ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
58.4K subscribers
68 photos
69 videos
19 files
1.72K links
ዳዒ ወሒድ በኢሥላም እና በክርስትና መካከል ያለውን ልዩነት እና አንድነት በንጽጽር የሚያስቀምጥ ወንድም ነው። ለዚህም የቋንቋ፣ የሰዋስው፣ የዐውድ፣ የተዛማች እና የሥነ አመክንዮ ሙግት በማቅረብ የሚታወቅ ተሟጋች እና ጦማሪ ነው። ለሙግቱ ነጥብ በዋነኝነት የሚጠቀምባቸው ቋንቋ ዐማርኛ፣ ግዕዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ዐረቢኛ፣ ዕብራይስጥ እና ግሪክ ናቸው። መልካም የንባብ፣ የጥናት፣ የማነጻጸር ጊዜ ይሁንልዎ!
Download Telegram
ነጥብ አምስት
"ሐጅ"
“ሐጅ” حَجّ የሚለው ቃል “ሐጀ” حَجَّ ማለትም “ጎበኘ” ከሚል ሥርወ-ቃል የተገኘ ሲሆን “ጉብኝት”pilgrimage” ማለት ነው፤ “ሐጅ” መደበኛ ዐብይ ጉብኝት ሲሆን “ዑምራ” عُمْرَة ደግሞ መደበኛ ያልሆነ ንዑስ ጉብኝት ነው፦
2፥158 *ሶፋና መርዋ ከአላህ ምልክቶች ናቸው፤ “ቤቱን በሐጅ ወይም በዑምራህ ሥራ የጎበኘ” ሰው በሁለቱ መካከል በመመላለሱ በእርሱ ላይ ኃጢአት የለበትም*፡፡ إِنَّ الصَّفَا وَالْمَرْوَةَ مِن شَعَائِرِ اللَّهِ ۖ فَمَنْ حَجَّ الْبَيْتَ أَوِ اعْتَمَرَ فَلَا جُنَاحَ عَلَيْهِ أَن يَطَّوَّفَ بِهِمَا

“የጎበኘ” ለሚለው ቃል የገባው “ሐጀ” حَجَّ መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል፤ የታወቁ ቀኖች 12ኛ ወር- ዙል-ሒጃህ ላይ የመጀመሪያዎቹ ዐሥሩ ሌሊቶች ናቸው። አላህ በዚህ ወቅት ቤቱን እንዲጎበኙ ያዘዘው ለኢብራሂም ነው፦
22፥27 *አልነውም፡- በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትዕዛዝ ጥራ*፡፡ እግረኞች ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎችም ሁሉ ላይ ሆነው ይመጡሃልና፡፡ وَأَذِّن فِي النَّاسِ بِالْحَجِّ يَأْتُوكَ رِجَالًا وَعَلَىٰ كُلِّ ضَامِرٍ يَأْتِينَ مِن كُلِّ فَجٍّ عَمِيقٍ
22፥26 *ለኢብራሂምም የቤቱን ስፍራ መመለሻ ባደረግንለት ጊዜ «በእኔ ምንንም አታጋራ፣ ቤቴንም ለሚዞሩት፣ ለሚቆሙበት፣ ለሚያጎነብሱት እና በግንባራቸውም ለሚደፉት ንጹሕ አድርግላቸው» ባልነው ጊዜ አስታውስ*፡፡ وَإِذْ بَوَّأْنَا لِإِبْرَاهِيمَ مَكَانَ الْبَيْتِ أَن لَّا تُشْرِكْ بِي شَيْئًا وَطَهِّرْ بَيْتِيَ لِلطَّائِفِينَ وَالْقَائِمِينَ وَالرُّكَّعِ السُّجُودِ

“ለሚዞሩት” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ሊጧዒፊነ” لِلطَّائِفِينَ መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል፤ “ጠዋፍ” طَواف የሚለው ቃል “ጧፈ” طَافَ ማለትም “ዞረ” ከሚለው ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ዙረት” ማለት ነው፤ ቤቱን በመጎብኘት ሰባት ጊዜ መዞር አምላካችን አላህ ለኢብራሂም የሰጠው ትእዛዝ ነው፦
22፥29 ከዚያም እንደ ጠጉርና ጥፍር ያሉትን ትርፍ አካላቸውንና ዕድፋቸውን ያስወግዱ፡፡ ስለቶቻቸውንም ይሙሉ፤ *በጥንታዊውም ቤት ይዙሩ*፡፡ ثُمَّ لْيَقْضُوا تَفَثَهُمْ وَلْيُوفُوا نُذُورَهُمْ وَلْيَطَّوَّفُوا بِالْبَيْتِ الْعَتِيقِ

“ይዙሩ” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “የጠወፉ” يَطَّوَّفُوا መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል፤ ቤቱን የሚዞሩት ዘዋሪዎች ደግሞ “ጧዒፍ” طَآئِف ይባላሉ፦
2፥125 ቤቱንም ለሰዎች መመለሻ እና ጸጥተኛ ባደረግን ጊዜ አስታውስ፡፡ ከኢብራሂምም መቆሚያ መስገጃን አድርጉ፡፡ *ወደ ኢብራሂም እና ወደ ኢስማዒልም ቤቴን “ለዘዋሪዎቹ”፣ ለተቀማጮቹም ለአጎንባሾች ሰጋጆቹም አጥሩ ስንል ቃል ኪዳን ያዝን*፡፡ وَإِذْ جَعَلْنَا الْبَيْتَ مَثَابَةً لِّلنَّاسِ وَأَمْنًا وَاتَّخِذُوا مِن مَّقَامِ إِبْرَاهِيمَ مُصَلًّى ۖ وَعَهِدْنَا إِلَىٰ إِبْرَاهِيمَ وَإِسْمَاعِيلَ أَن طَهِّرَا بَيْتِيَ لِلطَّائِفِينَ وَالْعَاكِفِينَ وَالرُّكَّعِ السُّجُودِ

አምላካችን አላህ ለሁሉም ሕዝቦች የሚዞሩባት ቂብላህ እና ወደ እርሱ መስዋዕት ማቅረብን ደንግጓል፦
2፥148 *“ለሁሉም እርሱ የሚያዞርባት አግጣጫ አለችው”*። وَلِكُلٍّ وِجْهَةٌ هُوَ مُوَلِّيهَا
22፥34 *ለሕዝብም ሁሉ ወደ አላህ መስዋዕት ማቅረብን ደነገግን*፡፡ وَلِكُلِّ أُمَّةٍ جَعَلْنَا مَنسَكًا لِّيَذْكُرُوا اسْمَ اللَّهِ عَلَىٰ مَا رَزَقَهُم مِّن بَهِيمَةِ الْأَنْعَامِ

ከነቢያችን"ﷺ" በፊት ያሉት ቂብላህ የሚቀጣጩበት የአላህ ቤት መስጂዱል አቅሳ ስለነበር ምናልባት የሚጎበኙት ያንን ቤት ይሆናል፥ ሆነም ቀረ ጉብኝት የተጀመረው በነቢያችን"ﷺ" ሳይሆን በጥንቱ ነቢይ በኢብራሂም ዘመን ነው። ስለዚህ የኢሥላም ማዕዘን የሆነው ሐጅ ኢሥላም እስካለ ድረስ ከጥንት ጀምሮ አለ ማለት ነው።
እንግዲህ አምስቱ የኢሥላም ምሰሶች ከጥንት ጀምሮ ያሉ ወደፊትም የሚኖሩ ዐቂደቱል ረባኒያህ ናቸው። ከእሥልምና ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከእርሱ ተቀባይ የለውም፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው። ያ አዩሀል ሙሽሪኩን የተውበት በሩ ሳይዘጋ ወደ ዲኑል ኢሥላም ኑ፦
3፥85 *”ከእሥልምና ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከእርሱ ተቀባይ የለውም”፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው*፡፡ وَمَن يَبْتَغِ غَيْرَ ٱلْإِسْلَٰمِ دِينًۭا فَلَن يُقْبَلَ مِنْهُ وَهُوَ فِى ٱلْـَٔاخِرَةِ مِنَ ٱلْخَٰسِرِينَ

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
መመሳሰል

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

4፥144 *"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከምእምናን ሌላ ከሓዲዎችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ*፤ ለአላህ በእናንተ ላይ ግልጽ ማስረጃዎችን ልታደርጉ ትፈልጋላችሁን? يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَتَّخِذُوا الْكَافِرِينَ أَوْلِيَاءَ مِن دُونِ الْمُؤْمِنِينَ ۚ أَتُرِيدُونَ أَن تَجْعَلُوا لِلَّهِ عَلَيْكُمْ سُلْطَانًا مُّبِينًا

አምላካችን አላህ ከሰው ጋር በሚኖረን ማሕበራዊ ዘይቤ እንዴት መኗኗር እንዳለብን እንዲህ ይነግረናል፦
4፥36 *አላህንም አምልኩ፤ በእርሱም ምንንም አታጋሩ፡፡ በወላጆች፣ በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞችም፣ በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በሩቅ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም፣ እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው መልካምን ሥሩ*፤ አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም፡፡ وَاعْبُدُوا اللَّهَ وَلَا تُشْرِكُوا بِهِ شَيْئًا ۖ وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا وَبِذِي الْقُرْبَىٰ وَالْيَتَامَىٰ وَالْمَسَاكِينِ وَالْجَارِ ذِي الْقُرْبَىٰ وَالْجَارِ الْجُنُبِ وَالصَّاحِبِ بِالْجَنبِ وَابْنِ السَّبِيلِ وَمَا مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ ۗ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ مَن كَانَ مُخْتَالًا فَخُورًا
4፥135 *እናንተ ያመናችሁ ሆይ! *በትክክል ፍትሕ ቀዋሚዎች በራሳችሁ ወይም በወላጆች እና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሀብታም ወይም ድኻ ቢኾን አላህ በእነርሱ ከእናንተ ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ እንዳታደሉም ዝንባሌን አትከተሉ፡፡ ብታጠምሙም ወይም መመስከርን ብትተው አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው*፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُونُوا قَوَّامِينَ بِالْقِسْطِ شُهَدَاءَ لِلَّهِ وَلَوْ عَلَىٰ أَنفُسِكُمْ أَوِ الْوَالِدَيْنِ وَالْأَقْرَبِينَ ۚ إِن يَكُنْ غَنِيًّا أَوْ فَقِيرًا فَاللَّهُ أَوْلَىٰ بِهِمَا ۖ فَلَا تَتَّبِعُوا الْهَوَىٰ أَن تَعْدِلُوا ۚ وَإِن تَلْوُوا أَوْ تُعْرِضُوا فَإِنَّ اللَّهَ كَانَ بِمَا تَعْمَلُونَ خَبِيرًا

እዚህ አንቀጽ ላይ “ተዕዲሉ” تَعْدِلُوا የሚለው ቃል ይሰመርበት፤ ይህ ቃል የስም መደቡ “ዐድል” عَدْل ሲሆን “ፍትሕ” ማለት ነው፤ ፍትሕ ለአላህ ፍራቻ ተብሎ እና አላህ በምንሠራው ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው ተብሎ የሚደረግ ነው። ይህ ለአላህ ተብሎ የሚደረግ ፍትሕ ለአማንያን ብቻ ሳይሆን ለከሃድያንም ጭምር ነው፦
60፥8 *ከእነዚያ በሃይማኖት ካልተጋደሏችሁ፣ ከአገሮቻችሁም ካላወጡዋችሁ ከሓዲዎች መልካም ብትውሉላቸው እና ወደ እነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም፡፡ አላህ ትክክለኞችን ይወዳልና*፡፡ لَّا يَنْهَاكُمُ اللَّهُ عَنِ الَّذِينَ لَمْ يُقَاتِلُوكُمْ فِي الدِّينِ وَلَمْ يُخْرِجُوكُم مِّن دِيَارِكُمْ أَن تَبَرُّوهُمْ وَتُقْسِطُوا إِلَيْهِمْ ۚ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُقْسِطِينَ

ዲናችንን አክብረው ካልተጋደሉንና ካላሳደዱን ከሃድያን ጋር በዝምድና፣ በባልደረባ፣ በጉርብትና መልካም መዋዋል እና ማስተካከል ይቻላል፤ “ብታስተካክሉ” ለሚለው ቃል አሁንም የገባው “ቱቅሢጡ” َتُقْسِطُوا ሲሆን የስም መደቡ “ቂሥጥ” قِسْط ማለትም “ፍትሕ” ነው፤ ለአላህ ብለን ስናስተካክል “ሙቅሢጢን” مُقْسِطِين ማለትም “ፍትኸኞችን” “ትክክለኞች” “አስተካካዮች” እንሰኛለን፤ አላህ ሙቅሢጢንን ይወዳልና፦
49፥9 *በነገሩ ሁሉ አስተካክሉም፡፡ አላህ አስተካካዮችን ይወዳልና*፡፡ وَأَقْسِطُوا ۖ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُقْسِطِينَ
ነገር ግን ከዚያ አልፎ ወደ ኩፍርና ሺርክ ሊያስገባ የሚችለውን ሥራ ከሌላ እምነት ጋር መሥራት ከኢሥላም ያስወጣል፦
ሱነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 15, ሐዲስ 311
ሰሙራህ ኢብኑ ጁንዱብ እንደተረከው፦ "የአላህ መልእክተኛ"ﷺ" እዲህ አሉ፦ *"ከሙሽሪክ ጋር ያበረ እና የተኗኗረ እርሱን(ሙሽሪኩን) ይመስላል"*። أَمَّا بَعْدُ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ مَنْ جَامَعَ الْمُشْرِكَ وَسَكَنَ مَعَهُ فَإِنَّهُ مِثْلُهُ ‏
ሱነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 12, ሐዲስ 34
ዐብደላህ ኢብኑ ዑመር እንደተረከው፦ "የአላህ መልእክተኛም አሉ፦ *"ከማንኛውም ሕዝብ ጋር የሚመሳሰል ከእነርሱ ነው"*። عَنِ ابْنِ عُمَرَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ مَنْ تَشَبَّهَ بِقَوْمٍ فَهُوَ مِنْهُمْ

ስለዚህ የማይመለከተን ነገር ውስጥ ለመመሳሰል ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያንና የጥምቀት ቦታ ማጽዳት፥ ታቦት መሸኘት፣ በዓላቸውን ማክበር፣ መዝሙራቸውን መዘመር ከኢሥላም አጥር ያስወጣል። አንዳንድ ቂሎች፦ "ለመረዳዳት ነው" ይሉናል፤ በጋራ እሴት ማለትም በልማት፣ በጉርብትና፣ በአስኳላ ትምህርት፣ በሰብአዊነት ወዘተ... ልንረዳዳ እንችላለን፥ ነገር ግን በእምነት ጉዳይ እረዳቶች አድርገን ከያዝናቸው ከእነርሱ እንደ አንዱ ነን፦
4፥144 *"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከምእምናን ሌላ ከሓዲዎችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ*፤ ለአላህ በእናንተ ላይ ግልጽ ማስረጃዎችን ልታደርጉ ትፈልጋላችሁን? يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَتَّخِذُوا الْكَافِرِينَ أَوْلِيَاءَ مِن دُونِ الْمُؤْمِنِينَ ۚ أَتُرِيدُونَ أَن تَجْعَلُوا لِلَّهِ عَلَيْكُمْ سُلْطَانًا مُّبِينًا
5፥51 *እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፡፡ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ ከእናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርሱ ከእነርሱ ነው*፡፡ አላህ አመጸኞችን ሕዝቦች አያቀናም፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَتَّخِذُوا الْيَهُودَ وَالنَّصَارَىٰ أَوْلِيَاءَ ۘ بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ ۚ وَمَن يَتَوَلَّهُم مِّنكُمْ فَإِنَّهُ مِنْهُمْ ۗ إِنَّ اللَّهَ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الظَّالِمِينَ
ሱነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 24, ሐዲስ 2939
ዓኢሻህ"ረ.ዐ." እንደተረከችው፦ "የአላህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ *"የሙሽሪክ እርዳታ አያስፈልገንም"* عَنْ عَائِشَةَ، قَالَتْ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ إِنَّا لاَ نَسْتَعِينُ بِمُشْرِكٍ ‏

ስለዚህ፦ "ገና እኛ ይመለከተናል፣ የጋራ በዓል አለን፣ የጋራ መዝሙር እናውጣ" እያሉ የሚያስተምሩ ኡስታዞች በግል ሊመከሩ ይገባል። አሻፈረኝ ካሉ በዑማው ላይ የሚረጩትን ፈሳድ ከነስማቸው መጋለጥ አለበት። ዝም ከተባሉ ትንሽ ቆይተው እምነታቸውንና አስተምህሮታቸውንም እንቀበል እንዳይሉን እሰጋለው። አንድነት እናመጣለን በሚል ሽፋን ዑማውን የዝቅተኝነት ስሜት በማከናነብ ከድጡ ወደ ማጡ አትክተቱት። ኢትዮጵያዊነት በመሆን እንጂ በመምሰል አይለካም። ምንም ሳይገባውና ሳያውቀው የሚሳተፈውን ሙሥሊም በትህትና የማስጠንቀቅ የሁላችንም ሃላፍትና ነው። ይህንን መልእክት ለሁሉም በማስተላለፍ ዲናዊ ግዴታዎን ይወጡ! አላህ ለሁላችንም ሂዳያ ይስጠን! አሚን።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
የኢየሱስ ፈጣሪ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

5፥117 «በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል፦ *ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን አምልኩ* ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَآ أَمَرْتَنِى بِهِۦٓ أَنِ ٱعْبُدُوا۟ ٱللَّهَ رَبِّى وَرَبَّكُمْ

በቁርኣን አስተምህሮት የተፈጠረ ማንነትና ምንነት ተመልሶ አይፈጥርም። የሚፈጠርን ምንም መፍጠር የማይችልን ማንነትና ምንነት ማምለክ በአላህ ላይ ማጋራት ነው፦
7፥191 *"ምንንም የማይፈጥሩትንና እነርሱም የሚፈጠሩትን በአላህ ያጋራሉን?* أَيُشْرِكُونَ مَا لَا يَخْلُقُ شَيْئًا وَهُمْ يُخْلَقُونَ

ኢየሱስ ሊያርግ ሲል የፈጠረውን አንዱን አምላክ "ፈጣሪዬ" ብሏል፦
ዮሐንስ 20፥17 *"ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ "ወዳባቴ ወዳባታችምሁ "ወደ ፈጣሪዬ" ወደ ወደ ፈጣሪያችሁ ዓርጋለው" ብለሽ ንገሪያቸው"*። (አንድምታ ትርጓሜ)

ካረገም በኃላ የፈጠረውን አንዱን አምላክ "ፈጣሪዬ" ብሏል፦
ራእይ 3፥2 *"በፈጣሪዬ ዘንድ ሥራህን ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም"*። (አንድምታ ትርጓሜ)

"ፈጣሪ" በሚለው ቃል ላይ "ዬ" የሚል አገናዛቢ ተውላጠ-ስም መድረሻ ቅጥያ ሆኖ ገብቷል፤ "ዬ" የመጀመሪያ መደብ ነጠላ አገናዛቢ ተውላጠ-ስም "የእኔ" የሚለው የሚወክል ህቡዕ ምጻረ-ቃል ነው። ኢየሱስ፦ "የእኔ ፈጣሪ" ብሎ ካለ የኢየሱስ ሙሉ "እኔነት" ፈጣሪ አለው ማለት ነው። የኢየሱስን ሙሉ ሁለንተናዊ እኔነት የፈጠረው አብ ነው። "ፈጣሪያችን" በማለት ፋንታ "ፈጣሪዬ እና ፈጣሪያችሁ" ማለቱ አንዳች የትርጉም ልዩነት የለውም። ይህንን በአንድ ጥቅስ ማየት ይቻላል፦
ዘፍጥረት 43፥23 እርሱም አላቸው፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ አትፍሩ፤ *አምላካችሁ እና የአባታችሁ አምላክ* በዓይበታችሁ የተሰወረ ገንዘብ ሰጣችሁ፤ ብራችሁስ ደርሶኛል።

“አምላካችሁ እና የአባታችሁ አምላክ” ስለተባለ አንዱ አምላክ ለአባታቸው ለያዕቆብ እና ለልጆቹ አምላክነቱ ይለያልን? "እና" በሚልስ አያያዥ መስተጻምር ስለተለየ ያዕቆብ እና ልጆቹ ምንነታቸው ይለያያልን? በፍጹም! አንዱ አምላክ ለያዕቆብ እና ለልጆቹ ሁለንተናዊ እኔነት አምላክ እንደሆነ ሁሉ ለኢየሱስ እና ለሐዋርያት ሁለንተናዊ እኔነት ፈጣሪ ነው።
ስለዚህ ኢየሱስ የተፈጠረ ማንነትና ምንነት ከሆነ ኢየሱስን የፈጠረውን የኢየሱስ ፈጣሪ በብቸኝነት አምልኩት። አላህ ዒሣን እንዲናገር ያዘዘው ቃል፦ "ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን አምልኩ" ማለትን ነው፤ ከዚያ አልፎ ግን ፍጡርን በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፦
5፥117 «በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል፦ *ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን አምልኩ* ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَآ أَمَرْتَنِى بِهِۦٓ أَنِ ٱعْبُدُوا۟ ٱللَّهَ رَبِّى وَرَبَّكُمْ
5፥72 እነዚያ «አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ *አልመሲህም አለ፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን አምልኩ*፡፡» እነሆ! *በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በእርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት*፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡ لَقَدْ كَفَرَ ٱلَّذِينَ قَالُوٓا۟ إِنَّ ٱللَّهَ هُوَ ٱلْمَسِيحُ ٱبْنُ مَرْيَمَ ۖ وَقَالَ ٱلْمَسِيحُ يَٰبَنِىٓ إِسْرَٰٓءِيلَ ٱعْبُدُوا۟ ٱللَّهَ رَبِّى وَرَبَّكُمْ ۖ إِنَّهُۥ مَن يُشْرِكْ بِٱللَّهِ فَقَدْ حَرَّمَ ٱللَّهُ عَلَيْهِ ٱلْجَنَّةَ وَمَأْوَىٰهُ ٱلنَّارُ ۖ وَمَا لِلظَّٰلِمِينَ مِنْ أَنصَارٍۢ

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
በስጋ ተገለጠ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

5፥72 እነዚያ *«አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው»* ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ

በክርስትና ስልታዊ ሥነ-መለኮት”systematic theology” የአምላክ ሰው መሆን አስተምህሮት “ተሰግዎት”Incarnation” ሲባል በአገራችን “ሚስጥረ-ስጋዌ” ይሉታል፣ “ስጋዌ” የሚለው ቃል "ስግው” ማለትም “ስጋ” ከሚለው የመጣ ነው፣ መለኮት በትስብእት ተገለጠ ብለው ድምዳሜ ላይ ያደረሳቸው ይህ ጥቅስ ነው፦
1 ጢሞቴዎስ 3፥16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ *"እርሱ በሥጋ የተገለጠ"*፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ *"በክብር ያረገ"*። (NIV)

እዚህ አንቀጽ ላይ በ 330 ዓመተ-ልደት የተዘጋጀው ኮዴክስ ሳይናቲከስ እና በ 350 ዓመተ-ልደት የተዘጋጀው ኮዴክስ ቫቲካነስ ላይ እንዲህ ተቀምጧል፦
"እርሱ በሥጋ የተገለጠ" Ὃς ἐφανερώθη ἐνσαρκί,

"ሆስ" Oς ማለት አንጻራዊ ተውላጠ-ስም ሲሆን "እርሱ" ማለት ነው፤ "እርሱ" የተባለው "ክርስቶስ" ነው። ነገር ግን በ 400 ዓመተ-ልደት የተዘጋጀው ኮዴክስ አሌክሳንድሪየስ ላይ ሌላ ተቃራኒ ቃል ተቀምጧል፦
"አምላክ በሥጋ የተገለጠ" Θς ἐφανερώθη ἐνσαρκί,

በግሪክ ኮይኔ አስራ አምስተኛው ፊደል "ሆሞክሮን" O መሃል ላይ "አግድም ሰረዝ" - ሲጨመርበት ስምተኛው ፊደል "ቴታ" Θ ይሆናል፤ በአስራ ስምንተኛው ፊደል "ሲግማ" ς መነሻ ላይ ሆሞክሮን ወይንም ቴታ ሲመጡ የትርጉም ልዩነት አላቸው፤ ይህም "ሆስ" Oς ማለትም "ሆሞክሮን ሲግማ" የነበረው "ቴስ" Θς ማለትም "ቴታ ሲግማ" ይሆናል ማለት ነው፤ "ቴስ" Θς የሚለው "ቴኦስ" θεός ለሚለው ምጻረ ቃል ሲሆን "አምላክ" ማለት ነው። እንግዲህ ኮዴክስ አሌክሳንድሪየስ ላይ "ሆስ" Oς (እርሱ) የነበረው "ቴስ" Θς (አምላክ) በማለት በርዘው የትርጉም ልዩነት አምጥተዋል። ሲበርዙ የአምላክ ንግግር ያልሆነውን የጳውሎስንም ንግግር አላስተረፉትም።
እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ 1690 ዓመተ-ልደት አይዛክ ኒውተን ሁለት የባይብል ብርዘት ካላቸው መካከል የመጀመሪያው 1 ጢሞቴዎስ 3፥16 ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 1 ዮሐንስ 5፥7 ናቸው። የሮሙ ቢሾፕ ጄሮም በ 382 ዓመተ-ልደት ባዘጋጀው በላቲን ቩልጌት ላይ ሆነ፥ በ 1611 ዓመተ-ልደት በተዘጋጀው በኪንግ ጀምስ ቨርዥን ላይ፦ "አምላክ በሥጋ የተገለጠ" የሚለውን አስቀምጠውታል። ይህ ስህተት ነው፤ ምክንያቱም 5800 የሚደርሱ የአዲስ ኪዳን የግሪክ እደ-ክታባት አሉ፤ ከኮዴክስ አሌክሳንድሪየስ ውጪ ሁሉም "ቴስ" የሚለውን አይጨምሩም።

ሲቀጥል ብዙ የአዲስ ኪዳን ንባባት፦ አምላክ ተገለጠ ሳይሆን የአምላክ ልጅ ተገለጠ ወይም ሰው ተገለጠ ነው የሚሉት፦
1 ዮሐንስ 3፥9 ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ *"የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ"*። the Son of God was manifested.
የሐዋርያት ሥራ 2፥22 የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም *ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ"*፤

እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከአንዱ እግዚአብሔር የተገለጠው ሰው ነው፤ እግዚአብሔር ከተገለጠ "ከእግዚአብሔር ዘንድ እግዚአብሔር ተገለጠ" ትርጉም ይሰጣል? ግን የተገለጠ ሰው ነበረ። ስለዚህ በስጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ የተባለው ሰው ነው።
ሢሰልስ አንቀጹ፦ "በክብር ያረገ" ይላል። "እግዚአብሔር በስጋ ተገለጠ፥ እግዚአብሔር በክብር ያረገ" ትርጉም ይሰጣልን? ምክንያቱም ዐራጊው ማንነት የሚያርገው ወደ እግዚአብሔር ነው፤ ዐርጎም የሚቀመጠው በእግዚአብሔርም ቀኝ ነው፦
ማርቆስ 16፥19 ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ *ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ*።
ዮሐንስ 17፥11 *"እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ"*።
ዮሐንስ 20፥17 *እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ"* ብለሽ ንገሪአቸው፥ አላት።

ልብ አድርጉ ኢየሱስ እራሱን በመጀመሪያ መደብ "እኔ" እያለ እግዚአብሔር ደግሞ በሁለተኛ መደብ "አንተ" እያለ በጸሎት ሲናነጋግረው ተመልከቱ፤ ዓራጊው ኢየሱስ ሲሆን ከሚያርግበት ከእግዚአብሔር ማንነት ለመለየት "ወደ" የሚል መስተዋድድ ተጠቅሟል፤ "ወደ አምላኬ ዓርጋለሁ" የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት፤ "አምላኬ" ማለቱ የሚያርገው ማንነት አምላክ አለው። እግዚአብሔር ከሆነ ወደ እግዚአብሔር የሚያርገው እግዚአብሔር አምላክ አለውን? አዎ! ብሎ ማመን ምን አይነት ድራማና ቁማር ነው? ፈጣሪ ፍጡር ሆኖ በተፈጠረ ማንነቱ ተገለጠ ማለት ክህደት ነው። እነዚያ፦ "አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው" ያሉ በእርግጥ ካዱ፦
5፥72 እነዚያ *«አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው»* ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ
5፥17 እነዚያ *"አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው"* ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ لَّقَدْ كَفَرَ الَّذِينَ قَالُوا إِنَّ اللَّهَ هُوَ الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
ቁርኣን ይጋጫልን?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

4፥82 *ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በእርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር*፡፡ أَفَلَا يَتَدَبَّرُونَ الْقُرْآنَ ۚ وَلَوْ كَانَ مِنْ عِندِ غَيْرِ اللَّهِ لَوَجَدُوا فِيهِ اخْتِلَافًا كَثِيرًا

“ኢኽቲላፍ” ٱخْتِلَٰف ማለት “መለያየት” “ግጭት”contradiction” ማለት ነው፤ የአእምሮ ባለቤቶችም ቁርኣን የአላህ ንግግር ብቻ መሆኑን አንዳች መለያየት እንደሌለበት እንዲያስተነትኑ ይጋብዛል፤ የቁርኣን ተናጋሪ የዐለማቱ ጌታ አላህ ነው፤ ቁርኣን ከአላህ ሌላ ከሆነ ማንነትና ምንነት ቢገኝ ኖሮ በውስጡ ብዙ መለያየት በተገኘ ነበር፦
4፥82 *ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በእርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር*፡፡ أَفَلَا يَتَدَبَّرُونَ الْقُرْآنَ ۚ وَلَوْ كَانَ مِنْ عِندِ غَيْرِ اللَّهِ لَوَجَدُوا فِيهِ اخْتِلَافًا كَثِيرًا

ከዚህ በተቃራኒው ክርስቲያን ሚሽነሪዎች፦ "ቁርኣን እርስ በእርሱ ይጋጫል" ብለው በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ይዶሶክራሉ፤ ይህ ትችት ባይብል እርስ በእርሱ ስለሚጋጭ ልከክልህ እከክልኝ ነገር ነው። እስቲ ይጋጫል ያሉትን አናቅጽ በጥራዝ ጠለቅ ዕውቀት እናስተንትን፦
ጥያቄውም፦ አላህ ቀድሞ የፈጠረው ምድርን ወይስ ሰማይን?
A. ምድርን
ምድርን ፈጥሮ በምድር ያለውን ከፈጠረ በኃላ ሰማይን ፈጠረ፦
2፥29 *"እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው"*፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡ هُوَ الَّذِي خَلَقَ لَكُم مَّا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا ثُمَّ اسْتَوَىٰ إِلَى السَّمَاءِ فَسَوَّاهُنَّ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ ۚ وَهُوَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ

B. ሰማይን
ሰማይን ገንብቶ ከፈጠረ በኃላ ምድርን ፈጠረ፦
79፥27 *"ባፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይንስ ሰማይ? አላህ ገነባት"*፡፡ أَأَنتُمْ أَشَدُّ خَلْقًا أَمِ السَّمَاءُ ۚ بَنَاهَا
79፥30 *"ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት"*፡፡ وَالْأَرْضَ بَعْدَ ذَٰلِكَ دَحَاهَا

ነጥብ አንድ
"ምድር"
አምላካችን አላህ ምድርን ፈጥሮ በምድር ያለውን ፈጠረ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው፦
2፥29 *"እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው"*፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡ هُوَ الَّذِي خَلَقَ لَكُم مَّا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا ثُمَّ اسْتَوَىٰ إِلَى السَّمَاءِ فَسَوَّاهُنَّ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ ۚ وَهُوَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ

እዚህ አንቀጽ ላይ፦ "በምድር ያለውን ከፈጠረ በኃላ ሰማይ ፈጠረ" የሚል ሽታው የለውም። ከዚህ ይልቅ "ወደ ሰማይ አሰበ" የሚል ሃይለ-ቃል አለ፤ "ኢላ"إِلَى ማለትም "ወደ" የሚለው መስተዋድድ መግባቱ በራሱ ሰማይ እንደነበረች ያሳያል። "ወደ" ፒያሳ አስቤአለው ማለት ፒያሳን ፈጠርኳት ማለት አይደለም፤ ፒያሳ ሳትኖር ወደ ፒያሳ ማቅናት አይቻልም። ሰማይ በህልውና ጭስ ኾና ሳለች አሰበ፦
41፥11 *"ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ኾና ሳለች አሰበ፡፡ ለእርሷም ለምድርም «ወዳችሁም ኾነ ወይም ጠልታችሁ ኑ» አላቸው"*፡፡ «ታዛዦች ኾነን መጣን» አሉ፡፡ ثُمَّ اسْتَوَىٰ إِلَى السَّمَاءِ وَهِيَ دُخَانٌ فَقَالَ لَهَا وَلِلْأَرْضِ ائْتِيَا طَوْعًا أَوْ كَرْهًا قَالَتَا أَتَيْنَا طَائِعِينَ

"ሳለች" የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት፤ ለሰማይም ለምድርም፦ ወዳችሁም ኾነ ወይም ጠልታችሁ ኑ" ማለቱ በራሱ ሰማይ እንደነበረች መረዳት ይቻላል። ከዚያም በጭስ ደረጃ የነበረችውን ሰማይ ሰባት ሰማያት አደረጋቸው፦
41፥12 በሁለት ቀኖችም ውስጥ *"ሰባት ሰማያት አደረጋቸው"*፡፡ فَقَضَاهُنَّ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ فِي يَوْمَيْنِ
2፥29 እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ *"ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው"*፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡ هُوَ الَّذِي خَلَقَ لَكُم مَّا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا ثُمَّ اسْتَوَىٰ إِلَى السَّمَاءِ فَسَوَّاهُنَّ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ ۚ وَهُوَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ
ነጥብ ሁለት
"ከዚያም"
"ሱመ" ثُمَّ ማለትም ከዚያም" የሚለው አያያዥ መስተጻምር ተርቲብ ነው፤ "ተርቲብ" ترتيب ማለት "ቅድመ-ተከተል" ማለት ነው፤ ይህ ቅድመ-ተከተል በሁለት ይከፈላል፤ አንዱ የጊዜ ቅድመ-ተከተል ሲሆን ሁለተኛው የንግግር ቅድመ-ተከተል ነው፤ የንግግር ቅድመ-ተከተል ናሙናዎችን ማየት ይቻላል፦
7፥11 *በእርግጥም ፈጠርናችሁ፥ ከዚያም ቀረጽናችሁ፡፡ ከዚያም ለመላእክት «ለአዳም ስገዱ» አልን*፡፡ ወዲያውም ሰገዱ፡፡ ኢብሊስ ዲያብሎስ ሲቀር ከሰጋጆቹ አልኾነም፡፡ وَلَقَدْ خَلَقْنَاكُمْ ثُمَّ صَوَّرْنَاكُمْ ثُمَّ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ لَمْ يَكُن مِّنَ السَّاجِدِينَ

ይህ አንቀጽ ለአደም እና ለሐዋ ቢሆን ኖሮ በሙተና “ኸለቅናኩማ” خَلَقْنَاكُما “ሰወርናኩማ” صَوَّرْنَاكُما ይሆን ነበር፤ ነገር ግን ከሁለት በላይ እኛን ለማሳየት በጀመዕ “ኸለቅናኩም” خَلَقْنَاكُمْ “ሰወርናኩም” صَوَّرْنَاكُمْ ነው የሚለው፤ ከዚያም ለመላእክት ለአደም ስገዱ አለ፤ በጊዜ ቅድመ-ተከተል ካየነው እኛ ከመፈጠራችን በፊት ነው አላህ ለመላእክት፦ "ለአዳም ስገዱ" ያለው፤ ነገር ግን መስተጻምሩ የገባው የንግግር ቅድመ-ተከተል ለማሳየት ስለሆነ "ፈጠርናችሁ" "ቀረጽናችሁ" በንግግር ይቀድማል፦
6፥153 *«ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ ተከተሉትም፡፡ የጥመት መንገዶችንም አትከተሉ"*፡፡ ከቀጥተኛው መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና፡፡እነሆ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ፡፡» وَأَنَّ هَـٰذَا صِرَاطِي مُسْتَقِيمًا فَاتَّبِعُوهُ ۖ وَلَا تَتَّبِعُوا السُّبُلَ فَتَفَرَّقَ بِكُمْ عَن سَبِيلِهِ ۚ ذَٰلِكُمْ وَصَّاكُم بِهِ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُون
6፥154 *"ከዚያም ለሙሳ በዚያ መልካም በሠራው ላይ ለማሟላት ነገርንም ሁሉ ለመዘርዘር መጽሐፉን ለእስራኤል ልጆች መሪና እዝነት ይኾን ዘንድ ሰጠነው*"፡፡ ثُمَّ آتَيْنَا مُوسَى الْكِتَابَ تَمَامًا عَلَى الَّذِي أَحْسَنَ وَتَفْصِيلًا لِّكُلِّ شَيْءٍ وَهُدًى وَرَحْمَةً لَّعَلَّهُم بِلِقَاءِ رَبِّهِمْ يُؤْمِنُون

"ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ ተከተሉትም" የተባለው ቁርኣን ሲሆን በንግግር ከቁርኣን በኃላ ስለ ተውራት ሲናገር፦ "ከዚያም" የሚል የንግግር ቅድመ-ተከተል ይጠቀማል፤ ያ ማለት ተውራት ከቁርኣን በኃላ መውረዱ ሳይሆን አላህ ስለ ቁርኣን ከተናገረ በኃላ ስለ ተውራት መናገሩ የሚያሳይ ነው፤ በተመሳሳይም አላህ ስለ ምድር ከተናገረ በኃላ ስለ ሰማይ መናገሩ የሚያሳይ ነው። እንደውም "ሱመ" የሚለውን ተርቲብ "እንዲሁ"simultaneously" በሚል ቃል ይመጣል። "እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ "እንዲሁ" ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው" ብለን መረዳት እንችላለን።

ነጥብ ሦስት
"ሰማይ"
አምላካችም አላህ ሰማይን በኀይል ፈጥሯታል፦
79፥27 *"ባፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይንስ ሰማይ? አላህ ገነባት"*፡፡ أَأَنتُمْ أَشَدُّ خَلْقًا أَمِ السَّمَاءُ ۚ بَنَاهَا
51፥47 *"ሰማይንም በኀይል ገነባናት"*፡፡ እኛም በእርግጥ ቻዮች ነን፡፡ وَالسَّمَاءَ بَنَيْنَاهَا بِأَيْدٍ وَإِنَّا لَمُوسِعُونَ
91፥5 *"በሰማይቱም በገነባትም ጌታ*፤ وَالسَّمَاءِ وَمَا بَنَاهَا

"በና" بَنَا የሚለው ቃል "ኸለቀ" خَلَقَ ለሚለው ቃል ተለዋዋጭ ቃል ሆኖ እንደመጣ እሙንና ቅቡል ነው። አላህ ሰማይን ጭስ እንድትሆን አድርጎ ከፈጠረ በኃላ ምድርንም ዘረጋት፦
79፥30 *"ምድርንም ከዚህ በኋላ ዘረጋት"*፡፡ وَالْأَرْضَ بَعْدَ ذَٰلِكَ دَحَاهَا

"ፈጠራት" ሳይሆን "ዘረጋት" ነው የሚለው፤ “ዘረጋት” ተብሎ የገባው ቃል “ደሓሃ” دَحَاهَا ሲሆን “ደሓ” دَحَىٰ ደግሞ በቁርኣን ላይ የመጣው በግስ መደብ እዚህ አንቀፅ ላይ ብቻ ነው፤ “ደሓ” በስም መደብ ሲመጣ “አድ-ደሕያ” الدِّحْية ነው፤ ትርጉሙም “የሰጎን እንቁላል” ማለት ነው፤ አላህ ምድርን “የእንቁላል ቅርጽ አደረጋት”He made the earth egg-shaped” የሚል ትርጉም አለው፤ ይህንን አንዳንድ የእንግሊዝኛ ትርጉም ላይ ይገኛል፦
1.Dr. Kamal Omar Translation
“And the earth, after this stage, He gave it *an oval form”*
2. Ali Unal Translation
“And after that He has spread out the earth in *the egg-shape”*
3. Shabbir Ahmed Translation
“And after that He made the earth *egg-shaped"*.
አላህ ምድርን ለእኛ የዘረጋት በርሷም ውስጥ እንመራ ዘንድ መንገዶችን አደረገልን፦
43፥10 *"እርሱ ያ ምድርን "ለእናንተ" ምንጣፍ ያደረገላችሁ በርሷም ውስጥ ትመሩ ዘንድ ለእናንተ መንገዶችን ያደረገላችሁ ነው"*፡፡ الَّذِي جَعَلَ لَكُمُ الْأَرْضَ مَهْدًا وَجَعَلَ لَكُمْ فِيهَا سُبُلًا لَّعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ
71፥19 *"አላህም ምድርን "ለእናንተ" ምንጣፍ አደረጋት"*፡፡ وَاللَّهُ جَعَلَ لَكُمُ الْأَرْضَ بِسَاطًا

