ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ጌታችንን አርአያ አብነት አድርገን ስለ ቅዱሳን እንናገራለን እናስተምራለን እናከብራለን።


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለቅዱሳን
ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ከሥጋዌው በፊት በሥጋዌው ጊዜና ከሥጋዌው በኋላ ስለነበሩና
ስለሚነሱ ቅዱሳን በብዙ መንገድ ተናግሯል፡፡ "አውሬውም
ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው በአርባ ሁለት
ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው እግዚአብሔርንም ለመሳደብ
ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን
ከፈተ" ራእይ 13÷5 ተብሎ እንደተነገረ ጠላት ዲያብሎስ
ስለቅዱሳን ሲነገር በልዩ ልዩ መንገድ ቢቃወምም የግብር ልጆቹም
ዮሐ 8÷44 ነገረ ቅዱሳን እንዳይነገር በአፍም በመጽሐፍም
ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቢቃወሙም ቢከላከሉም እኛ ግን
አምላካችን አባታችን ጌታችን መድኃኒታችን አምባ መጠጊያችን
ተስፋችን ከሆነ ከእርሱ ከክርስቶስ ተምረን እነሆ ስለቅዱሳን
እንናገራለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማያዊ መንግሥቱ ሕግ
የሆነች ወንጌልን በቅዱሳኑ ስም እንዲጠራ አድርጓል፡፡
የቤተክርስቲያን መሠረት የሆነ ወንጌልን በቅዱሳን ስም እንዲጠራ
አድርጎ ሳለና "እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ
ስለሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ …. በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ
ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም
እሰጣቸዋለሁ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ" ኢሳ
56÷4 ያለውንም ቅዱሱን ቃሉን ቸል ብለው ቤተክርስቲያን
በቅዱሳን ስም ለምን ተሰየመ ብለው የሚከራከሩ ሰዎችን ማየቱ
ያስተዛዝባል፡፡

#ጌታችን_ስለ_ዮሐንስ_መጥምቅ
ጌታችን ስለ ዮሐንስ "እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ"
ዮሐ 5÷35 "ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ
የሚበልጥ አልተነሳም" ማቴ 11÷11 ብሎ መስክሮለታል፡፡ ዛሬ
ግን በክርስቶስ እናምናለን የሚሉ እርሱን ተከትለው ግን ወዳጆቹ
ቅዱሳኑን ብርሃናት እያሉ መጥራትን የተጠየፉ ሰዎችን ማየቱ
የተለመደ ሆኗል፡፡

#ጌታችን_ስለ_ናትናኤል
"ተንኮል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ" ዮሐ 1÷48፡፡
በፈጣሪ አንደበት እንዲህ ስለተመሠከረለት ጻድቅ ሰው መናገርን
መጠየፍ ይህንንም የሚናገሩ ሰዎችንም "ጌታን ሸፈናችሁት" ብሎ
መክሰስ ምንኛ አለመታደል ነው?
ጌታችን ስለ ቅዱስ ጳውሎስ
"በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን
ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው ይህ ሰው ስለ ስሜ
መከራ ሊቀበል አለው" የሐዋ 9÷15-16፡፡ በማለት ታላቅነቱንና
ታማኝነቱን መስክሮለታል፡፡

ጌታችን_ስለ_ቅዱስ_ጴጥሮስ
ጌታችን ስለቅዱስ ጴጥሮስ ብዙ ተናግሯል፡፡ በምን አይነት አሟሟት
ፈጣሪውን ያከብር ዘንድ እንዳለው እንኳን ሳይቀር መስክሮለታል
ዮሐ 21÷18-19፡፡ ስለ እርሱ ብቻ ሳይሆን እርሱን የመሰሉ
ቅዱሳን ሁሉ እርሱን በመከተላቸው በዓለም እንደሚጠሉ በግፍ
አገዳደልም እንደሚገደሉ አስተምሯል ማቴ 5÷11 ዮሐ 16÷1-2፡፡

ጌታችን_ስለ_ወንጌላዊው_ቅዱስ_ዮሐንስ
ዛሬ ሞት ያላገኛቸው ከነሥጋቸው ወደ ሰማይ የተነጠቁ ቅዱሳን
እንዳሉ ስናስተምር በሥጋ መንገድ የሚያሽሟጥጡ በእንዴት
ይሆናል ጥያቄ የሚያደርቁን ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እርሱ
እስኪመጣ ድረስ ሞት እንደማያገኘው ከአንዴም ሁለት ጊዜ
መስክሮለታል ማቴ 16÷28 ዮሐ 21÷22፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ነቢዩ
ሔኖክ ነቢዩ ኤልያስ ሞት እንዳላገኛቸው ይመሰክራል ዘፍ 5÷24
2ነገ 2÷11፡፡ ሞት ያላገኛቸው ከነሥጋቸው የተሠወሩ ቅዱሳን
እንዳሉ ሲተረክላችሁ የማታምኑ የምትጠራጠሩ እናንተ ሆይ
ስለዚህ ነገር ምን ትሉ ይሆን? ቅዱሳን ዓለምን ዞረው አበል
ሳይቀበሉ እየደከሙ አልብሱን አንተርሱን አጉሩሱን ሳይሉ በትኅትና
እያገለገሉ ተከብረው በክብር ተከብበው እየተሞገሱ ሳይሆን
እየተገረፉ እየተሰደቡ በድንጋይ እየተወገሩ እየተጨበጨበላቸው
ሳይሆን በጥፊ እየተመቱ ስለራሳቸው ታላቅነት ሳይሆን
ስለክርስቶስና ከእነርሱ ቀድመው ስለነበሩ ንጹሐን ቅዱሳን አበው
ሰበኩ አስተማሩ፡፡ በዚህም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትና እርሱን
የመሰሉ ሌሎች ቅዱሳን "ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው ስለዚህም
ነፍሴ ፈለገቻቸው" መዝ 118÷129 ብለው ዘመሩ የክርስቶስ
መንፈስ ያደረበት ሁሉ የክርስቶስ የሆኑትን ይወዳልና፡፡ ከጻድቁ
አቡነ ተክለሃይማኖት እንዲሁም እልፍ ከሆኑ ወዳጆቹ
በረከትያሳትፈን አሜን!!!

በመምህር ቢትወደድ ወርቁ

👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit