ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ዛሬ የኪዳናት ሁሉ ፍጻሜ #ኪዳነ #ምሕረት ናት።ለቅዱሳኑ ለአዳም፣ለኖኅ፣ለመልከጼዲቅ፣ለአብር
ሃም፣ለዳዊት የተገባው ቃልኪዳን ሁሉ በእግዝእትነ ድንግል ማርያም ፍጻሜውን አገኘ።ይህ ኪዳነ እግዚአብሔር ምንድነው? ቢሉ የእግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆን ነው።ሰው ሆኖም መዳናችንን መፈጸም ነው።

#ቅዱስ ዳዊት “ማዳን የእግዚአብሔር ነው፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው።” መዝ 3፥8
ብሎ እንደተናገረው ሰውን ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ማዳን የሚቻለው የፈረደበት እግዚአብሔር ነው።

#“ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።”(መዝ 33፥5) በሚለው ቃልም ምን እግዚአብሔር ሰውን ማዳን(ጽድቅ) ቢችልም ፍርድንም ይወድዳል።ሰውን በቸርነቱ የማዳን ፈቃዱ ጽድቅ ሲሆን፤የበደለ ሰው ነውና ሊክስ የሚገባውም ሰው ነው፦ይህ ፍርድ ይባላል።
ሰው ደግሞ ራሱ የሞት ፍርድ ስላለበት ሰውን ማዳን የማይቻለው ነው።ታዲያ ምን ተሻለ? የሞት ፍርድ የሌለበት፤የባሕርይ ጉስቁልና (fallen nature)፤መርገመ አዳም መርገመ ሔዋን ያላገኘው ንጹሕና ቅዱስ ሰው ነዋ !!! ይህንን ነቢዩ ኢሳይያስ
“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።”
(ኢሳ1፥9) በማለት የገለጸው ከላይ ካነሣናቸው ጉዳዮች የቀረች ንጹሕ ዘር ታስፈልግ ነበር።ከዚህች ንጹሕ ዘር ነው ራሱ እግዚአብሔር የነሣውን ሥጋዋን ነፍሷን ተዋሕዶ የሚያድነን።

#ይህቺ አዳምና ሔዋን በበደሉት በደል ከመጣው ጣጣ ሁሉ ከአዳም ልጆች በተለየ መልኩ ያስቀራት ዘር እመቤታችን ናት።ልብ በሉ "ዘርን ባያስቀርልን" አለ እንጂ "ዘሮችን" አላለም።ዘርዪቱ አንዲት ናት።ልዩ ናት!!!አትደገምም፤አትነገርም።ይህቺ ሰዎች ሁሉ ላይ ከመጣው የሞት ዕዳ የቀረች (የተረፈች) ዘር እመቤታችን ለመሆኗ ሰማያውያን መላእክትን ምድራውያን ጻድቃንን ምስክር እናቆማለን።“እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ።”(ኢሳ 1፥2)

1.“በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።”
(ዘፍ 3፥15) የሰማዮች ሰማይ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ነው።ይህቺ ከእባቡ (ከሰይጣን) ጋር ጠላትነት ውስጥ የምትገባ ዘር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።ሔዋን ከመሰለችህ ተሳስተሃል።ስለ እርሷማ ቅዱስ ኤፍሬም "ከይሲ ዲያቢሎስ ያሳታት ሔዋንን እግዚአብሔር ምጥሽንና ፃዕርሽን አበዛዋለሁ ብሎ ፈረደባት"ብሎ ተናገረ ።በምክረ ሰይጣን የተስማማ ሰው ከሰይጣን ጋር ጠላትነት ውስጥ ሊገባም አይችልም።ይህ የእመቤታችንና የሰይጣን ጠላትነት “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ”
(ራእይ 12፥17) ተብሎ ተጽፎለታል።ዘንዶው ማንነው? ካልክ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”(ራእይ 12፥9) በማለት የቀደመው እባብ (ሰይጣን) መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ ይነግርሃል።ሴቲቱስ?“ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።”ራእይ 12፥1
የተባላለት ድንግል ማርያም ናት።በዘፍጥረት በሴቲቱና በእባቡ ጠላትነት እንደሚደረግ እግዚአብሔር ነገረን።ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ጠላትነት በተግባራዊ መልኩ በራእዩ አስረዳን።

2. “ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።”(መዝ 45፥4) ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን ለየ፤አመሰገነ፤አከበረ።
ቅዱስ እግዚአብሔር ማደሪያው የምትሆን ድንግል ማርያምን ከመርገመ አዳም ከመርገመ ሔዋን ጠበቀ ፤ በመጠበቁም አከበረ።

3.“ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።”ሉቃ1፥27
ቅዱስ ገብርኤል የተላከው "ከደናግል ወደ አንዲቱ" አይደለም፤ወደ "አንዲት ድንግል" እንጂ!!!በሥጋ ደናግል የሆኑ ሴቶች ሊኖሩ ይችላሉ።እነዚህ ግን እንደ ማንኛውም የሰው ዘር መርገመ አዳም ወሔዋን ደርሶባቸዋል።እመቤታችን ግን ከዚህ ሁሉ ንጽሕት ናትና "አንዲት ድንግል" አላት።"አንዲት ድንግል" ማለትም "ብቸኛዪቱ ድንግል" ማለት ነው።ይህ ዓይነቱ ድንግልና ነው "የድንግልናሽ ምስጋናና ክብር ታላቅ ነው" ተብሎ የተመሰገነ።

4. “መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።”(ሉቃ 1፥28)
ሰው ሁሉ ኃዘን አግኝቶት "ደስ ይበልሽ" የተባለች፤ሰው ሁሉ ከጸጋ እግዚአብሔር ጎድሎ "ጸጋ የሞላብሽ ሆይ" ተብላ የተመሰገነች፤በበደል በደሉንም ተከትሎ በደረሰብን መርገም ከእግዚአብሔር ተለይተን በነበርን ጊዜ መርገምም ሆነ በደል ካላገኛት ከእመቤታችን ጋር ጌታ እግዚአብሔር ነበር።ከሌሎች ሴቶች መካከል የተባረከች ናት እመቤታችን።መባረክ የመረገም ተቃራኒ መሆኑ ግልጥ ነው።ሌሎች ሴቶች ላይ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።” (ዘፍ 3፥16) የተባለው መርገም ሲደርስባቸው በእመቤታችን ግን ይህ ሁሉ የለባትም።

#በእውኑ #የእመቤታችን ሥጋ የወደቀው የአዳም ሥጋ እንዳልሆነ፤አዳም ሳይበድል የነበረው ሥጋ እንደሆነ ዐወቅን ተረዳን!!!ይህንን የገለጠልን ለእመቤታችን የምሕረት ቃል ኪዳን የሰጠ ቅዱስ እግዚአብሔር ስሙ ይክበር ይመስገን!!!

#የካቲት #ኪዳነ #ምሕረት /2017 ዓ.ም

#ኢዮብ ክንፈ