Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
531 photos
44 videos
1 file
841 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
ባለፈው ስህተትህ ንስሐ ግባበት እንጂ አትብሰልሰልበት። የጴጥሮስን እንባ ትተህ በማይጠቅመው በይሁዳ ጸጸት እየተብከነከንክ ራስህን አትጉዳ። "አንተነትህ" የሚያስፈልገው ላለፈው ትላንትናህ ሳይሆን ለሚመጣው ነገህ ነው።
ወደዚህም መንደር መጥተናል ለማለት ነው፤
እንግዲህ #Subscribe #Like #Share በማድረግ ይወዳጁን።

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
+++ ሕማም የማያውቀው +++

  በአካላዊ ቅርጹ ከእንጉዳይ (የጅብ ጥላ የምንለው) ጋር የሚመሳል፣ በክብደት መጠኑ ደግሞ በአማካይ ከ1.5 ኪሎ ግራም በላይ የማይመዝን፣ ነገር ግን ባለው የሥራ ድርሻ እና በማከማቻ ቋትነቱ ከምንኖርባት ዓለም በብዙ እጥፍ የሚበልጥ እጅግ በጣም ውድ የሆነን ስጦታ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ አኑሯል፡፡ ስለዚህ ስጦታ ምንነት እና ያለውን እምቅ ኃይል ፈልጎ ለማግኘት ብዙ ምርምሮች እና ብዙ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ የሚያስገርመው ግን አጥኚውም ተጠኚውም አንድ መሆኑ ነው፡፡ ራሱን በራሱ ያጠናል፣ ከጥናቱም ባገኘው አዲስ መረጃ በራሱ ይገረማል፣ ስለ ራሱም ብዙ የጥናት ወረቀቶችን ያሳትማል፡፡ አሁንም ይህን የምታነቡትን አጭር ጽሑፍ እያደረሳችሁ ያለው እርሱ ነው፡፡ ለመሆኑ እርሱ ማነው? የዚህም ጥያቄ ጠያቂና መላሹም እርሱ ነው፡፡ ማን? የሰው ልጅ ናላ (Human Brain)

  ለዛሬ ስለዚህ እጅግ አስደናቂ ሕዋስ ምንነት ሰፊ ትንታኔ ማቅረብ ወይም ስለ ሥሪቱ መናገር የጽሑፋችን ዓላማ አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለ ሰው ልጅ ናላ ሳይንሱ ከነገረን እውነታዎች ውስጥ አንዱን ብቻ መርጠን ጥቂት ነገር ለማለት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አብዛኛው የሰውነታችን ክፍሎች የሕመምን ስሜት ተሸክመው ወደ ናላ የሚወስዱ ጥቃቅን መልእክተኞች (pain receptors) ስላሏቸው፣ አንድ ሰው እጁ አካባቢ በመርፌ ቢወጋ ቶሎ የሕመሙ ስሜት ይሰማዋል፡፡ ይሁን እንጂ ናላን (Brain) ግን ክፍት ሆኖ የማግኘት ዕድሉ ቢኖረንና በዚሁ መርፌ የላይኛውን ክፍል (Cortex) ብንወጋው እንደ ቀድሞው ተመሳሳይ የሆነ የሕማም ስሜት አይኖረንም፡፡ ምክንያቱም ናላችን የራሱን ሕመም የሚሸከሙለት መልእክተኞች (pain receptors) የሉትም። (አሁን እየተናገርን ያለነው በዋናነት ስለ ናላ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ከናላ በላይ ያለው እርሱን የሸፈነው ክርታስ (membrane) pain receptors ስላሉት የሕመም ስሜት ይፈጥራል፡፡)

   በዚህም ምክንያት የናላ ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው አንዳንድ ሕመምተኞች ንቁ ሆነው ሳለ ቀዶ ሕክምናው ሊከናወን ይችላል፡፡ በዚህም ጊዜ የትኛው የናላቸው ክፍል የበለጠ ጉዳት እንደ ደረሰበት በመሳሪያ ታግዘው ጥቆማ በማድረግና በሌላም አስፈላጊ በሆኑ መንገዶች ሐኪሞቻቸውን ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ (በቀዶ ጥገናዋ ጊዜ የእጇን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው የአዕምሮ ክፍሏ እንዳይጎ ቫዮሊን በመጫወት ሐኪሞቹን ታግዛቸው የነበረችው ዳግማር ተርነር (Dagmar Turner) የተባለች የ53 ዓመቷ ታካሚ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ናት፡፡) ይገርማል የሰው ልጅን የሕመም ስሜቶች ሁሉ የሚቆጣጠረው ሕዋስ ለራሱ ግን ሕመም ተቀባይ የለውም።

     ይሁን እንጂ ይህ ውጋት የማያውቀው፣ በሕመም ለሚገኙ የአካል ክፍሎቻችንም የሚድኑበትን እዝ የሚያስተላልፈው ሕዋስ አንዳንድ ጊዜ ግን ለሰውነታችን መታመም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይኸውም ክፉ የኃጢአት ሐሳቦችን በሕሊናችን ባነገስን ጊዜ ናላ የሚያመነጨው ኮርቲሶል (Cortisol) የሚባል ኬሚካል አለ።  ኮርቲሶል የውጥረት ኬሚካል (Stress chemical) ሲሆን፣ ንቁ የሆነውን የአዕምሮ ክፍል እንቅስቃሴ የሚቀንስ ነው። በመሆኑም ይህ ኬሚካል በመነጨ ጊዜ አመክንዮአዊነት፣ ችግር ፈቺነት፣ የሌሎችን ስሜት መረዳት፣ ርኅራኄና ይቅር ባይነት በአዕምሮአችን ቦታ አይኖራቸውም።

     ክፉ ስላሰብን ናላችን ባመነጨው ኬሚካል (ኮርቲሶል) ምክንያት የሚፈጠረው ውጥረት (stress) ደግሞ መዘዙ ቀላል አይደለም። ሌሎች የአካል ክፍሎቻችንም እንዲታመሙ (psychosomatic disorder ይባላል) ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ ወደዚህ ሁሉ የጤና ቀውስ ላለመግባት ሕሊናን ከክፋት መጠበቅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። ሰይጣን በሚያመጣብን የክፉ ሐሳብ ሞገድ ላለመናወጽ ራስን በበጎነት አጽንቶ መጠበቅ ግድ ይለናል። አበው የክፉ ሐሳብ አማራጮችን በሕሊናችን የሚያንሸራሽረውን ሰይጣን በዝንብ ይመስሉታል። ዝንብ ወደ ቤታችን የሚገባው በር ወይም መስኮታችንን ክፍት ስናደርግ ነው። ባገኘው ክፍተት የገባውም ዝንብ ማረፊያ ቆሻሻ ነገር በቤትህ ካገኘ ይሰነብታል፣ ይራባል (ይባዛል)። ቤትህ ንጹሕ ከሆነ ግን እንደ ገባ ፈጥኖ ይወጣል። ሰይጣንም እንዲሁ ነው፤ ክፉ ሐሳብን ይዞ ወደ ሕሊናህ ሲበር ይመጣል። ለእርሱ ክፋት የሚስማማ ማንነት ይዘህ ከጠበቅኸው፣ ያድርብሃል። አዕምሮህን መናገሻ ከተማው ያደርገዋል። በንጹሕ ሕሊና በበጎ ሰብዕና ሆነህ ካገኘህ ደግሞ እንዲህ ካለው አዕምሮ ውስጥ ማደር ስለማይቻለው ፈጥኖ ከአንተ ይለያል። የውስጥ ሰላምህም እንደ ወንዝ ይፈስሳል። ነፍስህ እና ሥጋህንም ከሕመም ታድናቸዋለህ።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
Channel photo removed
Channel photo updated
ለቅዱሳን ቤተሰቦቹ የጸሎት መልስ ለሆነው፣ ለዚህች ዓለም የሚነድና የሚያበራ መብራት ለነበረው፣ የሥጋን ጣዕም ላልቀመሰ ፍጹም ተሐራሚ፣ ተፈጥሮው የሰው ኑሮው የመልአክ ለነበረው፣ ዕረፍትን ለማያውቅ ለበረሃው ሰው ለታላቁ ሰማዕት ለቅዱስ ዮሐንስ በዓለ ልደት እንኳን አደረሳችሁ!!!

"በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል"
                        ሉቃ 1፥14
"አባቶችህን ዕወቅ" ቁጥር አንድ መጽሐፍ ሁለተኛ እትም በገበያ ላይ ውላለች።

(ቁጥር ሁለት ደግሞ በመንገድ ላይ ነች)

መጽሐፏን በሁሉም የመጽሐፍት መደብር ያገኙዋታል።

ሳታገኟትና ሳታነቧት ለቆያችሁ ሁሉ መልካም ንባብ!!!
+++ "ሰይጣን ነገረኝ" +++

ጥቂት መነኮሳት ስለተመለከቱት ራእይ እውነተኛነት ወይም ከአጋንንንት ስለመሆኑ ለመጠየቅ አባ እንጦንስን ፈልገው ወደ ገዳሙ መጡ። እነዚህ መነኮሳት በመንገድ ሲመጡ ሳሉ የሞተባቸው አህያ ነበር። አረጋዊው እንጦንስንም ባገኙት ጊዜ ቀድመው ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳይጠይቁት በፊት "በመንገድ ስትመጡ ሳለ አህያቹ እንዴት ሞተ?" ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም "አባታችን ይህን እንዴት አወቅህ?" አሉት። እርሱም "አጋንንት ምን እንደሆነ አሳዩኝ (ነገሩኝ)" አላቸው። መነኮሳቱም በነገሩ እየተደነቁ እንዲህ አሉ :- "አባታችን፣ አንዳንድ ጊዜ እውነት ሆኖ የሚፈጸም ራእይ እናይ ነበርና በሰይጣን እንዳንታለል የምንፈራበትንና ወደ አንተም የመጣንበትን ጥያቄ አሁን መለስክልን"።

ጥያቄ :- ሰይጣን ራእይ ሊያሳይ ይችላል?

መልስ :- አዎን። ራእይ ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም። አንዳንዴ ሰይጣን ያደረገውን ወይም ሊያደርግ ያቀደውን ክፋት ቀድሞ ሊነግር ወይም ሊያሳይ ይችላል።

ጥያቄ:- ከሰይጣን የሚመጣውን ራእይ እንዴት መለየት ይቻላል?

መልስ:- ራእዩ መመለስን የማይሰብክ፣ የንስሐና የምሕረት ጭላንጭል የማይታይበት፣ ማምለጫ ተስፋ የሌለው ጥፋትን ብቻ የሚተርክ ከሆነ ይህ የሰይጣን ነው። በአጠቃላይ ትንቢቱ "እንዲህ ይመጣባችኋል!" ብቻ ሳይሆን "በዚህ ትድናላችሁ" የሚል ማጽናኛና ፍቅር የሚጎድለው ከሆነ "ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደማወቅ እንዲደርሱ ከሚወድ ከመድኃኒታችን" ከእግዚአብሔር አለመሆኑን በዚህ ማወቅ እንችላለን።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
Forwarded from Jafer Books 📚
የዲያቆን አቤል ካሣሁን ነገረ አበው መጽሐፍ በዚህ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጥናት ውስጥ ትልቅ ድርሻ የሚወጣውን የነገረ አበውን ምንነትና የመጀመሪያዎቹን አባቶች ማንነት የሚተነትን እጅግ ወሳኝ መጽሐፍ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የእርሱን ዘመን ከሐዋርያት ቀጥሎ ከተነሡት የመጀመሪያዎቹ አባቶች ዘመን ጋር ሲያነጻጽር ‘’እናንተ በጫካ ውስጥ መንገድ እየፈለገ እንደሚጓዝ መንገደኛ ናችሁ ፤ እኛ ግን በእናንተ የተጠረገ መንገድ ላይ የምንጓዝ ነን’ ብሎ አመስኞ ነበር፡፡ ዲያቆን አቤል ለቤተ ክርስቲያን በጫካ ተጉዘው መንገድ ከጠረጉት አበው ታሪክ በመጀመር በዚህ ዘርፍ ለሚያነቡና ለሚያጠኑ የነገረ መለኮት ተማሪዎች ፣ መምህራንና ጸሐፍት እጅግ ወሳኝ የሆነ ሥራን አበርክቶልናል፡፡ የጻፈው የጫካውን ዘመን እንደመሆኑም ወደ ጫካ መግባትና እጅግ አሰልቺ የሆነ ንባብና ምርምር ማድረግ እንደጠየቀው በጽሑፉ ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡

ይህ የዲያቆን አቤል መጽሐፍ በሃይማኖተ አበው የምንጠቅሳቸውን የብዙ አበው ታሪክና ተጨማሪ ሥራዎች በሰፊው የሚያስተዋውቀን ለሃይማኖተ አበውና መጻሕፍተ ሊቃውንት እንደ መቅድም ሊያገለግል የሚችል መጽሐፍ ነው፡፡ በመረጃ እጥረት የምንይዛቸው የተሳሳቱ የታሪክ ድምዳሜዎችም በዚህ ሥራ መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ አቀራረቡም ጸሐፊውን እንጂ አንባቢውን የማያደክም ፣ በብዙ ጥናት የተደረሱ ድምዳሜዎችን እንደ ዋዛ እንድናነባቸው የሚያደርግ ቀላል አቀራረብ ያለው መጽሐፍ ነው፡፡ እኛ ይህንን የመሰለ መጽሐፍ እንድናነብ ብዙ መጻሕፍትንና የመመረቂያ ጽሑፎችን ክርክሮችን አንብቦ ደክሞ በውብ አቀራረብ ይህንን መጽሐፍ ያበረከተልንን ዲያቆን ቤልን ከልብ እያመሰገንኩ ይህንን ድንቅ መጽሐፍ እስካሁን ያላነበባችሁት እንድታነቡት እጋብዛለሁ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሐምሌ 23 2012 ዓ ም
+++ "ክረምትን ለምን ፈራሁት?" +++

በጋና ክረምትን እያፈራረቀ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚመግብ እግዚአብሔር ነው። በክረምት ገበሬው ይዘራል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ከሰማይ ጠሉን ይልክለታል። በክረምቱ ጊዜ ተዘርቶ ያደገው ሰብል እንዲበስል ፈጣሪው የበጋውን ፀሐይ ያወጣለታል። ትጉሁ ገብሬም የደረሰውን አዝመራ ሊሰበስብ በበጋው ማጭዱን ይዞ ይታያል። ክረምት ለገበሬው የሥራ ጊዜ ነው።

ለእኔ ግን ክረምት ያስፈራኛል። እንዳልጽፍ እጆቼ በብርዱ ቆፈን ይያዛሉ፣ እንዳላነብ አይኖቼ በእንቅልፍ ሽፋሽፍት ይፈዝዛሉ። ማልጄ በቤቴ መስኮት የማያት ፀሐይ በደመና ስትሸፈን ቀኑ የጀመረ ሌሊቱም የነጋ አይመስለኝ። ከአልጋዬ ተነሥ ተነሥ አይለኝም። ውጪው ሲጨልም ቤቴም ይደበዝዝብኛል። ወጥቼ ሥራዬን እንዳልሠራ፣ ከወዳጆቼ ጋር ተገናኝቼ እንዳላወጋ ዝናቡ አላላውስ ይለኛል። ለእኔ ክረምት ያስፈራኛል።

ግን ለምን ክረምትን ፈራሁት? እንደ ገበሬው የዝናብን በረከት ማየት ስላቃተኝ ይሆን? ወይስ የምዘራው ዘር በእጄ ስለሌለ? እንዲጸድቅ የምፈልገው ተክል፣ ልምላሜውን ማየት የሚያጓጓኝ እጽ የለኝ ይሆን?

በሥራ እና በግል ጉዳዮቼ ተጠምጄ ከራቅኋቸው ከቤቸሰቦቼ ልብ ላይ የምዘራው ብዙ የፍቅር ዘርማ አለኝ። በሰዎች ሆታ እና ጩኸት ስከበብ የዘነጋሁት በመልካም ሰብእና እንዲጸድቅና እንዲለመልም የምፈልገው እኔነት አለኝ። ታዲያ ለራሴ የሚሆን በቂ ጊዜ አግኝቼ ውስጤን አርስ፣ እመረምርና አለሰልስ ዘንድ ክረምት የመጣው፣ ዝናቡስ የዘነበው ለእኔ ብሎ አይደል?

ለካ የብርዱ ቆፈን የበረታብኝ፣ የአይኖቼ ሽፋሽፍት በእንቅልፍ የደከሙብኝ ክረምትን ስለማልወደው ሳይሆን የክረምትን በረከት ማስተዋል ስላልቻልኩ ነው። ለካስ ክረምቱ የደበተኝ "ደግሞ ሊመጣ ነው" ብዬ ቀድሜ ስላወገዝኩትና ራሴን ለሥራ ስላላዘጋጀሁ ነው። ሰማዩ ሲደምን እና ዝናቡ አላስወጣ ብሎ ሲዘንብ በእኔ ውስጥ ያለችውን ፀሐይ ፈልጌ እንድገልጣት እድል እየሰጠኝ ነው። ክረምት የደረቀው እጽ መልሶ የሚያቆጠቁጥበት ብቻ ሳይሆን ያረጀውና ሊወድቅ ያዘመመው ውስጤ የሚታደስበትና የሚጠገንበት ጊዜ ነው። ለካስ ክረምት ለገበሬ ብቻ የመሰለኝ ስህተት ነው። ክረምት ለእኔም ነው!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
1
+++ ዳርዊን የእምነት ሰው +++

እዩት ዳርዊን መጣ ፈጣሪን ሊያንኳስስ
ምንቃር እያሳየ "መፈጠርን" ሊከስ
ግና ለመረዳት የሕይወትን ፍሰት
ዳርዊን በሰበከው በዝግመቱ ሂደት
ሚልዮን ዘመንን አሻግሮ ለማየት
ከአማንያን በላይ አይጠይቅም እምነት?

ዲ/ን አቤል ካሳሁን

ማስታወሻ: ቻርለስ ዳርዊን ቤአግል (Beagel) በተባለ መርከብ አምስት ዓመት ሲጓዝ ከሰበሰባቸው የፍጡራን ቅሪቶች ውስጥ አንደኞቹ የአእዋፋት ምንቃሮች (አፋቸው ላይ የሚገኝ አጥንት መሳይ ነገር) ነበሩ። በኋላም የተለያዩ ዝርያ ያላቸው "ፍጥረታት" ሁሉ አንድ መነሻ አላቸው የሚለውን የevolution ንድፈ ሐሳብን ካጠናከረባቸው ማስረጃዎቹ አንዱ እነርሱ ነበሩ።
+++ሳያቋርጡ የመጸለይ ጥበብ+++

የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ ሲኖር ለቅጽበትም ቢሆን አእምሮው ሊረሳውና ሊያቋርጠው የማይችለው ነገር ምን እንደሆነ አስባችሁት ታውቃላችሁ? ሰውነቱ በእንቅልፍ ተሸንፎ እንኳን ቢተኛም እያንቀላፋ አስታውሶ የሚያደርገው ክንውን የትኛው እንደሆነ አስተውላችኋል? እንደው አይሆንም እንጂ ሆኖለት ለደቂቃዎች ሰውነቱ ይህንን ተግባር በመርሳት ባያከናውነው ሕልውናው አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህ ሰውነታችን ልምድ ያደረገውና ለአፍታ እንኳን መቋረጥ የማይፈልገው ተግባር አየር ማስገባትና ማስወጣት ወይም መተንፈስ ነው፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ይህን የተፈጥሮ እውነት እንደ መነሻ የተጠቀምነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጸሎትን እንደ ነፍስ እስትንፋስ ይቆጥሯታል፡፡ አየር ያጠረው ወይም ወደ ሰውነቱ የማያስገባ ሰው በሕይወት የመቆየት ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ ፤ እንዲሁ ከጸሎት የተለየች ነፍስም ወደ ሞት መንደር የመውረዷ ነገር የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ነፍሳችን ሕያዊት የምትሰኘው በአረጋዊ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ ‹የነፍሴ ነፍሷ› ተብሎ ከተጠራው መንፈስ ቅዱስ ጋር በጸሎት ትስስርን ስትመሰርት ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙም እንደሚያስተምረው ሰው ከእስትንፋሱ የበለጠ ዘወትር ፈጣሪውን በጸሎት ሊያስታውስ ይገባዋል፡፡

ጸሎት ማለት ምን ማለት ነው? ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 14 ላይ ‹ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት› ሲሉ የጸሎትን ትርጉም ይነግሩናል፡፡ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በልዩ ልዩ አይነት መንገድ ሊያናግራቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በራእይ በመገለጥ ወይም ቅዱስ ዳዊት ‹እግዚአብሔር ለሕዝቡ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል› ሲል እንደ ዘመረው በመጽሐፍ በኩል ማናገር ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ የሰው ልጆች ደግሞ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚነጋገሩት ጸሎት በተባለ ድልድይ አማካኝነት ያነጋግሩታል፡፡

መተንፈስ ለሥጋዊው አካላችን የዕለት ተዕለት የማይቋረጥ ሥራው እንደሆነ ሁሉ የነፍስ እስትንፋስ የተባለች ጸሎትም ለክርስቲያን የየዕለት መንፈሳዊ ተግባር ናት፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹ሳታቋርጡ ጸልዩ› በማለት የሚመክረን (1ኛ ተሰ 5፡17)፡፡

በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ሶርያዊው አባ ይስሐቅ (ማር ይስሐቅ) ቅዱሳን ምንም ዓይናቸው በእንቅልፍ ሽፋሽፍት ቢያዝ እንኳን ነፍሳቸው ግን ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረግ የማይቋረጥ ንግግር (ጸሎት) ውስጥ ስለምትገኝ ተኝተውም ቢሆን ጸሎትን እንደማያስታጉሉ ይናገራል፡፡ እኛ በዓለም የምንኖር ግን የሥጋ ድካም ስላለብን ቀኑንም ፣ማታውንም በጸሎት የማሳለፍ ብርታቱ የለንም፡፡ በመሆኑም ‹ሳታቋርጡ ጸልዩ› የሚለው የሐዋርያው ትዕዛዝ ይከብድብናል፡፡

በዚህም ምክንያት እንደ እኛ ሥጋ ለባሽ የሆኑ አባቶቻችን ይህን ድካማችንን አይተው ቀኑን ሁሉ በጸሎት ማሳለፍ ባትችሉ እንኳን ቢያንስ በቀን ሰባት ጊዜ እግዚአብሔርን ስለ እውነተኛ ፍርዱ አመስግኑት ሲሉ ሰባት የጸሎት ጊዜያቶች ወስነውልናል (መዝ 119፡164)፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አሁንም ከፈጣሪው ጋር ቀኑን ሙሉ በጸሎት የማሳለፍ ጽኑዕ ፍላጎት ላለው ክርስቲያን አባቶች የሚያስተምሩት ሌላ ‹ሳያቋርጡ የመጸለይ ጥበብ› አለ፡፡ ይህንን ጥበብ የምናገኘው ቅዱስ ጰላድዮስ (St. Palladius) የተባለው አባት ባሰባሰበውና የብዙ አባቶችን ዜና ሕይወት ይዞ በሚገኘው ‹መጽሐፈ ገነት› ላይ ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው ፡-

በአንድ ወቅት አባ ሉቅዮስን (Abba Lucius) ለማየት የመጡ ጥቂት መነኮሳት እንዲህ አሉት ‹በእጃችን ምንም አይነት ሥራን አንሠራም፡፡ የቅዱስ ጳውሎስን ትዕዛዝ በማክበር ሳናቋርጥ እንጸልያለን እንጂ!›፡፡ አረጋዊው መነኩሴ አባ ሉቅዮስም ‹አትመገቡም? ወይም አትተኙምን?› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹አዎን! እንተኛለን ፤ እንመገባለን› ሲሉ መለሱ፡፡ አባ ሉቅዮስም ‹ወንድሞቼ ይቅርታ አድርጉልኝና የምትሉትን ነገር (ሳያቋርጡ መጸለይን) እየፈጸማችሁ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በእጆቼ ሥራን እየሠራሁ እንዴት ሳላቋርጥ እንደምጸልይ አሳያችኋለሁ፡፡ ዘወትር ጠዋት በእግዚአብሔር እርዳታ የዘንባባ ዛፍ ቅሪቶችን እሰበስብና እነርሱን ሽጬ አሥራ ስድስት ሳንቲሞችን አገኛለሁ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ሳንቲሞች ከቤቴ በር ደጃፍ ላይ አስቀምጥና በቀረው ምግብ እገዛበታለሁ፡፡ የገዛሁትንም ምግብ ተመግቤ ስተኛ ፤ ያ ከቤቴ ደጃፍ ላይ ሁለቱን ሳንቲሞች የወሰደው ነዳይ ደግሞ ስለ እኔ ይጸልያል፡፡ እንዲህ እያደረግሁ በእግዚአብሔር ረድዔት ሳላቋርጥ እጸልያለሁ› በማለት ልምዱን አካፈላቸው፡፡

ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ከጸሎት ጋር በቀን ማከናወን ያለበትን ሥራ ሥርቶ ከጨረሰ በኋላ አመሻሽ ላይ ከሚያገኘው ትርፍ ለነዳይ ቢመጸውት ብዙውን ሰዓት በእንቅልፍ የሚያሳልፍበትን ሌሊት በምጽዋት እያካካሰ ሳያቋርጥ ሊጸል ይችላል ማለት ነው፡፡

ሳናቋርጥ እንጸልይ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg

https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12
+++ "ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና" +++                                                       ፊል 1፥21

እነሆ ምሳሌ፣ 

በምንኩስና ይኖር የነበረ አባት ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ ገነት ሄደ። ከውጭም ቆሞ እንዲከፈትለት ደጁን ያንኳኳ ጀመር። ወዲያውም "ማን ነህ?" የሚል ድምጽ ከውስጥ ሲወጣ ሰማ። መነኩሴውም "እኔ ነኝ" ሲል መለሰ። ይሁን እንጂ ያንኳኳው በር ግን ሊከፈትለት አልቻለም። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም  እንደ ገና  ተመልሶ ወደ ገነት በመምጣት ደጁን አንኳኳ። እንዳለፈውም ጊዜ ከውስጥ "ማን ነህ?" የሚል ድምጽ ሰማ። እርሱም እንደ ለመደው "እኔ ነኝ" አለ። አሁንም በሩ ሳይከፈትለት ቀረ።

መነኩሴው በዚህ ተስፋ አልቆረጠም። ይህ ከሆነ ከብዙ ዓመታት በኋላ እርሱም በመንፈሳዊው ጥበብ ጎልምሶ ተመልሶ ወደ ገነት ሄዶ በሩን አንኳኳ። እንደ ከዚህ በፊቱም "ማን ነህ?" የሚል ድምጽ ሰማ። ያም አባት የቀድሞው መልሱን ተወና "በእኔ ውስጥ የምትኖረው አንተ ነህ" ሲል ለጠየቀው አካል መለሰ። በዚህ ጊዜ ተዘግቶ የነበረው በር ተከፈተለት ይባላል።

ክርስትና ምንድር ነው? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ማብራሪያዎች ሊሰጡ ይችላሉ። በአጭሩ ግን እንመልሰው ካልን፣ ክርስትና ማለት "ክርስቶስ የሚያድርበት መቅደስ መሆን" ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲገልጽልን "እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል" ይለናል።(ገላ 2፥20) ክርስቲያን ማለት "አንተ ማን ነህ?" ተብሎ ሲጠየቅ ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "በእኔ የሚኖር ክርስቶስ ነው"፣ "አነ ዘክርስቶስ" - "እኔ የክርስቶስ ነኝ" ብሎ መመለስ የሚችል ነው።

ጌታችን በወንጌል ለደቀ መዛሙርቱ "በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ" ሲል እንደ ተናገረ፣ እኛ ለክርስቶስ መኖር ስንጀምር እርሱ ደግሞ በእኛ ይኖርብናል፤ እኛ ለክርስቶስ ማደር ስንጀምር እርሱ ደግሞ በእኛ ያድርብናል።(ዮሐ 15፥4)

እንዲህ ያለውን ሕይወት የሚኖር እውነተኛ ክርስቲያን የሥጋን ሞት አይፈራም። ስለ ሃይማኖቱ መከራ መቀበልን አይሰቀቅም። ክርስቶስን ከሚያሳጣው ሕይወት ይልቅ ወደ ክርስቶስ የሚወስደውን ሞት ይመርጣል። ፈጣሪው ከሌለበት ምቾት ይልቅ ፈጣሪን ይዞ መሰቃየት ለእርሱ ያስደስተዋል።

ሰይፍ ይዘው በሚያስፈራሩትም ጨካኝ ወታደሮች ፊት "ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና" እያለ በሐሴት ይዘምራል።(ፊል 1፥21)

በሰይፍ ለሚገድለው ወታደር በኩራት የልብሱን ኮሌታ ከፍ አድርጎ አንገቱን ስለ ክርስቶስ በደስታ ለሰጠ፣ ለታላቁ ሐዋርያ ለቅዱስ ጳውሎስ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሰን!

የአገልግሎቱ ድካም፣ በረከት በሁለችን ላይ ይደርብን!!!



ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg

https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12
+++ ጆሮ ሽፋን የለውም +++

ጆሯችን የተለያየ መጠን ያላቸውን ድምጾች ለመስማት የሚያስችለን የአካላችን አንደኛው እና አስፈላጊው ሕዋስ ነው፡፡ ከጥቃቅን በራሪ ሕዋሳት ከሚወጡ የሰለሉ ድምጾች ጀምሮ ሁከት እና ድንጋጤን እስከሚፈጥሩት የሰማይ መባርቅት ጩኸት ድረስ የማድመጥ ችሎታ አለው፡፡ ይሁን እንጂ ለእኛ በጣም ቅርብ የሆኑና በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱትን የልመት ስርዓት ፣የልብ ምት ድምጾችን በመሳሪያ እስካልታገዝን ድረስ አጥርተን አለመስማታችን ደግሞ እጅግ የሚያስደንቅ ነገር ነው፡፡ አስባችሁታል በደም ቧንቧዎቻችን "ሽሽ" እያለ የሚያልፈውን የደም ዝውውር፣ ምግብ ከበላን በኋላ ያለውን የልመት (የመፍጨት) ሥርዓት፣ የማይቋረጥ የልባችንን ምት ሁል ጊዜ የምንሰማ ቢሆን ሰላም የሌለን ተቅበዝባዦች እንሆን ነበር። ተመስገን ነው!!!

እኛ የሰው ልጆች ድምፅን ከመቀበል በተጨማሪም መልእክትን ባዘለ መልኩ በቃላት ሞሽረን የማስተላለፍም ልዩ ስጦታ አለን፡፡ በመሆኑም መስማት እና መናገር ለመግባባት የሚረዱን መሠረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ በጆሯችን በኩል የሚገቡ የድምጽ ሞገዶችን መልእክት ለመለየት የሚረዳ በናላ ላይ የሚገኝ ጣቢያ አለ፡፡ ያለዚህ የናላ ክፍል በፍጹም መልእክት ያለው ድምጽን መስማት አንችልም፡፡

ጆሯችን ከዚህች ዓለም ጋር ለሚኖረን መስተጋብር ልክ እንደ ዓይናችን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የሰው ዘር የሆንን ሁላችንም አጎንብሰን አለመሄዳችን እና ቀጥ ያለ አቋም ያለን መሆኑ ብዙ ነገሮችን እንድናከናውን ረድቶናል። በተለይ የአካልን ሕዋሳት ተጠቅመን ለምንሠራቸው እንደ ንባብ ፣ጽሕፈት ፣ማሽከርከር የመሳሰሉትን ተግባራት በቀላሉ እንድናከናውን ያግዘናል፡፡ ነገር ግን ምንም ቀጥ ያለ አቋም ቢኖረንም ሚዛናችንን ጠብቀን እግራችን ሳይጠላለፍ ሰውነታቸን ሳይዛነፍ ባለንበት መጽናት የምንችለው እና ቀጥ ብለን የምንሄደው ሚዛን ጠባቂው ጆሮ እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሔር ለምን ባለ ሁለት ጆሮዎች አድርጎ አዘጋጀን? ለመስማት አንዱስ ቢሆን በቂ አይደለምን? የሚል ጥያቄ ጠይቀን እናውቅ ይሆን? ጆሯችን መስማት ብቻ ሳይሆን ድምጹ የመጣበትን አቅጣጫ እና የድምጹ ምንጭ ቋሚ ይሁን ተንቀሳቃሽ ለመለየት ይጠቅማል፡፡ አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ የመጣን ድምጽ ፍለጋ ወደኋላ ዞሮ የማያስሰው ሁለት ጆሮዎች ያሉት በመሆኑ ነው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄ እና በምክንያት መዘጋጀቱን ከሚያመለክቱ የሰውነት ክፍል ሕዋሳት መካከል አንዱ ጆሮ እንደሆነ ተመልከቱ።

ሁላችሁም እንደምታውቁት ደስ የማያሰኘውን ነገር ዓይናችን እንዳያይ የምንከለክልበት የተፈጥሮ የዓይን መሸፈኛ ቆብ አለን። ጆሮአችን ግን ልክ እንደ ዓይናችን ሲፈለግ የሚዘጋ እና የሚከፈት ቆብ ወይም ሽፋን የለውም። ስለዚህም ማንኛውም ሰው በየትኛውም ጊዜ የሚያደርጋቸው ያልተገቡ ንግግሮች በቀላሉ በጆሮአችን አልፈው ለመግባት ሰፊ እድል አላቸው ማለት ነው። በመሆኑም ከአንደበታችን የሚወጣው ክፋ ቃል መዝጊያ ባልተዘጋጀለት በሌላ ሰው ጆሮ አልፎ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል። የምንናገርም ሁሉ የሚያንጸውን እና በጎውን ብቻ እየተናገርን የሰሚዎቻችንን ጆሮ እንታደግ።

እንዲህ ፈጣሪ ጥበቡን አፍሶ የፈጠረው ጆሯችንን ክፉ እየሰማ እንዲባክን አናድርገው!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን

https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg
አብ የማይጠልቅ ፀሐይ እንደ ሆነ ፣ ወልድም ዘወትር በቅዱሳን ላይ የሚያበራ ፀሐይ ነው። መንፈስ ቅዱስም ቤተ ክርስቲያንን የሚያስጌጣት ብርሃን ነው።

ሥሉስ ቅዱስ ሆይ፣ እንደ እስጢፋኖስ የድንጋይ ልብስ አልለበስኹም፣ እንደ ቂርቆስም በእሳት አላጌጥኹምና ምሕረታችሁ ልብስ ሆኖ እርቃኔን ይሸፍንልኝ።

እንኳን አደረሳችሁ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://tttttt.me/Dnabel
https://youtube.com/channel/UCRvatZyeFOJtXnAjZSOdrZg