ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
" #በቸርነትህ_ዓመታትን_ታቀዳጃለህ።"
____________________________

እግዚአብሔር አምላክ ለሰዎች ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች አንዱ ጊዜ ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የዘመናት ጌታ የጊዜ ባለቤት እግዚአብሔር አምላካችን እንደቸርነቱና እንደ ምሕረቱ ብዛት ዓመትን እንደሚያቅዳጅ፣ እንደሚሰጥ ሲገልጥ "በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ" በማለት ዘምሯል።

ዘመን ለሰው ልጆች የተሰጠ ድንቅ ስጦታ ነው። ይህን ድንቅ ስጦታ አስረዝሞ የመጠቀም አልያም አሳጥሮ መጎዳት ያለው በሰው እጅ ላይ ነው።

#ዘመናችን እንዴት ይርዘም?
___________________


አንደበትን ከክፉ እንከልከል ፡ አንደበታቸውን ክፉ ከመናገር ያልከለከሉ ብዙዎች በጎውን ዘመን አላዩም። በዙዎች ዘመናቸው እንደ ምድረ በዳ አበባ ቶሎ ረግፏል። ሐናንያ እና ሰጲራ በአንደበታቸው ሐሰት ቢገኝ ከሰይጣን ጋር ተወዳጅተዋልና በጎውን ዘመን እንዳያዩ ዘመናቸው አጥሮ በሞት ተሸኝተዋል። የሐዋ 5፡1 በአንደበታቸው ክፋት የገባባቸው ሌሎችም እግዚአብሔር ዘመናቸውን አሳጥሮባቸዋል። መዝሙረኛው ዳዊት በመዝሙር 34፡12 ላይ"ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ።" በማለት ይናገራል።

ሌላው ዘመንን ማርዘሚያ ብርቱ መድኃኒት እግዚአብሔርን መፍራት ነው። እግዚአብሔርን መፍራት ከሚያስገኛቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አንዱ ዘመንን ማስረዘም ነው። "እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፤ የኀጥኣን ዕድሜ ግን ታጥራለች።" ምሳ 10፡27

ከኃጢአት መጠበቅ ራስን በቅድስና ሕይወት ኖር ፡ በዘመነ አበው የነበሩ ቅዱሳን ከአዳም አንስተን ብንመለከት በዘመናቸው እጅግ የሸመገሉና በርካታ ዓመታትን የኖሩ ነበሩ። ለአብነትም አዳም 930 ማቱሳላ 969 ኖህ 950 ወዘተ ... የእነዚህ ሰዎች ረጅም ዘመን በምድር ላይ የመኖራቸው ምሥጢር ምንድን ነው ብለን ብንመረምር በአካሄዳቸው እግዚአብሔር አምላካቸውን ማስደሰታቸውና ከኃጢአት መጠበቃቸው በቅድስናም መኖራቸው ነው። የሰው ልጅ በሚሠራቸው ገቢር ኃጢአት ምክንያት ዘመኑ ማጠር ጀመረ። በኖህ ዘመን የነበሩ ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ አባቶቻቸው ዘጠኝ መቶ የሚቆጠር ዓመትን መኖር አልቻሉም። ይልቁንም የኃጢአት ግድግዳ ከእግዚአብሔር ቢለያቸው የዘመናቸውና የዕድሜ ጣርያ 120 ዓመት ሆነ። ዘፍ 6፡3 "እግዚአብሔርም፦ መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ።" በዚህም አላበቃም በዳዊት ዘመን ይህ የዕድሜ ጣርያ ወደ 70 እና 80 ዓመት ወረደ። "የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው።" መዝ 90፡10 እነ አዳም 900 ዓመት ኖረው ያልደከሙት በዚህ ዘመን በ80 እና 90 ዓመት የሚደከምበት ምሥጢሩ የሰው እግዚአብሔርን መበደልና ኃጢአትን የሙጥኝ ማለት ነው። በእምነታቸው በምግባራቸው እግዚአብሔርን ያስደሰቱት ቅዱሳኑ ግን ዘመናቸው ረዝሞ ዕድሜያቸውን ጠግበው አልፈዋል። 1ኛ ዜና 29፡28 ፣ 2ኛ ዜና 24፡15 ፣ ኢዮ 42፡ 17

#ምን_እናድርግ?
____________
እግዚአብሔር አምላካችን አዲሱን ዘመን እናይ ዘንድ አድሎናል። በቸርነቱም ዘመናትን አቀዳጅቶናል። ያቀዳጀንን ዘመን የመቀደስና የመጠቀም ኃላፊነቱንም አብሮ ሰጥቶናል። ይህን ዘመን እንዴት እንቀድሰዋለን? ቅድስናን በመጨመር፣ ኃጢአታችንን በመቀነስ ፣ ንስሐን በማብዛት ፣ ያለንን በማካፈል ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠንከር ዘመኑን መቀደስ እንችላለን።

ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ የሰጠን እግዚአብሔር አምላካችን ክብር ምስጋና ይግባው። ዘመኑ የሰላም የጤና የንስሐ በሥጋው ወደሙ ምንታተምበት በጎውን ምንሰማበት ቤተ ክርስቲያናችን ምታብብበት ያድርግልን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

(አቤኔዘር ወልደ ተክለሃይማኖት)

05/13/2013 ዓ.ም