አትሮኖስ
286K subscribers
121 photos
3 videos
41 files
572 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ምንዱባን


#ክፍል_አሰር


#ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ


የፋንቲን ታሪክ ምን ዓይነት ታሪክ ነው? ያሽከር ታሪክ! አሽከርን
የሚገዛው ሕብረተሰቡ ነው?
ከማን?
ከችግር? ከመከራ? ከስቃይ? ከረሃብ? ከብቸኝነት? የሚቀፍ ግዢ ነፍስ በዳቦ ሲለወጥ! ችግር ግለሰቦች ያልፈቀዱትንና ያልፈለጉትን እንዲሠሩ
ሲያስገድዳቸው! ሕብረተሰቡ ደግሞ በግዳጅ የሚያደርጉትን በደስታ ሲቀበል አይገርምም!

ባርነት ቀርቷል ይባላል፡፡ ውሸት ነው፧ አልቀረም:: አሁንም አለ።
ግን በአሁኑ ጊዜ ጎልቶ የሚታየው በሴቶች ላይ ነው:: ስሙን ቀይረው
ዝሙት አዳሪ ይሉታል፡፡

እስካሁን ባየነው ድራማ ፋንቲን ቀደም ሲል የነበራትን ሁሉ አሟጥጣ ጨርሳ የቀራት ነገር የለም :: ክብርም፧ ስምም፧ እናትነትም፤ ውበትም ምኑ ቅጡ ሁሉም ሄዶአል:: ቢነኳት አካልዋ እንደ በረዶ ቀዝቅዟል። ስሜትዋም ሞቷል፡፡ የፈለገችውን ነው የምታደርገው:: እያወቀች
አታውቅም ፡ እየሰማች አትሰማም፡፡ የተከፋን ፊት አንግታ፤ ሆድ የባሰውን ልብ ተሸክማ እያየ የማያይ ዓይን ሰክታ እየሰማ የማይሰማ ጆሮ አንጠልጥላ እንደፈቀደችው ትኖራለች:: ሕብረተሰቡም ሆነ ሕይወት ከፋንቲን ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ፡፡ እሷም ለምንም ነገር ደንታ አጣች፡፡ሊደርስባት የሚችል መጥፎ ነገር ሁሉ ደርሶባታል፡፡ እርሷም የቻለችውን ያህል ተሸክማዋለች፡፡ ሁሉንም አየችው:: የነበራትን ሁሉ አጣች:: ለሁሉም
አለቀሰች፤ አነባች፡፡ ታዲያ አሁን ምን ይሁን? ሁሉንም እርግፍ አድርጋ ተወችው:: ምቾትና ድሎት ችግርን ስለማያውቁት እንደማይጨነቁለት
ሁሉ እንዲሁም ሕፃን ሞት እንቅልፍ መስሎት ዝም እንደሚል ሁሉ እርስዋም ምንም ነገር እንዳልሆነ ቆጥራ ችግር አልተው ቢላት እርስዋ ተወችው:: የምትፈራው ወይም የምትሸሸው ነገር የለም:: ደመና
ቢያጠልልባት፣ ውቅያኖስ ቢደፋባት ምን ደንታ አላት! የኑሮዋ ስፍንጎና ሞልቶ ፈስሷል፡፡

የፋንቲን እምነት ይህ ነበር፡፡ ግን ተሳስታለች:: ማነው እስቲ
መጨረሻውን የሚያውቅ? ዛሬ እንዴት እንደሚያልፍ፤ ነገ ደግሞ እንዴት ሆኖ እንደሚመጣ ማን ያውቀዋል? ሁሉንም የሚያውቅ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው::

ትንንሽ ከተማዎች ውስጥ አሉ አይደል ኣንዳንድ ልባቸው ያበጠ
ጎረምሶች! በትንሽ ገቢ እንደ ሀብታም የሚንቀባረሩ! ጉራቸው አያድርስ፤ ሳይኖራቸው ሀብታም፧ ሳይማሩ ተመራማሪ፧ ያልሆኑትን ለመሆን ሞካሪ፤ ቡና ቤት ሲገቡ የሚጀነኑ፤ ሲጃራ ማጨስ፤ ሸሚዝ መጠቅለል፤ የጫማ ተረከዝ ማስረዘም፧ ሳይነኩ መነጫነጭ፤ «እስቲ ቅጂ እባክሽ» ማለት፧ ሻይ
ቤት የሚያዘወትሩ፤ አላፊ አግዳሚውን የሚለክፉ፧ ይህን የመሰሉ ሰዎች የትም አሉ:: በተለይ ትንንሽ ከተማ ውስጥ እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ
እየደደቡ የሚሄዱና በአንጎላቸው ሳይሆን በቂጣቸው የሚያስቡ ሞልተዋል፡፡

በ1823 ዓ.ም. ይህን የመሰለ ጠባይ የነበረው አውደልዳይ፤ ጎፈሬ ብርቁና ዘመናዊ መስሎ በሰው ስቃይ የሚደሰት ጎረምሳ ነበር:: ይህ ጎረምሳ ሰው ከተሰበሰበበት ቡና ቤት ላይ ታች የምትለውን፧ ኑሮ ያንገላታትን፤
የማይሆን ልብስ የለበሰችውና ክበር ገላዋን ለጎረምሳ አሳልፋ የምትሸጠዋን ሴት ደጋግሞ የሚለክፍ ወጣት ነበር፡፡ አንድ ቀን ፋንቲንን እንደልማዱ ለከፋት:: እንዳልሰማ ዝም አለችው:: ሲጃራ ማጨስ ፋሽን ነውና ተመልሳ
በአጠገበ ስታልፍ የሲጃራ ጭስ አቦነነባት:: በአጠገቡ በአለፈች ቁጥር «ፉንጋ፧ ኡኡቴ፣ የምን መኮሳተር ነው? ጥርስ አልጠፋብሽም? እና ሌላም
ሌላም እያለ ሰደባት:: ይህ ሰው ፋንቲንን ሲያናግራት ቀና ብላ እንኳን አላየችውም:: ልክ ቅጣት እንደተወሰነበት ወታደር ከወዲያ ወዲህ ገልመጥ ሳትል ወደፊት ትሄድና ትመለሳለች:: አሁንም እንደገና ወደፊት ትሄድና
ተመልሳ ትመጣለች:: ሰውዬው ብዙ ጊዜ ከለከፋት በኋላ በመጨረሻ ዝም ስትለው በጣም ተናድዶ ኖሮ ቀስ ብሎ ተከትሎአት ይሄድና ልክ ለመመለስ ፊትዋን ስታዞር መንገድ ግራና ቀኝ ተቆልለ ከነበረው በረዶ ያነሳና
በጀርባዋ በኩል ይመታታል፡፡ ይህን ጊዜ ልክ እንደነብር ዘልላ አንገቱ ላይ በመጠምጠም በጥፍርዋ ፊቱን ደም በደም አደረገችው:: ሰምቶት የማያውቅ
የስድብ ናዳ አወረደችበት፡፡

ጩኸትዋ በአካባቢው ከነበረው ሻይ ቤት ተሰምቶ ሰዎች ምንድነው ብለው ወጡ፡፡ ቀስ በቀስ ብዙ ሰው ተሰበሰ ሰውዬው አልሞት ባይ ተጋዳይ ከሚቧጥጠው ጥፍር ይከላከላል፡፡ የተሰበሰበው ሕዝብ «ብራቮ እያለ ይስቃል፤ ያጨበጭባል፡፡ ፋንቲን መቧጠጥ ብቻ ሳይሆን በጥፊ በርግጫ
ትማታለች፡፡
ድንገት አንድ እረጅም ሰው እየሮጠ መጥቶ ሴትዮዋን በጭቃ
የቦካውን ወገብዋን ይዞ «በይ ተከተዪኝ አላት::

እንገትዋን ቀና አደረገች፡፡ የጋለው ሰውነትዋ በረደ ፣ በቁጣ የነደደው
ድምፅዋ ቀዝቀዝ አለ፡፡ በፍርሃት ተንቀጠቀጠች፡፡ የፖሊሱ አዛዥ ዣቬር እንደሆነ አውቀች::

በግርግር አውደልዳዩ ሹልክ ብሎ ከዚያ ጠፋ::

ከዚያ ከብበው የቆሙትን ሁሉ ዣቬር በተናቸው:: ከዚያም ሴትዮዋን እየጐተተ ወደ ቢሮው ወሰዳት፡፡ ቢሮው ከዚያ ሩቅ አልነበረም:: ሴትዮዋ ብዙም ሳታመነታ ተከተለችው:: ቃል አልተነፈሰችም፡፡ ተሰብስቦ የነበረው ሕዝብ ሴትዮዋን ለእብደት በሚዳርግ ፌዝና ሰቆቃ አሽሟጠጣት::

ከፖሊስ ጣቢያ እንደደረሱ ዣቬር በር ከፍቶ ፋንቲንን ይዞ ገባ፡፡ በሩን
መልሶ ዘጋው:: ፋንቲን እንደ ፈራ ውሻ ቃል ሳታሰማ ጥግ ይዛ ከወለሉ ላይ ቁጭ አለች፡፡ ዘበኛው መብራት አበራ፡፡ ዣቬር ከኪሱ ወረቀት አውጥቶ መጻፍ ጀመረ::

የፖሊሱ አዛዥ ኮስተርተር ያለ ሰው በመሆኑ ፊቱ ላይ የመቅበጥበጥ
ምልክት አይታይበትም፡፡ ሕግን የማስከበር ጥማቱ የሚያረካባት ቅጽበት በመሆኑ ሥልጣኑን ለማሳየት ተነሳሳ፡፡ የተቀመጠበት ወንበር ትክክለኛ ፍርድ የሚሰጥበት ሥፍራ እንደሆነ ከልቡ ያምናል፡፡ ከሳሽም፧ ፍርድ
ሰጪም ራሱ ነው፡፡ የሴትዮዋን አድራጎት በይበልጥ በአጤነ ቁጥር ወንጀለኝነቷን ከመጠራጠር ይገታል፡፡ ወንጀል ስትፈጽም በዓይኑ አይቷል፡፡ አንዲት
ሴት አዳሪ አንዱን የከተማ ነዋሪ ከሰው ፊት ደብድባለች፡፡ ለዚህ ጥፋት ዣቬር ራሱ የዓይን ምስክር ነው፡፡ ፀጥ ብሎ ሁኔታውን መዘገበ፡፡

የጊዜውን ራፖር መዝግቦ ሲጨርስ ፊርማውን አኖረበት፡፡ ወረቀቱ አጣጥፎ ለዘበኛው ሰጠው::
«ሦስት ሰዎች ይዘህ ይህችን ሴት እስር ቤት ውሰድዋት፡፡»
ወደ ፋንቲን ዞር ብሎ «የስድስት ወር እስራት ተፈርዶብሻል» አላት፡፡
እድለ ቢስዋ ሴትዮ ሰውነትዋ ተንቀጠቀጠ፡፡
«ስድስት ወር! ወህኒ ቤት ውስጥ ስድስት ወር ሙሉ!» ብላ በኃይል
ተነፈሰች፡፡ «ልጄስ!» ስድስት ወር ሙሉ ምን ልትሆን ወይኔ ልጄ! እስከዛሬ ለእነቴናድዬ ያልከፈልኩት ከመቶ ፍራንክ በላይ እዳ አለብኝ፡፡ ጌታዬ ይህን
ያውቃሉ?» ስትል ዣቬርን ጠየቀችው::

መሬት ላይ ተንከባለለች:: ሦስቱ ሰዎች ከአፈሩ ላይ እንደወደቀች
ጎትተው አስወጥዋት::
«መሴይ ዣቬር ማሩኝ፡ ይቅር በሉኝ» ስትል ጮኸች:: «ምንም
ዓይነት በደል እንዳልፈጸምኩም! እምልልዎታለሁ:: ከመጀመሪያው ጀምሮ ከሥፍራው ቢኖሩ ኖሮ እውነቱን ያዩ ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ!
👍161🔥1
ሰውዬውን አልበደልኩትም:: ያ የማላውቀው ሰውዬ በረዶ አፍሶ ነው የመታኝ፡፡ ዝም ብሎ የሚሄድ መንገደኛን በበረዶ የመምታት መብት አለው? እስቲ ይፍረዱኝ! ያ ነው አውሬ ያደረገኝ፡፡ እንደሚያዩኝ ጤነኛ አይደለሁም፡፡ ሰውዬው አንቺ ወላቃ! አንቺ ዱርዬ' እያለ ሰድቦኛል፡፡ ጥርስ እንደሌለኝ አውቃለሁ! ቢሆንም ያስከፋኛል፡፡ ይህ ሆኖብኝ ነው እንጂ
ሆን ብዬ ያደረግሁት አይደለም:: እርሱ ዝም ብሎ ነካካኝ እንጂ እኔ
አልደረስኩበትም፡: ዝም ስለው በረዶ አንስቶ መታኝ፡፡ ጌታዬ መቶ ፍራንክ ያልተከፈለ እዳ አለብኝ፡፡ እዳዬን ካልከፈልኩ ልጄን ከቤታቸው አስወጥተው
ሜዳ ነው የሚጥሉብኝ፡፡ ጌታዬ ስለልጄ ብለው ይራሩልኝ፡፡ እኔ ዘንድ እንዳላመጣት አቅም የለኝም:: እዩ ጌታዬ ከቤታቸው አስወጥተው መንገድ
ከጣልዋት ራስዋን ለመጠበቅ የማትችል ሕፃን ናት፡፡ ጊዜው ደግሞ ክረምት ነው፡፡ ለጨቅላዋ ልጄ ይዘኑላት ጌታዬ! በእድሜ ከዚህ ትንሽ ከፍ ያለች ብትሆን እንኳን እንደምንም ብላ ከወዲያ ወዲህ ተሯሩጣ መኖር ትችል
ነበር፡፡ በዚህ እድሜዋ ግን አትችልም:: ይራሩልኝ፤ ይዘነልኝ ጌታዬ፡፡»
በዚህ ዓይነት ብዙ ለፈለፈች፡፡ ደግማና ደጋግማ መሬት ሳመች::
እጆችዋን ወደ ሰማይ ዘረጋች:: ጉንጮችዋ በእንባ እስኪርሱ ድረስ አለቀሰች ! ተንሰቀሰቀች:: አምርራ እየጮኸች ስታለቅስ ሳልዋ ተነስቶ ደረቅ ሳል ሳለች፡፡ መሪር ጭንቀትዋ ፊትዋ ላይ ጎልቶ ሲታይም የልጅነት ውበትዋን
ጨርሶ ሊያከስመው አልቻለም:: ከዚያ የነበሩ ሰዎች አትኩረው ሲመለከትዋት ቆንጆ ሴት ለመሆንዋ አልተጠራጠሩም፡፡ ብድግ ብላ የአዛዡን ኮት ጫፍ
ሳመች፡፡ ሁናቴዋ እንደ ድንጋይ የጠጠረ ፤ እንደ በረዶ የቀዘቀዘ ልብን በቀላሉ የሚያሟሟ ነበር፡፡ ሆኖም እንደ እንጨት የደረቀ ልብን ሊፈታ አልቻለም፡፡ ዣቬር ኣልተበገረም::

«በይ ተነሽ» አለ ዣቬር፡፡ «አትለፍልፊብኝ ፤ ይበቃል! ምን
ትነፈርቅብኛለች! መንገድሽን ቀጥይ፡፡ ስድስት ወር ተፈርዶብሻል፡፡ ክርስቶስ
እንኳን ይህን ውሳኔ ሊሽር አይችልም::»
በመጨረሻ የተናገረው ቃል እጅግ አስደነገጣት፡፡ «ክርስቶስ እንኳን
ይህን ውሳኔ ሊሽር አይችልም:: መሬት ላይ እንደ ሕፃን ልጅ ተንፈራፈረች። አሁንም «ማሩኝ» ስትል ጮኸች::

ዣቬር ፊቱን አዞረ:: ፖሊሶቹ ሁለት እጆችዋን ያዙ፡፡

ሴትዮዋ እንደዚያ ስትለፈልፍ ጥቂት ሰዎች ተሰባስበው ነበር፡፡ ከዚያ የማይሠራ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ደብለቅ ብሎ ቆሞአል፡፡ በግርግር ማንም ሳያየው የውጪውን በር ከፍቶ ገብቶ ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ ስለቆመ
ፋንቲን የተማጠነችውን ሁሉ ሰምቷል፡፡

ፖሊሶቹ እጆችዋን ይዘው ጎትተው ሲያወጥዋት ይህ ሰው ዘወር
ብሎ «አንድ ጊዜ እስቲ» ሲል አዘዘ፡፡ ፖሊሶቹ እጆችዋን ለቀቁ::
ዣቬር ወጣ ብሎ ሲመለከት ከንቲባው መሴይ ማንደላይን እንደሆነ አየ፡፡ ጎንበስ ብሎ እጅ ነሳው:: ሆኖም ፊቱ ላይ የመቆጣትና የመቀየም
ምልክት ይታይበት ነበር፡፡

«ይቅርታ፣ ክቡር ከንቲባ!»

ክቡር ከንቲባ የሚለውን ቃል ስትሰማ የፋንቲን ፊት ተለዋወጡ፡፡
ከመቅጽበት ብድግ ብላ ቆመች:: ሳይታሰብ በድንገት ማንም ሊያቆማት በማይችል ፍጥነት ተወርውራ ከንቲባው እግር ስር ወደቀች:: ወዲያው አንገትዋን ቀና አደርጋና ዓይንዋን አፍጥጣ ከንቲባውን እያየች የከተማው
ከንቲባ ማለት እርስዎ ነዎት» ካለች በኋላ የፌዝ ሳቅ ሳቀች፡፡ ከዚያም
ከከንቲባው ፊት ላይ ምራቅዋን ተፋች:: ከንቲባው መሀረቡን አውጥቶ ፊቱን ከጠራረገ በኋላ የሚከተለውን ተናገረ፡፡
«መሴይ ዣቬር ይህችን ሴት ልቀቅዋትና ትሂድ»
ዣቬር ከመደነቅ ብዛት የሚለውን አጣ፡፡ በጣም ገርሞት አፉን
እንደከፈተ ቀረ፡፡
ከንቲባው የተናገራቸው ቃላት በዚያው መጠን ፋንቲንንም አፈዘዛት ራሱን ያዞረው ሰው እንዳይወድቅ አንድ ነገር ለመያዝ እንደሚጣደፍ ሁሉ እርስዋም እጅዋን ዘርግታ ቶሎ ብላ የደረሰችበትን ቋሚ ያዘች፡፡ ከዚያም አካባቢዋን ከቃኘች በኋላ እርስ በራስዋ እንደምትነጋገር ድምፆዋን ዝቅ አድርጋ ተናገረች::

«ልቀቅዋት! በነፃ ሊለቁኝ! ወህኒ ቤት ኣልወርድም! ስድስት ወር
አልታሰርም ማለት ነው! ማነው ይህን ያለው? ማንም ይህን ሊል አይችልዎ፧ ተሳስቼኣለሁ:: ይህ ሰው ያ እኩይ ከንቲባ ሊሆን አይችልም:: ወይ መሴይ
ዣቬር ! እርስዎ ኖት፧ ሲያፌዝ ነው ልቀቅዋትና ትሂድ ያሉት አይደለም? ቤታቸወን ያከራዩኝን ሰው ሄደው ይጠይቁ:: የቤት ኪራይ በጊዜው
እንደምከፍልና ታማኝ ሰው እንደሆንኩ ራስዎ ሄደው ያረጋግጡ፡፡ እባክዎን
ይቅርታ ያድርጉልኝ፤ ይራሩልኝ::»
ወደ ፖሊሶቹ ዞር ብላ ደግሞ «ይህን ሰው ተመልከቱት ፤ እንደት
እንደተፋሁበት አያችሁ አይደል? የኛ ከንቲባ፤ ሊያስፈራሩኝ አይደለም ከዚህ
የመጡት? እኔ ግን እርስዎን አልፈራም:: እኔ የምፈራው መሴይ ዣቬርን ብቻ ነው:: ደጉን መሴይ ዣቬርን ብቻ ነው የምፈራው::»
ይህን እንደተናገረች ወደ ከተማው ፖሊስ እዛዥ ፊትዋን አዞረች::
«አይ ጌታዬ! እውነተኛ ዳኛ መሆን አለብዎት፡፡ መሴይ ዣቬር
ትክክለኛ ዳኛ እንደሆኑ አውቃለሁ:: ሴት ልጅን በጠጠረ በረዶ ወርውር መምታት ልክ አይደለም ፤ ያውም ሳትደርስበት:: ድብደባውን የተመለከቱት
መኮንኖች በትርኢቱ ተደስተው ሳቁ፡፡ እኛ ምስኪኖች የእነሱ መደሰቻና መሳለቂያ ነን፡፡ እርስዎ የደረሱት ከዚያ በኋላ ነው:: እርግጥ ነው እርስዎ
ሕግ የማስከበርና ሥርዓት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለብዎት:: ለዚህ ነው እኔን የያዙኝ:: ግን ነገሩ ትክክል አለመሆኑን ሲረዱ ልቃቅዋትና ትሂድ" አሉ፡፡ ትክክለኛ ዳኛ እንደመሆንዎ አሁንም በድጋሚ ሂጂ ይበሉኝ፡፡ ይህንንም
የሚሉት ለሕፃንዋ ልጄ ሲሉ እንደሆነ አውቃለህ::: ስድስት ወር ከታሰርኩ ልጄን ለመርዳትና ለማሳደግ አልችልም:: ሁለተኛ ሌላ ጥፋት አላጠፋም:: እንደፈለጉ ይሳለቁብኝ፤ ይዝለፉኝ፤ መልስ አልሰጣቸውም:: መሴያ ዣቬር
ሁለተኛ ጥፋት አጥፍቼ ከፊትዎ ብቆም እንደፈለጉ ያድርጉኝ እኔም ዝም እላለሁ:: ዛሬ እኮ ሰውዬው በጣም ስላናደደኝ ነው ዘልዬ ጉብ ያልኩበት:: ደግሞም ነግሬዎታለሁ ፤ አሞኛል:: ሳል ይዞ ያጣድፈኛል:፡ እንደዚህ ተይዤ ሳለ በበረዶ ሊመታኝ ስሜቴ ጋለ፤ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ ; ራሴን መቆጣጠር
ተሳነኝ:: ሐኪም ደግሞ ብትጠነቀቁ ይሻላል ሲል ነግሮኛል፡፡ ቆዩ እስቲ ጌታዬ እንዲያውም አይፍሩ እንጂ ሰውነቴን ይንኩትና ትኩሳቴን ይመልከቱ ፤ ይኸውሎት፡: »

በድንገት የቀሚስዋ መዛነፍ ተገንዝባ ሳብ ሳብ አድርጋ አስተካከለችው:: ሲጎትትዋት ለካ ቀሚስዋ ተዛንፎ መሸፈን የነበረበት ገላዋን ገሃድ
አውጥተውታል፡፡ ብድግ ብላ ተነስታ ፖሊሶቹን እጅ በመንሳት ወደ በር አመራች።

«ወንድሞቼ፤ የፖሊሱ ኣዛዥ ትሂድ ብለዋልና መሄዴ ነው» አለች
መሴይ ዣቬር እስከዚያች ደቂቃ ድረስ ቃል ሳይተነፍስ ወደ መሬት አቀርቅሮ ቀርቶ ነበር ለተመለከተው ቦታው ተስተካክሉለት እንዲተከል ተራውን የሚጠብቅ ሀውልት እንጂ ሰው አይመስልም:: ጨርሶ ነቅነቅ አላለም

ሴትዮዋ ራመድ ስትል አንድ ነገር ረግጣ ኖሮ አንኮሻኮሽች፡፡ ዣዤር
ይህን ጊዜ ከተዋጠበት የስሜት ባህር ነቅቶ አንገቱን ቀና አደረገ፡፡ የተሰጠው ሥልጣን ምን እንደሆነ ታሰበው:: መቼስ የበታች ሹማምንት ሥልጣ ሲሰጣቸው እንደ አውሬ ይባላሉ፡፡ ትምህርት ወይም የኑሮ ልምድ
እንዳልሞረደውና በአእምሮ እንዳልበሰለ ሰው ይጨክናሉ::

«የሃምሳ አለቃ» ሲል ጮኸ፡፡ «ይህች አገር በጥባጭና ዱርዬ ሴት መውጣትዋ እንደሆነ አይታይህም? ማነው ትሂድ ብሎ ያዘዘህ?»

«እኔ» አለ ከንቲባው::
👍9
ዣቬር የተናገረውን ስትሰማ ሲሰርቅ የተደረሰበት ሌባ የሰረቀውን ቀስ ብሎ እንደሚጥል ሁሉ ፋንቲን የያዘችውን ቀስ ብላ ለቀቀች:: የመሴይ
ማንደላይንን ድምፅ ስትሰማ ደንግጣ ሌላ ቃል ሳትናገር ፊትዋን አንድ ጊዜ ወደ ከንቲባው፣ መልሳ ወደ ፖሊስ አዛዥ እያዞረች ሁለቱን ሰዎች ማስተያየት ጀመረች:: «የትኛው ነው አሁን የተናገረው» ስትል ራስዋን ጠየቀች:: እንኳን መናገር በኃይል መተንፈስ እንኳን አልደፈረችም፡፡
«እኔ» ብሎ መሴይ ማንደላይን ሲናገር የፖሊሱ አዛዥ ዣቬር ፊቱን
ወደ ከንቲባው አዞረ፡፡ ፊቱ በንዴት ጠቆረ፧ ደሙ በብስጭት ፈላ፤ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፣፣ ድምፁን አክርሮ «ክቡር ከንቲባ፤ ይህ ሊሆን አይችልም አለ፡፡

«ለምን?» ሲል መሴይ ማንደላይን ጠየቀ፡፡

«ይህች ባለጌ ሴት አንድን የከተማ ነዋሪ ተሳድባለች፤ አስቀይማለች
«ዣቬር» ሲል መሴይ ማንደላይን ረጋ ባለ መንፈስና በዝቅተኛ
ድምዕ መለሰ፡፡ «ስማኝ፤ አንተ እውነተኛ ሰው ስለሆንክ ጉዳዩን ባስረዳህ ቅር አይለኝም፡፡ እውነቱን ልንገርህ:: እንደአጋጣሚ በዚያ ሳልፍ አንተ ይህችን ሴት ይዘህ ስትመጣ አይቻለሁ:: ብዙ ሰው ስለተሰበሰበ አላየኸኝም።
አንተ ከሄድክ በኋላ ስለግርግሩ ሰዎችን ጠየቅሁ:: ሁሉንም ተረድቼአለሁ።ጥፋተኛው አንተ የምትለው የከተማው ነዋሪ ነው:: እርሱን ነበር ፖሊሶች መያዝ የነበረባቸው::»

ዣቬር መልስ ሰጠ፡፡

«ይህች ባለጌ ሴት ከንቲባውን ተሳድባለች፤ አስቀይማለች፡፡»
«ይህ እኔን ነው እንጂ አንተን አይመለከትም» አለ መሴ ማንደላይን፡፡
«ስድቡ የተሰነዘረው በእኔ ላይ ስለሆነ ስለስደቡ እኔው ራሴ የፈለግሁትን እርምጃ እወስዳለሁ::»
«ይቅርታ ያድርጉልኝ ጌታዬ፡፡ ስድቡ የተሰነዘረው በእርስዎ ላይ
ሳይሆን በመንበርዎ ላይ ነው:: ይህ ደግሞ መዳኘት አለበት፡፡
«ዣቬር» አለ ከንቲባው፤ «ትልቁ ዳኛ ሕሊና ነው:: ይህች ሴት
የተናገረችውን ሰምቻለሁ፡፡ የምሠራውን የማላውቅ አይመሰልህ!»
«ክቡር ከንቲባ፣ በእኔ በኩል ደግሞ አሁን የማየውንና የምሰማውን ኣላውቅም» አለ የፖሊሱ አዛዥ::
«እንግዲያውስ ትእዛዜን ተቀበል::»
«ግዳጄን ነው የምታዘዘው:: ግዳጄ ደግሞ ይህቺ ሴት ስድስት ወር እስር ቤት መቆየት እንዳለባት ይጠይቃል::
መሴይ ማንደላይን በእርጋታ የሚቀጥለውን ተናገረ፡፡
«ስማ፤ አንድ ቀን እንኳን አትታሰርም::»
«ክቡር ከንቲባ፣ ቢፈቀድ…»
«ሌላ ቃል አትናገር፡፡»
‹‹ሆኖም...»
«አቁም ብያለሁ» አለ መሴይ ማንደላይን፡፡ ዣቬር ቅስሙ ተሰበረ::
እንደ መስኮብ ወታደር ደረቱን ገልብጦ ጥቂት ከቆመ በኋላ ለከንቲባው እጅ ነስቶ ከቢሮው ወጥቶ ሄደ::
ፋንቲን ወደ በር ሄዳ አየችው:: ነገሩ ሁሉ ተመሰቃቀለባት:: የሁለቱን
ሰዎች ንግግር በኃፍረት ሰማች፡፡ መሴይ ማንደላይን የተናገረው እያንዳንዱ ቃል ልብዋ ውስጥ የተቀሰረውን ጥላቻ እያሟሟ ልብዋን አስከዳት::

የምትሰማውን ማመን አቃታት:: በጥላቻው ምትክ ልብዋ በቃላት ሊገለጽ በማይችል ደስታና ፍቅር ተሞላ፡፡

ዣቬር እንደ ሄደ መሴይ ማንደላይን ፊቱን ወደ ሴትዮዋ አዞሮ በዝግታ አናገራት::

«ያልሽውን ሰምቻለሁ:: አንቺ ስላልሻቸው አንዳንድ ነገሮች የማውቀው ነገር የለም:: ነገር ግን የተናገርሽውን አምናለሁ:: ከፋብሪካዬ ሥራ ለቅቀሽ
መውጣትሽንም እንኳን አላውቅም ነበር፡፡ ለምን መጥተሽ አላነጋገርሽኝም አሁን ግን ያለብሽን እዳ እኔ እከፍልልሻለሁ:: ልጅሽንም አስመጣልሻለሁ
ከፈለግሽ ደግሞ እንቺ ወደ እርስዋ ትሄጃለሽ፡: ብትፈልጊ ፓሪስ ወይ ልቦናሽ ከፈቀደው ቦታ መኖር ትችያለሽ:: አንቺንም ሆነ ልጅሽን እኔ እረዳችኋለሁ:: ሥራ መሥራት ካስጠላሽ ከዛሬ ጀምሮ ምንም ሥራ ባትሰሪ ትችያለሽ: ለመኖር የሚያስፈልጋችሁን ገንዘብ እኔ እሰጣችኋለሁ፡፡ "ግን ታማኝነትሽን እንዳታጠፊ:: ከዚህ ሁለ ይበልጥ ጆሮሽን አቅንተሽ እንድትሰሚኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር ካአሁን ቀደም በእግዚአብሔር ፊት
ንጽህናሽን ጠብቀሽ እንደኖርሽ ስለማልጠራዉር አሁንም ቢሆን ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ክፋትና ምቀኝነት የተለየው ኑሮሽን እንድትቀጥይ አደራ ነው የምልሽ፡፡ ምስኪኒትዋ፣ አይዞሽ፤ በርቺ:: ››

ምስኪንዋ ፋንቲን ለመሸከም ከምትችለው በላይ ሆነባት፡፡ ከልጅዋ። ከኮዜት ጋር አብሮ ለመኖር! ከዚያ አስነዋሪ ኑሮ መላቀቅ! የገንዘብ ችግር
ሳይኖር በደስታና በታማኝነት ከኮዚት ጋር መኖር! ይህ ሁሉ ያልታሰበ ኑሮ ሲታያት እንዴት ትመነው? «ወይኔ ወይኔ» ብሎ ከመጮህ በስተቀር ሌላ ነገር ለማለት አልቻለችም:: ሰውነትዋ ያንን ችሮታ፣ ያንን ደግነት
ለመሸከም አቅም አነሰው:: ሰውነትዋ ተዝለፈለፈ:: ከመሴይ ማንደላይ እግር ስር ወደቀች፡፡ ጎንበስ ብሉ ሊያነሳት ሲል እጁን አፈፍ አድርጋ ሳመችው::
ከዚያም ሕሊናዋን ሳተች::..

💫ይቀጥላል💫
9👍9
አትሮኖስ pinned «#ምንዱባን ፡ ፡ #ክፍል_አሰር ፡ ፡ #ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ የፋንቲን ታሪክ ምን ዓይነት ታሪክ ነው? ያሽከር ታሪክ! አሽከርን የሚገዛው ሕብረተሰቡ ነው? ከማን? ከችግር? ከመከራ? ከስቃይ? ከረሃብ? ከብቸኝነት? የሚቀፍ ግዢ ነፍስ በዳቦ ሲለወጥ! ችግር ግለሰቦች ያልፈቀዱትንና ያልፈለጉትን እንዲሠሩ ሲያስገድዳቸው! ሕብረተሰቡ ደግሞ በግዳጅ የሚያደርጉትን በደስታ ሲቀበል አይገርምም! ባርነት ቀርቷል…»
#የነፍስ_ክረምት!

ከርስ የጎደለ እንደው ይሞሉታል በህል፤
የበረደም ዕለት..ኮት ያኮቱበታል የቁሩን ልክ ያህል።

ጤዛውን በጫማ ፤
ውርጩን በስብ ሸማ፤
ሌቱን በትኩስ ራት ፤
ደመናውን በሣት፤
አጉል የሰፈረን ወዲያልኝ ይሉታል፤
አልባሌን አየር ፤ ጢስ ይከልሉታል፡፡

ሙቀት ስጡኝ ለሚል..
ለበረደው ገላ ፤ መጋጋል ላነሰው፤
መድኃኒቱን አውቋል ፥ የተቃቀፈ ሰው ።

ግና!
ነፍስ የበረደ ዕለት፥ ምን ቤት ይጠልላል??
ለቀዘቀዘስ ልብ ፥ ማን ኮት ልሁን ይላል??

🔘ፓፒረስ🔘
9👍7
#ምንዱባን


#ክፍል_አስራ_አንድ


#ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ


ዣቬር

መሴይ ማንደላይን ከቤቱ ውስጥ የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ክፍል ስለነበረው ፋንቲንን ወደዚያ አስወሰዳት:: የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ ሴሮች አልጋ ላይ አስተኝዋት:: በኃይል አተኩሳለች:: ሕሊናዋን ሳታውቅ እንዲሁ እየቃዠች ጥቂት እንደቆየች እንቅልፍ ይዞአት ጭልጥ አለ፡፡

በሚቀጥለው ቀን ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ከእንቅልፍዋ ነቃች
ከአጠገብዋ ሰው እንደቆመ አየች:: መሴይ ማንደላይን ጣራ ጣራውን እያየ ቆሞአል፡፡ ፊቱ በሀዘኔታ ተሞልቷል:: ከንቲባው ጣራውን ሳይሆን ግድግዳ
ላይ ከፍ ብሎ የተሰቀለወን መስቀል ነበር የሚያየው፡፡
ይህ ሰው መልአክ እንጂ ሰው አይመስላትም:: ሰውነቱ በብርሃን
የታነጸ መሰላት፡፡ መሴይ ማንደላይን እየጸለየ ስለነበር ጸሎቱን ላለማቋረጥ ሳትናገር ለረጅም ጊዜ አፍጥጣ አየችው:: በመጨረሻ ግን እየፈራች ቀስ
ብላ ተናገረች::

«ምን እየሠሩ ነው?»

መሴይ ማንደላይን ከዚህ ሥፍራ የፋንቲንን መንቃት እየተጠባበቀ
ለአንድ ሰዓት ያህል ቆሞአል፡፡ እጅዋን ይዞ የልብዋን አመታት ቆጠረ::
«አሁን ምን ይሰማሻል? ደህና ነሽ!»
«በጣም ደህና ነኝ:: እየበረታሁ ነኝ፤ እንቅልፍ ወሰደኝ» አለች ፋንቲን፡፡
«እንግዲያውስ ወደ ጥያቄሽ ልመለስና ምን ትሠራለህ ስላልሽው ስላንቺው ፈጣሪን በመማጠን ጸሎት እያደረስኩ ነበር፡፡»
ያን እለት ማታ ስለፋንቲን የሕይወት ታሪክ ሲጠይቅ አምሽቶ
በሚቀጥለው ቀን ያንኑ ቀጠለ፡፡ ምንም ነገር ሳይቀረው ስለፋንቲን ኑሮ ሁሉንም አወቀ፡፡
«ከመጠን በላይ ስቃይ ተቀብለሻል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ሀዘን አይግባሽ፡፡በዚህ ዓይነት ነው ሥጋ ለባሾች ወደ መስዋዕትነት የሚለወጡት:: ከዚህ
የተለየ መንገድ እንዳለው አላውቅም:: ይህ አንቺ ያለፍሽበት ምድራዊ ገሀነም ወደ መንግሥት ሰማይ የሚወስድ የመጀመሪያ እርምጃ ነው:: ከዚያ መጀመር ግዴታችን ነው::»
ይህን ካለ በኋላ መሴይ ማንደላይን በኃይል ተነፈሰ:: ፋንቲን ጥቂት ፈገግ ስትል ወላቃ ጥርስዋ ታየ::
መሴይ ማደላይን ወደ እነቴናድዬ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ በደብዳቤው ፋንቲን
ያለባት እዳ አንድ መቶ ሃያ ፍራንክ እንደሆነ ገልጾ የላከላቸው ግን ሦስት መቶ ፍራንክ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ብልጫ ገንዘብ የላከላቸው የፋንቲንን
ልጅ ይዘው ወዲያውኑ እንዲያመጡ ነበር:: የልጅትዋ እናት እንደታመመችና
ልጅዋን ለማየት እንደጓጓች ገልጾ ነበር ልጅትዋን ይዘው እንዲመጡ
የጠየቃቸው::
እነቴናድዬ ደብዳቤውና ገንዘቡ እንደደረሳቸው በጣም ተደነቁ::
«ሰይጣን» አለ ሚ/ር ቴናድዬ ለሚስቱ:: «ልጅትዋን አንሰጥም::
ምናልባት አንድ ቂል በውበትዋ ተማርኮ ይሆናል ይህን የመሰለ ደብዳቤ የሚጸፈው::»
ሰውየው ልጅትዋን በመላክ ፈንታ ሂሳቡን በጥንቃቄ አስልቶ ፋንቲን ያለባት እዳ አምስት መቶ ፍራንክ እንደሆነ ገልጾ የመልስ ደብዳቤ
ለመሴይ ማንደላይን ጻፈለት:: ተጨማሪው ሁለት መቶ ፍራንክ ልጅት በታመመች ጊዜ ለመድኃኒት የወጣ መሆኑን አስረድቶ ነበር የጻፈው።

መሴይ ማንደላይን ደብዳቤው እንደ ደረሰው ሦስት መቶ ፍራ
ላከላቸው:: ከገንዘበ ጋር ደግሞ በተቻለ ፍጥነት ኮዜትን ይዘው እንዲመ መልዕክት አከለበት፡፡
«በምንም መንገድ ልጅትዋን አንለቅም» አለ ማ/ር ቴናድዬ::
ፋንቲን በሽታዋ ጠናባት እንጂ ስላልተሻላት አልጋ ላይ ቆየች
መሴይ ማንደላይን በቀን ሁለት ጊዜ ይጠይቃታል፡፡ በጠይቃት
ቁጥር «ኮዜትን ቶሎ በዓይኔ የማያት ይመስሎታል?» ስትል ትጠይቀዋለች።
እርሱም ሲመልስ “ምናልባት ነገ! በማንኛውም ሰዓት ልትደርስ
ትችላለች» ይላታል፡፡
በዚህ ጊዜ የእናተዬዋ የገረጣ ፊት ወገግ ይላል::
«አዬ! እንዴት ደስ ባለኝ!» በማለት ትቆጫለች::
ሕመምዋ እያደር ጠናባት:: አንድ ቀን ሐኪሙ የሳምባዋን አተነፋፈስ
በማዳመጫ መሣሪያ ካዳመጠ በኋላ ራሱን ነቀነቀ::
«እየተሻላት ነው?» ሲል መሴይ ማንደላይን ጠየቀው::
«ዓይንዋን ለማየት የጓጓችላት ልጅ አላት አይደል!» አለ ዶክተሩ
«አዎን፡፡»
«እንግዲያውስ ቶሎ ብታስመጠላት ይሻላል፡፡»
መሴይ ማንደላይን በድንጋጤ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፡፡
«ሐኪሙ ምን አለ?›› አለች ፋንቲን፡፡
መሳይ ማንደላይን ፊቱን ፈገግ ለማድረግ ሞከረ::
«ልጅሽን በቶሎ እንድናስመጣልሽና ይህም በሽታሽን ሊያቃል እንደሚችል ነው የነገረን» ካላት በኋላ ወደ ቢሮው ሄደ፡፡
መሴይ ማንደላይን ከቢሮው ውስጥ ቁጭ ብለ ሥራውን እየሰራ
ሳለ የፖሊስ አዛዥ ዣቬር ሊያነጋግረው እንደሚፈልግ ተገለጸለት።

«ይግባ! » አለ፡፡

ዣቬር ገባ፡፡
ለከንቲባው የአክብሮት ሰላምታ ሰጠ፡፡ ፊቱን ወደ መስኮት አዙሮ
ስለነበር ዣቬር ሲገባ የከንቲባውን ጀርባ ነው ያየው፡፡ መሴይ ማንደላይን ቀና ብሎ ሳያየው ወረቀት ማገላበጡን ቀጠለ፡፡

ዣቬር የክፍሉን ፀጥታ ሳያደፈርስ ቀስ ብሉ ወደፊት ተራመደ፡፡ ፊቱ
ላይ የቆራጥነት ብቻ ሳይሆን የድፍረትም ዓይን በግልጽ ይታያል፡፡ በመጨረሻ ከንቲባው ብዕሩን አስቀምጦ ቀና አለ፡፡
«ታዲያስ፣ ምንድነው ዣቬር? ምን አጋጠመህ?»
ዣቬር አሳቡን ለማሰባሰብ ብሎ ለአጭር ጊዜ ዝም አለ፡፡ ከዚያም
ድምፁን አለስልሶ ሀዘን በተሞላበት አንደበት «ክቡር ከንቲባ፤ አንድ ወንጀል ተሠርታል» አለ፡፡

«የምን ወንጀል?»
«አንድ ግለሰብ አንድን የመንግሥት ባለሥልጣን በስህተት ስለወነጀለ ራሱን ለማጋለጥ ይፈልጋል፡፡ እኔ ደግሞ አሁን የመጣሁት ሥራዬ
እንደመሆኑ መጠን ይህን ለማሳወቅ ነው::»
«ራሱን ለማጋለጥ የሚፈልገው ሰው ማነው?» ሲል መሴይ ማንደላይን ጠየቀው፡፡
«እኔ» አለ ዣቬር፡፡
«አንተ?»
«አዎን፤ እኔ!»
«ማንን በድለህ ነው ራስህን የምታጋልጠው?»
«ክቡርነትዎን፡፡»
መሴይ ማንደላይን ወንበሩን አስተካክሎ ተቀመጠ:: ዣቬር ሳይፈራ አሁንም በትህትና ንግግሩን ቀጠለ፡፡
«ክቡር ከንቲባ ፧ እኔ አሁን እርስዎን የምጠይቀው ላደረስሁት በደል
ከስራ እንዲያሰናብቱኝና ክስ እንዲመሠርቱብኝ ነው:: »
መሴይ ማንደላይን በጣም ተደንቆ ለመናገር እፉን ከፈተ:: ዣቬር
ቀድሞ ተናገረ፡፡
ስራህን ብቻ ልቀቅ ይሉኝ ይሆናል:: ግን ይህ ብቻ አይበቃም:: በገዛ
ፈቃድማ ሥራ ተመልቀቅ መቻል ክበር ነው:: ጥፋት ስላጠፋሁና በደል ስለሠራሁ ለፍርድ ቀርቤ መቀጣት አለብኝ:: ከስራም መባረር ይኖርብኛል
«እንዴ! በምን ምክንያት?»
«ክቡር ከንቲባ ጉዳዩን ሲያውቁት ይህን ጥያቄ አይጠይቁኝም::
ነገሩ ሁሉ ይገባዎታል፡፡
ዣቬር በኃይል ተነፈሰ፡፡ ሀዘን እየተሰማውና እያፈረ ንግግሩን ቀጠለ
«ክቡር ከንቲባ ከስድስት ሳምንት በፊት ያቺን ሴት በነፃ ከለቀቅዋት
በኋላ በጣም ተናድጄ ከስሽዎት ነበር፡፡»
«እኔን ነው የከሰስከው?»
«አዎን፤ ፓሪስ ድረስ ሄጄ ለፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ክሴን አቀረብኩ
ብዙ ጊዜ የማይስቀው መሴይ ማንደላይን ከት ብሎ ሳቀ::
«የፖሊስን ሥልጣን ተጋፋ ብለህ ነው የከሰስከኝ?»
«የለም፧ የጥንት ወንጀለኛ ናቸው ብዬ ነው የከሰስክዎት፡፡»
ከንቲባው ደንገጥ አለ። እንዳቀረቀረ የቀረው ዣቬር ንግግሩን ቀጠሉ
«አልተጠራጠርኩም ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜ ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡ መልካችሁ
👍18👎1🔥1
ቁመናችሁ፤ ጉልበታችሁ እና ሌላም ሌላም ነገራችሁ ሁሉ ፍጹም አንድ ስለሆነብኝ ዣን ቫልዣ ነዎት ብዬ ደመደምኩ፡፡»
«ማን አልክ? እንዴት ብለህ ነው ስሙን የጠራኸው?»
«ዣን ቫልዣ ፧ ከሃያ ዓመት በፊት የወህኒ ቤት ሹም በነበርኩበት
ጊዜ አንድ እስረኛ ነበር፡፡ ይህ ወንጀለኛ ከእስር ቤት ካመለጠ በኋላ የአንድ የተከበሩ ጳጳስ ንብረት ዘርፎአል፡፡ በዚህም አላበቃም፤ በመሣሪያ ኃይል
በማስፈራራት የሌላም ሰው ንብረት ሠርቋል:: ይህን ወንጀለኛ ለመያዝ ብዙ ፍለጋ ቢካሄድም ስምንት ዓመት መሉ የት እንዳለ ሳይታወቅ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ ምን አለፋዎት ብቻ ያ ሰው እርስዎ እንደሆኑ ስላመንኩ
ለጠቅላይ ፖሊስ አዛዥ ጠቆምኩዎት::»
ዣቬር ንግግሩን ሲያበዛ ወረቀት ማገላበጥ የጀመረው መሳይ
ማንደላይን ረጋ ባለ አነጋገር «እና ምን ተባልክ?» ሲል ዤቬርን ጠየቀው።
«አበድክ እንዴ!» አሉኝ፡፡
«ከዚያስ!»
«ከዚያማ እነርሱ ልክ መሆናቸውን አወቅሁ::
«ጥሩ ገምተሃል፡፡»
«እነርሱ ልክ መሆን አለባቸው:: ምክንያቱም እውነተኛው ዣን
ቫልዣ ተገኝቷል፡፡»
መሴይ ማንደላይን የያዘው ወረቀት ከእጁ አምልጦት ወደቀ፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ ዣቬርን አተኩሮ ተመለከተው:: ለስለስ ባለ አንደበት «ተገኘ!»
አለው፡፡
ዣቬር ንግግሩን ቀጠለ፡፡
«ክቡር ከንቲባ፣ ታሪኩ እንዲህ ነው:: ገጠር ውስጥ ሻምፕማትዩ
የሚባሉ አንድ የዋህና ደግ ካህን ነበሩ፡፡ እኚህ ካህን በጣም ድሃ ናቸው፡፡ የሚረዳቸው ሰው የላቸውም፡፡ እንደ እርሳቸው ያለ ምስኪን የእለት ተእለት
ኑሮ ምን እንደሚመስል ብዘም አይታወቅም፡፡ በመጨረሻ እኚህ
የቤተክርስቲያን ሰው ፍሬ ሰርቀው ይያዛሉ፡፡ ፍሬ መስረቃቸው ይህን
ያህልም የሚያስወነጅል አልነበረም፡፡ ፍሬ የያዙ ብዛት ያላቸው የፍራፍሬ ዛፎች ተቆርጠው ቅርንጫፎቻቸው በየመንገዱ ይበተናል፡፡ ይህም እንደ ከባድ ጥፋት ተቆጠረ፡፡ ካህኑ የተያዙት ተቀንጥሶው ከወደቁት ቅርንጫፎች
አንደኛው ከነፍራው በእጃቸው ስለተገኘ ነው:: በዚህ የተነሣ ነው ሌባ ተብለው የታሠሩት:: ይህ ጉዳይ ጥቂት ቀን የሚያሳስር እንጂ ብዙ የሚያስፈርድ አልነበረም፡፡ ግን እዚህ ላይ ነው የተፈጥሮ ኃይል ሥራውን
የሠራው:: አባታችን ሻምፕማትዩ የታሠሩበት እስር ቤት ስለጠበበ ወደ ሌላ እስር ቤት ይዛወራሉ፡፡ ከአዲሱ እስር ቤት ውስጥ ለብዙ ጊዜ የታሠረ ብራሼት የሚባል ሌላ እስረኛ ጥሩ ጠባይ በማሳየቱ የእስረኞች ተቆጣጣሪ ሆኖ ይሾማል፡፡ ይህ ሰው ካህኑን ገና ሲያያቸው 'ወንጀለኛውን አገኘሁት ፤ወንጀለኛውን አገኘሁት እያለ ይጮሃል፡፡»

«ጌታው ወደዚህ ይመልከቱ! ዣን ቫልዣ አይደሉም?» ሲል
ጠየቃቸው::
«ዣን ቫልዣ! ማነው እሱ?» በማለት በመደነቅ ሰውዬውን ላማታለል ይሞክራሉ::
«እንዳላወቀ መሆን አይሞክሩ» ይላል ብሪቬት:: ዣን ቫልዣ ማለት
እርስዎ ነዎት፡፡ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ቱሉን ከሚገኝ እስር ቤት እስረኛ ነበሩ። ከእዚያ አብረን ነበርን::»
«አባታችን ሻምፕማትዩ ጨርሰው ካዱ:: ስለጉዳዩ ብዙ ምርመራና
ክትትል ተደረገ፡፡ ሰተደረገው ክትትል የዣን ቫልዣ ቤተሰቦች ከሰላሣ ዓመት በፊት የት እንደነበሩ ተደረሰበት:: ሆኖም ቤተሰቦቹ ያን ጊዜ ከነበሩበት
አልተገኙም:: የት እንደሄዱ ደግሞ ማንም ሊጠቁም አልቻለም:: ጊዘው በጣም ስለቆየ ዣን ቫልዣንም ለይቶ የሚያውቅ ሰው ጠፋ፡፡ ሆኖም ፍለጋው ቀጠለ፡፡ ከብሪቬት ሌላ ዣን ቫልዣን የሚያውቁ ሌሎች ሁለት
እስረኞች አሉ፡፡ ሁለቱም የእድሜ ልክ እሥራት የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ናቸው:: ስማቸውም ኮሸልና ቬኔልድዩ ይባላሉ፡፡ እስረኞቹ ካሉበት እንዲመጡ ተደርጎ አዩዋቸው:: ገና ሲያዩዋቸው ምንም አልተጠራጠሩም:: እነርሱም ሆነ ብሪቬት ሰውዬው ዣን ቫልዣ እንደሆኑ አረጋገጡ፡፡ እንደ
ዣን ቫልዣ እድሜያቸው 54 ሲሆን ቁመታቸውና መልካቸውም ካዣን
ቫልዣ ጋር አንድ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህ እውነት ከተደበቀበት የወጣው ልክ እኔ እርስዎ ዣን ቫልዣ እንደሆኑ ክስ በመሠረትኩበት ጊዜ ሲሆን ኣብደሃል ወይ! ዣን ቫልዣ እኮ አራስ ከተባለ እስር ቤት ተገኝቶ አሁን ለፍርድ ሊቀርብ ነው' ሲሉ አባረሩኝ፡፡ ምን ያህል እንደደነገጥኩና እንዳፈርኩ ሊገምቱ ይችላሉ፡፡ ይህን ዜና እንደሰማሁ ሰውዬውን አምጡና አሳዩኝ ስል ጠየቅሁ::
አምጥተው አሳዩኝ፡፡»
«ከዚያስ!» በማለት መሴይ ማንደላይን ጣልቃ ገባ፡፡
ዣቬር ሳይወላወል ሀዘን እየተሰማው ምላሹን ሰጠ፡፡
«ክቡር ከንቲባ፣ እውነት ነው:: እውነት ነው:: ስለፈጸምኩት ስህተት አዝናለሁ:: ሻምፕማትዩ ነኝ ያሉት ሰው በእርግጥ ን ዣል ቫልዣ ሆነው ነው ያገኘኋቸው::»
«እርግጠኛ ነህ?»
ዣቬር የፌዝ ሳቅ ሳቀ፡፡

«እርግጠኛ ነህ!» አለ ሰውዬው:: «የምትሉት ነገር አይገባኝም:: እኔ
ሻምፕማትዩ እንጂ ዣን ቫልዣ ኣይደለሁም አለ»::
«በጣም ጮሌ ሰው ነው:: ግን አራት ሰው ስለመሰከረበት ዋሽቶ
ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ተገቢውን ቅጣት ይቀበላል፡፡ እኔም የምስክርነት ቃሌን ከሕግ ፊት እንድሰጥ ስለተጠራሁ ወደዚያ እሄዳለሁ፡፡»
መሴይ ማንደላይን ወደ መሬት አቀረቀረ:: ፀጥ ብሎ ጠረጴዛው ላይ ከነበሩ ወረቀቶች ላይ አፈጠጠ፡፡ ሥራ እንደበዛበት ሰው አንዴ ይጽፋል፧ ወረቀቶችን ያገላብጣል፡፡ ወደ ቬር ዞር አለ፡፡
«ይበቃናላ ዣቬር! የነገርከኝ ታሪክ ብዙም አላስደሰተኝም:: አስቸኳይ
የሆኑ ነገሮች ስላሉብኝ ከዚህ ይበልጥ ጊዜ ሳናጠፋ! ለመሆኑ ወደ አራስ እስር ቤት መቼ ነው የምትሄደው?»
«ቶሎ ሳልሄድ አልቀርም::»
«ከስንት ቀን በኋላ?»
«ሰውዬው ነገ ለፍርድ ይቀርባል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ማታ መንገድ
እጀምራለሁ ብያለሁ፡፡»
«ቶሎ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ይመስልሃል?»
«ሌላ ቀጠሮ የሚሰጥ አይመስለኝም:: ግን እኔ የፍርድ ውሳኔ እስኪሰጥ አልጠብቅም፡፡ የምስክርነት ቃሌን ሰጥቼ እንደጨረስኩ እመለሳለሁ፡፡»

መሴይ ማንደላይን «መልካም» ካለ በኋላ ዣቬር እጅ በመንሳት
አሰናበተው::

ዣቬር ግን ከቢሮው አልወጣም::

«ክቡርነትዎን በድጋሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ» አለ ዣቬር፡፡

«ከዚህ በላይ ምን ያስፈልጋል? እኔ እንደሆነ ትቼዋለሁ» አለ መሴይ ማንደላይን፡፡

«ክቡር ከንቲባ፣ የጠየቅክዎትን እንዲያስቡበት፡፡»

«ምንድነው እሱ?»

«ከሥራ እንዲያሰናብቱኝ ነዋ!»
«ዣቬር፣ መከበር ያለብህ ሰው መሆንህን አምናለሁ:: ስህተትህን
ከሚገባው በላይ ኣጉላኸው:: የተበደልኩት እኔ ስለሆንኩ ይህን ያህል ከቁም ነገር አላስገባሁትም:: ከሥራ መባረርን በተመለከተ ከሥራ መባረርህ ቀርቶ እድገት የሚገባህ ስለሆነ በሥራህ ላይ እንድትቆይ ነው የምፈልገው::»

ዣቬር መሴይ ማንደላይንን በጥሞና እየተመለከተ፡-

«ክቡር ከንቲባ፣ ይህ ሊሆን አይችልም:: በሌላው ሰው ላይ የማደርገው ነገር በእኔም ላይ መፈጸም አለበት:: 'ማንኛውንም የኅብረተሰብ አባልን የበደለ ግለሰብ ያለ ርህራሄ ከአለበት ፈልፍዬ በማውጣት ለፍርድ አቀርባለሁ እያልኩ ለራሴ ዘወትር ቃል ገብቻለሁ:: አሁን እኔ ራሴ ሌላውን ሰው በድያለሁና መታለፍ የለብኝም:: ስለዚህ ሥራዬን መልቀቅ ይኖርብኛል።እጆች ስላሉኝ የትም ሠርቼ አድራለሁ:: ግብርና ብገባም ይሆናል። ለሌሎች ሰዎች ደግሞ ምሳሌ መሆን አለብኝ:: ስለዚህ አሁንም ከሥራ እንዲያባርሩኝ በድጋሚ እጠይቃለሁ::
👍13🥰2
«እናያለና» ካለ በኋላ መሴይ ማንደላይን ሊጨብጠው እጁን ዘረጋለት::
ዣቬር ከቢሮ ለመውጣት ወደኋላ እያፈገፈገ፡ይቅርታ ክቡር ከንቲባ፤ እጅዎን መጨበጥ የለብኝም:: እንድ ከንቲባ አንድን ተራ ሰው መጨበጥ የለበትም:: ተራ ሰው ፤ አዎን ተራ ሰው፤ ሥልጣኔን መከታ በማድረግ የሠራሁት ሥራ አንድ ተራ ሰላይ ከሚፈጽመው
ተግባር የተለየ አይደለም» ካለ በኋላ ለጥ ብሉ እጅ ነስቶ ከቢሮው
ለመውጣት ወደ በሩ ኣመራ:: በሩን ከፍቶ ሲወጣም አንገቱን እንደሰበረ ነበር፡፡

«ክቡር ከንቲባ፣ የሥራ ስንብት እስከተሰጠኝ ድረስ ሥራዬን
እቀጥላለሁ፡፡»

በሩን ይዞ ይህን ከተናገረ በኋላ ወጥቶ ሄደ፡፡ መሴይ ማንደሳይን
በጣም ተክዞ ቁጭ አለ፡፡ የዣቬርን ውትወታ በመገረም ነበር ያደመጠው....

💫ይቀጥላል💫
👍87👏1
አትሮኖስ pinned «#ምንዱባን ፡ ፡ #ክፍል_አስራ_አንድ ፡ ፡ #ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ ዣቬር መሴይ ማንደላይን ከቤቱ ውስጥ የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ክፍል ስለነበረው ፋንቲንን ወደዚያ አስወሰዳት:: የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ ሴሮች አልጋ ላይ አስተኝዋት:: በኃይል አተኩሳለች:: ሕሊናዋን ሳታውቅ እንዲሁ እየቃዠች ጥቂት እንደቆየች እንቅልፍ ይዞአት ጭልጥ አለ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ከእንቅልፍዋ…»
#አወይ_ሰው

ህይወትን ልኖራት በምድር ተደስቼ
አንድ ብዬ ስጀምር ልበላ ሰርቼ
አርሼ አለስልሼ በትኜ ዘርቼ
በቅሎልኝ አርሜ ሰብስቤ ወቅቼ
ለቅሜ አበጥሬ አስጥቼ አዝርቼ
ልጋግር አቡክቼ ምጣዱን አስምቼ
ሰምቶልኝ ጋግሬ ልበላው አውጥቼ
አሁን ካአሁን ስለው ልበላ ጓገቼ
በሰለ አልበሰለ ብየ ቢወጣልኝ
በላሁ ስል እንጀራ ያሳሬን ቢያልፍልኝ።
ማባያ ነው ብለው አፈር በተኑብኝ
አወይ የሰው ነገር በዚችም ቀኑብኝ

?
👍25😁1
#እውነት_እናውራ_ካልሽ

“በይ" ስልሽ ..- “ወዶኝ ነው"
“ተይ” ስልሽ .. - “ቀንቶ ነው!"
ባልሽበት አንደበት፥
ዝም ስል .. - “ንቆኝ ነው"
ብትይ ምናለበት ?!

🔘ዮሐንስ ሞላ🔘
24👍18👏7🔥1🤩1
#ምንዱባን


#ክፍል_አስራ_ሁለት


#ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ


የሻምፕማትዩ ጉዳይ

የታሪኩ አንባቢ እስካሁን በተነገረው መሴይ ማንደላይን ማለት ዣን ቫልዣ እንደሆነ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ዣን ቫልዣ ማለት ራሱ እንደሆነ እያወቀ አሁን ሌላ ሰው ዣን ቫልዣ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉት ምን ይሰማው ይሆን? ሕሊናው ምን ይላል? ምን ዓይነትስ ፈተና ውስጥ ነው የገባው? ከባሕር ጥልቀትና ከሰማይ ርቀት የላቀው የሰው አእምሮ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲገጥመው ውስጣዊ ስሜቱ ምን ይመስል ይሆን?

እስከዚያን እለት ድረስ ከልቡ ውስጥ ቀብሮ የያዘውን ጉዳይ በድንገት ዣቬር ስላነሳው መሴይ ማንደላይን ከቢሮው ውስጥ ቁጭ እንዳለ መላ ሰውነቱ ራደ:: «መጨረሻዬ ምን ይሆን» ሲል አሰበ:: ውሽንፍር እንደሚያወዛውዘው ዋርካና ከባድ ጦር እንደገጠመው ወታደር ልቡ ከወዲያ ወዲህ ተንከራተተ:: ዣቬር ነገሩን አራዝሞ ከቢሮው አልወጣ ብሎት ሲናገር የአገር ደመና ተሰባስቦ ከባድ ዝናብና መብረቅ ከጭንቅላቱ ላይ
የሚያዘንብ መሰለው፡፡ ዣቬር እያነጋገረው «ሂድ ፤ ተነሳ፤ ሩጥ!
ሻምፕማቲዩን ነፃ አውጣ፤ ወደኋላ አትበል፤ ራስህን አጋልጥ» የሚል
ስሜት አደረበት፡፡

«አባ ሻምፕማትዩን ከእስር ቤት አስወጥተህ በእርሳቸው እግር አንተ ተተካ» የሚለው አሳብ ከሕሊናው አልወጣ አለው:: ሆኖም ቀላል ውሳኔ ሆኖ አላገኘውም:: ሀሳቡ ልክ ኣንድ ስለት ያለው ነገር አካል ውስጥ ዘልቆ ሲገባ የሚሰማው ዓይነት ስሜት አሳደረበት:: መጨረሻውን እንያ!» ሲል እርስ በራስ ተነጋገረ፡፡ በሌላ በኩል የምን ጀግንነት ነው» ሲል ከራሱ ጋር ተሟገተ፡፡ በዚህ ዓይነት ሕሊናውና ሥጋው ግብግብ ገጠመ፡፡
ገና ድሮ ከእስር ቤት እንደወጣ እኚያ ጳጳስ አጥንት የሚሰብር ንግግር ባይናገሩት ኖሮ የዚህ ዓይነቱ፡ ግብግብ ባልገጠመው ነበር፡፡ አንድ ጎኑ
«የሚበቃህን ያህል ተሰቃይተሃል፤ አሁን ራስህን አውጣ» ሲለው ሌላውዐጎኑ «እንዴት ባንተ ምክንያት ሌላ ሰው ይጐዳል» እያለ ወተውተው፡፡
ዣቬር ከቢሮው እስከወጣ ድረስ ስሜቱን ለመቆጣጠርና የተዝናና ለመምሰል ብዙ ታገለ፡፡ ዣቬር እንደወጣ ፋንቲንን ለመጠየቅ ወደ ተኛችበት ክፍል ሄደ፡፡ ከሌላው ቀን ይበልጥ ጊዜ ወስዶ አጫወታት:: ሴሮቹ የተለየ ጥንቃቄ
እንዲያደርጉላት በማሳሰብ ምናልባት እራስ ወደ ተባለ ሥፍራ ሊሄድ እንደሚችል ገለጸላቸው:: ከዚያም ገበታ ቀርቦለት እንክት አድርጎ በላ፡፡
ወደ መኝታ ክፍሉ ገብቶ ኣሳቡን ሰበሰበ፡፡ ሁኔታውን በአሳብ ሲገመግመው ከዚያ በፊት ተሰምቶ የማይታወቅ
ዓይነት ሆነበት:: ድንገት ሳያስበው ከመቀመጫው ብድግ ብሎ የነበረበትን ክፍል በር ቆለፈ:: በሩ የተቆለፈ እንደሆነ ማንም ገብቶ ሊያስፈራራው እንደማይችል አመነ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የክፍሉን መብራት አጠፋ::
መብራቱ ራሰ ኣናደደው:: መብራት አበራ አንድ ስው ከውጭ ሆኖ
ሊያየው እንደሚችል ተገነዘበ፡፡
«ማን? የትኛው ሰው?»
የሚገርመው ግን እንዳያየው የፈለገው ሰው ሁሉ አየው:: የቆለፈው በር ሁሉ ወለል አለ፡፡ ማን ከፈተው? ማን አየው? ሕሊናው::

ሕሊናው ማለት ሁሉንም የሚያይ አምላክ አየው:: በመጀመሪያ ራሱን ለማታለል ሞከረ:: ከተቆለፈ ቤት ውስጥ ብቻውን ራሱን ከደበቀ
ማንም የሚያገኘው አልመሰለውም ነበር፡፡ በሩ ተቆልፎአል፤ መብራቱ ጠፍቶአል፡፡ ታዲያ ማን ሊያየው ይችላል?

ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ያዘና ክርኑን ጠረጴዛ ላይ በማስደገፍ
ጨለማ ውስጥ ያሰላስል ገባ፡፡ አሳቡን ለማሰባሰብ ሲፈልግም አንጎሉ በቂ ኃይል አጣ፡፡ ሕሊናው ውስጥ የነበረው አሳብ ሁሉ እንደ ማዕበል ተወራጨ፡፡

አሳቡን ለማቆም ይችል ይመስል ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ጥብቅ አድርጎ ያዘ፡፡ ሆኖም በአሳብ ነጎደ እንጂ ከተጨበጠ ውሳኔ ይ ሊደርስ አልቻለም:: ጭንቀቱ እየጐላ ሄደ:: ጭንቅላቱ በእሳት ተያይዞ የሚቃጠል መሰለው::
ወደ መስኮቱ ሄዶ መስኮቱን በኃይል ከፈተው:: ሰማይ ላይ አንዲት ኮኮብ እንኳን አትታይም:: ተመልሶ እንደበፊቱ ጭንቅላቱን ይዞ ተቀመጠ፡፡ አንድ ሰዓት አለፈ::

ቀስ በቀስ አሳብ ተሰብስቦ ወደ አንድ ውሳኔ አመራ:: እኚያ ካህን
የገቡበትን ወጥመድ በጉልህ ለማየት ቻለ:: ከቅዠት ዓለም የነቃ መሰለው:: እኚህ ሰው የእርሱን ጦስ፣ የእርሱን እዳ ተሸክመው በአሳብ አያቸው::
እርሱ መግባት ከነበረበት አዘቅት ውስጥ ሊጣሉ ተመለከታቸው፡፡ ከዚያ የመከራ አዘቅት ውስጥ እንዳይገቡ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት አመነ ይህን ሊያደርግ የሚችል እርሱ ወይም አንድ ሌላ ሰው መሆን ይኖርበታል::
ግን ከእርሱ ሌላ ማነው ይህን ለመፈጸም የሚችለው?

ነገር ተምታታበት፤ የሚችለው ጉዳይ አልሆነም፡፡ ተጨነቀ፤ ተጠበቡ::አንጎሉ በጭንቀትና በአሳብ ብዛት ሊፈነዳ ሆነ፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ከዚያ
በፊት ከእንደዚያ ያለ ፈተና ውስጥ የገባ አልመሰለውም:: ሕሊናው
አሳደደው፤ እረፍት ነሳው:: «ማሽላ እያረረ ይስቃልና» የፌዝ ሳቅ ሳቀ::
በችኮላ መብራቱን እንደገና አበራው::

«ታዲያ፣ ምን ይጠበስ!» አለ። «ምን አርበተበተኝ? ምንስ አስጨነቀኝ? እኔ እንደሆነ ምንም አልሆንኩም:: ነገሩ ከፍጻሜ ደርሷል:: አንድ ግለሰብ
በደል ቢሠራ ጥፋቱ የእኔ አይደል! እኔ እንደሆነ ክብር ያለኝ ሰው ነኝ:: ይህ የፈጣሪ ሥራ ነው:: የእርሱ ፈቃድ ይህ ከሆነ እኔ ምን አገባኝ! እርሱ አስተካክሉ የቀየሰውን እኔ ማፍረስ እችላለሁ! ታዲያ ምን ጥልቅ አደረገኝ? አያገባኝም:: በሕይወቴ ዘመን በሕልሜም በውኔም የተመኘሁት ነገር ቢኖር
የኑሮ ዋስትና ነበር፡፡ የአምላክ ፈቃድ ሆኖ ያንን አግኝቻለሁ:: ይህን በአምላክ ፈቃድ ያገኘሁትን የኑሮ ዋስትና ማበላሸት የለብኝም:: ታዲያ ለምንድነው የጀመርኩትን እንዳልቀጥል፣ ለሰዎች በጎ ተግባር እንዳልፈጽም፣ ለሌሎች ሰዎች አርአያ እንዳልሆንና የአሳለፍኩት የረጅም ዘመን ስቃይ
ውጤት ደስታ እንዳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆነው? ለማንኛውም
ያለቀ ጉዳይ ነው:: በእግዚአብሔር ሥራ እኔ ልገባ አልችልም::»

ተጨባጭ የሆነ መፍትሔ ሲያጣ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ ክፍሉ
ውስጥ ተንቆራጠጠ፡፡ ና ወዳጄ ፣ ከዚህ ይበልጥ ራስህን አታሰቃይ» አለ እርሱ በራሱ ሲነጋገር፡፡ ሆኖም የመንፈስ እረፍት ሊያገኝ አልቻለም፡፡እንዲያውም ከነአካቴው ከመጠን በላይ ተጨነቀ፡፡ የጭንቀቱም ውጤት
ብስጭት ሆነ፡፡

ማንም ሰው ቢሆን የባህርን ውሃ ወደ ዳር እንዳይወጣ ለማገድ
እንደማይችል ሁሉ አእምሮውም ውስጥ አሳብ እንዳይገባ ለመከልከል አይችልም፡፡ በኃይል እየገፋ የሚመጣውን ውሃ ማዕበል እንለዋለን፡፡ ወንጀል ተሠርቶ የሚደርሰውን ሰቆቃና ጭንቀት ደግሞ የሕሊና ወቀሳ እንለዋለን፡፡
ተፈጥሮ ነፍስን ውሃን በልዩ ጥበቡ ወደታችና ወደላይ ያነጥራቸዋል፡፡
ጊዜው እያለፈ ሲሄድ እርስ በራሱ መነጋገሩን ቀጥሎ ተናጋሪም
ሰሚም ራሱ ሆነ፡፡ ግን በጣም የሚያስገርመው የሚናገረው ለመስማት የማይፈልገውን ሲሆን ለመናገር አፉን የሚከፍተው ደግሞ ከምንም ጊዜ
ይበልጥ ፀጥታ በፈለገስት ወቅት ነበር፡፡

«ይህ ሰው በዚያን ጊዜ የት ነበር? ይሄ ያለቀለት ጉዳይ አይደለም?»
👍16
ሲል ራሱን ጠየቀ፡፡ ይህን ጥያቄ እንደጠየቀ «እኔን አያገባኝም» ብሎ ማለፍ ስህተት መሆኑን ተገነዘበ፡፡ ንጹህ ሰው ባልሠራው ሥራ ከስቃይ ማጥ ውስጥ ሲወድቅ ዝም ብሎ ማለፍ ሕሊና ያለው ፍጡር ሊቀበለው የማይችል የአውሬ ጠባይ መሆኑን አመነ፡፡ ይህን እውነታ አለማየት «ራስ ወዳድ፣ ጨካኝ፣ ፈሪ፣ ወንጀለኛ ያሰኛል» ሲል ወሰነ፡፡
በመጨረሻዎቹ ስምንት ዓመታት የሕይወት ዘመኑ ውስጥ
ለመጀመሪያ ጊዜ የደካማ አሳብ መራራነትን ቀመሰ፡፡ ያንን ክፉ አሳብ ከአንጎሉ አውጥቶ ለመጣል ይችል ይመስል እየቀፈፈው ምራቁን ተፋ፡፡

«የሕይወቴ መጨረሻ ምንድነው? ስሜን መደበቅ? ፖሊስን ማታለል?እስከዛሬ የፈጸምኩት በጎ ምግባር መጨረሻው ይሄ ነው? በሕይወቴ ዘመን
ውስጥ ከዚህ የተለየ ዓላማ አይኖረኝም ማለት ነው? ነፍሴን ረስቼ ሥጋዬን ብቻ ለማዳን ነው የምጥረው ወይስ የሕይወቴ ግብ ቀና፣ እውነተኛና ታማኝ ሰው ለመሆን ነው? እኚያ ደጉ ጳጳስ ይህ አልነበር ያስደሰታቸው!»
እንደገና ከሕሊናው ጋር ሙግት ገጠመ:: ራሱን ለማውጣት ብሎ
የሌላውን ሕይወት ሊያጠፋ እንደሆነ ተረዳ፡፡ ታዲያ የዚያን ካህን ሕይወት ካላዳነ ምን ሰው ነው? ይህን ካላደረገ ሰው ሳይሆን እድገቱን ያልጨረሰ አውሬ መሆኑን ተገነዘበ፡፡ ሰው ደግሞ ለራሱ ብቻ ከኖረ መኖር ራሱ
ትርጉም አይኖረውም:: እኚያ ጳጳስ ከአጠገቡ ቁጭ ብለው የሚያዩት
መሰለው፡፡ በአካባቢው ያሉ ሰዎች የሚያውቁት እንደ ተወዳጅ ከንቲባ
ሲሆን ጳጳሱ ግን ከእስር ቤት ያመለጠው ዣን ቫልዣ እንደሆነ ነው የሚያውቁት፡፡ ሰዎች የሚያዩት የውጭ ኑሮውን ሲሆን ጳጳሱ ግን ሕሊናውን ነው የሚያዩት:: እንግዲያውስ ቶሎ ብሎ ወደ አራስ ሄዶ እኒያን ምስኪን ማዳን አለበት:: እውነተኛውን ዣን ቫልዣ አጋልጦ የተሳሳተውን ዣን ቫልዣን ማዳን ይኖርበታል፡፡ ይህን ካደረገ ታላቅ መስዋዕትነትና አስከፊ ድል
ይሆናል፡፡ ሆኖም ይህን ከማድረግ ወደኋላ ማለት የለበትም:: እጅግ በጣም አሳዛኝ የሆነ መጨረሻ! በሰዎች ዓይን የሚያስነቅፍ ውሳኔ ሊሆን ይችላል::
በሕሊና ዳኝነት ብቻ ያን ሁሉ ሀብት፣ ያን ሁሉ ደስታ ትቶ ያንን ካህን ለማዳን በገዛ ፈቃድ ራስን አሳልፎ መስጠት!
“ይሁና» ኣለ፤ «መደረግ ይኖርበታል ፤ ይህን ሰው ማዳን አለብኝ::»
እነዚህን ቃላት የተናገራቸው ሳይታወቀው በኃይል እየጮኸ ነበር።ከጠረጴዛው ላይ የነበሩትን መጻሕፍትና ሌሎች ጽሑፎች በመልክ በመልካቸው አስቀመጠ፡፡ አንዳንዶቹን እሳት ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ወረቀት
አንስቶ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ደብዳቤውን አሽገው፡፡ አድራሻውን ለአንድ ለታወቀ ባንክ ሥራ አስኪያጅ አደረገው፡፡ ደብዳቤውንና የማስታወሻ ደብተሩን ኪሱ
ውስጥ አድርጎ ከወዲያ ወዲህ መንቆራጠጥ ጀመረ::

«ሂድ! ወደኋላ አትበል፤ ራስህን በማጋለጥ ሰውዬውን ካልሠራው
ወንጀል አውጣው» የሚለው አሳብ እየጎላበት መጣ፡፡ በሕሊናው ዳኝነት የወደፊት ሕይወቱን የሚወስንበት ሰዓት ተቃረበ፡፡ ከእስር ቤት ከወጣ
ወዲህ የአዲስ ሕይወት ምዕራፍ የከፈቱለት እኚያ የሃይማኖት ሰው ነበሩ::
አሁን ደግሞ እኚህ ሻምፕማትዩ የተባሉ የሃይማኖት ሰው የሕይወቱን ሁለተኛ ምዕራፍ ሊከፍቱለት ሆነ፡፡ ከትልቅ ጭንቀት በኋላ የተደረሰበት የውሳኔ ሙግት ነበር፡፡

እኩለ ሌሊት ሆነ፡፡ አሁንም ከወዲያ ወዲህ መንቆራጠጡን ቀጠለ::ብርድ ብርድ አለው:: እሳት አቀጣጠለ፡፡ መስኮቶቹን መዝጋት እንደነበረበት ዘነጋ፡፡ በመጨረሻ «ራሴን ለማጋለጥና ሰውዬውን ለማዳን ወስኛለሁ» ሲል
ሳያውቀው ተናገረ፡፡በዚህ ጊዜ የፋንቲን ጉዳይ ድንገት ከፊቱ ድቅን አለበት::
«ቆይ እስቲ!» አለ፡፡ «ይህቺ ምስኪን ሴት ደግሞ እንዴት ትሆናለች? እርስዋ ደግሞ ከእዚህ አለች::» ሌላ ችግር ተፈጠረ፡፡ ጨርሶ ያልጠበቀውና
ያላሰበው ጉዳይ ነበር፡፡
«እስከዛሬ ለራሴ ብቻ ነበር የምኖረው:: ቢደላኝ፣ ቢከፋኝ፣ ራሴን ላጋልጥ ብል፣ ለነፍሴ ሳይሆን ለሥጋዬ ባድር፣ ያንን ውሳኔ ለማዛባት መንገዴ ላይ የሚቆም ነገር አልነበረም:: ለዚህ ነበር ራሴን አጋልጣለሁ ብዬ
የወሰንኩት:: አሁን ግን ይህቺ ሴት አለች:: ለካስ እስከዛሬ ስለሌለች ሳላስብ ለራሴ ብቻ ነው የኖርኩት? ለካስ ራሴን በጣም ነበር የምወደው? በሰዎች ዓይን ለሌሎች መኖር ታላቅ ክብር የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ ከሥራዎች ሁሉ ክቡር ነው:: እስቲ ነገሩን በንጹህ ልቦና እንየው:: ባለፉት አሥር ዓመታት ከአሥር ሚሊዮን ፍራንክ ይበልጥ ሀብት በማፍራቴና ፋብሪካዎችን
በመክፈቴ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ቤተሰቦች በደስታ ሊኖሩ ቻለ፡፡ በሰበቡ አገሪቱዋም ተጠቅማለች ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም የተወሰኑ ሰዎች ኑሮ
በእኔ ምክንያት በመሻሻሉ ውንብድና፣ ዝሙት አዳሪነት፣ ሌብነት፣ ነፍስ የማጥፋት ወንጀልና የመሳሰሉት በተወሰነ አካባቢዎች ተቀንሰዋል፡፡ እነዚህ
ከማጣት ጋር የሚሄዱ ለመሆናቸው እውን ነው:: ለሌሎች መኖር ማለት ይህ አይደለም? ታዲያ ራሴን የማጋልጠው ይህን ሁሉ ሕዝብ ለማን አደራ ብዬ ነው! እኔ ከሄድኩ ሥራዬ ሁሉ ተቃወሰ ማለት አይደለም ስራዬ ከተቃወሰ ደግሞ ሠራተኛዬ ሁሉ የትም መበተኑ ነው፡፡ ለሌሎች መኖር
ዋጋ የሚሆንው ለዚህ አይደል? ብዙ ቤተሰቦች እንዳይፋቱ፡፡ ልጆቻቸው የሰው እጅ እንዳያዩ፣ እናቶች በሰቀቀን ማኅፀናቸው እንዳይደርቅ ብዩ ራሴን ሳላጋልጥ ብቀር ሰዎች በእኔ ላይ ይፈርዳሉ? ሕሊናዩስ ወደፊት ይገስጸኝ ይሆን? ምን ዓይነት ጣጣ ነው እባካችሁ!»

💫ይቀጥላል💫
👍117
#ያንድ_ምሽት_አሳብ

በሺህ ፈረስ ጉልበት፥በሺህ ግመል አቅም
ሺህ ጊዜ ቢራመድ፥ሰው ከቤቱ አይርቅም::

ስጥል ዋልኩኝና፥ ስወድቅ አመሸሁ
ትግሉ ሲበረታ ፥ ወደ ቤቴ ሸሸሁ ፥
ሌቱ ጣራዬ ላይ ፥ እንደ እንጀራ ሰፋ
እፍ አልኩት ኮከቡን ፥ እንደ ኩራዝ ጠፋ::

እንግዲህ ምን ቀረኝ?
ምንድነው ያማረኝ?
ወገግ
ፈገግ ልበል?
ፊትሽን አስቤ?
አልጋ ላይ ልንበልበል
እንቅልፍን ከጎሬው ፥ እንደ ጋኔን ስቤ?

ወዲህ ውብ ትውስታ፤ ወዲያ ንጹህ አልጋ
የቱ ይመረጣል? ያም ተድላ፥ ያም ጸጋ
ገላ ሲስለመለም፤ ልብ ይቀሰቀሳል
ለጊዜውም ቢሆን
እንቅልፍ እና ፍቅር መከራን ያስረሳል፡፡

🔘በእውቀቱ ስዩም🔘
12👍4
#ምንዱባን


#ክፍል_አስራ_ሦስት


#ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ

....ሠራተኛዬ ሁሉ የትም መበተኑ ነው፡፡ ለሌሎች መኖር
ዋጋ የሚሆንው ለዚህ አይደል? ብዙ ቤተሰቦች እንዳይፋቱ፡፡ ልጆቻቸው የሰው እጅ እንዳያዩ፣ እናቶች በሰቀቀን ማኅፀናቸው እንዳይደርቅ ብዩ ራሴን ሳላጋልጥ ብቀር ሰዎች በእኔ ላይ ይፈርዳሉ? ሕሊናዩስ ወደፊት ይገስጸኝ ይሆን? ምን ዓይነት ጣጣ ነው እባካችሁ!»

እንደገና ብድግ ብሎ ከወዲያ ወዲህ መንጎራደድ ጀመረ፡፡ አሁን ግን የሚንጎራደደው አንደ በፊቱ፡ ከጭንቀት ማጥ ውስጥ በመርመጥመጥ ሳይሆን በረጋ መንፈስ ነበር።

እንቁ ጨለማ ከወረሰውና ጥልቀት ካለው መሬት ወስጥ ተፈልፍሎ
እንደሚገኝ ሁሉ እውነትም ከማሰብና ከማሰላሰል ብዛት ይደረስበታል፡፡መሴይ ማንደላይንም ከመጨነቅ፣ ከመጠበብና ከማሰብ ብዛት ከእውነት የደረሰ መሰለው፡፡ ይህም ትክክለኛውን ጎዳና እንዳያይ ጋረደለት:

«አልተሳሳትኩም» አለ ለራሱ፤ «ይኸው ነው ትክክለኛ ጎዳና:: ትክክለኛውን አቅጣጫ ነው የያገዝኩት፡፡ ለጭንቀቴ መፍትሔ አገኘሁለት:: ከእነዚህ
አሳብ ላይ መጽናት አለብኝ፡፡ ምርጫዬ ይኸው ነው፤ ወስኛለሁ:: ከዚህ ወዲያ ስለነገሩ ማውጣትና ማወረድ ወይም መጨነቅ አያስፈልግም::ይህንንም የምለው ለራሴ በማሰብ ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቤም በመጨነቅ
ጭምር ነው:: እኔ ማንደላይን ስለሆንኩ በማንደላይንነቴ እጸናለሁ:: ይብላኝ ለዣን ቫልዣ! ከአሁን ወዲያ እኔና ዣን ቫልዣ አንድ ሰው አይደለንም::
የዣን ቫልዣን ማንነት አላውቅም:: ዣን ቫልዣ ነው ተብሎ የተጠረጠረው ሰው ራሱን ያውጣ እንጂ እኔ ምን አገባኝ:: አዎን፤ ከዚህ ውሳኔና መደምደሚያ
ላይ በመድረሴ መንፈሴ ረካ፡፡ አሁን ገና የተለየ ሰው መሆኔን ተረዳሁ::"

ጥቂት እንደ መራመድ ብሎ ድንገት ቀጥ ብሎ ቆመ::

«ኧረ ወዲያ» አለ፡፡ «ከጥሩ ውሳኔ ላይ ነው የደረስኩት፧ ከዚህች
ውሳኔ ነቅነቅ የለም:: ብቻ አሁንም ቢሆንኮ አሳቡ ጨርሶ ከሕሊናዬ ውስጥ ተነቅሎ አልወጣም:: ቢሆንም መወገድ ያለበት ነው:: ከእዚህ ቤት ውስጥ እንደ ምስክር ሆነው ሊናገሩ፤ በአየኋቸው ቁጥር የዚህችን ሰዓት ጭንቀቴን
ሊያስታውሱ የሚችሉ ብዙ እቃዎች ስላሉ አሳቤ ብቻ ሳይሆን እነርሱም ጭምር ከዚህ መወገድ አለባቸው::»

ኪሱን ዳብሶ ቦርሳውን ካወጣ በኋላ ከውስጡ አንዲት ትንሽ ቁልፍ አወጣ፡፡ መክፈቻዋ በግድ ከምትታይ የቁልፍ መግቢያ ቀዳዳ ውስጥ ቁልፉን ጨምሮ ሳጥኑን ከፈተው:: ብዙ እቃ አልነበረበትም:: ያረጀ ሱሪ፣ የተበጣጠሰ ጫማ፣ የተቀዳደደ ሸሚዝና እንዲሁም አሮጌ ኮረጆ መሳይ ነገርና ያኔ አሁን
ወዳለበት ከተማ ሲገባ ይዞት የነበረው ዱላ ከዚያ ተቀምጠዋል፡፡ መቼ
እንዳስቀመጣቸው አስታወሰ፡፡
ወደ በሩ ተመለከተ፡፡ ምንም እንኳን በሩ በሚገባ ተቀርቅር ቢዘጋም የሚከፈት መስሉት ፍርሃት ፍርሃት አለው፡፡ ልብሱን፣ ጫማውን፣ ከረጢቱና
ዱላው በቅጡ እንኳን ሳይመለከታቸው ቶሎ ብሎ እሳት ውስጥ ጨመራቸው፡፡ እስከዚያን እለት ድረስ በክብር አስቀምጧቸው ነበር፡፡ በጥቂት
ሰከንድ ውስጥ ቤቱ ብርሃን በብርሃን ሆነ፡፡ ሁሉም ጋየ፡፡ ዱላው እየተሰነጣጠቀ
ሲነድ የእሳት ብልጭታ ራቅ ወዳለው ሥፍራ ሁሉ ይበተን ጀመር::

ከረጢቱ እየነደደ አንድ የሚያብረቀርቅ ነገር ከአመዱ ውስጥ ታየ:: ጠጋ ብሎ ቢመለከት የብር እቃ መሆኑን ተገነዘበ፡፡ ከእኚያ ጳጳስ ቤት የሠረቀው እቃ ለመሆኑ ታወሰው:: ወደ እሳቱ መመልከቱን ተወ፡፡ እርምጃውን ሳያዛባ ከወዲህ ወዲያ
መንቆራጠጡን ቀጠለ፡፡ ወደ እሳቱ ዞር ብሎ ቢያይ እነዚያ ሁለት ከብር የተሠሩ የሻማ ማብሪያዎች መሆናቸውን አረጋገጠ፡፡
«ቆይ እስቲ» በማለት ወደ አሳቡ ተመለሰ፡፡ «ዣን ቫልዣ ማን
እንደሆነ የሚያስታውሱ ስለሆነ እነርሱም መጥፋት አለባቸው» ሲል አሰበ::ነገር ግን እሳቱ ኃይለኛ ስለነበር ሊያቀልጣቸው ካልሆነም ደብዛቸው እስኪጠፋ ሊያበላሻቸው እንደሚችል ስለገመተ የሻማ ማንደጃዎቹን ቀስ ብሎ ከእሳቱ ውስጥ አወጣቸው:: ወደ እሳቱ ጠጋ ሲል ሰውነቱን ትንሽ ስለሞቀው ደስ አለው:: «እንዴት ደስ ይላል» ሲል ተናገረ፡፡
የሻማ ማንደጃዎቹን እያገላበጠ አያቸው:: ለአንድ ደቂቃ ቢቆይ እሳቱ ውስጥ መልሶ ይጨምራቸው ነበር፡፡ ግን ወዲያው ከመቅጽበት «ዣን
ቫልዣ ፣ ዣን ቫልዣ» ተብሎ የተጠራ መስሉት ጆሮውን አቀና፡፡
ፀጉሩ ቆመ፤ መርዶ የተረዳ መሰለው::

«አዎን! ይኸው ነው፤ አልቋል» በማለት ድምፅ ያሰማው ነገር
ንግግሩን ቀጠለ፡፡ «የጀመርከውን ብትጨርስ ይሻላል፡፡ የሻማ ማንደጃዎቹንም አቃጥላቸው:: እነርሱም አንተነትህን የሚያስታወሱ ስለሆኑ አጥፋቸው፡፡ እኚያ ጳጳስንም እርሳቸው! ሁሉንም ነገር እርሳ! በሻምፕማትዩ ሕይወት
ላይ ፍረድ፣ አዎን ብትፈርድ ይሻልሃል! ብራቮ፣ መልካም ሥራ! ይኸው ነው፣ አልቋል፡፡ ምን አለ! ይህ ሰው ምናልባት ንጹህ ሰው ሊሆን ይችላል።
ብቻ እድሉ ሆነና በአንተ ስም ተጠርጥሮ አዘቅት ውስጥ ሊገባ ነው።የአንተን ኃጥያት በመሸከሙ ብቻ መጨረሻው የከፋ፣ የስቃይና የመከራ ዘመን ሊያሳልፍ ነው:: ምን አለ፤ ይሁና! አንተማ ሰዎች በይበልጥ ሊያከብሩ |
'አንተን ያኑርልን፧ ሺህ ዓመት ከንቲባ ሁነህ ኑር፣ የተጠማን አጠጣ፤የተራበን ኣብላ፤ እናት አባት የሌለውን ጡር፤ ተባረክ! የሰው ፍቅር ይስጥህ' ሊሉህ ነው፡፡ እና አንተ እዚህ ስትደሰት፣ ስትዝዝናና አንድ ሰው ግን የአንተን የጥንት ልብስ ለብሶ፧ ባለማወቅ ስምህን ወርሶ የአንተን
የኃጢአት ሰንሰለት እየጎተተ ጨለማ ውስጥ ሊኖር ነው፡፡ ድንቅ፣ ዕጹብ ድንቅ ሥራ! እንዴት ያለው ድርድር ነው! አንተ ርኩስ!»
ፊቱ ላብ በላብ ሆነ:: የሻማ ማንደጃዎቹን በደበዘዘ ዓይኑ
ተመለከታቸው፡፡ ከውስጡ የሚወጣው ድምፅ አልተቋረጠም፤ ቀጠለ።
«ዣን ቫልዣ ፣ ድምፃቸውን ከፍ እያደረጉ የሚናገሩ ብዙ ድምፆች
ይኖራሉ፡፡ ድምፆቹ ለዘላለም ይጮሃሉ፤ አንተንም ያሞግሳሉ፡፡ ግን ከእነዚህ ድምዖች መካከል አንዱ ብቻ ሌሎች ሳይሰሙት አንተን ያሳድድሃል፤ በጨለማ ሁሉ ይከተልሃል፡፡ ስማ አንተ ርኩስ፤ የተረገምክ! ይሄ ሁሉ ሙገሣ፣ ይሄ ሁሉ አክብሮትና አድናቆት ሰማይ ቤት ሳይደርስ ይጠፋል፡፡
ርግማኑ ግን እስከ እግዚአብሔር ፊት ድረስ ይከተልሃል፡፡»

ስውር ሕሊናው ውስጥ በዝግታ የጀመረው ድምፅ ቀስ እያለ እየጎላና ለጆሮው እየቀረበ መጣ፡፡ ያ ድምፅ ንግግሩን ሲጀምር ከራሱ ሕሊና የሚወጣ መሆኑን ቢታወቀውም ከቃላቱ ኃይለኛነት፣ ከድምፁ ጥራትና ጉልህነት
የተነሳ እውነትም ከአጠገቡ ሰው ቆሞ የሚገስጸው ስለመሰለው ክፍሉ ውስጥ ሰው እንዳለ ለማረጋገጥ ሲፈራ ሲቸር እየተገላመጠ አየ::

«ማነው?» ሲል ተጣራ:: መጣራቱ ራሱን ስላስገረመው ከት ብሉ
የቂል ሳቅ ሳቀ፡፡ «ምን ጅል ነኝ እባካችሁ! ከዚህ ውስጥ ማንም ሊገባ እንደማይችል እያወቅሁ!» ነገር ግን ከክፍሉ ውስጥ አንድ ዓይነት ኃይል ነበር፡፡ ሆኖም ያ ኃይል ለሰዎች ዓይን ጉልህ አልነበረም::

የሻማ ማንደጃዎቹን ከፍ ካለ ሥፍራ ላይ አስቀመጣቸው:: በየተራ የተፈራረቁበትን የተለያዩ ሁለት አሳቦችን አገናዘበ፡፡ ሁለቱም አሳቦች እጅግ የሚያስፈሩ ሆኖ አገኛቸው:: አንዱ ከሌላው አይሻልም:: ሻምፕማቲዩ
👍15🔥1
«ዣን ቫልዣ ናቸው» ተብሎ በጥርጣሬ መያዛቸው ምን ዓይነት አጋጣሚ እንደሆነ አስደነቀው:: ስለወደፊት ሕይወቱ እንደገና አሰበ። ራሱን ያጋልጥ! ግን ስንቱን ሰው ሜዳ ላይ ጥሎ፣ ስንቱን ሰው ወደኋላ ትቶ! ራሱስ ቢሆን
ያን ሁሉ ከበሬታ፣ ሀብት፣ የሰው ፍቅር የምቾት ኑሮና መንደላቀቅን ትቶ እስር ቤት ገብቶ በእግር ብረት ይታሰር! ጨለማ ቤት ይግባ፤ ይልፋ ፤ ይሰቃይ፧ ከቀዝቃዛ ስሚንቶ ላይ ይተኛ:: የእስር ቤት ኑሮ ስቃይ ምን እንደሆነ ለአሥራ ዘጠኝ ዓመት ያየውና ተንገሽግሾ የወጣበት ነው:: የምን ርግማን ነው እባካችሁ! የሕይወት ብያኔም እንደ አዋቂ ተንኮለኛና እንደ
ሰው ልብ ምቀኛ ይሆናል? ሰው እንዲህ ያለ ወጥመድ ውስጥ ገብቶ መውጫ ያጣል? መንግሥተ ሰማይ ገብቶ ሰይጣን መሆን ወይስ ገሃነም ገብቶ መልኣክ መሆን? የፈጣሪ ያለህ፣ የቱ ይመረጣል? ምንስ ይደረጋል?
ስቃዩ እንደገና አዲስ ሆኖ አስጨነቀው፡፡ ሳፋ ላይ እንደተቀመጠ ውሃ በአሳብ ዋለለ፡፡ ተስፋ ሲቆርጡ የሚታየውና በቃላት ለመግለፅ የሚያዳግተው እንዲያው ዝም ብሎ ቅርጽ የሚያወጣው የተምታታ ዓይነት ነገር ከፊቱ ድቅን አለ። ከመዳህ ቆሞ መሄድ እንደጀመረ ሕፃን ተንገዳገደ..
ጉልህ ሆኖ የሚታየው ነገር አልነበረም፤ ሁሉም ደብዛዛ ሆነበት:: ከአንጐሉ የሚወጡ አሳቦች ሁሉ እንደጢስ የተነኑ እንጂ ተሰብስበው ቅርጽ ያላቸው
አልሆኑም:: ቀኝም ነፈሰ ግራ፣ ግልጽ ሆኖ የታየው ነገር ቢኖር የቁም ስቃይ መቀበሉን ነበር፡፡ በሕይወት እያሉ መሞት! እየተነፈሱ መቀበር

እንደገና ከጀመረበት ተመለሰ፡፡ ይህ ያልታደለ ነፍስ ከአሳብ አለንጋ
ግርፊያ መላቀቅ ስላቃተው በአሳብ መዋተቱን ቀጠለ፡፡

ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ሆነ፡፡ አምስት ሰዓት ሙሉ ቂጡ መሬት ሳይነካ
ከወዲህ ወዲያ እያለ ቆየ:: በዘጠኝ ሰዓት ሰውነቱ ዛለ ከወንበሩ ላይ አረፍ አለ፡፡ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ ለካስ እንቅልፍ ወስዶት ኖሮ ይቃዥ ጀመር::

እንደማንኛውም ቅዠት በሕልሙ ያየው ቀደም ሲል ሕሊናውን
ስላስጨነቀው ጉዳይ ነበር፡፡ ሕልሙ ምንም እንኳን ቅዠት ቢሆንም በይበልጥ
እንዲያስብና እንዲጨነቅ አደረገው:: ወደ ኣራስ ከመሄዱ በፊት በእጁ ፅፎ ያስቀመጠውን አሳብ ነበር በሕልሙ ያየው:: ምናልባት በወረቀቱ ላይ
ተጽፎ የነበረውን አሳብ ቃል በቃል ገልብጠን ብናስቀምጠው ሳይጠቅመን አይቀርም::

የዚህን ሕልም ፍሬ ሀሳብ ሳናክል ብናልፍ ደግሞ በዚያን እለት ምሽት የሆነውን ታሪክ በቁንጽል ማስቀረት ይሆናል፡፡ ሕልሙ አንዲት የታመመች ሴት ስለገጠማት ውጣ ውረድ የሚያወሳ ነበር:: ታሪኩ እንደሚከተለው ሲሆን በፖስታው ላይ የተጻፈው ቃል «በዚያን እለት ምሽት ያየሁት ሕልም» የሚል ነው::
ከአንድ እርሻ ውስጥ ነበርሁ:: የሚያሳዝነው ከእርሻ ውስጥ ሳር
እንኳን አልበቀለም:: ጊዜው ቀን ይሁን ማታ አይታወቅም::

ከወንድሜ ጋር አብረን እንጓዛለን፡፡ የልጅነት ወንድሜ ነው:: ስለዚህ
ወንድሜ ብዙም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ከነአካቴው መልኩ እንኳን
በቅጠ ትዝ አይለኝም፡፡እናወራለን፣ ከእኛ ጋር የሚጓዙ ሌሎች ሰዎች
አየን፡፡ ድሮ ስለምናውቃትና ዘወትር መስኮት ስለምትከፍት ጎረቤታችን ቤት ነው የምናወራው፡፡ እያወራን ሳለ በዚያ በተከፈተ መስኮት በኩል
አድርጎ በሚገባ ነፋስ የተነሳ ብርድ ብርድ አለን፡፡

ከእርሻው ቦታ ዛፍ አልነበረም:: አንድ ሰው በአጠገባችን ሲያልፍ
አየነው:: ራቁቱን ነው ፤ ምንም ነገር አልለበሰም:: ሰውነቱ በጣም
ጠቋቁሮአል። አፈርማ ቀለም ካለው ፈረስ ላይ ተቀምጧል። ሰውዬው መላጣ ሲሆን ከራስ ቅሉ ውስጥ ያሉ የደም ሥሮች በጉልህ ይታያሉ፡፡ እንደ ብረት የከበደ ዱላ ይዟል፡፡ ምንም ሳይናገር በአጠገባችን አለፈ::

«ጭር ባለው በዚያኛው መንገድ እንሂድ» አለኝ ወንድሜ፡፡

እርሱ ያለውን መንገድ ተከትለን ሄድን፡፡ የሚያደናቅፈን እንኳን ዛፍ
ቁጥቋጦ አልነበረም:: ቀይ አፈር ብቻ ነው የሚታየው:: ጥቂት
እንደተራመድን ለምሰጠው አስተያየት መልስ የሚሰጠኝ አጣሁ:: ዞር ብል ወንድሜን ከአጠገቤ ኣጣሁት:: በሩቅ ወደሚታይ መንደር አመራሁ::
እኚያ ካህን የታሠሩበት ከተማ መሰለኝ::

ወደ ከተማው ከሚያስገባው መንገድ ስጠጋ ጭር ማለቱን ተገነዘብኩ::ወደ ሌላ አቅጣጫ አቋርጬ ሄድኩ፡፡ ከሁለት መንገዶች መገናኛ አጠገብ
አንድ ሰው ግድግዳ ተደግፎ ቆሞአል:: «ይህች ከተማ ማን ትባላለች? ስል ጠየቅሁት፡፡ ሰውዬው መልስ አልሰጠኝም፡፡ የአንድ ቤት በር ሲከፈት
ስላየሁ ቤቱ ውስጥ ገባሁ፡፡»
ከፊት ለፊት ከነበረው ክፍል ውስጥ ሰው አልነበረም:: ወደሚቀጥለው ክፍል አመራሁ:: አንድ ሰው ግድግዳ ይዞ ቆሞአል:: «የማን ቤት ነው?
እኔስ የት ነው ያለሁት?» ስል ጠየቅሁት፡፡ መልስ አልሰጠኝም:: ከአጥር ግቢው ውስጥ የአትክልት ቦታ ነበር፡፡
ወደ አትክልቱ ሥፍራ ወጣሁ:: ጭር ያለ ሥፍራ ነበር፡፡ አንድ ሰው
ዛፍ ተደግፎ ቆሞአል:: «ይህ ቤት የማነው? እኔስ የት ነው ያለሁት?» ስል ጠየቅሁት:: መልስ አልሰጠኝም::
ቶሎ ብዬ ከዚያ ቤት ወጥቼ ሄድኩ፡፡ በየመንደሩ ተዟዟርኩ፡፡ መንገዱ ሁሉ ጭር ብሏል፡፡ የየቤቱ በር ግን ክፍት ነበር፡፡ መንገድ ላይ ወፍ እንኳን
ዝር አይልም:: ድምፅ የሚባል ነገር ፍጹም አይሰማም:: ነገር ግን ከየመንገዱ ጥግ፣ ከየቤቱ ግድግዳ ሥር ሰው ቆሞአል፡፡ ሆኖም ማንኛቸውም ቢሆኑ
ቃል አይናገሩም:: የሚደንቀው ደግሞ ማንኛውም ሰው ቢሆን ከቆሙት ሰዎች መካከል ሁለቱን በአንድ ጊዜ ማየት አይችልም፤ እነርሱም አይተያዩም::
በእያንዳንዱ ሰው አጠገብ ባለፍኩ ቁጥር አተኩረው ያዩኛል፡፡ ከከተማው ወጣሁና ወደ ሜዳው መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ጥቂት እንደተጓዝኩ ወደኋላ ብል ሠራዊት ተከትሎኛል፡፡ በየመንገዱና በየጥሻው ሥር ቁመው የነበሩ
ሰዎች መሆናቸውን ተገነዘብኩ፡፡ የፊት ገጽታቸው የተለየና አስገራሚ
ፍጡሮች ናቸው፡፡ የተቻኮሉ አይመስሉም፣ ግን ከእኔ ይበልጥ ነበረ የሚራመዱት፡፡ ሲራመዱ ድምፅ አያሰሙም፡፡ በድንገት ሲከቡኝ አየኋቸው::ፊታቸው ቀይ አፈር ይመስላል፡፡ ወደ ከተማው ስገባ በመጀመሪያ ያነጋገርኳቸው ሰውዬ 'ወዴት ነው የምትሄደው? ከሞትክ መቆየትህን አላወቅህም እንዴ? ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ መልስ ለመስጠት አፌን ስከፍት ከአጠገቤ ሰው አጣሁ»

መሴይ ማንደላይን በጣም በርዶት ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ ውርጭ ያዘለ ነፋስ ተከፍተው የነበሩትን መስኮቶች ያወዛውዛል፡፡ እሳቱ ጠፍቷል፡፡ አሁንም እንደጨለመ ስለሆነ አልነጋም፡፡ ተነስቶ ወደ መስኮቱ ሄደ፡፡ ሰማይ ላይ
ከዋክብት አይታዩም፡፡ ወደ ውጭ ተመለከተ፡፡ አንድ የሚያቃጭል ድምፅ ዓይኑን ሳበው:: የጋሪ ኮቴ ነበር የሰማው::

«በዚህ ሰዓት ደግሞ የምን ጋሪ ነው?» ሲል ራሱን ጠየቀ:: «ማነው
ገና ሳይነጋ በጋሪ የሚሄደው?»
ወዲያው የነበረበት ክፍል በር ሲንኳኳ ሰማ:: ከእግር እስከ ራሱ
አንድ ነገር ወረረው፧ በጣም ደነገጠ፡፡

‹‹ማነህ?»

አንድ ሰው መልስ ሰጠ፡፡

«ክቡር ክንቲባ፣ እኔ ነኝ፡፡»

አሮጊትዋ የቤት ሠራተኛ እንደሆነ አወቀ፡፡

«ምነው፧ ምን ፈለጉ?» ሲል ጠየቃቸው::

«ከንጋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ሆኖአል ጌታዬ!»

«ታዲያ ምን አለበት!»

«ክቡር ከንቲባ፣ ረሱት እንዴ! ጋሪ በጠዋት እንዲመጣ ብለው
አዝዘው ነበር እኮ!»

«ይቅርታ፣ አዎን አዝዤ ነበር፡፡»

አሮጊትዋ ቢያዩት ይደነግጥ ነበር:: የሻማ ማንደጃዎቹን ተመለከተ።
የቀለጠውን ሻማ ጠራረገ:: አሮጊትዋ በር ላይ ቆመው ይጠብቃሉ።
👍10👏3😁3
ሲዘገይባቸው «ጌታዬ ባለጋሪውን ምን ልበለው?» ሲሉ እንደገና ጠየቁ፡፡
«ጠብቅ ይበሉት! መጣሁ አንድ ደቂቃ!»
ጋሪው አራስ ከተማ ሲደርስ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ይሆናል፡፡ እስካሁን ታሪኩን የተከታተልነው ሰው ከጋሪው ወርዶ ወደ ከተማ በእግሩ ተጓዘ፡፡
ከተማውን ከዚያ በፊት አያውቀውም፡፡ ለአገሩ ባዳ ለሰዉ እንግዳ ነው፡፡ ብዙ ስለተጓዘ ለመመለስ መንገዱ ጠፋው፡፡ ከዚያ አካባቢ ፍርድ ቤት
እንዳለ እየፈራ አንዱን መንገደኛ ጠየቀው፡፡ «ጌታዬ» አለ ሰውዬው
«የፍርድ ቤት ሙግት ለመመልከት ፈልገው እንደሆነ ጊዜው መሽቷል፡፡
ሥራ የሚያቆሙት በአሥራ ሁለት ሰዓት ነው::
አደባባይ ካለበት ሲደርሱ ፍርድ ቤቱ ከአንድ ትልቅ ሕንፃ ውስጥ
እንደሆነ አመላከተው::
«ጌታዬ እድለኛ ነዎት፧ የፍርድ ቤቱ መብራት አልጠፋም፤ አሁንም
ዳኞች ችሎት ላይ ናቸው ማለት ስለሆነ መግባት ከፈለጉ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
ብርቱ ክርክር ገጥሞዋቸው ይሆናል እስካሁን የቆዩት፡፡»
ወደ ፍርድ ቤቱ አመራ:: ቤቱ ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ ከጠበቆች
አነስተኛ ድምፅ በስተቀር ብዙ ጫጫታ የለም:: ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል የሌሎች ሰዎችን ጉዳይ ካየ በኋላ አሁን የሚነጋገረው «ፍራፍሬ ሰርቀዋል» ስለተባለው ስለሻምፕማትዩ ነው:: እኚህ ሰው በእርግጥ ፍራፍሬ
ለመስረቃቸው ማረጋገጫ አልተገኘም:: ማረጋገጫ የተገኘለት ወንጀላቸው
ግን ከእስር ቤት መጥፋታቸው ነበር፡፡ ምርመራው ቀጥሎ የምስክሮች ቃል ተሰምቷል፡፡ አሁን የሚጠበቀው የአቃቤ ሕግ ክርክርና የዳኞች ውሳኔ ነበር፡፡ በአዝማሚያው እንደታየው በሰውዬው ላይ እንደሚፈረድ ነበር።ጠበቃቸው ግን በጣም ጎበዝ ሲሆን ከዚያ በፊት በያዘው ጉዳይ ተረትቶ አያውቅም:: ሰውዬው ጠበቃ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ጸሐፊም ነበር፡፡ የጠባቂዎች ኃላፊ በሩን ከፍቶ ብቅ አለ፡፡
«ጎበዝ እንዴት ነው፧ ልገባ እችላለሁ?»
«አይቻልም» አለ የጠባቂዎች ኃላፊ::
«ምነው?»
«ምክንያቱም ቤቱ ከአፍ እስከ ገደፍ ጢም ብሎ ሞልቶአል»
«ምን ማለትዎ ነው፤ አሁን አንድ መቀመጫ ጠፍቶ ነው?»
«አንድ መቀመጫ! በሩ የተዘጋው ለዚሁ ነው:: ካሁን በኋላ ሰው
አይገባም::››

የጠባቂዎች ኃላፊ ጥቂት ቆይቶ «እርግጥ ዳኞች ከተሰየሙበት አካባባ ሁለት ወይም ሦስት ሰው የሚያስቀምጥ ቦታ ነበር፤ ነገር ግን ከዚያ ቦታ እንዲቀመጡ የሚፈቀደው ለመንግሥት ባለሥልጣኖች ብቻ ነው፡፡»

ኃላፊው ይህን እንደተናገረ ፊቱን አዙሮ ሄደ፡፡ ይህን ጊዜ ኃላፊው
ያነጋገረው ሰዉ ጥቂት አሰበና ከኪሱ ወረቀትና ብዕር አወጣ፡፡ መብራቱ ወደነበረበት ጠጋ አለ፡፡ «መሴይ ማንደላይን የሞንቴስ ሱር ሞንቴስ ከንቲባ ብሎ ከጻፈ በኋላ የጠባቂዎች ኃላፊ ወደሄደበት አቅጣጫ ፈጠን ብሎ
ሕዝቡን አልፎ ሄደ:: ብጣሹን ወረቀት ለጠባቂዎች ኃላፊ ሰጠውና «ይህ ወረቀት ለዳኛው ስጣቸው» አለው::
የጠባቂዎች ኃላፊ ጽሑፉን ከተመለከተ በኋላ ለመሀል ዳኛው ወስዶ ሰጣቸው::

የሞንቴስ ሱር ሞንቴስ ከንቲባ ሳይታወቀው ሰው ያከበረውና ያደነቀው መሰለው:: ባለፉት ሰባት ዓመታት ዝናው በሚኖርበት አካባቢ ብቻ ሳይሆ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ተሰምቶ ነበር፡፡ ቢያንስ እርሱ ከነበረበት ክፍለ ሀገር
በየአቅጣጫው እስከ ሁለትና ሦስት ክፍለ ሀገሮች ዝናው ዘልቆ ሄዶ ነበር

የሻምፕማቲዩን ጉዳይ የያዙት መሐል ዳኛ ወረቀቱን ሲያዩ ሰውዬው የሚያውቁትና የሚያደንቁት ሰው እንደሆነ አወቁ፡፡ የጠባቂዎች ኃላፊ
ወረቀቱን ለዳኛው ሲሰጣቸው ከወረቀቱ በተጨማሪ በቃሉ «እኚህ ሰው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሰጡ ይፈልጋሉ» አላቸው:: ወዲያው ዳኛ ለጠባቂዎች ኃላፊ «አስገባው» ሲለ ትእዛዝ ሰጡት::
ይህ ታሪኩን የምንከታተለው አሳዛኝና የተከፋ ሰው ወረቀቱን ከሰጠበት ሥፍራ አልተነቃነቀም::

«ጌታዬ ይከተሉኝ» አለው:: ቀደም ሲል ፊቱን ያዞረበት ዘበኛ አሁን
ለጥ ብሎ እጅ ነስቶ ነው «ይከተሉኝ» ያለው:: የጠባቂዎች ኃላፊ ወዲያው በተራው አንድ ብጣሽ ወረቀት ብጤ ሰጠው:: ጽሑፉም «የመሐል ዳኛው
የአክብሮት ሰላምታውን ያቀርባል» የሚል ነበር፡፡

ወረቀቱን ጭምድድ አድርጎ ኪሱ ውስጥ ጨመረው፡፡ ወረቀቱ አቻ
ዓይነት ትዝታ ቀሰቀሰበት:: የጠባቂዎች ኃላፊን ተከትሉ ሄደ፡፡ ወንበር ተከልለው ከተቀመጡበት ሥፍራ ደረሱ::

«ጌታዬ ይቀመጡ» አለው የጠባቂዎች ኃላፊ:: ሰውዬው እንዲሄድለት ግድግዳውን ተደግፎ ቆመ፤ አላበው፧ መተንፈስ አቃተው፤ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፡ እንደገና ቁጭ አለ፡፡ የተቀመጠበት ቦታ ትንሽ ዞር ያለ ስለነበር ለሰው በግልፅ አይታይም

💫ይቀጥላል💫
👍175
#መኖር_የሚያስመኝ

ሀዘን ደስታ ሲዘባረቅ
እንባ ሲቀር ጥርስ ሲስቅ
አመት መንፈቅ ሲፈራረቅ
ኑሮ ለሕይወት መልስ ሲሰጥ
በሀሴት ተሞልቶ ባሕር ሲሰመጥ
ያፀላው ፅልመት ሲገለፅ
ተስፋ ሲያንዣብብ ሀሳብ ሲቀረፅ.............
ያኔ ነው እንጂ መኖር የሚያስመኝ
ልብ የሚጠግን የራስ ሰው ሲገኝ::

🔘ከቃልኪዳን ወርቁ🔘
20👍6
#ምንዱባን


#ክፍል_አስራ_አራት


#ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ

....«ጌታዬ ይቀመጡ» አለው የጠባቂዎች ኃላፊ:: ሰውዬው እንዲሄድለት ግድግዳውን ተደግፎ ቆመ፤ አላበው፧ መተንፈስ አቃተው፤ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፡ እንደገና ቁጭ አለ፡፡ የተቀመጠበት ቦታ ትንሽ ዞር ያለ ስለነበር ለሰው በግልፅ አይታይም
ቁጭ እንዳለ አሳቡን የመለወጥ ዝንባሌ ታየበት:: “እስቲ አሁን ማን
አስገድዶኝ ነው የመጣሁት» ሲል አሰበ:: ነገር ግን እንዴት እንደሆነ
ሳያውቀው ቶሎ ብድግ ብሎ በመራመድ ችሎቱ ውስጥ ዳኞች ከነበሩበት አካባቢ ተጠጋ::

አካባቢውን በሚገባ ቃኘው:: ዳኞች ከፊት ለፊት ከፍ ካለው ሥፍራ ተቀምጠዋል:: ጠበቆች አፍጥጠዋል:: ጠባቂ ወታደሮች በየጥጉ ተበታትነው ቆመዋል:: የዳኞች ጠረጴዛ በደማቅ ጨርቅ ተሸፍኖአል:: የበሮች እጄታ
አካባቢ በእድፍ ጠቁሯዋል:: «
ስው ሰራሽ ሕግ እውነትን ያወጣል» በሚል እምነት ከዚያ የነበረ ሁሉ በጥሞና ያዳምጣል:: የሰው ብዛት ከመጠን በላይ
ስለነበር እርሱን ማንም ልብ አላለውም:: ሰው ሁሉ ይመለከት የነበረው ከወንጀለኞች መቆሚያ ላይ በሁለት ጠባቂዎች ታጅቦ ቆሞ የነበረውን ሰው
ነው::

በሁለት ጠባቂዎች ታጅበው የቆሙት ተከሳሹ ሻምፕማቲዩ ነበሩ፡፡መሴይ ማንደላይን አተኩሮ ተመለከታቸው:: በመልክ መመሳሰላቸውን ተገነዘበ፡፡ በእድሜ ግን ከእርሱ በጣም ያረጁ ይመስላል::

እየቀረበ ሲሄድ የመሐል ዳኛውና አቃቤ ሕጉ በጉልህ ስላዩትና
ስለለዩት በአንገት ሰላም አሉት:: ዳኞቹን፣ ሕግ አስከባሪውና እዚያ የነበሩ ጠበቆችና ጠባቂዎች ከሃያ ሰባት ዓመት በፊት ያያቸው መሆኑን አስታወሰ፡፡
አሁንም ከስንት ዓመት በኋላ ከእነዚህ ሰዎች እጅ ሊወድቅ በመሆኑና ውሳኔያቸው ስለአስፈራው ዓይኑን ጨፈነ፡፡ ከፊት ለፊቱ የቆሙት ተከሳሽ
«ዣን ቫልዣ ናቸው ተብለው ነው የተከሰሱት» የሚል አሳብ ስለተሰረጸበትና ሕሊናው እንደ መሳት ስላለ ቶሎ ብሎ ተቀመጠ፡፡ እንደተቀመጠ ዣቬርን በዓይኑ ፈለገው ፤ አላገኘውም፡፡ ሕግ አስከባሪው መንገድ ላይ ስለተቀመጠ ምስክሮችን ሊያያቸው አልቻለም:: ክፍሉም ቢሆን በመጠኑ ጨለምለም
ያለ እንጂ ቦግ ብሉ የበራ ብርሃን አልነበረውም::

ክርክሩ የፈጀው ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ሲሆን ተከሳሹ ኣንደበተ
ርቱዕ ስልነበሩ የተከሰሱበትን ይካዱ እንጂ በሚገባ አላስረዱም:: እንዲያውም
ብዙውን ጊዜ ጣራ ጣራውን ነበር የሚያዩት:: ሲያዩዋቸው ቂላቂልና
ጅላጅል ቢጤ ይመስላሉ፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በእኚህ ሰው ዝምታ የተነሣ ሰው ሁሉ የጠበቀው ከባድ ቅጣት ነው።

ሕግ አስከባሪው የሚከተለውን ተናገረ::

«ተከሳሹ በቅድሚያ ክስ የቀረበባቸው በፍራፍሬ ስርቆት ወንጀል ነበር፡፡ ክሱ ሲመሠረት የቀረበው ማስረጃ 'የሠረቁት ፍሬ ከእነቅጠሉ በእጃቸው ላይ ተገኝቷል' የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ብቻ እንደ ማስረጃ
ተቆጥሮ ለመስረቃቸው ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም:: ተከሳሹ ከየት እንዳገኙት ሲጠየቁ ከመሬት ነው ያነሳሁት' ብለዋል፡፡ እርግጥም የፍራፍሬውን
ዛፍ ሌባ ቀጥፎ መንገድ ሊጥለው ይችላል፡፡ ስለዚህ ፍሬዎችን የያዘ
ቅርንጫፍ በመስበር የሰረቁት ሻምፕማትዩ ናቸው ለማለት ያስቸግራል።
ይህም በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ሊከሰሱ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከእስር ቤት ያመለጠ ወንጀለኛ ለመሆናቸው በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ ምንም እንኳን
ዣን ቫልዣ ለመሆናቸው ምስክሮች ቢያረጋግጡም ተከሳሹ እስከመጨረሻው ክደዋል፡፡ ክህደቱን ትተው የፍርድ ቤቱን አስተያየት ቢጠይቁ የሚሻላቸው
ለመሆኑ ቢገለጽላቸውም አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ በተከሳሹ አመለካከት ስለካዱ ከቅጣት የሚያመልጡ መስሎአቸው ይሆናል፡፡ በዚህ በኩል ተሳስተዋል፡፡ሆኖም ይህ ከእውቀት ማነስ እንጂ ሆን ብሎ የተደረገ ሊሆን አይችልም፡፡
ተከሳሹ በእርግጥ ንቃት ይጉድላቸዋል፡፡ ይህም የሆነው ምናልባት ለረጅም ጊዜ እስር ቤት ቆይተው በመሰቃየታቸው ከዚያም በኋላ ብዙ ስለተንከራተቱ
ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ በሌላም፣ በሌላም ምክንያት ሊሆን ይችላል።ሆነም ቀረም የእርሳቸው አነጋገር አለማወቅ ወይም ችሎታ ማነስ ከሚሰጠው
ብያኔ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር አይገባም:: ነገር ግን ተከሳሹ ዣን ቫልዣ እንደሆነና የቅጣት ዘመናቸውን ሳይጨርሱ አምልጠው ለመጥፋታቸው
ጥርጥር የለውም:: ስለዚህ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በወንጀለኛ
መቅጫ አንቀጽ መሠረት ተገቢውን ቅጣት ይቀበላሉ፡፡»

ሕግ አስከባሪው ዳኞች ስለሰጡት አስተያየትና ስለፈጸሙት ጥልቅ
ምርምር በቅድሚያ ምስጋናውን አቅርቦአል፡፡ ተከሳሹን ግን የዳኞቹን ትንተና መሠረት በማድረግ በጣም ነቅፎዋቸዋል፡፡ ተከሳሽ ዣን ቫልዣ እንደሆነ
ስለመረጋገጡ ሲያስረዳ «ዝም ማለታቸው ነገሩን አምነው እንደተቀበሉ ያሳያል» አለ፡፡

«ቀደም ሲል ግን ክደው ነበር:: ለመሆኑ ዣን ቫልዣ ማነው? ዣን ቫልዣ የተተፋ፣ አገር የጠላውና ሌላም ሌላም ሰው ነው፡፡»
ሕግ አስከባሪው ይህን ሲናገር ከዚያ የነበረ ሰው ሰውነት ሁሉ
ስቅጥጥ አለ፡፡ «ሻምፕማንቲዩ ማለት ዣን ቫልዣ ነው» ተብሎ ክስ
ሲመሠረት «ዦርናል ደ. ለ ፕሪፊትየር የተባለ ጋዜጣ ዣን ቫልዣ ማን እንደሆነ ሲያስረዳ «ዣን ቫልዣ ማለት ወሮበላ፣ ለማኝ፣ ቀጣፊ፣ መተዳዳሪያ
የሌለው አውደልዳይ፣ ሕይወቱን ወንጀል በመሥራት የሚመራ እንዲሁም ሌላም ሌላም ቅጽል ሊሰጠው የሚገባ ነው» ብሎ እንደጻፈ ተናገረ፡፡

«ይህ ሰው ፍራፍሬ ሠርቆ ቢያዝም አድራጐቱን ክዷል፡፡ እንዲሁም ከእስር ቤት ለማምለጡም ከሕግ ፊት ክዷል፡፡ የሚገርመው የገዛ ስሙን
እንኳን የካደ ሰው ነው:: ምን ያልካደው ነገር አለ! ሕልውናውን ጨምሮ ነው የካደው ለማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እርሱ ሽንጡን ገትሮ ቢክድም አራት ምስክሮች መስክረውበታል: የተከበሩትና ውሽት የማያውቁት የፖሊስ
አዛዥ ዣቬር እንኳን በእርሱ ላይ መስክረዋል፡፡ እስር ቤት ውስጥ ከተከሳሹ ጋር አብረው ታስረው ከነበሩት ሰዎች መካከል ሦስት እስረኞችም መስክረውበታል፡፡ እነዚህ ምስክሮች ከመሰከሩበት በኋላ እንኳን ወንጀሉን አምኖ ይቅርታ አልጠየቀም:: ስለዚህ ማኅበራዊ ኑሮን ሊያፋልስ ታጥቆ
የተነሣ ወንጀለኛ ስለሆነ ቅጣቱ ሊቀልለት አይገባም፡፡»

ሕግ አስከባሪው ይህን ማብራሪያ ሲሰጥ ካህኑ ተከሳሽ አፋቸውን
ከፍተው በመገረምና በመደነቅ አዳመጠ፡፡ ሕግ አስከባሪው አንደበተ ርቱዕ በመሆኑ ቢያደንቁትም በማያውቁት ነገር እንደዚያ ስለወረደባቸው ከልብ
ረገሙት:: ግራ ቀኙን ከቃኙ በኋላ ተከሳሹ ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡
ሕግ አስከባሪው ትችቱን በመቀጠል «ማንም ሰው ወንጀል ሊሠራ ወይም ውሸት ሊናገር ይችላል፡፡ ግን ከሕግ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ይህ ሰው ግን ወንጀል ከመፈጸም አልፎ ከሕግ ለማምለጥ ሞክሮአል፡፡ ይህም
ከባድ ወንጀል በመሆኑ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ አሳብ ኣቀርባለሁ::»

«ስለተሰጠው አስተያየት የምትሰጠው መልስ አለ?» ሲሉ ዳኛው ተከሳሹን ጠየቁዋቸው:: ቆባቸውን ያፍተለትሉ የነበሩት ተከሳሽ ምንም ነገር እንዳልሰማ ዝም አሉ::

ዳኛው ጥያቄውን ደገመላቸው::
አሁን ግን ጥያቄውን ስለሰሙ ዳኛው ምን ማለት እንደፈለጉ ገባቸው::ከእንቅልፍ እንደነቃ ሰው ከወዲያ ወዲህ ተመለከቱ፡፡ ዳኞቹን፣ ሕግ አስከባሪውን፣ ጠበቆቹንና ተመልካቹን ሕዝብ አፍጥጠው ካዩ በኋላ ከፊት
ለፊት የነበረውን መከለያ ብረት አጥብቀው ይዘው በድንገት በከፍተኛ ድምፅ መናገር ጀመሩ፡፡ ቃላት ተሽቀዳድመው «እኔ ልቅደም፧ የለም እኔ ልቅደም» ያልዋቸው ይመስል እየተቻኮሉ በጣም በፍጥነት ተናገሩ፡፡
👍194
«የምለውን በጥሞና አድምጡኝ:: ከመሴይ ባሉፕ ሱቅ ውስጥ ለጋሪ
የሚሆን የብረት ተሽከርካሪ ሰራተኛ ነኝ፡፡ ብረት መቀጥቀጥ በጣም ከባድ ሥራ ነው:: ሥራውን እንሰራ የነበረው ከቤት ውጭ ሲሆን አሠሪያችን ይህን ያህል ለሠራተኞች ደኅንነት ደንታ አልነበራቸውም.: ደግ የሆነ አሠሪ
ለሠራተኞቹ በማሰብ ለስራ የሚሆን የተለየ ቤት ይሠራል፡፡ እኛ ግን ሜዳ ላይ ነበር የምንሠራው:: ቆፈን ሲይዘን ሥራችንን አቁመን በትንፋሻችን እጃችንን ያሞቅን እንደሆነ አሠሪያችን በጣም ይቆጣናል፡፡ ለምን የሥራ
ጊዜ ታባክናላችሁ' እያሉ ይጮሁብናል፡፡ በተለይ በክረምት ከባድ በረዶ በሚጥልበት ጊዜ ብረት መቀጥቀጥ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የደረሰበት
ያውቀዋል፡፡ ሰውነትን በአጭር ጊዜ አሟምቶ በልጅነት ያስረጃል፡፡ በዚህ ሥራ የተሰማራው ሰው በአርባ ዓመቱ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነው የሚመስለው፡፡ እኔ በበኩሌ አምሳ ሦስት ዓመት ከሞላኝ በኋላ ብዙ ያመኝ ነበር፡፡ አሠሪዎች ያረጀ ሽማግሌን መቅጠር ስለማይወዱ እኔም ላይ
ጨከኑ፡፡ ሰው ሲያረጅ አሮራጌ ውሻ ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ በእርጅናዬ ዘመን በቀን ሰላሳ ሱስ ነበር የማገኘው:: ገንዘቡ በጣም አነስተኛ ቢሆንም ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ በዚህ ደመወዝ ሠራሁ:: በዚያን ጊዜ አንዲት
ልብስ አጣቢ ልጅ ነበረችኝ፡፡ ይህቺ ልጅ ልብስ እያጠበች ጥቂት ገንዘብ ታመጣ ነበር:: እርስዋ እየለፋች የምታመጣውን ገንዘብ በማዳመር እየተንገዳገድን እንደማይኖር የለምና እኛም እንዳቅማችን ኑሮ ካሉት
መቃብርም ይሞቃል እንዲሉ ኖርን፡፡ እድሜያችንን በዚህ ዓይነት ገፋነው:: ዶፍ ቢወርድ፤ ሐሩር ቢያቃጥል ልጂ ወደኋላ ሳትል ቀኑን ሙሉ ልብስ ታጥባለች:: ልብስ ቶሉ ቶሉ ማጠብ ነበረባት፡፡ አብዛኞቹ ደምበኞችዋ
ብዙም ቅያሪ የነበራቸው አይደሉም:: ስለዚህ የሚሰጥዋት ልብስ በእለቱ ታጥቦና ተተኩሶ የሚመለስ ነበር፡፡ ጥያቄያቸው ካልተጠበቀ ሁለተኛ ተመልሰው አይመጡም:: የልብስ አጣቢ ሰውነት ከእግር እስከ ጭንቅላት
ይርሳል፡፡ ልብሶቹን ታጥብ የነበረው እቤት ሳይሆን ወንዝ ወርዳ ነው::ከወንዝ የምትመለሰው አንዳንዴ ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ነበር፡፡ ወዲያው
እንደመጣች መደብዋ ላይ ትዘረራለች፡፡ በጣም ይደክማታል፡፡ ባልዋ እኔ ፊት እንኳን ጠዋት ማታ ይቀጠቅጣታል:: ዛሬ እርስዋ ከዚህ ሁሉ ተገላግላ አንድ ቀን እንኳን ሳይደላት ሞታለች:: መኳንንቶቼ ውሸቴን አይደለም፤
የምናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነው:: እኔ ማን እንደሆንኩ መሴይ ባሉፕን ጠይቁ፡፡ አሁኑኑ ሂዱና ጠይቋቸው:: ከዚህ ይበልጥ ከእኔ ምን እንደምትፈልጉ
አላውቅም::

ሰውዬው ንግግራቸውን አቆሙ፤ ቁጭ ግን አላሉም:: የተናገሩት
በቁጭትና በብሽቀት ነበር፡፡ ንግግራቸውን ሲጨርሱ ከእዚያ የነበረው ሰው ሁሉ ሳቁባቸው፡፡ የሚስቁትን ሁሉ ቀና ብለው ተመለከትዋቸው፡፡

እርሳቸውም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳያውቁ አብረው ይስቁ ጀመር፡፡የሚያስፈራና የማይገባ ነገር ነው ፧ አይደለም! የመሐል ዳኛው ቅን መንፈስ ያላቸው፣ ለሰው የሚያዝኑ ዓይነት ሰው ነበሩ:: ድምፃቸውን ከፍ
አድርገው «ይሄ መሴይ ባሉፕ የተባለውን ሰው ተከሳሽ ቀደም ብሎ የጠቀሰው ስለነበር ተፈልጎ ሊገኝ አልቻለም:: በሥራው ስለከሰረ አገር ጥሎ ኮብልሏል» ካለ በኋላ ወደ ተከሳሹ ዞር ብለው «ቢበቃህ ያሻላል፡፡
ሆኖም በመጨረሻ እንድትመልስልኝ የምጠይቃቸው ሁለት ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነርሱም አንደኛ «ዩሪናሪ ሰርቀሃል ወይስ አልሰረቅህም? ሁለተኛ
እስር ቤት ያመለጠውና ወንጀለኛው ዣን ቫልዣ” ማለት አንተ ነህ ወይስ አይደለህም?
የሚናገረው ሁለ አጥርቶ እንደሚያውቅና የተናገሩትን በትክክል የገባው ሰው እንደሚያደርገው ሁሉ ራሳቸውን ነቀነቀ፡፡ ወደ መሐል ዳኛ
ው ፊታቸውን አዙረው የሚከተለውን ተናገሩ::

«በመጀመሪያ ደረጃ» ካለ በኋላ ቀና ብለው ጣራውን ከዚያም ከቤቱ፡ውስጥ የተቀመውን ሁሉ ቃኘ::
«ምን ወዲህ ወዲያ ትላለህ? የተጠየቅንውን መልስ እንጂ:: በራስህ ላይ እኮ ነው የምትፈርደው» አለ ሕግ አስከባሪው::
ተከሳሸ ወዲያው ቀና ብለው በአፋጣኝ ተናገሩ፡፡
«ክፉና ጨካኝ ሰው ነዎት፤ ማለቴ እርስዎ አሁን የተናገሩት:: እኔ
የምሠራውንና የምናገረውን አውቃለሁ:: ፍሬ የሚባል ነገር አልሰረቅሁም፡፡ስርቆት የሚባል ነገርም አይነካካኝም፡፡ የእለት እንጀራ እንኳን የማላገኝ
ሰው ነኝ፡፡ ገላዬን ከወንዝ ታጥቤ ስመለስ መንገዱ ሁሉ ጭቃ ሆነብኝ::
ከጭቃ ለመሸሽ ጥግ ጥጉን ስሄድ ፍሬ የያዘ ቅርንጫፍ አየሁ:: 'የወደቀን አንሱ፤ የሞተን ቅበሩ ነውና አነሳሁት:: ያነሳሀት ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ ያስከትልብኛል ብዬ አልነበረም:: ኣሁን ግን በዚያ ሰበብ ከታሠርኩ
ሦስት ወሬ ነው:: ከዚያ ወዲያ የምናገረው ታሪክ የለኝም:: አንተ ታዲያ ክፉ ሰው በመሆንህ ትሰድበኛለህ፤ በእኔ ላይ ትፈርዳለህ:: የጠባቂዎች ኃላፊ ግን ደግ ሰው በመሆኑ ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ በትህትና 'መልስ ይስጡ እንጂ እያለ ይመክረኛል:: እኔ እንደሆነ ብዙ ባለመማሬና ድሃ በመሆኔ ንግግር ኣላውቅም:: ኣሳቤን በቁርጥ ማቅረብ ይሳነኛል፡፡ ሆኖም ቀረም እዚህ
ያላችሁት ሁሉ አለመስረቄፀን ለማየት ባለመቻላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ስለዣን
ቫልዣ ትናገራላችሁ:: እኔ ይህ ሰው ማን እንደሆነ አላውቀውም፡፡ እኔ
እሠራ የነበረው ከመሴይ ባሉፕ ዘንድ ሲሆን ስሜ ሻምፕማቲዩ ይባላል፡፡ጎበዞች ብትሆኑ ኖሮ የት እንደተወለድኩ ትጠይቁኝ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ስለ ራሴ ብዙ አላውቅም:: እያንዳንዱ ሰው የተወለደበት አገር ወይም ቤት
ሊኖረው ይችል ይሆናል:: እኔ ግን የት እንደተወለድኩ እንኳን አላውቅም፡፡እናትና አባቴ ዘላኖች ስለነበሩ የሚኖሩት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ነበር፡፡
ስወለድ 'ማሙሽ እያሉ ነበር የሚጠሩኝ:: አሁን ደግሞ ሽማግሌው እየተባልኩ ነው የምጠራው:: አሁን ያሉኝ ስሞች የክርስትና ስሞች ናቸው::
አንተ ደግሞ እንደፈለግክ በላቸው:: ብቻ እመነኝ እኔ ሌላ ሰው አይደለሁም::
እኔ እባ ሻምፕማትዩ ነኝ:: የኖርኩትም አአሀገሪዩ ከመሴይ ባሉ ቤት ነው፡፡ እኔ አሁን የሰለቸኝ እናንተ የምትሉትን ታሪክ መስማት ነው:: ልክ እብድ ውሻ እንደሆንኩ ዓይነት ሰው ሁሉ እኔን የሚከታተልበት ምክንያት
አይገባኝም፡፡»

💫ይቀጥላል💫
👍139👏1
አትሮኖስ pinned «#ምንዱባን ፡ ፡ #ክፍል_አስራ_አራት ፡ ፡ #ትርጉም_ከዬሐንስ_ገፃዲቅ ....«ጌታዬ ይቀመጡ» አለው የጠባቂዎች ኃላፊ:: ሰውዬው እንዲሄድለት ግድግዳውን ተደግፎ ቆመ፤ አላበው፧ መተንፈስ አቃተው፤ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፡ እንደገና ቁጭ አለ፡፡ የተቀመጠበት ቦታ ትንሽ ዞር ያለ ስለነበር ለሰው በግልፅ አይታይም ቁጭ እንዳለ አሳቡን የመለወጥ ዝንባሌ ታየበት:: “እስቲ አሁን ማን አስገድዶኝ ነው የመጣሁት»…»