TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
“ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መጥተው ከድልድዩ ቆመው አይተው ሄዱ ተመልሰው ” - የቦታው ነዋሪ
“ ምናልባት በኛ የማይሰራ ከሆነ ብዬ እንደዛም ገምቼ ነው፡፡ ይነግሩኝ ነበር ከሄዱ አሳውቃለሁ ” - ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11፣ ቀጠና 2፣ “ወይናምባ ማርያም” የተሰኘ አካባቢ ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ወንዝ በአፈር በመዘጋቱ ትላንት የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ንብረታቸው እንደተወሰደና ውጪ እንዳደሩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸው ነበር።
በዚህም ነዋሪዎቹ ወንዙ እንዲከፈትላቸው ተማጽነው የነበረ ሲሆን፣ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ለእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን በሰዓቱ አሳውቆ ነበር።
የነዋሪዎቹ ቅሬታ መፍትሄ ተሰጠው ?
የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መጥተው ነበር ? ስንል የጠየቅናቸው ከነዋሪዎቹ አንዱ፣“ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መጥተው ከድልድዩ ቆመው አይተው ሄዱ ተመልሰው ” ብለዋል።
“ ‘ሌላ ቀን እንመጣለን ይሄ በኛ መኪና የሚቻል አይደለም’ አሉ። ሌሎች ከእሳትና አደጋ ‘መጥተናል’ ብለው ደግሞ ሰውን መዝግቡ ብለው፤ ግማሹን ራሳቸው መዝግበው፣ ግማሹን 'መዝግባችሁ ወረቀቱን አምጡ’ ብለው ሄዱ” ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
“‘ወደ ወንዙ በመኪና ለመግባት በጣም ከባድ ነው፣ ይሄን መጀመሪያ ለምን ወረዳው፤ ቀበሌው አልተከታተሉም?’ አሉ” ብለው፣ የተዘጋው ወንዝ ገና አልተከፈተም ብለዋል።
ሌሎቹ ቅሬታ አቅራቢዎችም፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞቹ ደርሰው እንደተመለሱ፣ ነገር ግን ጉዳዩ መፍትሄ እንዳላገኘ፣ ንብረታቸውን ከወንዙ እየለቀሙ እንደዋሉ ገልጸዋል።
ትላንት በጣለው ዝናብ ከደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሳያገግሙ በድጋሚ ዝናብ ከጣለ ሌላ የከፋ አደጋ እንዳይደርስ የሚል ስጋት እንደገባቸው አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ ምን አለ ?
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ መጀመሪያ ጉዳዩን ካሳወቀበት ቆይታ በኋላም የነዋሪዎቹ ቅሬታ ከምን ደረሰ? በቦታው ሄዳችሁ? ሲል የኮሚሽኑን የሕዝብ ግንኑነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞን ምላሽ ጠይቋል፡፡
እሳቸውም በምላሻቸው፣ “ለዲስፓይ ሴንተር ስልካቸውን ሰጥቻለሁ፤ ቼክ አድርጉና ደውሉላቸው ብያለሁ፡፡ ምላሹን አልጠየኳቸውም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አክለው ፤ “ከተሰማሩ፤ ከሄዱ ችግር የለም፡፡ ምናልባት በኛ የማይሰራ ከሆነ ብዬ እንደዛም ገምቼ ነው፡፡ ይነግሩኝ ነበረ ከሄዱ አሳውቅሃለሁ” ብለው ነበር፡፡
በድጋሚ ከቆይታ በኋላ ስንሞክር ምላሽ አላገኘንም።
አቶ ንጋቱ በከተማዋ ሰምኑን የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ በተመለከተ ዛሬ ጠዋት በሰጡን ገለጻ፣ "ኮሚሽን መስሪያ ቤታችን ስሙ እሳት ብሎ ስለሚጀምር እዛ ላይ ብቻ አገልግሎት እንደምንሰጥ መረዳት አለ። ግን ማናቸውም አደጋ ይመለከተናል” ሲሉ አደጋ ሲያጋጥም ህዝቡ ወደ ኮሚሽኑ እንዲደውል አሳስበው ነበር።
(ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የከተማውን አካላት ሁሉ የምንጠይቅ ይሆናል)
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
😢264❤99🙏26🕊19😡17💔8😭8👏5😱2🥰1
" አምና ቁምሳጥኑን ፣ ቲቪውን ሽጦ እስከ 11 ሺሕ ብር የከፈለ አለ፡፡ ዘንድሮ ተሻሽሎ ወደ 20 ሺሕ ብር መሆኑ ደግሞ ከህዝቡ አቅም በላይ ነው " - ነዋሪዎች
➡️ " ያለደረሰኝ የሚሰበሰብ ገንዘብ የለንም፡፡ ልማት ሲባል መቼም መንግስት ከቅጠል ላይ ዘርፎ የሚሰበስበው ብር የለም " - የሸገር ከተማ ከንቲባ
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማና ዙሪያው ነዋሪዎች ከሚጠየቁት ከፍተኛ ግብር በተጨማሪ የቡሳ ጎኖፋን ጨምሮ ሌሎች ደረሰኝ እንኳ የማይቆረጥባቸው ክፍያዎች ከኑሮ ውድነቱ ጋር እንዳማሯቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።
" የግብር ክፍያውን በግለሰብ ወደ 20 ሺሕ ብር አደረሱት፡፡ በየዓመቱ ከ100 ፐርሰንት በላይ እየጨመሩ ህብረተሰቡ በጣም ሰቀቀን ላይ ነው " ሲሉ አማረዋል።
- ለማዘጋጃ ቤት14 ሺሕ 200 ብር፣
- ለቀይ መስቀል 500 ብር፣
- ለቡሳ ጎኖፋ ማኀበር 100 ብር፣
- ለኦሮሚያ ልማት ማኀበር 500 ብር
- ለስፖርት አካውንት 500 ብር፣
- ለጤና መድህን 1310 ብር ክፍያ እየተጠየቁ መሆኑን አመልክተዋል።
" የአፈር ግብር በምን ስሌት ተሰልቶ ነው 14 ሺሕ 200 ብር የሚሆነው? አምና ቁምሳጥኑን፣ ቲቪውን ሽጦ እስከ 11 ሺሕ ብር የከፈለ አለ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ተሻሽሎ 20 ሺሕ ብር በመሆኑ ከህዝቡ አቅም በላይ ነው " ሲሉ መፍትሄ ጠይቀዋል፡፡
" መዋጮው ከህብረተሰቡ አቅም በላይ ነው፡፡ ደረሰኝ የሚሰጠው ለቀይ መስቀል ለማዘጋጃ ቤት ክፍያው ነው፤ ለሌላው ደረሰኝ እንኳ የለውም " ብለው፣ " አምና ለማዘጋጃ ቤት 6 ሺሕ ብር፣ በ2015 ዓ/ም 2400፣ 2500 ብር ነበር የከፈልነው፡፡ 2016 ዓ/ም 6700 ብር ገባ፡፡ ዘንድሮ ወደ 14 ሺሕ 200 ብር ከፍ አለ " ነው ያሉት፡፡
ቅሬታውን ይዘን የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ምላሽ ጠይቀናቸዋል።
" ያለደረሰኝ የሚሰበሰብ ገንዘብ የለንም፡፡ ልማት ሲባል መቼም መንግስት ከቅጠል ላይ ዘርፎ የሚሰበስበው ብር የለም፡፡ ማህበረሰቡ በተለያየ የሚሰሩትን በአንድ ቦታ ለመሰብስብ ካልሆነ በስተቀር የበዛ ክፍያም የለም " ሲሉ መልሰዋል።
" የቡሳ ጎኖፋ ጉዳይ ዓለም የሚሰራው ነው፡፡ በኛ አገር በተለይ በኦሮሚያ ክልል ይሄው ጉዳይ ውጤታማ ሆኖ የተፈጥሮና ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ቡሳ ጎኖፋ የምንለው ሥርዓት ነው ላለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ብዙ ችግር የፈታልን፡፡ ስለዚህ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ይህንን ይከፍላል " ነው ያሉት።
ነዋሪዎች በግዴታ ተጠየቅን የሚሉትን የቡሳ ጎኖፋ ክፍያ እርስዎ አስገዳጅነት የለውም ነው የሚሉት ? ስንል የጠየቅናቸው ከንቲባው፣ " ሜምበርሽፕ ነው፡፡ ሰውን መርዳት ምን ችግር አለው ? የተወሰነ ገንዘብ ከገቢህ ሼር ማድረግ የሰውነት ግዴታ ነው " የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) አክለው ምን አሉ ?
" ይቺን መክፈል ይህን ያክል ከባድ አይደለም። ባደጉት ሀገራት ሰው 60 በመቶ እየከፈለ ነው ጠንካራ መንግስት ያቋቋመው፤ ከየትም መጥቶ አይደለም እነ አውሮፓ እነ አሜሪካ የተገነቡት፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ማውጣት ያለበትን ማውጣት አለበት።
ከእያዳንዱ ሰው የሚዋጣው ትንሽ ብር ነው ይሄን ያህል ብዙ አይደለም። ሁሉም ነገር ሥርዓት ያለው ነው፤ ክፍተቶች ካሉ ደግሞ እናያለን።
የኦሮሚያና ልማት ማህበር ክፍያን በተመለከተ የኦሮሚያ ልማት የራሱ ሜምበር አለው፤ የራሱ ሜምበር ይከፍላል፤ አልከፍልም ካለም መብቱ ነው። የማዘጋጃ ቤት ክፍያ ይጨምራል፤ አገልግሎት ላይ ዋጋ ይጨመር ስንል ሰው ለምን ይገረማል ? ድንችና ሽንኩርት ሲጨምር ሰው ዝም ብሎ የለ እንዴ።
መጨመር አለበት ብለን ሪቫይዝ አድርገናል። መንግስት አንድን ከተማ ጠንካራ የሚያደርገው ገቢ ሰብስቦ መስራት ከቻለ ነው። 3 ሚሊዮን ህዝብ ነው ያለኝ፤ ከ3 ሚሊዮን ህዝብ ባለፈው 24 ቢሊዮን ነው የሰበሰብኩት ይሄን 24 ቢሊዮን ምንድን ነው የማደርግበት ?
በዚህ በኩል ሳትከፍል በዚህ በኩል ውሃ፣ መንገድ የለም ማለት እኛ ጋ ስለተለመደ ነው፡፡ እኛም እንደ መንግስት ገቢ ሳናሰባስብ የምንሰራቸው ሥራዎች የሉም።
ስለዚህ ከፍሎ ከምን ዋለ ? ብሎ ነው ዘመናዊ ማህበረሰብ የሚጠይቀው። መንገድ አልተሰራልኝም ፣ ትምህርት ቤት አልተሰራልኝም ብሎ ከፍሎ ይጠይቅ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር የሚሰበሰበው የጂዲፒው 6% ነው " ሲሉ ተናግረዋል።
የነዋሪዎቹ ቅሬታ ግብር መክፈልን መቃረን ሳይሆን የሚጠየቁት የክፍያ አይነቶች መብዛትና መደራረብ ነው ከኑሮ ውድነቱ ጋር ሁነቱን ከባድ ያደረገው የሚል ሀሳብ ስናነሳላቸውም፣ " ማህበረሰቡ ይክፈል፤ የገባበትን ኦዲት እናድርግ። ዘላለም ' ለምን ከፈልኩ ' ማለት ግን ተቀባይነች የለውም " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
😭1.44K❤1.11K😡579🤔43😱33😢21🙏20🕊17👏13🥰11💔3