የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውስንል ECGBC
9.69K subscribers
9.36K photos
132 videos
1 file
1.55K links
ይህ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውስንል የቴሌግራም ቻናል ነው።

"ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ፤ እነሆ፤ መልካም ነው፤ እነሆም፤ ያማረ ነው።
Download Telegram
#አስቸኳይ_መግለጫ
#እግዚአብሄር_ላዘኑት_ሁሉ_መጽናናትን_ያብዛልን

በመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ላይ የደረሰው የጎርፍ አደጋ አስመልክቶ፤ ከኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ።

በካውንስሉ ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ አማካኝነት በተሰጠው መግለጫ

የመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ለረጅም አመታት ከቤተክርስቲያኒቷ አልፎ በአጠቃላይ ለወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ተቋም ነው። ብዙዎች ያደጉበት እና አሁንም በመንፈሳዊ፤ በአመራር እና በሁሉም ዙሪያ ላይ እየሰለጠኑ ያሉበት ተቋም ነው።

የመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ለቤተክርስቲያን ጤናማ የወንጌል አገልግሎት መሰረት የሆነ እና ትልቅ አስተዋጾ እያደረገ ያለ የሁላችንም ተቋም እንደሆነ ግልጽ ነው።
በውስጡም የሴሚናሪ ቤተሰቦችን ማለትም አስተማሪዎች፤ ተማሪዎች የያዘ ግቢ ነው።

ሆኖም የዛሬ ሳምንት ነሃሴ 11/2013ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ገደማ በረዶ ቀላቅሎ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ በተፈጠረው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ በተቋሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከንብረትም በላይ የስምንይ ወንድም እና እህቶቻችን እንዲሁም ልጆቻችንን ህይወት ቀጥፏል።

ይህ አደጋ የብዙዎችን ልብ የሰበረ፤ የሰው ህይወት የቀጠፈ፤ በርካታ ንብረቶችን ያወደመ በመሆኑ በቦታው ተገኝተንም ጭምሮ ሀዘናችንን ስንገልጽ ቆይተናል።

በአሁኑ ሰዓት በጎርፉ አደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ ቅዱሳንን እንደገና ማቋቋም የቤተክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ድርሻ ነው ብሎ ካውንስሉ ያምናል።
እናም በዚህ ወቅት ከመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ አገልጋዮች እና በአጠቃላይ ከመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና መሪዎች ጋር ከጎናቸው በመሰለፍ ፍቅራችንን እና አንድነታችንን ይበልጥ የምንገልጽበት እንደሚሆን እናምናለን።

ስለዚህ የካውንስሉ አባል አብያተክርስቲያናት እና ምዕመናን በአቅማችሁ ልክ፤ የምትችሉትን ሁሉ በማድረግ እንድታግዟቸው ጥሪ እናቀርባለን።

ካውንስሉ ከተቋቋመበት አላማ አንዱ የአንዱ ደስታ ለሌላው እንዲሆን የአንዱ ሀዘንም የሌላው እንዲሆን ነው እና አብረን በሁሉም ሁኔታ ውስጥ እንድንቆም፤ እንድንደጋገፍ ስለሆነ በዚህ ወቅት ከቤተክርስቲያኒቱ እና ከመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ጋር ተሰልፈን የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ለአብያተ ክርስቲያናት አደራ እንላለን።

በሌላ በኩል የአዲስ አበበ ከተማ መስተዳደር አደጋው ከተፈጠረበት ሰዓት ጀመሮ በቦታው በመገኘት አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ እና የገንዘብም ድጋፍ በመስጠት ከቤተክርስቲያኒቱ ጎን በመቆሙ እጅግ ደስ ብሎናል። የሃገር መሪዎች በችግር ጊዜ ከህዝባቸው ጋር ሲቆሙ ማየት የሚበረታታ ነው። ስለሆነም በካውንስሉ ስም ለከተማ መስተዳደሩ የላቀ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

ምዕመናን የተጎጂ ቤተሰቦች ይጽናኑ ዘንድ በጸሎታችሁ እንድታስቡዋቸው በድጋሜ እንጠይቃለን። እግዚያብሄር ላዘኑት ሁሉ መጽናናትን ያብዛልን። ሀገራችንንም በሰላሙ፤ በቸርነቱ እና በበረከቱ ይጎብኝ። አሜን!!!

ቄስ ደረጀ ጀምበሩ
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