አትሮኖስ
268K subscribers
111 photos
3 videos
41 files
433 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
🍁🍁ዲያሪው 📝

ደራሲ ፍስሐ ተክሌ
#ክፍል_3

ተወልጄ ያደግሁት ድሮ ቃጫ ፋብሪካ አሁን አዲሱ ኮካኮላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ከተማው ባልለማበትና ባልተሻሻለበት ዘመን ጫካ ውስጥ የነበረችው ጎጆ ቤታችን ትዝ ትለኛለች፡፡ ከቤታችን በስተጀርባ ያለው የቃጫ ፋብሪካ ግቢ ሰፊና በደን የተሸፈነ ነበር፡፡ ታዲያ እዚያ ውስጥ እንገባና እንደታርዛን ዛፍ ለዛፍ እየተንጠላጠልን፣ እንደ ቀይ ህንዶች (ሬድ ኢንዲያንስ) ቀስትና ጦር ሠርተን እየተዋጋን፣ እንደ ቬትናም ዘማች የአሜሪካ ወታደር ቅጠል ለብሰን፣ ፊታችንን ጥላሸት ተቀብተን ከእንጨት በተሠራ የማስመሰያ ጠመንጃ የምንታኮሰው፣ በፊልም እንዳየነው እንደ ኩንግ ፉ ካራቲስት ሆነን ያ!... ያ!... እያልንና እጆቻችንን እያወናጨፍን እንደ'ሱ ለመስራት ስንሞክር የነበረው ድርጊት ሁሉ ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ እንዲህ እንደዛሬው እምብዛም ለልጆቹ የሚጨነቅ ወላጅ አልነበረም፡፡ መርሁ "ልጅ በዕድሉ ያድጋል" የሚል ስለነበር ስለልጅ አስተዳደግ ማንም ደንታው አልነበረም፡፡ ልጅን በአግባቡ ቀርጾ ማሳደጊያ እድሜ የህፃንነት ዕድሜ ስለሆነ ለዚሁ ትኩረት መሰጠት አለበት የሚለው የሳይኮሎጂሰቶች የእነ ሲግመን ፍልስፍና ያኔ ቦታ አልነበረውም፡፡ ልጄ ያለው ተሰጥኦ ምንድነው ብሎ የሚከታተል፣ የሚጫወትበት አሻንጉሊት ወይም ኳስ የሚገዛለት፤ ልጄ ይዝናና ብሎ ቲያትር ቤት የሚወስድ ወላጅ ማየት የተለመደ አልነበረም፡፡ ለልጅ ገንዘብ መስጠት ያባልጋል፣ ሲኒማ የሰይጣን ሥራ ነው፣ ኳስ የሚጫወትና የሚዘፍን ልጅ ትምህርት አይገባውም፤ ወይ ቅሪላ አልፊ አሊያም አዝማሪ ሆኖ ይቀራል ወዘተ የሚሉ ማለቂያ የሌላቸው ምክንያቶች ይደረደራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ለእኔ ሁሉም ነገር ከዛሬው የተሻለ ነበር። በሌላ አንጻር ደግሞ ማህበረ-ሰቡ ድንቅና የጋራ የሆነ ባሕላዊ እሴቶች ነበሩት፡፡ ያን ጊዜ ልጅ ሲባል ልጅነቱ የወላጆቹ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ጎረቤቶች ነበር፡፡ ቢርበው ሁሉ ጋ ገብቶ ይበላል፤ ቢታመም ወላጅ ባይኖር እንኳን ጎረቤት ያሳክመዋል፣ ያስታምመዋል፡፡ ሁሉም ጎረቤት እንዳሻው ወደ ፈለገበት ቦታ "ወላጆቹ ቢያዩኝ ምን ይሉኛል?" ብሎ ሳይሳቀቅ ይልከዋል፡፡ ሲያጠፋም እንዲሁ ሁሉም ይገስጸዋል፣ ይቀጣዋል፡፡ ለልጁ ግድ የሌለው ካልሆነ በስተቀር ለምን ልጄን ተቆጣችሁብኝ ወይም መታችሁብኝ ብሎ የሚጣላ ወላጅ የለም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የጎረቤቱን ልጅ የሚቆጣውና

ሲያጠፋ የሚመታው ባለጌ ሆኖ ማየት ስለማይፈልግና እንደራሱም ልጅ ስለሚያየው ነውና፡፡ ስለዚህ "ልጅህን እንዲህ ሲያደርግ አይቼ መታሁት" ብሎ ጎረቤት ቢናገር፤ አባት ወይም እናት "እግዜር ይስጥልኝ፣ ደግ አደረክ˚ ብሎ ያመሰግናል እንጂ ለምን ብሎ አይጣላም፡፡ ለመጫወቻውም ቢሆን ሁሉ ነገር ነበረን፡፡ የጨርቅ ኳስ፣ የጨርቅ አሻንጉሊት፣ የመዋኛ ወንዝ፣ ሌላም ሌላም ነበረን:: በየጠጅ ቤቱ የነበረው ቴሌቭዥንም ቢሆንም ከሲኒማ ቤት የሚተናነስ አልነበረም፡፡ ጠጅ ቤት በራፍ ላይ ተኮልኩሎ ቆሞ በሰካራም ጫጫታ መሀል ፊልም አይቶና ዘፈን ሰምቶ መምጣት ትዝታው አይረሳም:: ያውም ይኸ የሚሆነው ባለቤቱ ሳያይ በር ስር ተደብቀን ነበር፡፡ በተለይ የአባባ ተስፋዬ ሣህሉ የልጆች ጊዜ ፕሮግራምና ህብረ-ትርዒት ከሆነ ውሀ እየተደፋብንም ቢሆን አያመልጠንም፡፡ እንደድንገት ባለቤቶቹ ካዩን ግን አንድ ጣሳ ውሀ እላያችን ላይ መደፋቱ የማይቀር ነበር: ብዙ ሌሎች ጨዋታዎችም ነበሩን፡፡ ድምቡሼ ገላ፣ ያዕቆብ፣ ኩኩሉ፣ ሌባና ፖሊስ ወዘተ፡፡ የጊዜው ባህል ፈትሮ ይያዘው እንጂ አባቴ ከሌሎች አባቶች ጋር ሲነፃፀር ዘመናዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ልጅን ያቀርባል፣ በመደብደብ ሣይሆን በመምከር ያምናል፣ ለትምህርት ትልቅ ግምት ስለሚሰጥ የጠየቁትን ለማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ የማስታውሰው ጎርመስ ባልኩበት ግዜና የሴት ጓደኛ መያዝ በጀመርኩበት ወቅት ገንዘብ ሳገኝ የነበረው፤ ወይ በደብተር መግዢያ አሊያም በትምህርት ቤት መዋጮ ሰበብ ነበር፡፡ አባቴ የመጠጥ ሱሰኛ ስለነበር ምንጊዜም መጠጥ ሳይጠጣ ወደ ቤት አይገባም፡፡ ታዲያ ሁሌ የማስታውሰው ነገር ቢኖር ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ከማድረግ ውጪ ለሌላ ጉዳይ ገንዘብ ለመስጠት ንፉግ ነበር፡፡ ለውጪው ሰው ግን በጣም ለጋስ ነበር፡፡ እናቴ በዚህ የተነሳ ስትናደድ "አንተ የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ ነህ" ትለው ነበር፡፡ አባቴ በተለይ ሞቅ ካለው መጠጥ ቤት ውስጥ ያገኘውን የሚያውቀውንም ሆነ የማያውቀውን ሰው ሲጋብዝ ነበር የሚያመሸው፡፡ እንዲያውም አንዴ ትዝ ይለኛል፣ ማታ አምሽቶ ሲመጣ እዘርፋለሁ ብሎ ሊገድለው፤ ወይም አባቴ ሁል ግዜ ሽጉጥ ይዞ ስለሚሄድ፣ እንዳይገለው የምንፈራው አንድ ማጅራት መቺ ነው ተብሎ የሚጠረጠር ጎረቤታችን ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን እስከ ምሽቱ ስምንት ሰዓት ወደ ቤት ባለመግባቱ እደጅ ወጥተን ስንጠብቀው አገኘነውና፤ "ምን እየጠበቃችሁ ነው?'' አለን፡፡ "አይ አባቴ ስላልገባ እየጠበቅነው ነው" ብዬ በፍርሀት መለስኩለት፡፡

"አርፋችሁ ቤት ግቡ! እሳቸው ዱርዬውንም ሆነ ደህናውን ሰው ሲጋብዙ እያመሹ ማንም አይነካቸውም" አለን፡፡ እናቴ ተናዳ፤ "አዎ፤ እኔ ቸገረኝ ስለው ገንዘብ ለመስጠት ይንሰፈሰፋል! እዛ ግን አዳሜን ይጋብዛል፣ ና እንግባ!'' አለችኝ፤ "ማምሸቱን _ ነግረነው ከገባንማ እሱ ራሱ ጠብቆ አንድ ነገር ያደርገዋል" ብዬ እናቴን በማሳመን ወደ ቤት ሳንገባ የጠበቅንበት ሌሊት ትዝ ይለኛል፡፡ ታዲያ እኔ እየጎረመስኩ ስመጣና የሴት ጓደኛ ስይዝ ለመዝናናት ገንዘብ ስለሚያስፈልገኝ ያለኝ አማራጭ አንድ ብቻ ነበር፡፡ ይኸውም እንደምንም ብዬ ምክንያት እፈልግና በትምህርት ቤት መዋጮ ወይም በደብተር መግዢያ ሰበብ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ ብር የሚደርስ ገንዘብ እንደምንም ብሎ ማግኘት ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ በዚያ ጊዜ ለመዝናናት ከበቂ በላይ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ አስተዳደጌ ነፃ በመሆኑ ከምንም መጥፎ ነገር የነፃ ስሜት ነበረኝ፡፡ ጓደኞቼም ብዙ ነበሩ፡፡ ለሴት ልጅም አክብሮት ነበረኝ፣ ተወዳጅም ነበርኩ፡፡ አዕምሮዬ ለፍቅር እንጂ ለተንኮል፣ ለሸርና ለቂም በቀል ቦታ አልነበረውም፡፡ ለሰው ያለኝ ፍቅር ሴትንም ይበልጥ እንድጠጋ አጋልጦኛል፡፡ ብዙ የሴት ጓደኞች የነበሩኝ ቢሆንም እንደአልማዝ ግን የማፈቅራት አልነበረችም፡፡ የመጨረሻ ፍቅረኛዬም እሷ ትሆናለች የሚል ግምትም ነበረኝ፡፡ ያልተጠናቀቀው ፍቅራችን በጋብቻ ይጠናቀቃል ብዬ ወስኜ ነበር፡፡ግን ምን ያደርጋል 'ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ' ሆነ እንጂ! "የት ሄድክ ወንድም?"አለኝ ሃምሳ አለቃው፡፡ በሀሳብ ባህር ውስጥ ሰምጬ ስለነበር መግባቱን እንኳን አላየሁም ነበር፡፡ "እሺ አቶ አማረ ወደ አቋረጥነው ጉዳይ እንመለስና፤ ከአልማዝ ጋር ስላለህ ትውውቅ የጀመርከውን ብትጨርስልኝ'' ብሎ እንደመኮሳተር አለ፤ ሰውዬው እንኳንስ ተኮሳትሮ እንዲያውም የሚያስፈራ ነው፡፡ ሲያዩት የሰው ጭንቀት የሚያረካው፣ ሰው ሲፈራ የሚደሰትና በአስፈሪ መልኩ ተጠቅሞ እውነትን ከጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ ፈልቅቆ ለማውጣት የሚታገል ይመስላል፡፡ በንግግር መሃል እስክሪፕቶውን ገልብጦ ጠረጴዛውን መታ መታ እያደረገ ሲያንኳኳ የሰው ሐሳብ እንዲሰባሰብ ከማድረግ ይልቅ እንዲበታተን ለማድረግ የሚጥር ይመስላል፡፡ ሥራውም እንደስሙ አደፍርስ ነው፡፡