"ለእናንተ" የሚለው ይሰመርበት፤ ለእኛ መንገድ መኪና ስንነዳ ዝርግ ሆኖ የሚታየን ልክ እንደ ምንጣፍ ነው፤ አላህ ሰማይን ከፈጠረ በኃላ ለእኛ የነበረችውን ምድር እንደ ምንጣፍ ዘረጋት። "በዕደ" بَعْدَ ማለትም "ከዚያም" የሚለው ተሳቢ የጊዜ ተውሳከ-ግስ ልክ እንደ "ሱመ" ቅድመ-ተከተል ሲሆን የንግግር ቅድመ-ተከተል ሆኖ ሊመጣ ይችላል፦
68.13 *"ልበ ደረቅን ከዚህ በኋላ ዲቃላን ሁሉ አትታዘዝ*"። عُتُلٍّ بَعْدَ ذَٰلِكَ زَنِيم

እዚህ አንቀጽ ላይ "ልበ ደረቅን እንዲሁ ዲቃላን ሁሉ አትታዘዝ" ተብሎ እንደተቀመጠ ሁሉ "ሰማይንም በኀይል ገነባናት እንዲሁ ምድርንም ዘረጋት" ተብሎ ሊቀመጥ ይችላል።
ስለዚህ ቁርኣን ላይ ግጭት የለም። ይጋጫል የሚል ተሟጋች ካለ ግን ያቀረብነውን ሙግት የሚያስተባብልበት የዐውድ፣ የተዛማች፣ የቋንቋና የሰዋስው ሙግት ማቅረብ ይጠበቅበታል።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሠራም ዐላውቅም

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

43፥43 ያንንም ወደ አንተ የተወረደልህን አጥብቀህ ያዝ፡፡ *አንተ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ነህና*፡፡ فَٱسْتَمْسِكْ بِٱلَّذِىٓ أُوحِىَ إِلَيْكَ ۖ إِنَّكَ عَلَىٰ صِرَٰطٍۢ مُّسْتَقِيمٍۢ

መቼም ሚሽነሪዎች ቆዳዬ ጠበበኝ ብለው የሚያላዝኑት ነገር ቢገርምም የአገራችን ሰዎች ደግሞ እነርሱን በቁርኣን ላይ የሚያነሷቸውን ኂሶች እንደ ገደል ማሚቱ ሲያስተጋቡ ማየት ያስደምማል፤ ሚሽነሪዎች እራሳቸው መጽሐፍት ላይ ያሉትን አበሳና አሳር እንደማይወጡት ስለሚያውቁት በጊዜ ቁርኣን ላይ መደበቁን መርጠዋል፤ የእኛ ጥያቄ ግን ተከድኖ ይብሰል ከተባለ ይኸው ጊዜ አስቆጠረ፤ እኛም ጠቃሚውን ነገር ከማይጠቅም ነገር ጋር ሳይሆን ጠቃሚውን ነገር ከሚጐዳ ነገር ጋር እያነጻጸርነው እንገኛለን። መቼም ስላቅና ፈሊጥ በአሉታዊ ሳይሆን በአውንታዊ ተመልክተን እዳው ገብስ ስለሆነ ሰው እንዲማርበት መልስ እንሰጣለን፤ ወደ ጉዳዩ ስንገባ ነቢያችን”ﷺ” ወሕይ ከመጣላቸው በኃላ በቀጥተኛው መንገድ ላይ እንደሆኑ አምላካችን አላህ ተናግሯል፦
43፥43 ያንንም ወደ አንተ የተወረደልህን አጥብቀህ ያዝ፡፡ *አንተ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ነህና*፡፡ فَٱسْتَمْسِكْ بِٱلَّذِىٓ أُوحِىَ إِلَيْكَ ۖ إِنَّكَ عَلَىٰ صِرَٰطٍۢ مُّسْتَقِيمٍۢ

አላህ ነቢያችን”ﷺ” በቀጥተኛ መንገድ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ጀነት ገብተውም በጀነት ያለው ፀጋ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸዋል፦
108፥1 *እኛ በጣም ብዙ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ*፡፡ إِنَّآ أَعْطَيْنَٰكَ ٱلْكَوْثَرَ

በዚህ አንቀጽ ላይ “በጎ ነገር” ተብሎ የተቀመጠው ቃል “ከውሰር” كَوْثَر ሲሆን በጀነት ውስጥ ያለ ከወተት የነጻና ከማር የጣፈጠ ወንዝ ነው፤ ይህ ከውሰር ለነቢያችን”ﷺ” የተሰጠ ዋስትና ነው፦
ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 47, ሐዲስ 3684
አነስ ኢብኑ ማሊክ እንደተረከው፦ “እኛ ከውሰርን ሰጠንህ” ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ *"በጀነት ወንዝ ነው፤ በጀነት ወንዝ ድንኳኖቹ ከድንጋይ የተሠሩ አየው፤ ጂብሪል ሆይ! ምንድን ነው? አልኩት፤ እርሱም ከውሰር ነው፤ አላህ ለአንተ የሰጠህ” አለኝ"*።
عَنْ أَنَسٍ ‏:‏ ‏(‏ إناَّ، أَعْطَيْنَاكَ الْكَوْثَرَ ‏)‏ أَنَّ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏”‏ هُوَ نَهْرٌ فِي الْجَنَّةِ ‏”‏ ‏.‏ قَالَ فَقَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم ‏”‏ رَأَيْتُ نَهْرًا فِي الْجَنَّةِ حَافَتَاهُ قِبَابُ اللُّؤْلُؤِ قُلْتُ مَا هَذَا يَا جِبْرِيلُ قَالَ هَذَا الْكَوْثَرُ الَّذِي قَدْ أَعْطَاكَهُ اللَّهُ ‏”‏ ‏.‏ قَالَ أَبُو عِيسَى هَذَا حَدِيثٌ حَسَنٌ صَحِيحٌ


ነቢያችን”ﷺ” ጀነት አይደለም መግባት በተጨማሪ የጀነት ጀረጃቸውንም አላህ እንደነገረን ከላይ ያለው አንቀጽ በወፍ በረር ለቅምሻ ያክል በቂ ነው፤ ታዲያ ይህ ዋስትና እያለ አላህ ነቢያችንን”ﷺ” “በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሠራም ዐላውቅም” በል ሲላቸው እውን ሚሽነሪዎች እንደሚሉት "ወደ ፊት የት እንደምንገባ ዐናውቅም" በል ማለታቸውን ያሳያልን? ይህንን የተንሸዋረረና የተወላገደ መረዳት ጥንልልና ጥንፍፍ ባለ መልኩ እንየው፦
46፥9 *ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም፤ በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሠራም ዐላውቅም፤ ወደ እኔ የሚወረደውን እጅግ ሌላን አልከተልም፤ እኔም ግልጽ አስጠንቃቂ እንጅ ሌላ አይደለሁም* በላቸው። قُلْ مَا كُنتُ بِدْعًۭا مِّنَ ٱلرُّسُلِ وَمَآ أَدْرِى مَا يُفْعَلُ بِى وَلَا بِكُمْ ۖ إِنْ أَتَّبِعُ إِلَّا مَا يُوحَىٰٓ إِلَىَّ وَمَآ أَنَا۠ إِلَّا نَذِيرٌۭ مُّبِينٌۭ

ነጥብ አንድ
“ብጤ የሌለኝ አይደለሁም”
ከነቢያችን”ﷺ” በፊት የመጡት በእርግጥ ምግብን የሚበሉ፣ በገበያዎችም የሚሄዱ ሰዎች ነበሩ፣ በተመሳሳይም ነቢያችን”ﷺ” ሰው ናቸው፣ በደረጃ እንጂ በሃልዎት ከሰው የተለዩ አልነበሩም፣ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆኑ መልክተኛ ነበሩ፦
36፥3 አንተ በእርግጥ *ከመልክተኞቹ ነህ*። إِنَّكَ لَمِنَ ٱلْمُرْسَلِينَ
2፥252 አንተም *በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነህ*፡፡ وَإِنَّكَ لَمِنَ ٱلْمُرْسَلِينَ
3፥144 ሙሐመድም *ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም*፤ وَمَا مُحَمَّدٌ إِلَّا رَسُولٌۭ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ ٱلرُّسُلُ
ነጥብ ሁለት
“ዐላውቅም”
ነቢያችን”ﷺ” በራሳቸውና በሰዎች ምን እንደሚከናወን የወደፊቱን ዐያውቁም፣ ያ ማለት ሰዎች የሚያስጠነቅቁበት ቅርብ ይሁን እሩቅ ዐያውቁም፣ ከሚወርድላቸው ግህደተ-መለኮት ውጪ ምንም ዐያውቁም፦
6፥50 «ለእናንተ የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልልም፡፡ *ሩቅንም አላውቅም*፡፡ ለእናንተም እኔ መልአክ ነኝ አልልም፡፡ *ወደ እኔ የሚወርድልኝን እንጅ ሌላን አልከተልም*» በላቸው፡፡ قُل لَّآ أَقُولُ لَكُمْ عِندِى خَزَآئِنُ ٱللَّهِ وَلَآ أَعْلَمُ ٱلْغَيْبَ وَلَآ أَقُولُ لَكُمْ إِنِّى مَلَكٌ ۖ إِنْ أَتَّبِعُ إِلَّا مَا يُوحَىٰٓ إِلَىَّ ۚ قُلْ هَلْ يَسْتَوِى ٱلْأَعْمَىٰ وَٱلْبَصِيرُ ۚ أَفَلَا تَتَفَكَّرُونَ
7፥188 አላህ የሻውን በስተቀር ለራሴ ጥቅምንም፣ ጉዳትንም፣ ማምጣት አልችልም፣ *ሩቅንም የማውቅ በነበርኩ ኖሮ* ከመልካም ነገር ባበዛሁና ክፉም ነገር ባልነካኝ ነበር፤ እኔ ለሚያምኑ ሕዝቦች አስጠንቃቂና አብሳሪ እንጂ ሌላ አይደለሁም”* በላቸው። قُل لَّآ أَمْلِكُ لِنَفْسِى نَفْعًۭا وَلَا ضَرًّا إِلَّا مَا شَآءَ ٱللَّهُ ۚ وَلَوْ كُنتُ أَعْلَمُ ٱلْغَيْبَ لَٱسْتَكْثَرْتُ مِنَ ٱلْخَيْرِ وَمَا مَسَّنِىَ ٱلسُّوٓءُ ۚ إِنْ أَنَا۠ إِلَّا نَذِيرٌۭ وَبَشِيرٌۭ لِّقَوْمٍۢ يُؤْمِنُونَ
21፥109 እምቢም ቢሉ በማወቅ በእኩልነት ላይ ሆነን የታዘዝኩትን አስታወቅኋችሁ፤ *የምትስፈራሩበትም ነገር ቅርብ፣ ወይም ሩቅ፣ መሆኑን ዐላውቅም*፤ በላቸው። فَإِن تَوَلَّوْا۟ فَقُلْ ءَاذَنتُكُمْ عَلَىٰ سَوَآءٍۢ ۖ وَإِنْ أَدْرِىٓ أَقَرِيبٌ أَم بَعِيدٌۭ مَّا تُوعَدُونَ
21፥111 እርሱም *ቅጣትን ማቆየት ምናልባት ለእናንተ ፈተናና እስከ ጊዜው መጣቀሚያ እንደኾነም “አላውቅም”*፤ በላቸው። وَإِنْ أَدْرِى لَعَلَّهُۥ فِتْنَةٌۭ لَّكُمْ وَمَتَٰعٌ إِلَىٰ حِينٍۢ

ነጥብ ሶስት
“ሚወረደው”
ወደ ነቢያችን”ﷺ” የሚወርደው ለቀደሙት መልክተኞች የሚወርደው የነበረው የአንድ አምላክ አስተምህሮት ነው፣ ከነቢያችን"ﷺ" በፊት ለነበሩት መልክተኞች የተባለው ይህ የተውሒድ ተስተምህሮት ነው ነቢያችን”ﷺ” የሚከተሉት፦
21፥108 «ያ ወደ እኔ የሚወረደው፦ *”አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው”* ማለት ነው፤ ታዲያ እናንተ ፍጹም “ታዛዦች” ናችሁን» *በላቸው*፡፡ قُلْ إِنَّمَا يُوحَىٰٓ إِلَىَّ أَنَّمَآ إِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌۭ وَٰحِدٌۭ ۖ فَهَلْ أَنتُم مُّسْلِمُونَ
18፥110 እኔም ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚወረድልኝ፦ *”አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው” ማለት ነው”*፤ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፡፡ በጌታውም አምልኮ አንድንም አያጋራ» *”በላቸው”*፡፡ قُلْ إِنَّمَآ أَنَا۠ بَشَرٌۭ مِّثْلُكُمْ يُوحَىٰٓ إِلَىَّ أَنَّمَآ إِلَٰهُكُمْ إِلَٰهٌۭ وَٰحِدٌۭ ۖ فَمَن كَانَ يَرْجُوا۟ لِقَآءَ رَبِّهِۦ فَلْيَعْمَلْ عَمَلًۭا صَٰلِحًۭا وَلَا يُشْرِكْ بِعِبَادَةِ رَبِّهِۦٓ أَحَدًۢا
21፥25 ከአንተ በፊትም፣ እነሆ *ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ፣ በማለት ወደ እርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም*። وَمَآ أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِىٓ إِلَيْهِ أَنَّهُۥ لَآ إِلَٰهَ إِلَّآ أَنَا۠ فَٱعْبُدُونِ
41፥43 ከአንተ በፊት ለነበሩት መልክተኞች *የተባለው ቢጤ* እንጅ ለአንተ ሌላ አይባልም፤ مَّا يُقَالُ لَكَ إِلَّا مَا قَدْ قِيلَ لِلرُّسُلِ مِن قَبْلِكَ ۚ إِنَّ رَبَّكَ لَذُو مَغْفِرَةٍۢ وَذُو عِقَابٍ أَلِيمٍۢ
ነጥብ አራት
“አስጠንቃቂ”
አላህ የነቢያችን”ﷺ” ቢጤዎች መልክተኞችን አብሳሪና አስጠንቃቂ አድርጎ ከነቢያችን”ﷺ” በፊት ልኳል፦
18፥56 መልክተኞችንም *አብሳሪዎችና አስጠንቃቂዎች* ሆነው እንጂ አንልክም፤ وَمَا نُرْسِلُ ٱلْمُرْسَلِينَ إِلَّا مُبَشِّرِينَ وَمُنذِرِين
4፥165 ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር *አብሳሪዎችና አስጠንቃቂዎች* የሆኑን መልክተኞች ላክን፤ رُّسُلًۭا مُّبَشِّرِينَ وَمُنذِرِينَ لِئَلَّا يَكُونَ لِلنَّاسِ عَلَى ٱللَّهِ حُجَّةٌۢ بَعْدَ ٱلرُّسُلِ ۚ وَكَانَ ٱللَّهُ عَزِيزًا حَكِيمًۭا
2፥213 አላህም ነቢያትን *አብሳሪዎችና አስጠንቃቂዎች* አድርጎ ላከ፡፡ وَٰحِدَةًۭ فَبَعَثَ ٱللَّهُ ٱلنَّبِيِّـۧنَ مُبَشِّرِينَ وَمُنذِرِينَ

በተመሳሳይ መልኩ በጀነት አብሳሪ በጀሃነም አስጠንቃቂ ይሆኑ ዘንድ ነቢያችንን”ﷺ” አብሳሪና አስጠንቃቂ አድርጎ ልኳል፦
2፥119 እኛ *አብሳሪና አስጠንቃቂ* ኾነህ በእውነት ላክንህ፡፡ ከእሳትም ጓዶች አትጠየቅም፡፡ إِنَّآ أَرْسَلْنَٰكَ بِٱلْحَقِّ بَشِيرًۭا وَنَذِيرًۭا ۖ وَلَا تُسْـَٔلُ عَنْ أَصْحَٰبِ ٱلْجَحِيمِ
34፥28 አንተንም ለሰዎች ሁሉ በሙሉ *አብሳሪና አስጠንቃቂ* አድርገን ቢሆን እንጂ አላክንህም፤ وَمَآ أَرْسَلْنَٰكَ إِلَّا كَآفَّةًۭ لِّلنَّاسِ بَشِيرًۭا وَنَذِيرًۭا وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ ٱلنَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ
33፥45 አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ መስካሪ *አብሳሪና አስጠንቃቂ* አድርገን ላክንህ። يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّبِىُّ إِنَّآ أَرْسَلْنَٰكَ شَٰهِدًۭا وَمُبَشِّرًۭا وَنَذِيرًۭا

አላህም፦ ”አላህን እንጂ ሌላን አታምልኩ፤ አንድ ከኾነው አላህ በቀር ምንም አምላክ የለም፤ እኔ ለእናንተ ከእርሱ የተላክሁ አስጠንቃቂ ነኝ” በል በማለት አስጠንቃቂ መሆናቸውን አውርዷል፦
11፥2 እንዲህ በላቸው ፦ አላህን እንጂ ሌላን አታምልኩ፤ *እኔ ለእናንተ ከእርሱ የተላክሁ አስጠንቃቂ ነኝ*። أَلَّا تَعْبُدُوٓا۟ إِلَّا ٱللَّهَ ۚ إِنَّنِى لَكُم مِّنْهُ نَذِيرٌۭ وَبَشِيرٌۭ
22፥49 ፦ እላንተ ስዎች ሆይ እኔ ለእናንተ *ግልጽ አስጠንቃቂ ብቻ ነኝ*፣ በላቸው። قُلْ يَٰٓأَيُّهَا ٱلنَّاسُ إِنَّمَآ أَنَا۠ لَكُمْ نَذِيرٌۭ مُّبِينٌۭ

ስለዚህ ከላይ ያለውን አንቀጽ የወረደበትም ዐውድ ስንመለከተው ነቢያችን”ﷺ” ጀነት ስለ አለመግባታቸው ምንም የሚያወራው ነገር የለም። ዐውዱ ለማስተላለፍ የፈለገውን በግድ ጠምዝዞ ይህን ለማለት ነው የፈለገው ብሎ ማጣመም ከሥነ-አፈታት ጥናት “hermeneutics” ጋር መላተም እና የደፈረሰ የተሳከረ መረዳት ነው፣ ይህ ሙግት የዐውድ ሙግት”contextual approach” ታሳቢና ዋቢ ያደረገ ነው።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
ሶላት

ገቢር አንድ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

4፥103 *“ሶላት” በምእመናን ላይ “በጊዜያት” የተወሰነች ግዴታ ናትና"*። إِنَّ الصَّلَاةَ كَانَتْ عَلَى الْمُؤْمِنِينَ كِتَابًا مَّوْقُوتًا

ከአምስቱ የኢሥላም ምሰሶዎች አንዱ ሶላት ነው፤ "ሶላት" صَّلَاة ማለት "የግዴታ ጸሎት" ማለት ነው። በእርግጥም ሶላት በአምስት ወቅት የሚፈጸም ነው፤ ሶላት በምእመናን ላይ “በጊዜያት” የተወሰነ ፈርድ ነው፦
4፥103 *“ሶላት” በምእመናን ላይ “በጊዜያት” የተወሰነች ግዴታ ናትና"*። إِنَّ الصَّلَاةَ كَانَتْ عَلَى الْمُؤْمِنِينَ كِتَابًا مَّوْقُوتًا

ነቢያችንም"ﷺ" በሐዲስ በጊዜያት የተወሰኑትን የሶላት ወቅት ዘርዝረውልናል፦
ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 2 , ሐዲስ 3
አቢ ሁራይራ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ የአላህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ *"በእርግጥም ሶላት ጅማሬ አለው ፍጻሜ አለው፤ የሶላቱ አዝ-ዙሁር ወቅት የሚጀምረው ጸሐይ በአናት ትይዩ ማለፍ ከጀመረችበት ነው፥ የሚጨርሰውም እስከ ዐስር መግቢያ ድረስ ነው። የሶላቱል ዐስር ወቅት የሚጀምረው ከጸሐይ መዘንበል ከጀመረችበት ነው፥ የሚጨርሰውም እስከ ጸሐይ መግቢያ ድረስ ነው። የሶላቱል መግሪብ ወቅት የሚጀምረው ከጸሐይ መጥለቅ ከጀመረችበት ነው፥ የሚጨርሰውም እስከ ፊተኛው ሌሊት ድረስ ነው። የሶላቱል ዒሻዕ ወቅት የሚጀምረው ከፊተኛው ሌሊት ማታ ከጀመረችበት ነው፥ የሚጨርሰውም እስከ ሁለተኛይቱ ሌሊት ድረስ ነው። የሶላቱል ፈጅር ወቅት የሚጀምረው ጎህ ከጀመረችበት ነው፥ የሚጨርሰውም እስከ ጸሐይ መውጣት ድረስ ነው"*። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ إِنَّ لِلصَّلاَةِ أَوَّلاً وَآخِرًا وَإِنَّ أَوَّلَ وَقْتِ صَلاَةِ الظُّهْرِ حِينَ تَزُولُ الشَّمْسُ وَآخِرَ وَقْتِهَا حِينَ يَدْخُلُ وَقْتُ الْعَصْرِ وَإِنَّ أَوَّلَ وَقْتِ صَلاَةِ الْعَصْرِ حِينَ يَدْخُلُ وَقْتُهَا وَإِنَّ آخِرَ وَقْتِهَا حِينَ تَصْفَرُّ الشَّمْسُ وَإِنَّ أَوَّلَ وَقْتِ الْمَغْرِبِ حِينَ تَغْرُبُ الشَّمْسُ وَإِنَّ آخِرَ وَقْتِهَا حِينَ يَغِيبُ الأُفُقُ وَإِنَّ أَوَّلَ وَقْتِ الْعِشَاءِ الآخِرَةِ حِينَ يَغِيبُ الأُفُقُ وَإِنَّ آخِرَ وَقْتِهَا حِينَ يَنْتَصِفُ اللَّيْلُ وَإِنَّ أَوَّلَ وَقْتِ الْفَجْرِ حِينَ يَطْلُعُ الْفَجْرُ وَإِنَّ آخِرَ وَقْتِهَا حِينَ تَطْلُعُ الشَّمْسُ

እዚህ ሐዲስ ላይ የተጠቀሱትን አምስት ወቅት ሶላት፦ ሶላቱል ፈጅር፣ ሶላቱ አዝ-ዙሁር፣ ሶላቱል ዐስር፣ ሶላቱል መግሪብ እና ሶላቱል ዒሻዕ ከቁርኣን ነጥብ በነጥብ እንመልከት፦

ነጥብ አንድ
"ፈጅር"
“ፈጅር” فَجْر ማለት “ጎህ” ማለት ሲሆን አምላካችን አላህ ይህን የጎህ ወቅት በሶላት እንድንቆም ያዘናል፦
17፥78 ሶላትን ከፀሐይ መዘንበል እስከ ሌሊት ጨለማ ድረስ ስገድ፤ *“የጎህ ሰላት ስገድ፣ የጎህ ሶላት መላእክት የሚጣዱት ነውና"*። أَقِمِ الصَّلَاةَ لِدُلُوكِ الشَّمْسِ إِلَىٰ غَسَقِ اللَّيْلِ وَقُرْآنَ الْفَجْرِ ۖ إِنَّ قُرْآنَ الْفَجْرِ كَانَ مَشْهُودًا
24፥58 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያ እጆቻችሁ የጨበጧቸው እነዚያም ከእናንተ ለአካላ መጠን ያልደረሱት *ከጎህ ስግደት" በፊት፣ በቀትርም ልብሶቻችሁን በምታወልቁ ጊዜ ከምሽት ስግደትም* በኋላ ሦስት ጊዜያት ለመግባት ሲፈልጉ ያስፈቅዷችሁ፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لِيَسْتَأْذِنكُمُ الَّذِينَ مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ وَالَّذِينَ لَمْ يَبْلُغُوا الْحُلُمَ مِنكُمْ ثَلَاثَ مَرَّاتٍ ۚ مِّن قَبْلِ صَلَاةِ الْفَجْرِ وَحِينَ تَضَعُونَ ثِيَابَكُم مِّنَ الظَّهِيرَةِ وَمِن بَعْدِ صَلَاةِ الْعِشَاءِ ۚ ثَلَاثُ عَوْرَاتٍ لَّكُم

ጌታችን አላህ ሶላቱል ፈጅርን ለማመልከት፦ “በምታነጉ ጊዜ” “በማለዳም” “በምትንነሳ ጊዜ” “ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት” በማለት በአፅንኦትና በአንክሮት ይናገራል፦
30፥17 *"አላህንም በምታመሹ ጊዜ "በምታነጉም ጊዜ" አጥሩት*"፡፡ فَسُبْحَانَ اللَّهِ حِينَ تُمْسُونَ وَحِينَ تُصْبِحُونَ
40፥55 ታገስም የአላህ ተስፋ እውነት ነውና፡፡ ለስህተትህም ምሕረትን ለምን፡፡ ከቀትር በኋላ በማታም *"በማለዳም" ጌታህን ከማመስገን ጋር አጥራው"*፡፡ فَاصْبِرْ إِنَّ وَعْدَ اللَّهِ حَقٌّ وَاسْتَغْفِرْ لِذَنبِكَ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ بِالْعَشِيِّ وَالْإِبْكَارِ
52:48 ለጌታህ ፍርድም ታገሥ፡፡ አንተ በጥበቃችን ውስጥ ነህና፡፡ *"ጌታህንም "በምትነሳ ጊዜ" ከማመስገን ጋር አወድሰው"*፡፡ وَاصْبِرْ لِحُكْمِ رَبِّكَ فَإِنَّكَ بِأَعْيُنِنَا ۖ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ حِينَ تَقُومُ
50፥39 በሚሉትም ላይ ታገሥ፤ ጌታህንም ከማመስገን ጋር *"ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት"* ከመግባቷም በፊት አወድሰው፡፡ فَاصْبِرْ عَلَىٰ مَا يَقُولُونَ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ قَبْلَ طُلُوعِ الشَّمْسِ وَقَبْلَ الْغُرُوبِ
20፥130 በሚሉትም ላይ ታገስ፡፡ ጌታህንም *"ፀሐይ ከመውጣትዋ በፊት"* ከመግባትዋም በፊት የምታመሰግን ኾነህ አጥራው፤ ከሌሊት ሰዓቶችም በቀን ጫፎችም አጥራው፡፡ በሚሰጥህ ምንዳ ልትወድ ይከጀላልና፡፡ فَاصْبِرْ عَلَىٰ مَا يَقُولُونَ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ قَبْلَ طُلُوعِ الشَّمْسِ وَقَبْلَ غُرُوبِهَا ۖ وَمِنْ آنَاءِ اللَّيْلِ فَسَبِّحْ وَأَطْرَافَ النَّهَارِ لَعَلَّكَ تَرْضَىٰ
ነጥብ ሁለት
"ዙሁር"
"ዙሁር" ظُهْر‎ ማለት “ቀትር” ማለት ሲሆን አምላካችን አላህ ይህን ሶላቱ አዝ-ዝሁር በሶላት እንድንቆም ያዘናል፦
24፥58 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያ እጆቻችሁ የጨበጧቸው እነዚያም ከእናንተ ለአካላ መጠን ያልደረሱት *ከጎህ ስግደት በፊት፣ "በቀትርም" ልብሶቻችሁን በምታወልቁ ጊዜ ከምሽት ስግደትም* በኋላ ሦስት ጊዜያት ለመግባት ሲፈልጉ ያስፈቅዷችሁ፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لِيَسْتَأْذِنكُمُ الَّذِينَ مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ وَالَّذِينَ لَمْ يَبْلُغُوا الْحُلُمَ مِنكُمْ ثَلَاثَ مَرَّاتٍ ۚ مِّن قَبْلِ صَلَاةِ الْفَجْرِ وَحِينَ تَضَعُونَ ثِيَابَكُم مِّنَ الظَّهِيرَةِ وَمِن بَعْدِ صَلَاةِ الْعِشَاءِ ۚ ثَلَاثُ عَوْرَاتٍ لَّكُم
30፥18 ምስጋናም በስማያትና በምድር ውስጥ ለርሱ ብቻ የተገባው ነው። በሠርክም *“በቀትር” ውስጥ በምትገቡም ጊዜ፤ አጥሩት*"። وَلَهُ الْحَمْدُ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَعَشِيًّا وَحِينَ تُظْهِرُونَ

