ዐውደ ምሕረት
3.68K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
"ዕግትዋ ለጽዮን ወሕቅፍዋ"
***************
“ጽዮንን ክበቧት በዙርያዋም ተመላለሱ” መዝ48፥12

የጽዮን በዓል አከባበር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ኅዳር21 ቀን በታላቅ ክብር ታከብረዋለች፡፡ በዚሁ ዕለት የእመቤታችን ወዳጆች ምእመናን በዓሉን ለማክበርና ለመሳለም ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን በብዛት ይገሠግሳሉ፡፡ ዕጣን፡ ጧፍ፡ዘቢብ መባውን ይሰጣሉ፡፡ ካህናቱም ከዋዜማው ጀምረው በከበሮናበጸናጽል ስብሐተ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፡፡ በድርሳነ ጽዮንመጽሐፍ እንደተገለጠው ካህናቱ በጽዮን ፊት እንደየመዓርጋቸው ቆመው“እግትዋ ለጽዮን ወህቅፍዋ” የሚለውን መዝሙር ከዳዊት እያወጣጡ ይጸልያሉ፡ ይዘምራሉ፡፡ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ የታቦተ ጽዮንን ተራዳኢነት በምእመናን ፊት ይመሰክራሉ፡፡
ነቢያት ክርስቶስ ወዲዚህ ዓለም በሥጋ ማርያም ከመገለጡ በፊት ከእግዚአብሔር ተልከው ሕዝቡን ከአምልኮተ ጣዖት ከገቢረ ኃጢአት እንዲጠበቅ የሚመክሩ የሚያስተምሩና የሚያጽናኑ ነበሩ፡፡ ሉቃ 16፤17፣ ኢሳ. 40፤1፣ ኢሳ. 44፤1-11፡፡ የነቢያት ትንቢት ዋናው ዓላማ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡን እንደተዋቸው እንደማይቀር፣ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰው ሆኖ ተገልጦ ወንጌልን አስተምሮ ስለእኛ መከራን ተቀብሎ እንደሚያድነን መግለጥ ነበር፡ ኢሳ. 7፤14፣ ማቴ. 1፤ 23፣ ሚክ. 5፤2፡፡ነቢያት ሁሉ ስለ ክርስቶስ በተለያየ ኅብረት ትንቢትና አምሳል እንደ ተናገሩ ሁሉ ክርስቶስ ስለሚገኝባት አማናዊት ድንግል ማርያምም ተናግረዋል፡፡ ስለ ክርስቶስ በትንቢትና በተምሳሌት የተናገሩ ሁሉ ስለርሷ ተናግረዋል፡፡
የጽዮን በዓል ለምን ሕዳር 21 ይከበራል?
በዋናነት በሕዳር 21 ቀን የምናከብረው የእመቤታችንየጽዮን ማርያም በዓልምክንያቱ ምንድን ነው? ጥንተ ነገሩስ እንዴት ነው? ቢባልኅዳር 21 ቀን የሚከበረውም የእመቤታችንበዓል ምሳሌዎች የተገለጡበት እና የተለያዩ ሥራዎች የተሰሩበት ዕለት ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህም፡- ምሳሌዎች የተገለጡበት እና የተለያዩ ሥራዎች የተሰሩበት ዕለት ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህም፡-
፩.ነቢዩ ዘካርያስ ሁለንተናው ወርቅ የሆነ፣ የዘይት ማሰሮ በራሱ ላይ የነበረበትንና ሰባት መብራቶች ያሉትን መቅረዝ ሲያበራ ያየበት ዕለት ነው፡፡ ዘካ. 4፤1-2፡፡ ዘካርያስ ያየው ብርሃን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ. 8፤12፡፡ ይህ ብርሃን የታየባትና የተገለጠባት መቅረዝ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ ብርሃን መቅረዝ እንዲያዝና እንዲገለጥ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ተገልጦልናል፡፡ ጨለማ ዓለምን አብርቷል፡፡ ብርሃን ክርስቶስን ወልዳለችና እርሷም እመ ብርሃን / የብርሃን እናት/ ትባላለች፡፡
፪.ታቦተ ጽዮን ዳጎንን ገልብጣ በመጣል ኃይሏን የገለጠችበት ዕለት ነው፡፡ በፍልስጥኤማውያን ተማርካ ቤተ ጣዖት ወስደው ከጣዖታቸው ከዳጎን በታች አስቀምጠዋት ነበር፡፡ ታቦተ ጽዮን ግን በላይዋ ያለውን ዳጎንን ገልብጣ ጥላ እርሷ ከላይ ተቀመጠች፡፡ በታቦት የሚገለጠው የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ ምክንያቱም በታቦቱ ላይ ያለው ሕገ እግዚአብሔርና ስመ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም የጸና ክንድ ነውና ሁሉን ያሸንፋል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ለጊዜው ስትማረክ ደካማ ብትመስልም መማረኳ ግን ኃይሏን ለመግለጥ፣ ለአሕዛብ የጣዖትን ከንቱነት የታቦትን ክቡርነት ለመግለጥ ነበር፡፡
፫. ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦቱን ይዞ አክሱም የገባበት፣ ንግሥት ሳባ ታላቅ በዓል አድርጋ የተቀበለችበት፣
፬. አብረሃ ወአጽብሐ በአክሱም ከተማ 12 ቤተ መቅደስ ያለው ቤተ ክርስቲያን በአስደናቂ ሁኔታ ሠርተው ከጨረሱ በኋላ ቅዳሴ ቤቱን ያከበሩበት፣ እንዲሁም
፭. በ9ኛው መ/ክ/ዘመን ዮዲት ክርስትና ለማጥፋት በተነሳች ጊዜ በእርሷ ምክንያት ታቦተ ጽዮን ወደ ዝዋይ ሐይቅ የተሰደደችበት፡፡ በኋላም የሰላሙ ዘመን ሲመጣ ተመልሳ አክሱም የገባችበት በዚሁ በኅዳር 21 ስለሆነ በእነዚህ በተደራራቢ ታሪኮች ምክንያት በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል “ኅዳር ጽዮን በአክሱም ጽዮን” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት
ሀ. ታቦተ ጽዮን በወርቅ የተለበጠች ናት፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነፍስ በሥጋዋ ንጽሕት የመሆንዋ ምሳሌ ነው፡፡ ወርቅ የንጽሕና የቅድስና ምሳሌ ነው፡፡ ሰብአሰገል ካመጡት እጅ መንሻ አንዱ ወርቅ ነው፡፡ ይኸውም የክርስቶስ ንጹሐ ባሕርይነት የሚገልጥ ነው፡፡
ለ. እስራኤላውያን በምድረ በዳ 40 ዓመት መና መግቧቸዋልና ይህን ለሚመጣ ትውልድ በታቦቱ ዘንድ እነዲያስቀምጡ ታዘው ነበር፡፡ አንድ ጎሞር መና በታቦቱ ፊት አሮን አስቀመጠ፡፡ ዘጸ. 16፤31-34፡፡ እስራኤላውያን የተመገቡት መና የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ. 6፤58፡፡ መናው የተቀመጠበት ጽላተ ኪዳን ደግሞ አማናዊ መና ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡
ሐ. በጽላቱ ላይ በእግዚአብሔር ጣት 10ቱ ቃላት ተጽፈዋል፡፡ ጽላቱ የእምቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጽላቱ ላይ የተጻፈው ቃሉ የሥግው ቃል የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐንስ በመጀመሪያ ቃል ነበር፡፡ ዮሐ. 1፤1 እንዳለ፡፡ በጽላቱ ላይ በአጻብአ እግዚአብሔር የተጻፈው ቃል ቃለ እግዚአብሔር ከእመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ሕዋሳቶቿን ሕዋሳቱ አካሏን አካሉ አድርጎ ሰው የመሆኑ ምሳሌ ነበር፡፡
በአጠቃላይ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን መቀጥቀጧና በክብር መመለሷ እመቤታችንም በእናቷ በሐና ማኅፀን ሳለች ጀምሮ የተነሱባትን ጠላቶቿን አይሁድ አጋንንትን በኃይለ እግዚአብሔር ድል አድርጋ የአምላክእናት ለመሆን ለመብቃቷና ከርሷ የሚገኘው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጋንንትን ድል አድርጎ ግእዛነን እንደሚመልስልን፣ ከሲዖል ነፃ እንደሚያወጣንና በክብር ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ጥንት አኗኗሩ እንደሚያደርግ የገለጠና ያስረዳ ተምሳሌት ነበር፡፡
ታቦተ ጽዮን በእግዚአብሔር ፈቃድ በቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ኢትዮጵያ ገብታ በአክሱም ከተቀመጠችበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራችን በረከት፣ ረድኤት ሳይለያት በየዘመኑ የተነሱ ጠላቶችን ድል እያደረገች መልሳለች፡፡ እግዚአብሔር በታቦተ ጽዮን ላይ በረድኤት እያደረ የሕዝቡን ችግር እንዳስወገደ ሁሉ ዛሬም ችግራችንን እንዲያቃልልን፣ በረድኤት እንዲጎበኘን ዘወትር በጸሎት ታቦተ ጽዮንን ልንማጸን ይገባል፡፡ ለእስራኤላውያን በታቦቱ ላይ እያደረ እየተገለጠ ያናገረ የባረከ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር አይለየን፡፡
ጽዮን የተባለች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጣዕመ ውዳሴዋ ሀብተ ረድኤቷ በሁላችን ላይ አድሮብን ይኑር፡፡ ለዘላለሙ አሜን፡፡

በዓሉን በዓለ ፍስሐ በዓለ ደስታ ያድርግልን!

አዘጋጅ #ተካልኝ_መገርሳ

👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit