አትሮኖስ
286K subscribers
119 photos
3 videos
41 files
569 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#አርፋጅ

አንድ ሰፈር ነው ያደግነው፡፡ አንድ ዩኒቨርስቲ ተማርን። ብሩክ ፈታ ያለ ነው፣ ጨዋታ ያደምቃል፣ ጨዋታም ያውቃል። እሱ ካለ የሳቅ ድምጽ አይጠፋም። ስድስተኛ ክፍል አልፈልግህም ተብሎ የተላከለትን ደብዳቤ አባቱ አግቶበት
የመታውን ጠረባ፣ ለፍቺም ደርሰህልኛላ እያለ የሚጦልበውን ጡለባዎችን እየቀመመ ሲያጫውት አፉን ከፍቶ የማይስቅ አልነበረም።

ታላቅ ወንድሙ ላይ የሚሠራውን ተንኮል፣ የግድያ ሙከራ የሚመስሉ ድብደባዎችን ኮስተር ብሎ በፌዛም ፊቱ እያወጋ ያዝናናን ነበር። ግሬድ ሲሰቅልም፣ ሲሾቅም ማላገጡ የሚጠበቅ ነው። በዙሪያው የማንጠፋው ፍሬንዶቹ ላይ እንዳይደብረን አድርጎ ለጨዋታ ፐርፐዝ ብቻ ይቀልድብናል።

ብሩክ እንደ ጃካራንዳ ዛፍ በዙሪያው ሚያጅበው አይጠፋም፣ ሰው ይወደዋል። ከሰው ጋ እይጋጭም፣ መከባበር የማይደራደርበት ዋነኛ ፖሊሲው እንደሆነ በደንብ የሚቀርበው ሁሉ ያውቃል፣ የጠበቀ ወዳጅነት ያለን ደግሞ በይበልጥ እናውቃለን።

ብሩክ ለእኔ ወንድሜ ነው የማልለው ባልጀራነትን ማሳነስ ስለሚመስለኝ ነው። ብዙ ሳቅ እና ጭንቀቶችን ተጋርተናል። በድዬ ሳለሁ ለእኔ አግዞልኛል፣ እስከ ድክመቱ ተቀብየዋለሁ፤ ጓደኛዬ ነው፣ ምንም ሳይኖረን ጊዜ ብቻ እያለን ነው ነፍሳችን የተናበበው፤ የጓደኝነት ትርጉም መተንተን ሳንጀምር ነው የተወዳጀነው።

እኔ ታላቅ ወንድሜ የጀመረውን ቢዚነስ ተቀላቅዬ በሂደት ብዙ ሳንቲም ማግበስበስ ጀመርኩ። ብዙ ሀብት ባገኘሁ ቁጥር መፍጨርጨሬ ጠነከረ፣ ነገሮችን በውሎዬ ስለምመዝን እነጫነጫለሁ፣ ብሩክ ነገሮችን ከእሱ አንጻር ስለሚያይ መነጫነጬ አይገባውም።

ብሩክ ቀልደኝነቱ መፍዘዝ ጀመረና መገለጫው ያልሆነ ጨለምተኝነት ወረሰው። ምሬቱን ቀልቤን ሰብስቤ አሰላስዬ አላውቅም፣ መንገዱን ለመደልደል አልጣርኩም። ከእጮኛው ጋ የሚያጋጥመውን ግጭት በምሬት ሲነግረኝ ቀልቤን ሰብስቤ ከጊዜያዊ ስሜት የገዘፈ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም።

የድሃ ልጅ መሆኑ፣ አይዞህ የሚለው አለመኖሩን ሲጠቅስ አብሬው ከማሸብሸብ የዘለለ ጊዜ ሰጥቸው ምን ላግዘው? ከእኔ ምን ይጠበቃል? ብዬ ለአፍታ አሰላስዬ አላውቅም።

እድገት ላይ በመመሰጤ ያሉኝን በረከቶች ለማስተዋል አልተቻለኝም ነበር። ያሉንን እየጣልን የምናመጣው አዲስ ስኬት እንደምን የምንፈልገውን ደስታ ሊያመጣልን ይቻለው ይሆን??

ለሥራ ኔትወርክ የማይሰራበት ቦታ ከርሜ ስመጣ እንድንጠጣ፣ እንድንስቅ ደወልኩለት ግን ስልኩ ዝግ ነው። ደጋግሜ ደወልኩ፤ አሁንም ስልኩ ዝግ ነው። ስልክ ማጥፋት፣ ስልክ አለማንሳት፣ ለብቻው መሆን አዲስ ያመጣው ፋሽኑ መሆን ጀምሯል። ቤቱ ልሄድ ተነሳሁ።

ፀሐዩ ሀሩር ነው፤ ዘንድሮ ፀሐዩን ለማምለጥ እንደዝናብ መጠለል እና መሮጥ መጀመራችን አይቀርም። የድሮ ሰፈሬ ደረስኩ፣ የነ ብሩኬ ደጅ ላይ ድንኳን ተደኩኗል፤ ብሩኬ አያቱ ጠንካራ ሕመም እያንገላታቸው እንደሆነ ነገሮኝ ነበር።

አያቱ በሕይወቱ ደማቅ ስፍራ አላቸው፤ ይወዳቸዋል፡፡ እንደ ወንድሙ ነበር የሚያዋራቸው፣ እንደ ጓደኛቸው ነበር የሚያጫውቱት። ከልጅነት ጀምሮ የምናቀውን ሰው ማጣት ሕመሙ ብርቱ ነው። ድብርት እና ምሬት ሳይጣባው አያቱ ሳይተኙ ለመድረስ ነበር የሚሮጠው።

እርምጃዬን ቀስ እያደረኩ ወደ ድንኳኑ ስሄድ የሰፈራችን ለቀስተኞች አይን እኔ ላይ አረፈ፣ አጎነበስኩ። ቀስ ብዬ የድንኳኑ መግቢያ በር ላይ ያገኘሁት ወንበር ላይ ቁጭ አልኩ፣ በቀስታ ቀና ብዬ ብሩኬን በአይኔ ሳስሰው ወንበርተደርድሮ በተቀመጠ ፍራሽ ላይ የደከሙ አያቱን አየኋቸው፤ ፍጥጥ ብዬ እንዳየኋቸው አስታውሳለሁ።

ከአጠገባቸው እናቱን አየኋት፣ በጥሩ መንፈስ አላየችኝም፤ አይኔ ወደ ተሰቀለው ፎቶ ተምዘገዘገ። ከዛ ሰዓት በኋላ የሆነውን ብዙ አላስታውስም። ለቀበሌ መታወቂያ ብሎ አብረን ሄደን የተነሳነው የብሩኬ ፎቶ ተሰቅሏል። በጣም እንደጮህኩ አስታውሳለሁ፤ እናቱን ሂሩቴን እየወደቅኩ፣ እየተነሳሁ የሆነውን ለመጠየቅ ፍራሹ ጋ ለመሄድ መሞከሬንም አልረሳሁትም። የሆነውን ሁሉ ፡ አለማወቄ ተገለጸላቸው፡፡ ረጭ ያለው ለቅሶ ቤት ታወከ፤ ሁኔታዬ ያሳዘናቸው ሰዎች አብረውኝ ያለቀሱ ይመስለኛል።

አያቱን አንቄ ጋሽ በላይ ጓደኛዎት የት ሄደ፣ ብሩኬ የት ሄደ? አልኳቸው። በዛለ እጃቸው አቅፈውኝ በትኩስ እንባ ታጅበው እጁን በእጁ በላ አሉኝ። እግሬ አልጸና ያለ ይመስለኛል፤ ብዙ ሰዎች ያዙኝ፤ ክንዴን ክንዴን ብዬ ጮህኩኝ፤ ሰው ለካ እንዲህ ደካማ ነው፤ የቻልኩት መጮህ እና የሆነውን መካድ ነበር።

በቀን ብዛት ተበረታታሁ ያወራነውን ሳሰላስለው ኋላ መቅረት ሲንጠው እንደነበር ገባኝ። ጨለምተኝነቱ ለመኖር ያለውን ፍላጎት ቀድሞ እንደገደለበት ገባኝ። ለካስ ማስተዋል አቅቶኝ ነው እንጂ ሁሉም ነገሩ ይገባ ነበር። አብረን ብንሆንም ለካ ተለያይተን ነበር፤ ለካ እሱ ነበር ጓደኛዬ እንጂ እኔ ጓደኛው አልነበርኩም። አናቱ ላይ በፍጥነት የወረረውን ሽበት ከ"stress"፤ ከመብሰልሰል የተፈጠረ መሆኑን አልጠረጠርኩም ነበር።

ተሳክቶለታል የምባለው እኔ ነገሮች ሲጠሙብኝ፣ አንዳንድ ነገሮች ሲከፉብኝ ይቺ ዓለም እንደምትሰለቸኝ አውርቼው አላውቅም።

ራሴን ልገድለው እንደነበር ነግሬው አላውቅም። ሽራፊ ፈገግታ በሀሩር ፀሐይ ጤዛ እንደመፈለግ ሆኖብኝ ሳለ፣ የሞከርኩት ሙከራዎች ሲከሽፉ፣ ከሰው ሁሉ አነስኩኝ ስሜቴ ሲበላኝ፣ ብቻ መሆን ሲጨፍርብኝ፣ አለመፈለግ ስሜት ሲወዘውዘኝ፣ ያለኝን ነገር ሁሉ ያፈሰስኩበት ተስፋዬ ሲጠፋ፣ ሕልሜ ሰፍቶኝ ስንከላወስ፣ የምሸሸግበት ጥግ ሳጣ፣ በማምነው ሰው ስካድ፣ ዕድለቢስነት እንዳልጠራጠር አድርጎ ሲመሰክርብኝ ራሴን ልገለው ዳድቶኝ ነበር። መዳዳቴን እንዴት ድል እነደነሳሁት ሳልነግረው!

አምላኬ ጋር ሙጥኝ እያልኩ፤

አንዳንዴ በረከቶቼን ፈልፍዬ ለራሴ እየተረኩ፣

አንዳንደ ጭላንጭል ብርሃኔ ላይ ተመስጬ፣

ብሞት የምሰብራቸውን ሰዎች አዝኜላቸው።

አንዳንዴ ክችች ያልኩበትን ጉዳይ እያላላሁ፣ አንዳንዴ ግትርነቱን እየገሰጽኩ፣ አንዳንዴ ሆስፒታል ያሉ አካላቸው የማይታዘዝላቸው ነፍሶችን እየረዳሁ፣ አንዳንዴ እስረኞችን እየጠየቅኩ ነው ራሴ ላይ የራራሁት ሳልለው
ይሄ ትግሌ ለብሩኬ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ማሰብ አልተቻለኝም ነበር። የምንወዳቸውን ሰዎች ምን ያህል እንደምንወዳቸው ካለ እጦት እንዴት መረዳት ያቅተናል? ለራስ ሰው አለመድረስን ያህል አርፋጅነት የለም።

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
36😢13👍11