ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
መድኃኔዓለም

#"ከአዳም ጎን አንዲት አፅም መንሣት ምን ይደንቅ!? ከእርሱ ሴትን ፈጠረ።የሰው ፍጥረትንም ሁሉ ፈጠረ።ጌታ የአብ ቃል ተሰጠ።" (ቅዱስ ኤፍሬም)

#እንደ ክርስቲያን ይህንን ቃል በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ ባነበብን ቁጥር የቀራንዮ በግ መድኃኔዓለም በዕፀ መስቀል ላይ ከፍ ብሎ ተሰቅሎ ስለኛ ሲሞሸር እኛንም ሲሞሽረን እንመለከተዋለን።ጌታችን ይህንን ስቅለቱን "ክብር" በማለት ጠርቶታል።"ጌታችን ኢየሱስም መለሰላቸው እንዲህ ሲል የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል።"(ዮሐ 12:23) እሰቀላለሁ እሞታለሁ ማለቱ ነው።ክብሩማ ለእኛ ነው፤ፍቅር ስለሆነ በሥጋ ማርያም ድንግል ስለተዛመድንም የእኛን ክብር የራሱ ክብር አድርጎ ተናገረ።"የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ" የሚለው አነጋገር የሰው ልጅ የተባለ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲከብር (ሲሰቀል)፤በእርሱ የባሕርይ አምላክነት (መድኃኒትነት) ያመኑ ሁሉ ከብረው በቀኙ እንደሚቆሙ (እንደሚድኑ) ያሳያል።ለዚህ ነው በቀኙ የተሰቀለው ወንበዴ በመድኃኒትነቱ አምኖ የዳነው።

እንዴት በዚህ ቃል የመድኃኔ ዓለምን የሙሽርነቱን በዓል እንመለከታለን? ቢሉ

#"ከአዳም ጎን አንዲት አፅም መንሣት ምን ይደንቅ!?" እውነት ነው ያለ ተረፈ ደዌ፣ያለ ሕማም፣ያለ ቁስል የሆነ ነውና ይደንቃል።ከዚህ በላይ ደዌአችንን ከመቀበል ጋር ፤ ሕማማችንን ከመሸከም ጋር ፤ ቁስላችንን ከመቁሰል ጋር የሆነ "ከዳግማዊ አዳም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን የንጹሕ ውኃና የትኩስ ደም መፍሰስ ምን ይደንቅ!!!?"

#"ከእርሱ ሴትን ፈጠረ" ከቀዳማዊ አዳም ጎን ከተነሣ አፅም ሴትን(ሔዋንን) በጥንተ ተፈጥሮ ፈጠረ።ዳግማዊ አዳም መድኃኒታችን ከጎኑ ባፈሰሰው ውኃና ደምም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በአዲስ ተፈጥሮ ሠራ።ሴትን ራሷ ከሆነው ወንድ እንዳስገኛት፤ቤተክርስቲያንንም ራሷ ከሆነላት ከራሱ አስገኝቷታል። አባታችን አዳም "ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ሥጋዋም ከሥጋዬ ነው ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል" እንዳለ፤ መድኃኔዓለምም "ይህቺ ጥምቀት ከጎኔ ከፈሰሰው ውኃ ፤ ማዕዷም ከእኔ ሥጋና ደም ነው ፤ ከእኔ ከክርስቶስ ተገኝታለችና ቤተክርስቲያን ትባል" ይላል።ሔዋን መባሏ የሕያዋን እናት በመሆኗ ነበር ፤ ቤተክርስቲያንም የሕያዋን (የክርስቲያኖች) እናት ናት።

#"የሰው ፍጥረትንም ሁሉ ፈጠረ" ከአዳምና ከሔዋን "ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት" ባለው አምላካዊ ቡራኬው የሰው ፍጥረትን ሁሉ እንደፈጠረ ፤ "ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም አጥምቋቸው።" በሚለው አምላካዊ ትእዛዙ ክርስቲያኖችን ሁሉ ፈጠረ።

#"ጌታ የአብ ቃል ተሰጠ" የጌቶች ጌታ፣ ቃለ አብ ፣የዓለም መድኃኒት በሥጋ ማርያም ተገልጦ ለሕማም ፣ ለመስቀል ፣ ለሞት ተላልፎ ተሰጠልን።"ሕፃን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል" እንዲል።እንዲህ ባለ መልኩ በዙፋኑ ዕፀ መስቀል ላይ ነግሦ አነገሠን፤ተሞሽሮ ሞሸረን፤ተርቦ አጠገበን፤ተጠምቶ አረካን፤ተራቁቶ አለበሰን፤ቆስሎ ፈወሰን፤ሞቶ ሕይወትን ሰጠን!!!

የመድኃኔዓለም ቸርነቱ አይለየን!!!
የመስቀሉን ፍቅር ያሳድርብን!!!

የካቲት 27/2016 ዓ.ም
ኢዮብ ክንፈ