TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
62.9K photos
1.61K videos
216 files
4.37K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

መረጃ እና መልዕክት ፦ 0919743630

ማርኬቲንግ ፦ 0979222111 ወይም
0979333111

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ፍትሕ

" አያንቱ ላይ የግብረ-ስጋ ድፍረት ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በፖሊስ አዛዥ ተባባሪነት እንዲሸሽ ተደርጓል " - የአያንቱ ታላቅ ወንድም

🚨 " ፖሊስ አዛዡን ከኃላፊነት ከማዉረድ የዘለለ ደፋሪዉን ለሕግ አቅርቦ ዉሳኔ የማሰጠት ስራ አልተሰራም !! "

በሲዳማ ክልል፤ በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ሻፋሞ ወረዳ ሹሮ ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ በእንጀራ አባቷ ቤት እያደገች የነበረች የ13 ዓመቷ ታዳጊ አያንቱ ቱና እሜ ለእናቷ መልዕክት ተልካ እየሄደች በነበረችበት ወቅት ባጥሶ በቀለ በተባለ ተጠርጣሪ ወጣት የግብረ-ስጋ ድፍረት ወንጀል ይፈጸምባታል።

በኋላም ተጠርጣሪዉ ተይዞ በሕግ ቁጥጥር ስር መዋል ሲገባዉ በፖሊስ አዛዥ ተባባሪነት በቤተሰቦቹ አማካኝነት ወደ ሌላ ክልል እንዲሸሽ መደረጉ ተነግሯል።

በወቅቱ የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ የነበሩትና የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸመው ከተጠረጠረው ወጣት ጋር ባላቸዉ ዝምድና ምክንያት በጉዳዩ ላይ ቸልተኝነትን በማሳየት ተጠርጣሪው ከአከባቢው እንዲሸሽ ስለማስደረጋቸው የአያንቱ ታላቅ ወንድም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ከፍተኛ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰባት ታዳጊዋ አያንቱ በቦና አጠቃላይ ሆስፒታል ስትታከም ቆይታ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀዋሳ ተወስዳ በጣሊታ የሕፃናት ማቆያ እንደምትገኝ የሚናገረው ወንድሟ " ፖሊስ አዛዡን ከኃላፊነት ከማዉረድ የዘለለ ደፋሪዉን ለሕግ አቅርቦ ዉሳኔ የማሰጠት ስራ አልተሰራም " ብሏል።

" አያንቱ በአካልና በስነልቦና በእጅጉ ተጎድታ ከትምህርት ገበታዋም ተለይታ ፍትሕ ሳይሰጣት በጣሊታ የሕፃናት ማቆያ ከ1 ዓመት በላይ እንድትቀመጥ መደረጉ እጅግ በጣም ጎድቷታል " ሲል ገልጿል።

" የክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ' ጉዳዩን ለምን በሚዲያ አወጣህ ሚዲያ ፍትህ ያሰጥህ ' ብለዉኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋረደኝ እንጂ እኔ ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪና አባታችን በሕይወት የሌለ፤ እናታችንም ሌላ ሰዉ አግብታ የምትኖር ምስኪኖች ነን " ሲል ታላቅ ወንድሟ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግሯል።

የፍትህ አካላት ምን አሉ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳይ ላይ የፍትህ አካላትን ምላሽ ለማካተት ፦
° የማዕላዊ ሲዳማ ዞን ዐቃቤ ሕግ መምሪያ
° የወረዳዉ ፍትህ ጽ/ቤት
° የወረዳና የዞኑን ፖሊስ
° የሻፋሞ ወረዳ ሴቶችና ሕፃናት ወጣቶች ጉዳይ መምሪያና የክልሉን ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮን ለማነጋገር ሞክሯል።

የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ ምን አለ ?

የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሙሴ አወል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለፁት በወቅቱ የነበሩት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት መነሳታቸዉን አስታወሰዋል።

እሳቸዉ ወደ አዛዣነት ከመጡ በኋላ ተጠርጣሪዉን የማፈላለጉ ስራ በተለያዩ ቴክኒኮች እየተሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

እስካሁን የተደረጉ ጥረቶች ለምን ዉጤታማ አልሆኑም ? በሚል ትክቫህ ኢትዮጵያ ላነሳላቸዉ ጥያቄ " ፖሊስ የሚችለዉን ሁሉ እያደረገ ነው " ሲሉ መልሰዋል።

የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ፍትሕ መምሪያ ምን አለ ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸዉ የማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዐቃቤ ህግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደማምሰዉ ታፈሰ ፥ ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን በቀረበለት መረጃና ማስረጃ ልክ ተመልክቶ ክስ በማዘጋጀት ሂደት ላይ እያለ ተጠርጣሪዉ እንዲሸሽ መደረጉንና የቀድሞ የሻፋሞ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን ተጠርጣሪውን አፈላልጎ ለህግ በማቅረቡ ሂደት ፖሊስ እያደረገ ያለዉን ክትትል በማጣራት በህግ አግባብ መሰረት ቀጣይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታዉቀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ፍፁም በላይነህን ለማግኘት መክሯል።

ኃላፊዋ በስልክ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ይህም በመሆኑ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ በአካል ቢሯቸው ተገኝቶ ኃላፊዋን ለማነጋገር ቢሞክርም ፈቃደኛ ባለመሆናቸዉ ሃሳባቸው ሳይካተት ቀርቷል።

ጉዳዩን እስከመጨረሻው ድረስ የምንከታተለው ይሆናል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
#TikvahEthiopiaFamilyHawassa

@tikvahethiopia
2😡1.97K😭384239🙏178💔104😢31🥰21😱21👏19🕊17🤔12