Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
530 photos
44 videos
1 file
841 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
+++የእስክንድር እንቁላሎች+++

ሕፃኑ እስክንድር እክል ካለበት ሰውነት ጋር የተወለደ ሲሆን፣ መለስተኛ የሆነ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ችግርም አለበት፡፡ እስክንድር ምንም ዕድሜው አሥራ ሁለት ዓመት ይሁን እንጂ በጊዜው ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር፡፡ ካለበት የጤና እክልም የተነሣ መማር ይቸግረው ነበር፡፡ ታስተምረው የነበረች ሴት መምህርቱም በልዩ እንክብካቤ ያለና በእነርሱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አብሮ መጓዝ እንደማይችል ተረድታዋለች፡፡ ጥሩ አስተማሪና እውነተኛ ክርስቲያንም ስለነበረች ተማሪዋ እስክንድርን በትኩረት ትከታተለው ነበር፡፡ የፀደይ ወቅት በመድረሱ እንዲሁም የፋሲካም በዓል ከፊታቸው እየመጣ ስለሆነ ከእስክንድር ጋር የሚማሩት ሕፃናት ተማሪዎች በተደሱበት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡

መምህርቷ ተማሪዎቿ ሁሉ ትላልቅ የፕላስቲክ እንቁላል በመስጠት ‹ይህን የፕላስቲክ እንቁላል ወደ ቤታችሁ እንድትወስዱትና ነገ መልሳችሁ እንድታመጡት እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ስታመጡ በውስጡ አዲስ ሕይወትን ሊያሳይ የሚችል ነገር ማስቀመጣችሁን እንዳትረሱ› ብላ ነገረቻቸው፡፡

በቀጣዩ ቀን ጠዋት ላይ ሕጻናት ተማሪዎቹ የተሰጣቸውን የፕላስቲክ እንቁላል ይዘው ወደ ትምህርት ቤት መጡ፡፡ እየተሳሳቁ እና እየተጫወቱ በክፍላቸው ውስጥ መምህርታቸው ወዳዘጋጀችው ትልቅ ቅርጫት እንቁላሎቻቸውን ወረወሩ፡፡ ከዚያም እንቁላሎቹ ተከፍተው የሚታዩበት ጊዜ ሲደርስ አስተማሪያቸው አንድ በአንድ ከቅርጫቱ ማውጣት ጀመረች፡፡

የመጀመሪያውን እንቁላል ስትከፍተው በውስጡ አበባ አገኘች፡፡ ለሕፃናቱም ‹በትክክል! በርግጥም አበባ የአዲስ ሕይወት ምልክት ነው› ስትል ግርምቷን ገለጸች፡፡ የዚህ እንቁላል ባለቤት የሆነችውም ተማሪ እጇን በማውጣት የእርሷ መሆኑን ስትገልጽ ‹ጥሩ አድርገሻል!› ብላ አመሰገነቻት፡፡ በቀጣይ ያነሣችው እንቁላልም በውስጡ ቢራቢሮ ነበረው፡፡ መምህርቷም እንቁላሉን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ‹አባ ጨጓሬ መሳዩ (ካተርፒለር) ነገር በመቀየር ወደ ውብ ቢራቢሮነች እንደሚሸጋገር እናውቃለን፡፡ በእውነትም ይህም አዲስ ሕይወት ነው፡፡› አለች፡፡

ቀጥላም ሦስተኛውን እንቁላል ከፈተችው፡፡ በውስጡ ግን ምንም የሌለው ባዶ ነበር፡፡ በእርግጠኝነት የእስክንድር እንቁላል መሆኑን አሰበች፡፡ በጊዜው የተናገረችውን ነገር በደንብ ስላልተረዳ ይህን ያደረገ መሰላት፡፡ ልትረብሸውም ስላልፈለገች እንቁላሉን ቀስ ብላ በማስቀመጥ ሌላኛውን ከቅርጫት ሳበች፡፡ ነገር ግን በሁኔታው የተደነቀው እስክንድር በድንገት ‹መምህርት፣ ስላመጣሁት እንቁላል ምንም አትይም እንዴ?› ሲል ጠየቃት፡፡ መምህርቷም ፊቷ ላይ የመረበሽ ምልክት እየታየባት ‹ግን እኮ እስክንድር፣ እንቁላልህ ባዶ ነው› አለችው፡፡ እርሱም ዓይን ዓይኗን እየተመለከታት ለስለስ ባለ ድምጽ ‹አዎ መምህርት! የክርስቶስ መቃብርም እኮ እንዲሁ ባዶ ነበር› አላት፡፡

አስተማሪዋ የቀሩትን እንቁላሎች ለተማሪዎቹ አሳይታ ስትጨርስ ወደ እስክንድር በመሄድ ‹ለመሆኑ መቃብሩ ለምን ባዶ እንደሆነ ታውቃለህ?› አለችው፡፡ እርሱም ‹አዎ፣ ክርስቶስ ተገድሎ በዚያ ውስጥ ተቀብሮ ነበር፡፡ ነገር ግን እርሱ ከሞት ተነሣ፡፡ ታዲያ ይህ ነገር አዲስ ሕይወትን አያሳይምን?› ብሎ መለሰላት፡፡ ያቺም መምህርት በነገሩ ልቧ ተነክቶ ፊቷን ሸፍና አነባች፡፡

ይህም ነገር ከሆነ ከሦስት ወራት በኋላ ተማሪው እስክንድር አረፈ፡፡ የቀብር ሥርዓቱንም ለመከታተል የተሰበሰቡት ሰዎች አንድ እንግዳ ነገር በመቀበሪያው ሳጥኑ ውስጥ ተመለከቱ፡፡ ይኸውም የተከማቹ ሃያ እንቁላሎች ነበሩ፡፡ በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ባዶ እንደ ነበረው መቃብር ሃያዎቹ እንቁላሎችም ባዶ ነበሩ፡፡

Source : ‹The Eggs of Alexander› - Orthodox Parables and Stories /ከመለስተኛ ማሻሻያ ጋር

ትርጉም ፡ ዲያቆን አቤል ካሳሁን

abelzebahiran@gmail.com
እንኳን አደረሳችሁ!
+++ ‹ወዴት ነው የምናየው?› +++

ለጌታ ቅዱስ ሥጋ ይሆን ዘንድ ያዘጋጀችውን ሽቱ በመያዝ የጨለማውን ግርማ ሳትፈራ መግደላዊት ማርያም በሌሊት ገስግሳ ወደ መቃብሩ መጥታለች፡፡ አይሁድ ያቆሟቸው ወታደሮች ጥቂት ርኅራኄ ካደረጉላት እንደ ልማዱ የጌታዋን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ትፈልጋለች፡፡ ነገር ግን በቦታው ደርሳ የተመለከተችው ነገር በድንጋጤ ሐሞቷን አፈሰሰው፡፡ ጎመድ የታጠቁ ብርቱዎቹ የመቃብሩ ጠባቂዎች የሉም። አይሁድ በሰንበት በመቃብሩ ያተሙትም ማኅተም ከነመዝጊያ ድንጋዩ ወዲያ ተንከባሏል፡፡ በስፍራው አንዳች መልእክት ያለው ዝምታ ነግሧል፡፡ ይህን ጊዜ መግደላዊት ማርያም ኃዘን ባደቀቀው አቅሟ እየወደቀች እየተነሣች ሐዋርያቱ ወደ ተሰበሰቡበት ቤት ሄደች፡፡ ለስምዖን ጴጥሮስ እና ለዮሐንስም ‹ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም› ስትል እንባ እየተናነቃት ነገረቻቸው፡፡

ይህን የሰሙ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ወደ ጌታ መቃብር መንገድ ጀመሩ፡፡ አብረውም ሮጡ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ በወጣትነት ጉልበት ከፊት ከፊት እየፈጠነ ቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፡፡ አረጋዊው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ቢሮጥም እንኳን እንደ ዮሐንስ ሊሆን አልቻለም፡፡ በእርግጥ ለክርስቶስ ከነበረው ፍቅር የተነሣ በእርጅና ጉልበቱ ቢሮጥም የሐሙስ ምሽቱ ክፉ ትውስታ (ዶሮ ሳይጮህ መካዱ) ግን ከዕድሜው ጋር ተደምሮ ጥቂት ሳያዘገየው አልቀረም፡፡ ወደ መቃብሩም ቀድሞ የደረሰው ሐዋርያው ዮሐንስ ከመጓጓት ብዛት ራሱን ዝቅ ቢያደርግ የመግነዙን ጨርቅ ተመለከተ፡፡ ወደ ውስጥ እንዳይገባ ግን ‹አክብር ገጸ አረጋዊ› - ‹ሽማግሌውን አክብር› የምትለው ደገኛይቱ ሕግ ከለከለችው፡፡ ዘግይቶ የመጣው ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ ቀድሞ በመግባት በመልክ በመልክ የተቀመጡትን የተልባ እግር ልብሱንና ፣ የራስ ጨርቁን አየ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ወደ ውስጥ ገብቶ ይህኑ ተመለከተ፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ የተጻፈውን የክርስቶስን ትንሣኤ አላመኑም ነበርና ማየታቸው ከኃዘን በቀር የጨመረላቸው ነገር የለም፡፡ ለካስ ማወቅ ብቻ ሳይሆን አለማወቅም ትካዜን ይጨምራል?!

ሐዋርያቱ ‹አይሁድ የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋ ለማንገላታትና ለማዋረድ ከዚህ አውጥተው ሌላ መቃብር ውስጥ አድርገዉት ይሆናል› የሚል ግምት ቢኖራቸውም፣ ነገር ግን እነርሱን ‹የት አደረጋችሁት?› ብሎ የመጠየቅ ድፍረቱ ስላልነበራቸው አንገታቸውን እንደ ሰበሩ በዝምታ ወደ መጡበት ቤት ተመለሱ፡፡ ማርያም መግደላዊት ግን ከመቃብሩ ውጭ ቆማ የፍቅር እንባን ታፈስ ነበር፡፡

በኋላም ወደ መቃብሩ ውስጥ ዝቅ ብላ ብትመለከት ሁለት ነጫጭ የለበሱ መላእክትን የክርስቶስ ሥጋ ተኝቶ በነበረበት ራስጌና ግርጌ ተቀምጠው አየች፡፡ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ ግን በወንጌላቸው ያናገራትን መልአክ ብቻ በመቁጠር መግደላዊት ማርያም አንድ መልአክ እንደታያት ይጽፋሉ፡፡ ይህችም ሴት ከደረሰባት የኃዘን ጽናት የተነሣ እንዳትሰበር የሚያረጋጉ መላእክት ተላኩላት፡፡ እነዚህም መላእክት ቀድሞ በጥል ዘመን (በኦሪት) እንደ ነበረው የምትገለባበጥ ሰይፍ ይዘው በዓይነ መአት (በቁጣ ዓይን) እያዩ ሳይሆን፣ የደስታ ምልክት የሆነውን ነጭ ልብስ ተጎናጽፈው ደስ በተሰኘ ብሩህ ገጽ ተገለጡላት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከነፋስ የረቀቁ፣ ሥጋዊ ጉልበት የሌላቸውን መላእክት በመቃብሩ ውስጥ ‹ተቀመጡ› ሲል ይነግረናል፡፡ ይህም አንደኛ መቆም መቀመጥ በሚስማማው ሰው አምሳል መገለጣቸውን የሚያሳይ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ መቀመጥ ዕረፍትን፣ መረጋጋትን እንደሚያሳይ የመቃብር አስፈሪነት ፣የሞትም ጣር እንደ ጠፋ ሲያመለክቱ በመቃብር ውስጥ ተቀምጠው ታዩአት፡፡

ከሁለቱ አንዱም መልአክ ‹አንቺ ሴት ለምን ታለቅሻለሽ?› ሲል ጠየቃት፡፡ ላዘነነ እና ለተጨነቀ ሰው በቀዳሚነት ሸክሙን የሚያቀሉለት በነጻነት ችግሩን እንዲናገር እድል በመስጠት ነውና መልአኩም አላዋቂ መስሎ ጥያቄውን አቀረበላት፡፡ እርሷም ‹ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም› ስትል መለሰችለት፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ማርያም መግደላዊት በእነዚያ መላእክት ፊት ላይ የተመለከተችው ነገር እጅግ ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡ ልክ ሕፃን ልጅ ገበያ ቆይታ የመጣች እናቱን ሲመለከት በጉጉት እንደሚንሰፈሰፈውና በደስታ የሚሆነውን እንደሚያጣ ፣ መላእክቱም እንደ እናት እንደ አባት የሚመግባቸውን ፣ ዘወትር ‹ሊያዩ የሚመኙትን› የፈጣሪያቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ገጽ ባዩ ጊዜ እንደ እነዚያ ሕፃናት ሆኑ፡፡ ገጻቸውን ከእርሷ መለስ አደረጉባት፡፡ ይህን ጊዜ በአንድ አቅጣጫ የተተከለውን የእነርሱን ዓይን ተከትላ ወደ ኋላዋ ብትመለከት ‹ኢየሱስን ቆሞ አየችው›፡፡ ምንም ለጊዜው ባታውቀውም በስሟ ሲጠራት ግን ወዲያውኑ ለይታዋለች፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊት ግን መጀመሪያ ክርስቶስን ያየችው የመላእክቱን የእይታ አቅጣጫ ተከትላ ነበር፡፡

እኛስ የእግዚአብሔር ቃል ባለ አደራ የሆንን የወንጌል መልእክተኞች ወዴት ነው የምናየው? ከፊታችን አስቀምጠን ለምናጽናናቸው ምእመናን የዓይናችን አቅጣጭ ወዴት እንዲመለከቱ ይመራቸዋል? አሁን ሕዝብ ሁሉ ጭልጥ ብሎ ወደ ፖለቲካው በመግባት ለሃይማኖቱ ግድ የለሽ ሆኗል፡፡ የእኛን የዓይን አቅጣጫ ተከትለው ይሆን?

በዘመናችን ሰውን ማክበር ፣እግዚአብሔርን መፍራት ብርቅ ሆኗል፡፡ ፍቅር ቀዝቅዞ ጥላቻ ነግሧል፡፡ ግድ የላችሁም ዓይናችን የፍቅር አምላክ የሆነው ክርስቶስን ሳይስት አልቀረም? ምክንያቱም የእኛን የእይታ አቅጣጫ ተከትለው የተመለከቱት ምዕመናን ከጥላቻ እና ይህን ከመሳሰሉት ክፋቶች በቀር ምንም አላተረፉምና? እስኪ አንዳፍታ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምረው? ግን ወዴት ነው የምናየው?

ታሕሣስ 2011 ዓ.ም
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ሴቶች ትንሣኤውን ተናገሩ!
የእግዚአብሔር ሰው ሰሎሞን ለአምላኩ ሕንፃ መቅደስን ሊያንጽ በተነሣ ጊዜ ፤ "በጥበብና በማስተዋል በብልሃትም የተሞላ" የናሱን ሠራተኛ ኪራምን ከጢሮስ አስመጥቶ ነበር። ከዚህም ጥበበኛ ጋር ሆኖ እጅግ አስደናቂ የሆነውን መቅደስ በታላቅ ጥንቃቄ አንጿል። በእውነት ይህን ሰሎሞን ያሳነጸውን ውብ መቅደስ ማየት ምንኛ ያጓጓ ይሆን? በእርግጥም መቅደሱንና የመሥዋዕቱን ሥርዓት የተመለከተች ንግሥተ አዜብ ማክዳ "ነፍስ አልቀረላትም" ነበር (1ኛ ነገ 10:5)።

ሆኖም ግን እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ "ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ?" ብሎ መጠየቁ አልቀረም (ኢሳ 66:48)። ለጊዜው በረድኤት የሚያድርበትን መቅደስ ንጉሥ ሰሎሞን ውብ አድርጎ ቢያንጽለትም ፤ በኋላ ግን የሰውን ልጆች ለመቤዠት በአካል የሚያድርበትን ሕያው መቅደስ ማንም ማዘጋጀት አልቻለም ነበር። ስለዚህም "ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም" ተብሎ ተጻፈ (ሐዋ 7:50)። በመሆኑም መቅደሱን ላነጹ ለሰሎሞን እና ለኪራም ጥበብን የሰጠው ጥበበኛ "ለራሱን ቤት ሊሠራ ፣ሰባት ምሰሶዎችንም ሊያቆም" ፈቃዱ ሆነ። የመቅደሱንም መሠረት እንቁ አደረገ። ቤቱንም እጅግ በከበሩ ድንጊያዎች አነጸ።

ይህች በአምላክ እጅ የታነጸች ፣እግዚአብሔር በረድኤት ሳይሆን በአካል የሚያድርባት ሕያው መቅደሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የተመሠረተችባቸውም አዕናቁ (እንቁዎች) ቅዱሳን ቤተሰቦቿ ናቸው። የታነጸችበትም የከበሩ ድንጊያዎች ንጽሕና ፣ቅድስና ናቸው።

"ይህች ዓለም አይቶ የማያውቃት በተስፋ ትጠበቅ የነበረችው ድንቅ አማናዊት መቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህች ምድር ላይ የታየችው በዛሬው ቀን ነበር"

ኪራም ያነጸው የሰሎሞንን መቅደስ መጎብኘት "ነፍስ የማያስቀር" ፣ልብን በሐሴት የሚሞላ ከሆነ ፤ በእግዚአብሔር እጅ የታነጸች ፣የአምላክ ጥበብ የፈሰሰባት እውነተኛ መቅደሱን የእመቤታችንን መወለድ የማየትና የመስማት የደስታ ጥጉ ምን ያህል ይሆን?

እንኳን ደስታን ወደ ዓለም ይዞ ለመጣ ተናፋቂው ለድንግል ማርያም ልደት አደረሳችሁ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኹት፥ እርስዋንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ የዘላለም ማረፊያው በሆነች በእናቱ ፍቅር እኖር ዘንድ፤ እርሷን ደስ አሰኝ ዘንድ ፤ ያማረው የፊቷንም ብርሃን እመለከት ዘንድ፤ በዓለም ካሉት አእላፋት ዝና ይልቅ ልቤ የድንግልን ፍቅር ይመኛል፣ የዓለሙ ዝና ነፍስን ለሚያቆስል ትዕቢት አሳልፎ ስለሚሰጥ ምን ይጠቅመኛል? የድንግል ፍቅር ግን ዕረፍትና ጸጥታ ይሆነኛል፣ ወደ መዳን መንገድም ስቦ ያስገባኛል፤ ልቡናዬ የክብርሽን ገናንነት ይናገር ዘንድ ይወዳል፥ መላሴ ግን በኃጢአት ፍሕም የተበላ ኮልታፋ ሆኖ ተቸግሯል፤ የልሳኔን ልቱትነት አርቀሽ፥ እኔ ደካማ ባሪያሽን በምስጋናሽ ቃል የምትሞይበት የኃይል ቀን መቼ ነው? ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደ ምትናፍቅ እኔም ምስጋናሽን እየተጠማሁ ያቺን ቀን እናፍቃለሁ። መቼ እደርሳለሁ? መቼስ አንቺን አመሰግንሻለሁ?

ዲ/ን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
አዲስ መጽሐፍ
(አባቶችህን ዕወቅ - ቁጥር 2)
በቅርብ ቀን!!!
ትምህርቱ እንዲደርስዎ ይህን የyoutube account
#subscribe ያድርጉ!

https://youtube.com/channel/UC-XzIXjfjoza6wkjtos8h2A
"ትዕቢተኛ ከሚያደርግህ ስኬት ይልቅ፣ ትሑት የሚያደርግህ ስህተት ይሻላል"