ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
💚💛 #አባ_መቃርስ_ካልዕ 💛❤️
@senkesar
ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል:: ትርጉሙ በ3ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም
ሥርወ ቃሉ በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና::

ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-2ኛው": አንዳንዴ ደግሞ "እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-2ኛው" የሚባለው ከቀዳሚው (ታላቁ መቃርስ) ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት::

አባ መቃርስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ: ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ40 ዓመት ሲኖር
እንደ ሕጉ ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና
ይህቺን ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል::

እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ: በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው ፈጣሪ አከበረው:: በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ ምኔት ሊሆን መረጡት::

እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን (መነኮሳትን) ከተኩላ (ሰይጣናት) ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ
የተነሳም ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ 40 ቀን ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ
ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር::

እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው
ብዛት የተነሳ ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል::

አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው:: አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን
ሆነው አገኛቸው:: እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ
ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል::

ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ ሰጥታዋለች:: (ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን
አይረሱምና) ቅዱስ መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት (አፈር) ላይ ይተኛ የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል::

በሃገሩ እስክንድርያም ለ2 ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት:: እርሱ መጥቶ
ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ ማቆም ለ2 ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ
ኃጢአታችን እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ (በፈጣሪው ኃይል) እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል::

የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው ስለሚገርመኝም
ነው::

ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ
ቦታን ( አጋጣሚን) ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም
እንደ ተርታ ነገር (ያለ ጥንቃቄ) ስንቀበል ይታያል:: 2ቱም ግን ስሕተት ነው::

ፈርተን (ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም) ስለ ራቅን በፍርድ ቀን ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ
የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: (ዮሐ. 6:52)

በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን: ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል::
"ሳይገባው ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት" ይለናልና:: (1ቆሮ. 11:27)

👉 ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት ሆኖ መቅረቡ ነው::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን
እያሰበ ለ60 ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት::

ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ:-
"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ::
አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ::
መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ::
ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ::
መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል::

ቅዱስ መቃርስም በ100 ዓመቱ በ5ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::

❖ጌታችን ከክብሩ: ከበረከቱ አይለየን::
From:- dnyordanos abebe
@senkesar