ስንክሳር
7.32K subscribers
825 photos
4 videos
37 files
237 links
በስንክሳር channal ስንክሳሩ ተገልጦ ቅዱሳን ይዘከራሉ፣ ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ ይከታተሉን!
Download Telegram
#ቅዱስ_ሚክያስ
ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ
ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው::
አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ
ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::
ሚክያስ ትውልዱ ከነገደ ሲሆን አባቱ ሞራት (ሞሬት)
ይባላል:: #ሚክያስ ማለት " #መኑ_ከመ_አምላክ - እንደ
እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ
እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው
እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::
ቅዱሱ ነቢይ ገና ልጅ እያለ #መላእክት ያነጋግሩት ነበር::
በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ
#እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በ3ቱ
ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን
ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ
ገስጿል::
አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ #የዳዊት_ከተማ ፈት ሁና:
ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት
ተናገረላት::
"ወአንቲኒ #ቤተ_ልሔም ምድረ # ኤፍራታ : ኢትቴሐቲ
እምነገሥተ #ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ:
ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እሥራኤል::"
"አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት
ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን
የሚጠብቃቸው ንጉሥ (መስፍን) ካንቺ ዘንድ ይወጣልና" አለ::
ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በሁዋላ ደጉ #ዘሩባቤል
ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነግሥት #ኢየሱስ_ክርስቶስ ከንጽሕት #ድንግል_ማርያም ተወልዶባታል::
ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: 7
ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና:
በንጉሡ #ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹ ቀብረውታል::
ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::
✿ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ:
በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም
አያጉድለን::
💚💛ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል💛❤️

ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት ሁሉ አለቃቸው: የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም.በሆነ ተአምር ከከተማው #ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

ከመድኃኒታችን #ክርስቶስ ልደት 700 ዓመታት በፊት #ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር:: ደጋጉ #ዳዊትና #ሰሎሞን ካረፉ በሁዋላ የሕዝቅያስን ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም ነበር::

ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት:: ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከ185,000 በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

"እገብርልሃለሁ:: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ሃገሬን ግን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል:: ሕዝቤንም
አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ : ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ ማነው? ሕዝቡንም #እግዚአብሔር ያድናል ብለህ አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ #ቅዱስ_ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን
መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ #ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ::"

በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት 185 ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ:: በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

በድንጋጤ ወደ #ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖ የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)
From:- d/n yordanos abebe
@senkesar @senkesar