#ጫማ_ለዘመን_ሰው…
፡
፡
#በናትናኤል
ፍትፍት አኩርፋኛለች። ለሁለት ሳምንታት ከቤቷ ተመላልሼ የለችም። ከቤተ ዘመዶቿ "አላየናትም" የሚል ምላሽ ተሰጥቶኛል። ናፍቃኛለች። ናፍቆቷ ደግሞ ብርቱ ነው፤ በበረዶ ዘመን የተወለደ ግመል በረሀ እንደሚናፍቀው አይነት ናፍቆት ነው ፣ ናፍቆቷ እንደ ውሀ ጥም ጉሮሮን የሚያንገበግብ አይደለም ፤ ፏፏቴ ከገደል ወደ ገደል እየዘለለ ሲተም ለማየት እንደመመኘት ነው።
በምን አስኮርፌያት ይሆን ? ምን ያህል ተቀይማኝ ይሆን? ልንጋባ ወስነን ፤ እንደ ደንቡ ፣ እንደ ወጉ ፤ ወደ ቤተሰቦቿ ሽማግሌ ልኬ ነበር። እኔ እንኳን በእንደዚህ አይነት ሂደት ትዳር ባይመሰረት እመርጥ ነበር። ባህል ፣ ወግ ፣ እሴትና ዘልማድ ፤ ከፍቅር ፊት ዋጋ ያላቸው አይመስለኝም። “ሁለት ልቦች ፍቅር ሲያጣምራቸው አንድ ይሆናሉ ፤ አንድ ሲሆኑ ደግሞ ይህ አንድ ልብ የማሰብን ወግ ዘወር ብሎ የሚያይበት አይን አይኖረውም” እንደዚያ ብያት ነበር። ጠይም ለስላሳ ከንፈሮቿን በከፊል ሸልቅቃ ፈገግታ ቸረችኝና “…ለአባባ እኮ ነው። እኔማ ምንም እንደማይመስለኝ ታውቃለህ” አለችኝ። እወዳታለሁ ፤ የምር እወዳታለሁ። በሆነ ምክንያት ፣ ልገልጸው በማልችለው ሚስጥር ተብትባ ይዛኛለች። አስቸጋሪው ጸባዬን(ሰዎች እንደሚሉኝ) ፈጣኑን ስልቹነቴን መግራት የቻለች ታጋሽ ሰው ናት።
ሽማግሌ ለመላክ የተስማማሁ ቀን ብቻዬን ወደ ቤቴ እያዘገምኩ ማንን እንደምልክ ሳስብ ነበር። ባወጣ ባወርድ ሁነኛ የምለው ሰው አጣሁ። ይሄኔ ክፍለ ሀገር ቢሆን ኖሮ አይወይ (አይወይ አያቴ ነው) እና አባቴ ይወጡት ነበር። እዚህ መሀል ከተማ ብቻዬን ሆንኩና አብዝቼ ተጨነኩ። ማታ እንቅልፍ የወሰደኝ ከብዙ ችግር በኋላ ነው። ጠዋት ቤቴን ስከፍት ጋሼ ዘበነ ከበራፌ ቁመው ተመለከትኩ ፤ “ሰላም አደርክ ልጄ” አሉኝ። “እንደምን አደሩ ጋሽ ዘበነ” ሞቅ አድርጌ ሰላም ብያቸው እንዲገቡ ጋበዝኳቸው። በተለመደው አረማመዳቸው ቀስ ብለው ገቡና ቤቷን መቃኘት ጀመሩ። “ሸጋ አድርገህ ይዘሀት የለም እንዴ?” አሉኝ በመደነቅ። “እንዲህ ቤት የሚንከባከብ ተከራይ የመጀመርያ አንተን እያየሁ ነው” አሉኝ ቀጥለው። ይኸው ስንት አመታችን ሁሌም ሲገቡ እንዲህ ይሉኛል። ልክ ነው ፤ ምንም ነገር ሲዝረከረክ አልወድም። በዚያ ላይ ደግሞ ፍትፍት ስለምትመጣ የጎደለውን ሳታስተካክልልኝ አትሄድም። አከራዬ ጋሽ ዘበነ ድንገተኛ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ሊወጡ ሲሉ አስቆምኳቸውና ጭንቀቴን አካፈልኳቸው። “የረዥም ጊዜ አብሮነታችን ለዚህ ካልሆነማ ምኑን አብረን ኖርነው? አታስብ በኔ ጣለው ልጄ” አሉኝ። ደስ አለኝ።5 በአዳሩ የሀሳብ ናዳ የናወዘው አይምሮዬ ጥቂት እረፍት ስለተሰማው ከማለዳው ድብርት በጊዜ ተላቀኩ።
ፍትፍት !!እንደጨረቃ ክብ የሆነ ፊቷ ፣ አጭር ቁመቷ ፣ ቀጭን ወገቧና ሰፋ ያለ ዳሌዋ ፣ ትንንሽና ለስላሳ ጣቶቿ…ከዚያ ከዚያ በላይ ስትኮረፍ የሚኖራት ገጽታ ድንቅ ይለኛል። ስትኮረፍ እንደ ህጻን ልጅ ትንቡክ ትንቡክ የሚሉ ጉንጮቿ ውስጣቸው ጠይም መልክ ያለው ደም ይፈስበትና ቀይ ዳማ ያደርጓታል ፤ የታችኛው ከንፈሯ አለወትሮው ይወፍራል ፤ አይኖቿ በአንዳች ወዝ ማብለጭለጭ ይጀምራሉ….በብዙው በጣም በብዙው ናፍቃኛለች!! መንገድ ላይ ዜማና እንጉርጉሮ ስሰማ ሆዴን ይብሰዋል። የኔ ፍትፍት…እንዴት እስካሁን አልደወለችም? የላኳቸው ሽማግሌዎች ሁለት ግዜ እንቢ መባላቸውን ነግረውኛል። ጋሽ ዘበነ እንደውም “ምን ሁነሀል? እንኳንስ ያችን የመሰለች የቀን ጨረቃ ፣ ምን ፉንጋ ብትሆን ልጅን ያህል ነገር ባንዴ አይሰጥም! ጊዜ ይፈልጋል ፤ መመላለስ ይጠይቃል” ብለውኝ ነበር። እኔ ግን እንቢታ ከባድ ነውና ፣ ሁለቴ እንቢ ሲባሉ ሽማግሌዎቹ የሚሰማቸውን ስሜት አስቤ አዘንኩ።
በሌላ ቀን ጋሽ ዘበነ ፤ ንዴት አይናቸውን እንደ ፍም አብርቶት ፣ ፊታቸውን ሸክላ አስመስሎት ፤ እጃቸውን እያወናጨፉ መጡ።
“ኸረረረ…ምነው ልጄ ምነው? ሽማግሌ ሁኘ ልለመንህ ባልኩ ፣ እድሜ ጸጋ ነው ብዬ እግሬን ባነሳሁ….ምነው ልጄ ምነው እኔን ማዋረድ?” ተደናግጬና ግራ ተጋብቼ አየኋቸው።
“ምነው ልጄ ፣ ከልጄ ቆጥሬህ ፣ ወዳጄ ነህ ብዬ አክብሬህ ባምንህ … ሰው ወደማያከብሩ ዋልጌዎች ሰደድከኝ?”
“ጋሽ ዘበነ…ኸረ እባክዎ ይረጋጉና ይንገሩኝ ፤ የተፈጠረውን ለምን አይነግሩኝም?” አልኩ። ፈርቻለሁ። ግማሽ ልቤ ምን እንደተፈጠረ ይገምታል።
“ባለጌዎች ናቸው፤ ባለጌዎች! ሽማግሌ እንደዛ ይባላል? እንኳንስ ላንተ ቀርቶ ለስንቱ ይሰረግ የለ?”
“እኮ ምንድን ነው የተፈጠረው ? ጋሽ ዘበነ ኸረ አስጨነቁኝ”
“እንቢ ማለትኮ መብትም ወግም ነው። በተከበርንበት ሀገር ሽማግሌዎቹን እንደውሻ ተረባርበው አባረሩን ፣ ሰደቡን ፤ ረገሙን”
“ስድብ? እርግማን?” አልኩ
“አዎ ልጄ፣ ለሽምግልና የማትበቁ ቀሊሎች ናችሁ ፣ ዘራችሁ ለክብር አይበቃም ፣ አስተዳደጋችሁ ለትልቅ ሰው ወግ አይሆንም ፤ ብለው ሰድበው አባረሩን! ..አንተን ብዬ እንጂ ልጄ…አርፌ ቁጭ ብል በተከበርኩበት ሀገር…”
የምለው ጠፍቶኝ ክው ብየ ቀረሁ። ወደ ፍትፍት ስልክ ደወልኩ…አታነሳም! በተደጋጋሚ ሞከርኩ...አታነሳም።
ሳምንቱን ያሳለፍኩት በጭንቀት ነበር። አይምሮዬ በሀሳብ ፤ ልቤ በናፍቆት ተወጥሮ እናቱ የታረደችበት ጥጃ መስዬ ተኮራምቻለሁ። ለቅጽበት ከተዘረርኩበት ምንጣፍ ላይ ሁኜ ቤቴን አስተዋልኩት። ተዝረክርኳል። የኖርኩበት የኖርኩበት አልመስልህ አለኝ። አዝኛለሁ። አለም ትከሻዬ ላይ የተደፋች ያህል እንዲሰማኝ በቂ ምክንያት ያገኘሁ መሰለኝ። ፍትፍት ከኔ ሸሽታለች ፣ ትታኛለች ፤ ጋሽ ዘበነ ቤት እንድለቅ ነግረዉኛል። ሰው የጎረቤቱንም የራሱንም ፍቅር ሲያጣ ሀዘኑ ጥልቅ ይሆናልና በጽኑ ታመምኩ። እንዳለፈው ቀን ሁሉ ቀኑን ሙሉ ምንጣፌ ላይ ተዘርግቼ አሳልፌ ፤ ምሽቱ ሲቃረብ ወክ ለማድረግ ወጣሁ። ምሽቱ ስለተቃረበ አስፓልቱ እንደኔ ግራጫ መልክ ይዟል። ከአስፓልቱ ግራና ቀኝ በቆሎ ጠባሾች ተኮልኩለዋል። ትንሽ ወረድ ብሎ ደግሞ ቤተክርስትያን አለ። ቤተ ክርስትያኑን አልፌ ቀጥታ አስፓልቱን መከተል ጀመርኩ። ትንሽ እንደተጓዝኩ ስልኬ ድንገት ጠራ። ልዘጋው ነበር። ዝም ብዬ ማን እንደደወለ ሳይ ፍትፍት ናት። በደስታ አነሳሁት።
“ምን ሁነሽ ነው ግን? ይሄን ያህል ጊዜ?” ብዙ ወቀስኳት። ጭካኔዋን በዝርዝር ነገርኳት። ምንም አላለችኝም። ስታዳምጠኝ ቆየችና
“ቤት ሽማግሌዎቹ ጋር ጥሩ ነገር አልተፈጠረም ነበር … ሰምተሀል አይደል የተፈጠረውን?”
“አዎ ሰምቻለሁ … ባለን ግንኙነት ቤተሰቦችሽ ደስተኛ አይደሉም” አልኳት። ዝም አለችና በረዥሙ ትንፋሿን ስባ የተፈጠረውን በግልጽ አብራርታ ነገረችኝ። አፈርኩ። ተገረምኩ፣ ተጠራጠርኩ…. ምን እንደምል ግራ ገባኝ።
“…ብቻ አንተ ተረጋጋ ለትንሽ ጊዜ ነው ቤተሰቦቼ ቢናደዱ … እንዲያውም አባባ ተበሳጨ እንጂ እናቴኮ ምንም አልመሰላትም ነበር…”
ያለችኝን ብዙ አልሰማኋትም። ወደ ቤት መመለስ አልፈለኩም ። በጥዋት ቤቱን እለቃለሁ። የሚቀርበኝን ፔንሲዎን ኣስልቼ በመጣሁበት መመለስ ጀመርኩ። ቤተክርስትያኑ ጋር ስደርስ ጋሽ ዘበነን እየተሳለሙ አየኋቸው። ከርቀት ባይናቸው ሰላም ቢሉኝም ያላየኋቸው መሰልኩ።
ከቤተክርስትያኑ እንደቆምኩ ጋሽ ዘበነ ወደኔ ቀረብ ብለው “አይ ልጄ…እንደው ያሁን ልጆች ትቸኩላላችሁ ፤ ምናለ አሁን ደህና ቤተሰብ ያላትን ደህና ልጅ ብታፈላልግ? ‘ባልኮ የሚስት ቤተሰብንም አብሮ ያገባል’ ይባላል። አየህ ልጄ…እኔና ሚስቴ ስንጋባ ተጠናንተን ነው። ቤተሰብ ለቤተሰብ በደንብ ተዋውቀን ነው”
ብታዘባቸውም እድሜ ክቡር ነውና ዝም አልኳቸው።

👍5
በመሀል አያቴ የነገረኝ ታሪክ ትዝ አለኝና ፈገግ አልኩ። ባንድ ወቅት ሁለት ሰዎች ወደ ገበያ አቅንተው ነው አሉ። አንደኛው ነጠላውን ትከሻው ላይ አድርጎ ስለ ገበያው በተመስጦ እያወራ ይገሰግሳል። ያኛው ቀስ ብሎ ትከሻው ላይ ያደረገውን ነጠላ አንስቶ ራሱ ላይ ጠመጠመው። ጥቂት ከተጓዙ በኋላ ያ ነጠላው የተነሳበት ሰውየ ወደ ትከሻው እጁን ቢሰድ ነጠላውን አጣው። “ጓዴ! ጨርቄን ጉድ ተሰራውልህ …..ጉድ ተሰራውልህ” እያለ ሲጮህ… ያኛው ቀበል ብሎ “ጥፋቱኮ ያንተ ነው ፤ እንደኔ እራስህ ላይ አትጠመጥመውም ኑሯል?” አለው ይባላል። ጋሽ ዘበነ ሰፈርም አንዳንዴ ሲወራባቸው እሰማ ነበር። “ተማሪዎችን ይሸኛሉ ፤ ወጣቶች ጋር ይቀጣጠራሉ ” እየተባለ። በዚህ ምክንያት ከሚስታቸው ጋር ተጣልተው እንደነበርም አስታውሳለሁ። ብቻ ፍትፍት ያለችኝን ግን አልጠበኩትም ነበር። ሽማግሌ ሁኑኝ ብየ ልኬያቸው ፣ የፍትፍትን ደምግባት ያዩ ጊዜ … ሽምግልናውን ወደራሳቸው ሊያዞሩት... ፍትፍቴን ለራሳቸው ሊያደርጉ… ብቻ ያስጠላል። ከተማዋ አስጠላችኝ። ይረጋል ያሉት እየሞቀ ፤ የሰክናል ያሉት እየተንቀዠቀዠ …ከተማዋን ፈራኋት። ጋሽ ዘበነ ትልቁን ቆዳ ጫማቸውን ገጭ ገጭ እያደረጉ ወደ ቤተክርስትያኑ ሲገቡ ከኋላቸው ሁኜ በጸጥታ አየኋቸው። ወድያው ከ“ተንኮለኛው እግዜር” ከሚል የግጥም ስብስብ ውስጥ አንዲት ግጥም ትዝ አለችኝ። በውስጤ እያብላላኋት ጉዞዬን ቀጠልኩ።
#ጫማ_ለዘመን_ሰው
የቆምህባት ምድር
የተቀደሰች ናት ፥ ጫማህን አጥልቀው
ቅድስት ናት ብለህ ፥ ከቶ እንዳታወልቀው
ስንቴ እርቃን ሄደሀል ፥ ከአገልጋይህ አልጋ ?
ስንቴ ተራምደሀል ፥ ዝሙትን ፍለጋ ?
ስንቱንስ ጠልፈኸው ፥ ወድቆ ተዘረጋ ?
በል አጥልቅ ተጫማ ፥ ለቅድስቷ ምድርህ
ጫማህ ይሻላታል ፥ ከተረገመ እግርህ !!
💫አለቀ💫
ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ።
#ጫማ_ለዘመን_ሰው
የቆምህባት ምድር
የተቀደሰች ናት ፥ ጫማህን አጥልቀው
ቅድስት ናት ብለህ ፥ ከቶ እንዳታወልቀው
ስንቴ እርቃን ሄደሀል ፥ ከአገልጋይህ አልጋ ?
ስንቴ ተራምደሀል ፥ ዝሙትን ፍለጋ ?
ስንቱንስ ጠልፈኸው ፥ ወድቆ ተዘረጋ ?
በል አጥልቅ ተጫማ ፥ ለቅድስቷ ምድርህ
ጫማህ ይሻላታል ፥ ከተረገመ እግርህ !!
💫አለቀ💫
ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ።
👍3