ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
" #እምዬ_ምኒልክ የታሪክ #ፈርጥ "
______________________
አፄ ምኒልክ ከአፄ ልብነድንግል ልጅ ከአቤቶ ያዕቆብ ትውልድ ሲያያዝ የመጣ የስመ ጥሩ ንጉሥ የሣህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የንጉሥ ኃይለ መለኮት ልጅ ናቸው።
#ትውልዱም_ከአቤቶ ያዕቆብ ዠምሮ ቢቆጠር አፄ ምኒልክ ፲ ፫ ተኛ ይሆናሉ፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ ና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ቅዳሜ ነሐሴ ፲ ፪ ቀን ፲ ፰ ፻ ፴ ፮ ዓ.ም. ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ከሚባል ሥፍራ ተወልደዋል፤ ከዚያም በ አንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሱ።
አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጁን መወለድ ሲሰሙ “ምን ይልህ ሸዋ” በሉት ብለው ስም አወጡ። እሳቸው “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያ ን ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበር ‘ምኒልክ’ የኔ ስም ነው ብለው ነበር። ሆኖም፣ በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ።
#ከዚህ በኋላ “ምኒልክ የኔ ስም አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት” ብለው አዘዙ ። ይላል ( ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፉ /ገጽ ፲፪)
አፄ ምኒልክ በተወለዱ በ፲ ፩ ዓመት በ፫ ወር በሺ ፰ ፻ ፵ ፰ ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ በመጡ ጊዜ ይዘዋቸው ወደ ጎንደር ሄዱ ፤ በዚያም አፄ ቴዎድሮስ ብልዕነታቸውንና አስተዋይነታቸውን ተመልክተው አብረው በማዕረግ ይዘዋቸው ሲኖሩ ቆዮ በመጨረሻም ሴት ልጃቸውን ወይዘው አልጣሽ ቴዎድሮስን ዳሩላቸው።

#በዓመት_በዓል የፈረስ ጉግስ ከምኒልክ በቀር ሌላ ሰው አይታይም ነበር ይባላል። በመጨረሻ ግን አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ አደርጋለሁ በማለት ያቀዱትን ዕቅድ ፣ በያሉበት መኳንቱና ሕዝቡ እየሸፈቱ ስላበላሹባቸው ከብስጭት የተነሳ ሰውን ሁሉ ያለ ሕግ በገደሉና ባሰሩ ጊዜ እንደዚሁ አቤቶ ምኒልክን አስረው ወደ መቅደላ ላኩዋቸው ፤ በዚያም ከታመኑ አሽከሮቻቸውና ከእናታቸው ከወይዘሮ እጅጋየሁ ጋር ሆነው ከሸዋ ባለ አባቶች ጋር ውስጥ ውስጡን እየተላላኩ ምቹ የማምለጫ ጊዜ ሲፈልጉ ወዲያው አፄ ቴዎድርስ የትግሬና የጎንደር፣ የበጌምድርም ሕዝብ ሸፍቶባቸው ወደ ላይና ወደ ታች ሲሮጡ አቤቶ ምኒልክ ከወሎዎች ጋር ውስጥ ውስጡን ተስማምተው ከመቅደላ ፲ ፰ ፻ ፶ ፯ ዓ.ም ሰኔ ፳ ፬ ቀን ሌሊት አምልጠው ወሎ ገብተው አደሩ ።
በዚህ ጊዜ አቶ በዛብህ እንደ ንጉሥ ሆነው ሸዋን ሲገዙ ይህንኑ ሰምተው ነበርና እሰሪልኝ ብለው ለወሎ ገዢ ለወዘሮ ወርቂት ገጸ በረከት ጨምረው ላኩላቸው ወይዘሮ ወርቂትም ስለ አቶ በዛብህ ሳይሆን መቅደላ ለታሰረው ልጃቸው ለውጥ አድርገው ለአፄ ቴዎድርስ ለመመለስ ምኒልክ የቁም እስረኛ አድርገው ወደ አፄ ቴዎድሮስ መልክተኛ ላኩ ።
#መልክተኞቹም ወደ መቅደላ በደረሱ ጊዜ አፄ ምኒልክ አምልጠው ስለነበር አፄ ቴዎድሮስ ተበሳጭተው እስረኛውን ሁሉ እጅና እግሩን እየቆረጡ ገደል ሲጥሉ እንዲ ተብሎ ተገጠመላቸው።

" #አፄ_ቴዎድሮስ_እጅግ_ተዋረዱ
#የሸዋን_ሰው_ሁሉ_እጅ_ነስተው_ሄዱ "

#የወይዘሮ ወርቂትም ልጅ አብሮ መጣሉን ሰሙ ስለዚህ መልክተኞቹ ተመልሰው ይህንኑ ለወዘሮ ወርቂት ነገሩ ወይዘሮ ወርቂትም በእግዚአብሔር ሥራ ተደንቀው ቦሩ ሜዳ ላይ ምኒልክን ተቀብለው፣ “ #የሸዋ_ሰው_አውራህ_መጥቷልና_ደስ_ይበልህ_ተቀበል ” ብለው አዋጅ አስነግረው፣ አጃቢ አድርገው በመለከትና እምቢልታ አሳጅበው ከሸዋ ድንበር ድረስ ላኳቸው። ሸዋን ‘ንጉሥ ነኝ’ እያሉ ይገዙ የነበሩት አቶ በዛብህ የምኒልክን ወደመሀል ሸዋ መግፋት ሲሰሙ ለመውጋት ጋዲሎ ከተባለ ሥፍራ ተሠልፈው ሲጠባበቁ፣ አንዲት ሴት እንዲህ ስትል ገጠመች።

«ማነው ብላችሁ ነው ጋሻው መወልወሉ፣
ማነው ብላችሁ ነው ጦራችሁ መሾሉ
ማነው ብላችሁ ነው ካራችሁ መሳሉ፣
የጌታችሁ ልጅ ነው ኧረ በስመ አብ በሉ»

በኃላ ግን አቶ በዛብህ ስለተሸነፈ ከዛ ሸሽተው አፍቀራ ገቡ ከዚህ በኃላ አቤቶ ምኒልክ ከሸዋ በመጡ በ፲ ዓመት ንጉሥ ተብለው ሲገዙ አቶ በዛብህ አፍቀራ ሆነው ታርቀው ለመግባት ወደ ንጉሥ አማላጅ ላኩ።
በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሊታረቋቸው ሲያስቡ የአቶ በዛብህን ሀሳብ አውቃለው ባይ ቀርቦ " አቶ በዛብህ አሁን ታርቄ ልግባ የሚለው ከገባ በኃላ መኳንንቶን እየሰበከ ለማስከዳት ነው እንጂ በእውነት እርቅ ፈልጎ አይደለም በእውነት እርቅ ፈልጎ ከሆነ የአፈቀራን ምሽግ አስረክበኝ ይበሉትና እስቲ ያስረክብሆ?! " ብሎ ተናገረ። ንጉሥ ምኒልክም አቶ በዛብህን የአፍቀራን ምሽግ እንዲያስረክብ ጠየቁት አቶ በዛብህም እኔስ ፈቅጄ ነበር አሽከሮቼ ግን ተው አታስረክብ ይሉኛል ስላሉ ይህም በቂ ምክንያት ሆኖ ስላልተቀበሏቸው ወዲያው ተያዙና ፍርድ ተጀመረ ።
#በፍርዱም_መጀመሪያ ጋዲሎ ላይ አላስገባም ብለው መዋጋታቸውንና ሁለተኛም የአፍቀራን ምሽግ አላስረክብም ማለታቸው እየተጠቀሰ ይሙት በቃ ተብሎ ተፈርዶባቸው በጥይት ተደበደቡ በጥይትም ሲመቱ ባሩዱ ከልብሳቸው ላይ ተያይዞ ገላቸው ስለነደደ አንዲት ሴት ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ገጠመች፤

" #አንተም_ጨካኝ_ነበርክ_ጨካኝ_አዘዘብህ
#እንደ_ገና_ዳቦ_ከላይም_ከታችም_እሳት_ነደደብህ "

አፄ ምኒልክ በአባታቸው ዙፋን ተቀምጠው ንጉሥ ምኒልክ እየተባሉ ይገዙ ዠመር። እንዲህም አድርገው እስከ ፲ ፰ ፻ ፸ ዓ.ም ድረስ ለ፲ ፪ ዓመት በሙሉ የበላይነት ሸዋን ሲገዙ ኖሩ።

የጽሁፉ ግብቶች፦
- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ " የኢትዮጵያ ታሪክ"
- ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ”

አ.አ ኢትዮጵያ
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
የካቲት ፲ ፰ /፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም