TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
63K photos
1.61K videos
216 files
4.38K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

መረጃ እና መልዕክት ፦ 0919743630

ማርኬቲንግ ፦ 0979222111 ወይም
0979333111

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ትኩረት🚨

ከሰሞኑን በርካታ ሰዎች በተለይ ትንንሽ ህጻናት በጉንፋን እና በጉንፋን መሰል የመተንፈሻ አካላት ህመም እየተያዙ ይገኛሉ።

ይህንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመክቶ ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ያጋራ መግለጫ ልከዋል።

ምን አሉ ?

➡️ የጉንፋን ሕመም በተፈጥሮ የላይኛውን የመተንፈሻ የሰውነት ክፍሎች ማለትም አፍንጫን፣ ጎሮሮን እና የአየር መተላለፊያ ባንቧን የሚያጠቃ ተላላፊ ሕመም ነዉ።

➡️ ሪኖ ቫይረስ ለጉንፉን መከሰት ዋና ምክንያት ሲሆን፣ ኮሮና፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ፓራ ኢንፍሉዌንዛ፣ አር ኤስ ቪ(RSV) ቫይረሶች ደግሞ ለጉንፉን መሰል ህመሞች መከሰት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸዉ። ከተጠቀሱት ቫይረሶችም ለጉንፋን ሕመም መከሰት 50 በመቶ ድርሻውን የሚይዘው ሪኖ ቫይረስ ነው፡፡ በደረቅ ነፋሳማ ወቅት የአፍንጫ የውስጠኛው ስስ ሽፋን “ ሙከስ መምብሬን ” ስለሚደርቅ የጉንፋን ሕመም እና ተላላፊነቱ ይጨምራል፡፡

➡️ የክረምት ወራት ወይም የዝናብ ወቅት ማብቃቱን ተከትሎ መስከረምን ጨምሮ በጥቅምትና ህዳር ወራት እንደዚህ አይነት ጉንፋን መሰል ህመም የሚጠበቅ ነው፡፡

➡️ ሕመሙ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ጊዜ እንደሆነና በተጨማሪም ሰዎች ቫይረሱ ያረፈበትን የበር እጀታ፣ ጠረጴዛ ወይም በሕመምተኛው የተነካካንን ሰው እጅ ከነኩ በኋላ አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሲነካኩ ቫይረሱ ለመተላለፍ በሚፈጠርለት ምቹ ሁኔታ ነው።

➡️ የጉንፋን ሕመም የመጀመሪያ ምልክቱ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት ተላላፊ ሊሆን ይችላል፤ ሕመሙ ከጀመረ ከ 5 እስከ 10 ባሉት ቀናት ደግሞ ሕመምተኛው ቫይረሱን ያስተላልፋል።

➡️ ህመሙ አብዛኛዉን ጊዜ እስከ 2 ሳምንት ሊቆይ ይችላል። ምልክቶቹም እንደ ፦
° የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት፣
° ሳል፣
° ትኩሳት፣
° ራስ ምታትና ጉሮሮን መከርከር፣
° ማስነጠስ፣
° አይን ማሳከክ እና መቅላት፣
° ማስታወክ፣
° ከፍ ሲልም የትንፋሽ ማጠር፣
° ከፍተኛ ድካምና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ።

➡️ ከመስከረም ወር ጀምሮ መሰል ህመም ተሰምቷቸው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ናሙና ከሰጡት ታካሚዎች ውስጥ አር ኤስ ቪ የተገኘባቸዉ ቁጥር የመጨመር ሁኔታ ያሳያል፡፡ በዚሁ ወቅት የተከሰተው ጉንፋን መሰል ህመም (አር ኤስ ቪ) በተለይ በህጻናት ላይ በብዛት የተከሰተ ሲሆን ለዚህም ወቅቱ ትምህርት ቤት የተከፈተበት በመሆኑ ለበሽታው መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

➡️ ባለፈዉ 1 ወር ዉስጥ ተመርምረዉ አር ኤስ ቪ ከተገኘባቸዉ ታካሚዎች መካከል 84% ያክሉ እድሜያቸዉ ከ5 አመት በታች ነዉ። እንደዚሁም ባለፈዉ ሳምንት ለአር ኤስ ቪ ከተመረመሩት 81 ናሙናዎች 49 (60.5%) ያህሉ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

➡️ አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ በሽታው የመዛመት እድሉ ከፍ ሊል እንደሚችል፤ በተለይ ቀዳሚ ተጎጅ ሊሆኑ የሚችሉ እንደ ህጻናትና አረጋውያን ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አና ተጓዳኝ የጤና ችግር እንደነ አስም፣ የስኳር በሽታ፣ ካንሰር እና ሌሎች ሥር የሰደዱ በሽታዎች ያሉባቸው ሕሙማን ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግላቸው እና ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊዉን ምርመራና ህክምና ሊያደርጉ ይገባል።

➡️ የጉንፋን ሕመም የጆሮ ኢንፌክሽን እና የሳንባ ምች ሕመምን ጨምሮ ለተለያዩ ሕመሞች ተጋላጭ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ጉንፋን መሰል በሽታን የምንከላከልባቸው መንገዶች ምንድናቸው ?
° የእጅ ንጽህናን መጠበቅ፣
° ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ የአፍና አፍንጫ ጭምብል(ማስክ) ማድረግ
° በዕለት ኑሯችን የምንጠቀምባቸውን በከባቢዎቻችን የሚገኙ ቁሳቁሶችን ማጽዳት
° የብዙሃን ማጓጓዣ ትራንስፖርት ላይ መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝዉዉር እንዲኖር በማድረግ የበሽታዉን የመተላለፍ ዕድል መቀነስ ይቻላል፡፡


#ማሳሰቢያ ፦ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስድና ጠንከር ያለ የበሽታው ምልክት የሚታይበት ሰው በፍጥነት በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን የህክምና ምክር አና ዕርዳታ ማግኘት አለበት፡፡

#MoH #EPHI

@tikvahethiopia
668🙏292😭42🕊37😱25😡24🥰19🤔19👏18😢16
#ትኩረት🚨

" የጤና ተቋሙ ሳይፈርስ ከላይ ያሉ አካላት አስቸኳይ ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ነው "  - ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በክልሉ ተፈጥሮ ከነበረው ጦርነት በፊት ለመድሃኒትና ለላብራቶሪ ግብዓቶች ይመደብለት የነበረው በጀት ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ነበር።

በሆስፒታሉ የመድኃኒት እና የላብራቶሪ መመርመሪያ ግብዓቶች እጥረት ስለማጋጠሙ በተደጋጋሚ ሲነገር ቢቆይም ችግሩን እስካሁን መቅረፍ እንዳልተቻለ ተነግሯል።

በሆስፒታሉ ላይ ላጋጠመው እጥረት ለዩኒቨርሲቲው ይመደብ የነበረው በጀት በግማሽ መቀነሱ እንደምክንያት ይነሳል።

ለሆስፒታሉ ለመድኃኒትና ለላብራቶሪ መመርመሪያ ግብዓቶች አቅርቦት በ2016 በጀት ዓመት ተመድቦለት የነበረው 18.9 ሚሊየን ብር ሲሆን ለ 2017 በጀት ዓመት የተመደበለት ደግሞ 30 ሚሊየን ብር ብቻ ነው።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዓይደር ኮምፕረንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስተዳደር እና ልማት ዳይሬክተር ዶ/ር ኃይለስላሴ በርኸ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ሆስፒታሉ በ2016 በጀት ዓመት ከ ኢትዮጵያዊ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በብድር የወሰደው መድኃኒት ከ 60-70 ሚሊየን ብር ይደርሳል ብለዋል።

በብድር የወሰደውን የመድኃኒት ክፍያ ሆስፒታሉ መክፈል ባለመቻሉ 14.3 ሚሊየን ብር ከጤና ሚንስቴር ለመድኃኒት አቅራቢ ድርጅት እንዲከፈል ሆኗል።

ሆስፒታሉ የተወሰነ ክፍያ የከፈለ ቢሆንም ያልተከፈለ ከ 40 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ እዳ ከ 2016 ወደ 2017 በጀት ዓመት የተላለፈበት ሲሆን በዚህ ምክንያት ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት መድኃኒቶችን በካሽ እንጂ በብድር እንደማያገኝ ተነግሮታል።

ሆስፒታሉ ከውስጥ ገቢው እዳውን መክፈል ለምን ተሳነው ?

ዶ/ር ኃይለስላሴ እንደሚሉት በዓይደር ሆስፒታል የሚታከሙ ታካሚዎች ከ 80-90 በመቶ የነጻ ታካሚዎች ናቸው።

" ከፍለው መታከም የማይችሉ ታካሚዎች የደሃ ደሃ መሆናቸውን ከወረዳቸው ያጽፋሉ ወረዳውም ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በሚገባው ውል መሰረት ጤና ቢሮው ከእኛ ጋር ውል ያስራል ያከምናቸውን ታካሚዎችም በ3 ወር ወይም በ6 ወር ለሆስፒታሉ ይከፍላል" ብለዋል።

ስለዚህ የምናክማቸው ታካሚዎች እነርሱ በቀጥታ ባይከፍሉም ከጤና ቢሮው ክፍያው እንዲፈጸም የሚደረግ በመሆኑ ነጻ ናቸው ማለት አይደለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ በተጠቀሰው መንገድ ሲያክም ቆይቶ ክፍያው እንዲፈጸምለት ለጤና ቢሮው ጥያቄ ቢያቀርብም "በትግራይ የምዕራብ እና የደቡብ አካባቢዎች የሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች በትግራይ ስር ስላልሆኑ እና በርካታ መጠለያ ጣቢያዎች በመኖራቸው እንዲሁም ታካሚዎችም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ በመሆናቸው ከየትም አምጥቼ ገንዘብ መሰብሰብ አልቻልኩም " የሚል ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ሆስፒታሉ ከጤና ቢሮው ሊከፈለው የሚገባ በርካታ ሚሊየን ብር ስለቀረበት መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ላይ ያለበትን የ40 ሚሊየን ብር በላይ እዳ መክፈል እንዳልቻለ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩልም የማይገኙ እንደ የስነ-ልቦና እና የካንሰር መድሃኒቶች ፣ ካቴተር ፣ ለመስፋት የሚያገለግሉ ስቲቾች (Stitches) እንዲሁም እንደ ማግኒዢየም ሰልፌት ያሉ መድኃኒቶችም መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በአገልግሎቱ በኩል አይገኙም የተባሉትን መድኃኒቶች ለመግዛት ወደ ሌሎች አቅራቢዎች ለግዢ ጨረታ ይወጣል ፤ ከውጭ ሲገዛ በጣም ውድ በመሆኑ ሳቢያ ሆስፒታሉ ለመድኃኒት ካለው ትንሽ በጀት ጋር ተደምሮ ለገንዘብ እጥረት እንዳጋለጠው ጠቁመዋል።

አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጫና ጋር ተደምሮ ከዚህ በፊት ለዓመት ያስገዛ የነበረ ገንዘብ ለሁለት እና ሦስት ወርም አይቆይም ብለዋል።

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሆስፒታሉ እዳውን መክፈል እንደተሳነው ገልጸዋል።

" በካሽ ካልሆነ በብድር ይሰጥ የነበረ መድኃኒት ከዚህ በኃላ እንደሌለ ከአገልግሎቱ ተነግሮናል " ብለዋል።

በዚህም ሳቢያ በሆስፒታሉ በተለይም የስነ አዕምሮ ፣ የማደንዘዣ እና ለመስፋት የሚያገለግሉ ግብዓቶች እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ማጋጠሙን ተሰምቷል።

በሆስፒታሉ የማይገኙ መድኃኒቶችን ታካሚዎች ከውጭ በውድ ዋጋ እንዲገዙ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

እንደሆስፒታሉ መረጃ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስነ አዕምሮ መድኃኒቶች ፍላጎት እየጨመረ ነው።

ሆስፒታሉ ካለበት የበጀት እጥረት በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የባለሞያዎች ፍልሰት እንዳጋጠመው የተሰማ ሲሆን ከህክምና ት/ቤቱ ብቻ ከ300 በላይ ሐኪሞች መሰደዳቸውን ተናግረዋል።

አብዛኛዎቹ ባለሞያዎች የተሰደዱት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ነው።

ዶክተር ፥ " አብዛኛው ሃኪም የሄደው ወደ ሶማሊያ፣ ፑንትላንድ እና ሶማሊላንድ ነው ለመኖር አስቸጋሪ ቢሆኑም የሚከፈላቸው ክፍያ ጥሩ ስለሆነ ለመኖር አዳጋች ወደ ሚባሉ ቦታዎች እየተሰደዱ ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ለህክምና ባለሞያዎች ያልተከፈለ የ17 ወር ደሞዝ እና የ22 ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ እስካሁን እንዲከፈል አልተደረገም።

በሆስፒታሉ ስላጋጠመው እዳ በቀጣይ ምን ታስቧል ? ለሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ " ምንም እንኳን በጽሁፍ ያቀረብነው ጥይቄ ባይኖርም ጤና ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲያደርግልን ወይም የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የእዳ ስረዛ እንዲያደርግልን ለመጠየቅ እያሰብን ነው " ብለዋል።

" ሆስፒታሉ ከሚገኝበት ውስብስብ ችግር ምክንያት የጤና ተቋሙ ሳይፈርስ ከላይ ያሉ አካላት አስቸኳይ ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

በመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል የማናገኛቸው መድኃኒቶች አሉ ስለሚለው ቅሬታ እና ሆስፒታሉ ስላለበት እዳ ምን ታስቧል ? የሚለውን በሚመለከት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመቀሌ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ገብረማርያምን አነጋግረናል ምላሻቸው በቀጣይ ይቀርባል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
😢480186🕊44🙏38🤔30😭26🥰21😡21👏13😱9
🚨 #ትኩረት

ዝም አትበሉ !!

በሴቶች ፣ በተለይም ምንም በማያውቁ ፤ ክፉ ደጉን እንኳን በማይለዩ ትንንሽ ህጻናት ላይ የሚፈጸመው የግብረ ስጋ መድፍረት ተግባር እጅግ አሳሳቢ እጅግም እየከፋ እየሄደ ነው።

ውድ የቲክቫህ ቤተሰብ አባላት ፥ መቼም ሴት ልጆቻችን ፣ እህቶቻችን ላይ ስለሚፈጸም የአስገድዶ መድፈር / የግብረ ስጋ ድፍረትናከዛ ጋር ተያይዞ ስለሚሰጡ ፍርዶች ብዙ ጊዜ መልዕክት መለዋወጣችን ይታወሳል።

ብዙዎችሁ በምትሰሙት ፍርድ እንደምታዝኑም ህጉ ሊስተካከል እንደሚገባ ስትገልጹ ኖራችኋል።

አንዳንድ ጊዜ " እንደው የሚሰጠው ፍርድ ለጆሮ የሚቀፍ ፣ ሰው ለማስተማርና ለመቅጣት ሳይሆን ወንጀለኞችንና ግፈኞችን ለማበረታታ " እንደሚመስል በመግለጽ መሰል መረጃዎች ለብዙሃን እንዳይሰራጩ የጠየቃችሁ ሁላ አላችሁ።

በተለይ በተለይ ሴት ህጻናትን የሚደፍሩ ሰዎች ምንም በማያጠያይቅ ሁኔታ ' የሞት ቅጣት ' እንዲጣልባቸውም የሚገልጽ ሀሳብ ስትፅፉ ነበር።

ከሰሞኑን ደግሞ የተሰሙት ከህጻናት የግብረ ስጋት ድፍረት / መድፈር ጋር የተያያዙ ፍርዶች በርካታ የቲክቫህ አባላትን አስቆጥቷል፤ አሳዝኗል።

ለመረጃ ይሆናችሁ ዘንድ ...

1. ተከሳሽ ሙሉነህ ኡጋሞ የ37 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን የባለቤቱን እህት የሆነችውን የ12 ዓመት ህጻን ከ3 ዓመት በላይ በቆየ ጊዜ ውስጥ  " ለማንም ሰው ከተናገርሽ እገልሻለሁ ! " በማለት በማስፈራራት በተደጋጋሚ አስገድዶ የግብረ ስጋት ድፍረት እንደፈጸመ የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳ የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ገልጿል።

ተከሳሹ ወንጀሉን የፈጸመው ባለቤቱ በወሊድ ምክንያት ታማ ለ2 ወር ሪፌራል ሆስፒታል ከተኛችበት ከቀን 11/04/2013 ዓ.ም. ወንጀሉ እስከታወቀበት 27/05/2016 ዓ.ም. ድረስ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የቀረበውን ክስ ተቀብሎ ሲያከራክር የቆየው የሀዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ በቀን 16/04/2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሽን ጥፋተኛ በማለት
#በ14_ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

2. የገዛ የአብራኩን ክፋይ የ9 ዓመት ልጁን የደፈረ ወላጅ አባት 17 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ተከሳሽ አዶኒያስ አቡታ 40 ዓመቱ ሲሆን የ9 ዓመት ህጻን ልጁን በቀን 07/07/2016 ዓ.ም.ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ ከቤተሰቦቹ ጋር ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ውስጥ መድፈሩን የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል።

ተከሳሹ ድርጊቱን የተበዳይ እናት ቤተሰቧን ለማስተዳደር በከፈተችው የቁርሳ ቁርስ ቤት ውስጥ ለማደር በሄደችበት ዕለት የፈጸመ ሲሆን ተጎጂ ህጻን ተኝታ ካለችበት ቀስቅሶ አስገድዶ መድፈሩ ነው የተጠቀሰው።

የቀረበውን ክስ ተቀብሎ ሲያከራክር የቆየው የሀዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ በቀን 16/04/2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሽን ጥፋተኛ በማለት
#በ17_ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

3. የ31 ዓመቱ ከሳሽ ልደቱ አስፋ የ7 ዓመት ህጻን ከቀን 01/01/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ አመት ያህል የተለያ ማባበያዎችን በመስጠት የግብረ ስጋ ድፍረት ወንጀል ሲፈጽም መቆየቱን የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያስረዳል።

የቀረበውን ክስ ተቀብሎ ሲያከራክር የቆየው የሀዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ በቀን 16/04/2017 ዓ.ም. በዋለው በህጻናት ችሎት ተከሳሽን ጥፋተኛ በማለት
#በ18_ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

4. የ5 ዓመት ህፃን ልጅ የደፈሩ 2 ግለሰቦች የ19 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

በወናጎ ከተማ ቱቱፈላ ቀበሌ ኦዶላ ተብሎ በሚጠራበት አከባቢ የ5 ዓመቷ ህፃን ከቀኑ 8:00 ሰዓት ዳቦ ለመግዛት በሄደችበት የግብረ ስጋ ድፍረት ወንጀል ተፈጸሞባታል።

ወንጀሉን የፈጸሙት አቶ ኤልያስ ኤቶ እና አቶ ታምሩ ንጋቱ የተባሉ የዳቦ መጋገሪያ ቤቱ ሰራተኞች ናቸው።

በግብረ ስጋ ድፍረት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ክስ የቀረበባቸው ወንጀለኞቹ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በወናጎ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዋለ ችሎት ሁለቱም ተከሳሾች እያንዳንዳቸው
#በ19_ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

5. የ3 ዓመት ከ6 ወር ህጻን ላይ የመድፈር ሙከራ ያደረገው ግለሰብ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል።

ወጣት ኤርምያስ ፀጋዬ 3 ዓመት ከ 6 ወር በሆነችው ተበዳይ ህፃን ከምትጫወትበት ቦታ ወደ ኤት ኤል ትምህርት ቤት ይዞ በመሄድ የመድፈር ሙከራ ማድረጉን በምስክር ያረጋገጠው የወናጎ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ግለሰቡን
#በ10_ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

ተጨማሪ ፦ የ28 ዓመት እድሜ ያለው ክብሮም ኣብርሃ የተባለ በትግራይ እንዳስላሰ ከተማ የሚኖር ወጣት የ11 እና 12 ዕድሜ ህፃናትን እንዲቀርቡትና እንዲላመዱት በማድረግ በጨርቅ እና በማጣበቂያ ማስቲሽ እንዳይጮሁ አፍኖ የግብረ ስጋ ድፍረት ወንጀል መፈጸሙ በመረጋገጡ
#የ16_ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶበታል።

ውድ የቲክቫህ አባላት ሆይ ፥ እነዚህ ያጋራናችሁ ከሰሞኑን የተላለፉ የፍርድ ውሳኔዎች ናቸው።

ድርጊቶቹ እጅግ አሰቃቂና ለጆሮም የሚከብዱ አስደንጋጭ ናቸው።

በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ የጭካኔ ተግባራት በየጊዜው ይሰማሉ።

እኛ አሁን እየሰማን ያለነው ወደ ፍ/ቤትና ሚዲያ እየቀረቡ ያሉትን ነው በየመንደሩ በየአካባቢው ምን ያህል ልጆቻችን ጥቃት እየደረሰባቸው ይሆን ?

የፍርድ ውሳኔዎች አስተማሪ ናቸው ?

ልጆቻችንን ከዚህ የከፋ እና አስፈሪ ጊዜ ለመጠበቅ ምን መደረግ አለበት ?

መፍትሄው ምን ይሆን ?

በዚህ ጉዳይ ላይ የህግ ባለሙያ አስተያየት በቀጣይ የምናቀርብ ይሆናል። እናተም የሚሰማችሁን በ @tikvahethiopiaBot ላይ ፃፉ።

@tikvahethiopia
😢1.47K😡418😭296165😱44🙏35🕊27👏19🥰15🤔10
🚨#ትኩረት

ያቄር ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች !

ያቄር በትግራይ ማእከላዊ ዞን ቆላ ተምቤን ወረዳ የምትገኝ የገጠር ቀበሌ ነች።

ቀበሌዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስምዋ ከደርቅ ተያይዞ ይነሳል።

የወረዳው አስተዳደር ፤ በቀበሌዋ የተከሰተው ድርቅ መፍትሄ ካልተበጀለት አስከፊ እልቂት ያስከትላል በማለት መግለጫ አውጥቷል።

" በቀበሌዋ እስከ ሀምሌ 23/2017 ዓ.ም ዝናብ ስላልዘነበ ገበሬዎቹ የነበራቸው የምግብ እህልና የእንስሳት ቀለብ ተሟጦ አልቋል። በዚሁ ምክንያት ፦
➡️ 184 ከብቶች
➡️ 900 አህዮች
➡️ ከ17 ሺህ በላይ በጎችና ፍየሎች አልቀዋል። 200 ያህል የንብ ቆፎ ጠፍቷል " ሲል ገልጿል።

" በቀበሌው ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ በአረጋውያንና ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የሚያመልክቱ የሰውነት መጠውለግና የማበጥ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል " ሲልም አክሏል።

በዝናብ እጦት የተከሰተው ድርቅ በ700 ሄክታር የተዘራ እህል ከጥቅም ውጭ ማድረጉ የሚጠቅሰው ወረዳው ሽሉም እምኒ፣ ምውፃእ ወርቂ ፣ ዘላቅመ ፣ ዓረና ፣ ነዊ ፣ ጯሞ ፣ ደደረ ፣ ስምረት ጉያ በሚባሉ የቀቤዋ ጎረቤት መንደሮችም ተመሳሳይ ምልክቶች መኖራቸው አስታውቋል።

በቀበሌዋ የተከሰተው ድርቅ በሰውና እንስሳት ላይ አሁን ካለው የባሰ አስከፊ አደጋ ከማድረሱ በፊት እንዲገታ ለተለያዩ ለጋሾች ጥያቄ ማቅረቡ የጠቅሰው ወረዳ እስከ አሁን የተሰጠ አስቸኳይ ምላሽ ባለመኖሩ ምክንያት ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ እንዳደረገው አመልክቷል።

በያቄር ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተከስተዋል ስለተባለው አደገኛ ድርቅ አሰመልክቶ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ የቀረበለት የክልሉ የአደጋና ስጋት መከላከል ኮሚሽን ጉዳዩ እየተከታተለው እንደሆነ ጠቅሷል።

ያለውን ሁኔታ በአካል ተመልክቶ በጥልቀት የሚያጠና ቡድን መላኩንና ከሰኞ ሀምሌ 28/2017 ዓ.ም ጀምሮ የተሟላ መረጃ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
#TikvahEthiopiaFamilyMekelle

@tikvahethiopia
1😭965477💔80😢64🕊41🙏33🥰12👏12😡12