አትሮኖስ
286K subscribers
121 photos
3 videos
41 files
573 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ሁቱትሲ


#ምዕራፍ_አስራ_ስድስት


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ


#የጌታዬ_ሥራ

ሰዎች በመንገድ ላይ ለመዘዋወር እንኳን በሚፈሩበት ከተማ ሥራ የት እንደማገኝ የሚያውቀው አምላክ ነው፡፡ ውድቅዳቂ ፈንጂዎች የኪጋሊን መንገዶች ሞልተዋቸዋል፤ ለመሥራት ከፈለግሁ ግን በነዚህ ጎዳናዎች ሥራን እያነፈነፍኩ መኳተን ይኖርብኛል፡፡ የሕዝብ ማጓጓዣ ተሸከርካሪዎች መንቀሳቀሳቸውን ትተዋል፤ ለአነስተኞቹም ማጓጓዣዎች የምከፍለው ምንም ገንዘብ አልነበረኝም፡፡
ፋሪን በቤቱ አቅራቢያ ያሉ ክፍት የሥራ ቦታ ያላቸውን ድርጅቶችን ያውቅ እንደሆነ ጠየቅሁት፡፡ ‹‹አሁን ማንም እየቀጠረ ስላልሆነ አማራጮችሽ በጣም ውሱን ናቸው›› ሲል መለሰልኝ፡፡ ‹‹ያለው ብቸኛ አማራጭ የተመድ ነው … እዚያ ለመግባት ግን እንግሊዝኛ መናገር ያስፈልጋል፡፡››
በአእምሮዬ የሆነ ነገር ብልጭ አለልኝ፡፡ በእርግጥ! እግዚአብሔር በመታጠቢያ ክፍሉ እንግሊዝኛ እንዳጠና ያደረገኝ ዋነኛው ምክንያት እኮ የተመድ ነው፡፡ በተመድ የመሥራት ሕልምም ነበረኝ፡፡
በዚያን ምሽት ልብሶቼን በሚገባ አጥቤ አምላክ በተመድ ሥራ እንዳገኝ ያግዘኝ ዘንድ ጸለይኩ፡፡ በመጨረሻ እንግሊዝኛዬን በሥራ ላይ የማውልበት መሆኑን አስቤ በጣም ተደስቼ አብዛኛውን የሌሊቱን ጊዜ መስታወት ሳይና ራሴን በራሴ ያስተማርኳቸውን ሐረጋት ስለማመድ ቆየሁ፡፡
‹‹እንደምን አደራችሁ››
‹‹እንዴት ነዎት?››
‹‹ሥራ ፈልጌ ነው፡፡›› ስሜ ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ ነው፡፡››
‹‹ሩዋንዳዊት ነኝ፡፡››
‹‹ቡታሬ ባለው ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ አጥንቻለሁ፡፡››
‹‹ሥራ ፈልጌ ነው፡፡››
አቤት! እንዴት ደስ ይላል! ትክክለኛ የእንግሊዝኛ አረፍተ ነገሮችን መናገር ጀምሬያለሁ፤ ነገ በአዲስ ቋንቋ እነጋገራለሁ … ከዚያም አዲሱን ሥራዬን እሠራለሁ! ተመስገን አምላኬ!
ልክ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ በተመድ ሕንጻ በር ፊት ለፊት ሄጄ ቆሜያለሁ፡፡ ጋናዊ ዘበኛ እንግሊዝኛ በሚመስል ቋንቋ ሞቅ አድርጎ ሰላምታ ሰጠኝ፡፡ ‹‹እንደምን አደርሽ፣ ምን ልርዳሽ?›› ያለኝ ይመስለኛል፡፡ እኔ የሰማሁት ግን ‹‹ታታታ ታታታ ታታታታ?›› ዓይነት ነገር ነው፡፡ ምንም እንዳለ አንዳች ፍንጭ ባላገኝም የገባኝ አስመሰልኩ፡፡ ራሴን ከፍ፣ አገጬን ወጣ አድርጌ ‹‹እንዴት ነዎት? ስሜ ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ ነው፡፡ ሥራ ፈልጌ ነው›› አልኩ በእንግሊዝኛ፡፡
ውይ፡፡ የዓይኖቹ አኳኋን አነጋገሬ እንዴት አስቂኝ እንደሆነበት ነገረኝ፡፡ ቢሆንም ግን እንደገና ሞከርኩ፡፡ ይህን ሁሉ ርቀት የመጣሁት ተመለሽ ለመባል አልነበረም፡፡ ‹‹እንዴት ነዎት? ስሜ ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ ነው፡፡ ሥራ ፈልጌ ነው››
‹‹አሃ! ሩዋንዳዊት ነሽ… የምትችይው ፈረንሳይኛ መሆን አለበት›› አለኝ፡፡ ፈገግ ብዬ በአዎንታ ራሴን ነቀነቅሁ፡፡ ዋናውን በር ከፍቶልኝ ሌላ ዘበኛ ወደ አንዲት ትንሽ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ወሰደኝ፤ ብዙ ቅጻቅጾችን ሞልቼ እንድጠብቅ ተነገረኝ፡፡ ጠበቅሁም … ጠበቅሁ… ጠበቅሁ … ጠበቅሁ፡፡ የተመድ ሠራተኞች ማታ ከሥራ ሲወጡ እንግዳ ተቀባይዋን ሥራውን እስካገኝ ምን ያክል መጠበቅ እንዳለብኝ ጠየኳት፡፡
‹‹ረጅም ጊዜ ትጠብቂያለሽ ውዴ … ሥራ የለም፡፡››
ወደ ቤቴ ተበሳጭቼ ግን ተስፋ ሳልቆርጥ ሄድኩ፡፡ በተመድ መሥራት ዕጣ ፈንታዬ - የማልመውና ቆርጬ የተነሣሁበት ጉዳይ ነው፡፡ ፈጣሪ እዚያ እንድሠራ ከፈቀደ ከግቤ ከመድረስ ምንም አያስቆመኝም፡፡
በቀጣዩም ቀን ተመለስኩ፣ እነዚያኑ ቅጾች ሞላሁና ከሰዓቱን ጠበቅሁ፡፡ በቀጣዩም ቀን ይህንኑ አደረግሁ፤ በቀጣዩም፤ በቀጣዩም፡፡ ቅጾችን ስሞላና ስጠብቅ ከሁለት ሳምንታት በላይ ፈጀሁ፡፡ በየቀኑ ወደ ቤቴ ስሄድ እንግዳ ተቀባይዋ ‹‹እኔ አንቺን ብሆን ተመልሼ አልመጣም ነበር ውዴ፡፡ ምንም ሥራ እኮ የለም›› ትለኛለች፡፡ በሁለተኛው ሳምንት መጨረሻ ተስፋዬ እየተሟጠጠ መጣ፡፡ ሥራ ሳላገኝ ወደ አሎይዜ ቤት መሄድ አስፈራኝ፡፡ ስለሆነም ለራሴ አዝኜ በቤታችን ሰፈር በፈራረሱ መንገዶች እዞር ገባሁ፡፡ በራሴ ዐቅም ላይ ለማተኮር ከአምላክ ጋር ጸጥታ የተሞላበት ተግባቦት እያደረግሁ ለመቀመጥ ፈለግሁ፤ ለዚያ ተመስጦ ግን የአሎይዜ ቤት በጣም ረብሻ የሚበዛበት ነው፡፡ እርስዎ አመኑኝም አላመኙኝ ከአምላኬ ጋር ለሰዓታት ያለማቋረጥ የማወራበትን በቄሱ መታጠቢያ ክፍል ያሳለፍኩትን ወቅት ናፈቅሁ፡፡ በነዚያ ረጃጅም ጸጥ ያሉ ጸሎቶቼ ወቅት ልቤን የሞላበትን ደስታና ሰላም አስታወስኩ
- ከዚያ በኋላ አገኝ የነበረውን የአእምሮ ንጽሕናም ጭምር፡፡
ከአሎይዜ ቤት ሁለት ግቢ አልፎ ወደተቃጠለ ቤት ፍርሥራሽ ሄድኩ፡፡ በጉልበቶቼ በተቃጠለው ፍርሥራሽና በተሰባበረው መስታወት ላይ ተንበርክኬ ጸሎቶቼን ጀመርኩ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሆይ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሊቱን ሙሉ ዐሳ ለማጥመድ ቢሞክርም ምንም ሳይዝ ቀርቶ ተስፋው ቢሟጠጥ፤ አንተ ግን በዚያው ቦታ ላይ ሄዶ እንዲያጠምድ ነገርከው - እናም ብዙ ዐሳ አጠመደ! በጣም ደስተኛም ሆነ! እኔንም ታዲያ ወደ ተመድ ስለመራኸኝ እስካሁን ይህን ሁሉ ቀን ሥራ ‹እንዳጠመድኩ› አለሁ፡፡ ግን ምንም ዓሶች እዚህ የሉም፡፡ እግዚአብሔር፣ ምን እንደማደርግ አላውቅም፡፡ ገንዘብ የለኝም፤ ልብሶቼ እየተበጣጠሱ ነው፤ ሥራም አያስገኙኝም፡፡ ስለዚህ እገዛህን እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህን የተመድ ሰዎች እንዲያዩኝና ጥሩ የጽሕፈት ቤት ሥራ እንዲሰጡኝ አድርግ፤ አንተ እንደምፈልገው ታውቃለህ፡፡ አግዘኝ፤ እኔም በበኩሌ ራሴን አግዛለሁ! ይሁን ይደረግልኝ፡፡››

ራሴን አጸዳድቼና የፈራረሰውን ቤት ትቼ በታደሰ የራስ መተማመን ሄድኩ፡፡ እግዚአብሔርን እገዛውን ጠየቅሁት፤ የምፈልገው አሁን እንዲከሰት ማድረጉ የራሴ ድርሻ እንደሆነ ታውቆኛል፡፡ በተመድ መሥራት የምፈልገውን በአእምሮዬ መቅረጽ ጀመርኩ - ማስታወሻ መያዝ፣ ስልክ መመለስና ጠቃሚ ውሳኔዎች ሲደረጉ ማገዝ፡፡ ወደ ቤት ስሄድ የተመዱን ሥራዬን አንዴ ካገኘሁ በኋላ ስለሚያስፈልጉኝ ነገሮች ሳስብ ቆየሁ፡፡ የተወሰኑ ለሰው ፊት የሚቀርቡ ልብሶች ሊኖሩኝ ይገባል፤ እናም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀኩበት ምስክር ወረቀትና ዩኒቨርሲቲ ለሦስት ዓመታት መከታተሌን የሚያረጋግጥ መረጃ ያስፈልጉኛል፡፡ ያለመታደል ሆኖ ሁሉም ንብረቶቼ አራት ሰዓት በተሽከርካሪ በሚያስነዳው ቡታሬ በሚገኘው በትምህርት ቤት የመኝታ ክፍሌ ናቸው፤ እንደሚታወቀው ወደዚያ ለመሄድ ደግሞ የምከፍለው ገንዘብ የለኝም፡፡
በሐሳብ በጣም ተውጬ አንድ ተሸከርካሪ በአጠገቤ አልፎ ነጂው ስሜን ሲጣራ ልብ አላልኩትም ማለት እችላለሁ - በዩኒቨርሲቲዬ መምህር የሆነው ዶክተር አቤል፡፡ ‹‹መች አወቅሁሽ ኢማኪዩሌ›› አለኝ፡፡ በጣም ከስተሻል! በመትረፍሽ በጣም ተደስቻለሁ … እንዲያው ምግብስ እየበላሽ ነው? የምትኖሪበትስ ቦታ አለሽ?›› ዶክተር አቤል የህክምና ዶክተር በመሆኑ ስላለፍኩበት ሁኔታና ስለጤናዬ ጉዳይ ጠየቀኝ፡፡ ለማገገም እንዲያግዘኝ ከእርሱ፣ ከሚስቱና ከቤተሰቡ ጋር ቡታሬ እንድኖር ቢጋብዘኝም አመስግኜው የምቆይባቸው ቤተሰብ እንዳሉኝ ነገርኩት፡፡ በቅርቡ ግን ቡታሬ የሚሄድ ከሆነ እንዲወስደኝ ነገርኩት፡፡
‹‹ምን ችግር አለ? በእርግጥ ነገ ሂያጅ ነኝ፡፡››
እንደገና የዕድል ገጠመኝ ነው ብዬ ባሰብኩት በዚህ ጉዳይ የአምላክን
👍4
እጅ አየሁት፡፡ በቀጣዩ ቀን ዶክተር አቤል በዱሮ ዩኒቨርሲቲዬ የፊት በር ጋ ጣለኝ፡፡ ትምህርት ቤቱ ተዘርፎ፣ ወታደሮች በበሩ ስር ተቀምጠው አገኘሁት፡፡ ጠባቂዎቹ ወደ መኝታ ክፍሌ አናስኬድም አሉኝ፡፡ ‹‹ትምህርት ቤቱ ከነጭራሹ ተዘግቷል›› በማለት፡፡ ይባስ ብለው ወደ ኪጋሊ እንድመለስ ነገሩኝ፡፡
እግዚአብሔር እንዴት ወደ ግቢው እንደሚያስገባኝ እስኪያሳየኝ እየጠበቅሁ በመንገዱ ዳር ተቀምጬ በአባቴ መቁጠሪያ ጸለይኩ፡፡ በአሥር ደቂቃ ውስጥ የወታደሮቹን አለቃ ኮሎኔል የጫነች ተሽከርካሪ ዋናው በር ጋ ቆመች፡፡ ለኮሎኔሉ ወታደሮቹ ሰላምታ ለማቅረብ ሲራኮቱ እኔም ሄጄ ተዋወቅሁ፡፡
‹‹እዚህ ምን እያደረግሽ ነው ሚጡ?›› ሲሉ መለሱልኝ፡፡ ‹‹ወላጆችሽ የት ናቸው? እዚህ ብቻሽን መሆንሽ አደገኛ እኮ ነው፡፡››
ሃያ አራት ዓመቴ ቢሆንም በጣም ከመክሳቴ የተነሣ የ12 ዓመት ልጅ መስያለሁ፡፡
‹‹ጌታዬ ወላጆቼማ ሞተዋል፡፡ ከተቀረው ቤተሰቤ ጋር በዘር ጭፍጨፋው ነው የተገደሉት፡፡ በዓለም የቀረኝ ነገር መኝታ ክፍሌ ብቻ ነው፤ ወታደሮችዎ ወደ ትምህርት ቤቱ አናስገባም አሉኝ እንጂ፡፡ ሊያግዙኝ ይችላሉ?›› ስል በተቻለኝ መጠን ተሸቆጥቁጬ ጠየቅኋቸው፡፡
ኮሎኔሉ በሩን ከፍተውልኝ ከአንደኛው ወታደር ጋር ገባሁ፡፡ በበሩም ገብተን ወደ መኝታ ቤቴ አሳዛኙንና አጭሩን ጉዞ አደረግን፡፡
ብዙ አስደናቂ ትዝታዎቹ ያሉብኝና ግሩም ጓደኞችን ያፈራሁበት ውቡ ትምህርት ቤቴ እንዳልነበር ሆኗል፡፡ በየቦታው የቆሻሻ ክምር ይታያል፤ ብዙዎቹ ሕንጻዎችም ጋይተዋል፤ ፈራርሰውማል፡፡ የተማሪዎችን የትምህርት ማስረጃ በግቢው ሙሉ ደርቆ እንደረገፈ ቅጠል ነፋስ ያንገላታቸዋል፤ ከእነዚህ ሁሉ ሳምንታት በኋላም እንኳን አሁንም መሬት ላይ እጅግ ብዙ አስከሬኖች ይታያሉ፡፡ የሳራንና የሌሎቹን የሴት ባልንጀሮቼን አስከሬን እንዳላይ ፈርቼ ደፍሬ ማየት አልቻልኩም፡፡ ከተዝናናሁባቸው የትምህርት ቤት ጭፈራዎች አንዱን፣ የተሳተፍኩባቸውን ተውኔቶችና ከዮሐንስ ጋር ያደረኳቸውን የፍቅር ሽርሽሮች ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ ግን ሁሉም አስቀድሜ ባየሁት የወዳጆቼና የንብረቶቻቸው በየቦታው መውደቅ ሰበብ ጠፉ፡፡ ኮሎኔሉ መኝታ ቤቴ ጋ አውርደውኝ ተሟጦ ወደተዘረፈው መኝታ ክፍሌ ስሄድ ወታደራቸው ተከተለኝ፡፡ በሩ በመጥረቢያ ተገንጥሎ እያንዳንዷ የነበረችኝ ነገር ተወስዳለች - ቦርሳዎቼን፣ ልብሶቼን፣ ጫማዎቼንና ፍራሼን ሳይቀር ዘርፈዋቸዋል፡፡ ይመስገነው፤ የተወሰኑ የወላጆቼ ምስሎች - የአብሮነት ሕይወታችን ብቸኞቹ ማስታወሻዎቼ - በግንቡ ላይ እንደተሰቀሉ አሉ፡፡ ከወለሉ ላይ የተወሰኑ የተበታተኑ የደብዳቤ ኪስ ወረቀቶችን ብለቃቅምም ወታደሩ ከእጄ እየመነጨቀ ያነባቸው ያዘ፡፡
ከትከሻው ጠመንጃውን አውርዶ በማስፈራራት፣ ‹‹ኤይማብል ማነው?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡
መሣቅ ስጀምር አስገረምኩት፡፡ ከዘር ጭፍጨፋው መትረፌ አስቆኛል፣ ግን ባዶ የመኝታ ክፍሌን በመዝረፍ ሰበብ በቱትሲ ወታደር በጥይት ተመትቼ ሊያበቃልኝም ይችላል፡፡
‹‹ኤይማብል ወንድሜ ነው፡፡ ያ ደብዳቤ እርሱ ከሚኖርበት ከሴኔጋል የተላከ ነው›› አልኩት፡፡ አያጉረመረመ ደብዳቤዎቼን ሊያነብ ወደ አዳራሹ ገባ፡፡ መሬት ላይ ያሉትን ሌሎች የተወሰኑ ወረቀቶች ሳስተካክል ያየሁትን አላመንኩም፡፡ እዚያ በአንድ ትልቅ ኪስ ወረቀት የሁለተኛ ደረጃ ምስክር ወረቀቴ፣ የዩኒቨርሲቲ ውጤቴና ትምህርት ቤቱ በትምህርት እድሉ ሰበብ ሰጥቶኝ የደበቅሁት ወደ 30 የሚጠጋ ዶላር አለ፡፡ በድንገት ሃብታም ሆንኩ … ከዚያም በኋላ ይህን የተገኘውን ማስረጃ ተጠቅሜ የተማርኩ መሆኔን ማስረዳት እችላለሁ ማለት ነው!
ከትምህርት ቤቱ ግቢ ወዲያውኑ ወጥቼ ከአሜሪካ ዶላሮቼ አንዱን ወደ ኪጋሊ ለመመለስ ተጠቀምኩበት፤ አንድ ሌላ ጸሎቴን ስለመለሰልኝ እቤት እስክደርስ እግዚአብሔርንም አመሰገንኩት፡፡ በእውነት ቃሉን ጠብቆ እንደ ልጁ ተከታትሎኛል፡፡ በከተማው የተወሰኑ ሱቆች ስለተከፈቱ የተወሰኑ ልባሽ ጨርቆችን፣ አዳዲስ ጫማዎችንና ሽቶ ገዛሁ፡፡ ከዚያም በአምስት ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ ጸጉሬን ተሠራሁ፡፡ መልሶ ሴትነት እየተሰማኝ ወደ ቤት ሄድኩ፡፡ አሎይዜ ለባብሼና አምሮብኝ ከክፍሌ ብቅ ስል ስታየኝ የልብ ድካም የተነሣባት ያህል አደረጋት፡፡
‹‹ምንም ነገር እንድታገኚ ስትጸልዪ እኔም ትንሽ እንዳገኝ እስኪ ጸልዪልኝ›› አለች ካንጀቷ እየሳቀች፡፡ በተረፈኝ ገንዘብ የገዛሁትን ለአንድ ሌላ ወር የሚበቃንን መጠጥ ሳሳያትማ ይበልጥ ሳቀች!
በቀጣዩ ቀን ጠዋት ሥራ ፍለጋዬን እንደገና ለመቀጠል ወደ ተመድ አመራሁ - አምሮብኝ፣ አልባብ አልባብ እየሸተትኩ፣ የትምህርት ማስረጃዬን ይዤ ሙሉነት ተሰምቶኝና በራሴ ተማምኜ፡፡ በአዲሱ ዓለሟ ስፍራዋን ለመያዝ የተዘጋጀች ሥራዋን የምታስቀድም ሴት ወጥቶኛል፡፡
ጋናዊው የጥበቃ ጓድ በዚህ ወቅት በሩ ጋ አላስቆመኝም፤ በእርግጥ ያለ ምንም ጥያቄ ሳልፍ ፈገግ ብሎ ስላስገባኝ ያወቀኝም አልመሰለኝ፡፡ ሕንጻው ጋ እንደደረስኩ ወደ ሰው ኃይል ኃላፊው ክፍል አቅንቼ በሩን አንኳኳሁና ኃላፊውን በወሬያቸው መካከል አቋረጥኳቸው፡፡
‹‹ምን ልርዳሽ እህቴ?›› ሲሉ በፈረንሳይኛ ጠየቁኝ፡፡
‹‹ሥራ ፈልጌ ነው ጌታዬ›› አልኩ በእንግሊዝኛ … ወይንም ያልኩ መሰለኝ፡፡ ተምታታባቸው፡፡ ‹‹ሥራ እፈልጋለሁ ነው የምትዪው?››
‹‹አዎን ጌታዬ፣ ልክ ነው - ሥራ ፈልጌ ነው›› ስል በፈረንሳይኛ መለስኩ፡፡ እንግሊዝኛዬ የሆነ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው አያጠራጥርም፡፡
‹‹አሃ … እስኪ አንዴ እዚሁ ጠብቂኝ›› አሉኝና ወደ ክፍሉ ገቡ፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ጸሐፊያቸው ልታነጋግረኝ መጣችና ከላይ እስከ ታች ምንጥር አድርጋ አየችኝ፡፡ ሩዋንዳዊት ነች፡፡ ብቻ በሆነ ምክንያት ገና ስታየኝ ዓይነ-ውኃዬን አልወደደችውም፡፡ ‹‹ወደዚህ ሕንጻ እንዴት ልትመጪ ቻልሽ? ምንድነው
የምትፈልጊው?›› ስትል በኪንያሩዋንዳ ቋንቋ ጠየቀችኝ፡፡
‹‹ሥራ ነው የምፈልገው፡፡››
‹‹ምን ልምድ አለሽ?››
‹‹ኤሌክትሮኒክ ምህንድስናና ሒሳብ ሳጠና በዩኒቨርሲቲ ነው የቆየሁት፡፡››
‹‹እዚህ ያሉት ሥራዎች የጽሑፍ ሥራዎች ናቸው - ያም የሚሆነው ደሞ ሥራው ሲኖረን ነው፡፡ መቀምር መጠቀም ወይንም እንግሊዝኛ መናገር ትችያለሽ?››
‹‹የጽሕፈት ሥራ ሰርቼ አላውቅም፣ ግን ትንሽ ትንሽ እንግሊዝኛ እሞካክራለሁ፡፡››
‹‹አሃ›› አለች እንደዋዛ፡፡ ‹‹እንግዲህ ምንም ሥራ የለንም - ምናልባት በሦስትና አራት ወር ውስጥ ካለ ነው፡፡ ግን ባለሽ ክህሎት ምንም ሥራ የምናገኝልሽ አይመስለኝም፡፡ እባክሽ ስትወጪ በሩን ዝጊው፡፡››
ክፍሉን ለቅቄ ስወጣ በጣም ስለተበሳጨሁ ወደ ጓሮ በሚያስወጡት ደረጃዎች ማንም ሳለቅስ እንዳያየኝ ብዬ እየሮጥኩ ወረድኩ፡፡ የተወሰኑትን ደረጃዎች እንደወረድኩ አንድ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉ ሰውዬ በፈረንሳይኛ ጠሩኝ፡
‹‹ጠብቂኝ! አንዴ ቆይ እህቴ! ላናግርሽ?››
ሩጫዬን ለመቀጠል ብፈልግም ለታላላቆቼ አክብሮት ስላለኝ ምላሽ መስጠት አለብኝ ብዬ ቆምኩ፡፡ እንባዬን ወዲያውኑ ጠራረግሁና ‹‹አቤት?›› አልኩ፡፡ሰውዬው ሲያዩኝ አኳኋናቸው ከሆነ እንግዳ መንፈስ ጋር ግጥምጥም እንዳሉ ሁሉ አስመሰላቸው፡፡ ‹‹እም… እ… እዚህ ምን እንዳመጣሽ አልገባኝም?››
ዘበኛ ሊጣሩ ነው
1👍1
ብዬ ባስብም ‹‹ሥራ ጌታዬ … ሥራ ፈልጌ ነው›› ስል መለስኩላቸው፡፡
‹‹የሰው ኃይል ኃላፊውን አናገርሽው?››
የደረጃ ላይ ጥያቄያቸው ቢያበሳጨኝም እንደገና በአክብሮት መለስኩላቸው፡፡ ‹‹አዎን ጌታዬ፣ አናግሬያቸዋለሁ፡፡ ግን ምንም ሥራ እንደሌለ ተነግሮኛል፡፡››
‹‹እ … እንግዲህ እንደዚያ ካለ›› ብለው በአድራሻ ወረቀታቸው ላይ የሆነ ነገር ጻጽፈው ሰጡኝ፡፡ ‹‹ነገ ጠዋት ዋናው በር ላይ ይህንን አሳይተሽ ግቢ›› አሉ፡፡ ‹‹አራት ሰዓት ላይ እኔ ሥራ ቦታ እንድትመጪ፡፡ ሥራ እንድታገኚ ማድረግ የምንችለውን ነገር እስቲ እናያለን፡፡››
ምን እንደምል አላወኩም፤ ብቻ እርሳቸው ደረጃውን ሲወጡ በሰጡኝ ወረቀት ላይ አፍጥጬ ቆየሁ፡፡ ጽሑፉ ሳነበው አንዲህ ይላል፡- ፒየር ሜሁ ቃል አቀባይ፣ ዩናሚር የተመድ የሩዋንዳ አጋዥ ተልዕኮ
ቃል አቀባይ ምን እንደሆነ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ ሲያዩት ግን ትልቅ ነገር ይመስላል፡፡ ዩናሚር ከጦርነቱ በፊት የተቋቋመው በሩዋንዳ የተሻለ የመንግሥት አሠራር ለማምጣት ነበር፡፡ ምን አልባት ባልደረባው ልሆን እችል ይሆናል!
በቀጣዩ ቀን ጠዋት ከአቶ ሜሁ ጋር ስገናኝ በዋዜማው በደረጃው ላይ እንዳዩኝ በጣም የሚወዷት ከጦርነቱ በፊት ሠራተኛቸው የነበረችውን ወጣት ሩዋንዳዊት መስያቸው እንደነበር ነገሩኝ፡፡ በዘር ጭፍጨፋው ወቅት ከነቤተሰቧ ነው አሉ የተገደለችው፡፡ ከዚያ በኋላ ታሪኬን አንድነግራቸው ጠይቀውኝ ነገርኳቸው፡፡
‹‹እንዲያው ወርሃዊ ገቢሽ ስንት ነው?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡
‹‹ምን?››
‹‹ምን ያህል ገንዘብ ታገኛለሽ በወር?››
‹‹ምንም፡፡ ለዚያ ነው እኮ እዚህ የመጣሁት፡፡››
‹‹እስኪ እንግዲህ … ግን የለንም፡፡ ያው መቼም ሥራ እንድታገኚ አግዝሻለሁ፡፡ ወላጆችሽ በደንብ እንዳሳደጉሽ ያስታውቃል፡፡ ወላጅ-አልባ የምትሆኚው መሆን ከፈልግሽ ብቻ እንደሆነ እወቂ፡፡ ከአሁን ጀምሮ የተመድ ቤትሽ ነው፤ እኔንም እንደ አባትሽ ቁጠሪኝ፡፡››
እስኪያመኝ ድረስ ፈገግ አልኩ - እግዚአብሔር በእውነት የሚንከባከቡኝ
መላዕክት በመላክ ቃሉን ጠብቋል፡፡
‹‹በእርግጥ ሁሉንም ፈተናዎች መፈተን ይኖርብሻል›› አቶ ሜሁ ቀጠሉ፤ ‹‹ይህን ትምህርትሽን ይዘሽ ግን ያ አያዳግትሽም፡፡ የመቀምር ጽሑፍና የእንግሊዝኛ ክህሎትሽ እንዴት ነው?››
‹‹መተየብ ባልችልም በመታጠቢያ ቤቱ እንደተደበቅሁ ግን ራሴን እንግሊዝኛ አስተምሬያለሁ፡፡››
‹‹እንደዚያ ከሆነ እንግዲህ …. አስቸኳይ የአጭር ጊዜ ትምህርት ያስፈልግሻል፡፡›› አቶ ሜሁ ከጸሐፊያቸው ከዣኒ ጋር አስተዋወቁኝ፤ እርሷም መቀምር አጠቃቀም፣ ቃለ - ጉባኤ አያያዝና የአቀማመጥ ዝርዝሩን ሁሉ አሳየችኝ፡፡ በመቀምሩ ላይ ያሉትን ሁሉንም ቁልፎች ማስታወስ ቻልኩ፡፡ በተጨማሪም የመጻፊያ ሰሌዳውን ትክክለኛ አምሳል በቁራጭ ክላሴር ላይ ሣልኩት፡፡ በመቀምሩ ላይ ሦስት ቀናት በመፍጀት ሦስት ሌሊቶችን ሙሉ ሳልተኛ አድሬ በእጅ በተሳለው ሰሌዳዬ ላይ ስጽፍና ስለማመድ ቆየሁ፡፡
እግዚአብሔር ጣቶቼን መርቷቸው ሳይሆን አይቀርም፤ በአራተኛው ቀን የተመድን የትየባ ፈተና በአጥጋቢ ውጤት አለፍኩ፡፡ ከተወሰኑ ቀናት በኋላም የእንግሊዝኛውን ፈተና አለፍኩና በተመድ ለመሥራት ብቁ ነሽ ተባልኩ፡፡ በአእምሮዬ ስዬው፣ አልሜው፣ ጸልዬበት ነበረና አገኘሁት!
ለጊዜው ባይነገረኝም የመዝገብ ቤትን ሥራ ቀጥ አድርጌ ይዤው ኖሯል፡፡ ወዲያውኑም ሁሉንም ከውጪ ወደ ሩዋንዳ የሚገቡ የተመድ አቅርቦቶች የመከታተል ኃላፊነት የኔ ሆነ - ከአዳዲስ አነስተኛ ተሸከርካሪዎች እስከ ግዙፍ የምግብ አቅርቦቶች፡፡ ወሳኝ ሥራ ስለሆነ ከተወሰኑ ወራት በፊት እሞት እድን ሳላውቀው በአንድ ሌላ ሰው ትንሽ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ቁጢጥ ብዬ እንደነበር ላምን አልቻልኩም፡፡
ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆኑት የጸሎትና የአዎንታዊ አስተሳሰብን ዐቅም ቋሚ ማሳያ ነኝ፡፡ አምላክ የሁሉም አዎንታዊ አስተሳሰብ ምንጭ ነው፤ ጸሎትም የእርሱን ዐቅም ለማጉረፍ ሁነኛው መንገድ ነው፡፡
አምላክ ከመታጠቢያ ቤቱ ስንትና ስንት መንገድ አምጥቶኛል፤ ይህን መንገድ ስጓዝም እያንዳንዷን እርምጃ አብሮኝ ተጉዟል፡፡ ከገዳዮች አድኖኛል፤ ልቤን በይቅር ባይነት ሞልቶታል፣ እንግሊዝኛ እንድማርም ረድቶኛል፣ ወደ ደህንነትም መርቶኛል፤ ጓደኞች፣ መጠለያና ምግብ ሰጥቶ፤ በመጨረሻም አቶ ሜሁንና የማልመውን ሥራዬን አስተዋውቆኛል፡፡ ባለፉት ብዙ ወራት ያለፍኩበት ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር ከአጠገቤ አልተለየም፤ ብቻዬንም አልሆንኩም፡፡
አዲሱን ሥራዬን ወድጄዋለሁ፤ እያንዳንዷ ቀን ካለፈው የበለጠ አስደሳች ነች፡፡ በተመድ ብዙ የተለያየ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ስላሉ በገዛ አገሬ ጎብኝ የሆንኩ ያክል ተሰማኝ፡፡ አዳዲስ ክህሎቶችን በተከታታይ ስማር፣ ሰዎችን ስተዋወቅና እንግሊዝኛዬን ሳሻሽል ቆየሁ፡፡
ያለኝ የእግዚአብሔር ቡራኬ ብቻ ሳይሆን ደሞዜም ጭምር ነው! ወዲውያኑም ለአክስቶቼ ገንዘብ መላክና አሎይዜና ልጆቿን ላደረጉልኝ ነገር ሁሉ ለማመስገን ምግብና አዳዲስ ልብሶች መግዛት ቻልኩ፡፡ ቤትና ቤተሰብ በጣም በፈለግሁበት ወቅት ሰጥተውኛል … ግን የመሄጃ ጊዜዬም እንደተቃረበ አውቄያለሁ፡፡ በጥቅምት መጀመሪያ ሁሉም ከፈረንሳይ ምሽግ የመጡት ጓደኞቼ የአሎይዜን ቤት ለቀው ስለሄዱ በአቅራቢያዬ ያለው ሁሉም ነገር መቀያየር ጀምሯል፡፡ በ1959ኙና 1973ቱ የዘር ጭፍጨፋዎች ያመለጡ የነበሩ ከሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ቱትሲ ስደተኞች ከዓለም ዙሪያ ልጆቻቸውን፣ የልጅ ልጆቻቸውንና ያላቸውን አዲስ የባህል ቅርስና እንግዳ ቋንቋዎች ይዘው መመለስ ጀማምረዋል፡፡ የሀገሪቱንም ገጽታ እየቀየሩት ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን ስደተኛ ተመለሰ፡፡ በዘር ፍጅቱ የተፈጀውን ያህል ቱትሲ መሆኑ ነው - ልረዳው የማልችለው ቁጥር፡፡
ቱትሲዎቹ ሲመለሱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሁቱዎች የበቀል ግድያዎችን ፈርተው ሩዋንዳን ለቀው ተሰደዋል፡፡ አብዛኞቹ በሌሎች አገሮች ባሉ ቆሻሻ የስደተኞች መጠለያዎች መሰቃየት ዕጣቸው ሲሆን ብዙዎች በበሽታና በምግብ እጥረት ሞተዋል፡፡ በየስፍራው ሥቃይ ነግሷል፡፡ አንድ ቀን ብዙ እንዳወቅሁና በቂ ገንዘብ እንዳጠራቀምኩ በሀገሬ ሆኜ የተሸከምኩትን ብስጭት ትቼው ርቄ እሄዳለሁ፡፡ ለአሁኑ ግን የማደርጋቸው ትናንሽ ለውጦች አሉኝ፡፡ ሕይወት በሩዋንዳ እየተለዋወጠ ስለሆነ እኔም አብሬው እለዋወጥ ይዣለሁ፡፡
አምላኬን በፍቅርና በበጎ ስሜቶች የምከበብበትን አዲስ ቤት እንዲሰጠኝ ለመንኩት፡፡ በዚህ ወቅት የአሎይዜን ቤት የፊት በር ስከፍት የራሴን ጸሎት ራሴው እንድመልስ አደረገኝ፡፡ ውድ ጓደኛዬና አንድ ክፍል በኮሌጅ አብራኝ ትማር የነበረችው ሳራ በሩ ላይ ቆማ እኔን በማግኘቷ በደስታ ታነባለች፡፡ ስትፈልገኝ ቆይታ ነው ያገኘችኝ፤ ሁለታችንም ተጯጩኸን ተቃቀፍን፡፡ ለሰዓታት ስለነበረው ነገር ሁሉ እንዲሁ ስንጠያየቅና እንባችንን ስናዘራ ቆየን፡፡ ቄሱ ወንድሞቻችንን ኦገስቲንንና ቪያኒን እንዴት አድርገው በሌሊት እንዳባረሯቸውና ልጆቹ እንዴት አብረው እንደሞቱ ስነግራት ልቤ እንደገና ተሸበረች - በጣም እንወዳቸው ስለነበሩት

ስለወንድሞቻችንና ስለተቀረው ቤተሰቤ በጣም ተላቀስን - ሳራ ሁሉንም ታውቃቸዋለች፤ ትወዳቸውማለች፡፡
‹‹ሁሌም ቢሆን እኛ
👍3
ቤተሰብሽ እንሆናለን›› አለች ሳራ፡፡ ‹‹ነይ እኔ ቤት ኑሪ… መልሰን እህቶች እንሆናለን!›› ሳራ ለኔ እጅግ ልዩ ስለሆነችና ችሮታዋንም ስለምፈልገው ወዲያውኑ ተቀበልኩት፡፡ በዚያኑ ቀን እቃዎቼን አስሬ ወደ ወላጆቿ ቤት ሄድኩ፡፡ አሎይዜ የሳራ ቤት ከቤቷ አምስት ደቂቃ ራቅ ብሎ ስለሚገኝ መሄዴ ምንም አልመሰላት፤ ቶሎ ቶሎ እንደምጠይቃትም ቃል ገባሁላት፡፡
በወቅቱ ከሳራ ቤት የበለጠ ሰላማዊና ፍቅር የሞላበት ቤት አልተመኘሁም፡፡ በዕድሜ የገፉት ወላጆቿ ለ55 ዓመታት ያህል በጋብቻ ኖረዋል፤ እርስ በርሳቸው ግን አሁንም በአሥራዎቹ ዕድሜ ያለን ነን እያሉ ይቀላለዳሉ፤ ይኩራሩማል፡፡ አጥባቂ ክርስቲያኖች ሲሆኑ በየቀኑ ጠዋት አብረው ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ይጸልያሉ፡፡ ቤታቸው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረኝን የግል ግንኙነት መልሶ ለመገንባት ትክክለኛው ስፍራ፣ ስለ ቤተሰቤም ለማልቀስና ራሴን መልሼ ለማዳን ሁነኛው ቦታ ነው፡፡ ቀስ በቀስ የቆሰለው ልቤ እነ ሳራ ቤት አሁንም እንኳን ወረቀት ላይ ላሰፍራቸው የማልችላቸውን ቃላት እንድናገር ብርታቱን አገኘ፡፡ በዚያን ወቅት ሴኔጋል ሆኖ ልኑር ልሙት ለማያውቀው ለወንድሜ ለኤይማብልም የምጽፍበት ሰዓቱ ደረሰ፡፡ በከፊል ምንም የመላላኪያ አገልግሎት ባለመኖሩና በዋነኛነት ቃላቱን ካላየኋቸው እነዚያ አሰቃቂ ተግባራት በእውነት እንዳልተከሰቱ አስባለሁ በማለት ይህን አስቸጋሪ ተግባር በይደር አቆይቼዋለሁ፡፡ ችግሮቹ ግን ያው ተከስተዋል - እውንም ናቸው፡፡ ስለሆነም መጨረሻ ላይ መቀበል ጀማመርኩ፡፡
የአባቴን መቁጠሪያ በአጠገቤ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጬ መጻፉን ተያያዝኩት፡- የኔ ውድ ኤይማብል፣ ይህ በሕይወቴ የጻፍኩት እጅግ አሳዛኙ ደብዳቤዬ ነው፣ አንተም የምትቀበለው እጅግ ዘግናኙ …

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
አትሮኖስ pinned «#ሁቱትሲ ፡ ፡ #ምዕራፍ_አስራ_ስድስት ፡ ፡ #የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች ፡ #ትርጉም_በመዝምር_ግርማ ፡ ፡ #የጌታዬ_ሥራ ፡ ሰዎች በመንገድ ላይ ለመዘዋወር እንኳን በሚፈሩበት ከተማ ሥራ የት እንደማገኝ የሚያውቀው አምላክ ነው፡፡ ውድቅዳቂ ፈንጂዎች የኪጋሊን መንገዶች ሞልተዋቸዋል፤ ለመሥራት ከፈለግሁ ግን በነዚህ ጎዳናዎች ሥራን እያነፈነፍኩ መኳተን ይኖርብኛል፡፡ የሕዝብ ማጓጓዣ ተሸከርካሪዎች…»
#ዕውነቴን_የበሉ

ጠግቤአለሁ ብለህ

ሰልፍ ውጣ ቢሉኝ
መፈክሬን ይዤ

በድንገት አዛጋኝ
እነሱም መለሱ

እውነቴን አበሉ
እርቦት አይደለም

እንቅልፍ ነው አሉ።
#ይህች_ሀገር

#ትላንት
ሀገሬ ኢትዮጵያ መመኪያዬ እያለ
የጠቀማት መስሉት ስንቱን ሰው ገደለ፤

#ዛሬ
ይህች ሀገር እንዳለ ስሟን ሳያነሳ
ክብር ተሸለመ በስሟ ሲወሳ ፤

#ነገ
ሰብሳቢ ከጠፋ ደርሶ የሚያድናት
ኢትዮጵያዬ ብለን በስሟም አንጠራት!!
#ሁቱትሲ


#ምዕራፍ_አስራ_ሰባት


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ


#ሙታኑን_ስቀብር


‹‹ወላጆችሽ የት ነው የሚኖሩት?›› ይህ ጥያቄ በተመድ ሥራዬን ከጀመርኩ ከጥቂት ወራት በኋላ የቀረበልኝ፡፡
‹‹ልቤ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በሕይወት የሉም›› በማለት በትዕግሥት መለስኩ፡፡
‹‹በዘር ፍጅቱ ተገድለዋል፡፡››
የተመድ ሰቆቃዬን ለመርሳት የምችልበት ስፍራ አይደለም፡፡ እዚያ የሚሰሩት አብዛኞቹ ከሀገሪቱ ውጪ የመጡ ስለሆኑ የቤተሰቤን ዕጣ ፈንታ ሲያውቁ የዘውጌ አባላት አብዛኞቹ በተገደሉበት ሁኔታ እኔ እንዴት ልተርፍ አንደቻልኩ ለማወቅ በጣም ይጓጓሉ፡፡
‹‹ይቅርታ›› አሉኝ እያዋሩኝ ያሉት ሰውዬ፡፡ ‹‹አላወቅሁም፡፡ እንዳላበሳጨሁሽ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡›› ስማቸው ኮሎኔል ጉዬ ሲሆን ወደ ሩዋንዳ አገሪቱን በማረጋጋቱ ተግባር ለማገዝ የመጣው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር አዛዥ ሴኔጋላዊ ናቸው፡፡ እኔን ስለማበሳጨት እንዳይጨነቁ ለኮሎኔሉ ነገርኳቸው፡፡ ጥያቄ መጠየቅ ያለፍኩትን ሁሉ ከግምት ውስጥ ሳስገባው ከሚያሳስቡኝ ነገሮች በጣም ዝቅተኛውን ደረጃ ነው የሚይዘው፡፡ አሁንም ቢሆን ከጦርነቱ ወዲህ ባላያቸውም አክስቶችና በመጣሁበት ኪቡዬ ክፍለሀገር የሚኖር አጎት እንዳለኝ አሳወቅኋቸው፡፡
‹‹አሃ፣ ኪቡዬ … እዚያ የሰፈሩ የተወሰኑ ወታደሮች አሉኝ›› በማለት መለሱልኝ፡፡ ‹‹ዘመዶችሽን መጠየቅ ካስፈለገሽ ላጓጉዝሽና ራሴ ላጅብሽ እችላለሁ፡፡ ጓደኛም ከፈልግሽ ማምጣት ትችያለሽ፡፡››
በሀገሪቱ መዘዋወር ያን ጊዜም ቢሆን አስቸጋሪና አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ የእርሳቸው ግብዣ ትልቅ ችሮታ ነው፡፡
‹‹በእውነት? መቼ እንደሆነ ይንገሩኝና እንሄዳለን ኮሎኔል፡፡›› ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሳራና እኔ ወታደራዊ ጠያራ ላይ በቀበቶ ታስረን አንዳችን የሌላችንን እጆች እየያዝንና በደስታ እየሣቅን በሩዋንዳ አረንጓዴ ተራሮች ላይ እንበር ጀመር፡፡ ሁለታችንም በአየር በርረን ስለማናውቅ ኮሎኔሉ የመብረር እድሉን ሲሰጡን እውነት አልመሰለንም ነበር!
ውቧን አገሬን ቁልቁል ሳያት የዘር ጭፍጨፋውን አስቀያሚ እውነታ ማመን አስቸገረኝ፡፡ በነዚያ ጨለማ ቀናት ምን ያህል ጊዜ ነው ወፍ ሆኜ በተወለድኩ ብዬ የተመኘሁት? ምን ያህልስ ጊዜ ነው ከመታጠቢያ ቤት እስር ቤቴ ወጥቼ ከአሰቃቂው ሰቆቃ በላይ ርቄ መብረርን ያለምኩት? እና አሁን እዚህ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ስፍራ ተመልሼ ለመጎብኘት ይኸው እበር ይዣለሁ፡፡ ከማታባ አምልጬ ኪጋሊ ለመድረስ ስንት ጊዜ ፈጅቶብኝ እንደነበር አውርቼልዎታለሁ - ለመመለስ ይኸው 30 ደቂቃ ብቻ ፈጀብኝና አረፈው፡፡
ኤይማብል ከኔ ጋር ቢሆን ብዬ ተመኘሁ፤ ግን አልተቻለም፡፡ የመልዕክት መላላኪያ አገልግሎቱ ገና ቀርፋፋ ሲሆን፤ በዚያም ላይ ከእርሱ የመልስ ደብዳቤ እንኳን ለማግኘት ሳምንታት ፈጅቶብኛል፡፡ ከኔ ይህ ደብዳቤ ስለደረሰውና በሕይወት መኖሬን በማወቁ በጣም ደስተኛ ስለሆነ ስሜቱን ለመግለጽ ቃላት ሊያገኝልኝ እንዳልቻለ ገልጾ ጻፈልኝ፡፡ በዘር ፍጅቱ ወቅት የዜና ዘገባዎችን ይከታተል ስለነበር ሁሉም የቤተሰባችን አባል ከሌላው ሩዋንዳ ውስጥ ካለ ሁሉም ቱትሲ ጋር ወድሟል ብሎ አምኖ ተስፋ ቆርጦ ነበር፡፡ ለመገደል ካልሆነ በቀር በዘር ፍጅቱ ወቅት ወደ ሀገሪቱ የሚመለስበት ምንም መንገድ አልነበረውም፡፡
ለመምጣት ችግር የሆነበት ደግሞ በወቅቱ ለመመለስ ወጪውን መሸፈን አለመቻሉ ነው፡፡ ተማሪ ስለሆነ ገቢ የለውም፣ የሚኖረው 5 000 ኪሎሜትር ርቆ በሴኔጋል ነው፡፡ የአየር መሳፈሪያ ወጭው ብቻ 2 000 የአሜሪካን ዶላር ይፈጃል፤ ይህም የማይታሰብ ነው! ሙሉ ወጭውን ሸፍኖ የሚያስተምረው የአውሮፓ ድርጅትም ሩዋንዳ በጣም አደገኛ የጦርነት ቀጠና ስለሆነ ወደዚያ የምትሄድበትን ክፍያ አልከፍልልህም ይለዋል፡፡ ወንድሜ ትምህርቱን አቋርጦ መጥቶ ከኔ ጋር ለመኖር ቢፈልግም እማማንና አባባን የሚያኮራበት ሁነኛ መንገድ ትምህርቱን በከፍተኛ ውጤት መጨረስ እንደሆነ ነገርኩት፡፡ በየሳምንቱ ለመጻጻፍ፣ ለወደፊቱ ለመጠያየቅና ገንዘብም ለማጠራቀም ተስማማን፡፡ እናም አሁን ወደ ማታባ ላገኘሁት የነጻ የአየር ጉዞ ምስጋና ይግባውና ቤታችንን ያለ ብቸኛው ቀሪ ወንድሜ እጎበኛለሁ፡፡

ትንሿ ወታደራዊ ጠያራ መሬት ላይ ካረፈች በኋላ ኮሎኔል ጉዬ ትራኦሬ ለሚባል ብርቱ ወጣት መኰንን አደራ ብለው በወታደሮቹ ምሽግ አስቀምጠውን ይሄዳሉ፡፡ እርሱም ለእያንዳንዱ ወታደር የኮሎኔል ጉዬ ልጆች ናቸው ብሎ አስተዋወቀን፡፡ ከዚህን ጊዜ በፊት በነበሩኝ የወታደር ምሽግ ቆይታዎቼ አግኝቼው የማላውቀውን አገኘሁ - ሳራና እኔ የየራሳችን ክፍል፣ የምንተኛባቸው አልጋዎች፣ ምርጥ ምግብ ብሎም የእያንዳንዱ ወታደር አክብሮትና እገዛ ተቸረን፡፡ እንዲያውም እስከ ንጋት ድረስ ባህላዊ የሴኔጋል ዘፈኖችን ሲዘፍኑና እርስ በርሳቸው ሲቀላለዱ አብረን አነጋን፡፡ ሳራ በአቀባበሉ ደስ ከመሰኘቷም በላይ ደኅንነት ሲሰማት እኔም አገሬ በመግባቴ ደስ ተሰኘሁ፡፡
በማግስቱ ወደ መንደሬ ለመሄድ ስምንት ኪሎሜትር የሚርቀውን የእግር መንገድ ለመጓዝ ስዘገጃጅ መኰንን ትራኦሬ ስለደህንነታችን ያለውን ሥጋት ይናገር ጀመር፡፡ የዘር ፍጅቱ ቢያበቃም በሀገሪቱ ግልጽ የሆነ ጥላቻ ስለነገሰ በዚያን ወቅትም ግድያ ይፈጸማል፡፡ መኰንኑ በትጥቅ አጀብ ሊልከን ወሰነ - አጀቡም ከሁለት ደርዘን ያላነሱ ወታደሮችንና አምስት ብረት-ለበስ ተሸከርካሪዎችን ያጠቃልላል፡፡ ማታባ በጀግና ኩራት እንገባለን እንጂ እንደ ተመላሽ ስደተኛ አንሹለከለክም፡፡ በዚያች መንደር ያን ያህል ጊዜ በፍራቻና ሥጋት ተሸሽጌባታለሁ፤ አሁን ግን ራሴን ቀና አድርጌ መሄዴ መልካም ነው፡፡
በልጅነቴ በጣም በማውቀው ሰማይ ስር ተሸከርካሪዎቻችንን ስንነዳ ስሜቴ በፍጥነት ወደ ኃይለኛ ብስጭት ተለወጠ፡፡ ወንድሞቼና እኔ ብዙውን ጊዜ እንሄድበት ወደነበረው መንገድ ስንገባ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ከዚያም በወቅቱ ጭር ባለው እናቴ ታስተምርበት በነበረው ትምህርት ቤት አልፈን አባታችንን ተከትለን በጠዋት ኪቩ ሐይቅ ወርደን ልንዋኝ በምናልፍበት መንገድ ቁልቁል ወረድን፡፡ ሳራ እጇን በትከሻዬ አድርጋ ልታጽናናኝ ብትሞክርም አልሆነም - መጽናናት የምችል አልነበርኩም፡፡ በፈራረሱ መስኮቶችና በተዘጉ የውጪ በሮች አጮልቀው የሚያዩን ፊቶች ጥላ ይታየኛል … ብዙ ወገኖቼን አሳደው የገደሉ ጽንፈኛ ሁቱዎች ፊቶች፡፡ ብዙዎቹን የቱትሲዎችን ቤቶች ራሳቸው ካቃጠሉ በኋላ አሁን ብቻቸውን ቆመው ያሉትን ብቸኛ ቤቶች በንብረትነት ይዘዋቸዋል፡፡ ከዚያም የራሴ ቤት ጋ ደረስን፡፡
ጣራ የለ፣ መስኮት የለ፣ በር የለ፤ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ ገዳዮቹ ለጭፍጨፋቸው ሲዘገጃጁ እኛ ለቀናት ሬድዮ ስናዳምጥበት የነበረውን የተቃጠለውን መሬት የተወሰኑ ከፊል ግንቦች እየጠበቁት ዘብ ቆመዋል፡፡ አንድ ወቅት የወላጆቼ ሕልም የነበሩትን ባዶ ክፍሎች እየቃኘሁ በድንጋይ መዋቅሩ ውስጥ ተዟዟርኩ፡፡ የተጎዱ የቤት እቃዎችም ሆኑ የተቃጠሉ ልብሶች አሻራ የለም - ማንም ሊገምት እንደሚችለው ቤቱ ከመጋየቱ በፊት ንብረታችን ተዘርፏል፡፡
ብዙ በሕይወት የተረፉ ቱትሲ ጎረቤቶቻችን ወታደራዊ አጀባችንን አይተው ሰላም ሊሉኝ መጡ፡፡ በተደበቅኩባቸው ጊዜያት ስለተከሰቱት መጥፎ ነገሮች ነገሩኝ፤ እናቴ በተቀበረችበት ቦታ ላይ ሆነንም እምዬ እናቴ አንዴት እንደተገደለች ያስረዱኝ
👍1
ገቡ፡፡ የተወሰኑ የዳማሲን ጓደኞች ሊያገኙ የቻሏቸውን የሰውነቱን ክፍሎች በችኮላ ወደቀበሩባት አነስተኛ ጉድጓድ ወሰዱኝ፡፡ ዘበኛችን የነበረው ካሩቡ ወንድሜ ሲገደል ስላየ ንግግሩን ቃል በቃልና እያንዳንዷ ጥቃት ስትሰነዘርበት የነበረውን ክስተት ነገረኝ፡፡
ዘግናኞቹ ትውስታዎች፣ ጭካኔ የተሞላባቸው አረመኔያዊ ዝርዝሮቹ በዝተው ከምችለው በላይ ሆኑብኝ፡፡ ከሃዘኑ ገና ማገገሜ ስለሆነ ቁስሎቼ እንደገና በዚህ አሰቃቂ እውነታ ምክንያት በግድ ሲቀረፉ ተሰማኝ፡፡ ጎረቤቶቼንና ወታደሮቹን ለእናቴና ለወንድሜ የሚገባቸውን ቀብር እንዳደርግላቸው እንዲያግዙኝ ለመጠየቅ ፈለግሁ፤ መናገር ግን አቃተኝ፡፡ በጉሮሮዬ የተፈጠረው እብጠት ድምጼን ስላቆመው ለወታደሮቹ መልሰው ወደ ምሽጉ እንዲወስዱኝ በእጄ ምልክት ሰጠኋቸው፡፡ እማማንና ዳማሲንን ከሸፈነው ምልክት-አልባ የአቧራ ክምር አልፈን ከቤቴ ርቀን እየነዳን ሳለን በአፌ መራራ፣ ቆሻሻ የጥላቻ ጣዕም በአፌ መጣብኝ፡፡ በመልስ ጉዟችን ወቅት ስናልፍ አጨንቁረው የሚያዩንን ፊቶች አየሁና እነዚያ ሰዎች በእጃቸው ደም እንዳለባቸው በሙሉ ልቤ ታወቀኝ - የጎረቤቶቻቸው ደም … የቤተሰቤ ደም፡፡ ወታደሮቹ ማታባ ላይ ነዳጅ አርከፍክፈውልኝ ወደ አመድነት የሚቀይራትን ክብሪት ጭሬ እንድለኩስባት እንዲያደርጉኝ ፈለግሁ፡፡
ምሽጉ ጋ ስንደርስ ከማንም ጋር ሳላወራ በቀጥታ ወደ መኝታዬ ሄድኩ፡፡ ነፍሴ ከራሷ ጋር ተጣላች፡፡ ምኅረት ለማድረግ በጣም ብሟሟትም ይህን በማድረጌ እንደተታለልኩ ተሰማኝ፤ ጭላጭ ምኅረት እንኳን አልቀረኝም፡፡ የቤቴን መፈራረስ ማየቴና የምወዳቸውን ሰዎች የተተዉና ብቻቸውን የቀሩ መቃብሮች መጎብኘቴ መሃሪዋን መንፈሴን አስጨነቃት:: ጎረቤቶቼ የቤተሰቤን አሰቃቂ የግድያ ወሬ በጆሮቼ ሲያሠራጩት ከነፍሴ አስወግጄዋለሁ ብዬ ያሰብኩት የጥላቻ ስሜት ከማንነቴ ጥግ በታደሰ ጉልበት በግድ ተስፈንጥሮ ወጣ፡፡ ልቤ በቀልን ተርባ በውስጤ በገንኩ፡፡
እነዚያ ክፉ እንስሳት! አራዊት ናቸው፣ አራዊት፣ አራዊት፣ አራዊት!
ለሰዓታት መኝታዬ ላይ ተገላበጥኩ፡፡ ዲያብሎስ እየፈተነኝ እንደሆነ ታውቆኛል - ከእግዚአብሔር ብርሃን፣ ከምህረቱም ነጻነት አርቆ እየወሰደኝ አንደሆነ፡፡ የአሉታዊ ሐሳቦቼ ክብደት በጨለማው እየመራ ካመጣኝ ብርሃን ሲነጥለኝና ሲጎትተኝ ይታወቀኛል፡፡ በዚያ ሌሊት እንደተሰማኝ ዓይነት ብቸኝነት ፈጽሞ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ እግዚአብሔር እውነተኛው ባልንጀራዬ ነው፤ እነዚህ ስሜቶች በመሀላችን እንደ ግንብ ቆመዋል፡፡ ሐሳቦቼ እንዳሳመሙት አወቅሁ፤ ይህም አሰቀቀኝ፡፡ ከአልጋዬ ወርጄ ተንበረከክሁ፡፡ ‹‹ስለ ርኩሳን ሐሳቦቼ እግዚአብሔር ሆይ ማረኝ›› ስልም ጸለይኩ፡፡ ‹‹እባክህ … ሁልጊዜ እንዳደረከው ይህን ህመም ከኔ አርቀህ ልቤን አንጻልኝ፡፡ በፍቅርህና በምኅረትህ ኃይል ሙላኝ፡፡ እነዚያን አሰቃቂ ነገሮች ያደረጉት አሁንም ቢሆን ልጆችህ ናቸው፡፡ ስለዚህም ልርዳቸው፤ አንተም እንድምራቸው
አግዘኝ፡፡ ኧረ አምላኬ፣ እንድወዳቸው እርዳኝ፡፡››
ሳንባዎቼን ድንገተኛ የአየር መአት ሞላቸው፡፡ በከባድ የእፎይታ ትንፋሽ አቃሰትኩ፤ ራሴንም ትራሱ ላይ እንደገና አሳረፍኩት፡፡ ሰላሜን እንደገና አገኘኋት፡፡ አዎን፣ ተበሳጭቼ፣ በእጅጉ በግኜም ነበር፤ ብስጭቴ ግን ለበጎ ሆነ፡፡ እንዲቆጣጠረኝ የፈቀድኩለት ይህ ብስጭት ንጹሕ መሆኑን አወቅሁ፡፡ ምሬት ወይንም ጥላቻ የሚባል ነገር የሌለበት፡፡ ቤተሰቤን በእጅጉ ብናፍቅም እንደ ግርሻ ወጥሮ ይዞኝ የነበረው ንዴቴ ግን ለቆኛል፡፡
ቤተሰቤን የጎዱት ሰዎች እንዲያውም ራሳቸውን በበለጠ ጎድተዋል፤ በመሆኑም ላዝንላቸው ይገባኛል፡፡ በሰብዓዊነትና በእግዚአብሔር ላይ ለፈጸሟቸው ግፎች መቀጣት እንዳለባቸው ማንም ጥርጥር አልነበረውም፡፡ ተጠያቂ የሚሆኑትን ለመያዝ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለማቋቋም በተመድ ውይይት ተጀምሯል፤ ይህም እንዲከሰት፣ ርህራሄም እንዲኖር ጸልዬአለሁ፡፡ እግዚአብሔርን የጥላቻን ዑደትና ጽንፍ የረገጠን ጥላቻ የሚያቆመውን ምኅረት እንዲለግሰን ጠይቄዋለሁ፡፡ ልቤና አእምሮዬ ሁሌ ንዴት ሊሰማቸው እንደሚዳዳቸው አውቄዋለሁ - ውንጀላንና ጥላቻንም እንደሚፈልጉ፡፡ አሉታዊ ስሜቴ ሲመጣብኝ ይህን ችግር ፈታሁት፤ እንዲያድግ ወይንም እንዲባባስ አልፈለግሁም፡፡ የሁሉም እውነተኛ ኃይል ምንጭ ወደሆነው ወዲያውኑ ፊቴን እመልሳለሁ፡፡ ወደ እግዚአብሔር እዞራለሁ፤ ፍቅሩና ምህረቱም ከለላና ድኅነት ይሆኑኛል፡፡
ራሴን ቀና ሳደርግ ጨረቃ እንደወጣች አየሁ፡፡ ወታደሮቹ ሲስቁና ሲዘፍኑ ስለሰማኋቸው ወደ ውጪ ወጣሁ፡፡ ሳራና እኔ እርስ በርሳችን ተሣሣቅንና እንደገና እዚያ ባሉት በሁሉም ላይ ፈገግ አልኩ፡፡ ወታደሮቹ እየተዝናኑ ስለሆነ እኔ በጣም ደስ ያለኝ መስዬ ስቀላቀላቸው ተገረሙ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ሲጨፍሩ ሳራና እኔ ታዳሚ በመሆን ስናደማምቅላቸው ቆየን፡፡

በቀጣዩ ቀን እናቴንና ወንድሜን እንደ ደንቡ ለመቅበር መኰንኑ መልሶ ወደ መንደሩ ይወስደኝ እንደሆን ጠየቅሁት፡፡ በዋዜማው የገባሁበትን ሐዘን አስቦ በእውነት አስፈላጊው ጥንካሬ እንዳለኝ ጠየቀኝ፡፡ ጥንካሬው እንዳለኝም አረጋገጥኩለትና ወደ መንደሩ ያለፈውን ቀን የሚያህል የወታደር አጀብ ፈቀደልኝ፡፡ መንገዳችን ላይ በድሮው ቤታችን አቅራቢያ የሚኖሩትን አክስቶቼን ዣኒንና ኢስፔራንስን ለመጠየቅ ቆምን፡፡ ከፈረንሳውያኑ ምሽግ ከወጣን ወዲህ አልተገናኘንም፡፡ ሁለቱም ከሰቆቃቸው ሙሉ በሙሉ ባያገግሙም (እንዳያያዛቸውማ መቼም የሚያገግሙ አይመስሉም) በወቅቱ ግን ቢያንስ በጣም በተሻለ ሁኔታ ላይ ነበሩ፡፡ ስሜት በተቀላቀለበት ሁኔታ በመንገድ ዳር መልሰን ተገናኘን፣ እኔ ግን ልቤን ወደፊት ለሚጠብቀኝ ጽኑ ግዳጅ በደኅና አቆየሁት፡፡ የእማማና የዳማሲን ቀብር ላይ የሚገኙ ሰዎችን እንዲፈልጉና አሮጌው ቤቴ ጋ እንዲያገኙኝ ነገርኳቸው፡፡
አብዛኞቹ በመንደሬ ያሉት ቱትሲ የዘር ፍጅት ተራፊዎችና የተወሰኑ ሁቱ ወዳጆቻችን ተገኙ፡፡ አንድ ካይታሬ የተባሉ ሽማግሌ የቤተሰቤ ወዳጅ ሁለት የሬሳ ሣጥን፣ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ አካፋና መጽሐፍ ቅዱስ አምጥተው ሁላችንም አስከሬናቸውን ፍለጋ ሄድን፡፡ በመጀመሪያ ዳማሲንን ፍለጋ ተቆፈረ፤ የተወሰኑ ጎረቤቶቻችን እንዳላይ ለመከለል ከበቡኝ - ቀስ ብለው የተገኘውን የአካሉን ክፍል እንዳላይ ከለከሉኝ፡፡
ተጋፍቼ አለፍኳቸው፡፡ ‹‹ወንድሜ አይደል እንዴ - ማየት አለብኝ›› ብዬ አስቸገርኩ፡፡ አስከሬኑን በዓይኔ ባላይ ኖሮ ዳማሲን ሞቷል ብዬ መቼም የማምን አይመስለኝም፡፡ ከዚያ አካፋው ከአጥንት ጋር ሲጋጭ ሰማሁት፤ ከዚያም አየሁት … የጎድን አጥንቶቹን አየሁ፡፡ መጀመሪያ ያየሁት ምንም ልብስ እንዳልለበሰ ነው፤ ከመግደላቸው በፊት ምን ያህል ክብሩን ሊገፉት እንደሞከሩም አስታወስኩ፡፡
‹‹አትዪ›› አለችኝ ኢስፔራንስ፡፡ ግን ግድ ይለኛል - የጎድን አጥንቶቹን እንጂ ምንም አላየሁም፡፡ ከታትፈውታል - ክርኖቹን፣ ራሱን … ወይኔ፣ እግዚአብሔር፣ የኔ ውድ ዳማሲን፣ ምንድነው ያደረጉህ? ስል እንደ እንስሳ ግሳት ዓይነት ድምፅ አወጣሁ፡፡ አንድ ሰው ወደ መቃብሩ ጎንበስ ብሎ የወንድሜን የራስ ቅል በእጁ ይዞ ቀና አለና ወደኔ ዞረ፡፡ መንጋጭላው ወጣ ብሎ ጥርሱን አየሁት … በጥርሱ አወቅሁት፡፡ ጥርሱ ከአማላይ ፈገግታው የቀረው ብቸኛው ነው፡፡ እኔ ላይ በአሰቃቂና አስፈሪ ፈገግታ አተኩሮብኛል፡፡ አይ ዳማሲንዬ! እንዲህ መጨረሻህ
ሳያምር ይቅር!
‹‹እንዴ አይሆንም! … እንዴ ዳማሲን! … ወይኔ! ቅድስት ማርያም! የአምላክ እናት!›› መሬቷ ወደኔ ሮጠችና ራሴንም ድንጋይ መታው፣ ከዚያማ በቃ ጽልመት ብቻ፡፡
ራሴን እስታለሁ ብዬ ባልጠበቅም አእምሮዬ በመጨረሻ የወንድሜን ሞት ሲያምን ከዓለም የምንተነፍሰው አየር ተመጦ እንዳለቀ ተሰማው፡፡ ዘመዶቼና ጎረቤቶቼ እንድነቃ አድርገው ደጋግፈው በእግሮቼ አቁመውኝ የዳማሲንን አስከሬን ወደ ሣጥን አስገብተን ደግሞ የእማማን ፍለጋ ይዘነው እንዞር ገባን፡፡ አንዴ ለጉድ ጎልቶኝ! ሰዎቹ በዚህን ሰዓት የሰውነቷ ክፍሎች አይለዩም፤ ደግሞ በጣም አፈር ስለበላው እጅጉን ያበሳጭሻል ብለው አስቸገሩኝ፡፡ የሕመሜ ወሰን ላይ ስለደረስኩም ተስማማሁ፡፡ ምንም ያህል ልቤን ባጠነክረውም እናቴን በእንደዚያ አይነቱ ሁኔታ ማየቱ ለአፍቃሪ ዓይኖቼ መቻል ከሚችሉት በላይ ይሆንባቸዋል፡፡ አስከሬኗን ሳላይ ለመቅበር ተስማማሁ፡፡ ይልቅ በሕይወት እንደነበረችው ባስታውሳት ይሻለኛል … ዘላለም በልቤና በህልሞቼ እንደምትኖረው ሁሉ፡፡
አንድ ሰው እናቴ ባለችበት ሣጥን ክዳን ላይ ሚስማር ሲመታ የጓደኞቼንና የዘመዶቼን ፊቶች አየሁ - የተሸበሩ ሕይወቶችን የሚያንጸባርቁ የተሸበሩ ፊቶች፡፡


ሶስቱ ልጆቿ እፊቷ ሲታረዱ እንድታይ የተገደደችው የአክስቴ ልጅ፤ በሚወዳት ሚስቱና በሰባት ልጆቹ ሞት ከበፊቱ ማንነቱ ጥላው ብቻ የቀረው በአንድ ወቅት የሚንቀለቀል ቁርጠኝነት የነበረው አጎቴ ፖልና ባሎቻቸው ሞተውባቸው ልጆቻቸው መዳን በማይችሉበት ሁኔታ ታመው ያሉት አክስቶቼ ሁሉ ቆመዋል፡፡ ከተራራ የከበደ ሐዘን የተሸከሙ ፍጡራን!
በመንደሩ ላይ የወረደውን ትካዜ ሁላችንም እንጋራዋለን፣ ግን በዙሪያዬ የተሰበሰቡት ሰዎች ከኔ በላይ ብዙ ሰው እንደተነጠቁ አውቄያለሁ፡፡ እምነታቸውን አጥተዋል - በዚያም ተስፋ አጥተዋል፡፡ በእናቴና ወንድሜ አስከሬኖች ላይ አፍጥጬ አስከሬኖቻቸውን ላገኘው የማልችላቸውን አባቴና ቪያኒን አሰብኩ … አምላክንም አመሰገንኩት፡፡ ሁሉንም ባጣም እምነቴን ግን ጠብቄያለሁ፤ እሱም ያጠነክረኛል፡፡ አበርትቶኛል፤ አሁንም ሕይወት ዓላማ እንዳላት አሳውቆኛል፡፡
‹‹የት እናድርጋቸው በይ? የት እንቅበራቸው?›› እጆቹን በጽድ ሳጥኖቹ ላይ ወዲያና ወዲህ እያላወሰና እያነባ አጎቴ ፖል ጠየቀኝ፡፡
‹‹እቤት›› አልኩት፡፡ ‹‹እቤት ወስደን እናሣርፋቸው፡፡››
የእናቴንና የወንድሜን አስከሬኖች ይዘን ወደ ቤታችን ፍርሥራሽ ወሰድንና በአንድ ወቅት ሣቅና ፍቅር የሚያስተጋባበት የነበረው አንደኛው ቤት በነበረበት ስፍራ ወለል ላይ ትልቅ የመቃብር ጉድጓድ ቆፈርን፡፡ በመንደሩ ያሉ የቀሩ ምንም ቄሶች ስለሌሉ ራሳችን የደንቡን አደረግን፡፡ እማማ ትወዳቸው የነበሩ የተወሰኑ መዝሙሮች ዘመርን፤ ብዙ ጸሎትም አደረስን፡፡ እግዚአብሔርን ቤተሰቤን ወደራሱ አቅርቦ እንዲይዝልኝና ንጹሕ ነፍሶቻቸውን በገነት ባለህ እንዲልልኝ ጠየቅሁት … ከዚያም ደኅና ሁኑ አልኩ፡፡
‹‹በቃ መሄጃችን ሰዓቱ አሁን ነው ሳራ - ኪጋሊ መሄጃችን ደርሷል›› ስል ለውዷ ባልንጀራዬ፣ በማደጎ ተቀብላ ለምታኖረኝ እህቴ ብሎም አዲስ ቤተሰብ ለሰጠችኝ ለሳራ አንሾካሾክሁ፡፡
ወዲያውኑም ተመልሰን በደመና ውስጥ ገብተን ከመንደሬ በላይ ከፍ ብዬ እበር ጀመር፤ ሕይወታችንን ካጨቀዩት ሰቆቃዎች በላይ … በጣም ከፍ በማለቴም የእግዚአብሔርን ፊት መንካት የምችል መሰለኝ፡፡

ቤተሰቤ በገነት እንዳለ ማወቄ እነሱን የማጣቴን ሕመም አላቀለለልኝም፡፡ አሟሟታቸው በታሰበኝ ቁጥር ልቦናዬን የሚቆጣጠረውን ሰንካዩን ሰቀቀን ላራግፈው አልተቻለኝም፡፡ እንቅልፍ ከሚነሳኝና ቀን ከሚያስቸግረኝ ሥቃይ ለመገላገል በየምሽቱ ጸልያለሁ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ወሰደብኝ፣ ግን እንደሁሌው እግዚአብሔር ጸሎቴን ሰማኝ፡፡ በዚህ ወቅት ይህን ያደረገው እስከዚያን ጊዜ አይቻቸው ከነበሩት የተለየ ሕልም በማሳየት ነው፡፡
በቤተሰቤ ቤት ላይ በወታደራዊ ጠያራ እየበረርኩ ሳለሁ ጥቁር ደመና ከበበኝ፡፡ እማማን፣ አባባን፣ ዳማሲንንና ቪያኒን ከኔ በላይ ከፍ ብለው በሰማይ ቆመውና ጸጥታን በሚያንጸባርቅ ልዩ፣ ነጭ ብርሃን ተጥለቅልቀው ታዩኝ፡፡ ብርሃኑ የሸፈነኝን ጥቁር ጨለማ እስኪገፈው ድረስ በሰማይ ላይ ተንሠራፋ፡፡ በድንገትም እንደገና ከቤተሰቤ ጋር ተገናኘሁ፡፡ ሕልሙ በጣም እውን ስለሆነ በእጄ ተንጠራርቼ የሰውነታቸውን ሙቀትና የንክኪያቸውን ሃያልነት ተረዳሁ፡፡ በጣም ደስ ስለተሰኘሁ በአየሩ ላይ ዳንኪራ ረገጥኩ፡፡
ዳማሲን አዲስ፣ ንጹሕ፣ ምርጥ ነጭ ቲሸርትና ሰማያዊ ሱሪ ለብሷል፡፡ በደስታ በፈካ ፊት ካየኝ በኋላ ፈገግ አለ፡፡ ከኋላው እማማ፣ አባባና ቪያኒ እጅ ለእጅ ተያይዘው እኔን ሲያዩ በደስታ ፈክተው ቆመዋል፡፡ ‹‹ታዲያስ ኢማኪዩሌ፣ አሁንም አንቺን ለማስደሰት መቻላችንን ማየታችን መልካም›› አለ መልከ ቀናው ወንድሜ፡፡ ‹‹ይህን ሁሉ ጊዜ ደብቶሻል፤ ለቅሶሽን መተው አለብሽ፡፡ ያለሽበትን ድንቅ ስፍራ እስኪ እዪ … እንዴት ደስ እንዳለን አታዪም? በሥቃይ ላይ እንዳለን በማመንሽ ከቀጠልሽበት ትተነው ወደሄድነው ህመም እንድንመለስ ታስገድጅናለሽ፡፡ ምን ያህል እንደምትናፍቂን አውቃለሁ፣ ቢሆንም ግን … ተመልሰን መጥተን እንድንሰቃይ ትፈልጊያለሽ?››
‹‹አይሆንም፣ አይሆንም፣ ዳማሲን!›› ስል ጮህኩ የደስታ እንባ ከዓይኖቼ እየወረደ፡፡ ‹‹እዚህ አትምጡ! እዚያው ጠብቁኝ፤ ስመጣ ሁላችሁንም አገኛችኋለሁ፡፡ አምላክ በዚህ ሕይወቴ በቃሽ ሲለኝ ወደናንተ እመጣለሁ፡፡››
‹‹እዚሁ እንጠብቅሻለን እህት ዓለም፡፡ አሁን ልብሽን ፈውሺ፡፡ ማፍቀር አለብሽ፤ በኛ ላይ የተላለፉትንም መማር አለብሽ፡፡››
የቤተሰቤ አባላት ቀስ በቀስ ወደ ሰማይ እያፈገፈጉ መንግሥተ-ሰማያት ውስጥ ተደበቁ፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላም በቤቴ ላይ እያንዣበብኩ ቢሆንም ከጨለማው ደመናና ከምበርበትም ጠያራ ወጥቻለሁ፡፡ በመንደሬ ላይ እንደ ወፍ በረርኩባት፤ በቄሱ ቤትና በፈረንሳዮቹ ምሽግ ላይ፣ በውድ ሀገሬ ሁሉም ወንዞችና ፏፏቴዎች በላይ
- በሩዋንዳ ላይ አንዣበብኩባት፡፡
ከሐዘንና ከመሬት ስበት በጣም ነጻ ስለወጣሁ በደስታ መዘመር ጀመርኩ፡፡ ከልቤ ዘመርኩ፤ ቃላቱ በደስታ ከአፌ ጎረፉ፡፡ መዝሙሩ ‹‹ምዋሚ ሺሚርዋ›› የሚል ሲሆን በኪንያሩዋንዳ ‹‹እግዚአብሔር ሆይ ከአእምሮ በላይ ለሆነው ፍቅርህ አመሰግናለሁ›› ማለት ነው፡፡
እኩለ ሌሊት ስለሆነ ዝማሬዬ ቤተሰቡን በሙሉ ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው፡፡ የሳራ እናት ወይ አመማት ወይ ትኩሳት ያዛት ብለው በመሥጋት ወደ ክፍሌ ሲሮጡ መጡ፡፡
ከዚያን ምሽት በኋላ እንባዬ መድረቅና ሕመሜም መቀነስ ጀመረ፡፡ ስለቤተሰቤ ዕጣፈንታ አስቤ ድጋሚ በፍጹም አልተሰቃየሁም፡፡ ሁሌም አለቅስና እናፍቃቸዋለሁ ብዬ ባምንም አንዲትም ቀን ስላዩት ሥቃይ ስጨነቅ አላሳልፍም፡፡ አምላክ የቤተሰቤ አባላት ሥቃይ ካለበት ስፍራ ርቀው ወዲያ ማዶ እንዳሉ በሕልም አሳየኝ፡፡ ወደ መንደሬ ሌላ ጉዞ ማድረግ እንዳለብኝም አሳይቶኛል፡፡

ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ኮሎኔል ጉዬ እንደገና ወደ ሀገር ቤት የመሄድ ዕድል ሰጡኝ፣ በዚህ ጊዜ ግን የነዳነው በሀገር አቋራጭ ነው፡፡ የአገሬ መልከዓ-ምድር በዚያን ወቅት አላበሳጨኝም፤ እንዲያውም በዙሪያዬ ባሉት ትዕይንቶችና ድምጾች ሰበብ በሚነሳሱት ትኩስ ትዝታዎቼ ተነቃቅቻለሁ፡፡ በእናቴ የሙዝ ልማትና በተራራ ጥግ
👍2
በሚገኘው የአባቴ የቡና ማሳ ውስጥ ከጓደኞቼ ጋር ተዘዋውሬያለሁ፡፡ ለአክስቶቼ ዱር መሄድ ካልፈሩ የአትክልቶቹን አላባ እንዲጠቀሙበትና ኑሯቸውን እንዲደጉሙበት ነግሬያቸዋለሁ፡፡
አክስቴ ዣኒ ስለመፍራቱ እንዳላስብ ነገረችኝ፡ ጠመንጃ በቅርቡ ስለምታገኝ አተኳኮስም ትማራለች፡፡ ‹‹ለወደፊቱማ ዝግጁ እሆናለሁ›› አለች፡፡ ለወደፊቱ በማለት፣ በጣም ተንፍሼ አሰብኩ፡፡
እማማንና ዳማሲንን ለመጠየቅ ወደፈራረሰው ቤታችን አቀናሁ፡፡ በመቃብሮቻቸው አጠገብ ተንበርክኬ ለመጨረሻ ጊዜ ካየኋቸው በኋላ የተከሰተውን ሁሉ ነገርኳቸው፡፡ በተመድ ስላገኘሁት ሥራና ወደፊት ምን ለማድረግ እንዳሰብኩ ነገርኳቸው፡፡ ፊቶቻቸውን ማየትና ድምጾቻቸውን መስማት ስለናፈቀኝ አለቀስኩ፡፡
የዚያን ሰዓቱ እንባዬ ግን የነጻነት እንጂ የሰቆቃ አይደለም፡፡
ከዚያ በኋላ ላደርግ የመጣሁትን ነገር ማድረጊያው ጊዜ ደረሰ፡፡

ከሰዓት በኋላ ዘግየት ብዬ ማረሚያ ቤት ስደርስ አዲሱ የኪቡዬ አስተዳዳሪ ሴማና ተቀበለኝ፡፡ ሴማና ከዘር ፍጅቱ በፊት መምህር፣ የአባቴ የሥራ ባልደረባና ጥሩ ጓደኛ ሲሆን፤ እኔ ደግሞ እንደ አጎቴ አየው ነበር፡፡ ከስድስት ልጆቹ አራቱ በእርዱ አልቀዋል፡፡ ስለሆነም እኔ ልጆቹ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሆኑ እምነቱ እንዲኖረው ነገርኩት፡፡
‹‹ዓለም ምን ያህል እንደተቀየረች ማየት ቻልኳ፤ ልጆች ወላጆቻቸውን ያጽናናሉ›› በማለት በሆድ ብሶት መለሰልኝ፡፡
እንደ አስተዳዳሪነቱ ሴማና አካባቢያችንን ያሸበሩትን ገዳዮች የማሰሩንና በቁጥጥር ስር የማቆየቱን ሥራ የሚሠራ ትልቅ ዐቅም ያካበተ ፖለቲከኛ ሆኗል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢንተርሃምዌዎችን ስለመረመረ ከማንም በተሻለ የትኛው ገዳይ ማንን እንደገደለ ያውቃል፡፡
በመሆኑም ለምን ጉዳይ እንደመጣሁ አውቋል፡፡ ‹‹እናትሽንና ዳማሲንን የገደለውን ቡድን የመራውን ማግኘት ትፈልጊያለሽ?››
‹‹አዎን ጋሼ፣ እፈልጋሁ፡፡››
በጽሕፈት ቤቱ መስኮት ስከታተል ሴማና ግቢውን አቋርጦ ወደ ወንጀለኞች ማቆያው ክፍል ደርሶ ሲመለስ አየሁት፡፡ ሁሉ ነገሩ የቆሻሸሸና የሚያነክስ ሽማግሌ እየነዳ ተመለሰ፡፡ እየቀረቡኝ ሲመጡም ወዲያውኑ ሰውዬውን ስላወቅሁት በድንገት ወደ ሰማይ ዘለልኩ፡፡ ይህ የተሳካለት ሁቱ ነጋዴ አያ ፌሊሲን ነው፡፡ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስማር ከልጆቹ ጋር እጫወት ነበር፡፡ ረጅም፣ መልከ መልካም፣ ሁሌ ውድ ሱፍ ልብሶች የሚለብስና ለንጽሕናው ጥንቁቅ ነበር፡፡ ገዳዮቹ ወደ ቄሱ ቤት መጥተው ሲፈልጉኝ ስሜን እየተጣራ ሲፈልገኝ ድምጹን ስለሰማሁት ተንቀጠቀጥኩ፡፡ ፌሊሲን ሊገድለኝ ሲያድነኝ ሰንብቷል፡፡
ሴማና ፌሊሲንን ወዳለሁበት ክፍል ሲገፈተረው በጉልበቱ ወደቀ፡፡ ከወለሉ ቀና ብሎ የምጠብቀው እኔ መሆኔን ሲያስተውል አመዱ ቡን አለ፡፡ ድንገትም እይታውን ወደ ሌላ አቅጣጫ መልሶ መሬቱ ላይ አፈጠጠ፡፡
‹‹ተነሥ፣ አንተ ነፍሰ-በላ!›› ሲል ሴማና ጮኸበት፡፡ ‹‹ቆመህ ለዚህች ልጅ ቤተሰቧ ለምን እንደሞተ ንገራት፡፡ እናቷን ለምን እንደገደልክና ወንድሟን ለምን እንዳረድክ አብራራላት፡፡ ተነሥ ብያለሁ! ተነሥና ንገራት!›› ሴማና የበለጠ ጮክ ብሎ ተናገረ፤ የተጎዳው ሰውዬ ግን ተነሥቶ ዓይኔን ማየቱ በጣም አሸማቆት እንደተንበረከከና እንዳቀረቀረ ቀረ፡፡ ቅስሙ ተሰብሯል፡፡
አዳፋ ልብሱ በመነመነው ሰውነቱ ላይ ተቀዳዷል፡፡ ቆዳው ከመገርጣቱ፣ ከመቆሳሰሉና ከመሸብሸቡም በላይ ዓይኖቹን አንዳች ነገር አድርቶባቸዋል፡፡ ፊቱ በአዳፋና ጎፍላላ ፂም ተሸፍኗል፡፡ ጫማ የናፈቃቸው እግሮቹም ቆሳስለዋል፡፡ ሁኔታውን ሳይ አነባሁ፡፡ ፌሊሲን ዲያብሎስ ልቡ ውስጥ እንዲገባ ፈቅዷል፤ ርኩሰትም ሕይወቱን እንደ ነቀርሳ ሆኖ አበላሽቶበታል፡፡ አሁን በሥቃይና በጸጸት እንዲኖር የተፈረደበት የተጠቂዎቹ ተጠቂ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ሰውዬ የተሰማኝ የመራራት ስሜት ጎዳኝ፡፡
‹‹የወላጆችሽን ቤት ዘርፏል፤ የማሳቸውን አላባ ጠቅሎ ወስዷል፣ ኢማኪዩሌ፡፡ የአባትሽን የእርሻ ማሽኖች እቤቱ አግኝተናቸዋል፣ አላገኘንም እንዴ?›› ሴማና ፌሊሲን ላይ ጮኸበት፡፡ ‹‹ሮዝንና ዳማሲንን ከገደለ በኋላ አንቺን መፈለጉን ቀጥሎ ነበር … ንብረትሽን ለመውሰድ ሲል አንቺ እንድትሞቺለት ፈልጎ ነበር፡፡ አልፈለግህም አንት አሳማ?›› ሴማና በድጋሚ አምባረቀበት፡፡
ድንገት ሳላስበው ሴማና ሲያየኝ ጊዜ ወደ ውስጥ በረጅሙ ተንፍሼ ወደ ኋላዬ ሸሸት አልኩ፡፡ ሴማና ባሳየሁት ምላሽ ተደናግጦና በፊቴ ላይ በሚወርደው እንባ ግራ ተጋብቶ አየኝ፡፡ ፌሊሲንን የሸሚዙን ኮሌታ ይዞ በጡጫ መታው፡፡ ‹‹ምን የምትላት አለህ? ምን የምትነግራት አለህ ለኢማኪዩሌ?››
ፌሊሲን አለቀሰ፡፡ ሐፍረቱ ተሰማኝ፡፡ ለአፍታ ቀና ብሎ ቢያየኝ ዓይኖቻችን ተገጣጠሙ፡፡ ተንጠራርቼ እጁን ነካሁና ልናገር የመጣሁበትን በፍጥነት ተናገርኩ፡፡
‹‹ምሬሃለሁ›› ስለው ልቤን ወዲያውኑ ቀለል አለኝ፡፡ ሴማና ወንጀለኛውን በሩን አሳልፎ ወደ ግቢው ከማስወጣቱ በፊት በፌሊሲን ትከሻ የነበረው ጭንቀት ሲቀል አየሁት፡፡ ከዚያም ሁለት ወታደሮች ፌሊሲንን አንጠልጥለው ወደ ማረፊያ ክፍሉ እየጎተቱ ወሰዱት፡፡ ሴማና ሲመለስ እንደተናደደብኝ አየሁ፡፡
‹‹ምን ማለትሽ ነው፣ ኢማኪዩሌ? ይህ እኮ ቤተሰብሽን የጨረሰው ሰውዬ ነው፡፡ ያመጣሁት እኮ በጥያቄ እንድታፋጥጪው … ከፈለግሽ እንድትተፊበት ነበር፡፡ ግን አንቺ ማርሽው! እንዴት እንደዚያ ታደርጊያለሽ? ለምን ማርሽው?›› እውነቱን ነገርኩት፡ ‹‹የምሰጠው ነገር ምኅረት ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ ››


💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍1
አትሮኖስ pinned «#ሁቱትሲ ፡ ፡ #ምዕራፍ_አስራ_ሰባት ፡ ፡ #የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች ፡ #ትርጉም_በመዝምር_ግርማ ፡ ፡ #ሙታኑን_ስቀብር ፡ ፡ ‹‹ወላጆችሽ የት ነው የሚኖሩት?›› ይህ ጥያቄ በተመድ ሥራዬን ከጀመርኩ ከጥቂት ወራት በኋላ የቀረበልኝ፡፡ ‹‹ልቤ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በሕይወት የሉም›› በማለት በትዕግሥት መለስኩ፡፡ ‹‹በዘር ፍጅቱ ተገድለዋል፡፡›› የተመድ ሰቆቃዬን…»
#እጠብቅሻለው

ዝምታሽ ሲበዛ
እንቢታ እንደሆነ ለኔ ቢጠባኝም
ማፍቀሬን ከልቤ
መሆኑን ባታምኚም
ብዙም አይደንቀኝም
ብቻ የኔ ልዕልት. . .
ላንቺ መፈጠሬን
ዘግይተሽ ስታውቂ
ማፍቀሬን ተረድተሽ
ኋላ ስትቆጪ
ሰማይ ቤትም ቢሆን
ልብሽ ከፈለገኝ
ተስፋዬ ነሽና መልሱን እንድትኘግሪኝ።
#ሴት_እና_የነገር_ቱባ


#በሕይወት_እምሻው


ቁርሳችንን ለኮፍ ለኮፍ አድርገን ለመውጣት እየተጣደፍን ነው ያለ ቅጥ ረፍዶብናል፡፡

“ብርድ ነው ፀሐይ..? እስቲ ውጣና ዕይልኝ!” አልኩት፡፡ “ሹራብ ልልበስ ሸሚዝ?” በሚል ከተመሣቀለው ቁምሣጥን ልብስ ለመምረጥ
እየተጣደፍኩ፡፡

በቁሙ፧ በግማሽ ልብ ቴሌቪዥን እያየ የሚጠብቀኝ ባሌ፣ መልስ አልሰጠኝም፡

“በረከት!” አልኩት እየጮኽኩ፡፡

“ወ.. ይ...” አለና ከሲ ኤን ኤንዋ ዜና አንባቢ ዐይነን አንስቶ እኔ
ላይ አሳረፈ፡፡

“አትሰማኝም እንዴ?”

“አልሰማሁም...ምን አልሽኝ....?”

“ወይ ጉዴ...! ብርድ ነው ፀሐይ... ውጣና ዕይልኝ... ልብስ እንድመርጥ...”

“ወይ ቆንጂት!... ገና አልለበስሽም እንዴ... ቶሎ ቶሎ በይ እንጂ አለኝ እንደ ነገሩ እያየኝ፡፡

“ወየው.... ከላይ ብቻ ነው የቀረኝ... ዕይልኝ ይልቅ....”

ተበሳጭቻለሁ፡፡

በግብር ይውጣ አካሄድ ወጣና መለስ ብሎ፣ “ደመና ነው... ሹራብ
ያዢ!” አለኝ፡፡

ይሄን ጊዜ ! ከሱሪዬ ጋር የሚሄድ ሹራብ ፍለጋ ቁምሳጥኔን ማተራመስ ጀመርኩ፡፡

“እረ ቆንጂት በፈጠረሽ እንውጣ...! ይቺ ዐሥር ደቂቃ ካለፈች
ታውቂያለሽ የታክሲ ሰልፉ መከራ ነው” አለኝ ቴሌቪዥኑን እያጠፋ፡፡

ሹራብ ፍለጋዬን አቆምኩና ዞር ብዬ ዐየሁት፡፡

ደግሞ ልንጨቃጨቅ ነው፡፡

አሁን አሁን ከምንም ነገር በላይ አብዝተን የምናደርገው ነገር፣
መጨቃጨቅ ነው፡፡

ስለ አለባበሴ እንጨቀጨቃሰን፡፡

ስለ ከጓደኞቹ ጋር ማምሸቱ እንጨቃጨቃለን፡፡

ስለ ገንዘብ አያያዜ እንጨቃጨቃለን፡፡

ስለ ልጆቻችን ጠባይ እንጨቃጨቃለን፡፡

ስለ እናቱ እኔን አለመውደድ ጉዳይ እንጨቃጨቃለን፡፡

ስለኔ ታናሽ ወንድም መበላሸት እንጨቃጨቃለን፡፡

ስለምንም ነገር እንጨቃጨቃለን፡፡

ሹራብ ነው የቀረኝ... ታገሰኝ..." ኣልኩት፤ “ዋ ሌላ ነገር ተናገረኝና
ጉድ ይፈላል” በሚል ዓይነት ድምፅ፡፡

ግን ሌላ ነገር ተናገረኝ፡፡

“ስንት ሰዐት እታገስሻለሁ....? ልብስ ለመልበስ አንድ ሰዓት ሊያውም እንዲህ እረፍዶ?”

አሁን በደንብ ልንጨቃጨቅ ነው፡፡

በኔ በረፈደ ሰዐት ላይ ልብስ ለመልበስ መቆየት መነሻነት የተጀመረው ጭቅጭቅ መዳረሻው የት እንደሆነ አላውቅም..
ጭቅጭቃችን የራሱ ቦይ አለው፡፡ ራሱ እየቀደደ የሚፈስበት ቦይ::
ከቀበና ወንዝ ተነስቶ ሜዲትራኒያን የሚገባበት የራሱ ረጅ....ም....ቦይ፡፡

“አንድ ሰዐት አልፈጀብኝም! አታጋንን፤ ማጋነን ስትወድ "አልኩት፣ ሰማያዊውን ሹራቤን አውጥቼ እየለበስኩ፡፡
“እኔው ነኝ አጋናኙ...?” አለኝ ደክሞት ውሎ እንደመጣ ሰው ሶፋው ላይ ተመልሶ እየተቀመጠ፡፡

“ምን ማለት ነው እኔው ነኝ አጋናኙ..? አንቺ ታጋንኛለሽ ለማለት ነው...?” አልኩት ገንፈል ብዬ፡፡

ዝም አለ፡፡

በአሸናፊነት መንፈስ ሹራቤን ለብሼ የቁምሳጥኑ መስታወት ጋር
ሄጄ ከሱሪዬ ጋር ያለውን ቅንጅት አየሁ፡፡

አያምርም፡፡

ሮዙን ሹራብ ባደርግ ይሻለኛል፡፡

ሰማያዊውን ሹራብ አውልቄ አልጋ ላይ ጣልኩና ሮዙን ሹራብ መፈለግ ስጀምር የሆነ ነገር ሲል ሰማሁት፡፡

“ምን አልክ?”

“ምንም አላልኩም ቆንጂት ”
“ለምን ምንም አላልኩም ትላለህ ...? የሆነ ነገር ስትል
አልሰማሁህም አሁን...?” ወደ ሳሎን መጥቼ አፈጠጥኩበት፡፡

“ምንም አላልኩም.... ....... በይ ይልቅ ፤ ትናንት ብፈልገው አጣሁት... የእዚህ ሪሞት አንዱ ባትሪ የት ገባ...? ወድቆ ጠፍቷል” አለኝ፣ መክደኛ የሌለውን የቴሌቪዥናችንን ሪሞት ኮንትሮል
አገላብጦ እያየ፡፡

“ምን እኔን ትጠይቀኛለህ... አንተ ነህ ተሰክተህበት የምትውልበት
ቲቪውን፤ ...ራስህ አትፈልገውም...?” ሹራቤን ፍለጋ እየተመለስኩ መለስኩ፡፡

“እኔ የት እንዳለ ባውቅ አንቺን ምን አስጠየቀኝ?”

“እንጃ! ምናልባት ለሁሉ ነገር ጥፋተኛ የምታደርገው እኔን ስለሆነ”

“ለሁሉ ነገር?”

አዎ! ....ቲቪ ተበላሸ... ቆንጂት ምን አረግሽው...? የቤቱ ግድግዳ
ለቀቀ ፤ ቆንጂት ምን ስትሰሪ እንዲህ ሆነ..? የልጆቹ ፀባይ ተበላሽ
ቆንጂት አንቺ እኮ ነሽ እያቀበጥሻቸው...? አሁን ደግሞ ሚጢጢ ባትሪ ጠፋ እኔኑ ጥፋተኛ...”

ሳላሰበው ሁለመናዬ ሲግል እየተሰማኝ ተናገርኩ፡፡

“በ...ይ ተይው እገዛለሁ... ሆሆ!” ብሎ ሪሞት ኮንትሮሉን ጠረጴዛው ላይ ሲወረውር ተሰማኝ፡፡

ግዛ አንተ ምን አለብህ...! ሽሮ በርበሬ ብዬ የምሣቀቀው እኔ...
አንተማ መዥረጥ አድርገህ ያሻህን ትገዛለህ..." አልኩ።ግለቴ ሳይበርድ፤ ሮዙን ሹራብ እያደረግኩ፡፡

“ታዲያ ከጠፋ ምን አድርግ ትይኛለሽ...? ደሞ ለባትሪ...”

“ደሞ ለዚች እያልክ ነው ገንዘብ የምታባክነው፡፡ ገንዘብ በትንሹ
ካልተቆጠበ ብዙ ይሆናል...?”

“ደሞ አሁን ገንዘብ አባካኝ ሆንኩ..!.”

ድምፁ ይንቀጠቀጣል፡፡ ድምፁ ከተንቀጠቀጠ ተናዷል ማለት ነው፡፡

“አይ ቆጠብክልኝ እንጂ! ቆጠብክልኝ የኔ ጌታ! ይሄ በየማታው የምትጋተው ድራፍት እንኳን ቢደማመር የልጆቹን አስጠኚ የወር ደሞዝ ቀጥ አድርጎ አይችልም....?” አልኩት ድምጼን ከፍ አድርጌ ፤ ወገቤን በነገረኛ ሴት ቄንጥ ይዤ ወደ ሳሎን እየተመለስኩ፡፡

ፊቱ ቀልቷል፡፡

“በየማታው...? እኔ ነኝ በየማታው ድራፍት የምጋተው....? ከቅዳሜ
ውጪ ...ሊያውም ከሁለት ድራፍት በላይ ስጠጣ አይተሸኛል....?
ደሞ ለነገሩስ ለልጆቹ አስጠኚ ይቀጠር ስልሽ... ተወው ፤ ማቲ እየመጣ እንደፈለጋቸው ያስጠናቸዋል' ብለሽ አይደለም የተውነው እንዴ!”

እሱማ ነበር! ....የሚሆን መስሎኝ፡፡ ገንዘብም እንዲቆጠብ ብዬ .. ግን
ምስኪን ወንድሜን በሳምንት ሦስቱ ለሚመጣው እየገላመጥክ
ከቤቴ አራቅከው... አሁን እስቲ ምን አደረገህ ...? ልጆችህን በነጻ ባስጠናልህ...”

አሁን ቅድም እንደ ዋዛ የጣልኩትን የአንገት ልብሴን እየፈለግኩ
ነው፡፡

“ተይ ቆንጂት ግፍ አትናገሪ፡፡ እኔ ነኝ ወንድምሽን ከዚህ ቤት
ያራቅኩት? ራሱ አይደለም፣ ልጆቹ ማቲ ሲጋራ ሲያጨስ እያዩ እንዳይሰላሹ ምከሪው' ስልሽ ሰምቶ እዚህ ቤት አልመጣም ያለው...? እሱ ዱርዬ በሆነው ለልጆቼ ማሰቤ ነው እኔን
የሚያስወቅሰኝ!”

አሁን በማቲ መጣብኝ፡፡ የማቲ ነገር እንደማይሆንልኝ እያወቀ በጠዋቱ በማቲ መጣብኝ፡፡

“በረከት! ማቲ ዱርዬ አልሆነም... ወጣት ነው….. ሊሳሳት ይችላል...
እንደ ታላቅ ወንድም ልትመክረው ሲገባ እንደ እብድ ውሻ ከገዛ እህቱ ቤት አባረርከው... ይሄ ልክ ነው?” አልኩት የአንገት ልብሴን ፍለጋ ትቼ እያየሁት፡፡

“እህ... ተይው... አንቺ ልጄ..... ታክሲው... ይልቅ በናትሽ ለብሰሽ
ጨርሺ አሁን... እንሂድ፡፡” አሁንም ያንን ሪሞት ኮንትሮል እያገላበጠ ያያል፡፡

እንዲህ በነገር እየለበለብከኝ ምኑን ከምኑ አድርጌ ልልበስ.
ስካርፌ ጠፋብኝ” አልኩት ቀዝቀዝ ብዬ፡፡

“ራስሽ በጀመርሽው ነገር መልሰሽ እኔን... ይልቅ አሁን ጨረስሽ..
እንውጣ?” አለኝ ቦርሳውን እንስቶ እያነገተ፤

“ምነው ስታየኝ ያልጨረስኩ እመስላለሁ....?”

ያለ እቅዱ ነገረኛ ድምፄ ተመለሰ፡፡

“ደሞ ይሄ ምን ማለት ነው?”
“የለበስኩ አልመሰልኩም?... ለነገሩ ስታየኝ አይደል የምታውቀው በጠዋት
ቲቪ ላይ እያፈጠጠክ... ሦስተኛ ጡት አብቅዬ ባድርም እስከ ሁለት ወር የሚታይህ አይመስለኝም”

ሣቀ፡፡

እኔ ግን አልሣቅኩም፡፡ እየተጨቃጨቅን ሲስቅ ያናድደኛል።

“ሶስተኛ ጡት...? ምን?” አለኝ አሁንም እየሣቀ፡፡
👍1
ሣቅ አንተ ምን አለብህ! ...እኔ ነኝ የማውቀው... እኔን ማየት ከተውክ እኮ ቆየህ አንተ”

“ቆንጂት.. እንዴት ነው ደሞ ማየት...?”

“ማየት ነዋ ! እንደ ድሮው... እንደ ወንድ፡፡ አይ ወንድ... “ማታ ልሙትልሽ ጠዋት ልግደልሽ አለች ያቺ ዘፋኝ.... ሰለቸሁህ ...በረከት አታየኝም!” ሆድ እየባሰኝ ተናገርኩ፡፡

“ዐይሻለሁ... አሁን እያየሁሽ ኣይደለም?” አለኝ፣ እንደታዘዘ ከላይ
እስከታች በዐይኑ ከከተተኝ በኋላ።

“ድንቄም ማየት እቴ!... እንዴት ነኝ አሁን? ዕየኝ እስቲ... 360ኛ እየተሽከረከርኩ ጠየቅኩት፡፡

ምንም ሳይል እንደገና ዐየኝና ፤

“እ... የላዩ ጥሩ ነው ፀሐይ ወጥቶ በጣም ካልሞቀሽ... ግን ይሄ...
እ... እንይ...! ይሄ የእህትሽ ሱሪ አይደለም እንዴ...?” ከወገቤ በታች በታላቅ አትኩሮት እያየኝ ጠየቀኝ፡፡

እንደ አዲስ ተበሳጨሁ፡፡

“ወይ ጉድ! ይሄ ታየህ?”

“ምነው... ልክ አይደለሁ..?”

ደንግጧል፡፡

“ልክ ነህ አባቴl.ልክ ነህ የኔ ጌታl... የኔ አስተዋይ" አልኩ አሸየጮኹ፡፡

“እህ... ትንሽ ጠቦሻል መሰለኝ...."

ንግግሬ የስላቅ መሆኑ የገባው አልመሰለኝም፡፡

በጣም ፤ በጣም ፤ በጣም ተናደድኩ፡፡
“ወፈርሽ ለማለት ማሽሞርህ ነው..?” አልኩት በቆመበት እየገላመጥኩት፤ እንደ ኳስ አንጥሬ ብለጋው እየተመኘሁ፡፡

እንደዛ ማለቴ አይደለም.... እሷ ቀጭን ስለሆነች የሷ ልብስ ላንቺ..”

ወይ ጉድ! ሰፍቷት ሰጥታኝ ነው አረ ቆይ! የትዕግስት መሆኑን በምን አወቅህ ግን...? ካለ አንድ ቀንም አርጋው አልመጣች እዚህ ቤት...” .

እንጃ ቀይ ስለሆነ ዓይኔ ገብቶ ይሆናል እንግዲህ ... እንሂድ እንጂ”
አላ ቦርሳውን እያስተካከለና ወደ በረንዳው እየተራመደ፡፡

ተከተልኩት፡፡

“ቀይ ስለሆነች ዐይኔ ገባች በል እንጂ..ባለጌ!” አልኩት፡፡

“ምን አልሽ...?” አለኝ፡፡

“ገብቶሃል”

“ኧረ ተይ ተይ! ጠምዝዘሽ ጠምዝዘሽ...”

“ምንድነው የምጠመዝዘው ...ፊት ለፊት እየተናገርክ...! ሌላ ነገር ካላሰብክ ...አሁን የእህቴን ሱሪ ምን አሳየህ!”

“...እኔን በእህትሽ...? በስማም... ዛሬስ የሰፈረብሽ ባለቀንዱ ነው...
እኔን በእህትሽ....? ሊያውም በታናሽ እህትሽ...?”

“ምነው... ታላቄ ነበር ያማረችህ...? ሮማንን ፈለግክ ደሞ!”

“በስመ አብ... ኧረ አንቺ ምነው ዛሬ!”
“ድሮም አውቀው ነበር ባክህ... አንሻፈህ ስታያት.... ባለጌ

ልክ ይሄን ስለው የተቋጠረ ምሳ እቃ ይዛ ወደ እኔ የምትመጣው
ሠራተኛችንን አይቼ የድምፄን ከፍ ማለት ሳስብ ደንገጥ አልኩ።

“አንቺ .....አሁንስ በዛ.. ጠነዛ... በጠዋቱ... በስመአብ! በይ እኔ
ልሂድ...”

ሂድ...የለመደብህን...ሂያጅ መሆንህንማ ዐውቃለሁ” አልኩ ድምጼን ለሱ እንዲደርስ ከፍ፣ ለሠራተኛዬ እንዳይደርስ ዝቅ አድርጌ፡፡

እኔ የምሳ እቃዩን በሌላ ኮተት ወደ ተሞላው ቦርሳዬ ለማስገባት
ስታገል ጥሎኝ ሄደ፡፡

ስወጣ የለም፡፡

ያለ ሰልፍ ታክሲ አግኝቶ መሆን አለበት፡፡
እንደተንጨረጨርኩ፣ እየተከፈተ ያስቸገረኝ የጠበበኝን የቀጭኗ
እህቴን ቀይ ሱሪ ዚፕ ወደ ላይ ለመመለስ ስታገልና ቦርጬነሸ እና በረከትን ስራገም ቀኑ አለቀ፡፡

ማታ ቀድሜው ገባሁና በርዝመቱና ጥልቀቱ ጊነስ ላይ ሊመዘገብ
የሚችል ታላቅ ኩርፊያ አኩርፌ ጠበቅኩት፡፡

ከዓመታት የነገር ቱባ አተራተር ልምዴ እንደማውቀው ፣ በረከት
እንደ ጠዋቱ ያለ ጭቅጭቅ በተጨቃጨቅን ዕለት እንዲህ አኩርፌ
ስጠብቀው ፤ ዝምታውና ግልምጫው ከአቅሙ በላይ ሲሆን ፤

ለልጆቹ ሲል፣ ለቤቱ ሰላም ሲል፣ “ቆንጅትዬ...! እሺ በቃ ይቅርታ የኔ ጥፋት ነው...” ይልና ሠርቶ ለተቀጣበትም ፤ ሣይሰራ ስተፈረደበትም ፤ ሠርተሃል ተብሎ ላልገባውና ለተገረፈበት
ኃጥያትም ይቅርታ ጠይቆኝ እንታረቃለን፡፡

ስለዚህ ለዚሁ ተዘጋጅቼ ጠበቀኩት፡፡

መጣ፡፡

ይቅርታ ጠየቀኝ፡፡

ታረቅን፡፡

የእርቃችን ጨዋታ ጣእሙ ሳያልቅ፣ አልጋ ላይ እንደተዘረጋን እናቱ ደወሉ፡፡
እናቱ ከባድ የጭቅጭቅ ማገዶ እንደሚሆኑ ስለሚያውቅ ኣጣድፎ
አነጋገራቸውና ስልኩን ዘጋ፡፡

“ምነው ከመሸ ደወሉ... ምን አሉህ?” አልኩት ተነስቼ ጋቢ እየደረብኩ፡፡

“ምንም...! ለሰላምታ ነው... ስላም ብላሻለች” ድምጹ ውስጥ ሰቀቀን
አለ፡፡

“አይ በረከት... ለምን ትዋሻለህ...? አሁን የአንተ እናት እኔን ሰላም
ለማለት ሲደውሉ ታየኝ! ያንተና የሳቸው ሚስጥር መቼም አያልቅም” አልኩት ጸጉሬን ለመጠቅለል ቢጎዲኖቼን ከመሳቢያ ውስጥ እያወጣጣሁ፡፡

ዐይን ዐይኔን አየኝና፣ “እንደሱ አይደለም፡፡ ጠፋች ደህና ናት ወይ....
ሥራ በዛባት አይደል.... ሠራተኛም ሳይኖራት...... ላንተና ለልጆቹ
ምግብስ መሥሪያ ሰዐት አገኘች ወይ... ምናምን ነው ያለችው ...
አለኝ በተኛበት፡፡

ቢጎዲኑን ጣል አደርጌ ዞር ብዬ ዐየሁትና፤

“ሠራተኛ ሳይኖራት አሉህ?” አልኩት፡፡

“አዎ... ያው ላንቺ አስባ"

አላስጨረስኩትም፧

“እኮ... መች አጣሁት...! ያው እኔን ነው የሚቦጭቁልህ መቼም!
በስተርጅና ሰው መቦጨቅ ....ምግብ አትሠራለትም እና ልጄ በርኀብ
አለመሞቱን ልይ ብለው ነው የደወሉት አይደል..?”

ዝም ብሎ ያየኛል፡፡

“ለምን አገልግል ተሸክመውልህ አይመጡም ነበር?” ብዬ ቀጠልኩ
እምባዬ እየመጣ፡፡ ምንም አላለም፡፡

“በረከት... እሳቸው ግን ለምንድነው እንዲህ ጥምድ ያደረጉኝ..?
ልጃቸውን አግብቼ ሰው ባደረግኩ.. የልጅ ልጅ ባሳምኩ... ንገረኝ እስቲ ምን አደርጌያቸው ነው...?”

ብስጭት እና ፍንጥር ብሎ ከአልጋው ላይ ተነሳና ጥሎኝ ወደ ሳሎን ሄደ፡፡ “በረከት...”
ተከተልኩት፡፡

💫አለቀ💫

ለአስተያየቶ @atronosebot ን ይጠቀሙ መልካም ቅዳሜ። 🙏
አትሮኖስ pinned «#ሴት_እና_የነገር_ቱባ ፡ ፡ #በሕይወት_እምሻው ፡ ፡ ቁርሳችንን ለኮፍ ለኮፍ አድርገን ለመውጣት እየተጣደፍን ነው ያለ ቅጥ ረፍዶብናል፡፡ “ብርድ ነው ፀሐይ..? እስቲ ውጣና ዕይልኝ!” አልኩት፡፡ “ሹራብ ልልበስ ሸሚዝ?” በሚል ከተመሣቀለው ቁምሣጥን ልብስ ለመምረጥ እየተጣደፍኩ፡፡ በቁሙ፧ በግማሽ ልብ ቴሌቪዥን እያየ የሚጠብቀኝ ባሌ፣ መልስ አልሰጠኝም፡ “በረከት!” አልኩት እየጮኽኩ፡፡ …»
#ስም_አነሳት


እኔስ አለኝ እናት
አባትም ባይኖረኝ
እግዜር የካስልኝ
እኔስ አለኝ እናት
ስታመም ከጐኔ
የማትርቅ ሁሌ
እኔስ አለኝ እናት
ከራሷ አሳልፋ
ለኔ የምትለፋ
እኔስ አለኝ እናት
እንባዋ ለፍቅሯ
አይቶኝ የሚያነባ
እኔስ አለኝ እናት
በደሏን ተሸክማ
ለኔ የምትደማ
አዎን ... ነበረችኝ
ፍቅሯ የገረመኝ
ስያሜ አተውላት
በሦስት ፊደላት
እናት ብቻ ብለው
ስሟን ባይቀንሱት
እናትስ ነበረኝ
በቃል የማልገልፃት
የህይወቴ ውበት
የኔነቴ ስምረት፡፡
#ሁቱትሲ


#ክፍል_አስራ_ስምንት
(የመጨረሻ ክፍል)


#የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች

#ትርጉም_በመዝምር_ግርማ

#ድህረ_ታሪክ


#አዲስ_ፍቅር_አዲስ_ሕይወት

አንድ የተሰበረ ልብ ለማገገም ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል ብሎ ለመተንበይ ያዳግታል፤ እኔ ግን ተባርኬያለሁ፡- በእግዚአብሔር እርዳታ ልቤ ከሁለት ዓመት በኋላ ሌላ ለማፍቀር ችሏል፡፡ ስድን ግን የኖርኩት ዝምተኛና አመዛዛኝ ሕይወት ነው ፡፡በተመድ እየሠራሁና ከሳራ ቤተሰብ ጋር እየኖርኩ በትርፍ ጊዜዬ ኪጋሊ በሚገኝ አንድ የእጓለማውታ ማሳደጊያ በደርዘኖች ለሚቆጠሩ የተሸበሩ ብቸኛ ልጆች በታላቅ እህትነት በማገልገል በበጎ ፈቃደኝነት ሥራ አሳለፍኩ፡፡ በፈረንሳይ ምሽግ እንከባከባቸው የነበሩትን ሁለት ወንድማማቾች ሥራዬ ብዬ ብፈልጋቸውም ላገኛቸው አልቻልኩም፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች ብዙ ፍቅር ፈላጊ ወጣቶችን አግኝቻለሁ፡፡ በ1995 መጨረሻ ከኤይማብል ጋር ተገናኘሁ፡፡ ነጻ የትምህርት ዕድል የሰጠው አካል በሩዋንዳ ሰላም ተመልሷል ብሎ ስላመነ ወደ አገሩ የሚመጣበትን የአየር መጓጓዣ ወጪ ሸፈነለት፡፡ ከመምጣቱ በፊት ብዙ ጊዜ ተጻጽፈናል፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያትም በስልክ አውርተናል፡፡ በአካል ለመገናኘት ግን በመንፈስ አልተዘጋጀንም፡፡ በአየር ማረፊያው የተገናኘንበትን ሁኔታ መቼም አልረሳውም፡፡ ልቦቻችንን ከክፉ እየጠበቅን ይመስል ስሜታችን ፈንቅሎ በመውጣት ወይም እንባ በመራጨት ፈንታ አቀባበሉ በስሱ ተከናወነ፡፡ ተቃቀፍን፣ ተሳሳምን፤ እኔ የእርሱን፣ እርሱም የኔን ህመም ላለመንካት ግን ተፈራርተን ጥንቃቄ አደረግን፡፡ ዓይን ለዓይን ለመተያየት ተፈራራን፡፡ እውነተኛ ስሜታችን ከወጣ መቆጣጠር እንደሚያቅተን አውቀን ከበደን፡፡ ማልቀስ ከጀመርን ማቆሚያ እንደሌለን ገብቶናል፡፡
ወንድሜና እኔ ከተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር ወደ ምግብ ቤት ሄደን ራት እየበላን ስለ እርሱ ትምህርትና ስለኔ ሥራ እያወራንና በጓደኞቼም ቀልዶች እየሣቅን እናስመስል ያዝን፡፡ በዚያ ሌሊት ግን ብቻዬን መኝታዬ ላይ ሆኜ እንባዬን ዘረገፍኩት፡፡ ወንድሜም እንዲሁ እንዳደረገ እርግጠኛ ነኝ፡፡
በቀጣዩ ቀን አብሮ መሆኑ ይበልጥ ቀለለን፡፡ ምንም እንኳን እርስ በርስ መተያየቱ የቤተሰባችንን አሳዛኝ ፍጻሜ አሰቃቂ ትውስታ የሚቀሰቅስብን ቢሆንም በጣም ስለምንዋደድ አንዳችን በሌላችን መኖር ምቾት ተሰምቶናል፡፡ ህመሙን ለመቋቋም የሚያግዘኝን ጥንካሬ እንዳገኘሁ ልነግረውና ላጽናናውም ፈልጌያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የማያጽናኑት ዓይነት እንዳልሆነ ወዲያውኑ ታወቀኝ፡፡ ከአፍታ በኋላም በቤተሰባችን ስለተከሰተው ሰቆቃ ላለማንሳት ሳንነጋገር እንደተስማማን ገባን፡፡ የቤተሰባችንን አባላት ሁሉ በስም ጠቃቀስን፡፡ ያኔም ቢሆን አሁንም በሕይወት እንዳሉ አድርገን ነበር ያወራነው - የምንቋቋምበት ብቸኛው መንገዳችን ይህ ነው፡፡ ለቀጣዮቹም ሁለት ዓመታት በደብዳቤና በስልክ እንደዚያው ስናደርግ ቆየን፡፡ ኤይማብል የእንስሳት ሕክምና የድህረ ምረቃ መርሃ-ግብሩን ጨርሶ ወደ ኪጋሊ ሲመለስም ሁኔታው አልተቀየረም፡፡ በየቀኑ በአካል ብንገናኝም ስለ ዘር ጭፍጨፋው የምናወራው አንድ የሆነ ሰው ላይ የተከሰተ ይመስል እንዲያው በደምሳሳው ነው፡፡ የእማማንና የዳማሲንን መቃብርም ሲያይ እንኳን እንዳካሂደው አልጠየቀኝም፤ ብቻውን ሄደ፡፡ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያው እንዲሁ አለን፡፡ ኤይማብል አሁንም የሚኖረው ኪጋሊ ነው፤ ስኬታማ ሐኪም ሲሆን ቆንጅዬ ሚስትና ልጆች አሉት፡፡ እርስ በርሳችን በጣም እንዋደዳለን፤ ከመቼውም በላይ ቅርርብ አለን፡፡ በየጊዜው እንደዋወላለን፤ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜም እንጻጻፋለን፡፡ አሁንም ቢሆን ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም ስለቤተሰባችን ስንነጋገር ‹ነበር› አንልም፡፡ ትዝታቸውን ህያው አድርጎ ማቆያ መንገዳችን ይህ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡

ብዙ ምሽቶቼን በአቅራቢያዬ ባለና ሁለተኛ ቤቴ ሆኖ በነበረው በጀስዊቶች ማእከል በጸሎትና ተመስጦ ተጠምጄ አሳልፋሁ፡፡ በተደበቅሁባቸው ረጅም ወራት ወቅት ያዳነኝን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረኝን የጠበቀ ቁርኝቴን በድጋሚ የጀመርኩት በነዚያ ርጭ ባሉ ስፍራዎች ነው፡፡
ልቤ ቀስ በቀስ ሲያገግምልኝ የወደፊቱን ሕይወቴን አብሬ የሚጋራ አንድ ልዩ የራሴ የምለው ሰውና የምንከባከበው ቤተሰብ ማለም ጀመርኩ፡፡ ግን ሐሳብ ገባኝ … ከዮሃንስ ጋር የነበረኝን ሁኔታ አስታወስኩና በቀላሉ ሊሰበር የሚችለውን ልቤን የትም ለማይደርስና በሚያሳምም መልኩ ለሚቋጭ ግንኙነት ላለመስጠት ወሰንኩ፡፡ ስለዚህ ችግር ወይም ፈተና በሚያጋጥመኝ ጊዜ ሁሉ እንደማደርገው የአምላክን እገዛ ጠየቅሁ፡፡ በገነት የሚሆን ጋብቻ ከፈለግሁ ከአምላኬ በተሻለ የሚኩለኝና የሚድረኝ ከቶ ማን ይኖራል?
መጽሐፍ ቅዱስ ከጠየቅን እንደምናገኝ ይነግረናል፤ በእርግጥም ያንን አደረግሁ፡፡ እግዚአብሔርን የማልመውን ሰው እንዲያመጣልኝ ጠየቅሁት፡፡ ራሴን ማጭበርበር አልፈልግሁም - እግዚአብሔር እንዲልክልኝ የምፈልገው ሰው ምን ዓይነት እንደሆነ በጣም ግልጽ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ስለሆነም ወረቀት ይዤ ተቀመጥኩና ላገባው የምፈልገውን ሰው ፊት ነደፍኩ፡፡ ከዚያም ቁመቱንና ሌሎቹን ገጽታዎቹን ዘረዘርኩ፡፡ ጠንካራ ማንነትና ምቹ ስብዕና ያለው፣ ደግ፣ አፍቃሪና ርህሩህ፣ ተጨዋች፣ ምግባረመልካም፣ ማንነቴን የሚወድልኝ፣ እንደኔ ልጆችን የሚያፈቅርና ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ይሰጠኝ ዘንድ ጠየቅሁ፡፡
ለእግዚአብሔር ቀን አልቆረጥኩለትም፡፡ በዘር፣ በዜግነት ወይንም የቆዳ ቀለም ላይም ምንም ገደብ አልጣልኩ፡፡ በዓለም ላይ ከአምስት ቢሊየን በላይ ሰዎች እንደመኖራቸው - ጌታዬ የሕይወቴን አጋር የሚልክበትና እኔም የምጠብቅበት አግባብ ያለው የቆይታ ጊዜ ስድስት ወራት እንዲሆን አቀድኩ፡፡ አንድ ማስጠንቀቂያንም ጨመርኩ፡- ድንግል ማርያምን እጅግ ስለምወዳት እግዚአብሔር ከእምነቴ ተመሳሳይ የሆነ ባል ቢልክልኝ እንደሚሻል ነገርኩት፡፡ በሃይማኖት ሳቢያ በትዳሬ ምንም ዓይነት ውጥረት እንደማይኖር ማረጋገጥ እንዲሁም ባሌ እግዚአብሔርን እኔ በማመልከው መልኩ እንዲያመልክ ፈለግሁ፡፡
ምን እንደምፈልግ በትክክል ካወቅሁ በኋላ ፍላጎቴን አልመው ጀመር፡፡ ጌታ የተመኘሁትን ባርኮ እንደሚሰጠኝ፣ የልቤ መሻት እንደሚሆንልኝና የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ አምኜ ሁሉንም ለእርሱ ተውኩት፡፡ ሂደቱን ለማፋጠን የአባቴን ቀይና ነጭ መቁጠሪያ አወጣሁና ባሌ እንዲመጣልኝ መጸለይ ጀመርኩ፡፡ ከሦስት ወራት በኋላም መጣልኝ፡- ከእግዚአብሔር የተላከውና የተመድ የሸለመኝ አቶ ብርያን ብላክ ከአሜሪካ ድረስ ከተፍ አለ! የነገሩ መገጣጠም ደሞ ብርያን ወደ ሀገሪቱ የመጣው የዘር ማጥፋቱን በማቀድ የተሳተፉትን ለፍርድ ለማቅረብ የሚጥረውን የተመዱን ዓለም አቀፍ የሩዋንዳ ፍርድ ቤት በማቋቋሙ ሂደት ለማገዝ ሆኖ እርፍ፡፡ ብርያን ለተመድ ለብዙ ዓመታት ስለሠራ ገዳዮቹን ፍትሃዊ ቅጣት እንዲያገኙ የሚያደርገው የተልዕኮው አካል በመሆኑ ይደሰታል፡፡ በግሌ እርሱ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ተልዕኮ በማስፈጸም ላይ ነው፡፡
ብርያንን ለመጀመሪያ ጊዜ በተመድ ግቢ ሳየው በትክክል እግዚአብሔር እንዲልክልኝ የጠየቅሁትን ሰውዬ መሰለኝ፡፡ በኋላ በአዳራሹ ሳልፈውና በዓይኖቹ የነበረውን ጥልቅ እርጋታ ሳይ እርሱ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ ግን በእግዚአብሔር እምነቴን ስላደረግሁ ብርያንን ወደኔ እንዲያመጣው ጠበቅሁት አመጣልኛ ብርያን አብረን እንድንዝናና ጋብዞኝ ግሩም ጊዜ አሳለፍን
👍2
በምሽቱ መጨረሻም ሁነኛ ጥንዶች እንደሆንንና የተቀረውን ሕይወቴን አብሬው የማሳልፍ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩ... ክርስቲያን ቢሆንልኝ! ራሴን አረጋግቼ ትልቁን ጥያቄ ጠየቅሁት፡ ‹‹ሃይማኖትህ ምንድነው?››
‹‹ክርስቲያን ነኝ፡፡››
ዘልዬ እቅፉ ውስጥ ገብቼ ‹‹አምላኬ ምስጋና ይግባህ! ወደ ሕይወቴ እንኳን በደኅና መጣህ - አብረን ኖርናታ!›› ማለት አሰኘኝ፡፡ ግን ያንን ምስኪን ሰው እንዳላስደነብረው ፈራሁ፡፡ ስለዚህ እንዲያውም እጁን ይዤ፣ ፈገግ አልኩና ‹‹እኔም ነኝ›› አልኩት፡፡

ብርያንን በዘር ጭፍጨፋው ወቅት ያለፍኩበትን ነገር ሁሉ በመንገር በፍጹም ባላጨናንቀውም ልቤ በተከፋ ቁጥር ያዳምጠኛል፡፡ ሲያስፈልገኝም ትከሻው ላይ ደገፍ ብዬ እንዳለቅስ ይፈቅድልኛል፡፡

ከሁለት ዓመታት በኋላ ብርያንና እኔ በባሕላዊ የሩዋንዳ የሰርግ ሥነ ሥርዓት ተጋብተን ከተወሰነ ጊዜም በኋላ፣ በ1998፣ ወደ አሜሪካ መጣን፡፡ በፍቅር የተሞላና መተጋገዝ ያለበት ትዳር አለን፤ እግዚአብሔር ሁለት ቆንጆ ልጆችንም ሰጥቶናል - ሴቷ ልጃችንን ኒኬይሻንና ወንዱን ብርያን ትንሹን፡፡ በየቀኑ ከእንቅልፌ ነቅቼ ሁለቱን ትናንሽ መላዕክቴን ሳይ የአምላክን ውበትና ዐቅም በፊታቸው አነባለሁ፡፡ ስለ ውድ ስጦታዎቹ ሁሉ እርሱን ማመስገኔን መቼም አላቆምም፡፡
በማናቸውም ቀንና መንገድ እግዚአብሔር የሕይወቴ አጋር ሆኖ ይቀጥላል፤ የሚያኖረኝ፣ የሚጠብቀኝ፣ የሚያረካኝ እርሱ ነው፡፡ የተሻለች ሚስት፣ እናት ብሎም ሰው ያደርገኛል፡፡ ሥራ እንዳገኝ አድርጎኛል፡፡ ልጆቼን ከወለድኩ በኋላ የሥራ ሕይወቴን መቀጠል ብፈልግም ኒው ዮርክ ከተማ ላይ ሥራ ማግኘት ኪጋሊ ላይ ከዘር ፍጅቱ በኋላ ከነበረው በላይ ፈታኝ ነው - ብዙ ሰዎች፣ ግን በጣም ጥቂት ሥራ፡፡ እግዚአብሔር እንዲመራን ጸለይኩ፤ በማንሃታን፣ በተመድ ውስጥ የምሻውን ሥራም ፈለግሁ፡፡ አንዴ የት መሥራት እንደምፈልግ ካወቅሁ በኋላ እዚያ ሥራ እንዳለኝ አድርጌ አለምኩ - ሁሌ የምጠቀመውን በጎ አሳቢነት መሳሪያ በማድረግ፡- እመኑ ታገኛላችሁ! ወደ ተመድ ድረ-ገጽ ገብቼ የሠራተኞቹን ስምና ማዕረግ የሚዘረዝረውን ክፍል አትሜ አወጣሁና ስሜን በዝርዝሩ ውስጥ ጨመርኩት፡፡ ለራሴ የውስጥ ስልክ መሥመር ሳይቀር ሰጠሁ! የስልክ መዘርዝሩን ግድግዳዬ ላይ ለጥፌ በየቀኑ አየዋለሁ፡፡ ማመልከቻ በእርግጥ ሞልቻለሁ፣ የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃ ሰነዶችን አስገብቻለሁ፣ በስልክም እየደወልኩ ከምን ደረሰልኝ እላለሁ - በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎችም ሰዎች ግን ይህንኑ ያደርጋሉ፡፡ መዘርዝሬን ማየቴንና ሥራው የኔ መሆኑን ማመኔን በመቀጠል በየቀኑ ስልኬ እስኪጮህ እጸልያለሁ፡፡ እንደጠበኩትም ከመቶዎች ሌሎች አመልካቾች ተመርጬ ቃለ መጠይቅ ከተደረገልኝ በኋላ ሥራውን በጄ አስገባሁ፡፡ የእግዚአብሔርን ኃይል በተግባር በማየቴ መገረሜን በፍጹም አላቆምኩም!
ይህ ወደ ሕይወቴ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሸጋገር ወደፊት የሚገፋፋኝ ተመሳሳይ ኃይል ነው፡፡ አምላክ ሕይወቴን ያዳናትና ነፍሴን ያተረፋት ለምክንያት ነው፡፡ ከሞት ያስቀረኝ ታሪኬን ለሌሎች አንድነግርና በተቻለኝ መጠን ለብዙ ሰዎች የፍቅሩንና የምህረቱን የማዳን ኃይል እንዳሳይ ነው፡፡
ትቻቸው የመጣኋቸውና ልረዳቸው የሚገባኝ ሰዎች አሉኝ፡፡ በዘር ፍጅቱ ተራፊዎች በተለይ በእጓለማውታ ልብ ውስጥ ተስፋን መልሶ በማምጣቱ ሂደት ለማገዝ በቻልኩት መጠን ቶሎ ቶሎ ወደ ሩዋንዳ እየተመላለስኩ ለመሥራት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት በማናቸውም ስፍራ ያሉ የዘር ፍጅትና የጦርነት ሰለባዎችን በአካል፣ በአእምሮና በመንፈስ እንዲድኑ የሚያግዝ ድርጅት በማቋቋም ላይ እገኛለሁ፡፡

