Dn Abel Kassahun Mekuria
15.2K subscribers
527 photos
43 videos
1 file
840 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚያገኙበት በባለቤቱ የተከፈተ ቻነል ነው።

ይወዳጁን

ለፌስቡክ ገጽ
https://www.facebook.com/AbelKassahunMekuria12?mibextid=ZbWKwL

ለyoutube
https://youtu.be/s6Cn-jMYjrk?si=Tw7lXr62xkGQtL9_

ለInstagram
https://www.instagram.com/abelkassahunm?igsh=OW
Download Telegram
+++ "እመቤታችን ከጌታ ዕርገት በኋላ" +++

መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቅዱስ መስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ክቡር ደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያቱ አደራ ሰጥቷል፡፡ በመጀመሪያው ምዕት ዓመት በነበረው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የጌታ እናቱ እመቤታችን የነበራት ድርሻ ትልቅ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ እመቤታችን በሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቤት ሳለች፣ የሐዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ራስ እና ፈጻሚ የሆነው ክርስቶስ የተገኘባትን እርሷን ለማየት ከሁሉም የዓለም ክፍላት የሚመጡ ሰዎች ብዙ ነበሩ፡፡ ድንግልም ወደ እርሷ የመጡትን ሁሉ እየባረከች፣ ያዘኑትንም እያጽናናች፣ በንስሓ ሕይወት እንዲኖሩ በመምከር ተስፋና ደስታን እየሞላች ትሸኛቸው ነበር፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በምድር ላይ ለመገለጡ፣ እንደ ሕፃናት ጥቂት በጥቂት ለማደጉና በመጨረሻም ለፈጸመው የቤዛነት ሥራው ሁሉ እናቱና አገልጋዩ ከምትሆን ከእመቤታችን የበለጠ ምስክር ከየት ሊመጣ? እርሷን ለማየት ባይጓጉ ነበር የሚደንቀን፡፡

ከሰባ ሁለቱ አርድዕት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሉቃስም ወንጌሉን ሲጽፍ በሕይወቷ ውስጥ የተፈጸሙ እርሷ ብቻ የምታውቃቸውንና ብቻዋን ሆና የሰማቻቸውን እንደ ብሥራት ያሉ ታሪኮችን በመንገር እረድታዋለች፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በቃልም በመጽሐፍም አይሁድን ተከራክሮ ድል ባደረጋቸው ጊዜ፣ ተቆጥተው ድንጋይ ሲያነሡበትና ሲከቡት ከሩቅ በማየቷ የሰማዕትነት ሥራውን በጽናት ይፈጽም ዘንድ በጸሎቷ እንዳበረታችው በጥንታውያን የታሪክ መዛግብት ሰፍሮ እናገኛለን፡፡

እመቤታችንን የማየት ዕድል ካገኙት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዲዮናስዮስ ዘአርዮስፋጎስ እርሷን ባየ ጊዜ ሐዋርያቱ ሰው መሆኗን ባይነግሩት ኖሮ አምላክ መስላው እንደ ነበር ጽፏል፡፡ የፊቷን ደም ግባትና ሰላም፣ በእርሷም ላይ ይንጸባረቅ የነበረውን የቅድስና ብርሃን አይቶ በልጇ የማያምን እንደ ሌለም መስክሯል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀ መዝሙርና የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስም ለመምህሩ (ቅዱስ ዮሐንስ) በላከለት መልእክት፣ ክርስቲያኖች በሚሳደዱበት በዚያ ዘመን የእግዚአብሔር እናቱ እመቤታችን በስደቱ ደስተኛ እንደ ሆነች፣ በመከራዎችም ውስጥ ሆና እንደማታጉረመርምና እርሷንም ይነቅፉ በነበሩ ሰዎች እንዳልተቆጣች ይናገራል፡፡

