ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
929 photos
24 videos
271 files
192 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ወንድማማችነት_በመጽሐፍ_ቅዱስ
___________________________

በወንዶች ወገን መናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ልማዱ ሆኖ ነው እንጂ ወንድማማችነት በሚለው እርዕስ ውስጥ እህታማችነት የሚል ሀሳብም እንዳለው ልብ ማለት ይገባል ።
መጽሐፍ ቅዱስ ወንድሞች ሆይ እያለ ሲናገር እህቶች ሆይ ማለቱ ጭምር እንደሆነ በአንጻሩ መረዳት አለብን። ጾታና ከአገልግሎት ድርሻ ውጪህ ያሉ ነገሮች ላይ መጻሕፍ ቅዱስ ጠቅለል አድርጎ ወንድሞች የሚለውን መጠሪያ ይጠቀማል ሴት ከወንድ ጎን ተገኝታለችና ውክልናው ለእርሷም ጭምር ነው ። እንዲያውም #እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ከፈጠራቸው በኃላ ሁለቱንም አዳም ብሎ ይጠራቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል “ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን #አዳም ብሎ ጠራቸው።” #ዘፍጥረት 5፥2 ስለዚህ ወንድማማችነት በመጽሐፍ ቅዱስ ሲባል እህታማችነት በመጽሐፍ ቅዱስ ማለት ጭምር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወንድም ወይም እህት የሚለውን መጠሪያ ለማግኘት የግድ የእናትና የአባት ወይም የአንዱ ብቻ ልጅ መሆን አያስፈልግም። መጽሐፍ ቅዱስ በተለየ ሁኔታ የሚቀራረቡ ሰዎችን ወንድማማቾች ወይም እህታማቶች እያለ ይጠራቸዋል።በቤተሰብ አንድ የሆኑ ሰዎች ወንድማማቾች መባላቸው ግልጽ ስለሆነ እርሱን ለጊዜው እናቆየዋለን።

#ባልንጀራ_ወንድም
_____________
መጽሐፍ ቅዱስ የቅርብ ወዳጅ የሆኑ ጓደኛማቾችን ወንድማማቾች ብሎ ይጠራቸዋል። ቅዱስ ዳዊትና የሳዖል ልጅ ዮናታን እጅግ በጣም ይወደዱ የነበሩ ባልንጀሮች ነበሩ ነገር ግን አንዳቸው ላንዳቸው ወንድሜ እየተባባሉ ነበር የሚጠራሩት። ለምሳሌ ዮናታን በሞተ ግዜ ዳዊት ሞሾ እያወጣ ሲያለቅስለት “ #ወንድሜ_ዮናታን_ሆይ ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ #ከሴት_ፍቅር_ይልቅ_ፍቅርህ_ለእኔ_ግሩም ነበረ።” #2ሳሙ 1፥26 ከዚህም የምንረዳው እጅግ የሚዋደዱ፣ የሚቀራረቡ ፣በደጉም ፣በክፉሁም ጊዜ የማይለያዮ ጓደኛማቾች ወንድማማቾች ተብለው ሊጠሩ እንደሚችሉ ነው።

ጓደኛ ማለት በራሱ ላላ አድርገን ስናነበው ጓ..ደ...ኛ... ጓዳ ከቤት በውስጥ እንደሚገኝ ጓደኛም የቤተ ልቡናችን ጓዳ ዘልቆ ገበናችንን የሚያውቅ የውስጥ ሰው ማለት ነው። ዘመናችን ከፋና አሁን አሁን ጓደኛ ጠፍቶ ጉደኛ በዛ እንጂ ይህ ጓደኛ ከእናት ልጅ ወንድም እኩል አንዳንዴም በልጦ ሊገኝ ይችላል።

#የዘመድ_ልጅ_ወንድም
________________
በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት በቅዱስ ሚካኢል ተራዳኢነን ሙሴ ሕዝቡን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ባሕረ ኤርትራን አሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዝ የኤዶምያስ ንጉሥ በሰላም እንዲያሳልፋቸው መልእክት ሲልክ " #ወንድምህ_እስራኤል እንዲህ ይላል " ሲል መልክቱን ጀምሯል #ዘኁ20÷14 ከግብጽ የወጡት እስራኤላውያን ወይም እነ ሙሴ ለኤዶምና ለኤዶማውያን አንዴት ወንድም ሊሆኑ ይችላሉ? ሊባል ይችላል ምክንያቱም ሙሴና ኤዶምያስ የአንድ እናትና አባት ልጆች አይደሉምና። ነገሩ እንዲህ ነው ኤዶም የኤሳው ሌላኛው ስሙ ነው ኤሳውና ያዕቆብ ደግሞ የአንድ እናት ተከታታይ ልጆች ናቸው ።ያዕቆብ ደግሞ እግዚአብሔር እስራኤል ብሎ የጠራው ዘሮቹም እስራኤላውያን ተብለው በስሙየተጠሩለት ሰው ነው። #ዘፍ 36÷1
ስለሆነም ሙሴ ኤዶምያስ በተባለው በዔሳው እና እስራኤል በተባለው በያዕቆብ መካከል ያለውን ዝምድና አምጥቶ መናገሩ ነው።

#የነገድ_ልጅ_ወንድም
_______________
ንጉሥ ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር መልዕክት ሲልክ "ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲ ብላችሁ ተናገሯቸው የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሷልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለምን ዘገያችሁ እናንተ ወንድሞቼ የአጥንቴ ፍላጭ ና የሥጋዬ ቁራጭ ናችሁ" 2ሳሙ 19÷11 በንግግሩ ንጉሥ ዳዊት የይሁዳ ሽማግሌዎችን ወንድሞቼ ብሎ የጠራቸው እርሱ ከ12ቱ ነገደ እስራኤል የይሁዳ ልጅ ስለሆነና በነገድ አንድ ስለሆኑ ነው እንጂ ከአንድ እናትና አባት ስለተወለዱ አይደለም።

#የሀገር_ልጅ_ወንድም
_______________
የአንድ ሀገር ልጆችን ወይም የሀንድ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ወንድማማቾች ተብለው ይጠራሉ። "ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ #ወንድሞቹ ወጣ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ የግብጽም ሰው #የወንድሞቹን_የዕብራዊያንን_ሰው ሲመታ አየ " #ዘጸ2÷17 ዘዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ የወንድሞቹን የዕብራዊያንን ሰው የሚለው ሐረግ የሀገሩ የዕብራዊያን ሰዎችን ሁሉ ወንድሞቹ እንዳላቸው ያመለክታል።ከዚህ ወንድም ለመባል የአንድ እናትና አባት ልጆች ወይም ከሁለቱ የአንዱ ልጆች መሆን እንደማይጠበቅብን ያሳያል እናስተውል የአንድ ሀገር ልጆችን ነው ያልነው የአንድ ብሔር ልጆችን፣ የአንድ ጎጥ ልጆችን፣የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ልጆችን አልተባለም ሀገር ከተባለ ሁሉን አቀፍ ነው ኦሮሞ፣ ትግሬ ፣አማራ፣ ሶማሌ አይልም ሀገር የነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ናትና።

ተክለ ኤል ኃ/ማርያም
ሰኔ ፲ ፰ /፳ ፻ ፲ ፫ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