Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
531 photos
44 videos
1 file
841 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
Dn Abel Kassahun Mekuria pinned «+++"እውነትም የመከር በዓል"+++ ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ በጋራም በተናጠልም ለሐዋርያቱ እየታያቸው የትንሣኤውን አማናዊነትና ‹ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገር እየነገራቸው› አርባ ቀን ቆይቷል፡፡(ሐዋ 1:3) በአርባኛውም ቀን ሲያርግ ‹የሚያጸና፣ የሚያነጻ እና የሚያጽናና መንፈስ ቅዱስን› እንደሚልክላቸው ተስፋን ሰጣቸው፡፡ ነገር ግን ከላይ ኃይልን እስከሚቀበሉባት ቀን ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ እንዲቆዩ…»
አዳም "አትብላ" ለሚለው የመጀመሪያ ድምጽ ቢታዘዝ ኖሮ፣ "አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ" የሚለውን ሁለተኛውን ድምጽ ባልሰማ ነበር።

"ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ" የሚለውን የዐሣማ ፍልስፍና (pig philosophy) እንተው።

"ነገ እንሞታለንና እንጹም!"

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ ጽድቅን መተወን +++

ጌታችን ከአደገባት ናዝሬት ወደ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቃ ያለች ሴፎሪስ (Sepphoris) የምትባል በገሊላ የምትገኝ ከተማ ነበረች። ይህችም ከተማ በጣም ደማቅ በመሆኗ "የገሊላ ጌጥ" ተብላ ትጠራለች። በውስጧም ታላቅ የቴያትር አዳራሽ ነበራት። በጥንታውያን የሮምና የግሪክ ቴያትር ታሪክ ልክ እንደ ዛሬው ገጸ ባሕርይን ለመላበስ (ለመምሰል) የሚረዳ የሜካፕ ሙያ ሳይመጣ በፊት፣ ተዋናይዎቹ የኃዘንና የደስታ መልክ ያላቸውን ጭንብሎች ለብሰው ነበር የሚተውኑት። እነዚህም ጭንብሎች "persona" የሚል መጠሪያ ሲኖራቸው ትርጉሙም "ጭንብል"/"mask" ማለት ነው። (በነገራችን ላይ personality የሚለው ቃል persona or mask ከተባለው ከዚሁ ግንድ መውጣቱን ልብ ይሏል።)

የሥነ ቅርስ ተመራማሪዎችን ትኩረት ከሳቡ እና በብዛት የኀሠሣ ቁፋሮ ከሚደረግባቸው የዓለማችን ክፍሎች አንዷ ሴፎሪስ ነች። ታዲያ ጌታችን ላደገባት ናዝሬት ቅርብ በሆነች በዚህች ከተማ በተደረገ የarcheology ቁፋሮ የተለያዩ የቴያትር ጭንብሎች ተገኝተው ነበር።

ጌታችን በወንጌል ጻፎችና ፈሪሳውያንን "ግብዞች"
እያለ ይጠራቸው ነበር። ግብዝ የሚለው ቃል ደግሞ በግሪኩ "Hypocrite" የሚለው ሲሆን ትርጉሙም "ተዋናይ"/"Actor or play maker" ማለት ነው። በመሆኑም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩትን የማይኖሩ ነገር ግን በሰው ፊት ፍጹም መስለው ለመታየት የሚፈልጉትን አይሁድ፣ በዘመኑ በነበሩትና ጭንብል ለብሰው በሚጫወቱት የቴያትር ባለሙያዎች ስም "ተዋናይ" ብሎ መጥራቱ ያለ ምክንያት አይደለም።

ኑሮው በግልጽ የሚታወቅ እውነተኛ ሰው ቢሳሳት እንኳን ተመክሮ የመታረምና የመመለስ እድል አለው። የሚያስመስል ሰው ግን ለትምህርትና ለተግሳጽ እንኳን ያስቸግራል። እንዲሁ እንዳስመሰለም የእውነት ሳይኖር ይሞታል። ታዲያ ከዚህ ሰው በላይ ራሱን የሚበድል ከየት ይገኛል?

ጻድቅ መስሎ በሕዝብ ተከብሮ ከመኖር ይልቅ ድክመቱን ያመነ ኃጥእ ሆኖ በሰው ፊት መመላለስ ይሻላል። ፈጣሪ አንድ ቀን የኃጢአቱን ብዛት የሚቀንስለት፣ ከእሳት ነጥቆ የሚያወጣው ቸር መካሪ አያሳጣውምና።

ከአስመሳይ ጻድቅ እውነተኛ ኃጥእ ይሻላል!
አናስመስል!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ "ለውኃ ለውኃማ..." +++

ብቻ መሆን ከባድ ነው። ለብዙ ፈተናዎች ያጋልጣል። የቀደመች እናታችን ሔዋን ሰይጣን አሰነካክሎ የጣላት ብቻዋን መሆኑዋን አይቶ ነው። ብቻ ሲሆኑ እያየ መፈተን የለመደ ሰይጣን ክርስቶስንም በቆሮንቶስ በረሃ ብቻውን ባየው ጊዜ ፈተናውን ይዞ ወደ እርሱ ቀርቦ ነበር። ክርስቶስ ግን የማንም ምክርና እገዛ የማያስፈልገው አምላክ በመሆኑ በገዛ ሥልጣኑ ድል አድርጎታል። በኋላም የሰው ልጅ "ያለ መካሪ ሲቀር ደስ የሚለው" የሰይጣን መጫወቻ እንዳይሆን የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዎቹ ካህናት ሐዋርያትን ሰጠን።

የክርስቶስ አካሉ የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿ በራሳቸው ማስተዋል ተደግፈው እንዳይጠፉባት፣ ቀዛፊ እንደ ሌለው ታንኳ በየአቅጣጫው በሚነፍሰው የወሬ ነፋስ እንዳይነዱ የሚጠብቁላትና በቀናው ጎዳና እየመሩ በጎውን መንገድ የሚያስተምሩላት ካህናት አሏት። እነዚህም ካህናት በዋናነት ሁለት አገልግሎት አላቸው። አንደኛው "በምድር የፈታችሁት በሰማያት የተፈታ ይሆናል" ተብሎ በተሰጣቸው አምላካዊ ሥልጣን መሠረት ንስሐ ለሚገቡ ምእመናን ላለፈው በደላቸው ሥርየትን ማሰጠት ነው።(ማቴ 16፥19) ሁለተኛው ደግሞ እነዚያ ንስሐ የገቡ ምእመናን ከገቡበት የኃጢአት ወጥመድ የሚወጡበትንና ጤናማ የሆነ የተረጋጋ ሕይወት የሚመሩበትን በጎ ምክር መለገስ ነው።

ይሁን እንጂ አንዳንዶቻችን ንስሐ ለመግባት ካልሆነ በቀር ካህናትን ቀርቦ ለማማከር ብዙም ፈቃደኝነት አናሳይም። ችግሮቻችን ተረድተው መፍትሔ የሚሰጡንም አይመስለንም። እንደውም ትንሽ የዘመኑን ሳይንስ የቀመስን ከሆንማ "አባም ጋር ብሄድ ያው የሚሉኝ ነገር የታወቀ ነው። ታዲያ ለምክሩ፣ ለምክሩ አንደኛዬን የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ጋር ብሄድ አይሻልም" የሚል አስተያየት እንሰጣለን። በርግጥም በዚህ ረገድ ጥሩ አገልግሎት የሚሰጡ በዓለም ያሉ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች አሉ። ወደ እነርሱ መሄድም ኃጢአት አይደለም። አንተን የሚያስወቅስህ የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ጋር መሄድህ ሳይሆን፣ በካህናቱ በኩል ልታገኝ የምትችለውን ጠቃሚ ምክርና መፍትሔ አሳንሰህ ማየትህ ነው።

የሶርያ የጦር ሠራዊት አለቃ የነበረው ንዕማን ሰውነቱ በለምጽ በነደደ ጊዜ ፈውስን ፍለጋ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መጥቶ ነበር። ነቢዩም ንዕማንን ከደጃፉ እንደ ቆመ ባወቀ ጊዜ "ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ" ብሎ መልእክተኛ ላከበት።(2ኛ ነገ 5፥10) ንዕማንም የነቢዩን ቃል ሲሰማ ተቆጣ። እኔ የአምላኩን ስም እየጠራ በእጆቹ ዳስሶ ይፈውሰኛል ስል፣ እርሱ እንደ ቀላል ነገር በዮርዳኖስ ታጠብ ይለኛል። ደግሞ ለውኃ ለውኃ "የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን?" አለ። ወታደሩ "በዮርዳኖስ ውኃ ታጠብ" የሚለውን ትእዛዝ እንጂ በነቢዩ ቃል አድሮ የሚሠራውን ኃይለ እግዚአብሔር አላስተዋለም። ስለዚህም የዮርዳኖስን ወንዝ እርሱ ከሚያቃውቃቸው የአገሩ ዝነኛ ተፋሰሶች ጋር አነጻጸረው። በኋላ ግን በባሪያዎቹ አሳሳቢነት ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ቢል ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ሥጋ ለመለመለት።

በርግጥ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ ካህናት የሚሰጡህ ምክሮች ከሌላ ባለሙያዎች ልታገኛቸው የምትችላቸውን ዓይነት ሊሆኑብህ ይችላሉ። አንዳንዴም አንተ የምታውቀው ቦታ ላይ የሚሰጠው የምክር አገልግሎት ልክ እንደ ደማስቆ ወንዞች ካህናቱ ከሚሰጡህ ምክር የበለጠ በንድፈ አሳቦችና በትግበራዎች የበለጸጉ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ። ነገር ግን ከካህናቱ አንደበት የምትሰማው ምክር "ለውኃ ለውኃማ" ብለህ የምታቃልለው ባዶ ቃል አይደለም። በውስጡ ልቡናን የሚመረምርና የሚለውጥ ኃይለ እግዚአብሔርን፣ ረድኤተ እግዚአብሔርን የተሸከመ ክቡድ ቃል ነው። እንደ ለምጽ ከወረረህ ችግር ሁሉ ሊገላግልህ የሚችል የሚሠራ ቃል ነው።

በትዳር ጉዳይ በሮማውያን ሸንጎ ፊት እየተካሰሱ ካህናቱን ያሳጡ እንደ ነበሩት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች፣ እኛም አንዳች እክል ሲገጥመን መካሪ እንደ ሌላት ነገር ፈጥነን ቤተ ክርስቲያንን እየጣልን  ወደ አንኮብልል። አንዱን ለመያዝ ሌላውን ማንጠልጠልና ማንኳሰስ አይጠበቅብንም። ካህናቱን እናማክር፣ የሥነ ልቡና ባለሙያዎችንም ቸል አንበል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
ሰው ባከበረህ ጊዜ ልቡናህ ደስ አይበለው። ይልቅ ፈጽመህ አልቅስ። ጳውሎስና በርናባስ ሰዎች ባከበሯቸው ጊዜ ልብሶቻቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጠዋልና፤ ጴጥሮስና ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ያለ ወንጀል ተከስሰው በጅራፍ በተገረፉ ጊዜ ደስ አላቸው። በሸንጎ ፊት እንደ ልጅ ተቆጥተው ስላሳነሷቸው አልተከፉም። ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ተቆጥረዋልና።

የዚህ ዓለም ክብር እንደ ጤዛ ነው። መጥፋቱም ገና ከመታየቱ ነው።

ማር ይስሐቅ እንደ ተናገረው የዓለሙ ክብር እንደ ጥላ ነው። ከሚያሳድዱት ሰዎች ይሸሻል። የሚሸሹትንም ይከተላል።

"አንተ ግን አቤቱ፥ መጠጊያዬ ነህ፥ ክብሬንና ራሴንም ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ"
መዝ 3፥3

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ "ሳስበው የሚገርመኝ!" +++

የሰው ልጅ በምድር ከተፈጠሩት ፍጥረታት ሁሉ ያማረና ድንቅ ፍጥረት በመሆኑ፣ ዘውድ የአካል መጨረሻ በሆነው በራስ ላይ እንዲደፋ ጌታም ‹የክብር አክሊል ነህ› ሲለው በመጨረሻው የፍጥረት ቀን በእጁ አበጃጅቶታል፡፡

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ያስገኘው አስቀድሞ በዕለተ እሑድ ከፈጠረው ከመሬት አፈር ነው፡፡ በእርግጥ የሰው ገላ የአፈር ብቻ ውጤት እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ሙሴም ቢሆን በመጽሐፉ ‹ከምድር አፈር አበጀው› ይላል እንጂ ‹ከምድር አፈር ብቻ› አይልም፡፡ ይህም የቀሩት ነፋስና እሳት፣ ውኃም ቢሆኑ በመጽሐፉ በአፈር በኩል ተካተው መቆጠራቸውን ያመለክታል፡፡ ሰው ከእነዚህ አራት ምድር ከተገነባባቸው መሠረታዊ ነገሮችም ስለተገኘ በከርሰ ምድር እና በውቅያኖሶች የምናገኛቸው ካርቦን፣ ናይትሮጅን፣ ሰልፈር፣ ፎስፈረስና ሌሎችም ማዕድናት ሁሉ በሰውነቱ ውስጥ ይታያሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ ሊቃውንት የሰውን ልጅ ‹ንኡስ ዓለም› (Microcosm) ሲሉ ይጠሩታል፡፡

በእውነት በሰው መሬታዊ ተፈጥሮ ውስጥ የታየውን የእግዚአብሔርን ጥበብ እስኪ ለአፍታ እናድንቅ፡፡ አንዱን አፈር አጥንትና ጅማት ፣ደም ሥርና ጉበት ፣ኩላሊትና ልብ አድርጎ መክፈል እንዴት ያለ አምላካዊ ጥበብ ነው? አንዱንስ ውኃ ሲፈለግ ደም ፣ሲፈለግ ሀሞት ሲያሻ ደግሞ ቅባት (ዘይት) ማድረግ ምን ዓይነት መራቀቅ ነው?

እንደ ውኃ ካለው ፈሳሽ እና እንደ አፈር ካለው ብናኝ ደካማ ነገሮች ራሱን ችሎ ጸንቶ የሚቆምና የሚንቀሳቀስ ጉልበተኛ ሰው መፍጠርስ እንደምን ያለ ሙያ ነው?

አዳምን ከአፈር የፈጠረ ጌታ ሔዋንን ያበጃጃት ከአጥንት ነው። ስለዚህ ነገር የሚላኑ ሊቅ አምብሮስ ሲያብራራ ‹አዳም ከተፈጠረበት መሬት ሔዋን አለመፈጠሯ፣ የሴት እና የወንድ የሰውነት ባሕርይ አንድ መሆኑንና ለሰው ዘር መስፋፋት ሁለቱም እንደ አንድ ምንጭ (ግንድ) መሆናቸውን ለማሳየት ነው› ይላል፡፡ እውነት ነው! በርግጥም ከዚህ መሠረታዊ ሐሳብ በመነሣት ለሰው ልጆች ልክ ልዩ ልዩ ‹ዝርያዎች›/‹Species› እንዳሏቸው ሌሎች ፍጥረታት ‹የሰው ዝርያዎች› ተብሎ አይነገርም፡፡ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሁሉ ምንጭ በአንድ አዳም እና ከእርሱ በተገኘች በአንዲት ሔዋን በኩል አንድ ዘር አድርጓቸዋልና፡፡

እግዚአብሔር ከአንዲት አጥንት ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ያቺን ስፍራ መልሶ በሥጋ እንደዘጋት ሊቀ ነቢያት ሙሴ ጽፎልናል፡፡ አንድ የቀዶ ጥገና የሚያደርግ ሐኪም የሚፈልገውን አጥንት ከሰውነት ውስጥ ቆርጦ ካወጣ በኋላ በተቆረጠው አጥንት ምትክ ሰወነቱ ሌላ አጥንት ማፍራት እንዲችል የቀድሞውን የአጥንት የላይኛውን ሽፋን (Periosteum) በጥንቃቄ ይተወዋል፡፡ ልክ እንደዚሁ በጠቢቡም አምላክ የተከናወነው የቀዶ ጥገና ተግባር ይህን ይመስል ነበር፡፡ ያቺን አንዲት አጽም ከአዳም ከወሰደ በኋላ መልሶ እንዲተካ የሚያደርገውን ሽፋን (ሥጋ) /Periosteum/ አልብሶታል፡፡ ከዚህም የተነሣ በሰው የጎድን አጥንቱ ላይ ምንም አይነት የጉድለት ምልክት አይታይም፡፡ ከአዳም ተወስዶ የነበረው አጥንት ራሱን እንዲተካ ተደርጎ ተዘጋጅቷልና ዛሬ በወንዶች ላይ የሚታይ የጎድን አጥንት ስንኩልነት (ጎዶሎነት) የለም፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ እንደ ተናገረው ከአዳም አንዲት አጽምን ወስዶ ሴት አድርጎ መሥራት እንዴት ዓይነት ግሩም ነገር ነው? ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዳደነቀው ከብቻዋ ከአንዲት ዐፅም ሦስት ዐፅቆች ያላት፣ መናገርና ሌሎችንም መርዳት የምትችል ውብ ፍጥረት አድርጎ ማበጃጀት እንደምን ያለ አምላካዊ ‹ሁሉን ቻይ›ነት ነው? ‹ግሩምና ድንቅ አድርጎ› የፈጠረን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ "የልጅነትን ጠባይ እንሻር" +++

በአካባቢያችን የሚገኙ ሕጻናት ሲቦርቁ እና ሲጫወቱ ማየት ልብን ደስ ያሰኛል። በፊታቸው ላይ የምናየው ንጹሕ ፈገግታ በሐዘን የጠወለገው ያዋቂ ገጻችንን እንደገና በደስታ እንዲለመልም ያደርገዋል። ሕጻናት ሲያዝኑ ከመመልከት የበለጠ ምን የሚያሰቃይ ነገር አለ? እነርሱን ሊጎዷቸውና ሊያሳምሟቸው የሚችሉ ነገሮችንስ ከማድረግ የበለጠ ምን ክፋት አለ? ። ሆን ብሎ በጭካኔ ሕጻናትን በስለት እየወጋ የሚያደማ ሰው ቢያጋጥማችሁ ምን ትሉታላችሁ? ። "ኸረረረ እንዲህ ዓይነቱን አውሬማ…" ብሎ መጀመር ሁላችንንም ሳያመሳስለን ይቀራል?!

ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እንዲህ የምናወግዘውንና ለደቂቃ እንኳን ማሰብ የማንፈልገውን ነገር ሁኔታዎች ሲያስገድዱንና አማራጭ ስናጣ በልጆቻችን ላይ እንዲፈጸም ፈቃደኞች ልንሆን እንችላለን። ምኑን ነው የምንፈቅደው? በስለት መወጋታቸውን ነዋ!!!። እንዴት?

ለምሳሌ ወላጆች ልጃቸው በጸና የታመመ ከሆነና ከሕመሙ በፍጥነት እንዲያገግም ከተፈለገ ፤ በሐኪሙ ትዕዛዝ የተሰጠውን አስፈላጊውን መድኃኒት በጥንቃቄ እንዲወስድ ማድረግ አለባቸው። ስለ መድኃኒት አስተዳደር /አሰጣጥ/ (Drug Administeration) በተመለከተ እንደ በሽታው ጽናትና ፣አስፈላጊነት ከሽሮፕ ውጭ በደም ሥሩ በኩል በመርፌ የሚሰጠው ጊዜ አለ። በዚህ ወቅት ወላጆች እንዴት ዓይናችን እያየ ልጃችን በስለት ሲወጋ ዝም እንላለን? ብለው ነርሷን አይቃወሙም። "ጨካኝ ፣አረመኔ" እያሉም ሐኪሞቹን አያወግዙም። ይህ ነገር ለተሻለ የልጃቸው ጤና ሲባል የሚደረግ እንክብካቤ እንደሆነ በማሰብ ፤ ልጃቸው በመርፌ ሊወጋ በመሆኑ ውስጥ ውስጡን ቢያዝኑም የወደፊት መዳኑን ተስፋ በማድረግ አንጀታቸውን ጠበቅ ያደርጋሉ።

በሕመም የተዳከመው ልጃቸው ግን መድኃኒት የተሸከመውን መርፌ ወደ እርሱ ባቀረቡት ጊዜ አሻፈረኝ ይላል። በልቅሶና በዋይታ ዓይኖቹን ወዲህ እና ወዲያ እያንከራተተ እንዲተዉት በሕጻን አንደበቱ ይለማመጣል። ነርሷ እና ወላጆቹ ግን አይዞህ እያሉ ያበረታቱታል። በስተመጨረሻም መርፌው ወደ ልጁ ሰውነት ዘልቆ በገባ ጊዜ መድኃኒትነቱን ሳይሆን ሕመሙን ብቻ አስቦ "እሪሪ " ብሎ ያለቅሳል። ይህን ያደረጉበት ሁሉ እንደ ጠሉት ሊያስብ ይችላል። እውነቱ ግን ሌላ ነው። ይህ ሁሉ ልቅሶ ፣ይህ ሁሉ መድኃኒትን መካላከል ከአላዋቂነቱ የሚመነጭ ነው። እድሜ ሲጨምርና የበለጠ አስተዋይ ሲሆን ግን ያለ ማንም አበረታችነት የመድኃኒትነት ጥቅሙን በማሰብ ሕመሙን ዋጥ አድርጎ ይወጋል። መርፌውን ያዘዘለትንም ሐኪም ስለ መልካም ባለመድኃኒትነቱ ከልቡ ያመሰግናል።

የነፋችን ባለመድኃኒት የሁላችን አባት የእግዚአብሔርም አሠራር እንዲሁ ነው። የእኛ የልጆቹ ምሬትና ልቅሶም ከዚያ ሕጻን የተለየ አይደለም። እርሱ በነፍስ ስለ ደረሰብን ጽኑዕ ሕመም (ከእርሱ መለየት) ምክንያት ልክ መድኃኒት እንደ ተሸከሙ መርፌዎች ወግተው የሚያድኑ "ደዌያትና ፣ማጣትን" ሊልክብን ይችላል። እኛ ደግሞ የእነዚህን "ደዌያትና ፣ማጣትን" ጥቅም ስለማንረዳ በሥጋ የሚደርስብንን ጊዜያዊ ጉዳት ብቻ በማሰብ "እሪሪ" ብለን እናለቅሳለን። "ይቅርብኝ አይመመኝ ፣ግድ የለም አልጣ" እያልን ፈጣሪን እንለምናለን። ነገር ግን እየተከላከልን ያለነው መድኃኒታችንን እንደሆነ አላወቅንም። እግዚአብሔር ግን ለእኛ የሚሻለውን ነገር ስለሚያውቅ ያ የጠላነውን ግን የሚጠቅመንን ነገር ያደርግብናል። በዚህም አምላካችን እንደማይወደን እና ስለ እኛ ግድ እንደማይሰጠው እናስብ ይሆናል። ይህ እንደ ልጅ ሆኖ ማሰብ ነው።

ነገር ግን በመንፈስ ስንጎለምና የልጅነትን ጠባይ ስንሽር ፤ ያኔ በሕመምና በማጣት ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ቸርነት እናያለን። በዚያን ጊዜ ያለ ምንም ምሬት እና ማጉረምረም "ደዌያትና ፣ማጣትን" በምስጋና እንቀበላለን። ስለ ነፍሳችን ጤና ሲል ሰውነታችንን በደዌ እና በማጣት የጎበኘ አምላካችንንም እናከብረዋለን።

አሁን ግን በመንፈስ ልጆች ስለሆንን እንደ ልጆች እናስባለን ፣ እንደ ልጆችም እንናገራለን። መድኃኒቱን ሳይሆን መርፌነቱን እያሰብን እናለቅሳለን። ፈጣሪያችንንም መሐሪ እና የነፍሳችን ባለመድኃኒት አድርገን ሳይሆን በጭካኔ እና በግድ የለሽነት እንፈርጀዋለን። ግድ የላችሁም እስኪ አንድ ጊዜ መርፌውን ትተን መድኃኒቱን እናስብ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
"በጣም አስፈላጊው ነገር መንፈሳዊ መጻሕፍትን በምናነብበት ጊዜ ያለን ማንነት ሳይሆን፣ አንብበን ስንጨርስ የሚኖረን ማንነት ነው"

ስምዖን ዘደብረ አቶስ

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ "ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው" +++
1ኛ ጢሞ 3፡15

በትምህርቱ ለቤተ ክርስቲያን ፋና የሆነላት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው በዚህ የመልእክት ክፍል ለክህነት ስለሚገቡ ሰዎች ያነሣል፡፡ ከኤጲስ ቆጶስነት እስከ ዲቁና ያሉትን መንፈሳዊ መዓርጋት የሚቀበሉ ወንድሞች ምን መስፈርት ሊያሟሉ እንደሚገባቸው በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ቀጥሎም መልእክቱ ወደሚላክለት ጢሞቴዎስ መለስ በማለት ‹ፈጥኖ ወደ እርሱ ለመምጣት› ያለውን ተስፋ ይገልጽለታል፡፡ ደግሞ ነገር ቢያዘገየው እንኳ ጢሞቴዎስ ‹በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ› ያውቅ ዘንድ ካለበት ሆኖ በጽሑፍ እንደሚያስተምረው ይነግረዋል፡፡ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት የሚኖሩ ሁሉ ለቤቱ ክብር የሚመጥን አኗኗር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ ሕይወት ደግሞ የቤቱን ምንነትና የባለቤቱን ማንነት ከማወቅ የሚመነጭ ነው፡፡ በመሆኑም ሐዋርያው ይህ እንዴት መኖር እንዳለብህ የምነግርህ ቤት ‹የእውነት ዓምድና መሠረት ፤ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው› ሲል ያብራራለታል፡፡ በዚህ ጽሑፋችን ‹የእውነት ዓምድ› ስለተባለችው አንዲቷ ቤተ ክርስቲያን እናወሳለን፡፡ ለመሆኑ
እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት ?

ብዙ ጊዜ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን አንሥቶ ለውይይት ማቅረብ በብዙኃኑ ዘንድ ሳያስተች አይቀርም፡፡ በአንዳንዶችም ዘንድ እንደ አክራሪነት እና ጠባብነት ያስቆጥር ይሆናል፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያው ላደረገ ሰው በሃይማኖት ወይም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚነሡ የብዙኃን አሳቦች እንዳሉ ቢያውቅና ቢያክብርም ፤ እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ግን አንዲት እንደሆነች የሚጠፋበት አይመስለንም፡፡ ማንኛውም ክርስቲያን ትርጉሙ በተዛባ የዓለም የእኩልነት ስብከት ተውጦ ትክክለኛውን የሃይማኖትን ትውፊታዊ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን ትምህርት ሊያፋልስ አይገባውም፡፡ በሌላ የትምህርት እና የእምነት ጎዳና ላይ ያሉ ወገኖችን ምርጫቸውን ማክበር እና ሁሉም ትክክል ናቸው ብሎ መቀበል ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በሁለቱ ሐሳቦች መካከል ያለውን ሰፊ የልዩነት መስመር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ‹እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ማን ናት?› ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሾች ሁለት መልክ ያላቸው ናቸው፡፡ አንደኛው በዓለም ላይ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የእምነት ተቋማት ሲኖሩ፣ በሁሉም ዘንድ ያለው ተመሳሳይ ስብከት ‹ትክክለኛው ሃይማኖት እኔ ነኝ!› የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ወደ ያዙት እምነት በማዘንበል እኔ ልክ ነኝ ስለሚሉ የትኛው ትክክለኛ እንደሆነች ከዚህ ሁሉ ለይቶ ለማወቅ ይከብዳል፡፡ በመሆኑም ‹እውነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን ማወቅ አይቻልም!› የሚለው ነው፡፡ ይህን አስተያየት ቀመራዊ በሆነ መንገድ ከገለጽነው የዚህ የሐሳብ ንድፍ ‹Nihilism› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም አስተሳሰብ እውነትን ለማወቅ የሚደረግ ጉዞን የሚያደናቅፍና የወንጌላዊነትንም ሥራ የሚያቀዘቅዝ ነው፡፡

ሁለተኛው መልክ ደግሞ "ሃይማኖትን (ቤተ ክርስቲያንን) አንዲት የሚያደርጓት የተወሰኑ ነጥቦች ናቸው፡፡ ቢያንስ እነርሱን አሟልተው የተገኙት የእምነት ተቋማት እንደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሊቆጠሩ ይችላሉ" የሚለው ነው፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ዝንባሌ ለብዙ በተሰነጣጠቁትና ‹Branch Theory› የሚል ትምህርት ባላቸው በፕሮቴስታንቱ ዓለም አይሎ ይንጸባረቃል፡፡ ንድፈ አሳቡም ‹Minimalism› ይሰኛል፡፡ በዚህ የአሳብ መስመር የሚገኙ ወንድሞቻችን ግን ሊያስተውሉት የሚገባው ነገር እነዚያ ጥቂት የሚባሉትን ተመሳሳይ የእምነት ትምህርት ዝርዝሮች ምን ምን እንደሆኑ የሚያጸድቀው የትኛው ባለ ሥልጣን እንደሆነ ነው፡፡

በእኛም (በኦርቶዶክሳውያንም) ወገን ካሉ ጸሐፊዎችም ቢሆን አልፎ አልፎ ከእነዚህ ከሁለቱ አስተሳሰቦች በአንዱ ላይ የሚወድቅ ለዘብተኛ አስተያየት ሲሰጥ እናያለን፡፡ ለምሳሌ ቀደም ባለው ጊዜ ባዘጋጇቸው እምነታዊ እና ፍልስፍና ነክ የሆኑ መጻሕፍቶቻቸው የምናውቃቸው ልዑል ራስ ካሳን እናንሣ፡፡ እኚህ የአገር ሊቅ ‹ፍኖተ አእምሮ› በተባለ ብዙ ቁም ነገሮችን ባካፈሉበት ድርስታቸው ላይ ‹ስለ ሃይማኖት ልክ› ብለው በሰየሙት ምዕራፍ ስር ያሳዩት ዛነፍ ያለ የግል አመለካከት አለ፡፡ ይኸውም በልዩ ልዩ እምነት ውስጥ ሆነው የሚሟገቱትን ሰዎች ‹ከሩቅ ባዩት በአንድ የጌታቸው መልክ እንደሚከራከሩ አገልጋዮች› ይመስሏቸዋል፡፡ በዚህም ምሳሌያቸው ውስጥ የሚገኘው አደገኛው መልእክት የቤተ ክርስቲያንን አንዲትነት በሚሽር መልኩ የተላለፈው ‹ሁሉም እምነት የሚጠራው ጌታ አንድ ነው!› የሚለው ሐሳብ ነው፡፡ ሁሉም ከእርሳቸው መጽሐፍ ያገኙት ነው ባይባልም ትምህርቱ ግን ብዙዎችን ‘እኛም ጋር የምንጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ እነርሱም ጋር የሚጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው!’ ለሚል ጎዶሎ አስተሳሰብ ሳይዳርግ አልቀረም። ቅዱስ ጳውሎስ ግን የስም መመሳሰሉ እንደ ማዕበል እየገፋ እንዳይወስደን በቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በሌላ ስፍራ የሚጠራ እኛ ከምንሰብከው እና ከምናመልከው ኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ ‘ሌላ ኢየሱስ’ እንዳለ በመንገር ያስጠነቅቀናል።(2ኛ ቆሮ 11፥4) በመጨረሻም እኒሁ ሊቅ ይህ የተሳሳተ ምልከታቸውን ሲያጠቃልሉ «ሀልዎቱን የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ምንም እርስ በርሳቸው መናፍቅ እየተባባሉ ቢነቃቀፉም ሁሉም በያዙት ሃይማኖት በእግዚአብሔር ስም እየጸለዩ ተአምራትን ለመሥራት የሚችሉ መሆናቸውን አስተውል፡፡› ይላሉ (ፍኖተ አእምሮ ፣ገጽ 17)፡፡

የሃይማኖት ትክክለኛነት እንዴት በተአምር ሚዛንነት ሊለካ ይችላል ? ተአምርስ የሚያደርግ ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለመሆኑ ‘ተአምሩ’ ብቻውን ማስረጃ ይሆናልን? በርግጥ አምላካችን እግዚአብሔር "የማይመረመረውን ታላቅ ነገር ፤ የማይቆጠረውንም ተአምራት" የሚያደርግ አምላክ ነው፡፡(ኢዮ 9፡10) ተአምሩም ከሐሰት የራቀና ‹ተአምራቱ እንዴት ድንቅ ነው፤ ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው!› ተብሎ የሚያስመሰግነው እውነተኛ ነው፡፡(ዳን 4፡3) ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሱ ሌላም ከፈጣሪ ውጪ የሚፈጸም ሰይጣናዊ የማጭበርበር ተአምር እንዳለ በሙሴ ዘመን ከነበሩት ኢያኔስና ኢያንበሬስ ጀምሮ በሐዋርያት ዘመን እስከ ነበረው ጠንቋዩ ናዖስ ድረስ በመዘርዘር ይናገራል፡፡(2ኛጢሞ 3፡8) ስለዚህ ሐሰታዊ ተአምርና ፈውስ በሰይጣንም ሊደረግ ስለሚችል ተአምርን መነሻ ምክንያት አድርገን የቤተ ክርስቲያንን አንዲትነት አንጠረጥርም።

በጉባዔ ኒቅያ በረቀቀው ጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ ከተገለጹት የቤተ ክርስቲያን ባሕርያት መካከል አንዱ ‹አሐቲነት›/‹አንዲትነት› /‹Oneness› ነው፡፡ ‹አንዲትነት› ለዘመናት ሁሉ የማይቀየር የእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን መለያ ጠባይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ጌታ ፣ ስለ ሃይማኖትና ስለ ጥምቀት ባስተማረበት ክፍል በመጀመሪያ ‹አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ› በማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን አንዲትነት ይመሰክራል፡፡(ኤፌ 4፡4-5) መቼም ማንም ሐዋርያው “አንድ አካል” ያለው ቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን እግዚብሔርን ነው ወደሚል ሙግት እንደማይገባ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአካል ሦስትነት እንጂ አንድነት ስለሌለው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን በእውነት የሚመራት መንፈስ ቅዱስ አንድ እንደሆነ ፤ በመንፈስ ቅዱስም የምትመራዋ የክርስቶስ አካል እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ናት፡፡
እረኛ የሆነ መድኃኒታችንም ከበረት ስለወጡ በጎቹ እነርሱን ፍለጋ እንደሚወጣ ‹ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ› በማለት የተናገረው ቃል ለቤተ ክርስቲያን አሐቲነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡(ዮሐ 10፡16) ልብ በሉ ጌታችን ከበረቱ ስለወጡት በጎች ሲናገር ‹ከዚህ በረት የወጡ በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል› አለ እንጂ ‹ባሉበት ቦታ ላደራጃቸው ይገባኛል› አላለም፡፡ በረቷ አንድ ፣እረኛውም አንድ ስለሆነ የጠፉት በጎች ወደ በረቷ ይመጣሉ እንጂ ባሉበት ሥፍራ ሌላ በረት ሊሠራላቸው አይችልም።

የነገረ ቤተ ክርስቲያን ሊቁ ቅዱስ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያንን አንዲትነትን ሊረሱ በማይችሉ ሁለት ምስል ከሳች ምሳሌዎች ያስተምረናል፡፡ የመጀመሪያው ምሳሌ ‹እርሱም (ክርስቶስም) የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው› በማለት የራስንና የአካልን ግንኙነት በማንሣት በዚህ አንጻር ክርስቶስን በራስ ፣ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ በአካል ወክሎ ያቀረበበት ነው (ቆላ 1፡18)፡፡ እንደሚታወቀው ልማዳዊ የሆነውን የተፈጥሮ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ የተዋቀረ የሰው አካል ሊኖረው የሚችለው ራስ አንድ ሲሆን፣ አንድ ራስም አንድ አካል ብቻ ነው የሚያስተዳድረው፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ራሷ ክርስቶስ አንድ ሲሆን በእርሱም የምትመራዋ አካሉ የተሰኘች እውነኛይቱ ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ናት፡፡ ስለሆነም ብዙ አካል አንድ ራስ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ያልተለመደ እና ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ እንደሆነ፣ በብዙ "አብያተ ክርስቲያን"ም ዘንድ አንዱ ራስ ክርስቶስ ይገኛል ብሎ ማሰብም ሆነ ማስተማር ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መውጣትና ከተለመደውም የቀደምት አበው ትምህርት ማፈንገጥ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ቅዱስ አትናቴዎስ ‹በእንተ ተሠግዎተ ቃለ እግዚአብሔር› /‹On the Incarnation› በተሰኘ ድርሰቱ ላይ የቤተ ክርስቲያንን አንዲትነት ክርስቶስ በመስቀል ከመሞቱ ጋር አያይዞ ያስተምራል፡፡ ይኸውም መድኃኔዓለም ክርስቶስ በሰይፍ አንገቱን ተመትሮ ወይም በእሳት ተቃጥሎ ቢሞት ኖሮ ከሰውነቱ ሕዋሳት የሚጎድል ወይም የሚጠፋ በኖረ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሕዋሳቱ አንዱም ሳይጎድል ከአጥንቱም አንዲቱ ሳትሰበር አካሉን ጠብቆ በመስቀል መሞቱ ፤ የአካሉ የቤተ ክርስቲያንን አንዲትነት እንደጠበቀ ያሳያል ይለናል፡፡

ሁለተኛው ማስረጃው ደግሞ በባልና ሚስት ምሳሌነት (Husband-wife analogy) የሚያስተምረው ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ስለ ክርስቶስ ‹ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው› ሲል እንደተናገረ ሐዋርያው ሙሽራውን በክርስቶስ ፣ሙሽራይቱን በቤተ ክርስቲያን ይመስላል (ዮሐ 3፡29 ፣ኤፌ 5፡23)፡፡ አንድ ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን ዕውቅና የሚሰጠው ምሥጢሩ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል እስከ ተፈጸመ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ይህንንም አምላካዊ ትምህርት በመያዝ አንድ ለሆነው ሙሽራ ታጭታ የቀረበችው ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ብቻ እንደሆነች ያስረዳናል፡፡

ቅዱስ ቆጵርያኖስም ‘On the Unity of the Church’ በተባለ ድርሰቱ ቤተ ክርስቲያንን ባልተቆራረጠችና ስፌት በሌለባት ወጥ የክርስቶስ ቀሚስ መስሎ ያተምራል። ስለዚህም የክርስቶስ ቤተ ክርቲያኑ በትምህርቶች ልዩነት ያልተበጫጨቀችና በተመረጡ ጥቂት የእምነት አቋሞች ክርነትም የማትሰፋ ናት። ይኸውም ቅዱስ ቀጠል አድርጎ እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን አንዲት በመሆኗ መዳንን የሚሹ ሁሉ ወደዚህ በረት እንዲገቡ በማሳሰብ ‘ከቤተ ክርስቲያን ውጪ መዳን የለም’ እያለ ይሰብካል።

በስተመጨረሻም የቤተ ክርስቲያንን አንዲትነት ባምንም እንኳን ትክክለኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የትኛዋ እንደሆነች በምን ላውቅ እችላለሁ? ሲሉ ለሚጠይቁን ቅን ወገኖቻችን የሚሆን መልስ ተናግረን ጽሑፋችን እንፈጽም። አንድ ሰው ትክክለኛይቱ ቤተ ክርስቲያን (ሃይማኖት) ማን እንደሆነች ለማወቅ ከፈለገ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነውን ቅዱስ ይሁዳን ሊጠይቀው ይችላል። ቅዱስ ይሁዳ አንድ ምዕራፍ ባለው አጭር መልእክቱ ላይ ስለ ትክክለኛይቱ ቤተ ክርስቲያን መለያዎች ጽፎልናል። ምን አለ? «ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ…» አለ። በዚህ ንግግር ውስጥ ለቅዱሳን የሚለው በትክክለኛይቱ ሃይማኖት ውስጥ ‘አማልዱን’ ተብለው የሚለመኑ ቅዱሳን፣ አንድ ጊዜ – የሚለው ደግሞ ሃይማኖት አማራጭ የሌላት አንዲት እና አንድ ጊዜ ብቻ የምትሰጥ መሆኗን፣ ፈጽሞ ስለተሰጠ – ሲል ሃይማኖት ወይም ቤተ ክርስቲያን ፍጽምና ያላትና ምንም ዓይነት ማሟያ እንዳስፈልጋት ተደርጎ በምልዓት መሰጠቷን እንዲሁም፣ ሃይማኖት የሰው ልጅ በጠረጴዛ ዙሪያ ተስብስቦ በሚያደርገው ስምምነት የምትገኝ ሳይሆን የፈጣሪ ስጦታ መሆኗን ፣ እንድትጋደሉ -የሚለው ደግሞ በእውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ "ተጋደሉ፣ መልካም ሥሩ" የሚሉ ትምህርቶች እንዳሉ ገልጧል። ስለዚህ እነዚህን በሐዋርያው ንግግር ውስጥ የተዘረዘሩትን ነጥቦች እንደ መስፈርት በመቁጠር በአካባቢያችን ያሉትን እምነቶች መመዘን እና ወደ ትክክለኝይቱም ሃይማኖት በንጹሕ ኅሊና መድረስ እንችላለን።

ሌላው በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ሊቁ ጠርጠሉስ (Tertullian) የአንድን ሃይማኖት ወይም ቤተ ክርስቲያን እውነተኛነት ለማወቅ የሚረዱ ሁለት መስፈርቶችን ይጠቁመናል። ከእነዚህ ከሁለቱ መስፈርቶች አንደኛው በተለይ በክህነቱ “ተላውያነ ሐዋርያት – የሐዋርያት ተከታይ” /(Apostolic sucession) መሆን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከ“ቀደምት አበው ትምህርት”/ (Early Church Fathers Teaching) አለማፈንገጥ ነው። ብዙዎቹን እምነቶች በመጀመሪያው መስፈርት ስንመዝናቸው ከአንድ እምነት በቀር ሌሎቹን ውድቅ ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህችውም እምነት የካቶሊክ እምነት ነች። የካቶሊክን የክህነት ሰንሰለት ወደ ላይ እንቁጠር ብንል መጨረሻ ላይ የምናገኘው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ነው። ታዲያ የካቶሊክን እምነት ልክ ነው ብለን እንቀበል? አይደለም!። መስፈርቱ መቼ አለቀና ወደ ሁለተኛው ሚዛን እንዲወጣ ይደረጋል። የካቶሊክን እምነት በሁለተኛው መስፈርት ሚዛንነት ስንለካው ግን ያነሰ ሆኖ እናገኘዋለን። ሁለተኛው መስፈርት የሚለው የትኛውም በቤተ ክርስቲያን የሚሰጥ ትምህርት ሐዋርያት እና ሐዋርያውያን አበው እንዲሁም ቀደምት አባቶች ካስተማሩት ትምህርት ጋር የሚጋጭና አዲስ ስብከት መሆን የለበትም ነው። በመሆኑም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ በጨመረቻቸው እንደ immaculate conception ፣ pope infallibility በተሰኙ በቀደምት አበው ትምህርት ውስጥ በሌሉ አዳዲስ ትምህርቶቿ ከትክክለኛው መንገድ እየራቀች ሄዳለች።

ከላይ ባነሣናቸው መስፈርቶች ሁሉ ስትለካ ሚዛኗን ጠብቃ የምናገኛት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ነው። ስለዚህ አንድ ሰው በተሰጠው የማመዛዘን አቅም ተጠቅሞ እነዚህን ማመሳከሪያዎች በመያዝ በእግዚአብሔር እርዳታ ወደ ቀጥተኛና እውነተኛይቱ መንገድ ሊመጣ ይችላል። በቅንነት ቢያደርገው!!!

እኛንም የዚህች ቤተ ክርስቲያን ልጆች ያደረገን አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን!


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
ቤተ ክርስቲያን ታመሰግንሻለች!!!

"ያዘነች ስትሆን በልጅሽ በወዳጅሽ ትንሣኤ የተጽናናችው፡፡ የተዋረደች ስትሆን በድንግልናሽ ቡቃያ መውጣት ከፍ ከፍ ያለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታመሰግንሻለች፡፡ በዕለተ ዓርብ ከልጅሽ ቀኝ በፈሰሰው ውሀ ተጠምቃ የውግታቱን ደም ተቀብታ ቅድስት ቤተክርስቲያን ታመሰግንሻለች። የልዑል እግዚአብሔር በግ የተባለ ልጅሽ ዐማኑኤልየተሞሸረባት መርዓዊ ሰማያዊ የተባለባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታመሰግንሻለች"

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

እንኳን እመቤታችን ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ "አባቴ እንጦንስ ውጣ ይልሃል"+++

በቤተ ክርስቲያናችን "ጳውሊ" በሚል ስም የሚታወቁ ከአንድ በላይ ቅዱሳን አሉ። ብዙዎቻችን የምናውቀው የመጀመሪያው ባሕታዊ የሆነው አባ ጳውሊን ነው። ይሁን እንጂ አስቀድሞ በሕግ (በትዳር) ተወስኖ ልጆች ወልዶ ይኖር የነበረ፣ በኋላ ግን ሚስቱን በገዛ አልጋው ከሌላ ጎልማሳ ጋር ስታመነዝር አግኝቶ ሳይቆጣ ሀብት ንብረቱን አውርሶ፣ ልጆቹን አደራ ሰጥቶ ወደ ገዳም የገባና በብዙ አመክሮ የመነኮሰ "የዋሑ አባ ጳውሊ"(Paul the simple) የሚባል ሌላም ደገኛ አባት አለ። "የዋሑ" እያሉ ይጠሩት የነበሩት ወንድሞቹ መነኮሳት ናቸው። ታሪኩንም ዜና አበውን ይመዘግብ የነበረው ጰላድዮስ "በገነተ አበው" ጽፎልናል።

ይህ ቅዱስ አባት ታላቁ መነኩሴ አባ እንጦንስ ያለበት ገዳም ውስጥ የሚኖርና የእርሱም ረዳት የነበረ ነው። አባ ጳውሊ ከምንም በላይ በትሕትና ሕይወቱ ይታወቃል። የሚገርመው እርሱ በነበረበት ገዳም ውስጥ በተጋድሎ ዘመን የሚቀድሙት ብዙ መነኮሳት ቢኖሩም፣ አባ ጳውሊ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የደረሰበት መንፈሳዊ ጸጋ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ይህ ሁሉ የሆነውም ስለ ታላቅ ትሕትናው ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን ሰዎች በክፉ መንፈስ የሚጨነቅ አንዱን ጎበዝ ይዘው ወደ ገዳሙ አበምኔት ቅዱስ እንጦንስ አመጡት። አባ እንጦንስም ይህን ታማሚ ወደ አባ ጳውሊ እንዲወስዱት አዘዛቸው። እነርሱም ሕመምተኛውን ወደ አባ ጳውሊ ባመጡት ጊዜ ቅዱሱ በትሕትና ሆኖ ይህንስ በተጋድሎው የከበረ አባቴ እንጦንስ ቢያደርግላችሁ፣ እባካችሁ ወደ እርሱ መልሱት ብሎ ለመናቸው። ተመልሰው ወደ አባ እንጦንስ ቢሄዱ፣ ዳግመኛ አባ እንጦንስ ወደ አባ ጳውሊ እንዲሄዱ ነገራቸው። በኋላም እነዚያ ሰዎች በጋኔን የተያዘውን ሰው ወደ አባ ጳውሊ አቅርበው ቅዱስ እንጦንስ በጥብቅ እንደ መራቸው ነገሩት። አባ ጳውሊም አይሆንም ብሎ አይቃወም ነገር የአባት ትእዛዝ ሆነበት፣ ስለዚህ ነገሩን ተቀበለና ቀስ ብሎ ወደ ታማሚው በትሕትና ተጠግቶ ክፉውን መንፈስ "አባቴ እንጦንስ ውጣ ይልሃል!" አለው። ጋኔኑ ግን ከትሕትናው ቃል የተነሣ የፈራው ስለመሰለው "እንጦንስ ማን ነው?" እያለ ፎከረ።

በዚህ ወቅት አባ ጳውሊ ጊዜው ቀትር ስለ ነበር ከአጠገቡ ባለ የጋለ ዐለት ላይ ባዶ እግሩን በመውጣት "ሕያው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፣ ይህ ጋኔን ካልወጣ ከዚህ አልወርድም" ብሎ ከፈጣሪው ጋር በጸሎት ይነጋገር ጀመር። ክፉው መንፈስ የአባ ጳውሊን ጸሎት ሊያስተጓጉል ብዙ የስድብ ቃላት ይናገር ነበር። ቅዱሱ ግን አንዲትም ቃል ሳይመልስለት ጸሎቱን ቀጠለ። ያም ጋኔን ተሸንፎ ከዚያ ሰው ሰውነት ውስጥ በዘንዶ አምሳል በመውጣት በአካባቢው ወደ ነበረው ባሕር ውስጥ ገብቷል።

አባ ጳውሊ የዋሕ በስንክሳራችን ሰኔ 22 ቀን መታሰቢያው ይደረጋል። እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን።

========ወደ አባቶቻችን ጥበብ እንመለስ======

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
ቅዱስ ባስልዮስ "ሰውነታችን ያለ እስትንፋስ መኖር እንደማይችል፣ ነፍሳችንም ፈጣሪዋን ሳታውቅ ሕያው ሆና ልትኖር አትችልም። የነፍስ ሞቷ እግዚአብሔርን አለማወቋ ነውና" ይለናል፣ እውነት ነው፤ ለመሆኑ እግዚአብሔርን ማወቅ ምን ማለት ነው?

እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት ስለ እርሱ የተጻፉ መጻሕፍትንና የተነገሩ ትምህርቶችን ማንበብ፣ መስማት ብቻ አይደለም። እነዚህ ብቻቸውን "ስለ እግዚአብሔር እንድናውቅ" እንጂ "እግዚአብሔርን እንድናውቀው" አያደርጉንም። "ስለ እግዚአብሔር ማወቅ" የመጨረሻው ዓላማችን ወደ ሆነው "እግዚአብሔርን የማወቅ ሕይወት" የምንገሰግስበት መንገድ እንጂ ራሱን ችሎ መዳረሻና ማረፊያ ወደብ አይደለም።

"እግዚአብሔርን ማወቅ" በተግባር የሚገለጥና ከፈጣሪ ጋር የምናደርገው የአንድነት ሕይወት ነው። እኛ በእርሱ፣ እርሱም በእኛ የሚኖርበት ልዩ ምሥጢራዊ ውሕደት ነው። "እግዚአብሔርን ማወቅ" ማለት ስለ እርሱ ሲነገር በጆሮ የሰሙለትን አምላክ ከብቃት ደርሶ ማየትና በፍጹም ልብ መውደድ ነው። ይህ ደግሞ ራሱ ጌታችን በወንጌል እንደተናገረው የዘላለም ሕይወት ነው።(ዮሐ 17፥3)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++‹‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም›› ሉቃ 6፡37+++

ብዙ ጊዜ ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማን ከምንሠራቸው ኃጢአቶች መካከል አንዱ ‹‹በሌሎች ላይ መፍረድ›› ነው፡፡ ደግሞ ነገሩን ከባድ የሚያደርገው የምንፈርድባቸው የወንድሞቻችንን ውድቀት በዓይናችን ማየታችን በጆሯችን መስማታችን ነው፡፡ ያዩትን አይተው፣ የሰሙትን ሰምተው ሲጨርሱ ወዲያው አለመፍረድ እንደ ተራራ የረጋ ትልቅ ሰብዕናን ይፈልጋል፡፡ ትሑት የሆነ ሰው የሌሎች ሰዎችን ድክመት ለማየት የሚገለጥ ዓይን የለውም፡፡ ዘወትር ራሱን እየመረመረ ድክመቶቹን በመቁጠር ላይ ይጠመዳል፡፡ ዓይኖቹም እንደ አሸዋ በበዛው በገዛ ኃጢአቱ ላይ ብቻ ናቸው፡፡ ደግሞ ወደ ሌላው ከተመለከቱ ሊያመሰግኑ እና ሊራሩ እንጂ ሊንቁና ሊፈርዱ አይደለም፡፡

በወንድሞች ላይ መፍረድ የእግዚአብሔር የሆነውን የጌትነቱን ንብረት እንደ መስረቅ፣ በክርስቶስም የፍርድ ዙፋን ላይ ራስን እንደማስቀመጥ ይቆጠራል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ድፍረት፣ ከዚህ የሚበልጥ ኃጢአትስ ከየት ይገኛል? አበው ‹ሌሎች ላይ መፍረድ› የትዕቢት ታማኝ ልጅ ሲሆን፣ መጋቢና አሳዳጊውም እርሱው (ትዕቢት) እንደ ሆነ ይናገራሉ፡፡ ራስን መውደድ እና በራስ አስተዋይነት ላይ መደገፍ ሌላው ላይ ጨክኖ ከመፍረድ እንደሚያደርስም ያስተምራሉ፡፡ በርግጥ በሌሎች መፍረድ የሚወድ ሰው ‹‹ክፉ ሲደረግ ተመልክቼ ማለፍ አልችልም!›› እያለ ለከሳሽነቱ ምክንያት ይደረድር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በሰዎች ላይ የመፍረድ ኃጢአት ምንጩ የሌሎች ደካማ ምግባር ሳይሆን የተመልካቹ (የፈራጁ) የልብ ክፋት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የልብ ቅንነቱ ቢኖርማ በተሳሳተ ወንድሙ ፊት ቆሞ ወይ የራሱን ድክመት እያሰበ የሚያለቅስ፣ አልያም ደግሞ ለወደቀው ወንድሙ እየራራ የሚመክርና የሚጸልይ ይሆን ነበር፡፡

በሌሎች መፍረድና አቃቂር ማውጣት የለመደ ሰው ዓለሙ ሁሉ በእርሱ ፊት ሞኝ ሆኖ ይታየዋል፡፡ ሰው ሁሉ አስተዋይነት በጠፋበት ሰፊ ጎዳና ሲርመሰመስ፣ እርሱ ግን ከፍ ካለው የብስለት ሰገነት ላይ እንደ ቆመ ስለሚሰማው፣ ቁልቁል እያየ የሚሰጠው እርማትና የትዝብት እይታው አይጣል ነው፡፡ ፈራጅ ‹እኔ ተሳስቼ ይሆን?› የሚል ትሑት ሕሊና የለውም፡፡ ልክ በአገጩ ላይ ያለው ሪዝ (ጽሕም) ከመቆሸሹ የተነሣ በፈጠረው መጥፎ ጠረን በሄደበት ሁሉ አፍንጫው ሲረበሽ (መጥፎ ጠረን ሲሸተው) ‹ዓለሙ ሁሉ ሸቷል› እንዳለው ሰው፣ በራሱ ድክመት ምክንያት በተፈጠረበት የእይታ መንሸዋረር ሁሉን ሲተች በሁሉ ሲፈርድ ይኖራል፡፡ የሥነ ልቡና ሳይንሱም እንደሚናገረው አንዳንድ ጊዜ በራስ ውስጥ ያለ የዕውቀት እና የልምድ ክምችት እያነሰ ሲመጣ፣ በሰው ፊት ዝቅ ብሎ ላለመታየት ሲባል በሁሉን ፈራጅና ነቃፊነት መጋረጃ ራሳችንን ልንከልል እንሞክራለን። ይህም አንዱ የሰብዕና መቃወስ (personality disorder) ምልክት ነው።

ቅዱስ አንስታስዮስ ዘሲና ‹‹ማንም ላይ አለመፍረድ››ን በተመለከተ በአንድ ወቅት በገዳሙ ይኖር ስለ ነበረ ደግ መነኩሴ ታሪክ የተናገረውን አንሥተን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ ይህም መነኩሴ እርሱ በሚኖርበት ገዳም እንዳሉት ሌሎች መነኮሳት ከፍ ያለ ትጋት አልነበረውም፡፡ ታዲያ የሚሞትበት ቀን ደርሶ በአልጋው ላይ ሳለ ከሞት ፍርሐት ይልቅ በፊቱ ላይ የሚነበበው ታላቅ ደስታ ነበር፡፡ በሁኔታው የተገረሙት በዙሪያው የተቀመጡ መነኮሳትም ‹‹ወንድማችን ሆይ! ሕይወትህን በስንፍና (ትጋት ሳታበዛ) እንዳሳለፍክ እናውቃለን፡፡ አንተስ ይህን ስታውቅ በዚህ በመጨረሻው ሰዓት ስለ ምን ደስተኛ ሆንክ? ምሥጢሩን ልናውቅ አልተቻለንም›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ ያም ደግ መነኩሴ ‹‹አዎን! ክቡራን አባቶቼ! ሕይወቴን ሁሉ በስንፍና እና በእንቅልፍ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ነገር ግን አሁን በዚህች ሰዓት መላእክት መነኩሴ ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ የሠራኋቸው ሥራዎች ሁሉ የተመዘገቡበትን አንድ መጽሐፍ አምጥተውልኛል፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ስመለከት በማንም ላይ እንዳልፈረድኩ፣ ማንንም እንዳልጠላኹ፣ በማንም እንዳልተቆጣኹ ተረዳኹ፡፡ ስለዚህም ‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም› የሚለው የጌታዬ ቃል በእኔ ላይ እንደሚፈጸም ተስፋ አደረኩ፡፡ በዚህም ቅጽበት ይህችን ትንሽ ሕግ ስለፈጸምኩ ሌላው ሁሉ የዕዳ ጽሕፈቶቼ ተቀደዱልኝ›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከተናገረ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡ መነኮሳቱም በምክሩ ተምረው የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነቁ በምሥጋና ቀበሩት፡፡

በእውነትም ‹‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁም›› የሚለው የመድኃኒታችን ቃል በዚህ ታሪክ ውስጥ ትክክለኛ ትርጉሙን አግኝቷል፡፡ በወንድሞች ድክመት አለመሳለቅና በውድቀታቸው አለመፍረድ ወደ ዘላለማዊው እሳት ከመጣል ያድናል፡፡

+++እግዚአብሔር በሰው ያልፈረዱ ቅዱሳን ካሉበት ገነት በቸርነቱ ያግባን!+++

ጥፋት ባጠፋ መነኩሴ ላይ እንዲፈርድበት ሲጠራ በሚያፈስ ጆንያ አሸዋ ተሸክሞ ወደ ጉባኤው በመግባት "የሠራኋቸው ኃጢአቶች ከኋላዬ ቢከተሉኝም እኔ ግን አላየኋቸውም። ይኸው ዛሬ ደግሞ በሌላ ሰው በደል ልፈርድ እዚህ መጥቻለሁ" ሲል ተናግሮ ወንድሞቹን ከፈራጅነት ነጻ ያወጣ የቅዱስ ሙሴ ጸሊም በዓለ ዕረፍት ዛሬ ይከበራል። እንኳን አደረሳችሁ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ "ወደ ሰማይ መውጫ መሰላሎች" +++

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጸሙ ምሥጢራት እንዲሁ ወግ ለመጠበቅና ለመታሰቢያ የሚደረጉ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከድኅነታችን ጋር እጅግ በጣም የጠበቀ ቁርኝነት ስላላቸው ነው፡፡ ምሥጢራት በኃይለ መንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጥልቅ መንፈሳዊ ተሐድሶ የሚተላለፍባቸው ረቂቅ ቧንቧዎች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ጸጋ የማይቃወሙ ኃጥአን ከገቡበት የኃጢአት ጉድጓድ ዳግመኛ የሚወጡባቸው መሰላል ናቸው፡፡ እነዚህ ምሥጢራት የማዳን ኃይላቸውን ያገኙት በወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የሚፈጸሙ ምሥጢራት ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምሥጢራት ጸጋ የተጓደለባቸው ስለነበሩ ፍጹም የነፍስ ድኅነትን ማሰጠት አልቻሉም፡፡ እንደ ምሳሌ እንደ ጥላ አገለገሉ እንጂ።

‹ጸጋንና እውነትን ተመልቶ› በእኛ ያደረ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነቱን ሥራ በመስቀል ከፈጸመ በኋላ ግን ለምሥጢራት መክበር ምክንያት የሆነው መንፈስ ቅዱስ ተሰጠን፡፡ ከክርስቶስ ሞት በፊት እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ጠላቶች ነበርን፡፡(ሮሜ 5፡10) መለኰታዊው ደም ከመፍሰሱ አስቀድሞም ዕርቅ እንዳልወረደ፣ መንፈስ ቅዱስም እንዳልተሰጠ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሲገልጽ ‹ክርስቶስ ገና አልከበረምና (አልተሰቀለምና) መንፈስ ቅዱስ አልተሰጠም ነበር› ይላል፡፡(ዮሐ 7፡39) አሁን ግን የዕርቁ ሥራ በመፈጸሙ ምሥጢራትን የሚያከብር፣ የሚለውጥ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት ይወርዳል፡፡ ስለዚህም ‹ሚ መጠን ግርምት ዛቲ ዕለት ወእጽብት ዛቲ ሰዓት እንተ ባቲ ይወርድ መንፈስ ቅዱስ እመልዕልተ ሰማያት› - ‹ይህች ዕለት እንደ ምን ያለች የምታስፈራ ዕለት ናት፤ ይህችስ ሰዓት ምን ያህል የምታስጨንቅ ናት፤ መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት…› እያልን ዘወትር በቅዳሴ እናደንቃለን፡፡

ታዲያ እነዚህ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የሚከብሩት ምሥጢራት ትልቁ አገልግሎታቸው ነፍሳችንን ማንጻትና ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ማድረግ ነው፡፡ ይህም መዳን ይባላል፡፡ ብዙዎች በየጎዳናው ‹ኢየሱስ ያድናል!› እያሉ በስሜት ሲናገሩ እንሰማቸዋለን፡፡ እንዴት እንደሚያድነን ግን ዘርዝረው አያስተምሩንም፡፡ ‹ጌታን ተቀበሉ›ም እያሉ ይሰብኩናል፡፡ እንዴት እንደምንቀበለው ግን መንገዱን አያሳዩንም፡፡ ማቀበያውም የላቸውም። ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያድነን ብቻ ሳይሆን የሚያድንበትንም አቅጣጫ ታሳያለች፣ ክርስቶስን ስለመቀበል ብቻ ሳይሆን የምንቀበልበትን መንገድ ትመራናለች፣ ታቀብለናለች። የክርስቶስ የማዳን ሥራው መገለጫዎች የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ናቸው፡፡

ምሥጢራት ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ እና ከእርሱም ጋር ለመኖር በሚያስፈልጉ እንደ ጸሎትና ቃለ እግዚአብሔር ባሉ መንፈሳዊ ተግባራትም ሊተካ አይችልም፡፡ ራሱን ችሎ ሊኖር የሚገባው የክርስትና ዐምድ (ምሰሶ) ነው እንጂ፡፡ ጸሎትን ለማያስታጉል ፣እጅግም ምጽዋት ለሚያደርግ መቶ አለቃው ቆርኔሌዎስ የእግዚአብሔር መልአክ ‹ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረገ› ሲል የተናገረውን እስኪ እናስተውል። መልአኩ ‹ጸሎትህና ምጽዋትህ አድኖሃል› አላለውም፡፡ ነገር ግን ጸሎቱ እና ምጽዋቱ እግዚአብሔር በምሕረት እንዲያስበው ምክንያት ሆነውታል፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ከአገልጋዮቹ አንዱን ልኮ ቅዱስ ጴጥሮስን እንዲያስጠራውና እርሱም ወደፊት ሊያደርግ የሚገባውን እንደሚነግረው አስረዳው፡፡ ስለዚህ ከጸሎት፣ ከምጽዋት በኋላ ግድ ማድረግ የሚገባ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ግድ ባይሆን ኖሮ ‹ጸሎትህና ምጽዋትህ አድነውሃል፤ በዚሁ ቀጥል!!!› ሲል ብቻ ባበረታታው ነበር፡፡ እንደዚህ ግን አላለውም፡፡ ምክንያቱም እስከ አሁን ቆርኔሌዎስ ያደረጋቸው ምግባራት ድኅነትን እንዲቀበል አዘጋጁት እንጂ ብቻቸውን መዳኛ አልሆኑለትም፡፡ ታዲያ ከጸሎት እና ከምጽዋት በኋላ ሊያደርገው የሚገባው ነገር ምንድር ነው? ካላችሁ ተምሮ መጠመቅ ወይም ምሥጢራትን መፈጸም ነው፡፡ ካህኑ ቅዱስ ጴጥሮስም የተፈለገበት ምክንያት ምሥጢራትን እንዲፈጽምለት ነበር፡፡(ሐዋ 10፡1-48)

የእግዚአብሔርን ቃል መማር መልካም ነው፡፡ እንደ ልድያ ልቡናን ለእምነት ያነሣሣልና፡፡(ሐዋ 16፡14) ነገር ግን ምሥጢራት ካልታከሉበት ቃሉ ፍሬ አልባ ሆኖ ይቀራል፡፡ መንፈሳዊውን ዕውቀት ደጅ የሚጠና፣ መጻሕፍትንም እየከፈተ ልቡናውን በትርጓሜ የሚያቃጥል ቢሆን እንኳ ከምሥጢራቱ እስካልተካፈለ ድረስ ክርስቶስ ይህንን ሰው በአካሉ ሕዋስነት አያውቀውም፡፡ ቃለ እግዚአብሔር የሚሰማ ወይም የሚያነብ ሰው በቃሉ ተጽዕኖ ሥር ወድቆ ለውጥ የሚያመጣው ከረድኤተ እግዚአብሔር በተጨማሪ በእነዚህ በሁለት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡ ይኸውም አንደኛው እንደ ሰባኪው ወይም ጸሐፊው ክህሎት፣ ሁለተኛው ደግሞ ሰሚው ወይም አንባቢው እንዳለው የመረዳት አቅም ነው፡፡ የምሥጢራት ውጤታማነት ግን በአገልጋዮቹ ሙያ ወይም ሥነ ምግባር ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፡፡ ፈዋሽነታቸውም ፈጣን አእምሮ ላላቸው ጎበዞችም ሆነ ሕፃናተ አእምሮ ለሆንነው ለእኛም እኩል ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ምሥጢራት ከሌሎች መንፈሳዊ ተግባራት ይልቅ ብልጫ አላቸው፡፡

በመጨረሻም በትምህርትና በንባብ እንዲሁም ይህን በመሳሰሉት ሥራዎች ብቻ እግዚአብሔርን ካወቅነው ይበቃናል ለሚሉ ወንድም እኅቶቻችን አንድ ጥያቄ እናቅርብ፡፡ እነርሱ ያለ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ መንገዶች ብቻ ከሆነ ከፈጣሪያቸው ጋር መተሳሰር የሚፈልጉት፣ አንድ ግለ-ታሪክ የሚያነብ ሰው ከታሪኩ ባለቤት ጋር ከሚፈጥረው የመንፈስ ትስስር የእነርሱ በምን ይለያል?

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
"የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው" 2ኛ ሳሙ 22፥31

የመዳን ራስ ቁር የመንፈስ ሰይፍ የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ለእርስዎ ይደርስዎት ዘንድ፣ ለሌላውም እንዲያጋሩት እነዚህን መንፈሳዊ ገጻት ይውደዱ :-

የአማርኛ ገጽ

https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12/

የእንግሊዝኛ ገጽ

https://www.facebook.com/DnabelKassahunEnglish/

የአፋን ኦሮሞ ገጽ

https://www.facebook.com/Dn-Abeel-Kaasauun-Afaan-Oromoo-110724427437046/
+++‹ግመል በመርፌ ቀዳዳ›+++

ሕግ ዐዋቂ ነኝ እያለ ራሱን የሚያመጻድቅ አንድ ጎበዝ (ወጣት) ወደ አምላካችን ቀርቦ ጥያቄ ጠየቀ፡፡(ማቴ 19፥16-24) ጥያቄው ‹የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?› የሚል ነበር፡፡ ወጣቱ በርግጥም ይህን ጥያቄ የጠየቀው ስለ መልካም ነገር የዕውቀት ችግር ኖሮበት ወይም በመጽሐፍ "አድርጉ" ተብሎ ስለታዘዙት ትእዛዛት ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም፡፡ የዕውቀት ችግር እንደሌለበት በኋላ አምላካችን መልስ ሲሰጠው በተናገራት ‹ብትወድስ› በሚለው ቁልፍ ቃል ታውቋል፡፡ የዚህ ሰው የጥያቄው ምክንያት የነበረው በጊዜው ጌታችንን ብዙ ሕዝብ ይከተለው ስለነበር፣ ‹ይህ ሰው እኛ ከምናውቀው ከሙሴ ሕግ ምን የተለየ ነገር ቢያስተምር ነው? እስኪ ልፈትነው?› ከሚል ቅንነት ከጎደለው ሐሳብ የመነጨ ነበር፡፡

ጌታችንም ሲመልስለት ‹ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው› አለው፡፡ ይህ የአምላካችን ንግግር በቀላል የሚታለፍ አይደለም፡፡ በተለይ ሁሉንም ነገር አንጽራዊ በሆነ መንገድ ለምናይና የመልካምነት መለኪያው ለተዛባብን ለእኛ የሚያስተላልፈው አንዳች ቁም ነገር አለ፡፡ እስኪ አስቡት! በእኛ ዘንድ መልካም የምንለው ነገር አንድ ነውን? እንደ በለስ ቅጠል እየሰፋ ከመጣው ክፋት የተነሣ ‹ከበጣም መጥፎ ይልቅ መጥፎ ይሻላል› በሚል ትርክት፣ በጣም ከከፋው ይልቅ መለስተኛ ክፋት የሚያደርገውን ሰው ማመስገን አልጀመርንም? የመልካም ነገር ልኬታችን ተዛንፎ ብዙ መልካም ያልሆኑ እኛ ግን መልካም ብለን የምንጠራቸው በዙሪያችን አልከበቡንም? በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ፍጽምት ከሆነችው ከብቻዋ በጎነት በቀር በአጠገቧ የሚቀመጥ ለመልካም የቀረበ ተነጻጻሪ የሆነ ትንሽ ክፉነት የለም፡፡ መልካም የሆነ አንድ ነው።

ጌታም ንግግሩን ቀጠል አድርጎ ወደ ሕይወት ለመግባት ከፈለገ በሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዛት ሁሉ እንዲጠብቅ ነገረው፡፡ ጎበዙም ሰው ‹ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤ ደግሞስ የሚጎድለኝ ምንድር ነው?› ሲል ጌታን ጠየቀው፡፡ መድኃኒታችንም ‹ፍጹም ልትሆን ብትወድ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ መዝገብም በሰማይ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ› አለው፡፡ ባለጠጋው ወጣት ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ተመለሰ፡፡ ያዘነውም ከፈጣሪው ይልቅ ገንዘቡን አይብልጦ ይወድ ስለነበር ነው፡፡ ሰው ሕግጋትን ሁሉ ቢፈጽም ምጽዋትን ካላከለበት ምን ጥቅም አለው? እየጾመ እየጸለየ ነገር ግን ስለተራቡት ወንድሞቹ የማያስብ ከሆነ ወደ ሕይወት መግባቱ የሚያጠራጥር አይመስላችሁም?

ጌታችን ለዚህ ወጣት በመለሰለት መልስ ውስጥ ‹ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ› ብቻ ሳይሆን ‹መጥተህ ተከተለኝ›ም ብሎታል፡፡ ብዙ ባለጠጎች ካፈሩት ሃብት ለተቸገሩት ለመስጠት ብዙ ላያቅማሙ ይችላሉ። ለቤተ ክርስቲያንም እርዳታ ሲጠየቁ ዓይናቸውን ሳያሹ የሚሰጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ይህን ካደረጉ በኋላ ተመልሰው ክርስቶስን ለመከተል ጭንቅ የሚሆንባቸውና የሚቸገሩ ከሆነ ያስነቅፋቸዋል፡፡ ነቀፌታውም ስለሰጡ ሳይሆን ክርስቶስን ስላልተከተሉ ነው። ትእዛዙ "ስጡ" ብቻ ሳይሆን "ተከተሉኝ"ም ነው። ስለዚህ የምድር ባለጠጎች "ኑ ባሳነጻችሁት መቅደስ ቅዳሴ አስቀድሱ፤ ባስገነባችሁት አዳራሽ ቃለ እግዚአብሔር ተማሩ" ሲባሉ፣ ‹ሰጠሁ አይደል? ባለኝ ነገር ተባበርኩ አይደል? ይህ አይበቃም?› እያሉ ጥሪውን ከመግፋት መቆጠብ አለባቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ለፍጹምነት፣ ለቅድስና አያበቃምና፡፡ በስም የምናውቃቸው ብዙ ታላላቅ የዓለም ፈላስፎች ያላቸውን ገንዘብ ለድሆች ሰጥተዋል። ምድራዊውን ብልጭልጭ ነገር ስለ መናቅም እጅግ አስተምረዋል። ነገር ግን ያላቸውን ሁሉ ለድሆች ከሰጡ በኋላ ተመልሰው ክርስቶስን ስላልተከተሉ ፍጹማን (ቅዱሳን) አይባሉም።

ያ ባለጠጋ ወጣት "ሃብት ንብረትህን ለድሆች ስጥ" በሚለው ትእዛዝ ምክንያት ፊቱ በኃዘን ደምኖ ወደ ኋላው አንደተመለሰ ክርስቶስ ባየው ጊዜ ‹እውነት እላችኋለሁ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው…ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል› በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ ጌታ የባለጠጋ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት ጭንቅ መሆኑን ለምን ተናገረ? ለምንስ ካልጠፋ ነገር ግመልና የመርፌን ቀዳዳ ለምሳሌነት መረጠ? ለመጠን ለመጠን ከሆነ እነ ዝሆንና ሌሎቹም ግዙፋን እንስሳት አይሻሉም ነበር?

ጌታችን ይህን አባባል የተጠቀመው በጊዜው በእስራኤል ከነበረው ሁኔታ አንጻር ነው፡፡ የጥንቷ የእስራኤል ከተማ የራሷ ቅጥሮች የነበሯት ሲሆን ወደ ከተማይቱም የሚያስገቡ በሮች ነበሩ፡፡ እነዚህም በሮች የተለያዩ ስያሜዎች ነበሯቸው፡፡ በወቅቱ አንድ በጥንቷ የእስራኤል ከተማ ውስጥ የሚኖር ነጋዴ ከከተማዋ ውጪ ሥራውን ሲሠራ ቆይቶ ጀንበር ሲያዘቀዝቅ ወደ ከተማይቱ መመለስ ቢፈልግ፣ አብዛኛዎቹ የከተማዋ በሮች ለደኅንነት በሚል ዝግ ስለሚሆኑ የሚጠቀመው ክፍት የሆነውን አንደኛውን አማራጭ በር ብቻ ነው፡፡ ይህም በር ‹የመርፌ ዓይን›/‹The Needle’s Eye› ተብሎ ይጠራል፡፡

የመርፌ ዓይን ተብሎ የሚታወቀው በር በጣም ጠባብ ሲሆን፣ ሲነግድ ውሎ ንብረቱን በግመል ጭኖ የመጣ እስራኤላዊም በቀላሉ የሚያልፍበት አልነበረም፡፡ ባለ ግመሉ ነጋዴ በዚህ በር ለማለፍ አንደኛ ግመሏ ላይ ያለውን ጭነት ማራገፍ አለበት፣ ሁለተኛ ደግሞ ግመሏ ቆማ ማለፍ ስለማትችል ጉልበቷን ሰብራ እንድትንበረከክ በማድረግ እየገፋ በዚያ ጠባብ "የመርፌ ቀዳዳ" በተባለው በር እንድታልፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ስለዚህ ግመል ከነጭነቷ የመርፌ ቀዳዳ በተባለው በር አለማለፏን እንደ ማሳያ አድርጎ ጌታችን ለትምህርቱ የተጠቀመው ከዚሁ የጊዜው ታሪክ በመነሣት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጌታችን ‹ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል› ሲል፣ ግመል ‹የመርፌ ዓይን› በተባለው በር ለማለፍ ሸክሟን ማራገፍ፣ ጉልበቷን መስበር እንደሚጠበቅባት፣ ባለጠጋም ወደ እግዚአብሐር መንግሥት ለመግባት ያከማቸውን ሃብት ለድሆች መስጠት፣ እንዲሁም በገንዘቡ ምክንያት የሚመጣበትን የትዕቢትና የደንዳናነት ስሜት ብረከ ልቡናውን (የልብ ጉልበቱን) በመስበር በትሕትና ዝቅ ማለት አለበት ለማለት ነው፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com