አትሮኖስ
286K subscribers
119 photos
3 videos
41 files
568 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ምንትዋብ


#ክፍል_ስምንት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ


“እምዬ ጐንደር እንግዳ ተቀባይ እኮ ናት።”

ጥላዬ፣ እምነቱንና ተስፋውን ጐንደር ላይ ጥሎ ሐሙስ ቀን እዚያች ብርቅየ ከተማ ገባ። ጨለማ የከተማዋን ሰማይ ለማልበስ በመጣደፍ ላይ
ነው። ጐንደሬዎች ቤታቸው ለመከተት ፈጠን ፈጠን እያሉ ሲራመዱ፣ጥላዬ፣ ብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ዓይነታቸው አስደነቀው። እንደ ግሪኮች፣ አርመኖች፣ ህንዶችና አረቦች የመሳሰሉ የውጭ ሃገር ዜጎች ሕዝቡ መሃል ውር ውር ሲሉ፣ የቆዳቸው፣ የመልካቸውና የአለባበሳቸው
መለየት አስደመመው።

ጭቃ ምርጎቹን ባለሳር ክዳን ጎጆዎች ትክ ብሎ አያቸው። ባዘቶ
የለበሱ የሚመስሉ ዋንዛ ዛፎች ስር ችምችም ማለታቸውና እንደ ቋራ ተሰባጥረው አለመቀመጣቸው ገረመው። በየቦታው ጣል ጣል ያሉት
የድንጋይ ግንቦችና ነገሥታት ብቻ የታደሉባቸው የኖራ ቅብ ቤቶች
የከተማዋ ጌጥ መስለው ታዩት። ያየው ሁሉ ከቋራ የተለየ ሆነበት።
ጐንደር ልዩ ስፍራ ሆነችበት፤ አስገረመችው።

ዐዲስ ሕይወት ልትሰጠው ቃል ኪዳን ገባችለት። እየተዘዋወረ ከተማዋን ማየት ፈልጎ ጨለማው በፍጥነት ማደሪያ እንዲፈልግ አስገደደው። ቤተክርስቲያን ፍለጋ ዐይኑን ሲያዘዋውር፣ አንድ የቆሎ ተማሪ በፍጥነት ሲራመድ አየና ሮጦ ደረሰበት።

“ከርመህ ነው? ላገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ነኝ። ማደሪያ ሚሆነኝ
ደጀሰላም ባገኝ ብየ” አለው።

“ኸደብረብርሃን ሥላሤ ማታድር? ምን የመሰለ ዛኒጋባ በቤተክሲያን
ዙሪያ እያለልህ። ወደዛው ነው ምኸድ፤ በል ና። አገርህ ወየት ነው?”

“እማር ብየ መጥቸ” አለ ጥላዬ፣ መናገር አልፈለገም።

“ጐንደር ደሞ ለትምርት። ኸየቦታው ሚመጡ ተማሮች፣ ሊቃውንት፣ ካህናትና መምህሮች ሁሉ ኸዝሁ ማዶል ያሉት?” ብሎ ነጫጭ ጥርሶቹን አሳየው፣ ተማሪው።

ገራ ገር ፈገግታው ጥላዬን ማረከው። ዕድሜ ልኩን የሚያውቀው መስሎ ተሰማው። ቀደም ብሎ ማደሪያውን ሲያስብ ባይተዋርነት የተሰማውን ያህል፣ ከትከሻው ሸክም እንደወረደ ሁሉ ቀለል አለው።

“ቅኔ ልትማር ነው የመጣህ?”

“ሥዕል ልማር ብየ ነው የመጣሁ።”

“ዛዲያ ጐንደር ምን ገዷት! እደብረብርሃን ሥላሤ መምህሮቹም ተማሮቹም አሉልህ፡፡”

ጥላዬ ተደሰተ። ተማሪው ገዱ ሆኖ ተሰማው። ልባዊ ፈገግታው ደግ
ሰው እጅ ላይ እንደወደቀ ጠቆመው። “ምን እየተማርህ ነው?” ሲል ጠየቀው።

“ቅኔ እየተማርሁ ነው። መወድስ እያኸድሁ ነው።”

“ደሕና አኸደሀል።”

“አንተስ ሞካክረኻል?”

“ሥላሤ ደርሻለሁ። ማድርበት ደጀሰላም የት አገኝ ይሆን እያልሁ?”

“ጐንደር መጥተህ ነው ስጋት ሚያድርብህ? አንተስ አለማወቅህ ...እምዬ ጐንደር እንግዳ ተቀባይ እኮ ናት። ሴቶች ወጥ ሲሰሩ ኸደረስህ
ይሽተዋል ብለው ሳትበላ ማትኸድባት አገር እኮ ናት። ጐንደር የሁሉ ናት፤ ማንም ኸየት መጣ ኸየት ቤቴ፣ የኔ ብሎ ሚኖርባት። አልሰማህም
እንዴ፣
ቤተስኪያን ስሞ ለመኖር፣
መልካም አገር ነው ጐንደር።
ሲባልላት?” እያለ ግጥሙን በዜማ አወረደለት።

ጥላዬ ሳቅ አለና፣ “ገና መድረሴ፣ ምኔ ሰምቸ? ጐንደሬ ሁሉ እንዳንተ
ጥሩ ነው?” ሲል ጠየቀው።

“እኔስ ኸተምብየን ነው የመጣሁ። ዐራት ዓመት አርጌያለሁ ኸዝኸ።”
ተማሪው ከላይ የደረበውን ለምድ፣ ትከሻው ላይ ያንጠለጠለውን
አኮፋዳና ለውሻ መከላከያ የያዛቸውን ሁለት በትሮች ጥላዬ ትክ ብሎ ተመለከተና ከልመና እንደመጣ ገባው። ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲደርሱ
ደጀሰላሙን ተሳልመው ውስጥ ገቡ።

“እንዴት ያለ ቤተክሲያን ነው በል” አለው፣ ጥላዬ።

“አጤ አድያም ሰገድ ኢያሱ መዠመሪያ አሠሩትና ተቃጠለ። ኸዚያ በኋላ፣ ልዣቸው... ሦስተኛው ሚባሉት አጤ ዳዊት እንደገና አሠሩት።

እሳቸው ግና ባባታቸው ስም እንዲጠራ ስለፈለጉ እኔ አሰራዋለሁ ስሙ ግን ባባቴ ይሁን አሉ።”

ጥላዬ ፈዞ ቆሞ የቤተክርስቲያኑን አሰራር ሲያደንቅ ተማሪው፣ “እኛ
ስንገባ ስንወጣ ለምደነዋል። እንግዲህ አንዱን ጥግ ይዘህ ተኛ። ኸኛ ዘንድ ምኝታ የለም ሁኖ ነው” ብሎት ሄደ።

ጥላዬ ቤተክርስቲያኑን እንደገና ተሳልሞ ዙርያውን ሲመለከት፣
እየጨለመ በመምጣቱ በወንዶቹ መግቢያ በኩል ጭንቅላቱን ጉልበቶቹ መሃል ቀብሮ ተቀመጠ። ግቢው ጭር ብሏል። መንገድ ሲመሽበት፣
“ቤት ያብርሃሙ ሥላሤ ነው” እያሉ ቁርበት ጣል፣ ትኩስ ሽሮ እንጀራ
ላይ ፈሰስ አድርገውለት፣ አለበለዚያ ቆሎ እንዲቆረጥም ወይ ቂጣ እንዲያላምጥ ሰጥተውት ያሳደሩት ሁሉ ትዝ አሉት። ከነጋ እህል አፉ አላደረገም። ሆዱ ከረሀብ ብዛት ዋይ ዋይ አለበት፤ ያለማቋረጥ
አዛጋው።

በዕድሜ ከእሱ ትንሽ ከፍ ስለሚለው ተማሪ አሰበና ባይለየው መረጠ። ስሙን እንኳ ሳይጠይቀው በመሄዱ ተቆጨ። አንገቱን እንደደፋ ሲያሰላስል ድምፅ ሰማ። ቀና ሲል ተማሪዎች ወደ መማሪያ ቦታቸው ወደ ቤተክርስቲያኑ ጀርባ ይሄዳሉ። ተማሪው ከእነሱ ነጠል ብሎ ወደእሱ ሲመጣ አየው። ሁለመናው ተበራታ።

“ራት ቢጤ አመጣሁልህ። የውሃ ቅሌን ልተውልህና ገሠሣ ሲያበቃ
መጥቸ ወስደዋለሁ። ስትተኛ ኸዚሁ ተወው። አነሳዋለሁ” ብሎት
መንገድ ሲጀምር ጥላዬ ከተቀመጠበት ተነስቶ፣ “ሥላሤ ያክብሩልኝ።ስሜንም ሳልነግርህ... ጥላዬ እባላለሁ... ከቋራ ነው የዘለቅሁ” አለው::

ቀደም ብሎ አባቱ ፈልገው እንዳያገኙት ሲል ማንነቱን ደብቆ፣
አሁን የተማሪው ደግነት ምሥጢሩን አሟሸሸበት።

“በል ነገ ያገናኘን። አብርሃ ነው ስሜ። ገሠሣ እንዳያመልጠኝ
ብሎት ተማሪዎቹ ወደሄዱበት አቅጣጫ አመራ።

ጥላዬ፣ አብርሃ የሰጠውን ፍርፋሪ በልቶ፣ ውሃውን በላዩ ቸልሶና
አምላኩን አመስግኖ የመንገድ ድካም ስለተጫጫነው አንዱ ዛኒጋባ ጋ ተጠግቶ ጋደም እንዳለ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው።

ጠዋት ድምፅ ሲሰማ ብንን አለ። የት እንዳለ ለማወቅ ጥቂት ጊዜ
ወሰደበት። የሌሊቱ ብርድ፣ ልብሱን ውሃ የነካው አስመስሉታል። አንድ ጋቢ መኝታም ከላይ የሚለበስም ሆኖ አገልግሎታል። ከተቀመጠበት
ተነስቶ የቤተክርስቲያኑን መግቢያ በር ተሳለመና ወንዶቹ መግቢያ
ትይዩ ያለ አንድ ዋንዛ ዛፍ ስር ሄዶ ዳዊቱን አውጥቶ መድገም ጀመረ።

“አድረህ ነው?” የሚል ድምፅ ሲሰማ ቀና አለ። አብርሃ ነው ።

“ደሕና... ደሕና ... ይመስገነው።”

“አንደዜ ጠሎት ላድርስና ኸየንታ ሔኖክ ዘንድ ወስድሀለሁ” ብሎት
ሄደ።

ጥላዬ፣ በእሽታ ራሱን ነቀነቀለትና ወደ ዳዊቱ ተመለሰ። የዕለቱን
አድርሶ ሲጨርስ ዳዊቱን ማኅደሩ ውስጥ ጨምሮ፣ ስንጥር አንስቶ
መሬት ላይ መሞነጫጨር ጀመረ። እንደለመደው የወለተጊዮርጊስን ምስል ሊሥል ፈልጎ እዚያ ያደረሰው ምን እንደሆነ ትዝ ሲለው
ስንጥሩን ወረወረው።

ከቤት የወጣበት ምክንያት በመንገድ ድካምና በረሐብ በአእምሮው ውስጥ እየደበዘዘ መጥቶ ነበርና አሁን ቁጭ ሲል ሁሉ ነገር ፊቱ ላይ ድቅን አለበት። ወለተጊዮርጊስ ጐንደር መግባት ከለመግባቷን የማወቅ ፍላጎቱ ጸና። እሷ ሐር ቀሚስ ለብሳ ከቤት እንደወጣችው ሳይሆን፣ እሱ
እሑድ ቤተክርስቲያን ስትሳለም እንደሚያያት የዐዘቦት ልብሷን ለብሳ፣ ነጠላ ተከናንባ በበቅሎ ስትሰግር በዓይነ ኅሊናው ታየው፤ ሆዱ ባባ።

ያርባ ቀን ዕድሌ ነው እንግዲህ ምን አረጋለሁ? አለ፣ ለራሱ።
እናቱንና አባቱን አስታወሰ። በእሱ መጥፋት እናቱ እንዴት ጨርቃቸውን እንደሚጥሉ አሰበና ሆድ ባሰው። አባቱም ቢሆኑ አመል ሆኖባቸው ይነዛነዙ እንጂ፣ የእሱ ነገር እንደማይሆንላቸው ያውቃልና ጉዳታቸው ተሰምቶት ለመጀመሪያ ጊዜ አዘነላቸው። ሳያስበው ፊቱ በእንባ ርሷል። በጋቢው ፊቱን ጠራርጎ ቀና ሲል አብርሃ ፊቱ ቆሟል።
👍152