የእግዚአብሔር መልዕክት ድንበር ሳይገድበው የትም ቦታና ከማንም ልብ ውስጥ ይደርሳል፡፡ ማንም በዓለም ላይ ያለ ግለሰብ የጎዳውን ማንንም ሰው እንዴት እንደሚምር መማር ይችላል - ጉዳቱ አነሰም በዛ፡፡ የዚህን እውነትነት በየቀኑ አየዋለሁ፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስም ያህል ታሪኬን ያጋራኋት አንዲት አዲስ ጓደኛዬ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የኔ ታሪክ አንድ ወቅት በጣም ትቀርበው ከነበረና ለዓመታት ካኮረፈችው አጎቷ እንድትታረቅ እንዳነሳሳት ደውላ ነገረችኝ፡፡
‹‹በጣም በመጨቃጨቃችን ስለበገንኩ ከእርሱ ጋር ሁለተኛ አልነጋገርም ብዬ ምዬ ነበር›› ስትል ምስጢሯን አጋራችኝ፡፡ ‹‹ቤተሰብሽን የገደሉትን ሰዎች እንዴት መማር እንደተቻለሽ ከሰማሁ በኋላ ግን ስልኩን አንስቼ ልደውልለት ግድ አለኝ፡፡ ይቅርታ አልጠየቅሁትም - በቀጥታ ልቤን ከፍቼ ማርኩት እንጂ፡፡ ወዲያውኑ በፊት እናወራበት በነበረው መንገድ እናወራ ጀመር - በልዩ በፍቅር፡፡ በኩርፊያ ብዙ ዓመታት እንዳመለጡን ማመን አቃተን›› አለችኝ፡፡
በተመሳሳይ አንድ ከዘር ፍጅቱ የተረፈችና በቅርቡ ወላጆቿ ሩዋንዳ ላይ የተገደሉባት ሰው በስልክ አራጆቹን ለመማር ያደረግኋቸውን ነገሮች ቅደም ተከተል እያለቀሰች ጠየቀችኝ፡፡
‹‹እነርሱን ስትምሪ በልቤ አብዳለች አልኩሽ፣ ኢማኪዩሌ - የእጃቸውን ከማግኘት ስታድኛቸው፡፡ ለ11 ዓመት በልቤ የያዝኩት ሕመምና ምሬት ሊገድለኝ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ሕይወቴ አሰቃቂ ስለነበር ከአሁን በኋላ የምኖርበት ምንም ዐቅም የለኝም፡፡ ሰዎች ግን አንቺ የቤተሰብሽን ገዳዮች ምረሽ ሕይወትሽን እንደቀጠልሽ ሲያወሩ ስሰማ ቆይቻለሁ … ደስተኛ እንደሆንሽና ባል፣ ልጆችና ሥራም እንዳለሽ! እኔም ጥላቻዬን ለመተው እንዴት እንደምችል መማር ያስፈልገኛል፡፡ እንደገና መኖር መጀመር አለብኝ፡፡ ››
በአምላክ እንዴት እንደምታመን ነገርኳት፤ ምኅረት ለማድረግና ወደ ፊት ለመራመድም ያደረግሁትን ሁሉ ተረኩላት … በዚህ መጽሐፍ ያሰፈርኩትን ነገር ሁሉ፡፡ አመስግናኝ እርሷም ገዳዮቹን እንድትምር እግዚአብሔርን እንዲያግዛት መጠየቋን ነገረችኝ፡፡

ከዚያም በአትላንታ ካቀረብኩት ንግግር በኋላ እያለቀሰች የቀረበችኝን ሴትዮ አስታውሳለሁ፡፡ በሕጻንነቷ ወላጆቿ በናዚ ጭፍጨፋ እንደተገደሉባት ነገረችኝ፡ ‹‹ዕድሜዬን ሙሉ ልቤ በንዴት ተሞልቶ ኖሯል… ሥቃይ ሲሸነቁጠኝ ኖሬያለሁ፤ ስለ ወላጆቼ ለብዙ ዓመታት አልቅሻለሁ፡፡ ያሳለፍሽውን የስቃይ ታሪክና ምኅረት ማድረግ መቻልሽን መስማቴ አነሳሳኝ፡፡ ዕድሜዬን ሙሉ ወላጆቼን የገደሉትን ሰዎች ለመማር ስጥር ኖሬያለሁ፤ አሁን ግን የማደርገው ይመስለኛል፡፡ ንዴቴን ትቼ ደስተኛ ሳልሆን አልቀርም፡፡››
በትምህርታዊ ጉባዔው ላይ የ92 ዓመት ሴት አዛውንት እጃቸውን ጠመጠሙብኝና አጥብቀው አቀፉኝ፡፡ በጣም ስሜታዊ ስለሆኑም መናገር አዳግቷቸዋል፤ ቢሆንም እንደ ምንም ድምፅ ለማውጣት ተችሏቸዋል፡፡ ቃላቸውን አልረሳውም፡- ‹‹ምኅረት ለማድረግ እጅግ ዘገየሁ ብዬ ነበር፡፡ እንዲያው አንድ ሰው አንቺ ያልሽውን ሲል ለመስማት ስጠብቅ - የማይማረውን መማር እንደሚቻል ማወቅ አስፈልጎኝ ነበር፣ ልጄ›› አሉኝ፡፡
የትውልድ ሐገሬን ሩዋንዳን በተመለከተ እያንዳንዱ ሰው የምኅረትን ትምህርት ለመቅሰም ከቻለ ሀገሬ ራሷን ማዳን እንደሚቻላት አውቃለሁ፡፡ በዘር ማጽዳቱ ወቅት የግድያ ወንጀል በመፈጸማቸው የታሰሩት በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስር እየተፈቱ ወደ ቀድሞ ከተሞቻቸውና መንደሮቻቸው እየገቡ ነው፡፡ ስለሆነም ከመቼውም ጊዜ በላይ ምኅረት የማድረጊያው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ሩዋንዳ መልሳ ገነት መሆን ትችላለች፤ ሆኖም እናት ሀገሬ እንድትድን መላው ዓለም ፍቅሩን ሊሰጣት ይገባል፡
መቼም ያለፈው አልፏል፤ በሩዋንዳ የተከሰተው ግን በሁላችንም በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ በመሆኑ መላው የሰው ዘር በዘር ማጥፋቱ ቆስሏል፡፡ ከአንዲት ልብ የሚመነጭ ፍቅር የልዩነት ዓለምን መፍጠር ይቻለዋል፡፡ በአንድ ጊዜ አንዲትን ነፍስ በማዳን ሩዋንዳን ብሎም ዓለማችንን ማዳን እንደምንችል አምናለሁ፡፡

#ምስጋና
በመጀመሪያ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን ድንቅ አባት፣ ሁነኛ ጓደኛ፣ እውነተኛው ምስጢረኛ … ብሎም አዳኜ ስለሆነልኝ ማመስገን ግድ ይለኛል፡፡ ጌታ ሆይ፣ በደጎቹም ሆነ በእጅግ መጥፎዎቹ ጊዜያት ቋሚ ባንጀራዬ እንደሆንክ አለህ፡፡ ልቦናዬን ስለከፈትክልኝና እንደገና እንዳፈቅር ስላስቻልከኝ ክበር ተመስገን፡፡ ያላንተ ምንም አይደለሁም፤ ካንተ ጋር ግን ሁሉንም ነገር ነኝ፡፡ ጌታዬ፣ ላንተ እጄን እሰጣለሁ - በሕይወቴ ሙሉ ፈቃድህ ይፈጸምልኝ፡፡ ባንተ ዱካ መራመዴን እቀጥልበታለሁ፡፡ ለተባረክሽው ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ሁሌ አለሁ ለምትዪኝ - ዘወትር ካጠገቤ እንዳለሽ ይታወቀኛል፡፡ ስለ ፍቅርና እንክብካቤሽ ያለኝን ምስጋና ግዝፈት ቃላት አይገልጹትም፡፡ ልቤን ለልብሽ አቅርቢልኝ፣ እናቴ - ሙሉ ታደርጊኛለሽ፤ እስከ ዘላለሙ እወድሻለሁ፡፡ በኪቦሆ ተገልጠሽ ከፊታችን እየመጣ ስለነበረው አደጋ ስላስጠነቀቅሽን አመሰግንሻለሁ … ምነው ሰምተንሽ ቢሆን ኖሮ!
ዶክተር ዌይን ዳየር - ከገነት የተላኩ መልአክ ነዎት፡፡ እግዚአብሔር እርስዎን ወደኔ ሕይወት ስላመጣዎት አመሰግነዋለሁ፣ መንፈሶቻችንም እርስ በርሳቸው ለዘላለሙ እንደተዋወቁ ይሰማኛል! ወደር-የለሹ ደግነትዎ፣ በዕውቀት የተገነባው ምክርዎና አባታዊ ፍቅርዎ ለእኔ እንደ አጽናፍ ዓለም ሰፊ ነው፡፡ እጅግ በርካታ ሰዎች ለምን በእርስዎ ቃል እንደተነሣሱ መገንዘብ ቀላል ነው - እርስዎ የኔ ጀግና ነዎ፣ እወድዎማለሁ፡፡ ስለተማመኑብኝና ወደ ሕልሜ ስለመሩኝ፣ እውነተኛውን የነፍሴን ጥሪም እንዳውቅ ስላደረጉኝ ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ በተጨማሪም ይህንን መጽሐፍ እውን ስላደረጉልኝና ታሪኬን እንድናገር ስላደረጉኝ ገለታ ይግባዎት፡፡ ስካይ ዳየር፡- ከአባትሽ ጋር ስላስተዋወቅሽኝ እንዴት እንደማመሰግንሽ! እወድሻለሁ!
ለሄይ ሃውስ ድንቅ ቡድን፡- ጂል ክራመር፣ ሻነን ሊትረል፣ ናንሲ ሌቪን፣ ክሪስቲ ሳሊናስ፣ ጃክዊ ክላርክ፣ ስቴሲ ስሚዝና ጃኒ ሊበራቲ - አብረዋችሁ ሲሰሩ ማስደሰታችሁ! ስለ መንገድ ጠቋሚነታችሁ፣ ትዕግሥትና ማበረታቻችሁ ገለታ ይግባችሁ፡፡
ተባባሪዬ፣ ስቲቭ ኤርዊን፣ በዚህ መጽሐፍ ዝግጅት አብረኸኝ ከሠራህ በኋላ ማንም ሰው አንተ የምታውቀኝን ያህል ያውቀኛል ብዬ አላስብም፡፡ አንተ አስገራሚ ሰው ነህ፤ አሁን ለኔ እንደ ወንድም ማለት ነህ፡፡ እንደዚህ ያለህ ጥሩ ሐኪም ስለሆንክልኝ አመሰግንሃለሁ - ስለቤተሰቤ በርካታ ግላዊ ነገሮችን ስትጠይቀኝ ያሳየኸው ሆደ-ቡቡነት ለኔ ብዙ ቁምነገር አለው፡፡ ስለ ተዓምራዊ አጆችህ አምላክን አመሰግናለሁ - ጽሑፍህ ቃላቴንና ስሜቴን ነፍስ ዘርቶባቸዋል፡፡ በተጨማሪ ሁለታችንም እናቶቻችንን ገና ሳንጠግባቸው የማጣትን ሕመም ስለምንጋራ በዚህ መጽሐፍ የገለጽኳቸውን ሁሉንም ስሜቶች ለምትረዳው ለባለቤትህ ለናታሻም ምስጋናዬ ይድረስ፡፡ ናታሻ፣ አንቺ እኮ ለኔ እንደ እህቴ ነሽ!
ቪንሴንት ካዪዡካና ኤስፔራንስ ፉንዲራ፡- ከመጀመሪያው እንዴት እንዳበረታታችሁኝና እንደተማመናችሁብኝ በጭራሽ አልረሳውም፡፡ እወዳችኋለሁ! ለዋሪያራ ምቡጋ፣ ሮበርት ማክማሆን፣ ሊላ ራሞስ፣ አና ኬሌት፣ ቢል በርክሌይና ርብቃ ማርቴንሰን ለእገዛችሁ፣ ለለገሳችሁኝ ሐሳብ፣ ለምክራችሁና አስፈላጊ ማበረታቻችሁ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ
ስማችሁን ያላነሳኋችሁ ግን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ያገዛችሁኝ በርካታ ውድ ጓደኞቼ፡- አመሰግናችኋለሁ - ሁላችሁም በልቤ አላችሁ፡፡
ተጨማሪ በጣም ልዩ ምስጋና ለሁለት እጅግ ልዩ ቄሶች፣ ለአባ ጋንዛ ዢን ባፕቲስትና ለንስሐ አባቴ ለአባ ዢን ባፕቲስት ቡጊንጎ፡፡
እጅግ ብዙ የፍቅርና የሰቆቃ ትውስታዎችንና ብዙ የማይነገር ሰቆቃ ለምጋራህ ለወንድሜ ለኤይማብል ንቱካንያግዌ፡- ሁቱትሲ ውስጥ ልትጠይቃቸው ላልቻልካቸውና እኔም መልስ ልሰጥህ ላልቻልኳቸው ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ ታገኛለህ ብዬ እመኛለሁ፡፡ አንተ በሕይወት ስላለህልኝ አምላክን አመሰግነዋለሁ - አንተ ለኔ ሁሉ ነገር ነህ፡፡ ስለ ሰዎቻችን አትጨነቅ … ደስተኞችና በገነት የኛ ልዩ ጠበቆች ናቸው! ወንድም ጋሼ፣ ግሩም ወንድም ስለሆንክልኝ ምስጋና ይግባህ - ከማስታውሰው ጊዜ ጀምሮ ላሳየኸኝ የማያሰልስ ፍቅር፣ በኔ ላይ ስላለህ እምነትና ሁልጊዜ የቤተሰባችንን ታሪክ እንድጽፈው ስላበረታታኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ባያሌው የማመሰግናት ደግሞ ሳውዳ ነች፡፡ ምራቴና ጓደኛዬ ብዬ ስጠራሽ ተባርኬያለሁ - ዘራችንን ስላበዛሽው ምስጋና ይግባሽ፡፡ እንደ ዘር ጭፍጨፋ ተራፊ የታሪክ ተጋሪነትሽ ይህ መጽሐፍ ላንቺ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ በእጅጉ እፈቅርሻለሁ፡፡ ሾንታል ንዪራሩኩንዶ፣ ኮንሶሊ ንሺምዌና ስቴላ ኡሙቶኒ፡ ትናንሽ እህቶቼ ናችሁ! በዚህ መጽሐፍ ስለተነሣሳችሁ አመሰግናችኋለሁ - ትልቅ መነሳሳትን
አምጥታችሁልኛል፡፡ ለእናንተም መሆኑን እወቁልኝ፤ ስለመዳናችሁ፡፡ ቆንጆዎቹ ልጆቼ ንኬይሻና ብርያን ትንሹ፣ ትንሹ የወንድሜ ልጅ ርያን፡- ውዶቼ፣ እንደ አበቦች ሁሉ ከፈጣሪ ዘንድ የመጣችሁ ትናንሽ መላዕክቴ ናችሁ፡፡ ለፍቅራችሁ ንጽሕናና እንደገና እንድኖር ምክንያት ስለሆናችሁኝ አመሰግናችኋለሁ፡፡ ንጹሃን ነፍሶቻችሁ በጥላቻ በማይጎዱባት ዓለም ብንኖርና የዘር ፍጅትና ጭፍጨፋ የሚሉትን ቃላትም ባትሰሟቸው ምኞቴ ነበር፡፡ ስታድጉ አያቶቻችሁንና አጎቶቻችሁን ሁቱትሲ ገጾች ውስጥ ታገኟቸዋላችሁ - ትውስታዋቻቸው በመጽሐፌ ይኖራሉ፡፡ ለአሁኑ ግን ውድ እጆቻችሁን እኔን ለማቀፍ በኔ ዙሪያ በዘረጋችሁ ቁጥር ፍቅራቸውን አስተላልፍላችኋለሁ፡፡ ሕይወቴ ናችሁ፤ እወዳችኋለሁ፡፡
በመጨረሻም፣ በእርግጠኛነት ግን መጨረሻ ላይ ያደረኩህ ከሌሎቹ አሳንሼህ አይደለም፣ ድንቁ ባሌ፣ ብርያን፣ አመሰግንሃለሁ፡፡ ከብቸኝነት አድነኸኛል፤ በእውነት ግማሽ አካሌ ነህ - ከአምላክ እኔን እንድታሟላ የተላክህ ግማሽ ገላዬ፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ስለጣርክና ታሪኬን እንድነግር ስለረዳኸኝ፤ በአያሌው ስላበረታታኸኝ፣ አምሽተህ ስለምታነብልኝና ስለምታርምልኝ አመስግኛለሁ፡፡ ለማይነጥፍ ፍቅርህና ከለላነትህ ገለታ ይግባህ፤ እግዚአብሔርን እንደ ወዳጃችን በመቀበልህም ጭምር፡፡ የኔ ፍቅር፣ በሙሉ ልቤና ነፍሴ እወድሃለሁ

#ኢማኪዩሌ

የደራስያኑ ማንነት ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ
ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ በሩዋንዳ ተወልዳ በብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ኤሌክትሮኒክና ሜካኒካል ምህንድስና አጥንታለች በ1994 በተፈጸመው ጭፍጨፋ አብዛኛዎቹን የቤተሰቧን አባላት አጥታለች፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላም ከሩዋንዳ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰዳ በኒው ዮርክ ለተባበሩት መንግሥታት መሥራት ጀመረች፡፡ ሌሎች ከዘር ማጥፋትና ከጦርነት የረጅም ጊዜ ተጽዕኖዎች ይድኑ ዘንድ ለመርዳት የኢሊባጊዛ ፋውንዴሽንን በማቋቋም ላይ ትገኛለች፡፡ ኢማኪዩሌ በሎንግ ደሴት ከባለቤቷ ከብርያን ብላክና ከልጆቿ ከኒኬይሻና ብርያን ትንሹ ጋር ትኖራለች፡፡

💫ተፈፀመ 💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም በድርሰቱ ላይ ያሎትን አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
አትሮኖስ pinned «#ሁቱትሲ ፡ ፡ #ክፍል_አስራ_ስምንት (የመጨረሻ ክፍል) ፡ ፡ #የወጣቷ_ልብ_አንጠልጣይ_ትውስታዎች ፡ #ትርጉም_በመዝምር_ግርማ ፡ #ድህረ_ታሪክ ፡ ፡ #አዲስ_ፍቅር_አዲስ_ሕይወት አንድ የተሰበረ ልብ ለማገገም ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል ብሎ ለመተንበይ ያዳግታል፤ እኔ ግን ተባርኬያለሁ፡- በእግዚአብሔር እርዳታ ልቤ ከሁለት ዓመት በኋላ ሌላ ለማፍቀር ችሏል፡፡ ስድን ግን የኖርኩት ዝምተኛና አመዛዛኝ…»