ዐውደ ምሕረት
3.66K subscribers
932 photos
24 videos
271 files
195 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ተከተሉኝ

ይህ የተስፋ ቃል ፍቅሩ የማያልቀው የህያው እግዚአብሔር አብ ልጅ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ ነው። ይህም ታላቅ ጥሪ ከጥንት ጀምሮ እስካሁኗ ሰዓት ዘወትር ይጣራል ብዙኀኑ ሰምተውት ነገር ግን ጥቂቶች ኖረውበታል። አንድ ቀን ጌታችን ደቀመዛሙርቱን "እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ያጠፋታል፤ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።" አላቸው ከዛም ከሐዋርያት ወገን በችኩልነቱ እና በፍጥነቱ የሚታወቀው እንዲሁም በእርሱ አለትነት ላይ ቅድስት ቤተክርስትያን የተሰራችበት ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ ጠየቀ " እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን ?" ሲል ጠየቀ ጌታችንም መልሶ " እውነት እላችኀለው እናንተስ የተከተላችሁኝ፣ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በዐሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገድ ልትፈርዱ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።" ብሎ በምጽዐቱ ዕለት ፈራጅ ዳኛ አድርጎ እንደሚሾማቸው ቃል ገባላቸው። ቀጥሎም " ስለ ስሜም ሴቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል። የዘላለም ህይወት ይወርሳል ነገር ግን ብዙዎች ፊተኞች ኋለኞች ፤ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ" ብሎ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ፊተኞች ሐዋርያቱን ኋለኞች እንደሚሆኑ ነግሮአቸዋል ። መቶ እጥፍ ይቀበላል ማለት ፍፁም ክብርን ያገኛል ማለት ነው።....ታድያ ስንቶቻችን ነን ያህን ጥሪ ያስተዋልን? ማነውስ ፍፁም ክብርን መንግስተ ሠማያትን የማይፈልግ? ክብሩን እምንፈልገው ያክል ጥሪውን እንፈልገዋለን? ...ብርሃንን ለማየት በጨለማ ማለፍ ግድ ይለናል ምክንያቱም እሥራኤል ብርሃን ሽተው በጨለማ ተጉዘዋልና ፤ ከፍ ለማለት ዝቅ ማለት ግድ ይለናል ቅድስ ዳዊት ከክብሩ ይልቅ ክርስቶስን አስቀድሞ ዝቅ ብሎ የክብር ጌታ ከፍ ያደረገው ፤ ሰማያዊቷን ርስት መንግስተ ሰማያትን ለማግኘት ትንሹን ምናምንቴውን ዓለም ንቀን ትተን መስቀል የተባለውን መከራ በመሸከም ራስን መካድ ፣ ሥጋችንን መተው ፣ ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ መኖር ያስፈልጋል። ስለዚህ እንከተለው ሕጉ ለመንገዳችን ብርሃን ነውና ...."ሰው አለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ሁሉን ቢገዛ ነፍሱን ቢያጎድል በነፍሱ ከተጎዳ ገሃነመ እሣት ከወረደ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? መሪረ ገሃነምን ፣ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ባያውቅ ነው እንጂ ፤ ቢያውቅማ ኖሮ ለነፍሱ ቤዛ በሰጠ ነበር.. ብሏልና ጌታችን። በአጠቃላይ ይህ ጥሪ እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍቅር የምናውቅበት ነው እንዴት ብንል የበጎች ጠባቂ ለበጎቹ ካለው ፍቅር የተነሳ ቀን በመስክ በማሰማራት ይውልና በማታ አውሬ እንዳይወስድበት እየገፋ በጩኸት እየተናገረ አንዳንዴም እየቀጣ ከቤቱ ያስገባቸዋል የኛ አምላክ ክርስቶስም ዘወትር ከዚህ አብልጦ በብዙ ነገር ወደ ፈተና ገብተን ወድቀን እንዳንቀር በመላእክቱ ያስጠብቀናል ፣ ተከተሉኝ እያለ ወደ ሕይወት ጎዳና ይመራናል። እስቲ ይህን እናስተውል እኛ ከመኖራችን በፊት ወደደን ስለዚህ ፈጠረን ከጥልቅ ፍቅሩም የተነሳ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረን። ከመፈጠራችን አስቀድሞ ሁሉን ነገር አዘጋጀልን ሰማይን እንደጣሪያ ሠራና መሬትን አዘጋጀ በመቀጠል ብርሃናትን ፣ውኀ፣አትክልቶችን እና ገነትን አዘጋጀልን በኋላ እኛን ፈጠረ። በኀጢአት ተሰነካክለን በወደቅን ጊዜ የምንድንበትን የድኅነት በር ንስሃን አዘጋጀ ፤ ከፍቅሩ የተነሳ ይመሩን ይመክሩን እና ያስተምሩን ዘንድ ነቢያትን ላከ ክፉውን እና ደጉን የምንለይበትን አስተዋይ ልቡና ሰጠን አስተዋይነታችንንም እንዲያበራልንም የተጻፈ ሕግን ሰጠን በኀጢአት ስንጎብጥ በንስሃ ቀና እንድንል የምትረዳንን ምርኩዝ ድንግል እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለዘለዓለም እናት አድርጎ ሸለመን። የእኛን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ ሰው የሆነውም ለኛ ካለው ጥልቅ ፍቅር ነው በእኛ እንደኛ ሆኖ ሕግንም አከበረ ስለወደደን ስለኛ ራሱን ለሕማም ለሞት አሳልፎ ሰጠ። በመስቀልም የፍቅር ስጦታ ሆኖ ቀረበ የዓለምን ኀጢአት ተሸክሞ በደሙ ፈሳሽነት አነጻው ስለኛ ሲል ኀጢአት ሳይኖርበት እንደ ኀጢአተኛ ተቆጠረ።
፦ ለኛ ካለው ፍቅር የተነሳም እነዚህን የተስፋ ቃላት ሰጠን
+ አዲስም ልብንም እሰጣችኃለሁ፤ አዲስም መንፈስንም በውስጣችሁ አኖራለው ..ሕዝ 36፥26
+ በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል እኔም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ ለዘለዓለም አይጠፋም ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም ዮሐ 10፥27
+ በአባቴ ቤት ብዙ መደሪያ እን ማረፊያ አለ ፤እንዲህ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበር። ከሄድሁና ቦታ ካዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤እናንተም እኔ በአለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ። ዮሐ 14፥2-7
+++እነዚህ ሁሉ ለእኛ የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው እርሱ እግዚአብሔር እንደወደደን እና እንዳፈቀረን እርስ በእርሳችን ተዋድደን ተፈቃቅረን እሩስም በመራን እና በሚመራን መንገድ እንድንከትለነው የእርሱ ፈቃድ ይሁንልን።
...+++ በቸርነቱ ልቦናችንን አብርቶ የጥሪው ታዳሚ አድርጎ ወደ ሰማያዊዉ መሰብሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ይሰብስበን..አሜን!


ቀን 20/8/12
አዘጋጅ ብሩክ መልሣቸው

👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit