ግጥም ብቻ 📘
67.5K subscribers
1.53K photos
31 videos
61 files
174 links
በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።

@getem @serenity13
@wegoch @Words19
@seiloch @shiyach_bicha
@zefenbicha

@leul_mekonnen1
Download Telegram
#የፈረሱ_መልኮች

( ኤፍሬም ስዩም )

ከዘመናት ኋላ
ድንገት ባጋጣሚ አንድ ቀን ያየኋት
እሷን እያሰብኩኝ
በበራቸው በኩል ትላንትና አለፍኩኝ።
ገረመኝ
ደነቀ…
ለካ . .
ስፍራቸውን ለቀው
ቤተሰቡ ሁሉ ከዚያ ቦታ ጠፍቷል
ኮረብታው ላይ ያለው መኖሪያቸው ግና…
ግድግዳና ጣሪያ አጥሩ ፈራርሶ ወለሉ ይታያል
እኔ በበኩሌ… ከዚህ የበለጠ ላወራ ምችለው
አንድም ቃል የለኝም
ፈርሶ ለማየው ቤት አራት ኪሎ ላለው
ሁኔታው…

ክፍት የእንጨት አጥር
ትንሽ ገደድ ያለ… ልሙጥ ቆርቆሮ በር
መላ ቅጥ የሌለው
ለቅሶና ሙዚቃው የማይለይ ሰፈር
ነበር …
ግን…
ፈገግታ የሞላው
በቤቱ ጥበት ልክ… ደስታ የማያጣው
ግድግዳውን የሚያልፍ ሃዘን የወረረው
ላ'መት በዓልና
ላ'መት በዓል ዋዜማ ብቸኛ ቀናቸው
እፎይ የሚሉበት
ህፃናት ተጫውተው
ጠግበው የሚያድሩበት አዋቂዎች በልተው
ሰፈር…
እዚያ ነበር።
አሁን ግን የለችም
ውበቷ ተረስቶ የገባችበትን አንድም የሚያውቅ የለም
የትገባ - ያ - ውበት
የትገባ- ያ - ቁመት
ሲያስጨንቅ የኖረው ወንዱን ሁሉ ባምሮት
ተስፋ የነበረው ለመንደሯ ጭንቀት።
እልፍ መአት ወንዶች በበሯ አልፈዋል
ባይተኟትም እንኳ
አይኗን አይተው ብቻ እድሜ ቀጥለዋል
ግና…
ያሳዝናል…
እድሜ የጠገቡ ጉልበተኛ ወንዶች ቤቷን አፍርሰዋል
እንኳን ቤቷ ፈርሶ
አንድ ቀን ስታኮርፍ እድሜ እንደምትቀንስ መች ይገባቸዋል።

ድንገት ባጋጣሚ
አንድ ቀኑን ያየኋት እሷን እያሰብኩኝ
ከዘመኋላ
በበራቸው በኩል ትላንትና አለፍኩኝ
ገረመኝ
ደነቀኝ
ለካ…
ስፍራቸውን ለቀው
ቤተሰቡ ሁሉ ከዚያ ቦታ ሄዷል
ኮረብታው ላይ ያለው መኖሪያቸው ግና…
ግድግዳና ጣሪያው አጥሩ ፈራርሶ ወለሉ ይታያል
እኔ … በበኩሌ…
ከዚህ የበለጠ ልናገር የምሻው
አንድም ቃል የለኝም ፈርሶ ለማየው ቤት . . አራት ኪሎ ላለው
ልደታ ላይ ላለው
ሰንጋ ተራ ላለው
የትም ሰፈር ላለው።
ስለሷ ግን ላውራ
ውበት ጠፍቶ እዳይቀር ከግድግዳው ጋራ
በእርግጥም መንደሯ
ተስፋው የሞተላበት
ጦር የወደቀበት
በተራ ወታደር የተረታ ንጉሥ የሚመስል አይነት።
ሞቱን የሚጠብቅ
ታስሮ የሚማቅቅ
መሞት አለመሞት የኑሮ ትንቅንቅ
እሷ መንደር መሃል ይታያል ይሄ ሃቅ።

የፈረሱ መልኮች
የገጠጡ ገፆች … የወየቡ እጆች … ያፈጠጡ አይኖች
የጠቆሩ ቀዮች
ወዝ አልባ ጥቁሮች
ቆዳውን የበላ እረዣዥም አጥንት
ብዙዎች የሞሉበት
ሞልተው ሚሞቱበት
ከሕይወት ተፋተው በተስፋ እጦት ምክንያት።
ሕዝቡ ሚደርበው
ነጠላና ጋቢው
ሀዘን የሸመነው ጨለማ ብርድልብስ
ግራ ጎረቤቷ ህፃን የሚያለቅስ
እናቱን የሞተች በዐዋላጅ እጦት።
የቀኝ ጎረቤቷ እናት ምታቃስት
ሴት ልጇ ያበደች የምታስታምማት።
እወዲያ ጥግ ላይ…
ቤት አልባ- ጎልማሳ
በረሃቡ ምክንያት. . አካሉ የከሳ
ከዘመና በፊት…
በሺህ ዘጠኝ መቶ . . ዘጠና ሁለት ዓመት
ሁለት ዓይኑን ያጣ …በወንድሞቹ ቀስት…
ወዲህ ከትቦው ጎን
ያገሩ ቆሻሻ በሚያልፍበት በኩል
መምጫው ያልታወቀ… አንድ ትንሽ ህፃን…
እድሜው የሚመጥን አስር ዓመት ያህል
የሰውና የከብት ቆሻሻ ካለበት
ትቦ- ጎንሚተኛ
በልጅነት እድሜ የሌሉት ወላጆች
በልጅነት ዕድሜው የሽማግሌ አይኖች
ችግር የሰራበት…
ትንሽ ግንባሩ ላይ አንድ ሺህ መስመሮች
መንተራሻው ድንጋይ ፍራሹ ኮረኮንች
በጀርባዋ በኩል

ሰባት የወለደ አባት የሚያነክስ
ሰባቱን ልጆቹን ድንጋይ ፈልጦ ሚያጎርስ
ሰባቱን ልጆቹን. . ለምኖ የሚያለብስ።
ከፊቷ ትንሽ ሱቅ
ሃሊማና ከድር
ሁለት ባለትዳር… የሰፈሩ ህይወት. . የሰፈሩ አለኝታ
በጭልፋ የሚሸጡ የሃምሳ ሳንቲም ፓስታ
ይህን የሚመስሉ ብዙዎች የሞሉበት
በቁም የሚያለቅሱ ብዙዎች የሞቱበት
የፈረሱ መልኮች. . የሕይወት ግምጃ ቤት።

ነበረ…
ዛሬ ፈርሶ ማየው
መንደሯን የሞላው
የሚገርመው ግና?…
መሶብ ሙሉ ስቃይ . . እንስራ ሙሉ እምባ
የሆነው ይህ ቦታ
የመንገድኛውን. . ዓይን. . የመንገደኛውን. . ልብ ባዘን እያጓጓ
እሷ ግን ነበረች ቀይ ፅጌረዳ የእሾህ ማል አበባ
እናም በዚያ ሰፈር
እናም በዚያ መንደር
የርሷ መኖር ብቻ ለሰፈሩ ሰዎች ሳቅ ይፈጥር ነበር
ተስፋ ይሰጥ ነበር
ጥጋብ ይሆን ነበር
*
ባለማወቅ እንጅ
ጤዛውን ለማበስ
ፅጌውን መቀንጠስ… ማስተዋል ቢመስለን
ባለማወቅ እንጂ…
ላንድ ዝግባ ሲባል
እልፍ አበባ መቁረጥ እልፍ አበባ መጣል
ማስተዋል ቢመስለን
ባለማወቅ ነው እንጅ
ያለማወቅ እውቀት ስልጣኔ መስሎን
ልማት ነው እያልን የሙጥኝ ስላልን
እንጂ…
ብናውቀው ኖሮማ ውበት ቅርስ እንዲሆን…
ብናውቀው ኖሮማ. .
በህይወት ግምጃ ቤት.. ተጥሎ የሚኖር ተምሳሌት እንደሆን
ብናውቀው ኑሮማ
በውበት ብናምርን ቅርስን ብናከብር
ያን ያህል ጨክኖ ይህን የርሷን መንደር
ይህን የእርሷን ሰፈር
ማን ያፈርሰው ነበር።…

ዛሬ…
በዚያ መንደር
ከልጅት መኖሪያ ፍርስራሽ ጣውላ ስር
ከቤተ-መንግስቱ አረንጓዴ ሰፈር
ክፉ ጠረንይዞ ነፋስ ይጓዝ ነበር።

(ኑ፦ግድግዳ እናፍርስ ከተሰኘው መድብል የተወሰደ ገፅ፦84 - 88)

#ገፅ

@getem
@getem
@gebriel_19
👍1