አትሮኖስ
286K subscribers
119 photos
3 videos
41 files
573 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ምሶሶ_እና_ማገር

ሸክሜን ሳላስተያየው፣ ፍላጎቴን ቸል እያልኩ ከኔ በቀር ማን አለው ለምለው ቤተሰቤ ስል ፍላጎቴን አቀዝቅዤ መናገር የምፈለገውን ሁሉ ሳልናገር እንደ ጓደኞቼ ፋሽን ልከትል ሳልል ኑሮን ለማሸነፍ ስለምባትል ...

የቤታችን ምሶሶ እኔ ነኝ ባይ ነበረኩ!!

ድንገት እናቴ በአስር ቀን ሕመም ተለየችን። ቤታችን በፍጥነት ቀዘቀዘ።

እናታችን የአባቴን ስኳር፣ ደምብዛት እና ኮሌስትሮሉን ያማከለ ምግብ አቀናብራ አቅራቢ ነበረች። ተኝቶ ሳለ ከውጪ ሆነ ከቤት ውስጥ የሚረብሽ የመሰላት ድምጽ ከተተነፈሰ ቀስስ ቀስ ገረመው ተኝቷል ትላለች ድምጿን ለምልክት በቀረበ ማንሻካሾክ። አባታችንም እንዳይረበሽ ድምጽ ቀንስ ለምትለውም ሰው እንዳይቀየም እየተጨነቀች። አባታችን እናታችን ከሌለች ቤት ውስጥ ያገኘውን ሰው 'አልሚ የት ሄዳ ነው? በቃ አንዴ ከወጣች አትመለስም?' እያለ በስሱ ይነጫነጫል። ምቾቱ ሲሰወርበት ማን ዝም ይላል?

የታናሽ ወንድሜ ሱስ ያመጣበትን ግትልትል ብልግና የምትደበቅለት፣ የምትሸሽግለት፣ ብላ እንጂ ገንዘብ የለህ እንደው አንዱ ቦታ ገባ ብለህ የምትጎርስበት፤ እነዛ ጓደኞች እንደሆኑ ሊያጠጡህ ነው የሚፈልጉህ... ደግሞ ሰውነትህ እየቀነሰ ነው... ወይ እንደ ጎረምሳ ጎረስ ጎረስ አድርገህ አትበላ፣ በየትኛው አንጀትህ መጠጡን እንደምትችለው... እያለች ሳትሰለች ግሳጼ እና ምክር እያቀላቀለች ትኩረቷን የማትነግፈው፣  የምትቆረቆርለት፣ ከብልግናው መሀል መልካምነትን አነፍንፋ የምትመሰክርለት እሷ ብቻ ናት።

“ምዕራፌ እኛን እኛን እያልሽ ራስሽን አየበደልሽ እኮ ነው። ጸጉርሽን ተሰሪ እንጂ ደግሞ አማረልኝ እያልሽ ትጎምጂው እና ትጣይኛለሸ! ሴት ልጅ ጸጉሯ ነው ውበቷ..."

ውጪ ስትንገላታ ነው የምትውለው እያለች ታቀብጠኛለች፣ ትመክረኛለች፣ ገመናዬን ትሰማኛለች፣ ትገስጸኛለች፣ ጠዋት ማታ መግባት እና መውጣቴን፣ ሁኔታዬን፣” ገጼን፣ እንቅስሰቃሴን ትከታተላለች።

አደራህን ጌታዬ ከልጆቼ በፊት አድረገኝ፣ የልጅ ሐዘን አታሳየኝ፤ ከጓደኛ በታች አታውላቸው፣ ከክፉ ነገር ጋርዳቸው፤ ለኔ ያደረከውን ለማን አደረክ? ተመስገን፤ ተመስገን አያለች ስታጉተመትም ለሚሰማት ከአምላኳ ጋር የምታወራ አትመስልም፤ ከወዳጇ ጋር እንጂ!! በርግጥ ለታመነ ካምላክ በላይ ወዳጅ ማን አለ!

ምዕራፌ በርቺልን፣ ካላንቺ ማን አለን? አያለች መኖርያ ምክንያት ትለግሰኛለች። ለመመረቅ ሽራፊ. ምክንያት የምትፈልግ ይመስል ላደረኩት ትንሽ ነገር  ስትመርቀኝ ትውላለች።

ለውሻችን ቦቸራ እንኳን በሰዓቱ ምግብ የምትወረውርለት፤ አሞታል እንዴ? ፈዘዘሳ ብላ የምታስተውለው እናቴ ብቻ ናት።

ዘመዶቻችን እንዲመጡ ወትዋች፣ ጠፋችሁ ብላ ወቃሽ፤ ሲመጡ ተንከባካቢ፤ ካልበላችሁ፣ ካልጨመራችሁ፣ ካልቆያችሁ፣ ካላደራችሁ እያለች የምትለማመጥ፤ ሰፈራችን ውስጥ ለቅሶ ሲኖር፣ ሰርግ ሲሰረግ፣ ዝክር ሲዘከር ግንባር ቀደም አጋዥና አድማቂ እናታችን ናት። ለሚውል መዋል፣ ለደግ ደግ መሆን ስለማይከብድ ቤታችን ጉዳይ ሲኖር የሚያግዘን፣ ስንታመም የሚጠይቀን፣ መንገድ ላይ ሰላምተኛችን ብዙ ነው።

ስናጣት ልካችን ተገለጠልን!! እንዴት ይሄን ሁሉ ስትሸከም በዚህ መጠን  አላስተዋልኳትም? ተሸክሞ ሸክምን አለማሳየት ምን ዓይነት ጥበብ ነው?? እናቴን ያሳረፍኳት መስሎኝ ነበር፤ ለካ አሳርፋኝ ነው።

እናቴ ስንት ቀን ፍቅሯ እውነቷን ሲያስደብቃት፤ በድዬ ለእኔ ስታደላ አይቻታለሁ። ልጅ ሳለሁ በንዴት ከገረፈችኝ በኋላ ሲቃ እየተናነቀኝ ጉያዋ ስወሸቅ፣ ተንሰፍስፋ ያባበለችኝ ዕለት ትውስታ ልቤ ውስጥ አለ።

ድከመቴን የማታጎላብኝ፤ መውደዷ · የማይወላውል፣ እንደምወዳት ማስረጃ የማታስስ፤ ተዝረክርኬ ዝንጥ እንዳልኩ የምታሰማኝ፤ ሕመሜ የሚያማት፤ ስኬቴ ከሁሉ በላይ የሚያስፈነድቃት፣ ነገሬን ሁሉ ጉዳዬ ነው የምትል፤ እንደምወደድ እስትንፋሴ ዓለም ላይ ካረፈ ጀምሮ እያሳየች

የመሰከረችልኝ። እምወደድ እንደሆንኩ ልቤ ላይዐያሰረጸችልኝ፤ መወደድን የሚያክል ምንም በረከት እንደሌለ በምርቃት እና በጸሎቷ ያሰማችኝ።

ጥንካሬዋን ፈተና የማይበግረው፣ በደል ሆነ መከፋት የማይሽረሽረው፤ ትሕትና የተላበሰች፣ በየቀኑ ስለ ልጇ ከአምላኳ ጋ የምታወራ  አመስጋኝ፣ ስጉ : ፍጥረት : ናት። እስክንጠግብ የማይርባት፤ አሟት በድካም የምታሳብብ፤ እየረገመችን የምትጸልይልን፣ አንደበቷ ከእውነቷ ጋ የማይገጣጠም ድብቅ ፍጡር ናት። ፍላጎቷን አሽሻ፣ የምትፈልገውን አጣጥላ ለምንወድው ነገር ፍላጎቷን የሰዋች፣ ለልጆቿ ቸር፣ ለራሷ ስስታም ናት።

የልጇን ፊት እንደ ዳዊት ዘወትር የምታነብ፤  ስትናፍቅ፣ ስናረፍድ በስጋት የምትቃዥ እናት፤ የፍጡር ፍቅር ጥግ ናት።

ዋርካችን ሲገነደስ የከለለልን ገበና ገለጠን!

ሞቷ ከእንባ በላይ ነው። አልቅሼ ላውጣው ብል አይወጣም። አንዳንድ ጊዜ አጠገቤ ያለች ይመስለኛል፤ ባትመልስልኝም የልቤን እንዲህ እያልኩ አወራታለሁ።

ለምን የሚወዱሽ ሲያለቅሱ፣ ደረታቸው ሲደቁ፣ ጸጉራቸውን ሲነጩ ዝም ብዬ ፈዝዤ ተመለከትኳቸው?  አቅፈውኝ፣ አዝነውልኝ፣ እያለቀሱ ሲያባብሉኝ ለምን ደነዘዝኩኝ?
ግድ የለም አብሬሽ ሞቼ ነው የሚሆነው። አብሬሽ ሞቼ ባይሆን ድንኳኑ ውስጥ ወዳጅ አዝማድ ተስብስቦ ሲጨዋወት፣ ሲያጽናና እኔ ለምን ብቻዬን ዲዳ ሆንኩኝ?

አብሬሽ ሞቼ ባይሆን

የሚቀርበኝ ጉድሽ ፈላ እያለ ሲመለከተኝ፤ በርቺ አይዞሽ እያለ ማጽናኛ የቃላት ጋጋታ ሲያንጋጋ እንዴት በዚህ ሁሉ መሀል የእንባ ቋቴ አልተረታም? ከሩቅ፣ ከቅርብ ቀዬ ሐዘኔን በአካል ሊጋሩኝ መጥተው አይኔን እያዩ ሲያጨዋውቱኝ፤ ሊያበረቱኝ ሲታገሉ እንዴት ሆድ አይብሰኝም?

አብሬሽ ሞቼ ባይሆን

ቆሌ፣ ቅስሜ፣ ደመነፍሴ፣ ትውስታዬ፣ መጓጓቴ፣ ሕልሜ አብሮ ከአንቺ ጋ ባይቀበር እንዳሁኑ መች እሆን ነበር?

ከዚህ በኋላ አለመኖርሽ አንዴት አያባባኝም?

አንቺ ሞተሽ እኔ አብሬሽ ሞቼ ባይሆን አንድ ዘለላ እንባ እንዴት አልወጣኝም?

ይሁን ሁሉም... አብሬሽ ሞቼ ባይሆን ለምን ምሳዬ አይርበኝም? እንደሁሌው ውሃ ጥሜ ለምን አይታወቀኝም? ቆይ እሺ ለምን አትናፍቂኝም? አብሬሽ ሞቼ ባይሆን፣ ዋርካዬ ሲገነደስ እንዴት ዝም እላለሁ?

ነገሩ ምሰሶው ሲወድቅ ነው ማገር ማንነቱን የሚያውቀው።

🔘አድኀኖም ምትኩ🔘

#Share #like and #subscribe እያደረጋቹ።

👇Sebscribe

YouTube link👇
https://www.youtube.com/@atronose
23😢16👍1