አትሮኖስ
286K subscribers
117 photos
3 videos
41 files
568 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ


#ድርሰት_በትክክል_ገና


...ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ሆኗል። እማማ ወደሬ የፀበል ፃዲቅ ተጋባዦቻቸውን ለማስተናገድ ጉድ ጉድ እያሉ ናቸው። ወዳጃቸው ታደሰንም ፀበል ቅመስልኝ ብለው ስለጠሩት በጊዜ ተገኝቷል። ሌሉች ፀበል ፃዲቅ እንዲቀምሱ የተጠሩ እንግዶችም የእማማ ወደሬን ቤት አጨናንቀዋታል።ከፊሉቹ ደጅ አግዳሚ ወንበር ላይ ተኰልኩለው ጠበል ጠዲቁን እየቀማመሱ ይጨዋወታሉ።

ጥሪ ሳይደረግለት ፀበል ፃዲቅ ለመቅመስ በራሱ ፍላጐት የመጣ እንግዳም አለ፡፡ እብዱ ምንሽንሽ፡፡ ከአጥሩ ውጭ ድንጋይ ላይ ተቀምጧል።የሰፈሩ ስዎች ለምደውታል፡፡ እሱም ለማዳ እንስሳ እንጂ እንደ እብደቱና እንደ አስፈሪነቱ ተናካሽ አውሬ አልነበረም፡፡ የአንዳንዱ እብድ ጥሩ ፀባዩ ስው ያለመንካቱ ጉዳት ያላማድረሱ ሲሆን አንዳንዱ እብድ ደግሞ ስው አያሳየኝ በሚል ልክፍት የተለከፈ ይመስል ድንጋይ ተሸክሞ መንገደኛውን ሁሉ ሲያስበረግግ የሚውል ነው። ምንሽንሽ በፍፁም ሰው አይነካም፡፡ ዛሬም እንደ ወትሮው ሰውነቱ በምናምን ተድበስብሶ አመድ ላይ የተንከባለለች እንትን መስሏል፡፡ ወይዘሮ ወደሬ ወደ ደጅ ወጣ ሲሉ ምንሽንሽን አዩት።

“ምንሽንሽ እንደምን ዋልክ?! እንካ!” አሉና ኩባያ አቀበሉት። ምንሽንሽ አንገቱን በአክብሮት አቀርቅሮ ኩባያውን ተቀበለ። የሚያውቁት ምንም ።መስሎ አይታያቸውም። የማያውቁት ግን ድንገት ሲያዩት ይደነግጣሉ።
ምንሽንሽ ዛሬም የለበሳት ያቺኑ ቀንም ሆነ ማታ ከላዩ የማትወልቀውን፣ ጭቅቅት የበላትና የተበጫጨቀች ሱሪውን ነው፡፡ ፀሀይ አያቃጥለው፣
ብርድ አይበርደው፣ ቅማል አያሳክከው ለሁሉ ነገር ደንታ ቢስ ነው።ከላይኛው ከንፈሩ ላይ የበቀለው ጢሙ አድጎ የተዘቀዘቀ የፍየል ቀንድ መስሏል። ፊቱም ደም የማይዘዋወርበት ያልታሸ ቁርበት መስሏል።

በስመአብ ወልድ አለች ከዚህ ቀደሞ ምንሽንሽን አይታ የማታውቅ አንድ ልጅ እግር የጠበል ጠዲቅ ተጋባዥ በግርምት አፏን በእጅዋ እየሽፈነች
አይዞሽ ምነው?አታውቂውም እንዴ ምንሽንሽን?” አጠገቧ የነበሩት አሮጊት በድንጋጤ የተሸማቀቀችውን ልጅ አተኩረው እያዩ።
“አሁን ተነስቶ በድንጋይ ቢጨርስንስ?!” አለች በፍርሀት ተውጣ፡፡
“አይዞሽ የኔ ልጅ አትፍሪ ምንሽንሽ ድንጋይ ይዘሽ ብታሯሩጪው እንኳ
የሚሸሽ እንጂ የሚተናኮል አይደለም፡፡ አህያ ነው” በማለት ሊያረጋጓት ሞከሩ፡፡የአሮጊቷ አነጋገር ልጅቷን ሊያረጋጋት አልቻለም፡፡ እሷ እንደዚያ
ተጨነቀች እንጂ ምንሽንሽ እንደሆነ ዳቦ እየገመጠ በጠላ ከማወራራድ ውጪ የሚያስበው ሌላ ጉዳይ፥ አልነበረውም። ሀሣቡ በሙሉ በጠላውና በዳቦው ላይ ተጠምዷል። ሌሎቹም እንደ ዝንጀሮ ቁጢጥ ብሉ ዳቦውን
ስለሚገምጠው እብድ እያወሩ ነበር።
“ፍቅር ነው ያሳበደው ይባላል!” አለ አንዱ።
“ፍቅር ደግሞ ያሳብዳል እንዴ?” ሌላው።
“እሱን የደረሰበት ነው የሚያውቀው። ምን ማለትህ ነው? እንኳን ማሳበድ ህይወት ያስጠፋ የለም እንዴ? ሮሚዎና ጁልዬትን አላነበብክም መሰለኝ፡፡ኦቴሎ ዴዝዴሞናን የገደላትና በኋላ የሞተላት በፍቅር ምክንያት አይደለም እንዴ? ፍቅር ይዞህ አያውቅ እንደሆነ እንጂ!”
“ምንሽንሽን በጤነኛነቱ ጊዜ እናውቀዋለን የሚሉ ሰዎች ሲናገሩ የሰማሁት አንተ ከምትለው የተለየ ነው ! ብዙ ሰው የገደለ አረመኔ ነበር አሉ፡ የሟቾቹ ዘመዶች ተከታትለው ሊያገኙት ባለመቻላቸው በሴት ካጠመዱት በኋላ መድኃኒት አጠጥተው ጨርቁን ጥሎ እንዲሄድ አደረጉት
ሲባል ነው የሰማሁት”
“አቤት! አቤት! የሰው ወሬ” አለ ከወዲያ ማዶ የተቀመጠው፡፡ እሱ
ስለምንሽንሽ የስማው ሌላ ነበረ። ሰው እየፈጠረ የሚያወራው ወሬ አስደንቆት “በእናታችሁ ስው ዝም ብሎ ሲያወራ አይገርምም? እኔ የሰማሁት እናንተ ከምታወሩት ፍፁም የተለየ ነው። ሰውዬው በጣም የተማረና ፈረንጅ አገር ብዙ ዓመት የኖረ ነው አሉ፡፡ ያበደው ደግሞ በትምህርት ብዛት አንጐሉ ተቃጥሎ ነው አሉ” ሌሎቹ የተናገሩት ሀሰት፣
ሌሎቹ የሰሙት የፈጠራ ወሬ እሱ የሰማው ወሬ ግን እንከን የሌለበት
እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ለማስረዳት ቀበጣጠረ፡ታደስ ስለ እብዱ ምንሽንሽ የተለያዩ ወሬዎችን ሰምቷል፡፡ እሱ የሰማውንም ያልሰማውንም እየ
ጨማመሩ ሲያወሩ እያዳመጠና እሱ የሚያውቀውን እውነታ በልቡ እያብሰለስለ አይ መቀስ?አይ አንበሴ? መጨረሻህ እንደዚህ ይሆን? ሲል በልቡ አወራ፡፡ የእብደቱ መንስኤ በትምርት ብዛት አለመሆኑን በሚገባ ያውቃል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን እንደሚባለው ወይ በፍቅር፣ ወይ በጭካኔ፣ወይ በመድኃኒት ወይንም ደግሞ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በእብደት ላይ ሌላ እብደት እየጨመረ፣ የእብደትን ሪኮርድ የሰበረ አዲስ ፍጡር ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ መሆን አልቻለም፡፡ ምናልባት በፍቅር ማበድ
ከዚያም መዳን፡፡ቀጥሎ በመድኃኒት ማበድ ከዚያ መዳን፡፡ ከጭካኔ ብዛት ለእብደት ተዳርጎ ጨርቅ መጣል...ማን ያውቃል ሌላውም እንደዚሁ ስለ ምንሽንሽ ቢጠየቅ ሌላ የእብደት ምክንያት ሊጨምርለት ይችላል።

“ስላምዬ አንቺስ ስለምንሽንሽ እብደት የሰማሽው የለም?” እየሳቀ
ጠየቃት፡፡
ገለል ብለው ሁለቱ ከቤቷ ጥግ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ ሰላማዊትም እየሳቀች “አይ ታዴ? እንኳንስ ስለምንሽንሽ እብደት ላጠና ይቅርና ስለ ራሴ
ህይወት ስለ ራሴ እብደት የማሰላስልበት ጊዜ የለኝም”
“አንቺ ደግሞ ታሳብጃለሽ እንጂ ታብጃልሽ እንዴ ሰላም?”
“ማንን ነው ደግሞ የማሳብደው?” ጨዋታውን ወዳዋለች። የታደሰን
የፍቅር ጽናት ከአንደበቱ እንደ አዲስ መስማት ያስደስታታል።
“ፍቅር እንደሚያሳብድ እየሰማሽው መሰለኝ?”
“እና?”
“ያው ነዋ! ፍቅርሽ እኔንም እንዳያሳብደኝ ማሰብ አለብሽ”
“ያንተን ፍራልኝ እንጂ የኔ እንደማይነካህ እርግጠኛ ነኝ ታዴ። ስውን የሚያሳብድ ፍቅር የፍቅር ወንጀለኛ ነው፡፡የኔ ፍቅር ወንጀለኛ ሳይሆን ጤናማ ፍቅር ነውና አይዞህ አትፍራ” እብዱ ምንሽንሽን በሃዘኔታ እያስተዋለች ሳም አደረገችው።
ልክ ነሽ ስላም ጤናማ ፍቅር አፍቃሪና ተፈቃሪን የሚያስጨንቅ የሚያሳብድ መሆን የለበትም፡፡ጤናማ ፍቅር መተሳሰብን ኣንቺ ትብሽ አንተ ትብስን የሚፈጥር በጋብቻ አጣምሮ ቤተሰብን ለማፍራት የሚያስችል የህይወት ቅመም ነው”
“በትክክል”
“እና?”
“እናማ ያው እንዳልከው ነዋ ታዴ!”
“ያንቺ ሃሳብ ምንድነው ሰላም? የኔን ዳር ዳር እያልኩ ስገልፅልሽ ኖሬአለሁ። የኔ ብቻውን ደግሞ ውጤት ሊኖረው ስለማይችል በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንዳይሆን እሰጋለሁ”
“ታዴ ዛሬ እኮ ፀበል እንድትቀምስ እንጂ ሚስት እንድትለምን አልተጠራህም” የተለመደውን የከንፈር ካሳ ልትሰጠው አንገቷን ቀና ካደረገች በኋላ መቅበጥ መሰላትና እያማራት ተወችው፡፡ ይህንን የሚጨዋወቱት
ሰው እንዳይሰማቸው አፍ ለአፍ ገጥመው ነበር፡፡
“የምጠጣው ጠላ አስካሪ ፈሳሽ ሳይሆን ፈዋሽ ፀበል እንዲሆንልኝ በዛሬዋ ዕለት ሃሳቤን ልትደግፊ ምኞቴ ምኞትሽ ሊሆን በእትዬ ወደሬ የማርያም ፀበል ፍቅራችን እንድትለመልምና አንድ ሆነን እንድንጠመቅ ፍላጐትህ
ፍላጐቴ ነው በይና ቃል ግቢልኝ...”
“ተነስ ወደ ጓዳ እንግባ!” እጁን ሳብ አድርጋ አስነሳችው፡፡ አነጋገሩ ልቧንነካው። የሆነ ስሜት ተሰማት፡፡እንዲህ እንደዋዛ እሱ ደጋግሞ እየጠየቃት እሷ እየሳቀች ስታሳልፈው እውነቱ ሁሉ ቀልድ ይሆንና እምቢ ካለችኝ ሁለተኛ አልጠይቃትም ይልና በእማማ ወደሬ የማርያም ፀበል ስትይ የልብሽን ግለጭልኝ እያለ ሲማጠናት አይሆንም ብትለው በዚያው አኩርፎ እስከ መጨረሻው የሚሄድ መሰላትና ሃሳቧን ልትገልፅለት ምኞቷን ልታስረዳው ማንም ሰው ወደሌለበት ወደ ጓዳዋ ውስጥ ይዛው ገባች።ቀና ብላ
👍5
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_አንድ


#ድርሰት_በትክክል_ገና


...ከምሽቱ አምስት ሰዓት ተኩል ሆኗል፡፡ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ከአስፋልቱ መንገድ ፈንጠር ብሎ
ከአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ወደ መርካቶ በሚወስደው መንገድ ላይ በስተቀኝ በኩል እርስ በርሳቸው ተደጋግፈው
ከቆሙት የጭቃ ቤቶች መካከል በአንደኛዋ ዳንኪራው ጦፏል፡፡
ቀን ቀን ቡና ቤት ውስጥ በገንዘብ ተቀባይነት በምትሰራውና ማታ ማታ ደግሞ በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ የአልኮል መጠጦች እየሸጠች እንግዶቿን
በምታስተናግደው በማህሌት ቤት እየተደነከረ፣ እየተጨፈረ ነው።
ማህሌት በዚያ አጭር ቁመቷ ላይ የለበሰችው ጮማ ተከምሮ በድንገት ስትታይ የምትገላበጥ እንጂ የምትራመድ መሆኗ የሚያጠራጥር ቀይ አፍንጫ ጎራዳ ሴት ናት። ማህሌት ወደዚያ ስትሄድ ወደዚህ የመጣች እየመሰላቸው ቁጭ ብለው የጠበቋት ጓደኞቿን ብዙ ቀን ጉድ
ያደረገች ጉደኛ ሰው ነች።በዚች ጠባብ ቤቷ ውስጥ የመሽኛ ግብዣ የተደረገላቸው ሰዎች ተሸኝተዋል። በመሥሪያ ቤት እድገት ያገኙ ሠራተኞች ማህሌት ቤት እያሉ እየተቀጣጠሩ ፅዋቸውን አንስተዋል፡፡ ለእንኳን
ደህና መጣችሁ እንግዶች ተጋብዘዋል፡፡ የተለያዩ የግብዣ ሥነ ሥርዓቶች በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ተካሂደዋል፡፡ ማለፊያ ገንዘብ እስከተከፈላት ድረስ ማህሌት የሚያምሩ ጥርሶቿን ፍልቅቅ፣ ትሙክ፣
ትሙክ የሚሉ ጉንጮቿን ስርጉድ እያደረገች በጥሩ አስተናጋጅነት እንግዶቿን አስደስታ ሽኝታበታለች። ዛሬ በታደሰ አስተባባሪነት የመሸኛ ይሁን የመዝናኛ ውሉ ያልታወቀ ግብዣ እንድታዘጋጅ ተነግሯት አልኮል በያይነቱ ቀርቦ ጮማ እየተቆረጠ ሊጠጣ... ሊዘለል... ሊጨፈር... የጠየቀችው ሞቅ ያለ ክፍያ ተከፍሏታል። በዚህ የግብዣ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚገኙት አምስት ወንዶች ናቸው።
ሙዚቃው ጦፏል!ተጋባዦቹ ከሙቀቱና ከሙዚቃው ጋር እንደ ውሃ የሚጨልጡት አልኮል ተጨምሮበት መስከር ብቻ ሳይሆን እብደት ቀረሽ ዝላይ እየዘለሉ ናቸው። በስካር ላይ ስካር የሚጨምረው የሚያብረከርከው ሙዚቃ ደግሞ በረጅሙ ተለቋል...
አንቺ ከቶ ግድ የለሽም፣
ስለፍቅር አልገባሽም፣
ሁሉን ነገር እረስተሽው፣
ችላ ብለሽ ስለተውሽው፣
ቻልኩት ፍቅርን... ለብቻዬ፣
ስለዚህ ትቼሻለሁ ይቅር፣
ስላልገባሽ የፍቅር ሚስጥር፣
ትቼሻለሁ አትምጪ ይቅር፣
እችክ፣ እችክ፣ እችክ፣ እችክ፣እችክ.....
ወገብ ብጥስ ቅንጥስ ይላል፡፡ አንዳንዱ ደናሽ ሳይሆን ዳንግላሳ የሚመታ ፈረስ ይመስላል፡፡ ማህሌት የወንዶቹ ጭፈራና ዝላይ ፈንቅሏት እዚያ እመሀላቸው ገብታ እንደ ግንድ እየተገላበጠች ነው።መቼም ከጭንቅላት ቀጥሎ ያለው የሰው ልጅ አካል በማህሌት ዘንድ አለ ለማለት የሚያስደፍር አልነበረም፡፡ ያቺኑ አንገት ተብዬ እየወዘወዘች ከትከሻዋ እየ
ተርገፈገፈች እያሳበደቻቸው ነው። በአምስት ወንዶች መካከል የተገኘች ብርቅዬ... ሞናሊዛ ሆናላቸው ደብለል. ደብለል.. ዞር ዞር...ደግሞ ከትከሻዋ መታ መታ ወረድ... ቀና... እያለች ልባቸውን እያጠፋችላቸው ነው፡፡
ከታደሰ በስተቀር ሌሎቹ በደስታ ብዛት የሚሆኑትን አሳጥቷቸዋል።
አራቱም በየልባቸው ማህሌትን ተመኝተዋታል፡፡ ምን ችግር አለ? የራሳቸውን ስሜት የሚያረኩበት ብቻ ሳይሆን የሌላ ሰው ስሜት ጭምር የሚማርኩበት ረብጣ ገንዘብ ተይዟል። በዚሁ መካከል ግን ሰዓቱ እየበረረ ነበር። ማህሌት ወደ ታደሰ ጆሮ ጠጋ አለችና.....
“ታደስ እስከ ስድስት ሰዓት ብቻ አልነበረም እንዴ የተነጋገርነው? ሩብ ጉዳይ ሆነ እኮ! ሁኔታችሁን ስመለከተው ሙሉ ሌሊት የሚበቃችሁ አልመስለኝም” አለችው።ታደሰ እጇን ሳብ አደረገና
ወደ ጓዳዋ ውስጥ ይዟት ገባ።
“ማህሌት ከስድስት ሰዓት አንድ ደቂቃ ቢያልፍ የተነጋገርንበትን ዋጋበእጥፍ እከፍልሻለሁ፡፡ በዚህ በኩል በፍፁም ሃሳብ አይግባሽ፡፡ በኔ ተይው። ሰዓት አልፏል ብለሽ ጨዋታሽን እንዳትቀንሺባቸው ፊት እንዳትነሻቸው፡፡ እንደ ልባቸው ይጨፍሩ ይዝለሉ። ዛሬ የመዝለያ የመጨፈሪያ ቀናቸው ስለሆነ ሌላ ንግግር ተናግረሽ እንዳታስቀይሚያቸው”
ለስለስ ደግሞም ኮስተር ባለ አነጋገር አስጠነቃቃት። ልቧ ተረጋጋና ተያይዘው ወደ ጭፈራው መሃል ገቡ... አንዱ በአንዱ ላይ እየወጣ እየቦረቀ ለጤናችን እያለ መለኪያ ለመለኪያ እያጋጨ ተዝናና። ለሁሉም ነገር
ድፍረትና ወኔ የሚስጠውን አልኮል በብዛት ወስዶ ሰውነቱን በሚገባ
ወደ ሁለተኛዋ ክፍል አሟሟቀ፡፡ ታደሰ ወጣ ገባ እያለ አካባቢውን ያጠናል።
“የሙዚቃ ድምፅ ይቀነስ... ጩኸት ቀንሱ” እያለ የአካባቢው ነዋሪ እንዳይረበሽ ማስጠንቀቂያ እየስጠ ብቅ ጥልቅ ይላል።በዚያ ሀድራው በሚጨስበት፣ሙቀቱ ጨፋሪዎቹን በትኩስ ላብ በሚዘፍቅበት፣ ሙዚቃው
ልብ እየነጠቀ እንደ ጋላቢ ውሃ ሽቅብ በሚያዘልልበት፣ አልኮል እንደ ፏፏቴ በሚፈስበት፣ የሚገኘው የወደፊት ብሩህ ተስፋ የሚቆጠረው የገንዘብ ብዛት በሚያጓጓበት አስደሳች ዓለም ውስጥ እያሉ ልክ ስድስት
ሰዓት አናቱ ላይ ሲሆን “እጅ ወደ ላይ!” የሚል ድምፅ ሲሰማና በሩ ሲበረገድ አንድ ሆነ፡፡

ማህሌት ከድንጋጤዋ የተነሳ ያ ዝሆን የሚያክለው ግዙፍ ሰውነቷ እንደ ባሉን ቀላላትና እንደ ህፃን ልጅ ሮጣ አልጋዋ ስር ገብታ ተደበቀች።ከሁሉ ቀድሞ እጁን ያነሳው ታደሰ ነበር።

አለቃቸው እጅ መስጠቱን ሲያስተውሉ ሁሉም ተስፋ ቆረጡና እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ሰቀሉ።በየኪሳቸውና በጉያቸው የደበቋቸውን ሰንጢዎች፣ ስንስለቶች፣ መሰርሰሪያ ለመሽሽግ ወይንም ለመወርወር ፋታ ኣላገኙም ነበር፡፡ ፖሊሶቹ እጅግ ቅልጥፍና በተሞላበት መንገድ ኪሶቻቸውን ፈተሹና መሳሪያዎቹን በቁጥጥር ስር አዋሉ፡፡ ብዛት ያለው ገንዘብና
ከታደሰ ኪስ የተገኘው አንድ ሽጉጥም በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደረገ፡፡በዚህ ሁሉ ትርምስ ውስጥ ግን ያ ሽለምጥማጥ አበራ በጓዳ በር በኩል ተሽሎክሉኮ በር በርግዶ አጥር ጥሶ አጥር ዘሎ ሲያመልጥ ከታደስ ጋር አራቱ ተያዙ።

ፖሊሶቹ ወሮበሎቹን በቁጥጥር ሥር በማዋላቸው ምክንያት ዛሬ በሌሊት ቤቱን ሰብረው በመግባት ህይወቱን ለማጥፋት ቀብድ የተቀበሉበት የቡና ነጋዴው የአደም ሁሴን ህይወት ተረፈች። አስር ሺህ ብር ከአደም ላይ
የተበደረው ኡስማን አብደላ የተበደረውን ገንዘብ ለመመለስ ፈቃደኛ ሆኖ አልተገኘም። ጫማው ላይ ወድቆ ምሎ ተገዘቶ የተበደረውን ገንዘብ ከለከለው።
"ኡስማን ገንዘቡን ስትቀበለኝ የነበረህን ሁኔታ ታስታውሳለህ አይደለም?
ዘመድ አዝማድ ልከህ ደጅ ጠንተህ ከነወለዱ ለመክፈል ተስማምተህ ነበር። የኔ ፍላጎት ወለዱ ቀርቶ ዋናውን ብቻ እንድትመልስልኝ ነው፡፡
ከገባኸው ውለታ ውጪ አራት ወር ከአስራ አምስት ቀን ጠብቄሃለሁ።
እምቢ የምትለኝ ከሆነ ግን በህግ ልጠይቅህ እገደዳለሁ” ሲል አስጠንቅ ቆት ነበር።
ኡስማን የአደምን ማስጠንቀቂያ ከሰማ በኋላ አደም ገንዘቡን ስታበድረኝ የጽሁፍም ሆነ የሰው ማስረጃ እንዳለህ አውቃለሁ። እኔም ገንዘብህን ላለ
መስጠት ሳይሆን ሀጃዬ ስላልሞላልኝ ነው። እባክህ ትንሽ ጊዜ ስጠኝ?"በማለት ዋሽቶት ነበር። ጊዜ ስጠኝ ያለው ዕዳውን ለመክፈል ሳይሆን ነፍሰ ገዳዮችን በሁለት ሺህ ብር ገዝቶ አደምን ለማስገደልና ስምንት ሺህ
ብር ለማትረፍ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት እነኝህ ኡስማን የገዛቸው የወሮበላ ቡድን አባላት ለወንጀል መፈፀሚያ ከያዟቸው መሳሪያዎች በተጨማሪ ወንጀሉን ለመፈፀም የተቀበሉት ቀብድ ታደስ በሰጠው መረጃ መሠረት በቡድኑ አባል በጥጋቡ ኪስ ተገኘ፡፡ ታደስም ከወሮበሎቹ ጋር አብሮ እየተነዳ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደ፡፡
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_ሁለት


#ድርሰት_በትክክል_ገና

...ጉለሌ አካባቢ ታደሰ የተከራያት ሁለት ክፍል ቤት ለብዙ ጊዜ ተዘግታ የከረመች ሸረሪት ያደራባትና ግድግዳዋ የተላላጠ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀለም ተቀብታ ሲረግጡት ቡን... ይል የነበረ ጣውላዋ በሰም ታሽቶ አብረቅርቃለች፡፡ ጠረጴዛና ወንበሮች ተኮልኩለዋል፡፡ ጠጅና ጠላ በጠርሙስ ተሞልቶ ከላይ በነጭ ወረቀት በቄንጥ ተሸፍኖ በየጠረጴዛው ላይ ተደርድራል። ሸክላ ሳህኖች በየጠርሙሶቹ መሀል መደዳውን ተቀምጠዋል፡፡
የሸረሪቶችና የአይጦች መፈንጫ ሆና የከረመችው ጎጆ ሰርገኞች የሚታደሙባት፣ ዋንጫዎቻቸውን እያጋጩ የሚጨፍሩባት፣ ሙሽሮች ደግሞ የፍቅር አክርማቸውን የሚቀጩባት ጫጉላ ቤት ለመሆን ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ ልዩ ሆና ደምቃለች፡፡ አዎን ታደሰ ሰላማዊትን የሚያገባበት ቀን፡፡ ዕለተ እሁድ.…የዛሬዎቹ ሙሽሮች በማዘጋጃ ቤት በሽማግሌ
ዎች ፊት በወረቀት ፊርማ ሳይሆን ተፈቃቅደውና ተማምነው ሊቆራኙ
የተዘጋጁበት ቀን ነው፡፡

ዛሬ ሰላማዊት ከእሥር ቤት ወጥታ ወደ ነፃ ህይወት ለመቀላቀል ከዚያ ስቃይ ከበዛበት የሴተኛ አዳሪነት ህይወት ተላቃ ከምትወደው ሰው ጋር አብራ ለመኖር እምነትን ብቻ ውል አድርጋ ፍቅርን ብቻ ሰማንያ አድርጋ አዲስ ህይወት ለመጀመር የተዘጋጀችበት ቀን ነው።

እማማ ወደሬ ዕድለኛ ሆኑ። የወይዘሮ ስመኝን እጅ መድኃኒት አድርጎላቸው ከሞት ተረፉና በልባቸው ስቀው፣ አጨብጭበው መርቀው ያስተሳሰሯቸው ልጆቻቸውን ለመዳር በቁ፡፡ እንደተመኙት በጥርሶቻቸው
እየሳቁ በእጆቻቸው እያጨበጨቡና ልባቸው በደስታ እየጨፈረች በአዲስ ነጭ የአገር ባህል ልብስ አጊጠው በእናትነት ወግ ሙሽሪትን ለሙሽራው ለማስረከብ ጉድ ጉድ ለማለት ታደሉ፡፡ ሰላማዊት አምራለች። ተውባለች፡፡ የውቦች ውብ! የቆንጆዎች ቆንጆ! ሆናለች። ባማረ አለባበስ አጊጣ ፀጉሯን በወጉ ተሰርታ ዐይኖቿ ኩል ተኩለው እንደ ጽጌረዳ አበባ ፈክታላች። ሸርሙጣ ከሚል ወራዳ ስም ተላቃ ሙሽሪት የመባል ወግ ማዕግረ ደርሷታል፡፡ የተለያዩ ወንዶችን በወሲብ እያስተናገደች መኖር ከጀመረች ወዲህ ወደር የሌለው ደስታ ያገኘችበትና እንደ አዲስ የተወለደችበት ቀን
ሆኖ የተሰማት ገና ዛሬ ነው። ከዛሬዋ ዕለት ጀምሮ ከምትወደው ሰው ጋር እስከመጨረሻው በፍቅርና በደስታ ልትኖር የእገሌ ሚስት ባለ ትዳር ተብላ ልትጠራ ነው፡፡
"ሰላም እንግዲህ ጣጣችሁን ቶሎ ቶሎ በሉና ጨርሱ። የመምጫ ሰዓታቸው እየደረሰ ነው” አሉ ወይዘሮ ወደሬ ተፍ ተፍ እያሉና የምትኳኳላውን ልጅ በፍቅር እየተመለከቱ።

ዛሬ ሰላማዊትን በማስዋብና አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ በኩል ሙሉ ሃላፊነቱን የወሰደችው ጽጌ ነች።ያቺ
ገበያዋን የዘጋችባት ልጅ
ያቺ ለሰፈሩ ሴተኛ አዳሪዎች ምላስ አሳልፋ የሰጠቻት ልጅ ሰፈሩን እስከመጨረሻው ጥላላት ልትሄድላት ነውና ከዚያ በፊት የነበረውን ቂም ከዚያ በፊት የነበረውን የጥላቻ ስሜት ፍፁም እርግፍ አድርጋ ረስታ እንደ ታላቅ እህት እየተንከባከበች የውበቷን እንከን እየነቀሰች አሳምራ
እያዘጋጀቻት ነው።

“እሺ እማማ ጨርሰናል እኮ!" አለች ጽጌ እየተጣደፈች፡፡ ወይዘሮ ወደሬ የዛሬ ሁኔታቸው መቼም ለጉድ ነው። ወልደው አሳድገው ለትዳር እንዳበቋት ልጃገረድ ሰላማዊትን አሥር ጊዜ እየተመለከቱ ውበቷን እያደነቁ
ሁለመናቸው በደስታ ስቋል። የፊታቸው ፈገግታ ከእርጅናቸው ውስጥ ደብዝዞ ብቅ ባለው የልጅነት ውበታቸው ምክንያት ለወትሮው መወላገዱ ከሩቁ ይታይ የነበረው ጥርሳቸውን ሁሉ አሳምሮታል። ሰላማዊት
ጣጣዋን ጨራረሰች።ዝግጁ ሙሽሪት! ሽቅርቅር፣ ዝንጥ አለች። የዛሬው የሰላማዊት ሙሽርነት በሚስጥር ቢያዝም አልፎ አልፎ ማፈትለኩ አልቀረም ነበር፡፡ ጽጌ ለጓደኞቿ ሹክ... ብላቸው ውስጥ ውስጡን ወሬው ተዳርሶ ለአንዳንዶቹ የቡና ማጣጫ ሆኖላቸዋል።

በሰላማዊት ጉዳይ የተነጋገሩባት ሴተኛ አዳሪዎቹ ብቻ አልነበሩም፡፡
ከእማማ ወደሬ መሸታ ቤት ፊት ለፊት ባለው ትልቅ የመኖሪያ ግቢ
ውስጥ የሚኖሩት የነጋዴው የአቶ ዘላለም ልጅ ተማሪዋ ምንተስኖትም የዚሁ የሃሜት ሱሰኞች በሽታ ለክፏት የውጪውን በር ከፍታ ጓደኛዋ ሊባኖን ስታስገባት ሰላማዊትን እያማችላት ነበር፡፡
“ኡ. ኡ. ቴ! የሸርሙጣ ሙሽራ አይተንም ሰምተንም አናውቅ!” ከንፈሯን ወደ ጎን እየሽረመመች፡፡
“በቀደም የነገርሽኝን ነው አይደል? እውነት ልታገባ ነው እንዴ?” አለች
ሊባኖስ ወደ ግቢው እየዘለቀች።

"ከየት የመጣ ፋራ ነው በናትሽ ? የጠላ ቤት ሸርሙጣ ሚስቱ ለማድረግ አበሳውን የሚያይ አይገርምም? አ.ሃ..ሃ..ሃ.ሃ." እንጥሏ እስከሚታይ ድረስ አፏን ከፍታ ሳቀች።
"ፍቅር ከያዘው ምን ታደርጊዋለሽ? እንኳን ሴተኛ አዳሪ ሰው ከወደደ
ቆማጣና እውር ማግባቱ ይቀራል ?” አለች ሊባኖስ፡
“ከሽርሙጣ ቆማጣ ይሻላል።ለጊዜው መደበሪያ ልታደርገው ካልሆነ በስተቀር አብራው ትኖራለች የሚል እምነትም የለኝም" “እንደሱ ብለሽ ባትደምድሚ ይሻላል። አብዛኛዎቹ ሴተኛ አዳሪዎች የችግር ማእበል ገፍትሮ ዳር ላይ ሲጥላቸውና ዙሪያው ገደል ሲሆንባቸው እንጂ ፈልገው የገቡበት አይደለም፡፡
አጋጣሚውን ካገኙ ቤተሰብ
መስርተው በታማኝነት ለመኖር ምንም የሚያግዳቸው ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ቅድስት እንደነገረችኝ ከሆነ ደግሞ ሰላማዊት በጣም የምታሳዝን ልጅ ናት። ወላጆቿ የሞቱባት፣ምን የመሰለ ወንድሟን ማጅራት
መቺዎች ደብድበው ያለረዳት ያስቀሯትና ትምህርቷን አቋርጣ በዚህ ህይወት ውስጥ ለመግባት የተገደደች አሳዛኝ ልጅ መሆኗን አጫውታኛለች። እንደኔ እሷን ያገኘ ባል የታደለ ነው" ስትል ሊባኖስ ምንተስኖትን ተቃወመቻት።

"ምነው ጠበቃ ሆንሽላት በናትሽ ? እኔ በበኩሌ በየቀኑ አዳዲስ ባሎችን እያገባችና ገላዋን እየቸረቸረች የኖረች ሴት ስፊ ልማዷን እርግፍ አድርጋ
በጠባብ ጐጆ ውስጥ ዲቃላዋን እያጫወተች መኖርን በቀላሉ ትለምደዋ ለች ብዬ አላስብም”

“ምን እያልሽ ነው ምንተስኖት? በአልኮል የተሟሽ የሰካራም አፍ ጠረን እንደ ሰንደል እየታጠኑ የአባለዘር በሽታን በጅምላና በችርቻሮ ከሚያከፋፍሉ ዝሙተኞች ጋር ለግብረ ሥጋ መውደቅና መነሳት ኑሮ መሆኑ
ነው እንዴ? ሰፊ ልማድ የምትይውስ ከፍላጐት ውጪ ስሜት አልባ ገላን እየቸረቸሩ ሳንቲም በመለቃቀም የሚገኝ ነው እንዴ? በየቀኑ መኳኳሉና
አዳዲስ ልብስ መቀያየሩ ትርጉም ያለው መሰለሽ? ውጫዊ መብለጭለጭ እኮ ውስጣዊ መብለጭለጭን አያመጣም፡፡ ቢከፍቱት ተልባ ነው፡፡ የምትወጂውና የሚወድሽ የትዳር ጓደኛ ስታገኚ፣ተስመው የማይጠገቡ ህፃናት እናት ሆነሽ መኖር ስትጀምሪ ብቻ ነው ኑሮ ኑሮ የሚሆነው። ትዳሬን ሚስቴን ልጆቼን የሚል አሳቢ ባል ካገኘሽ ደግሞ ከዚያ በላይ ደስታ ከዚያ
በላይ እርካታ ይኖራል ብዬ አላስብም”

“አንቺ እንደምትይው አይነት ባል እንደዚህ በቀላሉ የሚገኝ ቢሆን እሰየው ነበር፡፡ ትዳሬን፣ ልጆቼን የሚልና ከራሱ በፊት ለትዳሩና ለልጆቹ የሚያስብ ወንድ ደግሞ ሚስት ለማግባት የጠላ ቤት ሽርሙጣን የመጀመሪያ
ምርጫው ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም” አለች ምንተስኖት ባለመሸነፍ ስሜት ።
👍21
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_ሶስት


#ድርሰት_በትክክል_ገና


....አሥር አለቃ ንጉሤ ብድግ
አለ፡፡ በቤቱ ውስጥ ያሉቱ በሙሉ ዐይኖቻቸውን ተከሉበት።
“እህህ..እህ... እናቶቼ ወንድሞቼና እህቶቼ..” ጉሮሮውን አፀዳና ቀጠለ..
“መቼም የዛሬው ደስታ የሁለቱ ሙሽሮቻችን ብቻ ሳይሆን የኛ የሁላችን በዚች ቤት ውስጥ ተሰባስበን ፅዋችንን ያነሳንላቸው ተጋባዦች ጭምር ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። እንደ ባህላችን ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ ጠጁ ተጥሎ ጠላው ተጠምቆ ሻኛ እየተቆረጠ ዘመድ አዝማዱ ያለገደብ እየበላ፣እየጠጣ፣ እየጨፈረ ሃይሎጋ እያለ ጋብቻ ሲፈፀም ለተመልካች ደስ ይላል፡፡ ይህቺ የኛዋ ሠርግ ግን በዚህ በሚቆረጠው ጮማ በሚጣው ጠጅና በወገን ብዛት ደምቆ በሚፈፀመው የጋብቻ ደንብ ውስጥ የምትጣፍና ከቁጥር የምትገባ አይደለችም፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ ይቺ በእኛ ሃያ በማንሞላው ሠርገኞች የታደመችው ሠርግ ግን እልፍ
አእላፍ ሠርገኞች የጨፈሩበትን ጋብቻ የምታስንቅበት አንድ ትልቅ ምክንያት አላት። ሁለቱ ልጆቻችን ወይንም ደግሞ ወንድማችን ታደሰና እህታችን ሰላማዊት ያለምንም ፊርማና ያለአንዳች የሃብት ድርድር ፍቅርን ብቻ ዋስትና ጠርተው ፍቅርን ብቻ የጋራ ሃብት አድርገው ትዳር ለመመስረት መወሰናቸው በሁለቱም ልብ ውስጥ ያለው የመተማመንና የመፈቃቀድ ደረጃ ምን ያክል ከፍተኛ እንደሆነ የሚያረጋግጥልን ነው።

