ዐውደ ምሕረት
3.69K subscribers
930 photos
24 videos
271 files
193 links
"ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት"
Download Telegram
#ለሰው ባደረገው በጎነት ላይ ለሕዝቡ ታዛዥ ነውና ከከበሩ መላእክት አንዱ ሚካኤል ነው ሔኖክ 6÷1-2

የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ የቅዱስ ያዕቆብ ወንድም የሆነ ይሁዳ መናፍቃኑ አንቀበልም ብለው የዓመጽ ቃል ካንደበታቸው ከሚወረውሩበት ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ከሆነና አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉ ሞተ ሥጋ ሳያገኘው ከተሠወረ ከነቢዩ ሔኖክ የትንቢት መጽሐፍ ጠቅሶ ሲናገር "ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ በኃጢአተኛነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም በእርሱ ላይ ስለተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳን ጋር መጥቶአል" ይሁዳ 1÷14 ሔኖክ 1÷9 ብሎ

የሔኖክን መጽሐፍ ጠቅሶ ስለጌታችን ፈራጅነት ስለእኩያን ሰዎች የክፋት ሥራና ክርስቶስ ከቅዱሳን ጋር የሚመጣበትን ነገረ ምጽዓትን አንስቶ ይነግረናል፡፡ እኛም የሐዋርያው ልጆች ነንና እርሱን ተከትለን ነቢዩ ስለ ቅዱስ ሚካኤል የተናገረውን ቃል ጠቅሰን ጥቂት ነጥቦችን እናንሳ፡፡ በነቢዩ ሔኖክ መጽሐፍ ቅዱስ ሚካኤል

* ለሰው በጎን የሚያደርግ መልአክ ነው *

ቅዱሳን መላእክት ከተፈጠሩበት ዓላማዎች መካከል አንዱ ለሰው በጎ ነገርን ማድረግ ነው ፡፡ ከእነዚህ በጎ ነገሮች መካከል አንዱ በእግዚአብሔር የታመኑና የሚታመኑ ሰዎችን ከሚቃጣባቸው ክፉ ነገር ሁሉ ማዳንና መታደግ ነው ፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ "የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል ያድናቸውማል" መዝ 33÷7 ብሎ እንደመሠከረ ፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ታቃኝቶ በቃል የመሠከረውን የቅዱሳን መላእከት ሰዎችን ከክፉ ነገር የመታደግ ሥራ የእግዚአብሔር ሰው ቅዱስ ያዕቆብ በተግባር እንደተፈጸመለት ሲመሠክር "ከልጅነቴ ጀምሮ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር ከክፉ ነገርም ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እነዚህ ብላቴኖችን ይባርክ" ዘፍ 42÷12-16 ብሏል፡፡ በዚህ የቅዱስ ያዕቆብ ምስክርነት የጌታችን የኢየሱስ መላእክት ሰዎችን ከክፉ እንደሚያድኑና ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ እንደሚባርኩ እንረዳለን ፡፡ ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምርጥ ዕቃ የዓለም ብርሃን ብሎ የመሠከረለት ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱሳን መላእክት ለሰው የሚያደርጉትን በጎ ሥራ አንስቶ ሲያስተምር "ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መላእክት አይደሉምን?" ዕብ 1÷14 ይላል፡፡ የቅዱሳን መላእክት ታላቅ ትጋትና ማገዝ የሰው ልጅ መዳን የተባለ መንግሥተ ሰማያትን ይወርስ ዘንድ እንደሆነ ከተነገረን ይህን ለመቀበል ሰዎች ለምን ቸገራቸው ? ቅዱስ ሚካኤልም ለሰው በጎ ነገርን በማድረግ የሚታወቅ መልአክ ነው፡፡ ይህ ለሰው የሚያደርገው በጎነትን መጻሕፍት አምልተው ይመሰክራሉ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል "በዚያ ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል" ዳን 12÷1 ይላል ፡፡ ይህ የነቢዩ ቃል አስጨናቂ የተባለው የምጽዓቱ ቀን ዋዜማ እየቀረበ ሲመጣ ፈታኙም ሲበረታ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለምእመናን እንደሚለምን በግልጽ ያሳየናል ፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ለሰው በጎ ነገር ነገር ማድረግ የት አለ ? ቅዱስ ሚካኤል ዲያብሎስ ስለ ሙሴ ሥጋ የማይገባውን እየተናገረ በወሻከተም ጊዜም በእግዚአብሔር ስም ገሥጾታል ይሁዳ 1÷9 ፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ነቢዩ ዳንኤልን ሊረዳው በመጣ ጊዜ የፋርስ መንግሥት አለቃ ዲያብሎስ ሊቋቋመው እንደሞከረና ቅዱስ ሚካኤል እንዴት እንደረዳው ሲገልጽ "ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ" ዳን 10÷13 ብሏል፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ለሰዎችም ለመላእክትም በጎ ነገርን የሚያደርግ የዋህ ፈጣሪው በሰጠው ኃይልም ብርቱ መልአክ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል ራእይ 10÷1፡፡

* ለሕዝቡ ታዛዥ መልአክ ነው *

ቅዱስ ሚካኤል ለሕዝቡ በጎ ነገርን ለማድረግ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝ መልአክ ነው "ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል" መባሉም ይህን ያጠነክርልናል ፡፡ ሊቃነ መላእክት ሠራዊተ መላእክት ለፈጣሪያቸው ይታዘዛሉ የመታዘዛቸውም ዓላማ የእግዚአብሔር ሕዝብን ከክፉ ነገር ሁሉ መታደግ ነው ፡፡ ታዛዥነት ከማገልግል ጋር በእጅጉ ይያያዛል ፡፡ ቅዱሳን መላእክት "ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም" ዕብ 1÷14 መባላቸውም በእውነት ለክርስቲያኖች ደኅንነት የሚታዘዙና ትሑታን መሆናቸውን ያመለክተናል፡፡

* የከበረ መልአክ ነው *

ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሔኖክ ቅዱስ ሚካኤል የከበረ መልአክ መሆኑን መሠከረ ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልን ያከበረ እግዚአብሔር ነው ሮሜ 8÷30-31፡፡ ክብር ጌትነት ከፍተኛነት ዋጋ ጥቅምና መወደድ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ለቅዱሳን የሰጣቸውን ክብር መግለጽ ከቃላት ከሐሳቦችና ከስብከትም በላይ ነው ምሳ 28÷12 1ጢሞ 5÷17 በመሆኑም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በፍጥሞ ደሴት ከሰማይ ሲወርድ ያየውን መልአክ ክብር ሲገልጽ "ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች" ራእይ 10÷1 ራእይ18÷1 ብሏል ፡፡ የቅዱሳን መላእክት ክብር ምድር የተባለ የሰውን ፍጹም ልብ በእውነት እንደሚያበራ ወደ ብርሃን ክርስቶስም እንደሚበራ ያሳየናል ፡፡ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ያከብራሉ ስለሚያከብሩትም እርሱም ያከብራቸዋል "ያከበሩኝን አክብራለሁ የናቁኝም ይናቃሉና" ብሎ እንደተናገረ 1ሳሙ 2÷29-30፡፡ የጌታ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል የጌቶቹ ጌታ ነገሥታቱ ንጉሥ የሆነ እርሱ ፈጣሬ ፍጡራን አምጻኤ ዓለማት ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ክብርን ሰጥቶታልና ከምጽዓቱ አስቀድሞ "አንተ የምትተኛ ንቃ ክርስቶስ ያበራልሃል" የሚለውን የወንጌል መለከት ድምጽ እያሰማ ምጽዓቱን እንዲያበሥር ሹሞታል ማቴ 24÷31 ማቴ 25÷31 ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲመሠክር "ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክት አለቃ (በቅዱስ ሚካኤል) ድምጽ በእግዚአብሔር መለከት ከሰማይ ይወርዳልና" 1ተሰ 4÷16 ይሁዳ 1÷9 ብሏል ፡፡
ይቆየን።

በመምህር #ቢትወደድ ወርቁ

👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit
👉 @AwediMeherit