አትሮኖስ
286K subscribers
120 photos
3 videos
41 files
571 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ፍቅር_ከፈላስፋ


#ክፍል_ሀያ_ሁለት


ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ


#ፍሰሀ
===
መቼስ ያለውበትን ሁኔታ በጥቂቱም ቢሆን ግንዛቤው ይኖራችሆል ብዬ አስባለው፡፡ለዚህ ለዓላማዬ መሳካት ቁልፍ ለሆነው የፕሮፖዛል ዝግጅት ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ጠብ እርግፍ እያልኩ ነው….በሌላ ጎን ደግሞ ይህቺ ፌናን የምትባል ልጅ እራሷን የቻለች የቤት ስራ ሆናብኛለች፡፡በቃ የሆነ ነገር ሳታውቁት ከቁጥጥራችሁ ውጭ በሆነ ስሜት ስተት ብሎ ከደምስራችሁ ጋር በመስረግ በመላ ሰውነታችሁ ጋር ተዋህዶባችሁ ያውቃል…በቃ ልቤ ላይም ፤ አዕምሮዬ ውስጥም፤ እታች የእግሯቼ ጥፍሮች ላይም በእኩል መጠን ያለች ነው የሚመስለኝ..፡፡እንደእዚህ እንዴት ሆነ ……?አላውቅም….፡፡በቃ አፍቅሬያታለው፡፡ማፍቀሬን ደግሞ በውስጤ ስላፈንኩት እየተጎዳው ነው...ህመሙ ልቤ ስር እስኪሰማኝ ድረስ የተጎዳውበት ነው….
ስራውን በተመለከተ ረዳቴ ሆና በጣም እያገዘቺኝ ነው..እርዳታዋ በጣም ጠቃሚና ወሳኝ ከመሆኑ የተነሳ እራሴን እስክታዘብ ድረስ ነበር ስደመምባት የነበረው፡፡ ….አሁን ተሰርቶ በመጠናቀቅ ላይ ያለው ፕሮፖዛል እሷ ባታግዠኝ ኖሮ በራሴ እሰራው ከነበረው ጋር በሀሳቤ ሳመዛዝነው ደነግጣለው..፡፡ልጅን እንደ ቁጥር አንድ ጀግና በሚያስበው አባቴ ፊት ተዋርጄ ነበር…፡፡አሁን ግን እድሜ ለፌናን አይደለም ከአንዲት ልምድ አልባ ወጣት ሴት ጋረ ይቅርና ከማንም በስራው እድሜ ጠገብ ልምድ ያለው ሰው ጋር ተወዳድሬ ቦታውን በእጄ ማስገባት እችላለው፡፡፡የዛን ያህል በራሴ እንድተማመን አድርጋኛለች ፡፡አሁን በዛ እርግጠኛ ሆኜያለው ፤ ይገርማችሆል ፌናን ጭቅጭቆ እራሱ ሱስ ይሆንባችኃል…….አሁንም ቢሮ ጭቅጭቅ ላይ ነን፡፡ ስለዚሁ የፕሮፖዛል አንዱ ክፍል የሆነ የሰራተኛ ደሞዝን በተመለከተ እየተነጋገርን ነው…
‹‹አሁን ለሰራተኟች እየተከፈለ ያለው ደሞዝ መስተካከል አለበት ..››የሚል ሀሳብ አቀረበች
ወዲያው ነው የተቃወምኳት‹‹ትቀልጂያለሽ እንዴ……?በተመሳሳይ የስራ መደብ በመንግስት ቤት ከሚከፈላቸው ሰራተኞች ጋር ሲነፃፀር ቢያንስ አርባና ሀምሳ ፐርሰንት የእኛ ጭማሪ አለው..እና በዚህ ላይ አሁን በምናደርገው ማሻሻያ ላይ የ5 ፐርሰንት ጭማሪ ማድረጋችን በጣም ምክንያታዊና በቂ ነው ብዬ አስባለው፡፡››
‹‹አልስማማም..››አለቺኝና ንግግሯን ማብራራት ቀጠለች‹‹ይሄውልህ በመጀመሪያ ደሞዝን በተመለከተ የመንግስትን እስኬል ማነፃፀሪያ ማድረግ ትክክል አይመስለኝም፡፡››
‹‹ለምን ………..?መንግስት እንደዛ ለምን እንደሚከፍል ታውቂያለሽ ፡፡ሀገሪቱ ደሀ ስለሆነች ነው፡፡እኛም ደግሞ መክፈል ሰለቻልን ብቻ ዝም ብለን መክፈል የለብንም ….ገበያውን ማበላሸት ነው የሚሆነው››
‹‹ላስቁምህ..ይህቺ ገበያውን ማበላሸት ነው የምትለው ቀሺም ምክንያት ነች ..እዚህ ሀገር ላይ የሰው ጉልበት ዋጋን በተመለከተ በጣም የተዛባ አመለካከት አለ…መንግስት ሀገሪቱ ደሀ ስለሆነች ከዚህ በላይ የተሻለ ደሞዝ መክፈል አልችልም ይላል..ግን እውነቱ ያ ብቻ ይመስልሀል…?፡፡እንደእኔ ግንዛቤ ዋናው ችግሩ ያመለካከት ነው……በየመስሪያ ቤት በቋሚ እና አላቂ ንብረቶች ላይ የሚከሰትን ብክነትና ብልሽትን የተወሰነ ግንዛቤ በመፍጠር እና የተወሰነ የጥንቃቄ እርምጃ በማድረግ ለዓመታዊ ዕቃ ግዢ የሚወጣውን ወጪ በ50 ፐርሰን መቀነስ ብንችል ከዛ በተገኘ ገንዘብ ቢያንስ የእያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛ ላይ የ25 ፐርሰንት የደሞዝ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም ብለህ ታስባለህ…?.ባለስልጣኗች በሙስና የሚቀራመቱትን ገንዘብ የተወሰኑ ክፍተት ያላቸውን አሰራሮች በማሻሻል እና የተወሰነ ቁጥጥር በማድረግ ቢያንስ 50 ፐርሰንቱን ማስጣል ቢቻል የሰራተኛውን ደሞዝ 200 ፐርሰንት ማሳደግ አይቻልም ትላለህ…?የተቀላጠፈ የስራ ቢሮክራሲ ተፈጥሮ የእያንዳንዱን ሰራተኛ የስራ ውጤታማነትን በተወሰነ ስልተና እና ማነቃቃት በአንድ እጥፍ ማሰደግ ቢቻልና አጠቃላይ የሀገሪቱን ዓመታዊ ምርታማነትን የእውነት 11 ፐርሰንት ማሳደግ ማይቻል ይመስልሀል? እንደዛ ከሆነ ድግሞ በየአመቱ ስንት ፐርሰንት ለሰራተኛ ደሞዝ መጨመር ይቻላል…?አየህ የሀገሪቱን የድህነት ችግር ለመቅረፍ እየሞከርን ያለነው በተሳሳተ የድህነት አመለካከት ነው….
‹‹እኔ እንጃ የምትያቸውን ነገሮች በቀላሉ ማድረግ ይቻላል የሚለውን መቀበል ይከብደኛል››አለኳት…
ተቃውሞዬን ችላ ብላ ቀጠለች‹‹አንዳንዴ ይገርመኛል አንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ስንት እና ስንት ለሀገር ደህነንነት ወሳኝ የሆኑ ጉዳዩችን ሲዳኝ ውሎ፤ የሚሊዬን እና ቢሊዬን ሙስና ወንጀሎችን ሲመረምር ቆይቶ ወደቤቱ የሚወስደው አንድ ቪትስ መኪና እንኳን አጥቶ በታክሲ ሰልፍ ይዞ እየተጋፋ ወይም በባስ ታጭቆ እየተንገላታ ወደቤቱ ሲሄድ የሚፈጥርበት ስሜት ይታይህ…ይሄ ሰው የሚከፈለውስ ደሞዝ ስንት ነው…?ልጁ ቢታመምበት የግለሰብ ሆስፒታል ወስዶ ማሳካም አቅም ይኖረዋል ወይ ….?እና ሄዶ ሄዶ ሙስና ውስጥ ሳይገባ ምን የህል ጊዜ በጽናት መቆየት ይችላል …?በእሱ ላይ የሚመጣውን የድህንት ችግር መታገስ አለበት ብለን እንፍረድበት በልጁ ላይስ ሲሆን …?ክፋቱ ደግሞ ማንም ሰው ለወቅቱ የሚያስፈልገውን ለችግሩ ሚበቃውን ያህል ብቻ ዘርፎ አያቆምም..፡፡አንዴ መዝረፍ ከተጀመራ ሱስ ነው የሚሆነው…ለዛውም አደገኛ የሀሽሽ ሱስ አይነት …፡፡ለመኖር መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት ያቃተው ዳኛ ዘራፋ ሲጀምር…ለመኖር መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት ያቃተው መሀንዲስ መዝርፈ ሲጀምር…. ለመኖር መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት ያቃተው የባንክ ማናጀር መዝረፍ ሲጀምር ..ሀገር ሁሉ በዘራፊዎች መነኸሪያ ሆና ታርፈዋለች….. በጣም የሚያስጠላው ደግሞ መዝረፍ ውስጥ የገባ ሰው በዘረፋው ብቻ አይደለም ሀገሪቱን የሚጎዳው የስራ ሞራሉም ቀን በቀን አየወረደ ስለሚመጣ ነው…ተጫሪ ገንዘብ በቀጥታ ለኪሱ የሚያስገባለት ገንዘብ የማያገኝበትን ስራ ዞር ብሎ ለማየት ፍላጎቱ ወደ ዜሮ እየተንደረደረ ይሄዳል …
አሁን እኮ ለሙሰኞችና ቀማኞች ይቅራታ እንዲባሉ ምክንያት እየሰጠሽላቸው ነው››
በፍጽም እንደዛ አይደለም ..ምንም ሳይቸግረው በስነምግባር ጉድለትና በስግብግብነት በሽታ ብቻ በመጠቃታቸው በሙስና የሚጨማለቁ ቡዙ ዜጎች እንዳሉ አውቃለው…ግን ሳይፈልጉ ችግርና እጦት አንደርድሮ እዛ አዝቅጠት ውስጥ የጨመራቸው የመንግስት ሰራተኞች ቀላል ቁጥር የላቸውም እያልኩህ ነው…እንደዚህ አይነት ሰዎች ደግሞ አንድ ንጽህ ህሊናቸው በሆነ ምክያት ከጨቆየ ይሰባራሉ… በራሳቸውም ስለሚያፍሩ ብኩን ዜጎች እንደሆኑ ይቀራሉ..እያወራውልህ ያለውት ስለእነዛ ሰዎች ነው..በነዛ ጠቃሚ ሰዎች ውድቀት መንግስት የደሞዝ ክፍያ ስርዓትና አሰስተሳሰብ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ፡፡እያልኩህ ነው…
‹‹ቆይ…. እንደምታውቂው የሰው ልጅ ፍላጎት ማብቂያ የለውም፡፡የሆነ ነገር በሰጠሸው ቁጥር ሌላ ተጨማሪ ነገር ይጠይቅሻል..ታዲያ ምን ያህል ቢከፈል ነው በቂ ሚባለው?፡፡››
‹‹ለችሎታውና ለአገልግሎቱ የሚመጥነውን ቢያንስ ዝቅተኛውን ክፍያ ማግኘት አለበት….አንድ ምሳሌ ልስጥህ በመዘጋጃ ቤት የሚሰራ መሀንዲስ 5 ሺብር ደሞዝ እየተከፈለው የሀምሳ ሚሊዬን ብር ባጀት ያለው ሰማይ ጠቀስ ህንፃ እንዲቆጣጠር ይመደባል…. እና መንግስን ወክሎ ባለሀብቱ በተሰጠው ቦታና በፀደቀለት ዲዛይን መሰረት ህንጻውን እየገነባ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚሰማራበት ጊዜ ያገኘውን ስህተት ለባለቤቱ ተናግሮ የማሳገጃ ትዕዛዝ ሊፅፍ ሲል ባለሀብቱ 20 ሺብር ማለት የአራት ወር ደሞዙን በአንድ ቀን ቢሰጠው አልፈልግም ለማለት የሚያስችል ስብዕና ጽናት ከመቶ ሰው
👍1
መካከል በአንድ የሚገኝ ይመስልሀል…?ምክንያቱም ይሄ መሀንዲስ መጀመሪያውኑም እዛ ቦታ የገባው እስኪነቃበት እንዲህ አይነት ገቢዎችን በሙስና ለመሰብሰብ ነው…..በማንኛውም ሰአት ቢባረር የሚያጣው ደሞዝ የሚያስቆጭ አይደለም…ደሞዙ አስራአምስትና ሀያ ሺ ብር ቢሆንስ ያለኝ ይበቃኛል የሚሉት ከመቶ ሀማሳ ፐርሰንት ወይም ከዛ በላይ ይሆናል…፡፡ያን ያህል ስራውን በትክክል የሚሰራ በተቋሙ ውስጥ ከተገኘ ደግሞ የሌሎቹንም አጥፊዎች ጥፋት ለማረምና በጊዜ ለማጋለጥ የተሻለ ዕድል ይኖር ነበር…በዚህም ምክንያት መዘጋጃው በየወሩ ሚሊዬን ብር የሚያወጡ የሚባክኑ መሬቶችና መሰል ዘረፋዎችን ማዳን ይችል የነበረውን ቢያንስ ዝቅተኛውን ተገቢ ደሞዝ ለመክፈል ባለመቻሉ በብዙ እጥፍ ንብረትና መሬት ያዘርፋል፡፡…በዛ ላይ ጥሩ የሚከፍል አካል በጣም ጥሩና ተፎካካሪ ግለሰቦችን ወደራሱ መሳብና ያሉትንም ማቆየት እድሉ ሰፊ ነው፡
‹‹እና ምን እያልሺኝ ነው››
‹‹የምትከፍለው ደሞዝ ሳይሆን ሊያሳስብህ የሚገባው እንዴት እያንዳንዱን ሰራተኛ አሁን ካላቸው ውጤታማነት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ እችላለው የሚለውን ነው…በተለይ ጎበዝ እና ውጤታማ የሆኑት ላይ በማተኮር››
‹‹አልገባኝም››
‹‹አየህ ብልጥ የስራ መሪ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያጠፋው በጣም ውጤታማ እና ታታሪ በሆኑት ሰራተኛች ላይ ነው..እናሱን ይበልጥ በማትጋት..እነሱን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግ..እነሱ የቸገራቸው ነገር ከስር ከስር እየተከታተሉ በመቅረፍ…››
‹‹ይሄም ንግግርሽ አልገባኝ…. ጎበዞቹማ ሰራተኞች ቀድሞውንም ጎበዞች ናቸው..እንደውም ደካማውን ጎበዝ እንዲሆን መጣሩ ነው የሚያዋጣው››
‹‹እሱ የቀሹም የስራ መሪ ዘዴ ነው..ጊዜህን ከሰነፍ ጋር ስታጠፋና ስትጨቃጨቅ ብዙ ነገርህን ነው የምታጣጣው…ዝቅተኛ የስራ ትጋትና ውጤት ያለው ሰውን ጎበዙን ይበልጥ ጎበዝ እንዲሆን ስታደርግ ውጤታማዎቹን ሰራተኟችን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን እያደረግክ ስትሄድ ያንን እያዩ እራሷቸውን ቢያንስ ወደ መሀከለኛ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ይጥራሉ..….ከዛ መሀከል ድረስ ከመጡልህ በቀላሉ ወደላይ መሳብ አይከብድህም ……ግን ያንተ ቅድሚያ ትኩረት የካምፓኒውን ኮከቦች ላይ ነው መሆን ያለበት…፡፡ለምን እንዳዛ እንደምመክርህ ታውቃልህ ትኩረትህ ውጤታማዎቹ ላይ ሲሆን ሁሌ በፈገግታ ተሞልተህ ነው የምትውለው… ሁል ጊዜ በውጤት ላይ ተጨማሪ ውጤት ስለማምጣት ነው አዕምሮህን የምትጠቀምበት..
..ደካማ የሰራ አፈፃፀም ካላቸው ሰዎች ላይ ቀልብህ የሚውል ከሆነ ግን ሁል ጊዜ ስለተበላሸ ነገር ነው የምታስበው..ሁል ጊዜ እድታቆጣ ያደርጉሀል …ሁልጊዜ በብስጭት ነው የምታናግራቸው….ያንተንም የስራ ሞራል ያወርዱብሀል..እነሱን ለማስተካከልና ለማሳደግ ስትጥር ያንተም ብቃት አብሮ እየወረደ ሊሄድ ይችላል…እና 80 ፐርሰንቱን ጊዜህን ውጤታማዎቹን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የቀረህን 20 ፐርሰንት ደግሞ ደካሞችን ለማስተካከል እና ወደመስመር ለማስገባት ተጠቀምበት…..
እሺ ገባኝ ተቀብዬሻለው…..ግን ወደዋናው ነጥብ እንመለስና አሁን የካምፓኒውን ደሞዝ እንዴት እንዳርገው እያልሺኝ ነው››
‹‹ደሞዝ አከፋፈሉ በውጤት ላይ ያተኩር ባይ ነኝ ፡፡የተሻለ የሰራ የተሸለ ገንዘብ እደሚያገኝ እርግጠኛ የሚሆንበት አሰራር ነው መዘርጋት ያለበህ….ዲግሪና ማስተርስ ስለተሸከመ ወይም አስርና ሃያ አመት በካምፓኒው ውስጥ ስለኖረ ሳይሆን በእያንዳንዱ ወር የስራ ትጋቱ ለካምፓኒው ምን ያህል የተሸለ ስራ ስርቷል ?ምን ያህልስ ትርፍ አስገኝቷል…? በቀጥታ የስራ ውጤቱ ተመዝኖ መሆን አለበት…..የትምህርት ዝግጅትና የስ ልምድ የሚጠቅመው መጀመሪያ ሰው ለመቅጠር ብቻ ነው መጠቀም ያለብን ..ከተቀጠረ ቡኃላ የተሻለ ለማደግና የተሻለ ደሞዝ ለማግኘት የተሻለ ውጤታማ መሆን እንዳለበት ሁሉም ሰራተኛ በግልጽ አውቆ በዛ መልኩ መስራት አለበት..ከምፓኒውም ሁሉ ጊዜ በእድገት ላይ ላለ ሰው ተጨማሪ የሚገባው ክፍያ ሊከፍለው ይገባል …ትክክለኛ የሚለካ እና ሚመዘን ውጤት በትክክል ኪስ የሚገባ ገቢ እና ጥቅማ ጥቅማ ማስገኘት አለበት…
‹‹ስለዚህ ይሄን በጅምላ በዓመት 5 ፐርሰንት ጭማሪ የምንለውና አሰራር ይቅር ነው የምትይው፡፡››
‹‹ አዎ..ምን አልባት አሁን ያለውን መነሻ ደሞዝ አንዴ በትክክል አጥንቶ ማሻሻል ያስፈልግ ይሆናል ….ከዛ ቡኃላ ግን ይሄ ካምፓኒ ለሌላውም ካምፓኒ ሞዴል የሆኑ ሰራተኟችን የሚሰሩበት… ደካሞች በራሳቸው ለቀው የሚሄዱበት መሆን አለበት..እሱ እዛ ካምፓኒ እኮ አምስት አመት ሰርቷል ተብሎ የሚኮራበት መሆን አለበት….ቀላል ምሳሌ ልስጥህ ሁለት ተሳቢ መኪና ሚነዱ ሁለት ሸፌሮች አሉ እንበል..ሁለቱን አዲስ መኪና ሰጠሀቸው…ከስድስት ወር ቡኃላ ደሞዝ መጨመር ቢያስፈልግ…ጅቡቲ ስንት ጊዜ ተመላለሱ….በእያንዳንዱ መመላለስ ስንት ቀናት ነበር የፈጀባቸው…?፡እያዳንዳቸው የገጠማቸው ችግር ምንድነበር…?የካምፓኒውን እገዛ ሳይጠይቁ ወይንም ተጨማሪ ወጪ ሳያስወጡ እንዴት ተወጡት?መኪናቸው ላይ የደረሰበት አደጋ አለ….?.አደጋ ከደረሰስ በእነሱ እንዝላልነት ነው ወይስ ከቁጥጥራቸው በላይ በሆነ ችግር…?መኪናውስ ስንቴ ተበላሸቶ ገራዥ ገብቷል..? ስንትስ ብር ድርጅቱን አስወጥቷል…?እነዚህናን መሰል ነገሮች ተዘርዝረው ውጤት ተሰልቶ የውጤታማነታቸው ልዩነት ቁልጭ ብሎ ይታያል..በዛ ስሌት መሰረት ካስገኘው ተጨማሪ ጥቅም ሀያ እና ሰላሳ ፐርሰንት ቢጨመርለት ይሄ ሰው ለሚመጣውስ ምን ያህል ይተጋል.?.ያኛውስ ደካማ ውጤት ያገኘው ለማሻሻል ምን ያህል ይነሳሳል…?.መልሱ ቀላል ነው፡፡
‹‹አሁን ተስማምቼለው››
‹‹አመስግናለው››

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍31
አትሮኖስ pinned «#ፍቅር_ከፈላስፋ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ_ሁለት ፡ ፡ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ፡ ፡ #ፍሰሀ === መቼስ ያለውበትን ሁኔታ በጥቂቱም ቢሆን ግንዛቤው ይኖራችሆል ብዬ አስባለው፡፡ለዚህ ለዓላማዬ መሳካት ቁልፍ ለሆነው የፕሮፖዛል ዝግጅት ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ጠብ እርግፍ እያልኩ ነው….በሌላ ጎን ደግሞ ይህቺ ፌናን የምትባል ልጅ እራሷን የቻለች የቤት ስራ ሆናብኛለች፡፡በቃ የሆነ ነገር ሳታውቁት ከቁጥጥራችሁ ውጭ በሆነ…»
ውድ አንባብያን ያለፈው ክፍል ላይ በስተት ክፍል 21 22 የተባለው በስተት ነው ምንም የታሪክ መቆራረጥ የለም መልካም ንባብ

#ፍቅር_ከፈላስፋ


#ክፍል_ሀያ_ሦስት



ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ


#ፍሰሀ

‹‹አሁን ተስማምቼለው››
‹‹አመስግናለው››
‹‹አንድ ነገር ልጠይቅሽ ነበር?››
‹‹አለቃ እኮ ለመጠየቅ ፍቃድ አይጠይቅም››
‹‹አሁን እኮ የስራ ሰዓት አይደለም …ስለዚህ አለቃ ምናምን ብሎ ነገር የለም..››አልኳት
‹‹እሺ ጠይቀኝ››አለቺኝ አቀማጧን እያስተካከለች
‹‹የዛን ቀን እሷን ለማናደድ ብለሽ ያደረግሺውን እንደሆነ ባውቅም ግን በምንም አይነት ከአዕምሮዬ ላወጣው አልቻልኩም….ከአዕመሮዬም ብቻ አይደለም ከህልሜም ማስወገድ አልቻልኩም….ሙሉ አዕምሮዬ በአንቺ ከንፈር ተሞልቷል…ምነው አሁንም አንድ ሰው አበሳጭቷት በሳመቺኝ እያልኩ በየቀኑ ነው የምፀልየው…
‹‹እየቀለድክ ነው አይደል?››አለቺኝ በፈገግታ እና በመኮሳተር መካከል በሚዋልል ስሜት
‹‹አይደለም…››አልኩና እንደምንም እራሴን አደፋፍሬ እጇን በመዶፎቼ መካከል አስገባውና እያሻሸው ንግግሬን ቀጠልኩ..አልተቃወመችኝም፡፡
‹‹አይደለም..እውነቴን ነው…ከህይወቴ አንድ አመት ተቀንሶ ያንን አይነት መሳም አንድ ጊዜ ደግማ ትሳምህ ብባል እስማማለው …እና እባክሽ..››
‹‹እንዲህ አይጠየቅም እኮ …አንድን ሴት እንዴት ልሳምሽ ብለህ ትጠይቃታለህ…ነውር እኮ ነው፡፡ነው ወይስ ውጭ ስለኖርክ ነውር የሚባል ነገር እረስተሀል?››
‹‹እንደዛ ማለቴ አይደለም..ፍቅረኛዬ እንድትሆኚ እየጠየቅኩሽ ነው››
በጥያቄዬ ምንም የመገረም ስሜት አልታየባትም ‹‹ከዛም በፊት ፍቅረኛ አለሽ ወይ ተብሎ ይጠየቃል…በዛ ላይ አንተም ፍቅረኛ አንዳለችህ አውቃለው..ታዲያ ፍቅረኛ ያለችውን ሰው መጥበስ የምፈልግ ይመስልሀል…?››
‹‹የእኔን እርሺው አብቅቶለታል..አንቺን ፍቅረኛ አለሽ ወይ ብዬ ያልጠየቅኩሽ ግን መልሱን ስለፈራው ነው..አለኝ ካልሺኝ ምን እንደምሆን አላውቅም…››
‹‹የእውነት ልንገርህ አለኝ ብልህም ምንም አትሆንም ..ሁሉም ወንዶች አንዱን ሴት ለማሰመን እንዲህ ነው የሚሉት..››
‹‹እወነቴን ነው …ትክክለኛ የሚሰማኝን ነው እየነገርኩሽ ያለውት..እኔ እስከዛሬ የነበሩት የፍቅር ገጠመኞቼ በአጋጣሚ የተከሰቱ ስለነበሩ እንዲህ አይነት ውስብስብ ነገሮችን አላውቃቸውም…››
‹‹ይሁን ግን የእሳትእራትን የፍቅር ታሪክ ታውቃለህ
አላውቅም እስኪ ንገሪኝ…
የአሳት እራት ፍቅረኛው እየመሰለችው ነው አንፖል በበራ ቁጥር ሲሽከረከር እምታየው ….ሴቷ ለፍቅር ዝግጁ ስትሆን የራሷን ብርሀን ከሰውነቷ አመንጭታ በመርጨት ነው ምልክት የምትሰጠው.. በዛ ብርሀን ተስቦ ወደ እሷ ይሄድና ፍቅሩን ያጣጥማል…እና ይሄ የዋህ አፍቃሪ የሚያምር እና የሚንበለበል ብርሀን ባየበት ሁሉ አፍቃሪ ያገኘ እየመሰላው ተንደርድሮ ምስግ ነው…የሚንበለበል እወነተኛ እሷት ውስጥም ቢሆን ከመግባት ስሜቱን መግታት አይችልም…ከገባና ደግሞ ታውቃለህ እርር ክስም ማለቱ አይቀርም …
‹‹እና ምን ለማለት ነው..››አልኳት ምሳሌዋ ግራ አጋብቶኝ
‹‹ከእኔ ጋር የሚጠብቅህ ፍቅር መንደድ እና መክሰምንም ሊያስከትልብህ ይችላል ብዬ እያመከርኩህ ነው››
‹‹ሰምቼሻለው..እሺ በይኝ እንጄ መንደዱም መክሰሉም አያስጨንቀኝም››
‹‹ወደ እኔ ተሳበች እና ወደ ከንፈሬ ተጠጋች…ከበቀደም ለታው መሳም በላይ የጠለቀ..ከዛ በላይ የሚያደነዝነዝና ረጅም ትንፋሸ አስቋራጭ ነበር… ከተቀመጥኩበት ሶፋ ተንሸራትቼ ወለል ላይ በጉልበቴ እስከምንበረከክ ድረስ አቅል የሚያሳጣ አይነት መሳም ነበር የሳመቺኝ….ቆይ የአሳሳም ጥበብን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚያሰለጥን ተቋም አለ እንዴ…?.እንደዛ ካልሆነማ እንዲህ አይነትን አደንዛዣ አሳሳም ጥበብ ልትጎናፀፍ ትችላለች፡፡
እንደምንም ገፍታ ነበር ከንፈሯን ከከንፈሬ ያለቀቀችው….
ትንፋሽ ወስጄ እራሴን ካረጋጋው ቡኃላ‹‹እና እሺ አልሺኝ ማለት ነው..ፍቅረኛሞች ሆነናል ማለት ነው››ስል በመንሰፍሰፍ አይነት ስሜት ጠየቅኮት
‹‹በፍጽም አልሆንም….ስብሰባው ተካሄዶ የዚህን የፕሮፖዛል ውጤት ካወቅክ ቡኃላ መልሰህ ምትጠይቀኝ ከሆነ የዛን ጊዜ መልሱን ነግርሀለው››
ምን ማለቷ እንደሆነ ግልጽ ሊሆንልኝ አልቻለም‹‹ፕሮፖዛሉ ውጤትና የእኔ እና አንቺ ጉዳይን ምን አገናኘው…?.››
ተገናኘም አልተገናኘውም ያልኩህን ከማድረግ ውጭ ምንም ምርጫ የለህም…ከፈለክ ወይም ከዛ ቡኃላም ፍቅርህ የሚኖር ከሆነ እዚሁ አጠገብህ ጋር ስለምገኝ ጠይቀኝ….አንድ ሰምንት አይደል የሚቀረው..?ሳምንት መታገስ ያቅትሀል?
ይብላኝ ላንቺ እንጂ እኔስ ጠብቃለው….ስሜቴ በሳምንት የሚጠፋ መስሎሽ ነው…?ከአመታት ቡኃላም ብትይኝም ተመሳሳይ ጥያቄ ነው የምጠይቂኝ….የፍቅር ጓደኛዬ ሁኚ ብዬ…..
‹‹እናያለን…››አለቺኝ
‹‹እናያለን ››አባባሏ አስፈራኝ..የሆነ እሳት በውስጤ እንዲጫር አደረገብኝ….
❤️ፌናን
===
እለቱ እሁድ ነው…ያው ይሄ ዓረፍተ ነገር ብቻ የሚገልፀው ሀሳብ አለ አይደል…….?እለቱ ዕሁድ ከሆነ ብዙ ነገሮች የሚረጋጉበት ቀን ነው ማለት ነው..፡፡ወከባና መተረማማስ በጣም የሚቀንስበት ቀን…የስራ ስልክ ሲያወሩ ከመዋል ተገላግለው ቤተሰብን ወይም ወዳጅ ዘመድን በመደወል እንዴት ናችሁ….? የሚባልበት ቀን …የታመመ የሚጠየቅበት ፤ያዘነን የሚያፅናኑበት ለመንፈስ የቀረበ ስራ የሚሰራበት ቀን፡፡
በቤታችን ውስጥ ነው ምንገኘው..እኔ አባቴና እናቴ ብቻ ..ወይ ሳልነጋራችሁ እናቴ ከውጭ ተመልሳ ከመጣች ዛሬ ሶስተኛ ቀኗ ነው…ደግሞ በዚህ ዘመን ከውጭ ተመልሶ መምጣት ብርቅ ነው እንዴ….? እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለው…
ለማኛውም የዛሬዋ ቀን ልዩ ቀን እንድትሆን ስለፈለኩ ለሁሉም የቤቱ ሰራተኞች ፍቃድ ሰጥቼያቸዋለው…ግን ከመሄዳቸው በፊት ቀኑን ሙሉ ሲያግዙኝ እና ለእለቱ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ሲሰሩልኝ ነው የዋሉት ..ልክ እንደምፈልገው፡፡አሁን ሰዓቱ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ነው፡፡እናቴ የገዛ መኝታ ቤቷ እንደተኛች ነው..አባቴ ደግሞ ያው እንደልማዱ ላይብረሪው ውስጥ እራሱን ዘግቶ ወይ እያነበበ ነው ወይ ደግሞ እየጻፈ ነው..ብቻ እዛ ነው ያለው፡፡
እኔ ደግሞ የምግብ ጠረጵዛው በምግብ እየሞላው ነው….ልክ እንደጨረስኩና ነገሮች በፈለኮቸው መሰረት እንደተማቻቹና ቀልብ ሳቢ እንደሆኑ ካረጋገጥኩ ቡኃላ ወደእናቴ መኝታ ቤት አመራው
===
..በዝግታ ሳንኳኳ ‹‹ግቡ››የሚል የደከመ ድምጽ ፍቃድ ሰጠኝ… በራፉን ገፋ አድርጌ ገባው…እናቴ አልጋዋን በወረቀት ሞልታ አፍንጫዋ ላይ የሰካችው መነጻር ከፍ ዝቅ አያደረገች አንገቷን አቀርቅራ ወረቀቷቹ ላይ አፍጥጣለች፡፡
‹‹እንዴ እማ የተኛሽ መስሎኝ ነበር እኮ….?››
‹‹በዚህ ሰዓት…….?አረ አልተኛውም››
‹‹ይሄ ሁሉ ወረቀት ምንድ ነው….?››
‹‹የካምፓኒውን የስድስት ወር ሪፖርት ልከውልኝ ነው..እስኑ እያየውት ነው››
‹‹ምነው ተዲያ ተኮሳተርሽ ….….?የጠፋ ነገር አለ እንዴ…….?››
‹‹አይ የለም…..አንድ ብቻ ደስ ያላለኝ ነገር አለ…››
‹‹ልትነግሪኝ ትቺያለሽ….?››
‹‹የሰውዬው ልጅ ስር-አስኪያጅ ከሆነ ምን ያህል ጊዜ ሆነው….?››
‹‹ወር ከሀያ ቀን …››
‹‹እና ምን አድርጎ ነው በዚህ አጭር ጊዜ በጣም የተለየ ትርፍ ሊገኝ የቻለው…….?››
‹‹ጎበዝ ነው ብዬ ነግሬሻለው እኮ….›››አልኳት በፈገግታ ተሞልቼ
‹‹አይ ይሄንን ስራ ጥርሴን የነቀልኩበት ነው..የፈለገ ጎበዝ ቢሆን ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሊታይ የሚችል ልዩነት ማምጣት የሚችል ሰው አይኖርም… ምን አልባት ስራውን በደንብ የሚያውቅና ካምፓኒውን ቀድሞ
👍3
በጥልቀት ያጠና ሰው ካረዳው በስተቀር…››
‹‹እንደዛ አይነት ሰው ማን አለ…….?ማንን ጠረጠርሽ….?››
….የበታተነችውን ወረቀት እየሰበሰበችና ወደመህደራቸው እየመለሰች‹‹….አንቺ ካረዳሽው እንዲህ አይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም….አንቺን ነው የምጠረጥረው፡፡እንዴት ሰው እርሱ የሚታረድበትን ቢላዋ በፍቃደኝነት ይሞርዳል?››
‹‹ያው በደነዘ ቢላዋ ከመገዝገዝና ጣርን ከማብዛት መታረጃን በደንብ ሞርዶ ያለምንም ስቃይ በስል ቢላዋ ቶሎ መገላገል ይሻሸላል ብዬ ነዋ፡፡ያው መታረዱ ቁርጥ ከሆነ እንደዛ ይሻላል.››
‹‹እየቀለድኩ አይደለም››አለቺኝ በፊት ከነበራት የዘወትር መኮሳተር ላይ ሌላ መኮስተር አክላበት
ተጣጋዋትና ወደ አልጋው ጎንበስ ብዬ በማቀፍ ጉንጮን ሞጭሙጩ በመሳም…‹‹ዛሬ ስለዚህ ጉዳይ ማውሪያ ቀናችን አይደለም››አልኳት
...አልተስማማችም‹‹…ነው እንጂ …አምስት ቀን ብቻ ነው የቀረን፡፡ያንን ካምፓኒ እንድታስተዳድሪ እፈልጋለው፡፡.ነግሬሻለው
… አውቀሽም ሆነ በዚህ በቸልተኝነትሽ ቦታውን ካጣሽ ያበቃልኛል..››
‹‹ያበቃልኛል ስትይ….?››
‹‹ልትጠፋ ጭል ጭል እያለች ያለችው ልቤ ቀጥ ነው የምትለው፡፡ሄጄ የልብ ትርንስፕላንት ሳይደረግልኝ እዚሁ ያበቃልኛል እያልኩሽ ነው››
‹‹እማ እንዲህማ አታሳቂኝ፡፡››
‹‹እንድትሳቀቂ ሳይሆን እውነቱን አውቀሽ ማድረግ ያለብሽን እንድታደርጊ ነው እየነገርኩሽ ያለውት››
‹‹እሺ እሱን ነገ ተነገ ወዲያ እንነጋገርበታልን…ዛሬ ለእኛ ልዩ ቀን ነች… አሁን ተነሽ በ20 ደቂቃ ውስጥ ሽክ ብለሽ ለብሰሽ ሳሎን የእራት ጠረጵዛ ላይ ተገኚልኝ››
‹‹እንዴ!!! እውነትሽን ነው?››
‹‹እወነቴን ነው፡፡በይ ተነሽ 20 ደቂቃ ብቻ ነው ምሰጥሽ››ብዬ ድጋሚ ግንባሯን ስሜ ወጣው…..
===
ቀጥታ አባቴ ወደሚገኝበት ላይብረሪ ነው የሄድኩት…..
ጠረጵዛ ላይ አቀርቅሮ ይጽፋል….ስገባም አይሰማኝም…‹‹አባ..››
ትከሻውን ወዘወዝኩት….
‹‹ምን ተፈጠረ?››አለኝ ካቀረቀረበት ቀና ሳይል….
‹‹ተነስ… በቃ ፈልግሀለው››
‹‹ቆይ የጀመርኮትን ልጨርስ››
‹‹ነገ ትጨርሰዋለህ… ተነስ፡፡››
‹‹አይ ለደራሲ ነገ የሚባል ቀን የለውም ፡፡የመጣለትን ሀሳብ ወዲያውኑ በዛኑ ደቂቃ በወረቀት ካላሰፈረ በቃ ያ ሀሳብ በኖ ይጠፋል…መቼም ተመልሶ አይመጣለትም..ነገ ልፃፍ ቢል እንኳን ሌላ የተለየ ሀሳብ ነው ሊጽፍ የሚችለው፡፡.››
‹‹ውይ በቃ አባ ተነስ››እጁ ላይ ያለውን ብዕር ተቀብዬ ክዳኑን ከድኜ በማስቀመጥ ጎትቼ እስነሳውት…ይዥው ቀጥታ ወደመኝታ ቤታችን ነው የወሰድኩት
‹‹ …ምን እየሰራሽ ነው….?››ጠየቀኝ….የእሱን ቁም ሳጥን ከፍቼ ልብስ ስመርጥ እያየ…
ይሄንን ሸሚዝ ይሄንን ሱፍ፤ ይሄን ጫማ ..ሁሉንም መረጥኩና ከየቦታቸው እያወጣው ጠረጵዛ ላይ አድርጌ ‹‹ይሄንን ፂምህን ተላጭተህ፤ ይሄንን የመረጥኩልህን ልብስ ለብሰህ በ15 ደቂቃ ውስጥ ሳሎን ከች በልልኝ…››ብዬ ምን እንደሚለኝ ግራ ገብቶት በአግራሞት እየተመለከተኝ ሳለ ጉንጩን ስሜ ተንደርድሬ መኝታ ቤቱን ለቅቄ ወጣውና በላዩ ላይ ዘግቼ የቀሩ ነገሮችን ለማስተካከል ወደሳሎን ተመለስኩ
ቀድሞ የደረሰው አባቴ ነው፡፡እንደምፈልገው አምሮበታል‹‹….የምግብ ሽታ ያልተራበንም ሰው ያስርባል››አለኝ እና ቁጭ አለ
‹‹የእኔ ውድ አባት ትንሽ ታገስ››እያልኩት ሳለ ከላይ ከፎቅ ወደታች የሚወርድ ቋ…ቋ..ቋ የሚል የእግር ኮቴ ድምጽ ስንሰማ ሁለታችንም እይታችንን ወደ ላይ ላክን…. እናቴ ከአስደማሚ ግርማ ሞገሷ ጋር ንግስት የሚያስመስላትን ልብስ ለብሳ በእርጋታ ወደታች እየወረደች ነው…አባቴ ሳያስበው መሰለኝ ከተቀመጠበት ተነሳና ወደእሷ ተንቀሳቀሰ…መሀከል መንገድ ድረስ ሄዶ እጆን ያዘና አምጥቶ ወንበር ስቦ ካስቀመጣት ቡኃላ ከፊት ለፊቷ ሄዶ ተቀመጠ …..
‹‹አባትሽ እንዲህ ሲያምርበት አንቺስ ምነው በሽርጥ?››አለቺኝ እናቴ..ይሄንን አስተያየት የሰጠችው ቀጥታ አባቴን አምሮብሀል ማለት ከብዶት ነው..
‹‹እኔማ ዛሬ አገልጋያችሁ ነኝ..እራት ያዙ፤ ብሉ ፤ጠጡ …የጎደለ ነገር ካለ ጠይቁኝ››
በሁለቱም ፊት ላይ መደነቅ የወለደው ፈለገግታ ተረጨ
‹‹እንዴ ልጆቹ ሁሉ የት ሄዱ?››
‹‹በዚህ ግዙፍ ጊቢ ውስጥ ከአባት እናት እና ልጅ በስተቀር አንድም ፍጡር የለም… ድመትና ውሾች እራሱ የሉም …ሁሉም እረፍት እንዲወጡ አድርጌያለው››
ሁለቱ ተያዩ››ምን እየተካሄደ ነው?›› እየተባባሉ እርስ በርስ የሚጠያየቁ ይመስላል
‹‹የዚህ ሁሉ ዝግጅት ምክንያት ሊነገረን ቢችል.?››አባቴ ነው የተጠየቀው… ከቀረበው ምግብ የሚመቸውን ወደ ሰሀኑ እየወሰደ….
‹‹የቤተሰብ ቀን ነው››እኔ ነኝ የመለስኩት
‹‹ታዲያ ሁሉም እኮ ቤተሰቦቻችን ናቸው…ቤተሰብ ማለት እናትና አባት ወይም ልጅ እና እናት አይደለም..በአንዱ ቤት ውስጥ እየተሳሰብና እየተረዳዱ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰብ የሚለውን ስያሜ ያጠቃልላቸዋል…››አባቴ ነው
‹‹አባ አቁም..ዛሬ እንደዛ አይነት ዝርዝር ፍልስፍናዊ ትንተና ለመስማት ዝግጁ አይደለሁም::በአጭሩ ዛሬ እናትና አባቴን ፈልጋቸዋለው::ብቻቸውን..ለምን ፈልጋቸዋለሁ?ዝግጅቱ ገና መጀመሩ ነው..በቅድሚያ እራቱ ይበላ ..ተረጋጉ ..ጊዜው ሲደርስ የሚሆነው ይሆናል››ሁለቱም አቀረቀሩ
‹‹ሰምተናል እሺ … አንቺም ቁጭ በይና እራትሽን ብይ.››እናቴ ነች….ከጎኗ ቁጭ አልኩና ያዝኩ….
አባቴ እጅን ወደ እናቴ ሰሀን ይልክና ከራሷ እንጃራ ቆርሶ የእሷን ወጥ ከዚህም ከዛም አጠቃቅሶ ያጎርሳታል….እኛ ቤት ውስጥ የእናቴን ምግብ የሚበላ ሰው የለም…እሷ የምትበላው ምግብ እህል ቀጠል አይልም…ጨው የለው..ዘይት ለመደሀኒት ነው የሚገባበት..ጮማ በደረሰበት አትደርስም…ከምትበላቸው የህል ዘሮች የማትበላቸው በመቶ እጥፍ ይበዛሉ….ሰው ለደሀ ያዝናል….እያለው ሁሉ ነገር ፊቱ ተደርድሮለት ግን ደግሞ መብላት የማይችልስ ሰው አያሳዝንም.? ከፍቅረኛህ ጋር አንድ አልጋ ላይ ትተኛለህ ግን ደግሞ ጭኗን መግለጥ አትችልም ብትባል?ፍቅረኛ አጥቷ ባዶ አልጋ ታቅፎ ከሚተኛው ሰው የበለጠ የምትሰቃየው አንተ አይደለህን.? ቀድሞውንም የሌለው አንደምንም እራሱን አሳምኖ ሁሉን ነገር ለጊዜውም ቢሆን ረስቶ በእንቅልፍ ይዋጥና እፎይ ይላል..አጠገቡ ከተኛች ግን በተገላበጠች ቁጥር ልብ ትገላባጠላች.. ትንፋሿ ከሩቅ በገረፈው ቁጥር አንጀቱ በወሲብ እረሀብ ይገላበጥበታል..እና ስቃዩ ኖሮህ ግን ደግሞ መጠቅም ሳትችል ይብሳል….የእናቴ ነገር እንዲያ ነው፡፡
…እኔ ድግሞ አባቴን አጎርሳለው….እናቴ በህይወቷ ማንንም ሰው ስታጎርስ አይቼ አላውቅም…እኔ ደግሞ ማጉረስ ብወድም እሷን ግን አጉርሼት ማውቅበት ጊዜ መኖሩን አላስታውስም…ለምን ይመስላችሆል?ህፃን እያለው ጀመሮ እባቴ ሲያጎርሰኝ ለሳዕታት ስሬ ቁጭ ብሎ ልጄ ይህቺን የመጨረሻ ጉረሺልኝ...ለእኔ ስትይ …….እያለ እባብሎም፤ እያታለለም ሲያበላኝ እሷ አንድ ቀን ተሳስታ እንኳን እጆን ወደ አፌ ዘርጋታ አታውቅም..እኔም ሳለውቀው ይህቺን ቂም ይዤባት አድጌያለው መሰለኝ እጄ አሁን ሁሉን ነገር ረስቼያለው ባልኩበት ጊዜ እንኳን ለእሷ አይዘረጋልኝም::ምግቡ አልቆ ከምግብ ጠረጵዛው ተነስተን ወደ ሶፋው ተሸጋግረን ተቀምጠናል:: እኔም ሽርጤን አውልቄ ፊት ለፊቴ የወይን ብርጭቆዬን አድርጌ ለንግግር እየተዘጋጀው ነው::አባቴ ውስኪ ይዞል …እናቴ ግን ያው እንደተለመደው ንጽህ ውሀዋን ፊት ለፊቷ አስቀምጣለች…ምሲኪን…..
ሁለቱም ምን አስባ ነው….? በማለት የምለውን ነገር ለመስማትና በህይወቴ አድርጌው የማላውቀውን እና አሁን እያደረግኩ ያለውትን ይሄ ሁሉ ጠብ እርግፍ በምን ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ አፌ
👍1👎1
እስኪከፈት በጉጉት እየጠበቁኝ ነው..፡፡

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
አትሮኖስ pinned «ውድ አንባብያን ያለፈው ክፍል ላይ በስተት ክፍል 21 22 የተባለው በስተት ነው ምንም የታሪክ መቆራረጥ የለም መልካም ንባብ #ፍቅር_ከፈላስፋ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ_ሦስት ፡ ፡ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ፡ ፡ #ፍሰሀ ‹‹አሁን ተስማምቼለው›› ‹‹አመስግናለው›› ‹‹አንድ ነገር ልጠይቅሽ ነበር?›› ‹‹አለቃ እኮ ለመጠየቅ ፍቃድ አይጠይቅም›› ‹‹አሁን እኮ የስራ ሰዓት አይደለም …ስለዚህ አለቃ ምናምን…»
#ፍቅር_ከፈላስፋ


