Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
534 photos
45 videos
1 file
841 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
+++ ከፊልጶስ ቂሣሪያ እስከ ታቦር ተራራ +++

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ የደብረ ታቦርን መገለጥ በጻፈበት በአሥራ ሰባተኛው ምዕራፍ ላይ ሲጀምር ‹ከስድስት ቀንም በኋላ› በማለት ሲሆን፣ የቅዱስ ማርቆስም ቀን አቆጣጠሩ ከማቴዎስ ጋር ተመሳሳይ ስድስት ቀን ነው፡፡(ማቴ 17፡1 ፣ማር 9፡2) ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ጌታና ሐዋርያቱ ታላቁን የታቦር ተራራ ሲወጡ የወሰደባቸውን ሁለት ቀን ጨምሮ ይህንኑ ተመሳሳይ ታሪክ ሲመዘግብ ‹ስምንት ቀን ያህል ቆይቶ› በማለት ይጀምራል፡፡ በእነዚህ በሦስቱ ወንጌላት ላይ የተቀመጡት የቀናት ቁጥር ከደብረ ታቦር ጋር ተያይዘው ሊታወሱ የሚገባቸው መነሻ ሐሳቦች እንዳሉና ሐዋርያት በታቦር ተራራ ከቀናት በፊት የነበረባቸው ጥያቄ እንደ ተመለሰላቸው አመላካች ናቸው፡፡ እኒህ የደብረ ታቦር ቅድመ ታሪኮች ምን ምን ናቸው?

.አንደኛ

በደብረ ታቦር ከተፈጸመው ታሪክ ጋር ተያያዥነት ያለውን ጉዳይ ለማወቅ ከእርሱ በፊት አምላካችን የሄሮድስ ወንድም የፊልጶስ ግዛት በሆነችውና ለንጉሥ ጢባርዮስ ቄሣር ለክብሩ መታሰቢያ በስሙ ቂሣርያ ተብላ በተሰየመችው ቦታ ከሐዋርያቱ ጋር ያደረገውን ንግግር ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡(ማቴ 16:13)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን አምላክነቱን የሚያረጋግጥ ምልክትን ከሰማይ እንዲያሳያቸው ለምነውት ነበር፡፡ እርሱ ግን የልባቸውን ክፋትና አመዝረኛነት ነቅፎ ምልክት ሆኖ ከተሰጠውና የእርሱ ምሳሌ ከሆነው ከዮናስ በዓሣ አንበሬ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ማደር በቀር አንዳች ምልክትን ከለከላቸው፡፡ ሐዋርያቱም እንዲህ ካለው ተአምርን ከመከተል ፈሪሳዊ፣ ሰዱቃዊ ትምህርት ራሳቸውን ይጠብቁ ዘንድ ‹ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ› ብሎ አስተማራቸው፡፡(ማቴ 16፡6) ቀጥሎም ወደ ፊሊጶስ ቂሣርያ አገር በደረሱ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ ጌታ ለምን ሐዋርያቱ በፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን መካከል እያሉ አልጠየቃቸውም? ቢባል ጥያቄው የክርስቶስን ማንነት የሚመለከት በመሆኑ እውነተኛውን መልስ በግልጽ ቢናገሩ የሚደርስባቸውን ውግራት በማሰብ ገና ያልጸኑት ሐዋርያት በነጻነት አይመሰክሩምና ከዚህ ሥጋት ነጻ ሊያደርጋቸው ወደ ፊሊጶስ ቂሣርያ ይዟቸው ዞር አለ፡፡

ስለ እርሱም ሰዎች ምን እንደሚያስቡ ጥያቄን ሊጠይቃቸው በወደደ ጊዜ ‹አምላክ ስለሆንኩት፣ ጌታ ስለሆንኩት ስለ እኔ› የሚሉ ኃይልና ሥልጣንን የሚገልጹ ቃላቶችን በማስቀደም አልጠየቃቸውም። ራሱን ዝቅ በማድረግና በማያስደነግጥ ቃል ‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?› ሲል በትሕትና ጠየቃቸው እንጂ፡፡ ኃይሉንና ጌትነቱን በሚገልጽ ቃል ቢጠይቃቸው ኖሮ ‹እንደ ነቢይ ፣እንደ አንድ ጻድቅ ሰው ይመለከቱሃል› የሚለውን በሕዝቡ ዘንድ ያለውን አመለካከት ለመንገር ሐዋርያቱ በተሰቀቁ ነበር፡፡

ይህ ለተማሪዎቹ ሐዋርያት የቀረበው "ሰዎች ስለ እኔ ምን ይላሉ?" የሚለው የአምላካችን ጥያቄ ዛሬ ለእኛም ቢሆን ሁለት ቁም ነገሮችን ያስተላልፍልናል፡፡ የመጀመሪያው ብዙዎች በውጪ ስለሚያደርጉት አጉል ምግባር ‹ተዉ ሰዎች ይሰናከሉባችኋል!› የሚል አስተያየት ሲሰጣቸው፣ "እኔ ሰለ ሰዎች ምን ቸገረኝ፣ ‹ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን›" ብለው ለሚከራከሩ፣ አይደለም በኃጢአት ባሕር የምንዋኝ እኛ ቀርቶ በውስጥም በውጪም ነውር የሌለበት አምላክ እንኳን የሰዎችን አስተያየት ጠይቋል። ስለዚህ ስለ ሰዎች ስሜት መጨነቅና ኃላፊነት መሰማትን ከእርሱ እንማራለን፡፡ ሁለተኛው ቁም ነገር ደግሞ ስለ ራሱ በሰዎች ዘንድ የሚሰጠውን ትክክለኛ አስተያየት መስማት የሚፈልግ ሰው ጥያቄውን ቀላልና ሥልጣንን በማይገልጽ መንገድ እንዴት ለአስተያየት የማይቆረቁር አድርጎ ማቅረብ እንዳለበት ይህ ታሪክ ትምህርት ይሰጣል፡፡

ከጌታችን ጥያቄ የቀረበላቸው ሐዋርያቱም በሕዝቡ ዘንድ ሲነገር የሰሙትን አስተያየት ተራ በተራ ወደ እርሱ ሰነዘሩ፡፡ እነርሱም:- የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት አታገባም እያለ ይወቅሰው የነበረን መጥምቁ ዮሐንስን ንጉሥ ሄሮድስ ይፈራው ነበረና፣ ከሞተ በኋላ እንኳን የመጥምቁ ዮሐንስ ጌታ ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማ ጊዜ ዮሐንስ ከሞት የተነሣ እየመሰለው ይታወክ ነበር፡፡ ስለዚህም ሄሮድስና በእርሱ ወገን ያሉት አንዳንዶች "መጥምቁ ዮሐንስ ነህ ይሉሃል" አሉት፡፡ በሮማውያን ግዞት የነበሩም አይሁድ በኃይል እሳት አዝንሞ፣ ሰማይ ለጉሞ ጠላቶቻችንን በማስጨነቅ ነጻ ያወጣናል ብለው በማሰብ "ኤልያስ ነህ" የሚሉም አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ንጽሕናህን የተመለከቱ ከእናቱ ሆድ ጀምሮ በእግዚአብሔር የተመረጠ "ኤርምያስ ይሆንን" ይላሉ፡፡ የቀሩትም ደግሞ ‹ከነቢያት አንዱ (ሙሴ) ነህ› ይላሉ በማለት ነገሩት፡፡

በመቀጠልም መድኃኒታችን እነርሱ ማን እንደሚሉት ‹እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንኹ ትላላችሁ?› በማለት ጠየቃቸው፡፡ ከሐዋርያት መካከል ፈጣን የነበረው አረጋዊው ስምዖን ጴጥሮስም ‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ› ሲል መለሰ፡፡ ጌታችንም መልሶ ‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ› በማለት አመሰገነው፡፡

ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት በእውነትም በሥጋ በደም ዕውቀት የተነገረ አይደለም፡፡ ፀሐይን ትኩር ብለን መመልከት ቢሳነን እንኳን የምንችለውን ያህልም ቢሆን የምናያት ራሷ በምትለግሰን ብርሃን እንደሆነ ሁሉ፣ እግዚአብሔርንም በምልዐት ማወቅ ባይቻለንም ስለ እርሱ የምናውቃት ጥቂት ነገርንም ያገኘነው እርሱ ራሱ ወዶ ባደረገልን "የራስ መገለጥ" (Self Revelation) ብቻ ነው፡፡ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም "ይህን እንዴት ዐወቅህ?" ተብሎ ቢጠየቅ ‹እግዚአብሔር አብና መንፈሱ ገልጦ ካሳወቀኝ በቀር ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርኩም ነበር› ብሎ የሚመልስ ይመስላል፡፡(ገላ 1፡16) በእርግጥም ስለ ወልድ ለማወቅ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ በላይ መምህር ከየት ሊገኝ ይችላል?

ታስታውሱ እንደሆነ በዮሐንስ ወንጌል ናትናኤል የተባለ ሰው ጌታን ‹ከወዴት ታውቀኛለህ?› ብሎ በጠየቀው ጊዜ፣ ‹ፊሊጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ› ብሎ የቀድሞ ድብቅ ታሪኩን ነግሮት ነበር፡፡ በዚህም የተደነቀው ናትናኤል ‹መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ› ሲል መስክሮለታል፡፡(ዮሐ 1፡50) በናትናኤልና በቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት መካከል ምን ልዩነት አለው? ሁለቱም እኮ ‹የእግዚአብሔር ልጅ ነህ› ብለው ነው የመሰከሩት፡፡ ታዲያ ለምን ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተመሰገነው ናትናኤልም አልተመሰገነም? ከተባለ ምንም የሁለቱም ምስክርነት በቃል ደረጃ ይመሳሰል እንጂ ውስጣቸው የነበረው ትርጉም ግን ይለያይ ነበር፡፡ ናትናኤል ‹የእግዚአብሔር ልጅ› ሲለው በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ከተባሉት ነቢያትና የብሉይ ኪዳን ጻድቃን ጋር በማመሳሰል ሲሆን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ‹የእግዚአብሔር ልጅ› ያለው ቀዳሚና ተከታይ የሌለው የአብ አንድያ የባሕርይ ልጅ መሆኑን በመረዳት ነው፡፡ ስለዚህ የሚበልጠው አምላክነቱን ያየ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲመሰገን፣ እምነቱ ገና ሙሉ ያልሆነው ናትናኤል ግን ‹የሚበልጠውን ታያለህ› ተብሎ ተስፋ ተሰጠው፡፡ አያችሁ! እግዚአብሔር የቃል መመሳሰልን ሳይሆን በልባችን ውስጥ ያለውንም የቃሉን ትርጉም አይቶ ነው የሚለየን!፡፡

ይህም የቅዱስ ጴጥሮስ የእምነት ምስክርነት ዓለት ሲሆን በዚህችም ዓለት (እምነት) ላይ ቤተ ክርስቲያን የተባሉ ምእመናን በጥምቀት እንደሚታነጹ ጌታችን ተናግሯል፡፡ በርግጥም
ስ ክርስቶስን ‹እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም› ብሎ የተናገረው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ የማያምን ሁሉ ከተመሰገነች ከቅዱስ ጴጥሮስ እምነት የወጣ ነው፡፡

አረጋዊው ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን የማወቅ ጥበብ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ እንዳገኘ፣ እንዲሁ የማሰርና የመፍታት ሥልጣንን ከጌታችን ተቀበለ፡፡በዚህም ሰው የሆነ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ብቻ ገንዘብ የሆነውንና ማንም የማይፈታውን የኃጢአትን ማሰሪያ ይፈታና ያስር ዘንድ ሥልጣንን ለሐዋርያው ሰጥቶ "የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር" መሆኑን በመግለጥ እምነቱን አጸናለት፡፡

‹ሰዎች_የሰውን_ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?› በሚለው ንግግር ውስጥ የወልድን ፍጹም ሰው መሆን ስንረዳ፣ ‹አንተ ክርስቶስ የሕያው_እግዚአብሔር_ልጅ ነህ› በሚለው የቅዱስ ጴጥሮስ መልስ ደግሞ አምላክነቱን እናያለን፡፡ ታዲያ ምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ባጭሩ ይህ አይደለምን?! የሂፖው ሊቀ ጳጳስ አውግስጢኖስ "የእምነት ሽልማቱ ያመኑትን ነገር ማየት ነው" እንዲል ይህ ቅዱስ ጴጥሮስ አምኖ የመሰከረውን አምላክነት በዓይኑ ደግሞ የሚያየው በታቦር ተራራ ነበር፡፡
+++++++++++++++++++++++++++++++

.ሁለተኛ

ጌታችን በፊሊጶስ ቂሣርያ ይህን ጥያቄ ከጠየቀበት ቀን ጀምሮ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይሞት ዘንድ እንዳለው፣ በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ ለሐዋርያቱ ያስተምራቸው ነበር፡፡ እሞታለሁ ማለቱም ያሳሰበው ቅዱስ ጴጥሮስ አምላኩን ወደ እርሱ አቅርቦ ‹አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም› ሲል በመራራት ቃል ሊገስጽ ጀመረ፡፡ ጌታ ግን የቅዱስ ጴጥሮስን ፍቅሩን ተጠቅሞ ዓለም የሚድንበትን ሞቱን የሚቃወመውን ርኩስ መንፈስ በሚጠቁም ኃይለ ቃል ‹ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና እንቅፋት ሆነህብኛል› በማለት በረቂቅ ያናገረውን የጠላት መንፈስ አራቀለት፡፡ ይሁን እንጂ ‹አይሁንብህ!› የሚለው የቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር ግን በዚህ የአምላካችን ተግሳጽ ብቻ የሚያቆም ባለመሆኑ ይህን ጥፋቱን ለማረም ከፊቱ የታቦር ተራራ ትምህርት ቤቱ ፣ እግዚአብሔር አብም መምህሩ ሆነው ይጠብቁት ነበር፡፡

+++++++++++++++++++++++++++++++

👌.ሦስተኛ

በዚያው ሰሞን ጌታችን ከሐዋርያት መካከል እርሱ ዳግመኛ ለፍርድ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ እንዳሉ (ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ አልሞተም) ቢያስተምራቸውም፣ በሐዋርያቱ ኅሊና ግን ‹ሞትን ሳይቀምሱ ለዘመናት መሰንበት እንዴት ይቻላል?› የሚል ጥያቄ ተፈጥሮ ነበር። ስለዚህም ይህን ጥያቄ በጠየቁ በስድስተኛው ቀን ሞትን ያልቀመሰ ኤልያስን በማየት መልሱን ያገኙ ዘንድ ወደ ታቦር ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡

+++++++++++++++++++++++++++++

ስለ ደብረ ታቦር ታሪክ ከአራቱ ወንጌላት መካከል በሉቃስ፣ በማቴዎስና በማርቆስ ወንጌል ተጽፎ የምናገኘው ሲሆን፣ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ግን በፊሊጶስ ቂሣርያ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ መሰከረና በጌታው እንደተመሰገነ ብቻ ነው የተጻፈው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የታቦር ተራራ ላይ የተፈጸመውን ታሪክ ሳይመዘግብ አልፎታል። ይህም ያለ ምክንያት የሆነ እንዳይመስለን። በዚህ የወንጌላውያኑ ተግባር ውስጥ የምንፈናየው የትሕትና ትምህርት አለ፡፡ ይኸውም በደብረ ታቦር ተራራ ከጌታችን ጋር ለመውጣት የተመረጡት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ እና ያዕቆብ ቢሆኑም እነዚህ ሦስቱ በተራራው ላይ ያልነበሩ የወንጌል ጸሐፊዎች ግን እኛ ያልተጠራንበትን፣ እኛ ያልተመረጥንበትንማ እንዴት እንጽፈዋለን በማለት በምቀኝነት መንፈስ የሐዋርያቱን ክብር አልሸፈኑም፡፡ ደግሞ ወደ ተራራው ከወጡ ከሦስቱ ሐዋርያት አንዱ የነበረውም ቅዱስ ዮሐንስ፣ ከነበረው የትሕትና ሕይወት የተነሣ ‹እኔ ነበርኩ› ብሎ መጻፍን እንደሚገባ ነገር ስላልቆጠረው የወንድሙ የቅዱስ ጴጥሮስን ምስክርነትና ስለ እምነቱ መመስገን ሲጽፍ፣ እርሱ የተመረጠበትን የደብረ ታቦርን ታሪክ ግን ሳይጽፍ ቀርቷል፡፡ በአገልጋዮች ሐዋርያት መካከል ያለውን የትሕትና እና የገርነት መንፈስ ተመለከታችሁ?!

ጌታችን ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ‹አዕማድ መስለው የሚታዩ›ና ለፍቅሩ የሚናደዱ ሦስቱን የምሥጢር ሐዋርያት ጴጥሮስ ፣ያዕቆብና ዮሐንስን መረጣቸው፡፡(ገላ 2፡9) የቀሩት ስምንቱን ግን ከእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቷቸው ወጣ፡፡ ይህንንም ማድረጉ ‹የአትትዎ ለኃጥእ ከመ ኢይርዓይ ስብሐተ እግዚአብሔር›/‹ኃጢአተኛን የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ያርቁታል› እንዲል፣ ከመካከላቸው የእግዚአብሔርን ክብር ሊያይ የማይገባው ኃጢአተኛው ይሁዳ ስለ ነበር ነው፡፡ ነገር ግን ሃብተ ትርጓሜን እንደ ሸማ የተጎናጸፉት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንደሚነግሩን ከይሁዳ በቀር ለቀሩት ሐዋርያት ወደ ተራራ መውጣት እንጂ በተራራው ጫፍ ለነበሩት ሦስቱ ሐዋርያት የተገለጠላቸው ምሥጢር አልጎደለባቸውም፡፡

ወደ ረጅሙ ተራራ ወደ ታቦር ጌታ ሦስቱን ሐዋርያት ይዟቸው ከወጣ በኋላ እያዩት በፊታቸው ተለወጠ። ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ፣ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡ አበቦች ከቅርንጮፎቻቸው ላይ ተሸፍነው (ተጠቅለው) ኖረው ኖረው በኋላ እንዲገለጡ፣ አምላካችንም ቀድሞ በእርሱ ዘንድ ሰውሮት የነበረውን ክብር ገለጠላቸው፡፡ ሐዋርያቱም ያዩት ክብር ከዚያ በፊት ያልነበረው አሁን እንግዳ ሆኖ የመጣ ብርሃን አልነበረም፡፡ ይህንንም ክብሩን ሲገልጥላቸው ሐዋርያት ሊያዩትና ሊረዱት በሚችሉት መጠን እንደ ነበረ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹በፊታቸው ተለወጠ› በምትል አጭር ገላጭ ቃል ያስረዳናል፡፡ ለቅዱሳን ብርሃን የሚሆን ‹የጽድቅ ፀሐይ› አምላካችን ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፡፡(ሚል 4፡2) ኸረ እንደውም የፊቱስ ብርሃን ከፀሐይም ይበልጥ ነበር፡፡ ምክንያቱም እኛ ጠዋት ጠዋት ከቤታችን ስንወጣ የፀሐይን ብርሃን ባየን ቁጥር በግንባራችን አንደፋም፤ ሐዋርያት ግን ከፀሐይ ሰባት እጥፍ የሚያበራ የክርስቶስን ፊት ባዩ ጊዜ በግንባራቸው ተደፍተዋል፡፡

የለበሰውም ልብስ አጣቢ በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ፡፡ ይህ የአምላካችን አንጸባራቂው ልብስ ምሳሌና ምሥጢሩ ምን ይሆን? ሊቁ ጎርጎርዮስ ዘየዐቢ ከበረዶ ይልቅ የነጣውን የክርስቶስን ልብስ በምዕመናን መስሎ ያስተምራል፡፡ ኢትዮጽያውያን ሊቃውንትስ ቢሆኑ ‹አልባሲሁሰ ለክርስቶስ መሃይምናን ውእቱ›/‹የክርስቶስ ልብሶቹ ምዕመናን ናቸው› ሲሉ በትርጉም ከእርሱ ጋር ይተባበራሉ አይደል እንዴ!፡፡ የልብሱም ነጭ መሆን የቅድስና ምልክት ሲሆን፣ በኃጢአት ይህን ነጭነቱን ላቆሸሸ በደለኛ ደግሞ ተነሳሒው ቅዱስ ዳዊት እንዲህ የሚል ጸሎትን ደርሶ ሰጥቶታል :- ‹በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ›፡፡(መዝ 51፡7) ነጩን የክርስቶስን ልብስ በኃጢአት ጭቃ ከማቆሸሽ፣ አቆሽሾም ከመቅረት ፈጣሪያችን ይጠብቀን፡፡

ቅዱስ አምብሮስም ያንጸባረቀው የክርስቶስን ልብስ "የወንጌል ምሳሌ ነው" ብሎ ይተረጉመዋል፡፡ ልብስ ማንነትን እንዲያሳይ ክርስቶስም በተጎናጸፋት ወንጌል ማንነቱን ዐውቀናልና በደብረ ታቦር ላይ ብርሃን የፈነጠቀባት ልብሱ የወንጌል ምሳሌ ናት፡፡ ነቢዩ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ› ሲል የተናገረላት ብርሃናዊ የሆነች
ልብሱ ወንጌል ናት፡፡(መዝ 104፡2)

ከዚህም በኋላ ሙሴና ኤልያስ ከክርስቶስ ጋር ሲነጋገሩ ሐዋርያቱ በታቦር ተራራ ሆነው ይመለከቱ ጀመር፡፡ ከመድኃኒታችን ጋር የነበሩት ሐዋርያት ከነቢያቱ ከሙሴ እና ከኤልያስ ጋር መሆን ቻሉ፡፡ ጌታን የሚቃወሙት አይሁድ ግን እናውቃቸዋለን ከሚሏቸው ከነቢያቱም ጋር መሆን አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም የነቢያት የትንቢታቸው ማዕከል ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ካልሆኑ በቀር ሙሴና ኤልያስን ማየት አይቻልምና ነው፡፡

ጌታ ስለምን ከብዙ የብሉይ ኪዳን ጻድቃን መካከል ሙሴና ኤልያስን መረጠ? ቢባል

ሐዋርያቱ ከዚህ ቀደም ሰዎች ሙሴ ፣ ኤልያስ ነህ ይሉሃል ብለው ስለነበር፣ በጌታ እና በሎሌ መካከል ያለውን ልዩነት ያውቁ ዘንድ ‹የእኔን የሙሴን ጌታ ማን ሙሴ ይልሃል? የሙሴ ጌታ ይበሉህ እንጂ› እያሉ እንዲመሰክሩ ሙሴን ከብሔረ ሙታን ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቷቸዋል፡፡

ሙሴ አምላኩን ከአምስት መቶ ሰባ ጊዜ በላይ ቃል በቃል ቢያናግረውም ፊቱን ግን አይቶ አለማወቁ ይቆጨው ነበር፡፡ከዕለታትም በአንዱ ቀን ‹ፊትህን አሳየኝ?› ብሎ በለመነ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ‹ፊቴን አይቶ የሚድን የለምና ጀርባዬን ታያለህ› ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ጀርባዬን ታያለህ ሲል ልጅ በጀርባ እንዲታዘል በኋላ ዘመን ሰው ሆኖ የሚመጣ ‹የባሕርይ ልጄን› ታያለህ ማለቱ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ከሞት በፊት ለሙሴ የተገባ ቃል ኪዳን የተፈጸመው ከሞት በኋላ በዚህች ዕለት ነው፡፡ ኤልያስንም ‹አንተስ በኋላ ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ› ብሎት ነበርና ኤልያስም ቀነ ቀጠሮውን ጠብቆ በታቦር ተራራ ተገኘ፡፡

አይሁድ ክርስቶስን ሕግ አፍራሽ አድርገው ይከሱት ነበር፡፡ ለእግዚአብሔርም ክብር የቀኑ እየመሰላቸው ‹ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሏል› ብለው በመወንጀል ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ ስለዚህም ሕግን ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሙሴንና ለእግዚአብሔር ክብር የሚቀና ኤልያስን ምስክር አድርጎ የአይሁድን ሐሰት ለሐዋርያቱ ገለጸላቸው፡፡

በሞት እና በሕይወት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን ሲያሳይ ሙሴን ከመቃብር ኤልያስን ከሕያዋን ሀገር እንዲመጡ አደረገ፡፡

(ከዚህም የሚበዛ ትርጓሜ ስላለው የቀረውን በትርጓሜ ወንጌል መጽሐፍ ይመልከቱ)

የሙሴና የኤልያስን ንግግር የተመለከተው ቅዱስ ጴጥሮስም ጌታችንን ‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው ፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ› አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በባለቤቱ በእግዚአብሔርና በመረጣቸው ቅዱሳን መታሰቢያ ቤተ ክርስቲያን በማነጽ የሚያገለግሉ ሰዎችን ይመስላል፡፡ አንድም የእግዚአብሔርን ክብር ካዩ በኋላ ‹በዚህ መኖር ለእኔ መልካም ነው› ብለው ሀብት ንብረታቸውን፣ ርስት ጉልታቸውን ጥለው ለሚመንኑ መናንያን ምሳሌ ሆኖ ይታያል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግን ስለ ጴጥሮስ ንግግር ከዚህ የተለየ ነገርን ያሳየናል፡፡ ይኸውም አምላካችን አስቀድሞ ከዚህ ታሪክ መፈጸም በፊት ለሐዋርያቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድና በዚያም እንደሚሞት ነግሯቸው ቅዱስ ጴጥሮስ ተቃውሞት ነበር፡፡ ጌታም ዓለም የሚድንበት ሞቱን ስለተቃወመ የገሰጸው ቢሆንም፣ እርሱ ግን ከልቡ አልተቀበለውም፡፡ ስለዚህ አሁንም ከደብረ ታቦር ከወረዱ በኋላ እንደ ተናገረው ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ እና መሞቱ እንደማይቀር ስላሰበ ዳግመኛ ሞቱን ሲከላከል ‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው› ወይም እንደ ቅዱሱ አገላለጽ ‹ከዚህ ተራራ አንውረድ። ከወረድን ትሞታለህና፤ ጌታ ሆይ ለራስህ ምሕረትን አድርግ› ሲል እንደ ተናገረ ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ "አትሙት" ብሎ የሚከራከረው ቅዱስ ጴጥሮስ ቀድሞ በሚያየው አምላክ ወልድ እንደ ተገሠጸ፣ አሁን ደግሞ በማያየው አምላክ እግዚአብሔር አብ ‹እርሱን ስሙት› የሚል ወቀሳ ደረሰበት፡፡

አንድም ቅዱስ ጴጥሮስ ተምረው፣ ምሥጢር አይተው፣ በአገልግሎት ምክንያት የሚመጣባቸውን ረብሻና ሁካታ ፍርሃት በሰማነው ጸንተን እንኑር እንጂ ምስክርነቱ (አገልግሎቱ) ይቅርብን የሚሉ ሰዎችን ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር አብ ግን ከሰማይ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ምላሽ ‹የምወደው ልጄ እርሱ ነውና እርሱን ስሙት› የሚል ነበር፡፡ጌታችንን ቢሰሙት ምን የሚል ይመስላችኋል? ‹ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ› ነዋ!

ይቆየን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

ነሐሴ 12 2008 ዓ.ም.

(በድጋሚ የተለጠፈ)

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ የክርስቲያን አምላክ እንዲህ ነው! +++

ቅዱስ ጴጥሮስ መምህሩና አምላኩ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ልብሱ ከፀሐይ ይልቅ ሲያበራ፣ ነቢያቱ በክብር ተገልጠው ሲመሰክሩለት ቢመለከት "ከዚህ አትውረድ" አለው። ለጴጥሮስ:- እርሱም ፈርቶ እየወደቀ፣ ክርስቶስም በልዕልና እያበራ ቢኖሩ ሁሉ ጊዜ ደብረ ታቦር ቢሆን ምኞቱ ነበር። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አይደለም። እርሱ ከፍጥረቱ የራቀ ሉዓላዊ፣ የሚያስፈራ፣ የማይመረመርና የማይነገር ብቻ አይደለም። ለፍጥረቱ ባለው ፍቅር ደግሞ ትሑትም ይሆናል። አሁን የሰውነቱ ብርሃን አስደንግጦት ከእግሩ ስር የወደቀው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ከጥቂት ቀን በኋላ ግን መድኃኔዓለም እግሮቹን ሊያጥብ የማበሻ ጨርቅ እንደ ታጠቀ ከስሩ እንደሚያጎነብስ መቼ ዐወቀ?!