እመቤታችን በልጇ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ታሪኮች የተፈጸሙባቸውን ስፍራዎች መጎብኘት ትወድ ነበር፡፡ የልደቱን ነገር፣ የእረኞችና የመላክቱን ዝማሬ፣ የጥበበኞቹን ስጦታ አስባ ቤተልሔም ትሄዳለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን መከራ ወደ ተቀበለበት ስፍራ መሄድ ታዘወትራለች፡፡ በዚያም የተቀበላቸውን ሕማማት፣ የደረሰበትን ተዋርዶ እና መከዳቱን እያሰበች ታነባለች፡፡ ‹ይህ ልጄ የተገረፈበት፣ ይህ የእሾህ አክሊል የተቀዳጀበት፣ ይህ ደግሞ መስቀል ተሸክሞ የሄደበት፣ ይህ የተሰቀለበት ነው› ትላለች፡፡ ወደ መቃብሩ ስፍራ ስትመጣ ግን በልዩ ደስታ እየተሞላች ‹‹ይህ በሦስተኛው ቀን ከሞት የተነሣበት ቦታ ነው›› ትል ነበር፡፡

በተሰጣት ቃል ኪዳን እኛ ኃጥአን የሆንን ልጆቿን ታስምረን!


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
ኢጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፤ የክርስቲያን ደም በከንቱ አይፍሰስ፤ እርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም። ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን።

ንጉሥ አጤ ምኒልክ ለሙሴ ሸፍኔ ከላኩት ደብዳቤ የተወሰደ።
(ይህን ምርጥና ልቡናን ሰቅዞ የሚይዝ የገጣሚት ወርቅነሽ ቱፋን ግጥም ልጋብዛችሁ። ግጥሙ ትንሽ ዘለግ ያለ ቢሆንም በያዘው መልእክት ፋታ ሳይሰጥ የሚነበብ ነው)

መቼ ትመጣለህ ?

          መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
     በኃጢአት አልክበር
    እድሜዬን አልጨርስ
                   አልብላው መንዝሬ
     ንገረኝ ጊዜውን ቆሜ ልጠብቅህ
    ግራ ቀኝ አልባክን እንዴት ነው አመጣጥህ
    ትዘገይ እንደሆን ላትጠራኝ ቶሎ
     ከፀበለስ ልብላ ስሜቴ ገንፍሎ
    ምክያቴን አብዝቼ አግዝፌ ልቆይህ
    ሔዋን አስታኝ ነው ሰይጣን አሳስቷት
             መክሯት ነው ልበልህ
   ለሥጋዬ ልስጣት ሥልጣኑን በሙሉ ነፍሴን ትበድላት
    ለጊዜው ትጠቀም አንተ ከዘገየህ ትሁነው እንዳሻት
    ጊዜ አገኝ እንደሁ በተራገምኩበት መመረቅ እንድችል
   እስከጊዜው ድረስ ነፍሴ ታንጎራጉር ትንደደው ትቃጠል
   ሰዎች ተስፋ ቆርጠው ይኸው በዚህ ሰሞን ታሪክ ያወራሉ
  ያ! ስምንተኛው ሺህ ከተነገረ እንኳ ቆይቷል እያሉ
  ሰዉ ጽድቁን ትቷል ሁሉም በያለበት ሀሜቱን ቀጥሏል
  መጋደል መጣለፍ መቋሰል መቧደን ዝርፊያውም በርክቷል
  እንኳን ዳግም ም'ጻት የዓለም ፍጻሜ ስምህ ተዘንግቷል
  መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
                                 . . . . . . . . . . . .
  ግዴለም ንገረኝ ልክ እንደኖኅ ጊዜ ዘመኑን አስላና
  ሃያዋ ብትበቃኝ ለንሰሓ ጊዜ  በመቶው ልዝናና
ገና አልበረደኝም ሰውነቴ ግሎ ውስጥ አካሌ ዘንቶ
  ዓለሙን ያስሳል አንተ ከዘገየህ ለምን ሥራ ፈትቶ
እበላው እንደሆን የሰበሰብኩትን ከሌላው ዘርፌ
እኖረው እንደሆን  እንደማቱሳላ እድሜዬን አትርፌ
ሺህ ዓመቴን ወስደህ የአንተን አንድ ቀን ትሰጠኝ እንደሆን
ምናለበት ብዘርፍ ምናለ ብዘሙት መዘግየትህ ላይቀር
ከምድር እሰከ ሰማይ ተዘርግቶ 'ማያልቅ ለበዛው ኃጢአቴ
  ጊዜ ካበደርከኝ እንዲሰረዝልኝ እንዲፋቅ ጥፋቴ
  ልክ እንደ ኢያሱ ፀሐይን አቁመህ ከጠበቅኸኝ በቃኝ
ዛሬን ልዝናናበት ኃጢአት ልጨማምር  ጨለማ ሳይወርሰኝ
ይኸው ሰዉ ሁሉ ነገሩን ዘንግቶ ሁሉ ሆድ ብሶታል
"ይዘገያል "አሉ እያለ ያወራል ኃጢአት ይሸምታል
እኔም በቀደም 'ለት ከደጀ ሰላሙ ብዙ ጉድ አይቼ
ገዛሁት በርካሽ ኃጢአትን ከደጅህ ከቤትህ አግኝቼ
ግዴለም ንገረኝ ሃያው ይበቃኛል በሌላውስ ላትርፍ
እንዴት ከሌላው ህዝብ እኔ ተለይቼ እንደ ጅል ልንከርፈፍ
   መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
                                      . . . . . . . . . . . .
   ሌላውን ልበድል  ነገርን ልዶልት ህዝብህንም ልቁጠር
   ከድንኳን ደጃፍ ተቀምጬ ላሹፍ ዘፈን ላንጎራጉር
   ጊዜ ከሰጠኸኝ የምለይበትን ዘፈንን ከመዝሙር
    ንሰሐ ገባለሁ ልክ ስትመጣ ዛሬን ግን ልጨፍር
   ከጥብርያዶስ ባሕር ኃጢአት ዓሣን ላጥምድ
   ትዘገይ እንደሆን ምናል ይህን ብትፈቅድ?
    ይኸው ሰዉ ሁሉ ግራ ያጋባኛል ነገር እያማታ
   ኃጢአትን አግብቶ ትዳርን መስርቶ ጽድቅን እየፈታ
   በክፋት ላያ ክፋት በዚያ ላይ ስምህን በፍፁም ደርቦ
  ጽድቅና ኃጢአትን ባንድ እያካሄደ በደስታ ተከቦ
   ጻድቅ ሲሸማቀቅ አንገቱን ሲደፋ ተመልካችም ሲያጣ
  እንዳሻው በመሆን ኃጥህ ሲዝናናበት ሲስቅ በለበጣ
  ዘመናት አለፉ ይኸው ዛሬም የስምህ አጥፊዎች
   ሥራቸውን ሰደው በደንብ ተስፋፍተው ዙሪያውን ብዙዎች
  ከደሃው ላይ ሰርቀው ምስኪን አስለቅሰው ለታቦት ሲያገቡ
  ወገን ጦሙን አድሮ ሲበሉ ሲጠጡ ሲያገቡ ሲጋቡ
  እንኳንስ መምጣትህ ስምህ ተዘንግቶ አዳሜ ሲጨፍር
  እኔስ ምን ተዳዬ ከዚህ ህዝብ መሃል ተለይቼ ልቅር
  ይልቅስ ንገረኝ  ትመጣ እንደሆን ፀሐይ ሳትገባ 
   አሊያ ልደባለቅ ከምድር ወገኖቼ ከወጣው ወጥቼ 
                                ከገባው ጋር ልግባ
                            
  መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
                                     . . . . . . . . . . . .
      የበራፌ ጥላ ከበር እስኪከተት 'ማትመጣ ከሆነ
   አሸንክታብ ላርዝም ክብሬንም ልፈልግ ጊዜዬ ባከነ
   ዓለሙን ልከተል የዛሬን ልደሰት ነገ እመለሳለሁ
   አንተ ዛሬ ትመጣ ወይም እንደምትቀር በምን ዐውቀዋለሁ
  ይኸው በዚህ ሰሞን ሰዎቹ በሙሉ ታሪክ ያወራሉ
   እሱ ቀርቷል ብለው፣ ባንተም ላይ ደርበው ጣዖት ያመልካሉ
   ይኸው  በዚያ ሰሞን ሥጋ ቤቱ ደጃፍ ሁሉ ተኮልኩሎ  
    በሁዳዴ ምድር  ቁርጥ ያወራርዳል መስቀል  አንጠልጥሎ
    እኔስ አያምረኝም አንተ እንደው አትመጣ  ብበላ ምናለ
    ጠበል እረጫለሁ ወደፊት ጾማለሁ አንተ ከዘገየህ
    እንዲሁ በከንቱ ጊዜ ከሚባክን ቅዳሴ አስቀድሼ
     ዳንኪራ ቤት ብሄድ                         
   ጽድቅን እንደሆነ መቼም አላጣትም ለኃጢአት ብሰደድ
    የልቤ ግድግዳ ቢጠቁር በክፋት ደግሞም ቢበሰብስ
     ዛሬ አንተ ካልመጣህ ነገ እታጠባለሁ ንሰሐ ሳሙና
                                        እስካለልኝ ድረስ!
    ምናለ ብሳደብ ሌላውን ብጎዳ ማንም እናዳይነካኝ
   ግዴለም ለነገ ግራዬን ቢያጮሉኝ ቀኜን ሰጣለሁኝ
       እንደ  ሕፃን በርሬ ያሻኝ ቦታ ልድረስ ያሻኝን ልተንፍስ
   አኳኩሉ ልበል በኃጢአት ጫካ እስክትመጣ ድረስ

        መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
                                            . . . . . . . . . . . .
       ምናለ እንደዴማስ ይህችን ዓለም ብወድ አንዴ ብተፈቅድልኝ
  በኋላ መጣለሁ ልክ እንደ ድሮዬ አገለግላለሁ ቆመህ ከጠበከኝ
  ትዘገይ እንደሆን  በቶሎ ማትመጣ አሊያ የምትቀር
  ምናል ሳማ ሰንበት ብሄድ ለሽርሽር
  ቢራዬን ገዝቼ ቱታዬን አጥልቄ
  ልክ እንደቱሪስቶች ምግቤን ሰንቄ
  በውጭዎች ፈሊጥ እየተቀናጣሁ ደርሼ ብመለስ
  ምናለ ባልጸልይ ምናል ባላስቀድስ
  ይኸው ትናንት እንኳ ትናንትና ማታ
          ሰዎች ተኮልኩለው ከዐው ደምህረቱ
  አየሁኝ ሲጣሉ በቡድን ተከፍለው ነገር ሲዶልቱ
እኔስ ምን አለበት በነሱ ብጽናና በኃጢአት ባድግ
አንተ እንደሁ አትመጣ ስንት ዘመን ሆነኝ ቆሜ ሳደገድግ
ፍጹም ልመሳሰል ከዚህ ዓለም ጋራ ማንነቴ ጠፍቶ
አንተ ከዘገየህ ምናል ይህ አካሌ ቢኖር ህይወት አጥቶ
ጊዜዬን ልሠራበት ለኃጢአት ልነሣ ለጽድቅህም ሞቼ
  ክርስትናው እንደው መቼም አይቀርብኝ
                ነገ እቆርባለሁ በምርኩዝ መጥቼ
       መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
                            . . . . . . . . . . . .
  ይኸውና ዛሬ ሁሉ ቀላል ሆኖ መፈራትህ ጠፍቶ
  የነዲዮስቆሮስ የነጴጥሮስ እምነት ከኋላ ተገፍቶ
  ሰው ሰውን እያየ በሥጋ ሲጽናና አምላክን ረስቶ
   ከዐውደ ምሕረቱ አንተ ተሸፍነህ እኔን ስሙኝ በዝቶ
   እምነት እንደፋሽን ራሱን ተኩሎ ራሱን ቀብቶ
  በደፋሮች ጩኸት መቅደስህ ታውኮ መቅደስህ ሲረክስ
        ዐዋቂ አንገቱን በደፋበት መድረክ  ታዋቂ ሲነግሥ
       ነጠላና ቀሚስ የጽድቅ መገለጫ በሆኑበት ዘመን
     በስሜት ተነድቶ በስም ብቻ ሲሮጥ ህዝብህም ሲባዝን
     እኔስ ምን ተዳዬ ለግዜው ብደሰት
     ሆ! ካለው ሆ !ብዬ አብሬው
  ሆሳዕና ብዬ ዛሬ ብዘምርም
   ከሳምንት በኋላ በዚያው አንደበቴ
           ይሰቀል !ይሰቀል! ማለቴ አይቀርም 
እምነቱ ባይገባኝ እኔ ምን አገባኝ
                         ዝም ብዬ ሮጣለሁ
  ምን ችግር አለበት አንተ ከዘገየህ
  ምስጢረ ሥላሴን ውዳሴ ማርያምን
                        ቀስ ብዬ እማራለሁ
  አንተ እንደ ምትመጣ ወይ እንደ ምትቀር
                     በምን ዐውቀዋለሁ

              መቼ ትመጣለህ ነገ ወይስ ዛሬ?
                              . . . . . . . . . . . .

ገጣሚ መምህርት ወርቅነሽ ቱፋ
መቼ ትመጣለህ?
+++‹በተአምሩ አይደለም በቃሉ ድል ነሣው እንጂ!›+++

       በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ያለ አምላካችን በባሕረ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ከተጠመቀ ፣አብም በደመና ከመሰከረለት በኋላ የመልካም ሥራዎች ሁሉ መጀመሪያ የሆነችውን ጾም ይጾም ዘንድ ወደ ቆሮንቶስ በረሃ ሄደ፡፡ በኋለኛው ዘመን በፍቅሩ ሲነዱ ‹ከሀገር ምድረ በዳ ፣ከዘመድ ባዳ› ይሻለናል ብለው በበረሃ ለሚንከራተቱ መናንያን በር ይከፍት ዘንድ በሰው ልጆች ፍቅር ጥማት የታመመ እርሱ የውኃ ምንጭ ልምላሜ ወደ ሌለበት በረሃ ገሰገሰ፡፡ ይህንንም ሲያደርግ ማንም አላስገደደውም፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ በሆነች በገዛ ፈቃዱ ወደ ገዳም ወረደ እንጂ፡፡

       በዚያም በረሃ ለአርባ ቀናት ጾመ፡፡ አምላካችን ለምን አርባ ቀን ብቻ ጾመ? ወደ ሃምሳ ፣ወደ ስልሳ ቀናት ለምን አላሳደገውም? ካልን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክንያቱን ይናገራል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ትልቁን ጾም የጾሙት እነ ሙሴ አነ ኤልያስ አርባ ቀን ያህል ነበር፡፡ ስለዚህ አምላካችን እነርሱ ከጾሙት ቀን አትርፎ ለሃምሳ ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑ ቀናት ቢጾም ኖሮ ‹አይ ይህስ የሰውነት ጠባዕይ ፣ባሕርይ ቢጠፋለት ነው› ብለው ሰውነቱን የሚጠራጠሩ ይኖራሉና ‹ለአጽድቆተ ትስብዕት› (በእውነት የሰውን ሥጋ እንደተዋሐደ ያስረዳ ዘንድ) ሲል እንደ ቀደምት አበው እንደ ሙሴ እንደ ኤልያስ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ በእርግጥ ሌሎች ነቢያት እና የብሉይ ኪዳን ጻድቃን ቢጾሙ ኃይል ብርታት የሚሆናቸው፤ የሚያጸናቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ ግን በገዛ ሥልጣኑ ያለ ማንም አጋዥነት ይህን ጾም ጾሞታል፡፡
ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም የሙሴን ሕይወት ተርጉሞ ባስተማረበት ድርሳኑ ሙሴ በሲና ተራራ አርባ ዕለታት እንዴት ያለ ምግብ ሊቆይ ቻለ? ብሎ ይጠይቃል፡፡ እውነትም ያለ ምግብ ከሰባት ቀናት ያለ ውኃ ደግሞ ከሦስት ቀናት በላይ መሰንበት የማይችል የሰው ልጅ እንዴት አርባ ቀናት ያለምንም ሥጋዊ መብልና መጠጥ ሊቆይ ቻለ? የሚለው ጥያቄ እኛንም ያሳስበናል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ግን መልሱን እዚያው ሳይርቅ ይነግረናል፡፡ ምን የሚል ይመስላችኋል…? ረሃብ እና ጥምን የሚያስረሳ ሥጋዊ ድካምንም ሁሉ የሚያርቅ ‹የእግዚአብሔርን ፊት አይቷልና!!!›፡፡ በእርግጥም በጽድቅ የፈጣሪውን ፊት በመመልከት ክብሩን ሲያይ የማይጠግብ ማንም የለምና ፤ ሙሴ የፈጣሪውን ፊት እያየ ከገባባት ተደሞ እና መንፈሳዊ ጥጋብ እንዴት ሥጋዊ ረሃብ ፣ሥጋዊ ጥም ቀስቅሶ ሊያነቃው ይችላል? (መዝ 07.05)፡፡ ታዲያ ሙሴ ገጸ አምላኩን ተመልክቶ ረሃብ ከጠፋለት ‹እግዚአብሔር አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው› መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ አርባ ቀን አርባ ሌሊት መጾሙ ምን ያስደንቃል?

