ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
58.2K subscribers
68 photos
69 videos
19 files
1.72K links
ዳዒ ወሒድ በኢሥላም እና በክርስትና መካከል ያለውን ልዩነት እና አንድነት በንጽጽር የሚያስቀምጥ ወንድም ነው። ለዚህም የቋንቋ፣ የሰዋስው፣ የዐውድ፣ የተዛማች እና የሥነ አመክንዮ ሙግት በማቅረብ የሚታወቅ ተሟጋች እና ጦማሪ ነው። ለሙግቱ ነጥብ በዋነኝነት የሚጠቀምባቸው ቋንቋ ዐማርኛ፣ ግዕዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ዐረቢኛ፣ ዕብራይስጥ እና ግሪክ ናቸው። መልካም የንባብ፣ የጥናት፣ የማነጻጸር ጊዜ ይሁንልዎ!
Download Telegram
የዘካህ አወጣጥ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

2፥110 ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም ስጡ፡፡ وَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ وَآتُوا الزَّكَاةَ

የዘካ ገንዘብ ከተቀማጭ ላይ ከመቶ 2.5 % የሚሰጥ ነው፥ ነቢያችን”ﷺ” ከሁለት መቶ ዲርሀም 5 ዘካህ እንደሚወጣ ተናግረዋል። ያ ማለት የዘካህ ሒሳብ በመቶ ዲርሀም 2.5 ይሆናል፥ ስሌቱ 5፥2=2.5 ነው፦
ሡነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 9, ሐዲስ 18 ዐሊይ”ረ.ዐ” እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ ”ሁለት መቶ ዲርሀም ለአንተ በሆነች ጊዜና ዓመት ከሞላች አምስት ደራሂም ይወጣል፥ በአንተ ምንም ነገር አይሆንም ሃያ ዲናር እስኪሆን ድረስ”። عَنْ عَلِيٍّ، – رضى الله عنه – عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم بِبَعْضِ أَوَّلِ هَذَا الْحَدِيثِ قَالَ ‏”‏ فَإِذَا كَانَتْ لَكَ مِائَتَا دِرْهَمٍ وَحَالَ عَلَيْهَا الْحَوْلُ فَفِيهَا خَمْسَةُ دَرَاهِمَ وَلَيْسَ عَلَيْكَ شَىْءٌ – يَعْنِي فِي الذَّهَبِ – حَتَّى يَكُونَ لَكَ عِشْرُونَ دِينَارًا

በዚህ ሐዲስ መሠረት የአንድ ሰው ካፒታል 20 ዲናር ወይም 200 ዲርሀም ሲሆን ዘካህ ይወጅበታል። በሸሪዓህ የዘካህ አነስተኛ የክፍያ መጠን “ኒሷብ” نِصاب ይባላል፥ ይህም ኒሷብ የሚለካው 20 ዲናር ወይም 200 ዲርሀም ሲሆን ነው። “ዲናር” دِينَار‎ ማለት “የወርቅ ሳንቲም”gold coin” ማለት ሲሆን “ዲርሀም” دِرْهَم‎ ማለት ደግሞ “የብር ሳንቲም”silver coin” ማለት ነው። ይህ በጥንት ጊዜ የሸቀጥ ገንዘብ”commodity money” ነው። “ዲናር” እና “ዲርሀም” የሚለኩት በሚስቃል ነው፥ “ሚስቃል” مِثْقَال የሚለው ቃል “ሰቀለ” ثَقَلَ ማለትም “ከበደ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ክብደት” ማለት ነው።
1 ሚስቃል ወርቅ 4.25 ግራም ነው፥ 20 ሚስቃል ወርቅ ደግሞ 4,25x 20 = 85 ግራም ወርቅ ይሆናል ማለት ነው።
1 ሚስቃል ብር 2.975 ግራም ነው፥ 200 ሚስቃል ብር ደግሞ 2.975x 200= 595 ግራም ብር ይሆናል ማለት ነው።

በዘካህ ላይ የሚወጅበው ኒሷብ 85 ግራም ወርቅ ወይም 595 ግራም ብር ነው።
አንድ ሙሥሊም ያስቀመጠው ካፒታል ዓመት ከሞላው እና ያም ካፒታል 85 ግራም ወርቅ ወይም 595 ግራም ብር ያክል ከሆነ ዘካህ ማውጣት ግዴታው ነው።
ዘካቱል ማል የሚወጣበት አነስተኛ ዋጋ የብር ኒሷብ ስለሆነ አብላጫው ምሁራን የብር ኒሷብን መሠረት ባደረገ መልኩ ከዚያ እንዲወጣ ፈትዋ ሰተዋል፥ ስለዚህ አንድ ሰው ዓመት የተቀመጠ 148,750 ብር(ገንዘብ) እና ከዛ በላይ ካለው ዘካህ ማውጣት ግዴታ አለበት።

እንዴት? ካላችሁ የብር ኒሷብ ወደ ወረቀት ገንዘብ”Fiat money” ለመቀየር ብርን ዛሬ ባለው የወቅቱ ግብይት ለናሙና ያክል መሥራት ይቻላል። በኢትዮጵያ አንድ ግራም ብር"silver" አሁን ባለኝ መረጃ 250 ብር"ገንዘብ" ነው፥ ስናሰላው 250×595= 148,750 ብር(ገንዘብ) ይሆናል።
ለምሳሌ፦ እኔ 200 ሺህ ብር ቢኖረኝ ከ 200 ሺህ ብር ላይ 2.5 % ዘካህ ሲሰላ 5,000 ይወጅብብኛል፥ ስናሰላው 200,000×2.5፥100= 5,000 ይሆናል። ስለዚህ ዓመት የሞላው 148,750 ብር እና ከዛ በላይ ዘካህ ማውጣት ስለሚወጅብ ዘካህን መስጠት አንርሳ፦
2፥110 ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም ስጡ፡፡ وَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ وَآتُوا الزَّكَاةَ

ተውሒድ ኢሥላማዊ ጥሪ ማኅበር በመጅሊሥ ፈቃድ የሚንቀሳቀስ ተቋማችን ሲሆን ከቤት ለተባረሩ ሠለምቴዎች ማቋቋሚያ የዘካን ሐቅ ለመስጠት ስለተዋቀረ መስጠት የምትፈልጉ ከዚህ በታች ያሉትን የቦርድ አባላት ማናገር ትችላላችሁ።
ኢብኑ ረሻድ https://tttttt.me/IbunReshed
አቡ ኑዓይም https://tttttt.me/arhmanu
አቡ ሩመይሳ https://tttttt.me/aburumaisa037
ዐብዱ ረሕማን https://tttttt.me/Abi_Abik
እስሚዞ https://tttttt.me/@Esmitiz_hubi

አምላካችን አሏህ ዘካን ከሚሰጡ ባሮቹ ያድርገን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
እኚህ ሰው ማን ናቸው?