ጴጥሮስ ሆይ፣ ለምን ከታቦር አትውረድ ትለዋለህ? አንተስ በሰማያት በአባቱ እቅፍ የነበረውን አምላክ በታቦር ያየኸው ሥጋችንን ተዋሕዶ ወደ ምድር በመውረዱ አይደለምን? ለእኛ ሲል ከሰማያት የወረደውን ጌታ "በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" ብለህ በታቦር ልታስቀርብን ነውን? አንተ ቅን ሐዋርያ ሆይ፣ ታቦር ከአምላክህ ጋር የምትኖርበት የዕረፍት ቦታ እንዲሆንልህ ፈለግህ? ይህ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው ከፊትህ የቆመው የእግዚአብሔር በግ እኮ ያለ ቀራንዮም ማረፊያ የለው። ተወው ይውረድልን። ለእኛ አንተ በፊቱ ላይ ያየኸው ብርሃን ብቻ ሳይሆን ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ የሚወዛው የደም ወዝም ያስፈልገናል። ያለ እርሱ አንድንምና።

ጴጥሮስ ሆይ፣ መምህርህን "አትውረድ" ብለህ አትጠይቀው። ካለበት ልዕልና የሚያወርደው እኮ ፍቅር ነው። ለእርሱ "አትውረድ" ማለት "ፍጥረትህን አትውደድ" ከማለት አይተናነስም። አንተ የዋሕ ሐዋርያ "ብትወድስ" ብለህ ትጠይቀዋለህ? እርሱ በመልኩ ከፈጠረው ሰው አስበልጦ የሚወደው ምን ነገር አለ? ላያደርገው አትጠይቀው።

የክርስቲያኖች አምላክ እንደዚህ ነው። በአምላክነት ባሕርይው ልዑል ቢሆንም በመግቦቱ ግን ትሑት፣ በደስታ ጊዜ የማይለይ፣ በመከራ ጊዜም ሰው እስከ መሆን ደርሶ የሚዛመድ፣ የሰውን እግር የሚያጥብ፣ ስለ ሰው በመስቀል እርቃኑን የሚውል ነው። ይህ ለዚህ ዓለም ፈላስፎች ለጆሮ እንኳን የሚቀፍ ቢሆንባቸውም የእኛ የክርስቲያኖቹ አምላክ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ነው።

እንኳን ለበዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሰን!


ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
በክንፎቻቸው ተሸፋፍነው በፊቱ የሚቆሙለት ቅዱሳን መላእክት፣ ፈጣሪያቸው "እኔ በምድር ወዳጅ አለኝ። እርሱም አብርሃም ነው" ብሎ በነገራቸው ጊዜ እጅግ በመደነቅ ወደ አብርሃም ሄደው "አብርሃም አርከ እግዚአብሔር"/"አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ"/ እያሉ ዘምረውለት ነበር። በእውነት እግዚአብሔር "ወዳጅ አለኝ" ስላላቸው እንዲህ የተደነቁ መላእክት፣ "እኔ በምድር እናት አለኝ" ሲላቸው ምን ያህል ተገርመው ይሆን? እመቤታችንንስ በምን ዓይነት ቃል አመስግነዋት ይሆን?

በዛሬው እለት የአምላክን እናት ልዩ በሆነ ምስጋና እና እልልታ ያሳረጓት መላእክት፣ በምድር ሳለች "እይዋት የአምላክን እናት በምድር ትመላለሳለች" እያሉ በስስት የሚያይዋትና መምጣቷን የሚጠባበቁ እመቤታቸው ነበረች። ለዚህም ነው አባቶቻችን በሌሊት ማኅሌት "ተበሃሉ በሰማያት እለ ኪያኪ አፍለሱ፣ ማርያምሰ እንተ በምድር ታንሶሱ" እያሉ ሲወርቡ ያደሩት።

እኛም ንግሥታችንን ወደ ልጇ እልፍኝ ለሸኘንበት፣ መላእክትም እርሷን በደስታ ለተቀበሉባት ለበዓለ ዕርገቷ እንኳን በሰላም አደረሰን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
በዓመት ውስጥ ምንም ልንሠራ የማንችልባቸው ሁለት ቀናት ብቻ አሉ። አንደኛው 'ትናንት' ተብሎ ሲጠራ ሌላኛው ደግሞ 'ነገ' ይሰኛል። ስለዚህ ራሳችንን እና ሌሎችን የሚጠቅም በጎ ሥራ የምንሠራበት ትክክለኛው ቀን ዛሬ ነው።

"ዛሬ" የሥራ ቀን ነው!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
እኅታችን ቤዛዊት ታጠቅ "ግሩምና ድንቅ ፍጥረት" መጽሐፍን እንዲህ አድርጋ ዳስሳዋለች። ይመለከቱት ዘንድ ጋብዣለሁ።
+++ "የመውጊያውን ብረት አንቃወም" +++

ቅዱስ ጳውሎስ ወደሚደነቀው የክርስትና ብርሃን ከመምጣቱ በፊት፣ ለአባቶች ወግ የሚቀና እና የአይሁድን ሥርዓት ከሁሉ ይልቅ አብልጦ የሚጠብቅ ሰው ነበር።(ገላ 1፥14) በክርስቲያኖች አፍ የሚጠራው "ኢየሱስ ክርስቶስ" የሚለው ስም ኦሪታዊው እምነቱን ያጠፋዋል የሚል ስጋት ስለ ነበረበት ክርስቲያኖቹን ያለ ልክ ያሳድዳቸው ነበር። በተለየ እነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች በደማስቆ በሰላም እየኖሩ እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ ተቆጣ። እንደሚገድላቸውም እየዛተ በዚያ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ እንዲጽፍለት ሊቀ ካህናቱ ገብቶ ለመነ።(ሐዋ 9፥1-2)

የጠየቀውንም ደብዳቤ እንዳገኘ ጊዜ ሳያጠፋ ወዲያው በፈረስ እግር እየፈጠነ ወደ ደማስቆ ገሰገሰ። ወደ ከተማው መግቢያ ሲቃረብ ግን ያላሰበው ነገር ተከሰተ። ከሰማይ የወጣ አንጸባራቂ ብርሃን አይኑን ወግቶ ጣለው። አስፈሪው ሳውል ከፈረሱ ላይ እንደ ነገሩ ወደቀ። ጌታ ሳውልን ገና በኢየሩሳሌም ሳለ ደቀ መዛሙርቱን ሲያሳድድበት እዚያው በብርሃን መትቶ አልጣለውም። ሳውል በክርስቲያኖቹ መካከል እያለ በብርሃን ቢመታ ኖሮ፣ አይሁድ ክርስቲያኖቹን እንደ አስማተኛ ቆጥረው ይከስሷቸው ነበር። ለዚህም ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራ ሌላ ተገቢ ያልሆነ ስም ያወጡለት ነበር። ስለዚህ በደማስቆ ከተማ መግቢያው አፋፍ ላይ በብርሃን መትቶ ጣለው።

የጌታ አመጸኛን የሚስብበት ልዩ የሆነ የፍቅሩን ሰንሰለት ተመልከቱ። በብርሃን መትቶ ከጣለው በኋላ ያናገረው ግን "ስለ ምን ታሳድደኛለህ?" ("ምን አደረግኹ?") በሚል በሚለማመጥ ሰው ቃል ነበር። ልብ በሉ "አንተ ነህ እኔን የምታሳድደው?" አላለውም። ይህ የማስደንገጥና የቁጣ ቃል ነው። ቁጣ ብቻውን ደግሞ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያሠራም።(ያዕ 1፥20) ቢያሠራም የውዴታ አይደለም። ጌታ ግን ለአሳዳጁ ሳውል ያለውን ፍቅር በሚገልጥና ልብን በሚመረምር ቃል "ለምን ታሳድደኛለህ?" ሲል ጠየቀው።

በዚህ ፍቅሩም ምስኪን በጎቹን ለማጥቃት በአደገኛ ተኩላ ተመስሎ ሲበር የመጣውን፣ ከደማስቆ ደጃፍ ከከተማው በር አቅራቢያ ሲደርስ ተኩላነቱን አስጥሎ ከጎቹ መካከል እንደ አንዱ አደረገው። "ለምን ታሳድደኛለህ?" በሚለው ቃል ገዳዩ ሳውልን ጥሎ፣ በጎቹን የሚጠብቅና ስለ እነርሱም ሲል የሚሞት "እረኛው ጳውሎስ"ን አስነሣው።

ሳውል የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያሳድድ የነበረው ከክፋት ሳይሆን ለእግዚአብሔር ከነበረው ቅናት የተነሣ ነው። አሳዳጅነቱም የእውነት ጠላት ከመሆን ያይደለ፣ አምላክን አገለግላለሁ ከሚል የዋሕ አሳቡ የተወለደ ነበር። ስለዚህ የየዋሐን ሰዎች የክፋት ጽዋ ስትሞላ ተገስጸው ይማሩበታል እንጂ አይጠፉበትምና፣ እግዚአብሔር የዋሑ ሳውልን መገሰጽን ገሰጸው፤ ለሞት ግን አሳልፎ አልሰጠውም ።

ሳውል "ለምን ታሳድደኛለህ?" የሚለውን ድምጽ በሰማ ጊዜ፣ "ጌታ ሆይ ማን ነህ?" ሲል ጠየቀ። ጌታም "አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል" አለው። የአንድ ሕዋስ መታመም ለአካሉም ጭምር ይተርፋል። እጅ በስለት ቢወጋ አፍ ደግሞ ይጮሃል። ምእመናንም የክርስቶስ አካል በተባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ያሉ ሕዋሳት ስለሆኑ፣ እነርሱን ማሳደድ ክርስቶስን ማሳደድ ነው። ስለዚህም መድኃኒታችን ራሱን በክርስቲያኖች ቦታ አስገብቶ "የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ" አለው።

"የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል" የሚለውን ቃል ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ልክ እንደ እንቆቅልሽ ያለ ንግግር እንደ ሆነ ጽፈዋል። "የመውጊያ ብረት" የሚለውን የኢትዮጵያ ሊቃውንት "ሰይፍ" ብለው ተርጉመውታል። ኃይለ ቃሉን ሲያብራሩትም "ሰይፍን የረገጠ ሰው እርሱ ይጎዳል እንጂ ሰይፋ ምንም አይሆንም። አንተም ከእንግዲህ ወዲህ ምእመናንን ብታሳድድ ለእነርሱ ስደቱ ክብር ስለሆነ ይጠቀሙበታል። አንተ ግን ሳትጎዳበት አትቀርም" ሲለው ነው ይሉናል። ግሩም ትርጓሜ!

ከዚህ በተጨማሪ "የመውጊያ ብረት" ፈረስ የሚጋልብ ወይም በሬ የሚጠብቅ ሰው የሚገለገልበት መሣሪያ ነው። ገበሬዎችና ፈረስ ጋላቢዎች ፈረሱ ፍጥነት ሲቀንስባቸው፣ በሬውም አልሄድም ብሎ ሲለግምባቸው ሁለቱንም "በመውጊያው ብረት" እየወጉ ያነቁበታል። ቃለ እግዚአብሔርም የመውጊያ ብረት ነው። ሳውል ቀድሞ በቅዱስ እስጢፋኖስ በኩል የሰማውን የእግዚአብሔርን ቃል ቸል ብሎ ነበር። የቆመበትን አይሁዳዊነት ለቅቆ ወደ ክርስትናው እንዲሻገር የሚያነቃውን የመውጊያ ብረት ተቃውሞ ነበር። ስለዚህም ጌታችን አሁን "የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል" ሲል አስጠነቀቀው።

ከቆምንበት የኃጢአተኞች መንገድ፣ ከተቀመጥንበት የዋዘኞች ወንበር ቀስቅሶ የሚያነቃንን "የመውጊውን ብረት" ቃለ እግዚአብሔር አንቃወም። ልባችን አይደንድን፣ የቤተክርስቲያንን ድምጽ እንስማ።

"የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል"
ዕብ 4፥12

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
1
"ሰይጣን ከቶ እንደ ጸሎት ማስታጎል የሚወደው የለም። ጸሎት ፍላጻ ነውና ዓይኑን ይወጋዋል። ከሚጸልይ ሰው አንደበት እሳት ወጥቶ ሰይጣንን ያቃጥለዋል። ሰይጣንም ስለዚህ ከበጎ ሥራ ሁሉ ጸሎትና ትጋትን ይጠላል"

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (በአርጋኖነ ማርያም ዘሠሉስ)
+++ ዝምተኛው ፓትርያርክ +++

ከእለታት በአንዱ ቀን በግብጽ መንበረ ፓትርያርክ ሕንፃ እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ አረጋዊ ጳጳስ ቆመው ሳሉ አንድ ሰው ወደ ውስጥ ሲገባ ‹‹ብዙ ልጆች ያሉህ፣ ሸክምህ የከበደብህ ልጄ ሆይ ና!›› ጠሩት፡፡ ሰውየውም ግራ እየተጋባ ‹‹ማን? እኔን ነው አባቴ? እኔ እኮ አንድ ልጅ ብቻ ነው ያለኝ›› አላቸው፡፡ አቡነ ቄርሎስም ‹‹ልጄ ሆይ፣ አልተረዳህም እንጂ ሸክምህ ከባድ ልጆችህም ብዙ ናቸው›› አሉት፡፡ እርሱ ግን ‹‹እመኑኝ አንድ ልጅ ብቻ ነው ያለኝ›› እያለ ተከራከራቸው፡፡ አረጋዊውም ‹‹ልጄ፣ እንግዲያውስ ነገ ትረዳዋለህ›› ብለው ጥለውት ሄዱ፡፡ ይህ በሆነ በማግስቱ ሰባት ልጆች የነበሩት የዚህ ሰው ወንድም ድንገት በአደጋ ምክንያት ሞተ፡፡ ታዲያ የወንድሙን ሰባት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት በእርሱ ላይ ወደቀ፡፡ ትናንትና አንዲት ሴት ልጅ ብቻ የነበረው ዛሬ ግን የ8 ልጆች አባት ሆነ። ይህም ሰው ነገሩን ቀድመው ወደ ነገሩት እኚህ አባት ሄዶ የሆነውን ሲያብራራላቸው ‹‹ልጄ፣ ሸክምህ የከበደና ብዙ ልጆች ያለህ እንደ ሆንህ ስነግርህ እኮ አላመንከኝም?!›› አሉት፡፡ ለመሆኑ እኚህ አባት ማን ይሆኑ?

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ መጀመሪያ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በሙስና የተጥለቀለቀችበትና ትልቅ አስተዳደራዊ ችግር ውስጥ የገባችበት አሳዛኝ ጊዜ ነበር፡፡ በኋላም የሕዝቡ ቁጣ ገንፍሎ ፓትርያርኩን አግቶ እስከ መውሰድና ‹‹ሥልጣኔን በፈቃዴ ለቅቄያለሁ›› የሚል ደብዳቤ ላይ ተገድደው እንዲፈርሙ እስከ ማድረግ ደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ግርግር መሐል የጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ደርሰው ፓትርያርኩን ከዚህ እገታ በማዳን ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ ይህ ከሆነም ከአንድ ዓመት በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ጉባዔ ፓትርያርኩ ዮሳብ (ዳግማይ ዮሴፍ) ከኃላፊነታቸው እንዲነሡና በግብጽ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም እንዲኖሩ በአንድ ድምጽ ወሰነ፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ከሦስት ዓመት በላይ ያለ ፓትርያርክ ቆየች፡፡ ይህም የቅብጥ ቤተ ክርስቲያንን መንፈስ ያወከና በጉልበቷ ያንበረከከ አሳዛኝና የማይረሳ ጥቁር ትውስታ ሆነ፡፡

እንደ ጎልያድ ክንዱን አፈርጥሞ ይገዳደራት የነበረን የሙስና እና የብልሹነትን መንፈስ አንገቱን ቆርጠው የሚጥሉ እንደ ዳዊት ያሉ አባት ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ተገኙላት፡፡ እኚህም የከተማው መናኝ ፓትርያርኩ አቡነ ቄርሎስ ናቸው፡፡ አቡነ ቄርሎስ በሙስና እና በብልሹ አስተዳደር ምክንያት የምታነባ እና በልጆቿ ተወግታ እየደማች ያለች ቤተ ክርስቲያንን ቢረከቡም፣ በአሥራ ሁለት ዓመት (1959-71) ውስጥ ግን ይህ ሁሉ ተቀይሮ የቅብጧ ቤተ ክርስቲያን እንደ አዲስ ያንጸባረቀችበትና ያበራችበት ጊዜ ሆኗል፡፡ ይህ ወቅት የቅዱስ ማርቆስ አጽም ወደ ግብጽ የመጣበት፣ የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ወደ ዓለም መስፋፋት የጀመረችበት ወርቃማ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷ ፓትርያርክ እንዲኖራት ይደረግ በነበረው የንጉሡና የእኛ ሊቃውንት እንቅስቃሴም ላይ እርሳቸውም ጉዳዩ የራሳቸው እስኪመስል ድረስ ትልቅ ጥረትና ትግል አድርገዋል፡፡ በዚህም ድርጊታቸው የቅብጧ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን በተመለከተ አቅሌስያዊ አትሕቶን (Ecclesial kenosis) እንድትላበስ አድርገዋታል፡፡

አቡነ ቄርሎስ ለፓትርያርክነት ሲታጩ የታቃወሙ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ተቃዋሚዎች አንዱ በኋላ የቅዱሱ ቅርብ ወዳጅ የሆነው ናዝሚ ቡትሮስ የተባለው ጠበቃ ነበር፡፡ ይህም ጠበቃ ምንም የዚያን ጊዜውን አባ ሚናስን በአካል ባያውቃቸውም፣ ስለ እርሳቸው ሲወራ በሰማው አሉባልታ ግን የእርሳቸውን ለፓትርያርክነት እጩ መሆን በኃይል ተቃውሞ ጋዜጣ ላይ ጽፎባቸው ነበር፡፡ አባ ሚናስም ‹‹አቡነ ቄርሎስ›› ተብለው ከተሾሙ በኋላ ‹‹እንኳን ደስ አልዎት›› ለማለት ወደ እስክንድርያ መጣ፡፡ ፓትርያርኩም ደስ ብሏቸው ተቀበሉት፡፡ እርሱም ፊታቸው ላይ ያለውን የደስታ ስሜት ሲመለከት ‹‹እርሳቸውን ተቃውሞ ጋዜጣ ላይ የጻፈው ሰው እኔ መሆኔን ባያውቁ ነው›› ብሎ አሰበ፡፡ ቁጭ ብለው ግን ሲጨዋወቱ ‹አንዳንዶች ግን ስለ እኔ ይህንንም ያንንም ሲሉ ነበር…› ብለው እርሱ የጻፈባቸውን ክስ የሚመለከት ነገር ነገሩት፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ጠበቃ እያፈረ ‹‹ቅዱስነትዎ፣ እባክዎ ይቅር ይበሉኝ፡፡ እርሶን በሚገባ ባለማወቄ ነው፡፡›› አላቸው፡፡ አቡነ ቄርሎስም ፈገግ እያሉ ‹‹አይዞህ፣ ለዓለሙ ሙት የነበረውን ባሕታዊው አባ ሚናስን እንጂ እኔን አላጠቃህም፡፡ አሁን እኔ ቄርሎስ የሁሉ አባት ነኝ›› አሉት፡፡ ይህም ጠበቃ እውነተኛ ፍቅራቸውንና ይቅር ባይ ልባቸውን አይቶ የልብ ወዳጃቸው ሆኖ ቀረ፡፡

በSt. Vladmir Seminary press የታተመው የ‹‹A Silent Patriarch›› የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ ዶ/ር ዳንኤል ፋኑስ እንደሚናገረው የአቡነ ቄርሎስን የግል ሕይወት በተመለከተ የሚታወቁት በጣም ጥቂት ነገሮች ናቸው። የቅርብ አገልጋያቸው የነበረ ሰው እንኳን ስለኖሩት(የግል) ሕይወት ብዙ አያውቅም፡፡ በእርግጥም ዝምታ እንደ ጸጋ የሆነላቸው፣ የጸጥታን ሕይወት የመሩ፣ መላ የአገልግሎት ዘመናቸውን በቅዳሴና በጸሎት ያሳለፉ አባትን የተሰወረ ሕይወት እንዴት በቀላሉ መርምረን ማወቅ እንችላለን? ቅዱስነታቸው በኃዘናቸውም ቢሆን በሰዎች ከመከበብ ይልቅ መሸሸጊያና መጽናኛ ያደርጉት የነበረው ብቸኛው ቦታ ከመሠዊያው ታቦት ስር ሄዶ መውደቅ ነበር፡፡

አቡነ ቄርሎስ የግብጽን ቤተ ክርስቲያን አሥራ ሁለት ዓመት በቅድስና እና በጸሎት መርተው ክፋውን ዘመን ያሻገሩ ጻድቅ አባት ናቸው። ችግሮች ሁሉ የድርሻን ከመወጣት ጋር በጸሎት ይፈታሉ ብለው የሚያምኑ፣ "አባ ይህ ችግር አጋጠመን?" ሲሏቸው "እንጸልይበታለን" የሚለው መልስ ከአፋቸው የማይጠፋ በጸሎት ኃይል የሚተማመኑ ቅዱስ ነበሩ። የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አቡነ ቄርሎስ ካረፉ ከ42 ዓመታት በኋላ በ2013 ዓ.እ. ባደረገችው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቅድስናቸውን በግልጽ ለልጆቿ አሳውቃለች፡፡

ቅዱስነታቸው በሕይወት እያሉም ሆነ ካረፉ በኋላ በእርሳቸው ምልጃና ጸሎት የተፈጸሙ ተአምራትን የያዙ ወደ አሥራ ስምንት የሚሆኑ ተከታታይ ቅጽ ያሏቸው መጻሕፍትም ታትመዋል፡፡ አቡነ ቄርሎስ በግብጽ በጣም የሚወደዱ አባት ናቸው፡፡ በመላዋ ግብጽ ከሚኖሩ የክርስቲያን ቤቶች ውስጥ የእርሳቸው ፎቶዎች ያልተሰቀሉበት ቤት ማግኘት በጨለማ መርፌ የመፈለግ ያህል ከባድ ነው፡፡

እስኪ እኛም ለበረከት እንዲሆነን ከዕረፍታቸው በፊትና በኋላ ከአደረጓቸው ተአምራት ሦስቱን አንሥተን እንሰነባበት።

+++ "ለምን አልደወልሽም?" +++

የሴቶች ገዳም እመምኔት የነበረች አንዲት መነኩሲት አቡነ ቄርሎስን በስልክ ማናገር ስለፈለገች ወደ በቢሯቸው ሄዳ በግል የሚጠቀሙበትን የስልክ ቁጥር እንዲሰጧት ጠየቀች። በጊዜው እርሳቸው በሕመም ላይ ስለ ነበሩ የቢሮው ሠራተኞቹ ሲሻላቸው በአካል ታገኛቸዋለሽ ብለው ከለከሏት። ቅዱስነታቸው ግን በዚያው ቀን ሌሊት ለመነኩሲቷ በሕልሟ ተገልጠው አጽናንተው የስልክ ቁጥራቸውን ነገሯት። እርሷ ግን ነገሩን ችላ ብላ ሳትደውል ቀረች። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እመምኔቷ ከአቡነ ቄርሎስ ጋር በአካል ስትገናኝ "የግል ቁጥሬን ሰጥቼሽ አልነበር? ለምን አልደወልሽም?" ሲሉ ጠየቋት። እርሷም በነገሩ ስለተደናገጠች አፏ ተሳሰረ። የምትመልሰውም አጥታ ዝም አለች።

+++ "ቁርሷን በልታለች" +++

ቅዱስነታቸው ቅዳሴ ቀድሰው
1
ሚያቆርቡበት ጊዜ አንዲት እናት ሴት ልጇን እንዲያቆርብላት ዲያቆኑ ሳሊብን ጠየቀችው። እርሱም ሕፃኗን ታቅፎ ወደ አቡነ ቄርሎስ ሲያመጣት "ይህችን ልጅ መልሳት። ቁርሷን የባቄላ ቅቤ በልታ ነው የመጣችው" አሉት። ዲያቆኑም ልጅቷን ወደ እናቷ መልሶ "ቁርሷን በልታለች?" ብሎ ቢጠይቃት፣ "አዎ፤ ትንሽ ዳቦ በባቄላ ቅቤ በልታ ነው የመጣነው" አለችው። ዲያቆኑም በልቶ መቁረብ እንደማይቻል ለእናትየው ካስረዳ በኋላ፣ በአቡነ ቄርሎስ ይህን ማወቅ ግን እየተገረመ ወደ ቅዳሴው ተመለሰ።

(ከዕረፍታቸው በኋላ)

+++ "ማንም አይናደድም" +++

በእስክንድርያ የምትኖር አንዲት ሴት ልጅ የነበረቻት እመቤት፣ ለልጇ ወንድም የሚሆን ልጅ እንዲሰጧት ወደ አቡነ ቄርሎስ ጸለየች፡፡ ጸሎቷን ሰምተው ወንድ ልጅ ከሰጧትም ስሙን ‹ቄርሎስ› ብላ እንደምትጠራው ተሳለች፡፡ ያቺም ሴት ልመናዋ ተሰምቶ ጸነሰች፡፡ ባለቤቷም ‹‹የሚወለደው ወንድ ልጅ ከሆነ ለአባቴ መታሰቢያ እንዲሆን በእርሱ ስም ዛኪ ብዬ መጥራት እፈልጋለሁ›› አላት፡፡ እርሷም ወንድ ከሆነ ስሙን ‹ቄርሎስ› ልትለው ስእለት እንደ ገባች ብትነግረውም ባለቤቷ ግን በሞተው አባቴ ስም ካልተጠራ አይሆንም ብሎ ተቃወማት፡፡ እመቤቲቱም ነገሩን ለእግዚአብሔር እንዲያስተካክለው ተወችው፡፡ የመውለጃዋ ሰዓት በደረሰ ጊዜም መንታ ወንድ ልጆችን ተገላገለች፡፡ ለልጆቿም ስም ስታወጣ አንዱን እንደ ስእለቷ ቄርሎስ አለችው። ለሌላኛውን ደግሞ እንደ ባለቤቷ ፈቃድ ዛኪ ብለው ጠሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስም በሆስፒታሉ ውስጥ ሳለች ወደ እርሷ መጥተው ‹‹አንቺ ሴት አሁን ደስ አለሽ? በዚህ መንገድ ከሆነ ማንም አይናደድም›› አሏት፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
1
ከወንድሞች መነኮሳት አንዱ አባ ጳጉሚስን "አባታችን በራእይ ምን እንደ ተመለከትህ ንገረን?" በማለት ጠየቃቸው። አባ ጳጉሚስም "ንጹሕ እና ትሑት የሆነን ሰው ባየህ ጊዜ እርሱ ታላቅ ራእይ ነው። የማይታየውን (ረቂቅ) አምላክ በሚታየውና የእግዚአብሔር መቅደስ በሆነው ሰው ውስጥ ከማየት የሚበልጥ ምን ራእይ አለ?" ሲሉ መለሱለት።

ልቡናው ንጹሕ እና ትሑት የሆነን ሰው ማየት ራእይ ከማየት ይበልጣል። ረቂቁ አምላክ በእርሱ በኩል ግልጥ ሆኖ ይታያልና።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
"ሌቦች አድብተው በመግባት ሊሰርቁ ወደ ቤቱ በቀረቡ ጊዜ ከውስጥ የሚያወራ ሰው ድምጽ ሲሰሙ ለመግባት እንደሚፈሩ፣ እንዲሁ ጠላቶቻችን አጋንንትም ነፍሳችንን ሰርቀው የራሳቸው ገንዘብ ለማድረግ ወደ እኛ በቀረቡ ጊዜ፣ ከልብ የሚመነጨውን ጸሎት ሲሰሙ ወደ ውስጥ ለመግባት እየፈሩ በዙሪያችን ያደባሉ"

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
በዓለሙ ያለውን ዝና ለማግኘት ምን ያህል ደከምህ? በሰዎች ፊትስ ከፍ ብለህ ለመታየት ስንት ጊዜ ራስህን ለአደጋ ጣልህ? የታዋቂነትህ ዋጋው ስንት ነው? ነገር ግን ይህን ሁሉ መሥዋዕትነት ከፍለህ የሰበሰብከው ዝና እና ክብር ተከትሎህ ወደ ሰማይ አይሄድም። ያለበሱህ የክብር ካባ፣ በራስህ ያኖሩልህ የስኬት አክሊል እዚሁ እንዳገኘሃቸው እዚሁ ጥለሃቸው ትሄዳለህ። ጻድቁ ኢዮብ እንደ ተናገረው ከእናትህ ማኅፀን ራቁትህን እንደ ወጣህ፣ እንዲሁ ራቁትህን ትመለሳለህ።(ኢዮ 1፥21) ታዲያ እርቃኑን ያለ ንጉሥ ከተራው ሕዝብ፣ እርቃኑን ያለ ባለጠጋ ከደሃው፣ እርቃኑን ያለ ክቡር ከተናቀው በምን ይለያል?!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg