፩ ሃይማኖት
8.98K subscribers
246 photos
29 videos
21 files
96 links
ኦርቶዶክሳዊ ምላሾች
የሚቀርቡበት፡፡
👉"፩ ኃይማኖት"👈
@And_Haymanot
ቤተክርስቲያን ባህረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት
የገሀነም ደጆች አያናውጧትም
✞ እ...ና...ታ...ች...ን
#አ__ት__ታ__ደ__ስ__ም፡፡
@And_Haymanot
ኦርቶዶክስ መልስ አላት፡፡
ለአስተያየት
@And_Haymanot_bot

፩ ሃይማኖት ኤፌ 4፥5
Download Telegram
​​+++ ታቦትና ኢየሱስ ክርስቶስ +++

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታቦታት ላይ የተጻፈው ምንድር ነው? ተብለው ቢጠየቁ መልስዎ ምን ይሆን? ‹ዐሥርቱ ትእዛዛት ተጽፈዋል› ካሉ መልስዎ ትክክል አይደለም፡፡ እስኪ በመጀመርያ ጥቂት ነገሮች ስለ ታቦት እንመልከት፡፡
ብዙ ጊዜ ስለ ታቦት አስፈላጊነት በሚሠጡ ማብራሪያዎች ላይ ሰፊውን ቦታ የሚይዘው ስለ ብሉይ ኪዳን ታቦት የሚናገሩ ጥቅሶችን በመጥቀስ በመሆኑ ምክንያት ስለ ታቦት የሚነሡ ጥያቄዎች እንዳያቋርጡ ያደረገ ይመስላል፡፡ ስለዚህ በዚህች አጭር ጽሑፍ ‹ነገርን ከሥሩ› የሚለውን አካሔድ ሳንከተል በቀጥታ ስለ ሐዲስ ኪዳን ታቦት ብቻ እንመለከታለን፡፡
ስለ ታቦት በስፋት ከፈለጉም ይህን በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ
👉 ክፈት

ታቦት በሐዲስ ኪዳን ለምን ያስፈልጋል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጌታችን በመጨረሻዋ ምሽት ሐሙስ ምሥጢረ ቁርባንን ባስተማረ ጊዜ ያደረገውን እናስታውስ፡፡ ጌታችን ሐዋርያቱ በተሰበሰቡበት ‹‹እንጀራውን አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ሠጣቸው እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነ እንካችሁ ጠጡ ይህ ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው አለ›› (ማቴ. 26፡26) ጌታችን አስቀድሞ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› ብሎ በትምህርት የመሠረተውን ምሥጢረ ቁርባን በተግባር ለሐዋርያቱ በዚህ መልኩ አስተማራቸው፡፡ (ዮሐ. 6፡56) ሐዋርያቱም ከጌታችን ዕርገት በኋላ ወንጌልን እየሰበኩ ‹‹እንጀራውን በመቁረስ ይተጉ ነበር›› (ሐዋ.2፡42) ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ ሠጥቻችኋለሁ›› በማለት ሥጋ ወደሙን እንዴት መቀበል እንደሚገባና ‹ሳይገባው የሚቀበል የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ›› እንዳለበት በማስተማር የቁርባንን ሥርዓት ደነገገ፡፡ (1ቆሮ. 11፡23-30)

ልብ እንበል የክርስቶስ ሥጋና ደም መሠጠቱን የሚያምን አንድ ክርስቲያን ይህ የከበረ ሥጋና ደም እንደ ተራ ማዕድ በየቦታው ፣ በየጠረጴዛው ሊቀርብ ይችላል ብሎ ለማሰብ እጅግ ይከብደዋል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ስደትዋ እስካበቃበት ዘመን ድረስ በሒደት እየተሻሻለ በመጣ የቤተ መቅደስ ሥርዓት የሐዲስ ኪዳኑን መሥዋዕት በክብር ለመሠዋትና ለምእመናን ለማቀበል በቅታለች፡፡ የበግና የፍየል ደም ይሠዋ በነበረበት የኦሪት ዘመን እንኳን ለብቻው ትልቅ መሠዊያ ተዘጋጅቶ ፣ መሠዊያው ተቀድሶ ሰው በማይገባበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በክብር ተቀምጦ ነበር፡፡ በድንኳኒቱ ውስጥ የሚያገለግሉት አሮንና ልጆቹም የተለየ ልብስ ለብሰው የበጉን ደም በመሠዊያው ዙሪያ ባለው ቀርነ ምሥዋዕ (የመሠዊያ ቀንድ) ላይ እየቀቡ ሥርዓቱን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ለበግና ለፍየል መሥዋዕት ይህ ሁሉ ክብር ከተሠጠ እንደ በግ ስለ ሁላችን ኃጢአት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው የእግዚአብሔር በግ ፣ እንደ ሊቀ ካህናትነቱ እጁን በመስቀል ላይ ዘርግቶ የተሠዋውና ሥጋና ደሙን እንካችሁ ብሉ ብሎ የሠጠን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብበት መሠዊያ ምንኛ የከበረ ይሆን?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥጋ ወደሙ ‹መሠዊያ› የምትለው ታቦት በቅርጽም ፣ በአገልግሎትም ፣ በክብርም በኦሪት እግዚአብሔር ለሙሴ ከሠጠው ታቦት ጋር #አንድ_አይደለም፡፡ የቀደመው ታቦት በአራት ካህናት የሚያዝ በውስጡ ጽላት የሚቀመጥበት ሲሆን የአሁኑ ታቦት ግን የጽላት ቅርጽ ያለው ጽሌ (ሰሌዳ) ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሐዲስ ኪዳኑን ታቦት በሦስት ስያሜ ትጠራዋለች - የቃልኪዳኑ ታቦት ፣ ጽላት እና መሠዊያ ብላ፡፡ የቃልኪዳኑ ታቦት የሚባለው እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስላደረገው ስለ ቀድሞ ቃልኪዳን ሳይሆን ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› ተብሎ ስለተሠጠው እና ‹‹ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› ብሎ ጌታችን ስለ ሠጠን አዲሱ ኪዳን ነው፡፡ (ማቴ. 26፡26-30) የቃልኪዳኑ ታቦት የሚባለው በሥጋ ወደሙ ስለተሠጠን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ታቦት መባሉ ደግሞ እግዚአብሔር በረድኤት የሚያድርበት ፣ በሥጋ ወደሙ ደግሞ በአካል የሚገለጥበት ዙፋን ስለሆነ ነው፡፡

ጽላት (ሰሌዳ) የሚባለው ዐሠርቱ ትእዛዛት ተጽፈውበት አይደለም፡፡ የሕግ ሁሉ ፈጻሚ የሆነው የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› የሚለው የከበረ ስሙ በታቦቱ ላይ ስለተጻፈ ነው፡፡ (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን /ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ/ ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ /ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ/)

አንዳንድ ሰዎች ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታቦት ከኦሪቱ ጋር አይመሳሰልም!›› ብለው እንደ ትልቅ መከራከሪያ ሲያውጁ ማየት እጅግ ያስገርማል፡፡ አንዴ ‹ኦሪታዊት ነሽ› አንድ ጊዜ ደግሞ ‹‹ለምን እንደ ኦሪቱ አልሆንሽም›› ብሎ ንትርክ ግራ ያጋባል፡፡ የኦሪቱን ያልመሰለው አሁን ያለነው ሐዲስ ኪዳን ላይ ስለሆነና የታቦቱ አገልግሎት የተለየ ስለሆነ ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ ታቦ ት ከቀድሞው አንድ ታቦት ተለይቶ በቁጥር የበዛውም ለብዙዎች መድረስ ያለበት የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚፈተትበት መሠዊያ ስለሆነ ነው፡፡ መድኃኒት ቤት የሚበዛው መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሲበዙም አይደል? ታቦት የበዛው በታቦቱ የሚሠዋው መሥዋዕት ለብዙዎች ስለ ኃጢአት ይቅርታ የሚፈስሰውና ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻው ያለሱ ሕይወት የላችሁም የተባልነው ሥጋና ደሙ ለኃጢአት በሽተኞች ስለሚያስፈልገን ነው::

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ ‹‹የኦሪት ጽላት እግዚአብሔር በደመና ተከናንቦ ሙሴንና አሮንን የሚያነጋግርበት ለእስራኤል ብቻ በረድኤት የሚገለጥበት ዙፋን ነበር፡፡ ይህ ግን (የሐዲስ ኪዳኑ ታቦት) የአምላክ ሥጋና ደም የሚፈተትበት (ጌታችን) ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ እያለ ያመኑትን የሚጠራበት የምሕረት ምሥዋዕ (መሠዊያ) ነው፡፡ ክብርና ስግደትም የሚደረግለት ለዚህ ነው፡፡›› (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 109) ሌላው አስገራሚ ነገር አቡነ ጎርጎርዮስ በታቦት ሥርዓት ከግሪኮች አንዲሚስዮን ጋር እንደምንመሳሰል ጠቅሰው ሲጽፉ ግሪኮቹ ደግሞ ስለ አንዲሚስዮን ሲያብራሩ ከኢትዮጵያ ታቦት ጋር የሚመሳሰል ብለው መጻፋቸው ነው።

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በታቦታቱ ሁሉ ላይ የተጻፈው ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› የሚለው የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ስም ነው፡፡ ከስሙ ጋር ደግሞ በሁሉም ታቦታት ላይ የሚከተለው ጥቅስ በግእዝ ተጽፎአል፡፡ ‹‹ከመ ለስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይስግድ ኲሉ ብርክ ዘበሰማያት ወዘበምድር›› ‹‹ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ›› የሚል ነው፡፡ (ፊልጵ. 2፡10) በታቦቱ ፊት የሚሰግድ ሰው ለምን እንደሚሰግድ በታቦቱ ላይ የሚጻፈው ይህ ጥቅስ ያስረዳናል፡፡ ምክንያቱ ‹‹ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይሰግዱ ዘንድ›› ስለሚገባ ነው፡፡ የክርስቶስ ሥጋ እንደሚቆረስ ደሙ እንደሚፈስስ የሚያምን ሰው በዚህ መሠዊያ ፊት በፍርሃት ለክርስቶስ ይሰግዳል፡፡ ሥጋ ወደሙን ‹‹ተራ መታሰቢያ ብቻ ነው›› የሚል ሰው ግን በመሠዊያው ፊት እንዲሰግድና መሠዊያውን እንዲያከብር አንጠብቅም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በታቦቷ ጽፋ ክብር የምትሠጥ የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ልጆች ስለሆንን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
ታቦት 1
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥጋ ወደሙ ‹መሠዊያ› የምትለው ታቦት በቅርጽም ፣ በአገልግሎትም ፣ በክብርም በኦሪት እግዚአብሔር ለሙሴ ከሠጠው ታቦት ጋር
#አንድ_አይደለም፡፡
📌📌📌📌📌 ይቀጥላል
@And_Haymanot
@And_Haymanot_bot