ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
መስከረም 4 ቀን 2010ዓ.ም
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐራት በዚህች ቀን ቅዱስ አባት የእስክንድርያው
ሊቀ ጳጳሳት #አባ_መቃርስ ዐረፈ፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቀነ
ጳጳሳት ከቁጥራቸው ውስጥ ነው፡፡
ይህም አባት ከታናሽነቱ ጀምሮ በገድል የተጠመደ ሆነ፣
የምንኩስናንም ልብስ ሊለብስ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጣ፡፡
በዚያም በመጀመሪያው አባት በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን
ውስጥ መነኮሰ፣ በምንኩስና ያለውን ታላቅ ተጋድሎን
ተጋደለ፡፡
እርሱም ሁልጊዜ መጻሕፍትን የሚያነብና ትርጓሜያቸውንም
የሚያስረዳ ሁኗልና፣ በትሩፋት ሥራ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ቅስና
ተሾመ፡፡
ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል በዐረፈ ጊዜ
ኤጲስ ቆጶሳቱ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዱ፡፡ ከእርሳቸውም
ጋር ሃይማታቸው የቀና ብዙዎች አዋቂዎች ካህናት ነበሩ፣
በአስቄጥስ ገዳም ከሚኖሩ ከታላላቅ መነኮሳትም ጋራ
ስብሰባ አድርገው ለዚች ለከበረች ሹመት ስለሚገባው ሰው
እየመረመሩ ብዙ ቀኖች ተቀመጡ፡፡
ከዚህም በኋላ የተሻለና ለዚች ለከበረች ሹመት የሚገባ
ይህን አባ መቃርስን አግኝተው ሊቀ ጵጵስና ሊሾሙት ሁሉም
በአንድ ምክር ተስማሙ፡፡ ስለ ትሩፋቱና ስለተጋድሎው
በአስቄጥስ ገዳም የሚኖሩ መነኮሳት ምስክሮች ሆነዋልና
ይዘውትም ሊሔዱ ያለ ፈቃዱ ይዘው አሰሩት፣ እርሱ ግን
እንዲህ እያለ ይጮህ ነበር፡፡ እኔ ለዚች ለከበረች ሹመት
የማልገባ ሰው ነኝ፣ እናቴ ሁለት ባሎችን አግብታ ስለነበር፣
ይህንንም ያለው እንዲተዉት እንጂ እናቱ ግን በአንድ ባል ብቻ
የኖረች ሌላ የማታውቅ ንጽሕት እንደሆነች ስለእርሷ ብዙዎች
ምሥክሮች ሆነዋልና፡፡ ስለዚህ እርሱ የተናገረውን ምክንያት
አልተቀበሉትም፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፣
ከዚያም ወደ ምስር አውጥተው በመዓልቃ በሚገኘው
አምላክን በወለደች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሹመት ደብዳቤ በዮናኒ በቅብጥ
በአረብ ቋንቋ ተነበበች፡፡
ከዚህም በኋላ በሹመቱ ወራት በጎ ሥራ ትሩፋትን
ተጋድሎውን አብዝቶ የሚሠራ ሆነ፡፡ ሁልጊዜም ለሕዝቡ
እግዚአብሔርን እንዲፈሩ ያስተምራቸዋል፣ ስለ ነፍሳቸውም
ድኅንነት ይገሥጻቸው ነበር፡፡
በሹመቱ ወራትም ከራሱ ከሚገባው ከግብሩ ለቤተ ክርስቲያን
ይሰጣል ለድኆችና ለችግረኞችም ይመጸውታል እንጂ ከቤተ
ክርስቲያን ገንዘብ ምንም ምን አልወሰደም፡፡
በሹመቱም ሃያ ሰባት ዓመት ኖረ፣ እግዚአብሔርንም አገልግሎ
ደስ አሰኝቶ በሰላም በፍቅር ሳለ ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በዚህ አባት ጸሎት
ይማረን፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
በዚህችም ቀን ለነዌ ልጅ ለኢያሱ መታሰቢያው ነው፣ ደግሞ
በአንጾኪያ በሰማዕትነት የሞቱ የሁለት መቶ ሰዎች
መታሰቢያቸው ነው፡፡ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር
ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
💚💛 #አባ_መቃርስ_ካልዕ 💛❤️
@senkesar
ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል:: ትርጉሙ በ3ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም
ሥርወ ቃሉ በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና::

ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-2ኛው": አንዳንዴ ደግሞ "እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-2ኛው" የሚባለው ከቀዳሚው (ታላቁ መቃርስ) ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት::

አባ መቃርስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ: ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ40 ዓመት ሲኖር
እንደ ሕጉ ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና
ይህቺን ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል::

እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ: በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው ፈጣሪ አከበረው:: በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ ምኔት ሊሆን መረጡት::

እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን (መነኮሳትን) ከተኩላ (ሰይጣናት) ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ
የተነሳም ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ 40 ቀን ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ
ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር::

እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው
ብዛት የተነሳ ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል::

አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው:: አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን
ሆነው አገኛቸው:: እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ
ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል::

ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ ሰጥታዋለች:: (ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን
አይረሱምና) ቅዱስ መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት (አፈር) ላይ ይተኛ የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል::

በሃገሩ እስክንድርያም ለ2 ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት:: እርሱ መጥቶ
ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ ማቆም ለ2 ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ
ኃጢአታችን እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ (በፈጣሪው ኃይል) እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል::

የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው ስለሚገርመኝም
ነው::

ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ
ቦታን ( አጋጣሚን) ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም
እንደ ተርታ ነገር (ያለ ጥንቃቄ) ስንቀበል ይታያል:: 2ቱም ግን ስሕተት ነው::

ፈርተን (ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም) ስለ ራቅን በፍርድ ቀን ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ
የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: (ዮሐ. 6:52)

በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን: ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል::
"ሳይገባው ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት" ይለናልና:: (1ቆሮ. 11:27)

👉 ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት ሆኖ መቅረቡ ነው::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን
እያሰበ ለ60 ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት::

ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ:-
"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ::
አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ::
መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ::
ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ::
መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል::

ቅዱስ መቃርስም በ100 ዓመቱ በ5ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::

❖ጌታችን ከክብሩ: ከበረከቱ አይለየን::
From:- dnyordanos abebe
@senkesar