TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
63.1K photos
1.62K videos
217 files
4.39K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

መረጃ እና መልዕክት ፦ 0919743630

ማርኬቲንግ ፦ 0979222111 ወይም
0979333111

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኢሬቻ

የኢሬቻ በዓል ምንድነው ? ለምንስ ይከበራል ?

የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር መቆየቱን የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።

የማህበረሰቡ መሪዎችም ኢሬቻ " የምስጋና በዓል " እንደሆነ ይገልጻሉ።

የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን እንደሚያከብሩ ያስረዳሉ።

የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው።

የኦሮሞ ታሪክ ምሁሩ ዲሪቢ ደምሴ፤ " ኢሬቻ ማለት ዋቃ (ፈጣሪ) የፈጠረውን ማመስገን ማለት ነው " ይላሉ።

ማኅበራዊ ደረጃ እና የእድሜ ልዩነት ሳይፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለዘመናት በጋራ ሲያከብር ቆይቷል።

ኢሬቻ የዘመን መለወጫ በዓልም ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል።

በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል።

ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኝን ብሎ ምስጋና ያቀርባል።

የአንትሮፖሎጂ ባለሙያው ገመቹ መገርሳ (ዶ/ር)፤ " ክረምት ለሊት ነው። ለሊት ደግሞ ጨለማ ነው። ጨለማ ለአውሬ እንጂ ለሰው ልጅ አይሆንም። ጨለማው ሲነጋ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ብርሃን ሲሆን ሃሳብ የለም ደስታ እንጂ። 'መስከረም በረ'ባ ማለት ይህ ነው " በማለት የኦሮሞ ሕዝብ ከክረምት መገባደድ በኋላ የኢሬቻ በዓልን የሚያከብርበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

ዲሪቢ ደምሴ የኢሬቻ በዓልን ለማክበረ የሚወጣ ታዳሚ እንደ ሳር ወይም አበባ ያለ እርጥብ ነገር በእጁ ይዞ እንደሆነ ይገልጻሉ።

" ፈጠሪያችን ሆይ አንተ ያጸደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ ለዚህም እናመስግንሃለን' በማለት እርጥብ ነገር ተይዞ ይወጣል" ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ይናገራሉ።

ዲሪቢ በኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት ፈጣሪውን ዋቃን ይለምናል፤ ያመሰግናል ሲሉ ገልጸዋል።

የአንትሮፖጂ ምሁሩ አለማየሁ (ዶ/ር) ፤ " የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ትቶ በነጻ ልቦና ፈጣሪ ንጹህ ወዳደረገው የውሃ አካል ይሄዳል። ኢሬቻ ቀልብ የሚነጻበት ቦታ ነው " ሲሉ ነው የሚያስረዱት።

____

በኢሬቻ ላይ የሚቀርበው ፀሎት እና ልመና ምንድነው ?

(ከአፍሪካ ፍልስፍና መምህሩ ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር) መጣጥፍ ላይ የተወሰደ) ፦

" ሀዬ!  ሀዬ!  ሀዬ! (አሜን አሜን አሜን)
ሀዬ!  የእውነትና  የሰላም  አምላክ!
ሀዬ!  ጥቁሩና  ሆደ ሰፊው  ቻይ አምላክ!
በሰላም  ያሳደርከን  በሰላም  አውለን!
ከስህተትና  ከክፉ  ነገሮች  ጠብቀን!
ለምድራችን  ሰላም  ስጥ!
ለወንዞቻችን  ሰላም  ስጥ!
ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!
ለሰውም  ለእንስሳቱም  ሰላም  ስጥ!
ሀዬ!  ሀዬ!  ሀዬ! (አሜን አሜን አሜን! "

____

" ከመጥፎ አየር ጠብቀን!
ንፁሕ ዝናብ አዘንብልን!
ያለአንተ ዝናብ የእናት ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያለአንተ ዝናብ የላም ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያለአንተ ዝናብ መልካው ውኃ አይሰጥምና!
ያለአንተ ዝናብ ምድሩ ቡቃያ አይሰጥምና!
ከእርግማን ሁሉ አርቀን!
እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!
ከረሃብ ሰውረን!
ከበሽታ ሰውረን!
ከጦርነት ሰውረን!
ልጄ እያሉ አልቅሶ ከመቅበር ሰውረን!
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! " 

የ2016 ዓ/ም የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ከንጋት ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃውን ያሰባሰበው ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ / ሪፖርተር ነው።

ተጨማሪ ቲክቫህ አፋን ኦሮሞ ፦ https://tttttt.me/+UTMftkYHBuOGaQ23

@tikvahethiopia
😡1.74K713🙏49🥰40🕊40😢26😱13😭1