ቀድሞ ሔዋንን ብቻዋን አግኝቶ በፈተናው መረብ ጠልፎ የጣላት ሰይጣን አሁንም አምላካችንን በበርሃ ብቻውን ቢያየው የለመደውን ድል ፍለጋ ወደ እርሱ በፈተና ቀረበ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊው እንደሚነግረን ጌታችን የተፈተነው በአርባኛው ቀን ብቻ ሳይሆን አርባውን ቀን በሰይጣን እየተፈተነ ነው የሰነበተው (ማር 1.03)፡፡ መጻሕፍት በአርባኛው ቀን የተፈተናቸውን ፈተናዎች ብቻ ይዘው መገኘታቸው በሚበልጠው ለመናገር ነው እንጂ እነዚህን ብቻ ነው የተፈተነው ማለታቸው አይደለም፡፡ በፈተና የሚያልፉ ክርስቲያኖች በደል ሳይገኝበት ‹በነገር ሁሉ የተፈተነ› እና በድካማቸው የሚራራላቸው አምላክ እንዳላቸው አውቀው ይጽናኑ ዘንድ እርሱ በበጎ ለሚፈተኑ ሁሉ በኩር ሆነ (ዕብ 4:15)፡፡

            አምላካችን የተፈተነው ከተጠመቀ በኋላ ነበር፡፡ ይህ ለእኛ ምን ያስተምረናል? ምዕመናን ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ኃይል ፣ልጅነትን በጥምቀት ከተቀበሉ በኋላ የሚያስተናግዱት የፈተና ሕይወት እንዳለ ነው፡፡ ሰይጣን ደስ የሚሰኝበት ምንም አይነት የጽድቅ ሥራ ባለመኖሩ ፣የፈተና ወጥመዱን የሚዘረጋው ፈቃዱን ለሚፈጽሙ ደካሞች ሳይሆን በጥምቀት የእግዚአብሔርን ልጅነት ላገኙ እና የዲያቢሎስን ክፋት በመልካም ተጋድሎ ለሚቃወሙት ጽኑዓን ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹ኃይልን የምንታጠቀው እኮ ለመዋጋት ነው እንጂ ለመቀመጥ አይደለም› ይለናል! እውነት ነው!፡፡ እግዚአብሔር በጥምቀት መንፈሳዊውን ኃይል የሚያስታጥቀን ከጠላት ዘንድ ፋታ የሌለው ውጊያ ስላለብን አይደለምን? ታዲያ ለምን ለፈተና ሁል ጊዜ እንግዶች እንሆናለን? 

            አምላካችን በወንጌል በምሳሌ እንዳስተማረው ኢየሩሳሌም ከተባለች ልዕልና ኢያሪኮ ወደ ተሰኘች ትሕትና አንድ ሰው የተባለ አዳም ሲወርድ በመንገድ አጋንንት አግኝተው ፈትነው ፣ልጅነቱን ቀምተው ፣በኃጢአት ቁስል አቁስለው በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት እንደሄዱ ፤ የአዳምና የሔዋንን እዳ ለመክፈል ሰው የሆነ ክርስቶስም ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርዱ በሚያገኙት የቆሮንቶስ በረሃ አዳምን ያቆሰሉትን አጋንንት ድል ነስቶለታል (ሉቃ 10)፡፡ 

             መድኃኒታችን በሰይጣን ለቀረበበት ለእያንዳንዱ ፈተናዎች የሰጣቸውን ምላሾች አንስተን እንማር ብንል ብዙ ቁም ነገር የሚገኝበት ቢሆንም ዛሬ ግን በዚህ ጽሑፍ አናነሣቸውም፡፡ ነገር ግን ሦስቱንም ፈተናዎች ድል የነሣበትን አንድ መንፈሳዊ ጥበብ ፍለጋ እስኪ ደጅ እንጥና!፡፡ ታሪኩ ተሟልቶ የቀረበበትን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አራትን ስታነቡ ሦስቱም ፈተናዎች ጋር የሚገኝ ተመሳሳይ መልስ አላገኛችሁም? ‹ተብሎ ተጽፏል› የሚል አገኛችሁ አይደል፡፡ አምላካችን ሰይጣን በፈተነው ጊዜ ሰይጣንን ድል የነሣው በተአምራት ወይም አሁን እኛ ልንገልጸው በማንችለው መንገድ ኃይሉን ተጠቅሞ አይደለም፡፡ ሰይጣንን ድል የነሣው ተጽፎ በተቀመጠ ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ለምን ይመስላችኋል ? በእውነት ሰይጣንን በተአምራት ድል ቢነሣው ኖሮ በዛሬ ዘመን ያለን ደካሞች የሰይጣንን ፈተና ላለመቃወም ምክንያት ባገኘን ነበር፡፡ ‹እርሱን በተአምር ካልሆነ በምን ያሸንፉታል ፤ እኔ ደግሞ ይህ ጸጋ የለኝም› ብለን ተሳንፈን እና ተስፋ ቆርጠን በተቀመጥን ነበር፡፡ ነገር ግን የሰይጣንን ፈተና ከእኛ ቆርጦ ለመጣል አምላካችን የሰጠን በዋዛ የማይገኘውን ሰይፍ ተአምር ሳይሆን ፤ ለሁሉ በጸጋ የተሰጠውንና በየቤታችን የምናኘውን የቃሉን ሰይፍ ነው፡፡ ይህንን ሰይፍ እንጠቀምበት፡፡ አፋችን በዚህ ሰይፍ ይሞላ! እንደነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹አፈ ሰይፍ› ፣‹አፈ መጥባሕት› እንሁን!!!

                     መልካም የጾም ጊዜ ይሁንልን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com

(በድጋሚ የተለጠፈ)
"ትሕትና ምንድር ነው?"

https://youtu.be/O0aDoxLLJc8
"ጾም ከመላእክት ጋር በአንድ ማዕድ መቀመጥ ነው"
ቅዱስ አትናቴዎስ

መልካም የዐቢይ ጾም!!!
+++ ሌላ ቆሮንቶስ ከዚህ አለ! +++

ክብር ይግባውና መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሰይጣንን ወግቶ ድል የነሣው በቆሮንቶስ በረሃ ነበር። እንደ አይሁድ ትውፊት ከሆነ ሰይጣንና የክፋት መናፍስቱ ከእጽዋት የተራቆተ በረሃማን ስፍራ ለማደሪያነት ይመርጣሉ። በርግጥም ሕያዋን የሆኑ ጻድቃንን፣ ከውኃ ዳር እንደ ተተከለ ዛፍ የለመለሙ እና ፍሬያማ የሆኑ ቅዱሳንን የማይወድ ሰይጣን፣ ለማደሪያነት የውኃ ምንጭ እና ልምላሜ የሌለበትን በረሃ ይመርጣል ቢባል የሚደንቅ ነገር አይደለም። ይህም በመሆኑ መድኃኒታችን ሰይጣንን አጎሳቁሎ እና አዋርዶ ያሸሸው ሰልጥኖ ከሚኖርበት በረሃ ገብቶ ነው። ዛሬም የቅድስና ምንጭ የደረቀበት፣ ከበጎ ምግባር ተራቁቶ ገላጣ መሬት በመሆን ለሰይጣን ምቹ ማደሪያ የሆነ ሌላ በረሃ በዚህ አለ። ይህም በረሃ ሃይማኖት የሰለለበት፣ የመልካምነት ፍሬም ደርቆ የረገፈበት የእኛ ሰውነት ነው። በቆሮንቶስ በረሃ የነበረውን ፈታኝ ድል የነሣ ጌታ፣ በእያንዳንዳችን ሰውነት መሽገው የተቀመጡትን መናፍስት "ከኋላቸው ሂዱ" ብሎ ገስጾ ከእኛ ያርቅልን።

መልካም የጾም ጊዜ ይሁንልን!
እጅግ የሚያስፈራው ዘላለማዊ እሳት ሳይሆን፣ ያለ ክርስቶስ ዘላለማዊ መሆን ነው!
+++ ተዋናይ +++

ጌታችን ከአደገባት ናዝሬት ወደ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቃ ያለች ሴፎሪስ (Sepphoris) የምትባል በገሊላ የምትገኝ ከተማ ነበረች። ይህችም ከተማ በጣም ደማቅ በመሆኗ "የገሊላ ጌጥ" ተብላ ትጠራለች። በውስጧም ታላቅ የቴያትር አዳራሽ ነበራት።  በጥንታውያን የሮምና የግሪክ ቴያትር ታሪክ ልክ እንደ ዛሬው ገጸ ባሕርይን ለመላበስ (ለመምሰል) የሚረዳ የሜካፕ ሙያ ሳይመጣ በፊት፣ ተዋናይዎቹ የኃዘንና የደስታ መልክ ያላቸውን ጭንብሎች ለብሰው ነበር የሚተውኑት። እነዚህም ጭንብሎች "persona" የሚል መጠሪያ ሲኖራቸው ትርጉሙም "ጭንብል"/"mask" ማለት ነው። (በነገራችን ላይ personality የሚለው ቃል persona or mask ከተባለው ከዚሁ ግንድ መውጣቱን ልብ ይሏል።)

የሥነ ቅርስ ተመራማሪዎችን ትኩረት ከሳቡ እና በብዛት የኀሠሣ ቁፋሮ ከሚደረግባቸው የዓለማችን ክፍሎች አንዷ ሴፎሪስ ነች። ታዲያ ጌታችን ላደገባት ናዝሬት ቅርብ በሆነች በዚህች ከተማ በተደረገ የarcheology ቁፋሮ የተለያዩ የቴያትር ጭንብሎች ተገኝተው ነበር።

ጌታችን በወንጌል ጻፎችና ፈሪሳውያንን "ግብዞች"
እያለ ይጠራቸው ነበር። ግብዝ የሚለው ቃል ደግሞ በግሪኩ "Hypocrite" የሚለው ሲሆን ትርጉሙም "ተዋናይ"/"Actor or play maker" ማለት ነው። በመሆኑም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩትን የማይኖሩ ነገር ግን በሰው ፊት ፍጹም መስለው ለመታየት የሚፈልጉትን አይሁድ፣ በዘመኑ በነበሩትና ጭንብል ለብሰው በሚጫወቱት የቴያትር ባለሙያዎች ስም "ተዋናይ" ብሎ መጥራቱ ያለ ምክንያት አይደለም። 

ኑሮው በግልጽ የሚታወቅ እውነተኛ ሰው ቢሳሳት እንኳን ተመክሮ የመታረምና የመመለስ እድል አለው። የሚያስመስል ሰው ግን ለትምህርትና ለተግሳጽ እንኳን ያስቸግራል።
እንዲሁ እንዳስመሰለም የእውነት ሳይኖር ይሞታል። ታዲያ ከዚህ ሰው በላይ ራሱን የሚበድል ማን ነው?

በክርስትናችን እና በኑሯችን ተዋናይነት ይቅርብን!


ዲያቆን አቤል ካሳሁን
abelzebahiran@gmail.com
አንዱ ሰው ፈንክቶ ፍርድ ቤት ቀረበ። ዳኛው "በምን ብትመታው ነው እንዲህ ያቆሰልከው?" ብለው ጠየቁት። ወንጀላኛውም "ኸረ በቲማቲም ነው" ሲል መለሰ። በመልሱ የተገረሙት ዳኛው "ደግሞ ቲማቲም እንዲህ መጉዳት ጀመረ?" ቢሉት፣ " እርሱማ ማሸጊያው ቆርቆሮ ነበር" አላቸው ይባላል።

ሐሳቦቻችንን ለምናሽግባቸው ቃላት እንጠንቀቅ። ሐሳቡ ለስላሳ ሆኖ በቃላቶቻችን መሻከር የሰው ነፍስ እንዳናቆስል።