አትሮኖስ
286K subscribers
120 photos
3 videos
41 files
573 links
╔╦╦╦═╦╗╔═╦═╦══╦═╗
║║║║╩╣╚╣═╣║║║║║╩╣
╚══╩═╩═╩═╩═╩╩╩
ግጥሞች አዳዲስና ቆየት ያሉ የታዋቂ ደራሲያን መፅሐፍቶችን በ PDF እንዲሁንም
ያልተነበቡ ድርሰቶችን ግጥሞችን ታሪኮችን ያገኙበታል።


Contact. @atronosebot
please dont touch the leave button.😔😳😳
Download Telegram
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_አንድ


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

...“ቤተመንግሥት ገብተሻል አሁን ዐዲስ ወግ አምጫ እንግዲህ
አሏት፣ ምጸት በተቀላቀለው አነጋገር። ቀጠሉና፣ “አንቺ ብትሆኚ ኑሮ ምን ታረጊ ኑሯል? እስቲ በይ ንገሪኝ” አሏት።

“እኔማ እዚያ ማን አድርሶኝ ... ብቻ መላ ፈልግ ነበር።”

“መላ? ለነገሩ አንቺ መለኛ ነሽ።”

ፈገግ ብላ ዝም አለች።

“ምን አይተሽ የኔ እህት” ሲሉ ቀጠሉ። “አንዳንዶቹ ሲነግሡ
ሲሻቸው የገዛ ወንድሞቻቸውን እጅና እግር እየቆረጡ ነው እወህኒ
ሚሰዱ... እንዳይነግሡ” አሉና አፄ በካፋ ወንድማቸውን አቤቶ ዮሐንስን አንድ እጃቸውን ማስቆረጣቸውን ሊነግሯት ፈለጉና ለራሳቸው ወደ ፊት ትደርስበት የለ? ብለው ለእሷ፣ “ኣካሉ የጎደለ ደሞ መንገሥ አይችል” አሏት።

“ስለምን? አካሉ ቢጎልስ?”

“አካሉ ኸጎደለ እንዴት ብሎ ጦር ይመራል? እስቲ ንገሪኝ በይ?
ብቻ አሁን እሱን ተይውና ስንት የሞቱ ነገሥታት ዝርያዎች አሉ
መሰለሽ ኸተራራው... እወህኒ አምባ። ወህኒ አምባ ማለት ለጐንደር ቅርብ ናት... ኸማክሰኚት ብዙም አትርቅ። ብቻዋን የቆመች ተራራ ናት። አንድ በር ብቻ ነው ያላት። አናቷ ሜዳ፣ መውጫም መውረጃም የላት። ኸዛው ኻምባው ላይ የደንጊያ ቤቶችም አሉ።”

ወለተጊዮርጊስ የሰማችው ሁሉ እንግዳ ነገር ሆነባት። “ዛዲያ እንዴት ነው ሰዎቹ ከተራራው ሚወጡ ሚወርዱ?”

“በመጫኛ። ተራራይቱን ኻየሻት ዝንዥሮ ወይ ጦጣ መሆን ኣለብሽ
እዛ ላይ ለመውጣትም ሆነ ለመውረድ። ዙርያዋ ጥድ ነው። ምሽግም አላት አሉ። ብቻ እንዳው ንጉሥ ሞተ ኸተባለ ወይ ደሞ አንዱን እናንግሥ ያሉ እንደሁ፣ በቃ እግር ብረቱን ፈታተው ያኮበልሉታል።”

“ጠባቂም የለባቸው?”
“አሉዋቸው እንጂ! ያውም ንጉሡ ራሳቸው የመረጧቸው ወታደሮች
ናቸዋ ሚጠብቁ! ወታደሮቹ ዘብ ሚቆሙበት ቦታ ሁሉ አለ እኮ።

ወታደሮቹ ኸቀደሙ ነገሥታት ልገባች እንዳይመሳጠሩ፣ ለንጉሡ
መሐላ ገብተው ነው ሚጠብቁ። ኸዛ ቦታ ያለ ንጉሡ ፈቃድ ማንም
ሊገባ ወይም ሊወጣ አይችልም። ግና ለዘበኞቹ ጉርሻ ይሰጧቸዋል።
ለጉርሻ ማይተኛ ስንት አለ? የሰው ልዥ እኮ ተላላ ነው፣ በቀላሉ
ይደለላል። ዛዲያ ለእንዲህ ያለው ክደት ቅጣቱ ሞት ነው። እንንገሥ
ባዮቹም አንዴ ኸተራራይቱ ኸወረዱ፣ ጭፍራ አስከትለው ጫካ ይገባሉ፣ ኸዚያ ነፍጥ ይዘው ገስግሰው ይመጣሉ። እልቂት ነው አልሁሽ ኸዝያ ወዲያ። አንዴ ያችን አልጋ ኸመዳፋቸው ኻረጉ ወዲያ ደሞ ሹም ሽር ያረጋሉ። ኸባላገሩ ርስት እህላሙን መሬት እየመረጡ ለሚፈልጉት በጉልት ይሰጣሉ፣ ሲፈልጉ ርስት ይተክላሉ፣ ገባርም ይሰጣሉ፣ ከብትም እንዲወስዱ ያረጋሉ። የጃንሆይ አባት አጤ አድያም ሰገድ ኢያሱ ሰላም አምጥተው እሳቸው ከሞቱ በኋላ፣ ረብሻ፣ ጦር ሰበቃ ሆነ።
የጭንቅ ዘመን ነበር።”

ዮልያና፣ ስመ መንግሥታቸው አድያም ሰገድ የሆነው ቀዳማዊ ኢያሱ ከሞቱ በኋላ፣ የነገሡ ነገሥታት ተክለሃይማኖት፣ ቴዎፍሎስ፣ ዮስጦስና ሣልሳዊ ዳዊት፣ እያንዳንዳቸው ለአጭር ጊዜ እየገዙ ሃገሪቱ ሰላም
አጥታ ስትታመስ፣ በሃይማኖት ክርክርና ንትርክ ስትብረከረክ ብሎም በእልቂት ስትንጠራወዝ እንደነበረች በዝርዝር ሊነግሯት ፈልገው፣ ፊቷ ላይ በግልፅ የሚታየውን የመሸበር ስሜት አስተውለው ዝም አሉ።

ወለተጊዮርጊስ የሰማችው ነገር ሁሉ ከበዳት። ቤተመንግሥት
መግባት አስፈሪ ነገር ሆነባት። ፋሲል ቤተመንግሥት ቅጥር ግቢ
ስትገባ ያየችው ግርማ ሞገስ ሁሉ በውስጡ የማይመጥኑት አናሣ
ነገሮች ያቀፈ መሰላት።

“ማትቀመጪ? ቁመሽ ትዘልቂዋለሽ?” አሏት።

“እሚታዬ ለመሆኑ ሰዎቹ ምን እየበሉ ይኖራሉ፣ኸተራራ
ተቀምጠው?”

“ንጉሡ እኮ ቀለብ ይሰጣል። ውሃም ቢሆን ኸታች ምንጭ አለ::
እነሱም ኸዛው ይዋለዳሉ። ትምርት ይማራሉ፤ ቤተክሲያንም..
ጊዮርጊስና ማርያምም እኮ አሉ ኸዛው።”

“ሚገርም ነው። ስለዝኸ ስታወሪ ሰምቸሽም አላውቅ።”

ትናንት ፋሲለደስ ቤተመንግሥት ግቢ ስትገባ የነበራት የመደነቅ
ስሜት ኹሉ ጠፍቶባት ጭንቀት ያዛት። ለራሷ እኼ ቤተመንግሥት
ሚባል ነገር አስፈሪ ነው አለችና ወደ አልጋው ጫፍ አመራች።

ልብሶቹን በጥንቃቄ ወደ ኋላ ገፋ አድርጋ ተቀመጠች።

“ጌጦቹን አልጋው ላይ አኑሪያቸው” ብለው በቀኝ እጃቸው ኣልጋውን መታ አደረጉት።

“ልብሶቹን ደሞ እመንጠቆዎቹ ላይ ስቀያቸው” አሏት፣ ግድግዳ ላይ የተተከሉትን ከቀንድ የተሰሩ የልብስ መስቀያዎች
በእጃቸው እየጠቆሟት።
ጌጦቹን አልጋው ላይ ትታ ሄዳ ልብሶቹን አንድ በአንድ
ሰቀለቻቸውና ጫማዎቹን መሬት ላይ አስቀምጣ ተመልሳ አልጋው
ጫፍ ላይ ተቀመጠች።

“ምን እያልሽኝ ነበር? አዎ 'ስለዝህ ስታወሪ ሰምቸሽም አላውቅ
ነው ያልሽኝ” አለና፣ “ፊት ብታቂ ኑሮ ምን ይጠቅምሽ ኑሯል?
የዠመርሁትን ልጨርስልሽ እንጂ። ጃንሆይ እንዳልሁሽ በንጉሥ
ዮስጦስ ግዝየ ኸወህኒ አምባ ሲያመልጡ እኝሁ ዮስጦስ መልሰው አሰሯቸው። ያለቤታቸው ገብተው።”

“ያለቤታቸው ገብተው?”

“ዮስጦስ ማለት ልደታ ማርያምን እዝሁ እጐንደር የተከሉት
ያጤ ቴዎፍሎስ እንደራሴ ነበሩ እንጂ የነጋሢ ዘር የላቸውም። ኋላ
ጃንሆይ ደሞ ሲነግሡ ወህኒ አምባ ያሉ የነጋሢ ዝርያዎች ሁሉ የገዛ ወንድሞቻቸው ሳይቀሩ ተንጫጩ።”
“ምን ይሁን ብለው?”
“ሚነግሠውን እኛ እንመርጣለን፤ በካፋ ኃይለኛና ጨካኝ ነው
ብለው። ያው አልቀረም መሲሕ ሰገድ ተብለው ነገሡ። ይነግሣሉ ሚል ንግርትም ነበር። ጃንሆይ ወህኒ ሳሉ በሳቸው ልክ ጧሚና ጠሎተኛ አልነበረም ነው ሚሉ።

ምጥዋትም መስደድ ያዘወትሩ፣ መጻሕፍቱንም ያገላብጡ ነበር። ቅኔ አዋቂም ናቸው። ኸዛው እናታቸው አገር... ዲማ ነው ቅኔውን የተማሩ። ደሞ ምን የመሰለ ታንኳም አሠርተዋል እኮ።
ግብጦች ናቸው አሉ የሠሩላቸው። ኸጣና ነው ያለ...”

ድንገት ደንገጡሮቹ ሲገቡ ዝም አሉ። ሴቶቹ ወለተጊዮርጊስን
አልብሰው፣ አስጊጠውና እላይዋ ላይ ሽቱ አርከፍክፈው ግብር መታደሚያ ሰዐት ሲደርስ እንደሚመለሱና ግብር እንደ ንጉሠ ነገሥቱ ፍላጎትና
እንደ ሁኔታው የተለያየ አዳራሽ ውስጥ እንደሚደረግና ለዛሬ ግን ባለ ሁለት ደርቡ ወርቅ ሰቀላ ምድር ቤት አዳራሽ ውስጥ እንደሚሆን ነግረዋቸው ወጡ።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

“ምንትዋብ ብያታለሁ።”

ወርቅ ሰቀላ ጥቁር እንግዳ ለመቀበል ዝግጁ ሆኗል። የእልፍኝ
አስከልካዩ በሥሩ ያሉትን እንደየደረጃቸው ነጠላ ያደገደጉትን፣ ወይም ካባ የደረቡትን ዐራቱን ጭፍሮቹን አሰማርቷል። ጠርዙ ባለወርቅ ቅብ
የሆነው የንጉሠ ነገሥቱ መንበረ መንግሥት የለበሰው የፋርስ ባለቀይ፣ባለሰማያዊና ባለነጭ ምንጣፍ በትክክል መነጠፉን፣ ከጎኑ ያለው ጠርዙ የወርቅ ቅብ የሆነው ድንክ አልጋ ዝግጁ መሆኑንና ከአልጋዎቹ ሥር
የተነጠፈው ቀይ የፋርስ ስጋጃ ላይ የሐር ምንጣፍ በትክክል መነጠፉን አረጋግጧል።

ከንጉሡ መንበር በስተጀርባ ያለውን ግድግዳ በቀይና በልዩ ልዩ
ቀለማት ያጌጠ ከቱርክ የመጣ ምንጣፍ ሸፍኖታል። ድንክ አልጋዎቹ የተቀመጡበትን አካባቢ ከሐር የተሠራ ነጭ አጎበር ከላይ ከልሎታል።አናቱ ላይ የዘውድ ቅርጽ ያለው ጉልላት ተቀምጦለታል። ንጉሠ
ነገሥቱ ሆኑ አብረዋቸው የሚቀመጡት እንግዶች እስኪገቡ አጎበሩ በግራና በቀኝ ያሉ እንጨቶች ላይ በቀጭን ሐር ሻሽ ታስሯል።ሲያስፈልግ የሚጋርዱትና የሚገልጡት ሁለት የቤተመንግሥት ባለሟሎች አደግድገው ግራና ቀኙን ቆመዋል። በአዳራሹ ግራና ቀኝ
ያሉ መስኮቶች የሐር መጋረጃ ተጋርደውባቸዋል።
👍181
ከንጉሠ ነገሥቱ በስተግራ መጋረጃ ውስጥ የሚመገቡት መሣፍንቱ፣ራሶቹና የቤተመንግሥቱን መማክርት የሚይዙት፡ የቤተመንግሥቱ
ዋነኛ አባላት የሆኑት ዐቃቤ ሰዐቱ፣ ጸሐፌ ትዕዛዙ፣ አፈ ንጉሡ፣ አዞዦች (ሕግ አዋቂዎቹና ፈራጅ ሊቃውንቱ)፣ የቤተክህነት አባላቱ፡ ከቡኑ ዕጨጌው፣ ሊቀ ካህናቱ እንዲሁም የየግዛቶቹ አስተዳዳሪ መኳንንት የጦር አበጋዞቹና ሊጋባው እንደ ቅደም ተከተላቸው ተርታውን መቀመጫዎች ተዘጋጅተውላቸው ግቡ እስኪባሉ ድረስ ሌላ ክፍል ውስጥ መከዳ ላይ ተቀምጠው ሲጠብቁ ቆይተው ገብተው ተቀምጠዋል።
እግራቸው ሥር እንደየማዕረጋቸው ብርሌዎችና ዋንጫዎች ተደርድረውላቸዋል ።

ከንጉሠ ነገሥቱ በስተቀኝ የሚቀመጡት ቢትወደዱ፣ ብላቴን ጌታው ፊታውራሪዎቹ፣ ከንቲባው፣ ካባ መልበስ የተፈቀደላቸው መኳንንት
በፈርጥና በልዩ ልዩ ጌጦች የተዋበውን ካባቸውን ደርበው፣ ወገባቸው
ላይ ከሐር የተሸመነ መቀነት ታጥቀው፣ ቆዳ ጫማ ተጫምተው
ጎምለል፣ ከብለል፣ ጀነን፣ ቀብረር፤ ድክ ድክ እያሉ፣ ወይዛዝርት ቁንን፣
ኮራ እያሉና አረማመዳቸውን እየመጠኑ መደዳውን እንደየማዕረጋቸው
በተሰናዱት መናብርት ላይ ገብተው ተሰትረዋል።
እግራቸው ሥር እንደየክብራቸው ለአረቄ ዋንጫ፣ ለጠጅ ብርሌ
ተቀምጦላቸዋል።

ቀኛዝማች፣ ግራዝማች፣ ባላምባራስና ባሻ ያሉት በማዕረግ ዝቅ ያሉት ደግሞ እንደየደረጃቸው የተዘጋጀላቸው መቀመጫ ላይ ቦታቸውን ከያዙ በኋላ፣ ሊቃውንትና ካህናት ገብተው እንደየክብራቸው ተሰይመዋል።

በመጨረሻም የውጭ አጋፋሪው አዳራሹ መሃል ቆሞ ከበር ላይ
የላካቸው እንግዶች እንደየክብራቸውና ማዕረጋቸው መቀመጣቸውንና መግባት የሌለበት እንግዳ አለመግባቱን ለማረጋገጥ ዐይኑን ከወዲያ
ወዲህ አዘዋወረ። ሁሉ ትክክል ሲመስለው የመኳንንቱ መጠጫ
ዋንጫዎች እንደዚሁ እንደየማዕረጋቸው መቅረባቸውንና ስሕተት አለመኖሩን ዞር ዞር ብሎ ተመለከተ።

ሁሉ በአግባቡ ነው።

ለማዕረጉ የማይመጥነው ቦታ ላይ በስሕተት እንዲቀመጥ የተደረገ፣
ወይንም ለማዕረጉ የሚገባ ዋንጫ ያልቀረበለት መኰንን ማኩረፍ ብቻ ሳይሆን ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ሊጋጭ የሚችልበት ጉዳይ በመሆኑ የእልፍኝ አስከልካዩ ልዩ ጥንቃቄ ያደርጋል።

ዝቅተኛ ማዕረግ-በማዕረግ ያለው መኰንን ለክብሩ የማይገባ ገበታ
ላይ በስሕተት ከፍ ብሎ እንዲቀመጥ ከተደረገ ማዕረግ-
በማዕረግ የሚበልጡት መኳንንት “ክብሬ ተነካ” ብለው ኣካኪ ዘራፍ በማለታቸው፣ እልፍኝ አስከልካዩ ሁሉም በደንቡ መሠረት መደረጉን ማረጋገጥ አለበት።

ማንኛውም ዓይነት ግድፈት ሆነ ተብሎ የተደረገ ሊመስል ስለሚችል መኳንንቱን ቂም ማስያዝና ማስኮረፍ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ አሰላለፍንና
የኃይል ሚዛንን የሚያዛባ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የሚያጋጭና እሳቸውንም ቢሆን የሚያስቆጣ በመሆኑ በቀላሉ የሚወሰድ ጉዳይ አይሆንም። ከዛም
አልፎ እልፍኝ አስከልካዩ እሱንም ሆነ ጭፍሮቹን የሚያስቀጣ ብሎም ከሥራ የሚያስባርር ጉዳይ ስለሚሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ወስዷል።

ንጉሠ ነገሥቱ ማዕድ እንደቀረበ ተነግሯቸዋል። እንግዶቹ
ከተቀመጡበት ተነሥተው በንቃት ይጠባበቃሉ።

አፄ በካፋ በወርቅና የተለያየ ቀለም ባሏቸው ልዩ ልዩ የከበሩ
ድንጋዮች ያጌጠውን ዘውዳቸውን በሐር ሻሽ የተሸፈነ ሹሩባቸው ላይ
ጭነው፣ ፊታቸው ከዐይናቸው በስተቀር በሐር ጨርቅ ተሸፍኖ፣ ከወርቅ የተሠራ በትረ መንግሥታቸውን በቀኝ እጃቸው ጨብጠው፣ ጠርዙ በሐር ክር የተጠለፈ ነጭ ተነፋነፍ ሱሪያቸው ላይ ነጠላ አጣፍተው፣
በነጠላው ላይ በወርቅና በልዩ ልዩ ጌጦች ያሸበረቀውን ካባቸውን
ደርበው፣ አንገታቸው ላይ ወፍራም የወርቅ ሀብል ከትልቅ የወርቅ
መስቀል ጋር አድርገው፣ ከቆዳ የተሠራ ጫማ ተጫምተውና ንጉሣዊ ግርማ ተጎናፅፈውና ታጅበው ሲገቡ እንግዶቹ ለጥ ብለው እጅ ነሷቸው።

በተመጠነ እርምጃ እየተራመዱ መንበረ መንግሥታቸው ላይ
ሲቀመጡ መሣፍንቱና ራስ አጃቢዎቻቸው ቦታቸውን ያዙ ::
እሳቸው ግን ትንፋሻቸውን ውጠው ዐይናቸውን የአዳራሹ
ላይ ተክለው የሚጠባበቁት የወለተጊዮርጊስን መምጣት ነው። የመምጣቷ ዜና በመላ ጐንደር አስተጋብቶ ኖሮ እንግዶቹም ዐይናቸውን አዴራሹ መግቢያ ላይ ሰክተው ሲጠባበቁ ወለተጊዮርጊስ ብቅ ስትል፣ የአፄ ባካፊ ዐይን ሲርገበገብ፣ አዳራሹ በሁካታ ተናወጠ።

“ኸቋራ ነው አሉ የመጣች።”
“በተክልየ ኸቋራ? ስንት አጥንተ ጥሩ የጐንደር ወይዛዝርት እያለን
“ያጤ ሚናስ ነገድ ናት አሉ።”
“ደመ ግቡ ናት!”
“አብረዋት ያሉት እሚታዋ ወይዘሮ ዮልያና ናቸው።”
ጫጫታው ጋብ አልል በማለቱ፣ እልፍኝ አስከልካዩ አዳራሽ ውስጥ
ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት አለበትና ዐይኑን ከወዲያ ወዲህ ሲያማትር አዳራሹ ባንድ ጊዜ እረጭ አለ።

ወለተጊዮርጊስ ያንን ያህል ሕዝብ አንድ ቦታ ተሰብስቦ አይታ
ባለማወቋ ተደናገጠች። ልቧ ድቅ ድቅ ሲልባት፣ እጆቿ ላብ ሲያርሳቸው ጉንጮቿ በጥፊ እንደተመቱ ሲግሉ፣ እግሮቿ ተሳሰሩ። እንደምንም አንገቷን ሰበር ደረቷን ቀና አድርጋ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ አመራች።

እንግዶቹ ትንግርት ያዩ ያህል ቀልባቸው እሷ ላይ ሲያድር፣ አያቷ
እንዳሉት ወይዛዝርቱ ዐይናቸው ደፈረሰ። እሷ ይህን ሁሉ ማስተዋያ ልብም፣ ጊዜም የላት። ማድረግ ያለባት ሰዐቱና ሁኔታው የሚጠይቀውን ብቻ በመሆኑ፣ ቀጥ ብላ ሄዳ ወገቧ የሚሰበር እስኪመስል አጎንብሳ፣
ንጉሠ ነገሥቱን እጅ ነሳች። እግራቸውን ልትስም ስታጎነብስ አገጫን በእጃቸው ቀና አደረጉት።

በአድናቆትና በደስታ ብዛት እጃቸው ተንቀጠቀጠ። እንደምንም ብለው፣ “እንከንም የለሽ” አሏት። መቀጠል ፈልገው ግን ቃል አጠራቸው።

ብርታታቸውን አከማቹና፣ “ምንተ ምንውህብ?” አለ፣ በግዕዝ። ምን
እንስጥ? - መልከ መልካም ቆንጆ ናት እንደማለት። በመጨረሻም፣
ምንትዋብ ብያታለሁ” ብለው በቀኛቸው ያለው ድንክ አልጋ ላይ
እንድትቀመጥ አደረጓት። እሷን ተከትለው የገቡት አያቷ፣ በካፋን
ለጥ ብለው እጅ ነስተው በእልፍኝ አስከልካዩ መሪነት ከንጉሣውያን
ቤተሰቦች ጋር የተዘጋጀላቸው ቦታ ሄደው ተቀመጡ።.....

ይቀጥላል
👍11
#ያልታበሱ_እንባዎች


#ክፍል_ሀያ_ስምንት


#ድርሰት_በአሰፋ_በቀለ_ገየሱስ

....ስድስት ወር ተብሎ የሄደው አስቻለው እንኳን መመለስ ድምፁ እንኳ ሳይሰማ ድፍን ሰባቶ ወረሰ አልፈዋል። ይህ ሁኔታ በዲላ የፍቅር ቤተሰቦቹ ላይ ስጋትና
ጭንቀት ፈጥሮ ያተረማምሳቸው ይዟል ከሁሉም በላይ ደግሞ ሔዋንን።
አስቻለው ወደ አስመራ ሲሄድ ለዲላ የፍቅር ቤተሰቦቹ የገባው ቃል ነበር ቶሎ ቶሎ ደብዳቤ ሊፅፍ ሁኔታዎች በፈቀዱለት መጠን ስልክም ሊደውል ለነገሩ አንዲት ደብዳቤ ፅፏል።ያቺም ብትሆን ገና አስመራ በገባ ሦስተኛ ቀን ላይ ድንገት ወደ አዲስ አበባ የሚመለስ ሰው አግኝቶ ኖሮ ደህና መድረሱን የገለፀበት እንጂ
ዝርዝር የናፍቆት ሀሳብና የተሟላ አድራሻውን የያዘች አልነበረችም። በዚያች ደብዳቤ ላይ የጠለፀው ነገር ቢኖር ወደፊት ቋሚ አድራሻውን ሲያውቅ ሌላ ደብዳቤ እንደሚፅፍና ምናልባት ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ በአውሮፕላን ላይ በነበረበት ወቅት ከሔዋን በመለየቱ ምክንያት ሆዱ ባብቶ በናፍቆት ስሜት ውስጥ ሆኖ የቋጠራቸው እንደሆኑ የሚገመቱ ጥቂት የግጥም ስንኞችን ብቻ ነበር።ያቺ ደብዳቤ ዲላ የደረሰችውም ስትጣጣል ሰንብታ ከተጻፈች ከአንድ ወር በኋላ ነበር፡፡
በቃ ሌላ የለም።
ሔዋን በልቧ ከአንድ ድምዳሜ ላይ ደርሳለች፤ እስቻለው ደህና ባይሆን ነው። ከሚል። የአስቻለውን ደህና አለመሆን ባሰበች ቁጥር ሁለት ነገሮች በሁለት ቦይ እየፈሰሱ በሀሳብ ይወስዷታል። በአንድ በኩል የአስቻለው ደህና አለመሆን
ፍቅሯን ሊያሳጣት ነው የዕድሜ ልክ የመንፈስ ስብራት፡፡ በሌላ በኩል ስለ እሷ "ብልግና" ሸዋዬ ለቤተሰቦቿ የጻፈችባትን ደብዳቤ ታስታውሳለች። ያ ደግሞ የቤተሰቦቿን በተለይም የእናቷን ሆድ እንዳሻከረባት ትገምታለች፡፡ ይህን ሁኔታ ማስቀየር ያስችላል ብላ የምትገምተው የአስቻለውን መልካም ሰውነት ነበር፡፡
እናትና አባቷ አንድ ቀን አስቻለውን ሲያውቁትና መልካም ሰውነቱን ሲረዱት ምርጫዋ ትክክል እንደሆነ በመረዳት የሻከረ ሆዳቸው ይሽርልኛል ብላ ትጓጓ ነበር፡፡አስቻለው ደህና ካልሆነና ምናልባትም ያልተመለሰ እንደሆነ ግን ከሁለት ዛፍ የወደቀች ልትሆን ነው። ጭንቅና ፍርሀቷም ከዚሁ ስጋት ይመነጫል።
ታፈሡ፣ በልሁና መርዕድ የሔዋንን ጭንቀት በብዙ መንገድ ይጋሩታል።
የአስቻለው ደብዳቤ አለመጻፍ፣ ስልክ አለመደወልና የመምጫው ጊዜም በአንድ ወር የዘመኑን እውነታዎች በራሳቸው መንገድ እየተረጎሙ ራሳቸውንም ሆነ ሔዋንን ማፅናናት አልቦዘኑም፡፡ ወትሮም እንደሚያደርጉት ሁሉ ጫት በመቃም ሰበብ ቀደም ሲል በልሁ፤ አሁን ደግሞ ሔዋንና ትርፌ በሚኖሩበት ቤት እየተሰበሰቡ መዋልና ማምሸታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዚያው ሂደት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ደጋግመው ይነጋገራሉ፡፡ የአስቻለውን ደብዳቤ አለመጻፍ ጉዳይ ያነሱና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ለማገናዘብ ይሞክራሉ። በዚያን ወቅት መንግስት በፖስታ ቅብብሎሽ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርግ ነበር። ተቃዋሚዎች ከደጋፊዎቻቸው ጋር ምስጢር
ይለዋወጣሉ በሚል ስጋት በተለይ የተጠርጣሪ ሰዎችን ፖስታ እየቀደዱ መንገድ ላይ ያስቀሩ እንደነበር በሰፊው ይታወቃል። በተለይ ከኤርትራ ወደ ሌሎች
የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚላኩ ደብዳቤዎች ለተላከሳቸው ሰዎች የመድረሳቸው ዕድል
አስተማማኝ አልነበረም፡፡ ምናልባት አስቻለውም የሚጽፈው ደብዳቤ መንገድ ላይ ተቀዶ እየቀረ ይሆናል። እሱ ደግሞ የተከፋ ብሶተኛ ነውና ይህንኑ ስሜት በደብዳቤው ላይ አስፍሮ ከተገኘ የባሰ ይጠረጠርና ሁለተኛውም ሦስተኛም ደብዳቤዎቹ የዚሁ ሰለባ እየሆኑ ቀርተው ሊሆን ይችላል በማለት
ግምትና ጥርጣሪዎቹን ይገልፃሉ። ስልክ ያለመደወሉንም ጉዳይ ከዚሁ ከወቅቱ እውነታ ለይተው
አያዩትም።በወቅቱ ከአዲስ አበባም ሆነ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች አስመራን በሽቦ የሚያገናኝ ስልክ አልነበረም፣ በዓመታት ጦርነት ተበጣጥሰው
አልቀዋልና። አማራጭ የመገናኛ መንገዶች ራዲዮና ቴሌ ግራም አሊያም ገመድ አልባ ማይክሮ ዌቭ ስልክ ናቸው። ራዲዮና ቴሌ ግራም ደግሞ ለአብዛኛው ሰው እንደ ልብ አይገኙም፡፡ የማይክሮ ዌብ ስልክም ገና በጅምር የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ነው
ከሚሰራበት ጊዜ የማይሰራበት ጊዜ ይበልጣል። በሚሰራበትም ወቅት ወረፋው አስልቺ ነው፡፡ የእነታፈሡ ግምት ታዲያ አስቻለው በዚህም ቢል በዚያ አልሆንለት እያለ ተቸግሮ ነው›› በሚል ሀሳብ ይደመድማል። የአስቻለው የመመለሻ ጊዜ ማለፉንም ካነሱ ምናልባት የአይሮፕላን ጉዞ ወረፋ አልደርስ ብሎት ይሆናል ከሚል ግምት አያልፍም፡፡
ይህ ሁሉ ምክንያታዊ ትንተና ግን ለሔዋን አይገባትም ትሰማቸዋለች እንጂ አታዳምጣቸውም፡፡ ለእሷ አንድ ነገር ብቻ ግልፅ ነው፤ በቃ አስቻለው አልመጣም ድምፁም አልተሰማም ምክንያቱ ደግሞ ደህና አለመሆኑ ነው። የሚያስጨንቃት የእሱ ደህና አለመሆንና ምናልባትም ያልመጣ እንደሆነ የሚፈጠርባት የመንፈስ ቁስል ነው። የዚህ ሁሉ አጠቃላይ ውጤት ታዲያ ራሷ ተጨንቃ እነታፈሡንም ማስጨነቋ ነው።
ሁኔታዋ ሁሉ ያሳዝናቸው ይዟል።
በልሁ ታዲያ ይህንን ችግር አንድ ቀንም ቢሆን የቀረፈ መስሎት ነው በሙዚቃ ዘና ትልለት ዘንድ የመግቢያ ትኬት መግዛቱ።
በልሁ ትኬቶቹን ይዞ በቀጥታ ያመራው ቀድሞ የእሱ፣ ዛሬ ደግሞ የሔዋንና የትርፌ መኖሪያ ወደ ሆነው ቤት አቅጣጫ ነበር። ነገር ግን ከአንደኛ መንገድ ብዙም ሳይርቅ መርዕድ ከታች በኩል አስፋልቱን ይዞ ወደ ላይ ለመጣው አገኘውና «ትኬት ገዝተሃል?» ሲል በቅድሚያ ጠየቀው፡፡ የምን ትኬት?» አለ መርዕድ በርገግ ብሎ።
«ዛሬ እኮ የፖሊስ ኦርኬስትራ መጥቷል»
ባክህ ተው ለአንድ ቀን ምሽት እሥር ብር ከማወጣ በቋሚነት የምስማው አንድ ካሴት ብገዛ አይሻልም?» አለው።
«እስቲ በልጅ እግርህ ወደነ ሔዋን ልላክህ!»
«ለምን?»
በልሁ ቲኬቶቹን ከኪሱ አውጥቶ እያሳየው «ሔዋንና ትርፌ ዛሬ እንኳ ይዝናኑ ብዬ ትኬት ገዝቼላቸዋለሁ:: ስጣቸውና ስዓቱ ሲደርስ አዳራሹ ድረስ
እንዲመጡ ንገራቸው:: እነሱን አስገብተን እኛ ወደየጉዳያችን እንሄዳለን» አለው።መርዕድ አላቅማማም፣ ቲኬቶቹን ተቀበለውና ሲመለስ የት እንደሚገናኙ ቀጠሮ ይዘው ወደ ሔዋንና ትርፌ ቤት ገሰገሰ፡፡
የሙዚቃ ድግሱ ማስታወቂያ በድምጽ ማጉያ ይነገር በነበረበት ወቅት ብዙዎች ያለ መታደም
አዝማሚያ የሚያመለክት አስተያየት ይሰጡ የነበረ ቢሆንም
በወቅቱ እስከ ሰላሳ ሺህ ህዝብ የሚኖርባት ዲላ ከተማ ውስጥ ከእንድ ሺ በላይ የማይዘውን የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚሞላ የሙዚቃ አፍቃሪ አልጠፋም፡፡ሰዓቱ ደርሶ ሔዋንን እና ትርፌን በቀጠሩበት ቦታ አግኝተዋቸው ወደ አዳራሹ ይዘዋቸው በመግባት ቦታ ሊያሲዟቸው ቢሞክሩም እነሱ
ቲኬት ስላልያዙ ወደ አዳራሹ ለመግባት ተከለከሉ።በዚያ ምትክ ትዕይንቱ፡ እንዳይርቃቸው ወደፊት ሄደው መቀመጥ እንዳለባቸው
መከሯቸውና እነሱ ወደ ውጭ ተመለሱ።
ሔዋን እና ትርፌ ግን አገባቡ ጭንቅ አላቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ዝግጅትና አዳራሽ ውስጥ ታዳሚ ሁነው አያውቁም፡፡ የዝግጅቱ ተካፋይ ለመሆን የጓጉ ቢሆንም
ሌላ ሰው እንደሚያደርገው ቦታ መርጠው ለመቀመጥ ድፍረቱን አጡ። እንዲያውም
👍10
ድብልቅልቋ አስፈራራቸው፡፡ አዳራሹ ውስጥ ገብተው በመተላለፈያው ኮሪደር ላይ
እንደ ቆሙ በርካታ ሰዎች ከኋላቸው እየመጡ አልፏቸው ቦታ ሲይዝ ተመለከቱ።እንደ ምንም ጨከኑና በአዳራሹ መሀል አካባቢ ከቆሙበት የመተላላፊያ ኮሪደር
በስተቀኝ በኩል በርካታ ባዶ ወንበሮች መኖራቸውን በማየታቸው ወደዚያው ለማለፍ
ወሰኑ፡፡ ሔዋን ፊት እየመራች ትርፌ ከኋላ እየተከተለች በሰው እግር ስር እየተሽለኮለኩ በሚያልፉብት ወቅት ሔዋን ድንገት ተወላከፈች፡፡
«ውይ ይቅርታ!» ብላ ወደ ተወላከፈችበት ሰው ቀና ብላ ስትመለከት ክው ብላ ደነገጠች። ያወላከፋት ሰው ከአሁን በፊት የምታውቀው ነው፣ በድሉ አሸናፊ፡፡
«አይተሸ አትራመጅም እንዴ?» አላት በድሉ እንደ መንሽ የገጠጡ
ጥርሶቹን ገለጥ አድርጎ በሀፍረት ፈገግታ ዓይነት እያያት፡፡
ሔዋን ግን ስትራመድ በነበረችበት ወቅት ታደርግ የነበረውን ጥንቃቄ
አስታውሳ ያ ሰው ሆን ብሎ እንዳወላከፋት ገብቷት እየተናዷደች ዝም ብላው ወደ
ባዶዎቹ ወንበሮች አለፈች። ከትርፌ ጋር ፈንጠር ብለው ለብቻቸው ተቀመጡና እንደ ማንኛውም ሰው የሙዚቃውን መጀመር ይጠባበቁ ጀመር፡፡
ዝግጅቱ ደግሞ በጣም ተጓተተ። ለአስራ ሁለት ሠዓት ጥሪ የተደረገ
ቢሆንም ነገር ግን ከአንድ ሠዓትም አለፈ፡፡ በዚያው መጠን ታዳሚው ጀምሩ በሚል የድምጽ ጥሪ ያፏጫል። አንዳንዴም ያጨበጭባል፡፡ አልፎ አልፎም
ያጉረመርማል፡፡ በዚህ መሀል ሔዋን ከአንዴም ሁለት ጊዜ ወደ በድሉ አሸናፊ ገልመጥ ባለችበት ወቅት እሱም አከታትሉ እንደሚያያት ተገንዝባለች።
ልክ ከምሽቱ አንድ ሠዓት ተኩል ሲሆን በመድረኩ ላይ ለየት ያለ ነገር መታየት ጀመረ፡፡ መጋረጃ ሙሉ በሙሉ ተገለጠ፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ከነመሳሪያዎቻቸው ለተመልካች ዓይን ገጭ አሉ::
ተጨበጨበላቸው፡፡
ወዲያው ከወደ ጀርባ በኩል አንድ ቀላ ረዘም ያለ ልጅ እግር ሰው ብቅ አለና በቋሚ ብረት ላይ ተሰክቶ የነበረ የድምጽ ማጉያ ነቅሉ ያዘና እጅ ነሳ።
ለእሱም ተጨበጨበለት።

«አመሰግናለሁ» እለና ቀልድ ቢጤ ጣል አርጎ ቀጣይ የሙዚቃ
ዓይነቶችንና ዘፋኞችን አስተዋወቁ
ምስጋናውን ተቀብሎ ወደ ጀርባ ክፍል ገባ ያን ተከትሎ ሦስት ሙዚቃዎች በተከታታይና ተሰሙ።
ያ አስተዋዋቂ እንደገና ብቅ አለ፡፡ ድምጽ ማጉያውን ይዞ "እጅ ያንሳል እጅ ያንሳል አለ።
ተጨበጨበለት።
«እስቲ እንደገና»
አሁንም አጨበጨቡለት::
የዚቃ ድግስ ገና ያልተነካ መሆኑን አበሰረና አሁንም ሦስት መዚቃ
እንደሚቀርቡ አስታዋውቆ ተመለሰ። ወዲያው አንድ ጠየም ስልከክ፡ ያለ ድምጻዊ ብቅ አለና የድምጽ ማጉያውን ከተሰቀለበት ቋሚ ብረት ላይ አነሳ፡፡ ሙዚቀኞች አስቀድመው መሳርያቸውን መጫወት ጀምረዋል። ድምጻዊው ማዚም" ጀመረ፡፡

«እስታወሽኝ፣ እስታውሽኝ
አስታወሽኝ አስታውሽኝ
ያለ አንቺ ማን አለኝ።»

ብሎ ገና የዘፈኑን አዝማች ግጥሞች ሲጀምር ሔዋንን አንዳች የትዝታ ማዕበል ልቧን አናወጠው:: ከቁጥጥሯ ውጭ በሆነ ስሜት ትርፍዩ!» ብላ ከጭኗ
ላይ ወድቅ አለች፡፡ በዚያው ድፍት እንዳለች ሆዷ እስከሚቦጫቦጭ እስከሚርገፈገፍ ድረስ ስቅስቅ ብላ ታለቅስ ጀምር።
«ምነው እታለምዬ? ምነው? አለች ትርፌ ለራሷም ድንግጥ በማለት፡፡
ከጭኗም ላይ ልታነሳት ሞከረች፡ ሔዋን ግን በጄ አላለችም፡፡ ይልቁንም በትርፌ ጭን ላይ መሽጎጫ የምትፈልግ ይመስል የባሰ ትጣበቅባት ጀመር፡፡
የሔዋን ድንገተኛ የትዝታ ማዕበል የተነሳው አስቻለው ጽፎላት ከነበረ
ደብዳቤ ነው:: ከሰባት ወራት በፊት የጻፋት ብቸኛ ደብዳቤ ከሔዋን አዕምሮ ሊወጣ
የማይችል መልዕከት ይዛ ነበር። ደህና መድረሱንና ወደፊት ቋሚ አድራሻውን ሲያውቅ ሁሉንም ነገር እጠቃልሎ እንደሚገልጽላት ከጠቆመ በኋላ በስተ መጨረኣ
ሳይ የትዝታ ግጥሞችን ጣል አድርጎባት ነበር፡፡

«መች አሰብኩት ነበር መሄድ ከሲዳሞ፣
ከአንቺ ዓይን መራቁን መለየቱን ደሞ፣:
ወይ ዕድሌ ጠሞ ወይ ሰዎች ጨክነው፥
አወጡኝ ከመንገድ ዕቅዴን አምክነው::
ማስተዋልን ላጡ ይብላኝ ለእነሱ እንጂ፣
ለኔስ አንቺ አለሽኝ የልቤ ወዳጅ ፣
አንቺ የዘላለሜ የኔ ፍቅር መውደድ፣
ምንጊዜም አትርሺኝ አስታውሽኝ የኔ ሆድ፡፡"

ሔዋን ያቺን ደብዳቤ የፊት መስታወቷ አድርጋት ጠዋት ማታ ስታያት ቆይታለች። እስቻለው በዚያች ደብዳቤ ላይ ስጋና ደሙ ያለ እስኪመስላት ድረስ አምልካታለች:: እያባባቻትም ታስለቅሳት ነበር። ዛሬ ታዲያ ድምጻዊው በመረዋ ድምፁ በሚያሳዝን ዜማ አስታውሸኝ አስታውሺኝ ሲል በመስማቷ አስቻለው ትዝ ብሏት ነው የማልቀሷ ምከንያት፡፡

«ወደ ቤታችን እንሂድ'» አለቻት ትርፊ ግራ ሲገባት።
«እሺ ተነሽ አለችና እንባዋን እየጠረገች ፈጥና ቀና አለች።
ዝግጅቱን አቋርጠው መውጣት ይፈቀድ አይፈቀድ የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ ግን ጨክነው ተነሱ፡፡ ከአሁን አሁን ቁጭ በሉ አትነሱ የሚል ድምጽ የሚሰሙ እየመሰላቸው በመጨነቅ ርምጃቸውን ቀጠሉ፡፡ በአዳራሹ የቀኝ ግድግዳ ጥግ ካለው መተላላፊያ መንገድ ላይ ተከታትለው ወደ መውጪው በር አቀኑ፡፡ ብዙ በተራመዱ ቁጥር
ከልካይ እንዴለላ እየገባቸው ሄደና በመጠኑም ቢሆን ዘና አሉ፡፡
ከአዳራሹ ወጡና ቁልቁል ወደ ቤታቸው የሚወስደውን መንገድ ተያያዙት።
ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ ሆኗል፡፡ በርካታ ህዝብ ወደ አዳራሹ ስለ ገባ የከተማዋ
መንገዶች ጭር ብለዋል። ግራና ቀኝ መንገድ ዳር ባሉ ቡና ቤቶች
የቴፕ ጩኸትና የሰካራሞች ጫጫታ ጎልቶ በሚሰማበት ሁኔታ የሁላቱ ብቻ መንገድ ላይ መታየት እጅግ ያስፈራ ነበር። ሁለቱ ጆሮ ለጆሮ ገጥመው ግራና ቀኝ
ገልመጥ እያሉ ሲራመዱ ከቆዩ በኋላ ንብረትነቱ የዲላ ማዘጋጃ ቤት ከሆነው የህዝብ መድሀኒት ቤት አካባቢ ሲደርሱ ከኋላቸው አንዲት ቶዮታ መኪና መጣችና እነሱን አልፋ እንደ መሄድ ካለች በኃላ እንደገና ወደ ኋላዋ ትሽከረከር ጀመር ወደ እነሱ፡፡
ደግሞ በቀኝ በኩል ታጥፈው ዜሮ ሁለት ቀበሌ ውስጥ 'ግሪን ፓርክ' ተብሎ ከሚጠራው መዝናኛ በታች ወደሚገኘው ቤታቸው ሊያመሩ ሲሉ ሾፈሩ ከመኪናዋ ላይ ወርዶ ወደ እነሱ ሲራመድ አዩት፡፡ ደንገጥ ደንገጥ ብለው እያዩት ሳሉ ከአጠገባቸው ደረሰ።.....

💫ይቀጥላል💫
👍14
ሚካኤል ስለው ስሙን ስጠራ
የአምላኬ ብርሃን በእላዬ በራ
አዛኝ ነው በእውነት ፍፁም አዛኝ
የሚጠብቀኝ የሚያፅናናኝ

እንኳን አደረሳችሁ
👍2
#አልሄድሽም_ሄደሻል

መስኮት መጋረጃ የተከፈተ በር
የውሃ ብርጭቆ መሬት ላይ ሲሰበር
ባለ መቶ ብር ካርድ ሳይፋቅ የነበር
በሳንቲም ተፍቆ ስልኬ ሆድ ሲቀበር
ለማን ልደውል ነው? አንቺ እንደሁ ሄደሻል
ኦናዉ ቤታችንም ናፍቆት ሞልቶልሻል

አንቺ የለሽምና

ሂደቴ ተዛባ ሥርዓት ገደፈ
የእራታችን ሰዓት ሳላውቀው አለፈ
ቁርሳችን ቁር ሆነ ምሳም ተጣደፈ

አንቺ የለሽምና

ከሸሚዜ በፊት ጃኬቴን ለበስኩት
ሙዚቃውን ትቼ ዜናውን ዘፈንኩት
የእንዴት ነህ ?” ሰላምታ
የጦርነት አዋጅ መስሎ አስደነገጠኝ
ሳይቀድሙኝ ለመቅደም
ካ'ብሮ አደጎቼ ጋር መጣላት አማረኝ

መሄድሽን ማወቄ ግራ እንዲህ ካጋባኝ
ማወቅ አልፈልግም ዕውቀት ምን ሊረባኝ?

የለም የለም የለም አልሄድሽም ሄደሻል
በሻማሽ ብርሃን ቤትሽን አድምቀሻል
መሳብያው ውስጥ ሽቶሽ ደረቴ ላይ ሽታሽ
መኖሩን እያውኩ መኖሩን እያወቅሽ
አልሄድሽም ሄደሻል ግን ቶሎ ተመለሽ

🔘ሰለሞን ሳህለ🔘
9👍4
#የዜማ_ምትሐት

ፍቅርን በትዝታ - ፍቅርን በባቲ - ፍቅርን በአንቺ ሆዬ
ፍቅርን በአምባሰል -
ሳሽሞነሙንላት - ክራሬን ቃኝቼ - ጉሮሮየን ስየ ፤
ይመስገነው ድምፄ - ይመስገን ክራሬ
ይመስገን ውበቷ - ይመስገነው ፍቅሬ
ይመስገነው ዜማ - ይመስገን ሙዚቃ
ዜማዊ ውበቷን -
በዜማ ማርኬ - የእኔ አረኳት በቃ፡፡

?
👍3
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_ሁለት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ


....በመጨረሻም ምንትዋብ ብያታለሁ” ብለው በቀኛቸው ያለው ድንክ አልጋ ላይ
እንድትቀመጥ አደረጓት። እሷን ተከትለው የገቡት አያቷ፣ በካፋን
ለጥ ብለው እጅ ነስተው በእልፍኝ አስከልካዩ መሪነት ከንጉሣውያን
ቤተሰቦች ጋር የተዘጋጀላቸው ቦታ ሄደው ተቀመጡ።
ወዲያው ሙሉ ቤት አዛዥ እንጀራ አሳላፊውንና እንጀራ የያዙ
ተከታዮቹን፣ በወጥ ቤቱ መሪነት ሰታቴ ተሸክመው ወገባቸው
እየተንቀጠቀጠ የሚራመዱትን ሴቶችና ወንዶች፣ ወጥ ቤቶቹንና ወጥ ጨላፊዎቹን፣ የጠጅ መልከኛው የጠጅ ገንቦ፣ ብርሌዎችና ዋንጫዎች የያዙ ጠጅ ቀጅዎቹን፣ ጠላና አረቄ ቤቶቹ ጠላና አረቄ ቀጂዎቹን፣
ግምጃ ቀሚስ ያጠለቀው ሥጋ ቤት ሥጋ ተሸክሞ የተሳለ ቢላዋዎች ያቀፉትንና ዐዋዜና ድቁስ የያዙትን ተከታዮቹን እየመራ ሲገቡ እንግዶቹ ተነሥተው ቆሙ።

እልፍኝ አስከልካዩ ገበታ እንዲወርድ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ያደገደጉ የእልፍኝ አስከልካዩ ጭፍሮች ንጉሠነገሥቱ የተቀመጡበትን አካባቢ በነጩ መጋረጃ ጋረዱት። ባለ ሦስት ጭፍራው የአስታጣቢ
ሹም አሸርጦ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ላይ ውሃ እንዳይፈናጠቅ ክንዱ ላይ
አንጠልጥሎት የነበረውን ያማረ የእጅ መጥረጊያ ጨርቅ ጭናቸው ላይ አስቀመጠላቸው። ለብ ያለ ውሃ በወርቅ ቅብ ማንቆርቆሪያ አድርጎ፣ የወርቅ ቅብ ሳህን ላይ ሊያስታጥባቸው በርከክ ሲል መሣፍንቱ፣ መኳንንቱና ሌሎቹ እንግዶች እንደቆሙ ፊታቸውን ወደ ውጭ አዙረው በኩታቸው ሸፈኑት። አፄ በካፋ እጃቸውን ከታጠቡ በኋላ፣ አስታጣቢው
ትከሻው ላይ ጣል ያደረገውን እጅ መጥረጊያ ሰጣቸው። እጃቸውን
አድርቀው መልሰው ሲሰጡት ተቀብሎ ከቀኛቸው የተቀመጠችውን
ወለተጊዮርጊስን በርከክ ብሎ አስታጠባት።

ያደገደገ አጋፋሪ በግርዶሽ ተከልሎ፣ በቀኝ እጁ የተከበረውን የንጉሠ ነገሥቱን የወርቅ ዋንጫ፣ በግራ እጁ ፍንጃል ይዞ በሕዝቡ መሃልዐሰንጥቆ ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ሲደርስ፣ ግራ መዳፉ ላይ ወይን ጠጅ ጠብ አድርጎ ቀመሰና ዋንጫቸውን ሞላላቸው። ዋንጫውን ከእጁ ላይ
ወሰዱ።

ሙሉ ቤት አዛዥ የነጠላውን ጫፍ ከትከሻው ላይ አጠፍ አድርጎ፣
ቀደም ሲል በቀማሽ በኩል ያለፈውን፣ ወርቀ ዘቦ ቀሚስ ባጠለቀ መሶብ የተሰናዳውን እንጀራ ይዞ በቆሙት ታዳሚዎች መሃል፣ “እንጀራ ይስጣችሁ” እያለ አልፏቸው ሄዶ፣ በቀኝና በግራ ረድፎቹ መሃልና ንጉሡ ፊት ለፊት በወርቀ ዘቦ ተሸፍኖ የተቀመጠው የንጉሠ ነገሥቱ መመገቢያ ጠረጴዛ ላይ አኖረው። ዓይነታቸው ለቁጥር የሚያታክት፣ ዶሮ፣ ቀይ ስጋ፣ ምንቸታብሽ፣ አይብ፣ አልጫና ሌሎችም የወጥ
ዓይነቶች የያዙት አነስተኛ ሸክላ ድስቶች ጠረጴዛው ላይ ቀረቡ። አቡነ ክርስቶዶሉ ተነሥተው መስቀላቸውን ጨብጠው ቡራኬ ከሰጡ በኋላ፣ቆመው የነበሩት እንግዶች ተቀመጡ።

ያን ጊዜ ያሸረጠ አሳላፊ የንጉሠ ነገሥቱን መሶብ ልብስና ክዳን
አንስቶ ከኋላው ለቆመ አስተናጋጅ ሰጠው። ከመሶቡ ጥግ እንጀራ
ቆረስ አድርጎ ግራ እጁ ጀርባ ላይ አስቀመጠ። ወጥ አውጭው ከየድስቱ ውስጥ በትንሹ ጨለፍ እያደረገ እንጀራው ላይ ሲያፈስለት፣ አሳላፊው
እጁ ከንፈሩን እንዳይነካ ተጠንቅቆ ፊቱን ዞሮ ምግቡን ቀመሰ። ወጥ
አውጭው ከየዓይነቱ ወጥ መሶቡ ላይ ሲያደርግ፣ አሳላፊው ንጉሠ
ነገሥቱን ማጉረስ ጀመረ።
ወለተጊዮርጊስም ለመጀመሪያ ጊዜ ከንጉሠ ነገሥት ጋር ማዕድ ተቋደሰች።

ንጉሠ ነገሥቱ፣ ወለተጊዮርጊስና መጋረጃ ውስጥ የተፈቀደላቸው እንግዶች በልተው ካበቁ በኋላ፣ መጋረጃው ሲከፈት
አስተናጋጆች ከመጋረጃ ውጭ ደረጃቸው ተጠብቆ የተቀመጡትን
እንግዶች እንደየክብራቸው እጃቸውን በብር፣ በነሐስ ወይንም በብረት ማስታጠቢያ አስታጠቡ።

በእንጀራ ቤቱ ሥር ያሉት አስተናጋጆች በቀረበው ገበታ ላይ
እንጀራ ሲያደርጉ፣ ወጥ ቤቶቹ የተለያየ ወጥ የያዙ ሰታቴዎችን ይዘው እየተንገዳገዱ ሲቀርቡ፣ ወጥ ጨላፊዎች እየጨለፉ የተዘረጋው እንጀራ ላይ አወጡ፤ እንግዶቹም በፀጥታ መብላት ጀመሩ።

ወጥ ቤቶች እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ወዲህ ወዲያ እየተዘዋወሩ ባዶዎቹን ሰታቴዎች ይዘው በፍጥነት ሲወጡ፣ ሌሎች ወጥ የያዙ ሰታቴዎችን ይዘው ከመቅጽበት ይመጣሉ። ለንጉሠ ነገሥቱ የመጣ ገፀ በረከትና ደጅ መጥኚያ ሙክት፣ ሰንጋ፣ ቅቤና እህል በሙሉ ቤት አዛዥ የበላይ ተቆጣጣሪነት ለድግሱ በመዋሉ፣ የምግቡ ዓይነት ልክ
አልነበረውም።

በትልልቅ ድስቶች ጥብስ እየተንቸሰቸሰ፣ ሽታው እያወደ ሲመጣ፣እንግዶቹ ቀዩን ከጮማው እያማረጡ፣ ዐዋዜ ወይንም ድቁስ ላይ እየተመተሙ፣ በጠጅ አለበለዚያም በአረቄ አወራረዱት።

ቀጥሎም የሥጋ ቤት ሹሙ ተሸክሞት ከመጣው ሥጋ ሻኛው፣
ብርንዶው፣ ጎድን ተዳቢቱ፣ ሽንጡና ሌሎችም ዋና ዋና የሥጋ ብልቶች በየገበታው ሲቀርቡ፣ ቢላዋ ለእያንዳንዱ ሰው ታደለ። ዐዋዜና ድቁስ የያዙት አስተናጋጆች ደግሞ በእያንዳንዱ ገበታ አንፃር ሲያስቀምጡ፣
እንግዶቹ እንደየምርጫቸው እያነሱ ሥጋውን አጣጣሙ።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ግርዶሹ እንደ ተከፈተ ነው። ወለተጊዮርጊስ፣ ውስጣዊና ውጫዊ ብርሃን እየረጨች በተመስጦ ዕድምተኛውን ትመለከታለች። ዐይኗን
ከአስተናጋጆቹ ላይ ማንሳት አቅቷታል። በሥራቸው የተካኑት ሙሉ ቤት አዛዥ፣ የእልፍኝ አስከልካዩና ጭፍሮቹ፣ ሰታቴ ተሸካሚዎቹና ወጥ ጨላፊዎቹ፣ የሥጋ ከብቱን ተረክቦ ያሳረደው ሥጋ ቤቱና ጭፍሮቹ
ነጠላቸውን ትከሻቸው ላይ አጣፍተው ወይንም ቡሉኮ ደርበው በየቦታው ተሰማርተው እንደየኃላፊነታቸው በቅልጥፍና ማስተናገዳቸው አስደንቋታል።

ጠጅ አሳላፊው አስተናጋጆቹ የት ሄደው የጎደሉትን ብርሌዎች
መሙላት እንዳለባቸው በዐይኑ ሲጠቁም፣ እንጀራ ቤቱ እንጀራ አለቀ አላለቀ እያለ ከሩቅ መሶብ ሲያማትርና ገበታ ደንገጥ ያለበትን በጥቅሻ ለእንጀራ አሳላፊዎች ሲያመለክት፣ ወጥ ጨላፊዎች እየዞሩ ከየዓይነቱ ወጥ ሲጨልፉ፣ ሥጋ ቤቱ አንጓ አንጓ ሥጋ ተሸክሞ በየገበታው ሲያዞር፣ሥርዓታቸው፣ ትጋታቸው፣ ፍጥነታቸው፣ ቅልጥፍናቸውና ለሥራቸው
ያላቸው ፍቅርና አክብሮት አስደምሟታል።

በልቶ የጨረሰውም እንግዳ ሲወጣ ሌሎች እንደየተራቸው እየገቡ፣ያለግርግርና ያለትርምስ ሁሉም ደንብና ሥርዐት ተከትሎ መደረጉ አስገርሟታል።

ያለ የሌላትን መረጋጋት አጠረቃቅማ ሙሉ ጨረቃ መስላ
ተቀመጠች። ድፍረት እንዳይሆንባት ተጠንቅቃ ንጉሠ ነገሥቱን ሰረቅ አድርጋ አየቻቸው። እንደዚያ በወርቅ ተንቆጥቁጠው፣ ግርማ ሞገስ ተጎናጽፈው፣ ያ ሁሉ ሰው ቁጭ ብድግ የሚልላቸውን ሰውዬ፣ ቋራ እነሱ ቤት መደብ ላይ ተኝተው በወባ ትኩሳት ከተንደፋደፉትና ቤት ያፈራውን እየተመገቡ ካገገሙት ሰውዬ ጋር ማዛመድ አልሆንልሽ
አላት። ለማመንም አቃታት።

ዕጣ ፈንታ ይሁን ሌላ እዚህ ሕይወት ውስጥ የጨመራትን አሰላስላ ተገረመች። እሷ፡ አባቷና የጥላዬ አባት ታርቀው ከጥላዬ ጋር ጎጆ ቀልሰው ለመኖር አልማ ነበር እንጂ እንደዚህ የተንጣለለ ሕይወት ውስጥ እገባለሁ ብላም አልገመተች። ከጥላዬ ውጭ ከሌላ ጋር የመኖር ፍላጎትም ሐሳብም አልነበራት። ጥላዬ ራሱ በዚያን ሰዐት ቢያያት ምን
ሊል እንደሚችል መገመት አቃታት። የንጉሠ ነገሥቱ ታመው ወላጆቿ ቤት መምጣት፣ የእሷ ማስታመምና የእሳቸው አገግሞ መመለስ፣ ለእሷ ቤተመንግሥት መግባት መነሻ ምክንያት መሆኑ ታምር ሆነባት።
👍16
ዙርያውን ስትቃኝ፣ በስተግራዋ የአንገታቸው ንቅሳት ከሩቅ
የሚጣራ ሴቶች የወርቅ ጌጣ ጌጦችና በረጃጅም የሐር ሸማ ተውበው፣ በወርቅና በክቡር ድንጋይ የተሰተረ ካባ ትከሻቸው ላይ ጣል አድርገው ተሰድረው አየች። ከግብፅ የመጣው ሽቱአቸው አካባቢውን በመልካም
ሽታ አናውጦታል። አያቷ የነጋሢ ዘር ያልሆነ ወርቅ አያረግም ያሉት
ትውስ አላትና እነዝኽ በወርቅ ያጌጡት የነጋሢ ዘር መሆናቸው ነው አለች።

በስተቀኝ በኩልና ከንጉሠ ነገሥቱ ጠረጴዛ እልፍ ብለው፣
እንደየደረጃቸው የተደረደሩትን በነጭ ተነፋነፍ ሱሪያቸው ላይ ያጌጠ ካባ የደረቡ ባላባቶችና ነጭ ጥምጥም ራሳቸው ላይ ያዞሩትን ሊቃውንትና ካህናት ዐይኗ አማተረ። አፄ በካፋ ጥንት የነበረውን የወንድና የሴት ግብር ላይ ተለያይቶ መቀመጥ በማስቀረት ወንዶችና ሴቶች አብረው ገበታ እንዲቀርቡ ባዘዙት መሠረት አብረዋቸው የተቀመጡትን ወይዛዝርት አየች።

ወይዛዝርቱ ጠርዙ የተለያዩ ቀለማት ባሉት የሐር ክር የተጠለፈ
ሸማ ለብሰው፣ በጐንደር ወግ የተሠራው ሹራባቸው ትከሻቸው ላይ ወድቋል። ገሚሶቹ የተለያየ ቀለም ያለው የሐር ሻሽ ሹሩባቸው ላይ ጣል ሲያደርጉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከብር ወይንም ከከበረ ድንጋይ የተሠራ ወሸባ በቄንጥ ወሸቅ አድርገውበት ተሰይመዋል። አንዳንዶቹ ጆሯቸው ላይ
የብር ጌጥ ሲያንጠለጥሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ተለጣፊ ጉትቻ አድርገዋል።

ንቅሳት የተረበረበበት አንገታቸውና ጣታቸው በብር ጌጦች አምረዋል።በሕብረ ቀለማት የተጠለፈ አለዚያም የተለያየ ቀለም ባላቸው ጨሌዎች
ያጌጡ በርኖሶች ወይንም ካባዎች ደርበዋል። ሽቱአቸው የወጡንና የጠጁን መዓዛ አሸንፎ አዳራሹን ዐውዶታል፤ ልብሳቸውና ጌጣቸው ለአዳራሹ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል። እነዝያ በብር ያጌጡት ደሞ እሚታዬ የጐንደር ወይዛዝርት ምትላቸው
መሆናቸው ነው። እንዴት ደማሞች ናቸው? አለች፣ ወለተጊዮርጊስ።

ያንን መሰል ድምቀት አይታ ባለማወቋ ተደነቀች። አባቷ
በዓላትን ሲያከብሩ የሚያገቡትን አነስተኛ ግብር ከምታየው ታላቅና
የተትረፈረፈ ግብር ጋር አወዳደረች። ያም እኼም እኩል ግብር? ብላ ፈገግታ ቃጣት።

የቤተመንግሥቱ ግርማ ሞገስ የገባችበትን ሕይወት
እመርታውን ሲያስረዳት እየታደመችበት ያለችበት ታላቅ ግብር ግዝፈቱን አመላከታት።

ምንም እንኳ አያቷ የተቻላቸውን ያህል የምትገባበትን ኑሮ ምንነት
ሊያስረዱ ቢሞክሩም፣ ግብሩ የሚጠብቃትን ሕይወት ቁልጭ አድርጎ አሳያት። የእዚህ ዐዲስ ሕይወት ወግ ውስብስብነትና ብዛት እሷነቷን ተፈታተናት። ላየችው ሥርዐትና ድምቀት ሁሉ ትመጥን እንደሆን ራሷን
ደጋግማ ጠየቀች። መኳንንቱና ወይዛዝርቱ ከቋራ የመጣች የንጉሥ ሚስት ይቀበሉና ያከብሩ እንደሆነ ጠየቀች። አያቷ፣ “መኳንንቱና ወይዛዝርቱ ባንቺ ቢያጉረመርሙ ኸቋራ የመጣች በሚል ነው” ያሉትን አስታወሰች። ኸቋራ ብመጣስ? ቋራ ብለው ሚያጉረመርሙ፣ አሁን
እነዝኸ ወይዛዝርት አንዳቸው ስንኳ ኸሚታዬ ይተካከላሉ ደርሰው ሰው
ሚንቁ? አለች።

ሴቱ ወንዱ ዐይኑ እዚያ የሚያባብለው እንክብል ዐይኗ ላይ ተተክሎ ስታይ መንፈሷ ተረበሸ። በመልኳና ባስተጋባችው ለዛ ተማርከው እንደሆነ አልገባ አላት። ቋራ እያለች ነፍሷን ሲያንገላታት የነበረው
በራሷ ላይ የነበራት ጥርጣሬ ሊመለስባት ሞካከረው።

ፊት አልሰጥ አለችው።
አያቷን በዐይኗ ፈልጋ አገኘቻቸው። በቁንጅናቸው፣ በመረጋጋታቸውና
ኮፍነን ብለው በመቀመጣቸው ተደሰተች፤ ብርታት ጭምር አገኘች።ምነው አሁንስ እኼ ሁሉ ጭንቀት ብላ በለዘብታ ተነፈሰች።
ተሳስሮ የነበረ ሰውነቷን ለማፍታታት እግሮቿን በጥንቃቄ
ዘረጋቻቸው። ሰውነቷ ሲፍታታ አእምሮዋ ዘና አለ። እስከዚያ ሰዐት ድረስ አካሏን በፍርሐት ያራደውን፣ አእምሮዋን በጭንቀት የወጠረውን ሳብ ገፍተር አደረገችና፣ አሁንስ ምነው? አንዴ እንደሁ ገብቸበታለሁ።
ኸንግዲህ ፍራት ምን ያረጋል? ራሴንስ እስተዝኸ ድረስ ማስጨንቀው ለምነው? አለች። አያቷን ድጋሚ ተመለከተችና “ንግሥት እሌኒን አረግሻለሁ” ያሉትን አስታውሳ አላሳፍራትም፣ ሁሉን እንዳመጣጡ እወጣዋለሁ፣ ኸንግዲህ አልፈራም አለች።

ቀለል አላት፤ ግንባሯም ተፍታታ። ጃንሆይም ቢሆኑ ምንትዋብ
ብለውኛል። ምን ዋብ! እንዴት ያለ ድንቅ ስም ነው? ኸዛሬ ወዲያ
ምንትዋብ ነኝ፡፡ እሌኒን ሳይሆን ምንትዋብን ሆናለሁ ስትል ለራሷ
ቃል ገባች።

ከፍታ ላይ፣ ያውም ከንጉሠ ነገሥት ጎን ተቀምጣ የግብር ታዳሚውን ወደ ታች ስታይ ልዩ ስሜት ተሰማት። ለመጀመሪያ ጊዜ ክብር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተገነዘበች፤ ወደደችው። የደስታ ስሜት መንፈሷን አነቃቃው። ለእዚያ ላየችው ሁሉ ባለቤት ስትሆን ታያት። እዚያ
የተሰበሰቡት ሴቶች ሁሉ ከተቀመጡበት ወንበር የእሷ ድንክ አልጋ ይበልጣልና ከእሱ ላይ ባትነሳ ፈቀደች። እዚያ ላይ ላስቀመጣትና ከሴቶች ሁሉ መርጦ ያን መሰል ዕድል ባለቤት ላደረጋት ፈጣሪዋ ብላም ለቁስቋም ማርያም ምስጋና አበረከተች።

ቁስቋም ለካንስ እኼን አዘጋጅታልኝ ኑሯል ያን ያህል ግዝየ ጥላዬን
ስጠብቅ አልሳካ ያለው! ባላምባራስ ሁነኝ እኔና ጥላዬን አለያዩን እያልሁ ስኮንናቸው ለኖርሁት ይቅር ይበሉኝ። የኔና የጥላዬ ነገር አብቅቶለታል። ግዝየ እኔን ለዝኸ እንዳበቃኝ ሁሉ ለሱም ሚበጀውን ይስጠው። ወይ አንድ ቀን እንገናኝ ይሆናል አለች።

አፄ በካፋ በበኩላቸው ስሜታቸው እንደፍም ግሎ ተቀምጠዋል።
ያን ጊዜ ታዲያ ደስታቸውን እንጂ፣ በቀኛቸው በኩል ያስቀመጧት፣
ምንትዋብ ብለው ስም ያወጡላት ለጋ ወጣት የታሪክን እርከን
ለመውጣት የታጨች መሆኗን እሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ እንኳ መገመት አልቻሉም።

ለወትሮው “እከሌ ምን እየዶለተ ይሆን?” እያሉ የመኳንንቱን ፊት
ሲፈትሹ ጊዜ የሚያጠፉት ንጉሠ ነገሥት፣ ዛሬ ልባቸው አደብ አልገዛ ብሎ በደስታ ሲዘል፣ ዕንቁ የመሰለች ኮረዳ ከጎናቸው መቀመጧን ለደቂቃ ሳይረሱ፣ የፍቅር ተገዥ ሆነው የታደሙበት ግብር፣ የዘወትር የፖለቲካ ድጋፍ ማረጋገጫና የሀብት ክፍፍል ማደላደያ መድረክ ሳይሆን፣ ቆንጆዋ ወጣት ከሰማይ የወረደችበት ልዩ አጋጣሚ አድርገው ቆጥረውታል። የሚሏት እየጠፋቸው፣ አልፎ አልፎ ፈገግታ ከመለገሥ በስተቀር፣ ዝምታን መርጠዋል።

ምግብ ተበልቶ አብቅቶ አዳራሹ ሞቅ ደመቅ ብሏል። እንግዶቹ
ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው ጠጅ በብርሌ፣ አለያም በብር ወይንም
በቀንድ ዋንጫ አረቄ እየተጎነጩ ጨዋታውን ተያይዘውታል።

ምንትዋብ ቤተክርስቲያን እንጂ፣ ግብር አዳራሽ ውስጥ አይታው
በማታውቀው ሁናቴ ካህናት ሲያሸበሽቡ አይታ ተገረመች።

እግዚአብሄርም ንጉሥም ባንድ ጊዜ ሲመሰገኑ ሰማች። በዐይነ ኅሊናዋ ግብር ስትጥል፣ ካህናትን ስታዘምር ታያት።

ቀጥሎም ባለ ክራሩ ክራሩን እየገረፈ ለንጉሠ ነገሥቱ ሙገሳና ውዳሴ ሲያዥጎደጉድ፣ ለአዝማሪ እንግዳ ባትሆንም አዝማሪዎች ተራቸውን ጠብቀው መሰንቋቸውን እያነጋገሩ፣ የንጉሠ ነገሥቱን ጀግንነትና ደግነት ሲያደንቁ፣ ለምግቡና ለመጠጡ ምስጋና ሲያቀርቡ በችሎታቸው
ተገረመች። ስለእሷ ውበት ግጥም ሲደረድሩ ግን እንደማፈር አደረጋት።

ሊቃውንት ንጉሠ ነገሥቱን በቅኔ ሸንቆጥ ሲያደርጉ፣ እንግዶቹንም
በችሎታቸው ሲያስደምሙ፣ ቅኔ ባይገባትም መንፈሷ ይበልጥ ተረጋጋ፤ መረጋጋቷ በውበት ላይ ውበት አከለላት።

የጐንደር መኳንንት ዐይናቸው ከእሷ ላይ መነሳት ተስኖት ውበቷን በጠጅና በአረቄ ሲያወራርዱ፣ አያቷ እንዳሉት የጐንደር ወይዛዝርት
ግንባራቸውን ኮምተር አደረጉባት።
👍12
በመጨረሻም አፄ በካፋ ከመነሳታቸው በፊት አቡኑ ተነሥተው
“ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ” ብለው
የምስጋና ጸሎት አደረሱ። ንጉሠ ነገሥቱ ለመሄድ ሲነሡ እንግዶቹ
ተነሥተው እጅ ነሡ። ምንትዋብም ተነሥታ ተከተለቻቸው። መሄዷ
ቢያስደስታትም አያቷ ያስተማሯትንና የነገሯትን በትክክል ፈጽማ እንደሆን የማወቅ ጉጉቷ አደገ፡፡ ወደ ማረፊያ ክፍሏ ስትጠጋ አያቷ ጆሮዋ ስር ተጠግተው፣ “የኔ ልዥ ታየሽበት” ሲሏት፣ ፈገግ አለች።
አላሳፍራትም ባለችው መሠረት እንዳላሳፈረቻቸው ገባትና ደስ
ተሰኘች።

እንግዶቹ ከወጡ በኋላ፣ እልፍኝ አስከልካዩ፣ ባለሟሉ፣ የመኰንኑን
መሣሪያ ያነገተ ጋሻ ጃግሬው፣ ወታደሩ፣ ተማሪው፣ የቁም ጸሐፊው፣ ድኃው አንዱ ሲወጣ ሌላው እየተተካ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አግዳሚ ወንበርና ዱካ ላይ ተቀምጠው ግብር ተካፈሉ፤ ጥሬ ሥጋ
ጎመዱ፤ በቁማቸው ጠላና ለተራው ሰው የተጣለውን ጠጅ በጉሮሯቸው አንቆረቆሩ።.....

ይቀጥላል
👍9
አትሮኖስ pinned «#ምንትዋብ ፡ ፡ #ክፍል_አስራ_ሁለት ፡ ፡ #ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ ....በመጨረሻም ምንትዋብ ብያታለሁ” ብለው በቀኛቸው ያለው ድንክ አልጋ ላይ እንድትቀመጥ አደረጓት። እሷን ተከትለው የገቡት አያቷ፣ በካፋን ለጥ ብለው እጅ ነስተው በእልፍኝ አስከልካዩ መሪነት ከንጉሣውያን ቤተሰቦች ጋር የተዘጋጀላቸው ቦታ ሄደው ተቀመጡ። ወዲያው ሙሉ ቤት አዛዥ እንጀራ አሳላፊውንና እንጀራ የያዙ ተከታዮቹን፣ በወጥ…»
#ያልታበሱ_እንባዎች


#ክፍል_ሀያ_ዘጠኝ


#ድርሰት_በአሰፋ_በቀለ_ገየሱስ


...በቀኝ በኩል ታጥፈው ዜሮ ሁለት ቀበሌ ውስጥ 'ግሪን ፓርክ' ተብሎ ከሚጠራው መዝናኛ በታች ወደሚገኘው ቤታቸው ሊያመሩ ሲሉ ሾፈሩ ከመኪናዋ ላይ ወርዶ ወደ እነሱ ሲራመድ አዩት፡፡ ደንገጥ ደንገጥ ብለው እያዩት ሳሉ ከአጠገባቸው ደረሰ።
«ምነው በምሽት ብቻችሁን?» አላቸው ለሰላምታ እጁን በተለይ ወደ ሔዋን እየዘረጋ።
ሔዋን የስውየውን ማንነት ወዲያው አወቀችው፤ በድሉ አሸናፊ ነው፡፡ እጇን መዘርጋት ትታ ወደ ትርፌ ደገፍ አለች፡፡ ዓይኖቿ ግን በበድሉ ላይ ስክት አሉ።

በድሉ አጭር ወፍራም ነው። ከአንገቱ ማጠር የተነሳ ጭንቅላቱ ትከሻው ላይ ቁጭ ያለ ይመስላል። መልኩ ጠቆር ያለ ጠይም ነው፡፡ አራት የፊት ጥርሶቹ
ወጣ ብለው ገጠጥ ያሎና ዓይኖቹ ትናንሽና ድፍርስርስ ያሉ ናቸው፡፡ በዕለቱ ጥቁር ቆዳ ጃኬት በነጭ ቲሸርትና ነጣ ያለ ሱሪ ለብሷል፡፡

«የእግዚአብሔር ሰላምታም ልነፈግ እንዴ?» አላት በድሉ የዘረጋውን እጁን ወደ ክንዷ አዙሮ
ያዝ እያደረጋት።
«ልቀቀኝ!» አለችው ሔዋን በጨለማው ውስጥ ፊቷን ጭምድድ አድርጋ እያየችው።
«የማነጋግርሽ ጉዳይ አለኝ፡፡» አላት ክንዷን ጠበቅ አድርጎ በመያዝ፡፡
«ስለምን ጉዳይ?»
«ቅድም አዳራሽ ውስጥ ያለቀስሽው እኔ ስላወላከፍኩሽ ከሆነ ይቅርታ ልጠይቅ እፈልጋለሁ»
«አይ! በእሱ አይደለም»
«ታዲያ ምን ሆነሽ ነው?»
«ዝምብዬ!»
«ዝምብሎማ ለቅሶ የለም !
የሆንሽው ነገር ካለ ንገሪኝ' ምናልባት ልረዳሽም እችላለሁ»
«አይ አይ ምንም ዕርዳታ አልፈልግም፡፡ ልቀቀኝና እንሂድ መሽቶብናል፡፡»አለችው ሔዋን አሁንም ክንዷን ለማስለቀቅ እየታገለች።
«በመኪና አደርሳችኋለሁ»
«አያስፈልገንም ቤታችን ቅርብ ነው»
«ቅርብ ከሆነ ታዲያ ምን አስቸኮላሽ»
ሔዋንን ንድድ አላት፡፡ ክንዷን ደግሞ ጥብቅ አድርጎ ነው የያዛት፡፡ አሁንም እየታገለች ልቀቀኝ አለበለዚያ እጮሀለሁ!» አለችው።
«እጮሀለሁ? ሲል በድሉ የሔዋንን ቃል ደገመው፡፡
«አዎ፣ እንዳልጮህ ከፈለክ ልቀቀኝ»
«እኔም እጮሀለሁ አለች ትርፌም፡፡» እስካሁን ድረስ ከአሁን አሁን የሚለቃት መስሏት ዝም ብትልም አሁን ግን የበድሉ አያያዝ አላምር አላት።
«አሃ! እንደ ከዚህ ቀደሙ ልታስደበድቢኝ ነዋ!» አላት በድሉ በተለይ ሔዋንን አየት እያረገ፡፡
«መቼ እስደብድቤህ አውቃለሁ?»
«ረሳሽው?»
ሔዋን በድሉ ምን እያለ እንደሆነ ሊገባት አልቻለም:: በእርግጥም ጩሂ ጩሂ የሚል ስሜት መጣባት። ነገር ግን በዚያ ጭር ባለ ቦታና ሰዓት ግን ማን
ሊደርስላት እንደሚችል አታውቅም::
«በእናትህ ልቀቀኝ!» አለች አዝኖ እንዲለቃት ለመለማመጥ።
«በልሁ ለሚባለው ሰውዬ ስለኔ ምን ብለሽ ነግረሽው ነው ሊደበድበኝ የተነሳው
««እሱ ሰው አይደባደብም»
«የተሞከረብኝ እኮእኔ ነኝ»
ነበር «ምን አደረክ ብሎ ይደበድብሃል?» በማለት ትኩር ብላ ስትመለከተው በድሉ የታችኛውን ከንፈሩን ነክሶ መሬት መሬት እያየ ያስብ ጀመር፡፡
" ያስታውሳል' በድሉ ሔዋንን በሽዋ ቤት ውስጥ እጇን ጎትቶ ፍራሽ ላይ ሊያስቀምጣት በሞክረበት ሳምንት ውስጥ ነበር፡፡ ከአንድ ቡና ቤት ውስጥ ብቻውን
ቁጭ ብሎ በሚጠጣበት ወቅት በልሁ በዚያ ቡና ቤት ውስጥ ገባ ሲል ሁለቱ ይተያያሉ፡፡ በልሁ ጠጋ ብሎ ስላም ካለው በኋላ አጠገቡ ቁጭ ይላል፡፡ ወዲያው
ያናግረዋል፡፡
«ይቅርታ የኔ ወንድም ፣ መቸም በዓይን እንተዋወቃለን»
«አዎ፡፡» ይለዋል በድሉ ፈዘዝ ብሎ ከነበረበት ስሜት ነቃ እያለ፡፡
«ላናጋግርህ የምፈልገው አንድ ጉዳይ ነበር፡፡»
«የምን ዓይነት ጉዳይ?»
«ሸዋዬ የምትባል መምህርት ታውቃለህ?» ሲል ይጠይቀዋል፡፡
«አልፎ አልፎም ቢሆን ወደ እሷ ቤት የምትሄድ መሰለኝ»
«ምነው?»
«ሔዋን የምትባል እህቷ ጋር የተለየ ጉዳይ አለህ? ወይ ደሞ ሊኖርህ የምትፈልገው ነገር ይኖር ይሆን?»
«አልገባኝም የኔ ወንድም» ካለ በኋሳ በድሉ በደረቁ ፈገግ ብሎ በልሁን እያየ እርግጠኛ ነኝ ፖሊስ አይደለህም"
«ትክክል። ፖሊስ አይደለሁም::
ልነግርህ የምፈልገው ግን ያቺ ልጅ
እጮኛ አላት ስለዚህ ላትጠቅምህ ነገር አንተም ባትለፋ እሷን" ባታስቸግራት ልልህ ፈልጌ ነው፡፡ ቅር ይልሀል?
ይህንንም ለመግለፅ ራሷ ልጅቷ ትበቃለች። የእንተ ጣልቃ መግባት
ያስፈልግ አልመሰለኝም"» ይላል በድሉ ፊቱን ኮስተር አድርጎ፡፡
«ጣልቃ መግባት እይደለም በድሉ፣ ጣልቃ ገቦችን ማስጠንቀቅ ፈልጌ ነው።
ሳታውቅ ላደረከው ነገር ይቅርታ ይደረግልሀል፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ብትሞክር ግን ሰው እየተዳፈርክ መሆኑን አውቀህ ብታስብበት ብዬ ነው
«ብታስብበት።» በማለት በድሉ ቃሉን ይደጋግማል «ጨርሻለሁ» ብሎ በልሁ ትቶት ይወጣል።
ይህ ብቻ አልነበረም በወቅቱ በድሉን ትዝ ያለው ነገር፡፡ እንድ ዕቅዱም እንደከሸፈበት አስታወሰ፡፡ ሔዋን ጓዟን ጠቅልላ ከቤቷ በወጣች ዕለት ሽዋዬ ያላሰበችው ዱብ ዕዳ ሆናባት የምታደርገውን አጥታ ተሸብራ ነበር፡፡ ሔዋን
ለታፈሡ ቤት የገባች መስሏት ዓይኗን በጨው አጥባ ካታፈሡ ቤት በመግባት ታፊሡን ራሷን ጠይቃት ነበር። ታፈሡ የሰጠቻት መልስ ደግሞ ሔዋን እኔ ቤት
ልትኖር አትችልም፡፡ የራሷን መኖሪያ አግኝታለች። ከእንግዲህ አታገኚያትምና ባትለፌ ጥሩ ነው የሚል ነበር። የታፈሡ መልስ እና የሔዋን ድራሽ መጥፋት
በማግስቱ ደሞ መሠረተ ትምህርት ወደ ምታስተምርበት ጣቢያ ሄዳ እግኝታት «የት ነው የሄድሽው አንቺ» ስትል ነበር ዓይኗን አፍጣ ጥርሷን አግጥጣ
የጠየቀቻ
«እዚሁ ዲላ ውስጥ ነኝ»
«ወደ ቤትሽ ትመለሻለሽ ወይስ አትመስሽም?»
«ፈጽሞ አልመስም»
አስደንጋጭ አቋም ነበር ለሽዋዬ፡፡ ለአንድ ሳምንት ያህል ስትብከነከን ቆይታ መጨረሻ ላይ በተለይ ከባርናባስና በድሉ ጋር በመሆን የቀቢፀ ተስፋ ምክክር አድርገው ስምምነት ላይ የደረሱበትም ዕቅድ ነበር። ሸዋዬ ያለ እስታራቂ ሔዋንን ለምናም ቢሆን ልትታረቃት፣ እናታችን ጠርታናለች ክብረ መንግስት ደርሰን
እንምጣ ብላ ልታታልላት! ሔዋን ስራዬስ ያለቻት እንደሆነ በአንድ ቀን አድርሶ የሚመልስን ሰው አለ ልትላት፣ እሺ ካለች በድሉ አለታ ወንዶ ድረስ ይዟቸው ሊሄድና እዚያው እለታ ወንዶ ከተማ ውስጥ መኪናዬ ተበላሸች ብሎ እየጎረጎረ ሊያስመሻቸው ከዚያም ማረፊያ ሆቴል ይዘው ሊያድሩና በድሉ ሔዋንን ሊደፍራት፡፡ ከዚያም እዚያው አለታ ወንዶ ስነባብተው ሔዋንን ሊያባብሉና
ሊያለማምዱ አስበው ነበር።
በእርግጥም ሽዋዬ ሔዋንን ለማታለል ብዙ ጥራ ነበር፡፡ ሔዋን ግን ፍንክች አላለችም፡፡ የእናቷ ጥሪ ትንሽ አሳስቧት በማማከር ሽዋዬ ያስቻትን ሁሉ
ለታፈሡ፣ ለበልሁና ለመርዕድም ነግራቸው ነበር፡፡ በተለይ በልሁ በአንድ ቀን አድርሶና የሚመልስ ሰው አለ የሚለው ቢነገርም ገብቶት በጣም ይናደዳል። አንድ ቀን መርዕድን አስከትሎ ወደ ሸዋ ቤት ይሄዳል፡፡ በአጋጣሚ ሸዋዬና በድሉ ፍራሽ ላይ ቁጭ ብለው ሲቅም ያገኛቸዋል፡፡ ቁጭ ሳይል በቋሙ ስሚ እንቺ!» ብሏት ነበር ሸዋዬን።
«አቤት!» ሸዋዬ በድንጋጤ ክረምትምት እያለች፡፡
እየሰራሽ ያለሽው ነገር ያልታወቁ እንዲይመስልሽ ዳግም ሔዋን ወደምትሰራበት ቦታ ብቅ ትዬና
👍7
ወየውልሽ ሄዋን እንኳን በአንድ የከረከሰች ቶዮታ አውሮፕላን ብታቀርቢላት አስቻለው ሳይመጣ ክብረ መንግስት አትሄድም ገባሽ ካለ በኋላ በልሁ ቀጠል አድርጎም
«ይህ ለአንቺም ሆነ ላባለ ኪናው የመጨረሻ ማስጠንቀቅያ ነው።» በማለት እግረ መንገዱን በድሉንም ወረፍ አድሮጎት ነበር ለነገሩ በድሉ ምንም አልተናገረም እንጂ አንዲት ቃል ተንፍሶ ቢሆን ኖሮ በልሁ ከዚያው ሊደፍቀው ከጀል አድርጎት ነበር።
«እ..እሺ ነበር ያለችው ሸዋ'ዩ በድንጋጤ ድምጿ እየተቆራረጠ፡፡
በድሉ አሸናፊ ታዲያ ይህን ሁለ ውርደት ተሽክሞ ሲኖር ጠላቱ አደርጎ የሚያስባት ሔዋንን ነው፡፡ ዛሬ ያ ሁሉ መጥፎ ስሜት መጣበትና «ግን በአንቺ የተነሳም ሲደነፋብኝ የምኖር ይመስልሻል?» ሲል ክንዷን ጠበቅ አደረገ ጠየቃት።
«ምን አርጊ ነው የምትለኝ?» አለችው ሔዋን ጮክ ቆጣ ባለ አነጋገር፡፡»
«የምትሰሚ ከሆነ አንድ ነገር ልነግርሽ እፈልጋለሁ::!»
«..ሌላ ጊዜ ትነግረኛለህ፡፡»
«ሌላ ጊዜማ የምነግርሽ ነገር እውነት መሆኑን የምታረጋግጪበት ነው፡፡ ብሎ በድሉ ክንዷን ነቅነቅ እያረጋት ሞኝ አትሁኝ! ኤርትራ የሂደ ሰው
ይመለሳል ብለሽ ወርቃማ ጊዜሽን በከንቱ አታሳልፊ። አላት፡፡

ሔዋን ድንገት ዋ……ይ…..ብላ በረጅሙ ጮኸች፡፡ የመጮኋ ምክንያት ቀድሞ እንዳሰበችው በድሉ እንዲለቃት ብላ
አልነበረም' የአስቻለውን ከኤርትራ ያለ መመለስ ጉዳይ ከተላያዩ ነገሮች ጋር አያይዛው እውነትም ሊቀር እንደሚችል ድንገት ታይቷት ደንግጣና ተሳቃ ነው።
እስቻለሁ ከመዘግየቱ፡ በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ ሰው ሲያወሩ እገሌ ኤርትራ ዘምቶ ነበር ነገር ግን አለ አይባል ፡ ሞተ አይባል ይኸው ደብዛው ጠፋ
ሲባል ደጋግማ ሰምታለች፡፡ የበድሉ አስተያየት .ከዚህ የመነጨነና እውነትም
እስቻለው እዚያው የሚቀር መስሏት አንጀቷ ተቆርጧ ነው፡፡ በድሉም ጩህቷ አስደንግጦት ወዳያው ለቀቃትና ወደ መኪና በመሮጥ አስነስቶ ተፈተላከ::
ሔዋንም እያለቀሰች በትርፌ ድጋፍ ወደ ቤቷ አመራች፡፡
በልሁና መርዕድ የትርፌንና የሔዋንን የሙዚቃ ምሽት ቆይታ ሊጠይቁና በዚያውም ትንሽ ሊያጫውቷቸው በማሰብ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ሄደው ከቤት ሲገቡ የሔዋንን ስሜት ልውጥውጥ ብሎ አገኙት። ያለቀሰችበት ዐይኗ ሁሉ አባብጧል፡፡ እንዲት ወረቀት በእጇ ጭብጥ አድርጋ ይዛ ትክዝ ብላ ተቀምጣለች ።
«ምነው ሒዩ! ሙዚቃው አስለቃሽ ነበር እንዴ?» ሲል በልሁ ፊትለፊቷ
እንደቆመ ጠየቃት።
«አይ» አለችና ሔዋን እንባዋ በዓይኗ ላይ ግጥም ሲልባት ወደ መሬት አቀረቀረች።
«ምንድነው ችግሩ?» በማለት በልሁ የያዘቻችን ወረቀት ተጠራጠረና ከእጇ ላይ ንጥቅ አድርጎ ሲያያት ያው የአስቻለው የመጀመሪያም የመጨረሻም ደብዳቤ ሆና አገኛት።
«ዛሬም እዛው ነሽ» አላት ቆጣ ብሎ
መርዕድ ደግሞ ወደ ትርፌ ዞር አለና ምን ሆናለች? ሲል ጠይቋት
መልሷን ሲጠብቅ ሄዋን ድንገት ቀደመቻቸው።
«በልሁዬ አታለሉኝ ኤርትራ የሄደ ሰው አይመለስም። በቃ አስቹ
እንደሆን ቀርቷል።»አለችው ቀና ብላ ዓይን ዓይኑን እያያች።ዓይኖቿ በእንባ ተሞልተው ሰማይ መሰሉ።

«ምን።» አለ በልሁ ክው ብሎ በመደንገጥ፡፡
«በቃ አሁን ነገሩ ሁሉ ገብቶኛል። እስቻልው ከኤርትራ አይመጣም፡፡» ብላ ፊቷን በጉልበቷቾ ላይ እስደግፋ ስቅስቅ ብላ ታለቅስ ጀመር፡፡
በልሁ አንድ ነገር ፡ ወለል ብሎ ታየው! የአስቻለሁ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለና ምናልባትም መመሰስ ባይችል በሔዋን አእምሮ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው አደጋ!!

💫ይቀጥላል💫
👍12
#መሰቀል_እና_መስቀል

“መሰቀል ምንድን ነው?
“መስቀልስ ምንድንነው?

በተሰቀልክ ቁጥር - ከፍ ከፍ ትላለህ
የሚሰቅልህን ሰው - ቁልቁል ታየዋለህ::
(ስትሰቅልም እንደዛው) -
'ስሙ' ድል ቢሆንም ፣ 'ወርቁ ግን ሽንፈት ነው
(የምትሰቅለውን ሰው) -
በሰቀልከው መጠን ፣ ከፍ እያረከው ነው::

🔘ሙሉቀን ሰለሞን🔘
6👍2
#ጣትና_ቅጣት

ብዕር ከወረቀት
ጣትም ከቀለበት
ተስማምተው እያረፉ
ምነው የሚስማሙ
ባለጣቶች ጠፋ

🔘ልዑል ሀይሌ🔘
👍64
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
የታቦት አታስገቡም ፍጥጫው ቀጥሏል።
ታቦቷ ባለችበት እንድታድርም መወሰኑ ተነግሯል።

#SHARE_SHARE_SHARE ይደረግ።
አዲስ አበባ ጫፍ ቀራንዮ ወይብላ ማርያም #ኦሮሚያ ክልል
👍4
ጭራሽ...
ደሞ ልብ እንዳለው
ሴት ላፍቀር እላለሁ፤
ደሞ ነፍስ እንዳለው
ቅኖና ፣ንስሐ ፣ምናምን እላለሁ፤

ደሞ ሰማሻቸው?
ለመልኩ ፣ለዐይኑ
ግድ የለውሞ ሲሉ።
ጎኑ ላለ ተድላ፣
ጎኑ ላለ ለቅሶ፣
ጎኑ ላለ እድር፣
ጎኑ ላለ እቁብ፣
የለውም አንዳች ቁብ።
ሲሉ ሰማሻቸው?
ጺሙ በንዠረገግ ፣መሬት ቢዘረጋ፣
እሱ ግድ የለውሞ ፤ አፈር ቢኾን አልጋ።
ሲሉ ሰማሻቸው?
ዝም አትበያቸው፤
“በየትኛው ነፍሱ"
ይሄን ሁሉ ያስብ ፣ብለሽ ጠይቂያቸው።
በየትኛው ነፍሴ ፣ ከትናንቴ ልማር፤
አንቺን አገኝ ብዬ ፣ አስይዢዉ በቁማር።
(አስመልሽው ባክሽ)
ደሞ ልብ እንዳለው
ሴት ላፍቅር እላለሁ፤

🔘ኤልያስ ሽታኹን🔘
👍152
#ምንትዋብ


#ክፍል_አስራ_ሶስት


#ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ

....ምንትዋብ ማረፊያ ክፍሏ ቆይታ ማታ ላይ ራት ከበላች በኋላ፣ በሁለት ደንገጡሮች ታጅባ ወደ አፄ ፋሲል ቤተመንግሥት አቀናች። ደረጃውን ከወጡ በኋላ፣ ሁለት ያደገደጉ ደጅ አጋፋሪዎች መግቢያው በር ላይ ቆመው ለጥ ብለው እጅ ነሥተው መግቢያው ላይ ባለው በወንዶች የግብር አዳራሽ በኩል እንዲሄዱ መሯቸው።

ምንትዋብ ቆም አለች።

የግብር አዳራሹ ወለል ከፋርስ በመጣ ምንጣፍ አሸብርቋል። በክፍሉ ዙርያ ያሉት ባለመስተዋት መስኮቶች በሐር መጋረጃዎች ተሸፍነዋል ::በፋና ወጊዎች የተለኮሱት በየማዕዘኑ የተቀመጡት ትልልቅ ጧፎች
ክፍሉን አድምቀውታል።

ምንትዋብ ባየችው ሁሉ ተማረከች።

ሴቶቹ ግብር አዳራሽ ስትገባ ተመሳሳይ ድምቀት አይታ ሦስተኛ
ደርብ ላይ ወደሚገኘው የንጉሠ ነገሥቱ መኝታ ክፍል ለመግባት ደረጃ ስትወጣ፣ ደንገጡሮቹ እጅ ነሥተዋት ከኋላዋ ተመለሱ።

ደረጃውን ወጥታ ስትጨርስ፣ አፄ በካፋ ቀን አድርገውት የነበረውን
ዘውዳቸውንና ካባቸውን አውልቀው፣ ማምሻ ክፍል ውስጥ፣ ቀይ ከፋይ የለበሰ ሰፊ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። ከፊት ለፊታቸው ያለ ጠረጴዛ ላይ፣ ጠጅ በብርሌ ተቀምጧል። በክፍሉ ጥግ ጥግ የቆሙ፣ ረጃጅም
መቅረዞች ላይ የተቀመጡት ማሾዎች ለክፍሉ ልዩ ውበት ሰጥተውታል።

አፄ በካፋ፣ ምንትዋብ ስትገባ፣ በፈገግታ ተቀብለዋት፣ ከጎናቸው
ያለ ወንበር ላይ እንድትቀመጥ በእጃቸው አሳይዋት። ስትፈራ ስትቸር ተቀመጠች። ዐይናቸውን ማየት አቃታት።

እሳቸው ግን በእዚያ ምትሐታዊ ውበቷ ዳግም ተማርከው ዐይናቸውን ከእሷ ላይ ማንሳት ተስኗቸዋል። ወዲያው ግን መርበትበቷን አስተውለው፣
“አይዞሽ የኔ ዐይናማ፤ ምንም ሚያስፈራ ነገር የለም እኮ” አሏት፣ እጇን እጃቸው ውስጥ አድርገው።

አቀርቅራ ዝም አለች።

“ያረግሽልኝን ሁሉ መቸም አልረሳውም። ኸኪዳነ ምሕረት ጋር አስታመሽ አዳንሽኝ። የልዥ አዋቂ። ኪዳነ ምሕረት ታክብርሽ።
እንዳው ነገሩን ሁሉ ሳጤነው... እዝጊሃር እንድንገናኝ ፈልጎ ነው እንጂ ኸናንተ ቤት ታምሜ መምጣቴ ተጎድቸ ነበር፤ ኪዳነ ምሕረትና ሩፋኤል እንዳንቺ ባለች ዐይናማ ካሱኝ” አሉ፣ በሠርጋቸው ማግስት ስለሞተችው ሚስታቸው አስበው።

ምንትዋብ እጇን እያፍተለተለች ዝም ብላ አዳመጠቻቸው።
በተናገሩት ነገር ልቧ ተነካ። እኛ እንደዛ በወርቅና በዕንቁ ተንቆጥቁጠው፣ሩቅ ይመስሉ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት እንደ እሷው ሰው መሰሏት።

“እስቲ ያነን ሚጥም ድምጥሽን አሰሚኝ፤ ተጫወቺ እስቲ። ኸናንተ
ቤት ሳለሁ ላነጋግርሽ እየፈለግሁ ማን መሆኔ እንዳይታወቅ ብየ ዝም አልሁ። ኸኛ ኸደግ አባትሽ ጋር ስንኳ ሳልጫወት ተመለስሁ” አሏት።

የምትለው ጠፋት። በመጨረሻ፣ ቁስቋም ታክብርልኝ። ለዝኽ
ላበቁኝ ለርሶም፤ እሷው ምላሹን ትስጥዎ” አለቻቸው።
“እኔ ምን ለዝኸ አበቃሻለሁ። ሁለተኛ እንዲ ስትይ እንዳልሰማ።
ሚገባሽ ቦታ ነው የመጣሽ። እኼ ደሞ ቤትሽ ነው፤ ቀስ እያልሽ ሁሉን ትማሪያለሽ። ሚቸግርሽ ነገር ሲኖር ሳትፈሪ ንገሪኝ። ደንገጡሮችሽም አሉ። ለኔም ኸንግዲህ ኻንቺ ሌላ ሚቀርበኝ የለም” አሉና ቀስ ብለው
ተነሥተው፣ ቀኝ እጇን ይዘው፣ መኝታ ክፍል ውስጥ ይዘዋት ሲገቡ፣ በአጎበር የተሸፈነውን ተደራራቢ የእንጨትና የጠፍር አልጋ ስታይ፣ ልቧ ተንተረከከ።

ይሁን እንጂ፣ ልጅነቷ ማክተሙን ብቻ ሳይሆን፣ የዚያን ዕለት
የጀመረችው ግንኙት ሕይወቷ የሚጓዝበትን መንገድ ዳግም እንደጠረገ አላስተዋለችም።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

“ዕድል ኸሰማይ አይወድቅም።”

ሰኞ ጠዋት ጥላዬና አብርሃ አለቃ ሔኖክ ቤት ሲደርሱ ባለቤትየዋ
ወጥታ ተቀበለቻቸው። ውስጥ ሲገቡ ሰባዎቹ መጀመሪያ ያሉ፣
የግርማቸው፣ የብልኅነታቸውና የደግነታቸው ድባብ የሚያስተጋባ
አዛውንት መደብ ላይ ተቀምጠው ብራና ላይ የተጻፈ ጸሎት ያነባሉ።
የጥምጥማቸው ንጣት አካባቢውን ደመቅ አድርጎታል።

“የዠመሩትን እስቲጨርሱ ነው። ዐረፍ በሉ” አለቻቸው ባለቤቲቱ፣
ከአለቃ ሔኖክ ፊት ለፊት ያለ አጎዛ ጣል የተደረገበት መደብ በእጄ
እያሳየቻቸው።

ጥላዬ፣ አለቃ ሔኖክን በፈገግታ ከላይ እስከታች ተመለከታቸው።
ቀልቡ ወደዳቸው፣ ከእሳቸው ዘንድ ጉዳዩ እንደሚቃናለት አንዳች ነገር ነገረው። ከእሳቸው ሌላ ማንም ባያስተምረው ፈለገ። ቤቱን ሲቃኝ፣ ጥግ ላይ ካለው የጠፍር አልጋ በስተቀር እምብዛም ዕቃ አይታይበትም።ከአልጋው ግርጌ የቀለም ቀንዶች፣ የቀርከሀ ስንጥሮች፣ ብራናና በዕራፊ
ጨርቅ የተጠቀለሉ ዱቄት መሳይ ነገሮች ተቀምጠዋል። ይህንን
እየተመለከተ ሳለ አለቃ ሔኖክ፣ “አድራችሁ ነው ልጆት?” ሲሏቸው
ከአብርሃ እኩል ብድግ ብሎ ለሰላምታቸው የአክብሮት ዐጸፋ መለሰ።

“ምን ፈልጋችሁ ነው?” በሚል ዓይነት ሲያይዋቸው አብርሃ፣ “እሱ
ኸቋራ ነው የዘለቀ። ሥዕል መማር ፈልጋለሁ ቢለኝ ኸርሶ ዘንድ
ይዠው መጣሁ” አላቸው።

“መልካም... ሥዕል ለመሣል ቅኔ መማር አለብህ። ሞካክረኻል?”
“ወፍታ ጊዮርጊስ የንታ አምሳሉ ዘንድ ሥላሤ አድርሽ... ወዲህ
መጣሁ።”
“ሥዕል ሥለህ ታውቃለህ?” አሉት፣ ትክ ብለው እያዩት። ዞር አሉና፣ ምድጃ ላይ ድስት ጥዳ የነበረችውን ባለቤታቸውን፣ “ወርቄ እስቲ ሚቀመስ ታለ፤ ለዛሬ ዕንግዶቻችን ናቸው እኒኸ ተማሮች” አሏት።

ጥላዬ፣ ለጠየቁት ጥያቄ አዎም የለም አልሣልኩምም ማለት ፈለገና አመነታ። ዐይናቸው እሱ ላይ ተተክሎ ሲቀር፣ “ጥቂት ሞካክሬአለሁ፤ ግና ብራና ላይ ማይዶል” አላቸው።

“ዛዲያ ኸምን ላይ ሣልህ?”
ሊናገር ፈልጎ ዐፈረ። እሳቸው መልስ ፈልገው ተጠባበቁ። ያን
ችምችም ያለና ወተት የመሰለ ጥርሱን ብልጭ አደረገና፣ “ግድግዳ
ላይ” አላቸው።
“ግድግዳ ላይ? ግድግዳ ላይ እኮ ማነም ተነሥቶ አይሥልም።”
እንጀራ በድቁስና ጠላ ይዛ የመጣችው ወርቄ ከት ብላ ሳቀች። ያን ጊዜ ሁሉም፣ አለቃ ሔኖክ ጭምር ሳቁ። ጥላዬ፣ ወርቄ ጠላውን መጀመሪያ
ለአለቃ ሔኖክ ከዚያም ለእሱናኸ ለአብርሃ ቀድታ እስክታስቀምጥ
ጠበቀና፣ “ኸቤታችን ግድግዳ ላይ ነው። በእናቴ ወንፊት ዐመድ
እየነፋሁ፣ በውሃ ለቁጨ ሳበቃ ኸቤታችን ዠርባ ግድግዳ ላይ በእናቴጸ አክርማ እሥላለሁ። አባቴ ሲያዩት ይቆጣሉ። ግድግዳውን መልሰው
በጭቃ ያስመርጉታል” አለ።
ወርቄ እንደገና ከት ብላ ሳቀች፤ ሁሉም አብረዋት ሳቁ። ጥቂት
ቆይታ በድቁስ ከቀረበው እንጀራ ላይ ግማሹን ተቃምሰው መተዋቸውን ተመልክታ ለጠላው ማጣጫ በአነስተኛ ጮጮ ላይ ቆሎ ይዛ መጣች።

አለቃን አዘግናቸው እነጥላዬን፣ “እየቆረጠማችሁ” ብላ አስቀምጣላቸው ሄደችው ።
አለቃ ሔኖክ ከዘገኑት ቆሎ ላይ ቆንጠር አድርገው አፋቸው
አደረጉና፣ “ሥዕል መሣልህ ነው ወይስ ግድግዳ ላይ መሣልህ ኣባትህን ሚያስቆጣቸው?” ሲሉ ጠየቁት።

“ወታደር መሆን አለብህ እያሉኝ... ሥዕል እንድሥል አይፈልጉም።
በቅኔውም ቢሆን እንድገፋ አይፈልጉም። እሳቸው እስታሉ ድረስ አገሬ አልመለስም ብየ ጠፍቸ ወዲህ ዘለቅሁ።”

አለቃ ሔኖክ ራሳቸውን ነቀነቁ፣ መሆን የለበትም በሚል ዓይነት።
“ላባትህ መልክትም ቢሆን ላክባቸው። ያዝናሉ። እናትህም ቢሆኑ በልቅሶ ይሞታሉ። ብዙዎቻችን ለትምርት ብለን ጠፍተን ነው ኸቤት ምንወጣ ግና ኋላ እንመለሳለን። አባትህ ላንተ ሌላ ተመኙ፣ ከንተ ደሞ ሌላ ፈለግህ። ክፋት የለውም። ባባትህ ቂም እንዳትይዝ። ለማንኛውም
👍16
ሥዕል መሣል ፈልገህ እዝኸ ድረስ መምጣትህ ለሥዕል ያለህን ፍቅር
ያሳያል። እኔም እንዲህ ያለውን ተማሪ ነው ምወድ።”
“ባባቴስ ቂም አልይዝም። ለግዝየው ሥዕል አላሠራ ቢሉኝ
ተቀየምሁ እንጂ። የንታ ታዛዥዎ ነኝ። ሲያመቸኝ ኸጀ አያቸዋለሁ”
ኣለና ተነሥቶ እጅ ነሣ፡፡
“እንግዲህ ...” አሉት አለቃ ሔኖክ። “ሥዕል ስትሥል ኸየት ዠምረህ ወዴት እንደምትኸድ ማወቅ አለብህ። መዠመሪያ እጅህን ታፍታታለህ።
ኸዚያ በኋላ ዓለማውያንን... ቄሱን፣ መነኩሴውን... የመሳሰሉትን ትሥላለህ። ቀጥለህ ጻድቃንን፣ ኸዚያ ሰማዕታትን ትሥላለህ። እነዝኽ በግብራቸው ቢለያዩም ለባስያነ ሥጋ ወይንም ሰዎች ናቸው። እነዝኽን
ከሣልህ በኋላ መላዕክትን ትሥላለህ። ከዚያም የፍጡራን ሁሉ ፈጣሪ የሆነውንና ለዝች ዓለም ቤዛ ሆኖ የመጣውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ውልደት፣ ሥነ-ስቅለትና ጌታችንን የወለደችልንን ድንግል
ማርያምን ሥዕለ ማርያምን... ትሥላለህ። እመቤታችን ንፁህ ናት።

ለመላዕክት የቀረበች ናት። ከፍታዋም የጌታችን ማደሪያ... ማህደረ መለኮት መሆኗ ነው። ሌላውን ስትደርስበት ትማራለኸ አሁን እጅህን ለማፍታታት በጥቁር ቀለም እኩያኖቹን... እባብ፣ ቁራና ሳጥናኤል የመሳሰሉትን በመሣል ትዥምራለህ።”

“ሳጥናኤልን በጥቁር ቀለም?” አለ ጥላዬ፣ ከተቀመጠበት ተነስቶ፡
“አዎ! ምነው?” አሉት፣ ሊል የፈለገውን ጠርጥረው::
“ትናንት ኸደብረብርሃን ሥላሤ ግቢ ውስጥ ኻንድ መነኩሴ ጋር
ስንጨዋወት፣ ሥዕል መማር ፈልጌ ኸቋራ እንደመጣሁ ነግሬያቸው አሉኝ። አንደኛ ሳጥናኤልም ቢሆን መልዐክ ነበር። መላዕክት ደሞ .
በወሬ በወሬ ጥቁር ስለምን የሳጥናኤል መገለጫ እንደሚሆን አይገባኝም ፍጥረታቸው ኸብርሃንና ኸነፋስ ነው። ብርሃን ነጭ ነው። ነፋስ ደሞ ቀለም የለውም። እሱም ቢሆን ብርሃን ተሸካሚ ነበር። በዝኸ ላይ ደሞ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኸጥቁር ተወልጀ ኸጥቁር አስራ ሁለቱን
ሐዋርያት አመጣለሁ ብሏል እና ጥቁር ስለምን የከሀዲያን... የርኩሳን መገለጫ ይሆናል ሲሉ ነበር።”

አለቃ ሔኖክ ፈገግ አሉ። “እንደሱ ሚሉ አሉ። አየህ ኸጐንደር
ነገሥታት ዘመን ዠምሮ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፤ ክርክሮችም ተደርገዋል። ከእነዝኸ መኻል አንዱ እኼ ነው። ለማንኛውም አሁን አንተ ሥዕል ልትማር ነው የመጣኸውና እኔ ደሞ ማስተምርህ የተማርሁትን ነው። ደሞስ ነፋስ ቀለም የለውም ያለ ማን ነው? 'እስመ ነፋስ ጸሊም በአርአያሁ' ይል የለምን? የነፋስ መልኩ ጥቁር ነው ማለትም አይደል?”
“ኧረ እኔ እሳቸው ሲሉ ብሰማ እንጂ ምኑን አውቄ!” አለና
ከተቀመጠበት ተነሥቶ፣ “ጥሩ ሠዓሊ ለመሆን ስንት ዓመት ይፈጃል?” ሲል ጠየቃቸው።
“የሰነፍ ተማሪ ጥያቄ ነው ይኸ። ለመጨረስ እሚቻኮል ተማሪ ጥበብ አይዝም። ጥበብ ትዕግስትን ትሻለች። በቀጠሮማ ከቶም አትገኝ።

ለማንኛውም ለዛሬ በእንግድነትህና ኸቋራ እዝኸ ድረስ በመዝለቅህ እነግርሃለሁ። የሥዕል ጥበብ እንደ ተማሪው ትጋት ነው እሚያዝ።
ይልቁንም ወደ ቅኔ ሳይቀርብ አይቀርም ምሳሌው። ቅኔ ማለቂያ
የለውም። እንዲያው መምህሩ ተማሪውን 'አሁንስ ይበቃዎታል፣ ኸኔ ያለውን ምሥጢር ወስደዋል፤ ይኸዱና ያስተምሩ' ብሎ መርቆ ይሰደዋል እንጂ። ተማሪው አልጠገብኩም ካለ ይቆያል፤ አለዚያም እሌላ መምር
ዘንድ ኸዶ ይገባል እንደገና። አስተምራለኹ ካለም ወንበሩን ዘርግቶ በያዘው ጥበብ ያነኑ እያስፋፋ ያስተምራል። ሥዕል ክፍልህ ተኾነና ተግተህም ኸያዝኸው ዋና ዋና ጥበቡን ተሎ ትይዛለህ።”

ትኩር ብለው አዩት። ወደ አብርሃም ዞር ብለው መልሰው ዐይናቸውን ጥላዬ ላይ አሳረፉ።
“አስቀድመህ” አሉት፣ “አስቀድመህ እጅህን እያፍታታህ ንድፍ ትማራለህ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብም ዋናው ትምህርትህ ነው። ቅኔ ብቻ ሳይሆን፣ ታሪክና አዕማደ ምሥጢር ማወቅ ይገባል።

የብሉይና የሐዲስ ታሪኮች እንደሐረግ የተሣሠሩ ናቸው፤ የብሉይ ነቢያት ለሐዲስ ሐዋርያት አርአያ ይኾናሉ። ስለዝኽ ነው መጽሐፍ ቅዱስን ሳያውቁ ሥዕል መሣል እማይቻለው።”

ወደ ባለቤታቸው ዞር ብለው፣ “ወርቄ ኸጠላው ቅጅላቸዋ” አሏት።ወርቄ ጠላውን እስክትቀዳ ጠብቀው ስትሄድ፣ “አየህ ልዣ” አሉት ጥላዬን ትኩር ብለው እየተመለከቱት። “ሥዕል መሣል ማለት የአንድን ሥዕል ንድፍ ማወቅና ብራና ላይ አሳምሮ መገልበጥ ብቻ አዶለም።
ብዙ ማወቅ ያለብህ ነገር አለ። ስለምትሥለው ነገር ምሥጢሩን
ማወቅ ያስፈልጋል። ከባዱ ነገርም እኼው ነው። የምትሥለውን ሥዕል
ታሪክ ማወቅም ብቻ ሳይሆን ሥዕሉ ቤተክሲያን ውስጥ የሚሣልበትን ቦታ…. በግራ ይሁን በቀኝ..እ... ሚሣልበትን ቀለም ሁሉ ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል። ምትለውን ሥዕል እንደ ተሣዩ ማንነትና ታሪክ ምትመርጠው ቀለም ይለያያል ማለቴ ነው። ጽፈትህ... አጣጣልህ
እንዴት ነው?”
“የንታ ኣምሳሉ መልካም ነው ይሉኝ ነበር።”
“ማለፊያ።”
አብርሃ፣ ከተቀመጠበት ተነስቶ።
“አለቃ ጥላዬ ማደሪያ የለውም።

ኸደጀሰላም ነው ሚያድር” አለ
“ጥሩ ግዝየ መጥተሃል” አሉት፣ ጥላዬን እያዩ። “ኸኛ ዘንድ ይኖር
የነበረ ተማሪ በቅርቡ ትምርቱን ኸኔ ዘንድ ጨርሶ ወደ ደብረ ወርቅ
ኸዷል። እኔም ባንዳንድ ነገር ሚረዳኝ ሰው ስለምፈልግ በጓሮ አንዲት የተማሪ ጎገር ምታህል ቤት አለችኝ። ኸዛ ትቀመጣለህ። የዕለት ጉርስህን አንነሳህም። ዛሬም ቢሆን ከኛ ዘንድ መጥተህ ማደር ትችላለህ።”

ጥላዬና ኣብርሃ፣ ሊሄዱ ሲነሱ ወርቄ፣ “ወጡ ደርሷል፣ ሳትበሉማ
አትኸዱም” አለቻቸው። ተመልሰው ተቀመጡና ምሳ በልተው፣ አለቃ ሔኖክን እጅ ነሥተው ወርቄን አመስግነው ወጡ።

ጥላዬ፣ ሥዕል የመማር ዕድል ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ጎኑን ማሳረፊያ ቤት ማግኘቱ አስደሰተው። ዕድል ለመጀመሪያ ጊዜ በእሱ ጎን የቆመች መሰለው። ሕልሙንና ምኞቱን ሊያጨናግፉበት የሞከሩትን አባቱን ይቅር አላቸው። አባቴ እስታሉ አገሬ አልመለስም ያልሁትን ሁሉ እዝጊሃር ይቅር ይበለኝ። እናቴ፡ “ዕርቅ፣ ደም ያደርቅ” ትል የለ? አለቃ ሔኖክም ቢሆኑ ባባቴ ቂም እንዳልይዝ መክረውኛል። እኔም
ቃል እገባለሁ። አባቴ ባሉበት ደሕና ይሁኑ። እዝጊሃር ያለ ቀን ኸጀ አያቸዋለሁ አለ፣ ለራሱ።
የኔና የወለቴ ነገር ገና ሳንወለድ ተጥፎ የተቀመጠ ይመስለኝ ነበር።

የእዝጊሃር ነገር ይገርመኛል። ባንድ እጁ ሰጥቶ በሌላው ይነጥቃል።
ወለቴን ለሌላ ሰጥቶ ለኔ ሥዕል ሰጠኝ። ሁለቱንም ቢሰጠኝ ይከብደው ኑሯል? ወይስ ዕጣ ፈንታዬ ወለቴ ሳትሆን ሥዕል ብቻ ኑሯል?
ኸዝጊሃር አልጣላ መቸም። ለነገሩ ነው እንጂ እኔ እንደ ንጉሥ ላኖራት
አልችል። ለማንኛውም እሱ ባለቤቱ ያውቃል፤ ምስጋና ይግባው።

ጐንደርም ትባረክ! ዕድል ተርታየን አበጃጀችልኝ፡ እንደኔ ያሉት
መጥተው አይፈሩባት ሲል አሰላሰለ።

ከሐሳቡ ሲመለስ አብርሃ ከጎኑ ይራመዳል። “በደስታ አሳብ ይዞኝ
ጭልጥ አለ” አለው።

“አይቸህ እኮ ነው ዝም ያልሁት። ደካክሜአለሁ ይበቃኛል ሲሉ
የነበሩት የንታ አንተን ሳያቅማሙ ተቀበሉህ። ኣንዳች ያዩብህ ተስፋ
አለ። መምህራን እንዲህ በአንድ ቀን ትምህርቱንም ማደሪያውንም
ቀለቡንም እሰጥሃለሁ አይሉም፤ እንዲያው አንዳች ብርቱ ሆሳዕና
ይዘሃል መሰለኝ” ሲል ቀለደ።

“አየ! ትምህርቱን በውል ሳልይዘው መድኃኒቱንና አስማቱን በየት ደርሼበት ብለኽ? ሆሳዕና ለእንደኔ ላለው ማን ያሳያል ብለኽ ነው? ባይኾን ያንተ ሆሳዕና ሳይኾን ይቀራል እንዲኽ ግንባር የሰጠኝ?” ሲል ቀልዱን በቀልድና በምር አዋዝቶ መለሰ ጥላዬ።
👍7
“አረ ቆይ እስቲ፤ እንዲያው ቀልዱ ይቈየንና አለቃ ኻሉት ውስጥ
የገረመኝ እጅህን ምታፍታታው ክፉ ክፉውን በመሣል ነው ያሉት
ነው። ለመሆኑ ሳጥናኤልን እንዴት አርገህ ልትሥለው ነው? መክሥተ
ኣጋንንት ልትደግም?” አለ አብርሃ “መክሥተ አጋንንት ልትደግም”
የሚለው አባባሉ ራሱን ሳይቀር እያሳቀው።

“በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ! የምን መክሥተ አጋንንት
አመጣህብኝ ወንድሜ! እንዲያው ክፉ ሰው አስመስየ ቁጭ አላረገውም እንዴ! ዐይኑን ያጐረጠ፣ ገባሮውን እንደ ቀንድ ያሾለ፣ ጥርሱን እንደካራ የሳለ አድርጌ ብሥለው ማንነቱ ግልጥ ነው። እንግዲያማ እሱን በድግምት በዐይነ ሥጋ አይቼ ብሥለው ሚካኤልን በምን ላየው
ነው? ከቶስ ሥላሴን በምን አስማት ላያቸው እችላለሁ? ሥዕል ግብርን እንጂ መልክን ሚከተል አይመስለኝም። እደብረብርሃን ሥላሤ ውስጥ ያየኋቸው ድንቅ ሥዕሎች ቅዱሳኑንም ሆነ ርኩሳኑን በዐይነ ሥጋ በተመለከቱ ሠዓሊያን አይደለም የተሣሉ። ቅድም የንታ እንዳሉት ታሪካቸውን፣ ገድላቸውን፣ ተአምራታቸውን ወይም እኩይ ግብራቸውን ባነበቡ ሠዓሊያን እንጂ' ብሎ ያንን እየቆጠበ የሚሰጠውን ፈገግታውን
አሳየው።

አብርሃ ተፍለቀለቀ። “ድንቅ ብለኻል፤ መምሩ ዛዲያ ምን ሊነግሩህ ሰይጣንን ስትሥለው ቁመቱን ኣለቅጥ ረዥም አርገው። ሰይጣን ከሀዲ ነው በል ይኸን ኹሉ ኻወቅህ?” አለና ቀልዱን በመቀጠል፣ “ለማንኛውም
ነው፣ እባብ አሳሳች ነው... ቁራ ምንድር ነው?” ሲል ጠየቀው።
“ሚመስለኝ ያው ቁራ አይታመንም። ተልኮ ሳይመለስ የቀረ በዋል ፈሰስ ማዶል?”
“ውነትህን ነው። እስቲ ጃን ተከል ወረድ ብለን ጥቂት ወሬ
እንቀላውጥና እኔም ወደ ቅኔየ ልኸድ።”
ጥላዬ ግን መሄድ አልፈለገም። የሰሞኑ ወሬ የምንትዋብ መምጣት በመሆኑ ሰምቶ ልቡን እንደገና ማድማት አልታየውም። ግን ደግሞ ያን ሁሉ ውለታ የዋለለትን አብርሃን ማስቀየም አልፈለገም።.....

ይቀጥላል
👍11
አትሮኖስ pinned «#ምንትዋብ ፡ ፡ #ክፍል_አስራ_ሶስት ፡ ፡ #ድርሰት_በሕይወት_ተፈራ ....ምንትዋብ ማረፊያ ክፍሏ ቆይታ ማታ ላይ ራት ከበላች በኋላ፣ በሁለት ደንገጡሮች ታጅባ ወደ አፄ ፋሲል ቤተመንግሥት አቀናች። ደረጃውን ከወጡ በኋላ፣ ሁለት ያደገደጉ ደጅ አጋፋሪዎች መግቢያው በር ላይ ቆመው ለጥ ብለው እጅ ነሥተው መግቢያው ላይ ባለው በወንዶች የግብር አዳራሽ በኩል እንዲሄዱ መሯቸው። ምንትዋብ ቆም አለች። …»