱም ያወጡህ ዘንድ ሊያሸብሩህ በእርግጥ ተቃረቡ"*፡፡ وَإِن كَادُوا لَيَسْتَفِزُّونَكَ مِنَ الْأَرْضِ لِيُخْرِجُوكَ مِنْهَا ۖ
8፥30 እነዚያም የካዱት ሊያስሩህ ወይም ሊገድሉህ ወይም "ከመካ ሊያወጡህ" በአንተ ላይ በመከሩብህ ጊዜ አስታውስ*፡፡ وَإِذْ يَمْكُرُ بِكَ الَّذِينَ كَفَرُوا لِيُثْبِتُوكَ أَوْ يَقْتُلُوكَ أَوْ يُخْرِجُوكَ

በተመሳሳይም የሻም አገርን "አርድ"أَرْض ይለዋል፦
21፥81 *"ለሱለይማንም ነፋስን በኀይል የምትነፍስ በትዕዛዙ ወደዚያች በእርሷ ውስጥ በረከትን ወደ አደረግንባት "ምድር" የምትፈስ ስትኾን ገራንለት"*፡፡ وَلِسُلَيْمَانَ الرِّيحَ عَاصِفَةً تَجْرِي بِأَمْرِهِ إِلَى الْأَرْضِ الَّتِي بَارَكْنَا فِيهَا
34፥18 *"በእነርሱ እና በዚያች በውስጧ በረከትን ባደረግንባት "አገር" መካከልም ቅጥልጥል ከተሞችን አደረግን፡፡ وَجَعَلْنَا بَيْنَهُمْ وَبَيْنَ الْقُرَى الَّتِي بَارَكْنَا فِيهَا قُرًى ظَاهِرَةً وَقَدَّرْنَا فِيهَا السَّيْرَ

"የሞተችው አገር" የሚለው "የሞተችው ምድር" በሚለው መምጣቱ በራሱ "አርድ"أَرْض የሚለው ቃል አንድ "አገርን" ለማመልከት እንደሚመጣ አመላካች ነው፦
43፥11 ያም ከሰማያ ውሃን በልክ ያወረደላችሁ ነው፡፡ *"በእርሱም የሞተችውን አገር ሕያው አደረግን"*፡፡ እንደዚሁ ትውወጣላችሁ፡፡ وَالَّذِي نَزَّلَ مِنَ السَّمَاءِ مَاءً بِقَدَرٍ فَأَنشَرْنَا بِهِ بَلْدَةً مَّيْتًا ۚ كَذَٰلِكَ تُخْرَجُونَ
36፥33 *"የሞተችውም ምድር ለእነርሱ ምልክት ናት! ሕያው አደረግናት"*፡፡ ከእርሷም ፍሬን አወጣን፥ ከእርሱም ይበላሉ፡፡ وَآيَةٌ لَّهُمُ الْأَرْضُ الْمَيْتَةُ أَحْيَيْنَاهَا وَأَخْرَجْنَا مِنْهَا حَبًّا فَمِنْهُ يَأْكُلُونَ

"አርድ"أَرْض የሚለው ቃል የወከለውን አሳብ እዚህ ድረስ ከተግባባን አላህ ሰባትን ሰማያት እና ከምድርም መሰላቸውን ፈጥሮአል፥ የሰባት ሰማያት ቁጥር መሰላቸው ሰባት ከምድር ላይ ያሉ ሰባት የተዘረጉ ምድሮች ናቸው፦
65፥12 *"አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው፡፡ ከምድርም መሰላቸውን ፈጥሮአል"*። اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ وَمِنَ الْأَرْضِ مِثْلَهُنَّ
ተፍሢሩል ኢብኑ ዐባሥ 65፥12 *"አላህ ያ ሰባትን ሰማያት የፈጠረ ነው" ማለት አንዱ ሰማይ በሌላው ሰማይ ልክ እንደ ጉልላልት ነው፥ "ከምድርም መሰላቸውን ፈጥሮአል" ማለት ሰባት ንጣፍ ናቸው"*። { ٱللَّهُ ٱلَّذِي خَلَقَ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ } بعضها فوق بعض مثل القبة { وَمِنَ ٱلأَرْضِ مِثْلَهُنَّ } سبعاً ولكنها منبسطة

"ሠማዋት" سَمَاوَات በብዜት "ሰማያት" ተብሎ ሲቀመጥ "አርድ"أَرْض ግን በነጠላ "ምድር" ተብሎ ተቀምጧል። ምድር ላይ ሰባት ንጣፎች ሰባቱ የመሬት ክፍሎች ናቸው፥ ይህ አንደኛው እይታ ነው። "በለድ" بَلَد በነጠላ "አገር" ማለት ሲሆን "አቃሊም" أَقالِيم ደግሞ በብዜት "አህጉር" ማለት ነው። ከምድር በውቂያኖስ የተከፋፈሉ ለሰዎች መኖሪያ ሰባት የተዘረጉ አህጉራት አሉ፥ እነርሱም፦
1. ኤሲያ 44,579,000 km²
2. አፍሪካ 30,370,000 km²
3. ሰሜን አሜሪካ 24,709,000 km²
4. ደቡብ አሜሪካ 17,840,000 km²
5. አንታርክቲካ 14,000,000 km²
6. አውሮፓ 10,180,000 km²
7. አውስትራሊያ 8,600,000 km² ናቸው፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 22, Hadith 171
ሠዒድ ኢብኑ ዘይድ ኢብኑ ዐምሪው ኢብኑ ኑፈይል እንደዘገበው፦ "የአላህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ *"ማንም ከምድር ያለ አግባብ የወሰደ አላህ በትንሳኤ ቀን ከሰባት መሬታትን በአንገቱ ዙሪያ እንዲሸከም ያደርገዋል"*። عَنْ سَعِيدِ بْنِ زَيْدِ بْنِ عَمْرِو بْنِ نُفَيْلٍ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ "‏ مَنِ اقْتَطَعَ شِبْرًا مِنَ الأَرْضِ ظُلْمًا طَوَّقَهُ اللَّهُ إِيَّاهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ مِنْ سَبْعِ أَرَضِينَ ‏"‏

በተረፈ በጃምዒ አት-ቲርሚዚይ መጽሐፍ 47, ሐዲስ 3611 ላይ፦ "የሰባቱ መሬቶች በመካከላቸው ያለው እርቀት 500 ዓመት ነው" የሚለው ዘገባ ዶዒይፍ ነው፥ "ዶዒይፍ" ضَعِيْف ማለት “ደካማ”weak” ማለት ሲሆን "መቅቡል" مَقْبُول ሳይሆን "መርዱድ" مَردُود ነው። ኢንሻላህ ስለ ምድርን ንጣፍ፣ ሹረት እና ቅርጽ ነጥብ በነጥብ እንመለከታለን፦
ነጥብ አንድ
"የምድር ንጣፍ"
አምላካችን አላህ ምድርን ለእኛ ፍራሽ አድርጎ ዘርግቷታል፦
2፥22 *"እርሱ ያ ለእናንተ ምድርን "ምንጣፍ" ሰማይንም ጣራ ያደረገ ነው"*። الَّذِي جَعَلَ لَكُمُ الْأَرْضَ فِرَاشًا وَالسَّمَاءَ بِنَاءً

"ምንጣፍ" ለሚለው ቃል የገባው "ፊራሽ" فِرَاش ሲሆን "ፍራሽ" ማለት ነው፥ አንሶላና ብድር ልብስ ያለ ፍራሽ አይደላም። ምድር ለመኖሪያ የተመቻቸች ድሎት እና ማረፊያ ናት፥ የምንተኛበት አልጋ እራሱ "ፊራሽ" فِرَاش ይባላል፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 85, ሐዲስ 27
አቢ ሁረይራህ ሰምቶ እንዳስተላለፈው፦ "ነቢዩም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ *"ልጅ ለአልጋ ባለቤት ነው"*። أَنَّهُ سَمِعَ أَبَا هُرَيْرَةَ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏"‏ الْوَلَدُ لِصَاحِبِ الْفِرَاشِ ‏"‌‏
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 85, ሐዲስ 27
ሑደይፋህ እንደተረከው፦ *"ነቢዩም"ﷺ" ወደ አልጋቸው በሄዱ ጊዜ፦ "አሏሁማ! ቢሥሚከ አሕያ ወአሙት" ይሉ ነበር"*። عَنْ حُذَيْفَةَ، قَالَ كَانَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم إِذَا أَوَى إِلَى فِرَاشِهِ قَالَ ‏"‏ اللَّهُمَّ بِاسْمِكَ أَحْيَا وَأَمُوتُ ‏"‌‏

ሁለቱም ሐዲሳት ላይ "አልጋ" ለሚለው የገባው ቃል "ፊራሽ" فِرَاش መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። አምላካችን አላህ ምድርን ለእኛ ማመቻቸቱን በግስ መደብ "ፈረሽናሃ" فَرَشْنَاهَا በማለት ይናገራል፦
51፥48 *"ምድርንም ዘረጋናት፡፡ ምን ያማርንም ዘርጊዎች ነን!"* وَالْأَرْضَ فَرَشْنَاهَا فَنِعْمَ الْمَاهِدُونَ

"ዘረጋን" ለሚለው የገባው "ፈረሽና" فَرَشْنَا ነው። "ዘርጊዎች" ለሚለው ደግሞ "ማሂዱን" مَٰهِدُون ሲሆን "አልጋ" እራሱ "መህድ" مَهْد ነው። ምድር ለእኛ ልክ እንደ አልጋ ምቹ መኖሪያ ናት፦
43፥10 *"እርሱ ያ ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ ያደረገላችሁ በእርሷም ውስጥ ትመሩ ዘንድ ለእናንተ መንገዶችን ያደረገላችሁ ነው"*፡፡ الَّذِي جَعَلَ لَكُمُ الْأَرْضَ مَهْدًا وَجَعَلَ لَكُمْ فِيهَا سُبُلًا لَّعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ምንጣፍ" ለሚለው ቃል የገባው "መህድ" مَهْد ሲሆን "አልጋ" ማለት ነው። "ለኩም" لَكُم ማለት "ለእናንተ" ማለት ነው። የምድር የላይኛው ቅርፊት"crust” በአብዛኛው ከተለያዩ የቋጥኝ አይነቶች የተገነባ ሲሆን፥ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ የሚኖሩት በዚህኛው የመሬት ክፍል ላይ ነው። ይህንን ክፍል አላህ "ለእኛ" እንደ ፍራሽና አልጋ ንጣፍ አርጎ ፈጥሮታል፥ መዘርጋት ከእኛ እይታ አንጻር ነው። ምክንያቱ "በእርሷም ውስጥ ትመሩ ዘንድ ለእናንተ መንገዶችን ያደረገላችሁ ነው" ይለናል፥ በምድር የላይኛው ቅርፊት ላይ መኪና ስንነዳ መንገዶች ሁሉ የሚታዩን ዝርግ ሆነው ነው። አጠቃላይ የምድር ሹረት እና ቅርፅ ምን ይመስላል? ኢንሻላህ በሚቀጥለው ጊዜ እናያለን.....

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ምድር

ገቢር ሁለት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፦ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

39፥5 ሰማያትንና ምድርን በእወነት ፈጠረ፡፡ *"ሌሊትን በቀን ላይ ይጠቀልላል፡፡ ቀንንም በሌሊት ላይ ይጠቀልላል"*። خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ بِالْحَقِّ ۖ يُكَوِّرُ اللَّيْلَ عَلَى النَّهَارِ وَيُكَوِّرُ النَّهَارَ عَلَى اللَّيْلِ

ነጥብ ሁለት
“የምድር ሹረት”
የሥነ-ፈለክ ጥናት ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናጠና እና ስንቃኝ በጥንት ጊዜ ያሉ ሰዎች፦ “ምድር የሥርዓተ-ፈለክ እምብርት”geocentric” ናት" ብለው ያምኑ ነበር። ነገር ግን በ1533 ድኅረ-ልደት ኒክላስ ኮፐርኒኮስ ምድር ሳትሆን ፀሐይ የሥርዓተ-ፈለክ እምብርት”heliocentric” መሆኗን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለማችን አበረከተ። ምድር በፀሐይ ዛቢያ ስትሽከረከር 365 ቀናት ይፈጃል፥ የዚህ ውጤቱም ክረምት፣ በጋ፣ ፀደይ እና መከር የተባሉ አራት ወቅቶች ይፈራረቃሉ። ምድር በደቡብና በሰሜን በሚገኙት ዋልታዎ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ በራሷ ዛቢያ በ 360 ድግሪ ስትሽከረከር መዓልት እና ሌሊት ይፈራረቃል፥ ይህ ሂደት በአማካኝ 24 ሰዓት ይፈጃል። ይህን ሂደት የሥነ-ፈለክ ምሁራን “ሹረት”rotation” ይሉታል። ምድር ጠፍጣፍ ብትሆን ኖሮ ሌሊት ሲሆን ሁሉም የምድር ይዞታ ላይ ጨለማ ይኖር ነበር፥ እንዲሁ መዓልት ሲሆን ደግሞ ሁሉም የምድር ይዞታ ላይ ብርሃን ይሆን ነበር። ቅሉ ግን ምድር በራሷ ዛቢያ ስለምትሽከረከር መዓልት እና ሌሊት በአንድ ጊዜ እየተደራረቡ ይፈራረቃሉ፦
39፥5 ሰማያትንና ምድርን በእወነት ፈጠረ፡፡ *"ሌሊትን በቀን ላይ ይጠቀልላል፡፡ ቀንንም በሌሊት ላይ ይጠቀልላል"*። خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ بِالْحَقِّ ۖ يُكَوِّرُ اللَّيْلَ عَلَى النَّهَارِ وَيُكَوِّرُ النَّهَارَ عَلَى اللَّيْلِ

"ይጠቀልላል" ለሚለው የገባው ቃል "ዩከወሩ" يُكَوِّرُ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይለዋል። "ከወረ" كَوَّرَ ማለት "ጠቀለለ" "ደረበ" ማለት ነው፥ አንድን ነገር በሌላ ነገር መደረብ"overlap" እራሱ "ከወረ" كَوَّرَ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ብርሃን ሆኖ መአልት ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ አሜሪካ ጨለማ ሆኖ ሌሊት ይሆናል፥ አሜሪካ ብርሃን ሆኖ መአልት ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ኢትዮጵያ ጨለማ ሆኖ ሌሊት ይሆናል። በእኩል ጊዜ መዓልት እና ሌሊት እየተደራረቡ ይፈራረቃሉ፥ ምድር የማትንቀሳቀስ እና ጠፍጣፋ ብትሆን ኖሮ ሁሉም ጋር ሌሊት ወይም ሁሉም ጋር መዓልት ይሆኖ ነበር። ቅሉ ግን መሬት ትንቀሳቀሳለች፥ ቅርጿም የሰጎን እንቁላል ቅርፅ እንጂ ጠፍጣፋ አይደለም።
የሚያጅበው አእዋፍ ሰማይ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ተንሳፋፊዎች ሆነው ባየር ላይ ሲበሩ እንዳይወድቁ የሚይዛቸው ኤሮዳይናሚክ"Aerodynamics" ሕግ አለ፥ በዚህ ሕግ እንዳይወድቁ የሚይዛቸው አላህ ነው፦
67፥19 *"ወደ አእዋፍ ከበላያቸው ክንፎቻቸውን ዘርግተው ተንሳፋፊዎች የሚሰበሰቡም ሲኾኑ አላዩምን? ከአልረሕማን በቀር ባየር ላይ የሚይዛቸው የለም"*፡፡ أَوَلَمْ يَرَوْا إِلَى الطَّيْرِ فَوْقَهُمْ صَافَّاتٍ وَيَقْبِضْنَ ۚ مَا يُمْسِكُهُنَّ إِلَّا الرَّحْمَـٰنُ

በተመሳሳይም ምድር በራሷ ዛቢያ ስትዞር የማትወድቀው አንዱ በአንዱ ባለው የመሳሳብ”Gravity” ሕግ ነው፥ ይህንን ሕግ አርቅቆ እንዳትወድቅ የያዛት አላህ ነው። ምድርም ያለምሰሶ በትዕዛዙ እንዳትወድቅ መቆሟ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፦
35፥41 *"አላህ ሰማያትንና ምድርን እንዳይወገዱ ይይዛቸዋል፡፡ ቢወገዱም ከእርሱ ሌላ አንድም የሚይዛቸው የለም*፡፡ እነሆ እርሱ ታጋሽ መሓሪ ነውና፡፡ إِنَّ اللَّهَ يُمْسِكُ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ أَن تَزُولَا ۚ وَلَئِن زَالَتَا إِنْ أَمْسَكَهُمَا مِنْ أَحَدٍ مِّن بَعْدِهِ ۚ إِنَّهُ كَانَ حَلِيمًا غَفُورًا
30፥25 *"ሰማይ እና ምድርም ያለምሰሶ በትዕዛዙ መቆማቸው፥ ከዚያም ከምድር ጥሪን በጠራችሁ ጊዜ እናንተ ወዲያውኑ የምትወጡ መሆናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው"*፡፡ وَمِنْ آيَاتِهِ أَن تَقُومَ السَّمَاءُ وَالْأَرْضُ بِأَمْرِهِ ۚ ثُمَّ إِذَا دَعَاكُمْ دَعْوَةً مِّنَ الْأَرْضِ إِذَا أَنتُمْ تَخْرُجُونَ
ነጥብ ሦስት
“የምድር ቅርጽ”
አላህ ለሰማይ እና ለምድር "ኑ" ሲላቸው ታዛዦች ሆነው መምጣታቸው በራሱ ምድር እንደምትንቀሳቀስ ቁልጭና ፍንትው አድርጎ ያሳያል፦
41፥11 *"ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ኾና ሳለች አሰበ፡፡ ለእርሷም ለምድርም «ወዳችሁም ኾነ ወይም ጠልታችሁ ኑ» አላቸው፡፡ «ታዛዦች ኾነን መጣን» አሉ"*፡፡ ثُمَّ اسْتَوَىٰ إِلَى السَّمَاءِ وَهِيَ دُخَانٌ فَقَالَ لَهَا وَلِلْأَرْضِ ائْتِيَا طَوْعًا أَوْ كَرْهًا قَالَتَا أَتَيْنَا طَائِعِينَ

ሰማያትና ምድርን፣ ሌሊትንና ቀን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም ሁሉም ለተወሰነ ጊዜ ይሮጣሉ፥ ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዞራሉ፦
39፥5 *"ሰማያትንና ምድርን በእወነት ፈጠረ፡፡ ሌሊትን በቀን ላይ ይጠቀልላል፡፡ ቀንንም በሌሊት ላይ ይጠቀልላል፤ ፀሐይንና ጨረቃንም ገራ፡፡ ሁሉም ለተወሰነ ጊዜ ይሮጣሉ"*፡፡ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ بِالْحَقِّ ۖ يُكَوِّرُ اللَّيْلَ عَلَى النَّهَارِ وَيُكَوِّرُ النَّهَارَ عَلَى اللَّيْلِ ۖ وَسَخَّرَ الشَّمْسَ وَالْقَمَرَ ۖ كُلٌّ يَجْرِي لِأَجَلٍ مُّسَمًّى
21፥33 እርሱም ሌሊትንና ቀንን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም የፈጠረ ነው፡፡ *"ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዋኛሉ"*፡፡ وَهُوَ الَّذِي خَلَقَ اللَّيْلَ وَالنَّهَارَ وَالشَّمْسَ وَالْقَمَرَ ۖ كُلٌّ فِي فَلَكٍ يَسْبَحُونَ

"ይሮጣሉ" ለሚለው ቃል የገባው "የጅሪይ" تَجْرِي ሲሆን "ይዞራሉ" ማለት ነው፥ "ይዋኛሉ" ለሚለው ቃል የገባው ደግሞ "የሥበሑነ" يَسْبَحُونَ ሲሆን "ይዞራሉ" ማለት ነው። ሁሉም አላህ በወሰነላቸው የጊዜ ቀመር በምህዋራቸው ይዞራሉ፥ “ፈለክ” فَلَك የሚለው ቃል “ምህዋር”orbit” ማለት ሲሆን ምድር በፀሐይ ዛቢያ ስትሽከረከር ወቅቶች ይፈራረቃሉ፥ ይህ ሁሉ የሚሆነው ምድር ሞላላ ሆና ስትገኝ ነው። አላህ ምድር ሞላላ መሆኗን ይናገራል፦
79፥30 *"ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት"*፡፡ وَالْأَرْضَ بَعْدَ ذَٰلِكَ دَحَاهَا

እዚህ አንቀጽ ላይ “ዘረጋት” ለሚለው የገባው ቃል "ደሓሃ" دَحَاهَا መሆኑን ልብ በል። "ደሕያህ" دِّحْيَة የሚለው ቃል “ደሓ” دَحَىٰ ማለትም "የሰጎን እንቁላል ቅርጽ አደረገ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "የሰጎን እንቁላል" ማለት ነው። ስለዚህ ምድር እንደ ሰጎን እንቁላል ሞላላ”ellipse” መሆኗን ሰዎች በዚህ ዘመን ከማስተንተናቸው በፊት አላህ ቀድሞ በቁርኣን ተናግሯል። የተለያዩ በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ የቁርኣን ትርጉማት፦ "”He made the earth egg-shaped” ብለው አስቀምጠውታል፦
Dr. Kamal Omar Translation፣
Ali Unal Translation፣
Shabbir Ahmed Translation ተመልከት።

"ደሕያህ" دِّحْيَة የሚለው ቃል “ደሓ” دَحَىٰ ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ መሆኑን ዋቢ የዐረቢኛ ሙዳየ-ቃላት ይመልከቱ፦
1. Lisan Al-Arab dictionary , Book 7, Page 456:
2. Lisan Al-Arab dictionary , Book 2, Page 790.
3. Al-Mawrid dictionary Arabic-English section 4, Page 1132.
4. Al-Mawrid dictionary English-Arabic section 4, Page 227.

"አቅጧር" أَقْطَار ማለት "ክልል" "አጽናፍ" "አድማስ" "ቀበሌ"zone" ማለት ነው፥ ዛሬ በዘመናችን የሥነ-ፈለክ ተመራማሪዎች ከሰማያትና ከምድር አጽናፍ ወጥተው የምድርን አቀማመጥ፣ ሹረት እና ቅርጽ ከሞላ ጎደልና ከብዙ በጥቂቱ ዐውቀዋል፦
55፥33 የጂን እና የሰው ጭፍሮች ሆይ! ከሰማያትና ከምድር ቀበሌዎች መውጣትን ብትችሉ ውጡ፡፡ በሥልጣን እንጅ አትወጡም፡፡ يَا مَعْشَرَ الْجِنِّ وَالْإِنسِ إِنِ اسْتَطَعْتُمْ أَن تَنفُذُوا مِنْ أَقْطَارِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ فَانفُذُوا ۚ لَا تَنفُذُونَ إِلَّا بِسُلْطَانٍ

"ሡልጧን" سُلْطَان ማለት "ኃይል" "ሥልጣን" "ፈቃድ" ማለት ነው፥ የሰው ጭፍሮች በአላህ ኃይል፣ ሥልጣን፣ ፈቃድ በህዋ ጠፈር ላይ ወጥተዋል። እንግዲህ ስለ መሬት በግርድፉና በሌጣው ይህንን ይመስላል።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ቀኝ እና ግራ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፦ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

50፥17 *ሁለቱ ቃል ተቀባዮች መላእክት ከቀኝ እና ከግራ ተቀማጮች ኾነው በሚቀበሉ ጊዜ አስታውስ*፡፡ إِذْ يَتَلَقَّى الْمُتَلَقِّيَانِ عَنِ الْيَمِينِ وَعَنِ الشِّمَالِ قَعِيدٌ

“ኪራመን ካቲቢን” كِرَامًا كَاتِبِين ማለት “የተከበሩ ጸሐፊዎች” ማለት ነው፥ እነዚህ ጸሐፊዎች የምንሠራውን እና የምንናገረውን ይጽፋሉ። እነርሱም በእያንዳንዱ ሰው ቀኝ እና ግራ ያሉ ሁለት መላእክት ናቸው። በቀኝ ያለው ሰናይ ተግባራትን ይመዘግባል፥ በግራ ያለው ደግሞ እኩይ ተግባራትን ይመዘግባል፦
50፥17 *ሁለቱ ቃል ተቀባዮች መላእክት ከቀኝና ከግራ ተቀማጮች ኾነው በሚቀበሉ ጊዜ አስታውስ*፡፡ إِذْ يَتَلَقَّى الْمُتَلَقِّيَانِ عَنِ الْيَمِينِ وَعَنِ الشِّمَالِ قَعِيدٌ
10፥21 *አላህ ቅጣተ ፈጣን ነው፡፡ «መልክተኞቻችን የምትመክሩትን ነገር በእርግጥ ይጽፋሉ» በላቸው*፡፡ قُلِ اللَّهُ أَسْرَعُ مَكْرًا ۚ إِنَّ رُسُلَنَا يَكْتُبُونَ مَا تَمْكُرُونَ
43፥80 ወይም እኛ ምስጢራቸውን እና ውይይታቸውን የማንሰማ መኾናችንን ያስባሉን? አይደለም፤ *መልክተኞቻችንም እነርሱ ዘንድ ይጽፋሉ*፡፡ أَمْ يَحْسَبُونَ أَنَّا لَا نَسْمَعُ سِرَّهُمْ وَنَجْوَاهُم ۚ بَلَىٰ وَرُسُلُنَا لَدَيْهِمْ يَكْتُبُونَ

የምእምናን መጽሐፍ በእርግጥ በዒሊዮን ውስጥ ነው፥ “ዒሊዪን” عِلِّيِّين “ማለት “ከፍተኛ” ወይም “አርያም” ማለት ማለት ነው፦
83፥18 በእውነቱ *የእውነተኞቹ ምእምናን መጽሐፍ በዒሊዮን ውስጥ ነው*፡፡ كَلَّا إِنَّ كِتَابَ الْأَبْرَارِ لَفِي عِلِّيِّينَ
83፥19 *ዒሊዮንም ምን እንደ ኾነ ምን አሳወቀህ?* وَمَا أَدْرَاكَ مَا عِلِّيُّونَ
83፥20 *"የታተመ መጽሐፍ ነው"*፡፡ كِتَابٌ مَّرْقُومٌ

የከሓዲዎቹ መጽሐፍ በእርግጥ በሲጂን ውስጥ ነው፥ “ሢጂን” سِجِّين “እስር” ወይም “እንጦሮጦስ” ማለት ነው፦
83፥7 በእውነት *የከሓዲዎቹ መጽሐፍ በእርግጥ በሲጂን ውስጥ ነው*፡፡ كَلَّا إِنَّ كِتَابَ الْفُجَّارِ لَفِي سِجِّينٍ
83፥8 *ሲጂንም ምን እንደ ኾነ ምን አሳወቀህ?* وَمَا أَدْرَاكَ مَا سِجِّينٌ
83፥9 *"የታተመ መጽሐፍ ነው"*፡፡ كِتَابٌ مَّرْقُومٌ

በዒሊዮን ውስጥ ያለው የምእምናን መጽሐፍ ለአማንያን በቀኙ ይሰጠዋል፥ በተቃራኒው በሲጂን ውስጥ ያለው የከሓዲዎቹ መጽሐፍ ለከሃድያን በግራው ይሰጠዋል፦
69፥19 *መጽሐፉን በቀኙ የተሰጠ ሰውማ ለጓደኞቹ «እንኩ! መጽሐፌን አንብቡ» ይላል*፡፡ فَأَمَّا مَنْ أُوتِيَ كِتَابَهُ بِيَمِينِهِ فَيَقُولُ هَاؤُمُ اقْرَءُوا كِتَابِيَهْ
69፥25 *መጽሐፉንም በግራው የተሰጠማ «ዋ ጥፋቴ! ምነው መጽሐፌን ባልተሰጠሁ» ይላል*፡፡ وَأَمَّا مَنْ أُوتِيَ كِتَابَهُ بِشِمَالِهِ فَيَقُولُ يَا لَيْتَنِي لَمْ أُوتَ كِتَابِيَهْ

“አሽ-ሸማል” الشِّمَال ማለትም “ግራ” ማለት ሲሆን “አል-የሚን” الْيَمِين ማለትም “ቀኝ” ማለት ነው፥ ቀኝ እና ግራ መጽሐፉን ከሚቀበለው ሰው አንጻር ነው። በቀኝ የተቀበለው የጀነት ባለቤት “አስሓቡል የሚን” أَصْحَابُ الْيَمِين ማለትም "የቀኝ ጓድ" ሲባል፥ በተቃራኒው በግራ የተቀበለው የእሳት ባለቤት ደግሞ “አስሓቡ አሽ-ሸማል” أَصْحَابُ الشِّمَال ማለትም "የእሳት ጓድ" ይባላል፦
56፥27 *የቀኝም ጓዶች ምንኛ የከበሩ የቀኝ ጓዶች! ናቸው?*። وَأَصْحَابُ الْيَمِينِ مَا أَصْحَابُ الْيَمِين
56፥41 *የግራ ጓደኞችም ምንኛ የተዋረዱ የግራ ጓዶች! ናቸው?*፡፡ وَأَصْحَابُ الشِّمَالِ مَا أَصْحَابُ الشِّمَالِ

"አሏሁ አዕለም" اَللّٰهُ أَعْلَم‎

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
የጨረቃ አቆጣጠር

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥189 *ከለጋ ጨረቃዎች ይጠየቁሃል፥ እነርሱ ለሰዎች ጥቅም ለሐጅም ማወቂያ ጊዜያቶች ምልክቶች ናቸው በላቸው*፡፡ يَسْأَلُونَكَ عَنِ الْأَهِلَّةِ ۖ قُلْ هِيَ مَوَاقِيتُ لِلنَّاسِ وَالْحَج

የተቆጠሩ ቀኖች የያዘው 9ኛው ወር ረመዷን በመጣ ቁጥር የጨረቃ መታየት እና አለመታየት በፆም መጀመር እና መጨረስ ላይ የሚኖረውም አውንታዊ ተፅዖኖ ብዙ የክርስትና ዘላፊያን ሆኑ ኀያሲያን እንደ በቀቀን እየደጋገሙ መዝለፍና ኂስ መስጠታቸው አይቀሬ ነው። ይህንን ታሳቢና ዋቢ ባደረገ መልኩ ይህንን መጣጥፍ ለዚያ ምላሽ አቅርቤአለው። ግብጻውያን፣ ባቢሎናውያን፣ ሰመርያን፣ ሄለናውያን(ግሪኮች)፣ ሮማውያን፣ ዞራስተሪያን፣ ሂንዱ የየራሳቸው “የዘመን አቆጣጠር”calendar” ነበራቸው።
ይህ አቆጣጠራቸው ምንጩ “አል-ቀመርያ” ማለትም “የጨረቃ አቆጣጠር”lunar calender” እና “አሽ-ሸምሲያህ” ማለትም “የፀሐይ አቆጣጠር”solar calended” ናቸው። አምላካችን አላህ በተከበረ ቃሉ ፀሐይን እና ጨረቃን ለሰው ልጆች የዓመታትን ቁጥርና ሒሳብን መቁጠሪያ እንዳደረገ ይናገራል፦
6፥96 እርሱም ጎህን ከሌሊት ጨለማ ፈልቃቂ ሌሊትንም ማረፊያ *”ፀሐይንና ጨረቃንም ለጊዜ መቁጠሪያ አድራጊ ነው”*፡፡ فَالِقُ الْإِصْبَاحِ وَجَعَلَ اللَّيْلَ سَكَنًا وَالشَّمْسَ وَالْقَمَرَ حُسْبَانًا ۚ ذَٰلِكَ تَقْدِيرُ الْعَزِيزِ الْعَلِيمِ
10፥5 እርሱ ያ ፀሐይን አንጻባራቂ ጨረቃንም አብሪ ያደረገ ነው፡፡ *የዓመታትን ቁጥርና ሒሳብን ታውቁ ዘንድም ለእርሱ መስፈሪያዎችን የለካ ነው*፡፡ አላህ ይህንን በእውነት እንጂ በከንቱ አልፈጠረውም፡፡ ለሚያውቁ ሕዝቦች አንቀጾችን ያብራራል፡፡ هُوَ الَّذِي جَعَلَ الشَّمْسَ ضِيَاءً وَالْقَمَرَ نُورًا وَقَدَّرَهُ مَنَازِلَ لِتَعْلَمُوا عَدَدَ السِّنِينَ وَالْحِسَابَ ۚ مَا خَلَقَ اللَّهُ ذَٰلِكَ إِلَّا بِالْحَقِّ ۚ يُفَصِّلُ الْآيَاتِ لِقَوْمٍ يَعْلَمُونَ

የሥነ-ተረት ጥናት”mythology” እንደሚያትተው በተለይ በባቢሎናውያን “ሲን” የተባለው የጨረቃ አምላክ እና “ሻም” የተባለው የፀሐይ አምላክ ባልና ሚስት ተደርገው ይመለኩ ነው፤ “ሲን” ማለት “ጨረቃ” ማለት ሲሆን “ሻም” ደግሞ “ፀሐይ” ማለት ነው። ይህንን እሳቤ ቁርአን መንግሎ ይጥለዋል፤ መመለክ የሚገባው ፀሐይና ጨረቃን የፈጠራቸው አላህ ብቻ ነው፦
41፥37 ሌሊትና ቀንም፣ *”ጸሐይና ጨረቃም ከምልክቶቹ ናቸው፤ ለፀሐይና ለጨረቃ አትስገዱ፤ ለዚያም ለፈጠራቸው አላህ ሰገዱ፤ እርሱን ብቻ የምታመልኩ እንደሆናችሁ ለሌላ አትስገዱ”*። وَمِنْ آيَاتِهِ اللَّيْلُ وَالنَّهَارُ وَالشَّمْسُ وَالْقَمَرُ ۚ لَا تَسْجُدُوا لِلشَّمْسِ وَلَا لِلْقَمَرِ وَاسْجُدُوا لِلَّهِ الَّذِي خَلَقَهُنَّ إِن كُنتُمْ إِيَّاهُ تَعْبُدُونَ

የዘመናችን የሥነ-ፈለክ ጥናት እንደሚያትተው የጨረቃ ፈለክ ምድራችንን በ 384,408 km በሆነ ዑደት”Revolution” ለመዞር የሚወስድባት ጊዜ 27 ቀናት ነው። አምላካችን አላህም በቁርኣን “ቀመር” قَمَر ማለትም “ጨረቃ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው “27” ጊዜ ብቻ ነው። ጨረቃ ፕላኔታችንን በምእራባዊ አቅጣጭ 360 ድግሪ ለመዞር 19 ዓመት ይፈጅባታል።
የሚያስደምመው ነገር “ዓመት” የሚለው ቃል የተጠቀሰው “ሢኒን” سِنِين በብዜት 12 ጊዜ ወይም “ሠናህ” سَنَة በነጠላ 7 ጊዜ በጥቅሉ “19” ጊዜ ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የዓለማቱ ጌታ ነገርን ሁሉ በቁጥር ያጠቃለለ ስለሆነ ነው፦
72፥28 እነርሱ ዘንድ ባለው ነገር እውቀቱ የከበበ እና * ነገሩንም ሁሉ “በቁጥር” ያጠቃለለ ሲሆን”* የጌታቸውን መልክቶች ያደረሱ መሆናቸውን ያውቅ ዘንድ ጠባቂ ያደርጋል። لِّيَعْلَمَ أَن قَدْ أَبْلَغُوا رِسَالَاتِ رَبِّهِمْ وَأَحَاطَ بِمَا لَدَيْهِمْ وَأَحْصَىٰ كُلَّ شَيْءٍ عَدَدًا

የእኛ አቆጣጠር የጨረቃ አቆጣጠር ነው፦
2፥189 *ከለጋ ጨረቃዎች ይጠየቁሃል፥ እነርሱ ለሰዎች ጥቅም ለሐጅም ማወቂያ ጊዜያቶች ምልክቶች ናቸው በላቸው*፡፡ يَسْأَلُونَكَ عَنِ الْأَهِلَّةِ ۖ قُلْ هِيَ مَوَاقِيتُ لِلنَّاسِ وَالْحَج

የለጋ ጨረቃ መታየት የጊዜ ማወቂያ ምልክት ነው። ነቢያችን”ﷺ” የአላህ ነብይ ስለሆኑ በዐቂዳህ እና በፊቅህ ጉዳይ ላይ የሚናገሩት ወሕይ ስለሆነ ስለ ጨረቃ እንዲህ ይሉናል፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 6, ሐዲስ 2378
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ.” እንደተረከው የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *”መቼም ቢሆን ለጋ ጨረቃ በረመዳን ወር ስታዩ ፆምን ጀምሩ፤ የሸዋል ለጋ ጨረቃ ስታዩ ፆማችሁን ጨርሱ፤ ሰማይ ደመናማ ሲሆንላችሁ ፆም ሰላሳ ቀን መሆኑን አጢኑ”*። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، – رضى الله عنه – قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ إِذَا رَأَيْتُمُ الْهِلاَلَ فَصُومُوا وَإِذَا رَأَيْتُمُوهُ فَأَفْطِرُوا فَإِنْ غُمَّ عَلَيْكُمْ فَصُومُوا ثَلاَثِينَ يَوْمًا ‏”
የጨረቃ አቆጣጠር በኢሥላም በግርድፉና በሌጣው ይህ ያክል ካየን ዘንዳ የጨረቃ አቆጣጠር በባይብልና በትውፊት እናያለን፥ የጨረቃ መታየት ለጊዜ ማወቂያ እንደሆነ መዝሙረኛው ይናገራል፦
መዝሙረ ዳዊት 104፥19 *”ጨረቃን ለጊዜዎች አደረገ”* ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል።

በተለይ አይሁዳውያን የወር መባቻ ጠብቀው በዓላቸውን የሚያውቁበት ነው፥ የወር መባቻ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ቆደሽ” חֹ֫דֶשׁ ሲሆን ትርጉሙ “አዲስ ጨረቃ” ማለት ነው። ይህም ቃል በባይብል 28 ጊዜ ተወስቷል፥ ዕብራውያን ወራቸውን ሆነ ዓመታቸውን የሚጀምሩ በለጋ ጨረቃ መታየት ነው፦
ዘኍልቍ 10፥10 ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ *”በአዲስ ጨረቃ” חָדְשֵׁיכֶם֒ ፥”* በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። NIV Bible
መዝሙር 81፥3 *”በአዲስ ጨረቃ” חָדְשֵׁיכֶם֒ ቀን”* በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤ NIV Bible

በክርስትና ቀዳማይ የዘመን አቆጣጠር ከ 180 –222 ድኅረ-ልደት”A.D” ድረስ ለ 42 ዓመት የአሌክሳንድርያ ፓትርያርክ የነበረው ድሜጥሮስ የቀመረው ነው። ይህም የዘመን ቀመር “አቡሻኽር” ወይም “ባሕረ-ሐሳብ” ይባላል። “ባሕር” ማለት “ዘመን” ማለት ሲሆን “ሐሳብ” ማለት ደግሞ “ሒሳብ” “ቁጥር” “ኍልቅ” ማለት ነው። በዚህ የዘመን ቀመር ላይ ስለ “አዕዋዳት” ይናገራል፥ “አዕዋድ” ማለት “ዖደ” ማለትም “ዞረ” ከሚል የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን “ዙረት” ማለት ሲሆን በየጊዜው እየዞረ የሚመጣ ማለት ነው።
ዓውደ-ወርኅ በፀሐይ 30 ቀናት ሲሆን በጨረቃ 29 እና 30 ነው። ዓውደ-ዓመት በፀሐይ 365 ቀናት ሲሆን በጨረቃ 354 ቀናት ነው፦
ዘፍጥረት 1፥14 እግዚአብሔርም አለ፦ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ *”ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ*፤
ዘፍጥረት 1፥16 እግዚአብሔርም *”ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን”*፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።
መዝሙር 136፥8-9 *”ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ ለጨረቃና ለከዋክብትም ሌሊትን ያስገዛቸው”*፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን ፀሐይን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን ጨረቃን በሌሊት እንዲሰለጥን አደረገ። በተጨማሪም መጽሐፈ ሲራክ ጨረቃም ለሁሉም የዘመን መለኪያ፣ ለዓለም ሁሉ ምልክት እና የበዓላት ምልክት እንደሆነች ይናገራል፦
መጽሐፈ ሲራክ 43÷6-7 *”ጨረቃም ለሁሉም የዘመን መለኪያ ናት፤ ለዓለም ሁሉ ምልክት ናት፤ በእርሷም ቀን ይለያል፤ በጨረቃም የበዓላት ምልክት ይታወቃል”*።

ታዲያ ጨረቃን ጠብቆ ፆም መያዝና መፍታት እንዲሁ በዓልን ማክበር ለምን ኂስ ይሰጥበታል? ተዉ እንጂ እግር እራስን ያካል እንዴ? ወርቁ ቢጠፋስ ሚዛኑ ጠፋ እንዴ? እውነቱ ቢጠፋባችሁስ ህሊናችሁ ጠፋባችሁ እንዴ? የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ ወይም ቅቤ አንጣሪዋ እያለሽ ጎመን ቀቃይዋን ምች መታት ይላል የአገሬ ሰው። ቅድሚያ እሥልምናን ለመዝለፍ ባይብላችሁን እና ትውፊታችሁን ጠንቅቃችሁ ዕወቁ።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
የመልእክተኛ ቃል

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

81፥19 *"እርሱ የክቡር መልእክተኛ ቃል ነው"*፡፡ إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ

“ቁርኣን” قُرْءَان የሚለው ቃል “ቀረአ” قَرَأَ ማለትም “አነበበ" “አነበነበ” ከሚል ግስ የመጣ ሲሆን “መነባነብ”recitation” ማለት ነው፥ ቁርኣን የሚነበብ የአላህ አንቀጽ ነው፦
46፥7 *"በእነርሱም ላይ አንቀጾቻችን ግልጾች ኾነው በተነበቡ ጊዜ እነዚያ እውነቱን በመጣላቸው ጊዜ የካዱትን «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ"*፡፡ وَإِذَا تُتْلَىٰ عَلَيْهِمْ آيَاتُنَا بَيِّنَاتٍ قَالَ الَّذِينَ كَفَرُوا لِلْحَقِّ لَمَّا جَاءَهُمْ هَـٰذَا سِحْرٌ مُّبِينٌ

"አንቀጾቻችን" የሚለው አምላካችን አላህ ነው፥ ቁርኣን የአምላካችን የአላህ ንግግር ነው፦
9፥6 *"ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ የአላህን ንግግር እስኪሰማ ድረስ አስጠጋው"*፡፡ وَإِنْ أَحَدٌ مِّنَ الْمُشْرِكِينَ اسْتَجَارَكَ فَأَجِرْهُ حَتَّىٰ يَسْمَعَ كَلَامَ اللَّهِ

"የአላህ ንግግር" የሚለው ኃይለ-ቃል ይሰመርበት። አምላካችን አላህ ወሕይ የሚያወርደው በራእይ ወይም ከግርዶ ወዲያ ወይም መልእክተኛን መልአክን የሚልክ እና በፈቃዱ የሚሻውን በማውረድ ነው፦
42፥51 *ለሰው አላህ “በራእይ”፣ ወይም “ከግርዶ ወዲያ”፣ ወይም “መልእክተኛን መልአክን” የሚልክ እና በፈቃዱ የሚሻውን “የሚያወርድለት” ቢሆን እንጅ በገሃድ “ሊያናግረው” ተገቢው አይደለም”*። እርሱ የበላይ ጥበበኛ ነውና። وَمَا كَانَ لِبَشَرٍ أَن يُكَلِّمَهُ ٱللَّهُ إِلَّا وَحْيًا أَوْ مِن وَرَآئِ حِجَابٍ أَوْ يُرْسِلَ رَسُولًۭا فَيُوحِىَ بِإِذْنِهِۦ مَا يَشَآءُ ۚ إِنَّهُۥ عَلِىٌّ حَكِيمٌۭ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ረሡል" رَسُول የሚለው ቃል "አርሠለ" أَرْسَلَ ማለትም "ላከ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መልእክተኛ" ማለት ነው፥ "መልእክተኛን መልአክ የሚልክ እና በፈቃዱ የሚሻውን የሚያወርድለት ቢሆን እንጅ" የሚለው ይሰመርበት። በአላህ ፈቃድ ወሕይን የሚያወድ መልእክተኛ እንዳለ ከተረዳን ዘንዳ ቁርኣንን በአላህ ፈቃድ ወደ ነቢያችን"ﷺ" ልብ ያወረደው ጂብሪል ነው፦
2፥97 *ለጂብሪል ጠላት የኾነ ሰው በቁጭት ይሙት በላቸው፡፡ እርሱ ቁርኣኑን ከበፊቱ ለነበሩት አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና*፡፡ قُلْ مَن كَانَ عَدُوًّا لِّجِبْرِيلَ فَإِنَّهُ نَزَّلَهُ عَلَىٰ قَلْبِكَ بِإِذْنِ اللَّهِ مُصَدِّقًا لِّمَا بَيْنَ يَدَيْهِ وَهُدًى وَبُشْرَىٰ لِلْمُؤْمِنِينَ

ጂብሪል መልአክ እንደሆነ እሙን እና ቅቡል ነው። "መለክ" مَلَك ወይም "መልአክ" مَلْأَك የሚለው ቃል "ለአከ" لَأَكَ ከሚለው ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ተላላኪ" ማለት ነው፥ የመለክ ብዙ ቁጥር ደግሞ "መላኢክ" مَلَائِك‎ ወይም "መላኢካህ" مَلَائِكَة‎ ነው። ጂብሪል መልእክተኛ ከሆነ አላህ "ሙርሢል” مُرْسِل ማለትም "ላኪ" ነው፥ በላኪ አላህ እና በተላኪ ጂብሪል መካከል "ሪሣላህ" رِسَالَة ማለትም "መልእክት" አለ። ይህም ሪሣላህ ቁርኣን ነው፦
81፥19 *"እርሱ የክቡር መልእክተኛ ቃል ነው"*፡፡ إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ

"እርሱ" የሚለው ተሳቢ ተውላጠ-ስም "ቁርኣን" የሚለውን ተክቶ የመጣ ነው። እዚህ አንቀጽ ላይ "መልእክተኛ" የተባለው ጂብሪል ነው፥ ይህ መልእክተኛ ዐውደ-ንባቡን ስንመለከተው በዙፋኑ ባለቤት በአላህ ዘንድ ባለሟል እና ታማኝ የኾነ ነው፦
81፥20 *"የኀይል ባለቤት በዙፋኑ ባለ ቤት ዘንድ ባለሟል የኾነ"*፡፡ ذِي قُوَّةٍ عِندَ ذِي الْعَرْشِ مَكِينٍ
81፥21 *"በዚያ ስፍራ ትእዛዙ ተሰሚ፤ ታማኝ የኾነ ነው"*፡፡ مُّطَاعٍ ثَمَّ أَمِينٍ

ጂብሪል "ታማኝ" መባሉ በቀጥታ ከአላህ ወደ ነቢያችን"ﷺ" ልብ ሳይጨምር እና ሳይቀንስ ስለሚያስተላልፍ ነው። ቁርኣን የዚህ መልእክተኛ "ቀውል" ነው፥ "ቀውል" قَوْل የሚለው ቃል "ቀወለ" قَوَّلَ "ማለትም "አስባለ" ከሚል ሥርወ-ቃል ሲመጣ "የሚባል"saying" ማለት ነው። የቀውል "ትእዛዛዊ ግሱ እራሱ "ቁል" قُلْ ማለትም "በል" ነው፥ አላህ ለጂብሪል ይህንን "በል" ሲለው እርሱ ተቀብሎ ሲለው የመልእክተኛው ቀውል ነው። ጂብሪል በቁርኣን ላይ ያለው ድርሻ "ሙራሢል" مُرَاسِل ማለትም "አስተላላፊ"reporter" እንጂ "ሙአለፍ" مُؤَلَّف ማለትም "አመንጪ"author" አይደለም። ቀውልን በአስተላላፊው በጂብሪል ወደ ነቢያችን"ﷺ" ልብ የሚጥለው አላህ ብቻ ነው፦
73፥5 *"እኛ በአንተ ላይ ከባድ ቃልን እንጥላለንና"*፡፡ إِنَّا سَنُلْقِي عَلَيْكَ قَوْلًا ثَقِيلًا

እዚህ አንቀጽ ላይ "ቃል" ለሚለው የገባው "ቀውል" قَوْل የሚለው መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። ጂብሪል ሆነ ነቢያችን"ﷺ" በቁርኣን ላይ ያላቸው ጉልኅ ድርሻ መልእክቱን ማድረስ ብቻ ስለሆነ ነቢያችን"ﷺ" እራሱ ጂብሪል በተባለለት ቀመር እና ስሌት "የመልእክተኛ ቃል" ተብሎላቸዋል፦
69፥40 *"እርሱ የተከበረ መልክተኛ ቃል ነው"*፡፡ إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ

ጂብሪል ሆነ ነቢያችን"ﷺ" መልእክተኛ ከተባሉ ላኪው አላህ ነው፥ መልእክቱ ደግሞ የላኪ እንጂ የተላላኪ አይደለም፦
5፥67 *"አንተ መልክተኛ ሆይ! ከጌታህ ወደ አንተ የተወረደውን አድርስ፡፡ ባትሠራም መልክቱን አላደረስክም"*፡፡ يَا أَيُّهَا الرَّسُولُ بَلِّغْ مَا أُنزِلَ إِلَيْكَ مِن رَّبِّكَ ۖ وَإِن لَّمْ تَفْعَلْ فَمَا بَلَّغْتَ رِسَالَتَهُ

"ሪሣላህ" رِسَالَة በሚለው መድረሻ ቅጥያ ላይ "ሁ" هُ የሚለው ተውላጠ-ስም አላህን የሚያመላክት ነው፥ ሪሳላው ከጌታ አላህ ወደ ነቢያችን"ﷺ" እንዲያደርሱ የወረደ የራሱ የአላህ ንግግር ብቻ ነው።
እንግዲህ ጥልልና ጥንፍፍ ባለ መልኩ የሚበጀወን ከሚፋጀው ለይተን ካስቀመጥን ዘንዳ፥ ባይብል ላይም የፈጣሪ ንግግር ወደ መላእክት ተጠግቶ የመላእክት ቃል መሆኑ ተገልጿል፦
ዳንኤል 4፥24 *"በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው"*።
ዳንኤል 4፥17 *"ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው"*።

በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ከልዑል የወረደው ትእዛዝ "የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ የቅዱሳን ቃል" ተብሏል፥ እዚህ አንቀጽ ላይ "ጠባቂዎች" እና "ቅዱሳን" የተባሉት መላእክት እንደሆኑ ሸክ የለውም። ታዲያ የልዑል አምላክ ትእዛዝ እና ቃል የመላእክት ትእዛዝ እና ቃል ነውን? "ምን ነክቶካል? መላእክት እኮ የልዑል አምላክ ተላላኪዎች ናቸው" ይሉካል፥ እንግዲያውስ "ቀርኣን የክቡር መልክተኛ ቃል ነው" የሚለውን በዚህ ሒሳብ ተረዳው። “ቶራህ” תּוֹרָה ማለት “ሕግ” ማለት ነው፥ ይህ ሕግ ምንጩ ፈጣሪ ነው። ነገር ግን ይህ የአምላክ ሕግ የሙሴ ሕግ ተብሏል፦፦
ዘጸአት 16፥4 *ያህዌህ ሙሴን፦ ”በሕጌ” ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ"*።
ሚልክያስ 4፥4 *ለእስራኤል ሁሉ ”ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባሪያዬን የሙሴን ሕግ” አስቡ”*።

ታዲያ የፈጣሪ ሕግ የሙሴ ሕግ ነውን? "ምን ነክቶካል? ሙሴ እኮ የፈጣሪ መልእክተኛ ነው፥ "የሙሴ ሕግ" የተባለው በሙሴ በኩል ስለተላለፈ ነው" ይሉካል፥ እንግዲያውስ "ቀርኣን የክቡር መልክተኛ ቃል ነው" የሚለውን በዚህ ልክና መልክ ተረዳው። በሰፈሩት ቁና መሰፈር ይሉካል እንደዚህ ነው።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ሒዝብ እና ጁዝዕ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

17፥106 *ቁርአንንም በሰዎች ላይ ሆነህ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው፥ ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው*። وَقُرْآنًا فَرَقْنَاهُ لِتَقْرَأَهُ عَلَى النَّاسِ عَلَىٰ مُكْثٍ وَنَزَّلْنَاهُ تَنزِيلًا

"አሕዛብ" أَحْزَاب‎ የሚለው ቃል "ሐዘበ" حَزَبَ ማለትም "ከፈለ" ከሚለው ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ቡድን" "ክፍል" "አንጃ" ማለት ነው፥ የአሕዛብ ብዙ ቁጥር "ሒዝብ" حِزْب ይባላል። ቁርኣን ላይም "ሒዝብ" حِزْب የሚባል የአቀራር እሳቤ አለ፥ ነቢያችን”ﷺ” በሕይወታቸው ዘመን ማብቂያ ላይ ስለ ሙሉ ቁርኣን በልብ ውስጥ እንዴት እንደሚቀራ እንዲህ ተናግረዋል፦
ኢማም ቡኻርይ: መጽሐፍ 66, ሐዲስ 78
ዐብደላህ ኢብኑ ዐምር እንደተረከው፦ *”ነቢዩም”ﷺ” እኔን፦ “ሙሉ ቁርኣንን ቀርቶ ለመጨረስ ስንት ጊዜ ይወስድብሃል? ብለው ጠየቁኝ*። عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ عَمْرٍو، قَالَ لِي النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ فِي كَمْ تَقْرَأُ الْقُرْآنَ ‏”‌‏.‏
ኢማም ቡኻርይ: መጽሐፍ 66, ሐዲስ 79
ዐብደላህ ኢብኑ ዐምር እንደተረከው፦ *”የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ “ሙሉ ቁርኣንን በአንድ ወር ጊዜ ቅራ”። እኔም፦ “ከዛ በታች ለመቅራት ችሎታው አለኝ” አልኩኝ፤ እርሳቸው፦ “በሰባት ቀናት ቅራው፤ ከዚያ በታች ሙሉውን ለመቅራት አይቻልም*። عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ عَمْرٍو، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏”‏ اقْرَإِ الْقُرْآنَ فِي شَهْرٍ ‏”‌‏.‏ قُلْتُ إِنِّي أَجِدُ قُوَّةً حَتَّى قَالَ ‏”‏ فَاقْرَأْهُ فِي سَبْعٍ وَلاَ تَزِدْ عَلَى ذَلِكَ ‏”‌‏.‏

በሰባት ቀናት ከፋፍሎ መቅራት “መንዚል” مَنْزِل ይባላል። ሌላው ቁርኣን ሠላሳ ጁዝዕ” አለው፥ “ጁዝዕ” جُزْءْ‎ ማለት “ክፍል”part” ማለት ሲሆን በሠላሳ ቀናት ከፋፍሎ መቀራትን ያሳያል። በተለይ በተራዊህ ሶላት ላይ ሙሉ ሠላሳ ጁዝዕ ይቀራል፤ “ተራዊህ” تراويح‌‎ ማለትም “በረመዳን የሌሊት ሶላት” ማለት ነው፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 31, ሐዲስ 4
የነብዩ”ﷺ” ባልተቤት ዓኢሻህ”ረ.ዐ.” እንደተረከችው፦ *”የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” በረመዳን ሌሊት ይጸልዩ ነበር”*። عَنْ عَائِشَةَ، رضى الله عنها زَوْجِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم صَلَّى وَذَلِكَ فِي رَمَضَانَ‏.‏
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 31, ሐዲስ 1
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ” እንደተረከው የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” ስለ ረመዳን እንደተናገሩት፦ *”ማንም በረመዳን ሌሊት በእምነት እና ከአላህ ወሮታ አገኛለው ብሎ ተስፋ አድርጎ ከቆመ ያለፈው ወንጀሉ ሁሉ ይቅር ይባልለታል”*። أَنَّ أَبَا هُرَيْرَةَ ـ رضى الله عنه ـ قَالَ سَمِعْتُ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم يَقُولُ لِرَمَضَانَ ‏ “‏ مَنْ قَامَهُ إِيمَانًا وَاحْتِسَابًا غُفِرَ لَهُ مَا تَقَدَّمَ مِنْ ذَنْبِهِ ‏”‌‏.‏

በአንድ ጁዝዕ ላይ አራት ክፍሎች እራሱ "ሒዝብ" حِزْب ይባላል። አንድ ጁዝ ለሁለት ከፍሎ መቅራት "ሒዝባኒ" حِزْبَانِ ሲባል ይህ 30 ጁዝዕ የነበረውን ክፍል 60 ሲሆን "አሕዛብ" أَحْزَاب ይባላል፥ አምላካችን አላህ ቁርአንንም ይነበብ ዘንድ ከፋፈልነው፥ ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረደው፦
17፥106 *ቁርአንንም በሰዎች ላይ ሆነህ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው፥ ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው*። وَقُرْآنًا فَرَقْنَاهُ لِتَقْرَأَهُ عَلَى النَّاسِ عَلَىٰ مُكْثٍ وَنَزَّلْنَاهُ تَنزِيلًا

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ረመዷን

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥183 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! *”ጾም በእነዚያ ከእናንተ በፊት በነበሩት ላይ እንደ ተጻፈ በእናንተም ላይ ተጻፈ፥ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና”*፡፡ يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ كُتِبَ عَلَيْكُمُ ٱلصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

“ሰውም” صَوْم ወይም “ሲያም” صِيَام የሚለው ቃል “ተሱም” يَصُمْ ማለትም “ታቀብ” ከሚል ትእዛዛዊ ግስ የመጣ ሲሆን “መታቀብ” ማለት ነው፥ ይህ ቋንቋዊ ፍቺው ሲሆን “ሰውም” صَوْم ወይም “ሲያም” صِيَام በግርድፉና በሌጣው ደግሞ “ጾም” ማለት ነው። አንድ ሰው ምንም ነገር ሳይቀምስ ሲቀር “ጾሙን ዋለ” ይባላል፥ ያ ማለት ከምግብና ከመጠጥ “ተከለከለ” አሊያም “ተቆጠበ” ማለት ነው። ጾም ማለት “መከልከል” ወይም “መቆጠብ” መሆኑን የምናውቀው የአለመናገር ተቃራኒ የሆነውን “ዝምታን” ለማመልከት “ሰውም” صَوْم የሚለው ቃል አገልግሎት ላይ ውሏል፦
19፥26 «ብይም፣ ጠጭም፣ ተደሰችም፡፡ እኔ ለአልረሕማን *”ዝምታን ተስያለሁ”*፤ ዛሬም ሰውን በፍጹም አላነጋግርም» በይ፡፡ فَكُلِي وَاشْرَبِي وَقَرِّي عَيْنًا ۖ فَإِمَّا تَرَيِنَّ مِنَ الْبَشَرِ أَحَدًا فَقُولِي إِنِّي نَذَرْتُ لِلرَّحْمَـٰنِ صَوْمًا فَلَنْ أُكَلِّمَ الْيَوْمَ إِنسِيًّا

መርየም “ሰውማ” صَوْمًا ማለትም “ዝምታ” ስትል ከንግግር መቆጠቧን ካመለከተ ጾም ማለት ከምግብና ከመጠጥ መከልከል እንጂ ከስጋ እና ከስጋ ተዋእፆ ከሆኑት እንቁላል፣ ወተት፣ አይብ እየተቆጠቡ ነገር ግን በእጅ አዙር የስጋ፣ የእንቁላል፣ የወተት ምትክ የሆኑትን ባቄላ፣ አተር፣ በቆሎ፣ ገብስ የመሳሰሉት በሳይክል ተዙሮ የማያልቀውን ቡፌ መብላት አይደለም። ጾም ከምግብና ከመጠጥ ብቻ ሳይሆን ከሚታይ፣ ከሚሰማ፣ ከሚታሰብ ነገር መቆጠብን እንደሚጨም በቋንቋ ሙግት አይተናል።

አምላካችን አላህ ጾምን መጾም ያለባቸው ያመኑትን ምዕምናን ብቻ መሆናቸው ለማመልከት፦ “እናንተ ያመናችሁ ሆይ” በሚል መርሕ ስለ ጾም ይናገራል፦
2፥183 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! *”ጾም በእነዚያ ከእናንተ በፊት በነበሩት ላይ እንደ ተጻፈ በእናንተም ላይ ተጻፈ፥ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና”*፡፡ يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ كُتِبَ عَلَيْكُمُ ٱلصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

“ከእናንተ በፊት በነበሩት” የሚለው ኃይለ-ቃል ይሰመርበት፥ ከእኛ በፊት የነበሩት ነቢያትና ተከታዮቻቸው ናቸው፦
42፥3 እንደዚሁ አሸናፊው ጥበበኛው አላህ *”ወደ አንተ ያወርዳል፡፡ ወደ እነዚያም ከአንተ በፊት ወደ ነበሩት አውርዷል”*፡፡ كَذَٰلِكَ يُوحِي إِلَيْكَ وَإِلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكَ اللَّهُ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ
39፥65 ብታጋራ ሥራህ በእርግጥ ይታበሳል፡፡ በእርግጥም ከከሓዲዎቹ ትኾናለህ ማለት *”ወደ አንተም ወደ እነዚያም ከአንተ በፊት ወደነበሩት በእርግጥ ተወርዷል”*፡፡ وَلَقَدْ أُوحِيَ إِلَيْكَ وَإِلَى الَّذِينَ مِن قَبْلِكَ لَئِنْ أَشْرَكْتَ لَيَحْبَطَنَّ عَمَلُكَ وَلَتَكُونَنَّ مِنَ الْخَاسِرِينَ

ስለዚህ ጾም የተደነገገው ከነቢያችን”ﷺ” በፊት በነበሩትም ነቢያት ጭምር ነው፥ “ኩቲበ” كُتِبَ ማለት “ተደነገገ” “ተደነባ” “ታዘዘ”prescribed” ማለት ነው። ጾም የምንጾምበትን ምክንያት ደግሞ ለማመልከት፦ “ተቅዋ ታገኙ ዘንድ ነው” ይለናል፦
2፥183 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! *”ጾም በእነዚያ ከእናንተ በፊት በነበሩት ላይ እንደ ተጻፈ በእናንተም ላይ ተጻፈ፥ “ልትጠነቀቁ ይከጀላልና”*፡፡ يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُوا۟ كُتِبَ عَلَيْكُمُ ٱلصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

“ተተቁን” تَتَّقُون ማለት “መፍራት” ማለት ነው። ጾም የምንጾምበት ምክንያቱ አንደኛውና ዋናው አምላካችን አላህ ስላዘዘን ሲሆን ሁለተኛውና ተከታዩ ምክንያት “ተቅዋ” ለማግኘት ነው፥ “ይከጀላልና” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ለዐለኩም” لَعَلَّكُمْ ሲሆን “ለዐለኩም” በሚለው ቃል ላይ መነሻ ቅጥያ ሆኖ የመጣው ቃል “ለዐል” لَعَلّ ነው። “ለዐል” ማለት “ዘንድ” so that” ማለት ሲሆን ምክንያታዊ መስተዋድድ ሆኖ የገባ ነው። ስለዚህ የምንጾምበት ምክንያት አካልን ከሚበላና ከሚጠና በመከልከል እራስን ሙሉ ለሙሉ ለዒባዳህ በመስጠት “አላህን ለመፍራት” ነው፥ “ተቅዋ” َتَقْوَى ማለት “አላህ መፍራት” ሲሆን “ሙተቂን” مُتَّقِين ደግሞ አላህ የሚፈራው “ፈሪሃን” ነው። የጾም ድባቡ እራሱ ተቅዋ ያዘለ ዘርፈ ብዙ የአምልኮ መርሃ-ግብር ነው። ሌላው የምንጾምበት ሦስተኛ ምክንያት አላህ በመጠነ-ሰፊ አምልኮ ልናከብረውና ልናመሰግነው ነው፦
2፥185 ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ *”ታከብሩት እና ታመሰግኑት ዘንድ ይህን ደነገግንላችሁ”*፡፡ وَلِتُكْمِلُوا الْعِدَّةَ وَلِتُكَبِّرُوا اللَّهَ عَلَىٰ مَا هَدَاكُمْ وَلَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ

“ታከብሩት እና “ታመሰግኑት” ዘንድ የሚለው ኃይለ-ቃል ይሰመርበት። “ተክቢር” تَكْبِير በአምልኮ “አሏሁ አክበር” اَللّٰهُ أَكْبَرْ ማለት ሲሆን “ሊቱከብሩ” َلِتُكَبِّرُوا ማለት ይህንኑ ያሳያል። “ተሽኩር” تَشْكُر በአምልኮ አላህ የምናመሰግንበት ነው፥ አላህ “ሻኪር” شَاكِر ማለትም “ተመስጋኝ” ሲሆን ባሮቹ ደግሞ “ሸኩር” شَكُور ማለት እርሱን “አመስጋኝ” ናቸው፥ “ተሽኩሩን” تَشْكُرُون ማለቱ ይህንን ያሳያል። አላህ እንድናከብረውና እንድናመሰግነው ጾምን ደነገገልን።
በመቀጠል በሽተኛና መንገደኛ በፆም ወቅት መፆም እንደሌለበትና እንዴት ቀዳ ማውጣት እንዳለበት ይነግረናል፦
2፥184 የተቆጠሩን ቀኖች ጹሙ፡፡ *”ከእናንተም ውሰጥ “በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነ ሰው” ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን መጾም አለበት፡፡ “በእነዚያም ጾምን በማይችሉት ላይ ቤዛ ድኻን ማብላት አለባቸው፡፡ ቤዛን በመጨመር መልካምንም ሥራ የፈቀደ ሰው እርሱ ፈቅዶ መጨመሩ ለርሱ በላጭ ነው፡፡ መጾማችሁም ለእናንተ የበለጠ ነው፥ የምታውቁ ብትኾኑ ትመርጡታላችሁ”*፡፡ أَيَّامًا مَّعْدُودَاتٍ ۚ فَمَن كَانَ مِنكُم مَّرِيضًا أَوْ عَلَىٰ سَفَرٍ فَعِدَّةٌ مِّنْ أَيَّامٍ أُخَرَ ۚ وَعَلَى الَّذِينَ يُطِيقُونَهُ فِدْيَةٌ طَعَامُ مِسْكِينٍ ۖ فَمَن تَطَوَّعَ خَيْرًا فَهُوَ خَيْرٌ لَّهُ ۚ وَأَن تَصُومُوا خَيْرٌ لَّكُمْ ۖ إِن كُنتُمْ تَعْلَمُونَ

የምንጾምበት ወር ደግሞ በረመዷን ወር ነው፦
2፥185 *”እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ ያ በእርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድ እና እውነትን ከውሸት ከሚለዩም ገላጮች አንቀጾች ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡ ከእናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው”*፡፡ شَهْرُ رَمَضَانَ الَّذِي أُنزِلَ فِيهِ الْقُرْآنُ هُدًى لِّلنَّاسِ وَبَيِّنَاتٍ مِّنَ الْهُدَىٰ وَالْفُرْقَانِ ۚ فَمَن شَهِدَ مِنكُمُ الشَّهْرَ فَلْيَصُمْهُ ۖ وَمَن كَانَ مَرِيضًا أَوْ عَلَىٰ سَفَرٍ فَعِدَّةٌ مِّنْ أَيَّامٍ أُخَرَ ۗ يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ وَلِتُكْمِلُوا الْعِدَّةَ وَلِتُكَبِّرُوا اللَّهَ عَلَىٰ مَا هَدَاكُمْ وَلَعَلَّكُمْ تَشْكُرُونَ

የወር ስሞች ቅደም ተከተል፡-
1ኛው ወር- ሙሐረም
2ኛው ወር- ሰፈር
3ኛው ወር- ረቢዑል-አወል
4ኛው ወር- ረቢዑ-ሣኒ
5ኛው ወር- ጀማዱል-አወል
6ኛው ወር- ጀማዱ-ሣኒ
7ኛው ወር- ረጀብ
8ኛው ወር- ሻዕባን
9ኛው ወር- ረመዷን
10ኛው ወር- ሸዋል
11ኛው ወር- ዙል-ቀዒዳህ
12ኛው ወር- ዙል-ሒጃህ ናቸው።
የተቆጠሩ ቀኖች የያዘው ረመዷን 9ኛው ወር ሲሆን ይህ ወር የሚጾምበት ምክንያት ቁርኣን ከጥብቁ ሰሌዳ ወደ ቅርቢቱ ሰማይ የወረደበት ወር ስለሆነ ነው። ረመዷን የወር ስም እንጂ የጾም ስም አይደለም። “ረመዷን” رَمَضَان ማለት “ድርቀት” “ሞቃታማ” ማለት ነው።

ነገር ግን በክርስትና ያሉት ሰባቱ አፅማዋት ማለትም ፅጌ፣ ገና፣ ነነዌ፣ ሁዳዴ፣ ሰኔ፣ፍልሰታ እና እሮብና አርብ የቤተክርስቲያን መሪዎች ቀስ በቀስ በጊዜ ሂደት የደነገጓቸው ሰው ሠራሽ ሕግ እንጂ የመለኮት ትእዛዞች አይደሉም። የነነዌ ጾምም ለነነዌ ሰዎች ለሶስት ቀን የተሰጠ እንጂ አማኞች እንዲጾሙ የታዘዘበት አንቀጽ አይደለም።
በእርግጥም አላህ ለቀደሙት ነቢያት የጾም መርሕ ደንግጎ እንደነበር በተከበረ ቃሉ ነግሮናል። ነገር ግን የአላህ ጥንታዊ ነቢያት የተሰጣቸው ወሕይ የተዋቀረበት አንጓ፣ የተናገሩበት ቋንቋ፣ የመልዕክቱ ምጥቀት ሆነ የቃላቱ ልቀት በዘመናችን እንደሌሉ የታሪክ ምሁራን ያትታሉ፥ ምክንያቱም ከመለኮት የመጣውን እውነት ከሰው ትምህርት ጋር በመጨመር ቀላቅለውታል፤ ከመለኮት የመጣውን እውነት በመቀነስ ደብቀውታል። በዚህም ጾም መቼ እንደሚፃም፣ እንዴት እንደሚፆም፣ ለምን እንደሚፆም፣ ከምን እንደሚጾም ሥረ-መሠረታዊ ጭብጥ በባይብል የለም።

በቁርኣን ግን እነዚህ ምክንያቶች ተገልጸዋል። በጾም ማፍጠሪያ ጊዜ መብላት መጠጣት ብቻ ሳይሆን ከሃላል ጥንድ ጋር ተራክቦ ማድረግም ተፈቅዷል፥ መግሪብ አዛን ካለበት እስከ ፈጅር የኾነው ነጩ ክር የተባለው ብርሃን ጥቁሩ ክር ከተባለው ጨለማ እስከሚለይ ድረስ የፈለግነውን የምግብ አይነት እንድንመገብ አምላካችን አላህ ፈቅዶልናል፦
2፥187 *“በጾም ሌሊት ወደ ሴቶቻችሁ መድረስ ለእናንተ ተፈቀደላችሁ፡፡ እነርሱ ለናንተ ልብሶች ናቸው፤ እናንተም ለእነርሱ ልብሶች ናችሁ፡፡ አላህ እናንተ ነፍሶቻችሁን የምትበድሉ መኾናችሁን ዐወቀ፡፡ በእናንተም ላይ ተመለሰላችሁ፤ ከእናንተም ይቅርታ አደረገ፡፡ አሁን ተገናኙዋቸው፡፡ አላህም ለእናንተ የጻፈላችሁን ነገር ልጅን ፈልጉ፡፡ “ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር ለእናንተ እስከሚገልጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ ጠጡም”፡፡ ከዚያም ጾምን እስከ ሌሊቱ ድረስ ሙሉ”*፡፡ أُحِلَّ لَكُمْ لَيْلَةَ الصِّيَامِ الرَّفَثُ إِلَىٰ نِسَائِكُمْ ۚ هُنَّ لِبَاسٌ لَّكُمْ وَأَنتُمْ لِبَاسٌ لَّهُنَّ ۗ عَلِمَ اللَّهُ أَنَّكُمْ كُنتُمْ تَخْتَانُونَ أَنفُسَكُمْ فَتَابَ عَلَيْكُمْ وَعَفَا عَنكُمْ ۖ فَالْآنَ بَاشِرُوهُنَّ وَابْتَغُوا مَا كَتَبَ اللَّهُ لَكُمْ ۚ وَكُلُوا وَاشْرَبُوا حَتَّىٰ يَتَبَيَّنَ لَكُمُ الْخَيْطُ الْأَبْيَضُ مِنَ الْخَيْطِ الْأَسْوَدِ مِنَ الْفَجْرِ ۖ ثُمَّ أَتِمُّوا الصِّيَامَ إِلَى اللَّيْلِ ۚ وَلَا تُبَاشِرُوهُنَّ وَأَنتُمْ عَاكِفُونَ فِي الْمَسَاجِدِ ۗ تِلْكَ حُدُودُ اللَّهِ فَلَا تَقْرَبُوهَا ۗ كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ آيَاتِهِ لِلنَّاسِ لَعَلَّهُمْ يَتَّقُون

አላህ የሚጾመውን ወንድ ባሪያውን “ሷኢሚን” صَّآئِمِين ሲላቸው የምትጾመውን ሴት ባሪያውን ደግሞ “ሷኢማት” صَّآئِمَٰت ብሎ ይጠራቸዋል። አላህ ሷኢሚን እና ሷኢማት ከሚላቸው ባሮቹ ያድርገን! አሚን።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም