Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
529 photos
44 videos
1 file
841 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
"በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት።"
ዮሐ 5፥2

ቦታ: መጻጉዕ በተፈወሰበት በቤተ ሳይዳ የመጠመቂያ ስፍራ

Photo credit: Dil Travel
"የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ" ሉቃ 18፥39
ያላመኑ ሰዎችን የምትመልሰው በሙግት ሳይሆን እውነቸኛ ክርስቲያን በመሆን ነው። ለእነርሱ በቅርብ የሚያገኙህ መጽሐፍ ቅዱስ አንተ ነህ።
+++ ሦስቱ ስሜቶች +++

አንድ በጨለማ ቤት ውስጥ ለረጅም ሰዓታት የተቀመጠ ሰው የቤቱን መስኮት በከፈተ ጊዜ ከውጪ የሚገባውን ብርሃን ሲመለከት መልሶ ለጥቂት ደቂቃዎች ዓይኑ እንደሚጭበረበር (እንደሚታወር)፣ እንዲሁ ፈጣሪውን ካለማወቅ ጨለማም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ብርሃን የሚቀርብ ሁሉ አላዋቂነቱን ይረዳል፡፡ ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመደገፍ የሙሴን ታሪክ ማስረጃ አድርገን እስኪ እናቅርብ፡፡

ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ቤዛ እንዲሆን የመረጠው ሙሴን እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ሲያስተዋውቀውና ወደ አገልግሎት ሲጠራው የተገለጠለት በቁጥቋጦ ላይ በሚነድ ብሩህ እሳት አምሳል ነበር፡፡(ዘጸ 3፡2) ቀጥሎም ሙሴ ወደ ፈጣሪው ከቀረበ በኋላ ደግሞ ወደ ከነዓን የነጻነት ጉዞ ሲያደርጉ እግዚአብሔር ‹በደመና እና በእሳት ዓምድ› ተገልጦ መንገድ ይመራቸው ነበር፡፡(ዘጸ 13፡21) በስተመጨረሻም በሲና ተራራ ሕግን በሰጠው ጊዜ ራሱን ለሙሴ የገለጠለት ‹በጨለማ ፣በነፋስ ፣በጢስ› ነበር፡፡(ዘጸ 20፡18-21)

እስኪ የተገለጠባቸውን ሦስቱን ምሳሌዎች ቅደም ተከተሉን በደንብ እናስተውል፡፡ መጀመሪያ በብርሃን ፣ሁለተኛ ደመና በቀላቀለ የተከፈለ ብርሃን ፣በስተመጨረሻም በጨለማ ነበር፡፡ ይህም ሰው እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ በር ሲገባ የሚሰሙትን ሦስቱን ውስጣዊ ስሜቶች የሚያሳይ ነው፡፡ በመጀመሪያ በተማረው ጥቂት ትምህርት ብዙ ነገር ያወቀ፣ እግዚአብሔርንም በሰፊው የተረዳውና ሁሉ ነገር ብርሃን መስሎ ይሰማዋል፡፡ ከእኔ በላይ ዕውቀት ለሐሳር ይላል። ሆኖም ግን መንፈሳዊ ትምህርቱን እና ንበባቡን እያጠናከረ ሲመጣ ልክ ብርሃኑ በደመና እንደተከፈለ፣ ስለ እግዚአብሔር የሚያውቀው ዕውቀት ብዙ ተከፍሎ እንዳለበት እየተረዳ ይመጣል፡፡

በስተመጨረሻም የበለጠ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እየተቆራኘ ሲመጣ እስከዛሬ የተማረው እና ስለ ፈጣሪው ያወቀው ዕውቀት ሁሉ ወደ ኢምንትነት ይለወጥበታል፡፡ በብዙ ትምህርት ውስጥ ቢያልፍም  ምን ያህል አላዋቂ እንደሆነ ይረዳል፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
                +++ ይግባኝ! +++

አንድ ሰው ለብዙ ዘመናት አብሮት በፍቅር ይኖር የነበረ ወዳጁን በቅንዓት ተነሳስቶ ይገድለዋል፡፡ በዚህም የወንጀል ሥራው ተከስሶ የፍርድ ብይን ያገኝ ዘንድ ሰዎች ከችሎት ፊት አቆሙት፡፡ ዳኛውም ወንጀለኛው ለፈጸመው የጭካኔና ሰብአዊነት የጎደለው ክፉ ተግባር በሕጉ መሠረት የሚገባውን የዕድሜ ልክ እስራት ወሰኑበት፡፡ወንጀላኛውም በተሰጠው ፍርድ ፍትሐዊነት ላይ እንዳላመነበት እና  ለፍርዱ ማቅለያ የሚሆን የይግባኝ ጥያቄን ማቅረብ እንደሚፈልግ በእጁ እየጠቀሰ ዳኛውን ተለማመነ፡፡

በዚህ ጊዜ ዳኛው ምን ዓይነት ይግባኝ እንደሚያቀርብ ለመስማት የጓጉ መሆናቸውን በሚያሳብቅ መልኩ ቸኩለው እድሉን ሰጡት፡፡

ወንጀለኛ፡-ክቡር ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትልኝ የምፈልገው አንድ ነገር  አለ፡፡በርግጥ ይህን ሰው መግደሌን አልካድኩም፣ ነገር ግን እርሱን ለመግደል የፈጀብኝ እኮ አፍታ ነች እንደው ቢበዛ ዐሥር ደቂቃ ቢሆን ነው፡፡ ታዲያ እንዴት በዚህች አጭር ጊዜ ላጠፋሁት ጥፋት ዕድሜ ልክ ይፈረድብኛል? በማለት ጥያቄውን አቀረበ፡፡

      ዳኛው ምን ብለው የሚመልሱለት ይመስላችኋል? መቼም ወንጀሉን ለመፈጸም ከፈጀበት ጊዜ ጋር ተነጻጽሮ ፍርዱ ሊቀልለት ይችላል የሚል የየዋሕ ሰው ግምት እንደማይኖራችሁ አልጠራጠርም፡፡ በፍርዱ ሂደት የሚታየው ወንጀሉን ሲፈጽም የወሰደበት የጊዜ መጠን ሳይሆን በዚያች ሰዓት የፈጸማት የወንጀሏ ክብደት ናት፡፡

ውድ ምዕመናን!  አሁን እኛ የፍርድ ቤት ዘገባ ምን ይጠቅመናል ትሉ ይሆናል? ከዚህ በኋላ ግን የምንነጋገረው ፍትሕ ስለማይገኝባት ስለዚህች ምድር ፍርድ አይደለም፤ ስለ ሰማያዊው ፍርድ ነው እንጂ። ስለ ሥጋዊው የዳኝነትም ሥርዓት አይደለም፤ ስለመንፈሳዊው ፍርድ ነው እንጂ፡፡ ብዙ ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ስለ እግዚአብሔር ፍርድ ዘላለማዊነት (eternal punishment) ባሰቡ ቁጥር ‹የሰው ልጅ በዚህች ምድር የሚኖረው የዕድሜ ልክ ስልሳ እና ሰባ ቢበዛም ሰማንያ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የዕድሜ ወሰን ውስጥ ለተሠራ ኃጢአት እንዴት እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍርድን ይፈርዳል?› የሚል ጥያቄ በኅሊናቸው ይላወስባቸዋል፡፡

አንዳንዶቹም ለተገፉ ጠበቃ የሚሆን የእውነት ፈራጅ እግዚአብሔርን ፍርዱ ኢ-ፍትሐዊ (unfair judgment) ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ምንም ስለ ‹ዘላለማዊ ሽልማቱ› (eternal reward) ‹ለምን ዘላለማዊ ሆነ?› የሚል ጥያቄን አለማቅረባቸው ትዝብት ውስጥ የሚጥላቸው ቢሆንም እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ግን ከላይ ባለው አጭር ምሳሌ መልሳቸውን ያገኛሉ፡፡

አስተውሉ! ለወንጀለኛ መቼም ፍርድ እንደሚገባው ማንም የሚያምንበት ጉዳይ ነው፡፡ ወንጀለኛ ከወንጀል እስካልጸዳ ድረስ ፍርድ ከእርሱ ጋር እንደ ጥላ ትከተለዋለች፡፡ ቅጣትንም እንደ አክሊል በራሱ ላይ ደፍቶ ይመላለሳል፡፡ ለኃጢአተኛም እንዲሁ ነው፡፡ ራሱን በንስሓ መርምሮ ፣ወድቆ ተነሥቶ ፣በሥጋው በደሙ(ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል) አምላኩን እስካልታረቀ ድረስ ሁል ጊዜም ኃጢአተኛ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ኀዘኑን እጥፍ  የሚያደርገው ያ ኃጢአተኛ በዚህ አቋሙ እያለ በሞት ከተወሰደ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚድንበትን መንፈሳዊ ተግባር ማከናወን የሚችለው በምድር በሕይወተ ሥጋ እስካለ ድረስ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከራሷ ከክርስቶስ ከታነጸችበት የሐዋርያት ትምህርትም አላገኘችውምና ሰው ከሞተ በኋላ በሰማይ የሚሰግድበት ፣መንፈሳዊ ምግባራትን የሚያደራጅበትና ኃጢአቱን የሚያስወግድበት ሥፍራ አለ ብላ አታምንም፡፡ ‹እም ድኅረ ሞቱ ለሰብእ አልቦቱ ንስሓ›/ ‹ለሰው ከሞቱ በኋላ ንስሓ የለውም› የሚለውን የአበው ቃል መመሪያዋ ታደርጋለች እንጂ፡፡

ስለዚህም በዚህ መልኩ የሞተ ሰው ኃጢአተኝነቱ ለዘላለም ነውና ፍርዱም ለዘላለም በማይጠፋ በዲንና በሚቃጠል የእሳት ባሕር ይሆናል፡፡ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡(ራእይ 21፤8) ከእንግዲህስ ከነኃጢአታችን ብንሞት የምንድንበት መሥዋዕት የለምና፣ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ አምላክ በዓይነ ምሕረቱ እንዲመለከተን የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደተባሉት ወደ ተሾሙ ካህናት እንገስግስ። ንስሓ እንግባ፣ ቀኖናችንንም እንፈጽም። መጠየቅን በሚወድ በእርሱ ፊት ለፍርድ በቆምን ጊዜ መልስ የሚሆነንን የጽድቅን ጥሪት እናከማች!

‹አቤቱ እንደ ቸርነትህ ነው እንጂ እንደ በደላችን አይሁንብን!›

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
ጫካው ቢመነምንም፣
ዛፎች መጥረቢያውን መምረጥ አላቆሙም፤
ራሴን ተውና እየው እጀታዬን፣
በምን እለያለሁ አሁን ከአንተ ወገን፤
እያለ በመስበክ ሲያውቅ የኋላውን፣
ምሳሩም ጎበዝ ነው እጹን በማሳመን፤

(ሰውና ክፋትን ከማነጻጸር በቀር ሌላ ጭብጥ የለውም)
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
በዓመት ውስጥ ምንም ልንሠራ የማንችልባቸው ሁለት ቀናት ብቻ አሉ። አንደኛው 'ትናንት' ተብሎ ሲጠራ ሌላኛው ደግሞ 'ነገ' ይሰኛል። ስለዚህ ራሳችንን እና ሌሎችን የሚጠቅም በጎ ሥራ የምንሠራበት ትክክለኛው ቀን ዛሬ ነው።

"ዛሬ" የሥራ ቀን ነው!!!
በአፍ የገባ ማር ማረፊያው ሆድ ነው ተብሎ ሆድ ተቀዶ አይጨመርም። ሁሉም ሂደቱንና ሥርዓቱን ጠብቆ ሲከናወን መልካም ነው።

ሂደት የውጤት ያህል ቦታ አለው!
+++ ‹‹ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል›› መዝ 92፥12 +++

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተሰጋግሞ የመነሣት እድል ካገኙ እጽዋት መካከል አንዱ የዘንባባ ተክል ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤት ከሠራ በኋላ በመቅደሱ የውስጥ ግንቦች ላይ ከቀረጻቸው ምስሎች ውስጥ አንዱ የዘንባባን ቅጠል ነው፡፡(1ኛ ነገ 6፡29) በእስራኤላውያን ታሪክም ድል ሲቀናቸውና ሲደሰቱ በእጃቸው የሚገኘው እጽ ይኸው ዘንባባ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች የአንድ አገር መለያ አድርገው ከሚጠቅሷቸው ምልክቶች ውስጥ ‹‹የዘንባባ ዛፍ›› አንደኛው ነው፡፡(ዘዳ 34፡3) ከዚህ ሁሉ ደግሞ በጣም የሚያስደንቀው የሐዲስ ኪዳኑ ባለ ራእይ ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ጻፈው ሩጫቸውን በድል የጨረሱና ነጭ የለበሱ የጻድቃን ነፍሳት ‹‹የዘንባባን ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት›› መቆማቸው ነው፡፡(ራእይ 7፡19) ዘንባባ በምድር ላለ ደስታ ብቻ ሳይሆን በሰማይም ላለ የድል ነሺነትና የአሸናፊት መንፈስ መግለጫ ምልክት ሆኖ ያገለግላል፡፡

ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ጻድቃንን ለምን በዘንባባ ዛፍ ይመስላቸዋል? መዝሙረኛውስ ‹ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል› ሲል ለምን ዘመረ? ቅዱሳንን ከዘንባባ ጋር ምን አገናኛቸው?

ሁላችንም እንደምናውቀው ጣፋጭ ፍሬ ከሚሰጡ እጸዋት መካከል አንዱ ዘንባባ ነው፡፡ የዘንባባን ዛፍ ለየት የሚያደርገው ጣፋጭ ፍሬ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ሥሮቹ በጣም ጠንካራ እና ወደ ታች ጠልቀው የሚገቡ (የሚሰዱ) መሆናቸው ነው፡፡ ጸድቃንም እንደ ዘንባባ ፍሬ የሚጥም በጎ ምግባርን የተሸከሙ የሃይማኖት ተክል ሲሆኑ፣ የታነጹበትና የቆሙበት የእምነትና የፍቅር ሥሮችም በጣም የጸኑ እና ጥልቆች ናቸው፡፡

ሌላው የዘንባባ ዛፍ በየትኛውም ጊዜ ቢተከል ሊያፈራ የሚችልና በበረሃ የሚበቅል ልዩ ተክል ነው። ቅዱሳንም በጊዜውም ሆነ ያለ ጊዜው ጸንተው ይገኛሉ። በበረሃም እንደሚጸድቅ ዘንባባ በዚህች ክፋት በሞላባት ዓለም ውስጥ እየኖሩ በቅድስና ይገኛሉ።

የዘንባባ ዛፍ ልክ እንደ ሌሎች እጸዋት ብዙ ቅርንጫፎች የሉትም፡፡ በዚህም ምክንያት እንስሳት ፍሬው ወደሚገኝበት የዛፉ ጫፍ በቀላሉ ለመውጣትና ለመብላት ይቸገራሉ፡፡ እንዲሁ ጻድቃንም በጎ ሥራዎቻቸውንና መንፈሳዊ ደስታቸውን ከእነርሱ እንዲወስዱባቸው ለአጋንንት መግቢያ በር፣ መውጫ ቅርንጭፍ አያኖሩም፡፡ ሐሴቶቻቸውም ከፍ ያሉ ሰማያውያን በመሆናቸው ምድር ምድሩን የሚሄደው ሰይጣን በቀላሉ ሊተናኮላቸውና ደስታቸውን ሊያጠፋ አይችልም፡፡

ዘንባባ ብዙ ቅርንጫፎች የሌለው መሆኑ አንዳንዴ ድንጋይ እንዲወረወርበት እና በዱላ እንዲመታ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ ግን ‹‹ይቅር ባይ›› ተክል ነው፡፡ በተወረወረበት ድንጋይ እና ባረፈበት ዱላ ፈንታ የሚመልሰው ጣፋጭ ፍሬውን ነው፡፡ አንተ ድንጋይ ስትወረውርበት እርሱ ደግሞ እንደ ማር የሚጣፍጠውን ፍሬ ያዘንብልሃል፡፡ ሰይጣን ለእርሱ መግቢያ ምክንያት የማይሰጡትን ጻድቃን የሚፈትነው ለክፉ ዓላማው ማስፈጸሚያ የሚያደርጋቸውን ሰዎች በመጠቀም ነው፡፡ በእነዚህም ሰዎች አማካኝነት ብዙ የስድብ፣ የጥላቻና የስም ማጥፋት ድንጋዮችን ይወረውርባቸዋል፡፡ በበቀል ዱላ ሊያቆስላቸው ይሰነዝርባቸዋል፡፡ እነርሱ ግን የሰደቧቸውን ሰዎች በመመረቅ፣ የጠላቸውን በመውደድ፣ ለበቀል ስለሚያሳድዷቸው ሰዎችም በመጸለይ ጣፋጭ ፍሬዎቻቸውን ያዘንቡላቸዋል፡፡

በሆሳዕና ዘንባባ ይዘን ዘምረን፣ እንደ ዘንባባ ዛፍ አፍርተን፣ በኋላም ከጻድቃኑ ጋር ነጭ ለብሰንና በእጆቻችን የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘን ከበጉ ፊት ለመቆም ያብቃን!

=== ልክ እንደ ጻድቃኑ የዘንባባ ሕይወት ይስጠን!!! ===

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
በወዳጆቹ ቤት የቆሰለው ቁስል!
Channel photo updated
+++‹‹በለምጻሙ ስምዖን ቤት ሳለ›› ማቴ 26፥6+++

አይሁድ በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ግቢ ውስጥ ተሰብስበው በጌታ ሞት ላይ ሲመክሩ፣ መድኃኒታችን ግን በቢታንያ በስምዖን ቤት እራት ግብዣ ተቀምጦ ነበር፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ጌታ እራት የተጠራበት ቤት ባለቤት ‹ለምጻሙ ስምዖን› እንደ ሆነ ይናገራል፡፡ ጸሐፊው ስለ ምን ይህንን ሰው ስምዖን ብቻ ብሎ አልጠራውም? ‹ለምጻሙ› የሚለው ገላጭ ቃል መጠቀም ለምን አስፈለገው? በርግጥ ስምዖን በለምጽ ንዳድ የተያዘና በአይሁድ ዘንድም እንደ ረከሰ እና በደለኛ ተቆጥሮ የሚገለል ብቸኛ ሰው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ግን ጌታ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ በእርሱ ቤት ለእራት በተቀመጠ ጊዜ፣ ቅዱስ ጄሮም እንደሚናገረው ይህ ሰው ካለበት ለምጽ ሁሉ ነጽቶ ነበር፡፡ ታዲያ ወንጌላዊው ስለ ምን ከለምጹ የነጻውን ስምዖን ‹‹ለምጻሙ›› ሲል ጠራው?

ይህ ያለ ምክንያት አልሆነም፡፡ ጌታችን በስምዖን ቤት ለእራት ተቀምጦ ሳለ የሚፈጸም ቀጣይ ወሳኝ ታሪክ ስላለ፣ ‹ለምጻሙ› የሚለው ገላጭ ለዚያ መግቢያ የሚሆን ወሳኝ ቃል ነበር፡፡ ቀጥሎ የምናገኘው ታሪክም አንዲት በኃጢአት የተመረረችና ነፍሷ የጎሰቆለባት ሴት፣ መንፈሳዊውን ምሕረት ፈልጋ ጌታችን ወዳለበት መምጣቷና የያዘችውን እጅግ ውድ የሆነውን ሽቱ ከፍታ በጌታ በራሱና በእግሮቹ ላይ ማፍሰሷን የሚናገር ነው፡፡ ይህች ሴት ቀድሞ በዝሙት ትኖር ነበረች ብትሆንም ዛሬ ግን የሽቱና የእንባን መባ ይዛ ወደ ክርስቶስ ቀርባለች፡፡ በዘመኑ ብዙዎች ያስጨንቃቸውና የክርስቶስን መድኃኒትነት ይፈልጉት የነበረው ለሥጋዊ ሕመማቸው ነበር፡፡ ምንም የሥጋ ሕመም የሌለባት ይህች ሴት ግን ባልተለመደ ሁኔታ የነፍሷን ሕመም (ኃጢአት) በምሕረቱ መድኃኒትነት ለመሻር ወደ ጌታችን ስትሮጥ መጣች፡፡ ይህም ሥራዋ እጅግ በጣም የምትደነቅ መንፈሳዊት ሴት ያደርጋታል፡፡

በዚህ ወንጌል የተጠቀሰችው ባለ ታሪክ ትሠራ የነበረው ሥራ በሁሉ ዘንድ አስነዋሪ የነበረውን፣ እንኳን በአምላክ ፊት ቀርቶ በሰው ፊት እንኳን ቀና ብሎ የማያስቆመውን ዝሙት ነበር፡፡ ታዲያ ወደ ክርስቶስ ለመምጣት ድፍረት የሰጣት ነገር ምንድር ነው? እንዴት ወደ መድኃኔዓለም ቀርባ ‹‹ማረኝ›› ለማለት በቃች? ካልን መልሱ ቀላል ነው፤ ጌታ ‹በለምጻሙ ስምዖን› ቤት እንደ ተገኘ አይታ ነው፡፡ ክርስቶስ ራሳቸውን ከሚያመጻድቁ ፈሪሳውያን መካከል በአንዱ ቤት ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ ባለ ሽቱዋ ማርያም ድፍረት አግኝታ ወደ እርሱ ባልመጣች ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ሰዎች እንደ ርኩስና በደለኛ ቆጥረው ያገሉት በነበረው ስምዖን ቤት ነውሩን ሁሉ አስወግዶለት አብሮት ለእራት እንደ ተቀመጠ ስላየች፣ የሚበዛው ድካሜን አይቶ የበለጠ ይራራልኝ እንደ ሆነ እንጂ ለእርሱ ያደረገውን ቸርነት ለእኔ አይነሳኝም ብላ በተስፋ ወደ ፈጣሪዋ ገሰገሰች፡፡ እጅግ የሚያስደንቅ ተስፋ ነው!!!

ዛሬም መድኃኔዓለም ክርስቶስ በለምጻሙ ስምዖን ቤት አለ፡፡ ስለዚህ ‹አይሰማኝ ይሆን› የሚለውን ጥርጣሬያችንን ትተን ወገባችንን ያጎበጠውን ኃጢአት በንስሐ ከእግሩ ስር ለማራገፍ ፈጥነን ወደ እርሱ እንቅረብ፡፡ በለምጻሙ ስምዖን ቤት ለእራት የተቀመጠ አምላክ በፍጹም ጸጸት ብንመለስ የእኛንም ቤት (ሰውነት) አይንቅም፡፡ ይልቅ ሳይረፍድ ቶሎ ሄደን ከእግሮቹ ስር እንውደቅ!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
+++ትሕትና ምንድር ነው?+++

ትሕትና ምንድር ነው? ብዙ ጊዜ በእኛ ዘንድ የተናቀ ልብስ መልበስ ፣ አንገት መስበር ፣ ዝግ ብሎ ማውራት እና ‹እኔ በደለኛ የማይገባ ሰው ነኝ› እያሉ ደጋግሞ መናገር እንደ ትሑት ያስቆጥር ይሆናል፡፡ ነገር ግን የትሕትና ትርጉም ከዚህም በላይ ነው፡፡ በርግጥ ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮች የአንድ ትሑት ሰው ከፊል መገለጫ ጠባያት ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን በማድረግ ብቻ ትሑት መሆን ቢቻል ኖሮ፣ በዓለም ላይ ያለው የትዕቢተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ትሕትናን በተጠቀሱት ውጫዊ ምግባራት ብቻ የምንረዳው ከሆነ ከእውነተኛ ትርጉሙና ማንነቱ እንዳናሳንሰው ስጋት አለኝ፡፡

ትሕትና በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ እውነተኛ ኑሮ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ስለ ትሕትና ሲያስብ እነዚህን ሁለት ነገሮች አብሮ በትኩረት ሊያሰላስል ይገባዋል፡፡ እነርሱም አንደኛ ተፈጥሮውን (መሬታዊ ፣ትቢያ መሆኑን) አለመዘንጋት ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ ተቀባይነቱን ለዘወትር ማስታወስ ነው፡፡ ሰው በጫማው እየረገጠ የሚራመደው አፈር እንደሆነ ሲያስብ ደካማነቱን ይረዳል፡፡ ስለዚህም በነገሮች ሁሉ ‹አቤቱ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ› እያለ ረድዔተ እግዚአብሔርን የሚማጸን ትሑት ይሆናል፡፡ (መዝ 103፡14) ተቀባይነቱንም ሁል ጊዜ የሚያስታውስ ከሆነ ለሌሎች በሚያደርጋቸው በጎ ሥራዎች አይኩራራም፡፡ ብልጫም አይሰማውም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ሳይሆን ከአምላኩ ከተሰጠው ላይ ቀንሶ የሚያካፍል ምስኪን ምጽዋተኛ ስለሆነ፡፡ ሐዋርያውስ ቢሆን በቆሮንቶስ መልእክቱ በታላቅ ቃል ‹አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለምንድር ነው?› ሲል የሚገስጸው ስለዚሁ አይደለምን? (1ኛቆሮ 4፡7)፡፡

ሶርያዊው አባት ማር ይስሐቅ ስለ ትሕትና ትርጉም አንድ ቁም ነገር ያካፍለናል፡፡ ምን አለ? ‹ውድቀትና ኃጢአቱን እያነሣ ራሱን የሚወቅስና የሚያዋርድ ጥሩ ቢያደርግም ትሑት ተብሎ ግን አይጠራም፡፡ ትሑት ሰው ራሱን ማሳመንና ኅሊናውም ይህን ሐሳብ እንዲይዝ መጫን አይጠበቅበትም፡፡ እንዲሁ ራሱን ምንም አድርጎ ይቆጥራል እንጂ› ሲል አስተማረ፡፡ እንደ ማር ይስሐቅ ትምህርት ከሆነ ትሑት ለመሆን ሲባል ራስን ማስጨነቅ ወደ ትሕትና ጫፍ ለመድረስ ሯጭ(ተጋዳይ) መሆንን የሚያሳይ እንጂ ‹ትሑት› አያሰኝም፡፡ እውነተኞቹ ትሑታን ሌላ የሚጋፋ እና ትግል የሚጠይቅ አንዳች የበላይነት (የእኔነት) ስሜት ሳይሰማቸው እንዲሁ ራሳቸውን የሰው ሁሉ መጨረሻ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ባሕታዊም ‹ትሑት ሰው የሚባለው ራሱን የሚሰድብና የሚያዋርድ ሳይሆን ፤ ከሌሎች ሰዎች በሚደርስበት ስድብና ትችት ፊት ፍቅሩ ሳይቀንስበት መቆም የሚችል ሰው ነው› በማለት ያስተማረው ይህን የፍጹማኑን ትሕትና ለማሳየት ነው፡፡

አባ መቃርዮስ እንደተናገረ የትሕትና ተቃራኒ የሆነች ትዕቢት የኃጢአቶች ሁሉ ራስ (እናት) ናት፡፡ ታዲያ ትዕቢት ለኃጢአቶች ሁሉ እናት ከሆነች ትሕትና ለጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ራስ ብትሆን ምን የሚያስደንቅ ነገር አለ?!፡፡ ለዚህም ነው እኮ ቅዱሳን አበው ትሕትናን ‹እጸ ሕይወት›/‹የሕይወት ዛፍ› እያሉ የሚጠሯት፡፡ አዳም በገነት አንድ ሺ ዓመት ከኖረ በኋላ ወደማታልፈው መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) ለመግባት የሚታደስባትን እጸ ሕይወት አምላኩ በገነት ዛፎች መካከል ፈጥሮለት ነበር፡፡ እርሱም ትእዛዘ እግዚአብሔርን ጠብቆ ሺ ዘመን ቢቆይ ኖሮ ፤ ላይወድቅ ላይጎሰቁል በእጸ ሕይወት ታድሶ መንግሥተ እግዚአብሔርን ይወርስ ነበር፡፡ ከእጸ ሕይወት በኋላ መውደቅ የለምና፡፡ እንዲሁ ትሕትናም እጸ ሕይወት ነች፡፡ ትሕትናን ገንዘብ ካደረጉ በኋላ ውድቀት እና ከእግዚአብሔር መለየት የለም፡፡

ትሕትና በጎ ሥራዎች ሁሉ የሚጠበቁባት አጥር ቅጥር ነች፡፡ ከእግዚአብሔር የምናገኛቸው ጸጋዎችም ያለ ትሕትና ሊጸኑ ፣ ሊሰነብቱ አይችሉም፡፡ ቅዱሳን በጽኑዕ ተጋድሎ እና በፈጣሪ ቸርነት የገነቡትን የጸጋ ግንብ ሰይጣን እንዳያፈርስባቸው ፈጣሪያቸው የሚከላከልላቸው ትሑታን የሚሆኑበትን ደዌ ወይም አንዳች ነገር በእነርሱ ላይ በማምጣት ነው፡፡ ባለ ብዙ ጸጋ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የእግዚአብሔር አሠራር ሲያስረዳን ‹በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ…ተሰጠኝ ይኸውም እንዳልታበይ ነው› በማለት ግልጽ አድርጎ ይናገራል፡፡(2ኛ ቆሮ 12፡7) በሰውነቱ ጥላ እና በልብሱ እራፊ ሙት የሚቀሰቅሰው ፣ሕሙም የሚፈውሰው ሐዋርያ እንደ ስንጥር በሚወጋ ራስ ምታት መያዙ ፤ ተአምር ሲያደርግ በተመለከቱት ሰዎች በስህተት እንዳይመለክና ልብን ሰቅዞ በሚይዝ አጉል ውዳሴ እንዳይጠለፍ አድርጎታል፡፡ በርግጥም የገባሬ ተአምራት የቅዱስ ጳውሎስን ሕመም ያዩ ሰዎች በእርሱ ድካም ውስጥ የሚሠራ የእግዚአብሔርን ኃይል በግልጽ ተረድተዋል፡፡

እግዚአብሔር በጎውን ዋጋ የሚሰጠን መልካም ስላደረግን ይመስላችኋል? አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ መልካም የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር በጎውን ዋጋ ላይቀበሉ ይችላሉ፡፡ ለምን? ከአምላክ ዘንድ በጎ ዋጋ የሚያሰጠው መልካም ማድረግ ሳይሆን ፤ መልካሙን ነገር በትሕትና ማድረግ በመሆኑ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ከተነሡ ውዝግቦች (ክህደቶች) መካከል አንዱ የሆነው የ‹Pelagius controversy› ለዚህ ጉዳይ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የአየርላንድ መነኩሴ በሆነ ፔላጊዮስ የተጠነሰሰ ሲሆን ፤ አጠቃላይ ምልከታውም ‹ሰው ብቻውን በሚያደርገው በጎ ሥራ ይድናል› የሚል በረድዔተ እግዚአብሔር መደገፍንና ትሕትናን አውልቆ የሚጥል የክህደት ትምህርት ነበር፡፡ በእውነትም የማታልፍ የማትለወጥ የእግዚአብሔርን ርስት ፣ ፈራሽ በስባሽ በሆነው ሰውነቴ ብቻ ሠርቼ ገንዘብ አደርጋለሁ ከማለት በላይ ተሻለ ክህደት ከወዴት ሊመጣ ይችላል?

እስኪ ጽሑፋችንን በቅዱስ መቃርስ ምሳሌ እንዝጋው፡፡ አባ መቃሪ በአንድ ወቅት ስለ ትሕትና ሲያስተምር ‹አንድ ባለጠጋ የነበረ ንጉሥ ያለውን ሀብት በአደራ መልክ ከአንድ ደሃ ዘንድ ቢያኖር ፤ ያ ደሃ በእነዚያ ብሮች እና ወርቆች ሊመካ ይችላልን? እንደ ራሱ ንብረትስ በመቁጠር የባለቤትነት ስሜት ሊሰማው ይገባል?› ሲል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ቅዱስ አባት ምሳሌ መሠረት ያ ባለጠጋ ንጉሥ እግዚአብሔር ነው፡፡ አደራ ተቀባዩ ነዳይ ደግሞ እኛ ነን፡፡ አደራውም በእጃችን ያሉ በጎ ነገሮች ሁሉ ናቸው፡፡ ያሉንን መልካም ነገሮች እንደ ራስ ንብረት መቁጠርና በሌላው ላይ መኩራራት አደራ ተቀባይነትን እንደ መርሳት ነው፡፡ ሰው ባልፈጠረው በጎነት እንዴት ይኩራራል?

በትሑታኑ ቅዱሳን ጸሎት ይጠብቀን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
እጅግ ጥልቅ የጸሎት ሕይወት የነበረው፣ አካሉ አልቆ በአጥንቶቹ እስኪቆም ድረስ የሚጾመው ተሐራሚው ቅዱስ አባ ጳጉሚስ ከእለታት በአንዱ ቀን ይህን ተመለከተ፡፡ ቅዱሱ ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ሕማማት እያሰበ ከእንባ ጋር አብዝቶ ይሰግድ ነበር፡፡ ከዓይኑ የሚወርደው እንባ ከሰውነቱ ወዝ ጋር እየተቀላቀለ ወደ መሬት በመውረዱ ምክንያት የሚሰግድበትን ቦታ አረጠበው፡፡ አባ ጳኩሚስም ይህን ወደ ጌታው እያመለከተ "ይኸው አንተን አገኝ ብዬ እንዲህ እደክማለሁ" ሲል ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜም መድኃኒታችን ለአባ ጳጉሚስ ተገልጦ "እኔም እንጂ ላንተ ብዬ እንዲህ ሆኜ ተሰቅያለሁ" በማለት በእለተ ዓርብ እንደ ተሰቀለ ሆኖ የተወጋ ጎኑን፣ የፈሰሰ ደሙን አሳየው፡፡ ቅዱሱም የጌታው ሕማም ከሕሊናው በላይ ሆኖበት ወድቆ ምሕረትን ለምኗል፡፡

+++++++++++++

ሕሊናቸው የክርስቶስን ሕማም ከማሰብ አቁሞ የማያውቀው አባ መብዓ ጽዮን መድኃኔዓለምን :- ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ፡፡ ስለ ራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ›› ሲሉ ለመኑት፡፡ ጌታም ‹‹መከራ መስቀሌን ለማየት ትፈቅዳለህን?›› ብሎ ጠየቃቸው። ጻድቁ አባ መባዓ ጽዮንም ‹‹አዎ! አይ ዘንድ እወዳለሁ›› አሉት። ያን ጊዜም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረው ታየ፣ በራሱም ላይ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር። እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው ታያቸው። ይህን የመድኃኔዓለም መከራ የተመለከቱ የጻድቁ ዓይኖችም ፈዝዘው እስኪጠፉ ድረስ ትኩስ እንባዎችን ሲያዘንቡ ኖረዋል።

‹‹ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ›› - ‹‹ኃይሌና መጠጊያዬ እርሱ ጌታዬ ነው!››

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com