በፊርማ የሚፈፀመውን ትዳር ለመቃወም አይደለም። ፊርማ
በትዳር ላይ ሊፈፀም የሚችለውን ወንጀል ለመከላከልም ሆነ በተጋቢዎቹ መካከል በራስ መተማመን እንዲኖር የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ይሁን እንጂ የጋብቻ ውል የእስር ሠንሠለት ሆኖ የሚታያቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከፍቅር በኋላ ውሎ እያደር በሚመጣ አዲስ ስሜት የተነሳ የጋብቻ ውል መፈፀማቸው ከባድ ስህተት ሆኖ የሚታያቸው፣ ትዳር መመስረታቸው የሚያማርራቸውና
ያንን የሚማረሩበትን የጋብቻ ሠንሠለት በጣጥሰው በመጣል በአስቸኳይ ለመለያየት በየፍርድ ቤቱ የሚጓተቱ በርካቶች ናቸው። ለዘላቂ ትዳር ዋናው ቁም ነገር እውነተኛ ፍቅር እንጂ የጋብቻ ውል አይደለም። በከፍተኛ ወጪ ሠርጉ ተደግሶ በሺህ አጀብ ጋብቻው ከተፈፀመ በኋላ በሁለተኛው እና በሦስተኛው ወር ላይ ለፍቺና ለንብረት ክፍፍል በየፍርድ
ቤቱ መሯሯጥ የተለመደ ነው፡፡ ቁም ነገሩ የተጋባዡ ቁጥርና የግብዣው ብዛት ሳይሆን የተጋቢዎቹ ፅኑ ፍላጐትና እምነት ነው። ለእኔ እንደሚገባኝና እንደማምነውም ከሆነ በሁለቱ የዛሬዎቹ ሙሽሮቻችን መካከል
ያለው ሃብት ንብረት ሲኖር አንድና ብቸኛ የሆነው " ፍቅር" ብቻ ነው።
ፍቅር ሳይኖር የሚፈፀም ጋብቻ ከጥሩ ቪላ ቤት ከጥሩ መኪና በአጠቃላይ ከጥሩ ገንዘብ ጋር የሚደረግ ጋብቻ እንጂ ንብረቱን በሚያፈሩት የትዳር ጓደኛሞች መካከል የሚፈፀም ስላልሆነ አንድ ቀን ያ ገንዘብ እንደ
ጉም በንኖ ሲጠፋ የውሽቱ ፍቅርም አብሮ ሰናኝና ጠፊ ይሆናል። ስለዚህ በታደስና በሰላማዊት መካከል ያለው እውነተኛ ፍቅር አብቦ ከዚህ የበለጠ ሆነው ልጅ ወልደው ለመሳም በቅተው አብረው ጥረው ግረው ንብረት ሲያበጁ ደግሞ እምነት አለኝ አስር ልጆች ወልደውም ቢሆን እንኳ
በዛሬዋ እለት አልተደረገም ብለው ቅር የተሰኙበት ነገር ቢኖር በዚያን
ጊዜ እንደ አዲስ ተጋብተው እንደ አዲስ የሙሽራ ልብስ ለብሰው ሰንጋው ተጥሎ ጮማው እየተቆረጠ በሺህ አጃቢ ታጅበው እልል እየተባለላቸው
ጋብቻቸውን በድጋሜ ሊፈፅሙ እንደሚችሉ አልጠራጠርም፡፡ እኛም ዕድለኞች ከሆንና እድሜም ከሰጠን ያንን ደስታ ያንን አለም ለማየት እንበቃ ይሆናል። በእውነት ነው የምላችሁ ይህንን የምናገረው ስሜታዊ ሆኜ ሳይሆን ከዚህ በፊት ያየሁት እና ያጋጠመኝ ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ በድህነትና በችግር ላይ ሆነው ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ሀብት አግኝተው ወልደው
ከብደው በልጆቻቸው ሚዜነት እየታጀቡ እንደ አዲስ ሰርጋቸውን የሰረጉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ስለማውቅ ነው። የዛሬዎቹ ሙሽሮቻችን የተገናኙበትና ለጋብቻ የተጫጩበት አጋጣሚ ብዙዎች የማይደፍሩት ሆኖ
ሳለ እነሱ ግን ደፍረው ገብተዋልና ዛሬ የጋብቻቸው ቀን ብቻ ሳይሆን
የህይወታቸው አዲስ ምእራፍ የሚጀመርበት ቀን ጭምር ነው ብዬ አስባለሁ። በዚህ አዲስ የህይወት ምእራፍ ውስጥ አዲስ የኑሮ ትግል ጀምረው በድል በመወጣት ወልደውና ከብደው የምናይበት ጊዜ ሩቅ ይሆናል ብዬ አልገምትም፡፡ የዛሬዋን ጋብቻ እግዚአብሔር የአብርሃምና
የሳራ እንዲያደርግላቸው ቤት ንብረት ይዘው እንዲያስጨፍሩን ምኞቴን እየገለፅኩ መልካም የትዳር ዘመን ይሁንላቸው እላለሁ” አነጋገሩ የብዙዎችን ልብ የነካ በመሆኑ ጭብጨባው ቶሎ አላበቃም ነበር፡፡ በአስር አለቃ
ንግግር አንጀታቸው ቅቤ የጠጣው እማማ ወደሬ ትንሽ ንግግር ለማስማት፣ ልባቸው ላይ የምትንቀለቀል የደስታ ስሜታቸውን በቃላት ለመግለፅ ፈለጉ፡፡ በያዟት አሮጌ መሀረብ ከንፈሮቻቸውን አብስ አብስ አደረጉና የተወለጋገዱ ጥርሶቻቸውን ብልጭ አደረጉ።

እኔም ደስ ብሎኛል! አንጀቴ ቅቤ ጠጥቷል፡፡ ሞት ቀድሞኝ ቢሆን ኖሮ ይህን ዓለም ይህን ሲሳይ አላየውም ነበር፡፡ እመቤቴ ማርያም ጠሎቴን ሰምታ ለዚህ ታበቃችኝ ከእንግዲህ በኋላ ብሞት እንኳ ሞትኩ አይባልም፡፡ ልጅ ወልጄ ለመዳር ማህፀኔ ባይታደልም በስተርጅና በመሞቻ
ጋዜዬ ምስጋና ይግባትና እመቤቴም ሰላማዊትን የመሰለች ልጅ ሰጥታኝ ለዚህ ስትበቃ እንዳይ ስለረዳችኝ ደስታዬን የምገልጥበት ቋንቋ የለኝም።
እንደ ማር እንደ ወተት ያጣፍጣችሁ። ፍቅራችሁ ፍቅር ይሁን። አይለያችሁ። የምታስቀኑ ያድርጋችሁ። በክፉ የሚያያችሁን ዐይኑን ይያዝላችሁ" ብለው መረቁና ተንፈስ አሉ። ሙሽሮቹ እማማ ወደሬ ሲናገሩ
ልባቸው በደስታ ተሸበረ። ዐይኖቻቸው እምባ አቀረሩ... የደስታ እምባ...
እየተበላ እየተጠጣ እስክስታ እየወረዱ ሲደሰቱ ሲጨፍሩ ቆይተው መሸትሸት ሲል ሙሽሪት በአጃቢዎቿ በታደሰና በጓደኞቹ ታጅባ በአንድ ታክሲ ውስጥ ታጭቀው ወደ ታደሰ ቤት በረሩ...
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
አዲሷ ሙሽራ ሰላማዊት አዲሱን ህይወት በመላመድ ላይ ነች፡፡ ከታደስ እውነተኛ ፍቅርና መተሳሰብ ጋር ከዚያ አስቃቂ ኑሮ ከእስር ተላቃ የነፃ ህይወት አየር በመተንፈስ ላይ ነች፡፡ ከውስጥም ከውጭም አማረች፡፡ደመቀች። ታደስ በደላላነት ሥራው ከሚያገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ነጋዴዎች የቀናቸው እለት በተደሰቱበት ጊዜ የሚስጡት ድጉማ ላሌላ ባይተርፍም ሁለቱን በደስታ ሊያኖራቸው የሚችል ነው፡፡
የፋሲካ በዓል ደርሷል። ህዝቡ በሁሉም መስክ ለዝግጅቱ መሯሯጥ ጀምሯል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ሽሮ ያረረበት ለፋሲካ በዓል በቅቤ ያበደችውን ዶሮ ሰርቶ ከጐረቤቱ ከጓደኛው እንዳያንስ ራሱን እየበደለ በቋጠራት ሳንቲም ቢቻል በግ ካልቻለ ደግሞ የቅርጫ ስጋ ተቀራጭቶ ይገባል።
ልጆቹ ሚስቱ የጐረቤት ወጥ እንዳይሽታቸው የሌላ ሰው ቤት እንዳይቀላውጡ የበይ ተመልካች እንዳይሆኑ.. በፋሲካ ሰሞን ሁሉ ነገር ዋጋው እሳት ቢሆንም የአቅሙን ያክል ይዘጋጃል። ለፋሲካ የዶሮ ላባው ይበላ
ይመስል ገብስማ፣ ወሰራ፣ ልበወርቅ፣ ቀይ፣ነጭ.እየተባለ ዋጋው ይሰቀላል። እንደዚያም ሆኖ ግን ሁሉም ጥርሱን ነክሶ ይገዛታል እንጂ አይቀርም፡፡ ምን ዶሮ ብቻ? በበአል ሰሞን ምን የማይወደድ ነገር አለ?
👍4
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_አራት


#ድርሰት_በትክክል_ገና


...ባሏ ታደስ የሰውን የማይመኝ ከሰው የማይጠብቅ በራሱ የሚተማመን ኩሩ ባል መሆኑን ብቻ ነው፡፡ እንደዚህ ዛሬ በአይኗ እንዳየችውና ከአንደበቱ እንደምትሰማው የተበደለውን፣ የቆሰለውንና የደማውን ሰላማዊ
ህዝብ ለመካስ ቆርጦ የተነሳ ስለመሆኑ ምልክቱን ያየችው ገና ዛሬ ነው።

ታደሰ ብዙውን ጊዜ ይህንን ጉዳይ ሊገልጽላት እየፈለገ ህይወትህ አደጋ ላይ ትወድቃለች ይቅርብህ” ትለኛለች በሚል ሥጋት ነው የደበቃት፡፡ዛሬ ግን አጋጣሚው በተወሰነ መልኩ ራሱን እንዲያስተዋውቅ አደረገው።

“ይህ ሰው ምናልባት እኔ ሳላውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪ ይሆን እንዴ?"አለች በልቧ። መደበኛ ስራው ድለላ መሆኑን ተጠራጠረች።
“ታዴ ከድለላ ሌላ የምትሰራው ስራ አለ እንዴ? ድለላ አንዱን እየጎዱ ሌላውን የመጥቀም ነገር የለበትም? ሸፍጥ የለበትም? ለመሆኑ በዚህ ፀባይህ የድለላ ስራን እንዴት ልትመርጠው ቻልክ?” ከሚነግራትና በተግባርም ካየችው ባህሪው የተነሳ የድለላ ስራው የሚያሳድርበትን ተፅእኖ
ለማወቅና ከዚያ ጣፋጭ አንደበቱ የሚወጡ ተጨማሪ ቃላትን ለመስ
ማት ጥያቄ ጫና አደረገችበት።

“ስላምዬ ስራዬ የምታውቂው ድለላ ነው። የድለላ ስራዬ ሻጭና ገዥ በሚያዋጣቸው ዋጋ እንዲገበያዩ በማድረግ ሁለቱንም ወገኖች አስደስቼ ለኔም የሚገባኝን ጥቅም ማግኘት ነውና በሽተኛን የሚፈውሰው ዶክተር፣
የእውቀት ጮራ የሚፈነጥቀው መምህር፣ የአገር ድንበር የሚጠብቀው ወታደር ሥራቸውን የሚወዱትን ያክል እኔም በእኔ የእውቀት ደረጃ የደላላነት ስራዬን እወዳታለሁ፡፡ ያልተገባ የድለላ ስራን በመስራት ሰዎችን መጉዳት ግን ለበጎ ህሊና ተቃራኒ ከመሆን አልፎ ከሰዎች ጋር የሚያጋጭ ነውና እንዳልሽው ጥንቃቄን የሚጠይቅ ስራ ለመሆኑ ጥርጥር
የለውም። ድለላን የመረጥኩት ግን በማንበብና በመፃፍ የትምህርት ደረጃ ዶክተር መሆን ስለማልችል ነው” እየሳቀ መለሰላት። ሰላማዊት ባሏ
ታደስ በማንበብና በመፃፍ የእውቀት ደረጃው የርቱእ አንደበት ባለቤት መሆኑ እያስደነቃት የበለጠ እንዲያወራላት ስሜቱን በመኮርኮር ልትሞግተው ፈለገች፡፡
“ታዴ ገዥና ሻጭ በድለላ ስራህ ሁሌም ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም::
እያየህ ዝም አትልም፡፡ በመሃል ገብተህ በተሻለ ዋጋ አገበያያለሁ ማለት የማይቀር ይሆናል፡፡ ያንን ስታደርግ ደግሞ በውድ ዋጋ ሊገዛ የነበረው ሰው ሲደሰትብህ በውድ ዋጋ ሊሸጥ የነበረው ሻጭ ባንተ ቅር ይሰኝብሃል አይደለም?” አለችው። ታደሰ የሚስቱን የመከራከሪያ ነጥብ ስለወደደው
ለጠየቀችው ጥያቄ መልስ በመስጠት ሊያሳምናት ፈለገ፡፡

“በእርግጥ ሁሉም አይነት ስራ ሁሉንም ወገን እኩል የሚያስደስት ነው ብዬ ልከራከርሽ አልችልም፡፡ በጣም በርካሽ ዋጋ የሚገዛ ሰው ሻጨን ጎድቶ ነው የሚገዛው። በውድ ዋጋ የሚሸጠውም ገዢውን ጎድቶ ነው የሚሽጠው። በዚህ ጊዜ ሚዛን ማስጠበቅና ማካካስ ያስፈልጋል። በጣምም
ሳይወደድ፣ በጣምም ሳይረክስ፡፡ የኔ ስራ ሰዎች ተካክሰው ሳይጎዳዱ እንዲጠቃቀሙ ማድረግ ነው። ስራዬ ሻጭና ገዢ አሸናፊ የሚሆኑበትን መንገድ በማመቻቸት ሚዛኑን ማስጠበቅ ነው። የድለላ ስራ የሚያስጠላው ተዋዋይ ወገኖችን የሚጎዳ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባል
ሽፍጥ የተቀላቀለበት ሲሆን ነው። አይመስልሽም ?" አላት።

“ታዴ ሁሉንም ወገን እኩል የሚያስደስት ስራ እንደዚህ በቀላሉ የሚገኝ ይመስልሃል? ዳኛው ፍርድ ሲፈርድ እንኳ የተፈረደለት የሚደሰተውን
ያክል የተፈረደበት መከፋቱ የማይቀር ነው። ጠበቃው የሚጣላ፣ የሚደባደብ፣ የሚፋታ፣ የሚፈናከት በአጠቃላይ የሚካሰስ የጠፋ እንደሆነ አዝኖ ገበያዬ ቀዘቀዘ ይላል፡፡ የሬሳ ሳጥን ሻጩም ሰው ሞቶ የሰራው
ሳጥን ቶሎ ቶሎ ካልተሽጠለት ገበያ ጠፋ ብሎ ማዘኑ አይቀርም፡፡ እንዲያውም በነገራችን ላይ ስለ ሬሳ ሳጥን ሻጩ የሰማሁትን የሚያስቅ ነገር ልንገርህ፡፡ ስውዬው ዘመድ ሲሞትበት ሁል ጊዜ የሬሳ ሳጥን የሚገዛው
ከአንድ ቋሚ ደንበኛው ነበር አሉ፡፡ የሬሳ ሳጥን ሻጩ የዚህ የቋሚ ደንበኛው ውለታ ይከብደውና ሊክስው ይፈልጋል፡፡ በዚሁ መሀል እናት ይሞቱበትና ሳጥን ለመግዛት ሲመጣ የሬሳ ሳጥን ሻጩ ውለታውን ለመክፈል አስቦ በትልቁ ሳጥን ላይ አንድ ትንሽ የሬሳ ሳጥን ያስቀምጥለታል።
ሰውዬው ግራ ተጋብቶ ይሄ ደግሞ ምን ያደርግልኛል? ብሎ ቢጠይቀው ግድ የለም ጋሽዬ የዚህን ያክል ዘመን ደንበኛዬ ሆነው አንድ ቀን እንኳ
ክሼዎት አላውቅምና እሷን ደግሞ ለልጅዎ እንዲያደርጓት ምርቃት ነች አለና መለሰለት" ታደሰ በሳቅ ፍርስ አለ። “ሰላምዬ በጣም ያስቃል። ግን ምን ታደርጊዋለሽ የዓለም ነገር ይኸው ነው። ሳጥን ሻጩ ውለታ መክፈሉን እንጂ ልጅህን ይግደልልህ ማለቱን አላሰበውም። እሱ የታየው
በልጁ ሞት ምክንያት ደንበኛው የሚደርስበትን ሀዘን ሳይሆን ቋሚ ደንበኛውን መካሱንና ደንበኛነቱን ማጠናከሩን ብቻ ነው"እንደዚህ እየተጨዋወቱ ከቆዩ በኋላ ተቃቅፈው ወደ ጓዳ ገቡ።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ያቺ በናፍቆት የተጠበቀችው የፋሲካ በዓል ደረሰች። ታደሰና ሰላማዊትም በደስታ ሊቀበሏት ሽር ጉድ ሲሉ የከረሙላት፣ በለሊት ተነስተው የሚጐራረሱባት ዕለት ከተፍ አለች።
“ታድዬ...ተነስ...ዶሮ ጮኋል” አለችው። እስከ እኩለ ለሊት ዶሮ
ወጡን ስትስራ ቆይታ እንቅልፍ ሳይወጣላት ነበር የመፈሰኪያው ስዓት የደረሰው።
“ከምንጊዜው ሰላምዬ? ትንሽ እንኳን ሳንተኛ?" እሱም በቂ እንቅልፍ አላገኘም ነበር። በአንዳንድ ነገር ሲያግዛት ነው ያመሸው። ከአልጋቸው ላይ ተነስተው እየተጉራረሱ ፆም ይፈቱ ጀመር።
“ይሄኔ..” አለ ታደሰ።
“ይሄኔ ምን?” ወደ ጐን በፍቅር እያየች ጠየቀችው።
“እንትን...” ሳቅ አለና ሆዷን ተመለከተ።
“ገባኝ” እሱን ተከትላ እየሳቀች።
አንድ አድማቂ የመሀል አጫዋች፣ሌላ ፍቅርን የሚጨምር ፀጋ በመካከላችን ቢኖር ኖሮ ፋሲካው የበለጠ ፋሲካ ደስታው የበለጠ ደስታ ፍቅሩም የበለጠ ፍቅር ይሆን ነበር ማለቱ እንደሆነ ገባት ።
“እሱማ የዛሬ ዓመት ነዋ ታዴ?”
በሚቀጥለው ዓመት በዛሬዋ ቀን ፋሲካን ሲፈስኩ ድንቡሽቡሽ ያለ ልጅ ወልደው መጪዋን ፋሲካ በድምቀት እንደሚቀበሏት በምኞት ተጨዋወቱ፡፡ ሰላማዊት የወር አበባዋ ከቀረ ውሎ አድሯል። ማቅለሽለሽና ማስመለስ እያዘወተራት ነው። ታደሰ ይሄ ሁኔታ እርግዝና መሆኑን ካወቀ
በኋላ ልጅ የማግኘት ጉጉቱ በጣም ከፍተኛ ሆኗል። ዛሬም ይሄኔ...
የሚላት አንድ ልጅ በመካከላችን ቢኖር ደስታው ድርብ በአሉም በእጥፍ ደማቅ ይሆንልን ነበር ማለቱ ነበር፡፡
“ታዴ ወንድ ነው ወይንስ ሴት ብወልድ ደስ የሚልህ?“
“ስላምዬ ማሚቱም ማሙሽም ተወዳጅ የአምላክ ስጦታዎች
ናቸው። ሰው ነንና አንዳንድ ጊዜ ማሙሽን ከማሚቱ ማሚቱን ከማሙሽ የምንመርጥበት ጊዜ ይኖራል። ብዙውን ጊዜ እናት ሴት ልጅ ለመውለድ ትፈልጋለች፡፡ አባት ደግሞ ለወንድ ልጅ ያደላል ለምን እንደሆነ ግን አይገባኝም።
እኔ እንጃ ታዴ እኔ ግን አሁን አንተ እንዳልከው ሴት ልጅ ብወልድ ደስታውን አልችለውም”
እንደሱ ካልሽ እኔ ደግሞ ወንድ ልጅ ብትወልጅልኝ ደስታውን
👍53
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_አምስት


#ድርሰት_በትክክል_ገና

...የፖሊስ አዛዥ ያዘጋጁትን ንግግር ለመጀመር ጉሮሯቸውን አፀዱ “እህ..እህህ..ውድ የእለቱ የክብር እንግዶች ወንድሞቼ እህቶቼና የሥራ ባልደረቦቼ በዛሬው እለት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኛችሁበት
ይህን ፕሮግራም ማዘጋጀት አስፈላጊ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ያለፈው ዓመት አፈፃፀማችንን በመገምገም ጠንካራና ደካማ ጎናችንን ለመለየት ሲሆን ባለፈው ዓመት የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ አጠናክረን የተሻለ
ውጤት ለማስመዝገብና ድክመቶቻችንን በውል ተገንዝበን በማስወገድ በቀጣይ የስራ ዘመናችን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ የምንችልበትን
ስትራቴጂ ለመንደፍ ነው፡፡

የተቋማችን ዋነኛ ዓላማ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በየ አካባቢው እያቆጠቆጠ ያለውን የወንጀል ድርጊት በተቻለ መጠን ለመግታትና ለመቆጣጠር እንደመሆኑ መጠን ይህንን ዓላማ እውን ለማድረግ በርካታ ተግባራት ከፊት ለፊታችን ሆነው ይጠብቁናል፡፡ ወንጀል በተለያዩ
መንገዶች የሚገለፅ የማህበረሰቡ ቁስል ነው። ወንጀል አብሮ የመኖር እንቅፋት የመተሳሰብና የመተባበር ነቀርሳ፣ የልማትና የእድገት ፀር ነው። በአጠቃላይ ወንጀል የማህበረሰቡ ክፉ በሽታ ነው። በሽታ ካለ የመንፈስም ሆነ የአካል ጥንካሬ አይገኝም። በሽታን ለማጥፋት ሳይንቲስቶችና
ተመራማሪዎች የእያንዳንዱን በሽታ ባህሪ ለማወቅ የጀርሞች፣ የባክቴሪያና የቫይረሶችን አፈጣጠር በማጥናት መፈወሻ መድኃኒት ለመቀመም ቀን ከለሊት ይማስናሉ። በሽታ ሽባ ያደርጋል፣ በሽታ እብድ ያደርጋል፣
በሽታ የአልጋ ቁራኛ ያደርጋል። በሽታ ይገድላል። ወንጀልና በሽታ አንድ ናቸው፡፡ ወንጀል ከትንሹ ጀምሮ ቀስ በቀስ እያደገና እየሰፋ ሲሄድ ቀሳፊነቱ በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል። በጊዜውና በወቅቱ ያልተቀጨ በሽታ
ህይወት ይዞ እንደሚሄደው ሁሉ በወቅቱና በጊዜው ያልተቀጨ ወንጀል እያደገና እየሰፋ ሲሄድ ማህበራዊ ቀውስን ያስከትላል። አገራዊ ሰላምን አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ወንጀለኛ ከሌላ ወንጀል አይኖርም፡፡ ወንጀል እንዳይስፋፋ አስፈላጊው ጥረት ከተደረገ ደግሞ ወንጀለኛ አይኖርም፡፡ ወንጀልን
በማስወገድ የህብረተሰቡን አጠቃላይ የደህንነት ዋስትና ማረጋገጥ የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ አባል ለደህንነቱ መረጋገጥ የግልና የቡድን አስ
ተዋፅኦ ሲያደርግና የቆምንለትን ዓላማ መደገፍ ሲችል ብቻ ነው። እኛም እያንዳንዱ ሰው ይሄንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ያለመታከት ማስተማር ይጠበቅብናል።

አብዛኛው ነዋሪ ያለስጋት የሚዘዋወረው አምሽቶ የሚገባውና የሚወጣው እኛ የሱን ሰላም የምናስጠብቅ እንቅፋት ቢመታው ፈጥነን የምንደርስ፣ ያላግባብ በደልና ጥቃት ቢደርስበት ጥብቅና የምንቆም ባለአደራዎች በሰው ልጆች የተፈጠረና ሰዎችን በበላይነት እንዲመራ የተደነገገውን ህግ የምናስከብር አካላት መኖራችንን ተስፋ አድርጎ ነው። በመሆኑም ህጉንና ደንቡን ተላልፈው ወንጀል የሚፈፅሙ ህገወጦችን ለፍርድ
በማቅረብ የተረጋጋና አስተማማኝ የሰላም ዋስትናን ማረጋገጥ እስከሚቻል ድረስ አገልግሎታችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። የህብረተሰቡን ስላም ለማስጠበቅ የእያንዳንዱ ግለሰብ ሰላም መጠበቅ ይኖርበታል። ይህን ዓላማችንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰፊ የህዝብ ድጋፍና
ትብብር ያስፈልገናል።

የህብረተሰቡ እርዳታ የህብረተሰቡ ድጋፍና ትብብርና በሌለበት ብቻችንን የምናደርገው ሩጫ በአንድ እጅ እንደማጨብ
ጨብ ነው። ወንጀለኞች በህዝቡ ውስጥ ሆነው ወንጀል በህዝቡ ላይ እየፈፀሙ ተመልሰው ህዝቡ ውስጥ ገብተው የሚሸሸጉ ከሆነ የሚጐዳው ህዝቡ ራሱ ነውና የበለጠ የኃላፊነት ስሜት ተሰምቶት ራሱን ከአደጋ
ለመከላከል ወንጀለኞችን የማጋለጥ ግዴታውን እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቅብናል። ህብረተስቡ ወንጀለኛን የሚያቅፍ፣ የሚሽሽግ ከሆነ ደግሜ እናገራለሁ ድካማችን ሁሉ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ብቻ ሳይሆን ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው የሚሆነው። በንግግሬ መሃል አንድ ከዚህ ነጥብ ጋር አብሮ የሚሄድ ትምህርት ይሰጠናል ብዬ የምገምተውን ቀልድ ልንገራችሁ። ሁለት ወንድማማቾች የታጨደ የእህል ክምር ከሌባ ለመጠበቅ ማሳቸው ላይ ገለባ ለብሰው ይተኛሉ። ለሊት ላይ ጅብ ይመጣና
ያንን ገለባ ገላልጦ የአንደኛውን እግር መቆርጠም ይጀምራል። በስማው ድምፅ ግራ የተጋባው ወንድም “ምንድነው የሚሰማኝ ድምፅ?" ብሎ ወንድሙን ይጠይቀዋል።

“ቀስ በል አትጩህ የኔን እግር እየበላ ነው” ሲል በፍርሃት ተውጦ
ይመልስለታል። በዚህ ጊዜ ፎክሮ ይነሳና “አንተ ፈሪ አንተን በልቶ
ሲያበቃ ወደኔ መምጣቱ ይቀራል እንዴ?” በማለት ቆርጥሞ ሳይጨርሰው እሱንም ሳይጀምረው ጅቡን አባረረው ይባላል” በዚህ ጊዜ ሁሉም
በሳቅ ፈነዱ... የተሰብሳቢው ሳቅ ጋብ እስከሚል ድረስ ጠብቀው ቀጠሉ።
“እና ከዚህ ቀልድ ትልቅ ቁም ነገር እንማራለን፡፡ ዛሬ ወንጀለኛን ያቀፈ
ህዝብ ወንድሙ አጠገቡ ሲመታ ሲቆስል ሲሞት እያየ እኔ እስካልተነካሁ ድረስ ምን ቸገረኝ? በማለት ወንጀለኛውን ከማጋለጥ የሚቆጠብ ከሆነና ወንጀለኛን እንደ ጅቡ በጊዜ ማባረር ካልቻለ ተመልሶ በሱ በራሱ ላይ
የሚዘምትበት መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡በዚህ ረገድ የዛሬው ሁለተኛው የስብሰባችን ዋና አላማም ከህዝቡ መካከል ይህንን ተገንዝበው በቀጥታም
ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከእኛ ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመስራት ለከፍተኛ ውጤት ያበቁን ወንድሞቻችንን በመሸለም ለሌሎችም አርአያ እንዲሆኑና ሞራላቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት እነኝህን
ውድ የህዝብ ልጆች ለማታውቋቸው በማስተዋወቅ ላበረከቱት አስተዋፅኦ
ማበረታቻ ይሆናቸው ዘንድ የተዘጋጀላቸው ሽልማት በእናንተ ፊት ይስጣቸዋል። ሁላችንም እንደምናውቀው ወንጀል ይበዛባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል ዋነኛው እሪ በከንቱ እንደነበር ግልፅ ነው። ከስም አወጣጣቸው ጀምሮ ዶሮ ማነቂያ፣ እሪ በከንቱ በሚባሉት በእነዚህ ሰፈሮች ውስጥ በርካታ ወንጀሎች የሚፈፀሙበት ለእሪ ባይ ረዳት የማይደርስበት የሰው ልጅ እንደ ዶሮ ተቆጥሮ በዶሮ ማነቂያ ስም አንገቱ የሚታነ
ቅባቸው አካባቢዎች ነበሩ፡፡ እነዚያ አካባቢዎች እንደምታውቁት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ሰው በልቡ እምነት አሳድሮ የሚረማመድባቸው አልነበሩም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን እሪ በከንቱነቱና ዶሮ ማነቂያነቱ ቀርቶ ሰዎች
በፈቀዳቸው ሰዓት የሚመላለሱባቸው አልፎ አልፎ በጣም አልፎ አልፎ ንጥቂያዎች ቢፈፀሙ ለእርዳታ ድምፅ የሚያሰማ ፈጥኖ ደራሽ የሚያገ
ኝባቸው የሰላም ቀጠናዎች እየሆኑ መጥተዋል። ይሄ ውጤት የተገኘው በተአምር ሳይሆን ሌት ተቀን ከእኛ ጋር አብረው በተሰለፉ ወንድሞቻችን ድካምና ጥረት ነው፡፡ ለዚህ ውጤት መገኘት በርካታ ተባባሪዎች ቢኖሩንም የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን ከዚህ ቀጥሎ አስተዋውቃችኋላሁ”
አሉና ዐይኖቻቸውን ወደ ተሰብሳቢዎቹ መካከል ወረወሩ።ፈገግታ የተላበስ ፊታቸውን ወደ ታደስ በእውነቱ አዞሩና ሁለቱን እጆቻቸውን ዘረጉ።
ታደስ ተነስቶ ቆመ:: ጭብጨባው አስተጋባ፡፡ ታደሰ ወደ መድረኩ ሄደ። “አዎን እሱ ወንድማችን ታደሰ በእውነቱ ይባላል! ወንጀለኞችን መስሎ ወንጀለኞችን ተቀላቅሎ ቀን ከሌሊት ብርቱ ትግል ያደረገና ተደጋጋሚ
ውጤቶችን ያስመዘገበ ወንድማችን ነው!”
👍2
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_ስድስት


