ዐውደ ምሕረት
3.68K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ

1 ማቴ 1:1–17 እና ሉቃ 3:23-38 ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ የዘር ሐረጉን ይተነትናል። እነዚህ ሁለት የዘር ሐረግ ትንተናዎች በዮሴፍ በኩል የተቆጠሩ ናቸው። በዮሴፍ በኩል የተቆጠሩበት ምክኒያት ምንድን ነው? ማቴዮስ የዮሴፍን አባት ያዕቆብ ይለዋል። ሉቃስ ደግሞ ዔሊ ይለዋል። እነዚህ እንዴት ይስማማሉ? ለአንድ ሰው ሁለት አባት ሊኖሩት ይችላሉ?

#መልስ
በማቴ 1:1-17 በዚህ ክፍል ማቴዎስ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ድረስ 42 ትውልድ ቆጥሯል። የትውልዱ አቆጣጠር በእመቤታችን በኩል ሳይሆን በዮሴፍ በኩል ነው። ምክኒያቱ ምንድን ነው ቢሉ የሀረገ ትውልድ አቆጣጠር ልማድ መሰረት ትውልድ የሚቆጠረው በወንድ በኩል ስለሆነ ነው። በተጨማሪም ዮሴፍ ከእመቤታችን ጋር በአንድ የትውልድ ሀረግ ውስጥ ስለሆነ በዮሴፍ በኩል መቆጠሩ ሀረገ ትውልዱን አይለውጠውም።
ሉቃ 3:23–38 ሉቃስ "እንደመሰላቸው" (የዮሴፍ ልጅ) ብሎ በመግለጽ ከራሱ ከዮሴፍ ጀምሮ ወደ ላይ እስከ አዳም ድረስ 78 ትውልድ ይቆጥራል። ከማቴዎስ ጋር የሚገናኝበትም የሚለያይበትም አለ። ይህ እንዴት ነው ቢሉ ማቴዎስ የዮሴፍን አባት ያዕቆብ ይለዋል ሉቃስ ደግሞ የዮሴፍ አባት ኤሊ ይለዋል። ሲያዩት የሚጋጭ ይመስላል ግን አይጋጭም። እንዴት ቢሉ ዳዊት ናታን እና ሰሎሞን ሚባሉ ሁለት ልጆች አሉት ማቴዎስ የቆጠረው በሰለሞን የወረደውን ነው። ሉቃስ ደግሞ በናታን በኩል ቆጠረ። እንዲም ቢሆን ዮሴፍ ሁለት አባት አለው ማለት አይደለም። ማቴዎስ በልደት ሥጋዊ ቆጠረ። ይህ ማለት ያዕቆብ የዮሴፍ የሥጋ አባት ነው። ሉቃስ በልደት ሕጋዊ ቆጠረ። እንዴት እንደሆነ እንመልከት

ማቲ የተባለው ሰው ዔሊን ወለዶ ይሞታል። ሉቃ 3:24 ማታን የማቲን ሚስት አግብቶ ያዕቆብን ይወልዳል። ያዕቆብ እና ኤሊ በእናት የሚገናኙ ወንድማማቾች ናቸው። ዔሊ ታላቅ ነው ያዕቆብ ታናሽ። በእስራኤል ልማድ ታላቅ ሳያገባ ታናሽ አያገባም። ኤሊ አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ይሞታል። የኤሊን ሚስት ደግሞ ለያዕቆብ ያጋቡታል። የሙት ወንድምን ሚስት ማግባት በእስራኤል ልማድ ነው። ስለዚህ ሉቃስ ኤሊን የቆጠረው በልደት ሕጋዊ ነው። ኤሊ ዮሴፍን ባይወልደውም ሕጋዊ አባቱ ነው። ያዕቆብ ደግሞ ሥጋዊ አባቱ ነው።

ወደ እመቤታችን ሀረገ ትውልድ ስንመጣ ግን ከአላዛር እንጀምራለን። ማቴ 1:15

አላዛር ማታን እና ቅስራን ይወልዳል። ማታን ያዕቆብን ያዕቆብ ዮሴፍን ይወልዳል። ቅስራ ደግሞ የእመቤታችንን አባት ኢያቄምን ይወልዳል።

2 ዘዳ 34:4–5 "የእግዚአብሔር ባሪያም ሙሴ እንደ እግዚአብሔር ቃል በዚያ በሞዓብ ምድር ሞተ። በቤተ ፌጎርም ፊት ለፊት በሞዓብ ምድር በሸለቆው ውስጥ ተቀበረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም አላወቀም።" እንዲሁም ኢዮብ 42:16-17 "ከዚህም በኋላ ኢዮብ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፥ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ተውልድ ድረስ አየ። ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ።" ይላል። የኦሪት ዘዳግም ጸሐፊ ሙሴ ሲሆን የመጽሐፈ ኢዮብ ጸሐፊ ደግሞ ኢዮብ ነው። ሁለቱም ስለሞታቸው በመጽሐፋቸው እንዴት ጻፉ?

#መልስ
እግዚአብሔር አምላክ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲሁም ለጻድቁ ኢዮብ ከሰጣቸው ጸጋ አንዱ ነቢይነት ነው። ነቢይ ወደ ፊት የሚደረጉትን ነገሮች በሙሉ እግዚአብሔር ገልጦለት ያውቃል። በዚህም መሰረት ሙሴ እና ኢዮብም ነቢያት ስለሆኑ አሟሟታቸውንም ጭምር ያውቃሉ።

3 ዮሐ 14: 27 "ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም።" ይላል በማቴ 10:34 ላይ ደግሞ ጌታችን "በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።" ይላል። በአንድ ቦታ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ሌላ ቦታ ሰላምን ሳይሆን ሰይፍን ለማምጣት መጣሁ ይላል። እነዚህ ኃይለ ቃላት ይጋጫሉ? ካልተጋጩ እንዴት?

#መልስ
ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመምጣቱ ሰላማችን መረጋገጡ ምንም ጥያቄ የሌለው ነገር ነው። ኢሳ 9:6 ሉቃ 2:14 ኤፌ 2:14
ነገር ግን በማቴ 10:34 ላይ ሰይፍን ይዤ ወደ ምድር መጣሁ ማለቱ ሰይፍ በቁሙ የተሳለው ብረት ሳይሆን #ቃለ_እግዚአብሔርን ነው። ቃለ እግዚአብሔር እንደ ሰይፍ በማሰብ በመናገር በመስራት የተሰራውን የሰውን ኃጢአት መርምሮ ኃጥኡን ከጻድቁ ይለያል እንዲሁም ይፈርዳልና ነው። ዮሐ 12:48 ራዕ 1:16 ዕብ 4:12–16 ኤፌ 6:17

4 ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ላይ ስለ ካህኑ መልከጸዴቅ ሲናገር "አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። " ዕብ 7: 3 አለው። ሰው ያለ እናት እና አባት ሊወለድ ይችላል? ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ስለ መልከጸዴቅ ስለምን ተናገረ?

#መልስ
ለመልከ ጸዴቅ እናቱ እገሊት አባቱ እገሌ ነው ተብሎ የተነገረለት እንዲሁም በዚህ ቀን ተወለደ በዚህ ቀን ዐረፈ ተብሎ በሌዋውያን ወይም በእስራኤላዊያን ዘንድ የተጻፈ ምንም መጽሐፍ የለም። ስለ ነገረ ትውልዱም በእስራኤላዊያን ዘንድ አይታወቅም። የዘር ሀረጉም ከሌዋውያን ዘንድ አይቆጠርም። ዕብ 7:6 ነገር ግን መልከ ጸዴቅ የካም የዘር ግንድ ነው ያለው። ለዘመኑ ፍጻሜ የለውም የሚለውም የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር ሰው አይደለም ለማለት እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባል። ሰው ከሆነ በሥጋ መሞቱ የማይቀር ነገር ነው። ያ ማለት ግን ከዚህ በፊት ሞቷል ማለት አይደለም። ዕብ 7:8 በመጽሐፍ ቅዱስ እነ ሄኖክ እነ ኤልያስ ሞትን ሳያዩ እንደተወሰዱ ይታወቃል። መልከ ጸዴቅም ከእነርሱ መካከል አንዱ ነው። በሌዋውያን መጽሐፍ ጥንቱም ሆነ ፍጻሜው ባለመጻፉ ምክኒያት ለህይወቱ ፍጻሜ የለውም ሲል ጽፏል። በዚህም ምክኒያት መልከጸዴቅ ለጌታችን ምሳሌ ሆኗል።

👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit