አትሮኖስ
286K subscribers
120 photos
3 videos
41 files
568 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ከዘፈኖች_ጀርባ_የሚዘፈን_ዘፈን
:
ዘፈን ከሙሾ አነሰ፣
ትርጉሙ ተዛባ፣ ረከሰ ውሉ
ነጠላ ዜማና፣ ነጠላ ጫማ ነው፣ መንገዱ በሙሉ

ልክ እንደቶምቦላ ፣ልክ እንደሎተሪ
በዘፈን ውስጥ ያልፋል፣ እንጀራ ሞካሪ

ተሰጥኦ አፈር በላ
ገደል ገባ መክሊት፣ ኳኳታ ገነነ
ድምፅ ሞራጅ በዛ
ድምፅ ያወጣ ሁሉ ፣ዘፋኝ እየሆነ

ታዲያ ይህን ስናይ ፣ቧልታችን ገዘፈ
የሳቃችን ምንጩ፣ ከንዴት ባሕራችን፣ እየተጨለፈ

ቧልት አንድ
እኔ ደሃ ማለት ፣የፈራ አቀንቃኝ
የኖረውን እውነት
ከፍቅሩ አጣብቆ
የኔ ደሃ ይላል
እንዳይፈናፈን፣ በማጣቱ ታንቆ
ግርም ነው ሚለው
በጋራ ባዶነት ፣አብራ ካልማቀቀች
ፍቅርን ያሕል ነገር
ወደኋላ ገፍታ ፣እንዴት ተሰደደች?
የኔ ደሃ ይላል ፣የድሆች የበላይ
ኖሮት እንደሸኘ ፣ነፍሱን አስሯት ስቃይ!!
:
ቧልት ሁለት

በማጣቴ ምክንያት ፣ፍቅሬ ጥላኝ ሔደች
ገንዘብ አሸነፋት ፣ለንዋይ ተረታች
ብሎ እየጮኸ
ችግር በሚሰብኩ፣ ሽንፈታም ስንኞች፣
ማዘን ሲጀምረን
በምስል ቀረፃው
አዲስ ንድፍ መኪና ፣'ሚያስገርም ቪላ ቤት
እንዳለው ሲያሳየን
የእሱ አይነት ድህነት ፣ቢሰጠን ተመኘን!!
:
ቧልት ሦስት

መናኛ ሰባኪ
ነጋችንን ሊነጥቅ፣ ከዛሬ አጣብቆ
በርካሽ ሊገዛን
የእድሜ እረፍታችንን፣ በጫጫታ ጠምቆ
ዛሬ ትኖር፣ ነገ አታውቀው
ለምንድን ነው ፣ምትጨነቀው

አትጨናነቅ
አትጨናነቅ
አትጨናነቅ

ባለህ ተደሰት

የምናባቱ ቁጠባ ፣የምናባቱ ማስቀመጥ
እጅህን ወደላይ ፣ይጨፈር ይቀወጥ

ብሎ እየዘፈነ
እኛ ስንራገፍ ፣ስንቱ ሃብታም ሆነ!!
:
ቧልት አራት

ወገን ተሰብሰብ፣ ተሰብሰብ
ባገሬ ምድር ላይ ፣እንዲሆን ዓለም

ወዳ'ገርህ ግባ፣ ተሰብሰብ ባላገር

ኑ…… ኑ

አላስቀምጥ ብላው፣ ስደተኛ ነብሱ
ወዴት ነው 'ሚጠራን? የት ነው እሱ እራሱ?

የዚህ አይነት ዘፈኖች
እንሰማ እንሰማና ፣ዘፋኞቹን እዚህ ፣ፈልገን ብናጣ
ሌላ ኢትዮጵያ አለች
በሚል ይመስለኛል
በባህር በድንበር፣ ካ'ገር የምንወጣ!!
:
ቧልት አምስት

የመኳኳል ብዛት
አብዝቶ ፈሶባት
በዚህች ባንዲት ዘፈን
ብዙ የልብስ አይነት፣ እየቀያየረች
ከዘፈኗ በላይ፣ በልብሷ እየጮኸች
አንዴ መኝታ ቤት
አንዴ ደረጃ ላይ
ሳሎን ውስጥ
ጊቢ ውስጥ
እ~ያ~ው~ረ~ገ~ረ~ጋ~ት
ጊዜ ስንቷን ዘፋኝ
የልብስ አከራዮች፣ ደንበኛ አደረጋት
እምፅፅፅፅ
እሷን ከነልብሱ
አንድጊዜ ጠቅልሎ
ማነው ሚያሳርፈን? ማን ይሆን ሚገዛት?

ቧልት ስድስት

ብርሃን ፈሪ ፍቅር ፣ከቀን የተፋታ
ከፀሐይ ያሸሹት ፣የሰፉት ከማታ

ነይልኝ ማታ ማታ

ማታ ማታ

ይሄም መጥቶ ማታ
ያቺም መጥታ ማታ
ኳኳታ
ቱማታ

በመልክ የሚያፍር ነው፣ ወይደግሞ አተራማሽ
ውዱንና ፍቅሩን፣ የሚያስሰው ሲመሽ

ማቀፍስ በቀን ነው~ ማቀፍ ባደባባይ
ፀሐይ አይደብቅም
አበባ አያረግፍም
ያፈቀረ ሰማይ!!
:
ቧልት ሰባት

እንቺ እንካ
እንካ
ባደባባዩ
እንካ

ማታ ማታ ያምረኛል

ነይ እንመቻች

እሰይ ሰለጠንን ፣ነውር ገሃድ ወጣች

ዋናው መዝፈን ነው ጎበዝ
ያው ብልግናም ቢሆን ፣ትንሽ እናጣመው
ጫጫታ ሲነግስ
በሁሉም ጆሮ ላይ፣ እሱ ነው ሚጥመው

ፈሪሃ ሰው እግዜር፣ ከምድራችን ይብቀል
ስክነት ደህና ሰንብች፣ በደቦ እንቀልቀል
ታዛቢ አጥተን እንጂ
ጭራ ነው ሚቀረን~ ጭራ ለማስበቀል!!
:
:
:
ኧረ ብዙ ብዙ~ ብዙ የሳቅ ቋንቋ
እንፈበርካለን፣ እድሜ ለሙዚቃ

መረጋጋትን ሸኘናት
እሰየው መስከን ራቀ
በየጥጋጥጉ
የኳኳታ ሕጋችን፣ ባርምሞ ፀደቀ

ማዳመጥ ተረሳ፣ መስማት ለመለመ
አይምሮም ኳኳታን፣ እየተረጎመ


እንቺ እንካ

ከሽ
ማታ ነይ እባክሽ

ድዝ
ደሞ የምን መፍዘዝ

ድም
ዛሬ አንላቀቅም


ጆሯችን ተሰዋ
እድሜ ያለትርጉም፣ ለሚጮህ ሙዚቃ

እግዚሃር ይመስገን
ይህን ሁሉ ጯሂ
በአጭር ዓመታት፣ እንደቀልድ አፍርተን
ከቁም ነገር በላይ፣ ቧልት ነው የተረፈን

እግዚሃር ይመስገን
ብርዝ ዘፈንና ፣በራዥ ሙዚቀኛ
የለት ሳቃችንን ፣ጋብዞን ነው ምንተኛ!!!!!
:
🔘በፍቃዱ ጌታቸው🔘
👍1