ነጥብ ሦስት
"ዐስር"
“ዐስር” ْعَصْر ማለት “ሰርክ” ማለት ሲሆን የዓለማቱ ጌታ የማለበት ወቅት ነው፤ ይህቺ የሰርክ ሰላት በቁርኣን የመካከለኛይቱ ሶላት ትባላለች፦
103፥1 *"በጊዜያቱ እምላለሁ"*፡፡ وَالْعَصْرِ
2፥238 *"በሶላቶች በተለይ በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ"*፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡ حَافِظُوا عَلَى الصَّلَوَاتِ وَالصَّلَاةِ الْوُسْطَىٰ وَقُومُوا لِلَّهِ قَانِتِينَ

"አል-ዐስር" الْعَصْر በሚለው ቃል መነሻ ቅጥያ ላይ የመጣው "ወ" وَ የሚለው ሐርፉል ዐጥፍ ሳይሆን “ቢ” بـِ ለሚለው ሐርፉል ጀር ተለዋዋጭ ቃል ነው።
“መካከለኛይቱም ሶላት” የተባለችው ደግሞ ከሌሎች ሶላቶች ለመለየት እና ለማያያዝ “ወ” وَ የሚል አያያዥ መስተፃምር ይጠቀማል። ታዲያ መካከለኛነቷ ለማን ነው? ስንል ለሁለት ሶላቶች ቢሆን ኖሮ ሙተና”dual” ያለው በመንሱብና በመጅሩር "ሶላተዪን” صلاتين አሊያም በመርፉ "ሶላታን” صلاتان ይጠቀም ነበር፥ ነገር ግን መካከለኝነቷ ለሁለት ሳይሆን ለጀመዕ”plural” ያለው “ሶለዋት” صَّلَوَات የሚል ነው፣ ይህ የሚያሳየው ከፊቷ ሁለት ከኃላዋ ሁለት ያላት መካከለኛይቱ ሶላቱል አስር ናት፤ ይህቺ ሶላት በሌሎች አናቅጽ፦ “ሰርክ” “ፀሐይ ከመግባቷም በፊት” “ከፀሐይ መዘንበል” ተብላለች፦
30፥18 ምስጋናም በሰማያትና በምድር ውስጥ ለእርሱ ብቻ የተገባው ነው፡፡ *"በሰርክም"፤ በቀትር ውስጥ በምትገቡም ጊዜ አጥሩት"*፡፡ وَلَهُ الْحَمْدُ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَعَشِيًّا وَحِينَ تُظْهِرُونَ
50፥39 በሚሉትም ላይ ታገሥ፤ ጌታህንም ከማመስገን ጋር ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት *“ከመግባቷም በፊት” አወድሰው"*፡፡ فَاصْبِرْ عَلَىٰ مَا يَقُولُونَ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ قَبْلَ طُلُوعِ الشَّمْسِ وَقَبْلَ الْغُرُوبِ
20፥130 በሚሉትም ላይ ታገስ፡፡ ጌታህንም ፀሐይ ከመውጣትዋ በፊት *"ከመግባትዋም በፊት የምታመሰግን ኾነህ አጥራው"*፤ ከሌሊት ሰዓቶችም በቀን ጫፎችም አጥራው፡፡ በሚሰጥህ ምንዳ ልትወድ ይከጀላልና፡፡ فَاصْبِرْ عَلَىٰ مَا يَقُولُونَ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ قَبْلَ طُلُوعِ الشَّمْسِ وَقَبْلَ غُرُوبِهَا ۖ وَمِنْ آنَاءِ اللَّيْلِ فَسَبِّحْ وَأَطْرَافَ النَّهَارِ لَعَلَّكَ تَرْضَىٰ
17፥78 *"ሶላትን "ከፀሐይ መዘንበል" እስከ ሌሊት ጨለማ ድረስ ስገድ"*፤ የጎህ ሰላት ስገድ፣ የጎህ ሶላት መላእክት የሚጣዱት ነውና። أَقِمِ الصَّلَاةَ لِدُلُوكِ الشَّمْسِ إِلَىٰ غَسَقِ اللَّيْلِ وَقُرْآنَ الْفَجْرِ ۖ إِنَّ قُرْآنَ الْفَجْرِ كَانَ مَشْهُودًا

ኢንሻላህ በክፍል ሁለት ስለ ሶላቱል መግሪብ እና ስለ ሶላቱል ዒሻዕ በመዳሰስ እናጠቃልላለን።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
ገቢር ሁለት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥43 *"ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም ስጡ፡፡ ለጌታችሁ ከአጎንባሾች ጋርም አጎንብሱ"*፡፡ وَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ وَآتُوا الزَّكَاةَ وَارْكَعُوا مَعَ الرَّاكِعِينَ

ነጥብ አራት
“መግሪብ”
“መግሪብ” مَغْرِب ማለት "የጸሐይ መጥለቅ" ወይም "ምሽት" አሊያም "ምዕራብ” ማለት ነው፣ ይህ ሌላኛው የቀን ጫፍ ይባላል፦
11፥114 *"ሶላትንም በቀን “ጫፎች”፥ ከሌሊትም ክፍሎች ፈጽም"*፤ መልካም ሥራዎች ኅጢአቶችን ያስወግዳሉና፤ ይህ ለተገሣጮች ግሣጤ ነው። وَأَقِمِ الصَّلَاةَ طَرَفَيِ النَّهَارِ وَزُلَفًا مِّنَ اللَّيْلِ ۚ إِنَّ الْحَسَنَاتِ يُذْهِبْنَ السَّيِّئَاتِ ۚ ذَٰلِكَ ذِكْرَىٰ لِلذَّاكِرِينَ
20፥130 በሚሉትም ላይ ታገስ፤ ጌታህንም ፀሃይ ከመውጣትዋ በፊት ከመግባትዋም በፊት የምታመሰግን ሆነህ አጥራው፤ ስገድ፤ ከሌሊት ሰዓቶችም *“በቀን “ጫፎች” አጥራው"*፤ በሚሰጥህ ምንዳ ልትወድ ይከጀላልና። فَاصْبِرْ عَلَىٰ مَا يَقُولُونَ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ قَبْلَ طُلُوعِ الشَّمْسِ وَقَبْلَ غُرُوبِهَا ۖ وَمِنْ آنَاءِ اللَّيْلِ فَسَبِّحْ وَأَطْرَافَ النَّهَارِ لَعَلَّكَ تَرْضَىٰ

“ተረፍ” طَرَف ማለት “ጫፍ” ማለት ሲሆን እዚህ ጋር የተጠቀመው ቃል ሙተና”dual” ሆኖ “ተረፈዪ” طَرَفَيِ ነው፤ የቀን ጫፍ አንዱ "ጎህ" ሲሆን ሌላው "ምሽት" ነው፤ አምላካችን አላህ ይህንን ለማመልከት፦ “በምታመሹ ጊዜ” እያለ ይናገራል፦
30፥17 *"አላህንም "በምታመሹ ጊዜ" በምታነጉም ጊዜ አጥሩት"*፡፡ فَسُبْحَانَ اللَّهِ حِينَ تُمْسُونَ وَحِينَ تُصْبِحُونَ

ነጥብ አምስት
"ዒሻዕ"
“ዒሻዕ” عِشَآء ማለት “ማታ” ማለት ሲሆን አምላካችን አላህ ይህን የማታ ወቅት በሶላት እንድንቆም ያዘናል፦
24፥58 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያ እጆቻችሁ የጨበጧቸው እነዚያም ከእናንተ ለአካላ መጠን ያልደረሱት *ከጎህ ስግደት በፊት፣ በቀትርም ልብሶቻችሁን በምታወልቁ ጊዜ "ከምሽት ስግደትም"* በኋላ ሦስት ጊዜያት ለመግባት ሲፈልጉ ያስፈቅዷችሁ፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لِيَسْتَأْذِنكُمُ الَّذِينَ مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ وَالَّذِينَ لَمْ يَبْلُغُوا الْحُلُمَ مِنكُمْ ثَلَاثَ مَرَّاتٍ ۚ مِّن قَبْلِ صَلَاةِ الْفَجْرِ وَحِينَ تَضَعُونَ ثِيَابَكُم مِّنَ الظَّهِيرَةِ وَمِن بَعْدِ صَلَاةِ الْعِشَاءِ ۚ ثَلَاثُ عَوْرَاتٍ لَّكُم
40፥55 ታገስም የአላህ ተስፋ እውነት ነውና፡፡ ለስህተትህም ምሕረትን ለምን፡፡ ከቀትር በኋላ *"በማታም" በማለዳም ጌታህን ከማመስገን ጋር አጥራው"*፡፡ فَاصْبِرْ إِنَّ وَعْدَ اللَّهِ حَقٌّ وَاسْتَغْفِرْ لِذَنبِكَ وَسَبِّحْ بِحَمْدِ رَبِّكَ بِالْعَشِيِّ وَالْإِبْكَارِ
18፥28 ነፍስህንም ከእነዚያ ጌታቸውን ፊቱን የሚሹ ሆነው በጧት እና *“በማታ” ከሚግገዙት ጋር አስታግሥ"*። وَاصْبِرْ نَفْسَكَ مَعَ الَّذِينَ يَدْعُونَ رَبَّهُم بِالْغَدَاةِ وَالْعَشِيِّ يُرِيدُونَ وَجْهَهُ
7፥205 ጌታህንም በምስጢር ተዋድቀህና ፈርተህ ከጩኸት በታችም በኾነ ቃል በጧትም *"በማታም አውሳው"*፡፡ ከዘንጊዎቹም አትኹን፡፡ وَاذْكُر رَّبَّكَ فِي نَفْسِكَ تَضَرُّعًا وَخِيفَةً وَدُونَ الْجَهْرِ مِنَ الْقَوْلِ بِالْغُدُوِّ وَالْآصَالِ وَلَا تَكُن مِّنَ الْغَافِلِين

“ዙልፋህ” زُلْفَة ማለት "ፊተኛው የሌሊት ክፍል” ማለት ሲሆን ይህም ፊተኛው የሌሊት ክፍል ዒሻዕ ነው፦
11፥114 *"ሶላትንም በቀን ጫፎች፥ "ከሌሊትም ክፍሎች" ፈጽም"*፤ መልካም ሥራዎች ኅጢአቶችን ያስወግዳሉና፤ ይህ ለተገሣጮች ግሣጤ ነው። وَأَقِمِ الصَّلَاةَ طَرَفَيِ النَّهَارِ وَزُلَفًا مِّنَ اللَّيْلِ ۚ إِنَّ الْحَسَنَاتِ يُذْهِبْنَ السَّيِّئَاتِ ۚ ذَٰلِكَ ذِكْرَىٰ لِلذَّاكِرِينَ
ማጠቃለያ
ሶላት በውስጡ ሦስት አበይት ክፍሎች ያቅፋል፤ እነርሱም፦
1. “ቂያም” قيام “መቆም”
2. “ሩኩዕ” رُكوع “ማጎንበስ”
3. “ሡጁድ” سُّجُود “ስግደት” ናቸው።
አንድ ሙሥሊም በቂያም “ሙቂሚ” مُّقِيم ” ሲባል፣ በሩኩዕ “ራኪዕ” رَاكِع ሲባል፣ በሱጁድ ደግሞ “ሣጂድ” سَاجِد ይባላል፦
2፥238 በሶላቶች በተለይ በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ *"ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ"*፡፡ حَافِظُوا عَلَى الصَّلَوَاتِ وَالصَّلَاةِ الْوُسْطَىٰ وَقُومُوا لِلَّهِ قَانِتِينَ
22፥77 እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! *:በስግደታችሁ አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ፣ ጌታችሁንም አምልኩ"*፣ በጎንም ነገር ሥሩ፣ ልትድኑ ይከጀልላችኋልና፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا ارْكَعُوا وَاسْجُدُوا وَاعْبُدُوا رَبَّكُمْ وَافْعَلُوا الْخَيْرَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ ۩

"ቁሙ" "አጎንብሱ" "በግንባራችሁም ተደፉ" የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። ሶላት ደንብ አላት፤ ሶላት ደንቡን ጠብቆ ከተሰገደ ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለች፦
2፥43 *"ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም ስጡ፡፡ ለጌታችሁ ከአጎንባሾች ጋርም አጎንብሱ"*፡፡ وَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ وَآتُوا الزَّكَاةَ وَارْكَعُوا مَعَ الرَّاكِعِينَ
29፥45 ከመጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፡፡ *"ሶላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፡፡ ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና"*፡፡ አላህንም ማውሳት ከሁሉ ነገር በላጭ ነው፤ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ያውቃል፡፡ اتْلُ مَا أُوحِيَ إِلَيْكَ مِنَ الْكِتَابِ وَأَقِمِ الصَّلَاةَ ۖ إِنَّ الصَّلَاةَ تَنْهَىٰ عَنِ الْفَحْشَاءِ وَالْمُنكَرِ ۗ وَلَذِكْرُ اللَّهِ أَكْبَرُ ۗ وَاللَّهُ يَعْلَمُ مَا تَصْنَعُونَ

ሶላት በኢማን፣ በኢኽላስ እና በኢቲባዕ ከተፈጸመ ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ በመከልከል ይረዳል፤ ሶላት አላህን በሚፈሩ ላይ እንጅ በሌላው ላይ በእርግጥ ከባድ ናት፦
2፥45 በመታገስ እና *"በሶላትም ተረዱ፡፡ እርሷም ሶላት በፈሪዎች ላይ እንጅ በሌላው ላይ በእርግጥ ከባድ ናት"*፡፡ وَاسْتَعِينُوا بِالصَّبْرِ وَالصَّلَاةِ ۚ وَإِنَّهَا لَكَبِيرَةٌ إِلَّا عَلَى الْخَاشِعِينَ
2፥153 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በመታገስ እና *"በሶላት ተረዱ"*፡፡ አላህ ከታጋሾች ጋር ነውና፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اسْتَعِينُوا بِالصَّبْرِ وَالصَّلَاةِ ۚ إِنَّ اللَّهَ مَعَ الصَّابِرِينَ

ሶላት ላይ የሚቆሙ ሙሥሊሞች "ሙሰሊን" ይባላሉ፤ ሶላት የማይቆሙ "ሰቀር" በሚባለው የጀሃነም ሸለቆ ውስጥ ይቀጣሉ፤ እነርሱም ቅጣቱን ሲቀምሱ፦ "ከሙሰሊኖቹ አልነበርንም" ይላሉ፦
74፥43 እነርሱም ይላሉ፦ *"ከሰጋጆቹ አልነበርንም"*፡፡ قَالُوا لَمْ نَكُ مِنَ الْمُصَلِّين

ሶላት በወቅቱ የማይቆሙ እና ያለ ኢኽላስ ሶላት ላይ የሚቆሙ "ወይል" በሚባል የጀሃነም ሸለቆ ውስጥ ይቀጣሉ፦
107፥4 *"ወዮላቸው ለሰጋጆች"*፡፡ فَوَيْلٌ لِّلْمُصَلِّينَ
107፥5 *"ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት ሰጋጆች"*፡፡ الَّذِينَ هُمْ عَن صَلَاتِهِمْ سَاهُونَ
107፥6 *"ለእነዚያ እነርሱ ይዩልኝ ባዮች ለኾኑት"*፡፡ الَّذِينَ هُمْ يُرَاءُونَ

ወዮላቸው የተባሉት ሙሰሊን እነማን እንደሆኑ ለማመልከት "እነዚያ" የሚል አመልካች ተውላጠ-ስም ተጠቅሰዋል። እነዚያ እነርሱ በሶላታቸው ላይ ዘውታሪዎች ሆነው የሚቆሙ ሙሰሊን ሲቀሩ በተቃራኒው ሶላትን ያጓደሉ አሊያም የተዉ "ገይ" በሚባል የጀሃነም ሸለቆ ውስጥ ይቀጣሉ፦
70፥22 *"ሰጋጆቹ ብቻ ሲቀሩ"*፡፡ إِلَّا الْمُصَلِّينَ
70፥23 *እነዚያ እነርሱ በሶላታቸው ላይ ዘውታሪዎች የኾኑት"*፡፡ الَّذِينَ هُمْ عَلَىٰ صَلَاتِهِمْ دَائِمُونَ
19፥59 *ከእነርሱም በኋላ "ሶላትን ያጓደሉ" ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች ተተኩ! የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ*፡፡ فَخَلَفَ مِن بَعْدِهِمْ خَلْفٌ أَضَاعُوا الصَّلَاةَ وَاتَّبَعُوا الشَّهَوَاتِ ۖ فَسَوْفَ يَلْقَوْنَ غَيًّا

አላህ በሶላታቸው ላይ ዘውታሪዎች ሆነው ከሚቆሙትና ኢኽላስ ካላቸው ሙሰሊን ባሮቹ ያድርገን! አሚን።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
የነብያችን"ﷺ" አሟሟት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

3:144 ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፤ ታድያ ""ቢሞት፥ ወይም ቢገደል"" ወደኋላችሁ ትገለበጣላችሁን? ወደኋላዉ የሚገለበጥም ሰዉ አላህን ምንም አይጐዳም። አላህም አመስጋኞቹን በእርግጥ ይመነዳል።

ብዙ ሚሽነሪዎች በተለይ የክርስትናው አቃቤ እምነት ዴቪፍ ሁድ እና ሳም ሻሙስ የነብያችንን"ﷺ" አሟሟት አጣመው ነብያችንን"ﷺ" እንደ ኃሳዌ ነብይ ለማድረግ ሲቃጣቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ይሰማል፤ በነገራችን ላይ አንድ ነብይ ይቅርና አንድ አማኝ በአላህ ሃይማኖት የተሰደደ፣ የተገደለ ወይም የሞተ አላህ መልካምን ሲሳይ በእርግጥ ይሰጠዋል፦
22:58 እነዚያም በአላህ ሃይማኖት የተሰደዱ፣ ከዚያም የተገደሉ፣ ወይም የሞቱ፣ አላህ መልካምን ሲሳይ በእርግጥ ይስጣቸዋል፣ አላህም እርሱ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነው።

ነብያችን ከመላካቸው በፊት የእስራኤል ልጆች ነብያትን ያለ አግባብ ገድለዋል፦
2:91 «አማኞች ከኾናችሁ ከአሁን በፊት የአላህን ነቢያት ለምን ገደላችሁ?» በላቸው፡፡
4:155 ቃል ኪዳናቸውንም በማፍረሳቸው፣ በአላህም አንቀጾች በመካዳቸው፣ "ነቢያትንም ያለ አግባብ በመግደላቸው" እና ልቦቻችን ሽፍኖች ናቸው በማለታቸው ምክንያት ረገምናቸው፤

አንድ ነብይ በሰው እጅ መገደሉ እና አላህ ያንን ነብይ እንዲገደል መፍቀዱ ያ ነብይ ኃሳዌ ነብይ ለመሆኑ መስፈርት ነው ያለው ማን ነው? የእስራኤል ልጆች ነብያትን ያለ አግባብ ገድለዋል፤ ታዲያ የተገደሉት ነብያት ሰማዕታት ናቸው ወይስ ኃሳውያን? አይ የነብያት መገደል ቁርአን ላይ ብቻ ነው ያለው እዳትሉ ባይብሉ ላይ ፍንትውና ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል፦
ሉቃስ 11፥47 አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፥ ወዮላችሁ።
ሉቃስ 11፥49-51 ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፦ ወደ እነርሱ ""ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ"" ያሳድዱማል፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው ""የነቢያት ሁሉ ደም""፥ ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፥ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል።

ታዲያ የተገደሉት ነብያት ሰማዕታት ናቸው ወይስ ኃሳውያን? አንድ ነብይ የሚደርስበት ስደት፣ እንግልት፣ እስራት እና ሞት የአላህ ነብይ እንዳልሆነ መስፈርት ሊሆን አይችልም። ነብያችን"ﷺ" ላይ ከሃድያን ሊያስሯቸው፣ ሊያሳድዷቸው እና ሊገሏቸው እንደነበረ እና አላህ ይህንን ምክር እንዳከሸፈ ይናገራል፦
8:30 እነዚያም የካዱት "ሊያስሩህ ወይንም "ሊገድሉህ" ወይም ከመካ ሊያወጡህ" በአንተ ላይ በመከሩብህ ጊዜ አስታውስ፤ ይመክራሉም አላህም ተንኮላችውን ይመልስባቸዋል፤ አላህም ከመካሪዎች ሁሉ በላይ ነው።

ስለዚህ ነብያችን"ﷺ" ከበፊታቸው መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆኑ መልክተኛ አይነት እንጂ ሌላ አይነት አይደሉም፤ መሞት ወይም መገደል የአንድ ነብይ እጣ ፋንታ ነው፦
3:144 ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ታድያ ""ቢሞት፥ ወይም ቢገደል"" ወደኋላችሁ ትገለበጣላችሁን? ወደኋላዉ የሚገለበጥም ሰዉ አላህን ምንም አይጐዳም። አላህም አመስጋኞቹን በእርግጥ ይመነዳል።

ነብያችን"ﷺ" በ 628 AD በኸይበር ዘመቻ ጊዜ አይሁዳዊ ሴት ዘይነብ ቢንት ሀረስ የምትባል በበግ ወርች ስጋ ምግብ አመጣችላቸውና በሉ፤ ያ ምግብ የተመረዘ ነበር እና ከባልደረዎች አንዱ ሞተ፤ ከዚያም ጅብሪል መጥቶ የተመረዘ መሆኑን ለነብያችን"ﷺ" ነገራቸው፤ ከዚያም ማንም እንዳይመገቡ አዘዙ፤ ነገር ግን ያ መርዝ በደም ስራቸው ውስጥ እስኪሞቱ ድረስ አሉታዊ ተፅእኖ አድርጎባቸዋል፤ ይህንን እሳቸው እንዲህ በማለት ይገልፃሉ፦
ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 64 , ሐዲስ 450:
ዓኢሻ”ረ.ዐ.” እንደተረከችው፦ ነብዩ"ﷺ" ሊሞቱ በህመማቸው ሳሉ እንዲህ ይሉ ነበር፦ "ዓኢሻ ሆይ በኸይበር የበላሁት ምግብ እስካሁን ይሰማኛል፤ አሁንም በዚያ መርዝ "የደም ስሬ" እንደተቆረጠ ይሰማኛል قَالَ عُرْوَةُ قَالَتْ عَائِشَةُ ـ رضى الله عنها ـ كَانَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم يَقُولُ فِي مَرَضِهِ الَّذِي مَاتَ فِيهِ ‏ "‏ يَا عَائِشَةُ مَا أَزَالُ أَجِدُ أَلَمَ الطَّعَامِ الَّذِي أَكَلْتُ بِخَيْبَرَ، فَهَذَا أَوَانُ وَجَدْتُ انْقِطَاعَ أَبْهَرِي مِنْ ذَلِكَ السَّمِّ ‏"‌‏

"አብሀር" أَبْهَر ማለት "የደም ስር" ማለት ነው፤ ልብ አድርጉ አንዳንድ ሚሽነሪዎች ይህንን ሐዲስ ተንተርሰው፦ ""ነብያችሁ ከቀጠፉ አላህ የልባቸውን ደም ስር እንደሚቆርጥ ተናግሮ ነበር፤ ስለዚህ ነብያችሁ የደም ስራቸው መቆረጥ መሰማቱ መቅጠፋቸውን ወሊአዑዙቢላህ ያሳያል"" ይላሉ፤ ሲጀመር "ደም ስሬ ተቆረጠ" እና "እንደ-ተቆረጠ" የሚሉት ቃላት ለየቅል ናቸው፤ ሲቀጥል ቁርአኑ የሚለውን እና ገለባው ትችት እስቲ እንየው፦
69፥44-46 በእኛ ላይም ከፊልን ቃላት ያላልነውን "በቀጠፈ" ኖሮ وَلَوْ تَقَوَّلَ عَلَيْنَا بَعْضَ ٱلْأَقَاوِيلِ ፤ በኀይል በያዝነው ነበር لَأَخَذْنَا مِنْهُ بِٱلْيَمِينِ ፡፡ ከዚያም ከእርሱ የልቡን ሥር በቆረጥን ነበር ثُمَّ لَقَطَعْنَا مِنْهُ ٱلْوَتِينَ ፡፡
ነጥብ አንድ
"ቀጠፈ"
"ቀጠፈ" ለሚለው ቃል የመጣው "ተቀውወለ" تَقَوَّلَ ሲሆን አላፊ ግን እንጂ ወደፊት ከቀጠፈ የሚል ፍቺ የለውም፤ ስለዚህ ከአለፈ ድርጊት ጋር እንጂ ከወደፊት ሞታቸው ጋር እንዳይያያዝ ሰዋሰዉ አይፈቅድላችሁም። ይህንን "ተቀውወለ" የሚለው ቃል በሌላ አንቀፅ አላፊ ግን መሆኑን መረዳት ይቻላል፦
52፥33 ወይም «"ቀጠፈው" ይላሉን?» አይደለም፤ በእውነቱ አያምኑም أَمْ يَقُولُونَ تَقَوَّلَهُۥ ۚ بَل لَّا يُؤْمِنُونَ ፡፡

ስለዚህ አላህ ይህንን አንቀፅ ያወረደበት ምክንያት ከሃድያን ነብያችንን ከልብ ወለድ፣ ከቀድሞ ሰዎች ወይም ከባለቅኔ ወይም ከጠንቋይ አሊያም ከሸይጣን ቀጥፏል ላሉበት መሳለቂያ መልስ ነው፦
69፥41-43 እርሱም የባለቅኔ ቃል አይደለም ጥቂትን ብቻ ታምናላችሁ። የጠንቋይም ቃል አይደለም ጥቂቱን ብቻ ታስታዉሳላችሁ። ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው።
53፥3-4 ከልብ ወለድም አይናገርም وَمَا يَنطِقُ عَنِ ٱلْهَوَىٰٓ ፡፡
እርሱ ንግግሩ የሚወርረድ ራእይ እንጅ ሌላ አይደለም إِنْ هُوَ إِلَّا وَحْىٌۭ يُوحَىٰ ፡፡
25፥5-6 አሉም «የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናት፡፡ አስጻፋት፡፡ እርሷም በእርሱ ላይ ጧትና ማታ ትነበብለታለች፡፡» «ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው፡፡ እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና» በላቸው፡፡
81:25 እርሱም ቁርአን የርጉም ሰይጣን ቃል አይደለም።
41:42 ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም፤ ጥበበኛ ምስጉን ከሆነው ጌታ የተወረደ ነው።

ነጥብ ሁለት
"የልብ ስር"
"ወቲን" وَتِين ማለት "የልብ ስር" ማለት ሲሆን ይህ የልብ ስር ከተቆረጠ አንድ ሰው ይሞታል፤ አላህ ምንም አልቀጠፈም፤ ከዚህ በፊት ቢቀጥፍ ኖሮ የልቡን ስር እንቆርጠው ነበር እያለን ነው፤ ነገር ግን ነብያችን"ﷺ" በ 628 AD መርዙን በልተው ከእርሳቸው ጋር የነበረው ሰሃባ ሲሞት እርሳቸው ግን 4 ዓመት ቆይተው በ 632 AD አርፈዋል፤ ሐዲሱ የሚለው "አብሀር" أَبْهَر ማለትም "የደም ስር" እንጂ "ወቲን" وَتِين ማለትም "የልብ ስር" አይደለም።
ሲጀመር እንደው መርዝ እኮ ከገደለም ገደለ ነው ወይም ከማረም ማረ ነው እንጂ 4 ዓመት አቆይቶ ይገላልን?
ሲቀጥል ነብያችን"ﷺ" የተሰማቸው ነው እንጂ መርዙ ደም ስሬን ቆረጠው መች አሉ? እንደ ተቆረጠ ማለት ተቆረጠ ማለት ነውን?
ሲሰልስ "አብሀር" ማለት እና "ወቲን" ማለት በየትኛው ቀመር እና ስሌት ነው አንድ ቃላት የሚሆነው?
ሲያረብብ እውነቱ መርዙ የደም ስራቸውን ቆርጦት ከገደላቸውም የመርዙ መንስኤ ዘይነብ ቢንት ሀረስ ስለሆነች በሰው እጅ ከተገደሉ እንደማንኛው ነብይ ሰማዕት ይሆናሉ። ነብያችን"ﷺ" ቢሞቱ ወይም ቢገደሉ በክህደት ወደኋላችሁ ትገለበጣላችሁን? ወደኋላዉ ብትገለበጡ አላህን ምንም አትጎዱም፦
3:144 ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፤ ታድያ ""ቢሞት፥ ወይም ቢገደል"" ወደኋላችሁ ትገለበጣላችሁን? ወደኋላዉ የሚገለበጥም ሰዉ አላህን ምንም አይጐዳም። አላህም አመስጋኞቹን በእርግጥ ይመነዳል።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም
ሲኖፕቲክ ወንጌል

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥79 *ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው*፡፡ ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው፡፡ ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት ኃጢኣት ወዮላቸው፡፡ فَوَيْلٌۭ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ ٱلْكِتَٰبَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَٰذَا مِنْ عِندِ ٱللَّهِ لِيَشْتَرُوا۟ بِهِۦ ثَمَنًۭا قَلِيلًۭا ۖ فَوَيْلٌۭ لَّهُم مِّمَّا كَتَبَتْ أَيْدِيهِمْ وَوَيْلٌۭ لَّهُم مِّمَّا يَكْسِبُونَ

ኢየሱስ በዐረማይክ ዘዬ ተናግሮት የነበረው ቀዳማይ ወንጌል ጥናት በነጠላ "ሎጂኦን" λόγιον በብዜት "ሎጂያ" λόγια ይባላል። ይህም በቃል"oral" ሲተላለፍ የነበረ ወንጌል ነበር። ሐዋርያቱም ለተማሪዎቻቸው በቃል ሲያስተላልፉ ኢየሱስ ያስተማረውን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ያሳለፈውን የሕይወት ታሪክ፣ የሠራውን ታምር እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ያደርጋቸው የነበሩት ሙግቶችን ጨምረው አስተላልፈዋል። እነዚህም ተማሪዎች ከተለያየ ምንጭ ሲሰበስቡት የነበረው ስብስብ የሚያጠናው ጥናት "አንቶሎጂ" ἀνθολογία ይባላል።

"ሲኖፕቲክ"Synoptic" የሚለው የኢንግሊሹ ቃል "ሲኖፕቲከስ" συνοπτικός ከሚለው ከግሪኩ ቃል የተወሰደ ሲሆን "ተመሳሳይ" ማለት ነው። የማርቆስ፣ የማቴዎስ እና የሉቃስ ወንጌል ከዮሐንስ ወንጌል በተለየ መልኩ ታሪካዊ መመሳሰል ስላላቸው "ሲኖፕቲክ ወንጌል" ይባላሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ የተለያየ ንድፈ-አሳብ"theory" አሉ፤ እነዚህም፦ የማቲያን ተቀዳሚነት፣ የማርካን ተቀዳሚነት፣ የሉካን ተቀዳሚነት እና "Q" ምንጭ ናቸው።
± የማቲያን ተቀዳሚነት የሚባለው የአውግስቲን ንድፈ-አሳብ መሰረት ያደረገ ቅድሚያ የዘገበው ማቴዎስ ነው የሚል ንድፈ-አሳብ ነው፥ ይህም "ኤም" M ምንጭ ይባላል፤ "M" የሚለው "ማቴዎስ ምንጭ"source" ማለት ነው።
± የማርካን ተቀዳሚነት የሚባለው የአዩስቲን ፋረር ንድፈ-አሳብ መሰረት ያደረገ ቅድሚያ የዘገበው ማርቆስ ነው የሚል ንድፈ-አሳብ ነው።
± የሉቃን ተቀዳሚነት የሚባለው የሮበት ንድፈ-አሳብ መሰረት ያደረገ ቅድሚያ የዘገበው ሉቃስ ነው የሚል ንድፈ-አሳብ ነው፥ ይህም "ኤል" L ምንጭ ይባላል፤ "L" የሚለው "ሉቃስ ምንጭ"source" ማለት ነው።
± ማቴዎስ እና ሉቃስ ከማርቆስ እና ከሌላ ምንጭ ወስደዋል የሚለው ንድፈ-አሳብ "ኪው" Q ምንጭ ይባላል፤ "Q" የሚለው "ኪውለ" Quelle ከሚል ከጀርማኒክ ቃል የመጣ ሲሆን "ምንጭ" ማለት ነው።

አብላጫውን የአዲስ ኪዳን ዐበይት ለዘብተኛ ሆነ ጽንፈኛ ምሁራን ማርቆስ የማቴዎስ እና የሉቃስ ወንጌል ምንጭ እንደሆነ ይስማማሉ። ማርቆስ ከ 66-70 ዓመተ-ልደት"AD" ሲጽፍ ከእርሱ በኃላ የማቴዎስ ጸሐፊ ከ 80-90 ዓመተ-ልደት"AD" እንዲሁ ሉቃስ ከ 80-110 ዓመተ-ልደት"AD" እንደጻፉ ይገመታል።
ማቴዎስ ለዕብራውያን በ 50 ዓመተ-ልደት"AD" ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር፥ ይህ ደብዳቤ ሲጠፋ አንድ ማንነቱ በውል የማታወቅ ሰው በማቴዎስ ስም የማርቆስን ወንጌል ምንጭ አድርጎ 80-90 ዓመተ-ልደት"AD" የማቴዎስን ወንጌል ጽፋል።
ይህ የማቴዎስ ወንጌል ከማርቆስ ወንጌል ላይ እየወሰደ ቢጽፍም በማርቆስ ላይ የሚጨምረም፣ የሚቀንሰው እና የሚለውጠው ቃላት አለ። ይህንን ነጥብ በነጥብ እንመልከት፦

ነጥብ አንድ
"መጨመር"
“መሢሕ” مَسِيح የሚለው የዐረቢኛ ቃል፣ “መሢሐ” מָשִׁ֫יחַ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል፣ “ክርስቶስ” Χριστός የሚለው የግሪክ ኮይኔ ቃል ትርጉማቸው ተመሳሳይ ሲሆን "የተቀባ" ወይም "ቅቡዕ" ማለት ነው፥ ኢየሱስ አይሁዳውያን የሚጠብቁት መሢሕ ስለሆነ "መሲሕ" የሚለው ቃል ቁርኣን ውስጥ በዘጠኝ አንቀፆች 11 ጊዜ ተጠቅሷል። ኢየሱስ እርሱ ማን እንደሆነ ለሐዋርያቱ ሲጠይቅ ጴጥሮስ የመለሰው መልስ፦ "አንተ ክርስቶስ ነህ" ብሎ ነው፦
ማርቆስ 8፥29 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፦ *"አንተ ክርስቶስ ነህ"* ብሎ መለሰለት።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ፦ "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ" ብሎ ጨምሮበታል፦
ማቴዎስ 16፥16 ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ *"የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ"* አለ።
ነጥብ ሁለት
"መቀነስ"
የአንድ አምላክ አስተምህሮት የሙሴም ሆነ የኢየሱስ ቀዳማይ መርሕ ነው። "እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው" የሚለው እንዳስተማረ ማርቆስ ዘግቧል፦
ማርቆስ 12፥29-30 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ *"እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው"*፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፡ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ፦ "እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው" የሚለውን መርሕ ቀንሶታል፦
ማቴዎስ 22፥36-37 መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።

ነጥብ ሦስት
"መለወጥ"
አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ "ቸር መምህር ሆይ"*፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ "ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም" አለው፦
ማርቆስ 10፥17-18 እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ *"ቸር መምህር ሆይ"*፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ *"ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም"*።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ፦ "ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም" የሚለውን "ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው" በማለት ለውጦታል፦
ማቴዎስ 19፥16-17 እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ፦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። እርሱም፦ *"ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው"*፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ" አለው።

"ትለኛለህ" እና "ትጠይቀኛለህ" ሁለት የተለያየ ቃላትና ትርጉም ያላቸው ሐረግ ናቸው፤ "መልካም የሆነ ነገር" እና "አንዱ እግዚአብሔር" ሁለት የተለያዩ ምነቶች ናቸው። ነገር ሁሉ ፍጡር ነው፤ እግዚአብሔር የነገር ሁሉ ፈጣሪ ነው።
ማርቆስ ሐዋርያት ኢየሱስን፦ "መምህር ሆይ" ብለው እንደጠሩት ይናገራል፦
ማርቆስ 9፥5 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን *"መምህር ሆይ"*፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው።
ማርቆስ 4፥38 እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም፦ *"መምህር ሆይ"*፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ በአንድ አንቀጽ፣ በአንድ ጊዜና ክስተት "መምህር ሆይ" የሚለውን "ጌታ ሆይ" በማለት ለውጦታል፦
ማቴዎስ 17፥4 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን *"ጌታ ሆይ"*፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።
ማቴዎስ 8፥24-25 እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ *"ጌታ ሆይ"*፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት።

"ጌታ" ማለት እና "መምህር" ማለት ሁለት ለየቅ ቃላት ናቸው።
ማርቆስ ኢየሱስ፦ "የአምላክን ፈቃድ" ብሎ እንደተናገረ ይናገራል፦
ማርቆስ 3፥35 *"የአምላክን ፈቃድ"* የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።

ነገር ግን የማቴዎስ ጸሐፊ የማርቆስን ዘገባ ምንጭ አድርጎ በአንድ አንቀጽ፣ በአንድ ጊዜና ክስተት "የአምላክን ፈቃድ" የሚለውን "የአባቴን ፈቃድ" በማለት ለውጦታል፦
ማቴዎስ 12፥50 በሰማያት ያለውን *"የአባቴን ፈቃድ"* የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።

"አምላክ" ማለት እና "አባት" ማለት ሁለት ለየቅል ቃላት ናቸው።
እንግዲህ እኛ ሙሥሊሞች እነዚህን በማርቆስ ላይ የተጨመሩትንና የተለወጡትን፦ ኢየሱስን "የአምላክ ልጅ" እና "ጌታ" ፈጣሪን "አባት" የሚሉትን ቃላትና እሳቤ ሳንቀበል ማርቆስ ባስቀመጠው፦ ኢየሱስን "መሢሕ" እና "መምህር" ፈጣሪን "አምላክ" ብለን ብንቀበል በእውነት የሐዋርያት ሥረ-መሠረት ቅሪት ተቀበልን ማለት ነው።

ከዚህ ሁሉ የሚያጅበው ምሁራን አራቱ ወንጌላት ውስጥ ያልተካተቱ የኢየሱስ ንግግር እንዳሉ መቀበላቸው ነው፤ ይህ እሳቤ በነጠላ "አግራፎን" αγραφον በብዜት "አግራፋ" αγραφα ይባላል፥ የአሌክሳንድሪያ ክሌመንት፣ ጀስቲን ማርቲን፣ ኦሪገን ወዘተ ኢየሱስ ተናገረ ብለው የተናገሯቸው በቁና ንግግሮች አራቱ ወንጌላት ውስጥ ያልተካተቱ አሉ። ለናሙና ያክል ባይብል ውስጥም ማየት
ይቻላል፦
1ኛ ዮሐንስ 1፥5 ከእርሱ የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። *”እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም”* የምትል ይህች ናት።
የሐዋርያት ሥራ 20:35 እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። *”ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው”* እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።

ኢየሱስ፦ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ዮሐንስም፦ “ከእርሱ(ከኢየሱስ) የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት ይህች ናት” ብሎናል፤ ግን ይህ ከኢየሱስ የሰሙት መልእክት በአራቱ ወንጌላት የለም ማለት ኢየሱስ አልተናገረውም ማለት አይደለም፤ በተጨማሪ በተመሳሳይ መልኩ ኢየሱስ፦ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሎ ተናግሮ ነበር፤ ይህ ቃል አራቱ ወንጌል ላይ ማለት ኢየሱስ አልተናገረውም ማለት አይደለም። ይህ ከላይ እንደተጠቀሰው "አግራፎን" ወይም "አግራፋ" ይባላል።

ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም