አትሮኖስ
286K subscribers
118 photos
3 videos
41 files
567 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#የፍርምባ_ጦርነት


#በአሌክስ_አብርሃም


በንቃት ድንበር እየጠበቅኩ ነው ፤ ጠላት ፊት ለፊቴ አፍጥጧል፡፡ በማንኛውም ሰዓት ወደ እኔ
ሊንደረደር ይችላል፡፡ በመጠኑ ያደፈች ጅንስ ቁምጣዬን ከጉርድ ቀይ ካኒቴራ ጋር ለብሼ ነጠላ
ጫማዬ ከእግሬ ላይ ትበር ይመስል በእግሮቼ ጣቶች በመንከስ ከቤታችን በር ላይ ነው ያለሁት በእጄ ከአቅሜ በላይ የሆነ ብትር ይዣለሁ…የአያቴ የተሰበረ መቋሚያ ነው…መቋሚያውም
የተሰበረው እዚሁ በዓይነ ቁራኛ የምጠብቀው ጠላት ጀርባ ላይ ነበር :: አባቶቻችን ያወረሱንን
ጠላት አያቶቻችን ባወረሱን ሰባራ መቋሚያ እየተከላከልሁ ነው፡፡
ነገ በዓል ነው፡፡ ቤታችን ትንሽ ጠቦት ታርዶ ቤቱ ስጋ ስጋ ይሸታል፡፡ እናቴ ቤቱን እና ስጋውን
እንድጠብቅ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥታኝ ገበያ ሄዳለች፡፡ በዋናነት የተሰጠኝ ተልዕኮ፣

1. ዶሮዎች የተሰጣውን የሽሮ ክክ እንዳይበትኑ

2. ሌባ ወደቤታችን እንዳይገባ

3ኛው እና ዋናው…“ገንባው እዚህች ግድም ድርሽ እንዳይል…” ነው፡፡ (እዚህች ግድም ድርሽ
እንዳይል ? ማን ? ገንባው !!)

ዶሮዎች ስጡ አካባቢ መለቃቀም ይችላሉ፡፡ ስጡን መብላትም ሆነ መበተን ግን የለባቸውም፣…
ሌባ በአጥራችን ጥግ መሄድ ይችላል፣ “ደህና አደራችሁ” ብሎም ማለፍ አይከለከልም፡፡ ሰላምታ የእግዜር ነው ትላለች እናቴ….ዕርግጥ ሲደጋግሙባት ሦስት ጊዜ እንዴት አደራችሁ አንዱ ለነገር ነው ትልና የእግዜር ሰላምታ መደጋገም ባለቤትነቱ የሰይጣን ሊሆን እንደሚችል በተዘዋዋሪ
ትናገራለች፡፡ እና ሌባው እስካልደጋገመ ድረስ ሰላም ብሎ ማለፍ ይችላል፡፡ ገንባው ግን
እዚህች ግድም ድርሽ ማለት የለበትም :: መላ ሰላም ማለት ሁሉ አይችልም፡፡ ሰላምታውን
ደገመም አልደገመም ፤ በቃ የበላይ ትዕዛዝ ነው !!
ገንባው በመንደራችን የሚኖር ባለቤት የሌለው ትልቅ ድመት ነው :: የበግ ግልገል የሚያክል
ዥጉርጕር ድመት ! እኔ ከተቀመጥኩበት አንድ አስራ አምስት ሜትር ራቅ ብሎ ከኋላው ሸብረክ በማለት ሁለት የፊት እግሮቹን ቀጥ አድርጎና ደረቱን ነፍቶ ጉርድ ፎቶ ሊነሳ ፎቶ አንሽ ፊት የተቀጠ ጎረምሳ መስሎ ቁሟል ፡፡

ተራ ድመት እንዳይመስላችሁ.. በሰፈራችን ውስጥ ያልገለበጠው ድስት፣ ያልከፈተው መሶብ፣
የመንጠቅ ሙከራ ያላደረገበት የስጋ ዘር የለም፡፡ መንደራችን ውስጥ ዶሮም ይሁን በግ ሲታረድ
ገንባውን ጠባቂ ቃፊር ማቆም ቸል የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ “ገንባው ሲመቸው ቆሞ ከሚሄድ
በግ ሳንባ ይመነትፋል” ይሉታል..ሞኝ ሰፈርተኞች!! ታሪክ የሚተነፍሱበትን፣ የተዓማኝነት
ሳንባቸውን በቁማቸው እንደመነተፉቸው ማን በነገራቸው::

ገንባው ግዙፍ ቢሆንም የተጎሳቆለና በእድሜ የገፋ ድመት ነው:: ትንሽ ያነክሳል፡፡ በዛ ላይ
ዓንድ አይን የለውም፡፡ ጅራቱም ቆራጣ ነው፡፡ ሲጮኸ ድምፁ ያስፈራራል፡፡ እማማ ብርዘገን
ለፋሲካ የገነጣጠሏትን ዶሮ ላጥ አድርጎባቸው ሲሮጥ ጉሮሮውን በቢለዋ ወግተውት ነው ድምፁ
ተበላሽቶ የቀረው፡፡ የዛሬን አያድርገውና "ሚያውውውው" ሲል የአይጥ ሰራዊትን የሚያርድ፣
ሴት ድመቶችን የሚያማልል ድምፀ መረዋ ድመት ነበር ::

ድሮ የጋሽ ታምሩ ድመት ነበረ፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ፍርምባ የሚባል ነገር ሰረቀ ብለው አባ ታምሩ በአንካሴ ወጉት፡፡ ከዛ በኋላ እሳቸው ቤት መኖር አቆመ፡፡ ጨካኝ ናቸው:: ፍርምባ
ለምታክል ስጋ ብለው…ተወልዶ ካደገበት ቤት አባረሩት ፣ ያውም በአንካሴ ወግተው፡፡ እሳቸው
ግን፣ “ድመቱን ለፍርምባ ብዬ አልወጋሁትም” ብለው ዋሹ፡፡ ትልቅ ሰው ይዋሻል ? ደግሞ
እኮ ያኔ የሆነውን ሁሉ በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ…ማሪያምን አይቻለሁ !

ድመቱ ፍርምባውን በአፉ እንጠልጥሎ መሬት ለመሬት እየጎተተ እኛ ቤት ፊት ለፊት ወዳለው የውሃ መውረጃ ቱቦ ሲሮጥ አባ ታምሩ ልክ እንደኦሎምፒክ ተወዳዳሪ ግራ እጃቸውን ወደፊት ቀስረውና ጦር የጨበጠ ቀኝ እጃቸውን እስከቻሉት ድረስ ወደኋላ ለጥጠው በሰፋፊ ርምጃዎች
ተንደረደሩ 1..…2..3..ጦሩን ዥው ...አደረጉት፡፡ ድመቱ ሲሮጥ ጦሩ ሲከተለው፣ ጦሩ ህይወት ያለው ይመስል ነበር፡፡ ልክ ቱቦው ጫፍ ላይ ሲደርስ የድመቱ የኋላ እግር ታፋ ላይ ጦሩ ተቀበቀበ…አቤት ገንባው እንዴት አሰቃቂ ጩኽት እንደጮኸ ..እንዳንቡላንስ
ነው የጮኸው ሚያያያያያያያያያያያያያ…! ሲጮህ በአፉ የያዘው ፍርምሳ ወደቀ፡፡ አንድ ነጭ ያልቆሰለም ያልተወጋም ድመት ቀልቦት ወደቱቦው ውስጥ ጥልቅ አለ…!!

ጎረቤቱ ሁሉ፣ “አቤት አጨካከን እናትዬ የእግዜር ፍጡር ነው…ምን በደለ ?” እያለ ሲያጉረመርም
አባ ታምሩ ታሪክ ፈጠሩ፡፡ “የልጅ ልጄን ዓይኗን ሊያወጣት ነበር እኮ፣ ግዴላችሁም ይሄ ድመት
አውሬ ሆኗል...” በማለት የፍርምባውን ፀብ ትውልድ ለማዳን የተደረገ ጦርነት አስመሰሉት፡፡

የሚገርመኝ ታዲያ የመንደሩ ሰው ነው፡፡ በወሬ ወሬ “ ይሄ ድመት ምን ሆኖ ነው የሚያነክሰው?
ሲባል ፤ ..."ይሄ አውሬ ነው ጋሽ ታምሩን የልጅ ልጅ ዓይኗን ሊያወጣ ሲል አያቷ ሃይሌ
በአንካሴ ወጉት” ይላል :: ጭራሽ አይጦቻቸውን እያሳደደ እንዳልፈጀላቸው አውሬ የሚል
ስም ሰጡት ለዚህ ሚስኪን ገንባው !!

ትልልቆቹ ሰዎች ሁሉ፣ ፀጉራቸው የሸበተው አስተማሪው ሰውዬ (ትልቁ ግቢ ቤት ውስጥ የሚኖሩት
ሳይቀሩ ይሄን የፈጠራ ታሪክ ያወራሉ፡፡ታዲያ ስለ አገር ታሪክ እናውራ ሊሉ አላምናቸውም
ትላንት አፍንጫቸው ስር ያውም በጠራራ ፀሐይ የተፈፀመ የድመት ታሪክ ወጊው በፈለጉበት መንገድ
የተረኩ ሁሉ ስለአገሬ ታሪክ
እናውራህ ሲሉኝ እንዴት ልመናቸው? በመደራቸው
የድመት ታሪክ ያልታመኑ ሁሉ ስለአገራቸው አንበሶች ጀብዱ ሲደሰኩሩ እንዴት ልቤ እሺ ብሎ
ይቀበል ?ታሪክ ማውራት ታሪክ ከመስራት እኩል ጀግንነት እንደሚጠይቅ የገባኝ ያኔ ነው

ከዛን ቀን ጀምሮ ጦርነቶች ሁሉ የአደባባይ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ከኋላቸው ፍርምባ
የሚባል ስጋ ያለ ይመስለኛል፡፡ ገንባው አውሬ አይደለም፡፡ ገንባው የከለከሉትን የዕለት እንጀራ ነጥቆ “ተመስገን” የሚል ሚስኪን ድመት ነው፡፡ የዕለት እንጀራውን ቢነጥቃቸው የዘላለም
ስሙን ነጠቁት፡፡ “ያኔ ባንካሴ ሳንወጋው ኖሮ ትውልዱ ሁሉ እውር በሆነ እያሉ ከድመት
ጥፍር በባሰ የውሸት ጥፍራም ታሪከ ጭፍን ትውልድ ይፈጥራሉ፡፡

በሀሳብ ካቀረቀርኩበት ቀና ስል ገንባው የለም፡፡ “በስማም የት ሄደ ሰባራ መቋሚያዬን ወድሬ ወደ ጓዳ ሮጥኩ፡፡ መስኮቱ ገርበብ ብሏል፡፡ የጠቦቱ ታፋም ተሰቅሎ በነበረበት ቦታ የለም፡፡ .…ወይኔ ጉዴ ዛሬ እናቴ ገደለችኝ በቃ::

ሮጬ ወደ ውጭ ስወጣ ገንባው ታፋውን እየጎተተ ወደ ቱቦው ጥልቅ ሲል አየሁት፡፡

“ወይኔ አንካሴ ኖሮኝ በነበር..ይሄን አውሬ አልለቀውም ነበር" አልኩ ለራሴ፡፡


አለቀ
👍32👏4