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

15፥95 ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንልሃል፡፡ إِنَّا كَفَيْنَاكَ الْمُسْتَهْزِئِينَ

ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ ወጣትም ሆነ አዛውንት ስለ እሳቸው ሲወራ "ጆሮ ዳባ ልበስ" የሚል የለም፥ ሁሉ ስለ እሳቸው ሲወራ አዳሜ ሆነ ሔዋኔ ጆሮውን አስግጎ ይሰማል። ከሁሉም ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ የሚጠሏቸው ሳይቀር እንኳን ቢሆን ስለ እሳቸው ለመስማት እና ስለ እሳቸው ለማወቅ ይፈልጋሉ፥ ዝም ብለህ ሰው በተሰበሰበበት መሀል ገብተህ እና ድምፅህን ከፍ አድርገህ፦ "እከሌ" ወይም "እከሊት" ብለህ ብትጣራ ፊቱን እና ትኩረቱን ወደ አንተ የሚያዞረው የጠራከውን ስም ባለቤት ብቻ ነው። ከሌለም ደግሞ ማንም ፊት እና ትኩረት የሚሰጥክ አይኖርም፥ ነገር ግን ሰው የተሰበሰበበት ስፍራ ሄደህ የእሳቸውን ስም ጠርተህ ንግግር ብትጀምር ሁሉም ፊቱን እና ትኩረቱን ወደ አንተ ያደርጋል። ትኩረት የማይሰጥህ የለም ቢባል ቅጥፈት ወይም እብለት አሊያም ግነት አይሆንብኝም፥ ስለ እሳቸው ለማወቅ የማይሰለፍ አይኖርም።

፨ እኚህ ሰው የእልፍ አእላፋት መጻሕፍት ርእስ በመሆን ብዙ ጸሐፊያን የከተቡላቸው ናቸው፣

፨ እኚህ ሰው በሁሉም ልብ ውስጥ በአሉታዊ ሆነ በአንታዊ በሁለት ወገን እንደተሳለ ሰይፍ ሰርስረው የገቡ ናቸው፣

፨ እኚህ ሰው አስተምህሮታቸው የተሟላ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ የሕይወት ዘይቤ በመሆኑ "የዓለማችን ተግዳሮት ነው" የተባለላቸው ናቸው፣

፨ እኚህ ሰው "የዓለማችን ቁጥር አንድ አውንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖ አሳዳሪ" ተብለዋል፥ ለሕሩያን አውንታ ተጽዕኖ እንዲሁ ለእኵያን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳዳሪ ናቸው፣

፨ እኚህ ሰው ስለ እርሳቸው ማንነት የገባው ሰው፦ "ሕይወትህን መስዋዕት አርግ" ቢባል ያለ አንዳች ማቅማማት ሕይወቱን እስከ ሞት የሚያደርግላቸው ናቸው፣

፨ እኚህ ሰው በታሪክ ውስጥ እሳቸውን ለማነወር፣ ለማበሻቀጥ፣ ለማብጠልጠል ብዙ ጦማሪያን ጦምረዋል፣ ብዙ ኃያሲያን ኃይሰዋል፤ ብዙ ተቺዎች ተችተዋል፣ ብዙ ተሳላቂዎች ተሳልቀዋል። ቅሉ ግን የጦማሪያን ጦማር፣ የኃያሲያን ኂስ፣ የተቺዎች ትችት፣ የተሳላቂዎች ስላቅ ከሟቾች ጋር ሲያልፍ የእሳቸው ስም እና የሰዎችን ሕይወት የቀየሩበት መጽሐፍ እስካሁን አለ የተባለላቸው ናቸው።

እኚህ ሰው ማን ናቸው? አዎ! የዓለማቱ ጌታ የአሏህ መልእክተኛ እና የነቢያት መደምደሚያ ነቢዩ ሙሐመድ"ﷺ" ናቸው። በእርሳቸው ላይ የወረደው ሐቅ ለሰዎች የሚጠቅም ስለሆነ በምድር 1400 ዓመት ቆይቷል፥ ባጢል ቢሆን ኖሮ በእንጭጩ ኮረፋት ሆኖ ተግበስብሶ ይጠፋ ነበር፦
13፥17 እንደዚሁ አላህ ለእውነት እና ለውሸት ምሳሌን ያደርጋል። ኮረፋቱማ ግብስብስ ኾኖ ይጠፋል፥ ለሰዎች የሚጠቅመውማ በምድር ላይ ይቆያል፡፡ እንደዚሁ አላህ ምሳሌዎችን ይገልፃል"*፡፡ كَذَٰلِكَ يَضْرِبُ اللَّهُ الْحَقَّ وَالْبَاطِلَ ۚ فَأَمَّا الزَّبَدُ فَيَذْهَبُ جُفَاءً ۖ وَأَمَّا مَا يَنفَعُ النَّاسَ فَيَمْكُثُ فِي الْأَرْضِ ۚ كَذَٰلِكَ يَضْرِبُ اللَّهُ الْأَمْثَالَ

"ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፥ ከአምላክ እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም። በእርግጥ ከአምላክ ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ" እንዳለው ገማልያ ብዙ ሰዎችበእርሳቸው የተነሳ ከአምላክ ጋር እየተቆራረጡ ነው፦
ሐዋርያት ሥራ 5፥38-39 አሁንም እላችኋለሁ፦ ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም! ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፥ ከአምላክ እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም። በእርግጥ ከአምላክ ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ"።

ገማሊያ እንደተናገረው ይህ የነቢያችን"ﷺ" እሳቦት ከሰው ከሆነ ይጠፋ ነበር፥ ግን የነቢያችን"ﷺ" ግልጠተ መለኮት ከፈጣሪ ስለሆነ ገና በእንጭጭነቱ የመካህ ቁሬይሾች፣ የመዲና በኑ ቁሬይዛህ፣ የሮሙ ባዛንታይን በዕውቀት መሞገት ሲያቅታቸው በጉልበት ሊጠፉት ሞክረው አልተሳካላቸው። ከርሞም ሆነ ዘንድሮም እሳቸው ላይ ለሚሳለቁን ተሳላቂዎች አሏህ በቅቶላቸዋል፥ በእርሳቸው ላይ የወረደውን የአሏህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋት ቢፈልጉ እና ቢጠሉም አሏህ ብርሃኑን ገላጭ ነው፦
15፥95 ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንልሃል፡፡ إِنَّا كَفَيْنَاكَ الْمُسْتَهْزِئِينَ
61፥8 የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ሊያጠፉ ይሻሉ፥ ከሓዲዎቹ ቢጠሉም እንኳ አላህ ብርሃኑን ገላጭ ነው፡፡ يُرِيدُونَ لِيُطْفِئُوا نُورَ اللَّهِ بِأَفْوَاهِهِمْ وَاللَّهُ مُتِمُّ نُورِهِ وَلَوْ كَرِهَ الْكَافِرُونَ

ይህንን ብርሃን ለማጥፋት እፍ ባሉ ቁጥር እያነደዱት መሆኑን ይዘነጋሉ፥ ኢሥላም በፍጥነት መጠነ ሰፊ የእድገት መርሓ ግብር እየታየበት ያለው በምዕራባውያን መሆኑ እፍ ባሉ ቁጥር የሚያነዱበት ውጤት ነው። ሚስማር በተመታ ቁጥር እንደሚጠብቅ ዲኑል ኢሥላም በተነቀፈ ቁጥር ይስፋፋል። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

“ፊዳከ አቢ ወኡሚ ያ ረሡሉሏህ” فِدَاكَ أَبِي وَأُمِّي يَا رَسُول اللَّه

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
አሥ ሠላሙ ዐለይኩም ሙሥሊም ወንድሞቼ እና እኅቶቼ!

"እውን ኢየሱስ የባሕርይ አምላክ ነውን? የሚለው ይህ የንጽጽር መጽሐፍ በድጋሚ በገበያ ላይ ውሏል።

ክርስቲያኖች ሆይ!
ንጽጽር እኮ የጀመርነው እኛ ሳንሆን ፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች ናቸው፥ እኛም የሰጡንን መጽሐፍ አንብበን ማነጻጸር ጀመርን። ንጽጽር ክልክል አይደለም፥ በፕሮቴስታንት እና በኦርቶዶክስ ሥነ መለኮት ውስጥ የተካተተ ኮርስ አለ። አንዱ ከሌላው ቢማር ምን ችግር አለ? እወቁልን እያልን አንዱ ሌላው እንሰብክ የለ? በእርግጥ ተዛላፊዎች ቢኖሩም አሳብ መሞገት እና መዝለፍ ይለያያል፥ የሰውን እምነት መሳደብ፣ ማበሻቀጥ እና ማነወር ካለ ይህ ብሽሽቅ ንፕውና በሁለቱም እምነት የተወገዘ ነው።

እንደውም በቅርቡ "እውነተኛ አምላክ ማን ነው? አሏህ ወይስ እግዚአብሔር" በሚል የተጻፈ በቅድስት ሥላሴ ዩንቨርስቲ አዳራሽ አስመርቀዋል፥ መጽሐፉ በሁሉም የማኅበረ ቅዱሳን መጻሕፍት መደብር ሲገኝ የእኛ መጽሐፍ ግን በየትኛውም የኢሥላማዊ መጻሕፍት መደብር ውስጥ ነገር ተፈርቶ እንዳይረከቡ ሆኗል።

በ ንጽጽር ዙሪያ መጻፍ፣ መሞገት፣ መማማር፣ መወያየት በሁለቱም ሥነ መለኮት ችግር ስልፕሌለው እንደውም የሚበረታታ ነው። የሃይማኖት ገባኤ፦ "መጻፍ፣ መስበክ፣ መማማር፣ መወያየት እና ማነጻጸር ይፈቀዳል" ብሏል፥ "ክልክል ነው" ካሉን ግን ታዛዥ ነን ከሁለታችንም ወገን ሁላችንም እናቆማለን። ኢንሻላህ!

ስንክሳሩ በተሠግዎት መቅድም እና በአንድ ታሪካዊ ሥነ መለኮት መግቢያ የተሰነደ፣ በሰባት ዐበይት ሥልታዊ ሥነ መለኮት የተሰደረ እና በአንድ ጉልኅ ማጠቃለያ የተሰነገ ነው። መልካም የንባብ፣ የጥናት፣ የምርምር እና የማነጻጸር ጊዜ ይሁንልዎ!

መጽሐፉ የሚገኝበት አድራሻ! በቴሌ ግራም ነው፦
http://tttttt.me/merkatozon

ሌሎቻችን ሼር እናድርግ!
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተሠጠ መግለጫ!

በወቅታዊው በማኅበራዊ ሚዲያ እየተካሄደ ያለው የሃይማኖት ትንኮሳ ከማን እንደተጀመረ በግልጽ አስቀምጣችኃል፥ እውነት ነው ግለሰቡ ኦርቶዶክስን አይወክልም። ግለሰቡን በጭፍን የሚከተሉ ጀሌዎቹንም ልክ ማስገባት አለባችሁ። ሰው አመዛዝኖ ይፈርዳል በደንብ ታዝባችኃል እናመሰግናለን።

ሌሎቻችን ሼር እናድርገው!
አሥ ሠላሙ ዐለይኩም ያ ጀመዓህ

የሃይማኖት ንጽጽር ብዙዎች ዲኑል ኢሥላምን እንዲያውቁ እና እንዲሠልሙ ምክንያት የሆነ የማስተማር ጥበብ ነው፥ ያው አጠቃቀሙ ላይ ጥቂት ሰዎች ለብሽሽቅ ቢጠቀሙበት ማለት ነው። ከዚያ ጋር ተያይዞ "ንጽጽር ይቁም" የሚል ጥቂት ድምፅ እየሰማን ነው፥ ይህ ከበስተ ኃላ ሌላ አጀንዳ አለው። የጤናም አይደለም፥ የደዕዋን መስክ ሳይገባቸው ውኃ ሊቸልሱ የሚሞክሩ አካላት ናቸው። እንደ እኛ ግን እንደውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ባይ ነን፥ እንደውም የደዕዋን አድማሱን አስፍተን በይቱብ በስፋት ተከታታይ ትምህርት ለማስተማር አስበናል። ኢንሻላህ!
ይቱባችንን ስላገዱት 100 ሺህ እና ከዛ በላይ የዩቱብ ቻናል ያለው ካለ ከቻለ ሊላህ ብሎ በነጻ ይስጠን ካልቻለ እንገዛዋለን። የምትችሉ ልጆች ከዚህ በታች ያሉትን የቦርድ አባላት ማናገር ትችላላችሁ።
ኢብኑ ረሻድ https://tttttt.me/IbunReshed
አቡ ኑዓይም https://tttttt.me/arhmanu
አቡ ሩመይሳ https://tttttt.me/aburumaisa037
ዐብዱ ረሕማን https://tttttt.me/Abi_Abik
እስሚዞ https://tttttt.me/@Esmitiz_hubi

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
የአይሁድ ራባይ ስለ ሙሥሊም እና ኢሥላም እንዲህ አሉ፦ "ሙሥሊሞች ፍጹም አሓዳዊያን"Monotheists" ናቸው፥ ተመሳሳይ አምላክን እናመልካለን። በተለያየ ስም እንጠራዋለን። ... በእኛ መጻሕፍት ውስጥ ኢሥላም ጥንታዊ ሃይማኖት ነው፥ ይህ የኖኅ ሃይማኖት እንዲሁ የራሱ የአዳም ሃይማኖት ነው"።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom
Audio
«አቻነት ፍለጋ ⚡️ የ16 ዓመት ጉዞ» በሚል ርዕስ አሕመዲን ጀበል ዛሬ ያስነበበው ጽሑፍ በድምፅ

ጸሐፊ፦ ኡሥታዝ አሕመዲን ጀበል

አቅራቢ፦ ወንድም ሐቢቢ በሽር

የሌባ ዓይነ ደረቅ

መርካቶ ላይ ሌባ ሰርቆ እየሮጠ እራሱን ለማዳን "ሌባ ሌባ" ይላል፥ ከዚያ ሕዝቡ ተሰራቂ እንጂ ሰራቂ እርሱ አይደለም ብለው እንዲሉ ምክንያት ይሆናል፥ አሊያም ተሰራቂ ማን እንደሆነ እንዳይታወቅ ይሆናል። በተመሳሳይ ሶሻል ሚድያ ላይ ተሳዳቢዎቹ እራሳቸውን ለማዳን "ተሳዳቢ" እያሉ ከዚያ ሕዝቡ ተበዳይ እንጂ በዳይ እነርሱ አይደለም ብለው እንዲያስቡ ምክንያት እየሆነ አሊያም ተበዳይ ማን እንደሆነ እንዳይታወቅ እያረጉ ነው።
"የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ" የሚል አገርኛ ብሒል አለ።
ይህ የኡሥታዝ አሕመዲን ጀበል ጽሑፍ እውነታውን ቁልምጭ አርጎ ያስቀምጣልና ይደመጥ!

