ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ነገረ_ሥላሴ

ክፍል አንድ

ሥላሴ የቃሉ ትርጉም ሠለሰ ሦስት አደረገ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስትነት ማለት ነው። ነገረ ሥላሴ ልዩ ሦስትነት በመባል ይታወቃል። ልዩ ያሰኘው ምንድን ነው ቢሉ በሦስትነት ውስጥ ፍጹም አንድነት ስላለ ነው። ሥላሴ ሦስት ብቻ አይደሉም። አንድም ናቸው እንጂ። አንድነታቸው ሦስትነታቸውን አይከፍለውም። ሥላሴ አንድም ብቻ አይደሉም። ሦስትም ናቸው እንጂ። ሦስትነታቸው ደግሞ አንድነታቸውን አይጠቀልለውም አይጠቀልለውም። ሥላሴ በአንድ ቅጽፈት አንድም ሦስትም ናቸው። ይህ ከሌሎች አንድ አልያም ሦስት ከሆኑ ነገሮች ሁሉ ይለያቸዋልና ልዩ ሦስትነት ይባላሉ። አንድን ነገር አንድ ነው ካልን ፈጽሞ ሦስት ሊሆን አይችልም። እንደዚሁም ሦስት የተለያዩ ነገሮችም ፈጸመው አንድ ሊሆኑ አይችሉም። ሥላሴ ግን አንድም ሦስትም ናቸው።

#የሥላሴ_አንድነት
👉 ይህንን ዓለም በመፍጠር፣ በማሳለፍ፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና ይህን በመሳሰሉት ሁሉ አንድ ናቸው። ለምሳሌ ዮሐ 10:30 " እኔ እና አብ አንድ ነን።" የሚለው የእግዚአብሔር ወልድ ንግግር ከአብ ጋር በሥልጣን የተካከለ የአብ ሥልጣን የእርሱ የሆነ የእርሱም ሥልጣን ሁሉ የአብ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ዮሐ 5:17–23

ሌላ ምሳሌ ብንመለከት የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ስልጣንና ፈቃድ አንድ መሆኑን በክርስቶስ ትንሳኤ መመልከት እንችላለን። ክርስቶስ ከሞት የተነሳው በራሱ በአባቱና በመንፈስ ቅዱስ አንዲት ሥልጣን ነው። በራሱ ሥልጣን ለመነሳቱ ዮሐ 2:19 "ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።" ሌላም ቦታ “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” በማለት እግዚአብሔር ወልድ በሥልጣኑ እንደሚነሳ ተናገረ። ዮሐ 10፥17–18
በሐዋርያት ሥራ ላይ ደግሞ ክርሰቶስን ያስነሳው አብ መሆኑን ይናገራል። “እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።”
ሐዋ 2፥24፣ 2:32፣ 3:15፣ 5:30
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ ደግሞ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሳው መንፈስ ቅዱስ ነው በማለት ይናገራል። “ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።” ሮሜ 8፥11
በእነዚህ ክፍሎች የምንመለከተው የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ስልጣን አንዲት መሆኗን ነው።

በቀጣዩ ጽሑፋችን ሌሎች የሥላሴን አንድነት የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ይዘን አንቀርባለን።

ይቆየን።

ይቀጥላል።

👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit