🍁🍁ዲያሪው 📝
ደራሲ ፍስሐ ተክሌ
#ክፍል_4
በኋላ ግን ያለ የሌለ ኃይሌን ተጠቅሜ ከላዬ ላይ ገፍትሬ ጥዬው ተነሳሁ፡፡ እሱ ግን ከወደቀበት ተነስቶ "እወድሻለሁ አልሚ" እያለ እንደገና ሊታገለኝ ሲል ተፈትልኬ ከዶርም ወጣሁ፡፡ ከዛ በኋላ ከኤልሳ ጋር ቅልጥ ያለ ጠብ ተጣላን፡፡ እንዴት የእኔን ፍላጎት እንኳን ሳትጠይቀኝ ከእሱ ጋር ተማክራ እንዲህ ታደርጋለች ብዬ ሳኮርፍ፣ ምክንያቷ ባይገባኝም እሷ ደግሞ ከእኔው ብሳ ተናዳ ሳንነጋገር ለዕረፍት ወደየቤታችን ሄድን፡፡ አስራ አምስት ቀን ሙሉ ስልክ ሳንደዋወል ዕረፍት አልቆ ተመለስን፡፡ በኋላ የዶርም ልጆች መጣላታችንን ስላወቁ እናስታርቃችሁ ይሉናል፡፡ እኔም ሆንኩ እሷ ሌላ ጓደኛ ስለሌለን ሳንግደረደር ለመታረቅ ተስማማን፡፡ በኋላም እርቅ ላይ ስንነጋገር ለካስ አጅሬ ለእሷ፤ "ዛሬ እዚህ ከአልማዝ ጋር ስለተቀጣጠርንና ለአንቺ መንገር ፈርታ ንገራት ስላለችኝ፣ ስትመጣ ብትወጪልኝ ብሎ ስለጠየቃት እንደወጣችና የእሷን ምክንያት ሳልጠይቅ ስላኮረፍኳት መቀየሟን ነገረችኝ። ባለመነጋገራችን ምክንያትና ያውም በማይሆን ነገር አላግባብ አስራ አምስት ቀን ሙሉ ባለመገናኘታችን ተቃቅፈን ተለቃቅስን ወደ ድሮው ጓደኝነታችን ተመለስን፡፡ ከዚያ በኋላ የተሾመን ዓይን ማየት ባልፈልግም ኤልሳ፤ "አሁን ተቀያይመን የግቢው ሰው ሲያይ ያልሆነ ነገር ሊያወራብን ይችላል፡፡ እኔ ወደፊት እንዳያስቸግርሽ እነግረዋለሁ" ስላለችኝ እንደድሮው ሳልዘናጋ ይኸው በጓደኝነታችን ቀጥለናል"፡፡ ብላ ብዙ ተጨማሪ ነገር ስጠብቅ ታሪኩን መሀል ላይ አቆመችው፡፡ ድንገት የሃምሳ አለቃውን አየሁት፡፡ የሚነገረው ታሪክ እንዳልገባው ሰው ወይም የሚተረክለትን ተረት እንደጠላ ህፃን ፊቱን አጨማዶ ይመለከተኛል፡፡ ቀጥልም አትቀጥልም የሚል _ ሁኔታ ስላላየሁበት ለአፍታ ያህል ዝም ካልኩ በኋላ አወራሬ ፈሩን ይሳት ወይም አይሳት ሳላመዛዝን ትረካዬን ቀጠልኩ፡፡ ይህንን እንደነገረችኝ ሌላ ማወቅ የምፈልገው ጥያቄ ስለነበር፤ “ከዛስ በኋላ አላስቸገረሽም?" አልኳት፡፡ "ከዛም በኋላ ባገኘኝ ቁጥር እንደሚወደኝ፣ የፈለገውን መስዋእትነት ከፍሎ የሱ እንደሚደርገኝ ይዝታል፡፡ እኔን ትቶ ይልቅ የምትወደውን አብሮ
አደጉን ኤልሳን ቢጠይቃት እሺ እንደምትለው እየደጋገምኩ ብነግረውም፣ እሱ ዓይኑን ከእኔ ላይ ማንሳት አልፈለገም፡፡ እኔ ደግሞ ለእሱ ቅንጣት ታህል ፍቅር የለኝም፡፡ በተለይ አንተን ካገኘሁ በኋላማ ለዓይኔም አስጠልቶኛል፡፡ ግን ኤልሳን ላለማስቀየም ስል ሳልወድ በግድ አልፎ አልፎ ሲመጣ አዋራዋለሁ፡፡ እንዲያውም ተስፋ ቆርጦ እንዲተው በማሰብ የውሸቴን ከአንተ ጋር ፍቅር እንደጀመርኩ ብነግረውም እሱ ግን መሟዘዙን አልተወም፡፡ ያም ሆነ ይህ እኔ ድርሻዬን አግኝቻለሁ፣ እሱም ጊዜው ሳያልፍበት አጠገቡ ያለውን ድርሻውን ቢያፍስ ይሻለዋል" ብላ ወገቤን አቅፋ ደረቴ ላይ ጋደም አለች፡፡ ይሆናል ብዬ ያልገመትኩትን ነገር በመስማቴ ቅናት ቢጀማምረኝም፣ እንደምትወደኝ በማወቄ ግን ሰውነቴ በደስታ ተፍነከነከ፡፡ ሳብ አድርጌ እቅፌ ከንፈሯን ሳምኳት፡፡ እሷም ስትጠብቀው የነበረውን ነገር ያገኘች ይመስል ያለ አንዳች መግደርደር ትስመኝ ጀመር፡፡ ቀስ በቀስ እየተሳሳምን ሳሩ ላይ ጋደም አልን፡፡ በከፊል እላይዋ ጋደም ብዬ ጣቶቼን ፀጉርዋ ውስጥ ወሽቄ እያፍተለተልኩ ከንፈሯን፤ ጉንጮችዋንና አንገትዋን ሳምኳቸው፡፡ ሰውነቴ እሳት አጠገብ የተቀመጠ ያህል ጋለ፡፡ ሳላስበው ለዓመታት ከተዘፈቅሁበት የሐፍረት አረንቋ ውስጥ በደቂቃዎች ውስጥ ተስፈንጥሬ ወጣሁ፡፡ በአንድ በኩል ሁሌ ስመኛትና ሳልማት የነበረችውን የፍቅር እመቤቴ የእኔ እንደሆነች በማረጋገጤ የአሸናፊነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተሾመን ዛቻና ከሀብታም ቤተሰብ መምጣቱን ሳስብ የፈለገውን ማድረግ የሚያስችል ገንዘብ እንዳለውም ስለማውቅ ፍቅሬን እንዳይነጥቀኝ መፍራቴ አልቀረም፡፡ አዎ! አልማዝ ከዛ ቀን በኋላ እውነተኛ ጓደኛዬ ሆነች፣ ማለትም የፍቅር እመቤቴ፡፡ ነገር ግን ተሾመ በቀላሉ እጅ መስጠት ስላልፈለገ በየጊዜው ብቻዋን ባገኛት ቁጥር በጣም ያስፈራራት ጀመር፡፡ አንድ ቀን ከጥናት መልስ ከቤተመጻሕፍት ስንወጣ የአልማዝ ፊት ዓይኗ አካባቢ በልዟል፡፡ እንዳየኋት ደነገጥኩ፡፡ ምን እንደሆነች ብጠይቃትም ደህና ነኝ ከማለት ውጪ መልስ ልትሰጠኝ አልፈለገችም፡፡ ፈትሬ ስይዛት አማራጭ አልነበራትምና ተሾመ ማታ ብቻዋን ስትሄድ አግኝቷት "አንዴ አናግሪኝ" እያለ ሲለምናት፣ እሷ ግን ላለማናገር ብላ የያዘበትን እጁን መንጭቃ ለመሄድ ስትሞክር በጥፊ እንደመታትና በሕይወት እስካለ ድረስ ከእሱ ሌላ ባል አግብታ መኖር እንደማትችል ክፉኛ ዝቶባት እንደሄደ ነገረችኝ፡፡ በድርጊቱ ከመናደዴ የተነሳ ፊቴ ተለዋወጠ፡፡ "ይኸ አንተን የሚመለከት አይደለም፣ አትናደድ፣ ካላረፈ እኔ ራሴ እከሰዋለሁ፣ ዛሬ ልከሰው ነበር፡፡ አሁን እንዲህ ሆኜ ዲኑ ቢያይ ከትምህርት ቤት ስለሚያባርረው በእኔ የተነሳ ሕይወቱ እንዳይበላሽ ኤልሳ ስለለመነችኝና
ከእዚህ በኋላም አንዲት ነገር ቢያደርግ ለቤተሰቦቹ ስልክ ደውላ እንደምትነግራቸው ስላስፈራራችው ነው ዝም ብዬ ያለፍኩት" አለችኝ፡፡ እኔ የውስጤን በውስጤ ይዤ ያልተናደድኩ ለመምሰል ሞከርኩ፡፡ ይሁን እንጂ ማታ እንቅልፍ የሚባል ነገር በዓይኔ አልዞረም፡፡ ለበቀል ከመቸኮሌ የተነሳ ሌሊቱ አልነጋ አለኝ፡፡ ጠዋት መማሪያ ክፍልም ውስጥ ሆኜ ሳስብ የነበረው ምን ማድረግ እንዳለብኝ ነበር፡፡ ምሳ ከበላሁ በኋላ እየተጣደፍኩ ከግቢው ፊት ለፊት ወደአለችው ባቲ ተብላ ወደምትጠራው ጫት ወደሚሸጥባት መንደር ሄድኩ፡፡ ልክ ጫት እንደሚገዛ ሰው ሆኜ ስጠባበቅ፣ አጅሬ እንደተለመደው ብቻውን እየተጎማለለ ከሩቅ ሲመጣ አየሁት፡፡ ፌስታል ገዝቶ እኔ ወደ ነበርኩበት አካባቢ ጫት ለመግዛት ሲመጣ ድንገት ሳያስበው በቡጢ ፊቱ ላይ መትቼ ዘረርኩት፡፡ ድንጋጤው ሳይለቀውና ከወደቀበት ሳይነሳ ቁልቁል እያየሁትና የሌባ ጣቴን ቀስሬ በዛቻ እያወዛወዝኩ፤ "ሁለተኛ ትነካትና እገድልሀለሁ፣ በእሷ መጣህ ማለት በዓይኔ መጣህ ማለት ነው" አልኩት፡፡ አጅሬ እኔ መሆኔን ሲያይ ከወደቀበት ተስፈንጥሮ ተነሳ፡፡ ከአፍንጫው የሚወጣው ደም በአገጩ ላይ እየወረደ ደም የላሰች ውሻ መስሎ ከፊት ለፊቴ ቆሞ ሲያፈጥብኝ ፍርሀት ወረረኝ፡፡ ከመቅጽበት ለመከላከል እንኳን ፋታ ሳይሰጠኝ በቡጢ ነርቶ ብድሩን መለሰ፡፡ ምቱ ጠንካራ ቢሆንም ተንገዳግጄ ቆምኩ እንጂ እንደእሱ መሬት ላይ አልተዘረርኩም፡፡ ከዚያ በኋላማ ገላጋይ ደርሶ ባያድነኝ ኖሮ ይህ ግድንግድ ባላንጣዬ አዋርዶኝ ነበር፡፡ ደግነቱ ገላጋይ መሃላችን እንደገባ እኔ እንደእሱ ብዙም ያዙኝ ልቀቁኝ ሳልል ወደ ግቢ በጥድፊያ አመራሁ፡፡ ከኋላ ኋላዬ ለገላጋይ እያስቸገረ፤ "ቆይ አንተ የሴት ልጅ! እኔ ተሾመ አይደለሁም እሷን ካልደፋሁልህ፣ ያኔ ምን እንደምትሆን አያለሁ" እያለ ይፎክራል፡፡ ከአሁን አሁን ደረሰብኝ እያልኩ እፈራ ስለነበር ከድምፁ እየራቅሁ ሄጄ ዘበኞች ካሉበት ከግቢው በር ላይ ስደርስ "እፎይ" አልኩ፡፡ አገጬ አካባቢ ትንሽ አበጥ ከማለት ውጪ ባለመድማቴ የአሸናፊነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ እርግጥ ዕድሜ ለገላጋይ! ብድሩን የሚመልስበት ተጨማሪ ጊዜ አላገኘም እንጂ ትንሽ ዕድል አግኝቶ ቢሆን ኖሮ "የተጨማደደ ጣሳ" ሳያስመስል አይለቀኝም ነበር፡፡" ድንገት ሳላስበው ሃምሳ አለቃው የሚቀደድ የወፍራም ካርቶን ድምፅ የመሰለ ሳቅ ሳቀና፤ “አሃ! የተባለው ሁሉ ልክ ነዋ! ተደባድባችኋላ!'' አለኝ፡፡