ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
💚💛 ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም 💛❤️
ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "#ጥንተ_መድኃኒት#የድኅነት_መነሻ_ቀን" ሲሉ ይጠሯታል::

ስለ ምን ነው ቢሉ:-
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ::

"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::" (መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9, መኃ. 4)

ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ(አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::
የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::
ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ::

እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::
በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)
@senkesar @senkesar