#ንቀን_ያለፍነው_ቃል
ከለታት አንድ ቀን፣ ወደ ቤቷ ሄድኩኝ
ጥቅል ጎመን አርዳ፣ እንጉዳዩን ጠብሳ
ጋበዘችኝ ምሳ
ሙያዋን አደነቅሁ
ገበታው ሲነሳ
ካያቷ ተዋወቅሁ።
አረጋዊት ናቸው፣ እድሜያቸው የገፋ
ድሮ ልጅ እያሉ፣ አይናቸው የጠፋ
በድሜያቸው በረካ፣ በፅዋቸው ጭላጭ
አምሯቸው ብሩህ፣ ልሳናቸው ምላጭ
ወግ ማውጋት ጀመሩ
ቃል እያለዘቡ
ቃል እየጠረቡ፣ ቃል እያሳመሩ
ሀረግ አለዝበው፣ ዘይቤ እየነቀሱ
በጸጥታ ሞቶ፣ ያላጀብ ተቀብሮ
የተረሳ ታሪክ እየቀሰቀሱ
እንደ መቅረፀ ድምፅ፣ ጆሮየን ጠመድሁት
አጥብቆ ገረመኝ
ያረጋዊቷ ወግ፣ ቅድም ከበላሁት
ከንጉዳዩ ዝልዝል፣ የበለጠ ጣመኝ።
ጸሐፌ ትዛዛት ቸል ብለው ያለፉት
ዜና ነጋሪዎች፣ አይተው የገደፉት
ያገሬን ሰው ገድል፣ መከራ ፍስሐ
ሳልታክት ቀዳሁት፣ ልክ እንዳርብ ውሃ።
ከጥሞናየ ላይ ላፍታ ተፋትቼ
ጋባዤን ፈለግኋት
ፊትለፊቴ አየኋት
ያቻት ያቻትና
ከሶፋው ላይ ሆና
እግሮቿን ዝርግትግት፣ ሰውነቷን ዘና
እንደፊት መስተዋት
ዘመናይ ሞባይሏን፣ ፊቷ ስር ደቅና
ከስልኳ ሰሌዳ፣ ፊደል ትነካለች
ፎቶ ታምሳለች፣ ኢሜል ትልካለች
ያያቷ ጣፋጭ ወግ፣ ላፍታ እንኳ መች ደንቋት
ሜሴንጀር ዋትሳፕ፣ ኢሞ ቴሌግራም
ሁሉን የወሬ ቋት
ትበረብራለች፣
ካሥር አመት በፊት
ለረፍት ከከተማ፣ ወደ ገጠር ሄጄ
ደጅ ላይ ማለዳ፣ ፀሐይ ስር ተጥጄ
አያቴ ብቅ ብሎ
ከተቀመጥሁበት የወይራ ግንድ ላይ፣ ራሱን አዳብሎ
“ያኔ ጎበዝ ሳለሁ” ብሎ ወግ ሲወጥን
አልባሌ ወሬ፣ እኔን የማይመጥን
የሰማሁ ይመስል፣ በኀይል አዛግቼ
ከካፖርቴ ኪስ ውስጥ፣ መጽሐፍ አውጥቼ
(የማርክስ፣ የፍሮይድ ምናልባት የኒቼ?)
ገለብ ገለጥ ሳደርግ፣ እሱ ይህን አይቶ
የጀመረውን ቃል፣ አንጠልጥሎ ትቶ
ለጥናት ነው መሰል፣ እዚህ መቀመጥህ፣
ወግድልኝ በለኝ፣ እንዳልበጠብጥህ”
ብሎ ይወገዳል
አድማጭ ካጣጭ ጋራ ወደሚገኝበት፣ ጠላ ቤት ይሄዳል።
አያቴ ከሞተ፣ አመታት አለፉ
ፀፀት ጭንቅላቴን፣ በብረት መዳፉ
እየኮረኮመኝ
ሀፍረት በሸኮናው፣ እየረመረመኝ
በራሴ ስበግን
ምን ሆኘ ነበር ግን
ምን ነክቶኝ ነበር ግን?
በማለት አጥብቄ ራሴን ስረግም
ይሄውና ዛሬ
ጋባዤን አየኋት፣ ታሪኬን ስትደግም።
አንድም በመሰልቸት፣ አንድም በቸልታ
ወይ ባወቅሁሽ ናቅሁሽ፣ አለያም በወረት
የያዝነውን ዳቦ፣ ቆጥረነው ከኮረት
ጠላ ከሚጠጣ፣ ቆሎ ከሚበላ
እድፍ ከሚለብሰው
ለዐይን ከማይሞላ
ካንድ ስም አልባ ሰው
ምን ጥበብ ይገኛል? በሚል ተዘናግተን
በቻይና ቅፅር ጡብ፣ ጆሯችንን ዘግተን
ልቦና ቆልፈን
ንቀን ያለፍነው ቃል፣ ንቆ ነው ያለፈን።
#ክብር_ለአያቶቻችን_ለተንቀሳቃሽ #ላይብሬራችን
ከለታት አንድ ቀን፣ ወደ ቤቷ ሄድኩኝ
ጥቅል ጎመን አርዳ፣ እንጉዳዩን ጠብሳ
ጋበዘችኝ ምሳ
ሙያዋን አደነቅሁ
ገበታው ሲነሳ
ካያቷ ተዋወቅሁ።
አረጋዊት ናቸው፣ እድሜያቸው የገፋ
ድሮ ልጅ እያሉ፣ አይናቸው የጠፋ
በድሜያቸው በረካ፣ በፅዋቸው ጭላጭ
አምሯቸው ብሩህ፣ ልሳናቸው ምላጭ
ወግ ማውጋት ጀመሩ
ቃል እያለዘቡ
ቃል እየጠረቡ፣ ቃል እያሳመሩ
ሀረግ አለዝበው፣ ዘይቤ እየነቀሱ
በጸጥታ ሞቶ፣ ያላጀብ ተቀብሮ
የተረሳ ታሪክ እየቀሰቀሱ
እንደ መቅረፀ ድምፅ፣ ጆሮየን ጠመድሁት
አጥብቆ ገረመኝ
ያረጋዊቷ ወግ፣ ቅድም ከበላሁት
ከንጉዳዩ ዝልዝል፣ የበለጠ ጣመኝ።
ጸሐፌ ትዛዛት ቸል ብለው ያለፉት
ዜና ነጋሪዎች፣ አይተው የገደፉት
ያገሬን ሰው ገድል፣ መከራ ፍስሐ
ሳልታክት ቀዳሁት፣ ልክ እንዳርብ ውሃ።
ከጥሞናየ ላይ ላፍታ ተፋትቼ
ጋባዤን ፈለግኋት
ፊትለፊቴ አየኋት
ያቻት ያቻትና
ከሶፋው ላይ ሆና
እግሮቿን ዝርግትግት፣ ሰውነቷን ዘና
እንደፊት መስተዋት
ዘመናይ ሞባይሏን፣ ፊቷ ስር ደቅና
ከስልኳ ሰሌዳ፣ ፊደል ትነካለች
ፎቶ ታምሳለች፣ ኢሜል ትልካለች
ያያቷ ጣፋጭ ወግ፣ ላፍታ እንኳ መች ደንቋት
ሜሴንጀር ዋትሳፕ፣ ኢሞ ቴሌግራም
ሁሉን የወሬ ቋት
ትበረብራለች፣
ካሥር አመት በፊት
ለረፍት ከከተማ፣ ወደ ገጠር ሄጄ
ደጅ ላይ ማለዳ፣ ፀሐይ ስር ተጥጄ
አያቴ ብቅ ብሎ
ከተቀመጥሁበት የወይራ ግንድ ላይ፣ ራሱን አዳብሎ
“ያኔ ጎበዝ ሳለሁ” ብሎ ወግ ሲወጥን
አልባሌ ወሬ፣ እኔን የማይመጥን
የሰማሁ ይመስል፣ በኀይል አዛግቼ
ከካፖርቴ ኪስ ውስጥ፣ መጽሐፍ አውጥቼ
(የማርክስ፣ የፍሮይድ ምናልባት የኒቼ?)
ገለብ ገለጥ ሳደርግ፣ እሱ ይህን አይቶ
የጀመረውን ቃል፣ አንጠልጥሎ ትቶ
ለጥናት ነው መሰል፣ እዚህ መቀመጥህ፣
ወግድልኝ በለኝ፣ እንዳልበጠብጥህ”
ብሎ ይወገዳል
አድማጭ ካጣጭ ጋራ ወደሚገኝበት፣ ጠላ ቤት ይሄዳል።
አያቴ ከሞተ፣ አመታት አለፉ
ፀፀት ጭንቅላቴን፣ በብረት መዳፉ
እየኮረኮመኝ
ሀፍረት በሸኮናው፣ እየረመረመኝ
በራሴ ስበግን
ምን ሆኘ ነበር ግን
ምን ነክቶኝ ነበር ግን?
በማለት አጥብቄ ራሴን ስረግም
ይሄውና ዛሬ
ጋባዤን አየኋት፣ ታሪኬን ስትደግም።
አንድም በመሰልቸት፣ አንድም በቸልታ
ወይ ባወቅሁሽ ናቅሁሽ፣ አለያም በወረት
የያዝነውን ዳቦ፣ ቆጥረነው ከኮረት
ጠላ ከሚጠጣ፣ ቆሎ ከሚበላ
እድፍ ከሚለብሰው
ለዐይን ከማይሞላ
ካንድ ስም አልባ ሰው
ምን ጥበብ ይገኛል? በሚል ተዘናግተን
በቻይና ቅፅር ጡብ፣ ጆሯችንን ዘግተን
ልቦና ቆልፈን
ንቀን ያለፍነው ቃል፣ ንቆ ነው ያለፈን።
#ክብር_ለአያቶቻችን_ለተንቀሳቃሽ #ላይብሬራችን