#ድርሰት_በትክክል_ገና

....የህዝቡ ብዛት….በዚህ ላይ ጨለማ...ያ ሽለምጥማጥ አበራ ፍላጐቱን በቀላሉ ፈፅሞ ከአካባቢው ተሰወረ።..
ጓደኞቹ በሙሉ በመሀሌት ቤት እጅ ከፍንጅ ተይዘው ከታሰሩበት በኋላ ታደሰ ብቻውን ሊለቀቅ የቻለበትን ምክንያት ለማወቅ ስውርና ረቂቅ በሆነ መንገድ ሲከታተለው ነበር የሰነበተው፡፡
ባደረገው ክትትል ታደስ የነጣቂው ቡድን ዋነኛ መቅሰፍት መሆኑን እያወቀ መጣ፡፡ መረጃ እየሰበሰበ
ሲያቀብል ፖሊስ ፅህፈት ቤት ሲወጣ ሲገባ..ራሱን እየለዋወጠ ወንጀልና ወንጀለኛን ለማሳደድ የሚስራውን ሥራ በሙሉ ሲከታተለው ቆይቶ በመጨረሻ ላይ እውነታውን ደረሰበት።

ታደስ ከመረጃ አቀባይነቱ አልፎ ተርፎ እስከ መሸለም መብቃቱን፣
በዚያን እለትም ሌሎቹን ወንጀለኞች በሙሉ ካሳሰረ በኋላ እሱ በነፃ መለቀቁን፣ ለጊዜው የታሰረውም ለሽፋን መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በዚሁ መሰረት
ታደሰን ለመበቀል ሲያደባ ቆይቶ ሰላማዊትና ታደሰ ከመኖሪያ ቤታቸው ተነስተው ትያትር ቤት እስከገቡበት ጊዜ ድረስ በጥብቅ ሲከታተላቸው ዋለና ያን አስከፊ ድርጊት ፈጽሞ አመለጠ፡፡
በከፍተኛ የህዝብ ትብብር
ነፍሰ ጡሯ ግራና ቀኝ ተይዛ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ እንክብካቤ ተደርጉላት ከባሏ ጋር ወደ ሆስፒታል ተወስዱ። በመውደቋ ምክንያት መጠነኛ ንቅናቄ ደርሶባት ስለነበረ ወደ ማህፀን ክፍል ተወሰደች። ታደሰ ደግሞ
ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል እንዲገባ ተደረገ፡፡ በግራ ጐኑ የገባችው ጥይት ጉበቱን በስታ በቀኝ ጐኑ ወጥታ ነበር፡፡ ሆስፒታል እንደገባም አጣዳፊ
የሆነ የቀዶ ጥገና ህክምና ተደረገለትና ደም ከተሰጠው በኋላ ግሉኮስ በግራ ክንዱ ላይ ተሳካለት፡፡
ሰላማዊት የደረሰባት መጠነኛ ጉዳት በመሆኑ በማግስቱ ድና ተነሳች። ታደሰ ግን ክፉኛ ተጐድቷል፡፡ እማማ ወደሬ በጠዋቱ ጉዳቸውን ሲሰሙ
በድንጋጤ ክው ብለው ቀሩ፡ ያ እንደ እናቱ የሚያያቸው፤ ትንሽ ሲያማቸው የሚጨነቅላቸው፣ የዳሩት ልጃቸው የሆነውን ሰሙ። በተለይ ይህ አደጋ በደረሰበት እለት “እንኳን አደረስዎ” ሊላቸው የሚወዷትን ነጭ አረቄ ይዞላቸው ሄዶ ሊያጫውታቸው፣ ሲያስፈነድቃቸው ነበር የዋለው።

“ታዴን! ታዴን! ልጄን! .እኔ እናትህ ድፍት ልበል! የኔ ደም ክንብል
ይበል! ለካ ለዚህ ነው? ለካ አንጀቴን ሲበላው ነው? ምነው ከኔ በፊት? እኔ አሮጊቷ ቁጭ ብዬ...እኔን ያስቀድመኝ...” ልብሳቸውን ሳይቀሩ እየጮሁ ወደ ሆስፒታል ሮጡ አደጋውን የሰሙ
የቅርብ ጓደኞቹ ሲያስታምሙትና ሲጠይቁት ከረሙ:: ታደሰ ግን በየጊዜው የመሻሻል ምልክት ከማሳየት ይልቅ የድካም ምልክቱ እየጨመረ ሄደ። ጉበቱ ክፉኛ ተጐድቶ ነበር፡፡የመዳን ተስፋው የመነመነ መሆኑን ሆስፒታሉ አስታወቀና ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ከሆስፒታል ወጥቶ ህክምናውን በቤቱ ውስጥ እንዲ
ከታተል ተደረገ፡፡ ወይዘሮ ወደሬ ቤታቸውን ዘግተው ንግዳቸውን ርግፍ አድርገው ትተው በአንድ በኩል ነፍስ ጡር ልጃቸውን በሌላ በኩል በሽተኛ ልጃቸውን ለመርዳት ጉለሌ ተጠቃለው ገቡ።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ከገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ጀርባ በአንድ ትልቅ የባህር ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ የሆነ የተንጠለጠለ ነገር በርቀት ይታያል፡፡ በአካባቢው ግርግር እየ
ተፈጠረ ነው፡፡ የሰፈሩ ነዋሪዎች ከህፃናት ጀምሮ ወደ ጫጫታና ግርግሩ ስፍራ እየሮጡ ሲደርሱ ሙሉ ጥቁር ሱፍ የለበሰ፣ ክራቫት ያደረገ መልከ መልካም ወጣት በወፍራም ገመድ ላይ ዘለዓለማዊ የቁም እንቅልፍ አንቀላፍቶ ጠበቃቸው።
ዐይኖቹ ገርበብ ብለው ሲታዩ የሚያዝንለትና የሚያዝንበትን ህዝብ በትዝብት የሚያስተውል ይመስል ነበር፡፡ ቀይ ቀሚስ፣ እጅጌ ጉርድ ሰማያዊ ሹራብ የለበሰች ዕድሜዋ ከአስራ ሰባት ዓመት የማይበልጥ ጠይም መካ
ከለኛ ቁመት ያላት ሴት ልጅ ደግሞ በሟቹ እግር ላይ እየተንከባለለች እዬዬና ዋይታዋን በማሰማት ላይ ነበረች።

“የኔ አለኝታ! የኔ መመኪያ ! ምነው? እኔን ለማን ጥለኸኝ? የቀን ጅብ በላኝ እኮ! ሰማዩ ተደፋብኝ...” በሟቹ ምክንያት ስለሚደርስባት ችግር እያወራች ለራሷ የምታለቅስ ትመስላለች። በዚያን ሰሞን በሰፈሩም ሆነ
በመሥሪያ ቤቱ አካባቢ የሰመረ ሞት የሳምንቱ ዐብይ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ሰነበተ። ሰመረ በገዛ ህይወቱ ላይ እንዲፈርድ ያቺን የምታሳሳ ህይወት እንዲንቃት ያስገደደው ምን ይሆን? ምክንያቱን ለማወቅ ሁሉም
ጆሮውን አቁሞ ፍንጩን ለማግኘት አነፈነፈ። ገሚሱ በሰማው ላይ
የራሱን እየጨመረ ወሬውን አራገበ፡፡ ሰመረ ህይወቱን ለማጥፋት ያነሳሳውን ምክንያት ማወቅ አለማወቅ የሚያመጣው ለውጥ ግን አልነበረም።
የሰመረን የልብ ውስጥ ቁስል ከሚያውቁ ጓደኞቹ መካከል የቅርብ ጓደኛው ሳሙኤል ነበር፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ችግርና ደስታን የተካፈሉ ጓደኛሞች ናቸው፡፡
ሳሙኤል !" ጐረቤቱ ጌዴዎን ነው የጠራው፡፡
“አቤት!” አገር ሰላም ነው ብሎ የጠዋት ፀሀይ ለመሞቅ በረንዳው
ላይ ቁጭ ብሏል፡፡
“አልሰማህም ?”
“ምኑን?”
“የሰመረን?”
“ምን ሆነ?!”
“ሰመረ እኮ . . .”
“መኪና ገጨው እንዳትለኝ ጌዴዎን!!.…” ደንግጦ ተነሳ።
“እ…እ..እኔማ ሰምተህ መስሎኝ፡፡ መኪና አይደለም…ራሱን አጥፍቶ ነው...” ከሳሙኤል የወጣ ትንፋሽ አልነበረም። በድን ሆኗል።
አንጀቱ ድብን ብሏል። ጌዴዎን ሳያውቀው በቀላሉ ሞቱን ያረዳው ሰው ለሳሙኤል የወንድም ያክል ነበር።ቀሳሙኤል ጭንቅላት ውስጥ በርካታ የሰመረ ትዝታዎች ተመላለሱ። ሰመረ በልጅነቱ፣ ስመረ በቄስ ትምህርት ቤት፣ ሰመረ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት፣ ሰመረ በዩኒቨርስቲ በይዘታቸው አንድ በዓይነታቸው ግን ብዙ ሰመረዎች በዓይነ ህሊናው ላይ ሄዱበት። ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ይዞ በቤቱ በረንዳ ጠርዝ ላይ በክርኑ ተደግፎ አንገቱን ቁልቁል ደፍቶ ለረጅም ጊዜ ሲተክዝ ቆየ። ትዝታ የጓደኝነት ፍቅር....ከውስጥ እያቃጠሉት እንባ ያቆረዘዙ
ዐይኖቹ ያዘሉትን ውሃ ወደ ታች ለቀቁት...
ጌዴዎን የጓደኝነታቸውን ደረጃ ሳያጣራ በመናገሩ አዘነ። ድርጊቱ አንድ ችኩል መርዶ አርጂ ከፈፀመው ድርጊት ጋር ተመሳሰለበት፡፡ ሰውዬው
እናቱ የሞተች ባልንጀራውን በደንቡና በሥርዓቱ መሰረት በለሊት እንዲያረዳ ሃላፊነት ይሰጠዋል፡፡ ችኩሉ መርዶ አርጂ ግን እዚያው መሥሪያ ቤቱ ድረስ ይሄድና “ስማ እንጂ! ስለ እናትህ ስማህ እንዴ?”በማለት ይጠይቀዋል። አነጋገሩ ያስደነገጠው ልጅም “ምነው አመማት እንዴ?!”
በማለት መልሶ ጠያቂን ይጠይቀዋል፡፡
“ኽረግ ሊያውቅ ነው መሰል!" ይላል ችኩሉ መርዶ አርጂ። ይህ አባባሉ የበለጠ ያስደነግጠው ሰው "ምነው ባሰባት እንዴ?!” ሲል ደግሞ ይጠይቀዋል፡፡ ከዚያም ችኩሉ መርዶ አርጂ..“ጠረጠረ በለው!” ይላል። በዚህ ጊዜ ልጅ ክፉኛ ይደነግጥና...“ምነው?! ሞተች እንዴ?!” ብሎ በድጋሚ ይጮሃል፡፡ ችኩሉ መርዶ አርጂም “አወቀ በለው!ማን አባቱ
አረዳኝ ሊል ነው?!” አለና ፊቱን አዙሮ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ ጌዴዎንም የሳሙኤልን ሁኔታ ሲመለከት በችኩል መርዶ አርጂነቱ ደንግጦ ሊሮጥ
ቃጥቶት ነበር፡፡ ትውውቃቸውን እንጂ የቅርብ ባልንጀራሞች መሆናቸውን ቢያውቅ ኖሮ ሞቱን እንዲህ በቀላሉ አያረዳውም ነበር። ሳሙኤል በቀብሩ እለት እዬዬ ብሎ አለቀስ። ያቺ ሰመረ ራሱን በሰቀለ እለት እግሩ
👍61👎1
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_ሰባት


#ድርሰት_በትክክል_ገና

...ትናንትና አስተማሪው የሰጣትን የቤት ሥራ ሊያስረዳት ጀምሮ አቋርጦት ነበር። ቶሎ ብላ መጽሀፏን ደብተሯን ይዛ ከተፍ አለች። የለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ነው፡፡ ፀጉሯን በወፍራሙ ጐንጉናዋለች። ታደስ ጥሩ ፀባይ እንዳለው እየተረዳች በመምጣቷ ሰውነቷ መሸማቀቁን ዘንግቶ ዘና ፈታ ማለት ጀምሯል።በአልጋ ላይ በጎኑ ጋደም እንዳለ ማስጠናቱን ቀጠለ... አጥኚና አስጠኚ አለቅጥ ተቀራርበው ነበረና
ልብስ ባልለበሰ ክንዱ ልብስ ያልለበስ ክንዷን ሲተሻሽው ልስላሴዋና ሙቀቷ በክንዱ በኩል ዘልቆ ሁለመናውን አዳረሰው፡ሙቀቱ የፈጠረበት ስሜት ረበሽውና ቀና ብሎ ወደ ጎን አያት፡፡ እሷም እየተሽኮረመመች ወደ ጉን አየችው። ደማቅ የውበት ቀለም የተቀባች መሆኗን አጤነ፡ በቃ! አልቻለም፡፡ያንን ለብዙ ጊዜ ከራሱ ጋር ሲሟገት የቆየበትን ነገር ለማድረግ መገደዱን አመነ፡፡ሳብ አደረገና በክንዶቹ አቀፋት። አልተቃወመችም ሄዳ ልጥፍ አለችበት፡፡ ቀስ ብሎ ከንፈሯን ሳማት። እሷም አፀፋውን
መለሰች። ሲፈላለጉም ሆነ ሲገናኙ የነበረው ሁኔታ ከዚህ በፊት የሚተዋወቁ እንጂ አዲስ ጀማሪዎች አይመስሉም ነበር፡፡ ምግብ አብሳዩ እንጂ አቻው አለመሆኗ እየተሰማት እየተሸማቀቀች ለብዙ ጊዜ የቆየች ቢሆንም አስገዳጁ የጾታ ማግኔት ሳታስበው በስሜት አጋግሉ፣ ሰሜን ጫፍና ደቡብን አሳስቦ በድንገት ሲያስተቃቅፋቸው ምን ታድርግ? ከዚያም እግሮቿን በእግሩ ከታች ወደ ላይ ቢያስፈነጥራቸው ተወርውራ ሄዳ አልጋው ላይ በግራ ጎኑ ወደቀችና ከደረቱ ተጣበቀች፡፡ የአዳም የግራ ጎኑ ሄዋን...ታደሰ ከስድስት ወር የአእምሮ ሙግት በኋላ ዛሬ ዳበሳት... ዙሪያሽ ጨዋነቷን አስመሰከረች. . ልጃገረድ! ...
“ጋሼ ታደስ እኔ እኮ ድሃ የድሃ ልጅ ነኝ ካንተ ጋር እንደዚህ አይነቱን
ነገር መፈፀም አልችልም፡፡ ያለ አቅም መንጠራራት ትርፉ አደጋ ላይ መውደቅ ነው”
“ዙሪያሽ እኔም ድሃ የድሃ ልጅ ነኝ ነገር ግን ወላጆቼ የገንዘብ ድሆች
እንጂ የመንፈስና የሞራል ድሆች አልነበሩም፡፡ ከገንዘብ ድህነት የበለጠ ሰውን የሚጐዳው የመንፈስ ድህነት ነው። ያንቺም ወላጆች የገንዘብ ድሆች ከነበሩ እኔም እንዳንችው የድሃ ገበሬ ልጅ ነኝና ስለአቻነታችን በፍፁም አትጠራጠሪ፡፡ በዚያ በኩል ስላለን ልዩነት አትጨነቂበት” አላት።

“ጋሼ ታደሰ የሞራልና የመንፈስ ድህነት ከአጐቴ ሞት ጋር ተደምረው ጐድተውኛል። አጐቴ... አጐቴ... የሀብታም ልጅ የሆነችውን የትምርት ቤት ጓደኛው እመቤት መስፍንን ወደዳት... እሷም ወደደችው። ፍቅራቸው ግን አቻ አልነበረም፡፡ አጐቴ የድሃ ልጅ በመሆኑ ወላጆቿ አልወደዱትም፡፡ ዘረ ምናምንቴ የድሃ ልጅ እያሉ አንቋሸሹት። ቅስሙን ሰበሩት። ሁለቱ ይፋቀሩ ነበር፡፡ የእሷ ወላጆች ውሻ አደረጉት።ለሀብታም ልጅ ታጭታ ቀለበት እንድታስር አስገደዷት።ጋሼ ሞራሉ ወደቀ፡፡
ብስጩ ሆነ፡፡ እሷ ትወደው ነበር፡፡ እየተዋደዱ ግን ተለያዩ፡፡ጋሼ ጤንነቱ ተቃወሰ፡፡መጨነቅና መጠበብ አበዛ፡፡ ብቸኝነት፣ የሞራል ውድቀት በዚህ ላይ ፍቅር አለ፡፡ እያፈቀሩ ማጣት ሰላም ነሳው። ብስጩነቱ እንዳይታወ
ቅበት ጥረት ቢያደርግም ያስታውቅበት ነበር፡፡ የሃብታም ልጅ ባይወድ ኖሮ ቢጤውን ቢፈልግ ኖሮ ይሄ ሁሉ አይመጣበትም ነበር፡፡ ጋሽ ታደሰ
የኔና ያንተም ተመሳሳይ ነው፡፡ አቻ አይደለንም፡፡ የድሆች ልጆች ብንሆንም በእውቀት እንበላለጣለን፡፡ አንተ የተማርክ ጥሩ ሥራ ጥሩ ደመወዝ ያለህ ሰው ነህ፡፡ እኔ ግን እዚህ ግቢ የማልባል በትምህርት ያልገፋሁ
ገረድህ ነኝ፡፡ ዝቅ ብለህ ከገሪድህ ጋር...እኔ ደግሞ ያለአቅሜ ተንጠራርቼ የሚደረግ ግንኙነት ጥሩ ነው ብለህ ታስባለህ?”
“ዙሪያሽ እንደሱ አታስቢ። በዚች በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በሚገባ ተጠናንተናል።ያየሽብኝ ጉድለት ካለ ደግሞ ግለጪልኝና ላርም፡፡ በእውነት ነው የምልሽ ዙሪያሽ እኔ ከዚህ በፊት ብቸኛ ነበርኩ ጓደኞቼ አይጦችና
ሽረሪቶች ነበሩ። ቤቴ ብቻ ሳይሆን አእምሮዬ ሸረሪት አድርቶበት ነበር፡፡
ብቸኝነትና የመንፈስ ጭንቀት ነበሩብኝ፡፡ መንፈሴን የሚያስጨንቀኝ ነገር ከሞላ ጎደል መፍትሄ እያገኘ ሃሳቤ እየሰመረ በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ፡፡
ወንጀሎች እንዲቀንሱ የበኩሌን ጥረት በማድረጌና ውጤቱን እያየሁ በመምጣቴ ደስተኛ ሆኛለሁ። በዚህ ደስተኛ ብሆንም አንድ ነገር እንደሚጐድለኝ ሁሌም ይታወቀኝ ነበር፡፡በተለይ እንደዚህ እንደአሁኑ ከነ ክብርሽ አገኝሻለሁ የሚል ግምት ባይኖረኝም አብረን በቆየንባቸው ወራቶች ውስጥ
ሳጠናሽ ነበር የቆየሁት። ያንን በጭንቅላቴ ውስጥ አድርቶ የነበረውን የብቸኝነት ድር የበጣጠስሽልኝ ከግማሽ ወደ ሙሉነት የምሸጋገርበት ተስፋ
የፈነጠቅሽልኝ አንቺ ነሽ፡፡ ያደረ የሆቴል ቤት ምግብ ትርፉ ቃር ነው።ከዚያ ነፃ ሆኛለሁ። አፈር አፈር የምትሽተው ኦና ቤቴ ዛሬ ሞቅ ደመቅ ብላ ቄጤማ ተጐዝጉዞባት እጣን ጤሶባት ሽታዋ የሚስብ ሆኗል። የቆሽሽ
ልብሴ ታጥቦ ንፁህ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ በውጭ እስከዚህ ድረስ ለውጠሽኛል። ነገር ግን የውጭ ለውጥ ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ውስጤ መለወጥ
አለበት፡፡ ባዶነቴን ብቸኝነቴን ለማስወገድ ለኔ ካንቺ የተሻለ እንደማይኖር በተለይ በዛሬዋ ምሽት በይበልጥ አረጋግጫለሁ። ጥንድነት ለአልጋ ብቻ አይደለም፡፡ችግር ሲያጋጥም የምታማክሪው፣ ደስታና ሀዘንሽን የምታካፍይው፣ የኑሮ ብልሃቱ እክል ሲገጥመው ዘዴ የሚቀይስ የሚያፅናና ጓደኛ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከሁሉ የሚበልጠው ጓደኛ ደግሞ የቤተሰብ መሠረት የትዳር ጓደኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሄዋንን ለአዳም አዳምን ለሄዋን የፈጠረላቸው ይህን ችግራቸውን አውቆ ነውና የታደሰ ሄዋን
አንቺ ዙሪያሽ ብትሆኚለት ምን ይመስልሻል ? በዛሬዋ ምሽት በእምነት ክብርሽን እንደሰጠሽኝ ሁሉ እኔም ንፁህ ፍቅሬን ልሰጥሽ ዝግጁ ነኝ፡፡ ከዛሬዋ እለት ጀምሮ በደንቡና በወጉ ተፈራርመን ገሃድ እስከምናወጣው ድረስ በባልና ሚስትነት አብረን እንኖር ዘንድ ምኞቴን የተቀበልሽው ስለ
መሆኑ ማረጋገጫ..” አለና ከንፈሩን አስጠጋላት፡፡
“ጋሽ ታደሰ እኔ እኮ... እኮ...ደሃ ነኝ ቢጤዬን እንጂ” የታችኛው ከንፈ
ሯን ነከሰች።

“ዙሪያሽ ስለድህነትና አቻ ስላለመሆናችን የምታወሪውን ለመርሳት ሞክሪ፡፡ እንደሱ እያልሽ አታስጨንቂኝ፡፡ ድህነት በደማችን ውስጥ የሚዘዋወር አብሮን የተፈጠረ ወይም እንደሚባለው የአርባ ቀን ዕድላችን አይደለም፡፡ ድህነትን በሥራ ልንደቁሰው እንችላለን፡፡ የእመቤት ወላጆች ሌላ እኔና አንቺ ደግሞ ሌላ ነን። የአጐትሽ ሞት ያስከተለብሽ ሥነ ልቦናዊ ጫና ቀላል እንዳልሆነ ይሰማኛል። የእመቤት ወላጆች የገንዘብ ሃብታሞች ቢሆኑ የእውቀት ድሆች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከገንዘብ ድህነት የከፋው
ደግሞ የአእምሮ ድህነት ነው። እኔና እነሱን አታወዳድሪን፡፡ ቢያንስም ቢበዛም ፊደል የቆጠርኩ ነኝና የፍቅርና የገንዘብን አንድነትና ልዩነት ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ሁለቱም ለሰው ልጅ ህልውና አስፈላጊ ናቸው።
ገንዘብ ያለበት ፍቅር አይጠላም፡፡ ማለፊያ ነው። ፍቅር የሌለበት ገንዘብ ግን ገንዘብ አይደለም፡፡ አያረካም፡፡ እመቤትን ወላጆቿ ገንዘብ ላለው ሰው አሳልፈው ቢሰጧት የምትረካ እንዳይመስልሽ፡፡ ዋናውን ግምት
👍15
#የተወጋ_ልብ


#ክፍል_ሃምሳ_ስምንት


#ድርሰት_በትክክል_ገና

..ባሌ... በሬሳ!
( ከአራት ዓመታት በፊት)

ከቀኑ አስር ሰዓት ተኩል አናቱ ላይ! በፀጥታዋ የምትታወቀው በሬሳ
በኡኡታ ተደበላለቀች። ሰማዩ በነጎድጓድ ድምፅ ታረሰ... በሬሳ ወልዳ አሳድጋ ለከፍተኛ ቁም ነገር ያበቃችው ተወዳጅና ብርቅዬ ልጇን እንደ ክፉ ድመት መልሳ ወደ ማህፀንዋ ልታስገባ አፏን በሰፊው ከፍታ አዛጋች፡፡ መልአከ ሞት አስገምጋሚውን የነጕድጓድ ድምፅ አሰምቶ በመቅስፍት በትሩ የአስካለን ልብ ያለርህራሄ በረቃቀሰው... ልጅዋ ናፍቋት፣
በህልሟ እየተመላለስ ሲያቃዣት ከረመና፣ ናፍቆቱ ዐይኗን ሊያወጣው ደረሰና ዳቦ ቆሎ ቆርጣ አዘጋጅታ ወደ አዲስ አበባ ሄዳ ልጇን እቅፍ
አድርጋ ለመሳም ቸኩላ ዝግጅቷን በማፋጠን ላይ ነበረች። ያ እንደነ
ፍሷ የምትወደው የምትሳሳለት ልጇ ግን መንገዱን ሊያስቀርላት፣ አዲስ አበባ ድረስ ሄዳ እንዳትንከራተት ድካሙን ሊቀንስላት በእንጨት ሳጥን
ተሞሽሮ ወደሷ እየገሰገሰላት ነበር።

ዘይኑን፣ አማረችንና ባልንጀሮቹን የጫነው አውቶቡስ ከቀኑ አስር
ሰዓት ተኩል ላይ በሬሳ ሲደርስ መንደሪቱ በጩኸት ታመሰች። እማዬ! እማምዬ! ጉድ ሆን! ወንድም ጋሼ...ወንድም ጋሼ! ጌትዬ!ጌትሽ!…. የኔ ፍቅር! እናቱ አስካለ አስቀድሞ ምንም ፍንጭ እንዲደርሳት ሳይደረግ ተዘጋጂ! ተጠንቀቂ! ሳትባል ሳይነገራት መአት ወረደባት። ምፅአተ
ቁጣውን ያረገዘው የሰቆቃ ጭጋግ ጥቁር ደመናውን በደሳሳ ጎጆዋ ላይ በድንገት አጥልቶ እንደ ንስር አሞራ ሲያንዣብብ ቆየና በከፍተኛ ጭካኔ መአተ እርግማኑን እንደ በረዶ ያዘንብባት ጀመር።
የመኩሪያ አደራ! ስትል የኖረች እናት ከሷ በፊት ትንሹ ልጇ እሷን ቀድሞ አባቱን ጠያቂ ይሆናል ብላ ለደቂቃ እንኳ አስባ አታውቅም ነበር። እንኳን ሞቱ ረጅም
እንቅልፉ የሚያስጨንቃት ልጅ ጉንፋን ስለመታመሙ ወሬ ሳትሰማ አስከሬኑን እንድትሸከም ሲፈረድባት ምን ይባላል? ያልፍልኛል ብሉ ደፋ ቀና ሲል ከርሞ በማእረግ የተመረቀላት ልጇን ደስታ አጣጥማ ሳትጨርስ ከጎኗ በድንገት ስታጣው የሚስማትን ስሜት ምን ቃላት ሊገልጡት ይችላሉ? ምናልባት በአስካለ ላይ የደረሰባትን ሰቆቃ ምሳ ቋጥሮ እቅፎ ስሞ ትምህርት ቤት የሸኘውን ህፃን ልጁን በመኪና አደጋ የተነጠቀ ወላጅ፣ ለወሊድ ሆስፒታል ይዟት የገባ ጤነኛ ሚስቱን አስከሬን በድንገት የታቀፈ አባወራ፣ በሠርጓ ዋዜማ እጮኛዋ በተኛበት አልጋ ላይ እስትንፋሱ ተቋርጣ ያገኘች ሙሽራ የበለጠ ሊረዷት ይችሉ ይሆናል። በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የተደረገለት ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ በሶስተኛ ቀኑ በዚያው በሆስፒታሉ ውስጥ እንዳለ ህይወቱ ያለፈው ልጇ አስከሬኑ
ተጭኖ መምጣቱና ከሷ ቀድሞ ከአባቱ መቃብር አጠገብ የቀብር ስርአቱ በህዝብ ፊት በአደባባይ ተፈፅሞ አፈር መልበሱ በገሃድ እየታየ ለደቂቃ እንኳ ሞቱን አምና መቀበል ተስኗት በድን ሆና ቀረች፡፡
በቀብሩ ዕለት የአማረችን አሳዛኝ የለቅሶ ዜማ፣ የእናቱን ሁኔታ፣ የእህቱን እሪታ ሰምቶ አንጀቱ ያልተርገፈገፈ፣በእንባ ያልተራጨ፣ በእዬዬ ጉሮሮው ያልተዘጋ አልነበረም፡፡ ለዚያ ምግባረ ሰናይ ልጅ፣ ላዚያ አመለ ሽጋ ልጅ፣ለዚያ ትህትናው ለተመሰከረለት ልጅ፣ ለዚያ ገና በለጋነቱ የአባቱን አደራ ሊወጣ የቤተሰብ ሃላፊነት ቀንበርን በጫንቃው ተሸክሞ
ሲጎትት ለኖረ ልጅ የማያለቅስ ማን አለ? ከእያንዳንዱ ሰው እንባ እንደ
ውሃ ተቀዳለት፡፡ የሰማይ አእዋፍ ጭምር ተንጫጩለት። አጅሬ ሞት አይረታ የበላውን አይመልስ ሆነ እንጂ....
በዚያን እለት በማህፀኗ የተሸከመችው የአራት ወር ፅንስ ትንሹ ጌትነት ከሆዷ ውስጥ ሆኖ እየረገጣት አማረች የሚከተለውን የሃዘን እንጉርጉሮዋን አሰማች...

ስንዴ ዘርቻለሁ ቡቃያው ያማረ፣
ዛላው ተንዠርጎ ተስፋን ያሳደረ።
ዘሮች ተበትነው በእፍኝ አፈር ላይ፣
ጎልቶ እንዲወጣ ምርጡ እንዲለይ፣
ተመራማሪዎች ተወራረዱና፣
ውጤቱን ለማወቅ አወጡ ፈተና።
እኩል እየበሉ እኩል እየጠጡ፣
አንደኛው ከሌላው ከተበላለጡ፣
ሊመርጡ ፈጣኑን ለልማት ሊያወጡ፣
ተስማሙ ባንድ ድምፅ ሽልማት ሊሰጡ፡፡
አያጠራጥርም ቡቃያዬ አደገ፣
ቀድሞ ለመበላት ለመድረስ ፈለገ፡፡
በከባድ ልዩነት ሁሉንም በለጠ፣
ተፈላጊነቱን በኩራት ገለጠ።
ታዲያ ምን ያደርጋል ሳይታይ ውጤቱ፣
ታጭዶና ተወቅቶ ሳይመዘን ምርቱ፣
አብቦ እንዳሽተ ፍሬ እንዳጋተ፣
ስሩ ተበጠስ ሞተ ተከተተ።
ቡቃያዬ እንጭጩ ቡቃያዬ ሆዴ፣
እጦማለሁ ብዬ ነይ ነይ ከሁዳዴ፣
ተስፋ ያደረግሁት ባንተ አይደለም እንዴ?
ጌትሽ ቡቃያዬ ጌትሽ ቀለበቴ፣
አጊጬ ሳልጠግብህ አድርጌህ ከጣቴ፣
ምነው ሾልከህ ጠፋህ ሆድዬ አንጀቴ?
ቃልህን አታጥፍም ብዬ ስኮራብህ፣
ሚስጥር ጠባቂ ነህ ብዬ ስመካብህ፣
አሳፈርከኝ ዛሬ አመኔታም የለህ፡፡
አይታችሁ ያጣችሁ እናንተ ፍረዱ፣
እምነትን ዘርታችሁ ክህደትን ስታጭዱ።
አበቃ ተስፋዬ ሞተ መነመነ፣
የመኖሬ ትርጉም ባዶ ቀፎ ሆነ፡፡
አልችለውምና ጧት ማታ እዬዬ፣
ክብርና ኩራቴ ጥላ ከለላዬ፣
አልቀርም ጠብቀኝ ጌትሽ እጮኛዬ።

የእናቱ የአስካለ ሁኔታ እንዲህ ነበር ተብሎ በቀላሉ የሚገለፅ አል
ሆነም፡፡ የሚያዩ ዐይኖቿ ታወሩ...
የሚሰሙ ጆሮዎቿ ደነቆሩ... የሚናገረው አንደበቷ ተዘጋ፡፡በዚያ በደካማ ሰውነቷ ላይ የወደቀባትን ክምር የስቃይ ሸክም መቋቋም ተስኗት አቅም አጣችና ራሷን ሳተች። ቀወሰች።
ሁለት ቀን ሙሉ ነፍሷ ሳትወጣ የሞተ በድኗ እየተጠበቀ ሳለ በሶስተኛው ቀን ላይ ማንም ሰው ሳያያት በእኩለ ለሊቱ ሹልክ ብላ ሮጣ ወጣችና በባሏና በልጇ መቃብር መካከል ወዲያና ወዲህ ስትንከላወስ ከቆየች በኋላ
የምትወደው ልጇን ተከትላ ባሏ አዘጋጅቶ ወደሚጠብቃቸው አዲስ ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አብራ ተቀላቀለች። አይ የሰው ነገር?!

ከደሙ ንፁህ መሆኑን ሳያውቅለት ለዘለዓለም አንደበቱ በመዘጋቱ የሸዋዬ ባል ቶሎሳ እንኳ“ሞት ሲያንሰው ነው” ሲል ነበር የፈረደበት።

#የመጨረሻው_መጨረሻ
#ሳኦልና_ጳውሎስ

ታደሰ በእውነቱ ከሆስፒታል እንዲወጣ ተደርጐ በመኖሪያ ቤቱ
ውስጥ አልጋ ላይ ከዋለ ልክ ሳምንቱ.. ለሰው ጥሩ መስራት ለራስ ነው። ታደሰን ለመጠየቅና ለማፅናናት በየጊዜው የሚመጣው ሰው ቁጥሩ
በርካታ ነው፡፡ በጠያቂ ብዛት መዳን ቢቻል ኖሮ ታደሰ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን በቻለ ነበር። ዛሬ ግን እያቃሰተ ህመሙን የሚያዳምጥበት ቀን አልነበረም፡፡ የምራቅ ዕጢዎቹ ማመንጨት አቁመዋል። ከንፈሮቹ ኩበት መስለው ደርቀዋል። ጥቁር መልኩ የጣፊያ ዓይነት መልክ
እየያዘ ሄደ...ወይዘሮ ወደሬ ማዕድ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ እያሉ ነበር።
ለጊዜው ሁለቱ ብቻ ነበሩ። ሰላማዊት የታደሰን ሁኔታ አጤነች፡፡ በየጊዜው እየሰለለች የመጣች ተስፋዋ ልትበጠስ መቃረቧን ተረዳች፡፡ ውድ ባሏ ሊለያት እንደሆነ ጠርጥራ ፍርሃት አደረባት።

“ታዴ! እየበረታህ ነው?” አልጋው ጠርዝ ላይ ቁጭ ብላ በግራ
መዳፏ ትኩሳቱን እየለካች ጠየቀችው፡፡
“እህ!.. እህ!.. እህ.! ሰላሜ..” ዐይኖቹን በዐይኖቿ ላይ አንከራተ
ታቸው።ከሆስፒታል የወጣው የመዳን ተስፋው እየመነመነ በመምጣቱ ምክንያት መሆኑን አውቆታል፡፡ሚስቱን እያፈቀረና እየወደዳት ብቸኛ አድርጓት ሊሄድ በአስገዳጁ የሞት ጠንካራ ክንድ ተጨምድዶ መያዙን ተገንዝቦታልና ሙሉ ለሙሉ እጁን ከመስጠቱ በፊት አደራ ሊላትና የልቡን ሊነግራት ወሰነ።
👍10
​​የለወጥኩትን፣ እውነተኛ ስሜን ዘይኑ መኩሪያነቴን ሳልነግርህ መቅረቴ ነው የኔ ፍቅር፡፡ እስቲ አባዬ ባወጣልኝ እማዬና ወንድም ጋሻዬ ይጠሩኝ በነበረ ስሜ ጥራኝ? ዘይንዬ በለኝ? ኣንድ ጊዜ ብቻ ዘይኑ በለኝ? እንደ አባዬ፣ እንደ እማዬ፣ እንደ ወንድም ጋሻ ታዴ አንተም እንደነሱ ልትከዳኝ ነውና እስከምትለየኝ ድረስ ዘይንዬ እያልክ ጥራኝ?” በደረቱ ላይ
ድፍት ብላ ተንሰቀሰቀሰች። ከመክሳታቸው የተነሳ እንደ ጭራሮ በቆሙ ጣቶቹ ሆዷን እየደባበሰ “ስላምዬ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ያልነገርኩሽ እውነተኛ ስሜን ነበር። አጋጣሚው ግን በጣም ያስደንቃል፡፡ ታደሰ በእውነቱ የቆሸሽ አእምሮዬ የታደሰበት፣ በፈፀምኩት ክፉ ድርጊት የተፀፀትኩበት የቀድሞ ማንነቴን ለመሸሸግ የተጠቀምኩበት የምወደው መጠሪያ ቢሆንም በእውነተኛ ስሜ ላይ የተጀቦነ መከናነቢያ እንጂ እውነተኛውን የልጄን አያት ማንነት የሚገልፅ አይደለም።ታደሰ በእውነቱ በተግባርና
በአስተሳሰብ መታደሴን የሚያሳይ የምወደው መጠሪያዬ ቢሆንም እውነተኛው የልጄ አያት ስም ግን ሌላ ነው። የልጄ ትክክለኛው የአያቱ ስም ሐጂ ቦሩ ነው፡፡ እውነተኛው እኔነቴም ጉንቻ ቦሩነቴ ነው.....
የገደለው ባልሽ፣
የሞተው ወንድምሽ፣
ሃዘንሽ ቅጥ አጣ፣
ከቤትሽ አልወጣ፡
እንበላት ይሆን?......
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
አሟሟቱ በበርካታ ጓደኞቹና የሥራ ባልደረቦቹ ልብ ውስጥ ጥልቅ
የሆነ ሀዘንን ተክሎ ላለፈው ተሸላሚ የተበረከተለትን የአበባ ጉንጉን በመካነ መቃብሩ ላይ ያኖረው አብሮ ተሸላሚው ታደሰ ገብረ ማርያም ነበር።

ተ ፈ ጸ መ


#የተወጋ_ልብ ይሄን ይመስላል ብዙ አስተያየት እንደሚኖራችሁ አምናለው ጥሩም ይሁን መጥፎ አስተያየት ወዲህ በሉ እስቲ እጠብቃለሁ።

ሌላው በቅርቡ #ምንትዋብ የሚል ታሪካዊ ልብ ወለድ የደራሲ ሕይወት ተፈራ ስራን ለማቅረብ አስቢያለሁ እዚም ላይ በቅድሚያ ያላችሁን አስተያየት ልወቅ አድርሱኝ አመሰግናለው

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍6