Addis Standard Amharic
17.9K subscribers
4.87K photos
123 videos
3 files
3.88K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
#ፋኖ ኃይሎች በአንድ ድርጅት ሥር መሆን ድርድርን ያቀርባል ወይስ ውጊያን ያጠናክራል?

ከሁለት ዓመት ለተሻገረ ጊዜ በበርካታ የተለያዩ ዕዞች ስር ሆነው ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ የቆዩት የፋኖ ኃይሎች፤ በመጨረሻም ወደ አንድ ድርጅት የመጡ ይመስላል ሲል ቢቢሲ ሐተታውን ይጀምራል።

በዘመነ ካሴ የሚመራው አማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) እና በእስክንድር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ራሳቸውን "አክስመው" አንድ ታጣቂ ድርጅት መፍጠራቸውን ይፋ አድርገዋል።

"የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)" የሚል ስያሜ የያዘው አዲሱ ድርጅት፤ "የመጨረሻዎቹ የፋኖ ኃይሎች ተዋህደው" የፈጠሩት እንደሆነ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሆነው የተመደቡት አስረስ ማረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፋኖ ኃይሎች አዲስ ድርጅት መመሥረታቸውን ይፋ ያደረጉት፤ ለበርካቶች ሞት እና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ውጪ መሆን ምክንያት የሆነው የአማራ ክልል ግጭት ወደ ሦስተኛ ዓመቱ እያመራ ባለበት ጊዜ ነው።

እንደ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ፣ ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባው እና እያሱ አባተ ያሉ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አመራሮችም የትጥቅ ትግልን በመተው ከመንግሥት ጋር ስምምነት የፈጸሙትም በዚሁ ሰሞን ነው።

መንግሥት የሰላም ንግግርን በተመለከተ በተለይም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት በሚሰጣቸው ማብራሪያዎች ላይ የፋኖ ኃይሎች የተበታተነ ዕዝ ስር መሆንን እንደ አንድ እንቅፋት ሲጠቅስ ቆይቷል። አሁን የፋኖ ኃይሎች የአንድ ድርጅት ምሥረታ በመንግሥት በኩል ሲነሳ የቆየውን አንድ ተግዳሮት የሚያስወግድ ይመስላል።

ተጨማሪ ይመልከቱ:- https://www.bbc.com/amharic/articles/cpv7xmwdpn7o
#ኢትዮጵያ#ማርበርግ_ቫይረስ ወረርሽኝን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን አወጀች

ኢትዮጵያ የመጨረሻው የማርበርግ በሽታ ታካሚ በምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ለ42 ተከታታይ ቀናት አዲስ የቫይረሱ ተጠቂ አለመመዝገቡን ተከትሎ፣ የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን በቁጥጥር ሥር መዋሏን በይፋ አውጃለች።

የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ይፋዊ መርሐ-ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ ይፋዊ መግለጫው የተሰጠው በሀገራዊ የወረርሽኝ መቆጣጠሪያ መመሪያዎች እና በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርቶች መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

በመጀመሪያ በደቡብ ኢትዮጵያ ጂንካ ከተማ ተከስቶ የነበረው ወረርሽኝ በተሳካ ሁኔታ መገታቱንም አረጋግጠዋል።

እንደ ሚኒስቴሩ መግለጫ፣ የመጨረሻው ታካሚ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ ከተረጋገጠ ወዲህ ምንም ዓይነት አዲስ የኢንፌክሽን ሁኔታ ባለመታየቱ ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር መዋሉን በይፋ ለማወጅ ተችሏል።

በጂንካ ተከስቶ የነበረው ሄሞራጂክ ፌቨር በማርበርግ ቫይረስ አማካኝነት የመጣ መሆኑን በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ ላቦራቶሪ በተደረገ የጂኖም ምርመራ መረጋገጡን ሚኒስቴሩ ያስታወቀው በኅዳር 2018 ዓ.ም. ነበር።

ወረርሽኙ በኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ የመጀመሪያው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ክስተት ሲሆን፣ በቫይረሱ ከተያዙ 14 ሰዎች መካከል ዘጠኙ ለህልፈት መዳረጋቸውንና ቀሪዎቹ ታካሚዎች ግን ሙሉ በሙሉ ማገገማቸው አይዘነጋም።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/1HHZh7PgHh/
#ኦሮሚያን እና #ማዕከላዊ_ኢትዮጵያን የሚያገናኘው የ1.3 ቢሊዮን ብር የቱሉ ቦሎ - ኬላ የመንገድ ፕሮጀክት ተመረቀ

የኦሮሚያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችን የሚያገናኘውና 81 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቱሉ ቦሎ - ኬላ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት ትናንት ጥር 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ መመረቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ-መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ የከተማ እና መሠረተ-ልማት ሚንስትር ደኤታ የትምጌታ አሥራት (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የፌደራል መንግሥት 1.3 ቢሊዮን ብር ወጪ ያደረገበትን ይህንን መንገድ "ሁናን ሁንዳ" የተሰኘው የቻይና ኩባንያ የገነባው ሲሆን፣ "የተባበሩት የምህንድስና አማካሪዎች" የተባለው ሀገር በቀል ድርጅት የማማከርና የጥራት ቁጥጥር ሥራውን አከናውኗል።

በምረቃው ወቅት ንግግር ያደረጉት ሚንስትር ደኤታው የትምጌታ አሥራት (ዶ/ር)፣ የሀገሪቱ አጠቃላይ የመንገድ አውታር ከ182 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መድረሱን ገልጸዋል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት በየዓመቱ በአማካኝ 7 ሺህ ኪሎ ሜትር አዳዲስ መንገዶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ የመንገድ ሽፋኑን ከ245 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ለማድረስ መንግሥት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid0SdjEV3VJ2VGitMy1j45n1Mt4GvGpyqqgxQL9fidEreiiphasfHDTymPmnCXHEgJTl
ዜና፡ #ኢትዮጵያ የአየር ኃይሏን አቅም እስከ 2030 በእጥፍ ለማሳደግ አቀደች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጋፉ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ አካላትን አስጠነቀቁ

ኢትዮጵያ የአየር ኃይሏን አቅም በእጥፍ ለማሳደግ እና እስከ 2022 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2030) ድረስ ወደ አምስተኛ ትውልድ የውጊያ አቅም ለመሸጋገር ማቀዷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ስትራቴካዊ ጥቅሞች በሚፈታተኑ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ አካላት ላይም ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ጥር 16 ቀን 2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን 90ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ አቅሟን በተመለከተ ያረጁ አመለካከቶችን መሻፈሯንና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ቁርጠኛ እየሆነች የመጣች መሆኗን ገልጸዋል።

“ወዳጅም ሆነ ጠላት እንዲያውቅልን የምንፈልገው አንድ ነገር፤ ኢትዮጵያን በጥልቀት አታውቋትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያ እናንተ ከምታውቁት በላይ በሀብት፣ በታሪክ እና በአቅም ረድፍ አልፋለች፣ እያደገች ያለች ሀገር እና የአፍሪካ ሕዳሴ ምልክት ነች” ብለዋል።

ዐብይ፣ የኢትዮጵያን የአየር ኃይል ዘመናዊነት አሁንም ጊዜ ያለፈባቸው ወታደራዊ መሣሪያዎችን ከሚጠቀሙ ሀገራት ጋር በማነጻጸር፤ የኢትዮጵያን ስልታዊ ጥቅሞች ለማዳከም የሚደረጉ ሙከራዎች እንደማይሳኩ አስጠንቅቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የቤላሩሱ ሪፎርም ኒውስ የሀገሪቱን የመንግሥት ወታደራዊ-ኢንዱስትሪ ኮሚቴን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በኢትዮጵያ የተሞከሩ የቤላሩስ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች በአሁኑ ወቅት በቀጠናው ሥራ መጀመራቸውን አስታውቋል።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=10484
#ሶማሊያ#ፓኪስታን ጋር ለዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ባለቤቶች ከቪዛ ነፃ የጉዞ ስምምነት ተፈራረመች

ኢትዮጵያ እና ሕንድ ለዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ባለቤቶች የጋራ ከቪዛ ነፃ የጉዞ ስምምነት ከተፈራረሙ ከአንድ ሳምንት በኋላ፣ ሶማሊያ እና ፓኪስታን ተመሳሳይ ስምምነት ማድረጋቸውን አስታወቁ።

ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱ በዲፕሎማቲክ ሰነዶች ልውውጥ በይፋ የተረጋገጠ ሲሆን፣ በሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተፈርሟል።

ምንም እንኳን ከፓኪስታን ወገን ፈራሚዎች በኩል ዝርዝር መረጃ ወዲያውኑ ባይሰጥም፣ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነቱን አረጋግጧል።

እርምጃው በሀገራቱ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ይፋዊ ጉዞዎችን እንደሚያሳልጥ ይጠበቃል ተብሏል።

የሚኒስቴሩ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ የሶማሊያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዓሊ ዩሱፍ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንትን መልዕክት ለፓኪስታን ወገን ያደረሱ ሲሆን፤ ሶማሊያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

መግለጫው ፓኪስታን ለሶማሊያ ሕዝብና መንግሥት ላሳየችው አቀባበል እና የቆየ አጋርነት ምስጋና አቅርቦ፣ በጋራ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች የከፍተኛ ደረጃ ግንኙነቶችን በማስቀጠል ትብብሩን ለማስፋፋት ያለውን ፍላጎት አመልክቷል።

የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚ እና በስልታዊ ዘርፎች የተለያዩ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በስፋት እያከናወኑ ይገኛሉ።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/17oed5iJ2J/
#ኢትዮጵያ_ንግድ_ባንክ በግማሽ ዓመቱ ከዘጠኝ ትሪሊዮን ብር በላይ ግብይት በዲጂታል አማራጮች ማከናወኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶቹ በኩል ከዘጠኝ ትሪሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸሙን አስታወቀ።

ይህም በባንኩ በኩል ከተከናወኑ ጠቅላላ ዝውውሮች እና ክፍያዎች 88 በመቶ ገደማ ድርሻ ይይዛል ተብሏል።

ይህ ውጤት ይፋ የተደረገው ባንኩ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት ሲሆን፣ የስትራቴጂክ ዕቅድ እና ትራንስፎርሜሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ወጋየሁ ገብረማርያም የባንኩን የስድስት ወራት ሪፖርት አቅርበዋል።

እንደ አቶ ወጋየሁ ገለጻ፣ በተያዘው ወቅት በዲጂታል መሠረተ-ልማቶች ከዘጠኝ ትሪሊዮን ብር በላይ ግብይት የተከናወነ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላ የባንክ ግብይቱ 87.9 በመቶ ድርሻ አለው ብለዋል።

በባለፈው በጀት ዓመት ባንኩ በሀገሪቱ የዲጂታል ግብይት እና ክፍያ ውስጥ 73 በመቶ ድርሻ እንደነበረው የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ በዚህ ዓመትም ባንኩ በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ዘርፍ ያለውን የበላይነት እንደሚያስቀጥል አመልክተዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እና ይህም የደንበኞችን ተደራሽነትና የባንኩን የሥራ ቅልጥፍና በማሻሻሉ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተያያዘም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግማሽ ዓመቱ 36.19 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/18CrfusYMv/
ተወርሶ የነበረው የሰብአዊ እርዳታ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) መመለሱን የ #ሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ

#ሞቃዲሾ ወደብ ማስፋፊያ ሥራን ተከትሎ ከመጋዘን ተነስተው የነበሩ የረድኤት ቁሳቁሶች ለዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) መመለሳቸውን የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ሰኞ ዕለት አስታወቀ።

የሀገሪቱ መንገስት ይህን ያስታወቀው፤ በሞቃዲሾ ወደብ የሚገኝ የአርዳታ ቁሳቁስ ማከማቻ "ፈርሷል" እንዲሁም "እርዳታ ተዘርፏል" የሚሉ ዘገባዎች ሲወጡ መቆየታቸውን ተከትሎ ነው።

የሶማሊያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ “ከመጋዘኑ ተነስተው የነበሩት ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ተመልሰዋል” ብሏል።

በመግለጫው አክሎም መንግሥት “ለተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ” ገልጿል።
የሶማሊያ ባለሥልጣናት በአሜሪካ የሚደገፍ መጋዘንን አፍርሰዋል እንዲሁም ለተረጂዎች የታሰበ 76 ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታ “በሕገ-ወጥ መንገድ ወርሰዋል” ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መወንጀሉ ይታወሳል።

አሜሪካ ይህንን ድርጊት በመቃወም ለሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት የምትሰጠውን ሰብአዊ እርዳታ አግዳለች።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid02msRDkGxipLBFfCG7vfy3viVwQxY3BFtBPyEMZg5TmJds2dASiLfbocVer3as1mUWl
ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በማልማት ስራ ላይ የተሰማሩ ማህበራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸው ተገለፀ

ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በማልማት ስራ የተደራጁ ማሕበራት ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የአዲስ አበባ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙላት ተገኘ በመዲናዋ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በማልማት ሥራ ዙሪያ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች ከ400 በላይ በሚሆኑ ማሕበራት በመደራጀት በዘርፉ ተሰማርተው ገቢ እያገኙ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ እነዚህ ማህበራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆን ገቢ ማግኘታቸውን ለኤፍ ኤም ሲ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ወደ አዲስ ምርት በመቀየር ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስር እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተለያዩ ደረቅ ቆሻሻዎች በወንዞች እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ እየተጣሉ አካባቢዎችን ሲበክሉ እንደነበር የገለጹት አቶ ሙላት፤ ነገር ግን የጽዳት ሥራ ከተጀመረ ወዲህ ደረቅ ቆሻሻዎች በአግባቡ የሚሰበሰቡበት እና አካባቢን የማይበክሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተችሏል ብለዋል።
#ኢንተርፖል በመላው ዓለም ባካሄደው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ዘመቻ ከ3,700 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

ኢንተርፖል ያስተባበረው ዓለም አቀፍ የሕገ-ወጥ የሰዎች አጋቾች እና አዘዋዋሪዎች መከላከያ ዘመቻ፣ ከ3,700 በላይ ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ ማድረጉንና በዝውውር አደጋ ላይ የነበሩ ከ4,400 በላይ ሰዎችን ለመታደግ መቻሉን ተቋሙ ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

ኢንተርፖል እንደገለጸው፣ ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 12 ቀን ባሉት ቀናት ውስጥ 14,000 የፖሊስ መኮንኖች "ሊበርቴራ 3" የተሰኘ ዘመቻ አካሂደዋል።

በ119 አገራት ውስጥ በተከናወነው በዚህ ኦፕሬሽን 3,744 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ 4,414 ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ሰዎችን መታደግ መቻሉ ተጠቁሟል። በተጨማሪም በሕገ-ወጥ ደላሎች ሴራ ውስጥ የነበሩ 12,992 ሰዎች መለየታቸው ተገልጿል።

የተለያዩ አገራት ባለሥልጣናት ቢያንስ 720 አዳዲስ ምርመራዎችን መጀመራቸውን ተቋሙ ገልጿል። ዋና መሥሪያ ቤቱን በፈረንሳይ ያደረገው ኢንተርፖል፤ 196 የዓለም አገራት ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት የፖሊስ ትብብርን በማጠናከር ድጋፍ ይሰጣል።

የኢንተርፖል ዋና ፀሐፊ ቫልዲሲ ኡርኩይዛ “የወንጀል መረቦች አዳዲስ መንገዶችን፣ ዲጂታል መድረኮችን እና ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመጠቀም ስልታቸውን እያቀያየሩ ይገኛሉ” ያሉ ሲሆን አክለውም “እነዚህን የወንጀል አሰራሮች መለየት የሕግ አስከባሪ አካላት ሊመጡ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድመው እንዲረዱ፣ የወንጀል መረቦችን ገና በጅምሩ እንዲበታትኑ እና ተጎጂዎችን በተሻለ ሁኔታ እንዲጠብቁ ያስችላቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/17bgfwiyPT/
ዜና፡ የ #ትግራይና #አፋር ሕዝቦችን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ በአዲ-ጉደም ከተማ ተካሄደ

በትግራይ እና በአፋር ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት እና አብሮነት ለማጠናከር ያለመ የሰላም ኮንፈረንስ በትግራይ ክልል በአዲ-ጉደም ከተማ ተካሄደ። በኮንፈረንሱ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

እንደ ትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን ዘገባ፣ ኮንፈረንሱ ትኩረቱን ያደረገው በትግራይ ክልል ሕንጣሎ ወረዳ በሚገኘው አራ-ዓለም ሰገዳ እና በአፋር ክልል አባዓላ ወረዳ ጋሌሶን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች መካከል ሰላማዊ ግንኙነትን መፍጠር ላይ ነው ተብሏል። ይህም የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ለዘላቂ ሰላም መሠረት መሆኑ ተመልክቷል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ከላሊ ሐጋዚ፣ በትግራይና በአፋር ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት አስፈላጊነት ገልጸው በሁሉም ዘርፎች ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

“ባለሥልጣናት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ጎረቤትና ማኅበረሰብ ግን ዘላቂ ናቸው” ያሉት አስተዳዳሪው፣ ሰላምን ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን በጋራ መመከት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሕንጣሎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎይቶም ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ሁለቱ ማኅበረሰቦች በታሪክ በሰላም ሲኖሩ የቆዩ መሆናቸውንና አለመግባባቶችን በሽማግሌዎችና በጎረቤቶች አማካኝነት በውይይት እንደሚፈቱ ገልጸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ፡ https://addisstandard.com/Amharic/?p=10496
የገንዘብ ሚኒስትሩ የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ፤ ከባንኩ ከፍተኛ አመራር ጋርም በኢኮኖሚ ማሻሻያው ዙሪያ መክረዋል

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከዳር ለማድረስ፣ ከዓለም ባንክ የሚደረገላት የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቋን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ውይይቱ የተካሄደው ትናንት ጥር 18/2018 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና በዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዌንካይ ዣንግ መካከል ነው።

በውይይታቸውም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ መንግሥት እያከናወነ ስላለው የማሻሻያ ፕሮግራም ለዣንግ ገለጻ አድርገዋል። የዚህ ማሻሻያ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በግል ዘርፉ ወደሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ማሸጋገር እንደሆነም አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ዘርፎችን ለማነቃቃት፣ እንዲሁም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚደረግ የተሻለ ትስስር ቀጣናዊ ውህደትን ለማጠናከር የታቀዱ ዕቅዶች ላይ ገለፃ አድርገዋል።

አቶ አህመድ ሽዴ፣ የዓለም ባንክ በዋና ዋና የልማት ዘርፎች ላይ ለሚያደርገው "ከፍተኛ ድጋፍ" ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ጠቅሷል። አክለውም ባንኩ የኢትዮጵያን የማሻሻያ ሥራዎች እና ለልማት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ተግባራት በማስቀጠል ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/1CLXCv6zRA/
#አሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኤክስፖ ጎበኙ

የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው እና የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኤክስፖ መጎብኘታቸውን መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በኩል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጉብኝቱ መሳተፋቸውም ተገልጿል።

በዚህ ኤክስፖ አየር ኃይልን ጨምሮ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ፣መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ፣ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎችም አለም አቀፍ ደርጅቶች ምርቶቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል ተብሏል።

በኤክስፖው የቀረቡት ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ስኬት የሚያሳዩ ስለመሆናቸው መከላከያ ሠራዊት መረጃ አመላክቷል።

የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው ከጉብኝቱ በኋላ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀበባል ምስጋና አቅርበው፤ ኢትዮጵያ በመገኘታቸው ክብር እንደሚሠማቸው ገልፀዋል። በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም ተናግረዋል።

የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን በበኩላቸው ለቀጠናው ሰላም በተለይም እንደ አልሸባብ እና አይኤስኤስ ያሉ ሽብረተኞችን ለመከላከል እና ለመደምሰስ በጋራ እንሰራለን ማለታቸውን መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።
የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ዝውውር እና በሰው መነገድ ወንጀል በተሳተፉ 28 ተከሳሾች ላይ ክስ መሰረተ

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ 1 ሺህ 8 መቶ የሚሆኑ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር፣ በከባድ የሰው ልጅ መነገድ እና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል በተሳተፉ 28 ተከሳሾች ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ መመስረቱን ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ተከሳሾቹ የተደራጀ የወንጀል ቡድን በመመስረት ሰዎችን በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ለማሻገር በማታለል እጅግ አሰቃቂ ለሆነ እንግልት እና ዝርፊያ ዳርገዋል ተብሏል።

የዐቃቤ ሕግ ክስ፣ ተከሳሾቹ በስራቸው ሌሎች ደላሎችን በመመልመል ሰዎችን የተሻለ ኑሮ እንደሚያገኙ በማሳመን ወደ ባህርዳር እና ጎንደር በመላክ በኩል ወደ ሱዳን ድንበር በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያወጡ መቆየታቸውን ያመለክታል።

ተጎጂዎቹ የኢትዮጵያን ድንበር ካለፉ በኋላ በሊቢያ በሚገኙ መጋዘኖች ውስጥ እንዲታጎሩ በማድረግ፣ በሕይወት ለመቆየት ብቻ የሚበቃ ምግብ እየተሰጣቸው ለቤተሰቦቻቸው በመደወል ከፍተኛ ገንዘብ ሲጠየቅባቸው እንደነበር ተገልጿል።

ገንዘብ በፍጥነት መክፈል ያልቻሉ ተጎጂዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየተደበደቡና እየተሰቃዩ ምስላቸው በቪዲዮ ተቀርጾ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመላክ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ክሱ ያሳያል።

በዚህ የወንጀል ሰንሰለት ውስጥ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ስምንት ተከሳሾች ብቻ በባንክ ሂሳባቸው ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰባቸው መረጋገጡን የዐቃቤ ህግ ክስ ተመላክቷል።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid02nkdyiZa84kQ3YrMt29gntKtF5aBQskWZECkFbipqt9cYFNf7zW4sgwe1fLbbsUppl
#ኢትዮጵያና #አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተገለፀ

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በዛሬው ዕለት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰንን በቢሯቸው ተቀብለው ካነጋገሩ በኋላ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኢንጂነር አይሻ በዚሁ ወቅት ሁለቱ ሀገራት ከዚህ በፊት የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ አሁን ላይ እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ግንኙነት ወደላቀ ስታራቴጂካዊ የሥራ አጋርነት በማሳደግ የሁለቱን ሀገራት እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልፀው፤ የሁለቱንም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እና ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ታሪክን ለማሰላሰልና የወደፊት ትብብርን ለማጠናከር ትርጉም ያለው አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ አየር ኃይል አከባበር ላይ ለመገኘትና ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንደገና ለማየትም ዕድል እንደሰጣቸው በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም የጋራ ቀጠናዊ የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የአጋርነት ዕድሎችን ለመጠቀም እንዲሁም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተጨማሪ ለማንበብ: https://www.facebook.com/share/1C1JPYK1q3/
ዜና: በኢትዮጵያ በወርቅ ማልማት ተግባር የተሰማራው የካናዳው አላይድ ጎልድ በ4 ቢሊዮን ዶላር ለቻይናው ዚጂን ጎልድ ሊሸጥ ነው

በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የካናዳው የወርቅ ማዕድን ኩባንያ አላይድ ጎልድ በቻይናው ዚጂን ጎልድ ኢንተርናሽናል መገዛቱን ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል። ግዥው በሙሉ በጥሬ ገንዘብ የሚፈጸም ሲሆን፣ ዋጋውም በግምት 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው ተብሏል።

በሆንግ ኮንግ የአክሲዮን ገበያ የተመዘገበው ዚጂን ጎልድ ኢንተርናሽናል፣ አላይድ ጎልድን በ5.5 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር (4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) ለመግዛት ተስማምቷል። ፋይናንሺያል ታይምስ እንደዘገበው፣ ይህ ግዢ ሊፈጸም የቻለው የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ፣ በማዕድን ዘርፉ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች እርስ በርስ በመጣመር አቅማቸውን እያጠናከሩ በመሆናቸው ነው።

አላይድ ጎልድ በኢትዮጵያ፣ በማሊ እና በኮትዲቩዋር የማዕድን ማውጣት ሥራዎች አሉት። ኩባንያው በስምምነቱ መደሰቱን የገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ግዢ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 44 የካናዳ ዶላር እንዲሆን ተደርጓል። ይህም ስምምነቱ ከመታወቁ በፊት ከነበረው የ30 ቀናት አማካይ የአክሲዮን ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የ27 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል።

ይህ የዋጋ መናር የወርቅ ዋጋ በዓለም ገበያ በመጨመሩ ምክንያት ባለሀብቶች በማዕድን ሀብቶች ላይ ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ማደጉን ያሳያል።

ተጨማሪ ለማንበብ:- https://www.facebook.com/share/1FBCWxygmK/