#ክፍል_ሀያ_አራት



ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ



‹‹የዛሬዋን ቀን ለዓመታት ሳስባትና ስዘጋጅባት የነበረች ቀን ነች::በምን አይነት ሁኔታ ላድርገው?እንዴት ቢሆን ይሻላል?ለብዙ ለብዙ ቀናት ሳብሰለስለው ነው የኖርኩት….እና ይቺ ቀን ዛሬ ነች ደቂቃዋም አሁን…..››
‹‹ይሄን ያህል ያሰጨነቀሽ ነገር ምን ቢሆን ነው?››እናቴ ነች
‹‹እዚህ ቤት ያለው ሚስጥር..በእናንተ ሁለታችሁ መካከል ያለው ሚስጥር……የማትጨቃጨቁበት፤ የማትለያበት ሚስጥር….?››
<<እንዴ ልጄ ምን እያልሽ ነው…….?እንዲህ ይባላል እንዴ..….? ሰው እኮ አባትና እናቴ እየተጨቃጨቁና እየተጣሉ እረበሹኝ እያለ ነው ሚሰቃየው..ለምን አልተጣላችሁም ብሎ መጨነቅ ምን የሚሉት ነው….?››አለች እናቴ
አባቴ እንዳቀረቀረ ነው..ምን ለማለት እንደፈለኩ ለእሱ በደንብ እደሚገባው አውቃለው…በጥልቀትም ባይሆን ብዙ ጌዜ እያነሳሳውበት ስጨቀጭቀው ስለነበር ከእናቴ በተሸለ ምን ለማለት እንደፈለኩ ማወቁ ብዙም አይግርምም….
‹‹በመሀከላችሁ የታፈነው ነገር ነዋ የሚያስጨንቀኝ…መቼ ይሆን የሚፈነዳው ….?እያልኩ ሁሌ እንቅልፍ እስካጣ ድረስ አስባለው…ሲፈነዳስ?የፍንዳታው ፍንጥርጣሪ እያዳንዳችንን ምን ያህል ይጎዳናል? ከፍንዳታው ቡኃላም እንዲህ አንድ ላይ በአንድ ቤት ጣሪያ ውስጥ መኖር እንቀጥላለን?ወይስ ብትንትናችን ይወጣል?ሁሌ ያስጨንቀኛል››
‹‹የምን መአት ነው የምታወሪው?እኔና አባትሽን እንዴት ይለያያሉ ብለሽ አሰብሽ….ወደ አባቴ ዞረችና በጥርጣሬና ግራ በመጋባት እየመረመረችው‹‹ምን አልካት…….?››ብላ ጠየቀችውና ወዲያው እራሷ መልሱን መመለስ ጀመረች ‹‹ይቅርታ አንተ ምንም ልትላት እንደማትችል አውቃለው››ብላ መልሳ እኔው ላይ አፈጠጠችብኝ
‹‹ቆይ እናንተ ምንድን ናቹሁ.?››
‹‹ምን ማለት ነው.?ሰዎች ነና››
‹‹አይደለም… የሁለታችሁ ግንኙነት ምን ስያሜ ነው የምትሰጡት?የውጭ ሰዎች እንደሚሉት ባልና ሚስት ናችሁ?.እኔ እንደማውቀው አንድ የጋራ ቤት ተጋርተው የሚኖሩ ደባል ናችሁ…..….የትኛውን ናችሁ….?››
‹‹ተረጋጊ….አባትሽ ለእኔ ምኔ እንደሆነ ታውቂያለሽ .. ….?ባሌ ብቻ እንድልሽ ትፈልጊያለሽ.?ባልማ ማንም ወንድ ባል ሊሆን ይችላል ..እሱ ህይወቴ ነው…፡፡ህይወቴን ለማቆየት በየሰው ሀገር እየተንከራተትኩ ሰውነቴን በየጊዜው እያስተለተልኩ መከራዬን እደማይ ታውቂያለሽ…ለምን ይመስልሻል?ለሀብቴ አይደለም..አሁን ለእኔ ገንዘብ ምን ያደርግልኝ ይመስልሻል?ያማረኝን የማልበላና ያሰኘኝን የማልጠጣ ሰው ነኝ…፡፡እና ለተጨማሪ ጊዜያቶች አብሬው ለመኖር ፍላጎት ባይኖረኝ ኖሮ ምን እንደማደርግ ታውቂያለሽ?አንድ ወርም ሆነ ሁለት ወር ያሰኘኝን በልቼ ያማረኝን ጠጥቼ ይህቺን ህይወት እሰናበት ነበር..ግን ከእሱ ላለመለየት ስለምፈልግ ነው እያዳንዳን የሀኪም ቃል ከፈጣሪዬ ቃል በላይ በየቀኑ እየደገምኩ በዛ መሰረት ለመጓዝ ምጥረው….እና ደግሞ ከእሱ በተጨማሪ አንቺም አለሽ››ንግግሯ ፀጥ አሰኘኝ…ሀሳቤን በታተነቺብኝ….እሷ እንደዛ በስሜት እየተንቀጠቀጠች ስትናገር አባቴ ደግሞ እንባውን በጉንጮቹ እያረገፈ ነበር…እኔ ደግሞ አባቴ ጉንጮች ላይ እንባ ሲወርድ ከማይ አለም አብቅቶላት ምጽአት ቢታወጅ ይቀለኛል….ግን ይገርማችሆል በዚህ የስሜት መጨፍገግ ላይም ሆኜ ምን እንደተዛብኩ ታውቃላችሁ?እማዬ ስለአባቴ የሚሳማትን ተንትና በስተመጨረሻ ደግሞም አንቺም አለሽ ስትል…ለእሷ እኔ የሆን እንጎቻ ነገር እንደሆንኩ ነው የተሰማኝ….ልጣፊ ነገር፡፡
ጥያቄዬን ቀጠልኩ ‹‹እና እንድምትይው አባቴን የምታፈቅሪው ከሆነ እንዴት እንዲህ ትጨክኚበታልሽ? ሀያ አምስት አመት ሙሉ ልጅን አቅፎ ሲተኛ ትንሽ ህሊናሽን አይቆረቁርሽም?ነው ወይስ የአንድ ሚስትን ግዴታና ኃላፊነት አታውቂም.?››
አባቴ ንግግሬ አስጨንቆት ይንቋራጠጣል….
‹‹ስለማታውቂው ነገር አትዘባርቂ…››
‹‹እኮ አሳውቂኝ… የሆነው ነገር ሁሉ እንዴት እንደዛ ሲሆን እንደኖረ የማወቅ መብት አለኝ…ንገሪኝና ልረዳው….ከለበለዛ…!!!››
‹‹ካለበለዛ ምን ….?››አይኗን አጉረጥርጣ ጠየቀቺኝ..ዛሬ ምንም ብትቆጣ …ምንም ያህል ብትኮሳተር ልፈራትና ልሸነፍላት አልችልም ….አባቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከላችን ገባ
‹‹ወዴ በቃሽ….ይሄንን ነገር እንዳለ ተይው ››
‹‹አልተወውም አባ::ለአንተ ስል አልተወውም››
‹‹ለእኔ አስበሽ ከሆነ ብትተይው ነው በጣም የምትጠቅሚኝ…እናትሽ እንዳለቺው እስከዛሬም የኖርነው የፈለግነውን አይነት ኑሮ ነው …ሁለታችንም እየሆነ ባለው ነገር ደስተኞች ነን::ስለዚህ አንዳንድ ነገሮችን ባሉበት መተው መልካም ነው..››
‹‹አልተውም አልኩ እኮ..አባ ዛሬ እውነቷን ሳላውቅ አላድርም››
‹‹ተውሽም አልተውሽም እኛ ምንም የምንነግርሽም የምንልሽም ነገር የለም…እና ምን ልታደርጊ ነው?››እናቴ ነች…ምንም ልታመጪ አትቺይም በሚል ስሜት የተናገረቺው
‹‹አፋታችሁለው….አባቴ ካንቺ እንዲፋታና ይሄንን ቤት ለቆልሽ እንዲወጣ አደርጋለው::ከዛ በቅርብ ሌላ ሚስት እድረዋለው::እና ደግሞ ያንን ካምፓኒሽን አልፈልገውም::አንቺንም ጭምር አልፈልግሽም.››
ዝም አለች… ዝም ብሎ ማፈጠጥ ብቻ….የሆነ 5 ደቂቃ ያህል መሰለኝ ዝም ያለችው …ግን የ5 ዓመት ያህል ርዝመት ነበረው..አስፈሪ ምንጩ ከወደሲኦል ሚመስል ዝምታ….እና ከዝምታዋ ወደ መዳካምና አንገቷን ዘንበል አድርጋ ወደጎን ልትወቀድቅ ስትል አባቴ ፈጠን ብሎ ያዘት ..ከዛ ቡኃላ የነበረውን መሯሯጥና መተረማመስ አትጠይቁኝ..በስንት ማናፈስ …መዳሀኒቷ ከመኝታ ቤት አምጥተን አውጠናት በመከራ ነው አይኖቾን የገለጠችው….እና እንደገለጠች…
.‹‹ወደመኝታ ቤቴ ውሰደኝ …ደከመኝ ልተኛ >>አለችው አባቴን ስልምልም ባለ ድምጽ
‹‹እሺ›› አለና ከተቀመጠበት ተነስቶ ሰቅስቆ አቀፋትና የፎቁን ደረጃ ማውጣት ጀመረ….እኔም ቀደምኩና ከፊት ለፊቱ መኝታ ቤቷን ከፈትኩለት …ወደውስጥ ገባውና ብርድልብሱን ገለጥኩለት…. ቀስ ብሎ አስተኛት…
ወደእሷ ተጠጋውና ‹‹እማ ይቅርታ››እጆን አናሳችና ፊቴ ላይ እሰቀምጣ በመዳበስ‹‹‹..በጣም ነው የምወድሽ…የእኔ ልጅ በመሆንሽ ሁል ጊዜ እንደኮራውብሽ ነው…ግን እንድታውቂ የምፈልገው አባትሽን ደግሞ ካቺም በላይ ነው የምወደው››አለቺኝ …ከሳለፉነው ሁኔታ ጋር የማይገናኝና በተቃራኒ የሆነ ልስልስ ያለና ወደልብ የሚሰርግ የፍቅር ንግግር ነው ያሰማቺኝ…በመጠኑ ተንፈስ አልኩ
‹‹በቃ አሁን ሂዱ…ልተኛ ››
‹‹እኔ አብሬሽ ልቆይ››አባቴ ነው ተናጋሪው
‹‹አይሆንም… ካመመኝ መጥሪያውን እጫናለው…››
ባለችው ተስማምተን ለቀንላት ተያይይዘን ወጣን..ወደሳሎን ነበር የተመለስነው….‹‹አባ ውስኪውን መጠጣት ነው የምፈልገው›› አልኩት
ባዶ ብርጭቆ አናሳና ቀዳልኝ …የራሱንም ጎዶሎ ሞላ …..በዝምታ መጠጣት ጀመርን…እኩለ ለሊት ሊቃረብ ሲል ነበር አባቴ ማውራት የጀመረው….

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍3
አትሮኖስ pinned «#ፍቅር_ከፈላስፋ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ_አራት ፡ ፡ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ፡ ፡ ‹‹የዛሬዋን ቀን ለዓመታት ሳስባትና ስዘጋጅባት የነበረች ቀን ነች::በምን አይነት ሁኔታ ላድርገው?እንዴት ቢሆን ይሻላል?ለብዙ ለብዙ ቀናት ሳብሰለስለው ነው የኖርኩት….እና ይቺ ቀን ዛሬ ነች ደቂቃዋም አሁን…..›› ‹‹ይሄን ያህል ያሰጨነቀሽ ነገር ምን ቢሆን ነው?››እናቴ ነች ‹‹እዚህ ቤት ያለው ሚስጥር..በእናንተ ሁለታችሁ…»
#ፍቅር_ከፈላስፋ


#ክፍል_ሀያ_አምስት



ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ



❤️ፌናን
===
‹‹….ምን አልባት ትክክል ነሽ››አለኝ
‹‹ምኑን አባ…?››
‹‹እውነቱን የማወቅ መብት አለሽ …እናም ነገርሻለው››
አቀማመጤን አስተካከልኩ..በስካርና በድካም እየታጠፉ የነበሩ ጆሮዎቼን ሲነቃቁና ሲዘረጋጉ ይታወቀኛል…
‹‹በዚህ የታፈነ በምትይው የእኔ እና የእናትሽ ኑሮ ውስጥ ባጣም ተጎጂው እኔ ሳልሆን እናትሽ ነች››
‹‹ማለት…?››
‹‹የመፋታቱን ሀሳብ አንቺ ከመወለደሽም በፊት ሆነ ከተወለድሽ በኃላ ደጋግሜ አቅርቤላት ነበር::ግን ከተለየዋት እራሷን እንድምታጠፋ ደጋግማ ስላስጠነቀቀቺኝ ነው ጥያቄዬን አቁሜ ሀሳቤንም ቀይሬ ዝም ብዬ እንደምታይው መኖር የጀምርኩት..››
‹‹መኖራችሁ ካልቀረ ታዲያ እንደ ሰዎቹ በስርዓት አትኖሩም..…?እንደባልና ሚስት››
‹‹እንደዛ መኖር አንችልም..ታሪኩን ከመጀመሪያ ላስረዳሽ…እናትሽ የአዲስአባ ልጅ ብትሆንም የእናቷ ቤተሰቦች የአንቦ ኦሮሞዎች እንደሆኑ ታውቂያለሽ››የሚናገርውን ነገር ማስረዳት ስለከበደው ዙሪያ ጥምዝ እንደሚሽከረከር ገባኝ ..አሁን እያለኝ ያለው እኮ ያንቺ ሰም መቼስ ፌናን እንደሆነ ታውቂያለሽ አይደል …?ቢጤ ነው፡፡
‹‹…..እና ልክ እኔ እና እናትሽ እንደተጋባን ሰሞን የእናቷ ታናሽ ወንድም ስሙ ቶሌራ ይባላል ..በውድቅት ለሊት በራፋችንን አንኳክቶ ይመጣል….ሲመጣ ሰው አይመስልም…ልብሱ በጭቃና በከሰል ብናኝ በክቷ፤በደረቀ ደም ተለውሶ ነበር…ማንነቱን በመልኩ ሳይሆን በድምጹ ነበር እናትሽ የለየችው…ከዛ አፋፍሰን ወደቤት አስገብተን ሰውነቱን እንዲታጠብ አድርገን ልብሱን ቀይረን የቆሰለውን የተቻለንን ያህል የመጀመሪያ እርዳታ እንዲያገኝ አድርገን አስተኛነው…
‹‹ምን ሆኖ ነበር…?››
ይሄ ልጅ ብሩህ ጭንቅት ያለው ድንቅ ልጅ ነበር…ግን ያው እንደማንኛውም የዘመኑ ወጣት ፓለቲካ ውስጥ እስከአንገቱ ነበር የገባበት::እኔም ሆንኩ እናትሽ እንደው ባጋጣሚ ወይ እኛ ሄደን ወይ ደግሞ እሱ ሊጠይቃና በመጣ ቁጥር ነገሮችን በእርጋታ እንዲይዛቸው ልንመክረው ሞክረን ነበር::አዎ ያቅማችንን ጥረን ነበር:: ግን ያው ታውቂያለሽ አንዳንዴ ፓለቲካ ልክ እንደልክፍት ነው::ሰው ተይ ባለሽ ቁጥር ይበለጥ ይብስብሻል..እና ይሄ የማታውቂው አጎትሽ ሚስጥራዊ የኦነግ አባል ሆኖ በአንቦ ከታማ ይንቀሳቀስ ነበር::.እና ህዝቡን ያነሳሱና መንግስትን በመቃወም ከተማዋን ያምሶታል ::በዛም ምክንያት ብዙ የመንግስትና የግል ንብረት ይወድማል::ከወታደሩም ከኑዋሪውም ከ12 ሰዋች በላይ ይሞታሉ…እና የዚህ ጉዳይ መሪ ይሄ አጎትሽ እንደሆነ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ደህነነቶች መረጃ ይደርሳቸውና ለሊቱን አድፍጠው ሊይዙት ወደቤት ሄደው ሲከቡት አንዱን ገድሎ ሁለቱን አቁስሎ አጥር ዘሎ ያመልጣል፡፡እድል ከእሱ ጋር ነበረችና ከሰል በጫነ መኪና መሀል በድብቅ ተወሽቆ በለሊት አዲስአበባ ይገባና እንደነገርኩሽ በውድቅት ለሊት ወደእኛ ቤት ይመጣል፡፡
‹‹ታዲያ እንዲት አደረጋችሁ…?››ጥያቄዬን ቀጠልኩ..እኔ መስማት ከምፈልገው የወላጆቼ የጋብቻ ታሪክ ውጭ የሆነ ሀገራዊ እና ፓለቲካዊ ታሪክ ለምን እንደሚነግረኝ ፍንጩን እንኳን ማወቅ አቅቶኝ ፡፡
‹‹ለጊዜው ምን አልባት የእኛ ቤት አስታማማኝ ላይሆን ስለሚችል እና በጥቆማ መጥተው ቢፈትሹ ሊያገኙት ስለሚችሉ ብለን ሊነጋጋ ሲል አቃቂ የሚኖር አንድ ጎደኛዬ ቤት ወስደን አስተኛነውና እዛው ህክምና እንዲያገኝ አድርገን በዘላቂነት ምን ማድረግ እንዳለብን ማሰብ ጀመርን::እናትሽ ለእሱ ያላት ፍቅር ይሄን ያህል ነው ተብሎ ከሚለካው በላይ ነበር…‹አይኔ እያየ አይገሉብኝም ወይም አስርቤት አይጥሉብኝም ብላ በድብቅ ከሀገር ይዛው ልትስወጣው ተነሳች…ቢያንስ እስከድንበር ልትሸኘው::ስሰማ ተቃወምኩ….የተቃወምኩት ለማድረግ ያሰበቸው ነገር አግባብ አይደለም ብዬ አይደለም..ለእሱ ያላትን ፍቅር ስለማውቅ ከዛ በላይም ላድርግለት ብትል የምቃወምበት ምክንያት አይኖረኝም ነበር::ችግሩ ግን በዛን ጊዜ አንቺን እርጉዝ ነበረች::የአራት ወር አርጉዝ ነበረች….‹‹ልጄን ይዘሽ ይሄንን የመሰለ አደጋ ልጋፈጥ ስትይኝ ቁጭ ብዬ አላይሽም ››አልኳት
‹‹ታዲያ ምን ይሁን? ግደሉት ብዬ ብቻውን ልልቀቀው ወይ…?››ብላ ህሊና የሚሞግት ጥያቄ አቀረበችልኝ
‹‹እኔ እስከፈለግሺው ቦታ ይዤው እሄዳለው::ይሄን አደጋ ለመጋፈጥ ካንቺ ይልቅ እኔ እሻላለው››የሚል ሀሳብ አቀረብኩላት
በወቅቱ አሻፈረኝ አይሆንም አለች….‹‹ለምን…?››ያቀረብኩላት ጥያቄ ነበር
‹‹የሆነ ነገር ከሆንክ ምን ብዬ አወራለው ነው ያለቺኝ…‹‹በእኔ ቤተሰብ ይሄንን ያህል መከራ እንድትጋፈጥ አልፈቅድም›› አለቺኝ ….በዚህ ጉዳይ ከሁለት ቀን በላይ ተጨቃጨቅን… ቡኃላ ሽማግሌም መሀላችን ገብቶ በእኔ መሄድ ተስማማን…
ከዛ እኔና አጎትሽ ጨላማን ተገን አድርገን ከአዲስ አበባ በእግር ወጣን .. ግማሽ መንገድ በግር ሲመቻችልን ደግሞ መኪና በመጠቀም ሞያሌ ድረስ ሸኘውት..እዛ ለመድረስ 8 ቀን ነበር የፈጀብን…ከዛ ደላሎች ወደኬንያ እንዲያሸጋግሩት አመቻችቼ…ድንበር ማቋረጡንም ካረጋገጥኩ ቡኃላ በስኬት ተመለስኩ….
‹‹ከዛስ…?››
‹‹ከዛማ…ከከተማ ይዤው ወጥቼ እንዳስመለጥኩት ደህነቶች መረጃ ደርሶቸው ነበረና እቤቴ ሳልገባ ከመንገድ ነው የጠለፉኝ…››
‹‹ወይ አባ አንተን..…?ታዲያ ምን አደረጉህ…?››
‹‹ከዛም አሁን ሙዚዬም ይሁን ተብሎ የተዘጋው ማዕከላዊ አስገቡኝ::በፊልም ላይ አይቼው ማለውቀውን..በመፃፍም ላይ እንኳን ማንበቤን ትዝ የማይለኝን አይነት ስቃይ አሰቃዩኝ::መፈጠሬን እስክጠላ…ሰው ምን አይነት ፍጡር ነው? ብዬ እስክጠይቅ ድረስ……?እግዜር እንዴት እንደዚህ አይነት ፍጡር ይፈጥራል…? ብዬ ሙግት ውስጥ እስክገባ ድረስ….‹‹እግዜር ሰውን በመፍጠሩ ተፀፀተ› የሚትለው መፃፍ ቅዱስ ላይ ከአመታት በፊት ያነበብኩት ጥቅስ ትርጉም በደንብ እስኪገባኝ ድረስ አሰቃዩኝ››
‹‹አንተን..?ስለአስመለጥከው ብቻ…?››
‹‹አዎ …የት ነው ያደረስከው..…?በድርጅቱ ውስጥ አንተስ የነበረህ ኃላፊነት ምንድነው?ውጭ ካሉት ጋር መመሪያ እየተቀበልክ ክፍለሀገር ላሉት አባሎቻችሁ ሽብር እዲፈፅሙ ምታሰማራቸው አንተ ነህ ወይ?ቀጣዩ የድርጅቱ እቅድ ምንድነው?ሌሎችስ እዚህ ከተማ ውስጥ ሆነ በሌሎች የኦሮሚያ ከተሞች ያሉ አባሎቻችሁን ዝርዝር ?›› የማይጠይቁኝ ጥያቄ የለም..እያንዳንዶ ነጠላ ጥያቄ ከብዙ ማሰቃየትና ገሀነማዊ ቶርቸር ቡኃላ ነበር የምትከተለው፡፡እንዴት አንድ ሰው በገዛ ወንድሙ ላይ በዚህ መጠን ሊጨክን ይችላል?ምን ለማግኘት …?ስንት ዓመት በዚህ ምድር ላይ ለመኖር?በፓለቲካ ልዩነት ብቻ የገዛ ወገንን በየምክንያቱ ከዚህም ከዛም እየሰበሰብ በጭለማ ቤት አጉሮ ጥፍር እየነቀሉ እና ብልት ላይ ሀይላንድ እያንጠለጠሉ በማሰቃየት የሚያስገኘው ውጤት ስልጣን ብቻ አይደለም ዘላለማዊነትስ ቢሆን ያዋጣል እንዴ?በእኔ ሚዛን አያዋጣም፡፡ያንን መከራ በራሴ ላይ ደርሶ ከማያቴ በፊት በሰው ልጅ ላይ የሚሰራ የመጨረሻው አሰቃቂ ወንጀል ወይም ግፍ ግድያ ይመስለኝ ነበር…አንድን ሰው ግንባሩን በጥይት አፍርሶ መግደል፡፡ለካ አሱ ቸር እና አዛኝ የሆኑ ወንጀለኞች የሚፈጽሙት ቀላል ከሚባሉ ቅጣቶች ውስጥ የሚካተት ነው?ብዙም ሊጨክኑበት የማይፈልጉትን ሰው በእንክብካቤ የሚያስወግዱበት ዘዴ…ይህንነ አሁን እየተነጋርኩ ያለውትን ንግግር ሴሜቱ በትክክል የሚሰማው ተመሳሳዩ ነገር የደረሰበት ሰው ብቻ ነው፡ግን ከሰው ውጭ ሌላ ፍጡር በራሱ ፍጡር ላይ ይሄንን ያህል ይጨክናል?ለምሳሌ አንበሳ በአንበሳ
👍5
ላይ?ጅብ በጅብ ላይ…? ነብር በነብር ላይ..…?በፍጽም አይመስለኝም፡፡እና እኛ ከአውሬዎቹ በላይ አውሬነት በውስጣችን ተሸክመን የምንዞር አደገኛ ፍጥሮች ነን ማለት ነው…?፡፡
‹‹እንዴ አንተ ኦነግ ነበርክ እንዴ…?››
‹‹ወይ ኦነግ…የት ብዬ?አንደኛ እኔ በወቅቱ በነበረው የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም የማምን ሰው አልነበርኩም፡፡ሁለተኛ የማምንበትም ቢሆን እንኳን እኔ በፓለቲካ ጫወታ የሚያስደስተኝ አይነት ሰው አይደለውም፡፡እና እንኳን ልሆን ቀርቶ ኦነግ የሆነ ሰው የማውቀው እጎትሽን ብቻ ነበር፡፡ግን ለእነሱ እሱን እንዲያመልጥ መርዳቴ እና ስሜም ገመዳ መሆኑ ብቻ ለኦነግነቴ በቂ እንደውም ከበቂ በላይ መረጃ ነበር…››
‹‹እሺ ታዲያ እንዴት አደረጉህ…?››የዚህ አሰቃቂ ታሪክ መጨረሻ ማወቅ ጓጓው…አናቴን እዚህ ስሬ ቁጭ ብሎ እያየውት ገድለውት ይሆን እንዴ…? ብዬ እስካስብ ድረስ፡፡ምን ማለቴ ነው…? ያለፈውን ታሪኩን እየነገረኝ ስሬ ቁጭ ብሎ እየነገረኝ ያለው በህይወት ስለተረፈ አይደል እንዴ…? ለአንድ ወር ያህል የአምላክ እርግማን እንደወረደበት እባብ ከቀጠቀጡኝና ከተለተሉኝ ቡኃላ ምንም የሚፈልጉትን መረጃ ሲያጡ ደከማቸው መሰለኝ ጨለማ ቢት ወረወሩኝ፡፡ከሚሸት ቁስሌ፤ከሚከረፋ ላቤ ጋር ድቅድቅ ጨለማና የታፈነ ቤት ወስጥ ወረወሩኝ፡፡ለአንድ ሰው የመጨረሻው ቅጣት ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ…? ብቻውን እንዲሆን ማድረግ፡፡ በብቸኝነት ላይ ጭለማ፤ ረሀብና ጥማት ስትጨምርበት በቃ ሁሉን ነገር ነው የምትጠይው… እያንዳንዷን ደቂቃ እንዴት እንደምትረዝምብሽ ልነግርሽ አልችልም?ሰው በተፈጥሮ ብቻውን እንዲኖር አይደለም የተፈጠረው….መከራም ሆነ ስቃይ ረሀብም ሆነ መታረዝ ከሰው ጋር ከሆነ ይችለዋል…፡፡ማንኛውም እስረኛ ጨለማ ቤት ውስጥ ለብቻው ስድስት ወር ከሚዘጋበት ከሰው ጋራ እድሜ ልክ ቢታሰር ይምርጣል….፡፡
እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም…
‹‹ቡኃላ እናትሽ በምታውቃቸው ሰዎችን የእያንዳንዱን ባለስልጣን ደጅ ፀንታ ለአራት ለአምስቱ ባለስልጣናት ያላትን ብር አስረክባ አስፈታቺኝ…፡፡ቀጥታ ከማዕከላዊ በለሊት አምጥተው በራፎ ላይ ጣሉላት፡፡ወዲያው አፋፈሳ ሆስፒታል ወሰደቺኝ …አንድ ወር ከ15 ቀን አልጋ ይዤ ተኛው…በስንት ጥረት እና የህክምና እርዳታ በመጨረሻ ዳንኩ፡፡ግን አንድ የዘላለም ጠባሳ ሸልመውኝ ነበር…ፈጽሞ ልድነው የማልችለው››
‹‹ምን..?››
‹‹የዘር ፍሬዬን አፍርሰውት ነበር፡፡ሽንት ለመሽናት ከምጠቀምበት በስተቀር ለሴት የሚሆን የስሜት መነሳሳት ሆነ የማድረግ ችሎታ እንዳይኖረኝ አድርገውኝ ነበር…እና ይህ እንደተፈጠረ እናትሽን በዛ ወጣትነት ጊዜዋ ቀሪ ዘመኗን ሙሉ ከእኔ ጋር እንድታባክነው አልፈለኩም ነበርና እንድንፋታ የተቻለኝን ጥሬ ነበር፡፡ግን ይሄው 25 ዓመት እስከዘሬ አልተሳካልኝም፡፡በዚህ ታሪክ ውስጥ በእሷ ልክ የተጎዳ የለም፡፡የእኔ እንኳን አንዴ የሆነው ሆኖብኛል.. እሷ ግን ሁሉን ነገር ማድረግ እየቻለች ነው…፡፡እናም ደግሞ አብራኝ እንዳትተኛ እና እልጋችንም እንዲለያየ ያስገደድኳት እኔ ነኝ ፡፡ሰውነታችን ሲነካካ የእሷ አካል ሲግል እኔ ግን በንዴትና በቁጭት ሲሸማቀቅ፤ እሷ ልትሰመኝ ሲያምራት እኔ ደግሞ ያንን እያየው ስሳቀቅ ..፡፡በቃኝ አልኳት..፡፡በቃን አካላችንን በማነካካት ስቃያችንን ለምን ገሀነማዊ እናደርገዋለን እልኳት…?ጥዬሽ እንዳልጠፋ ከፈለግሽ በማሀከላችን ያለውን ክፍተት ጠብቂ አልኳት.፡፡.መለያየት የለብንም ምትይ ከሆነ የፈለግሽውን ነገር በፈለግሽ ጊዜ ከሌላ ሰው ጋር በውጭ ብታደርጊ ምንም ተቃውሞ የለኝም አልኳት …፡፡ሀሳብሽን ቀይረሽ መፋታት አለብኝ በምትይበት ቀን በደስታ እሸኝሻለው ብያታለው፡፡ያው እስከዛሬ ያንን ጥያቄ ይዛ አልመጣችም..እና አልጋችንንም ብቻ ሳይሆን መኝታ ቤታችንንም እንደለየን ይሄው ለዓመታት አለን፡፡
ተቃቅፈን እስኪደክመን ድረስ ነው የተላቀስነው……አንዳችን አንዳችንን ማፅናናት አላሰኘንም፤ አልሞከርንምም፡፡አዎ የምንወደውን የጋራ ዘመዳችንን እንደተረዳን ነገር ነው ሁኔታችን፡፡እያንዳንዱ ሰው ለካ በውስጥ የሆነ ሀገር የሚያህል ሚስጥር ቀብሮ ነው የሚኖረው፡፡እንዴት ይሄን ጉድ እኔ ልጃቸው እንኳን ሳላውቅ እንባውን እየጠራረገ እና የኔንም እያበሰልኝ መናገሩን ቀጠለ‹‹እና እናትሽ ለእኔ ስትል ነው እንዲህ የሆንከው የሚል ፀፀት ውስጧን እንዳሰቃያት ነው..ለዛ እራሷን በመቅጣት እድሜዋን ጨርሳዋለች፡፡እንደዛ የተበሳጨችብሽ ለዛ ነው፡፡ቁስሏን ነካክተሸ ስለደማሽባት…››
‹‹አሀ እኔንም ከተወለድኩ ጀምሮ ትኩረት ምትነፍገኝ በዚህ ታሪክ ምክንያት ነዋ..እኔን እርጉዝ ሆና ባይሆን እሷ ነበረች የምትሄደው..አንተ ላይ ሚደደረስብህ ነገር አልነበረም..እና እኔን ስታይ በአንተ ላይ የደረሰው መከራ ነው የሚታያት ማለት ነው..አይደል..?፡፡››
‹‹እሱን እርሺው ልጄ ..አንዳንድ ነገሮች እኛ ፈለግንም አልፈለግንም መሆን ባለበቸው መልኩ ከመሆን አያመልጡም፡፡ያው መቼስ እኛ ሰዎች ነንና እንዲህ ቢሆን ኖሮ …?እንዲ ባደርግ ኖሮ እያልን በፀፀት እራሳችንን እንቀጣለን እንጂ መሆን ያለበት ይሆናል››
‹‹አንድ የመጨረሻ ጥያቄ››
‹‹አሁንማ ዋናውን ነገር አውቀሻል.. የፈለግሺውን ጠይቂኝ… ከነገርኩሽ በላይ ሚከብድ ጥያቄ ልትጠይቂኝ አትቺይም..››
‹‹እማዬ…?›› ጥያቄውን ጀምሬው መጨረሱ ከበደኝ
‹‹እማዬ ምን..?››
‹‹እማዬ ታዲያ ይሄን ሁሉ አመት ..ማለቴ ጓደኛ እንኳን የላትም ብለህ ታስባለህ?ማለት ላንተ ላትነግርህ ትችላለች…››
‹‹ግዴለም ሳትጨናነቂ ጠይቂኝ ….ለማለት የፈለግሺው ገብቶኛል…በስንት ውትታና ጭቅጭቅ ከአስር አመት በፊት አንድ በጣም የሚወዳት ሰው ነበርና ከእሱ ጋር ጀምራ ነበር….እኔ አውቄ ማለት ነው ..ነግራኝና አስፈቅዳኝ፡፡አስፈቅዳኝ ብቻ ሳይሆን ገፋፍቼያት፡፡እንደዛ ብታደርጊ እኔም ስለአንቺ መጨነቁ ይቀንስልኛል ብያት..››
‹‹ታዲያ እንዴት ሆኑ..?››
‹‹ስድስት ወር እንኳን አልዘለቀችበትም..››
‹‹ምነው ..?ተጣሉ.. ..?››
‹‹አይ መጣላት እንኳን አይመስለኝም….ሰውዬው በፊት ከሚያፈቅራት በላይ እያፈቀራት ሲመጣ ይረብሻት ጀመር…››
‹‹እንዴት እድርጎ ነው የሚረበሻት..?››
‹‹ትተሸው ነይ ላግባሽ እያለ ነዋ››
‹‹እንዴ!!!! ሰውዬው በአንተ ላይ ስለተፈጠረው ነገር ያውቃል እንዴ..?››
‹‹በፍጽም አያውቅም…፡፡ያው እንደማንኛውም ለትዳሯ ታማኝ እንዳልሆነች ሴት ወይም ባጋጣሚ እንደተሳሳተች እና ከእሱ ፍቅር ይዟት በዛው ግንኙነቱ ውስጥ የቆች አድርጎ ነበር የሚያስበው፡፡ግን ያ አይበቃኝም አለ…እሱም ሚስቱ የሞተችበት እና ለአመታት ብቻውን የሚኖር ነበርና ሙሉ በሙሉ ፈለጋት…››
‹‹ምን አይነት ደፋር ነው!!!››
‹‹ድፍረት አይደለም… እናትሽ አሻፈረኝ አለች እንጂ አኔም በሰውዬው ሀሳብ ተስማምቼ ነበር፡፡ለእናትሽ በጣም ጥሩ ሰው ነበር…ያፈቅራት ነበር…..በዛ ላይ ስራቸው አንድ ላይ ነው…››
‹‹ምን…..?ማነው አውቀዋለው…..?››
‹‹የአለቃሽ የፍሰሀ አባት ነው፡፡ሁለቱም የተለያዩ ካምፓኒዎችን ነበር የሚመሩት ከዛ አዋህደውት ነው አሁን የምታውቂውን ግዙፍ ካምፓኒ የመሰረቱት፡፡ግን በትዳሯ መወሀድ ካምፓኒዎቻቸውን እንደማዋሀድ ቀላል አልሆነላቸውም....››
‹‹አሁን ገባኝ…››
‹‹ምኑ ነው የገባሽ..?››
‹‹አይ ከምሰማቸው ነገሮች ተነስቼ ብዙ ጊዜ በዚህ ሰውዬ እና በእናቴ መካከል የሆነ አለመጋባባት እንደለ እገምት ነበር….አሁን ምክንያቱ ግልጽ ሆነልኝ…ሁለቱም የየራሳቸው ልጆች ካምፓኒውን ተረክበው እንዲመሩላቸው አጥብቀው የሚጥሩበትንም ዋና ምክንያት ተገለፀልኝ…..ሳያስቡት
ጦርነት ውስጥ ገብተዋል….››
‹‹ይሆናል ››አለኝ አባቴ….
‹‹አዎ እንዳዛ ነው ..››አልኩት
‹‹አንድ የመጨረሻ ነገር ልንገርሽ››
‹‹ምንድነው አባ››
‹‹አጎትሽ..ያ አስመለጥኩት ያልኩሽ፡፡ከዘመናት የስደት ኑሮ ቡኃላ ሰሞኑን ሊመጣ ነው፡፡ በመንግስት ጥሪ ወደሀገሩ ሊመለስ መሆኑን ደውሎ ነግሮኛል…››
‹‹የራሱ ጉዳይ›› አልኩት
‹‹ዝም አለኝ…
ሁለታችንም ድክምክም ብለን በስካር እና በሀዘን አንገታችንን ደፍተን… ተደጋግፈን ወደመኝታ ቤታቸን ስንሄድ ከላሊቱ 10 ሰዓት አልፎ ነበር ፡፡እንደገባን አልጋችን ላይ ወጥተን እቅፍቅፍ ብለን ስንተኛ ወደጆሮ ተጠጋውና ‹‹አባ አይዞህ እሺ እኔ ልጅህ ሁሌ ከእቅፍህ ውስጥ አልወጣም …ሁሌ …እና ደግሞ በጣም ነው ውደድድድድ ማደርግህ››አልኩት
ግንባሬን ሰመና ‹‹አውቃለው …እኔም ሁለ ነገሬ ነሽ….አሁን ሁሉን ነገር እርሺና ተኚ ››አለኝ
‹‹እ……ሺሺሺሺ››ረጂም ትንፋሽ...


💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
አትሮኖስ pinned «#ፍቅር_ከፈላስፋ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ_አምስት ፡ ፡ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ፡ ፡ ❤️ፌናን === ‹‹….ምን አልባት ትክክል ነሽ››አለኝ ‹‹ምኑን አባ…?›› ‹‹እውነቱን የማወቅ መብት አለሽ …እናም ነገርሻለው›› አቀማመጤን አስተካከልኩ..በስካርና በድካም እየታጠፉ የነበሩ ጆሮዎቼን ሲነቃቁና ሲዘረጋጉ ይታወቀኛል… ‹‹በዚህ የታፈነ በምትይው የእኔ እና የእናትሽ ኑሮ ውስጥ ባጣም ተጎጂው እኔ ሳልሆን…»
#ፍቅር_ከፈላስፋ


#ክፍል_ሀያ_ስድስት



ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ



#ፍሰሀ
===
በህይወቴ በጣም የተፈተንኩበት አንድ ሳምንት ነው እያሳለፍኩ ያለውት…በጣም አስጨናቂና ትንፋሽ የሚያሳጣ አይነት ሳምንት…. ደግነቱ ስራዎቼን ቀድሜ ማጠናቀቄ በጀኝ እንጂ በዚህ አይነት የጨፈገገ ስሜት እንዴት እሰራው እንደነበር ማሰቡ እራሱ ይከብደኛል ፡፡
ምክንያቱ አለመኖሯ ነው……ይሄው አይኖቼ አይኖቾን ካዩ አንድ ድፍን ሳምንት ተቆጠረ…የቤተሰብ ጉዳይ ስላጋጠመኝ ድሬደዋ ሄጃለው ነበር ያለቺኝ…እኔማ ደርሶ መልስም ቢሆን ልምጠና አንዴ አይቼሽ ልመለስ ብያት ነበር..ብትመጣም አታጋኘኝምና አትልፋ.. ይልቅ ዝግጅትህ ላይ አተኩር ፤ፍልሚያውን በድል ከተወጣህ ቡኃላ ደውልልኝ..እስከዛ እኔም እዚህ ያለውን ነገር ጨርስና እመለሳለው ካልሆነም ያለውበትን አድራሻ እነግርህና ትመጣለህ›› ስላለቺኝ… ምርጫ አጥቼ በናፍቆቷ እየተሰቃየሁ ባለቺው ተስማምቼ እጄን አጣጥፌ ቁጭ አላልኩም፡፡ምናልባት ድሬደዋ የሄደችበትን አድራሻዋን ባገኝ ብዬ ከሶስት ቀን በፊት በፊት ትሰራበት ወደነበረ ከዚህ በፊትም እንዲህ በጠፋችበት ጊዜ ወደአገኘዋት ሜክሲኮ መጽሀፍት ቤት ሄጄ ነበር ……መኪናዬን ቦታ አስይዤ በማቆም ወደ መጻሀፍ መደብሩ አመራው::ሁለት በአስራዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው ያሉት…አንደኛው ደንበኛ እያስተናገደ ስለነበረ ነፃ ወደሆነው ተጠጋሁ…
‹‹ምን መፃሀፍ ልስጥህ…..? ››አለኝ… እዚህ ቤት መፃሀፍ እንጂ ሴት ፍለጋ የሚመጣ ሰው ይኖራል ብሎ ስላልገመተ መሰለኝ ቀጥታ ስለመፃፍ የጠየቀኝ ፡፡
‹‹ፌናንን ፈልጌ ነበር..ሰሞኑን መጥታ ነበር?››
‹‹አይ ቆየች.. አስራ አምስት ቀን ሆኗታል››
‹‹ጓደኛዋ ነኝ …ማለቴ የመስሪያ ቤት ጎደኛዋ..ስልኳ አልሰራ ብሎኝ ነው ..ቢሮ ደግሞ እሷ ብቻ የምትሰራው አፋጣኝ ስራ ነበር..እና እቤቷን ልትጠቁመኝ ትችላለህ፡፡››
‹‹እቤታቸው ቤቴል አካባቢ እንደሆነ ነው እንጂ ትክክለኛውን ቦታ አላውቅም…ግን ትንሽ ብትጠብቅ እኮ ጋሼ ስለሚመጡ ትጠይቃቸዋለህ››
‹‹ጋሼ ማነው…..?››
‹‹አባቷ ናቸዋ››
‹‹እርግጠኛ ነህ ይመጣሉ?››
‹‹አዎ እንደሚመጡ ደውለው ነግረውኛል፡፡››
‹‹አይ እንደዛ ከሆነማ አሪፍ ነው.. እጠብቃቸዋለው ››አልኩ…ግን ደግሞ ወዲያው ሌላ ጥያቄ በውስጤ ተፈጠረ…‹‹ከአባቷ በጣም ትግባባላችሁ ማለት ነው?››ጠየቅኩት
‹‹እንዴ አሰሪዬ አይደሉ ለምን አንግባባም?››ሲለኝ እየገባኝ የመሰለኝ ጉዳይ መልሶ ድንግርግር አለብኝ
‹‹አሰሪዬ ስትል..…..?››
‹‹ይሄ የመፅሀፍ መደብር እኮ የእሷቸው ነው …ሌላም ቦታዎችም አላቸው››ሊያብራራልኝ ሞከረ…
‹‹ይሄ መጻሀፍ ቤት የፌናን አባት ነው?››
‹‹አዎ ››አለኝ ይሄን ሁሉ ሳታውቅ ነው እንዴ ጓደኛዋ ነኝ የምትለው በሚል ስሜት ..
ገረመኝ..ከዚህ በፊት እዚህ ባገኘዋት ጊዜ በትርፍ ጊዜዋ ተቀጥራ እንደምትሰራ ነበር የነገረቺኝ ፡፡ይሄ ሁሉ መዋሸት ለምን አስፈለገ?
በውስጤ የተፈጠረ የመደነቅ ጥያቄ ነበር…
‹‹አባቷ ጎበዝ ናቸው ማለት ነው?››አልኩት ልጁን….ስለእዚህች ሚስጥር ስለሆነች ልጅ ሌላ ተጨማሪ ሚስጥር እንዲነግረኝ በመፈለግ ለመጎትጎት ፈልጌ
‹‹እንዴ…!!!››አለና ዝም አለ
‹‹ምነው…..?››
‹‹ጋሼን አታውቃቸውም እንዴ?››
ነገሮች እንዳይበላሹ ዋሸውት‹‹አውቃቸዋለው››
‹‹አይ ጎበዝ ናቸው ስትል ገርሞኝ ነው››
‹‹ለምን ይገርምሀል…..?››
‹‹ጎበዝ ናቸው ማለት ነው ስትል በጉብዝናቸው ጥርጣሬ ያለብህ ይመስላል..እሷቸው እኮ ይሄንን የከፈቱት እኛንም ለመርዳት ነው እንጂ ጎበዝ ለመሆን አይደለም…አስተማሪነታቸው እና ደራሲነታቸው ብቻ ለጉብዝናቸው በቂ ነው››
‹‹እሱስ እወነትህን ነው››አልኩት ልክ አስተማሪም ሆነ ደራሲ መሆናቸውን እንደማውቅ ሆኜ…‹‹ አሀ የአስተማሪና የደራሲ ልጅ ነሻ?.ለዛ ነው ነገሮችን መበታተን እና መልሶ መሰብሰብ ሚያስደስታት….አሁን ገባኝ››ብዬ በወስጤ አብሰለሰልኩ…አሁን በዘዴ ብዙ ነገር እያወቅኩ ነው…ይበልጥ ለማወቅ ሌላ ዘዴ መጣልኝ፡፡
‹‹እስቲ የእሳቸው መፃሀፍ ይኖራል..…..?››
‹‹የቱን ልስጥህ……..?››
‹‹ሁሉንም የለኝም… አሪፍ ያልከውን …››
በፈገግታ ከዚህም ከዛም አየመዘዘ አምስት መፃሀፍ እጄ ላይ ዘረገፈ…
‹‹እንዴ…? ይሄን ሁሉ እንደፃፍ አላውቅም ነበር››መደነቄን መደበቅ አልቻልኩም
‹‹11 መፃሀፍ እኮ ነው ያላቸው..ይበዛብሀል ብዬ ነው የቅርቦቹን ብቻ መርጬ የሰጠውህ…. ልጁን እያዳመጥኩ ግን ደግሞ መፃሀፎቹን እያገላበጥኩ በማየት ላይ ሳለው አይኖቼ የመፃፍ ጀርባ ላይ የታተመ የደራሲው ፎቶ ላይ አረፈ ..ደነገጥኩ…. እባብ ሱሬው ውስጥ እንደገባበት ሰው አይነት ነው አደነጋገጤ ..ሰውዬውን አውቃቸዋለው፡፡ሌላውን መፃሀፍ ጀርባ ገለበጥኩ ፎቶ የለውም……ሌላውን ገለጥኩ አዎ እራሳቸው ናቸው…ከመቀመጫዬ ተነሳው….
‹‹ሂሳቡ ስንት ነው…..?››
‹‹የየትኛው…..? ››
‹‹የሁሉም››
መፃሀፎቹን ከእጆቼ ወሰደና ጀርባቸው ላይ ያለውን ዋጋ ደምሮ ነገረኝ..ከፍዬ መልስም ሳልጠይቅ ወጣሁ…
‹‹እንዴ አትጠብቃቸውም……..?››ልጁ ግራ ተጋብቶ ጠየቀኝ
‹‹ተመልሼ መጣለው ››ቻው..ተንደርድሬ መኪናዬ ውስጥ ገባውና አሁንም ድጋሜ የመጽሀፉን ጀርባ ላይ ያለውን ፎቶ አየሁት…ንዴትም ደስታም የተቀላቀለበት ስሜት ነው ተሰማኝ፡፡እኚን እኮ ነው ሹገር ዳዲዋ እንደሆኑ የነገረቺኝ ፡፡ለካ አባቷ ናቸው…?ሲያስደስት..ግን እንዴት ነው የምታስበኝ ?ይሄን ሁሉ ውሸት እንዴት ስትዋሸኝ ትከርማለች……? ስለእሷ የማላውቀው ሌላስ ምን አለ……?ይህቺ ልጅ እስከመቼ ነው እየራቀቀችብኝና እየጠለቀችብኝ የምትሄደው…?ለማንኛውም በእሷ በመታለሌ ከተበሳጨውት ይበልጥ ሹገር ዳዲዋ ናቸው ብዬ ለቀናት በንዴት ስንጨረጨር እና እንቅልፍ ሳጣበት የነበረው ጉዳይ ውሸት ሆኖ አባቷ በመሆናቸው የተደሰትኩት በእጥፍ ይበልጣል…
ከዛን ቡኃላም ስልኳ አይሰራም…ካላጋነንኩት ለመቶ የቀረብ መልዕክቶችን ልኬላታለሁ…ምንአልባት ከከፈተችው ወዲያው እድትደውልልኝ በማለት..ግን አንደዛ አልሆነም…ይገርማችሆል አንዳንዴ በውድቅት ለሊት ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ከእንቅልፌ ድንገት በርግጌ እነሳና ስልኬን አንስቼ እሞክርላታለው….ግን የተለወጠ ነገር አልነበረም፡፡ዛሬ ግን በተቻለኝ መጠን ስለእሷ ከማሰብ እራሴን መግታትና እና ትኩረቴን ሰብሰብ አድርጌ ስለፍፃሜው ጦርነት ብቻ ማሰብ ነው የምፈልገው፡፡ቀኗ ዛሬ ነች…ማንነቴን ለአባቴም ለሌላውም ሰው የማሳይበት ቀን፡፡ይህቺን ቀን አብራኝ ለወራት የለፋችው ፊናን ከጎኔ ብትሆን ኖሮ የበለጠ ጠንካራ የበለጠ ልበሙሉ እሆን ነበር…አይ የኔ ነገር አሁንም መልሼ ወደእሷ ወሰድኮችሁ አይደል፡፡

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍51
አትሮኖስ pinned «#ፍቅር_ከፈላስፋ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ_ስድስት ፡ ፡ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ፡ ፡ #ፍሰሀ === በህይወቴ በጣም የተፈተንኩበት አንድ ሳምንት ነው እያሳለፍኩ ያለውት…በጣም አስጨናቂና ትንፋሽ የሚያሳጣ አይነት ሳምንት…. ደግነቱ ስራዎቼን ቀድሜ ማጠናቀቄ በጀኝ እንጂ በዚህ አይነት የጨፈገገ ስሜት እንዴት እሰራው እንደነበር ማሰቡ እራሱ ይከብደኛል ፡፡ ምክንያቱ አለመኖሯ ነው……ይሄው አይኖቼ አይኖቾን…»
#ፍቅር_ከፈላስፋ


#ክፍል_ሀያ_ሰባት



ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ


#ፍሰሀ


ብቻ አሁን ከንጋቱ 12 ሰዓት ነው…መኝታዬን ለቅቄ ቢጃማዬን እያወላለቅኩ ወደሻወር ቤት አመራው…የሻወሩን ውሀ ለብ እንዲል አደረግኩና ገባውበት…አዎ ንጹህና ቀለል ብሎኝ መዋል ነው የምፈልገው፡፡
ዛሬ የምለብሰውን ልብስ ከአስር ቀን በፊት ነበር የተዘጋጀው…ሙሉበሙሉ በፌናን ምርጫ በጥንቃቄ ተመርጠው የተገዙ አዳዲስ ናቸው፡፡ከሻወር ወጥቼ እራሴን ካደራረቅኩ ቡኃላ ከቁም ሳጥኔ ውስጥ እያወጣው ሙሉ ቁመናዬን በጥራት የሚያሳየ መስታወት ፊት ቆሜ በጥንቃቄ ለበስኩ፡፡ፀጉሬን አስፈላጊውን ቅባት በተገቢው መጠን በመቀባት አስተካከልኩ፡፡ካሉኝ ሽቶዎች ምርጥ የተባለውን ሽቶ ሳይበዛም ሳያንስም ከተጠቀምኩ ቡኃላ ለመጨረሻ ጊዜ መስታወቱ ፊት አየተሸከረከርኩ..እየቀረብኩ ..እየራቅኩ የጎደለ ወይም የተዛነፈ ነገር ካለ አረጋገጥኩና ስልኬንና የመኪና ቁልፌን ይዤ ከመኝታ ቤቴ ወጣው
በዚህን ጊዜ ለአንድ አስር ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ፕሮግራሙ የሚጀመረው ሶስት ሰዓት ስለሆነ ገና ቡዙ ጊዜ አለኝ፡፡አባቴ እየተዘጋጀ መሆኑን ለማረጋገጥ ወደእሱ መኝታ ቤት አመራው…፡፡አዎ ተንስቷል… ምክንያቱም መኝታ ቤቱ ገርበብ እንዳለ ነው፡፡እየተቃረብኩ ስመጣ ድምጹን ሰማው …ያወራል፡፡ስልክ ላይ እንደሆነ ገባኝና ልመለስ ስል ከአንደበቱ ወጥተው ጆሮዬ የደረሱ ዓ/ነገር ጭራሽ ተጠግቼ እንዳዳምጥ ገፋፋኝ፡፡የኮቴዬን ድምጽ እንዳይሰማ ተጠንቅቄ ወደ በራፉ ቀረብኩና አጨንቁሬ ወደውስጥ እያየው ጆሮዬን ለጠፍኩ፡፡አባቴ ፊቱን ከበሩ በተቃራኒው አዙሮ የአልጋው ጠርዝ ላይ ተቀምጦ እያወራ ነው፡፡
‹‹ስሚኝ ክብረወርቅ …ዛሬም ድረስ እንደማፈቅርሽ አትዘንጊ››ይሄንን መስማቴ ነው በፈገግታ ቀሪውን የስልክ ልውውጥ እንዳዳምጥ የገፋፋኝ..‹‹አባዬ ውሽማ አለችው እንዴ..?..የሚገርም ነው….››
ከዛኛው ወገን የሚነገረው ከርቀቱ አንጻር አይሰማኝም…
‹‹ይሄውልሽ…አንቺ ለልጅሽ እንደምታዳይ ሁሉ እኔም ልጄ የፈለገውን እንዲያገኝ የማልፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም››
‹‹አይደለም..ፈፅሞ አንቺን ለመበቀል እየሰራው ያለውት ስራ የለም፡፡እርግጥ ለዓመታት እንድታገቢኝ ስማፀንሽ አሻፈረኝ ስላልሺኝ ሁሌ እንደተበሳጨውብሽ ነው፡፡አሁንም ከንዴቴ ጋር ነው ያለሁት…፡፡ቢሆንም ግን ላንቺ ያለኝ ፍቅር እዛው ድሮ ያለበት ቦታ እንደሆነ ልደብቅሽ የሚያስችል ጥንካሬ አይኖረኝም…
‹‹አዎ ባል እንዳለሽ አንድ ሺ ጊዜ ነግረሺኛል..አውቃለውም…፡፡ግን አንቺ ለእኔ የተፈጠርሽ ሴት ነበርሽ፡፡ባልሽ እኮ ምኑም ካንቺ ጋር አይሄድም፡፡አንቺን የምታህል ሚኒዬነር ነጋዴ አንድ ተራ የሀይ-እስኩል አስተማሪ አግብታ እድሜ ልኳን ከእሱ ጋር……….››
‹‹ይቅርታ ..ሁል ጊዜ ስለእሱ ሳወራ እንደምትበሳጪ አውቃለው፡፡ግን እይውእስቲ…እኔ እና አንቺ በጋራ ይሄን የመሰለ ካምፓኒ መመስረት ችለናል፡፡ለአመታት በጣም ውጤታማ ነን፡፡ይሄንን የቢዝነስ ስኬታችንን ለልጆቻችን አስተላልፈን እኔና አንቺ ወደ ፍቅር ውህደት ማለቴ ወደ ትዳር ብንገባና ቀሪ ዘመናችንን የተረጋጋ እና የሰከነ ኑሮ ብንኖር ደስ ይለኛል፡፡ምንኖረው ሀገር ውስጥም ላይሆን ይችላል ፡፡አንቺ ተስማሚ እንጂ የፈለግሽው የሀገር ጫፍ ብትይ ይመቸኛል፡፡ሰው ማይኖርበት አንታርቲካም ቢሆን ..››
‹‹የምሰማው ንግግር ከአባቴ አንደበት እየወጣ መሆኑን ማመን ተሳነኝ ‹‹…ወይ ጉድ!! ለካ ሼባው አደገኛ የፍቅር አክተር ነበረና…እኔ እንኳን እሱ በሚያወራው መጠን የማወራትና የምጀነጅናት ሴት ኖራኝ አታውቅም….. ደግሞ ተፈቃሪዋ እኮ የካምፓኒው አንዷ ባለድርሻ ነች …ለካ ይህ ጉዳይ ለእሱ ወሳኝ እንደሆነ ለመቶ ምናምነኛ ጊዜ ደጋግሞ ሲነግረኝና ሲያስጠነቅቀኝ የነበረው ሌላ ምክንያት ስላለው ነበር… አዎ አሁን ገባኝ … በመካከላቸው ያለው ጦርነት ቢዝነሳዊ ብቻ ሳይሆን ፃታዊም ነበር ማለት ነው…፡፡
‹‹ቀጥሏል አባቴ››
‹‹…በቃ እንግዲህ ….የልጅሽና የልጄ ፊልሚያ ላይ እንገናኝ፡፡እና የመጨረሻው ደስታ የእኔ ስለሚሆን ፅዋችንን በእኔ ወጪ ነው የምናነሳው…››
‹‹አታስቢ.. የልጄን ዕወቀትና ብቃት ስለማታውቂ ነው…እኔን ስለምታውቂኝ እሱንም ያወቅሽ እንዳይመስልሽ፡፡እኔን ቁጭ አድርጎ ሊያስተምረኝ ሚችል ጀግና ነው››
ከአባቴ አንደበት በዚህ አይነት ሁኔታ የራስን ልጅ ግነታዊ በሆነ ደረጃ ከፍ ከፍ እያደረገ ሲናገር መስማቱን አልወደድኩትም …ከዚህ የባሰ ነገር ተናግሮ ለወራት የገነባውትን ማንነቴን እና በራስ መተማመን እንዲሸረሽርብኝ ስለማልፈልግ ቀስ እያልኩ ወደኃላ አፈገፈግኩና ወደሳሎን ወረድኩ….
ሰራተኛዋ በምግብ ጠረጵዛው ላይ ቁርስ ደርድራ እንደጨረሰች አባቴም መጣ…
‹‹ፐፐፐፐ…ጠቅላይ ሚኒስቴር መስለሀል.››ብሎ ወደኔ ቀረበና ግንባሬን ሳመኝ..ደስ አለኝ…
ሌላውም ሰው እንደእሱ ከተሰማው አሪፍ ነው ስል አሰብኩ…በፌናን ምክር መሰረት አንዱ ነገር ተሳክቷል ማለት ነው…በዝግጅቱ ቀን የገምጋሚዎቹን ቀልብ ሰብስቦ የሚይዝ ፤በራስ መተማመንኔን በራሱ የሚያስረዳ አይነት አለባበስ መልበስ የመጀመሪያ መመሪያዋ ነበር…ሌላው ፕሮፖዛሉ ሙሉ ሰነድ እንደመሆኑ መጠን ከዛ ዋና ዋናውን ሀሳብ በአንድ ሰዓት ውስጥ ለሶስቱ ወሳኝ ሰዎች ለማቅረብ መከተል የሚገባኝን አካሄድ …
*
To make sticky idea you should be focuse on the following criteria
1/simplicity
2/un expected
3/Cridibel
4/concerete
5/Emotional
6/Story ……ትለኛለች
**
ሶስት ቀን ሙሉ ነው ስለእያንዳንዱ ነጥብ ምሳሌ በመስጠት ያስጠናቺኝ…፡፡እናም ጥናቱን ፍሬ ነገር ጨምቄ ቀላልና ግልጽ በሆነ አገላለጽ በገምጋሚዎች ላይ ያልጠበቁትን መደመም በመፍጠር ሚዛን ሚደፍ ሀሳቦችንና በሚያስምን አቀራረብ ሙሉ የጥናቱን ታሪክ በሚያስረዳ መልኩ የተጨመቀውን ሀሳብ በተሰጠኝ አንድ ሰዓት ውስጥ ማቅረብ እንድችል የተቻላትን ያህል አዘጋጅታኛለች… እኔም ብዙ ጊዜ እያፈረስኩ እየገነባው ሳምንቱን ሙሉ ተለማምጄዋለው፡፡እና አሁን ከአንድ ሰዓት ቡኃላ ይሄን የወራት ልፋቴን ውጤት የእኔም ብቻ ሳይሆን በዚህ መጠን እንድዘጋጅና ተፎካካሪዬን በብቃት እንድረታ በሚስችለኝ መጠን እንድዘጋጅ ለረዳችኝ ፊናን ልፋትም ፍሬው የሚለቀምበት ሰዓት ደርሷል፡፡ዝግጅቱን የማቀርብበት ሰዓት ….
በነገራችን ላይ ፕሮግራሙን ሳልነግራችሁ፡፡ከሶስት እስከአራት ሰዓት ባለው ጊዜ እኔ ሙሉ ሰነዱን አስረክቤ የተዘጋጀውበትን ሀሳብ በተሠጠኝ አንድ ሰዓት ውስጥ አቀርባለው…፡፡ከዛ ከአራት ሰዓት እስከ ተኩል ድረስ የምጠየቀውን ጥያቄ የምመልስበት ሰዓት ይሆናል፡፡. ከዛ የሻይ እርፍት ይኖርና፡፡ ከ5 እስከ ስድስት ሰዓት ደግሞ የሴትዬዋ ልጅ ትገባና በተመሳሳይ እንደ እኔ ያዘጋጀችውን ሰንድ አስረክባ በአንድ ሰዓት ውስጥ አቅርባ ስድስት ሰዓት ትጨርሳለች፡፡ከስድስት እስከ ስድስት ተኩል ልክ እንደእኔ በተመሳሳይ የጠየቋትን ጥያቄ የምትመልስበት ወቅት ይሆናል…፡፡
ከዛ አምስታችንም ወደምሳ ፕሮግራም እንሄዳለን፡፡ከ 6:30 እስከ 8 ሰዓት የምሳ ሰዓታችን ነው፡፡ከ8 እስከ 10 ሰዓት ሶስቱ የካምፓኒው ባለቤቶች ለብቻቸው ሰብሰባ ያደርጋሉ፡፡ በሰነዱና በቀረበላቸው ሀሳብ ላይ ይወያያሉ፡፡ለተኩል ሰዓት ሻይ ይወጣና ተፎካካሪዎቹም ባሉበት የመጨረሻ ድምጽ ይሰጣል፡፡የተሰጠው ድምጽ በግልጽ ሁሉም እያየ ይከፈታል አሸናፊው ይለይና ሙሉ ፕሮግራሙ ይጠናቀቃል፡፡
አሁን ከጥዋቱ 2፡40 ሆኗል እኔና አባቴ ቢሮ ደርሰናል፡፡ጋሼ ከበደ ከእኛ አምስት ደቂቃ ዘግይተው
👍4
ደረሱ… ሳላስበው ስሜታዊ ሆኜ ከወትሮ ሞቀ ባለ እና ቀብድ በሚመስል አይነት ሰላምታ ሰጠዋቸው፡፡እውነቱን ለመናገር አሁን ለማየት የፈለኩት ሴትየዋን ነው፡፡ወ/ሮ ክብረወርቅን ፡፡እወነቱን ንገረን ካላችሁ ምን እሷን ለማየት ጓጓለው ..ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ በአካልም በቴሌቬዝን ላይም አይቻታለው፡፡ስለዚህ ጉጉቴ ሌላ ነው …ለማየት የጓጓውት ልጇን ነው፡፡ተፎካካሪዬን…ምን ትመስል ይሆን …?ቆንጆ ነች አስጠሊታ? ዘናጭ ነች ዝርክርክ..?ንግግር አዋቂ ነች ወይስ ሞዛዛ ዝም ብላ የሀብታም ልጅ.?
አባቴንና ሽማግሌውን አንድ ላይ ጥያቸው የግል ቢሮዬ በመግባት መስኮት ላይ ተለጥፌ ወደታች እያየው ነው፡፡ወደታች ወደ መግቢያው በር…ማንን ነው የምጠብቀው……? ተፎካካሪዬን፡፡ምንድነው እንደዚህ ያስጨነቀኝ……?ምንም ቢሆን ምንም ከደቂቃዎች ቡኃላ ማየቴ እደሆነ አይቀር…ስል አንድ የማውቃት ግን የካምፓኒው ያልሆነች መኪና ስትገባ አየው፡፡ልቤ ትርትር ነው ያለችው፡፡ይህቺን መኪና አውቀታለው፡፡ በቢሾፍቱው የካምባኒው ዝግጅት ጊዜ ፊናን ይዛት የነበረችው አይነት መኪና ነች፡፡ፌናን መጣች ማለት ነው?፡፡በውስጤ ደስታ ሲፈስ ታወቀኝ … መስኮቱን ለቀቅኩና በፍጥነት ቢሮዬን ለቅቄ በመውጣት ሊፍቱን አንኳን መጠበቅ አቅቶኝ ወደታች ወደግራውንድ በደረጃ እየተንደረደርኩ መውረድ ጀመርኩ፡፡ሰራተኞቹ ሁሉ ምን ተፈጠረ እያሉ በአግራሞት ሲመለከቱኝ ብታዘብም ቁብም አልሰጠኝም ፡፡አዎ ታፈቅራኛለች ማለት ነው.? በዚህች ቀን ከጎኔ ልትሆን ከወሰነች ይህን አይነት አሳቢነት ከፍቅር ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ምን አይነት ብርሀናማ ቀን ነው…? ፌናን የእኔ ቆንጆ ግራውንድ ወርጄ እሷን ለማየት አይኖቼን ሲቅበዘበዙ ሴትየዋ ከፊት ለፊቴ ገጭ አለች…. የተፎካካሪዬ እናት ወ/ሮ ክብረወርቅ ፡፡ፊቴን እንደጨመዳድኩ ወደእሷ ቀረብኩና ሰላምታ ሰጠዋት…..
‹‹…ትልቅ ሰው ሆነህ የለ እንዴ…? ››በሚል አድናቆት በሞቀ ሰላምታ ምላሽ ሰጠቺኝ..ግራ ገባኝ..፡፡ዙሪያዋን ቃኘው ብቻዋ ነች ፡፡ልጇስ …..?…ተፋላሚዬ የት አለች……..?ደግሞ ፌናንስ …?መኪናዋን ልታቆም ቤዝመንት ገብታ መሆነ አለበት
‹‹ልጆትስ……..?››
‹‹እየመጣች ነው››
‹‹አሪፍ ነው በቃ ይግቡ መጣው ››ብያት አልፌ ወደቤዝመንት ገባው ..ከላይ ያየዋት የፌናን የመሰለቺኘ መኪና በስርዓት ቆማለች፡፡ፌናን ግን የለችም፡፡በየት ጋር አልፋኝ ወደላይ ወጣች፡፡በሊፍት ይሆናል…ወጣውና ዘበኛውን ጠየቅኩት፡፡
‹‹አይ እሷ አይደለችም..እሳቸው ናቸው… አሁን ሰላም ያልካቸው ትልቅ ሴትዬ..መኪናዋ የእሳቸው ነች›› አለኝ..
በቅርብ የተቀጠረ ስለሆነ ሴትየዋን አያውቃቸውም::ደሜ በአንዴ ረጋ…ካልጠፋ መኪና የእኔን ቀልብ ለመረበሽ እንዴት ተመሳሳይ መኪና እየነዳች ትመጣላች?በፊትም ብዙም አልወዳትም አሁን ደግሞ አስጠላችኝ::አይ ማስጠላት እንኳን አላስጠላቺንም ምንም ቢሆን የአባቴ ውሽማ አይደለች..?ግን አናዳኛለች…በጣም..፡፡
አሁን በደረጃ የመውጣቱ ሞራል ስለሌለኝ ጠብቄ በሊፍት ወጣው::ሶስቱም በስብሰባ አዳራሽ ዝግጁ ሆኖ እየጠበቁኝ ነው::ሰዓቱም 5ደቂቃ ብቻ ነው የቀረው::ሰዓት ማክበርም አንዱ መስፈራታቸው ሊሆን ስሚችል ብዬ ቤሮዬ ገባውና ሠነዶችንና ለገለፃ ሚረዱኝን ማቴሪያሎች ሁሉ በፀሀፊዬ አስይዤ ወደ አዳራሹ ገበው::አባቴና አቶ ከበደ ከግራና ከቀኝ ወ/ሮ ክብረወርቅን መሀካል አድርገው አስፈሪ በሆነ ሁኔታ በመደዳ ተቀምጠዋል::የሆነ በሞት ወንጀል ተጠርጥሮ የመጨራሻ ፍርድ ሊሠጡ የተሰየሙ ዳኞች መስለው ታዩኝ::የገዛ አባቴ እራሱ አኮሰታተሩ ይገፋተራል::ከደቂቃዎች በፊት በፈገግታ ሲያበረታታኝ እና ግንባሬን እየዳበሰኝ ሲያጀግነኝ የነበረው አባቴን አልመስል አለኝ::እንዴ ይሄ ሁሉ ጨለማ ፊት ምንድነው …?የድንበር ጉዳይ አደረጉት እኮ..፡፡
….ልጀምር ሰዓቴን ለማየት ሞባይሌን እያወጣው ባለውበት ቅጽበት ስልኬ ጠራ አየውት::ቀጥታ እየተንደረደርኩ ወደውጭ ነው የወጣውት:: ፌናን ነች ፡፡ደወለቺልኝ…፡፡በረንዳ ላይ እደደረስኩ አነሳውት
‹‹አንቺ አለሽ?ምን ሆነሽ ነው ግን..…..?ሰው ይጨነቃል አትይም እንዴ…..?››ወቀሳዬን አዝጎደጎድኩት
‹‹ተረጋጋ..አሁን እኮ መጥቼያለው…››ዘናና ለስለስ ባለ ድምፅ
‹‹የት ነው ያለሽው .. …..?ቢሮ ነሽ ልምጣና ልይሽ…››
‹‹አረ ገና እቤት ነኝ…ከአንድ ሰዓት ቡኃላ እመጣለው…››
‹‹እፎይ በመደወልሽ እና ድምጽሽን በመስማቴ አንዴት ደስ እንዳኝ ልትገምቺ አትቺይም ..››
‹‹ ልፋታችንን አደራ ልልህ ነው የደወልኩት..አሪፍ አድርገህ በሙሉ በራስ መተማመን አቅርብላቸው…ለአንድ ስራአስኪያጅ ከሚሰራው ስራ እኩል ኮሚኒኬሽን እስኪሉም ወሳኝ ነው፡፡ተናግሮ የማሳመንና የመደራደር ብቃትህን ይፈልጉታል::በምታቀርበው:: ሁለት ዲግሪ ስለሌላቸው ዝቅ አድርገህ እንዳትገማታቸው::ከህይወት ውጣውረድ በልምድ ያገኙት በብዙ ዲግሪዎች የሚመነዘር የዳበረ ዕወቀት ባለቤት ናቸው››
‹‹ይሄን እኮ ብዙ ጊዜ ነግረሺኛል ::እንኳን ድምጽሽን ሰማው እንጂ አደርገዋለው…››
‹‹እንደምታደርገው አውቃለው…ከአንድ ሰዓት ቡኃላ እንገናኛለን…››
‹‹እሺ በጣም ነው የማፈቅርሽ ::ጨርሼ ስወጣ ቢሮዬ ወይም በረንዳው ላይ እንደማገኝሽ እርግጠኛ ነኝ››
‹‹እሺ ቻው››
‹‹ስልኬን መዝጋት ብቻ ሳይሆን አጠፋውና በፈገግታ ወደውስጥ ገባው…ቀጥታ ለሶስቱም የተዘጋጀውን ሰነድ ካስረከብኩ ቡኃላ
ፊት ላፊታቸው ቆሜ ወደ ገለፃዬ ለመግባት ጉሮሮዬን አፀዳዳው፡፡በፋካ ፊት…በተረጋጋ ስሜት….በሙሉ የራስ መተማመን…..

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
👍2
አትሮኖስ pinned «#ፍቅር_ከፈላስፋ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ_ሰባት ፡ ፡ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ፡ ፡ #ፍሰሀ ፡ ፡ ብቻ አሁን ከንጋቱ 12 ሰዓት ነው…መኝታዬን ለቅቄ ቢጃማዬን እያወላለቅኩ ወደሻወር ቤት አመራው…የሻወሩን ውሀ ለብ እንዲል አደረግኩና ገባውበት…አዎ ንጹህና ቀለል ብሎኝ መዋል ነው የምፈልገው፡፡ ዛሬ የምለብሰውን ልብስ ከአስር ቀን በፊት ነበር የተዘጋጀው…ሙሉበሙሉ በፌናን ምርጫ በጥንቃቄ ተመርጠው የተገዙ አዳዲስ…»
#ፍቅር_ከፈላስፋ


#ክፍል_ሀያ_ስምንት



ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ



#ፍሰሀ
===
ልዩ የሆነ ቆይታ ነበር፡፡ሶስቱንም ፈታኞቼን እንዳስደመምኮቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡መድረኩን በስነስርዓት፤ ባጠናውት እና በተዘጋጀውት መጠን ነበር የተወጣሁት፡፡በመጨረሻ ሁሉም ወ/ሮ ክብረወርቅም ጭምር ቆመው ነበር ያጨበጨብልኝ፡፡እኔም በደስታ ሰክሬ ከወገቤ ሽብርክ ብዬ አመሰገንኳቸው፡፡
ለመውጣት ቸኩያለው ቀልቤ ያለው ፌናን ጋር ነው፡፡እስከአሁን ከቤቷ መጥታ ውጭ በረንዳ ላይ ወይም ቢሮዬ ቁጭ ብላ እደምትጠብቀኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡አዎ አይኖቼ መላ እሷነቷን ተርበዋል፡፡ከራሴ በላይ እወደዋለው፡፡ ብዬ የማስበው አባቴ እንኳን ከስድስት ወር ባላይ ተለይቶኝ ሲኖር በዚህ መጠን ናፍቆኝና ተርቤው አላውቅም…
ናፍቆቴ የቱንም ያህል ቢሆን ግን እነሱን ቀድሜ መውጣት በአይን አውጣነት የሚያስፈርጀኝ መስሎ ስለተሰማኝ እንደምንም ስሜቴን ተቆጣጥሬ እየታገስኩ ነው፡፡እነሱ በእርጋታ የሚንቀሳቀሱትን ሽማጊሌውን አስቀድመው እየተጎተቱ ክፍሉን እስኪለቁልኝ መጠበቅ ግድ ሆነብኝ፡፡ይባስ ብሎ አባቴ ወደእኔ መጣ፡፡ተጠመጠመብኝ ፡፡ምን ላድርግ …?መልሼ በተመሳሳይ አቀፍኩት፡፡ለዚህች ቀን አይደል ስንት ወር ሙሉ ሲወተውተኝ የነበረው?እሱ ያልተደሰተ ማን ይደሰታል……?ግን እሱ ያላወቀው እንዲህ መታቀፍ ያለብኝ እኔ ሳልሆን ፌናን መሆኗን ነው፡፡ግድ የለም ..እሱ እኔን ባቀፈኝ መጠን እኔ ደግሞ ከደቂቃ ቡኃላ እሷን አቅፋታለው፡፡.ጭምቅ አድርጌ አቅፋትና ምስጋናዬን አቀርብላታለው፡፡ምስጋናዬን ብቻ ሳይሆን ዛሬ ማታ አፕል አበረክትላታለው፡፡አዎ ጥንት ግሪካዊያን ለሚያፈቅሩት ሰው አፕል ነበር የሚልኩት አንተም የምታፈቅረኝ ከሆነ ከዝግጅቱ ቡኃላ አፕል ላክልኝ የዛን ጊዜ መልሱን ነግርሀለው አይደለ ያለቺኝ?ዋው..ማታ እራት ጋብዛታለው::ከዛ አፕል እሰጣታለው::አፕሉ ውስጥ ደግሞ ቀለበት ይኖርታል::አብረቅራቂ የአልማዝ ቀለበት::ይህንን በማሰቤ ውስጤ ዘላለማዊ በሚመስል ደስታ ተጥለቀለቀ
‹‹በጣም ነው ያኳራኸኝ…እጅግ በጣም ከጠበቅኩት በላይ ጀግና ሆነህልኛል ለካ?አሁን እርግጠኛ ሆነህ ካማፓኒውን በቋሚነት ለመረከብ ተዘጋጅ..››አለኝ አባቴ ሌሎቹ ሊሰሙት በማይችሉት ዝቅተኛ ድምጽ
‹‹እሺ አባዬ አመሰግናለው፡፡››
‹‹ና እንውጣ›› አለኝና ትከሻዬን በኩራት አቅፎ ወደውጭ ይዞኝ ወጣ::በራፍ ላይ እንደደረስን በሃያ ሜትር ርቀት ፌናን ቀድመውን ከወጡት ጋሽ ከበደ እና ከወ/ሮ ክብረወርቅ ጋር ሲያወሩ ለዛውም እየተሳሳቁ ተመለከትኩ
እኔም አባቴም ሳንነጋገር እርምጃችንን እዛው በራፍ ላይ ገታነው::እንዴት አምሮባታል ?ይህ ሁሉ ውበት እንዲህ ጎልቶ እና ፈክቶ የወጣው ከእራሷ ከአፈጣጠር ነው ወይስ ከአለባበሷ…?ልቤ እንደለመደችው ቅልጥልጥ አለች…ግን ከሰዎቹ ጋር የት ተዋውቃ ነው እንዲህ በመፈንጠዝያና በፈገግታ የምታወራቸው……?
‹‹አንተ ተፋላሚህ መታልሀለች::ደግሞ እንዴት ታምራለች……?ልክ እንደእናቷ ››አባቴ ነው በአድናቆትና በስጋት መሀከል በሚዋልል ስሜት የተናገረው…
‹‹አባ እሷ አይደለችም::ይህቺ እኮ የእኔ ረዳት ነች››አረምኩት
‹‹እርግጠኛ ነህ…?ፎቶዋና እኮ እናትዬው ያሳየቺኝ መሰለኝ..ለማንኛውም ና ወደ እነሱ እንሂድ..››አለኝና ተያዘን ስራቸው ደረስን …ፌናን ዞር ብላ እንዳየችኝ ተሸከርክራ ተጠመጠመችብኝ….በጣም እንደናፈቀቺኝ ያወቅኩት ሁሉም እያዩኝ ያለይሉኝታ ልክ እንደ ህጋዊ እጮኛዬ አቅፌ በአየር ላይ ሳንጠለጥላት ነው….
አባቴ ‹‹ክብረወርቅ ልጅሽ ነች እንዴ…?››ብሎ ሲጠይቅ በጆሮዬ ገባ..
‹‹አዎ ልጄ ነች::ፌናን ሰላም በይው…››የሰማውትን መልስ ማመን አቃተኝ….. ምንድነው እየተካሄደ ያለው..?.ከእሷ ሸሸት እልኩና እናትዬው ላይ አፈጠጠኩባት
<<…ምን ተፈጠረ …?በሚል ግራ በተጋባ አሰተያየት ንግግሯን ቀጠለች‹‹እንዲህ ምትግባቡ አይመስለኝም ነበር››ለእኔ ነው የምትለኝ ፡፡
‹‹ፌናን ያንቺ ልጅ ነች…?››አንቱነታውንን እረስቼ የአባቴን ጥያቄ መልሼ ደገምኩ
‹‹አዎ ..ፌናን ልጄ ነች..ምነው …?አልነገረችህም እንዴ……?››
ወደ እሷ ተንደረደርኩና ሁለት ትከሻዋን ጨምድጄ ያዝኳት …ሶስትም ደነገጡ‹‹በጣም ባለጌ ነሽ..በጣም አታለሺኛል..መቼም ይቅር አልልሽም….››
ይሄን ሁሉ ስላት እሷ ምንም እንዳልተፈጠረ በግማሽ ፈገግታ እያደማጠቺኝ ነው…ገፍትሬ አባቴ ትከሻ ላይ ወረወርኳትና ወደቢሮዬ ተንደረደርኩ…
‹‹ምንድነው ነገሩ?ልጄን ምን አደረጋችሁት…?››የአባቴ ድምጽ እየተሰማኝ ነው…ቤሮዬን ገባውና ከውስጥ ቀረቀርኩ.. ቢያንኳኩም ልከፍትላቸው አልፈለኩም..ትንሽ ይብረድለት ብለው መሰለኝ ትተውኝ ዞር አሉ….እኔም ምፈልገው ያንን ነበር፡፡
…….ታንቄበት የዋልኩትን ከረባት ከአንገቴ ፈትቼ ጥዬ ኮቴን አውልቄ በመወርወር ወንበሬ ላይ ቁጭ ብዬ አንገቴን ጠረጳዛ ላይ ደፍቼ አነባው ጀመር::እንዲህ አይነት ለቅሶ ካለቀስኩ ስንት ዓመት እንዳለፈኝ ትዝ አይለኝም::ንፍጤ እስኪዝረከረክ ድረስ ነው ያለቀስኩት፡፡በህይወቴ አንድ ሰው በዚህ መጠን ተጫውቶብኝና አታሎኝ አያውቅም::እንዴ አምኜያት ነበርኮ..?በአድናቆት ፈዝዤያለት አፍቅሬያትና ብዙ ብዙ ህልም አልሜላት ነበር…?እንዴት አንዲህ ትሰብረኛለች?ይህችን ካምፓኒ ለማስተዳደር ብላ……?እኔ እኮ ከካምፓኒው ስራ በላይ ነበር ያፈቀርኳት…
…እያንዳንዷን የሰራዋትን ጥናት ቃል በቃል ታውቀዋለች፤ ምክንያቱም አብረን ነው የሰራነው.፡፡ስለዚህ የእሷ ዝግጅት የእኔን ጥናት አይታና ከእዛ በበለጠና ያንን በሚያጠቃ መልኩ ለማዘጋጀት እድሉን አግኝታለች… .በዛ ላይ ችሎታዋን አውቃዋለው..እና እንዴት ነው ከእሷ በልጬ ይሄን ቦታ የማገኘው…?ተዋረድኩ….፡፡በቃ ሁሉ ነገር አስጠላኝ ::ስራው አስጠላኝ ..ካምፓኒውም አስጠላኝ ..ያፈቀርኮት ልጅ አስጠላቺኝ…ሀገሬም አስጠላቺኝ …፡፡መመለስ አለብኝ…አዎ ወደመጣውበት ሀገር እመለሰላው..ስደት ይሻለኛል..ስራዬን እየሰራው ሶስትኛ ዲግሪዬን ብማር ይሻለኛል..::እንደውም በተጨማለቀ ሀገር የተጨማለቀ ኑሮ ለመኖር ምንድነው እንደዚህ አፈር የሚያስግጠኝ..…?ወሰንኩ…እንባዬን ከጉንጬ ላይ ጠራረግኩ…ኮምፒተሬን ከፈትኩና መጻፍ ጀመርኩ…ለቦርድ አባላቱ ነው::የካምፓኒውን ስራ ስለማልፈልገው ውድድሩ እንዲቀርና ስራውንም በገዛ ፍቃዴ መልቀቄን የሚገልጽ ደብዳቤ …ፕሪንት አድርጌ ፈረምኩበትና ኮቴን መልሼ በመልበስ ወጣው…ሰራተኞቹ ሁሉ ለምሳ የወጡ ቢሆንም ጸሀፊዬ ግን ስጠብቀኝ ነበር….
‹‹አሁን የቦርድ አባሎቹ ሲመጡ ይሄንን ማመልከቻ አስገቢልኝ›› አልኩና በካኪ ፓስታ የታሸገውን ማመልከቻ ሰጠዋት
‹‹አባትህ ደጋግመው ሲደውሉ ነበር…ምሳ እየጠበቅንህ ነው ፤ደውልኝ ብለውሀል…››
‹‹ዝም በይው::ስልኬን ዘግቼዋለው …ከደወለ ወጥቼ እንደሄድኩና እንደማልመለሰም ንገሪው……››
‹‹አንተ ግን ሰላም ነህ…?›ሁኔታዬ ስላላማራት መሰለኝ የጠየቀቺኝ
‹‹ሰላም ነኝ ….አመሰግናለው…››ጥያት ወጣው…..

💫ይቀጥላል💫

Like 👍👍 ማድረግ እንዳይረሳ

ማንኛዉንም አስተያየት በ @atronosebot አድርሱን
አትሮኖስ pinned «#ፍቅር_ከፈላስፋ ፡ ፡ #ክፍል_ሀያ_ስምንት ፡ ፡ ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ ፡ ፡ #ፍሰሀ === ልዩ የሆነ ቆይታ ነበር፡፡ሶስቱንም ፈታኞቼን እንዳስደመምኮቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡መድረኩን በስነስርዓት፤ ባጠናውት እና በተዘጋጀውት መጠን ነበር የተወጣሁት፡፡በመጨረሻ ሁሉም ወ/ሮ ክብረወርቅም ጭምር ቆመው ነበር ያጨበጨብልኝ፡፡እኔም በደስታ ሰክሬ ከወገቤ ሽብርክ ብዬ አመሰገንኳቸው፡፡ ለመውጣት ቸኩያለው ቀልቤ…»