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom
ሴት እርሻ ናት!

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

2፥223 ሴቶቻችሁ ለእናንተ እርሻ ናቸው፥ እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹኔታ ድረሱ፡፡ نِسَاؤُكُمْ حَرْثٌ لَّكُمْ فَأْتُوا حَرْثَكُمْ أَنَّىٰ شِئْتُمْ

በቁርኣን አምላካችን አሏህ ወንድ ለሴት "ልብስ" እንደሆነ እንዲሁ ሴት ለወንድ "ልብስ" እንደሆነች ይነግረናል፦
2፥187 በጾም ሌሊት ወደ ሴቶቻችሁ መድረስ ለእናንተ ተፈቀደላችሁ፡፡ እነርሱ ለእናንተ ልብሶች ናቸው፥ እናንተም ለእነርሱ ልብሶች ናችሁ፡፡ أُحِلَّ لَكُمْ لَيْلَةَ الصِّيَامِ الرَّفَثُ إِلَىٰ نِسَائِكُمْ ۚ هُنَّ لِبَاسٌ لَّكُمْ وَأَنتُمْ لِبَاسٌ لَّهُن

እዚህ አንቀጽ ላይ ወንድ ለሴት ሴት ለወንድ "ልብስ" ናቸው ሲል በፍካሬአዊ ሃፍረትን፣ ነውርን እና ገበናን "መሸፈኛ" ማለት እንጂ በእማሬአዊ ወስዶ "ጃኬት" ወይም "ቀሚስ" አሊያም "ሱሪ" ማለት አይደለም። በተመሳሳይ ሴት ለወንድ እርሻ ናት፦
2፥223 ሴቶቻችሁ ለእናንተ እርሻ ናቸው፥ እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹኔታ ድረሱ፡፡ نِسَاؤُكُمْ حَرْثٌ لَّكُمْ فَأْتُوا حَرْثَكُمْ أَنَّىٰ شِئْتُمْ

መቼም ቂል የሆነ ሰው ካልሆነ ሴት ለወንድ "እርሻ" ናት ሲባል ሞፈርና ቀንበር አዋዶ የሆነው የጓሮ አትክልት አሊያም ሰብል ናት ማለት እንዳልሆነ እሙንና ቅቡል ነው፥ ቃሉ የወከለው እሳቤ እማሬአዊ ሳይሆን ፍካሬአዊ ነው። የሴት ልጅ ማኅፀን ዘር የሚዘራበት "እርሻ" ሲመሰል የእንሥት ማህፀን ላይ ላይ የሚገናኘው የተባእት ዘር ሕዋስ ደግሞ ገበሬ እርሻ ላይ በሚዘራው "ዘር" ተመስሏል፥ ወንድ ዘሩን ዘሪ ሲሆን ሴት ያንን ዘር የምታፈራበት እርሻ ናት። ምክንያቱም አንድ ገበሬ እርሻው ላይ ከዘራ በኃላ ዘሩ ዳብሮ ለፍሬ የሚበቃው በእርሻ ውስጥ እንደሆነ ሁሉ አንድ ተባእትም አንድ እንስት ማኅፀን ውስጥ ዘሩን ተገናኝ ሆኖ ከዘራ በኃላ ሂደቱ ሁሉ ተከናውኖ ለፍሬ የሚበቃው ማኅፀን ውስጥ ስለሆነ ነው። በማኅፀን ውስጥ በመፍሰስ የሚዘራው ዘር የተንጣለለ ደካማ ውኃ የሆነው የፍትወት ሕዋስ ነው፥ ይህም ሕዋስ በተጠበቀ መርጊያ በእርሻው ውስጥ ለፍሬ እስኪበቃ ይቆያል፦
56፥58 በማኅፀኖች የምታፈሱትን አያችሁን? أَفَرَأَيْتُم مَّا تُمْنُونَ
56፥63 የምትዘሩትንም አያችሁን? أَفَرَأَيْتُم مَّا تَحْرُثُون
32፥8 ከዚያም ዘሮቹን ከተንጣለለ ከደካማ ውኃ ያደረገ ነው፡፡ ثُمَّ جَعَلَ نَسْلَهُ مِن سُلَالَةٍ مِّن مَّاءٍ مَّهِينٍ
23፥13 ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ የፍትወት ጠብታ አደረግነው፡፡ ثُمَّ جَعَلْنَاهُ نُطْفَةً فِي قَرَارٍ مَّكِينٍ

ታላቁ የቁርኣን ሙፈሢር ኢብኑ ከሲር የኢብኑ ዐባሥን ንግግር ዋቢ በማድረግ የፈሠሩት በዚህ መልክ እና ልክ ነው፦
ተፍሢሩል ኢብኑ ከሲር 2፥223
ንግግሩ፦ "ሴቶቻችሁ ለእናንተ እርሻ ናቸው" የሚለውን ኢብኑ ዐባሥ፦ "እርሻ የሚለው የእርግዝናን ቦታ ነው”" ብሏል"። وقوله : ( نساؤكم حرث لكم ) قال ابن عباس : الحرث موضع الولد

"ሴት" እና "ወንድ" የሚለው የፆታ መደብ የፍትወት ሕዋሳችንን ታሳቢ እና ዋቢ ያደረገ ቢሆንም ነገር ግን አጠቃላይ ስብዕናችንን እንደሚያሳይ ሁሉ በተመሳሳይ "እርሻዎቻችሁ" ማለት "ሴቶቻችሁ" ማለትን ይይዛል፥ እርሻ ዘር የሚዘራበት እንደሆነ ሁሉ ሴትም ዘር ስለሚዘራባት እርሻ ተብላለች። "እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹኔታ ድረሱ" የሚለው አንቀጽ የወረደበት ሠበቡ አን-ኑዙል መዲና ላይ የነበሩ አይሁዳውያን፦ "ማንም የሚስቱን ሃፍረት በጀርባ በኩል ተራክቦ ያደረገ ልጁ ጠንጋራ ይሆናል" የሚል የተንጋደደ መረዳት ስለያዙ ነው፦
ጃምዒ አት ቲርሚዚይ መጽሐፍ 47, ሐዲስ 3245
ከጃቢር ኢብኑ ሙንከዲር ሰምቶ እንደተረከው፦ "አይሁዳውያን፦ "ማንም የሚስቱን ሃፍረት በጀርባ በኩል ተራክቦ ያደረገ ልጁ ጠንጋራ ይሆናል" አሉ፥ ከዚያም አላህ፦ "ሴቶቻችሁ ለእናንተ እርሻ ናቸው፥ እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹኔታ ድረሱ" የሚለውን አንቀጽ አወረደ"። عَنِ ابْنِ الْمُنْكَدِرِ، سَمِعَ جَابِرًا، يَقُولُ كَانَتِ الْيَهُودُ تَقُولُ مَنْ أَتَى امْرَأَتَهُ فِي قُبُلِهَا مِنْ دُبُرِهَا كَانَ الْوَلَدُ أَحْوَلَ فَنَزَلَتْ ‏:‏ ‏(‏نِسَاؤُكُمْ حَرْثٌ لَكُمْ فَأْتُوا حَرْثَكُمْ أَنَّى شِئْتُمْ ‏)‏

"በፈለጋችሁ ሁኔታ" ማለት በጀርባ በኩል ተራክቦ"Doggy sex" ማድረግም ክልክል አይደለም ማለትን ይጨምራል፥ ያ ማለት በመቀመጫ በኩል ተራክቦ”Anal sex” ማድረግ ይቻላል ማለት እንዳልሆነ ለማሳየት እዛው ዐውድ ላይ፦ "አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው" በማለት ይናገራል። በመቀመጫ ተራክቦ ማድረግ ሐራም ነው፥ ሐራም ብቻ ሳይሆን ኩፍሩል አስገርም ነው፦
2፥222 ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው"፡፡ فَإِذَا تَطَهَّرْنَ فَأْتُوهُنَّ مِنْ حَيْثُ أَمَرَكُمُ اللَّهُ
ጃሚዒ አት ቲርሚዚይ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 135
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ” እንዳለው፦ “ነቢዩ”ﷺ” እንዲህ ሲሉ ሰምቻለው፦ ማንም በሓይድ ላይ ካለች ሴት ወይም በመቀመጫዋ በኩል ተራክቦ ቢያደርግ በሙሐመድ”ﷺ” ላይ በተወረደው ክዷል"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏”‏ مَنْ أَتَى حَائِضًا أَوِ امْرَأَةً فِي دُبُرِهَا أَوْ كَاهِنًا فَقَدْ كَفَرَ بِمَا أُنْزِلَ عَلَى مُحَمَّدٍ صلى الله عليه وسلم ‏”‏
እዚህ ድረስ ከተግባባን የጴጥሮስ ተማሪ የሮሙ ክሌመንት ሴት እርሻ እንደሆነች አበክሮ እና አዘክሮ ይናገራል፦
ቀለሜንጦስ 10፥50 "አንቲ ገራህት ዕቀቢ ርእሰኪ! ወኢትደምሪ ዘርአ ነኪር፥ እንዘ ሁሉ ዘይናዝዘኪ ሐዘነኪ ሶበ ከመዝ ዘርእኪ ቡሩክ ውእቱ"።

ትርጉም፦ "አንቺ እርሻ ራስሽን ጠብቂ! ሌላ ዘርን አትጨምሪ፥ የሚያጽናናሽ እና ከሐዘንሽ የሚያረጋጋሽ ባልሽ ብቻ ነው"።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ቀኖና 35 ናቸው፥ የአዲስ ኪዳን መደበኛ የቀኖና መጽሐፍት 27 ሲሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መጽሐፍት ተጨማሪ ቀኖና 8 ናቸው። ከስምንቱ አንዱ "መጽሐፈ ቀለሜንጦስ" ነው፥ እና ቀለሜንጦስ ሴትን እርሻ ሲል ሞፈርና ቀንበር አዋዶ የሆነው የጓሮ አትክልት አሊያም ሰብል ናት ማለቱ ነውን? በጣም ስመ ጥርና ገናና የአዲስ ኪዳን አራት እደክታባት መካከል ኮዴክስ ኤፍራኤሚ(ኤፍሬም) ሲሆን በ 450 ድኅረ ልደት ያዘጋጀው ሶርያዊው ኤፍሬም ነው፥ ይህ የሶርያ ኤጲጵ ቆጶስ ድንግል ማርያምን እርሻ እንደሆነች አስረግጦ እና ረግጦ በውዳሴም ማርያም ላይ ይናገራል፦
ውዳሴ ማርያም ዘማክሰኞ ቁጥር 4
"አንቲ ውእቱ ገራህት ዘኢተዘርአ ውስቴታ ዘርእ፥ ወጽአ እምኔኪ ፍሬ ሕይወት"።

ትርጉም፦ "ዘር ያልተዘራባት እርሻ አንቺ ነሽ፥ የሕይወት ፍሬ ከአንቺ ወጣ"።

እዚህ ዐውድ ላይ "ዘር" የተባለው የወንድ የዘር ሕዋስ ነው፥ ድንግል ማርያም ኢየሱስን ስትፀንስ የወንድ የዘር ሕዋስ የሌለው ቢሆንም በተፈጥሮዋ የወንድ የዘር ሕዋስ የሚዘራበት ማኅፀን ስላላት "እርሻ" ተብላለች። እና ድንግል ማርያም ሞፈርና ቀንበር አዋዶ የሆነው የጓሮ አትክልት አሊያም ሰብል ናትን? እሩቅ ሳንሄድ አማንያን እርሻ ተብለዋል፦
1 ቆሮንቶስ 3፥9 እናንተ የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ”*፤ you are God’s field. NIV

መልሳችሁ፦ "ውይ ወሒድ ደግሞ ይህ ቀላል ነገር እኮ ነው፦ "እርሻ ናችሁ" ሲለን "የጓሮ አትክልት ናችሁ" ማለት ሳይሆን ልባችን በእርሻ ተመስሏል፥ ቃሉ ደግሞ በዘር ይመሰላል። ይህ እንዴት አይገባህም?" ትላላችሁ፥ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነገር ነው። ከላይ ያለውንም በዚህ ቀመር ተረዱት! "አመድ በዱቄት ይስቃል" እንዲሉ የአሏህ ንግግር ላይ ስትስቁ እና ስትሳለቁ ትውፊት ላይ ሴት እርሻ እንደሆነች ኩልል እና ጥርት ብሎ ተቀምጧል። ለነገሩ ባይብል እና አዋልድ ሴት "ደካማ ፍጥረት ናት፥ በተፈጥሮዋ ደካማ ናት፥ የሰማችውን ሁሉ ሳታመዛዝን አሜን ብላ ትቀበላለችና" ይለናል፦
1 ጴጥሮስ 3፥7 እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤
ቀለሜንጦስ 2÷14 ሴት በተፈጥሮዋ ደካማ ናት፤ የሰማችውን ሁሉ ሳታመዛዝን አሜን ብላ ትቀበላለችና።

አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን!

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
የነቢያችን"ﷺ" ቅጣት

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

42፥40 የመጥፎም ነገረ ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ናት፡፡ وَجَزَاءُ سَيِّئَةٍ سَيِّئَةٌ مِّثْلُهَا

"ቂሷስ" قِصَاص የሚለው ቃል "ቋሶ" قَاصَّ ማለትም "አመሳሰለ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ማመሳሰል" ማለት ነው፦
2፥179 ባለ አእምሮዎች ሆይ! ለእናንተም በማመሳሰል ሕግ ውስጥ ሕይወት አለላችሁ፡፡ ትጠነቀቁ ዘንድ ገዳይን መግደል ተደነገገላችሁ፡፡ وَلَكُمْ فِي الْقِصَاصِ حَيَاةٌ يَا أُولِي الْأَلْبَابِ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ማመሳሰል" ለሚለው ቃል የገባው "ቂሷስ" قِصَاص መሆኑ ልብ አድርግ! ሰው ጤናማ ሕይወት ይኖር ዘንድ አምላካችን አሏህ ቂሷስን ደንግጓል፥ በቂሷስ ነፍስ ያጠፋ ነፍሱ ይጠፋል፣ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጠፋል፣ አፍንጫም ያጠፋ አፍንጫው ይጠፋል፣ ጆሮም ያጠፋ ጆሮው ይጠፋል፣ ጥርስ የሰበረ ጥርሱ ይሰበራል። እነዚህ ቁስሎችን በቂሷስ ይፈታሉ፦
5፥45 በእነርሱም ላይ በውስጧ፦ «ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ ይያዛል፥ ቁስሎችንም "ማመሳሰል" አለባቸው» ማለትን ጻፍን፡፡ وَكَتَبْنَا عَلَيْهِمْ فِيهَا أَنَّ النَّفْسَ بِالنَّفْسِ وَالْعَيْنَ بِالْعَيْنِ وَالْأَنفَ بِالْأَنفِ وَالْأُذُنَ بِالْأُذُنِ وَالسِّنَّ بِالسِّنِّ وَالْجُرُوحَ قِصَاصٌ

አሁንም እዚህ አንቀጽ ላይ "ማመሳሰል" ለሚለው ቃል የገባው "ቂሷስ" قِصَاص መሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። መጥፎ ለሠሩ ሠዎች መጥፎ ቅጣት መቅጣት ቂሷስ ነው፥ የአሏህ መጽሐፍ ጭብጡ ቂሷስ ነው፦
42፥40 የመጥፎም ነገረ ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ናት፡፡ وَجَزَاءُ سَيِّئَةٍ سَيِّئَةٌ مِّثْلُهَا
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 65, ሐዲስ 26
አነሥ እንደተረከው፦ “ነቢዩም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "የአሏህ መጽሐፍ ቂሷስ ነው"። أَنَّ أَنَسًا، حَدَّثَهُمْ عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ “‏ كِتَابُ اللَّهِ الْقِصَاصُ ‏”‌‏.‏

የመጥፎም ነገረ ዋጋ ብጤዋ መጥፎ ስለሆነ በአንድ ወቅት ነቢያችን"ﷺ" እረኛቸውን ለዑረይናህ ሰዎች እንዲንከባከባቸው ሰተዋቸው ሳሉ የዑረይናህ ሰዎች ግን በተቃራኒው የነቢያችንን"ﷺ" እረኛ እጅና እግር ቆርጠው እና ዓይን አጥፍተው በመግደላቸው ቂሷስ ተደርጎ እጃቸውንና እግራቸውንም እንዲቆረጥ እና ዓይኖቻቸውም እንዲጠፋ ተደርጓል፦
ሡነን ነሣኢይ መጽሐፍ 37, ሐዲስ 62
አነሥ እንደተረከው፦ "ሰዎች ከዑክል ወይም ከዑረይናህ ወደ ነቢዩ"ﷺ" መጡ፥ የመዲናህ አየር ንብረት ተጨናንቋል። ነቢዩም"ﷺ" ለእነርሱ፦ "ወደ ግመሎች ሂዱና ወተታቸውን ጠጡ እንዲሁ ሽንታቸውን ለመድኃኒት ተጠቀሙ" ብለው አዘዟቸው፥ እነርሱ ግን እረኛውን ገድለው ግመሎቹን ሰረቁ። ነቢዩም"ﷺ" ከኃላቸው ሰው ልከው እጃቸውን እና እግራቸውንም ቈረጡ፥ ዓይኖቻቸውም አጠፉ"። عَنْ أَنَسٍ، قَالَ أَتَى النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم نَفَرٌ مِنْ عُكْلٍ أَوْ عُرَيْنَةَ فَأَمَرَ لَهُمْ - وَاجْتَوَوُا الْمَدِينَةَ - بِذَوْدٍ أَوْ لِقَاحٍ يَشْرَبُونَ أَلْبَانَهَا وَأَبْوَالَهَا فَقَتَلُوا الرَّاعِيَ وَاسْتَاقُوا الإِبِلَ فَبَعَثَ فِي طَلَبِهِمْ فَقَطَّعَ أَيْدِيَهُمْ وَأَرْجُلَهُمْ وَسَمَلَ أَعْيُنَهُمْ ‏.‏

"ሠመለ" سَمَلَ ማለት "አጠፋ" ማለት ነው። አምላካችን አሏህ፦ "ዓይንም በዓይን ይያዛል፥ ቁስሎችንም "ማመሳሰል" አለባቸው" ስላለ እነዚህ ሰዎች የእረኛውን ዓይን ስላጠፉ ዓይናቸው እንዲጠፋ ተደርጓል፦
ሡነን ነሣኢይ መጽሐፍ 37, ሐዲስ 78
አነሥ እንደተረከው፦ "ነቢዩ"ﷺ" የእረኛውን ዓይኖች በማጥፋታቸው ምክንያት የእነዚያን ሰዎች ዓይኖች ብቻ አጥፍተው ነበር"። عَنْ أَنَسٍ، قَالَ إِنَّمَا سَمَلَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم أَعْيُنَ أُولَئِكَ لأَنَّهُمْ سَمَلُوا أَعْيُنَ الرُّعَاةِ ‏.‏

በኪታቡ አት-ተሕሪሙ አድ-ደም ዐውድ ውስጥ "እነዚያ" የተባሉት የዑረይናህ ሰዎች እንደሆኑ አንባቢ ልብ ይለዋል። በባይብልም ቢሆን ዓይን ያጠፋ ዓይኑ እንዲጠፋ ትእዛዝ አለ፦
ዘጸአት 21፥23-25 ጕዳት ግን ቢያገኛት ሕይወት በሕይወት፣ ዓይን በዓይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በእግር፣ መቃጠል በመቃጠል፣ ቍስል በቍስል፣ ግርፋት በግርፋት ይከፈል።
በባይብል የገደለ ብቻ ሳይሆን አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደላል፦
ዘሌዋውያን 27፥17 ሰውንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።
ዘጸአት 21፥17 አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል።

ኢየሱስ ሲመጣ ደግሞ ሕጉ ጠብቆ እና አጥብቆ የሞት ፍርድ የሚገባው የገደለ ብቻ ሳይሆን በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ የሞት ፍርድ እንደሚገባው አበክሮ እና አዘክሮ ተናግሯል፦
ማቴዎስ 5፥21-22 ለቀደሙት፦ አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል።

"የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል" ማለት በዘሌዋውያን 27፥17 "ፈጽሞ ይገደል" የሚለው ከሆነ "በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል" ማለት "ፈጽሞ ይገደላል" ማለት ነው። እንደውም ኢየሱስ እንቅጩን ፍርጥ አርጎ፦ "በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል" ብሏል፦
ራእይ 13፥10 "በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል"።

በተጨማሪ ሬካብ እና ወንድሙ በዓና ወደ ኢያቡስቴ ቤት ገብተው ኢያቡስቴን ገድለዉት እራሱን ቆረጡት፥ ዳዊትም ሬካብን እና ወንድሙ በዓናን አስገድሎ እጃቸውን እና እግራቸውን እንዲቆረጥ አድርጓል፦
2 ሳሙኤል 4፥7 ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ እርሱ በእልፍኙ በምንጣፉ ላይ ተኝቶ ሳለ መቱት፥ ገደሉትም፤ ራሱንም ቈርጠው ወሰዱት።
ሳሙኤል 4፥12 ዳዊትም ጕልማሶቹን አዘዘ፥ ገደሉአቸውም፤ እጃቸውን እና እግራቸውን ቈርጠው በኬብሮን በውኃ መቆሚያ አጠገብ አንጠለጠሉአቸው።

ኢዮአብ እና ሠራዊቱ በአሞን ከከተማ ይኖሩ የነበሩትን የአሞን ልጆች አውጥተው በመጋዝ ተረተሩአቸው፤ በመጥረቢያም ቈራረጡአቸው። ዳዊትም በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ፦
1ኛ ዜና መዋዕል 20፥3 በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥተው በመጋዝ ተረተሩአቸው፤ በመጥረቢያም ቈራረጡአቸው። ዳዊትም በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። καὶ τὸν λαὸν τὸν ἐν αὐτῇ ἐξήγαγε καὶ διέπρισε πρίοσι καὶ ἐν σκεπάρνοις σιδηροῖς καὶ ἐν διασχίζουσι· καὶ οὕτως ἐποίησε Δαυὶδ τοῖς πᾶσιν υἱοῖς ᾿Αμμών. καὶ ἀνέστρεψε Δαυὶδ καὶ πᾶς ὁ λαὸς αὐτοῦ εἰς ῾Ιερουσαλήμ.

"ዳዊትም በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ" በማለት ዳዊት ልክ እንደ ኢዮአብ የአሞን ልጆችን በመጋዝ ተረተሩአቸው፤ በመጥረቢያም ቈራረጡአቸው፥ ግሪክ ሰፕቱአጀንት በዚህ ልክ ያስቀመጡት ሲሆን የ 2 ሺህ የኦርቶዶክስ ባይብል እና King James Version በዚህ አግባብ ተርጉመውታል፦
1 Chronicles 20፥3 KJV And he brought out the people that were in it, and cut them with saws, and with harrows of iron, and with axes. Even so dealt David with all the cities of the children of Ammon. And David and all the people returned to Jerusalem.

ነቢያችን"ﷺ" በቂሷስ ፍርድ እና ቅጣት ማድረጋቸው ነቢይ ላለመሆናቸው መስፈርት ከሆነ እንግዲያውስ በነካ አፋችሁን "ሙሴ፣ ኢየሱስ፣ ዳዊት የፈጣሪ ነቢይ አይደሉም" በሉና! ምን ይሻላችኃል ግን? ባይብል ሲጠቀስ እንቡር እና ፒርር እንዲሁ ቡፍ እና ኩፍ ከምትሉ ቁርኣንን እና ሐዲስን ለማሳለጥ ፊጥ እና ቁጢጥ የምትሉትን ተዉ! አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ብዙ ሰው ፕሮቴስታንት ሁሉ ጴንጤ ይመስለዋል፥ ጴንጤ በልሳን መናገር የሚቀበል ሲሆን ጴንጤ ፕሮቴስታንት ውስጥም ከፕሮቴስታንት ውጪም አለ። ፕሮቴስታንት ውስጥ በልሳን መናገር የማይቀበል ብዙ አለ፥ ጴንጤ ሁሉ ፕሮቴስታንት አይደለም። ለምሳሌ፦ በሥላሴ የማያምኑ ኦንሊ ጂሰስ ጴንጤ ውስጥ ይመደባሉ። ከ 1900 ድኅረ ልደት በፊት ጴንጤ ያልነበረበት ጊዜ ሲሆን ፕሮቴስታንት ግን በ 1517 ድኅረ ልደት የተጀመረ ነው፥ የፕሮቴስታንት ሐዳስያን ማርቲን ሉተር፣ ዮሐንስ ካልቪን፣ ያዕቆብ አርሚነስ፣ ሉድሪች ዝውንግሊ ወዘተ በልሳን የማይናገሩ ሲሆኑ ጴንጤ አልነበሩም። በልሳን መናገር ምንድን ነው? ይህንን ቪድዮ እየተመለከቱ ያድምጡ እና ይህንን መጣጥፍ ያንብቡ፦ በልሳን መናገር
ነቢዩ አደም

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

20፥115 ወደ አደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን፡፡ وَلَقَدْ عَهِدْنَآ إِلَىٰٓ ءَادَمَ مِن قَبْلُ

“ነቢይ” نَبِيّ የሚለው ቃል “ነበአ” نَبَّأَ ማለትም “አወራ” ወይም “ተናገረ” ከሚል ሥርወ ቃል ሲሆን “አውሪ” ወይም “ተናጋሪ” ማለት ነው፥ “ነበእ” نَبَأ ማለት “የሩቅ ወሬ” ወይም “የሩቅ ንግግር” ሲሆን አንድ ሰው ከአሏህ ነበእ ሲወርድለት ነቢይ ይሰኛል። አምላካችን አሏህ ወደ አደም ኪዳንን አውርዷል፦
20፥115 ወደ አደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን፡፡ وَلَقَدْ عَهِدْنَآ إِلَىٰٓ ءَادَمَ مِن قَبْلُ

"ከዚህ በፊት" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት! "ከዚህ በፊት" ለሚለው የገባው ቃል "ሚን ቀብሉ” مِنْ قَبْلُ ሲሆን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ነው፥ "ከዚህ በፊት" አሏህ በአደም ጊዜ "ሙሥሊሞች" ብሎ ሰየመ፦
22፥78 "እርሱ "ከዚህ በፊት" ሙሥሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል፡፡ هُوَ سَمَّاكُمُ الْمُسْلِمِينَ مِن قَبْلُ

"ከዚህ በፊት" ለሚለው የገባው ቃል "ሚን ቀብሉ” مِنْ قَبْلُ ሲሆን የአደምን ጊዜ ያስታውሰናል። "እርሱ" የተባለው "አሏህ" የሚለውን ስም ተክቶ የመጣ ተውላጠ ስም ነው፥ አሏህ "ሙሥሊሞች" ብሎ የጠራን ሲሆን "ሙሥሊም" مُسْلِم ማለት አንዱን አምላክ "ተገዥ" "አምላኪ" "ታዛዥ" ማለት ነው። አደም በምድር ላይ የመጀመሪያው ነቢይ ነው፦
ኢማም አሕመድ መጽሐፍ 5, ሐዲስ 1781
አቡ ዘር እንደተረከው፦ "የአሏህ ነቢይ ሆይ! የመጀመሪያው ነቢይ ማን ነው? ብሎ አለ። እርሳቸውም፦ "አደም ነው" አሉ። እርሱም፦ "የአሏህ ነቢይ ሆይ!እርሱ ነቢይ ነበርን? ብሎ አለ። እርሳቸውም፦ "አዎ" አሉ"። عَن أَبُو ذَرٍّ قُلْتُ : يَا نَبِيَّ اللَّهِ، فَأَيُّ الْأَنْبِيَاءِ كَانَ أَوَّلَ. قَالَ : " آدَمُ ". قَالَ : قُلْتُ : يَا نَبِيَّ اللَّهِ، أَوَنَبِيٌّ كَانَ آدَمُ ؟ قَالَ : " نَعَمْ،

“ረሡል” رَسُول የሚለው ቃል “አርሠለ” أَرْسَلَ ማለትም “ላከ” ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን “መልእክተኛ” ማለት ነው፥ “ሪሣላህ” رِسَالَة ማለት “መልእክት” ማለት ሲሆን አንድ ነቢይ ሪሣላህ ሲወርድለት ረሡል” ይሰኛል፦
22፥52 ከመልእክተኛ እና ከነቢይ ከአንተ በፊት አንድንም አልላክንም፥ ባነበበና ዝም ባለ ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ላይ ማጥመሚያን ቃል የሚጥል ቢሆን እንጂ። وَمَا أَرْسَلْنَا مِنْ قَبْلِكَ مِنْ رَسُولٍ وَلَا نَبِيٍّ إِلَّا إِذَا تَمَنَّىٰ أَلْقَى الشَّيْطَانُ فِي أُمْنِيَّتِهِ

እዚህ አንቀጽ ላይ “ነቢይ” نَبِيّ እና “ረሡል” رَسُول በሚሉት የማዕረግ ስሞች መካከል “ወ” وَ ማለትም “እና” የሚል መስተጻምር አለ፥ ይህም ነቢይ እና ረሡል ሁለት የተለያየ ደረጃ መሆኑን ቁልጭ እና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህንን ከተረዳን ዘንዳ ኑሕ ደግሞ የመጀመሪያው ረሡል ነው፦
ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 65, ሐዲስ 4476
አነሥ እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ *”……(አደምም)፦ “ኑህ ጋር ሂዱ! እርሱ በምድር ላይ የተላከ የመጀመሪያው መልእክተኛ ነው፥ ወደ ምድር ባለቤቶች አሏህ ልኮታል” ይላቸዋል”። ائْتُوا نُوحًا فَإِنَّهُ أَوَّلُ رَسُولٍ بَعَثَهُ اللَّهُ إِلَى أَهْلِ الأَرْضِ‏.‏

"ነባይ" የሚለው የግዕዝ ቃል “ነበየ” ማለትም “ተናገረ” ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን “ነባቢ” “ተናጋሪ” "ነቢይ" ማለት ነው፥ "ነቢብ" ማለት "ንግግር" ማለት ሲሆን አንድ ሰው ከፈጣሪ ነቢብ ሲመጣለት ነቢይ ይሆናል። አዳም ነቢብ መቶለት ነበር፦
ቀሌምንጦስ 1፥37 አዳም ጥበብን፣ ነቢብን እና ዕውቀትን ሁሉ እንዲቀበል ነው።
ቀሌምንጦስ 1፥40 በዚህ ጊዜ ንጉሥነትን እና ነቢይነትን ሠጠው በክብር መንበር ላይም አስቀመጠው።

አዳም "ነቢይነት" ሲቀበል ነቢይ ሆኗል፥ ፈጣሪ "አዳም ሆይ! እነሆ ንጉሥ፣ ካህን እና "ነቢይ" መስፍን ለፍጥረት ሁሉ ገዢ ስላንተ በፈጠርሁት ሁሉ እንድትሆን አደረግሁ" ሲል መላእክት ሰምተዋል፦
ቀሌምንጦስ 1፥43 በዚህ ጊዜ መላእክት የእግዚአብሔር ቃል፦ "አዳም ሆይ! እነሆ ንጉሥ፣ ካህን እና "ነቢይ" መስፍን ለፍጥረት ሁሉ ገዢ ስላንተ በፈጠርሁት ሁሉ እንድትሆን አደረግሁ...ሲል ሰሙ።

ከ 451 እስከ 521 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረ ያዕቆብ ዘሥሩግ"Jacob of Serugh" በእንተ ወላዲተ አምላክ በሚል መጽሐፉ ላይ አዳም ነቢይ እንደነበረ ተናግሯል፦
"አዳም ድንግል ሔዋንን አስገኝቷል፥ "የሕይወት እናት" ብሎ ጠርቷታል። እርሱ ነቢይ ነበረ"።
On the Mother of God (Jacob of Serugh) Homily (I)1 Number 634

በአበው ትምህርት "አዳም ነቢይ አልነበረም" የሚል አሉታዊ ዕይታ አልበረም፥ "አዳም ነቢይ ከነበረ ለእነማን ነበረ" ብላችሁ የምትጠይቁን ጥያቄውን ገልብጣችሁ እራሳችሁን ጠይቁ! አዳም የፈለገውን ያደርግ ዘንድ ሥልጣን ተሰቶት ነበር፦
ቀሌምንጦስ 1፥44 "የፈለግኸውን ታደርግ ዘንድ ይህንን ሥልጣን ሠጠሁህ" ሲል ሰሙ።

ሥልጣን ስለተሰጠው አዳም ከነቢይነትም አልፎ "አምላክ" ተብሎ እንደሚጠራ ቴዎፍሎስ ዘአንጾኪያ"Theophilus of Antioch" ተናግሯል፦
"ሁሉን ቻይ አምላክም አዳምን ​​ከተፈጠረባት ምድር ወደ ገነት አዛወረው፥ እንደገናም እንዲበስል፣ ፍጹም እንዲሆን፣ "አምላክ" ተብሎ እንዲጠራ እና የኢ-መዋቲነትን ርስት ይዞ ወደ ሰማይ እንዲወጣ የእድገት ዘዴዎችን ተሰጠው"።
To Autolycus (Theophilus of Antioch) Book II(2) Chapter 24

በእርግጥ አንድ ሰው ፈጣሪ ካናገረው እና ንግግር ከእርሱ ከተቀበለ ነቢይ ስለሚሆን የግድ መላክ እና "ለእነማ ተላከ" የሚል አጠይቆት ላያስፈልገው ይችላል፥ "አጠይቆቱ አግባብ እና አገባብ አለው" ከተባለ እንግዲያውስ አዳም ቤተሰብ እስካለው ድረስ ለቤተሰቡ ነቢይ መሆን ይችላል። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://tttttt.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም