ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
" #በእናቴ ስም ጽንፍ እስከ ጽንፍ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽ ፍቃዴ ነው"
_________________________


#እመቤታች_ቅድስት_ድንግል_ማርያም እንደ ልጇ ባለ ሞት ሞታ እንደ ልጇ ባለ ትንሳኤ ከሞት ተነስታ ባረገች በ4ዓመቷ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ፊልጵስዮስ ገብተው አስተማሩ ሕዝቡም አምነው ተጠመቁ። ከእግዲህ ወደ ቤተ ጣዖት አትሂዱ አሏቸው የለመድነውን ከከለከላችሁንማ መካነ ጸሎት(የጸሎት ቦታ) ስጡን ፣ ሥሩልን አሏቸው።

#በእውነቱ የሚገባ ጥያቄ ነው ! አንድ ውኃ የያዘ ብርጭቆን ውኃውን ከገለበጥንለት በኋላ ባዶዎን የሚቀመጥ አይደለም ምንም እንኳ በዐይን ባናየውም በእርሱ ፋንታ ብርጭቆውን አየር ይሞላዋል። ሰውም እንዲሁ ነው ሲሰራው የነበረን አንድ ክፉ ልማድ ከሕይወቱ ሲያስወጣ በዛ ባስወጣው ቦታ ሌላ ሰናይ የሆነ ነገርን ሊተካበት ይገባል ።ካልሆነ ግን ክፉ መስራት ትቻለው ደግ ባልሰራ ችግር የለውም ብሎ ክፋትን ትቶ በጎንም ሳይሰሩ መቀመጥ አያጸድቅም " መልካም ሥራ መሥራትን እያወቀ ለማይሰራት ኃጢያት ትሆንበታለችና"


በተጨማሪም ያን ክፉሁን አስወጥቻለው ብሎ ያለ ደግ ሥራ የተቀመጠው ሰው ቤቱን ባዶ አድርጎ እንደጠረገ ሰው ይመስላል ከእርሱ የወጣ አጋንንትም በምድረ በዳ ሲዞር ቆይቶ የዚያ ሰው ቤት(ቤተ ልቡናው) በደግ ሥራ ያልተሞላ ሆኖ ሲመለከት ወደ ቀደመ ቤቴ ልመለስ ይልና ከእርሱ የከፉ ሌሎች ሰባት አጋንንትይ ይዞ ተመልሶ ይገባበታል ለሰውየውም ከድሮ ይልቅ የአሁኑ ሕይወቱ የከፋ ይሁንበታል #ማቴ 12÷45 #ሉቃ 10÷26

#የፊልጵስዮስ አማኞች ጥያቄ የተገባ ነው ያልነው ለዚሁ ነው ሰው ወደ ቤተ ጣዖት መሄዱን ሲያቆም በአንጻሩ በዚያ ፈንታ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሄድ መጀመር አለበት አለበለዚያ ግን ከቤተ ጣዖት ከቀረው ወደ ቤተ እግዚአብሔር ባልሄድም ችግር የለውም ማለት አይገባውም እርሱ ወደ ቤተ ጣዖት መሄድ አቆመ ማለት የቤተ ጣዖቱ ሥርዓትና ልማድ በሀሳብ ሁሉ ወደ እርሱ መምጣታቸው አቆሙ ማለት አይደለምና።

ቤተ መቅደስ እንዲሰሩላቸው የተጠየቁት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ምንም እንኳ ጥያቄው የተገባና ደገኛ ጥያቄ ቢሆንም ማንንም ሳያማክሩ በራሳቸው ውሳኔ መሠረት ጣሉ ግድግዳ ለስኑ ጣራ ክደኑ መስቀል አኑሩ ቤተ ክርስቲያን ተከሉ ብለው ወዲያው አላዘዙም። ከዛይ ይልቅ ወደ ወንድሞቻቸው ወደ ጴጥሮስና ወደ ዮሐንስ የፊልጵስዮስ አማኞች ቤተ መቅደስ እንድንሰራላቸው ጠየቁን ምን ይሻላል ? ብለው መልክት ላኩባቸው እነርሱም ያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቃድ አንዳች ልታደርጎ አይገባም እናንተም ጸልዮ እኛም እንጸልያለን ብለው መለሱላቸው። ቤተ መቅደስ ዝም ተብላ አትሰራም፣ አትተከልም" ሁሉ በአግባቡና በሥርዓት ይሁን" እንደተባለ በአግባቡና በሥርዓት ልትሰራ ያስፈልጋታል 1ኛ ቆሮ 14፥40

#ቤተ_መቅደስ ወይም ቤተ እግዚአብሔር ለመሥራት በመጀመሪያ ፈቃደ እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት መጠየቅ ይገባል ። እንደ ቅድስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ በቀራኒዮ አደባባይ ለሰው ልጆች ቤዛ ሲል በመስቀሉ ብዙ ደም አፍስሷል ይህንንም ደም ቅዱስ ዑራኤል መላእክ በጽዋው ቀድቶ በብርሃን መነሳንስ ፍጥረት ዓለሙን ለመቀደስ ወደ ምድር እረጭቶታል። ታድያ ቤተ ክርስቲያን ስትሰራ ይህ የደሙ ነጠብጣብ ባለበት ወይም በነጠበበት ቦታ ላይ መሆን አለበት እስካሁን የተሰሩ ቤተ ክርስቲያናት ሁሉ እግዚአብሔር ባወቀ ለቅዱሳኑ በመግለጥ የተሰሩ ናቸው ታዲያ ይህን መሰሉን ቦታ ለማወቅ ከእግዚአብሔር ጋር በጸም በጸሎት መነጋገር ፍቃደ እግዚአብሔር መጠየቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። "ያለ እኔ አንዳች ልታደርጉ አይቻላችሁም" #ዮሐ 15÷5

ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስም የቅዱስ ጴጥሮስን እና የቅዱስ ዮሐንስ ምክር ተቀብለው በያሉበት ሱባዔ ያዙ ጾም ጸሎት በማድረግ ፍቃደ እግዚአብሔር ጠየቁ ሰባዔያቸውን ሲጨርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሩቅም ከቅርብም ያሉ ሐዋርያቱን በደመና እየጫነ በፊልጵስዮስ ከተማ ሰበሰባቸው። ቅዱስ ዮሐንስም ጌታዬ ስለምን ሰበሰብከን ብሎ ጠየቀው በእናቴ ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰራ ፍቃዴ ነው አሁንም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ላሳያችሁ ሥርዓት ላስተምራችሁ ሰበሰብኳቹ አለው።

#ከዚያም ምሳሌዋ ወደሆነው ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ወሰዳቸው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝቅኤት በትንቢቱ “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ብሎ እንደጻፈ....።” #ት.ሕዝ 44፥1 በዚያም ተራርቀው የነበሩ ሦስት ድንጋዮችን በተአምራት አቀራርቧ ቁመቱን ወርዱን መጥኞ ሰጣቸው እሳት እንዳየው ሰም ከእጃቸው ሳለ እየለመለመ ቁመቱ 24 ወርዱም12 ክንድ አድርጎ ሰርቶ አሳይቷቸዋል።

"ወይዜኒ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ" እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ ብሏቸው ዐረገ ። ዛሬም በቅድስሀ ቅዱሳን በእናቱና በድንግል ማርያም ስም እና በቅዱሳኑ ሰም ለምን ቤተ መቅደስ ትሠራላችሁ ፣ ለምን ታቦት ትቀርጻላችሁ ለሚሉን ሁሉ ልጇ ሰርቶ ስላሳየንና ፍቃዱ ስለሆነ ይልቁኑ እናንተም እንዲሁ ሥሩ እንላቸዋለን ።“በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።” #ኢሳ 56፥5

#ቤቴ አላት ቤተ ክርስቲያንን በቅጥሬም ውጥ አለ በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚታነጹ ጠቀል እና ጠበል ቤት፣ቤተ ልሔም ፣ ደውል ቤት ፣ሕሙማን ማረፊያ፣ ክርስትና ቤት ፍትሐት ቤት ግምጃ ቤት፣ወዘተ የመሳሰሉን በእናቴና በቅዱሳኖቼ ሰም ቢሰየም እወዳለው ፍቃዴ ነው ሲል ነው።


የእመቤታችን ቤተ ክርሰቲያን፣ የእመቤታችን ጽላት ፣የእመቤታችን ጠበል ፣የእመቤታችን እምነት ማለታችን ትክክል የሆነ ሁሉም በምስጢርና በምክንያት የሆነ ነው ።
#የጀመርነውን ለመጨረስ ያክል ሰኔ 20ቀን ጻሕጻ ቤተ ክርስቲያኗን ሰርቶ ከሰጣቸው በኋላ በማግስቱ ሰኔ 21ቀን በዛችሁ ቤተ መቅደስ እመቤታችንን መንበር ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዲኢ ካህን(ንፍቅ) ካህን ፣ እስጢፋኖስን ሰራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቁርቧቸዋል ።ዳግመኛም ቅዱስ ጴጥሮስን እጁን ጭኞ ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞታል በዚህ ጊዜ ሰማያዊያን መላእክት ምድራዊያን ሐዋርያት በአንድነት ሆነው ይሰብሖ ለእግዚአብሔር እያሉ አመስግነዋል ።
______ይቆየን__________
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የልጇ የወዳጇ የኢየሱስ ክርስቶስም ቸርነት የቅዱሳኑም ሁሉ ረድኤትና በረከት አይለየን !

አ.አ ኢትዮጵያ
ሰኔ 21/2013 ዓ.ም
ተክለ ኤል ኃ/ማርያም